የአድዋ ድል የሁላችንም ነውአስገራሚዎቹ የሀዲያና የከምባታ ዘማቾች በአድዋ

በአፄ ዳግማዊ ምኒልክ የጦር አበጋዞች የከምባታና የሀዲያን ክልል ህዝቦችን ለማስገበርና በማእከላዊ መንግሥት ስር ለማጠቃለል በ1882 አም የተጀመረው የጦርነት ዘመቻ የተጠናቀቀው በ1885 አም ላይ ሲሆን ከሶስት አመታት በሁዋላ በተቀሰቀሰው የአድዋ ጦርነት ላይ ገና ከቁስላቸው ያላገገሙት የክልሉ ህዝቦች ለአገራቸው ነፃነትና ሉአላዊነት ስሉ በግንባር ቀደምትነት ተሰልፈው ተዋግተዋል፣ ከፍተኛ መስዋዕትነትም ከፍለዋል። የአድዋ ጦርነት የክተት አዋጅ በአፄ ዳግማዊ ምኒልክ የታወጀው በመስከረም ወር 1888 አም ነበር። የክተት አዋጁ እንደታወጀ የጎጃም፣ የቤጌምድር ፣የወሎና የላስታ ህዝብ ከ300 እስከ 500 ኪሎሜትር ያህል፣ የሸዋ፣ የሐረር ፣ የባሌ፣ የአርሲ፣ የከምባታና ሀዲያ፣ የሲዳሞ፣ የጅማ፣ የከፋ፣ የወላይታ፣ የወለጋና የኢሉባቡር ጦር ደግሞ ከ600 እስከ 1,000 ወይም 1,500 ኪሎሜትር ድረስ ርቀት ያለውን አገር በእግሩ እያቋረጠ ቀንና ሌሊት፣ ሃሩርና ቁር ሳይገታው አቀበቱንና ቁልቁለቱን እየወጣና እየወረደ ያለማወላወል ለወሳኙ ጦርነት ወደሰሜን የጦርነት ግንባር እንደተጓዙ የአካባቢው ተወላጅ የሆነው የዲልባቶ ደጎዬ ፅሁፍ ያስረዳል።

የከምባታና የሐዲያ ክልል የገባር ገበሬ ሠራዊትን በዋና የጦር አበጋዝነት የመሩት በ1888 አም የክልሉ ገዥ የነበሩት የአፄ ምኒልክ ያክስት ልጅ የነበሩት ደጃዝማች በሻህ አቦዬ ነበሩ። የከምባታን ዘማቾች የመሩት በወቅቱ የከምባታ ባላባት የነበሩት ቀኛዝማች ሞሊሶ ሄላሞ ድልበቶ ሲሆኑ ከእርሳቸው ጋር የዘመቱትን የከምባታ ገበሬ ጦረኞች የተሟላ ዝርዝር ለማግኘት ባንችልም 1) ላላምዳ መሎሮ፣ ከሄጎ ጌዮጣ፣ 2) አበጋዝ ትሮሬ ዋዶሌ፣ ከቃጫ፣3) ጌንቤራ ግዴቦ፣ ከደጋ ቀዲዳ፣ 4) ወልደማርያም ባጂ ፣ከገረምባ፤ 5/ መልከቶ ለታ ለቾሬ፣ ከሰረራ መዝመታቸውን የከምባታ አዛውንት አረጋግጠዋል። የሐዲያ ዘማቾች የተመሩት በፊታውራሪ ጌጃ ገርቦና በሌሎችም የሐዲያ መሪዎች እንደነበር ይነገራል፣ በጽሑፍ የተቀመጠ መረጃ ስለሌለን የዘማቾቹን ብዛትና የስም ዝርዝር ለማቅረብ አልተቻለም። በነበረው የዘመቻ ልማድ መሰረት ደጃዝማች በሻህ አቦዬ ወንድ ሴት ሳይባል በብዙ ሺህ የሚቆጠር የከምባታና የሀዲያን ገበሬ ሠራዊት ይዘው አድዋ ከደረሱ በሁዋላ ዳግማዊ ምኒልክ በሰጡዋቸው መመሪያ መሰረት ቀድመው የጠላትን ምሽግ የከበቡና ያስጨነቁ ጀግና ሰው እንደነበሩ ይተረካል።

ደጃዝማች በሻህ አቦዬ የከምባታና የሐዲያ ጀግኖችን አስከትለው በአድዋ የጦር ሜዳ በአምባ ኪዳነምህረት ግንባር ከኢጣሊያ የጦር አዛዥ ከጄኔራል አልቤርቶኒ ጦር ጋር በተደረገው ብርቱ ትንቅንቅ በከፍተኛ ወኔና ጀግንነት ሲዋጉና ሲያዋጉ ሳለ በጠላት ጥይት ተመትተው የወደቁ ስመጥር የጦር ሰው ነበሩ። በመሪ አዝማቻቸው ሞት የተቆጩት ጭፍሮቻቸው ከጦርነቱ ፍፃሜ በሁዋላ ብዙ የኢጣልያ ምርኮኞችን ለአፄ ምኒልክ በማስረከብ ፈንታ በበቀል መፍጀታቸው በታሪክ ተመዝግቦ ይገኛል።

የአድዋ ጦርነትና የተገኘው አንፀባራቂ የኢትዮጵያውያን ድል መላውን አለም ያስደነቀ የታሪክ ክስተት ነበር፣ ለዝንተአለም የሚቆይ ታሪካዊ ድል። የአንዲቷ አፍሪቃዊት ነፃ አገር ኢትዮጵያ በኃይል ነፃነቷን ለመግፈፍ፣ ግዛቷን ለመድፈርና በሕዝቦቿ ላይ የተገዥነት ቀንበር ለመጫን ባህር ተሻግሮ የመጣን ጠላት የካቲት 23/1888 አም አድዋ ላይ ድባቅ መታች፣ ድል አደረገች። ከሁለት ሺህ አመታት በፊት ሀኒባል በሮማውያን ላይ ካገኘው ድል በማያንስ ሁኔታ በአለም ያስተጋባውና ኢጣልያኖችን ያሸማቀቀው የአድዋ ድል አፍሪቃ በአውሮጳ ላይ እንዳገኘው ድል የሚቆጠር ታላቅ የተጋድሎ ውጤት ነበር፣ ነውም። የአድዋ ድል የከምባታና የሐዲያ እንዲሁም የሌሎች ክልሎች ህዝቦች ሁሉ የአንድነት፣ የህብረትና የመስዋዕትነት ውጤት ከመሆኑም በላይ ማናቸውንም ተመሳሳይ ብሔራዊ ወይም አገርአቀፍ ችግርና ፈተና ለመቋቋምና በድል ለመወጣት የምንችለው እንደአድዋው ወቅት በህብረትና በአንድነት ስንቆም ብቻ እንደሆነ የሚያረጋግጥ ታሪካዊ ድል ነው። በሌላ አንፃር ብዙ ሺህ ኢትዮጵያውን ውድ ሕይወታቸውን የሰውበት ጦርነት ስለነበር ለበርካታ ሺህ ቤተሰቦች በመላ አገሪቱ የመሪር ሐዘን ወቀት እንደነበር መዘንጋት የለበትም። ሆኖም ለነፃነት የተከፈለ ውድ ዋጋ ነበር፣ ነፃነትም ምንኛ ውድ እሴት እንደሆነ ምንጊዜም መዘንጋት አይኖርብንም። አዎን፣ “ነፃነት ነፃ አይደለም”(“Freedom is not free”).

ምንጭ:- ዲልባቶ ደጎዬ

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s