ጅጂን ለመታደግ ግብረኃይል ይቋቋም! (መስቀሉ አየለ)

ተቀማጭነቱ በአሜሪካን አገር የሆነው የአድማስ ሬዲዮ ኒዮርክ ድረስ ተጉዞ ለረጅም ግዜ አነጋጋሪ በነበረው የጅጅ ህይወት ዙሪያ አጠር ያለ ዘገባ በመስራት በአይነ ህሊና ሲማትሯት ለነበሩ አድናቂዎቿ ጆሮ የሚሆን የጥቂት ደቂቃ የቃላት ልውውጦች በመቅረጸ ድምጽ አስቀርቶ ከማሰማትም ባለፈ ከመድረክ የተሰወረችበት ዋነኛው ምክንያት በገጠማት የጤና እክል መሆኑን በመጥቀስ ” ጅጅ በጣም ብዙ ጽሎትና ትንሽ እርዳታ ትፈልጋለች ” ሲል ዝምታውን ሰብሮታል። ጋዜጠኛው የራሱን ግዜ ወስዶ ይኽን ያህል አመት እንቆቅልሽ የነበረውን የጅጅን ሁኔታ በከፊል ማሳወቅ በመቻሉ አድናቆት ሊቸረው ይገባል።

ጅጅ የኢትዮጵያን ሙዚቃ ወደሌላ ከፍታ የወሰደችና ገና ወደፊትም ይዛን ብዙ ልትጓዝ የምትችልበት የጸጋ ጥግ ላይ ሳለች እንዲህ እንቅፋት ሲመታት እርሷ ያለችበትን ትክክለኛ እውነት ፈልጎ በማወቅና “የቤተሰቧንም ሆነ የእርሷ ፕራይቬሲ ሊጠበቅላቸው ይገባል” በሚሉ ተጻጻሪ ኩነቶች መካከል ተወጥረን ብዙ መስቀል አስተኩሰናል። ነገር ግን በአንድም በሌላም የዚህች የንጋት ኮከብ ችግር ሳይፈታ ምናልባትም ከድጡ ወደማጡ እየሆነ እዚህ ደርሷል።ዛሬ ደግሞ ይኽ ባይተዋርነት አንድ ነጥብ ላይ ሊቋጭ ይገባል ስንል ዝም ብለን አይደለም።

ጅጅ የህዝ ሃብት ናት። ጅጅ የትናት ማንነታችንን የምናይባት እትሮኖስ፤ የዛሬውን ክፉ ቀን የምንሻገርባት ምርኩዛችን የነገውን ራእያችንን የምንሰንቅባት ሰባሰገል ናትና የእርሷ ጉዳይ የጥቂት ቤተሰቦቿ የግል ችግር ሆኖ የቆየበት አያያዝ እዚህ ላይ ሊያበቃ ይገባል። የሃገራችን ከያኔያን አንድ ነገር ሲገጥማቸው ወደ ሸህ አላሙዲን ማንጋጠጡ ለዛሬው እውነት የማይመጥንባቸው በርካታ ምክኛቶች እንዳሉ የታወቀ ነው። እንዲህ ያሉ የጥበብ ፈርጥችን በግዜው አለመታደግ ማለት ደግሞ ምን ማለት እንደሆነ ትናንት በአቶ ፍቃዱ ተክለማርያም ፍጻሜ የደረሰው የልብ ስብራት ገና በቅጡ አልተጠገንምና ከእርሱ መማር ያለብን ነገር እንዳለ ይሰማኛል።

ዝምታው በዚሁ ከቀጥርልር ለጅጅ ከዛሬ ይልቅ ነገ ይበልጥ የማይከብድበት አመክንዮ የለምና አንድ ነገር በፍጥነት እንዲተገበር የግድ ይላል። ስለዚህ ታዋቂ ሰዎች፣የኃይማኖት አባቶችና የጅጅ ቤተሰቦች እንዲሁም ማናቸውም “ቴዎድሮስ ተሾመ” ከተባለ የተስቦ ዓይነት ነጻ የሆኑ በሙዚቃውና በጥበቡ ኢንደስትሪ ውስጥ ያሉ ባለሙያዎችና የሚዲያ ሰዎች የተካተቱበት አንድ ሁነኛ ግብረኃይል ተዋቅሮ በቶሎ ወደ ስራ ሊገባ ይገባል።

ነፍሳቸው ለኪነጥበብ ምን ያህል ቅርብ እንደሆነ በዚህ አጭር ግዜ ውስጥ የታዘብን በመሆኑ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የዚህ ግብረኃይል ሰብሳቢ ቢሆኑ ፈርጀ ብዙ ጥቅም ይኖረዋል። ያም የማይቻል ከሆነ ደግሞ ከአንጋፋዎቹ ባለሙያዎች ጋሽ ማህሙድ ወይንም ቴዲ አፍሮ ቦታውን እንዲሸፍኑት ሊደረግ ይችላል።

ምንም ይሁን ምንም ግን ዝምታው እዚህ ላይ ያብቃ እና እንቁዋን እንታደግ። እርሷን መታደግ ታሪክንም፣ ኪነጥበቡንም መታደግ ነው።

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s