የኢትዮጵያ ልሂቅ Vs እስክንድር (አቤል ዋቤላ)

አቤል ዋቤላ

የኢትዮጵያ ልሂቅ የፖለቲካ ስልጣንን በመግራት ሂደት ውስጥ ከህዝብ ጎን ቆሞ አያውቅም። የፓሊቲካ ፓወርን ከተጋጨም የሚጋጨው በመንበሩ መቀመጥ ሲፈልግ ብቻ ነው። ከዚያ ውጭ መንግስት ጨቋኝ እና አምባገነን ሆኖ ዜጎችን እንዲረግጥ እጀታ (enabler) በመሆን ሲያገለግል ነው የኖረው። አጭበርብሮ ያገኛትን እፍኝ የማትሞላ እውቀት ያለ ልክ አጋኖ እና አሽሞንሙኖ ወደ ባለጊዜው በመጠጋት፣ ባለጊዜው በድፍረት እና በእብሪት ለሚወስደው እርምጃ አፕሩቫል በመስጠት እንጀራውን የሚያበስል ነው።

እስክንድር እድገቱ እና ትምህርቱ ከየትኛው ደጅ ጠኚ ልሂቅ በተሻለ ወደስልጣን ሊያቀርበው የሚችል ነበር። ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በስታንፎርድ የተማረ እና በአሜርካን ሀገር ፖለቲካን ያጠና ሆኖ ሳለ ህዝብን በመምረጡ ህዝብን በጋዜጠኝነት ማገልገል ከጀመረ ሰነባብቷል። ከህዝብ ጋር ያለውን ህብረት ፖለቲካል ስልጣንን ፊትለፊት በመጋፈጥ ጭቆናን በመቃወም አረጋግጧል። እስር፣ ግርፋት፣ እንግልት የፖለቲካ ስልጣን በኢትዮጵያ ስርዓት እንዲይዝ የሚያደርገውን ጥረት አልገቱትም።

አሁንም እየሆነ ያለው ይሄ ነው። ከሰባት ዓመታት እስር በኋላም እስክንድር ደከመኝ ብሎ የኢትዮጵያ ህዝብን ለጅብ አሳልፎ እንዲሰጥ አላደረገውም።

በህዝባዊ አመፅ ይቅርታ ጠይቆ ፍትሃዊ ምርጫ እስኪካሄድ ስልጣን የያዘው የአብይ አህመድ መንግስት ከምርጫ በፊት፣ አሁን ያለው ፓርላማ ፊት እንኳን ከመቅረባቸው በፊት መሰሪ የሆኑ አረመኔያዊ ተግባሮች እየፈፀመ ይገኛል። ከዚህ ውስጥ አንዱ የአዲስ አበባ ጉዳይ ነው። መንግስት ላጠፋው ጥፋት ይቅርታ ጠይቆ ለሽግግር ሲባል ብቻ የቆመ መሆኑን ዘንግቶት አውሬነት በተሞላ መልኩ ከተማዋን ስሪት እየሰራ ይገኛል። ይህንን ተግባሩን ልክ አይደለም የሚል የፖለቲካ ማኀበርም ሆነ ግለሰብ በጠፋበት ሰዓት የህዝብ ልጅ እስክንድር ነጋ እኔ አለኹ ብሏል።

ይህ በአርያነት ሁሉም ዜጋ ሊከተለው የሚገባ ተግባር ሆኖ ሳለ ልሂቁ የተለመደ የአድርባይነት እና እበላባይነት እድሉን የሚጨናግፍበት እየመሰለው ይቃዥ ጀምሯል። እስክንድርን ካልሰለጠነ የሞብ መሪ በማስተካከል ይተች ጀምሯል። የእስክንድርን የጋዜጠኝነት ስልት እና አክቲቪዝም መተቸት በራሱ ችግር የለውም። በዚህ ላይ ውይይት ማካሄድ ይቻላል። እንደኔ እንደኔ ይህ ዝንባሌ የልሂቁ የተለመደ ወራዳነት መገለጫ ነው። ከአውራ ሆድ አደር ልሂቃን እስከ አፍላ አንበጣ ልሂቃን(በወያኔ እስከ እስር፣ ስደት የሚደርስ ስቃይ የደረሰባቸው እና የአምናውን ባለጊዜ አበርቺ ልሂቅን አብዝተው ይተቹ የነበሩ) ሀገርን የመዝረፍ እቅዳቸው እንዳይፈርስ ሲሉ የሚያደርጉት ነው።

