ዶ/ር አብይ ለኢትዮጵያ አንድነት ካሰበ የሸዋ ሁኔታ ሊያጤነው ይገባል – ተስፋዬ መኮንን

በሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይና በኦሮሞ ነጻነት ግንባር መሪዎች ፊታውራሪነት የተዘጋጀውና የፀደቀው የሽግግር ቻርተርም ሆነ አሁን በሥራ ላይ ያለው ሕገ መንግሥት ተቀዳሚ ዓላማ፣ በ1960ዎቹ ሲቀነቀን የነበረውን ታሪካዊ መሠረት የሌለው የብሔር ብሔረሰብ ትርክት መሠረት በማድረግ፣ ጨቋኝ ተብሎ የተፈረጀውን አማራ ማሳነስ ነው፡፡ የሕወሓትና ኦነግ መሪዎችና ሌሎች የኢትዮጵያን የአገረ መንግሥት ግንባታ ታሪክ በቅጡ ያልመረመሩ ኀይሎች እንደያወሩለት የዚህ ሕገ መንግሥት ዋና ዓላማ የሕዝቦችን እኩልነት ማረጋገጥና ዲሞክራሲያዊ አንድነትን አይደለም፤ አማራውን በሕዝብ ቁጥር (ዲሞግራፊ) እና በግዛት (ጆግራፊ) ማሳነስ ነው፡፡

ባለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት የታየው እውነታ እንዳረጋገጠው ይህ በመሠረተ-ቢስ ትርክት ላይ የተመሠረተ ሕገ መንግሥት በኢትዮጵያ ነገዶች መካከል እጅግ አደገኛ መጠራጠርና ግጭት ፈጥሯል፤ ሕዝብ በነጻነት መክሮና ዘክሮ ያፀደቀው ሕገ መንግሥት እስከሌለ ድረስ አሁን በተያዘው መንገድ ከቀጠልን አገራችን ወደከፋ መከራና የእርስ በርስ ጦርነት ልትገባ የምትችልበት ዕድልም በጣም ሰፊ ነው፡፡ ሦስት ዐሥርት ለሚጠጉ ዓመታት እንዳነው ከዚህ ሕገ መንግሥት ያተረፍነው የኢትዮጵያዊያንን መፈናቀልና መሳደድ ነው፤ የምንታዘበው የማያባራ ግጭት ነው፡፡

ይህ ሕገ መንግሥት በሥራ ላይ እስካለ ድረስ የመሬት ይገባኛል ጥያቄ ይቀጥላል፡፡ በመሬት ይገባኛል ምክንያት እየተከሰተ ያለው የዜጎች ስደትና ሞት አይቆምም፤ እንዲያውም በግልጽ እንደሚታየው እየጨመረ ይሄዳል፡፡ ዘላቂው መፍትሔ በውሸት ትርክትና በቋንቋ ላይ የተመሠረተውን ግጭት ፈልፋይ አወቃቀር ከሥረ መሠረቱ መቀየር ነው፡፡ ከዚያ መለስ ያለው እርምጃ ሁሉ ጊዜያዊ ማስታገሻ ካልሆነ በስተቀር ሀገርና ሕዝብ በዘላቂነት የሚጠቀሙበት መፍትሔ አይደለም፡፡

እንደሚታወቀው መቶ በመቶ በኢሕአዴግና አጋሮቹ የተያዘው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በቅርቡ የማንነትና አስተዳደራዊ ኮሚሽንን በአዋጅ አቋቁሟል፡፡ ኮሚሽኑ በየአካባቢው በማንነትና ወሰን ጉዳዮች የሚነሱ ጥያቄዎችን እያጠና የመፍትሔ ምክረ-ሐሳብ የሚያቀርባና ከሚመለከታቸው መንግሥታዊ አካላት ጋር በመሆን የሚያስፈፅም ነው ተብሏል፡፡ በእኔ አስተያየት በተሳሳተ ትርክት በቋንቋ ላይ የተመሠረተው ፌደራላዊ ሥርዓት ምክንያት የሚፈጠሩ ችግሮች በዚህ ኮሚሽን አማካይነት ሊፈቱ ባይችሉም፣ ዘላቂ መፍትሔዎችን በመጠቆም ረገድ የራሱ አስተዋጽዖ ይኖረዋል፡፡

ከሁሉ አስቀድሞ፣ ይህ ኮሚሽን ሕዝበ-ውሳኔ የሚያስፈልጋቸውንና ሕዝበ-ውሳኔ ሳያስፈልግ መታጠፍ ያለባቸውን አካባቢዎች በግልጽ ለይቶ ማስቀመጥ ይኖርበታል፡፡ ለምሳሌ ያህል የሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ መሪዎች የወልቃይት ጠገዴን መሬት ነባሩን ሕዝብ በመመንጠርና የራሳቸውን ታጋይና የቀን ሠራተኞች እንዳሰፈሩበት በግልጽ ይታወቃል፡፡ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ሊገነዘበው የሚገባ ሐቅ አለ፤ ወልቃይት ጠገዴ ላይ ከየትኛውም የአገራችን አካባቢ በከፋ መልኩ በመንግሥት የተቀነባበረ ዘር መንጠራ ተካሂዷል፡፡ ነባሩ ሕዝብ ተመንጥሯል፡፡ ለዚህ አስከፊ ወንጀል ኀላፊነት የሚወስዱት ደግሞ ከሕወሓት የለቀቁትም ይሁኑ አሁንም ድርጅቱን የሚመሩት ግፈኛ የድርጅቱ መሪዎች፣ እንዲሁም የእነሱን ጉዳይ ሲያስፈፅሙ የነበሩት እንደ አዲሱ ለገሰና በረከት ስምኦን ያሉ የብአዴን መሪዎች ናቸው፡፡ ስለሆነም ይህ ኮሚሽን ወልቃይት ጠገዴ ላይ የተከሰተውን ዘግናኝ ወንጀል በሚገባ መርምሮ ይህን ወንጀል የፈፀሙና ያስፈፀሙ አካላት ተጠያቂ የሚሆኑበትን መንገድ ማመቻቸት ይገባዋል፡፡ በአገራችን በየትኛውም አካባቢ፣ በየትኛውም ሕዝብ ላይ ግፍ ሊፈፀም አይገባም የሚል እምነት ያለው የመንግሥት ባለሥልጣን፣ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪ፣ ምሁር፣ የሃይማኖት አባትና የአገር ሽማግሌ ሁሉ ወልቃይት ጠገዴ ላይ በሕወሓት መሪዎች ፊታውራሪነት የተፈፀመውን ኢሰብአዊ ድርጊትና የሕዝብ ምንጠራ በማያሻማ ቃል ማውገዝ ይጠበቅበታል፡፡

በሌላ በኩል ከወንጀለኞች በቀር ሁሉም ኢትዮጵያዊ ወልቃይት ጠገዴ የጎንደር/አማራ ታሪካዊ ግዛት መሆኑን ጠንቅቆ ስለሚያውቀውና ሐቁም እሱ ስለሆነ፣ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ወደ ነባር ማንነቱ እንዲመለስ ያስፈልጋል፡፡ ወልቃይት ጠገዴ ሳይመለስ በትግራይና በአማራ ሕዝቦች መካከል ዘላቂ ሰላም ይፈጠራል ማለት ዘበት ነው፡፡ ወደ ቀልባቸው ከተመለሱ ይህን ሐቅ የሕወሓት መሪዎችም ሊስቱት አይችሉም፡፡

በተመሳሳይ መልኩ አማራውን በመሬትም በሕዝብ ቁጥርም ለማሳነስ በተቀየሰው በሕገ መንግሥት በተደገፈ እርምጃ ምክንያት የተወሰዱት ራያና መተከልም ወደ ነባር ይዞታቸው መመለስ ይገባቸዋል፡፡ ራያና መተከል ላይ ሕዝበ-ውሳኔ ብሎ ነገር ቀልድ ነው፡፡ ስለ ሕዝበ ውሳኔ መወራት ያለበት አናሳውን መብት ለማስከበር ሲባል ብዙሃኑ በርስቱ በአስከፊ ጭቆና ውስጥ እንዲገባ ስለተደረገበት ኬሚሴ ነው፡፡ የነገዶችን በቋንቋቸው የመጠቀም መበት አስከብራለሁ የሚለው ሕወሓትና ኦነግ ሥርዓት ለአማሮች ሲሆን አይሠራም፡፡ ኬሚሴ ላይ ያለውን እጅግ አሳዛኝና በምንም ዓይነት መልኩ ተቀባይነት የሌለው ሁኔታ መመልከት በቂ ነው፡፡ ስለሆነም የተቋቋመው ኮሚሽን ኬሚሴ ላይ ሕዝበ-ውሳኔ የሚደረግበትን መንገድ ማመቻቸት ይጠበቅበታል፡፡

ሸዋ እና ኢትዮጵያ
****
ባዕዳን የኢትዮጵያ ጠላቶችም፣ የኢትዮጵያ የትንሽነት ኀይሎችም ሸዋን በሚመለከት የሚጋሩት ነገር አለ፡፡ ሁሉም ሸዋን በከፍተኛ ጥርጣሬና ጥላቻ ነው የሚያዩት፡፡ ሁሉም ሰንድ አዘጋጅተው ዘምተውበታል፡፡ ስለ “አንኮበርና አንጎለላ ሥነ-ልቦና” ብዙ ጽፈዋል፤ ሸዋ ስለሚዳከምበት ሁኔታ የተቀናጀ ዘመቻ አድርገዋል፡፡ አሁንም አልቆመም፡፡
የዚህ ሁሉ ውርጅብኝ ምክንያቱ በሚገባ ይታወቃል፤ ሸዋ የመካከለኛውና የዘመናዊቷ ኢትዮጵያ እምበርት ስለሆነች ነው፡፡ የዘመናዊት ኢትዮጵያ አርክቴክቶች የዚህ አካባቢ መሪዎች ስለሆኑ ነው፡፡ በእርግጥ ምክንያቱ ይህ ብቻ አይደለም፤ ከዚህም በእጅጉ ይሰፋል፡፡ ሸዋ አማራው፣ የጉራጌው፣ የኦሮሞው፣ የሃድያው፣ የከምባታው፣ የየሙና የሌላውም ነገድ ውሕድና ኅብር ስለሆነች ትንሿ ኢትዮጵያ ናት፡፡ በዚህም ምክንያት ኢትዮጵያን ማሳነስና ማዳከም የሚፈልግ ማንኛውም ኀይል ሸዋን ማሳነስና ማዳከም ይፈልጋል፡፡

የሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ ባለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት ሰነድ አዘጋጅተው ከተማሪ እስከ ፕሮፌሰር፣ ከመንግሥት ሠራተኛ እስከ ጥቃቅንና አነስተኛ ማኅበር አባላት ስለ ሸዋ እኩይነት አሰልጥነዋል፡፡ ከፍ ብሎ እንደተጠቀሰው የዚህ ሁሉ የጥፋት ተግባር ዋና ዓላመው ኢትዮጵያን ለመቆጣጠር የኢትዮጵያ ምልክት የሆነችውን ሸዋን ማሳነስና ማዳከም አስፈላጊ ነው የሚል ስትራቴጅ ስላላቸው ነው፡፡

ከኢትዮጵያ ፍርስራሽ ኦሮሚያን እንመሠርታለን የሚለው ኦነግና የእሱን ዓላማ የሚያስፈጽሙ ኀይሎችም ሸዋን ለማሳነስና ለማዳከም የማይፈነቅሉት ድንጋይ የለም፡፡ የእነሱን አካሄድ ለየት የሚያደርገው የማሳነስና የማዳከሙ ሥራ መልኩን ቀይሮና የሸዋን ኅብር አጥፍቶ ኦሮሞ በማድረግ የሚገለጽ መሆኑ ነው፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ መንግሥት ለኢትዮጵያ አንድነት፣ ሁለንተናዊ ልማትና ሰላም የሚጨነቅ ከሆነ፣ የሸዋን ጉዳይ በልዩ ሁኔታ ሊያጤነውና መፍትሔ ሊሰጠው ይገባል፡፡ ሸዋ ውስጥ የማይኖር ነገድ ስለሌለ፣ በዚህና ለአገረ መንግሥት ግንባታ ባደረገችው ግንባር ቀደም አስተዋጽዖ ምክንያት፣ ሸዋ የኢትዮጵያ ቀንዲል ስለሆነች፣ በልዩ ሁኔታ ታይታ የራሷ አስተዳደራዊ ግዛት እንዲኖራት ማድረግ ይገባል፡፡

“ድምፅ አልባ ጩኸት!” የታፈነው የመድፈር እና የሕገ ወጥ ጉዲፈቻ ታሪክ

በጌታቸው ወርቁ

ሦስት ጉስቁል ኢትዮጵያዊያን በዕድሜ የገፉ ሴቶች ቁጭ ብለው በምልክት ቋንቋ እያወሩ ለስላሳ ይጠጣሉ፡፡ ፊታቸው የተጎሳቆለ፣ አለባበሳቸውም እነደነገሩ ቢሆንም፣ ልብ የሚያሞቅ እውነተኛ ፈገግታ አላቸውና ተግባቦቴን ቀለል አድርገውልኛል፡፡ አንዲት ረዘም ያለች ግዙፍ ፈረንጅ (አሜሪካዊት) እና አቶ መላክነህ፣ ሦስቱን ሴቶች ያስተናብራሉ፡፡ በምልክት ቋንቋ ያወሯቸዋል፡፡ሠላምታ ከተለዋወጥን በኋላ፣ ለአሜሪካዊቷ ራሴን እና የጋዜጠኝነት ሙያዬን አትኩሮትና ማኅበራዊ ኃላፊነት በተመለከተ አጭር ገለጻ አደረግኩ (ይህንኑ በምልክት ቋንቋ ነገረቻቸው)፡፡

ወደ እኔ ዘወር ብላ፤ “የታሪኩ መቼት (Setting) የሆነው መስማት የተሳናቸው ዜጎች ት/ቤት፣ ወላጆቼ ከአሜሪካን አገር መጥተው የመሠረቱት ነው፡፡ አዝናለሁ፤ በት/ቤቱ ተፈጥሯል የተባለውን የሰብኣዊ መብቶች ጥሰት አሁን በቅርቡ ወደ አዲስ አበባ ስመለስ ነው የሰማሁት፡፡ ግለሰቡን (የትምህርት ቤቱ ዳይሬክተር የነበረ) በሕግ ተጠያቂ ለማድረግ ‹ይርጋ› ይዘጋዋል የሚል የሕግ ባለሙያዎች ስለገለጹልን በብዙኃን መገናኛ ጉዳዩን ወደ አደባባይ ማውጣት ከቻልን ለሌሎች መማሪያና መነጋገሪያ ሊሆን ይችላል በሚል ነው አንተን ያገኘንህ፡፡” (ለእነርሱም ይህንኑ በምልክት ቋንቋ አስረዳቻቸው፡፡)

ታሪኩ ባጭሩ

በ1970ዎቹ መጨረሻ እና በ1980ዎቹ መጀመሪያ በቀድሞ አጠራሩ “የኢትዮጵያ ደናቁራን ማኅበር”፣ በአሁኑ ስያሜው ደግሞ “መካኒሳ መስማት የተሳናቸው ትምህርት ቤት” ዳይሬክተር (ሥሙ ለዚህ ጽሑፍ ሲባል የተሸሸገ) በወቅቱ የትምህርት ቤቱ ተማሪ የነበሩ ታዳጊ ወጣት ሴቶችን ቢሮ ውስጥ አስገድዶ እየደፈረ፣ ወጣቶቹ ሲያረግዙ፣ ከት/ቤቱ ገለል እንዲሉ በማድረግ፣ ሲወልዱ ደግሞ ልጆቻቸውን በግብረ ሰናይ ድርጅት በኩል በጉዲፈቻ ወደ ውጭ አገራት የሚልክ ተባባሪ በመምሰል ድርጊቱን ሲያዳፍን እንደነበረ ተጎጂዎቹ ለዚህ ጽሑፍ አቅራቢ አስረድተዋል፡፡ የትምህርት ቤቱን ሴት ተማሪዎች የመድፈር ተደጋጋሚ ድርጊት መስማት በተሳናቸው ማኅበረሰብ ዘንድ በጉልህ የታወቀ ሲሆን፣ በንግግር በሚግባባው አብዛኛው ማኅበረሰብ ዘንድ ግን የተሰወረ ነበር፡፡ እነሆ አሁን ከሠላሳ ዓመታት በኋላ ሴቶቹ ልጆቻቸውን ከመፈለጋቸው ጋር በተያያዘ ወደ አደባባይ እየወጣ ነው፡፡ “በድብቅ የሠሩትን በአደባባይ…” ይሏል ይህ ነው፡፡ ባለታሪኮቹ መስማት የተሳናቸው ሦስት ጉስቅል ወልደው የተቀሙ ሴቶች ናቸው፡፡ ፅጌ መኮንን፣ ወጋየሁ ወርቁ እና ታደለች አረዳ ይባላሉ፡፡ ከእነርሱ ጋር በምልክት ቋንቋ ለመግባባት በአስተናባሪነት የረዱን አቶ መላክነህ ሙሉጌታ እና በማስተርጎም የተባበሩን ደግሞ አቶ አምሳሉ ደሴ ናቸው፡፡ ተጠቂዎቹ ይናገራሉ!የፅጌ ታሪክ“በመጀመሪያ መንታ ልጆቼን ማግኘት ነው የምፈልገው፡፡ በታዳጊ ወጣትነቴ ጊዜ በአሁን አጠራሩ “መካኒሳ መስማት የተሳናቸው ት/ቤት” በምማርበት ጊዜ በዳይሬክተሩ ተደፍሬ የወለድኳቸው ሁለት ልጆች አሉኝ፤ እነርሱን ማግኘት ነው የምፈልገው፡፡ እናታችሁ እኔ ነኝ ብዬ ልገልጽላቸው እፈልጋለሁ፤ ልስማቸው እፈልጋለሁ፡፡ ልጆቼ ይናፍቁኛል፡፡ ልጆቼ ያለፈቃዴ፣ በጉዲፈቻ ወደ ውጪ አገር የተወሰዱት ገና አንድ ዓመት እንኳ ሳይሞላቸው ነው፡፡ እነዚህ ልጆች የተፈጠሩት የአምስተኛ ክፍል ተማሪ ሳለሁ፣ ዳይሬክተሩ ወደ ቢሮ ይጠራኝና ቢሮውን ቆልፎ አስገድዶ ከደፈረኝ በኋላ ነው፡፡

“ስድስተኛ ክፍል ደርሼ በመማር ላይ ሳለሁ ሚያዚያ አካባቢ ሆዴ ገፍቶ እርግዝናው ስላስታወቀብኝ እና የመውለጃ ጊዜዬም ስለደረሰ፤ ትምህርቴን አቋርጬ፣ መንታ ልጆቼን ወለድኳቸው፡፡ ያኔ ዳይሬክተሩ ጠርቶኝ ሲደፍረኝ፣ ተማሪዎቹ ሁሉም ያውቃሉ፡፡ መምህራንም ያውቃሉ፡፡ ዳይሬክተሩ ተማሪዎችን ቢሮ እያስገባ ምን እንደሚያደርግ ሁሉም ያውቃሉ፡፡ ግን ማንም አልተከላከለልኝም፡፡“ተደፍሬ ስወጣም ልጆች ‹ምንድን ነው› ብለው ሲጠይቁኝ ምንም አይደለም ብዬ ዋሸኋቸው፡፡ ምክንያቱም ዳይሬክተሩ ቢሮ አስገብቶኝ ከደፈረኝ በኋላ፣ ‹ለማንም እንዳትናገሪ!› ብሎ አስፈራርቶኝ ነው የለቀቀኝ፡፡ በዚህ ላይ ‹ምንድን ነው ብለው ከጠየቁሽ፣ ቤተሰብ ፈልጎኝ ስልክ ስለተደወለልኝ መልዕክቱን ለማስተርጎም እንደረዳሁሽ ተናገሪ› ብሎ አስጠንቅቆና አስፈራርቶ ነው የለቀቀኝ፡፡ “ግን እዛ ትምህርት ቤት ያለን በሙሉ እርስ በእርስ ሁኔታውን እናውቃለን፡፡ እዛ ውስጥ እንዲህ ዓይነት የመደፈር ሁኔታ ያልገጠማት የለችም። [ወደ ሌላኛዋ ጓዳቸው እየጠቆሙ] እርሷ (ታደለች) ግን ከአንዴም ሁለት፣ ሦስት ጊዜ ታግላ አምልጣው ወጥታለች፤ ጠንካራ ነበረች። ለዚህ ነው ‹ጀግና ሴት ነኝ› የምትለው፡፡ የምትፎክረው፡፡ “መንታ ልጆቼን የወለድኩት ሐምሌ 16 ቀን 1987 እ.ኤ.አ ነበር፡፡ ያኔ የ14 ዓመት ልጅ ነበርኩ፡፡ ልጆቼ ሁለቱም ሴቶች ናቸው፤ ገና አንድ ዓመት ሳይሞላቸው ነው የተወሰዱብኝ፡፡ ልጆቼን በጉዲፈቻ የወሰዷቸው ፈረንጆች ናቸው፡፡ ልጆቼንም የሰጠኋቸው እኔ ፈቅጄ አይደለሁም፡፡ እኔ ሁለቱንም ልጆቼ በጣም ነው የምወዳቸው፡፡ እናቴ ናት የሰጠቻቸው፡፡ ለዚህ ሁሉ የዳረገን ድህነታችን ነው፡፡ ልጆቼ የተሰጡት በእናቴ ተሸንፌ ነው፤ ግን ስላላስቻለኝ በጣም እጨነቅ ነበረ፡፡ ድሀ ብንሆንም እናቴ ምንም ዓይነት ብርም ሆነ ቁሳቁስ ከፈረንጆቹ አልተቀበለችም፡፡ “በጉደፈቻ ከሄዱም በኋላ ስለነርሱ ሰምቼ አላውቅም፤ ግን የተለያዩ መረጃዎችን ቀበሌ ተቀምጠው ነበረ፡፡ እንዲሁም በተለያየ ጊዜ ደብዳቤ ይላክልን ነበር፡፡ እናም የመንትያ ልጆቼን ፎቶ ተልኮልኛል፡፡ የልጆቼ አሳዳጊ ፈረንጅ ልጆች ፎቶዎችም አብሮ አለ፡፡ ልጆቼ ሲወሰዱብኝ በጣም ተበሳጭቼ ስለነበር፣ አንጀቴ አልችል ስላለ ትቼ ሔጄ ነበር፤ ተመልሼ በምመጣበት ሰዓት፣ ይዘዋቸው ሲሔዱ አየሁ፤ ፈረንጆቹ ከመውሰዳቸው በፊትም ፎቶ አንስተዋቸዋል፡፡ ያንን ፎቶ እና ከወሰዷቸው በኋላ ያነሷቸውን ፎቶዎች አብረው ልከውልናል፡፡ የሔዱት ምን አልባት አሜሪካ ሊሆን ይችላል፤ ወይም አውሮፓ፡፡ ሰዎቹ ፈረንጅ ናቸው፡፡ በትክክል ሀገሩን አልነገሩኝም፤ ስለዚህ አላውቅም፡፡”ፅጌ መንታ ልጆቻቸው በጉዲፈቻ ሲሰጡ፣ (በደርግ ጊዜ) ጉዲፈቻ የሰጠው ድርጅት ይኑር አይኑር ለጊዜው ባይታወቅም፤ ሙሉ የተሟላ መረጃ ባይሆንም ከፊል ሰነዶች ግን አሉ፡፡ ምርመራ ቢጀመር ጠቃሚ ፍንጮች አሉ ባይ ናቸው፡፡ወጋየሁም እንደ ፅጌ “እኔም የምፈልገው ልጄን ማግኘት ነው፡፡ ልጄ በሕፃንነቱ ነው የተወሰደብኝ፡፡ ከዛ በኋላ ልጄን አይቼው አላውቅም” ይላሉ፡፡ ከወጋየሁ ገለጻ ለመረዳት እንደሚቻለው ልጃቸውን የወለዱበት ቦታ ዘውዲቱ ሆስፒታል ይመስላል፡፡ አጠገቡ ቤተክርስቲያን አለ፣ ጠበል አለ፤ በማለት ያስረዳሉ፡፡ (የእርሳቸው የምልክት ቋንቋ መደበኛው አይደለም፤ ልማዳዊው ነው፡፡ ጠበል የሚሉት ፍልውኃን ሊሆን ይችላል፡፡) የወጋየሁ ታሪክአስተርጓሚው እንደተረከው “ትምህርቷን ያቋረጠችበት ምክንያትም ይኸው የትምህርት ቤቱ ዳይሬክተር በ13 ዓመቷ ደፍሯት በማርገዟ ነው፡፡ አፍራና ተሸማቃ ነው ከትምህርት ገበታዋ የቀረችው፡፡ መጀመሪያ ሰውየው ከትምህርት ቤት እንድትወጣና ወደ ሆነ ቦታ እንድትሔድ አደረጋት፡፡ ቦታውን ስትገልጽ ጫካ አለ፤ ቤተክርስቲያን አለ፤ ወደ አሮጌው ኤርፖርት አካባቢ ነው (አሁን ጦር ኃይሎች የሚባለው ሠፈር) ከትምህርት ቤት አስወጥቶ ወደዚህ ሥፍራ ወሰዳት፡፡ ከትምህርት ቤት እንድትወጣ የተደረገው በትዕዛዝ ነው፡፡ አንዲት ሴት መምህርት ናት ሒጂ ብላ ያስወጣቻትና የዚህ ሰውዬ መኪና ውስጥ ታስገባታለች፡፡ 

“በመኪና ወስዷት በወቅቱ ጫካ ወደ ነበረ ሥፍራ ወስዶ ከደፈራት በኋላ፣ የመመለሻ የትራንስፖርት ብር ሰጥቷት ይመለሳል፡፡ ከዛ ከወትሮው አምሽታ ወደ ቤት በመመለሷም ከቤተሰብ ጋር ትጋጫለች- የት አመሸሽ በሚል፡፡ በዚህ የተነሳም ከዚህ በኋላ ትምህርት ቤት አትሔጂም ተባለች፤ ለሕይወቷ የሚያስፈልጋትን መደበኛ የምልክት ቋንቋም ሳታውቅ ቀረች፡፡ ምክንያቱም ትኖር የነበረው ከአያቷ ጋር ስለነበር፣ ቤት ውስጥ ቀረች፡፡ “ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ይኸው የደፈራት ሰው በተመሳሳይ ቤት ይመጣና፣ ምንም እንደማያውቅ ሰው፣ ለምን ከትምህርት ቤት እንደቀረች ይጠይቅና ልጅ እንደተወለደ ይነገረዋል፡፡ ልጁ ጉዲፈቻ ለፈረንጅ እንዲሰጥ ሐሳብ አቅርቦ ተፈፃሚ ያስደርጋል፡፡ የእሷም ልጅ (ወደ አሜሪካ ይመስላታል) በጉደፈቻ ተሰጠ፡፡ “የሁለቱም ሴቶች ደፋሪ የተባለው፣ የትምህርት ቤቱ ዳይሬክተር የነበረ ነው፡፡ ልጇንም ወደ ውጪ በጉዲፈቻ የላከው ይኸው ሰው እና የእርሷ አያት ተስማምተው ነው፡፡ ይህ ሲሆን እርሷ አታውቅም፤ ፈቃደኛም አልነበረችም፡፡ ካደገ በኋላ የልጇ ፎቶ በአያቷ በኩል ደርሷታል፡፡ ፎቶ ይላክላቸው ነበር፡፡ የተለያዩ ሰነዶችም ይላካሉ፡፡ የልጇ ፎቶም የአንድ ዓመት፣ የሁለት ዓመት፣ የአራት ዓመት እያለ የተነሳቸውን ፎቶዎች ነው የተመለከተችው፡፡ ልጁ ሲወሰድ የነበረውን ትክክለኛ ዕድሜ አታውቅም ግን ‹ገና እያጠባሁ በነበረበት ወቅት ነው› ትላለች፡፡ “በዚህ ሒደት ውስጥ አያቴ ገንዘብ ስትቀበል አላየሁም፤ የማውቀውም ነገር የለም፤ እንዲህ ታደርጋለች ብዬ አላስብም፤ ‹እኔ ያየሁት ልጁን ወስደው ወደ መኪና ውስጥ ሲያስገቡት ነው፡፡ ያኔ አያቴ ልጁን ለፈረንጆች በጉዲፈቻ ለመስጠት ስትወስን፣ እኔ ተበሳጭቼ ስለነበር እየሮጥኩ ሸሽቼ ሔጄ ብቻዬን ሳለቅስ ነበር፣ በኋላ ስመለስ ነው ወደ መኪና ሲያስገቡት የተመለከትኩት፡፡ ከሔዱ በኋላ ምናልባት አያቴ በስልክ አግኝታ አነጋግራቸው ከሆነ አላውቅም እኔ ግን በግሌ ልጄን ማየት እፈልጋለሁ፤ ማግኘት እፈልጋለሁ፤ መሳም እፈልጋለሁ› ነው የምትለው” ይላል፡፡የታደለች ታሪክበዚህ መስማት የተሳናቸው ዜጎች ትምህርት ቤት ውስጥ ከዳይሬክተሩ ብርቱ የብረት መዳፍ ከአንዴም ሁለትና ሦስት ጊዜ በልጅነታቸው በትግል ያመለጡት እና ገፍትረውን እንደተረፉ ጓደኞቻቸውም ጭምር የሚመሰክሩላቸው ታደለች ናቸው፡፡ ዛሬ በኑሯቸው ቢጎሳቆሉም ቁመታቸው ዘለግ ያለ፣ ሰውነታቸውም ደንዳና እንደ ነበር ያስታውቃል፡፡ “እኔ ሰውዬው ቀደም ብሎ ሌሎች ላይ የሚያደርገውን ስለምታዘብ፣ በጭራሽ አላምነውም፡፡ ሌሎቹን ባታለለበት ወጥመድ፣ ለምሳሌ የስልክ መልዕክት እንደመጣልንና እርሱ እያስተረጎመ ሊያግባባን እንደሆነ አድርጎ ወደ ቢሮ ሲጠራኝም በሩን ይዤ ነው የምቆመው፡፡ ወይም ወደ ሌላ ቦታም እንድሔድ ከፈለገ ሌሎች ተማሪዎችና ሰዎች ከሌሉ አልሔድም፡፡ ገፍቶ መጥቶም ከቢሮው በር አታሎ ወይም በጉልበት ሊያስገባኝ ሲል እኔም ያለ የሌለ ጉልበቴን ተጠቅሜ ታግዬው አመልጣለሁ፡፡ ሦስት ጊዜ አሸንፌው ወጥቻለሁ” ብለዋል።

ታደለች እየሳቁ ሲቀጥሉ እነዚህ [የክፍል ጓደኞቿን] ደካሞች ነበሩ፡፡

ያምኑታል፡፡ እኔ ግን ጀግና ነኝ፤ እንደገና ጀግና ነኝ፤ እንደገና ጀግና ነኝ፤ ሦስት ጊዜ ጀግና ሆኜ አሸንፌው አልተደፈርኩም” ይላሉ።መስማት የተሳናቸው ዜጎች ጉዳዮች ላይ በቅርበት የሚሠሩት አቶ መላከ ሙሉጌታ፣ ከስምንት ዓመታት በፊት መስማት ከተሳናቸው ዜጎች ጋር አዘውትረው በመገናኘት የተለያዩ ሥራዎችን ይሠሩ እንደ ነበር ገልጸዋል፡፡ በማስተርጎም፣ መስማት የተሳናቸው ዜጎች ትምህርት የሚያገኙበትን መንገድ በተመለከተ ዝግጅት በማድረግ ሠርተዋል፡፡ በዚህም መስማት ከተሳናቸው ማኅበረሰብ ጋር የቅርብ ትውውወቅ አላቸው፡፡ ሆኖም፣ “ይሄን ታሪክ ከሰማሁ ግን ሁለት ሳምንት አይሆነኝም›› ይላሉ፡፡ መጀመሪያ በሕግ ጉዳዩን መከታተል የሚችሉበትና፣ ልጆቻቸውን ማግኘት የሚችሉበት ጉዳይ ካለ በሚለው ጥረት አድርጌ ነበር፡፡ ግን ያው በአገሪቱ ሕግ መሠረት የይርጋ ጊዜ ስላለ ይሔንን ጉዳይ በዛ መንገድ ማሳካት እንደማይቻል ከሕግ ባለሙያዎች ስለተረዳሁ ነው ጉዳዩን ወደ እዚህ ያመጣሁት፡፡ ይሔ ጉዳይ የእነርሱ ብቻ ሳይሆን፣ የአገሪቱም ጉዳይ ሊሆን ይችላል በሚል ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ “መካኒሳ መስማት የተሳናቸው ት/ቤት” ከጥበቃ ሠራተኞች እስከ አስተዳደር ድረስ ተደራጅቶ በመንግሥት ዕይታ ውስጥ እየሠራ ነው፡፡ በእርግጥ የመንግሥት ድርጅት አይደለም፡፡ ግን በመንግሥት ቁጥጥር ሥር የሚሠራ ነው፡፡ አሁንም በዕርዳታ ድርጅቶች ነው የሚተዳደረው ይላሉ መላክነህ፡፡ መስማት በተሳናቸው ማኅበረሰብ አባላት ልማድ መረጃ እርስ በእርስ የሚለዋወጡ ቢሆንም፥ ወደ እኛ መስማት ወደ ምንችለው ማኅበረሰብ አይደርስም የሚሉት መላክነህ በዚህ በኩል መንገዱ ዝግ ስለሆነ ነው ብዙ ሰው ጉዳዩን ያልሰማው ይላሉ። ይህንን የመደፈር ታሪካቸውን ሳይቀር እንደቀላል እና የለት ተለት የሕይወት ገጠመኝ የሚቆጥሩትም ለዚያ ነው። “ምክንያቱም የእነርሱ ማኅበረሰብ ይሔን ነገር አይቶት፣ ሰምቶት በቃ ኖርማል ሆኖ ተላምደውታል፡፡ እንደ ተራ ታሪክ ነው የሚያወሩት፡፡ እነርሱ ሲያወሩት እንደ ቀልድ እየሳቁ ሊሆን ይችላል፤ ይሔ በእኛ እና በእነርሱ መካከል ያለው የተግባቦት ችግር የፈጠረው ይመስለኛል” ይላሉ አቶ መላክነህ። የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ ከተጠቂዎቹ ሴቶች ጠይቆ እንደተረዳው ሁለቱም የተደፈሩ ሴቶች ከዚያ በኋላ ትዳር አልመሠረቱም፤ ፅጌ ግን ከፈቀደችው ሰው አንድ ልጅ ወልደዋል። ለዚህም የዳረጋቸው በተደፈሩበት ጊዜያት የገጠማቸው የሥነልቦና ተፀዕኖ እንደሆነ ይገልጻሉ። ፅጌ “እኔ ማግባት አልፈልግም፣ የሥነልቦናው ጥቃት ከአእምሮዬና ከልቦናዬ አልጠፋም፡፡ ምክንያቱም በመጀመሪያ እነዚያ መንታ ልጆች እንዲወለዱ በፈቃዴ የተፈፀመ ግንኙነት አልነበረም፤ ሲቀጥል ልጆቼ ያለፈቃዴ ደግሞ ተወስደውብኛል፡፡ እና ይመጣሉ የሚል ተስፋ ነበረኝ – ብዙ ጊዜ፡፡ አሁንም እንደገና ባገባና ብወልድ፣ ያኛውን ታሪክ ስለሚያስታውሰኝ፣ እንደዛ ለማድረግ በፍፁም አስቤ አላውቅም” ብለውኛል።ወጋየሁም በተመሳሳይ በታዳጊ ልጅነቷ እንዲህ ዓይነት ችግር ስለደረሰባት፣ የሥነ-ልቦና ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡ በተጨማሪ ግን አያትዋ “በፍፁም ከወንድ ጋር እንዲህ ዓይነት ንክኪ እንዳታደርጊ!” በሚል እንዳስጠነቀቋቸው ይናገራሉ። እነዚህ ሴቶች ዛሬም ድረስ ለደረሰባቸው በደል ፍትሕ ባይጠይቁም ልጆቻቸውን ለማየት ድምፅ አልባ ጩኸት እየጮኹ ይገኛሉ። (የኢትዮጵያ ሰብኣዊ መብቶች ፕሮጀክት (ኢሰመፕ) የነዚህን ባለታሪኮች ቀጣይ ሁኔታ ተከታትሎ ለማቅረብ ይሞክራል።)

እውን ሀገራችን “አሁኑኑ ምርጫ ይካሄድ!” የሚባልበት ደረጃ ላይ ናት?

