የማንነት ብሔርተኝነት የተጠላው አማራ ይጠቅመኛል ብሎ ስለያዘው ነው (ባየ ተሻገር)

* ማሳሰቢያ፤ ጽሑፉ ረጅም ነው። ከመጀርያው እስከ መጨረሻው *
* ብታነቡት ቁም-ነገር አታጡበትም። ዋና መጽሐፍቶቹን*
* እና አርቲክሎቹን እንትታነቡ ትበረታታላችሁ። *

መግቢያ

በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ አማራን በሚመለከት በተለያዩ አጀንዳዎች ዙሪያ ውይይቶች የተከፈቱ ቢሆንም የበርካታ ፖለቲከኞች ትኩረት ግን የዜግነት ብሔርተኝነትን መሠረት አድርገው የሚንቀስቅቀሱ ድርጅቶች የአማራን ማንነት መሰረት አድርገው ከሚንቀሳቀሱ ድርጅቶች ይሻላሉ ወይንም የአማራን ብሔር የሚወክሉ ድርጅት/ድርጅቶች አያስፈልጉም፣ ለአማራ ህዝብ አይመጥኑም አገር አፍራሾች ናቸው የሚል እና ይህንን አስተያየት ለመመከት የሚሰጥ ግብረ-መልስ ነው። ከዚህም በተጨማሪ በአገራዊ ቴሌቪዥንና ራዲዮ ሳይቀር እጅግ የተዛባ ፅንሰ-ሃሳብ ያላቸው አንዳንዴም ትርጉም የለሽ ቃላት መጠቀም የተለመደ ሆኗል። ለምሳሌ “የአንድነት ጎራ” የሚለው ቃል ትርጉም የለሽ ነው። የማንነት ብሔርተኞችን (ethnic nationalists) “ብሔርተኞች” ብቻ ብሎ መግለጽ ከመደበኛ የሚዲያ አካል የሚጠበቅ አይደለም። በአጠቃላይ የብሔርተኝነት ጽንሰ-ሃሳብ እጅግ ተዛብቶ እየቀረበ ይገኛል። በእርግጥ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ አማራ የሚያራምደው የፖለቲካ አጀንዳ ዘወትር እንደተገፋና እንደተጠላ ነው፤ የማንነት ብሔርተኝነት የተጠላው አማራ ይጠቅመኛል ብሎ ስለያዘው ነው።

በዚህ ጽሑፍ ውስጥ ትኩረት የማደርገው ብሔርተኝነት ምንድን ነው? የብሔርተኝነት መንሥኤዎች ምንድን ናቸው? በዓለም አቀፍ ደረጃ የማንነት ብሔርተኝነት እንዴት ይታያል? ማንነትን መሠረት አድርጎ የሚካሄድ ብሔርተኝነት መጥፎ ጎን ብቻ ያለው እንቅስቃሴ ነውን? እና በዜግነት ላይ ያተኮረ ኢትዮጵያዊ ድርጅቶች የማንነት ብሔርተኝነትን ለምን ይጠሉታል? የሚሉትን መዳሰስ ይሆናል።

በመሠረቱ ብሔርተኛ (nationalist) ያልሆነ ድርጅት የለም። የሚለያየው ድርጅቱ ለሚያራምደው ብሔርተኝነት በመንስኤነት የያዘው ሃሳብ እና የመታገያ አጀንዳው ነው። አንድ ድርጅት የመታገያ አጀንዳውን ቋንቋ፣ ባህል፣ ምጣኔ ሐብት፣ ዜግነት ወይንም እንደየአካባቢው ሁናቴና እንደ ሕዝብ ፍላጎት ሌላ ሊያደርግ ይችላል። ድርጅቱ የመታገያ አጀንዳውን ከፖለቲካ ርዕዮት ጋር አዛምዶ የትግል ፍኖት ይቀርጻል ። በብሔርተኛው ድርጅት መታገያ ሆኖ የቀረበለትን አጀንዳ እና የምርጫ ቅስቀሳ መዝኖ ህዝብ ይበጀኛል፣ ጥያቄዎቸን ይመልሳል፣ ኑሮዬን ያሻሽላል ያለውን ይመርጣል። ኢትዮጵያ ውስጥ በብሔር ማንነታቸው ተደራጅተው ከሚታገሉት በስተቀር በዜግነት ብሔርተኝንት የሚንቀስቅቀሱ ድርጅቶች የጠራ የመታገያ አጀንዳ የላቸውም፤ የዜግነት ብሔርተኝነትን የሚያምዱ ድርጅቶች አሉ ለማለት በራሱ አያስደፍርም። በእርግጥ የሌሉት የዜግነት ብሔርተኝነት እንዳይኖር የሚያደርግ ምክኒያት ስለለ ነው። ይኸውም ኢትዮጵያ የመድብለ-ብሔር አገር ከመሆኗ ባሻገር እያንዳንዱ ብሔር አንገብጋቢ ችግሬ ነው ብሎ እንዲመለስለት የሚፈልገው ጥያቄ ያለው መሆኑ ነው፤ ጥያቄ መኖሩ ብቻ ሳይሆን የአንዱ ብሔር ጥያቄ ከሌላው ብሔር ጥያቄ የተለየ አልፎ አልፎም የሚቃረን በመሆኑ ነው። ይህ ደግሞ በዜግነት ብሔርተኝነት ላይ የተመሰረቱ ድርጅቶች የመታገያ አጀንዳ እንዳይኖራቸው አድርጓል።