ይህ የልሂቃን መርከብ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ተለዋዋጭ እና አታላይ የአደባባይ ገፅታ ምክንያት በርካታ ባለሙያዎች እና እንደብርቱካን ሚደቅሳ ያሉ በቀድሞ ጊዜ የህዝብ ልጅነታቸውን ያስመሰከሩ ሰዎችን/ ልሂቃንን ጭኗል። ይህ የጎራ መደበላለቅ ፈጥሯል። እንደኔ እንደኔ አዲሱ አስተዳደር ምንም አይነት እገዛ የማያስፈልገው መፍረስ ያለበት መንግስት ነው የሚል ድምዳሜ ላይ አልደረስኩም። ከዚህ በመነሳት በሀገር ግንባታ ሂደት ውስጥ በባለሙያነት እና ከፍተኛም ሆነ ዝቅተኛ ኃላፊነቶችን በመውሰድ ሀገርን እና ለህዝብ የሚሰራ መንግስትን ማገልገል ተገቢ ነው ብዬ አምናለኹ። ይሁንና የጋራ ቤትን አብረው እየሰሩ ሳሉ በመንግስት የሚፈፀሙ ከባድ ጥፋቶችን ባላየ ባልሰማ ማለፍ አይገባም። ከቀድሞ የሀገሪቱ የቆየ ልማድ እና ባለፉት ወራት እንዳየነው ልሂቁ ከዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት በበረታ ዝምታ እና ክህደት ላይ ይገኛል።

ይህ የአድርባይነት እና አስመሳይነት ባህል ካልተሰበረ መቼም ቢሆን የፖለቲካ ስልጣንን መግራት አንችልም። ስለዚህ የእስክንድር ፈለግ ተከተለን እርሱን በርታ እያልን ሌሎች በመንግስት ውስጥ የሚገኙ እና ከመንግስት ውጭ ያሉ ሁሉንም አይነት ልሂቃንን በስም በመጥራት ማንቃት ይገባናል። እስክንድር የዚህ የሰለጠነ ማኀበረሰብ እሴት(የፖለቲካ ስልጣንን መግራት) መተከል ሂደት ምልክታችን እና የልሂቅነት ሞዴል ነው።

የጎሳ ፌደራሊዝምበቃሉ አጥናፉ ታዬ(ዶ/ር) ኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ

በቃሉ አጥናፉ ታዬ(ዶ/ር)
ኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ

ብዝሃነትን ለማስተናገድ እና ስልጣንን ወደ ታችኛው የመንግስት መዋቅር ለማከፋፈል የፌደራል ስርዓት ተመራጭ እንደሆነ እንዳንድ ፀሃፍት ቢያተቱም፤ በተቃራኒው ደግሞ የፌደራል ስርዓት በተፈጥሮዎ ግጭትን እንደሚጋብዝ እና ተመራጭ እንዳልሆነ የሚያትቱም ተመራማሪዎች አሉ(አለማንተ, 2003).