መስከረም አበራD

ሃገራችን ለፖለቲካ ህመመሟ ፈውስ በምታገኝበት ወይም ጨርሳ የአልጋ ቁራኛ በምትሆንበት ወሳኝ የታሪክ ምዕራፍ ላይ ትገኛለች፡፡ ዋነኛ ህመሟ የዘር ፖለቲካ አመጣሽ ደዌ ነው፡፡ የዘር ፖለቲካ በደም ሥሯ ገብቶ መላ አካሏን የሚያናውጣት ይህች ደሃ ሃገር ሲባል የሰማችው እንዳይቀባት ስታደርግ የኖረችው ሃገራዊ ምርጫም ቀነቀጠሮው ደርሷል፡፡ እንደ ፅዋ ማኅበር ወራቱን ጠብቆ ምርጫ ማድረግ እና ተመልሶ በዘር ፖለቲካ ኋላ ቀር ዘይቤ መመላለስ ከዲሞክራሲዊ ምርጫ ትርጉም ጋር የማይዛመድ ልማዳችን ነው፡፡ ይህ ልማዳችን የፖለቲካችንን ጉልበት ለዝለት ዳርጎ እንዳንራመድ ሲያንፏቅቀን የኖረ ክፉ ቁራኛችን ሆኖ አለ፡፡

ምርጫ የዲሞክራሲ እምብርት ነው ቢባልም ሁሉም ምርጫ የዲሞክራሲ እምብርት ሊሆን አይችልም፡፡ከዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ጋር የሚዛመደው ዲሞክራሲያዊ ምርጫ ብቻ ነው፡፡ እንደ ሰንበቴ ወር እየጠቁ ምርጫ ማድረግ ለሃገር ዲሞክራሲን አያመጣም፡፡ በአፍሪካ አህጉር የሚደረጉ እንደ ትጥቅ ትግልም የሚሞክራቸው ምርጫዎች ለአምባገነኖች የተመርጫለሁ ሽንገላ ይረዱ ይሆናል እንጅ ለሃገር እና ለህዝብ ዲሞክራሲን ሊያመጡ አይችሉም፡፡

ሃገራችንን ጨምሮ ከምርጫ ማግስት ደም መፋሰስን እና በፍርድ ቤት መካሰስን አስከትሎ የሚመጣው የአፍሪካ ሃገራት ምርጫ ለህዝብ ጭንቅን እንጅ ደስታን ይዞ አይመጣም፡፡ በቅርቡ በኬንያ የተደረገው (የምርጫ ኮሚሽነሩን መሰዋት ያደረገው) ምርጫ ሲቃረብ የሃገሪቱ ህዝብ ምርጫው በሰላም እንዲያልፍ በየእምነት ተቋሙ ሱባኤ መግባት ጀምሮ ነበር፡፡ ጎረቤት ሩዋንዳ፣ ብሩንዲ፣ ዩጋንዳ በተመራጭ አምባገነኖች የሚንገላቱ፣ የእኛ ቢጤ “የምርጫ ሰለቦች” ናቸው፡፡

በሃገራችን የተደረጉ ምርጫዎች ታሪካዊ ዳራ ቢጠና የህወሃትን በተለይ ደግሞ የአቶ መለስ ዜናዊን ጉልበት ከቀን ቀን እያበረቱ በስተመጨረሻው ወደ ተሟላ ተመራጭ አምባገነንነት ያደረሱ ሃዲዶች ናቸው፡፡ በኢህአዴግ ስር የተደረጉ ምርጫዎች የእድገት ጫፍ በፓርላማው መቀመጫ ሁሉ የአንድ ፓርቲን ካድሬዎችን መኮልኮል ነው፡፡ ተገዳዳሪ ለማይወደው ኢህአዴግ ይህ ብቻ ድል ሆኖ አሳርፎ አያስቀምጥም፡፡ ይልቅስ የድሉ ማህተም ከፓርላማ ወንበር ርቀው በቆሙ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ጓዳ ገብቶ ህብረታቸውን ማፈራረስ፣ ስማቸውን ከህይወት መዝገብ መሰረዝ ነው፡፡

ይህን ካደረጉ በኋላ ደግሞ ተቃዋሚ ጠፋ እንዳይባል ነፍስ ያላቸውን ተቃዋሚዎች ለማፍረስ የተጠቀመባቸውን የፖለቲካ ወንጀለኞች ተቃዋሚ ብሎ ደሞዝ ሳይቀር እየከፈለ የፈለገውን ያናግራቸው ነበር፡፡የሚወደውን ወንበሩን ለመጠበቅ የራሱን ተቃዋሚ ፈጥሮ ደሞዝ መክፈል ድረስ ርቆ ወደታች የሚምዘገዘገው ህወሃት መራሹ ኢህአዴግ ጠላት ከሩቅ ሲጠብቅ አቤት ወዴት ሲያስብላቸው የኖሩ የራሱ ሎሌዎች ባላሰበው መንገድ ገፍተር አድረጉት፡፡ የገዛ አቤት ባዮቹ በፅኑ ፍቅር የጣለውን ወንበሩን ሲይዙ ራሱን አግዝፎ የሚያየው ህወሃት ዕብድ የሚያደርገውን ንዴቱን ብቻ ይዞ ቀረ፡፡

ህወሃት ቀርቶ እኛም ባላመንነው መንገድ የፖለቲካችን/የኢኮኖሚያችን መዥገር የሆነው የህወሃት አገዛዝ ቢወገድም ዲሞክራሲን አርቆ ለመቅበር ሳይታክት ሲሰራው የኖረው ስራው ግን ለሃገራችን ዲሞክራሲ ትልቅ ፈተና ደቅኗል፡፡ ህወሃት ዘረፋውን ለሚጋርድለት ስልጣኑ ሲል ያጠፋው ጥፋት የትየለሌ ቢሆንም በሃገራችን የዲሞክራሲያዊ ምርጫ ባህል ስር እንዳይይዝ ያደረገው ድርጊት ይቅር ለማለት አስቸጋሪው ጥፋቱ ነው፡፡

Voters queue to cast their votes in Ethiopia’s general election on Sunday in Addis Ababa, Ethiopia. PHOTO:ASSOCIATED PRESS

ዲሞክራሲያዊ ምርጫ በመሰረታዊነት የሃሳብ ውድድር ነው፡፡የሃሳብ ውድድሩ መሰረት የሚያደርገው ተወዳዳሪዎቹ የሚያመጡት የፖሊሲ ሃሳብ እንጅ የሚናጉትን ቋንቋ አይደለም፡፡ ተወዳዳሪ ፓርቲዎች የሚያቀርቡትን ሃሳብ የሰማው ህዝብ በምርጫ ካርዱ ለሚቀጥሉት አራት ወይም አምስት ዓመት ማን ፖሊሲ ያውጣልኝ የሚለውን ይወስናል፡፡ ህዝብ የተገዳዳሪ ፓርቲዎችን ሃሳብ ለመስማት፣ ተወዳዳሪ ፓርቲዎች የፖሊሲ ብልጫቸውን ለህዝብ ለማቅረብ ህዝብ እና ተወዳዳሪ ፓርቲዎች ያለገደብ መገናኘት አለባቸ፡፡ የውድድሩ ሜዳ ለማንም ያላዳላ ፍትሃዊ መሆን አለበት፡፡ እድሜው ለመምረጥ መመረጥ የደረሰ ሰው ሁሉ መምረጥም መመረጥም መቻል አለበት፡፡ ህዝቡም ሆነ ተወዳዳሪ ፓርቲዎች ምርጫ ቦርድን ጨምሮ በምርጫው አስፈፃሚዎች ላይ እምነት መጣል አለበት፡፡ ይህ በስተመጨረሻም በሃገሪቱ ባሉ የፖለቲካ ሃይሎች ዘንድም ሆነ በህዝቡ ዘንድ የምርጫ ውጤቱን አምኖ ለመቀበል ያስችላል፡፡

ወቅታዊ የዲሞክራሲያዊ ምርጫ እንቅፋቶች

አሁን ሃገራችን ያለችበት ሁኔታ ከላይ የተቀመጠውን የዲሞክራሲያዊ ምርጫ መሰረታዊ ይዘት ባሟላ ሁኔታ ማድረግ የሚያስችል ነው ወይ? የሚለው ጥያቄ ምርጫው ጊዜውን ጠብቆ ይደረግ አይደረግ ከመባሉ ቀደም ብሎ መነሳት ያለበት ወሳኝ ጥያቄ ነው፡፡ በግሌ ምርጫውን በታቀደለት ጊዜ ማድረግ የማይቻል ብቻ ሳይሆን አደገኛ መስሎም ይሰማኛል፡፡ምርጫውን በቀጠሮው ለማድረግ የማያስችሉትን ምክንያቶች በሶስት መክፈል ይቻላል፡፡

1. ህወሃት/ኢህአዴግ ሰራሽ እንቅፋቶች

የመጀመሪያው እና መሰረታዊው ችግር ከፍ ብሎ የተጠቀሰው ህወሃት ለስልጣኑ እና ዘረፋው ሲል ተገዳዳሪን ድምጥማጥ ለማጥፋት ያደረገው (ደደቢት ላይ ካደረገው ያላነሰ) ተጋድሎ ነው፡፡በዚህ እጅግ አሳዛኝ ስራው አንድነትን የመሰለ ጠንካራ ፓርቲ አጥፍቷል፡፡ በትንግርት የተረፈው ሰማያዊ ፓርቲም ቢሆን መሪዎቹን ለእስርቤት ገብሮ በመኖር እና ባለመኖር መሃል ብቅ ጥልቅ ሲል የኖረ ነው፡፡መኢአድም ገና ከጠዋቱ ያለ ርህራሄ በህወሃት ሰደፍ ሲደቆስ፣ ሰላማዊ ተቃዋሚ ሆኖ ሳለ እንደ ታጣዊ ቡድን በእጅጉ ሲታደን የኖረ፣እስከዛሬ መኖሩም የሚገርመኝ ፓርቲ ነው፡፡ ኢዴፓም ቢሆን በተመሳሳይ እንግልት የኖረ ከመሆኑም ባሻገር በቅርቡ ቤቱን ከማጥራቱ በፊት ከአንዳንድ መሪዎቹ ሁኔታ አንፃር ከህወሃት ጋር ያለው ግንኑነት በህዝብ ዘንድ በጥርጣሬ የሚታይ ነበር፡፡

ተቃዋሚ ፓርቲዎች እንዲህ ባለ የህወሃት/ኢህአዴግ ፀረ-ዲሞክራሲያዊ የሰፈር ጉልበተኛ አይነት ስራ በከፍተኛ መገለል እና የመጥፋት አደጋ ውስጥ በኖሩበት ዘመን አሁን እንደ ፓርቲ ይወዳደር የሚባለው ኢህአዴግ ደግሞ በፖለቲካው መስክ ሃገር ምድሩን በግድም በውድም አባል አድርጎ ኖሯል፡፡ በኢኮኖሚው መስክ ፓርቲ መሆኑ ሳያግደው ሲነግድ ኖሯል፡፡ ብቻውን ተቆጣጥሮ ልማታዊነቱን ሲነዛበት የኖረው የህዝብ ሚዲያ አሁንም በእጁ ነው፡፡ በንፃሩ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ደጋፊዎቻቸውን ሊያነቁበት፣ ከህዝብ ጋር ሊገናኙበት የሚችሉት የግሉ ሚዲያ በህወሃት/ኢህአዴግ ሰደፍ ተገዶ ተዘግቶ ኖሯል፡፡ ከዚህ ሁሉ በላይ በአመዛኙ ህዝብ ታግሎ ያመጣው ለውጥ ወሮታ በተለምዶ የለማ/ገዱ ቡድን ለሚባለው ለኢህአዴግ ፓርቲ አፈንጋጮች እየተሰጠ ነው፡፡ ይህ የቅድመ ለውጥ ምክንያት በድህረ ለውጥ ከተባባሰው የዘር ፖለቲካው ጋር ሲደመር ወደ ሁለተኛው የምርጫ እንቅፋት ያደርሰናል፡፡

2. ከለውጡ ጋር የሚዛመዱ እንቅፋቶች

ህወሃት/ኢህአዴግ ተደላድሎ ተቀምጦ ሃገርን አሳር መከራ ሲያሳይ የኖረበትን አገዛዝ ያስወገደው ህዝባዊ ትግል ተስፋንም ስጋትንም ያዘለ ድባብ አለው፡፡ ተስፋው አዲሱ የለውጥ አመራር ሃገሪቱን ሊያጠፋት ደርሶ የነበረውን መከፋፈል በማጠየቅ የጋራ ሃገርን ለመገንባት የሚያደርገው ጉዞ ሊያደርሰን የሚችለው ሃገራዊ ብልጽግና ሲሆን ስጋቱ ደግሞ ይህን ጉዞ ሊያደናቅፍ የሚችለው የዘር ፖለቲካ ወለድ መተላለቅ ነው፡፡ ለውጡ ብዙ ጥሩ ብስራቶች ቢኖሩትም እጅግ አስፈሪ የዘር ፖለቲካ መርገሞችንም ያመጣ፣ ወደፊትም የባሰውን ሊያመጣ የሚያስችል አዝማሚያ ያለው ነው፡፡

ይህ አስፈሪ የዘር ፖለቲካ ተዘርቶ የበቀለው እና እንዲህ ለውድመት ብቁ የሆነው ለውጡ በቆየበት የስምንት ወር እድሜ አይደለም፡፡ ዘረኝነት በእንክብካቤ አድጎ ያሸተው ህወሃት/ኢህአዴግ በኖረበት ረዥም ዘመን ነው፡፡ ህወሃት አስሮ ያሳደገው ዘረኝነት የሚባል አውሬ ጎልምሶ፣ ከጎሬው ወጥቶ አሳዳጊውን ቦጫጭቆ መግደሉ ደግ ቢሆንም ህወሃትን አጠፋሁ ብሎ ዝም ብሎ የማይተኛ መሆኑ ነው ጭንቁ፡፡ ህወሃትም ቢሆን ራሱ ተንከባክቦ ያሳደገው ዘረኝነት ራሱንም እንዳጠፋው ቢያውቅም ከእርሱ መጥፋት በኋላ ሃገሪቱ በዘረኝነት ጦስ ስትታመስ እሱ ስለሌለ የመጣ ችግር እንጅ እሱ ያልፈጠረው ችግር አድርጎ ለማውራት አይሰንፍም፡፡ ይህን እንደ ጥሩ አጋጣሚ ተጠቅሞ በስልጣኑ ወራት ዘቅዝቆ ሲገርፋቸው ከነበሩ አክራሪ የዘር ድርጅቶች ጋር እየተገናኘ የሃገርን ጣር ለማብዛት እንደሚሰራ የታወቀ ነው፡፡

ህወሃት እና የቀድሞ ጠላቶቹ የአሁን ወዳጆቹ አክራሪ የዘር ፖለቲከኞች ገንዘብ ጠመንጃቸውን አዋህደው በስልጣን ላይ ያለውን ቡድን እያስጨነቁ፣ ሃገር ወደ ገሃነም በር የምትደርስበትን መንገድ እየተለሙ ይገኛሉ፡፡ ከዚህ ስራቸው አንዱ የሃገሪቱ ምርጫ በተያዘለት ፕሮግራም ይደረግ የሚለው ህጋዊ መሰል ጥያቄያቸው ነው፡፡ ይህን ጥያቄ በዋናነት የሚያቀነቅኑት የኦሮሞ ብሄርተኛ ፓርቲዎች ሲሆኑ ህወሃትም እንደሚፈልገው ጥናት አቀርባለሁ ብለው መቀሌ የነጎዱት አቶ በረከት ጠቆም አድርገዋል፡፡ምርጫው በሰዓቱ ይደረግ የሚሉት የኦሮሞ ብሄርተኝነት ፖለቲካ መሪዎች አክራሪዎቹ ብቻ አይደሉም፡፡ ይልቅስ መሃል መንገድን እንደሚሹ አጥብቀው ሲናገሩ የኖሩት ዶ/ር መረራ ጉዲና ሳይቀሩ “ምርጫው ነገ ቢደረግ እኛ ደስታችነ ነው” ሲሉ ስሙን በማላስታውሰው ቴሌቭዥን ቀርበው ሲያወሩ ሰምቻለሁ፡፡

የዘር ፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች ምርጫው በሰዓቱ እንዲደረግ የሚፈልጉበት ምክንያት ግልፅ ነው፡፡ እነዚህ ፓርቲዎች ከድሮ እስከ ዘንድሮ ሲመረጡ የኖሩት እትብታቸው በተቀበረበት መንደር እየሄዱ ነው፡፡ ዕትብታቸው በተቀበረበት መንደር እስከሄዱ ድረስ እንደሚመረጡ እርግጠኛ ናቸው፡፡ በዚህ መሃል ይህን ጉዳይ በተመለከተ ዶ/ር መረራ በአንድ ወቅት ከኢሳቱ አቶ ግዛው ለገሰ እና ሟቹ አቶ ፈቃደ ሸዋቀና ጋር ባደረጉት ቆይታ “ፈቃደ አንተም አምቦ የተወለድክ (ያደግክ?) ቢሆንም አሁን አንተ እና እኔ ለምርጫ ልንወዳደር አምቦ ብንሄድ የምመረጠው እኔ እንደሆንኩ ጥርጥር የለኝም” ብለው ነበር፡፡

ከዚህ የምንረዳው በሰፈሩ የምርጫ ጣቢያ ብቻ ለመመረጥ የተሰየመ የዘር ፖለቲከኛ በምርጫ ለማሸነፍ የሚሰራው አንዳች ነገር የለም፡፡ አሸናፊነቱን የሚያፀናው ስራ ተሰርቶ ያለቀው በተፈጥሮ አደራጅነት፣ ከዛች መንደር፣ የዛን አካባቢ ቋንቋ ከምትናገር እናት የተወለደ ቀን ነው፡፡ እንዲህ ባለው በተፈጥሮ አጋፋሪነት በሚያልቅ መምረጥ መመረጥ ውስጥ የሃሳብ ውድድርን ገበያ አንደኛ የሚያደርገው የዘመናዊ ዲሞክራሲ ምርጫ እጣ ፋንታ የለውም፡፡ ምርጫ ይኖራል ዲሞክራሲያዊ ግን አይደለም፡፡ምርጫው የሚኖረውም እዛው ሰፈር እትብቱ የተቀበረ ሌላ ተገዳዳሪ ከመጣ ነው እንደጂ የሌላ ሰፈር ሰው ድርሽ እንዳይል የእትብት መማዘዙ ፖለቲካ ያግዳል፡፡ እንዲህ ባለው ውድድር ለማሸነፍ ደግሞ ክርክሩ የእናት የአባት የዘር ንጥረት ይሆን ይሆናል እንጅ የሃሳብ ሙግት ሊሆን አይችልም፡፡ በዚህ ውስጥ ዲሞክራሲን መፈለግ ላምም ሳርም በሌለበት ኩበት መልቀም ነው!

በአንፃሩ የዜግነት ፖለቲካ ተፈጥሮን ሳይሆን ተመክሮን እና ሃሳብን መሰረት ስለሚያደርግ ትልልቅ ስራዎች የጠብቁታልና ምርጫ ነገ ይሁን ለማለት አይደፍርም፡፡ አንደኛው ትልቅ ፈተና የዘር ፖለቲካ አለቅጥ እጅ እግሩን ዘርግቶ ተንሰራፍቶ በኖረበት ሃገር የፖሊሲ ሃሳብን ይዞ የወንዙ ልጆች ባልሆኑ ሰዎች ፊት መቅረቡ ነው፡፡ የሰፈሩን ሰው ብቻ እንዲያምን ሲነገረው የኖረ ህዝብ የሌላ ሃሳብ መስማት ቀርቶ በሰፈሩ መርገጡ ራሱ ሊያስቆጣው እንደሚችል አዝማሚያዎች እያየን ነው፡፡ እድል ቀንቶት፣ ሃሳብ የሚሰሙ ዜጎች አግኝቶ፣ በፖሊሲው መስህብ ማርኮ የመመረጥ እድል ቢያገኝ እንኳን የምርጫውን ውጤት የሚቀበለው ሰው ምን ያህሉ ነው የሚለውም ሌላ ጥያቄ ነው፡፡

3. ህገ-መንግስት ወለድ እንቅፋቶች

በሃሳብ የበላይነት ላይ የሚቆመው ዲሞክራሲያዊ ምርጫ የተፈጥሮን አጋፋሪነት ብቻ ተማምኖ ከሚቀመጠው የዘር ፖለቲካ ምርጫ ጋር ዝምድና የለውም፡፡ አሁን ሃገራችን የምትመራበት ህገ-መንግስት ደግሞ የዘር ፖለቲካን በህግ ያነበረ፤ የአዋቂዎች አካታች የመምረጥ መመረጥ (Adult Universal Suffrage) መብትን በተዘዋዋሪ የሚነፍግ ነው ፡፡ ይህ ህገ-መንግስት ዘር ቆጥሮ በከለለው ክልል ሰባት ጉልበቱ ያልተወለደ ሰው መራጭ ይሆናል እንጅ የመመረጥ መብት የለውም፡፡ ጭራሽ እሱ መጤ/ሰፋሪ/ወራሪ እየተባለ በሚኖርበት መሬት በወቅቱ የማይኖሩ ግን ከሃምሳ ስልሳ አመት በፊት እዛ ሃገር እንደ ተወለዱ የሚታመንባቸው፣ ሰባት ጉልበታቸው ተቆጥሮ ሃገሬነታቸው የተረጋገጠ ሰዎች ተመራጭ ሆነው ይመጣሉ፡፡ በዚህ ውስጥ የዲሞክራሲያዊ ምርጫ መስፈርት የሆነው በአካባቢው ከሁለት አመት በላይ መኖር እና እድሜ ለመመረጥ መድረስ ዋጋ የላቸውም፡፡

እንዲህ ያለው ህገ-መንግስት አንድ ዓረፍተ-ነገሩ ሳይነካ፣ የምርጫው ቀን አንድ ሰኮንድ ሳያልፍ ምርጫው ይደረግ የሚሉ የዘር ፖለቲካ መሪዎች ፍላጎት የሃሳብ ዘመን ሳይመጣ፣ በግርግር ስልጣን ላይ መቀመጥ እና በጥፋቱ ብዛት እየተጠላ ያለውን፣ የህልውናቸው መሰረት የሆነውን የዘር ፖለቲካ ከመጥፋት ታድጎ ማስቀጠል ይመስላል፡፡ የዘር ፖለቲካ የሚመቸው ዘራቸውን ጠርተው ብቻ ያለ ልፋት ስልጣን ላይ ለሚቆናጠጡ ልሂቃን እና ቅዝምዝምን ዝቅ ብለው የሚያሳልፉበት ትርፍ ሃገር ላላቸው አክቲቪስቶች ነው፡፡ እነዚህ ሰዎች ግላዊ ጥቅማቸውን እና ዝናቸውን ለለማጣት ሲሉ ብቻ የዘር ፖለቲካ ወለዱ የዘር ፌደራሊዝም እጅግ ድንቅ እንደሆነ ቢሰብኩም በተግባር የሚታየው ተቃራኒው ነው፡፡

ከሁለት አመት በፊት በዘር ፖለቲካው ምክንያት የሚሞተው የሚፈናቀለው አማራው ብቻ ነበር፡፡አማራው ደግሞ ለመጨቆን በሃገሪቱ ዳርቻ የተበተነ የሃገሪቱ ብሄረሰቦች ጠላት ተደርጎ ይወሰድ ስለነበረ ዘርን መሰረት ያደረገው ፖለቲካ ችግር ፈጣሪ ተደርጎ ሳይታይ፣ ጭራሽ አማራውን የቀጣ ጥሩ ለበቅ ተደርጎ ሲወሰድ ኖሯል፡፡ ሆኖም ዘመኑ ሲደርስ ኦሮሞው፣ ጌዲኦው፣ ሱማሌው፣ አማሮው፣ ጋሞው፣ ወላይታው፣ ጉራጌው፣ ከንባታው፣ ማረቆው፣ መስቃኑ፣ ቀቤናው ሁሉ የችግሩ ሰለባ ሲሆን የዘር ፖለቲካው አዋጭ እንዳልሆነ በተግባር እየታየ ነው፡፡በዚህ ምክንያት የዘር ፖለቲካው ችግር ወስጥ እንዳለ የዘር ፖለቲካ መሪዎች አጢነዋል፡፡ በአኖሌ ሃውልት ዙሪያ ሲሰበሰብ ነበረው የአቶ ለማ መገርሳ ኦህዴድ “ኢትዮጵያ ቅደሚ” ማለቱ በዘር ፖለቲካው ላይ ለመምሸቱ አይነተኛ ምልክትም፣ከባድ ስጋትም ሆኖ ሳይቆጠር አልቀረም-በዘር ፖለቲከኞች ዘንድ፡፡

አብልቶ አልብሶ የሚያኖራቸውን የዘር ፖለቲካ ክፉ የማይወዱ የፖለቲካው ልሂቃን ታዲያ የህልውናቸውን ዋስትና ለመታደግ በመራወጥ ላይ ይገኛሉ፡፡ ምርጫ ሳይውል ሳያድር ይደረግ የሚሉት መዋል ማደር ከመጣ የሃሳብ እና የምክንያታዊነት ፖለቲካ መድረኩን ሊረከብ ይችላል፤ ይህ ደግሞ ተከታይ ያሳጣናል ከሚል ስጋት ነው ምርጫ አሁኑኑ እተባለ ያለው፡፡ በአንፃሩ የዜግነት ፖለቲካ አራማጅ ፓርቲዎች ህብረት እየፈጠሩ መሄዳቸው፣ በስልጣን ላይ ያለው ቡድን ወደ ኢትዮጵያዊ ብሄርተኝነት ከማዘንበሉ ጋር ሲደመር የጎሳ ፖለቲከኞችን ጭንቅ ላይ መጣሉ አይቀርም፡፡ “ምርጫው አሁኑኑ ይደረግ፣ የሽግግር መንግስት የሚል ድምፅ እንዳንሰማ” ባሉበት አፋቸው ድንገት ብድግ ብለው “እንደውም ብሄራዊ የአንድነት እና የሽግግር መንግስት ይመስረትልን” እያሉ ያሉት ልብስ ጉርሳቸው የዘር ፖለቲካ ሊወድቅ ዘመም ዘመም ያለ ቢመስላቸው ነው፡፡

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ አሁን ያለበት ደረጃ ይፋ ሆነ

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት

የውሃና መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ያለበትን ወቅታዊ የግንባታ ደረጃ ዛሬ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ይፋ አድርጓል።

በዚህም መሰረት የግድቡ ሲቪል ስሰራዎች በአሁኑ ወቅት –

• የዋናው ግድብ የሲቪል ስራዎች 80 በመቶ ተጠናቋል፤

• የኃይል ማመንጫዎች የሲቪል ስራ በአማካይ 66 በመቶ ተጠናቋል፤

• የጎርፍ ማስተንፈሻ የሲቪል ስራዎች 99 በመቶ ተጠናቋል፤

• የኮርቻው ግድብ ስራዎች 93 በመቶ ተጠናቋል

• የስዊችያርድ የሲቪል ስራዎች 33 በመቶ ተጠናቋል፤

በአጠቃላይ የሲቪል ስራዎች 82 በመቶ ተጠናቋል።

የአሌክትሮመካኒካል ስራዎች

ተርባይን እና ጄኔሬተር ምርትና ተከላን ያለበትነ ደረጃ በተመለከተም ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጀነር ስለሺ በቀለ ለምክር ቤቱ አብራርተዋል።

በዚህም መሰረት –

• የዘጠኝ ተርባይን እና ጄኔሬተር በአብዛኛው የተከናወነ ሲሆን በፕሮጀክት የስራ ቦታ ጉባ እና አንዳነዶቹ በወደቦች ይገኛሉ። የተወሰኑት የተርባይንና ጄኔሬተር አካላት በሀገር ውስጥ ይመረታሉ ተብለው የታሰቡት አልተመረቱም፤

• የመጀመሪያ ሁለት ዩኒቶች የተርባይን አካል የሆኑትውሃን ለተርባይኖች የሚያመራ ተከላ 23 ነጥብ 7 በመቶ ተከናውኗል፤

የከፍተኛ ሀይል መቆጣጠሪያ እና ማስተላለፊያ ስዊችያርድ ተከላ

• የመጀመሪያ ሁለቱ ዩኒቶች ትርንስፎርመር ተመርተው ሳይት ደርሰዋል፤ የተከለ ስራ አልተጀመረም፤

• የከፍተኛ ሀይል መቆጣጠሪያ እና የማስተላለፊያ ስዊችያርድ እቃዎች ተመርተው የደረሱ ሲሆን ተከላ በጅምር ላይ ነው።

አጠቃላይ የኤሌክተሮ መካኒካል ስራዎች አፈጻጸም 25 በመቶ ሲሆን፤ የሃይድሮሊክስ ስቲል እስትራክቸር ስራዎች አፈጻጸም 13 በመቶ ብቻ ነው።

በብረታብረትና ኢንጅነሪንግ (ብኢኮ) የተሰራው ስራም 23 በመቶ ብቻ ሲሆን ፕሮጀክቱ አሁን የደረሰበት የግንባታ ደረጃም 65 በመቶ መሆኑን ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጅነር ስለሺ አብራርተዋል።

አቶ ጌታቸው አሰፋ ጉዳያቸው የህግ ጥያቄ ነው ወይስ ፖለቲካዊ? ለምንስ የትግራይ ክልል ጉዳይ ሆኑ?

የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ አቶ ብርሃኑ ፀጋዬ ከጥቂት ቀናት በፊት ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመስሪያ ቤታቸውን የአምስት ወራት የስራ አፈፃፀም ሪፖርት ባቀረቡበት ወቅት የእስር ትዕዛዝ የወጣባቸውን እና መቀሌ የሚገኙትን የቀድሞው የደህንነት መስሪያ ቤት ኃላፊ አቶ ጌታቸው አሰፋን በቁጥጥር ሥር ለማዋል ከትግራይ ክልላዊ መንግሥት በኩል ትብብር አለማግኘታቸውን ገልፀዋል።

ከክልሉ ይሁንታ ካለመገኘቱም ጋር ተያይዞ “እሳቸውን ለመያዝ ሌላ ሰው መግደል የለብንም” በማለት ጠቅላይ አቃቤ ህጉ የፌደራል መንግሥቱን አቋም አንጸባርቀዋል።

ይህንንም ተከትሎ በአንድ አገር ላይ የፌደራል መንግሥት በወንጀል የተጠረጠረን ግለሰብ ሲጠይቅ ክልሎች ያለምንም ማንገራገርና ለህገ መንግሥቱ ታዛዥ በመሆን አሳልፈው ሊሰጡ ይገባል የሚሉ እንዳሉ ሁሉ፤ የክልሉ መንግሥትና የፌደራል መንግሥት ተቀራርበው በመስራት ለጉዳዩ ፖለቲካዊ መፍትሄ ሊያበጁለት እንደሚገባ አስተያየታቸውን የሚሰጡም አሉ።

“ጌታቸው አሰፋ ለምን የትግራይ ክልል ጉዳይ ሆኑ?”