በዘመናዊ የፖለቲካ አሰራር የመታገያ አጀንዳ የሚወሰነው በህዝቡ ፍላጎት ነው። ለምሳሌ የአማራ ህዝብ በአስቸኳይ እንዲመለሱለት ከሚፈልጋቸው መካከል ቀዳሚው ወሰንን ማስከበር የተመለከት ነው። የወልቃይት፣ የራያ፣ የመተከልና የሸዋ መሬቶች ጉዳይ የሁሉም አማራ አፍ መፍቻ ሆኗል። በመሆኑም የአማራን ህዝብ ይሁንታ ማግኘት የፈለገ ድርጅት እነዚህን ጉዳዮች የግድ የመታገያ አጀንዳ ማድረግ አለበት። ይሁን እንጅ የዜግነት ብሔርተኝነት አራማጅ ድርጅቶች ቀደም ብዬ በገለጽኩት ምክኒያት የወሰን ማስከበርን ጉዳይ አጀንዳቸው ሊያደርጉትም አይችሉም። ከዚህ ቀደም የወልቃይትና መሰል አካባቢዎች የወሰን ማስከበር ጥያቄ አስመልክቶ ጥያቆአ የተቀረበላቸው እንደ ግንቦት 7 ያሉ የዜግነት ብሔርተኝነት እናራምዳለን የሚሉ ድርጅቶች እንኳን ጥያቄዎቹን በአጀንዳቸው ሊያካትቱ በእንዲህ ዓይነት ዘዴ እንፈታለን ለማለት ያስቸገራቸው ሲሆን በደፈናው የህወሓት (ትህነግ) ወያኔን መንግሥት እንደ ምክኒያት አድርገው ለበርካታ ጊዜያት ዋና ጠላታችን ካሸነፍን በኋላ እንመለስበታለን የሚል ማምለጫ መንገድ በማመቻቸት ሲሸሹት ቆይተዋል። ይህ በር ግን ዛሬ ላይ ማምለጫ አይሆንም ምክኒያቱም የህወሓት ወያኔ መንግሥት ባይወገድ እንኳን ተንኮታኩቶ የበላይነቱን ተነጥቋልና። በመሆኑም ምላሽ የላቸውም።

ቀጥሎ የብሔርተኝነትን ትርጉም እና ዓይነቶች እንመልከት።

ሀ) የብሔርተኝነት ትርጉም

እንደ ክርስቶፈር ሙስካቶ አገላለፅ “ብሔርተኝነት ማለት በአንዲት አገር የጋራ ሃሳብ ዙሪያ አንድነት ያለው ማንነት ከፍ ማለት ማለት ነው (Nationalism is the elevation of a unified identity around the shared concept of the nation: Christopher Muscato, University of Northern Colorado)።”ብሔርተኝነት የተቃውሞ ዝንባሌ ያለው ጽንሰ-ሃሳብ ነው። ብሔርተኝነት ከአገር ባለቤትነት ጋር ጥብቅ ቁርኝት ያለው ሲሆን የአገር ኅልውና መሠረትም ነው። ብሔርተኝነት አርበኝነት(patriotism) አይደለም። በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ የተለያዩ የፖለቲካ ኃይሎች አንጻራዊ የበላይነት ለማግኘ እና የሕዝቡን ወኔ በመቀስቀስ ከጎናቸው ለማሰለፍ ሲሉ ብሔርተኝነትንና አርበኝነትን በተለዋዋጭነት ይጠቀሙባቸዋል፤ ነገር ግን ሁለቱ አንድ ዓይነት ትርጉም የላቸውም። በዚሁ ዘርፍ ተመራማሪ የሆኑት ፕሮፌሰር ሙስካቶ አርበኝነት አንድ ግለሰብ ስለአገሩ የሚሰማው ኩራት ወይንም ክብር እና ለአገሩ ያለበትን ግዴታ እንደሆነ ያመለክታሉ። ብሔርተኝነት ደግሞ በአንዲት አገር የጋራ ሀሳብ ዙዙሪያ አንድነት ያለው ማንነት ከፍ በማድረግ ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት የሚረጋገጥበት ሥርዓት የመፍጠር ጉዳይ ነው ሲሉ ያስቀምጡታል። አርበኞች አገራቸውን ይወዳሉ (Patriots love their country) ፤ ብሔርተኞች ደግሞ አገራቸውን ናቸው (nationalists are thier country!)። በሌላ አገላለጽ አርበኞች ከትውልድ ትውልድ ሲተላለፍ የመጣን ድንበር እና አገራዊ እሴቶችን ለማስጠበቅ ዘብ በመቆም አገሪቱን ከውስጣዊና ውጫዊ ኃይሎች ወይንም አገራዊ እሴቶችን ሊጎዱ ከሚችሉ አስተሳሰቦች የመከላከል እንቅስቃሴ ሲሆን ብሔርተኝነት የሚያተኮረው ፖለቲካን እንደ መሣሪያ በመጠቀም በአገሪቱ ውስጥ ያለውን የሃብት ክፍፍል፣ ብልጥግና፣ እና ማህበረሰባዊ ለውጥ መቀመር ላይ ነው።በመሆኑም ብሔርተኝነት የአንድ ማኅበረሰብ አካል ብለን ከምንጠራው የኅብረተሰብ አካል ከመሆን ጽንሰ-ሀሳብ ጋር የተያያዘነው። በእርግጥ አርበኝነትን የተላበሰ ብሔርተኝነት አብቦ የጎመራባቸዋና ውጤታማ የሆነባቸው አካሄዶችም አሉ።

