ማንነትና የማንነት ፖለቲካ

ዛሬ በዚህ ርዕስ ለመጻፍ የተነሳሳሁት በጉዳዩ ባለሙያ ሁኜ ወይንም ልዩ ጥናት አካህጄ ሳይሆን የጉዳዩ ወቅታዊነትና አሳሳቢነት እንደ ዜጋ እረፍት ስለሚነሳኝ ትንሽ ልተንፍስ ብዬ ነው፡፡ አገራችን አሁን ያለችበትን ሁኔታ በተስፋና በስጋት አይን እመለከታለሁ፡፡ ተስፋዬ እድሜ ልኩን እውር ሆእኖ የኖረ ሰው ነገ ዐይንህ ይበራልሀል ሲሉት ሌሊቱን እንዴት አድሬ እንዳለው ግለሰብ ካልሆነ በቀር የተጀመረው የለውጥ ጉዞ እስካሁን ያልታዬና አበረታች መሆኑ የተስፋየ ምንጭ ነው ፡፡ ስጋቴ ደግሞ ለውጡ መጣብን ብለው የተሸበሩ ቡድኖች ያለ የሌለ ሀይላቸውን ተጠቅመው መቀልበስ እንደማይችሉ እርግጠኛ ብሆንም እያስከተሉት ያለው ወድመት ተባብሶ ብዙ ዋጋ እንዳያስከፍለን ከማሰብ ነው ፡፡

ማንኛውም ለሀገሩ ሉአላዊነት ፣ ለሕዝቡ አንድነት ፣ ለእድገት ፣ ለብልጽግና ፣ ለፍትህና ለእኩልነት የሚያስብና የሚጨንቀው ኢትዮጵያዊ ለውጡን ለማስቀጠል መረባረብና መንግሥትን ማገዝ የጊድ ይላል ፡፡ ያ ካልሆነ ግን እንደ ልማዳችን ሰደን ስናሳድድ እንኖራታለን እንጂ ዲሞክራሲያዊ ስርአት ለመገንባታ አንችልም ፡፡

ኢትዮጵያውያን ሁላችንም መቀበል ያለብን አንድ ሀቅ አለ ይሄውም ኢትዮጵያ የሚትባል እኛ ያልፈጠርናት እኛ ግን የተፈጠርንባት እንደየ ወቅቱ ሁኔታ በአዎንታዊም ይሁን አሉታዊ ምክንያቶች በመላዉ ዓለም የምትታወቅ ጥንታዊት አገር እንዳለችን ነው ፡፡ ይህቺን ተፈጥሮ ያደላትን ውብ ሀገር ለኛ በሚስማማን መንገድ አሳድገንና አበልጽገን በጋራ መጠቀም ሲገባን ራሳችን በፈጠርናቸው ችግሮች ምድርቱን ተጠያቂ በማድረግ ለእኔ ያልሆነች አገር ትፍረስ ማለት ድንቁርና ይመስለኛል ፡፡ ትናንትና ፊደል ሳይቆጥር ያስተማረን ወገናችን ብቻውን መወጣት የማይችላቸውን ችግሮች ለመቅረፍ እድር ፣ እቁብ ፣ ደቦ ፣ ጂጊ ፣ የወንፈልና የቃንጃ ወዘተ እያለ ሲደራጅና ሲተባበር ነበር የምናውቀው ፡፡ ዛሬ ግን የምንደራጀው አገር ለማፍረስ ፣ እርስ በርስ ለመገዳደልና ችግር በያይነቱ ለመፈልፈል መሆኑን ስናይ መሃይሙ ባለ ድግሩ ገበሬ የነበረውን ብቃትና ችሎታ የዘመኑ ባለድግሪ ምሁር ነኝ ባይ አጥቶ ለጥፋት ሲጋብዘን ማየትና መስማቱ አሳዛኝና አሳፋሪም ነው የሚሆነው ፡፡

ጽድቁ ቀርቶ በወጉ በኮነነኝ እንዲሉ ለአንድ ዓላማ መተባበሩ ቀርቶ የየራሳችችንን ይዘን መደማመጥም ጥፍቶ እንደ እብድ መጯጯህ ስፍኗል ፤ እናቱ እንደ ሞተችበትና ወንዝ እንደ ሄደችበት ህጻን ሁላችንም እኩል እያለቀስ ነው ፤ ማን ቀልደኛ ማንስ ቁምነገረኛ መሆኑን መረዳት ተስኖናል ።