በሰብዓዊ መብት ጥሰት ተጠርጥረው ክስ የቀረበባቸው አቶ ጌታቸው ጉዳይ፤ ፖለቲካዊ ወይም ህጋዊ መፍትሄ ሊሰጠው ይገባል የሚል የተከፋፈለ ስሜት በሚንሸራሸርበት ሰአት ከሕግ ጥያቄ ወጥቶ የፖለቲካ ጥያቄ የሚያደርገው ነገር መጀመሪያ ምላሽ ሊሰጠው እንደሚገባ የቀድሞው የኢዴፓ ፕሬዚዳንት አቶ ሙሼ ሰሙ ይናገራሉ።

ለዚህም የፌደራል ወይም የትግራይ ክልል መንግሥት ኃላፊነታቸውን ሊወስዱ ይገባል ባይ ናቸው።

ምንም እንኳን የፌደራል መንግሥቱ ባለው ስልጣን መሰረት የማንንም ፍቃድ ሳይጠይቅ ወደ የትኛውም ክልል ሄዶ በወንጀል የጠረጠረውን ግለሰብ በቁጥጥር ስር የማዋል ስልጣኑ ቢኖረውም፤ ባላቸው የሻከረ ግንኙነት ምክንያት የፖለቲካ መፍትሄ ሊሰጥ ይገባል የሚሉ አካላት አሉ። ለአቶ ሙሼ ይህ የማያስማማቸው ጉዳይ ነው።

“ለኔ ማንኛውም ነገር ከህግ በታች ነው። ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባው የህግ የበላይነት ላይ መተማመን ነው” ይላሉ።

የፌደራል መንግሥቱ የወንጀል ተጠርጣሪ አድርጎ ክስ እስከመሰረተባቸው ድረስ ማንኛውም ዜጋ በሚታይበት የህግ ስርአት መሰረት ነፃ፣ ገለልተኛ በሆነ ፍርድ ቤት ጉዳያቸው ሊታይ እንደሚገባ የሚናገሩት አቶ ሙሼ፤ የተሰጣቸውን ኃላፊነት በአግባቡ ተጠቅመዋል አልተጠቀሙም የሚለውን በፍርድ ቤት ሂደት ተጣርቶ የሚደረስበት እንደሚሆን ይናገራሉ።

ለዚህ ሁሉ ግን የህግ የበላይነት ፅንሰ ሃሳብ ላይ ከስምምነት ላይ ሊደረስ እንደሚገባ አፅንኦት ይሰጣሉ።

የፖለቲካ ጥያቄ ለመሆን የሚያስችለው ጉዳይ ምንድን ነው? በማለት በዋነኝነት ጥያቄ የሚያነሱት አቶ ሙሼ፤ ”አቶ ጌታቸው እንደ ግለሰብ ባላቸው የፖለቲካ አቅም ነው? በዙሪያቸው የተሰባሰበው ኃይል አለ? ወይስ ክልሉ ነው የፖለቲካ ጉዳይ ያደረገው?” የሚለው መልስ ሊሰጥበት ይገባልም ይላሉ።

“ከነበራቸው የኃላፊነት ሁኔታ ጉዳዩ ታይቶ የሚያመጣውን ደስ የማያሰኝ ሁኔታ ለማረምና ለማስተካከል ተፈልጎ ከሆነ ጉዳዩን በውስጥ ውይይት መጨረስ ተገቢ ነው።” ይላሉ አቶ ሙሼ።

በጉዳዩ ቢቢሲ ያነጋገራቸው ሌላናው ፖለቲካኛ ደግሞ ዶ/ር መረራ ጉዲና ናቸው።

የፌደራል መንግሥት ጥያቄ ባቀረበው መሰረት፤ የትግራይ ክልል አቶ ጌታቸው አሰፋን አሳልፎ የሚሰጥ ይመስልዎታል ወይ? በሚል ከቢቢሲ ለቀረበላቸው ጥያቄ ዶ/ር መረራ ጉዲና ሲመልሱ በወንጀል የተጠረጠረን ግለሰብ አሳልፎ መስጠት እንደሚገባ ገልጸዋል።

ይህ ካልተከናወነ ግን በቀጣይ ፈታኝ ሁነቶች ሊከሰቱ እንደሚችሉ ስጋታቸውን ይገልጻሉ።

“የፌደራል መንግሥት በወንጀል የጠረጠረውን ግለሰብ ክልል አላስረክብም ማለት ሌላ መንግሥት መፍጠር ነው የሚሆነው፤ ይህ ደግሞ ለትግራይም ሆነ ለኢትዮጵያ ህዝብ ቀጣይነት ፈታኝ ነው። መተባበሩ የሚመረጥ ይመስለኛል። ” በማለት ይናገራሉ።

በወንጀል የተጠርጠረ ሰው ሊያገኘው የሚገባው መብት ሳይነካ በፍትሃዊ መንገድ ጉዳያቸው እንዲስተናገድ ዋስትና ይሰጠኝ ብለው መጠየቅ ይገባቸዋልም ይላሉ ዶ/ር መረራ።

ወንጀለኛ ተብሎ የተጠረጠረን ሰው አሳልፎ ስለመስጠት ሕጉ የሚለው ግልፅ ቢሆንም፤ አሁን ባለው የሃገሪቱ ተጨባጭ የፖለቲካ ሁኔታ ከፍተኛ ስጋትና፣ የኃይል ፍትጊያ በናረበት፣ ሃገሪቷን በሚመራው ኢህአዴግ ውስጥ ከፍተኛ መከፋፈል እያለ በተለይም ኢህአዴግን እንደ ግንባር ተሰብስበው ከመሰረቱት ጥምር ፓርቲዎች መካከል አንደኛው ተነጥሎ ኢላማ በመደረግ ህብረተሰቡን ከፋፍሎታል የሚሉት በመቀለ ዩኒቨርስቲ የሕግ መምህር የሆኑት ዶ/ር መንግሥቱ አረፋይኔ ናቸው።

ስልጣን የያዘው ቡድን የብቀላ ፖለቲካ የሚመስል አካሄድ አለው በማለትም የፌደራል መንግሥቱን ይወነጅሉታል።

“አንድ ክልል እየተገለለ ለሁሉም ወንጀል ተጠያቂ ማድረግ ሰላምና መረጋጋትን ሊያመጣ አይችልም።” ይላሉ ዶ/ር መንግሥቱ አረፋይኔ።

ምንም እንኳን በፅንሰ ሃሳብ ደረጃ ወንጀል የሰሩ ግለሰቦች የየትኛውም ብሔር አካል ይሁን ማንኛውንም ቋንቋ ይናገሩ ተጠያቂ ሊሆኑ ቢገባም ቀዳሚ ሊሆን የሚገባው በሀገሪቱ ያሉ ግጭቶችንና ጦርነቶችን ማስቆም፣ መፈናቀልን መቀነስና ሃገሪቱ ከገባችበት ውጥንቅጥ የማረጋጋት ስራ መሰራት እንደሆነ ያስረዳሉ።

በዚህም ምክንያት ክልሉ አሳልፎ የመስጠት ያለመስጠት ቀላል ጥያቄ ነው ይላሉ።

“ለሃገሪቱ የሚያስብ መንግሥት ከሆነ የአንድ ወይም ጥቂት የግለሰቦች መታሰር ትልቅ ልዩነት አያመጣም።” ይላሉ

“ሃገሪቱ ውስጥ ብዙ ወንጀል የሰሩ ሰዎች ተፈትተዋል፤ መንግሥት ላይ ጦር ያነሱ ሰዎች በሰላም ግቡ ተብለዋል። በአንድ በኩል የእርቅ መንፈስና ሂደት መንግሥት እያከናወነ በሌላ በኩል ደግሞ ሌሎችን ሰዎች ማሰር ምን አመጣው?” በማለት ጥያቄ ያነሳሉ።

አቶ ሙሼ በበኩላቸው የትግራይ ክልል አሳልፎ ሊሰጥ ይገባል ወይም አይገባም ከሚለው በፊት፤ የአቶ ጌታቸው ጉዳይ የትግራይ ክልል ጉዳይ ለመሆን መነሻው ምንድን ነው? የሚለው መሰረታዊ ጥያቄ መመለስ ያለበት ጉዳይ ነው ይላሉ።

ከዚህ በተቃራኒው ግን ይላሉ አቶ ሙሼ “በአግባቡ ያሉትን ሕጎች፣ ሕገ-መንግሥቱን ማዕከል ከማድረግ ይልቅ ጉዳዩ የህዝብ ግንኙነትና የመድረክ ፍጆታ ነው የሆነው። ይሄስ ጉዳይ ለህዝብ ፍጆታ የሚውለው ለምንድን ነው?” ሲሉም ይጠይቃሉ።

ምንም እንኳን በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎች ዘንድ የአቶ ጌታቸው አሰፋን ተላልፎ መሰጠት የትግራይ ህዝብ እንደሚቃወም ተደርጎ ቢቀርብም የአረና ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ አብርሃ ደስታ አቶ ጌታቸው ለትግራይ ህዝብ አጀንዳ አይደሉም ይላሉ።

ለዚህም እንደ መነሻነት የሚያነሳው አቶ ጌታቸው ከነበራቸው ስልጣን ተነስተው ወደ ትግራይ ክልል በመጡበት ወቅት ጥያቄ አለመነሳቱን ነው።

“የትግራይ ህዝብ በአንድ ግለሰብ አቋም አይዝም ብየ ነው የማስበው። የአቶ ጌታቸው መያዝ ወይም አለመያዝ የህወሃት መሸነፍ ወይም አለመሸነፍ ተደርጎ መወሰዱ የብሔር ፖለቲካ ተደርጎ መወሰዱን ያሳያል።” ይላሉ አቶ አብረሃ።

ፓርቲያቸው አረናስ ሕጉን በተከተለ መልኩ ተላልፈው ሊሰጡ ይገባል ወይ ተብሎ ለቀረበላቸው ጥያቄ “የኢህአዴግ ጉዳይ ነው። እርስ በርሳቸው ተነጋግረው፤ ተስማምተው መወሰን ይችላሉ። አሁን እየተከሰተ ያለው የኢህአዴግ አባል ፓርቲዎች በውስጣቸው መከፋፈል ተፈጥሯል። ሕግም ማስከበር አይችሉም፤ ፖለቲካውን ማስተካከል አቅቷቸዋል። ህዝብን ማስተዳደር አቅቷቸዋል።” በማለት ይናገራሉ።

የአቶ አብርሃ አስተያየት ከአቶ ሙሼ የተለየ አይደለም። መፍትሄ ብለው የሚያቀርቡትም የክልሉ እና የፌደራል መንግሥታት በጉዳዩ ላይ በመወያየት ከስምምነት መድረስ ነው።

አቶ አብረሃ “ሕግ የሚኖረው ፖለቲካው ሲስተካከል ነው። ስምምነትና ትብብር ከሌለ ወደ ግጭት እንዲሁም ወደ ጦርነት ሊያመራ ይችላል። ሰላማዊ ሰዎችም ሊጎዱ ይችላሉ።”

ከሰብዓዊ መብት ጥሰትና በከፍተኛ ሙስና ተጠርጥረው የተያዙ የሜቴክ አመራሮችና ሌሎች ሰራተኞች እስርን ተከትሎ የትግራይ ክልላዊ መንግሥት ምክትል ፕሬዚዳንት ዶ/ር ደብረፅዮን ገብረ ሚካኤል “ጉዳዩ ከሰብዓዊ መብትና ሙስና ጥያቄዎች ወጥቶ የትግራይ ህዝብን ወደመምታት የፖለቲካ እርምጃ ሄዷል።” በማለት ማውገዛቸው የሚታወስ ነው።

የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ በበኩሉ ውንጀላውን በማጣጣል የትኛውም ብሔር ላይ ያነጣጠረ እንዳልሆነ ገልጿል።

የትግራይ ክልል ጌታቸውን አሰፋን አሳልፎ የማይሰጠው በአንድ ብሔር ወይም በትግሬዎች ላይ ኢላማ ያደረገ ነው በሚል እምነት ከሆነ በግልፅ ሊናገር እንደሚገባ ዶ/ር መረራ ጉዲና አፅንኦት ይሰጣሉ።

“ወንጀለኞቹ እነማን እንደሆኑ እነ ዶ/ር ደብረ ፅዮን የተሻለ ስለሚያውቁ እነዚህን ወንጀል የሰሩ ሰዎችን ትታችሁ አንድን ብሄር ለምን ኢላማ አደረጋችሁ? የሚለውን በአደባባይ ይዘው ሊወጡ ይገባል” የሚሉት ዶ/ር መረራ፤ አክለውም “የኦሮሞና አማራ ሌባ ቁጭ ብሎ የትግራይ ብቻ የሚታሰርበት ምንም ምክንያት የለም። ያንን ለመጠየቅ ዲሞክራሲያዊ መብታቸው ነው።” ይላሉ።

• “በአንድ ሀገር ውስጥ እስከ አፍንጫቸው የታጠቁ ክልሎች ሊኖሩ አይገባም” ፕሮፌ. ብርሃኑ ነጋ

የትግራይ ክልል እስሩ የትግራይ ተወላጆች ላይ ያነጣጠረ ነው የሚል ከሆነ የሚያቀርባቸው መረጃዎች ምንድንናቸው ብለው የሚጠይቁት ደግሞ አቶ ሙሼ ናቸው።

የትግራይ ክልል አሳልፌ አልሰጥም ቢል በቀጣይ ምን ሊከሰት ይችላል?

የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ሕግ አቶ ብርሃኑ ፀጋዬ አቶ ጌታቸውን ለመያዝ ሰው መግደል የለብንም ማለታቸው ይታወሳል። አቶ አብረሃም አቶ ጌታቸውን ለመያዝ የኃይል እርምጃ ሊወሰድ እንደማይገባ ይናገራሉ።

“አንድን ሰው ለመያዝ ተብሎ ወደ ጦርነት ይገባሉ ብዬ አላስብም የፌደራል መንግሥትም ፖለቲካውን ለማስተካከል ሲል ዝምታን ይመርጣል ፤ የትግራይ ክልልም የራሱን ህዝብ የራሱን ደህንነት ይጠብቃል ብየ አስባለሁ።” ይላሉ።

የኢትዮጵያና የአካባቢው ፀጥታ (Security) በሽግግር ወቅት (ከዳዊት ወልደጊዮርጊስ)

Major Dawit WoldeGiorgis.

ዳዊት ወልደጊዮርጊስ

ለቪዥን ኢትዮጵያ 7ኛ ኮንፈረንስ
አዲስ አበባ ታህሣስ 18-19 የቀረበ የምርምር ወረቀት

ከዳዊት ወልደጊዮርጊስ

መግቢያ

ከሰላሳ ዓመት በኋላ ይህችን የተወለድኩባት፣ እትብቴ የተቀበረባት፣ የተማርኩባት፣ በውትድርና ሙያም፣ በሲቪልም በተለያዩ ከፍተኛ የኃላፊነት ደረጃ የታገልኩላት፣ የቆሰልኩላት፣ ወድጄ ሳይሆን ተገድጄ ትቻት ሄጄ የነበረችውን ክቡር አፈር ለመርገጥ ላበቃኝ አምላክና ይህንንም ሁኔታ ላመቻቹልኝ ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ምስጋናዬ ታላቅ ነው፡፡ በቀሪ ዕድሜዬ ይህንን እመሰክራለሁ ብዬ አልገመትኩም ነበር፡፡ የዶክተር አቢይን አመራርና ራዕይ እንድንደግፍ  ጥሪ ካስተላለፉት የመጀመሪያዎቹ ነኝ፡፡ Let us Rally around Prime Ministir Abiy በሚል ፅሑፍ  ድጋፌን፣ አድናቆቴን ቀደም ብዬ ገልጫለሁ፡፡ አሁንም አቋሜ ይህ ነው፡፡

በሀገራችን ውስጥ ዘለቄታ ያለው ሰላምና ዕድገት እንዲኖር ይህ ሥርአት መለወጥ እንዳለበት አጠያያቂ ሊሆን አይገባም፡፡ ይህም ማለት ኢህአዲግና ይህ ሕገ መንግሥት ተለውጦ ወደ አዲስ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ካልተሸጋገርን ኢትዮጵያ ውስጥ ሰላም አይኖርም ከሚለው  ፅንሰ ሃሳብ ተነስቼ ነው ይህንን ወረቀት ያዘጋጀሁት፡፡

ዛሬ የምንጣላው ከራሳችን ጋራ እንጂ ከውጪ ጠላት ጋር አይደለም፡፡ ስለዚህም የኢትዮጵያ ህልውና በተለየ መልኩ ልዩ የሆነ ፈተና ውስጥ ገብቷል፡፡

ታሪካችን ባህላችን ማንነታችን የማይደግፈው ከጠባብ እውቀት የመነጨ አስተሳሰብ አሁን በሀያ እንደኛው ክፍለ ዘመን ለኢትዮጵያም ለአፍሪካም ለመላው ዓለምም የሚያሳየው ኋላ ቀርነትን ብቻ ስለሆነ ይህች የታሪክ መሰረት ያላት ኢትዮጵያ ጥሩ አመራር ካላት በአጭር ጊዜ ውስጥ ልታጠፋው ትችላለች::እውነት ጠፍታ ከርማለች፡፡ የሚያድነን እውነት ነው::

ዛሬ ትኩረት እንዳደርግበት የተሰጠኝ ርዕስ “ሴኩሪቲ በአገሪቱና በአካባቢው በሽግግር ላይ ያለው ተጽእኖ” የሚል ነው፡፡ሰፋ ያለ በመሆኑ በአጭር ጊዜ ውስጥ የሚሸፈን አይደለም፡፡ ዋና፣ ዋና አንኳር የሆኑትን በኔ ግምት አቀርባለሁ፡፡

በአሁኑ ዘመን በአፍሪካ ውስጥ ያለው የጸጥታ ሁከት ካለፈው ዘመን የተለየ ነው፡፡ ፀረ-ኮሎኒያሊዝም ጦርነቶች ወረራዎች  ዛሬ የሉም፡፡ ዛሬ በአፍሪካ የሚታዩ የጸጥታ ችግሮች የመብት ጥያቄዎች፣ የነጻነት ጥያቄዎች፣ የዲሞክራሲ ጥያቄዎች፣ ከዚሁ ጋር የተያያዙ በአክራሪዎች በተቋቋሙ ንቅናቄዎች የሚፈጠሩ የጸጥታ ችግሮች ናቸው፡፡ እኔ የምሠራበት የምርምር ተቋም የአፍሪካ የጸጥታና የጸጥታ ስትራቴጂ ጥናት ማዕከል (AISSS) ኢትዮጵያን የመሰሉ ሀገሮች በሚያንዣብብባቸው ችግሮች ላይ ጥናት የሚያካሄድ ድርጅት ነው፡፡ ሙሉ ጊዜዬንም በዚህ ላይ ስለማሳልፍ ከብዙ ሰው የተሻለ ግንዛቤ አለኝ፡፡

የተባበሩት መንግሥታት፣ በአፍሪካ አንድነት ድርጅቶች ንግግርና ስምምነት መሰረት ሴኩሪቲ የሚያተኩረው እንደቀድሞው በመንግሥትና በስርዓት ጥበቃ ላይ ብቻ ሳይሆን በሰውና በማህበረሰብ ላይ ነው፡፡ በእግንሊዘኛ (People Centric) ይሉታል፡፡ በሴኩሪቲ፣ በሰብአዊ መብቶች፣ በእኩልነት በጠቅላላው በእድገት ጥያቄ ላይ ያተኮረ ነው፡፡ እነዚህ በመጓደላቸው ለሚፈጠረው የጸጥታ ጉድለት በመጀመሪያ ተጠያቂ መንግሥት ነው፡፡ ከዚያ ቀጥሎ የኢንተርናሽናል ህጎችን ይመለከታል::

የዛሬው ውይይታችን የሚያተኩረው በህዝቦች መሀከል እና በህዝብና በመንግስት መሀከል ስላለው ግጭት እና ጉዳያችን ጉዳያቸው ከሆኑት የጉረቤት ሀገሮች ጋር ስላለው ግንኙነት ነው::

የፀጥታ መደፍረስና የሀገር መሪዎች ሚና

ኢትዮጵያ በሰላም ወደ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ለመሸጋገር በምትጥርበት በአሁኑ ወቅት፣ ብዙ የጸጥታ ችግሮች እንዳሉ ይነገራል፡፡ ከኢትዮጵያ ከወጣሁ በኋላ ለሃያ አምስት ዓመት በአፍሪካ ጸጥታ በደፈረሰባቸው፣ በተፈጥሮም ሆነ በሰው ሰራሽ ችግሮች  ምክንያት የመንግሥታት አቅም ፈተና ላይ በወደቀባቸው ከሱማሊያ በስተቀር በሁሉም ሀገሮች በአማካሪነት ሰርቻለሁ፡፡ በሩዋንዳ፣ አንጐላ፣ ላይቤሪያ፣ ሱዳን፣ ደቡብ ሱዳን ሴራሊዮንና በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጐ የህዝብ እልቂትን፣ የመንግሥታትንና የሀገር ውድቀትን መስክሪያለሁ፤ ጽፌአለሁኝ፤ ፕሮጀክቶችንም አስተዳድሬአለሁ፡፡ በሴንትራል አፍሪካ ሪፐብሊክ በሞዛምቢክ፣ ማሊ፣ አይቬሪኮስት ለአጭር ጊዜ ጥናት ሄጃለሁ:: ስለዚህም ካነበብኩት ካዳመጥኩት ብቻ ተነስቼ ሳይሆን የምናገረው በቦታው ላይ ተገኝቼ በመሰከርኩትና ባገኘሁት ልምድ ላይ ተመስርቼ ነው::

በሁሉም ሀገሮች የውድቀት፣ የዕልቂት፣ የጦርነት ዋና ምክንያቶችና ተጠያቂዎች መሪዎች ናቸው፡፡ ምክንያቶቹ የመልካም አስተዳደር ጉድለትና የመሪዎች ሆዳምነት ለህዝብ ፍላጐት ተገዢ ለመሆን አለመፍቀድ፣ ወይንም የህዝብን ፍላጐት ለማወቅ አውቆም ለመረዳት አለመቻል ናቸው፡፡ የሀገሪቱ ታሪክ መጀመሪያም፣ መጨረሻም እኛ ነን ብለው የተነሱ ብዙዎች ነበሩ፡ አሉም::በዓለም ታሪክ ታላላቅ ስህተቶች ተሰሩ የሚባሉት ሁሉ የታሪክ ድግግሞሽ ናቸው፡፡ መሪዎች ካለፈው መማር አለመፈለጋቸው፣ አለመቻላቸው፣ ጤናማ አስተሳሰብን (Reason and common sense ) ለመከተል ፍቃደኛ ባለመሆናቸው የራሳቸው የግል ምኞት፣ ማለትም (Ego) እያሸነፋቸው ራሳቸውን ከሚያስተዳድሩት ህዝብ በላይ በማየታቸው ለእነሱም ለሀገሪቱም ውድቀት ምክንያት ሆነዋል እየሆኑም ነው፡፡

ከክርስቶስ ልደት በፊት በግሪክ ሥልጣኔ ከተጀመረ እስካለንበት ዘመን ያሉን ታላላቅ ስህተቶችን (folly) መርምራ ያቀረበች የታሪክ ሊቅ፣ አዋቂ ባርባራ ቱክማን፣ (The March of folly) በሚለው መጽሐፍ እንዲህ ትላለች፡፡

“A phenomena noticeable throughout history regardless of place or period is the pursuit by governments of policies contrary to their own interests…..why do holders of high office so often act contrary to the way reason points and enlightened self interest suggests? Why does intelligent mental process seem so often not to function?”

 • Misgovernment is four kinds(የተሳሳቱ አስተዳደሮች 4 ዓይነት ናቸው)
 • Tyranny or oppression ( አምባገነነትና ጭቆና)
 • Excessive ambition ( ከልክ በላይ የሆን የስልጣን ጥማት)
 • Incompetence ( የችሎታ ማነስና የትምህርት መዳከም )
 • Folly or perversity ( በትክክል ሁኔታን እለመገመትና ሆን ብሎ በጥፋት መንገድ መሄድ መሪዎች የዚህ ሰለባ ሲሆኑ ሀገር መውደቅና ሰላም ማጣት ትጀምራለች፡፡)

መሪዎች መፈለግና ማቅረብ የሚገባቸው የሚጠይቃቸውን፣ የሚከራከራቸውን፣ ነው፡፡ በታሪክ እንደታየው ብዙ መሪዎች ስህተታቸውን ማወቅ አይፈልጉም፡፡ ቢያውቁም ማረም አይፈልጉም፡፡ ከጊዜ በኋላ ሁሉን ነገር አዋቂ ሆነው ይቀርባሉ፡፡ አካባቢያቸው በዕውቀትና በተሞክሮ ሳይሆን በሌላ መሥፈሪያ የተመረጡ ሰዎች እንዲሆኑ ሲደረግ በመሪዎች ፍላጐት ብቻ ሀገር ትመራለች፡፡ መከበር ቀርቶ መፈራት ይመጣል፡፡ መፈራት ሲመጣ በአካባቢው ያሉት ባለሙያዎች ሁሉ መሪው የሚፈልገውን እንጂ፣ እውነትን ከመናገር ይቆጠባሉ:: ያለው ሕገ መንግሥት ለእነሱ አገዛዝ መቆየት እንዲያመች ማረምና መለወጥ ይጀምራሉ፡፡ በዚህም ምክንያት ጥሩ ነገርን የጀመሩ መሪዎች መጨረሻቸው አያምርም፤ ከክፋትም ሆነ ከሞኝነት በመነጨ የግል ውሳኔ እየተመሩ ስህተት ውስጥ ይዘፈቃሉ:: የወደዳቸውን ያህል ህዝብ ይተፋቸዋል፣ ይወድቃሉ፣ አገርንም ለጊዜውም ቢሆን ያናጋሉ፡፡ ስለዚህ ነው መሪዎቻችንን በእክብሮት ግን በድፍረት ቀርበን የህዝብን ፍላጉትና ድምፅ ማሰማትና የሚወስዱ እርምጃዎች ሁሉ የተመከረባቸው የአብዛኛውን ህዝብ ፍላጎት ማንፅባረቅ እንዳለባቸው ማስገንዘብ ያለብን:: ከጥቂት ዓመታት በፊት የአፍሪካ Renaissance መሪዎች ተብለው ስማቸው ለጥቂት ጊዜ የገነነው መሪዎች የት እንደደረሱ መገንዘብ ያስተምራል፡፡ ስለዚህም ክቡር ጠቅላይ ሚንስትር አቢይ ከነዚህ ሁሉ ትምህርት ለመቅሰም የሚያስችል ዘመን ላይ ስላሉ ይህንን የመሰለ ታሪክን እንደማይደግሙ ሙሉ እምነት አለኝ፡፡

ለሰላምና ለሀገር ሕልውና አጣዳፊ ተግባሮች

በአገራችን ውስጥ የሰፈነውና የጸጥታ ችግር በህግ የበላይነትን አለመጠበቅ ምክንያት ነው እየተባለ ብዙ ይነገራል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን የጸጥታ ሁኔታ አሻሽሎ ህዝብ እንደፈለገ መንቀሳቀስና መሥራት አብሮ መኖር እንዲችል የህግ የበላይነት ማስጠበቅ ተገቢ ነው ፡፡ ግን የህግ የበላይነት ሊከበር የሚችለው ህግ ሲኖር ነው::አለ የሚባለው ሕግ የሁሉም ሕጐች ምንጭና መሰረት ሕገ መንግሥት በህዝብ ምክክር (ፓርቲሲፔሽን) ያልተደነገገ ሕግ ስለሆነ፣ አብዛኛው ህዝብ ይህንን ሕግ ነው ብሎ ሊያከብረው አልቻለም፡፡ ሊያከብረውም አይገባውም፡፡ ሕጉ እራሱ ህዝብ ለህዝብ እንዲጋጭ በጥቂቶች ተጠንቶ ከጫካ በመጣ በጥላቻና ከፉፍሎ የመግዛት ርእዪት ላይ የተመሰረተ ነው:: ዛሬ ጥያቄው መሆን ያለበት እንዴት እዚህ ደረጃ ላይ ደረስን ሳይሆን እንዲት እስከዛሬ ህዝቡ ርስ በርሱ አልተላለቀም ነው? ዛሬ የኢትዮጵያ ህዝብ እርስ በርሱ የማይተላለቀው

እግዚአብሔርን ፈርቶ፣ ወይንም ባህሉ፣ የብዙ ዘመናት የአብሮነትና የኢትየጵያዊነት ስሜት ስላሸነፈው እንጂ፣ እንደ ሕግ መንግሥቱ ቢሆንማ  ይህ ህዝብ ከብዙ ዓመታት በፊት ተላልቆ አገሪቱ ተበታትና ነበር::

የቀድሞ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ አርቃቂ ኮሚቴ አባልና ሕገ መንግሥቱን ያፀደቀው አካል ሰብሳቢ ነበሩ፡፡ የምክር ቤቱም ሊቀመንበር እሳቸው ነበሩ፡፡ ለአዲስ ስታንዳርድ ጋዜጣ በሰጡት ኢንተርቪው ላይ እንዲህ ይላሉ፡፡

That is one of the major points where looking back in retrospect we did not think properly. We knew that there was no proper atmosphere where different parties could organize meetings with their members to discuss on the draft constitution before it became final. That is one of the biggest shortcomings ….እንደገና ሌላ ቦታ ላይ ደግሞ ሌላ ትልቅ የሽግግሩ ፓርላማም ረቂቁን ካፀደቀው በሁዋሏ We should have presented it back to the people of Ethiopia in a form of referendum where the people could have had the chance to decide on whether what we formulated was according to their own wish. That we did not do. I believe it was a mistake…. I fear if something is not done this constitusion will not hold the country together.

ዛሬ የህዝብ ጥያቄ ያ ስህተት ይታረም ነው:: ያ ሬፈረንደም ይካሄድ ነው:: በዚህ ህግ አንገዛም ነው:: ይህንን ታሪካዊ ስህተቶች አርመው የኢትዮጵያ ህዝብ የመከረበት ሕገ መንግሥት እንዲረቀቅና እንዲጸድቅ ነው ጥያቄው::

የኢትዮጵያ ህዝብ ዶ/ር አብይ አህመድን ነው እንጂ፣ ሕገ መንግስቱን ወይም ኢህአዲግን አይደለም የተቀበለው:: ኢህአዲግንማ  ሲዋጋው፣ ሲታገለው ኖረ፡፡ ሕገ መንግስቱንማ የዘር ፖለቲካ ኤትኒክ ፖሊሲ መስርቶ ህዝቡን ሲያፋጀው ነው የኖረው፡፡ ዶ/ር አብይ አህመድን ህዝብ የተቀበላቸው የዘር ፖለቲካን ያጠፋሉ፣ የኢትዮጵያን ህዝብ ያስተባብራሉ፣ ያስማማሉ በሚል እምነት ነው፡፡ ዶ/ር አብይ የኢትዮጵያ ህዝብ አልመረጣቸውም፡፡ አንድ ፓርቲ ነው የመረጣቸው፡፡ ነገር ግን አብዛኛው የኢትዮጵያ ህዝብ እንደ አንድ ፓርቲ ተመራጭ ሳይሆን፣ እንደ ኢትዮጵያዊ ተመራጭ አድርጐ ነው የተቀበላቸው፡፡

ዶ/ር አብይ አህመድ የአንድ የብሄር ፓርቲ ሊቀመንበር የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር በመሆናቸው ኃላፊነታቸው እንደሚጣረዝ ያውቃሉ፡፡ ፓርቲው ከፓርቲው መሪነት ቢያነሳቸው ከጠቅላይ ሚኒስትርነትም ይነሳሉ፤ በኢትዮጵያ ውስጥ ታላቅ ሁከት ይፈጥራል፡፡ የብሄር ተወካይ ሳይሆኑ የኢትዮጵያ ህዝብ ተመራጭ ሲሆኑ ብቻ ነው ነው ዶ/ር አብይ ሙሉ ስልጣን ከመላው ኢትዮጵያ ተረክበው ህግን ማስከበር፣ ኢትዮጵያን የዲሞክራሲያዊ የሰላምና የአንድነት ሞዴል አድርገው የኢትዮጵያዊያንን ፍላጐትና የአፍሪካን ምኞት ሟሟላት የሚችሉትና ታሪክ የሚሰሩት፡፡ ሐቁ ግን ይህ አይደለም፡፡

በዚህ ሁኔታ ዶ/ር አብይ የመጀመሪያ ኃላፊነታቸው ለመረጣቸው ፓርቲ ነው ወይስ ለኢትዮጵያ ህዝብ? የሚለው ጥያቄ አነጋጋሪ ነው፡፡ ዶ/ር አብይ ከዚህ ወጥመድ ውስጥ መውጣት የሚችሉት ራሳቸውን ከፓርቲአቸው ተጽእኖ አላቀው የኢትዮጵያን አጀንዳ ይዘው ሲራመዱ ብቻ ነው፡፡ ይህንንም ማድረግ የሚያስችላቸው ብዙ አማራጭ እንዳለ እሳቸው ያውቃሉ፤ ወይዘሮ መስከረም አበራ ባቀረበችው ፅሁፍ ላይ በፓርሊያመንታሪ ስርአትና ፕሬዚዳንሺያል ስርዓት መካከል አማካኝ መንገድ እንዳለ ጠቁማለች:: ይህንንም ሌላ አማራጭ ለውይይት አቅርባለች ጥሩ የአዋቂ ተመራማሪ ትንተና ነው፡፡እኔ ደግሞ እንድንነጋገርበት የማቀርበው ሐሳብ ዶ/ር አብይ የኢህአዲግን ሕገ መንግሥትና ፓርላማ በአዋጅ እንዲያፈርሱ፣ እሳቸው በአዋጅ በሚሰጣቸው ሥልጣን መሰረትና የጊዜ ገደብ እስከ ምርጫው ድረስ በጠቅላይ ሚኒስትርነት እንዲያገለግሉ፡፡ አዋጁ የብሔር የተደራጁ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ሳይሆን ሀገራዊ አጀንዳ ያላቸውን ፓርቲዎች ብቻ ተፎካካሪ ፓርቲ እንዲሆን እንዲያውጅ፤ ጠቅላይ ሚንስትር አብይ የኦሮሞ ዲሞክራቲክ ፓርቲን ወደ ኢትዮጵያ ዲሞክራቲክ ፓርቲ ለውጠው ሀገራዊ አጀንዳ ይዘው ለውድድር እንዲያቀርቡ፤ የብሔር ድርጅቶች የብሔረሰባቸውን መብት ለማስጠበቅ በፖለቲካ ፓርቲዎች ላይ ተፅዕኖ የሚፈጥሩ የሲቪክ ድርጅቶች እንዲሆኑ ነው፡፡ ይህ የሆነ እንደሆን የዘር ፖለቲካ ቀስ በቀስ መጥፋት ይችላል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩም ከብሔር ፖለቲካ በላይ የሆኑ መሪ ይሆናሉ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩም የሙሉ  የኢትዮጵያ ህዝብ ድጋፍ ሊኖረው የሚችል የኢትዮጵያ አጀንዳ ይዘው በተጠናከረ ማዕከላዊ መንግሥት ሀገርን መምራት ይችላሉ፡፡ በግርድፉም ይህንን የሚመስል ሐሳብ አቀርባለሁ፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ለውጥ ሊመጣ የሚችለው የተለያዩ አማራጮችን መርምሮ ነው አዲስ ስርአት መገንባት የሚቻለው::

በዓለም ውስጥ በዘር ፓርቲ የተመሰረተ የፌዴራል ሲስተም ፈልጌ አጣሁ፡፡ በዘር የተመረጠ ፓርቲ ስልጣን ላይ የወጣ የትም ቦታ በዓለም ውስጥ የለም፡፡ በአፍሪካ ውስጥ ሶስት አገሮች ናቸው የፌዴራል ስርዓት ያላቸው፤ ኮሞሮስ፣ ናይጄሪያና ኢትዮጵያ፤ ኢትዮጵያ ብቻ ናት በዘር፣ በቋንቋ የተመሰረተ ፌዴራሊዝም ያላት፡፡

ለምንድነው አዲስ ዲሞክራሲዎች በአፍሪካም በሌሎችም አሁጉሮች ቶሎ የሚፈርሱት? በሚለው ጥያቄ ላይ ሁለት ታላላቅ የፖለቲካና የታሪክ ሊቆች በጻፉት ላይ፣ Athoritorianizm and Elite origins of Democracy የሚለውን መጽሐፍ መመልከት ይጠቅማል፡፡ “Over 2/3 of countries that have transitioned to democracy since World War II have done so under constitutions written by the outgoing regimes”

በእብዛኛው እነዚህ ሀገሮች ናቸው ሰላምና መረጋጋት አጥተው ያሉት:: ምክንያቱም ሕገመንግስቱን የቀረፀው ያፅደቀው መንግስት በመሆኑ ነው::  በዲሞክራሲ ስርአት ሕገመንግስት ነው መንግስትን የሚወልደው:: ኢትዮጵያ ይህንን የማድረግ እድልዋ አሁን ነው:: ይህ ጊዜ ካመለጠ ኢትዮጵያ የዘወትር ሽብርና ምንዓልባትም የመበታተን እድሏ ከፍተኛ ይሆናል ብዬ እገምታለሁኝ:: የአገሪቱን ሁኔታ በጥሞና ለተከታተለ ይህ እማራጭ የሌለው መፍትሄ እንደሆነ የሚስማማበት ይመስለኛል፡፡

ለዶ/ር አቢይ ይህንን ማድረግ አስቸጋሪ መሆኑ ጥርጥር የለውም፡፡ ግን ይህንን ውስብስብ ሁኔታ ጥሰው ለመውጣት የአብዛኛው የህዝብ ድጋፍ ይኖራቸዋል፡፡ ይህንን የመሰሉ ሀሳቦችን ይዞ ሕዝብ የሚነጋገርበት፤ ተነጋግሮም የሚስማማበት መድረክ ለመፍጠር እና የሀገርን አቅጣጫ ለመቀየስ ሁለት ጉባኤዎች ያስፈልጋሉ ብዬ አምናለሁ፡፡