በአጠቃላይ በምሁራን መካከል ብሔርተኝነት ከሁለት የተለያዩ ቅርጾች አንዱን ሊወስድ እንደሚችል የሚታመን ቢሆንም በርካታ የኅብረተሰብ ሳይንስ ተማራማሪዎች ከሁለት በላይ ብሔርተኝነቶች እንዳሉ ይጠቅሳሉ። እንደ ሚካኤል ኢግናቴፍ (Micheal Ignatieff) አገላለጽ ብሔርተኝነት ሁለት መልክ ሊኖረው ይችላል። የመጀመሪያው ማንነትን መሠረት ያደረገብ ሔርተኝነት (ethnic nationalism) ሲሆን ይኸውም የጋራ ቋንቋ፣ ሀይማኖት፣ ሥነ-ልቦና ያለው እና በተመሣሣይ መልክዓ-ምድር አካባቢ የሚገኝ ሕዝብ ወይንም ብሔር በጋራ ማንነቱ ከፍ ማለት ባለው ጥብቅ ሀሳብ ተመስርቶ የሚያንቀሳቅሰው የፖለቲካ አጀንዳ ነው። በአማራ አውድ ለ”ethnic nationalism” በጣም ተቀራራቢው ፍች የማንነት ብሔርተኝነት ነው። ሁለተኛው ዜግነታዊ ብሔርተኝነት (civic nationalism) ነው። ይህ የጋራ የሲቪክና የፖለቲካ እሴቶችን መሠረት ያደረገ ብሔተኝነት ሲሆን እነኛን የጋራ እሴቶች መሠረት በማድረግ ዜጎች ሁለንተናዊ ጥቅማቸው እንዲጠበቅ ለማድረግ የሚከተሉት የፖለቲካ ሥልት ነው።

ምሁራን ብሔርተኝነትን በአራት የተለያዩ መነጽሮች ተመልክተው ይተነትኑታል። ብሔርተኝነትን እንደ ፖለቲካ ርዕዮት (ideology)፣ ቡድናዊ አስተሳሰብ (group sentiment)፣ የአገር ምሥረታ ሂደት(process of nation building) ወይንም ማኅበረሰባዊ ንቅናቄ (social/collective movement) በመውሰድ ጥናቶች ይካሄዱበታል (Ethnic Nationalism and State Power – Mark Suzman (1999))። በኢትዮጵያ ውስጥ ከንጉሣዊ ሥርዓት መውደቅ በኋላ የታዩት ብሔርተኝነቶች አራቱንም ዓይነት ይዘት ያላቸው ሲሆኑ የሻዕቢያ፣ ትህነግ፣ ኦነግ፣ ኦብነግ እና የመሣሰሉት ብሔርተኝነቶች በአገር ምሥርታ ላይ ያተኮሩ ናቸው። በአንጻሩ ደርግ እና በደርግ አገዛዝ ወቅት የነበሩ እንደ መኢሶን፣ ኢሀፓ፣ ኢዲዩ ወ.ዘ.ተ. እና በዘመነ ኢህአዴግ የታዩት እነ መድረክ፣ ቅንጅት፣ ሰማያዊ ፓርቲ ወዘተ በደረቅ ፓለቲካዊ ፍልስፍና እና እሽቅድድም ላይ ያተኮሩ ብሔርተኝነቶች ናቸው። በትህነግ ፊታውራሪነት ተቀምረው ለተቀረው ኢትዮጵያዊ በአገዛዝ መሳሪያነት (ዲክታትነት) የተከፋፈሉት እነ ብአዴን፣ ኦህዴድ፣ ደህዴን ወዘተ በቡድናዊ አስተሳሰብ የተቃኙ ናቸው። በመጨረሻም በቅርቡ ህዝባዊ ተቀባይነትን ያገኙት የአማራ ብሔርተኝነት እና “ቄሮ” በሚል ቅፅል ስም የሚቀነቀነው የኦሮሞ ብሔርተኝነት በማኅረሰባዊ ንቅናቄ ደረጃ ያሉ ብሔርተኝነቶች ናቸው።

ለ) የብሔርተኝነት መንስኤዎች

የብሔርተኝነቶች መንስኤዎች የተለያዩ ትርክቶች ናቸው። በፖለቲካዊ ርዕዮት መነጽር ሲለኩ የዜግነት ብሔርተኝነቶች መንስኤ የብሔርተኝነቱ አራማጆች ስለዓለም አጠቃላይ ሁኔታ ያላቸውን ግንዛቤ (conscious strategic understanding) ለማስመስከርና ማኅበረሰቡ በተጽዕኖ ፈጣሪነትና ተሰሚነት እንዲኖራቸው በማሰብ የምሁርነታቸውመገለጫ እንዲሆን በፋሽንነት የሚያመጧቸው ሃሳቦች ነው። መሰረታቸው ፖለቲካዊ ፍልስፍናን ብቻ ትኩረት ያደረገ በመሆኑ ከብዙሃን ፍላጎት የሚመነጭ አይደለም። በአንዲት አገር ካለው ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ ወይንም ፖለቲካዊ እውነታ ይልቅ ዓለ’ማቀፋዊ ይዘት ባላቸው ፅንሰ-ሃሳቦች ላይ የሚያተኩር እንቅስቃሴ በመሆኑ የተለያዬ ማንነት እና የፖለቲካ ፍላጎት ያላቸው ብሔሮች በሚገኙበት አገር ለአካባቢያዊ ሁናቴዎች መፍትሔ የማምጣት ጉልበት የሚያንሰው እንቅስቃሴ ነው። በዚህም ምክኒያት ውጤታማ ሲሆኑ አይታይም። በተለይ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ፖለቲካዊ ፍልስፍን ብቻ መሠረት ያደረገና ውጤታማ የሆነ አንድም የዜግነት ብሔርተኝነት የሚያራምድ ድርጅት አልነበረም፤ የለምም።

