አርበኝነት ምንድን ነው? (ዶ/ር በቃሉ አጥናፉ ታዬ)

ዶ/ር በቃሉ አጥናፉ ታዬ
ኮተቤ ሜትሮፖሊን ዩኒቨርስቲ

Professor Berhanu Nega with Patriotic Ginbot7 fighters

ቅዳሜ ጥር 04/2011 በዋልታ ቴሌቪዥን ጋዜጠኛ ሳልሳዊት ባይነሳኝ አቶ መንግስቱ ወ/ስላሴን(የአርበኞች ግንቦት ሰባት የቀድሞ የፖለቲካ ጉዳዬች ቃል አቀባይ ወይም የአርበኞች ግንባር መስራች አባል) ቃለ-መጠይቅ አድርጋላቸው ነበር፡፡ በነበረው ውይይት አቶ መንግስቱ ከግንቦት ሰባት ጋር በነበራቸው ውህደት የእነርሱ ፈቃድ እንደሌለበት፣እንደ ድርጅት አብረው እንዳልኖሩ፣በመካከላቸው መለያየት እንደነበር፣ ኢሳት የህዝብ አይንና ጀሮ የሚባልለት ጣቢያ የግንቦት ሰባት እንደነበር፣ ከግንቦት ሰባት አባላት መካከል አንድም ወታደራዊ ዕውቀት ያለው አባል እንዳልነበር፣ ከፕሮፌሰር ብርሀኑ ነጋ ጋር እንደማይስማሙ ሰማሁ፤ ቀጠል አደረጉና አሁን የሚፈልጉት አርበኝነታቸውን እንደሆነ እና የአርበኝነት ታሪካዊ ዳራ እንዲጠበቅላቸው እንደሚፈልጉ እና ሌሎች ዘርዘር ያሉ ጉዳዬችን ሲናገሩ አዳመጥሁና የዝርዝር ጉዳዩ ጭብጥና አስፈላጊነት ልቃቂቱ ጠፋብኝና ግርምትን ጫረብኝ፡፡

ዘረኛ፤ አድሎዓዊ እና ከፋፋይን ስርዓት ተቃውመው በረሃ የወረዱ ጀግኞች የህብረት-ድምቀትን ፈጥረው ህዝቡን ሊታደጉት ሲገባ እንዴት አርበኞች ግንባር እና ግንቦት ሰባት የነበራቸውን መለያየት በአሁኑ ስዓት ይተርኩልናል? ማውራቱስ ውርደት እንጅ ምን ፖለቲካዊ ጠቀሜታ አለውበዘመነ ህወሃት የተወሰነው የማህበረሰብ ክፍል ከህወሃት አገዛዝ ለመላቀቅ የአርበኞች ግንቦት ሰባትን የጦር ሃይል ተስፋ ጥሎበት ነበር፡፡ ያ ተስፋ ከንቱ እንደ ነበር አሁን ለህዝቡ መተረኩ ፋይዳው ምንድን ነው? በወያኔ የድቅድቅ ጨለማ ዘመን በመረጃ እጦት ስር የነበረውን ህዝብ ቀን ከሌት ሳይታክት መረጃ ሲያቀርብ የነበረውን ትክክለኛ የመረጃ ቋት(ኢሳትን) ጥላ-ሸት መቀባት ለምን አስፈለገ? በዘመነ-ህወሃት በኢትዮጲያ ፖለቲካ ላይ ልዩ አሻራ ያለውን አንጋፋው ፖለቲከኛን  ፕሮፌሰር ብርሀኑ ነጋን የስልጣን-ጥም እንዳለበት አድርጎ ማቅረብ ለምን ተፈለገ?

በየትኛውም የፖለቲካ ድርጅት ውስጥ የሀሳብ ልዩነቶች ሊታዩ ይችላሉ፤ እነዚህን የሀሳብ  ልዩነቶችን በክርክር እና በሀሳብ ብልጫ ማሸነፍ ሲገባን ከስም ማጥፋት አዙሪት ውስጥ መውጣት ኢትዮጲያውያን ለምን ተሳነንበዘመናዊ የኢትዮጲያ ፖለቲካ ውስጥ ከ1960ዎች የተማሪዎች እንቅስቃሴ ጀምሮ ትልቁ ችግራችን የመጠላለፍ እና የሴራ ፖለቲካ ነው፡፡ ይህ መጠላለፍ እስካሁን እየተበተበን አንድ ስንዝር የፖለቲካ ለውጥ እንዳናሳይ ምክንያት ሁኖዓል፡፡ ፖለቲካን መሰረት አድርገው ህብረትን በፈጠሩ የፖለቲካ ድርጅቶች መካከል የሚታየው ሽኩቻ፤ ጥላቻ እና ስም ማጥፋት እጅግ አሳዛኝ ከመሆኑም ባሻገር አብዛኛው የገዥው ፓርቲ ተቃዋሚዎች የቆሙለትን ዓላማ በርካሽ የፖለቲካ ዝና ለመቀየር ሲታትሩ ይታያሉ፡፡ በዶ/ር አብይ ዘመን እንዲህ አይነት የፖለቲካ ሽኩቻ እጅጉን ያስፍራል፡፡