ብዝሃነትን ከማስተናገድ አንፃር እንዳንድ የአፍሪካ አገራት (ኮንጎ, ከ1960-1965፣ ማሊ, 1959፣ ኬንያ, 1963-1965፣ ዩጋንዳ, 1962-1966፣ ካሜሮን, 1961-1972) ከነጻነት በኃላ የፌደራል ስርዓት መርጠው መተግበር ቢጀምሩም አስከፊነቱን ተረድተው የፌደራል መዋቅርን ትተውታል(ኢርከ, 2014)፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ ሶስት የአፍሪካ አገራት(ደቡብ አፍሪካ፣ ናይጀሪያ፣ እና ኢትዬጲያ) በፌደራል ስርዓት የሚተዳደሩ አገራት ቢሆኑም የጎሳ የፌደራል ስርዓት የምትተገብረው  አገር በዓለም ላይ ኢትዬጲያ ብቻ ናት፡፡

ምንም እንኳን  የፌደራል ስርዓት በዘርፉ ተመራማሪዎች ዘንድ አወዛጋቢ ቢሆንም የጎሳ የፌደራል ስርዓት ግን ግጭትን እንደሚፈጥር እና አገርን እንደሚበትን ከአወዛጋቢነት ባለፈ የተረጋገጠ ሃቅ ነው፡፡ የጎሳ ፌደራሊዝም እንደ ዩጎዝላቪያ፣ የድሮዋን ሩሲያ(USSR)፣ ችኮዝላቫኪያን በመበታተን የሚታወቅ ስርዓት ሲሆን በእኛ አገርም እንዲተገበር የተፈለገበት ዋናው ምክንያት አገሪቱን ለመበታተን ታስቦ ነው፡፡ እኛ እና እነሱ፣ ነባርና መጤ፣ አፈናቃይና ተፈናቃይ በሚል የጎሳ ፖለቲካ ትርክት ውስጥ እንድንገባ ያደረገን የጎሳ ፌደራሊዝም ነው፡፡ አገርን በቋንቋ ከፋፍሎ ወጣቱ ለአገሩ ሳይሆን ለብሄሩ ብቻ ታማኝ እንዲሆን ያደረገው የጎሳ ፌደራሊዝም ነው፡፡ ጥርጣሬን፣ አለመተማመንን፣ ለጎሪጥ መተያየትን ያመጣው የጎሳ ፌደራሊዝም ነው፡፡ አገርን ብቻ ሳይሆን ቤተሰብን (ባልና ሚስትን፣ አባትን ከልጁ፣ ልጆችን ከወላጆች) እንዲለያዩ ያደረገው የጎሳ ፌደራሊዝም ነው፡፡

የኢትዬጲያ የጎሳ ፌደራሊዝም መስራቾች እና አቀንቃኞች አገሪቱን ለመበታትን የተጠቀሙበት ስልት እንደሆነ እየታወቀ፤ ይህን የጎሳ ፌደራሊዝም ማፍረስ ሲገባን በዶ/ር አብይ አስተዳደርም የብሄር ፖለቲካው፣ አድሎዓዊነት፣ ጎጠኝነቱ፣ መታየቱ እጅጉን ልብን ይሰብራል፡፡ ህወሃት የተጠቀመበትን የከፋፍለህ ግዛው የጎሳ ፖለቲካ እንዴት እንደነፃነት ምልክት አድርገን እንጠቀምበታልን? ሰብዓዊነትን ተላብስን፣ ኢትዬጲያዊነት ተጫምትን መቆም ሲገባን እንዴት ለጎሳ አባላቶቻችን ያደረግንላቸውን ነገር እንደ ታላቅ ጀብድ በሚዲያ እንተርካልን? ኢትዬጲያዊነት ሱስ ነው ብሎ የተረከ መሪ እንዴት ብሄርተኝነትን ያራምዳል? ልብ ይስጠን!!!

ጽንፈኞችን አንዴት አንታገላቸዉ !!!