በማንነት ላይ ያተኮሩ ብሔርተኝነቶ መንሥኤዎች ከሃብት ክፍፍል፣ፖለቲካዊ ውክልና እና ማኅበረሰባዊ ፍትህ ጋር የተያያዙ ትርክቶች ናቸው። መንሥኤዎቹ ከማኅበረሰቡ የቀን ተቀን ኑሮ ጋር የተቆራኙ በመሆናቸው ህዝቡን ለማነሳሳትና ተቀባይነት ለማግኘት ጊዜ አይወስድባቸውም።

የብሔርተኝነቶችን ስኬት የሚወሰነው ለመነሻነት መንስኤ ባደረጉት ሃሳብ ነው። ለምሳሌ በአገር ግንባታ ላይ ያተኮረው የሻዕቢያ ብሔርተኝነት መንስኤ የገዥና ተገዥ (ቅኝ ገዥና ቅኝ ተገዥ) ትርክት ሲሆን ምንም እንኳን ትርክቱ እውነትነት ያለው ባይሆንም ይኸው ይዞት የተነሳው ትርክት ግብ መትቶ ውጤታማ እንዲሆን አስችሎታል።ይህም ማለት የሻዕቢያ ብሔርተኝነት ውጤታማ ተደርጎ የሚታየው በአሁኑ ሰዓት ኤርትራ የተባለች ሉዓላዊት አገር መመሥረት ማስቻሉ ነው፤ ሉዓላዊት አገር ከተመሠረተች በኋላ ያለው አገዛዝ አምባገነን መሆን እና የአገሪቱ አለመበልፀግ ከፊተኛው መንስኤ (ገዥና ተገዥትርክት) ጋር ሊደባለቅ አይገባም ምክኒያቱም ኤርትራ ነጻ ሃገርከ ሆነች በኋላ ዴሞክራሲያዊና የበለፀገች መሆን ወይም አለመሆን ከራሳቸው የኤርትራዊያን የውስጥ ጉዳይ እንጅ እንደ ምክኒያት ይዘውት ከተነሱት የገዥ ተገዥ ትርክት አኳያ የሚመዘን አይሆንም።

ሐ) የማንነት ብሔርተኝነት ዓለም-አቀፋዊ ወቅታዊ ሁኔታዎች

የማንነት ብሔርተኝንት የቆዬ ነው በኢትዮጵያ አልተጀመረም። የማንነት ብሔርተኝነትን መሠረት ያደረገ ሌላ አገር የለም የሚለው ውሸት ነው። ማንነትን መሠረት ያደረገ ብሔርተኝነት አገር አፍራሽ፣ አደገኛ፣ የበላይነት ርዕዮት (supermacist ideology) ወዘተ የሚሉ አሉታዊ አስተያየቶች የሚሰነዘሩበት ብሔርተኝነት ቢሆንም ከ18ኛው እስከ 20ኛው ክፍለ-ዘመን በአውሮጳ ተስፋፍቶ የነበረ ብሔርተኝነት ነው። በቅርብ ጊዜ ደግሞ ባለፉት 30 ዓመታት ውስጥ በርካታ የምስራቅ አውሮጳ አገራትን ለነጻነት ያበቃ እንቅስቃሴ ነው። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ በተለይ በምዕራቡ ዓለም ተቀባይነት እያገኘ የመጣ አስተሳሰብ ነው። በአሁኑ ሰዓት ከአሥራ ሦስት በላይ በሚሆኑ የአውሮጳ አገራት ውስጥ የማንነት ብሔርተኝነት በአዲስ መልክ አንሰራርቷል። በኦስትሪያ፣ በኔዘርላንድ፣ በፈረንሳይ፣ በጀርመንና በጣልያን “far-right” በመባል የሚታወቁ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከፍተኛ ተቀባይነት በህዝብ ውስጥ እያገኙ መጥተዋል። እ.ኤ.አ. በ2016 ዓ.ም በኦስትሪያ ውስጥ በተደረገው አገራዊ ምርጫ የብሔርተኛው ድርጅት “Freedom Party” አመራር ኖበርት ሆፈር በምርጫው ተሸናፊ ይሁኑ እንጅ ከአጠቃላይ ድምፅ ውስጥ አርባ ስድስት ነጥብ ሰባት (46.7) በመቶ ድርሻው በማግኘት ብሔርተኝነቱ በህዝቡ ተቀባይነት ያለው መሆኑን አሳይተዋል። በፈረንሳይ የፕሬዚደንት ኢማኑአል ማክሮን ተገዳዳሪ ሰላሳ ሶስት ነጥብ ዘጠኝ (33.9) በመቶ ድምፅ ለማግኘት ችለዋል። በግልፅ “I am nationalist” የሚለው ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ አሜሪካን እያስተዳደረ ነው (ትራምፕ አሜሪካ ለአማሪካዊያን የሚል አስተሳሰብ ያለው ሲሆን ለዓለም-አቀፍ ተቋማት የሚደረጉ እርዳታዎች በመቀነስ ወይም በማስቀረት እንዲሁም አሜሪካን ለታላላቅ ዓለም-አቀፋዊ ድርጅቶች እንድትወጣ በማድረግ የሚታወቅ መሪ ነው)፤ ብራዚል አዲስ ብሔርተኛ ፕሬዚደንት መርጣለች። በኔዘርላንድ ፓርላማ ከ150 መቀመጫዎች ውስጥ 20ዎቹ በቅርብ በተመሠረተ ብሔርተኛ ድርጅት (the Dutch Party for Freedom(PVV)) የተያዙናቸው። የጀርመኑ “Alternative for Germanay (AfG)” የምርጫ ቅስቀሳው ትኩረት አገራዊ ደህንነት እና ስደተኞችን መቆጣጠር (national security and immigration) የሚል ሲሆን ከፓርላማው መቀመጫ 3ኛውን ትልቅ ቦታ ይዟል። The New York Times እ.ኤ.አ ዴሴምበር 28፣ 2018 ይዞት በወጣው እትሙ የጀርመን ብሔተኞች የተመለከተ ዘገባ ወጣቶች ሲሆኑ የተሻለ የሚለብሱ፣ የተሻለ የተማሩ ነገር ግን ቁጡ-ያልሆኑ (less angry) ሲል ይገልጻቸዋል፤ አላማቸው ጀርመንን የጀርመናዊያን ብቻ ማድረግ ነው በተለይም አገራቸውን ከአክራሪዎችንና ከስደተኞች ቀዳሚ አጀንዳቸው መሆኑን ዘግቧል ።