የሰው ልጅ ከሌሎች እንሰሳት የሚለየው በሁለት ምክንያቶች ይመስለኛል ፡፡ አንደኛው ተፈጥሮን እንዳለ ተጠቃሚ ሳይሆን ለራሱ በሚስማማው መልኩ ቀይሮ መጠቀሙ ሲሆን ሁለተኛው እንደ እንሰሳት ዘወትር ጉልበት ባለው እንደተጠቃ ለመኖር አለመፍቀዱ ነው ፡፡ በሌላ አገላለጽ የሰው ልጅ በህገ አራዊት ዝንተ ዓለም በጉልበትና በጉልበተኛ አይገዛም ማለት ነው ፡፡ ሕዝባችን በታሪኩ ድሞክራሲ የሚባል ነገር በተግባር ሊያገኝ ቀርቶ በትዎሪ ደረጃ በአግባቡ የሚያውቀው ጽንሰ ሀሳብ አይደለም። ይሁን እንጂ በህገ አራዊት በጉልበተኞች ይደርስበት የነበረውን ሁሉ አቀፍ ጭቆና አሜን ብሎ የተቀበለበት ወቅት አልነበረም ፡፡ ሆኖም ግን የሥርአት ለውጥ ለማምጣትና ዲሞክራሲያዊ መስተዳድር ያለው የሕዝብ መንግሥት ለመመስረት አልቻለም ፡፡

ለምን ?

ጥያቄው መሰረታዊና አግባብ ያለው ምላሽ የሚሻ ነው ፡፡ በመሆኑም ብዙም ሳንርቅ የቅርብ ታሪካችንን ብንዳስስ ከመሳፊንቱ ወደ ንጉሣዊ ከንጉሣዊው ወደ ሶሻሊስት መር ስርአት ከዚያም ወደ አብዮታ ድሞክራሲና ዘር ተኮር ፖሌቲካ የገባነው በሕዝቡ ፍላጎትና ነባራዊ ሁኔታ ስለፈቀድ ሳይሆን ጥቂት እኛ እናውቅልሃለን ባይ ግለሰቦችና ቡድኖች ለሥልጣን ሲሉ በጉልበት ስለምጭኑብን ነው ፡፡ ሩሲያውያን አንድ ቆንጆ አባባል አላቸው ይሄውም ብልህ ከሰው ስሕተት ይማራል ጅል ግን ከራሱም ስህተት አይማርም ይላሉ ፡፡ እኛም ከሌላው ይቅርና ከራሳችን ስህተቶች ለመማር አለመቻል ይሁን ካለመፈለግ አሁንም በጎጥ ፖሌቲካ አረንቋ ውስጥ ተረፍቀን መንቀሳቀስ ተስኖን እንወዛወዛለን ፡፡

ሃያ ሰባት ዓመት ሙሉ ኢትዮጵያዊነትን አስረስቶ በትውልድ ቀዬና በጎጥ ተከልለን እርስ በርስ እንድንጠፋፋ ሕወኃት የቀየሰው የጎሣ ፖሌቲካ ሀገሪቷ እንደ ሀገር ሕዝቡም እንደ አንድ ሕዝብ እንዳይኖር አድርጎት እዚያም እዝይህም ብጥብጥ እየተካሄደ የሰው ህይወት እያለፈ ፣ ንብረት እየወደመና ሰው እየተፈናቀለ ይገኛል ፡፡ ትናንትና እኔ አውቅልሃለሁ ባይ ዘረኛ ቡድኖች በጎጥ አደራጅተው መቀመቅ የከተቱን ትምህርት ሊሆነን ሲገባ በአሁኑ መልካም የለጥ ጅማሮ ወቅት አዲስ አይንአውጣ ጎጠኞች አዎን ትምክህተኞች ነን ትምክህተኛ በመሆናችን አናፍርም የሚሉ የተገኙበትን ጎሣ ታሪክና ኢትዮጵያዊ ማንነት ሲያኮሰምኑት ማየትና መስማት ያሳፍራል

፡፡

የጎሣ ፖሌቲካ በአገራችን ዲሞክራሲያዊ ያልሆነው ጎሰኞቹ እንደሚሉት የአፈጻጸም ችግር ኖሮት ወይንም ሕወኃት ስለመራው ሳይሆነ በተፈጥሮው ሰውን በሰውነቱና በግለሰብንቱ የሚገባውን ሁለንተናዊ መብቱን የሚያጎናጽፍ ሳይሆን በትውልድ የዘር ሀረጉ ከሌላው ለይቶ ተጠቃሚ እንዲሆን የሚያደርግና አግላይ በመሆኑ ነው ፡፡ ሕወኃት በፖሌቲካው ፣ በኢኮኖሚውና በማህበራዊ ዘርፉ ጠቅላይና የበላይ እንዲሆን አመቺ ሁኔታን የፈጠረለት የሄው የጎሳ ፖሌቲካ ነው። በመሆኑም ነው አቶ መለስ ዜናዊ ኢትዮጵያን