ኢዮብ ሳለሞት

ከቅርብ ግዜ አንስቶ በሀገራችን በከፍተኛና በአስፈሪ ሁኔታ አንደወረርሽኝ እየተዛመተ ያለዉን በዜጎች ላይ ማንነትን መሰረት ያደረገ ጥቃት፤ማፈናቀል ፤በደቦ መግደል ፤ሀብት ንብረት መዝረፍ የእምነት ተቋማትን ማቃጠል ..ወ.ዘ.ተ በአፋጣኝ የሚቆምበት ሁኔታ ላይ ሃላፊነት የሚሰማቸዉ ዜጎች ካልተረባረቡ እጃቸዉን አጣጥፈዉ ሜዳዉን ፅንፈኞች አንዲጋልቡበት ከፈቀዱ ዉጤቱ ሶርያ፤የመን፤ሊቢያ፤ደቡብ ሱዳን ነዉ ፡፡ ምንም አንኳን የአበራሽን ጠባሳ ያየ በእሳት አይጫወትም ብንልም ሌት ተቀን በሰንት አሳር ፤ዉጣ ዉረድ በትዉልድ ቅብብሎሽ የተገነባችዉን መተኪያ የሌላትን ሀገራችንን አሳልፈን ለበላተኛ ለመስጠት እየተጣደፍን እንገኛለን ፡፡ አንገታችንን ዞር አድርገን አለም-አቀፉ ማህበረሰብ ሶርያና፤የመን ፤ሊቢያ ላይ የደገሰዉን ድግስ ጠጋ ብለን ብንመረምር ሀቁን እናገኘዋለን  የሶርያና የመን ፖለቲከኞች ፤ሊሂቃን ልዩነታቸዉን በጠረቤዛ ዙርያ ፈተዉ ሀገራቸዉንና ህዘባቸዉን ማዳን ሲችሉ ለዉጭ ጣልቃ-ገብነት ሌማታቸዉን በርግደዉ ዛሬ ሩሲያና፤አሜሪካ ጡንቻ ሚለካኩበት ዘመናዊ የወታደራዊ አቅርቦቶች የሚፈተኑበት ቤተ-ሙከራ ሆነዉ ቁጭ አሉ ሃያላኖቹ ጋር አንደዉ ዘላቂ ጥቅም አንጂ ቋሚ ወዳጅና ጠላት የላቸዉም መመሪያቸዉ ግልጥ ነዉ  የጂ-ኦ ፖለቲካ የበላይነት፤ጥሬ ሀብት ፤ርካሽ ጉልበት ፤ሸቀጦቻቸዉን ማራገፊያ ገብያ ማፈላለግ ነዉ የሚለዉ ፡፡ ዛሬም የተለያዩ የሃያላኑ ሀገራት ወኪሎች ቤታችን በተለያየ ዳቦ ስም እየጎበኙት ነዉ ሱዳን አሜሪካ አልበሽርን ወርዱ ስትል ሩሲያ ከአልበሽር ጎን መቆመዋን ለማወጅ ሰከንድ አልፈጀባትም  ሱማሊያ በአሜሪካ፤በኢራን፤በኳታር፤በሳዉዲ እምሮት ተዉጣለች ፤ ሀገራችን ኢትዮጲያችን ላይም አሜሪካ፤ፈረንሳይ፤ሩስያ፤ሳዉዲአርብያ፤ቱርክ ፤ኳታር አይናቸዉን ከጣሉባት ቆዩ ለነገሩ በዚህ ደረጃ አለም-አቀፉ ማህበረሰብ ሲጎመጅብን ዛሬ የመጀመሪያዉ አይደለም ትላንት  በሃይማኖት ፤ ሀገር በማዘመን ፤ በህክምና አቅርቦት ፤ በብድር ፤በወታደራዊ ድጋፍ አቡጀዲ ሞክረዉናል ፤ ዛሬ በርእዮተ-ዐለም ፤ በብድር አቅርቦት ፤ ሽብርተኝነት በመዋጋት ፤ በኢኮኖሚ ፍልስፍና ፤ በድህንት ቅነሳ ፤ በጤና ፤በዲሞክራሳዊ ስርአት ግንባታ….