 1. 1. የሽግግር ጐባኤ፡- የሽግግር ጉባኤ አስፈላጊነት

ኢትዮጵያ ውስጥ የዘለቄታ ሰላምን ለመመስረት የኢትዮጵያ ህዝብም ከርስ በርስ ግጭት እንዲድን ህልውናውም እንዲጠበቅ የሚያስችል፣ ንድፈ ሀሳብ  የሚቀርጽ፣ ከህዝቡ ጋር ቀጥታ የሚያነጋግር ጉባኤ ማዘጋጀት አስፈላጊ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ የኢትዮጵያን አቅጣጫ የሚቀይሰው ህዝብ መሆን አለበት፡፡ ስለዚህ ዶ/ር አብይ አህመድን የሚያግዝና ህዝባዊ የሆነ አቅጣጫ ሊሰጣቸው የሚችል ጉባኤ በአስቸኳይ መጠራት አለበት፡፡ ሁሉም ብሔረሰቦች፣ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ የሰብአዊ መብት ጠባቂዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የወጣት ማህበራት፣ አክቲቪስቶች የተወከሉበት ጉባኤ ተጠርቶ የጥቂት ቀናት ወይም እንደ አስፈላጊነቱ የብዙ ቀናት ውይይት አድርጐ አቅጣጫ (Road Map) የሚያሳይ ውሳኔ ላይ እንዲደርስ መደረግ አለበት፡፡ እዚህ ጉባኤ ውስጥ ለመግባት መመዘኛው በግልጽ የማያጠያይቅ መሆን አለበት፡፡ በኢትዮጵያ አንድነት፣ በዳር ድንበሯ፣  በህዝቦቿ እኩልነት፣ በዲሞክራሲ ስርዓትና በሰላማዊ ትግል የሚያምኑ መሆን አለባቸው፡፡ ይህንን የማያሟሉ ድርጅቶች እዚህ አገርም፣ እዚህ ጉባኤም መገኘት የለባቸውም፡፡ አለበለዚያ የሚፈለገውን አጠቃለይ ስምምነት ላይ መድረስ አስቸጋሪ ይሆናል፡፡ ይህ ጉባኤ የሚነጋገርባቸው ዋና ዋናዎቹ፣ ህግ መንግሥቱን ስለማረም ወይንም ስለመለወጥ፣ የምርጫ ቦርድን ስለመመስረት የእውነት፣ የእርቅና የፍትህ ኮሚሽንን ስለማቋቋም በሚሉት ርእሶች ላይ ነው:: እነዚህ እባላት የሚመረጡት በመንግስት ሳይሆን በህዝብ ነው:: ይህንን አመራረጥ ዘዴ የሚያጠና ቡድን ማቋቋም የመጀመሪያው ሥራ ሊሆን ይገባል::

በእነዚህ ጉዳዮች ላይ የሚደረስባቸውን ስምምነቶች እንዴት አድርጐ ለህዝብ ማቅረብና ህዝብ እንዲወያይበት ለማድረግ ይህን ጉባኤ የሚቀርጽ አዘጋጅ ኮሚቴ ከመንግሥት ተቋማት ሳይሆን ከህዝብ መካከል ይመረጣል፡፡ ይህ ሁሉ ረጅም ጊዜ ሊወስድ ይችላል፤ ግን ይህ ፕሮሰስ እስከተጀመረ ድረስ ህዝቡ ወዴት አቅጣጫ እንደሚሄድ ስለሚያውቀው ተረጋግቶ የእለት ኑሮውን ሊቀጥል ይችላል፡፡

 1. 2. ሁለተኛው ጉባኤ

የሰው ልጅ ኑሮ ከእግዚአብሔር ሕግ ባሻገር በሀገራዊና በኢንተርናሽናል ሕግ ላይ የተመሰረተ ነው፡፡ መንግሥታት በሀገራቸው ውስጥ በተፈጠረው የጸጥታ መደፍረስ፣ ወንጀለኞችን ህግ ፊት ለማቅረብ ይገደዳሉ፡፡ ይህንንም ለማድረግ አቅም ከሌላቸው ወይንም ሁኔታው የማያመች ከሆነ ገለልተኛ ለሆኑ አቅሙ ላላቸው የኢንተርናሽናል ፍርድ ቤቶች ወይም ትሪቡናሎች ያቀርባሉ፡፡ እንደ Hague, ICC, Tribunal በሩዋንዳ ጉዳይ ላይ አሩሻ ላይ የተቋቋመ ኢንተርናሽናል ትሪቡናል ምሳሌ ነው፡፡ በላይቤሪያና በኬንያ፣ በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኦፍ ኮንጎ ለደረሰው ግፍ ተጠያቂ የሆኑ ወደ ICC ተልከዋል፡፡ አሁን በባለፈው ዘመን የተፈጠረ አዲስ ሀሳብ (transitional justices) ወይም የሽግግር ፍትህ (restorative justices)  በተወሰኑ የአፍሪካ ሀገሮች ተሞክሯል፡፡ ይህም የመጀመሪያው የሀቅ፣ የዕርቅና የፍትህ ኮሚሽንን በማቋቋም ነው፡፡ ዴሞክራሲያዊ ካልሆኑና ብዙ ኢሰብአዊ ድርጊቶች ከፈጸሙ ስርዓት ወደ ዲሞክራሲያዊያና ሰላማዊ ስርዓት ለመሸጋገር ብሔራዊ ዕርቅና መረጋጋት ያመጣል ተብሎ በብዙ ታዛቢዎችና አዋቂዎች ታምኖበታል፡፡ መንግሥት የጥፋቱ አካል ሆኖ፣ ተጠያቂ ሆኖ የጥፋቶች ሁሉ የበላይ ተመልካች ሆኖ ራሱ ይህንን አይነት ኮሚሽን ሊያቋቁም አይችልም፡፡ ትርጉምም አይኖረውም፤ ይህ አሰራር ከአፍሪካ ውስጥ ሶስት አገሮች ውስጥ ተሞክሯል፡፡ በመጀመሪያ ደቡብ አፍሪካ፣ ከዚያም ሩዋንዳና ላይቤሪያ በሶስቱም ሀገሮች ሰርቻለሁ፡፡ የሶስቱንም ሀገሮች የኮሚሽን የስራ ውጤት በቅርብ ተከታትያለሁ፡፡ ይህ አሰራር የሚያጠቃልለው አራት ነጥቦችን ነው፡፡ በወንጀል መጠየቅ(Criminal prosecution) እውነትን ፍለጋ (Truth seeking) ካሳ የመክፈል (Reparations) አዲስ ህጉችን(Reform laws) ስለማውጣት ጉዳይ ነው፡፡ ይህ (Prescriptive) ወይም ቋሚ የሆነ የአሠራር ሕግ ሣይሆን መንፈሱን ያዘለ ከሀገሩ ባህልና ተጨባጭ ሁኔታ ጋር የተዛመደ አሰራር እያንዳንዱ ሀገር መፍጠር ይኖርበታል፡፡

ኢትዮጵያን ወደፊት የሚያራምዳት ፍትህና ብሔራዊ እርቅ ነው፡፡ ብሔራዊ እርቅ ያለእውነት ሊኖር አይችልም በማናቸውም ወገን የተፈጸመው ግፍ ጥርት ብሎ መውጣትና መነገር አለበት፡፡ ያጠፉ ሰዎች በይፋ መውጣት አለባቸው፡፡ በዳይና ተበዳይ ፊት ለፊት መተያየት አለባቸው፡፡ የተበደለውም ካሳ ሊያገኝ ይገባል፡፡ አለፍትህና አለእውነት እርቅ አይኖርም በሚለው  ጽንሰ ሐሳብ ላይ የተመሰረተ ነው፡፡

በደቡብ አፍሪካ በቢሾፕ ዴዝሞንድ ቱቱ ይመራ የነበረው ትሩዝ ኤንድ ሪኮንሲሌሽን ኮሚሽን ለብዙ ዓመታት በይፋ ተካሂዷል፤ ውጤቱ አከራካሪ ነው፤ አብዛኛው ህዝብ አውነቱ በሚገባ አልወጣም፣ ፍትህም አልተሰጠም ይላል፡፡ ስለዚህ ነው ዛሬ የአፓርታይድ ውርስ በሀገሪቱ ሙሉ ለሙሉ ያልተገፈፈው፤ የርስ በርስ ጥላቻ በሀገሪቱ ውስጥ በእኩልነት ለመኖር የሚያስችል ሁኔታ ኮሚሽኑ አላመቻቸም እየተባለ የሚነገረው፡፡ የደቡብ አፍሪካ ህዝብ እንደተከፋፈለ ነው፡፡ በሶስቱ ዋና ህብረተሰቦች መካከል ያለው ግንኙነትና የሚያነጋግር ጥላቻ ገና ብዙ ጊዜ ይቀረዋል፡፡ እንደታሰበው በዳይና ተበዳይ ኮሚሽን ፊት ቀርቦ ለምን ያን ሁኔታ እንደተፈጸመ ተነጋግረው፣ ተላቅሰው፣ በኋላም ተባርከው በሰላም ይኖራሉ የሚለው ግምት ብዙ አከራክሯል፡፡ ምክንያቱም የአፓርታይድ መሪዎች ኢሰብአዊ ድርጊቶች በፈጸሙት ላይ ፍትህ አልሰጡም፡፡ ለተበዳዮችም ካሳ አልተሰጠም፤ ሁሉም እውነት አልወጣም የሚሉ ብዙዎች ናቸው፡፡ ከአፖርታይድ በኋላ በነጻዋ ደቡብ አፍሪካ የመጀመሪያው ፕሬዝደንት የMr Nelson Mandela ባለቤት የነበሩት  ወ/ሮ ዊኒ ማንዲላ የባለቤታቸውን ውሳኔና ይህንን አሰራር አውግዘዋል::

ወ/ሮ ዊኒ ማንዴላ ሲናገሩ እንዲህ አሉ “look at the truth reconciliation shared He should never have agreed to it what good dose a truth do how does it help any one where and how their loved once were killed and buried”

ከሀያ ስምንት ዓመት በፊት ያከተመው  የአርባ ሶስት ዓመታት የአፓርታይድ ስርአት ቁስልና መከፋፈል አልተፈወሰም፡፡

ላይቤሪያም ነበርኩኝ፤ በኮሚሽኑ ብዙ ስብሰባዎች ላይ ተገኝቻለሁ፡፡ ባጠቃላይ ከባድ ግፍ ፈጽመዋል የተባሉት አንዳንዶቹ በህዝብ ተመርጠው አዲስ መንግሥት ውስጥ ገቡ፡፡ ሌሎቹም በተፈጸመው ግፍ የሚጠየቁት ከተለያየ አቅጣጫ ድጋፍ ስላገኙ ትሩዝ ኤንድ ሪኮንሲሊዬሽን ኮሚሽን በአስራአራት ዓመት ውስጥ ለሞቱት፣ ለተሰደዱት፣ ለተቆራረጡት፣ ለተሰቃዩት እና ለቤተሰቦቻቸው ፍትህም፣ እርቅም ሳያገኝ ካሳም ሳይከፈል በብዙ መቶ ሺህ ገጾች የሚቆጠር ሪፖርት አቅርቦ ተበትኗል፡፡ የላይቤሪያ ችግር ኮሚሽኑን ያቋቋመው መንግሥት ስለሆነና የመንግሥቱ አባሎች አብዛኞቹ በወንጀሉ የሚጠየቁ በመሆናቸው ህዝቡን የሚያሰባስብ፣ የሚያቀራርብ፣ የሚያስታርቅ ባለመሆኑ ፋይዳ የሌለው ሙከራ ነበር:: የኢትዮጵያ ጉዳይ ይህንን አቅጣጫ የያዘ ይመስላል፡፡

ሩዋንዳ ወደ አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ ዜጎች ከተገደሉ በኋላ የመጀመሪያውን የዩናይትድኔሽን አርዳታ ሰጪ ቡድን የመራሁት እኔ ነበርኩ፡፡ ሬሳዎች ሲለቀሙ፣ ሲሰባሰቡ አገሪቱ ከባድ ትርምስ ውስጥ ላይ ሆና የሩዋንዳ ፓትሪዮቲቭ ፍሮንት(Ruwanda Patrotive Front) አገሪቱን ለማረጋጋት በሚሞክርበት ጊዜ እዚያው ነበርኩ፡፡ ሩዋንዳ ከዚያ እልቂት በኋላ ህዝቡን አንድ ለማድረግ ብዙ ጥረት አድርጋለች፡፡ እነዚህ ብዙ የተለያዩ ቅን ሙከራዎች፣ ህዝቡን አረጋግቶ ወደ እርቅ ጉዞ ማሸጋገር ተችሏል፡፡ እርቅ በአንድ ቀን በጥቂት ዓመታት የሚመጣ አይደለም፡፡ ጉባኤ ላይ ተገኝቶ በማጨብጨብና በመተቃቀፍ፣ በመላቀስ የሚፈታ አይደለም፡፡ ጊዜ፣ ጥረት፣ ትዕግስት እና መልካም አስተዳደር ይጠይቃል፡፡ በሩዋንዳ ጉዳይ ላይ እውነት ወጥቷል:: ያልተነገረ እውነት የለም፡፡ ከፍተኛ ወንጀል የሰሩ በአገር ውስጥ ፍርድ ቤትና በአሩሻ ትሪቡናል(Arushia Tribunial) እንዲሁም በሄግ(Hague) ፍርድቤት ቀርበው ፍርድ አግኝተዋል፡፡ በመካከል ላይ የሚገኙ ገዳዮች፣ አጥፊዎች፣ ተባባሪዎች በህብረተሰቡ ውስጥ ተቀላቅለው እንዲኖሩ፣ ጋቻ በሚባል ባህላዊ ስርዓት ህብረተሰቡ የእያንዳንዱን አጥፊዎች ወንጀል እየተመለከተ የሚቀጡበትንና ወይንም ከህብረተሰብ ውስጥ ተቀላቅለው የሚኖሩበትን ሁኔታ አመቻችቷል፡፡ አጥፊዎች ብዙ ስለነበሩ፣ ተበዳዮችም ብዙ ስለነበሩ የሀገሪቱን አንድነት ለማስከበር ሀገሪቱ በአንድነት ወደ እድገት እንድታተኩር እነዚህ የተለያዩ እርምጃዎች በመወሰዳቸው ዛሬ ሩዋንዳ በእድገት ከፍተኛ እምርታ አስመዝግባለች፡፡ ቁስሉ በቀላል የሚረሳ ስላልሆነ በጥንቃቄ ተይዞ ብዙ መሻሻል አሳይቷል::

የኢትዮጵያ ሁኔታ በመጠንም በአይነትም ከዚህ ጋር የሚወዳደር አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ በግልጽ የወጡ ወንጀሎች ተፈጽመዋል፡፡ በቅርቡ እንደተፃፈውና በይፋ በሚዲያ እንድተገለፀው መንግስት በህዝብ ላይ የፈፀመው በደል በጣም ዘግናኝና አስቃቂ ነበር:: ብዙ ጊዚያት በፅሁፍም በንግግርም ኢትዮጵያ እንደ ሩዋንዳ እንዳትሆን መጠንቀቅ አለብን ስል ብዙ ሰው እሹፎብኛል:: ” የኢትዮጵያ ህዝብ እንደዚህ ያለ ጨካኝ አይሆንም:: ባህል፣ ታሪክና እምነቱ ይህንን እንዲያድርግ እይፈቅድለትም ” ይሉኝ ነበር:: ህግና አመራር ሲጠፋ የባህልና የእምነትን መስመሮች አልፎ በስው ውስጥ ያለ ክፋት ገሀድ ይወጣል:: ማን እንደዚህ ያሉ ድርጊቶች በአገራችን ይፈፅማል ብሎ አስቦ ያውቃል? በህብረተሰቡ መካከል ዘርን አስመልክቶ ብዙ መፈናቅል፣ ብዙ የጥላቻ ዘመቻ፣ ብዙ ተነግሮ የማያልቁ ወንጀሎችና ጭካኔዎች ተፈፅመዋል:: እነዚህ ሁሉ በህዝብ መካከል በቀላሉ የማይሽሩ የአካልና የስነልቦና ጉዳቶች አድርሰዋል፡፡ ህዝቡም ተባብሮ፣ ተቻችሎ እንዳይኖር እንቅፋት ሆነዋል፡፡ እውነቱም አልታወቀም፤ እውነቱን ከውሸት አጥርቶ አውቆ ከፍተኛ ወንጀል የፈጸመ ፍርድ የሚያገኝበት ቀላል፣ ወንጀል የፈጸሙ ወይንም ተባባሪ የነበሩ፣ ጥላቻ ያሰራጩ ሁሉ በተበዳዮች ፊት እውነቱን ተናግረው በዳይና ተበዳይ ይቅርታ ሰጪና ይቅርታ ተቀባይ አብረው ሆነው ኢትዮጵያን ለመገንባት ብሔራዊ የእውነት፣ የይቅርታና የፍትህ፣ ከመንግስት ነፃ የሆነ ኮሚሽን መቋቋም አስፈላጊነቱ ሊፈተሽ ይገባል፡፡ ይህንን ሊያደርግ የሚችል ግን ኢህአዴግ አይደለም፡፡ ኢህአዴግ ራሱ ተጠያቂ ስለሆነ፡፡ እነዚህ የተፈፅሙት ብዙ ወንጀሎች ጥፋቶች በስርአቱ ተቋማት የተፈፅሙ እንጂ በግለስብ የተፈፀሙ አድርጎ ማቅረብ ትልቅ ስህተት ነው:: እያድበሰበሱ ማለፍ ችግሮችን ማካበት ነው:: ስለዚህ የመጀመሪያ ተጠያቂ ይህ መንግስት ነው:: ይህ መንግስት ከሳሽም ተከሳሽም ሊሆን አይችልም:: ፍትሃዊ ሥርዓት ተግባራዊ ሊሆን የሚችለው የስርአት ሽግግር ሲኖር ብቻ ነው፡፡ ሰላምም በመላው ኢትዮጵያ ሊስፍን የሚችለው ለግጭት ምክንያት የሆኑት ተጠይቀው እውነት ሲወጣ፣  ካሳ ሲከፈልና ፍርድ ሲሰጥ ብቻ ነው::

ወጣቱ ትውልድ

ይህንን ለውጥ ያሽከረከረው ታላቁ ሞተር ወጣቱ ትውልድ ነው፡፡ ኢትዮጵያን የመምራት ኃላፊትም፣ ብቃትም ሊኖረው የሚገባው ወጣቱ ነው፡፡ ታላቁ ፈላስፋ አርስቶትል እንዳለው፣ “ወጣቱ ተስፋ ለማድረግ ስለሚጣደፍ ስህተትም ይሰራል፤ በቀላሉም ይታለላል (youth is easly decived because it is quick to hope)”

ወጣቱ ትውልድ ለኢትዮጵያ እድልም ነው፣ ስጋትም ነው፡፡ ብዙ መስዋዕትነት ከፍሎ የኢትዮጵያን ህዝብ እዚህ አድርሷል፡፡ ነገር ግን ባለመማር፣ ባለማወቅ፣ ባለማንበብ፣ በስሜት በመገፋት፣ አውቆም ሆነ ሳያውቅ ከኢትዮጵያ አንድነት ውጪ ሌላ አጀንዳ ባላቸው የብዙዎች መሳሪያ ሆኗል፡፡ ባለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት በተጠና መንገድ ሲሰራጭ በነበረው የመንግሥት ፕሮፖጋንዳ በመታለሉ የአጥፊ ተልእኮ ያላቸው ለፈጠሩት ሐሰት ታሪክ የተጋለጠው ወጣቱ  ነው:: በዚህ ሁኔታ ላይ የሚገኘውን የወጣቱን አንድ ክፍል ወደ ኢትዮጵያ አጀንዳ ለመመለስና ገንቢ እንጂ አፍራሽ እንዳይሆን የሰላምና የአንድነት ዘብ እንዲሆን ብዙ ትግል ይጠይቃል፡፡ በትምህርት ቤት ከሚሰጠው መደበኛ ትምህርት ውጪ ለወጣቱ በያለበት ስለሚሰጠው ትምህርት አዲስ ስትራቴጂና ተቋማት መፈጠር አለባቸው፡፡ ካድሬዎች፣ አክቲቪስቶች አሰባስቦ በየቦታው በየቦታው ኢትዮጵያዊነትንና የጋራ ባህሎችን እሴቶችን፣ ስነምግባሮችን ለመስጠት ታላቅ አብዮታዊ ዘመቻ(Revolutionary Campain) ለመስጠት የሚያስችል ታላቅ የረዥም ጊዜ ዘመቻ (Revolutionary Campain) መከፈት አለበት፡፡ ይህ የፖለቲካ ፓርቲዎችንና የብሔረሰብ ድርጅቶችን ትብብር ይጠይቃል፡፡

በ2018 ዓ.ም. አልሙንዲ ኢንዴክስ እንደሚያሳየው የኢትዮጵያ ህዝብ ዲሞግራፊ ከ0-14፣ 43.4%፣ ከ15-24፣ 20.11%፣ ከ25-54፣ 29.58%፣ ከ55-64፣ 3.9% ከ65 በላይ 2.8% ነው የህዝቡ አከፋፈል፡፡ ይህ የሚያሳየው ምንድነው፣ 64% የሚሆነው የኢትዮጵያ ህዝብ እስከ 24 ዓመት ህጻንና ወጣት መሆኑን ነው፡፡ ከዛሬ 27 ዓመት ጀምሮ ከሰባት ዓመት በላይ የሆኑት ከ 10 እስከ 54 ያሉት ብቻ 70% በኢህአዴግ ጊዜ ያደጉ የተማሩ የሰሩ ወጣቶች ናቸው፡፡ ዛሬ 54 ዓመት የሆኑት የኢህአዴግ ሲገባ 27 እድሜ ስለነበራቸው ወጣቶች ነበሩ፡፡ በስራም ሆነ በትምህርት ዓለም ኢህአዴግ የዘር ፖለቲካ የተበከሉ፣ ወይንም የተጎዱ፣ ወይንም የተጋለጡ ናቸው፡፡ ይህ አስደንጋጭ ነው፡፡ አብዛኛው ሥራ አጥ እዚህ ውስጥ ይጠቃለላል፡፡ አብዛኛው የታሰረ፣  ወንድሙ፣ እህቱ፣  የቅርብ ዘመድ የታስረባቸው፣ የተገደለባቸው፣ በተለያዩ መንገዶች የተጠቁ ሁሉ እዚህ ውስጥ ይገኛሉ፡፡ ይህ ህዝብ በጣም የተቆጣ ህዝብ ነው:: ይህ የሚያሳየው ኢትዮጵያን ወደ ሰላማዊ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ለማሸጋገር ብዙ ስራ እንደሚጠይቅ ነው፡፡

በተባበሩት መንግሥታት (UNFPA) ጥናት መሰረት፣ በ2050 ከ0-24 ያለው ትውልድ ብዛት አፍሪካ ወስጥ በ50% ይጨምራል፡፡ በ2050 አፍሪካ በወጣት ህዝብ ብዛት ታላቋ አህጉር ትሆናለች፡፡ ከ18 ዓመት በታች ካሉት ወጣቶች በዓለም ውስጥ ከሰላሳዎች አንዷ ኢትዮጵያ ነች፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ ብዛት በ2050 መቶ ሰማንያ ስምንት ሚሊዮን አራት መቶ ሃምሳ(188,450,000) ሺ ይሆናል ተብሎ ይገመታል፡፡ ከናይጄሪያ ቀጥሎ በአፍሪካ ውስጥ ከፍተኛ የህዝብ ቁጥር ያላት ሀገር ሆና ትቀጥላለች ማለት ነው:: ኢትዮጵያ ዛሬ ከ18 ዓመት በታች ያለው ህዝብ ብዛት 48.7% ከሠላሳ ዓመት በኋላ ይኸው ትውልድ ከሚወልዳቸው ልጆች ጋር ተደምሮ ምን ዓይነት ደሞግራፊ እንደሚኖር ስንረዳ አሳሳቢነቱ ግልጽ ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ በዚያን ጊዜ የ72 ዓመት ዕድሜ ላይ ይደርሳሉ፡፡ በጡረታ ዘመናቸው ይህንን የመሰለ መድረክ ላይ ወጥተው ዛሬ ስላዘጋጁት ወይንም ስላላዘጋጁት ወጣት በጸጸት ወይንም በኩራት የሚናገሩበት ወቅት ይመጣል፡፡ ይህም ኢትዮጵያ ዛሬ እንደምናውቃት ትቆያለች በሚል ግምት ነው::

ያልተማረ፣ ስራ የሌለው፣ ማንበብ፣ ማዳመጥ፣ የማይፈልግ፣ የማይችል፣ ሁሉን የሚያውቅ የሚመስል፣ እውቀትን የሚያጣጥል፣ ከማናቸውም ወገን በሚነዛ ወሬ እንዳመቸው የሚዋዥቅ ወጣት በበረከተ ቁጥር የኢትዮጵያ ሴኩሪቲ ስጋት እየከረረ ይመጣል፡፡ እያደገ በሚመጣው ሥራ አጥነት ድንበር አቋርጦ የሚሄደው ቁጥር ብዛት ሌላ አማራጭ በማጣት ሽብርተኞች ሰፈር በመግባት(Rdicalization) በሰውና በመሳሪያ ሕገ ወጥ ትራፊክ ውስጥ በመሳተፍ የአካባቢውም የሀገሪቱም  የጸጥታ ችግሮች ምንጮች የሚሆኑት የዛሬዎቹ ወጣቶች ስለሚሆኑ፣ በሰውና በሰው ኃይልና ላይ ከባድ ኢንቨስትመንት (በማስተማር፣ በማሰልጠን፣ በማደራጀት) ካልተደረገ የኢትዮጵያና የአካበቢው ጸጥታ ወደ አልታወቀ አደገኛ ሁኔታ ያመራል፡፡

ህገወጥ የመሣሪያ ዝውውር

የህገወጥ መሣሪያዎች እንቅስቃሴ በኢትዮጵያ ውስጥ እየጨመረ መሄዱ ይነገራል፡፡ ለግል ጥበቃና ዝና ከሚያስፈልገው በላይ ብዙ መሣሪያዎች በአንድ ማህበረሰብ፣ በአንድ ቤተሰብ ውስጥ ይገኛሉ ይባላል፡፡ ይህ ከፍርሃት ከስጋት፣ በመንግሥትና በክልል ሃይሎች  እምነት ማጣት ላይ የተመሰረተ ነው፡፡ በቅርቡ ዘአበሻ በሚለው ድረ ገጽ እንደ አዳመጥኩት፣ መትረየስ፣ ስናይፐር፣ ሽጉጥ፣ ክላሽ፣ ጥይቶችና ቦንቦች በይፋ  ኢትዮጵያ ውስጥ ይሸጣሉ ይባላል፡፡ አርፒጂ መቶ ሃያ ሺ(120,000)ብር፣ ክላሽ ከስልሳ አምስት እስከ ሃምሳ ሺ (65,000-50,000) ብር፣ ሽጉጥ ከአርባ ሺ እስከ አስራ ሁለት ሺ(40,000-12000) ብር መግዛት ይቻላል ይባላል፡፡

ኢትዮጵያ አምስት ሀገሮችን ታዋስናለች፣ ከድንበሮች ባሻገር ያሉ ብዙ ጊዜ አንድ ባህል ያላቸው፣ ተመሳሳይ ቋንቋ የሚናገሩ አንድ ቤተሰብ ናቸው፡፡ የኢሚግሬሽን መስሪያ ቤቶች ወይንም የድንበር ኬላዎች ካሉባቸው አንዳንድ ስፍራዎች በስተቀር ከሀገር መውጣትም ወደ ሀገር መግባትም ቀላል ነው፡፡ በመኪና የሚገቡም በቀላሉ ድንበር  ያሉ ሰዎችን ጉቦ በመስጠት ያልፋሉ፡፡ በዚህም መልክ በዛሬ ጊዜ የሰው፣ የድራግ፣ የመሣሪያ፣  ህገ ወጥ እንቅስቃሴዎች በቀላሉ ይፈፅማሉ:: የተደራጁ ደላሎችና ነጋዴዎች በሽብርተኞች አማካይነት እንደልብ መንቀሳቀስ ችለዋል:: ኤኤክስኤክስ አፍሪካ (AXX Africa) የሚባለው በእንግሊዝ አገር የሚገኝ መረጃ ኢንቲትዩት ባለፈው ነሐሴ ወር “Arms Trade in the Horn of Africa” በሚል ርእስ ባወጣው ጥናት ላይ ጅቡቲ ዋና የህገ ወጥ መሣሪያ ማመላለሻ ማዕከል እየሆነች መሄዷን ዘግቧል፡፡

ነጋዴዎችና መሳሪያዎች የሚያገኙት ጦርነት ካለባቸው ሀገሮች ነው፡፡ በጅቡቲ የሚመጣው ከየመን ጦረኞች የሚገዛ ነው፡፡ ከሱማሊያ፣ ከሱዳን፣ ከደቡብ ሱዳን ከነሱ አዋሳኝ ሀገሮች፣ ሴንትራል አፍሪካ ሪፐብሊክ፣ ከዲሞክራቲክ ኮንጐና ከሊቢያ መሣሪያዎች በገፍ ይዘዋወራሉ፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት በመሣሪያ አጠቃቀምና አያያዝ ልውውጥ ንግድ ለየት ያለ ሕግ አውጥቶ የጠበቀ ቁጥጥር ካላደረገ ሕግ ማስከበር ከመንግሥትና ከክልሎች ቁጥጥር ውጭ ሆኖ ሀገሪቱ ወደ ውድቀት እየተንሸራተተች ትሄዳለች፡፡

ከጥቂት ዓመታት በፊት በኡጋንዳ ካምፖላ ዋና መስሪያቤቱ ለሆነው ዩናፍሪ ( UNAFRI) በአፍሪካ ውስጥ የቀላል መሣሪያዎች ሕገ ወጥ እንቅስቃሴ ጥናት እንዳደርግ ተመድቤ ለአንድ ዓመት ጥናቱን አከናውኛለሁ፡፡ የጥናቱንም ውጤት በአፍሪካ አህጉር የሚገኙ ሀገሮች ፖሊሲ ኮሚሽነሮች  ስብሰባ ላይ አቅርቤአለሁ፡፡ አቅራቢው እኔ ስለሁንኩ ይመስለኛል፤ የኢትዮጵያ መንግሥት ተጠሪ አልላከም፡፡ ይህን ጥናት ባደረኩበት ጊዜ በመሳሪያ አምራቾች፣ በመሳሪያ ደላሎች፣ መሣሪያውን በሚያጓግዙት የትራንስፖርት ባለቤቶች እና በተጠቃሚዎቹ መካከል (End users) ያለው ግንኙነት የተወሳሰበ መሆኑን ተረድቻለሁ፡፡ ምንም እንኳን ይህ ጥናት ትንሽ የቆየ ቢሆንም ሁኔታው ከመባባስ በስተቀር ሆዳሞች መሣሪያ ለመሸጥ ሲሉ በአንድ ሀገር ውስጥ እንዴት አድርገው ሽብርና ስጋት እንደሚፈጥሩ ለዚህም ሁኔታ የመንግሥት አካላት ሳይቀሩ ተባባሪ እንደሚሆኑ የሚያመለክት ነበር፡፡

ከአራት ዓመት በፊት በተደረገ ጥናት The Gulf of Guinea ብዙ የምዕራብ አፍሪካ ጠረፎችን የሚያካትተው ባህረ ሰላጤ The most dangerous maritime zone in the world ተብሎ ነበር፡፡ ከዚያ በፊት የኛው አጠገባችን ያለው Gulf of Eden ነበር አስጊው አካባቢ፡፡ ቀደም ብሎ ከኮሎምቢያ ድራግ ካርቴል በአውሮፓ አድርገው የሚያመላልሱት  ሕገ ወጥ እንቅስቃሴም መንገድ ለውጦ አሁን Gulf of Guinea የተመረጠ ሆኗል፡፡ በGulf of Guinea አድርጐ እስከ ሊቢያና በሜዲቴራንያን ጠረፍ አገሮች ለማጓጓዝ በጣም ቀላል ሆኖ አግኝተውታል:: ከባህረ ሰላጤው ጀምሮ እስከ ሜዲታራንያን ባህር ድረስ በቦኮሃራምና በሌሎች ህገወጥ እንቅስቃሴዎች የተወረረ ምድረበዳ ኮሪደር ፈጥረው አለብዙ ችግር ይንቀሳቀሳሉ፡፡ ይህ እንቅስቃሴ መሣሪያዎችን ይጨምራል፡፡ ከጥቂት ዓመታት በፊት ጊኒቢሳውም Narco Capital of the Wrold ተብላ ተሰይማለች፡፡ የጊኒቢሳው አድሚራል ዋናው ለዚህ ድራግና መሳሪያ አመላላሽ ካርቴል ኃላፊ ነው ተብሎ ተጠርጥሮ በFBI ተይዞ ፍርድቤት ቀርቧል፡፡ ብዙም የመንግስት ባለስልጣኖች ከዚህ ጋር በተያያዘ ፍርድ ቀርበዋል:: ይህን ያነሳሁበት የመንግስት ባለስልጣኖች በዚህ የተወሳሰበ ሕገ ወጥ እንቅስቃሴ ውስጥ ዋና ተዋንያን ሊሆኑ እንደሚችሉ ለማሳየት ነው::

ሕገ ወጥ መሣሪያ እንቅስቃሴ ብዙ ዘርፎችን ስለሚነካ ጦርነት ለመቀስቀስም ለማፋፋምም የንግድ ብቻ ሳይሆን እንደ ፖለቲካ አጀንዳ የተያዘ ስለሆነ ሕግና ቁጥጥር ያስፈልገዋል፡፡

የፅጥታ ሀይሎች ጥራት

የመከላከያና የፖሊስ ሀይሎች በአመራር ደረጃም ሆነ በሠራዊቱ ውስጥ ሙሉ ለሙሉ ብቃት አላቸው ብሎ ለመናገር ያስቸግራል፡፡ አንዳንድ የኢትዮጵያ የጦር መሪዎችን ሩዋንዳም፣ ሱዳን፣ ላይቤሪያም አግኝቻዋለሁ፤ አልኮራሁባቸውም፡፡ እኔ በተለያዩ ወታደራዊ ማሰልጠኛዎች ውስጥ  የሰለጠንኩ ወታደር ስለሆንኩኝ መመዘን እችላለሁኝ:: ብዙ ታላላቅ አዋቂ እዛዦችም ጋር ስርቺአለሁኝ:: ዛሬ በሜቴክ ሙስና የተያዙ ለክስ የቀረቡ ከፍተኛ ማዕረግ ያላቸው የሰራዊቱ አባሎች በሥነ ምግባራቸውና በዕውቀታቸው የሚያሳፍሩ ሆነው ተገኝተዋል፡፡ ህዝባችን በኃፍረት ነው የተሸማቀቀው:: በየደረጃው ያሉ ይህንን የመሳሰሉ አለቆች ለፀጥታው መደፍረስ መፍትሔ ሳይሆኑ ችግሮች ይሆናሉ፡፡

በየክልሉ ያሉት ኃይሎች ፖሊስና ልዩ ኃይል የሚባሉት የክልሉን ጥቅም ወይም መመሪያ የሚጠብቁ እንጂ በፌዴራል መንግሥት የሚመሩ ባለመሆናቸው ታላቅ ቀውስ ፈጥሯል፡፡ የፖሊስና የልዩ ኃይሎች ገደብ የሌለው ሥልጣን አደገኛ መሆኑ ለሁሉም ግልጽ ነው፡፡ በመከላከያ ኃይልና በልዩ ኃይል የሥራ ኃላፊነት ልዩነት የለም፡፡ በተግባር ሲታይ በክልል ያሉ ፖሊስና ልዩ ኃይሎች ኃላፊነታቸውን የሚመለከቱት ሰፋ ባለ ኢትዮጵያዊነት መነጽር ሳይሆን በክልላቸውና በብሔራቸው መነጽር ነው:: የክልል ሕገ መንግሥቱ የፌዴራል ሕገ መንግሥቱን ይጣረዛል:: የየክልሉ ሠራዊቶች ይዋጋሉ፣ ይገድላሉ:: ልክ የሁለት ሀገሮች ጦርነት የሚመስል በየድንበሩ ጦር አሰልፈው ያጠቃሉ፤ ይከላከላሉ: አቅም ሲያጥራቸው የፌዴራል መንግሥቱን ኃይሎች ይጠራሉ፣ ባላቸው ኃይል ከሥልጣናቸው በላይ የሆነ ምንም ነገር የለም፡፡