እየመሩ ለትግራ አዲስ የኢድገትና የብልጽግና ፕላን ነድፈው ሳይተገብሩት ሞቱ ብላ ባለቤታቸው አዜብ መስፍን ሙሾ ስታወርድ የሰማናት።

ሕዝባችን ለሃያ ሰባት ዓመት ጎራ ለይቶ ሲገዳደልና ከቄዬው እንዲፈናቀል የተደረገው በየደረጃው ሥልጣን ላይ የነበሩ በሙሉ ክፋተኞች በመሆናቸው ሳይሆን የዘር ፖሌቲካው እትዮጵያን ለማፈራረስና ሕዝቧንም ለመበታተን ላቀደው ህወኃትና ግብረአበሮቹ አዋጭ የመጫወቻ ካርታ በመሆኑ ነው ፡፡ እነኚህ ግለሰቦችና ቡድኖች የመዘዙት ካርድ የተወሰነ መንገድ አስክዷቸዋል ፡፡ ውጤቱም አሁን መሬት ላይ ያለው የስጋታችን ምንጭ የሆነው ትርምስ ነው ፡፡ ከላይ ለመግለጽ እንደሞከርኩት የዘር ፖሌቲካው ከድጡ ወደ ማጡ የከተተን የአፈጻጸም ችግር ኖሮት ወይንም ካሁን በፊት ተዋናይ የነበሩ የጎሣ መሪዎች የመተግበር ብቃት አጥተው ሳይሆን በዘር ላይ የተመሰረተ ፖሌቲካ የደም ትስስር ላላቸው የጎሣው አባላት ፖሌቲካዊ ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጥቅሞች ለማስጠበቅ የቆመ በመሆኑ ይህንን ተልእኮ ከማስፈጸም ሌላ አማራጭ ስላልነበረው ነው ፡፡

አሮጌዎቹ ጎጠኞች ዳክረው ዳክረው አላዋጣ ያላቸውን የዘር ፖሌቲካ አሁን ደግሞ አዲስ ጎሰኞች በአዲስ አቁሟዳ አሮጌውን የጎጥ ፖሌቲካ ይዘውብን ብቅ አሉ ፡፡ ቁምነገሩ ከአቁሟዳው ሳይሆን በውስጡ ከያዘው ጎሰኝነት ነው ፡፡ ጎሰኝነት የዘር ሀረግ መዞ የሚያቀርብና የሚያገል ዘረኝነት ነው ፡፡ ዘረኝነት ደግሞ ሰወን በስብዕናው ፣ በችሎታው ፣ በስነምግባሩና በአስተዋጽዖው የሚመዝን ሳይሆን የእኔ ወገን ነው በሚል የደም ትስስር የሚለካ ነው ። በመሆኑ አግላይና ጸረ ዲሞክራሲያዊ ነው ፡፡ በመሆኑም በሃያ ሰባት ዓመት የጎጥ ፖሌቲካ በየክልሉ የተካሄደውን የዘር ማጽዳት ዘመቻ ያስከተለውን አሰቃቂ እልቂት ማስታወሱ ብቻ በቂ መረጃ ነው።

ማንነት ምንድን ነው ?

ማንነት አንድ ግለሰብ በህብረተሰቡ ወይንም ማህበረሰቡ ውስጥ ራሱን የዚያ አካል አድርጎ የተቀበለበትና ራሱን ያገኘበት ስፍራ ነው ማለት ይቻላል ፡፡ ራሱን ያገኘበት ስፍራ ደግሞ የሱነቱ መገለጫ የሆኑ የተለያዩ ኤለሜንቶች ወይንም ናኡሳን ክፍሎች ይኖራሉ ። እነዚህን የማንነቱ ናኡሳን ክፍሎች እንዲያድጉ ፣ እንዲበለጽጉ በማህበረሰቡ እኩል ተቀባይነት እንዲኖራቸው ይፈልጋል ። ይህ ተፈጥሮአዊና ተቀባይነት ያለው ነገር ነው። ይህንን ተጻሮ መቆም ግን አግባብነት የለለውና ጸረ መብትና ጸረ ነጻነት ነው ። የሰው ልጅ በህይወት ዘመኑ የተሟላ ደስታ የሚያገኘው በማንነቶቹ ውስጥ ( የሰው ልጅ የተለያዩ ማንነቶች ስላሉት ማለት ነው) መጣጣም (harmony) ሲኖር ነው ፡፡ መጣጣሙ እንዲኖር ደግሞ ሀላፊነቱ የግለሰቡ ብቻ ሳይሆን የማህበረሰቡም ጭምር ነው ።