ወ.ዘ.ተ ዛጎል ዉስጥ ተደብቀዉ እዉነተኛ መልካቸዉ ሲገለጥ ግን ጥሬ-ሀብት ፤ርካሽ ጉልበት ፤የጂ-ኦ ፖለቲካ የበላይነት ፤ ገብያ ፍለጋ ነዉ ፡፡ ጥያቄዉ በዚህ ደረጃ አለም-አቀፉን አሰላለፍ ተገንዘበን አንዴት ምላሽ አንስጥ ነዉ  ቅደመ-አያቶቻችን በዲፕሎማሲም ፤በመረጃ የበላይነት ፤በወታደራዊ ሰልት ሁለንተናዊ በሆነ መልኩ በየአቅጣጫዉ ደልን የተገናጸፉበት ምክንያት በቅድሚ የቤት-ስራቸዉን በሚገባ ሰርተዉ በአለም-አቀፍ ደረጃ ለሚጠብቃቸዉ ተግዳሮት ራሳቸዉን በማዘጋጀታቸዉ ነዉ ፡፡  ዉስጣዊ ሽኩቻቸዉን ፤የወንበር(የስልጣን ሽሚያ) ቅራኔያቸዉን ባዳበሩት ሀገር-በቀል የግጭት አፈታት ባህል መሰረት አድረገዉ በይቅርታ ተካክሰዉ ጠላት ይጠቀምበታል የተባለዉን ቀዳዳ ሰፍተዉ በጋራ አቅማቸዉን በማይመች ሁኔታ ዉስጥ አስተባብረዉ ተጠቅመዉ ነዉ ፡፡ በቂ የመሰረተ-ልማት አቅርቦት በሌለበት ፤ የመገናኛ አዉታሮች ባልተዘረጉበት በአይነ-ስጋ ለመገናኝት አንኳን አባይ እስኪጎደል በሚጠበቅበት ፤ ህብረተሰቡ በተለያየ አስቸጋሪ መልከ-ምድር ተሰባጥሮ በሚኖርበት ፤ …ወ.ዘ.ተ በአንዚህ ሁሉ ተግዳሮቶች ዉስጥ አልፈዉ ሁሉም የበኩሉን ድርሻ ተወጥቶ ሀገርን ለትዉልድ አሻግረዋል ፡፡ ዛሬ እኛ በዘመነ ሉላዊነት አለም የአኗኗር  ዘይቤያችን በተለያዩ የቴክኖሎጂ ዉጤቶች የቀለለ መረጃዎች በሽርፍራፊ ሰከንዶች ከተለያዩ የአለማችን ክፍሎች በሚዘዋወሩበት ወቅት አፍንጫችን ሲመታ አይናችን እንባ አላመነጭ ብልዋል ፡፡ የአኩሪ ታሪክ፤ባህል፤እሴቶች ሆነን ሳለ በእጅ ያለ ወርቃችንን አንደመዳብ እየቀጠርን ካለን ግዙፍ ታሪክ፤ባህል፤እሴት የወረደ የማይመጥነን ድርጊት ፤የአኗኗር ዘይቤ ዉስጥ አንገኛለን ጽንፈኘት መለያችን ሆንዋል ፤ዘረኝነት ፤ጠባብነት ንባባችን ሆንዋል በቂ የሆነ መነሻ ካፒታል ይዘን ዛሬም አንራባለን እንጠማለን ይሄ ሁኔታ አንዲቀየር ሃላፊነት የሚሰማን ዜጎች የበኩላችንን ደርሻ ለመወጣት በቅድሚያ በእምንት፤በቋንቋ፤በነገድ ለምድ ተወሽቀዉ አፍራሽ ቅስቀሳ የሚያደርጉ ተኩላዎችን ፤ጽንፈኞችን አምርረን ልንዋጋ ፤አንጋለን ልንተፋቸዉ ይገባል ፡፡