አቶ መንግስቱ ወ/ስላሴ የሚፈልጉት አርበኝነታቸውን እንደሆነ እና የአርበኝነት ታሪካዊ ዳራ እንዲጠበቅላቸው እንደሚፈልጉ ገልፀዋል፡፡ በርግጥ አቶ መንግስቱ ህወሃትን ለመዋጋት ኤርትራ በረሀ ሂደው ከነበር አርበኛ ናቸው፡፡ ግን አርበኝነት ትርጉሙ ምንድን ነውአርበኝነት ከፅንሰ-ሀሳባዊ ትርጉሙ (Conceptual definition) ይልቅ አውዳዊ ትርጉሙን (operational definition) ስንመረምረው በዘመነ ፋሽስት አርበኛ ማለት ፋሽስትን የተዋጋ፤ የፋሽስትን ስርዓት ተቃውሞ ለፋሽስት ስርዓት እና አገዛዝ ያልተንበረከከና፤ያላጎበደደ ዜጋ ማለት ሲሆን የዚህን ቃል አውዳዊ ትርጉም ካለንበት ዘመን አንፃር ስንቃኘው አርበኛ ማለት በረሃ የወረደ ጀግና  ብቻ ማለት ሳይሆን ሰው በጠፋበት ጊዜ በሰዎች መካከል ሁኖ ስለ-ህዝብ እና ስለ-ሀገር ጥቅም ስርዓቱን በድፍረት የተዋጋ፤ በስርዓቱ ውስጥ ሁኖ ስልታዊ በሆነ የፖለቲካ ጥበብ ስርዓቱን ያዳከመ፤ ለህወሃት አገዛዝ እጅ ያልሰጠ፤ ስርዓቱን የነቀፈ፤የተዋጋ፤የተቸ እና ስርዓቱን ለመቀየር በየትኛውም መንገድ የተገዳደረ በሙሉ አርበኛ ሊባል ይችላል፡፡

ስለሆነም መላ/ዘዴ  በጠፋበት፣ ነገሮች  እስርስር ባሉበት፣ እና ብርሀን በማይትይበት በህወሃት ዘመን በጠፍ ጨረቃ ላይ  እንደ አጥቢያ ኮከብ ጎልተው ብቅ ያሉት እነ ለማ መገርሳ፤ዶ/ር አብይ አህመድ፤እነ ገዱ እንዳርጋቸው፤ ኮ/ር ደመቀ ዘውዱ፤ፖሮፌሰር ብርሀኑ ነጋ፤አንዳርጋቸው ፅጌ እና በርካታ ፀሀፊያን፤ጋዜጠኞች፤ እውነተኛ የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች፤ በህወሃት ዘመን በፖለቲካ ጉዳይ ህይወታቸውን የገበሩ፤ አካላቸውን ያጡ፤ እስር-ቤት የነበሩ ጀግኖቻችን፤ህወሃትን ለማንበርከክ በየትኛውም መንገድ እውነተኛ ትግል  ያደረጉ በሙሉ አርበኞቻችን ናቸው፤ ልናወድሳቸው እና ልንዘምርላቸው ይገባል፡፡ አርበኝነት ማለት ለትግል በረሀ መውረድ ብቻ ነው ብለን የምንተረጉመው ከሆነ፤ የቃሉ ትርጉም ብቻ ሳይሆን የዘመናዊ የፖለቲካ ትግል ስልትም አልገባንም ማለት ነው፡፡

ከፖለቲካ ዳራው ባሻገርም መለያየት በሰፈነበት ጊዜ አንድነትን፤ ጥላቻ ባንዣበበበት ስርዓት ፍቅርን፤ ቂምና ኩርፊያ በተንሰራፋበት ወቅት  ይቅር-ባይነትን፤ርኩሰት በበዛበት ማህበረሰብ ቅድስናን መስበክና ማስተማርም አርበኝነት ነው፡፡ አርበኝነት ትርጉሙ ሰፊ ነው፡፡

Leave a comment