ምንም እንኳን ከላይ የተጠቀሱት ብሔርተኛ ፓርቲዎች ጥቃቅን ልዩነቶች ይኑሯቸው እንጅ የእንቅስቃሴያቸው አስኳል ህዝባቸውን ከመድብለ-ባህላዊና ግሎባላይዜሽን (ዓለም አቀፋዊነት) ተፅዕኖ በመከላከል ተመሳሳይ ማንነት ያለው ማኅበረሰብ (ethnically homogeneous society) በመፍጠር አገራቸውን ማዳን ነው።

መ) ሉታኒያ – የማንነት ብሔርተኝነት መልካም ምሳሌ

ከ30 ዓመት በፊት ገደማ ነጻነቷን ያገኘችውና ከማንነት ብሔርተኝነት ጋር ስሟ ተያይዞ የሚነሳው የማንነት ብሔርተኝነት አቀንቃኞች እንደ መልካም ማሳያ የሚወስዷት አገር ሉታኒያ ነች። ሉታንያ በምሥራቅ አውሮጳ የምትገኝ ትንሽ አገር ስትሆን እ.ኤ.አ.ከ 1940 ዓ.ም ጀምሮ በሶብዬት ህብረት ውስጥ የተጠቃለለች አገር ነበረች። ይሁን እንጅ ሉታንያዊያን በሶብዬት ህብረት ውስጥ መብታችን ሊከበር አልቻለም፣ ሉታኒያዊያን ሊተዳደሩ የሚገባቸው በሉታንያዊያን ነው፣ ሉታንያ ጥንትም የነበረች በመሆኑ ወደቀደመ ማንነቷ ልትመለስ ይገባል ወዘተ የሚሉ ጥያቄዎችን በማንሳት እንቅስቃሴ አድርገው መጨረሻ ላይ ትግላቸው ውጤታማ ሆኖ ሉታንያ ነጻ አገር መሆኗን እ.ኤ.አ. ከማርች 11 ቀን 1990 ዓ.ም ጀምሮ አውጃለች። ሉታንያ ነጻ አገር መሆኗን ካወጀች ጀምሮ ሠላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊና የዜጎች መብቶች የሚከበሩባት አገር በመሆን ትታወቃለች። በሉታንያ ውስጥ የግለሰብ መብት ዘር፣ የቆዳ ቀለም፣ ሃይማኖት ሳይለይ እስከ ጥግ ድረስ ይከበራል፣ ሉታንያ ለጎረቤቶቿም ሆነ ለቀሪው ዓለም ሠላማዊና ተባባሪ ነች፤ በተለይ ሉታንያ ነጻነቷን በአወጀችበት በጥቂት ጊዜያት ውስጥ የአውሮጳ ህብረት አባል አገር ለመሆን ያቀረበችው ጥያቄ በእርግጥም የሉታንያዊያን እንቅስቃሴ ራስን በራስ የማስተዳደር (Lithuania for Lithuanians) እንጅ ከሉታንያ ውጭ ያለው ጠላት ነው ወይንም ሉታንያዊያን የበላይ ናቸው (Lithuania above everything else) የሚል አንድምታ ያለው አለመሆኑን አሳይታለች። የችካጎ ዩኒቨርሲቲ ባልደረባ የሆኑት ስኮማታስ ፖሲስ “In defence of Ethnic nationalism” በሚል ርዕስ The American Conservative ላይ ባስነበቡት ጽሑፋቸው “በማንነት ብሔርተኝነት ላይ ቁልፉ ነጥብ ራስን በራስ የማስተዳደር ጉዳይ እንጅ ከራስ ወገን ያልሆነን ኅብረተሰብ ወይንም ህዝብ በማጥቃት ላይ ያነጣጠረ አይደለም” ይላሉ። ይህ ከአማራ የማንነት ብሔርተኝነት ጋር ተመሳሳይነት ያለው ነው። የአማራ ብሔርተኝነት መንሥኤ የአማራ ህዝብ ህልውና አደጋ ላይ መውደቅ ሲሆን ይህን ችግር የፈጠረው ቀዳሚው ምክኒያት የአማራ አማራ ባለፉት 27 ዓመታት ባልሆኑ ግለሰቦች መመራቱ ነው የሚል እምነት ያለው ነው፤ የአማራን ህዝብ እንደ በረከት ስምዖን ያሉ አማራ ያልሆኑ ሰዎች ሲመሩት መቆየቱ ይታወሳል።