ግለሰቦች ከተለያዩ የማንነቱ መገለጫዎች አንዱን ወይንም የተወሰኑትን የራሱ አድርጎ ሊቀበል ይችላል መብቱም ነው። ኢትዮጵያ የብዙ ጎሳዎች አገር እንደመሆኗ መጠን ኢትዮጵያዊነት የዜጎቿ የሁሉም የማንነት መገለጫ ሲሆን ጎሣ ደግሞ የእያንዳንዱ የጎሳው አባላት ማንነቱ ነው ። የማንነት መገለጫ የሆኑ ሌሎች ንኡሳን ክፍሎች ቢኖሩም ለአንድነትም ሆነ ለልዩነት የጎላ ተጽእኖ አሳዳሪ ናቸው የሚል ግምት ስለሌለኝ ለመዘርዘር አልፈለኩም ። የሕዝባችንን ታሪክ መለስ ብለን ከመረመርነው አብሮ ተዋልዶና ተዋህዶ የኖረ ሕዝብ በመሆኑ የማንነት መዛነቅ ስላለ የእኔ ማንነት ይህና ይህ ብቻ ነው ብሎ ለመናገር ድርቅና ካልሆነ በቀር በዲኤንኤ አስመርምሮ የሚያረጋግጥ ኢትዮጵያዊ አይኖርም። ስለሆነም የጋራ ማንነታችንን (ኢትዮጵያዊነትን) እየተንከባከብን ሌሎቹን የማንነት መገለጫዎቻችንን በጋራ በማሳደግና በማበልጸግ አማራጮቻችንን ማስፋት ይኖርብናል ። ከዚህ በተቃራኒው ሄደን ኢትዮጵያን እናፍርሳት ማለት የቆጡን እናወርዳለን ብለን የብብታችንን መጣል ነው የሚሆንብን ።

እንድ ኢትዮጵያ ባሉ ባለ ብዙ ጎሣ አገሮች የመብት ጥያቄዎች የማንነትን ጨምሮ ሊፈቱ የሚችሉት ዲሞክራሲያዊ ሥርአትን በማስፈን ብቻ ነው ። የዲሞክራሲያዊ ሥርአት መፍትሄ የሚሆነው ደግሞ የግለሰብን መት ያለምንም ልዩነት ስለሚያረጋግጥና በዘር ቆጠራ፣ በቁጥር መብዛትና ማነስን መስፈርቱ አድርጎ በቁመቱ ልክ ለአንዱ ቀሚስ ለሌላው ጥብቆ የሚያሰፋ ባለመሆኑ ነው ።

ፖሌቲካችን መሬት የረገጠ ነባራዊ ሁኔታውን ያገናዘበና ካለፉት ስህተቶቻችን ትምህርት የቀሰምንበት መሆን አለበት እንጂ እያንዳንዱ አዋቂ ነኝ ባይ በሚያቀርበው ፋንታዚ ሊሆን አይገባም ። ሕዝባችንም ዘወትር የአዲስ ርእዮተአለምና የዘር ፖሌቲካ መሞከሪያ አይጥ መሆኑ ማብቃት አለበት ። የዘር ፖሌቲካውን ሁለተኛ ዙር እንሞክር ያለፈው የአተገባበር ችግር እንጂ በራሱ ችግር አይደለም የሚለው ትርክት ሙሉ በሙሉ ስህተት ነው ። ያንን የሚሉት ደግሞ አተገባበሩ ምን መሆን ሲገባው ሳይሆን እንደቀረ በንድፈሃሳብ ደረጃ የሚያቀርቡት አማራጭ እንኳን የላቸውም ። ከሃያ ሰባት አመቱ ተሞክሮ በመነሳት ለሚቀርበው ትችት ምሁራዊ ምላሽ ሳይሆን የድሮን ናፋቂ፣ አሀዳዊ መንግሥት ፈላጊ ፣ በጎሣ የተከለለ ፌደራሊዝም አያዋጣንም ሲባል ጸረ ፌደራሊዝም እያሉ ስድብ ይደረድራሉ ። የጎሣ ፖሌቲካን መቃወም በምንም መስፈርት የሌላውን ጎሣ ቋንቋ ፣ ባህል ፣ወይንም ራስን በራስ የማስተዳደር መብት መቃወም ሊሆን አይችልም ። በጎሣ ፌደራሊዝም የሁሉም መብት የተከበረባት ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን መመስረት አይቻልም ብሎ መተቸት የፌደራል ሥርአትን አልቀበልም የሚል ትርጉም ሊሰጥ አይችልም ። መፍትሔው የግለሰብ መብት የተረጋገጠባት ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን መገንባት ብቻ ነው ። ለዚህም የሚያስፈልገው የጎጥ ድርጅትና ፖሌቲካ ሳይሆን ሕብረ ብሔራዊ አደረጃጀትና የዜጊነት ፖሌቲካ ነው ።

ስም አልባው ጸሐፊ (Anonymous)

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s