ወደ ምርጫ እየተቃረብን ባለንበት ወቅት እንዴት አድርጐ ነው አንድ ክልል አቋርጦ ሌላ ክልል ሲገባ፣ ሌላ አገር የገቡ በሚመስል በተወጠረ የፖለቲካ ሁኔታ ህዝብ ተንቀሳቅሶ የፖለቲካ ፖርቲዎች እንደልብ ተናግረው፣ አስተምረው ህዝቡን አደራጅተው ነው ለምርጫ የሚያዘጋጁት? ይህ ስንት ዓመት ሙሉ በካድሬዎች ሲታጠብ የነበረ ሰራዊት እንዴት አድርጐ ነው ኢህአዲግ ውጪ ለሌላ ተመራጭ ሁኔታውን ማመቻቸት የሚቻለው? ከስር ጀምሮ   ኢትዮጵያ በሚለው ታላቁ ስእል ክልል ውስጥ ለማሰብና ለመስራት እንዲቻል በሠራዊቱ ውስጥ ብዙ ስራዎች እየተሰሩ ቢሆንም ብዙ ይቀራል፡፡

ትጥቅ መፍታትና ከህብረተቡ ጋር መቀላቀል

(Demobilization Re-Intigration)

ምንም እንኳን ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የትጥቅ ትግል በሌሎች የአፍሪካ ሀገሮች ከምናያቸው የተለየ ቢሆንም፣ የትጥቅ ትግልን በመጠቀም መንግሥትና ሥርዓትን እንለውጣለን ብለው የተነሱ ኃይሎች ነበሩ፡፡ አሁን ዶ/ር አብይ እንደ ጀመሩት፣ እነዚህ ኃይሎች፣ የቀረበላቸውን ጥሪ ተቀብለው ወደ ሀገር እየተመለሱ ናቸው፡፡ እኔ የአንጎላ ጦርነት ሲቆም፣ የትጥቅ መፍታትና ከህብረተቡ ጋር መቀላቀል (Demobilization Re-Intigration Technical Officer) ሆኜ በተባበሩት መንግሥታት ፕሮግራም ውስጥ ሰርቻለሁ፡፡ ትጥቅ ማስፈታትና ከህብረተሰቡ ጋር መቀላቀሉ ለዘለቄታዊ መፍትሔ ወሳኝ ነው፡፡ ይህም አካሄድ ሥርዓት አለው፡፡ ሥርዓቱ ካልተጠበቀ ሰላምን ሊያደፈርስ የሚችል ሁኔታ ይፈጠራል ተብሎ ይታመናል፡፡ የአንጎላን ፕሮግራም ስንሰራ ከሞዛምቢክ ልምድ ለመውሰድ የሞዛምቢክንም ተሞክሮ ፈትሸናል፡፡ የናሚቢያ ነፃነት በሁዋላ የነበረውን የትጥቅ መፍታትና ወደ ሰላማዌ ሕይወት መቀላቀል ስኬታማ የሆነውን እንደ ሞዴል አድርገን ተጠቅመንበታል፡፡ የሩዋንዳ Ministry of Rehabilitation Social Intigraion ሲቋቋም አማካሪ ሆኜ ሰርቻለሁ፡፡ የታጠቁትንም ያልታጠቁትንም በGenocide ጊዜ የተፈናቀሉትን፣ የተሰደዱትን መልሶ ህብረተሰቡ ውስጥ ለመቀላቀል እንዲቻል የተቋቋመ ሚኒስትሪ ነበር፡፡ እነዚህ የተለዩ ሁኔታዎች ቢሆኑም ከልምዶቻቸው ብዙ ተመክሮ መውሰድ ይቻላል፡፡

ትጥቅ መፍታት በመንግሥስትና በታጣቂ ኃይሎች መካከል ከሚኖር ስምምነት ይጀምራል፡፡ በስምምነቱ መሰረት የታጠቁ ኃይሎች ስም ዝርዝር፣ የታጠቁት መሳሪያ ብዛትና ዓይነት ይመዘገባል፡፡ ትጥቅ የፈቱት ኃይሎች አንድ ማረፊያ ሰፈር ይገባሉ፡፡ በዚህም ማረፊያ ሰፈር ህብረተሰብ ውስጥ ተቀላቅለው በሰላም እንዲኖሩ የሚያስደርጋቸውን ትምህርት ይቀበላሉ፡፡ በሀገሩ የመከላከያ ኃይል ውስጥ ለመቀላቀል ብቃትና ፍቃደኝነት ያላቸው ወደ ሰራዊቱ ይቀላቀላሉ ሌሎቹም እንደ ጥያቄአቸው ሥራ እየተፈለገ ይሰጣቸዋል፡፡ በሙያ ለመሰልጠን የሚፈልጉ ትምህርት ቤት እንዲገቡ ይደረጋል፡፡ የመቋቋም ችግር ያለባቸው በስምምነቱ መሰረት እርዳታ ይደረግላቸዋል፡፡ ይህ ሳይደረግ የቀድሞ ተዋጊዎችን ህብረተሰቡ ውስጥ እንዲቀላቀሉ ማድረግ ለሰላም ጠንቅ ሊሆን ይችላል:: ይህንንም በተመለከተ ብዙ ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑን እገነዘባለሁኝ፡፡

ራስን የመግለጽ ነፃነት (Freedom of Expression)

ሀሳብን በነፃነት የመግለጽ መብትና ግዴታ በተለይም አዲስ የዲሞክራቲክ ስርዓት በሚገነቡ ሀገሮች በሚገባ ባለመታወቁ፣ በአንዳንድ ሁኔታ ውስጥ ሰላምን ሊያናጋ ይችላል፡፡ በአንድአንድ ሀገር እንደ ሁኔታው፣ በግዴታና በመብት መካከል መስመር መዘርጋት ይኖርበታል፡፡ ችግሩ መንግሥት ትንሽ ፍንጭ ሲያገኝ፣ ስንዝር ሲሰጡት አንድ ክንድ ይወስዳል፡፡ የፀረ ሽብርተኛ አዋጁ በምሳሌነት ሊጠቀስ ይችላል፡፡

በ2001 እ.አ.አ. ከደረሰው የአሜሪካ የሽብር ጥቃት (Nine Eleven) በኋላ ብዙ ሀገሮች የፀረ ሽብርተኛ አዋጅ እንዲኖራቸው አሜሪካ አበረታታለች፡፡ በአፍሪካና በሌሎች አህጉሮች ያሉ መንግሥታት ይህንን ሀሳብ ያለምንም ማንገራገር ቀለብ አድርገው ለራሳቸው መጠቀሚያ አደረጉት፡፡ ሽብርተኝነት የጠራ ዓለም አቀፍ የሆነ ትርጉም ስለሌለው እያንዳንዱ መንግሥት እንዳመቸው እየተረጐመ ነፃነትን፣ ክርክርን፣ ሰላማዊ ሰልፎችን፣ በአጠቃላይ ስላማዊ ትግልንና የሀሳብ መግለፅን ነፃነት ማጥቂያ ህጋዊ ዘዴ አድርገው ተጠቅመውበታል::

ዛሬ ኢትዮጵያ ውስጥ እውነትና ውሸትን መለየት በጣም ያስቸግራል፡፡ የመንግሥትን ሚዲያ እያዳመጥን ምንጫችን ከአንድ ወገን ብቻ ሲሆን እውቀታችን ውስን ይሆናል፤ ወይንም የመንግሥስት መሣሪያ እንሆናለን፡፡ የግል ሚዲያዎች የሚናገሩትን፣ የሚጽፉትን በሁሉም ሶሻል ሚዲያና ሌሎችም ወይንም ገንዘብ ለማግኘት፣ ወይንም ሰንሴሽን ለመፍጠር የፖለቲካ ተልዕኮ አጀንዳ ያላቸው፣ ወይንም የማያውቁ ሰዎች ሚዲያ ለመቅረብ እድል በማግኘታቸው የሚናገሩት፣ የሚጽፉት ሁሉ ሀገሪቱን ምን ያህል አደጋ ላይ እየጣለ እንደሆነ ማጥናት አስፈላጊ ነው፡፡

በተለይ ወጣቱ ከብዙ ዓይነት አስተማማኝነታቸው ካልተረጋገጠ ምንጮች በሚያገኘው ዜና ወይም ወሬ እየተዋከበ ለመወገን፣ ለማገዝ ይቸኩላል፡፡ ይህ ወጣት ትውልድ ብዙ የማያነብ ግን ብዙ የሚናገር፣  ለማሞጐስም ለማውገዝም የሚቸኩል፣ ሶሻል ሚዲያ ላይ ጥቂት አረፍተ ነገሮችን አንብቦ በታላላቅ የኢትዮጵያ ጉዳዮች ላይ አቋም መውሰድ የሚደፍር፣ በስድብ፣ በዘለፋ፣ የሃቀኞችን ልሳን የሚዘጋ፣ ከአንድ ከሚፈልገው አቅጣጫ ብቻ መረጃዎችን የሚቀበል፣ ሳያውቅ ሳያመዛዝን የጠላት መሣሪያ ሊሆን የሚችል በመሆኑ ለሀገራችን ጸጥታ ትልቅ ስጋት ይሆናል፡፡

አሁን ኢትዮጵያ ባለችበት በጣም ስስ፣ በቀላሉ የሚሰበር (Fragile) አሳሳቢ በሆነ ሁኔታ ውስጥ አንድ የሀሰት ወሬ ብዙ ህዝብ ሊያስጨርስ የሚችልበት ሁኔታዎች ብዙ ናቸው:: በሚዲያ አማካኝነትም ሆነ በአደባባይ ወጥቶ የሚነገረው ገደብ እንዲኖረው አንድ ሕግ መፈጠር አለበት፡፡ አሁን ባለበት ዲጂታል ጀነሬሽን መቆጣጠር በጣም አስቸጋሪ ቢሆንም በማስተማር፣  ግዴታንና ሀላፊነትን ከማሰወቅ ጋር የተያያዘ ፖሊሲ ሊቀየስ ይገባል::

ይህ በኢንተናሽናል ሕግም የተደገፈ ነው፤ የአፍሪካ ቻርተር Human and Peoples Right Freedom of Speech Shall be exercised in respect of the right of others collective security morality and common interest ይላል፡፡ ከዚያም ቀጥሎ ይህ ገደብ ዓላማው ምን መሆን እንዳለበት በዝርዝር አስቀምጦታል፡፡ በእንደዚህ ዓይነት የሽግግር ወቅት በግልጽ የኢትዮጵያን አንድነት የማይደግፉ፣ ድብቅ አጀንዳ አላቸው ተብለው የሚጠረጠሩ አናርኪስቶች ይሁኑ፣ በተለያዩ ምክንያቶች የተቆጡና የግልም ችግር ያለባቸው፣ ሀገር የመከፋፈል፣ ህዝብ የሚያጣላ ህዝብን ከማያቀራረብ፣  ከይቅርታ፣ ከፍቅር የሚያርቁ በሀሰት ላይ የተመሰረቱ ማስረጃ የሌላቸው ታሪክና ዜና በሚያስራጩ ድርጅቶችና ግለሰቦች ላይ ትኩረት መደረግ አለበት፡፡

የሚዲያና የፓለቲካ ድርጅቶች የገንዘብ ምንጫቸውን ለመንግሥት ማሳወቅ አለባቸው:: ይህ በሁሉም ዴሞክራቲክ ሀገሮች በሕግ የተደነገገ ነው:: ይህም የኢትዮጵያ የውስጥ ፓለቲካና የፀጥታ ሁኔታ በውጭ አጀንዳ እንዳይመራ ያረጋግጣል:: በንግግር በጽሁፍና በመሳሰሉት በfreedom of expression ነፃነት ሽፋን አድርገው የኢትዮጵያን አንድነት የሚጐዱ ግለሰቦች ካሉ የሚታገዱበት ሕግ ሊኖር ይገባል::

የአካባቢ ሁኔታና ሽግግር

የአካባቢያችንን የፀጥታ ሁኔታ ከውስጥ የፀጥታ ሁኔታ ለይቶ ማየት አስቸጋሪ ነው፡፡ የኢትዮጵያ የጸጥታ ሁኔታ፣ የኢኮኖሚ ዕድገት፣ የዲሞክራሲ መመስረት፣ የሰብአዊ መብት መጠበቅ፣ ከአካባቢው ሁኔታ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ የኢትዮጵያን ሁኔታ በቅርብም በሩቅም በአይነቁራኛ የሚከታተሉ ብዙዎች ናቸው፡፡ የአፍሪካ ቀንድ በአሁኑ ጊዜ The most militarized zone in the world ይባላል፡፡ ታላላቅ ሁኔታዎች በዓለም በተለይ በመካከለኛው ምስራቅና በአረቡ ዓለም ሲከሰቱ አዲስ የሃይል አሰላለፍ በአፍሪካ ቀንድ ውስጥ እየታየ ነው፡፡ የመካከለኛው ምስራቅ የፖለቲካ ሁኔታ ግልጽ በሆነ መንገድ ለሁለት መከፈሉና የአፍሪካ ቀንድ ከዚህ ሁኔታ በቀጥታና በተዘዋዋሪ መንገድ ከመቸውም ጊዜ ይልቅ ትኩረት የሚሰጡት ቦታ መሆኑ ኢትዮጵያን በቀጥታ ይመለከታታል::

ኤርትራ

ስለጎረቤት ሀገሮች ስንነጋገር በመጀመሪያ ከላይ ከጠቀስኩት ሁኔታ ጋራ ያልተያያዘ ስለ ኤርትራና ኢትዮጵያ ግንኙነት ትንሽ መናገር እፈልጋለሁ፡፡ እኔ የኤርትራ ፌዴሬሽን ከመፍረሱ ስምንት ወር በፊት በምክትል የመቶ አለቃ ማዕረግ ኤርትራ ነበርኩ፡፡ ፌዴሬሽኑ የፈረሰ ዕለት ጦር ይዤ አስመራ አካባቢ ተሰማርቼ ነበር፡፡ ከእዛን ጊዜ ጀምሮ የኤርትራን ሁኔታ በቅርብ ተከታትያለሁ፡፡ ኤርትራ በውጊያ ግንባር ተሰልፌአለሁ፣ ክፍለሀገሩን በበላይ አስተዳዳሪነት መርቻለሁ፡፡ ከአገር ከወጣሁም በኋላ ከኤርትራ መንግሥት ከፍተኛ አባሎች ጋር በግል ጓደኝነትም፣ በፖለቲካም በቅርብ ሰርተናል፡፡ የኤርትራን ህዝብ፣ የኤርትራን ፖለቲካ ከብዙ ሰዎች በተሻለ ሁኔታ አውቃለሁ፡፡

የኢትዮጵያና የኤርትራ እጣ ፋንታ ወደፊት አብሮ እንጂ ተለያይቶ እንደማይሆንም መገንዘብ ይቻላል፡፡ እኔ የአንድነት ወገን ነበርኩኝ:: ያ አልተቻለም፤ ነገር ግን ተቀራርቦ መስራት ለጋራ ጥቅም፣ ለጋራ ህልውና አማራጭ የለውም፡፡ በመንፈሴ አሁንም ኤርትራንና ኢትዮጵያን መለየት አልችልም፡፡ ከዚህ በፊትም፣ ከዚህ በኋላም ኤርትራ ኢትዮጵያ ነች፤ ኢትዮጵያ ኤርትራ ነች ብዬ ነው የማምነው፡፡ ግን በግልፅ መታወቅ ያለበት ኤርትራ እሯሳን የቻለች ዳር ድንበሯ በዓለም አቀፍ ሕግ የታወቀች ሀገር sovereign state  ነች፡፡ የሁለቱ መንግሥታት መለያየት የህዝቡን አብሮነትና አንድነት አይለውጠውም፡፡ በኤርትራ ላይ የሚመጣ ጉዳት ኢትዮጵያን ይጎዳል፤ በኢትዮጵያ ላይ የሚመጣ ጉዳት ኤርትራንም ይጎዳል፤ ይህ የመልካም ጉርብትና ፖሊሲ መሰረታችን መሆን አለበት:: ዶ/ር አብይ በወሰዱት እርምጃ በግል በጣም ተደስቻለሁ፡፡  “The moment of Truth: Eritrea and Ethiopia” በሚል ርእስ ድጋፌን ለመግለፅ በወቅቱ በሰፊው የተነበበ ጽሁፍም አቅርቤአለሁ፡፡

በሁለቱ ህዝብ መካከል ብዙ ጉዳት ደርሷል፡፡ ይህንን ያህል ዘመን በኤርትራ ምድር ላይ በአንድነትና በነፃነት ኃይሎች መካከል ውጊያ ሲካሄድ  ይህ ጦርነት ህዝባዊ ጦርነት(Civil War) ሆኖ አያውቅም፡፡ ጦርነቱ በሁለቱ ኃይሎች መካከል ነበረ፡፡ ህብረተሰቡ ተጋብቶ ተዋልዶ ባሕሉን አክብሮ እንደ አንድ ቤተሰብ ተቀራርቦ ጦርነቱ እንዲቆም ሰላማዊ ኑሮ እንዲኖር እየተመኘ እየፅለየ እዚህ ደርሰናል፡፡ በሁለቱም ወገን ብዙ ተዋጊዎች አልቀዋል፡፡ የኤርትራ ተዋጊዎች የሚገባቸውን ክብር አዲሱ መንግሥት ሰቷቸዋል፡፡ ነገር ግን አሁን የተጀመረው አብሮ የመኖርና የማደግ ፍላጐትና ምኞት እውነት ሊሆን የሚችለው ህዝባዊ ዕርቅ ሲፈፀም ብቻ ነው፡፡ የሁለቱ መንግሥታት መሪዎች መጨባበጥና መተቃቀፍ መሰረታዊ የሆነ ብሔራዊ ዕርቅ አያመጣም፡፡ በኢትዮጵያ በኩል በሰላሳ ዓመት ውስጥ ከመቶ ሺህ በላይ ወታደሮች በኤርትራ ምድር ላይ አልቀዋል፡፡ ቤተሰቦቻቸው ከመቀሌ ጀምሮ እስከ አዲስ አበባና ከዚያም ባሻገር በእያንዳንዱ የኢትዮጵያ ክፍለ ሀገራት ከተሞችና መንደሮች ተበትነው በጉስቁልና የሚኖሩ ብዙዎች ናቸው፡፡ ቆስለው፣ ተሰናክለው፣ የተጣሉም የተረሱም ብዙዎች ናቸው፡፡ ኤርትራ ውስጥ የሞተ፣ የቆሰለ፣ ዘመድ የሌለው ለማግኘት አስቸጋሪ ነው፡፡ ጦርነቱ የታሪካችን ጠባሳ ነው፤ ታሪክ ይዘግበዋል፡፡ የዛሬውና የሚመጣው ትውልድ ግን የተፈጸመውን ታሪክ ትቶ እንዴት እንደዚህ ያሉ ጥፋቶች እንደደረሱ የሁለቱን ህዝቦች የታሪክ ቅርበት ያገናዘበ ውይይት በማካሄድ  ከእንግዲህ ወዲያ መቼም እንደዜህ ያለ ሁኔታ አይፈጠርም (Never again) ብሎ ተነጋግሮ፣ ተላቅሶ፣ ተቃቅፎ፣ እውነቱን አውቆ፣ እርቅ የሚመሰርትበት ህዝባዊ ጉባኤ ማመቻቸት ተገቢ ነው::

ይህም ጉባኤ የትዮጵያ ሰማዕታትም የሚከበሩበት፣ የሚታወሱበት ኃውልት ከኤርትራ መንግሥት ጋር ተነጋግሮ ፈቃድ እንዲሰጥና በመንግሥት ወጪ ሳይሆን ከህብረተሰቡ በተዋጣ ገንዘብ እንዲቆም ይነጋገርበታል፡፡  መንግስትም ድጋፍ ሊሰጥ ይገባል:: በኤርትራ ምድር ላይ የፈሰሰው ደም፣ ያለፈው ሕይወት በሁለቱም ሀገሮች ታሪክ ውስጥ አቻ የለውም፡፡ ይህንንም የመሰለ ጉባኤ በሁለቱም ህዝቦች መካከል የሃይማኖት አባቶች፣ ወገኖቻቸውና ዘመዶቻቸው፣ የጠፋባቸው፣ የተጎዱባቸው ሰዎች፣ በሁለቱም ወገን በውጊያው ወቅት የነበሩ ታጋዮች፣ መስካሪዎች፣ ታሪክ አዋቂዎች ተሰባስበው ይህንን ምዕራፍ ዘግተው ለታሪክ አስረክበው በሰላም እንዲኖሩ ማድረግ ተገቢ ይመስለኛል፡፡ ይህ ዘላቂ ሰላምን ያስገኛል ያረጋግጣል፡፡

ሶማሊያ 

ሶማሊያ በ1978 ዓ.ም.  ኢትዮጵያን በወረረችበት ጊዜ እኔ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቋሚ ተጠሪ ነበርኩ፡፡ ይህንን በወቅቱ እጅግ አሳሳቢ የሆነ ሁኔታ ለInternational Community ለማስረዳትና ድጋፍ ለማግኘት ወደ United Nation delegation መርቼ ሄጃለሁ፡፡ በገለልተኛ ሀገራት መንግሥታት ስብሰባ አቤቱታችንን አሰምተናል፤ ድጋፍ ጠይቀናል፡፡ በኩባ፣ በአውሮፓ፣ በላቲን አሜሪካ፣ በየመን ተመላልሰን ድጋፍ ለማግኘት በዲፕሎማቲክ ዘርፍ ብዙ ትግል አድርገናል::

በሜዳ ላይ የሶማሊያ ጦር ጅጅጋን ያዘ፤ ሐረርንም፣ ድሬደዋንም ከበበ፤ አርሲ፣ ባሌ ሐረርጌን ማስታጠቅ ጀመረ:: በዚያን ወቅት በኮለኔል ብርሃኑ ባዬ የሚመራ ልጅ ጌታቸው ክብረት፣ ልጅ ሚካኤል እምሩ እና እኔ ያለንበት የልዑካን ቡድን ሶቪየት ዩኒየንን ለመማፀንና ለሶማሊያ የሚያደርገውን ድጋፍ እንዲያቆሙ አስራ ሰባት ቀናት የቆየ ውይይት አካሂደናል፡፡ ሶማሊያ  ወረራ የፈጸመችው ነፃነት ካገኘችበት ጊዜ ጀምሮ በሕገ መንግሥቷ አንቀጽ 6 እና በባንዲራዋ ላይ የተመለከተውን አምስቱን የሱማሌ ህዝብ የሚኖርባትን ሀገሮች አጠቃላ ታላቋ ሶማሌያን ለመፍጠር ነበረ፡፡ ለዚህም ወረራ ሽፋን እንዲሆን የምዕራብ ሶማሊያ ነፃነት ንቅናቄ ግንባር (Western Somalia Libration front) ብላ አቋቋመች፡፡ መሪዎቹም ከዚያው ከሱማሊያ ጦር ውስጥ ኃላፊዎች የነበሩ ታላላቅ የጦር መሪዎች ነበሩ፡፡ የONLF መሪ በዚያድ ባሬ መንግስት ወቅት  ከፍተኛ መኮንን የነበረው Rear Admiral Mohamed Omar Osman ነው፡፡

ሶማሊያ ከነፃነት ጊዜ ጀምሮ ወቅት እየመረጠች ኢትያጵያን ወራለች፡፡ በጄኔራል መንግሥቱ ነዋይ መፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ጊዜ ኢትዮጵያ ተዳክማለች ብላ በዳኖት በኩል ጦርነት ከፈተች፤ ተሸንፋ ተመለሰች፡፡ በደርግ ጊዜ አገሪቱ በአብዮተኞችና በፀረ አብዮተኞች መካከል በነበረው የሥልጣን ትግል፣ ከዚያም በሀገሪቷ ሰሜናዊ አካባቢ የነበረው ጦርነት ተፋፍሞ ስለነበረ ኢትዮጵያ ተዳክማለች በሚል ግምት በሶቭየት ዩኒየን የመሣሪያ ድጋፍ፣ ህዝብ ያለቀበት ወረራ ፈጸመች፡፡ ለዚሁም ሽፋን ያደረጉት የዚያድ ባሬ መንግሥት ያቋቋመው በራሱ ጄኔራሎች የሚመራው ይኽው የምዕራብ ሶማሊያ ነፃነት ንቅናቄ ግንባር (Western Somalia Libration front) በስሩ የኦጋዴን ብሔራዊ ነፃነት አውጪ ግንባር (Ogaden National Libration Front) ኦብነግ እና ከዚያም ደግሞ የሐረርጌን፣ የባሌና የሲዳሞን ኦሮሞዎች ሶማሌ አቦ የሚሏቸውን እያደራጁ፣ እያስታጠቁ ጦርነት ከፈቱ:: በተከታታይም ኦጋዴን የኢትዮጵያ ቅኝ ግዛት ናት እያሉ በየኢንተርናሽናል  መድረክ ብዙ ፕሮፖጋንዳ መንዛታቸው ይታወቃል፡፡ ዛሬ የምናየው ኦብነግ (ONLF) ይህ ነው፡፡ ክህደት በደም መሬት በሚለው መጽሐፌ ገጽ 49 ያለውን እጠቅሳለሁ፡፡

ኢብራሂም አብደላ የተባሉ የኦጋዴን ብሔራዊ ነፃ አውጪ ግንባር ተጠሪ በአንድ ወቅት ሲናገሩ የሚከተለውን ብለዋል፡፡

“ድርጅታችን የሚከተሉት ዓላማዎች አሉት፡- የእስልምናን ልዕልና ማረጋገጥ፣ እስላማዊ ትምህርት በሕዝቡ ዘንድ ሰርጎ እንዲገባ ብርቱ ትግል ማድረግ፣ ኦጋዴንን ከኢትዮጵያ ቅኝ አገዛዝ ነፃ በማውጣት ነፃ መንግሥት መመሥረትና የሕዝቡን ፍላጎትና ምኞት እውን ማድረግ፣ በእስልምናና በዲሞክራሲያዊ አመራር ሥር ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ነፃነቱ የተረጋገጠ እስላማዊ ኀብረተሰብ መገንባት፣ ከሶማሊያ ሕዝብ ጋር ያለውን የወንድማማችነትና የትግል አንድነት እንዲጠነክር፣ በሌላ በኩል ደግሞ ከዓረቡ ዓለምና ከሙስሊሙ ጋር ያለንን ግንኙነት በጋራ ጥቅሞች ላይ ተመርኩዞ የሚያድግበትን መንገድ መሻት…”

የኢትዮጵያ የደህንነት ሥጋቶችና የኡጋዴን ኢትዮጵያዊነት በሚሉ ርዕሶች ሰፊ ጥናት በመጽሐፌ ውስጥ እና ከዚያም በድረ ገጾች ላይ አስመዝግቤአለሁ፡፡ በቅርቡም የኢህአዲግ መንግሥት ከ ኦብነግ (ONLF) ጋር ኬንያና ዱባይ ላይ ድርድር በጀመረበት ጊዜ ይህ የሚፈጥረውን አጠቃላይ ሁኔታ እኔ፣ ዶ/ር ዲማ ነገዎና ፕ/ር ጌታቸው በጋሻው ያለንን ስጋት የሚጠቁሙ ጽሁፍ በትነናል፡፡

የሱማሌ ሕገ መንግሥት ብዙ ችግር ነበረበት፣ Transitional Federal Government አባል የነበረው የIsIamic Court የስልጣን ተቀናቃኝ በነበረበት ጊዜ ONLF ከIslamic Court ጋር በቅርብ ይሠራ እንደነበረ ታሪክ ውስጥ የተመዘገበ ነው፡፡ የlslamic Court በታላቋ ሶማሊያ ዓላማ እንደሚያምንም የታወቀ ነው:: በንግግሮቹም፣ በጽሁፎቹም ላይ ይህንኑ ጠቁሟል፡፡ የIslamic Court ከሥልጣን ሲባረር ወደ አልሻባብነት ተለወጠ፡፡ አልሻባብን የመሰረቱት Islamic Court ኃላፊዎችና አባሎች ናቸው፡፡ አሁን ያለው የጠቅላይ ሚኒስትር ፎርማጆ መንግሥት ከኢትዮጵያ ጋር መልካም ጉርብትና ስለሚፈልግ ኦብነግን አውግዟል፡፡ ከማውገዝም አልፎ ሽብርተኛ ነው ሲል ፈርጆታል፡፡

ኦብነግ (ONLF) ማን ምን እንደሆኑ ሥር መሰረታቸውን እንቅስቃሴአቸውን እናውቃለን፡፡  የኢትዮጵያ አንዱና ትልቁ የፀጥታ ሥጋት ONLF ነው፡፡ የሶማሊያ መንግሥት ቢለወጥ አቋማቸው እንደሚዋዥቅ ጥርጣሬ ሊኖር አይገባም፡፡ ዛሬ በዶ/ር አብይ አመራር የአፍሪካ ቀንድ መሪዎች ሰላማዊ የሆነ አካባቢን ስለፈጠሩ ONLF ዋና መስሪያ ቤቱ ያደረገባት ኤርትራም ከኢትዮጵያ ጋር መልካም ጉርብትና ስለመረጠች፣ ሶማሊያ ውስጥም እንቅስቃሴ ማድረግ ስላልቻሉ ከዚህ አሰላለፍ ቢወጡ በInternational Community ሽብርተኛ ተብለው ስለሚመዘገቡ፣ ስለሚወገዙ እና ጥቁር ሊስት ውስጥ እንሚገቡ ስለሚያውቁት እንጂ አጀንዳቸውን ለውጠዋል ማለት አይደለም፡፡

ሶማሊያን እንድትንኮታኮት ያደረጋት ይህ ፖሊስዋ ነው፡፡ ብዙ ሕይወት ከጠፋበት ከ1978 ዓ.ም. ወረራ በኋላ የኢትዮጵያ መንግሥት ሶማሊያን ለማዳከምና ሽብር ውስጥ ለመክተት አማራጭ የሌለው ፖሊሲ ሆኖ አገኘው፡፡ በሶማሌያ ውስጥ ያሉትን ተቃዋሚ ኃይሎች ማስታጠቅና ማደራጀት ጀመረ:: ዛሬ የምናያት ሱማሊያ የዚያው ውጤት ነች፤ አዲሱ መንግሥትም፤ መልካም ጉርብትናን መርጧል፡፡ ONLF እስከዛሬ የተናገረውን፣ የፃፈውን ሁሉ ቀልብሶ በኦጋዴን ኢትዮጵያዊነት የሚያምን በዚህ ውስጥ በህዝቦች መካከል የሚፈፀሙ ልዩነቶችን  በሰላማዊና በአንድነት መንፈስ እንደሚፈፅም ለኢትዮጵያ ህዝብ መግለጽ አለበት፡፡ በ1978 ዓ.ም. ጦርነት ምክንያት በአስቸኳይ ዘመቻ ጥሪ ተደርጐ ምስራቅ ግንባር ከተሰማራ ሁለት መቶ ሺ ሠራዊት ውስጥ አንድ ሶስተኛው እዚያው ኡጋዴን ውስጥ አልቋል፡፡ የነበርን ሰዎች አንረሳውም:: የአሁኑም ወጣቶች እና መሪዎች ሊረሱት አይገባም፡፡ ኦብነግ በጥንቃቄ መያዝ ያለበት ድርጅት ነው፡፡ ስለዚህ ዛሬ ONLF ያንን በፕሮግራሙ የተቀመጠውን አቋም ሰርዞ፣  በኢትዮጵያዊነት አምኖ ለመስራት መዘጋጀቱንና ፕሮግራሙንም መለወጡን በስምምነት አፅድቆ ለህዝብ በግልፅ ማሳወቅ አለበት፡፡

አካባቢው

በካባቢያችን ያለው የኃይል አሰላለፍ ያስደነግጣል፡፡ የአሜሪካን የውጭ ፖሊሲ በአፍሪካ ቀንድ ውስጥ በፀረ ሽብርተኝነት ዘመቻ ላይ ያተኮረ ነበር፡፡ ዛሬ ከዚህ ፖሊሲ እየራቀ America First የሚለውን የአሜሪካ ጥቅም የሚያስጠብቅ አዲስ ፖሊሲ እየቀየሰ ነው፡፡ አንድ የአሜሪካ የመከላከያ ሀላፊ እንደተናገሩት “Great power competition not terrorism is now primary focus of national interest” በአንድ ሀገር ውስጥ የሽብርተኛ እንቅስቃሴ ኖረም አልኖረም አንድ መንግሥት ራሱ ሽብርተኛ ሆኖ State Terorism ቢያካሂድም፣ ቀዳሚነት የሚሰጠው የአሜሪካ የኢኮኖሚ ጥቅምን ነው፡፡ ይህም በቅርቡ በግልጽ በሳውዲ ጋዜጠኛው ጀማል ካሹጊ ላይ የተፈጸመው ግድያና የአሜሪካ ዝምታ ብዙ መልዕክት ያስተላልፋል፡፡ ይህንን በተመለከተ በቅርቡ የፃፍኩት  “The Unholy Alliance Between the most Democratic and the most Autocratic Washington and Riad Should we be worried” የሚለውን ጽሁፍ ማንበብ ይቻላል፡፡

Global politics 09 Nov, 2018 G.C የወጣው ጽሁፍ እንዲህ ይላል “The new Cold War brewing in the Gulf has rapidly rewritten the geo political rule book in the Horn of Africa….Saudi Arabia and the UAE versus their bitter adversaries Qatar and Turkey are looking to forge closer connections with Ethiopia…..in the background you have Iran which is an enemy of Saudi and ally of the US. It is very complex background”

ዛሬ በጅቡቲ ላይ ያሉት የጦር ሰፈር ክምችቶች አፍሪካ ቀንድ የብዙ መንግሥታት ጥቅም መነኸሪያ መሆኑን ያመለክታል፡፡ አሜሪካ ቀድሞ የፈረንሳይን ቤዝ ካምፕ አድሳ፣ አስፋፍታ ታላቅ የጦር ሰፈር አድርጋዋለች፡፡ ፈረንሳዮችም እንዳሉ ናቸው፡፡

በተጨማሪም ለመጀመሪያ ጊዜ ጃፓን እና ቻይና  በጂቡቱ ጦር ሰፈሮች ሰርተዋል፡፡ ህንድም በቅርቡ ትልቅ የጦር ሰፈር ጅቡቲ ላይ እያቋቋመች ነው፡፡ ጣሊያንም እዚህ የሀያላን ስብስብ ውስጥ ገብታለች፡፡ ዩናይትድ አረብ ኢሜሬትና ሳውዲ አረቢያ ትልቅ የጦር ሰፈር አቋቁመዋል፡፡ ባህረ ሰላጤውንም ከመቆጣጠር ባሻገር የመን የሚያካሂዱትን ውጊያ የሚያግዝ የሎጅስቲክስ ቤዝ አድርገውታል፡፡ ኳታር በጅቡቲና በኤርትራ መካከል በነበሩ የድንበር ግጭት ሰበብ ሰላም ለማስጠበቅ ጦር ሰፈር ነበራት፡፡ በሳውዲና ዩናይትድ አረብ ኢሜሬት ግፊት ከጅቡቲ ተባራለች፡፡

ሳውድ አሪቢያም በአሰብ ላይ ጦር ሰፈር እንዳላት የታወቀ ነው፡፡ የመን ከኤርትራ የ30 ኪሎ ሜትር ርቀት ነው የሚለያያት:: የደቡብ የመን ጦር ከኢትዪጵያ ጦር ጋር ተስልፌ ከኤርትራ ህዝብ እርነት ግንባር ጋር መዋጋቱን ማስታወስ ይጠቅማል::

ጅቡቲ ያለችው በቀይ ባህርና በኤደን በህረ ሰላጤ በስዊዝ ካናል አገናኝ ሥፍራ ላይ ስለሆነች በባህር ላይ ለሚደረገው እንቅስቃሴ ታላቅ የሴኩሪቲ የኤኮኖሚ ሚና ትጫወታለች፡፡ ዩናይትድ አረብ ኢሜሬት በሶማሌ ላንድ በርበራ ወደብ ላይ ጦር ሰፈር ከማቋቋም በላይ አዲስ አይሮፕላን ማረፊያም እየስሩ ናቸው፡፡ ቱርክ በሱማሊያ፣ ሩሲያም በሱዳን፣ ግብጽ በደቡብ ሱዳን፣ ቱርክን የሱዳን ደሴት የሆነችውን ስዋኪን ላይ ጦር ሰፈር ለመመስረት መሞከሩ ይህንን የመሳሰሉ በየጊዜው በፈጣን ሁኔታ የሚለዋወጠው ለኢትዮጵያም ለአፍሪካ ቀንድም በጥቅሉ አስጊ ነው::