ሠ) ጆርጅያ – የማንነት ብሔርተኝነት ውድቀት ማሳያ

የማንነት ብሔርተኝነት እንቅስቃሴ እንደ ማንኛውም እንቅስቃሴ ህፀፆች የሚኖሩበት ሲሆን በተለይ በማንነት ብሔርተኝነት ስም የበላይነትን ለማስፈን የሚደረግ ሸፍጥ ለከፋ ጉዳት ሊዳርግ ይችላል። የማንነት ብሔርተኝነት የበላይነት ስሜት ባላቸው ቡድኖች ሲጠለፍ አደገኛና አጥፊ እንደሚሆን ምሳሌዎችን ጠቅሶ ማሳየት ይቻላል። የመጀመሪያዋ ምሳሌ ሌላዋ
የምስራቅ አውሮጳ አገር ጆርጅያ ስትሆን ሁለተኛዋ ኢትዮጵያ ነች። ጆርጅያ የማንነት ብሔርተኝነትን ተጠቅማ ከሶቪዬት ኅብረት አገዛዝ ራሷን ነጻ ያወጣች ቢሆንም የበላይነት የሚሰማቸው ቡድኖች(ብሔሮች) የሩሲያን መንግሥት እንደ ከለላ በመጠቅም አገራዊ አመለግባባትና ግጭት እንዲፈጠር እያደረጉ ይገኛሉ። በጆርጅያ ግዛት ውስጥ ሦስት ብሔሮች ይገኛሉ፤ አብኻዚያ (Abkhazians)፣ ኦስሺያ (Ossetians) እና ቲቢሊሲ (Tbilisi) ናቸው። የብላድሚር ፑቲን መንግሥት አብኻዚያኖችንና ኦስሺያኖችን በጥቅም በመደለል ቲቢሊሲዎች ከእናንተ ጋር እኩል አይደሉም የሚል ትርክት በመፍጠር የጆርጅያን አንድ አምስተኛ ግዛት ለመያዝ የበቃ ሲሆን በአገሪቱ ውስጥ በብሔሮች መካከል ግጭትን በመፍጠር ጆርጅያ የተረጋጋ ማዕከላዊ መንግሥት እንዳይኖራት አድርጓል። በተለይ”ምርጫው ተጭበርብሯል” የሚሉ ቡድኖችን በማሰማራት አለመረጋጋቱ እንዲቀጥል ሆኖል። በሩሲያ ጣልቃ ገብነት ምክኒያት ጆርጅያ የሚያባራ ጦርነት ውስጥ ለመግባት የተቃረበች አገር ሆናለች (ይህ ጉዳይ ህወሓት በቅማንት ስም የአማራ ህዝብ ሁለንተናዊ ሰላም ለመንሳት ከሚያደርገው እንቅስቃሴ ጋር ተመሳሳይ አካሄድ ያለው ነው)። ። በኢትዮጵያ ውስጥ ባለፉት 27ዓመታት በማንነት ብሔርተኝነት ስም ተጀቡኖ የትግራይን የበላይነት ለማረጋገጥ በትግራይ ህዝብ ነጻ አውጭ ግንባር (ህወሓት) ሲካሄድ የቆየው እንቅስቃሴ ከዚህ ዘርፍ የሚመደብ ነው፤ አማራን በጨቋኝነት በመፈረጅ በመላ አገሪቱ የእርስበርስ ግጭትን የሚያስፋፉ ቡድናዊ አመለካከቶችን (group sentiments) በማስረፀና በማቧደን (ብአዴን፣ ኦህዴድ፣ ደህዴን ወዘተ) ተቋማዊ አሰራር በመፍጠር ከፍተኛ ሰቆቃና የሰብዓዊ መብትጥሰት ሊያስከትል ችሏል። ኢትዮጵያ ውስጥ በየቦታው አስተዳደራዊ በደል ከማድረሱም ባሻገር የዘር ማፀዳት፣ የዘርማጥፋት፣ የማንነት ቀውስ፣ እና አገራዊ ሃብትና ንብረት ብክነትን አስከትሏል።