ለመሆኑ የፅንፈኞች መለያ የትኞቹ ናቸዉ

 • በችግር-ፈቺ አስተሳሰብ ፤ በአማራጭ ፖሊሲ ሳይሆን ተፈጥሮአዊ በሆኑት ነገድ፤ቋንቋ፤ጎሳ፤እምነት ፤መልከዓ-ምድር አቀማመጥ መሰረት አድረገዉ አፍራሽ ቅስቀሳ ያካሄዳሉ ፡፡
 • በሀሰተኛ ትርክት ተመስርተዉ መለወጥ ፤ማሻሻል በማይቻለዉ ሁኔታ በትናትና ታስረዉ ወደኋላ 400 አመታት ሄደዉ ታሪክን ይበይናሉ ፤ይፈርጃሉ
 • የወቅቱን ተግዳሮት ለመፍታት የሚያችል ቀመር ፤ስትራቴጂ የማመንጨት እዉቀት፤ክህሎት ፤ዘዴ በአጠገባቸዉ የለም
 • የጽንፈኝነት በሽታ የሚያጠቃቸዉ ጠባብ ፖለቲከኞች፤ጥራዝ-ነጠቅ ሊሂቃን ፤ የሃይማኖት ተቋማት፤ የመገናኛ ብዙኋንና ባለሙያዎች አክትቪስት ካባ የሚሽቀረቀሩ ..ወ.ዘ.ተ

አንዴት አንታገላቸዉ

 • በተለያዩ የመገናኛ አማራጮች (በማህበራዊ ደረ-ገጾች፤በህትምት ዉጤቶች ፤በመካነ-ድሮች፤በብሮድካስት) የምንመለከታቸዉን ፤የምንሰማቸዉን መረጃዎች ከተለያዩ ምንጮች አበርይቶ ፍሬዉን ከገለባዉ በመለየት
 • ነገድን፤ጎሳን፤ቋንቋን ፤እምነትን መሰረት አድርገዉ የሚያንቋሽሹ ፤አንዱን አግዝፈዉ ሌላኛዉን የሚያኮስሱ መልእክቶች እግር-በእግር እየተከታተሉ ማዉገዝ ፤ተጨባጩን ሀቅ ማስረዳት ፤አንድነትን ፤መከባበርን የሚገልጹ መልእክቶችን ማኖር
 • ግለሰቦችን ፤ደርጅቶችን፤ ፓርቲዎችን የዚህና የዛ ህዘብ ፤እምነት ወኪል ነኝ ብለዉ በስሙ ተጣብቀዉ ከሚነገድቡበት ማህበረሰብ ነጣጥሎ ማየት
 • ሴጣንም አነሳዉ መልአክ ፤ ደጋፊያችን አነሳዉ ባላንጣችን ሀሳብን በችግር-የመፍታት አቅሙ ብቻ የመመዘን ባህል ማዳበር

ማጠቃሊያ ፡-በየትኛዉም ጎራ ያሉ ጽንፈኞች አስተደደራዊ ቅራኔዎች የነገድና የጎሳ መልክ በመስጠት እርስ-በእርስ ዘመናትን በክፉ በደጉም ግዜ ምራቅ ተላልሶ ልዩነቱን አንኳን ለመለየት እስኪያቅት ድረስ ተዋህዶ የሚኖረዉን ማህበረሰብ ለመለያየት ሲያደቡ ሃላፊነት የሚሰማዉ ማነኛዉም ዜጋ አጁን አጣጥፎ ማየት የለበትም ፡፡ እነሱ በጥቃቅን ልዩነቶች የቅራኔ መነሾ ሲያደርጉ ሃላፊነት የሚሰማወቸዉ ዜጎች ገድሞ ግዙፉን ያስተሳሰረንን አሴቶች መሰረት አድርገን አብሮነታችንን ማስቀጠል አለብን ፡፡ ጽንፈኞች ለእኩይ ዓላማ ተደራጅተዉ ሲንቀሳቀሱ እኛ ሃላፊነት የሚሰማን ዜጎች ለሀገር ህልዉና በአመለካከት ዙሪያ ተደራጅተን እግር-በእግር እየተከታተልን ሚና አልባ ማድረግ አለብን ፡፡

ኢዮብ ሳለሞት

eyobmind@gmail.com

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር፣ ሚዛናዊነት ከራስ ቢጀምር … (በዓለማዬሁ ገበዬኹ)

በዓለማዬሁ ገበዬኹ

Professor Mesfin Woldemariam's opinion about Ethiopia's new PM Dr. Abiy Ahmed.