ሁሉም ሀይሎች የየራሳቸው አጀንዳ አላቸው፤ ኢትዮጵያ እዚሁ መካከል ነው ያለችው::

ለጊዜው ይህንን የአረቦች በአፍሪካ ቀንድ ላይ የሚፈፅሙት ርብርቦሽ እንዲፈጠር ያደረገው የየመን ጦርነትና በባህረሰላጢው ባሉት አብዛኛው የአረብ አግርችና በኢራን መካከል ያለው ፍትጊያ ቢሆንም ከጥንት ጀምሮ አረቦች ቀይ ባህርን የአረብ ሃይቅ ለማድረግ ካላቸው ምኞትም ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ይህንንም በተመለከተ በቅርቡ በጣም ሰፋ ያለ ጥናት አቅርቤ አለሁ፡፡ ጊዜ ካላችሁ The Iran Saudi Rivalry and the Scramble for the Horn of Africa በሚል ርዕስ ያዘጋጀሁት ጽሁፍ The Africa Institute For Strategic and Security Studies(AISSS) ድረ ገጽ ላይ ይገኛል፡፡

ስዊዝ ካናል ከተከፈተበት ከ1869 ዓ.ም. ጀምሮ አረብና አፍሪካ ቢቀራረቡም በግሎባላይዜሽን ጊዜና ዓለም በሀይማኖትና በሌሎችም ምክንያቶች የአረብ አንድነት እየተፍረከረከ ታላቅ የነበረው የአረብ (Nationalism) ብሔርተኛነት ሲፈርስ አሁን አዲስ ሃይሎች ዩናይትድ አረብ ኢሜሬትና ሳውዲ የሚመሩት ብቅ ብሎ Gulf Alliance በሚል አሜሪካ የተወውን ባዶ ሥፍራ ለመሙላት አካባቢውን በገንዘብ ሃይል ለመቆጣጠር እየቻሉ ነው፡፡ አሁን ቀይ ባህር የአውሮፓና የአሜሪካ ጉዳይ ሳይሆን የአፍሪካና የአረብ ሀገሮች ጉዳይ እየሆነ መጥቷል፡፡ አካባቢው በጣም ተከፋፍሏል፡፡ በዩናይትድ አረብ ኢሜሬትና በሳውዲ አረብያ የሚመራው አሊያንስ፣ በአፍሪካ ቀንድ ውስጥ ያሉ ሀገሮችን ለመያዝ ለመቆጣጠር የሚፈፀመውን ሁለንተናዊ ዘመቻ ኢትዮጵያ በጥንቃቄ ልትመለከተው ይገባል፡፡ በቅርቡ 30 Nov, 2018 The National Interest በሚባል የonline ፅሁፍ አንድ የፖለቲካ ሰው እንዲህ ይላል፡፡

“Somalia remains troubled largely by foreign agents who weaken its government, who divide its people and who threaten to reverse its gains” ይህም የተባለበት ምክንያት የአረብ ኤሜሬትስ በሕግ የሶማሊያ አካል በሆነችው ፑንትላንድና ሶማሌ ላንድ ላይ እንቅስቃሴ በመጀመራቸው ነው:: ኬንያም በበኩሏ በአካባቢው ያለው እንቅስቃሴ የሚያሳስብ መሆኑን አሰምታለች::

የመን ውስጥ የሚደረገው ጦርነት የየመን ህዝብ ጦርነት አይደለም፡፡ ኢራን በአንድ ወገን፣ ሳውዲ አረቢያ በሌላ በኩል በአሜሪካ ድጋፍ የሚካሄድ የእጅ አዙር ጦርነት ነው፡፡ የመን ውስጥ ሃያ ሚሊዮን ህዝብ በረሃብ ላይ ይገኛል፡፡ አስራ አንድ ሚሊዮን ህፃናት በሞት እና በሕይወት አፋፍ ላይ ናቸው፡፡ የመን የምትባል ሀገር ጠፍታለች፡፡ ስንት ሺ ሞቷል ስንት ሺ ቆስሏል፤ የእጅ አዙር ጦርነቶች እየተበራከቱ ሲሄዱ ኢትዮጵያ ከእያንዳንዱ ልትማር ይገባል፡፡ ከሱዳን እና ከግብጽ ጋር ኢትዮጵያ ያላት የተፈጥሮ ቁርኝት ማለትም ኢትዮጵያ ለሁለቱ ሀገሮች የህልውና ጥያቄ ስለሆነች የኢትዮጵያን ሁኔታ በቅርብ ይከታተላሉ፡፡ በሚታይም በማይታይም መንገድ ዘወትር በኢትዮጵያ ጉዳይ ጣልቃ ከመግባት አይቆጠቡም፡፡

ኤርትራና ኢትዮጵያ የውጭ ፖሊሲያቸው እንዳይጋጭ ከባድ ጥንቃቄ ማድረግ አለባቸው፡፡ ኤርትራ በየመን ጦርነት ላይ አቋም ይዛለች፡፡ በሌሎችም በአካባቢው ካሉ የአረብና የአፍሪካ ቀንድ ሀገሮች ጋር አቋም አላት፡፡ ኢትዮጵያም እንደዚሁ አቋም አላት፡፡ ይህ አቋማቸው ሁል ጊዜ ተመሳሳይ ሊሆን አይችልም፡፡ እይገባምም:: ልዩነቶችን ማጥበብና ማጥፋት በማይቻልባቸው ሆኔታዎች አንዱ የአንዱን አቋም አክብሮ የመኖር ባሕል ሊገነቡ ይገባል፡፡

ከኤርትራ ብዙ ስደተኞች ነን የሚሉ ወደ ኢትዮጵያ እየመጡ ናቸው:: ከዚሁ ጋር ተያይዞ ብዙ የኤርትራ መንግሥት ተቃዋሚዎች ኢትዮጵያ ምድር ገብተው በኤርትራ መንግሥት ላይ ያላቸውን ተቃውሞ ለማሰማት ቢሞክሩ ምንድነው የሚደረገው? ከኢትዮጵያ አኩርፈው ወንጀል ፈጽመው ኤርትራ ለሚገቡ ምን አይነት አቋም ነው ኤርትራ የምትወስደው? በንግድም፣ በሌሉችም ሁለቱን ህብረተሰቦች በሚያገናኙ ጉዳዮች ሁሉ አለመግባባት እንዳይፈጠር ውይይት ተደርጎ ወረቀት ላይ የሰፈረ ስምምነት ማድረግ አስፈላጊ ነው፡፡ በሁለቱም በኩል ሊኖር የሚገባው ግዴታና ኃላፊነት በዝርዝር መጠቀስ ይገባዋል::

በአጠቃላይ የውጭ ፖሊሲን በተመለከተ በዚህ ሙያ ልምድ ያላቸው የፃፉ፣ የተመራመሩ አዋቂዎች ያሉበት እንደ አስፈላጊነቱ የሚሰበስብ ምክር ቤት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢያቋቁሙ ይረዳቸዋል ብዬ አምናለሁ፡፡

መደመደሚያ::

በመጨረሻም የሀገር ውድቀት የሚመጣው በአንድ ጊዜ አይደለም ቀስ በቀስ ነው፡፡ በየጊዜው የሚከሰቱ ጉዳዮች ውጤት ነው፡፡ ዛሬ ኢትዮጵያ ከባድ ሥጋት ላይ ነች ዛሬ ክልሎች ከኢትዮጵያ መንግሥት ቁጥጥር ውጭ እየሆኑ ከፌዴራሊዝም ያለፈ ስም የለሽ ሥርዓት ውስጥ ተሸጋግረዋል፡፡ አብረው የኖሩ በአንድነት ታሪክ የሰሩ፣ በእምነታቸው በባህላቸው ተሳስረው የኖሩ፣ ተጋብተው ተዋልደው የኖሩ፣ ቢጣሉም ልዩነታቸውን ሳያስቀድሙ ሀገርን ጠብቀው ሞቱን በአንድነት ሞተው ስቃዩን፣ ችግሩን ተደጋግፈው አሳልፈው ኢትዮጵያን አንዳልገነቡ ሁሉ ዛሬ በመጣው የዘር ፖለቲካ ምክንያት ጋብቻ በዘርቆጠራ፣ የትምህርትቤት ጓደኝነት በዘር ቆጠራ፣ እየሆነ በመምጣቱ የሚያስተሳስሩን እሴቶች እየጠፋ ለመራራቅ አመቺ ሁኔታ ይፈጠራል፡፡  የተደራጁ ተዋጊ ኃይሎች በግልፅ አይታዩም፡፡ አሁን ጸጥታውን የሚያደፈርሱት ትንንሽ ቡድኖችና የማይታዩ ሃይሎች ናቸው፡፡ የተደራጀ ኃይልን መቋቋም አያስቸግርም ግን የተበታተኑ ቡድኖች ግን አመጽና ወንጀል ለመቋቋም አስቸጋሪ ነው፡፡  ከሥር ጀምሮ ያሉ የመንግሥት ተቋሞች እየፈረሱ ከማዕከላዊ መንግሥት ቀርቶ ከክልላዊ አመራሮችም ቁጥጥር ውጪ ሲሆኑ፣ የታጠቁ ግለሰቦች ተከታይ እየመለመሉ አካባቢያቸውን መቆጣጠር ሲጀምሩ ሥልጣን እየጣማቸው የመንግሥት ሃይልን መቋቋም ሲጀምሩ ሊገቱ የማይችሉ የሰፈር ጦር መሪዎች (War Lords) ይፈጠራሉ፡፡ ይህንን ክፍተት ያዩ ሌላ አጀንዳ ያላቸው፣ መሳሪያና ድጋፍ በገፍ ያቀርባሉ፡፡ ክፍተቱ እና ጣልቃ ገብነቱም  እየሰፋ ሲሄድ የራሳችው ውጊያ መሆኑ ቀርቶ የሌሎች ውስጣዊ ኃይሎችና የባዕዳን ጉዳይ ፈፃሚዎች ይሆናሉ:: ጦርነቱ ኃይል መጠቀም ሲጀመር ሰላማዊ ህዝብና አማፂያንን መለየት ያስቸግራል፡፡ ቁጣውና ኩርፊያው ይበራከታል፤ ጠላትም ይጠቀምበታል፤ የዚህንም ሂደት መተንበይ ያስቸግራል፡፡

እዚያ ሳንደርስ ሳይቃጠል በቅጠል የምንለው ለዚህ ነው፡፡ መስረታዊ የስርአት ለውጥ ጊዜ የሚስጠው አይደለም:: የዘመናት ትርምስ ዛሬ ወሳኝ ደረጃ ላይ ደርሶአል:: ህዝብ በቀጥታ የተሳተፈበት ህገመንግስትን ማውጣት፣ በዘር ላይ የተመሰረተ ፌዴራሊዝምን ማጥፋት፣ ማዕከላዊ መንግሥትን ማጠናከር፣ በአካባቢያችንና ከዚያም ባሻገር ካሉ አገሮች ጋር የተጠና ሚዛናዊ ወዳጅነት መፍጠር፣ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ተፈርተው፣ ተከብረው የመልካም አስተዳደርና የአብሮነት ኑሮ ምሳሌ ሆነው የጥቁር ህዝብ ተስፋና ኩራት እንደነበሩ ሁሉ ዛሬም እንደሚሆኑ ሊያረጋግጡ ይችላሉ፡፡

በዶ/ር አብይና በመንግሥታቸው የሚፈጸመውንና የታቀደውን ባለማወቅ ተሳስቼ ከሆነ ይቅርታ እጠይቃለሁ፡፡ ዓላማችን ለማገዝ፤ የተለየ ሐሳብን ለማቅረብና ለማንሸራሸር እንዲረዳ በዕድሜና በተሞክሮ ከበለፀግን፤ ስልጣንና መታየትን ከማንፈልግ ወገኖች በቅንነት የቀረቡ  ጥናቶችና ሐሳቦች ናቸው፡፡

አመሰግናለሁ፡፡

ያለሽግግር መንግስት ሃገር ማሻገር (ለቪዥን ኢትዮጵያ የቀረበ – በመስከረም አበራ)

በመስከረም አበራ

Ethiopian writer, Meskerem Abera.

መስከረም አበራ

የጥናቱ ጨመቅ (Abstract)

ሃገራችን አሁን የምትገኝበት ሁኔታ ዲሞክራሲያዊ ሽግግርን የሚከለክል ስላልሆነ የሽግግር መንግስት ማቋቋም ሳያስፈልግ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ለመገንባት የሚያስችል የሽግግር ስራ መስራት ይቻላል፡፡ ይህን ሽግግር ለማድረግ ሃገሪቱ ለረዥም ዘመን ዲሞክራሲን እንዳታሰፍን ያደረጉ ችግሮችን በሽግግሩ ወቅት አቃሎ በምርጫ ለሚመጣው መንግስት ለዲሞክራሲያዊ አስተዳደር የሚመች ሁኔታ መፍጠር ያስፈልጋል፡፡ የዚህ ፅሁፍ አላማ እነዚህን ችግሮች ለይቶ የሚፈቱበትን መንገድ መጠቆም ነው፡፡ ይህን ለማድረግ የተለያዩ መፅሃፍት፣ጥናታዊ ፅሁፎች  እና ተመሳሳይ ለውጥ ያደረጉ የአለም ሃገራት ልምድ ዳሰሳ ተደርጓል፡፡ በተጨማሪም የፅሁፉ አቅራቢ እይታዎች ግብዓት ተደርገዋል፡፡ ከተዳሰሱ መዛግብት በተገኙ መረጃዎች  መሰረት ሃገራችን ዲሞክራሲን እንዳታሳድግ ካደረጉ ችግሮች ውስጥ ህገ-መንግስታዊ መሰረት ያላቸው እንደ የዘውግ ፖለቲካ/ፌደራሊዝም፣የመሬት ባለቤትነት ጉዳይ፣ፓርላመንታዊ የመንግስ ስርዓት እና ኢህአዴግ የመሰረተው የፓርቲ ፖለቲካ ዘይቤ ዋነኞቹ ናቸው፡፡እነዚህ ችግሮች በታሪክ እየተጠራቀሙ የመጡ በመሆናቸው በሁሉም የፖለቲካ ሃይሎች በተሳተፉበት ሰፊ ስራ እና በህዝብ ውይይት በሽግግሩ ወቅት መፈታት አለባቸው፡፡ ችግሮቹ በሽግግሩ ወቅት ሳይፈቱ በምርጫ ወደ ሚመረጠው መንግት ከተላለፉ የሚመረጠውን መንግስትም ሆነ የሃገሪቱን ህልውና አደጋላይ ሊጥሉ ይችላሉ፡፡በተቃራኒው ታሪካዊ ችግሯን የፈታች(ያቃለለች) ሃገር ለተመራጩ መንግስት ማስተላለፍ ከተቻለ ተመራጩ መንግስት ታሪካዊ ችግሮችን የመፍታት አስቸጋሪ ስራ ውስጥ ሳይገባ ሃገሪቱን ወደ ዲሞክራሲያዊ መስመር የሚያስገቡ ስራዎችን ወደ መስራቱ እንዲገባ ይረዳዋል፡፡ይህን ገቢራዊ ለማድረግ ታሪካዊ ችግሮችን መርምሮ፣የእልባት መንገድ አፈላልጎ፣ሽግግሩን/ለውጡን የሚያፀኑ ስራዎችን በመስራት ሃገር የሚያሻግር፣ ይህን ለማድረግ በቂ ስልጣን የተሰጠው ተቋም መዋቀር አለበት፡፡ 

መግቢያ

ከዘውዳዊው አገዛዝ መገርሰስ በኋላ ኢትዮጵያ ሁለት የሽግግር መንግስትን ዘመናትን አስተናግዳለች፡፡የመጀመሪያው የሽግግር መንግስት  የፊውዳሉን ስርዓት የተካው ጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ ሲሆን ሁለተኛው ኢህአዴግ የተለያዩ የፖለቲካ ሃይሎችን ጋብዞ የመሰረተው ከ1983-1987 የቆየው የሽግግር መንግስት ነው፡፡ ሆኖም ሁለት የሽግግር መንግስት ያስተናገደችው ሃገራችን እስከዛሬ ድረስ በተግባር ወደ ዲሞክራሲያዊ አስተዳደር መሸጋገር አልቻለችም1፡፡

ይህ ያልተቻለበት ምክንያት በወቅቱ የሽግግር መንግስታቱን ሲመሩ የነበሩ የፖለቲካ ሃይሎች ሃገርን ዲሞክራሲያዊ ከማድረግ ይልቅ ቅድሚያ የሰጡት የፖለቲካ ስልጣናቸውን በማቆየት ላይ በመሆኑ ነበር፡፡የሽግግር ጊዜውንም ለሃገር ሽግግር ከመስራት ይልቅ የወደፊት ስልጣናቸውን ለማደላደያ እና የፓርቲያቸውን/የቡድናቸውን ፍላጎት ማስጠበቁን በህግ ማዕቀፍ ያፀኑበት ሆኖ አልፏል2፡፡ ሃገራችን የሽግግር መንግስታትን ማስተናዷ ብቻውን ወደዲሞክራሲያዊ ሽግግር ሊመራት አልቻልም፡፡ ከዚህ የምንረዳው ሃገር ለማሻገር የሽግግር መንግስት የሚል መጠሪያ ያለው መንግስር መሰየሙ ዋነኛ ጉዳይ እንዳልሆነ ነው፡፡ዋነኛው ጉዳይ በሃገሪቱ የፖለቲካ ስልጣን ላይ ያለው መንግስት ሃገርን ዲሞክራሲያዊ ለማድረግ ያለው ቁርጠኝነት ነው፡፡

ሁለት የሽግግር መንግስታትን ያሳለፈችው ሃገራችን አሁንም  በወሳኝ የሽግግር ወቅት ላይ ትገኛለች፡፡በአሁኑ የሃገራችን ፖለቲካዊ ሁኔታ የሽግግር ሁኔታ እንጅ የሽግግር መንግስት የለም፡፡ የሽግግር መንግስት ያስፈልጋል ወይስ አያስፈልግም የሚለው ጉዳይም አከራካሪ ሆኖ ይገኛል፡፡ በርግጥ አምባገነን መንግስታት ስልጣን ሲለቁ ድርድር ተደርጎ ከሃገሪቱ የተውጣጡ የፖለቲካ ሃይሎች ለመሰረቱት የሽግግር መንግስት አስረክበው የሚለቁበት ሁኔታ በተፈጠረበት ሃገር ወደ ዲሞክራሲያዊ መንግስት ለመሻገር የሚደረገው ጉዞ ቀላል ይሆናል3፡፡ኢትዮጵያ ውስጥ የሆነው ግን ይህ አይደለም፡፡ይልቅስ የህዝብ ትግልን ተከትሎ ኢህአዴግ ውስጥ በተከሰተው ውስጠ-ፓርቲ ትግል ዲሞክራሲያዊ ሃገር ለመመስረት የሚሹ ቡድኖች ስልጣኑን ተረክበው የሽግግር መንግስት ባይሆኑም የሽግግር ሁኔታን ፈጥረዋል፡፡

ከአምባገነን ስርዓት ወደ ዲሞክራሲያዊ ሽግግር የሚያደርጉ ሃገራትን ሽግግር ስኬታማ ከሚያደርጉ ቅድመ-ሁኔታዎች ዋነኞቹ፤ በሽግግር ወቅት ሃገሪቱን የሚመሩ መሪዎች ለሽግግሩ ስኬት ያላቸው ቁርጠኝነት፣የፖለቲካ ልዩነቶችን አቻችሎ ፖለቲካዊ ችግሮች በሰላማዊ መንገድ መፍትሄ እንዲያገኙ የማድረግ ዝንባሌ/ችሎታቸው፣ በህዝባቸውና በአለም ዓቀፍ ማህበረሰቡ ዘንድ ያላቸው ድጋፍ የሚሉት ዋና ዋናዎቹ ናቸው3፡፡ አሁን ሃገራችንን የሚመሩ መሪዎች ወደስልጣን በመጡበት አጭር ጊዜ ከወሰዱት እርምጃ በመነሳት እነዚህ ቅድመ-ሁኔታዎችን የሚያሟሉ መሆናቸውን መገንዘብ ይቻላል፡፡ ስለዚህ በመሪዎች በኩል የሚያስፈልጉ ቅድመ-ሁኔታዎች ከሞላ ጎደል የተሟሉበት የፖለቲካ ሁኔታ ውስጥ የምንገኝ በመሆናችን የሽግግር መንግስት የመመስረት ሌላ ከባድ ሥራ ውስጥ መግባት ብዙ ትርፍ ያለው ነገር አይደለም፡፡

በስልጣን ላይ ያለው መንግስት የተለያየ የፖለቲካ አመለካከት ያላቸው ሃይሎችን አቻችሎ ይዞ የሚጓዝ የፖለቲካ ስርዓት ለመፍጠር ፍላጎት ባሳየበት ሁኔታ የሽግግር መንግስት ወደ ማቋቋም መሄዱ  በሃገሪቱ ከገነነው የጎሳ ፖለቲካ ጋር ሲደመር ከጥቅሙ ጉዳቱ ሊያደላ ይችላል፡፡ ከዚህ ይልቅ በሃገራችን ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ስልጣን ላይ ያለው መንግስት ዲሞክራሲያዊ ፖለቲካ ለመፍጠር ያሳየውን ዘንባሌ እንደ ጥሩ አጋጣሚ በመጠቀም የሃገሪቱን ፖለቲካ ወደ ዲሞክራሲያዊ ዘይቤ  ለማሻገር የሚያግዙ ስራዎችን መስራቱ ተመራጭ ይሆናል፡፡

በዚህ ፅሁፍ ሁኔታ “ሃገር ማሻገር” የሚለው ሃረግ  የሚገልፀው የሃገራችን ዲሞክራሲያዊ ፖለቲካ እንዳታራምድ ሲያግዱ የኖሩ ዋና ዋና ችግሮችን  በሽግግሩ ወቅት ፈቶ በምርጫ ለሚመጣው መንግስት ችግሯ የተቃለለ ሃገር ማስረከብ የሚለውን ሃሳብ ነው፡፡ በዚህ ፅሁፍ አቅራቢ እሳቤ የሃገራችን ፖለቲካዊ ችግሮች በታሪክ ሲንከባለሉ እዚህ የደረሱ እና በአሁኑ ወቅት ደግሞ በህገ-መንግስታዊ ድንጋጌ የተደገፉ ስለሆኑ በአንድ መንግስት አቅም የሚፈቱ አይደሉም፡፡እነዚህን ስር የሰደዱ ችግሮች በሚቀጥለው ሃገራዊ ምርጫ የሚመረጠው መንግስት እንዲፈታቸው ማቆየት ተመራጩን መንግስት ህልውናውን በሚፈታተን ችግር ሊከተው፣ ሃገሪቱንም መልሶ ለሌላ ህዝባዊ አመፅ ሊዳርግ ይችላል፡፡ ስለዚህ የሃገራችንን ፖለቲካ ዋና ዋና ችግሮች ሳይቃለሉ በምርጫ ለተመረጠው መንግስት መተላለፍ ስለሌለባቸው በሽግግሩ ወቅት በሁሉም የፖለቲካ ሃይሎች ትብበር መፈታት አለባቸው፡፡ የእነዚህን ችግሮች ምንነት መዳሰስ  እና እንዴት መፈታት እንዳለባቸው መጠቆም የዚህ ፅሁፍ ዋነኛ አላማ ነው፡፡

ሃገር ማሻገር እንዴት?

ከአምባገነን አገዛዝ ወደ ዲሞክራሲያዊ አስተዳደር የሚደረግ የለውጥ ጉዞ ስኬታማ የሚሆነው ለውጡ እንዲመጣ የህዝብን ትግል ያነሳሱ ዋና ዋና ፖለቲካዊ ጥያቄዎች ድጋሜ አገርሽተው የብጥብጥ ምክንያት እንዳይሆኑ አድርጎ ፖለቲካዊ መልስ መስጠት ሲቻል  ነው5፡፡ ለውጥን ያነሳሱ መሰረታዊ ጥያቄዎችን ለይቶ  በተሳካ ሁኔታ የመመለሱ ስራ ደግሞ ከሃገር አቀፍ እስከ አለም አቀፍ የደረሰ የፖለቲካ ሃይሎችን ተሳትፎ የሚፈልግ እንጅ በስልጣን ላይ ባለው አካል ብቻ የሚቻል ነገር አይደለም6፡፡ የሃገሪቱን አንገብጋቢ ጥያቄዎች  በርካታ ባለድርሻ አካላትን ባሳተፈ ሁኔታ ለመመለስ መሞከሩ እርምጃውን ተቀባይነት እንዲኖረው ከማድረግ ባሻገር በርካታ አማራጭ የመፍትሄ ሃሳቦችን ለማፍለቅ ያስችላል፡፡ ከእነዚህ ባለድርሻ አካላት ውስጥ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣የሲቪክ ማህበራት፣ምሁራን፣ዓለምአቀፍ የዲሞክራሲ እና ሰብዓዊ መብት ተቋማት፣ታዋቂ እና ተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች ይገኙበታል፡፡

የኢትዮጵያ ህዝብ ለለውጥ ትግል እንዲያደርግ የገፋፉ አንኳር ጥያቄዎች በከፊል አሁን በስራ ላይ ባለው ህገ-መንግስት ላይ የሰፈሩ አንዳንድ ድንጋጌዎች የፈጠሯቸው ናቸው7፡፡ የዘር ማንነትን ብቸኛ መገለጫ አድርጎ የሚያስበው ወቅታዊው የሃገራችን ፖለቲካዊ ባህል፣ይህን የሚከተለው የዘር ፌደራሊዝም፣ የሃገሪቱ ክልሎች በፈለጉ ሰዓት ሉዓላዊ መንግስት ሆነው መገንጠልን የሚፈቅደው ህገመንግስታዊ ድንጋጌ፣የመሬትባለቤትነትን ለብሄር ብሄረሰቦች እና ለመንግስት ሆኖ መደንገጉ ዋነኞቹ ህገ-መንግስት ወለድ የሃገራችን ፖለቲካ ችግሮች ናቸው8፡፡እንዲህ ያሉ ህዝቡን ለትግል ያስነሱ ዋና ዋና ጥያቄዎችን መመለስ  ካልተቻለ ሃገሪቱ ወደ ሌላ የብጥብጥ ምዕራፍ የማምራት አደጋ ሊገጥማት ይችላል9፡፡ ሃገራችን እያየችው ያለውን የለውጥ ጅማሬ  ለማፅናት እነዚህን ጥያቄዎች መመለስ ያስፈልጋል፡፡ ጥያቄዎቹ ፈርጀ ብዙ እና የብዙ አካላትን የተቀናጀ ጥረት የሚፈልጉ በመሆናቸው፤  የሁሉም የሃገሪቱ ፖለቲካዊ ሃይሎችን  ተሳትፎ ይፈልጋሉ፡፡

ስለዚህ ጥያቄዎቹ መመለስ ያለባቸው ወደፊት በሚደረገው ሃገራዊ ምርጫ ወደ ስልጣን በመጣ አንድ ፓርቲ ሳይሆን በሃገሪቱ ባሉ ሁሉም የፖለቲካ ሃይሎች ውይይት ተደርጎባቸው በስተመጨረሻው ለኢትዮጵያ ህዝብ ቀርበው መሆን አለበት፡፡ በአንድ የምርጫ ጊዜ የሚመረጥ መንግስት የህዝብን ውክልና የሚያገኘው የፓርቲ ፕሮግራሞቹን ተከትሎ በአምስት አመት ውስጥ እሰራለሁ ያላቸውን ተግባራት ለመከወን እንጅ እንደ ህገ-መንግስት ያሉ የሃገሪቱን ህዝቦች ዕጣ ፋንታ በዘላቂነት የሚወስኑ ጉዳዮች ላይ ለመወሰን አይደለም፡፡

ከአምባገነን መንግስታት ውድቀደት በኋላ የሚደረግ ምርጫ የሃገሮችን ወደ ዲሞክራሲ የሚደረግ ጉዞ በእጅጉ የሚወስን ነው9፡፡እንዲህ ያለው ምርጫ በስኬት ተከናውኖ የሚመጣው መንግስትም በተረጋጋ ሁኔታ ሃገሪቱን ለመመምራት እንዲችል በተቻለ መጠን ብጥብጥ ሊያስነሱ የሚችሉ ዋና ዋና የህዝብ ጥያቄዎች በሽግግሩ ዘመን መመለስ አለባቸው፡፡እነዚህ ዋነኛ የሃገሪቱ ችግሮች በሃገሪቱ የሚገኙ  የፖለቲካ ሃይሎች ሁሉ በተሳተፉበት የጋራ ጥረት በሽግግሩ ወቅት ቢፈቱ አዲስ የሚመረጠው መንግስት እነዚህን ችግሮችን ወደ መፍታቱ አስቸጋሪ ስራ ከመሄድ ይልቅ በብጥብጥ የቆየችውን ሃገር መልሰው የሚገነቡ ፖሊሲዎችን አውጥቶ መተግበሩ ላይ እንዲያተኩር ይረዳዋል10፡፡

ይህ ሳይሆን ቀርቶ ሃገሪቱን ለለውጥ ያነሳሱ ዋና ዋና የህዝብ ጥያቄዎች በዲሞክራሲያዊ ምርጫ በሚመረጠው መንግስት እንዲፈቱ ከተተወ ሃገሪቱ ተመልሳ ወደ ነውጥ የመግባት ከፍ ያለ ዕድል ይኖራታል11፡፡ይህ የሚሆንበት ምክንያት ሃገሪቱ ከአምባገነን መንግስት ወደ ዲሞክራሲ ለመጓዝ በሽግግር ወቅት እንደመሆኗ ህዝቡ ከለመደው የአምባገነናዊ አስተዳደር በተለየው የዲሞክራሲያዊ አስተዳደር ለመምራት ራሱን የቻለ ችግር ይጠብቀዋል12፡፡የሚቀጥለው የሃገራችን ምርጫ ሃገሪቱ ወደ ዲሞክራዊያዊ የምርጫ ዘይቤ የምትተላለፍበት ወሳኝ ጊዜ ነው፡፡የሚያሸንፈው ማኛውም ፓርቲ(ኢህአዴግን ጨምሮ) ለዲሞክራሲያዊ አስተዳደር እንግዳ ነው፡፡በምርጫው የሚያሸንፈው ፓርቲ ተቃዋሚ ፓርቲ ከሆነ ደግሞ እንግድነቱ ለዲሞክራሲያዊ አስተዳደር ብቻ ሳይሆን ለሃገር መምራትም ይሆናል፡፡ከሁለቱም ወገን ወደ ስልጣን የሚመጣ መንግስት የሚያስተዳደርው ለዲሞክራሲ እንግዳ የሆነን ህዝብ ነው፡፡በዚህ ምክንያት ብቻ ቀላል የማይባል ተግዳሮት ይጠብቀዋል፡፡

በዚህ ተግዳሮት ላይ የሃገሪቱ ህዝቦች ለረዥም ዘመን የታገሉባቸውን መሰረታዊ ጥያቄዎች ይሄው ተመራጭ መንግስት እንዲፈታ መጠበቅ ሃገሪቱን ወደ አደገኛ ብጥብጥ ሊመራት ይችላል፡፡ስለዚህ በሚቀጥለው ሃገራዊ ምርጫ ወደስልጣን የሚመጣው መንግስት መረከብ ያለበት በታሪክ እየተንከባለሉ የመጡ ሥር-ሰደድ ፖለቲካዊ ችግሮቿ የተቃለሉ ኢትዮጵያን መሆን አለበት፡፡

በሽግግሩ ወቅት መመለስ ያለባቸው መሰረታዊ የሃገራችን ችግሮች ምን ምን ናቸው?