ረ) በዜግነት ላይ ያተኮረ ኢትዮጵያዊ ድርጅቶች የአማራ ብሔርተኞችን የሚጠሉባቸው ምክኒያቶች

ኢትዮጵያ ውስጥ በማንነት ብሔርተኝነት ላይ በተለይም በአማራ ብሔርተኝነት ላይ የሚሰነዘሩ ትችቶችና አሉታዊ አስተያየቶች በተለያዩ ምንክኒያቶች የሚመነጩ ናቸው። የመጀመሪያው ምክኒያት በማንነት ብሔርተኝነት ላይ ጥልቅ ግንዛቤ የሌለውን የኅብረተሰብ ክፍል በዲስኩር (propaganda) በማምታታት እና የማንነት ብሔርተኝነትን በማንነት ካባ የተሸፈነ የበላይነት ብሔርተኝነት (superiority nationalism) አስመስሎ በማቅረብ ህብረተሰቡ ጠልቶ እንዲሸሽው የማድረግ ሂደት ነው። ለምሣሌ በአማራ ብሔርተኝነት ላይ ትችት የሚሰነዝሩት የኦሮሞ ኦንላይን ጋዜጦች (ayaantuu የተባለውን እና Addis Standardን መጥቀስ ይቻላል) የአማራ ብሔርተኝነት ጥርስ-አልባ (toothless) ነው በማለት የሚያናንቁት ሲሆን በምትኩ ግንቦት 7 ለአማራ ህዝብ የሚመጥን አድርገው ቅስቀሰ ይሰራሉ። እውነታው ግን ለአማራ ህዝብ ከአብራኩ ከወጡት ከአማራ ብሔርተኞች የበለጠ ግንቦት 7ም ሆነ የኦሮሞ ብሔርተኛ ጋዜጦች ሊቆረቆሩለት የማይችሉ መሆኑ ነው።

ሁለተኛው ምክኒያት የዜግነት ብሔርተኝነት አራማጆች የማንነት ብሔርተኝነትን ከአገር ምሥረታ ጋር ብቻ አቆራኝቶ የማየት አባዜ ነው። ይኸውም ብሔርተኝነት ከግዛት ክፍፍል ጋር ተያይዞ ጠብ ቀስቃሽ ነው የሚል ስጋት ማስተጋባታቸው ነው። ይህን ስጋት ፉርሽ የሚያደርገው እንደ ጀርመን፣ ጣሊያን፣ ኔዘርላንድ፣ ኦስትሪያ፣ ብራዚል ወዘተ ባሉ አገሮች ውስጥ ብሔርተኛ ድርጅቶች መፈጠራቸውና ጉልበት ማግኘታቸው ነው። በምዕራቡ አገራት ተቀባይነት እያገኙ የመጡት ብሔርተኛ ድርጅቶች አዲስ አገር የመመሥረት ዓላማ ያላቸው እንዳይደሉት ሁሉ ማንኛውንም ብሔርተኛ ድርጅት እንደ ተገንጣይ እና አገር መሥራች አድርጎ መመልከት ትክክል ያልሆነ አስተሳሰብ ነው። በመሠረቱ የማንነት ብሔርተኝነት የአገር ምሥረታን የሚመለከትበት አግባብ በቅጡ ከተጤነ እንዲህ ዓይነት የጅምላ ተቃውሞ ትክክል አለመሆኑን መረዳት ይቻላል።

ምሳሌ፤

ተመሣሣይ ቋንቋ የሚናገር አንድ ማህበረሰብ አለ እንበል። ይህን ቋንቋ አማርኛ እንበለው። ይህ አማርኛ ተናጋሪ ማህበረሰብ ተመሳሳይ ባህላዊ እሴቶችን፣ ባሕልን እና እምነቶችን ይካፈላል እና በአጠቃላይ አንድ ሃይማኖት አለው እንበል። በጊዜ ሂደት እነዚህ የማህበረሰብ አባላት (አማሮች) የራሳቸውን ማንነት ያዳብሩ እና የተለያዩ ቋንቋዎችን ከሚናገሩ ወይንም የተለየ እምነት ካላቸው ከሌሎች ቡድኖች የተለዩ ይሆናሉ። ብሔር ይሆናሉ ማለት ነው። ከጊዜ በኋላ ደግሞ እነዚህ የአማርኛ ተናጋሪ ብሔር አባላት ማንነታቸውን የሚስብ የጂኦግራፊያዊ አካባቢን (መልክዓ ምድርን) ይወስናሉ። ይህን አደረጉ ማለት ግን አዲስ አገር ፈጠሩ ማለት አይደለም። በዚህ ደረጃ ያለ ሁናቴ በእንግሊዝኛው አጠራር “nation” ይባላል፤ ወያኔ “nation” የሚለውን ቃል” ብሔር ብሔረሰቦች” ብሎ ይጠራዋል፤ ወያኔ የተጠቀመበት ቃል ትክክለኛ ፅንሰ-ሃሳቡን ካለመግለፁም በላይ ብሔር የሚለውን የማንነት መግለጫ ቃል ከ”nation” ጋር በድርብ መጠቀሙ ውዥምብርን ፈጥሯል። ለ”nation” በጣም የሚቀርበው ቃል ክፍለ-ሃገር የሚለው ነው። ክፍለ-ሃገር ሉዓላዊ ግዛት የለውም። ስለዚህ የማንነት ብሔርተኝነት ከግዛት (realm) ጋር የተያያዘ አይደለም፤ ብቻውን የቆመ ነው፤ የሚወክለው ማህበረሰቡን ነው፤ ግዛቱን አይደለም። የብሔሩ ያሉበት አካባቢ በሙሉ የብሔሩ ክፍል ነው። ለዚህም ይመስለኛል አብዛኞቹ የአማራ ብሔርተኛ ድርጅቶች የአማራ አገሩ መላው ኢትዮጵያ ነች የሚሉት።