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር፣

እባክዎ ይህችን ምክር አዘል ትችት ያንብቧት :-

ሚዛናዊነት ከራስ ቢጀምር …

ፍ/ቤት የቆመችው የፍትህ ምስል / Lady Justice / ተጠሪነቷና ምሳሌነቷ ለፍ/ቤት ስራ ብቻ አይመስለኝም ፡፡ አይኗን ሸፍና ያላጋደለ ሚዛን የያዘችው አስተዳዳሪዎች በሞራል ህግ ተመርተው ለዜጎች ሁሉ ሚዛናዊ አገልግሎትና ውሳኔ እንዲያስተላልፉ ነው ፡፡

ዶ/ር አብይ አህመድ ደጋግመው ስለሚዛናዊነት ይሰብካሉ ፡፡ ጋዜጠኞች የተመጣጠነ ዜና እንዲያቀርቡ ፣ አክቲቪስቶች ከዋልታ ረገጥ ሀሳብ ወደ መሃል እንዲመጡ ፣ ፖለቲከኞች እኔ ብቻ ነኝ አዳኝህ ወይም የማውቅልህ ከሚለው አባዜ ተላቀው ለሌላውም ስራ እውቅና እንዲሰጡ ወዘተ ወዘተ…

የሚዛን መንሻፈፍ ግለሰብን ፣ ማህበረሰብንና ሀገርን እየቆየ እንደሚጎዳና ለማይጠገን ቀውስ እንደሚዳርግ የሚገነዘብ ሁሉ በዚህ ሀሳብ ይስማማል ፡፡ ችግሩ ዶ/ር አብይ እንዳሉት ሁሉም ቀድሞ ጣቱን የሚቀስረው ሌሎች ላይ የመሆኑ አባዜ ነው ፡፡ ይህ የጣት ቅሰራ ራሳቸው ዶ/ር አብይንም ይመለከታል ፡፡ አንዱን ትልቅ ጥፋት ሸፋፍነህ ሌላው ላይ ጣትህን ስትቀስር ሚዛናዊነት ይንጋደዳል ፡፡ አንዱን ትልቅ ጥፋት አላየሁም ብለህ አይንህን ከሸፈንክ ሌላኛው ጥፋት ላይ የአይንህን መጋረጃ ቀደህ ለመጣል ሞራል ታጣለህ ፡፡

ከብዙ ምሳሌዎች የተወሰኑትን ብቻ እናንሳ ፡፡ ገና በጠዋቱ ሀገሪቱ መሪ እያላት ስርዓት አልበኝነት ነገሰ ፣ ህግ ረከሰ ፣ የንፁሃን ደም በከንቱ ፈሰሰ የሚል ጩኸት ብዙዋች ቢያሰሙም የሽግግር ባህሪው ነው በሚል ሚዛናዊ ምላሽ መስጠት አልተቻለም ፡፡ ከዚህ ይልቅ በቅድሚያ ለውጡ ያመጣቸውን ትሩፋቶች ሳትደባብቁ አሞግሱ ማለት መጣ ፡፡ ትክክል ነው ሚዛናዊ ለመሆን የበርካታ ባህሪያት/ ጥሩ ተናጋሪ ፣ ትዕግስተኛ ፣ ይቅር ባይ ፣ ትሁትና የሰላም አጋር / መሆናቸውን መመስከር ይቻላል ፡፡ በዚህ ጥሩ ባህሪ በመታገዝም መንግስታቸው አስደሳች ፖለቲካዊ ድሎች አስመዝግቧል ፡፡ ይህ ማለት ግን ለውጡ መሳ ለመሳ እየተጓዘ ያለው ከነውጥ ጋር ነው ነው ማለት ስህተት አይደለም ። ህገወጥነት ሀገሪቷን የወረረው ይቅርባይነት ስለበዛ ነው የሚል የቄለ ግምገማ የለኝም – በዚህ ረገድ መንግስታቸው ስትራተጂካዊ ብቃት የለውም የሚለው ሀሳብ የበለጠ ቅርብ ነው ። አሁን በቅርቡ እንኳን የሀገራችን ስርዓት አልበኝነት ተግባር ከ 8 እስከ 10 ወራት ይቀጥላል በማለት እንደ አመታዊ እቅድ ነግረውናል ፡፡ ህገወጥነትን አምርሮ ከመታገል ይልቅ ከህገወጥነት ጋር ተቻቻሎ ለመኖር ማሰብ ገራሚ አቋም ነው ፡፡ በተሸፋፈነች ፍትሃዊ አይን ሚዛናዊነትን እንይ ከተባለ ከዚህም በላይ ነው ፡፡