ሃገራችንን ወደ ዲሞክራሲያዊ ፖለቲካ ለማሻገር የሚቻለው ህልውናዋን የሚፈታተኑ፣የህዝቦቿን ሰላም የሚያደፈርሱ፣የዲሞክራሲ ግንባታን የሚያግዱ ችግሮቿን በሰፊው ለሁለት ይከፈላሉ፡፡አንደኛው ህገ-መመንግስታዊ ድጋፍ ያላቸው ነገር ግን የህዝቡን ሰላማዊ ኑሮም ሆነ የሃገሪቱን እንደ ሃገር የመቀጠል ዕድል አደጋ ውስጥ የሚከቱ ችግሮች ሲሆኑ ሁለተኛውዎቹ ከገዥው ፓርቲ ኢህአዴግ  የፓርቲ ፖለቲካ ባህል ጋር የሚቆራኙ ችግሮች ናቸው፡፡

ሀ. ህገ-መንግስት ወለድ ችግሮች፤

 1. የዘር ፖለቲካ/የዘር ፌደራሊዝም

በአሁኑ ወቅት በምንኖርባት ዓለም ህዝቦች በዘውጋቸው ሳሆን ሶሻል ዲሞክራሲ፣ሊብራል ዲሞክራሲ፣የወግ አጥባቂዎች በሚሉ የዲሞክራሲያዊ ፖለቲካ ትግበራ ቀመር ላይ ባተኮሩ ልዩነቶች ላይ ተመስርተው ማህበራዊ መስተጋብራቸውን እና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴያቸውን በማፋጠን ላይ ይገኛሉ፡፡ በዚህ የተነሳ አብዛኛዎቹ የዓለም ሃገራት የዘር ፖለቲካን ካነገበችው ሃገራችን በተሻለ ፖለቲካዊ መረጋጋት እና ኢኮኖሚያዊ እድገት ላይ ይገኛሉ፡፡ በአንፃሩ የፖለቲካን ይዘት  ዘውግ ብቻ እስከማድረግ የዘለቀችው ሃገራችን፣ በአስፈሪ የጎሳ ግጭት፣በማያቆም የክልሎች የድንበር ጥያቄ፣በኢኮኖሚ እድገት ዝግመት ውስጥ ትገኛለች፡፡

የሃገራችን ፖለቲካ ወቅታዊ ችግር ዋነኛ ምንጭ የዘር ፖለቲካ ነው13፡፡የዘርፖለቲካ/ፌደራልዝም በባህሪው ለዘመናዊ ፖለቲካ ግንባታ የማይመች፣ከዲሞክራሲ መሰረታዊ መርሆዎች ጋር የሚጋጭ፣ የሃገርን  ዘላቂ ሰላምን በማስፈን በኩል ቀላል የማይባል ተግዳሮት የሚደቅን፣ ለመድበለ ፓርቲ ስርዓት ግንባታ መሰናክል የሚፈጥር፣የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ የሚያስቸግር፣ከተፈጥሯዊው የሰውልጆች ባህሪ ጋርም የማይሄድ  ርዕዮተ-ዓለም ነው14፡፡ የዘር ፖለቲካ ከሰውልጆች ተፈሯዊ የእሳቤ ፈለግ ባፈነገጠ ሁኔታ የአንድ ዘር አባላት ሁልጊዜ ተመሳሳይ አቋም እንደ ሚይዙ ታሳቢ ያደርጋል15፡፡

በሃገራችን ህገ-መንግስት የተደነገገው የዘውግ ፖለቲካ ታሳቢ የሚያደርገው ይህኑ ከአንድ አይነት ዘር የሆኑ ሰዎች አንድ አይነት ፍላጎት እና ሃሳብ ይኖራቸዋል የሚለውን እሳቤ ነው፡፡ይህ እሳቤ የዘር ክልል ከመከለል የሚነሳ ችግር አለበት፡፡ የዘውግ ወይም የብሄረሰብ ክፍፍል ማድረግ እና ድንበር ማበጀት እጅግ በጣም አስቸጋሪ ነው፡፡ ምክንያቱም የተለያ ጎሳዎች እና ብሄረሰቦች የአሰፋፈራቸው ግንኙነት በጣም የተወሳሰቡ በመሆኑ ነው፡፡ የኢትዮጵያን ግዛት በዘር ፌደራሊዝም የከለለው የኢትዮጵያ ህገ-መንግስት የሃገሪቱን ብሄረሰቦች ታሪካዊ ግንኙነቶች በአግባቡ ሳይመረምር እና ሁሉን አቀፍና ህዝቦችን ያካተተ  ምክክሮችን ሳያደርግ የተደረገ አከላለል ነው17

በተጨማሪ በህገ-መንግስቱ አንቀፅ 47 ድንጋጌ መሰረት ፌደሬሽኑ በዘጠኝ ክልሎች ብቻ እንዲኖሩ ያደረገበት መመዘኛው ምን እንደሆነ ግልፅ አይደለም፡፡ ይህየህገመንግስቱ ቁልፍ ችግር ነው፡፡ በህገ-መንግስቱ አንቀፅ 8 ንዑስ ቁጥር 1 ውስጥ የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ብሄረሰቦችና ህዝቦች የኢትዮጵያ ሉዓላዊ ስልጣን ባለቤቶች ናቸው እያለ በሃገሪቱ ያሉ ብሄር ብሄረሰቦች ከ85 በላይ በሆኑበት ሁኔታ ስምንት ብሄረሰቦች ብቻ ተመርጠው የራሳቸውን መንግስት ማቋቋማቸውን  በህገ-መንግስት ማወጅና ሌሎቹ ብሄረሰቦች ከፈለጉ ወደ ፊት መንግስት ማቋቋም ይችላሉ ብሎ ማለፉ በብሄረሰቦች መሃከል ያለውን ግንኙነት የሚያሻክር ከመሆኑም በላይ  የዘር ፌደራሊዝሙ በበቂ ጥናት እና ትኩረት ያልተሰራ መሆኑን ያሳያል18፡፡ ለዚህ ጥሩ ማሳያው በአሁኑ ሰዓት የማያባራ የክልል ጥያቄ እየተነሳበት ያለው ደቡብ ክልል ነው፡፡

በክልል ደረጃ ያልተዋቀሩ ብሄሮችም የራሳችን ክልላዊ መንግስት ያስፈልገናል የሚል ጥያቄ ሲያነሱ የየራሳቸውን ክልሎች ማቋቋም እንደሚችሉ ነው በህገመንግስቱ የተገለፀው19፡፡ ይህን ጥያቄ ለማንሳት የመጀመሪያው ቅድመ-ሁኔታ ተደርጎ በህገመንግስቱ አንቀፅ 47 ንዑስ ቁጥር 3 ስር የተቀመጠው ማንኛውም ብሄር፣ ብሄረሰብ፣ህዝብ የራሱን ክልል የመመስረት መብት በስራ ላይ የሚውለው፤  “ሀ” የክልል መመስረት ጥያቄው በብሄሩ፣ ብሄረሰቡ ወይም ህዝቡ ምክር ቤት በሁለት ሶስተኛ ድምፅ ተቀባይነት ማግኘቱ ሲረጋገጥ እና ጥያቄው በፅሁፍ ለክልል ምክርቤት ሲቀርብ እንደሆነ ይደነግጋል፡፡ ይሁን እንጅ በሃገራችን ከደቡብ ብሄር ብሄረሰቦች ክልል በስተቀር በአንድ ክልል ውስጥ ያሉ የተለያዩ ብሄረሰቦች ይህን ለማድረግ የሚያስችል የብሄረሰብ ምክር ቤት የላቸውም20፡፡ለዚህ ጥሩ ምሳሌ የሚሆነው በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልለ ውስጥ  የጉሙዝ/በርታ ብሄረሰብ የራሱ ምክርቤት እንዲኖረው አቅርቦ የነበረው ጥያቄ በክልሉ ምክርቤትም ሆነ በፌደሬሽን ምክርቤት ተቀባይነት ሳያገኝ መቅረቱ ነው21፡፡

እንደ ደቡብ ክልል ብሄረሰቦች የራሳቸው ምክርቤት እንዲኖራቸው በተደረገበት ሁኔታ ያለው ችግር ደግሞ በህገ-መንግስቱ አንቀፅ 47 ንዑስ አንቀፅ 3 ስር ከሀ-ሠ የተዘረዘሩት ቅድመ ሁኔታዎች የክልል ጥያቄ የሚያቀርበውን ብሄር ጉዳይ ከመጀመሪያ እስከመጨረሻ የሚታየው ጥያቄው በተነሳበት ብሄር ምክርቤት እና በክልሉ ምክርቤት ብቻ መሆኑ ነው፡፡ በሌሎች ሃገራት ግን አዲስ ክልል ወይም አስተዳደር ለማደራጀት ጥያቄ ሲነሳ ገና ከመጀመሪያው ለማየት የሚችሉት ጥያቄው የተነሳባቸው ክልሎች ብቻ ሳይሆኑ ፌደራሉን ህገ-መንግስት መሰረት በማድረግ በሶስትዮሽ እንጅ በአካባቢያዊ ምክርቤቶች ብቻ አይደለም፡፡

ለምሳሌ በፌደራል ጀርመን ህገመንግስት አንቀፅ 29 ንዑስ ቁጥር 1 እና 2 ውስጥ እንደተገለፀው በፌደራሉ መንግስት ስልጣን ውስጥ አሁን ካሉት  የፌደራል አባል መንግስታት በተጨማሪ አዲስ የፌደራል መንግስት ወይም አስተዳደር ማደራጀት እንደሚቻል ያመለክታል፡፡ ይህ ተፈፃሚ የሚሆነው አዲስ አስተዳደር የሚፈልጉ አካባቢዎች ራሳቸውን ለማስተዳደር የሚያስችል የኢኮኖሚ ግንባታ ብቃታቸውና መንግስታዊ ሃላፊነቶችን እንደሌሎች ፌደራል አባል መንግስት ሊወጡ የሚችሉ መሆናቸው ሲረጋገጥ፣የመሬታቸው ጅኦግራፊያዊ አቀማመጥ አስተዳደር ለማቋቋም ምቹ መሆኑ ሲያስተማምን ፣በህዝቦች መሆከል የባህል ተቀራራቢነት መኖሩ ሲታወቅ እና የኢኮኖሚ ግንባታ ግንኙነቶችም በትክክል ይህንኑ ለማስፈፀም የሚያስችሉ ሆነው ሲገኙ የአስተዳደር ለውጥ ሊደረግ እንደሚችል ያመለክታል22፡፡

በኢትዮጵያ ሁኔታ ግን የአዳዲስ ክልሎች መፈጠር ጥያቄውም መልሱም በክልል ምክርቤት እና በአካባቢያዊ የብሄረሰቦች ምክርቤት ውሳኔ ብቻ እንዲያልቅ ተደንግጓል፡፡ ይህ ህገመንግስታዊ ድንጋጌ በተቀመጠበት ሁኔታ ጥያቄው አይነሳ ማለት ህጋዊ አካሄድ አይደለም፡፡ጥያቄው ህገ-መንግስታዊ ስለሆነ መፈቀድ ካለበት ደግሞ ክልሎቹ በተመሰረቱ ማግስት የድንበር፣ተፈጥሮ ሃብት ይገባኛል እና የማንነት ጥያቄን መሰረት ያደረጉ የእርስበርስ ግጭቶች የመከተል እድላቸው ከፍ ያለ ነው፡፡ይህ ደግሞ የሃገሪቱን እንደ ሃገር መቀጠል ፈተና ላይ የሚጥል ችግር ነው፡፡

ሌላው ትልቅ ችግር በሃገሪቱ ህገ-መንግስት አንቀፅ 39 ለሃገሪቱ ብሄረሰቦች እና ህዝቦች የተሰጠው ከሃገሪቱ ተገንጥሎ ሉዓላዊ ሃገር የመሆን መብት ነው፡፡ይህን ድንጋጌ በህገ-መንግስት ማስቀመጥ ለሃገር ህልውና አደገኛ በመሆኑ ከኢትዮጵያ በቀር በሌሎች የዓለም ሃገራት ከዘውግ ጥያቄ ጋር የተያያዙ እንደ መገንጠል ያሉ ጉዳዮች  የተለያዩ ዘውግ አባላት ተከባብረው በሰላም የሚኖሩበትን መንገድ ማመቻቸት ወደሚል  ፈለግ ተቀይሯል23፡፡ ሃገራችን ግን  ይህን  አንቀፅ የህገ-መንግስቷ አካል አድርጋ ቀጥላለች፡፡ የዚህ ምክንያቱ ህገ-መንግስቱ ሲፃፍ የሃገሪቱ ዋነኛ ወሳኝ የፖለቲካ ሃይል የነበረው ህወሃት በተፈጥሮው ስታሊናዊ ማንነት ያለው በመሆኑ እና ፓርቲው በትጥቅ ትግል ወቅት ከፃፈው የፓርቲ ማኒፌስቶች ቅጅ በመሆኑ አንቀፁ እንዲነሳ ፍላጎት ያለው ባለመሆኑ ነው24፡፡

በዚህ ድንጋጌ የአማርኛው ትርጉም ላይ ብሄረሰቦች “ያለምንም ቅደመ-ሁኔታ”፣በእንግሊዝኛው ደግሞ “unconditionnally” ከሃገሪቱ ተገንጥለው የራሳቸውን ሉዓላዊ መንግስት የመመስረት መብት እንዳላቸው ተደንግጓል፡፡በነባራዊው ዓለም ሃገርን መገንጠል የሚያክል ትልቅ እና ውስብስብ ጉዳይ ቀርቶ ማንኛውም ቀላል የሚባል ውሳኔ ያለቅድመ-ሁኔታ ሊደረግ አይችልም፡፡ በተግባር የታየውም ይሄው ነው፡፡ በወረቀት ላይ ያለ ቅድመ-ሁኔታ መገንጠልን የሚፈቅደውን ህገ-መንግስት የፃፈው ህወሃት መራሹ ኢህአዴግ  በሃያ ሰባት አመቱ ቆይታው የመገንጠልን መብት በተግባር ሲተገብር አልታየም፡፡በምትኩ እንገንጠል ከሚሉ እንደ ኦነግ እና ኦብነግ ያሉ ቡድኖች ጋር ሲዋጋ፣ሲከስ፣ሲያስር ነው የታየው፡፡ ሆኖም የአንቀፁ በህ-መንግስት ላይ ተፅፎ መኖር ሃገሪቱን ለከባድ የህልውና አደጋ መጋበዙ አይቀርም፡፡ ይህ ደግሞ በሃገሪቱ ለሚመጡ መንግስታት ፈተና መሆኑ አይቀርም፡፡

በጥቅሉ ሲታይ በኢትዮጵያ ህገ-መንግስት በተለያዩ የኢትዮጵያ ብሄረሰቦች መካከል ለሰላም እና ለጋራ ብልፅግና መታገለን የሚያመቻቹ ሁኔታዎች የሉም፤ጊዜን እና የፖለቲካ ውዝገቦችን እየጠበቁ የተለያዩ ብሄረሰቦች የመገንጠል ጥያቄዎችን ማንሳታቸው የማይቀር ነው25፡፡ ይህ ህገ-መንግስቱን ባስረቀቀው ኢህአዴግ በኩል የዲሞክራሲ መገለጫ ተደርጎ የሚቀርብ ቢሆንም በተቃራኒው ከአንድነት ይልቅ መከፋፈልን የሚያበረታታ ፣ሰላምን እና የጋራ እድገትን የሚያሰናክል አካሄድ ነው25፡፡

በዓለማችን ከኢትዮጵያ በቀር የፌደራል ሥርዓት እያራመደ  መገንጠልን በህገ-መንግስቱ የደነገገ ሃገር የለም፤ምክንያቱም የፌደራል ሥርዓት  በመስራች መንግስታት መሃከል ያለ ስምምነት ውጤት  ነው26፡፡ስለዚህ የመገንጠል ጥያቄን በህገ-መንግስት መደንገግ  አስፈላጊ ካለመሆኑም በላይ የራሱን የፌደራሊዝምን ትርጉም የሚያዛባ ነው፡፡ፌደራል ስርዓት እያራመዱ የመገንጠል ጥያቄ ከተነሳ የፌደራሉን መንግስት እድገትና በፌደራሉ መንግስት አባል መንግታት  መካከል ሊኖር የሚገባውን መደጋገፍ የሚያፋልስ፣የሃገርን ህልውናም ጥያቄ ውስጥ የሚከት ነው፡፡

እስከ መገንጠል በደረሰ ህገ-መንግስታዊ አንቀፆች የሚደገፈው የዘር ፖለቲካ በሃገራቸን በቆየበት የሃያ ሰባት አመት እድሜ በሃገሪቱ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ የዘር ግጭትን፣መፈናቀልን፣ሞትን፣ስደትን አስከትሏል፡፡የዘር ፖለቲካን በይፋ የፈቀደው የኢትዮጵያ ህገመንግስት በተግባር ዘር  ማፅዳትን ያስከተለ ነው27፡፡ በጉራፈርዳ አማሮች ላይ ፣በሶማሊ እና በኦሮሞ ዘውጎች መካከል፣በጉጅ እና በጌዲኦ፣በቤኒሻንጉል እና በኦሮሞ፣በአማራ እና ትግሬ፣በወላይታ እና ሲዳማ፣ማስቃን እና ማረቆ፣ቀቤና እና ጉራጌ ዘውጎች መሃከል የሚታየው ግጭት መነሻው በህገመንግስት የተደገፈው የጎሳ ፖለቲካ ነው፡፡

በዘውግ ዘይቤ ላይ ብቻ የቆመው ህገ-መንግስት ከሁለት ዘውግ የሚወለዱ/ረሳቸውን በዘውግ ማንነት ለመግለፅ የማይፈልጉ የሃገሪቱን ህዝቦች እንደሌሉ የሚቆጥር ነው፡፡ እነዚህ እንደሌሉ የተቆጠሩ እና ከዘውግ ፖለቲካው የተገለሉ  ህዝቦች ደግሞ ቁጥራቸው ቀላል የሚባል አይደለም፡፡ጥቂት የማይባል ቁጥር ያለውን የህብረተሰብ ክፍል ባገለለ ፖለቲካዊ ማዕቀፍ ውስጥ ሆነ የፖለቲካ መረጋጋት ማምጣት፣ስር ከሰደደ ድህነት ወጥቶ  የኢኮኖሚ እድገት ማስመዝገብ ያስቸግራል፡፡ ለእድገት አካታች ፖለቲካ ያስፈልጋል፡፡እንዲህ ያሉ ችግሮችን ያልፈታች ኢትዮጵያ ህልውናዋም አደጋ ላይ ነውና ሽግግር አደረገች ማለት አይቻልም፡፡ ሃገር ለማሻገር የመጀመሪያው ስራ መሆን ያለበት ሁሉንም ሃይሎች ባሳተፈ መንገድ የጎሳ ፖለቲካን የሚያበረታቱ  ህገ-መንግስታዊ አንቀፆችን ማሻሻል የሚቻልበትን መንገድ መፈለግ ነው፡፡

 1. የመሬት ባለቤትነት ጥያቄ

የኢትዮጵያ ህዝብ ለመሬት ባለቤትነት ከመጨረሻው የውዳዊ አገዛዝ ዘመን ጀምሮ እስካሁን ካሉትሶስት መንግስታት ጋር የታገለ ቢሆንም እስከ ዛሬ ድረስ የመሬት ባለቤትነቱን ሊያረጋግጥ አልቻለም28::የፊውዳሉን ስርዓት የተካው የወታደራዊው ስርዓት መሬት ለዓራሹ የሚለውን መፈክር አንግቦ በተደረገ ትግል ወደስልጣን የመጣ እንደመሆኑ መሬትን የህዝብ የግል ሃብት የማድረግ እርምጃ ይወስዳል የሚል ተስፋ ተጥሎበት ነበር፡፡ሆኖም ደርግ የፊውዳላዊውን ስርዓት የመሬት ስሪት ቀየረ እንጅ የመሬት ባለቤትነትን ወደ ህዝብ የግል ንብረትነት አላሻገረም29፡፡ይልቅስ በመሬት ከበርቴው ተይዞ የነበረውን የመሬት ባለቤትነት ወደ ወታደራዊው መንግስት ባለቤትነት ቀየረው፡፡ ደርግ ይህን ሲያደርግ ከፊውዳሉ ስርዓት በተሻለ ለአርሶ አደሩ በመሬት የመጠቀም መብት ሰጥቷል30፡፡

ደርግን የተካው ኢህአዴግ ወደ ስልጣን ሲመጣ የመሬት ባለቤትነት እንደ ደርግ ዘመኑ ሁሉ የመንግስት እንደሆነ በሽግግሩ ዘመን አውጆ የሽግግሩ ዘመን ሲልቅያም በህገ-መንግስት ይህንኑ አፅንቷ፡፡በኢህአዴግ የመሬት ፖሊሲ አርሶ አደሩም ሆነ የከተማ ነዋሪ ህዝብ በመሬት የመጠቀም እንጅ የባለቤትነት የመሆን መብት የለውም፡፡መሬትን በመጠቀም መብቱ መሬቱን እያረሰ ወይም እያከራየ መጠቀም ይችላል እንጅ መሸጥ መለወጥ ወይም መሬቱ አስይዞ መበደር አይችልም31፡፡ እንዲህ ያለው ሙሉ ባለቤትነትነ የማይፈቅደው የመሬት ፖሊሲ ምርታማነትን ለማሳደግ ማነቆ ከመሆኑም በላይ ገበሬው የግብርና ምርትን ለማሳደግ አስፈላጊ የሆነውን የተፈጥሮ ሃብት እንዲንከባከብ የማያበረታታ ነው32፡፡

ሌላው ችግር ለአርሶ አደሩ የተሰጠው ማከራይትን እና ማውረስን የጨመረው በመሬት የመጠቀም መብት ራሱ ሙሉ በሙሉ አስተማማኝ አይደለም፡፡ በሃገሪቱ የተለያዩ ክልሎች አርሶ አደሩ በያዘው መሬት የመተቀም መብቱን ለማስጠበቅ የተለያዩ ቅድመሁኔታዎችን ያስቀምጣሉ፡፡ ለምሳሌ የትግራይ ክልል ህገ-መንግስት አርሶ አደሩ መሬቱን ማውረስ የሚችለው በእርሱ ስር ለሚተዳደሩ ራሳቸውን ላልቻሉ ልጆቹ ብቻ እንደሆነ ይደነገግጋል፡፡በተመሳሳይ የአማራ ክልል ህገ-መንግስት አርሶ አደሩ በመሬቱ ላይ እየተጠቀመ የመቆየቱ ነገር መሬቱን ለመንከባከብ በሚያደርገው ጥረት ይወሰናል፡የአፈሩን ለምነት የሚያስጠብቁ እንደ ዛፍ መትከል እና ለመሬቱ ጎጅ ያልሆኑ ሰብሎችን ማብቀል የመሬቱን ባለቤትነት ለላማጣት እንደ ግዴታ ተቀምጦበታል33፡፡

ሌላው ትልቁ የመሬት ፖሊስው ችግር መሬትን የመሸንሸን ፣የማከፋፈል እና አስፈላጊ ሲሆንም የመውሰድ መብት ሙሉ በሙሉ ለመንግስት(ለክልል የፓርቲ ካድሬዎች) መሰጠቱ ነው34፡፡ ይህ  አርሶ አደሩ በመሬት ባለቤትነቱ እንዳይተማመን ያደርጋል፡፡ እንዳስፈላጊነቱ መንግስት ካመነበት በየጊዜው የሚደረገው ዳዲስ የመሬት ሽንሸና  እንደሚኖር የሚያዙ ክልሎች አሉ፡፡  ለምሳሌ  የአማራ ክልል እስካሁን ሁለት ጊዜ፣የትግራይ ክልል አንድ ጊዜ  የመሬት ሽንሸና አድርጓል፡፡በሽንሸናው ወቅት ለአርሶ አደሮቹ የሚደርሰውን የመሬት መጠን የሚወስኑት አካባቢው ካድሬዎች ናቸው35፡፡ተደጋጋሚ የመሬት ሽንሸናው የአርሶ አደሮችን መሬት መጠን  ይበልጥ እያሳነሰው ስለሚሄድ በዘመናዊ ቴክኖሎች ተጠቅመው እንዳያርሱ ይከለክላል፤ይህም ምርታማነት ይበልጥ እንዲያሽቆለቁል ያደርጋል፡፡ እንደ አማራ ክልል ያሉ ክልሎች እስካሁን ሁለት ጊዜ የመሬት ሽንሸና ማድረጋቸው የአርሶ አደሩ በመሬት ባለቤትነቱ እንዳይተማመን ከማድረጉም በላይ ምርታማትን ይቀንሳል፡፡

ከሁሉም የከፋው ደግሞ አርሶ አደሮቹ መንግስት መሬቱን ለልማት በፈለገው ጊዜ ከመሬታቸው መነሳት እንዳለባቸው የሚደነግገው ህግ የሁሉም ክልሎች ህግ መሆኑ ነው35፡፡ ይህ ህግ አርሶ አደሩን አንዳንዴ ያለበቂ/ያለምንም ካሳ ከመሬቱ ላይ ተፈናቅሎ ለከፋ ችግር እንዲዳረግ ያደርጋል፡፡ ሃገራችን ከሁለት አመት በፊት ያስተናገደቸው ህዝባዊ አመፅ መነሻው ይህ ህግ ነው፡፡ለአዲስ አበባ ከተማ መስፋፋት ሲባል አርሶ አደሮች ከቀያቸው ሊያነሳ የሚችል እርምጃ ከመንግስት ሊወሰድ መሆኑ ሲታወቅ በመላው ኦሮሚያ ረዥም ጊዜ የዘለቀ ህዝባዊ አመፅ እንዲደረግ ገፋፍቷል፡፡

በከተሞች በሊዝ የሚሰጠው የመሬት ይዞታም ሆነ በገጠር ያለው ይዞታ በብሄር ፖለቲካው ሳቢያ የአካባቢው ተወላጅ ያልሆኑ ሰዎች ተረጋግተው እንዲሰሩ የሚያስችል አይደለም፡፡የዘር ፌደራሊዝሙ ክልሎችን የተወላጅ ዘውጎች ብቻ ናቸው የሚል እሳቤን ስለፈጠረ ከሃገሪቱ የተለያየ ቦታ ተጉዘው ባልተወለዱበት ክልል የመሬት ይዞታ ያላቸው ሰዎች በመሬቱ የመጠቀም መብታቸው አጠያያቂ ነው፡፡ በተለያየ ወቅት በከተሞችም ሆነ በገጠር ሰዎች ንብረት ካፈሩ በኋላ ከአካባቢያችን ለቃችሁ ወደክልላችን ሂዱ እየተባሉ ሃብት ንብረታቸውን ተቀምተው ወደ ድህነት እንዲገቡ ሆኗል፡፡ ስለዚህ የመሬት ፖሊሲው ከዘውግ ፖለቲካው ጋር ተደምሮ የዜጎችን ተዘዋውሮ የመስራት መብት የሚገድብ በመሆኑ ለሃገር እድገት ትልቅ ተግዳሮት ነው፡፡

 1. ሃገራችን የምትመራበት ሥርዓተ-መንግስት

የሽግግር ወቅቱ ካከተመበት ወዲህ ሃገራችን በፓርላመንታዊ የመንግስት እንድትመራ ህገ-መንግስቱ ይደነግጋል36፡፡ በፓርላመንታዊ ስርዓት ከአሸናፊው ፓርቲ የሆነ ጠቅላይ ሚነስትር በፓርላማ ይመረጣል፡፡ጠቅላይሚኒስትሩ/ሯ በኩሉ/ሏ ሚኒስትሮችን ይሾምና/ትሾምና  ሹመቱ በፓርላማ ይፀድቃል፡፡በዚህ መንገድ አሸናፊው ፓርቲ የሃገሪቱን ህግ አውጭ እና አስፈፃሚው አካል ይቆጣጠራል፡፡እንዲህ ያለውን አሰራር የሚፈቅደው ፓርላመንታዊ ስርዓት በህግ አውጭው እና በአስፈፃሚው መሃከል ሊኖር የሚችውን ፍትጊያ ስለሚቀንስ ዲሞክራሲን በመሰረቱ ሃገሮች በተለይ የተረጋጋ መንግስት ለመፍጠር ተመራጭ ነው37፡፡ በተጨማሪም ይህ አይነቱ መንግስታዊ ስርዓት ቁጥራቸው በዛ ያሉ ፓርቲዎች እና ብዙ ዓይነት የፖለቲካ አመለካከት ለሚራመድበት ሃገር የሚመከር የመንግስት አይነት ነው፡፡ ምክንያቱም በሃገራቱ ፖለቲካ ያለው የሃሳብ ብዝሃነት መብላላት የሚችለው ፓርላማው ውስጥ ስለሆነ ነው38፡፡

ሆኖም ፓርላመንታዊ ስርዓትን ለረዥም ዘመን ስታካሂድ የኖረችው ሃገራችን ከላይ የተጠቀሱትን ስርዓቱን ቱርፋቶች ልታጣጥም አልቻልችም፡፡ ይልቅስ ፓርላመንታዊ ስርዓቱ ለአንድ ፓርቲ አምባገነንነት ህጋዊ ሽፋን የሚሰጥ፣ወደ መጨረሻዎቹ አመታት በተለይ የሃሳብ ብዝሃነት ፈፅሞ የጠፋበት፣ህግ አውጭውን ፍፁማዊ በሆነ የህግ አስፈፃሚው ተፅዕኖ ውስጥ የሚከት ሆኖ ኖሯል፡፡ ከዚህ የምንረዳው የመንግስት ስርዓት ብቻውን የአንድን ሃገር መንግስት አሰራር ዲሞክራሲያዊ ሊያደርገው እንደማይችል ነው፡፡ ይልቅስ ሃገሮች ፓርላመንታዊ ወይም ፕሬዚደንታዊ የመንግስት መዋቅር ከመመስረታቸው የበለጠ ሃገራቱ የሚገኙበት የፖለቲካ ባህል፣የዲሞክራሲ ተቋማት ጥንካሬ ዲሞክራሲያዊ ፖለቲካ በማራመዱ በኩል ትልቅ አስተዋፅኦ አለው39፡፡ በዓለማችን በሁለቱም አይነት የመንግስት አወቃቀሮች የተመሰረቱ መንግስታት ስኬታማ የሆነም ያልሆነም ዲሞክራሲን የመመስረት ሂደት ማስመዝገባቸው ለሃሳቡ ማጠናከሪያ ነው፡፡

በፕሬዚደንታዊ የመንግስት አወቃቀር ስኬትን ያስመዘገቡ ሃገራት አነስተኛ የፓርቲ ቁጥር ያላቸው እና የዲሞክራሲ ተቋማቶቻቸው ጠንካራ የሆኑ እንደ አሜሪካ ያሉ ሃገራት ናቸው፡፡ሆኖም እንደ አሜሪካ ባሉ ዲሞክራሲ በዳበረባቸው ሃገራትም በፕሬዚደንታዊ የመንግስት አወቃቀር ተፈጥሮ ሳቢያ የሚገጥሟቸው ተግዳሮቶች አሉ40፡፡ ከነዚህ ውስጥ በህግ አውጭው እና አስፈፃሚው መሃከል በሚኖር ፍትጊያ ምክንያት ህጎችን ለማውጣት፣በጀት ለማፀደቅ፣የአስፈፃሚውን ሹመት ለማፅደቅ መዘግየት ሊኖር መቻሉ ነው፡፡ ሌላው ችግር የፕሬዚደንት ምርጫ የሚደረገው በቀጥታ በህዝብ ተሳትፎ በመሆኑ በፕሬዚደንቱ/ቷ በኩል ጊዜው ሳይደርስ የስጣን መልቀቅ ጥያቄ ቢነሳ ወይም ፕሬዚደንቱ የፓርላማውን አመኔታ በማጣቱ ሳቢያ በኢምፔችመንት የሚወገድበት ሁኔታ ቢፈጠር ወዲያው ሃገራዊ ምርጫ ማድረጉ አስቸጋሪ ስለሚሆን የሃገሪቱ ላለመረጋጋት ልትዳረግ ትችላለች፡፡በዚህ ረገድ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር በአንድ ምክንያት ከሃላፊነት ቢነሱ ሃገራዊ ምርጫ ሳያስፈልግ በፓርላማ ወዲያወኑ ተተኪ ጠቅላይ ሚኒስትር መሾም የሚያስችለው ፓርላመንታዊ ስርዓት ተመራጭ ነው፡፡

የሃገሮች የመንግስት መዋቅር ፓርላመንታዊ ወይም ፕሬዚደንታዊ መሆኑ በራሱ እና ለብቻው የሚፈጥረው ችግር እንደሌለ ይልቅስ ችግሩ የሚነሳው ሃገሮች ከቆዩበት የፖለቲካ ባህል እና የዲሞክራሲ ግንባታ ጥልቀታቸው እንደሆነ ከላይ ተገልጧል፡፡ በዚህ ረገድ ሃገራችን በአንድ ፓርቲ አምባገነንነት ስር የቆየች እንደመሆኗ መንግስታዊ አሰራሩም በዚሁ ቅኝት ኖሯል፡፡ ፓርላመንታዊ ስርዓትን ስንከተል የኖርን ብንሆንም ይህንኑ የሚከተሉ ሌሎች ሃገራት የገኙትን የዲሞክራሲ ቱርፋት እና የመልካም አስተዳደር እሴቶች ማግኘት አልቻልንም፡፡ስለዚህ ሃገራችን በአንድ በኩል ጠንካራ የዲሞክራሲ ባህል ሳትገነባ  የፓርላመንታዊ ስርዓትን በመከተሏ ሳቢያ  በፓርላማ ውስጥ ስር ሰዶ ከኖረው የአንድ ፓርቲ አምባገነንነት የአሰራር ዘይቤ መውጣት ሲኖርባት በሌላ በኩል በፓርላመንታዊ ስርዓቱ የነበረውን የአስፈፃሚው ከባድ ተፅዕኖ ተላቃ በአስፈፃሚው እና በህግ አውጭው መሃከል ጤናማ የሃሳብ ፍጭት አድርጎ ውሳኔዎችን የሚያሳልፍ መንግስት ሊኖራት ያስፈልጋል፡፡ይህን ገቢራዊ ለማድረግ ፓርላመንታዊም ፕሬዚደንታዊም የመንግስት አወቃቀሮች ለብቻቸው ሲቆሙ የሚያመጡትን  ችግሮች ቀንሶ ነገር ግን የሁለቱንም ቱርፋቶች የሚያስገኝላትን ከፊል ፕሬዚደንታዊ ስርዓትን(Quasi-presidential) የሚከተል የመንግስት መዋቅር ቢኖራት ተመራጭ ይሆናል፡፡

በከፊል ፕሬዚደንታዊ ስርዓት ፕሬዚደንቱ በቀጥታ ሃገራዊ ምርጫ ድምፅ አሰጣጥ ሲ/ስትመረጥ ጠቅላይ ሚኒስትሩ/ሯ ደግሞ  በፓርላማ ብዙ ወንበር በያዘው ፓርቲ አቅራቢነት በፓርላማ ትመረጥ/ይመረጥና ተጠሪነቷ/ቱ ለፓርላማውም ለፕሬዚደንቱ/ቷም ይሆናል፡፡ የካቢኔ እጩዎች በፕሬዚደንቷ/ቱ እና በጠቅላይ ሚኒስትሯ/ሩ ይቀርብና በፓርላማ ይፀድቃል፡፡ይህ በፕሬዚደንታዊ የመንግስት መዋቅር የሚታየውን በህግ አውጭ እና አስፈፃሚ መሃከል ያለውን ፍትጊ ከመቀነሱ ባሻገር ለፕሬዚደንቱ የሚሰጠው  ስልጣን ስላለ በፓርላማ ብዙ ወንበር ያለው ፓርቲ አምባገነን እንዳይሆን ሚዛን ለማስጠበቅ ይረዳል፡፡በተጨማሪም ፕሬዚደንቷ/ቱ እና ጠቅላይ ሚነስትሩ/ሯ ከአንድ ፓርቲ ላይሆኑ ስለሚችሉ በሃገራችን በከፍተኛ ሁኔታ ተጣብቆ የሚገኘውን የመንግስት እና የገዥ ፓርቲ ጥምር አሰራር ተፅዕኖ ይቀንሰዋል፡፡ በከፊል ፕሬዚዳንታዊው የመንግስት ስርዓት የሃገሪቱ ፕሬዚደንት በሁሉም የሃገሪቱ ህዝቦች የምት/የሚመረጥ በመሆኑ በዘውግ ፖለቲካ ለተከፋፈለችው ሃገራችን ዘውግ ዘለል የመሪ ምርጫ ፈለግ ይዞ ስለሚመጣ ለሃገር አንድነት የሚሰጠው ጥቅም ይኖረዋል፡፡

ለ. ህገ-መንግስታዊ ያልሆኑ ችግሮች

 1. የካድሬ ፖለቲካ የባለሙያ አስፈፃሚዎችን ቦታ መተካቱ

ኢህአዴግ ሲመራው በኖረው የሃያ ሰባት አመት የፖለቲካ ታሪካችን የመንግስትን ፖሊሲ ለማስፈፀም አስፈላጊው ነገር ሙያዊ እውቀት እና ልምድ ሳይሆን የፖለቲካ ታማኝነት እንደሆነ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በፓርላማ ተገኝተው ከመናገራቸውም በላይ በተግባር ሲታይ የኖረ ነው፡፡ በዚህሳቢያ ፓርቲው በተደጋጋሚ ብርቱ የማስፈፀም ችግር እንዳለበት ሲገልፅ ኖሯል፡፡ በዚህም ምክንያት የሃገሪቱ  ህዝብ ለረዥም ዘመን በመንግስት አገልግሎት እንዳይረካ አድርጎት ከመኖሩም በላይ በሃገሩ ተስፋ እንዲያጣ እና ስደትን እንዲመርጥ አድረጎት ኖሯል፡፡ከፖለቲካዊ ታማኝነት በቀር ያለ በቂ እውቀት ስልጣን ላይ የተቀመጡ የኢህአዴግ ካድሬዎች ከማስፈፀም ውስንነትቸው በተጨማሪ ከመንግስት ባለስልጣን የማይጠበቅ ሌብነት ውስጥ የገቡ እንደሆኑ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር የመንግስት ሌቦች እንዳስቸገሯቸው በተናገሩበት የፓርላማ ውሎ ገልፀው ነበር፡፡ የመንግስት ባለስልጣናት የማስፈፀም አቅም ደካማነት እና ሌብነት ህዝቡ አሁን የታየውን ለውጥ ለማምጣት እንዲታገል ገፍቶታል፡፡