ኔሽን (ክፍለ-ሃገር) ሉዓላዊነት የለውም። ኔሽን ሉዓላዊ ሆኖ ወደ አገርነት ለመቀየር ሀገረ-መንግሥት (state-nation) መመስረት ይኖርበታል። ይህ ደግሞ እውን የሚሆነው ኔሽኑ ፖለቲካዊ አንድነት ለመፍጠር የሚያስችሉ የመንግስት መዋቅሮችን ማቋቋም ሲጀምርና ጂኦግራፊያዊ ወሰኑን መጠበቅ ሲጀምር ነው።

በመሆኑም የአማራ ብሔርተኝነት አሁን ባለበት ደረጃ የሀገረ-መንግሥትነት ጥያቄ የለውም። አለው እንኳን ቢባል ሊኖረው የሚችለው የነጻ-መንግሥትነት ጥያቄ እንጅ የሉዓላዊነት አይደለም።

ሶስተኛው ምክኒያት የአማራ ህዝብ በተለይም የአማራ ምሁራን የፕሮፓጋንዳ ሰለባ መሆናቸው ነው። ባለፉት አርባ አመታት አማራው “የኢትዮጵያ ጠባቂ” ተደርጎ እንዲሳልና የማንነት ብሔርተኝነት ኢትዮጵያን የማፍረስ እንቅስቃሴ ነው ብሎ እንዲያምን እና ዘወትር ተቃዋሚ ሆኖ እንዲሰለፍ በጥናት ላይ የተመሰረተ ፕሮጋንዳ ተሰርቶበታል። ይህ ፕሮፓጋንዳ አማራው ያለበትን ሁኔታ እንዳያስተውል ከመገደቡም በላይ የአማራው ህዝብ የማንነት ብሔርተኝነትን በሩቁ እንዲፀየፈው አድርጎታል። በፀረ-አማራ ቡድኖች የተዘጋጀለት አደገኛ ወጥመድ አማራው በኢትዮጵያ ስም ገንዘቡን፣ ሃብቱና ንብረቱን ለሌቦች እንዲገብር አድርጎታል። ከምንም በላይ ይህ የፕሮፓጋንዳ ወጥመድ አማራው በሁለት ጎራ ተከፍሎ እርስበርስ እንዳይስማማ አድርጎታል። አሁንም ቢሆን በህብረ-ብሔራዊነት ወይንም በዜግነት ብሔርተኝነትና በማንነት ብሔርተኝነት ጎራ ለይቶ እርስበርሱ እየታገለ የሚገኘው አማራው ነው።

አራተኛው ምክኒያት ህወሓት ያራምደው የነበረው የበላይነት ብሔርተኝነት (superiority nationalism) በዜግነት ብሔርተኝነት አራማጆች ላይ የፈጠረው የተጠቂነት ስሜት (victim mentality) ነው። ይህ የተጠቂነት ስሜት የማንነት ብሔርተኝነት ሁሉ እንደ ህወሓት ጨፍጫፊ፣ አሳሪ፣ ዘራፊ እና አፋኝ መስሎ እንዲታያቸው አድርጓል።

ማጠቃለያ
——-

ሲጠቃለል የማንነት ብሔርተኝነት እንደ ማንኛውም የብሔርተኝነት እንቅስቃሴ መልካምም መጥፎም ጎኖች ይኖሩታል። መጥፎ ነገሩን ብቻ እየነቀሱ አማራው ተደራጅቶ እንደ ብሔር የሚደርስበትን ጥቃት እንዳይከላከል ማድረግ በምንም መመዘኛ ትክክል ሊሆን አይችልም። ባለፉት 40 ዓመታት ኢትዮጵያዊ ነኝ ብሎ የሚታገል ድርጅት ወይንም ቡድን የቀድሞ ሥርዓት
ናፋቂ፣ ጨቋኝ፣ በዝባዥ እና ትምክህተኛ አድርጎ በመፈረጅ ከፖለቲካው ምህዳር እንዲገለል ሲደረግ ቆይቷል። አማራው ራሱን ያደረጀው ኢትዮጵያዊ በሚለው ብሔርተኝነት ሥር ብቻ ስለነበር ተጎጅ ሆኗል። በእቅድ የተፈፀመው አማራን የማግለል እኩይ ተግባር አማራው ከአገራዊ የፖለቲካ ተሳትፎ ውጭ እንዲሆን አድርጎታል። አሁን ደግሞ ሁኔታውን በአንክሮ ያጠኑ በአብዛኛው ወጣት አማሮች የአማራን ብሔርተኝነት በማራመድ ከፖለቲካ ውይይት ውጭ የተደረገውን ህዝብ ወደ ውይይት መመለስ ሲጀምር በማንነት ላይ የተመሰረተ ብሔርተኝነትን “አደገኛ” አድርጎ ማስቀመጥ አማራው ይዞት የሚነሳውን አጀንዳ በሙሉ ጥቅም የለሽ ወይንም ጎጅ በማድረግ አማራው በተቀውሞ ጎራ ብቻ እንዲሰለፍና የሥልጣን ተጋሪ እንዳይሆን የማድረግ የተለመደ አካሄድ ነው። የማንነት ብሔርተኝነት የተጠላው አማራ ሲያራምደው ነው። የማንነት
ብሔርተኝነት ዱሮም የነበረ ወደፊትም የሚኖር ነው። የማንነት ብሔርተኝነትን በማራመድ የአማራ ህዝብ የመጀመሪያም የመጨረሻም አይደለም።

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s