ሆኖም ከለውጡ በኋላም በህግ ተርጓሚው እና እንደ ምርጫ ቦርድ ያሉ አንዳንድ የዲሞክራሲ ተቋማትን እንዲመሩ ጥቂት ባለሙዎች ከመሾማቸው በዘለለ የመንግስት አስፈፃሚ ክንፍ አሁንም በገዥው ፓርቲ ካድሬዎች እንደተያዘ ነው፡፡ ነገር ግን አሁን ኢትዮጵያ እንዳለችበት ባለ የሽግግር ሁኔታ ባለበት ወቅት በቀድሞው ስርዓት የነበሩ ካድሬዎችን በነበሩበት ማስቀመጥ ሶስት ዋነኛ ጉዳቶች  አሉት41፡፡  አንደኛው ስኬታማ ለውጥ ለማድረግ የለውጥ ወቅት በዓለም አቀፍ እና ሃገር አቀፍ ደረጃ  ከፍተኛ እውቀት እና ልምድ ባላቸው ባለሙያዎች ጥምር ክንድ የሚመራ አመራር ያስፈልጋል42፡፡ ሁለተኛ በቀድሞው ስርዓት በዋና ዋና ቦታዎች ሲሰሩ ነበሩ ሰዎች ህዝቡን ለለውጥ ባነሳሱ ወንጀሎች ላይ የመሳተፍ ዕድላቸው ከፍ ስለሚል እነሱን በነበሩበት የስልጣን እርከን ላይ የሚያየው ህዝብ የለውጡን እውነተኝነት በመጠራጠር ለሌላ እውነተኛ ለውጥ ለመታከል ሊከጅል ይችላል፡፡ ይህ ደግሞ ሃገሪቱ ወደ ሌላ ብጥብጥ እንድታመራ ሊያደርግ ይችላል፡፡ በሶስተኝነት በቀድሞው ስርዓት ያለ እውቀት እና ልምድ በመንግስት ከፍተኛ ስልጣን ቦታ የተቀመጡ ሰዎች ለውጡ ወንበራቸውን እና ጥቅማቸው ሊያሳጣቸው እንደሚችል አስበው ለለውጠሉ አለመሳካት ሊሰሩ ይችላሉ፡፡ በአሁኑ ወቅት በሃገራችን የተለያዩ ክልሎች የሚነሱ ግጭቶችን ተከትሎ የቀድሞ ባለስልጣናት መታሰር እና ከስልጣን መነሳት ለለውጡ ቅልበሳ እንደሚሰሩ  አመላካች ነው፡፡ስለዚህ ከለውጡ በፊት በፖለቲካ ታማኝነታቸው ብቻ የሲቪልም ሆነ የውትድርና ስልጣን ይዘው የኖሩ የኢህአዴግ ካድሬዎችን ከስልጣናቸው ተነስተው ስራውን በሚያውቁ ባለሙያዎች መተካት አለባቸው፡፡ በተጨማሪ የሲቪክ ማህበራት(የሙያ፣የወጣቶች፣ የሴቶች..) መሪዎች ካድሬ ባልሆኑ ገለልተኛ ሰዎች መመራት አለባቸው፡፡

በፓርቲ ካድሬዎች እግር የሚተኩት ባለሙያዎች በሃገር ውስጥም ሆነ በውጭ ሃገር የሚገኙ የማንኛውም ፓርቲ ወገንተኝነት የሌላቸው መሆን አለባቸው፡፡ በውጭ ሃገር የሚገኙ ባለሙያዎች ወደሃገራቸው መጥተው ለተወሰነ ጊዜ ሃገራቸውን የማሻገሩን ስራ በሙያቸው እንዲያግዙ ሃገራዊ ጥሪ ማድረግ ይቻላል፡፡በቀድሞው ስርዓት በብሄራቸው ወይም በፖለቲካ አመለካከታቸው ሳቢያ እንዲሰደዱ የተደረጉ ባለሙያዎችን ይቅርታ ጠይቆ በሽግግር ወቅቱ ሃገራቸውን እንዲያገለግሉ ቢደረግ ይበልጥ ስኬታማ ሽግግር ለማድረግ ይረዳል፡፡

 1. የመንግስት ባለስልጣናት ስለቀደመ ስራቸው ተጠያቂ እየሆኑ ያለበት መንገድ

አምባገነን መንግስታትን የጣለ ህዝብ በወደቀው ስርዓት ለተሰሩ ወንጀሎች እርምት እንዲሰጥ፣ወንጀለኞች ተጠያቂ እንዲሆኑለት፣ለደረሰበት በደል ካሳ እንዲደረግለት ይፈልጋል43፡፡ በሽግግሩ ወቅትም ሆነ ከሽግግር በኋላ ሃገሮች አስተማማኝ ሰላም እንዲኖራቸው ፍትህ እና እውነት አስፈላጊ ነገሮች ናቸው44፡፡ በሽግግር ወቅት እውነት ተመርኩዞ የሚሰጥ ፍትህ የተጠያቂነትን እና  የህግ የበላይነትን ባህል በሃገሪቱ ለማስረፅ ከማገዙም በላይ በቀደመው ስርዓት ወንጀል የሰሩ ባለስልጣናት ተጠያቂ መደረጋቸው ለአምባገነኑ ስርዓት መፍረስ አስተማማኝ ምልክት ነው45፡፡

ስለዚህ ወንጀል የሰሩ ባለስልጣናትን ተጠያቂ የማድረጉ ነገር በከፊል የሚደረግ ከሆነ በቀድሞው አምባገነን ስርዓት መፍረስ ላይ በማህበረሰቡ ዘንድ ያለው መተማመን በግማሽ ይሆናል፡፡አሁን እንደሚታየው በፍርድቤት መጥሪያ የጣባቸው ወንጀለኛ ባለስልጣናት ከሃገሪቱ ክልሎች በአንዱ መሽገው መቀመጣቸው የለውጡ መንግስት የሃገሪቱን ግዛቶች ሁሉ የማይቆጣጠር ደካማ ነው፤ለውጡም ሊቀለበስ የሚችል ያልፀና ነው የሚል እሳቤ በህዝብ ዘንድ ሊያድር ይችላል፡፡ በተጨማሪም ማህበረሰቡ ወንጀለኛ እንደሆኑ የሚያውቃቸው የቀድሞ ባለስልጣናት በከፊል ብቻ ተጠያቂ ተደርገው ከፊሎቹ  የለውጡን ሃይል ከሚመራው አዲሱ ስርዓት ጋር ሲሰሩ የሚታይ ከሆነ ህዝቡ በለውጡ ላይ ያለው እምነት እየተሸረሸረ ሄዶ ቀስበቀስ ወደ ጥርጣሬም ሊገባ ይችላል፡፡ ይህ ደግሞ በህዝቡ ዘንድ ሌላ የትግል ምዕራፍ እንደሚጠብቀው እንዲያስብ አድርጎ ሌላ የብጥብጥ ምዕራፍ ሊያስከትል  ይችላል፡፡

ስለዚህ የቀድሞ መንግስት ባለስልጣናትን ተጠያቂ የማድረጉ አካሄድ የሚሸፍነው የጊዜ ሁኔታ፣በዋናነት ትኩረት የሚያደርግበት የወንጀል አይነት ሁሉ ግልፅ መደረግ አለበት፡፡ ለምሳሌ መንግስት የቀድሞ ባለስልጣናትን በሰብዓዊመብት ጥሰት ሲከስ ክሱ በይረርጋ የማይታገድ ስለሆነ ከኢህአዴግ ወደስልጣን መምጣት ጀምሮ በተፈፀሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ላይ የተሳተፉ መስሪያ ቤቶችን የመሩ የቀድሞ ባለስልጣና ሁሉ ተጠያቂ መሆን አለባቸው፡፡

ሐ. የሽግግር እርምጃዎቹን ለመውሰድ የሚገጥሙ ተግዳሮቶች እና የቢሆን መፍትሄዎች

ተግዳሮት አንድ፡ ለውጡን የማፅናት/ወደ ታችኛው የመንግስት መዋቅር የማስረግ ችግር

በአሁኑ ወቅት ሃገራችን የጀመረችው የሽግግር ሁኔታ ከላይ የተጠቀሱትን የሃገሪቱን መሰረታዊ ችግሮች ለመቅረፍ የሞከረ አይደለም፡፡ ያም ሆኖ እንኳን ለውጡ ወደታችኛው የመንግስት መዋቅር የሰረገ አይደለም፡፡ይህ ለውጡን ሊቀለብስ የሚችል ትልቅ ተግዳሮት ነው፡፡ ህገ-መንግስትን ማሻሻልን ጨምሮ በዚህ ፅሁፍ የተነሱ ዋነኛ የፖለቲካ ችግሮች የሚፈታ ሽግግር ለማድረግ ሲሞከር ደግሞ ሽግግሩን በማስረግ እና በማፅናት በኩል የበለጠ ተግዳሮት ሊገጥም እንደሚችል እሙን ነው፡፡ስለዚህ በዚህ ፅሁፍ ላይ ለተነሱ ችግሮች እልባት የሰጠ ሃገር የማሻገር ስራውን  በሁሉም ደረጃ ማስረግ የሚያስችል መንገድ መፈለግ አለበት፡፡የለውጡን አላማዎች የሚያስፈም የፖለቲካ ፓርቲዎችን ፣የሲቪክ ማህበራትን፣ታዋቂ ግለሰቦችን፣ከተለያየ የትምህርት መስክ የተውጣጡ ምሁራንን  በአባልነት ያቀፈ   ተቋም ማዋቀር ለለውጡ መፅናት እና ለሽግግሩ ስኬት እጅግ አስፈላጊ ነው46፡፡

ይህ ተቋም ለሽግግሩ ስኬት በጣም አስፈላጊ ስለሆነ ለውጡን ለማፅናት፣ሽግግሩን ለማፋጠን  ሊያግዙ የሚችሉ ስራዎችን ሁሉ ሊሰራ የሚችልበት ስልጣን ሊሰጠው ይገባል፡፡ ከነዚህ ስልጣኖች ውስጥ በሽግግሩ ወቅት የሚነሱ ብጥብጦችን ምንጭ አጥንቶ፣ አፋጣኝ መፍትሄ የሚያመጣ መፍትሄ ለመንግስት ማቅረብ አንዱ እና በአሁኑ ወቅት እጅግ አስፈላጊው ነገር  ሊሆን ይችላል፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ለለውጡ እንቅፋት የሚሆኑ ሃይሎችን እንቅስቃሴ ተከታትሎ ለህግ ማቅረብ፡፡የሃገሪቱ ፖለቲካ ችግር ምንጭ የሆኑ የህግ፣የፖሊሲ ማዕቀፎችን እና ሌሎች የሃገራችን ፖለቲካ ባህል ችግሮችን ነቅሶ አውጥቶ የሃገሪቱ የፖለቲካ ሃይሎች እና መላው ህዝብ በችግሮቹ ምንነት ላይ ከተነጋገረ በኋላ የሚለወጡበትን መንገድ ማመቻቸት ሌላው የተቋሙ ሃላፊነት ቢሆን ሽግግሩን በሰላማዊ መንገድ ለማስኬድ ይረዳል፡፡በዚህ ስራው ተቋሙ የዲሞክራሲ ተቋማትን የመገንባት ስራ ሰራል፣ መከለስ ያለባቸውን ህገ-መንግስታዊ አንቀፆች፣የምርጫ ህጎች፣እየመጣ ያለው ሃገራዊ ምርጫ የሚደረግበትን ወቅት የሚወስን ሁሉን አቀፍ ሃገራዊ ውይይቶችን አዘጋጅቶ ብዙሃኑን ያስማማ ሃገራችን ወደዲሞክራሲያዊ ስርዓት የምትሻገርበትን አቅጣጫ ተግባራዊ ያደርጋል፡፡ በለውጡ አስፈላጊነት እና ስኬት ላይ ሃገራዊ ውይይቶችን መድረጉ ለለውጡ ከላይ ወደታች ለማስረግ ይረዳል፡፡

አንድ ሃገር ከአምባገነን አስተዳደር ወደ ዲሞክራሲ ለምታደርገው ሽግግር ስኬታማነት ወታደሩ፣ፖሊሱ እና ሌሎች ህግ አስከባሪ እና አስፈፃሚ አካላት ትልቅ ሚና አላቸው45፡፡ ለውጡን እና ሽግሩን ስኬታማ በማድረጉ ረገድ እነዚህ አካላት ገንቢ አስተዋፅኦ እንዲያበረክቱ በለውጡ አስፈላጊነት ላይ በእውቀት ላይ የቆመ እምነት እንዲኖራቸው ያስፈልጋል፡፡ይህን እውን ለማድረግ ለሽግግሩን ለማፅናት የሚቋቋመው ተቋም በሃገሪቱ ክልሎች ሁሉም ደረጃ ላሚገኑ የህግ አስከባሪ እና አስፈፃሚ አካላት የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠናዎችን በመስጠት የሽግግሩ ተባባሪ እንጅ አደናቃፍ እንዳይሆኑ መስራት ይችላል፡፡ በሃገራችን የሚታዩ ብጥብጦች አንዳንዴ በፖሊሶች ጭምር የሚታገዙ እንደሆኑ የቡራዩው ግድያ ተጎጅ ቤተሰቦች እና የዓይን ምስክሮች የገለፁት ነው፡፡ ሃገራችን በዘውግ ፖለቲካ ውስጥ የኖረች እንደመሆኗ እነዚህ ህግ አስከባሪዎች ጭምር በዘውግ ላይ የተመሰረቱ ግድያዎችን እና ብጥብጦችን ለማስቆም ተነሳሽነት ለማሳየት ተቸግረውል፡፡ ይህን ችግር ለመፍታት ይህ አመለካከት ከህግ ማስከበር ጋር እንደማይሄድ፣ለሃገርም እጅግ አደገኛ እንደሆነ  በዚሁ የተነሳ እንደ ሩዋንዳ ያሉ ሃገሮች የደረሰባቸውን ጥፋት በሚያሳይ ሁኔታ በማስተማር የሚበጀው ለዲሞክራሲያዊ ሽግግር መስራቱ እንደሆነ ባስተማር ያስፈልጋል፡፡

ተግዳሮት ሁለት፡ የፖለቲካ ሃይሎች በሽግግሩ ሂደት እና ዓላማ ላይ ስምምነት ማጣት

በሃገራችን በርካታ የፖለቲካ ፓርቲዎች ቢኖሩም አሰላለፋቸውን ዘውግ ተኮር እና ዘውግ ዘለል ብሎ  ለሁለት መክፈል ይቻላል፡፡   ፖለቲካ የሃገራችን ፖለቲካ ሁነኛ ችግር  እነዚህ ተገዳዳሪ የፖለቲካ ሃይሎች ልዩነታቸው እንዳለ ሆኖ ለሃገር ህልውና እንከዋን ቢሆን በጋራ የሚሰሩለት አላማ ሊኖር አለመቻሉ ነው፡፡በሃገሪቱ ስር ሰዶ የኖረው ለዘውጉ ጥቅም  የሃገሪቱን መፈራረስ ጭምር ታሳቢ የሚያደርገው የዘውግ ፖለቲካ ለዚህ ትልቅ አስተዋፅኦ አለው፡፡ የዘውግ ፖለቲካን የሚያራምዱ የሃገራችን የፖለቲካ ሃይሎች  የህገ-መንግስቱን መከለስም ሆነ የምርጫውን ዘመን መሸጋገር እንደማይስማሙበት ይናገራሉ፡፡ እንዲህ እያሉም ለዲሞክራሲ ስፍነት እንደሚታገሉ ይገልፃሉ፡፡ዘውግ ዘለል የፖለቲካ ሃይሎችም በበኩላቸው ለዲሞክራሲ ስፍነት እንደታገሉ ይገልፃሉ፡፡ ይህ ሁለቱን በሰፊ የልዩነት ላይ ያሉ  የፖለቲካ ሃይሎች ሊያገናኝ የሚችል አንድ እና ብቸኛ ለማለት የሚያስደፍር ነጥብ ነው፡፡

ዘውግ ተኮርም ሆነ ዘውግ ዘለል ፓርቲዎች ለዲሞክራሲ እታገላለሁ ካሉ የዲሞክራሲዲሞክራሲ መርሆዎችን የሚጥስ አካሄድን ማበረታታት የለባችም፡፡ ዲሞክራሲ ማግለል መርሁ አይደለም፡፡ የዘውግ ፖለቲከኞች እንዳይቀየር የሚፈልጉት ህገ-መንግስት ደግሞ ከሁለት እና በላይ ዘውግ የተወለዱ እና/ወይም ራሳቸውን በዘውግ ማንነት የማይገልፁትን በርካታ የሃገሪቱን ህዝቦች ከሃገሪቱ ፖለቲካ የሚያገል ብቻ ሳሆን ለመኖራቸውም እውቅና የማይሰጥ ነው፡፡ በዚህ ሁኔታ እንዴት ዲሞክራሲያዊ ሃገር መገንባት እንደሚቻል ለህዝብ ክፍት የሆነ ፣በሚዲያዎች በቀጥታ የሚተላለፍ ሃገራዊ ክርክር ማድረግ ያስፈጋል፡፡ ይህ ክርክር የሃገራችን የፖለቲካ ፓርቲዎች በዲሞክራሲያዊ ሽግግር ላይ ያላቸው አቋም በደጋፊዎቻቸው ዘንድ በጠራ ሁኔታ እንዲታይ ያደርጋል፤ ሃገራችን ለዲሞክራሲ በምታደርገው ሽግግር ላይ የተጋረጡ እሳቤዎችም እንዲስተካከሉ ያደርጋል፡፡ ስለዚህ የዲሞክራሲ እነዚህ ሁለት ሃይሎች የፖለቲካ አመለካከት ልዩነታቸው እንዳለ ሆኖ ዲሞክራሲያዊት ሃገርን ለመገንባት በሚደረገው እንቅስቃሴ መተባበር ይችላሉ፡፡

ተግዳሮት ሶስት፡ የካድሬ ፖለቲካን በባለሙያ በመተካት በኩል ያለ ችግር

ኢህአዴግ ፓርቲን እና መንግስትን አዋህዶ ሲያስተዳድር የኖረ ፓርቲ ነው፡፡ወደስልጣን የመጣው የለውጥ ሃይል በተወሰነ ደረጃ ባለሙዎችን ወደ ዋኛ የስልጣን እርከኖች እያመጣ የሚገኝ ቢሆንም አሁንም ዋነኛ የማስፈፀም ስልጣኖች በተለይ የፌደራል እና የክልል ካቢኔዎች በፓርቲው ካድሬዎች እንደተያዙ ናቸው፡፡ የለውጥ ሃይሉ እነዚህን የስልጣን ቦታዎች በባለሙያዎች ለመተካት የሚያደርገው ጥረት ከፓርቲው ካድሬዎች ተቃውሞ ሊገጥመው ይችላል፤ከፓርቲው መስመር መውጣት ተደርጎም ሊታሰብ ይችላል፡፡ ይህን ችግር ለመፍታት ሃገሪቱ በአሁኑ ወቅት ያለችው አማራጭ በሌለው የለውጥ እና የሽግግር ወቅት እንደሆነ፣የቀድሞው አካሄድ እንደ ፓርቲም ሆነ እንደ ሃገር ለመቀጠል የማያስችል እንደሆነ በፓርቲ ደረጃ ተነጋግሮ አቋም መያዝ ያስፈልጋል፡

መደምደሚያ

በአሁኑ ወቅት ሃገራችን ለሚቀጥሉት በርካታ አመታት የምትጓዝበትን መንገድ በሚወስን ታሪካዊ ሁኔታ ላይ ትገኛለች፡፡ ከዚህ ቀደም ሁለት የሽግግር ወቅቶችን ብናሳለፍም ወደ ዲሞክራሲያዊ አስተዳደር መጓዝ አልቻልን፡፡የዚህ ዋነኛ ምክንያቱ በሽግግር ወቅት ስልጣን የያዙ መንግስታት ዲሞክራሲን ለመገንባት የሚያስችል ሁሉን አቀፍ የፖለቲካ ማዕቀፍ መፍጠር ስላልቻሉ ነበር፡፡ በአሁኑ ወቅት ስልጣን ከያዘው ከመንግስት በኩል  ዲሞክራሲን ለመገንባት የሚያስችሉ ሁኔታዎችን ከመፍጠሩ አንፃር በጎ ዝንባሌ ይታያል፡፡  ስለዚህ የሽግግር መንግስት የመመስረት ነገር ውስጥ መግባት ሳያስፈልግ ሃገሪቱን ከአንድ ፓርቲ አምባገነን አስተዳደር ወደ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ የሚያሻግሩ ስራዎችን መስራት ይቻላል፡፡

ይህን በጎ አጋጣሚ ተጠቅሞ ሃገሪቱን ለማሻገር በሃገሪቱ ፖለቲካዊ ምህዳር  ለዲሞክራሲ ስፍነት ጋሬጣ ሆነው የቆዩ ችግሮችን መለየት ያስፈልጋል፡፡ የጎሳ ፖለቲካ/ፌደራሊዝም፣የመሬት ባለቤትነት ጥያቄ፣ሃገራችን የምትመራበት የመንግስት ስርዓት፣ኢህአዴግ ለሃያ ሰባት አመት ያራመደው የፓርቲ ፖለቲካ ባህል ሃገራችን ወደ ዲሞክራሲያዊ ፖለቲካ እንዳትገባ የከለከሉ ዋነኛ ችግሮች ናቸው፡፡

ህገ-መንግስታዊ መሰረት ያለው የጎሳ ፖለቲካው ሃገሪቱ በማንኛውም ሰዓት የምትፈራርስበትን፣ ክልሎቿም በፈለጉት ሰዓት ወደ ብዙ የዘውግ ክልሎች የሚሸነሸኑበትን ሁኔታ ህግ አድርጎ ያስቀምጣል፡፡ ይህ የህዝቦችን አንድነት፣ የሃገርን ህልውና(ሰላም)እንደ ቅድመ-ሁኔታ ለሚፈልገው የዲሞክራሲ አስተዳደር ምስረታ ትልቅ እንቅፋት ነው፡፡ ሃገራችን በአሁኑ ወቅት በከባድ ዘውግ ተኮር ግጭት እና የሃገር ውስጥ ስደት በመታመስ ላይ ትገኛለች፡፡ ይህ ባልተወገደበት ሁኔታ ዲሞክራሲያዊ ሽግግር ማድረግ አይቻልም፡፡

የመሬት ባለቤትነትን ለብሄር ብሄረሰቦች እና  መንግስት የሚሰጠው የሃገራችን ህገ-መንግስት ከዘውግ ፌደራሊዝሙ ጋር ሲጣመር ከትውልድ ቦታቸው ወደሌላ ክልል ሄደው በሚሰሩ የሃገራችን ህዝቦች እና በሄዱበት አካባቢ ተወላጆች ዘንድ ዘውግን ያማከለ ግጭት እንዲነሳ እያደረገ ይገኛል፡፡ ይህ ሁኔታ  ለኢኮኖሚ እድገትም ሆነ ለዲሞክራሲያዊ ስርዓት ትልቅ ተግዳሮት ነው፡፡

የፓርላመንታዊ የመንግስት ስርዓት በራሱ ችግር ባይሆንም ሃገራችን ከኖረችበት ዲሞክራሲ የራቀው የፖለቲካ ባህል አንፃር የአንድ ፓርቲ አምባገነንነትን ለማስፈን መንገድ ተደርጎ ኖሯል፡፡ ከዚህ ችግር ለመውጣት የፓርላመንታዊውንም የፕሬዚደንታዊውንም የመንግስት ስርዓት ጠንካራ ጎኖች ለመጠቀም በሚያስችለው በግማሽ ፕሬዚደንታዊ(Quasi-presidential) ስርዓት ሃገራችን እንድትመራ ቢደረግ  የአንድ ፓርቲ አምባገነንነትን ለማስወገድ ይረዳል፡፡ ይህ አይነቱ አስተዳደር  በዘውግ በተከፋፈለው ህዝብ ዘንድ ተቀባይነት ባገኘ በአንድ ተመራጭ ፕሬዚደንት ስር እንዲተዳደር በማድረግ የጎሳ ፖለቲካውን ለማርገብ ያስችላል፡፡

ያለንበት የሽግግር ወቅት እውቀት ያላቸውን ዜጎች አስተዋፅኦ የሚሻ ስለሆነ ኢህአዴግ የኖረበት በፖለቲካ ታማኝነት ብቻ ሃገር የማስተዳደር ዘይቤ ተቀይሮ በካድሬዎቹ ቦታ እውቀት እና ሰፊ ዓለም አቀፍ/ሃገር አቀፍ ልምድ ባላቸው ሰዎች መተካት አለበት፡፡ በተጨማሪም በቀድሞው አስተዳደር ሁኔታ ወንጀል የሰሩ የመንግስት ባለስልጣናት ያለምንም አድሎ ለህግ መቅረብ አለባቸው፡፡ ይህ በህዝቡ ዘንድ ለለውጡ እውነተኝነት ማመሳከሪ ተደርጎ የሚወሰድ ነገር ነው፡፡ የፍድቤት መጥሪያ ወጥቶባቸው እያለ በትግራይ ክልል ተደብቀው የሚገኙ ባለስልጣናት ተይዘው ወደፍርድ መቅረብ አለባቸው፡፡ ይህ ካልሆነ መንግስት የሃገሪቱን ክልሎች ሁሉ ማስተዳደር የማይችል ተደርጎ ሊወሰድና ሌላ ብጥብጥ ሊነሳ ይችላል፡፡ ይህ ደግሞ ለውጡን ሆነ ሽግግሩን ይጎዳል፡፡

እነዚህን ችግሮች መርምሮ በቀጣይ ዘመናት በሃገሪቱ የፖለቲካ ስርዓት ውስጥ ህልውና እንዳይኖራቸው ማድረግ በአሁኑ ወቅት ለሃገራችን ሽግግር  የሚያስፈልግ ዋነኛ ስራ ነው፡፡ችግሮቹን አቃሎ ወይም ፈትቶ በሚቀጥለው ምርጫ ወደስልጣን ለሚመጣው መንግስት ለዲሞክራሲ መንገድ የጠረገች ሃገር ማስረከብ ከተቻለ የሚመጣው መንግስት ስራ ዲሞክራሲ ስር እንዲሰድ የሚያደርጉ ስራዎችን መስራት እና ሃሪቱን ከድህነት የሚያወጡ ፖሊሲዎችን መተግበር ይሆናል፡፡ ይህ ሃገሪቱ ከአምባገነንነት አዙሪት ወጥታ ወደ ዲሞክራሲያዊ የፖለቲካ ባሕል ግንባታ እንድትገባ ያስችላታል፡፡

ይህን ገቢራዊ ለማድረግ ሃገራችን ያላት ብቸኛ መንገድ ዲሞክራሲያዊ ስርዓትን መመስረት ብቻ እንደሆነ በሁሉም የፖለቲካ ሃይሎች እና በህዝቡ ዘንድ መስማማት ላይ መደረስ አለበት፡፡ ስምምነቱ ለዲሞክራሲያዊ ስርዓት መፈጠር ችግር የሆኑ ታሪካዊ፣ህገ-መንግስታዊ እና የገዥው ፓርቲ የፖለቲካ እና አስተዳደር ባህል እንዲቀየሩ ማስቻል አለበት፡፡ይህን ለማድረግ የሽግግሩን/ለውጡን የሚያስፈፅም ሃገራዊ ተቋም መገንባት ያስፈልጋል፡፡ተቋሙ የተልዕኮውን ትልቅነት የሚመጥን ስልጣን ሊሰጠው ይገባል፡፡የለውጡን አላማ በሁሉም ደረጃ ማስረፅ፣በሃገራችን  ዲሞክራሲን ለመገንባት ደንቃራ በሆኑ ችግሮች ላይ ሃገራዊ ውይይት አድርጎ እንዲለወጡ መስራት፣ የለውጡን ተግዳሮቶች ተከታትሎ ማስወገድ፣የምርጫ ህጎችን ማሻሻል፣የሃገራችን ቀጣይ ምርጫ መደረግ ያለበትን ቀን ለመወሰን የሚያስችል ሃገራዊ ውይይት ማካሄድ ከስልጣኖቸ መካከል ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ የዚህ ተቋም ከነዚህ ስልጣኖች ጋር መምጣት አሁን በስልጣን ላይ ያለው መንግስት በአንድ በኩል በርካታ የፀጥታ እና የኢኮኖሚ ችግር ያለባትን ሃገር በመምራት በሌላ በኩል ለውጡን በመምራት እና የሃገሪቱን ሽግግር በማፅናት ሁለት ትልልቅ ሚናዎች ከመወጠር ይታደገዋል፡፡

ለአስተያየት meskiduye99@gmail.com

End notes

Crisis Group, Ethiopia: Ethnic Federalism and its DiscontentsAfrica Report No 153, November 4, 2009,Nirobi/Brussels, P.29 ; African Studies Center, Political Culture in Ethiopia: A balance sheet of post 1991 ethnically based Federalism, Info sheet, April 8,2010, p.3-4

2 Semahagn Gashu, The Last Post-cold war socialist Federation; Ethnicity, Ideology and Democracy in Ethiopia, University of connecticut, 2014, p.167;

Geddes, et al, Autocratic Breakdown and regime transition; perspective on politics,2014, p. 37

lowenthal and Bitar, From Authoritarian rule to democratic governance: Learning from political leaders, Stockholm,2015, P.50-53

Gracia, Adressing social change in situation of violent conflict: A practitioner perspective, Berghof Handbook dialogue, 2006, p. 4

6 Ibid,P.5-7

Alem Habtu, Multiethnic Federalism in Ethiopia: A study of the secession clauses in the constitution, Queens college,2005, p.11-23; John Young, Regionalism and democracy in Ethiopia, Third world quarterly, vol 19፣ No 2, p. 195-203; ዘውዱ ውብእንግዳ፣ የፌደራላዊ መንግስትታሪካዊ አመጣጥ እና የመንግስት ግንባታ ችግሮች በኢትዮጵያ፣ 2009፣ገፅ. 253-259;Semahagn Gashu,The Last Post-cold war socialist Federation; Ethnicity, Ideology and Democracy in Ethiopia, University of connecticut, 2014,p.78-82; African Studies Center,P.1-2;

ዘውዱ ውብእንግዳ፣ የፌደራላዊ መንግስት ታሪካዊ አመጣጥ እና የመንግስት ግንባታ ችግሮች በኢትዮጵያ፣2009፣ ገፅ. 256

9 Gracia, Adressing social change in situation of violent conflict: A practitioner perspective, 2006, p. 4 and 5

10 Ibid, p.10

11 Anna Louise, Factors Affecting Success or Failure of Political transitions, Helpdesk Report, 2017, p.6-8

12 Gracia, Addressing social change in situation of violent conflict: A practitioner perspective, 2006, p.2-9

13  ዘውዱ ውብእንግዳ፣ የፌደራላዊ መንግስት ታሪካዊ አመጣጥ እና የመንግስት ግንባታ ችግሮች በኢትዮጵያ፣ 2009፣ ገፅ. 249፤ Crisis Group, Ethiopia: Ethnic Federalism and its DiscontentsAfrica Report No 153, November 4, 2009, p.3-4

14 Ibid, p.249-53; African Studies Center, Political Culture in Ethiopia: A balance sheet of post 1991 ethnically based Federalism, Info sheet, April 8,2010, p.1-3

15 ዘውዱ ውብእንግዳ፣ የፌደራላዊ መንግስት ታሪካዊ አመጣጥ እና የመንግስት ግንባታ ችግሮች በኢትዮጵያ፣2009፣ ገፅ. 250

16 Semahagn Gashu, The Last Post-cold war socialist Federation; Ethnicity, Ideology and Democracy in Ethiopia, University of connecticut, 2014, p.25

17 ዘውዱ ውብእንግዳ፣ የፌደራላዊ መንግስት ታሪካዊ አመጣጥ እና የመንግስት ግንባታ ችግሮች በኢትዮጵያ፣2009፣ ገፅ.258፤

18 Ibid, p. 258-260፤ Alem Habtu, Multiethnic Federalism in Ethiopia: A study of the secession clauses in the constitution, Queens college,2005, p.319

19 የኢትዮጵያ ህገመንግስት፣ 1995፣ አንቀፅ 47፣ ንዑስ ቁጥር 3፣ ከ “ሀ” – “ሠ”

20 Semahagn Gashu, The Last Post-cold war socialist Federation; Ethnicity, Ideology and Democracy in Ethiopia, University of connecticut, 2014, p.156

21 Ibid

22ዘውዱ ውብእንግዳ፣ የፌደራላዊ መንግስት ታሪካዊ አመጣጥ እና የመንግስት ግንባታ ችግሮች በኢትዮጵያ፣2009፣ ገፅ. 258-259

23 Semahagn Gashu, The Last Post-cold war socialist Federation; Ethnicity, Ideology and Democracy in Ethiopia, University of connecticut, 2014, p.155

24 Ibid,165-187

25 Yash Ghai, Autonomy and Ethnicity: Negotiating competing clams in multi-ethnic states, Cambridge University Press,2000,p.11 ; Murat Somer, Cascade of ethnic polarization: Lessons from Yugoslavia, annals of the American academy of political and social science,Vol.573,Sage Publication,2001,p.128-129; ዘውዱ ውብእንግዳ፣ የፌደራላዊ መንግስት ታሪካዊ አመጣጥ እና የመንግስትግንባታ ችግሮች በኢትዮጵያ፣ 2009፣ ገፅ. 254-255

26 Semahagn Gashu, The Last Post-cold war socialist Federation; Ethnicity, Ideology and Democracy in Ethiopia, University of connecticut, 2014, p.165-168

27 ዘውዱ ውብእንግዳ፣ የፌደራላዊ መንግስት ታሪካዊ አመጣጥ እና የመንግስት ግንባታ ችግሮች በኢትዮጵያ፣2009፣ ገፅ. 252

28 Wibke Crewett et.al, Land Tenure in Ethiopia: Continuity and Change, Shifting Rulers, and the Quest for State Control, CGIAR System wide Program on Collective Action and Property Rights (CAPRi), C/- International Food Policy Research Institute, Working Paper No. 91,2008, pp.5-19

29 Daniel Ambaye, Land Rights Expropriation, Stockholm, Springer publication, 2015, p.29

30 Belay Zerga, Land Resources, Uses and Ownership in Ethiopia : Past, present and Future, International Journal of Scientific research and engineering Trends, V.2,Issue 1, 2016, P.19

31 Desalegn Rahmato, Searching for tenure security?: The land system and new policy initiatives in Ethiopia, FSS Discussion paper, 2000, p.2

32 USAID/Ethiopia, Ethiopia Land Policy and Administration Assesment,Report,2004, P.ix

33 Desalegn Rahmato, Searching for tenure security?: the land system and new policy initiatives in Ethiopia, FSS Discussion paper, 2000, p.4

34 Belay Zerga, Land Resources, Uses and Ownership in Ethiopia : Past, present and Future, International Journal of Scientific research and engineering Trends, V.2,Issue 1, 2016, P.20 and 22

35 Ibid, P.20

36 የኢትዮጵያ ህገመንግስት፣1987፣ አንቀፅ ….

37Kaare Strøm et.al, Delegation and Accountability in Parliamentary Democracies, Oxford University press, 2006, P. 3-8

38 Scott Mainwaring, presedentialism, multiparty systems, and democracy: the difficult equation, University of Notre Dame, working paper #144, 1990 p.3

39 José A. Cheibub, Presidentialism, Parliamentarism, and Democracy, University of Illinois Cambridge University Press,2007, p.2

40 Scott Mainwaring, presedentialism, multiparty systems, and democracy: the difficult equation, University of Notre Dame, working paper #144, 1990 p.6

41 Gracia, Adressing social change in situation of violent conflict: A practitioner perspective, Berghof Handbook dialogue, 2006, p. 4

42 Ibid, P.5

43 Sanam Naraghi et.al, Transitional Justice and Reconciliation, A toolkit for advocacy and action, 2007,p.1

44 Julie Macfarlane, working towards restorative justice in Ethiopia, cardozo j. of conflict resolution ,2007,vol. p.487.

45 Sanam Naraghi et.al, Transitional Justice and Reconciliation, A toolkit for advocacy and action, 2007,P.2-3

46 Sarsar,M.C, Tunisia: Revolution as a new form of political transition persuasion,  Italian Institute of International Political studies, Analysis N.o 194, 2013,p.3-4

47 Awad, Breaking out of Authoritarianism: 18 months of political transition in Egypt, Constellations, 2013, p.289