መንግስት ባለበት ሀገር አስራ ምናምን ባንኮች በጠራራ ፀሃይ ሲዘረፉ የሽግግር ሂደት ባህሪው ነው የምትል ከሆነ ሌላውን ሌባ ወይም ሙሰኛ ለመገሰጥም ሆነ ፍርድቤት ለማቆም ይከብዳል ፡፡ ምክንያቱም ፍ/ቤት የቆመችው የፍትህ ምስል ስለምትታዘብ ፡፡ ለተቃውሞ ዱላና ገጀራ አደባባይ ይዞ የወጣ ማህበረሰብ በቸልታ አልፈህ ያለዱላ ስብሰባ የከተመውን ወጣት በማያሳምን ምክንያት አስረህ የምታሸማቅቅ ከሆነ የሚዛናዊነት መሰረትህ ተናደ ማለት ነው ፡፡ ይከበር እየተባለ የሚለፈፈው ህግ ባለመከበሩ ዱላና ገጀራው አድጎ እነሆ ዛሬ የጦር መሳሪያ ይዞ አደባባይ መውጣት ተጀምሯል ፡፡ በገዛ ፍቃድህ ሚዛናዊ ካልሆንክ ብሎም ቸልተኝነት እንደ ኩይሳ ካሳደግክ ሌሎች አደባባይ የተገተረውን የፍትህ ሚዛን በሌላ ጡንቻ ይሰብሩብሃል ፡፡ ትርፉና ውጤቱም ይሄው ነው ፡፡

የቸገረው የከተማ ህዝብ ከሰውነት ተራ ወጥቶ በሰራው ኮንዶሚኒየም አትገባም ተብሎ ገጀራ ሲወደርበት< < የባለገጀራዋች ሀሳብ ይለምልም >> ብሎ መግለጫ ማውጣት እንዴት ሚዛናዊ ሊሆን ይችላል ? በቡራዩና ለገጣፎ ሰላማዊ ዜጎች ላይ የደረሰው መፈናቀል ፣ እንግልትና አግላይ ርምጃዋች ከልብ ሳታወግዝ ሌላ ታፔላ ለጥፎ አደባብሶ ማለፍ የሚዛናዊነትን ጥያቄ ያስነሳል ፡፡ ጠ/ሚ/ሩ ሀገር የሚበትኑ ሀሳቦች ይወገዙ ይላሉ ፡፡ በሀገሪቱ ያለው ሁለት መንግስት የአብይና የቄሮ ይባላል የሚል ትንታኔ የሚሰጠው ጃዋር የበርካታ በታኝ ሀሳቦች ባለቤት ቢሆንም ውግዘት አይመለከተውም ፡፡ ኦሮሞ ከቋንቋው ውጭ ሌሎችን ማነጋገር የለበትም ፣ ከሌሎች ጋር መጋባትም ማቆም አለበት የሚለው የ < ምሁሩ > በቀለ ገርባ አፖርታዳዊ አስተያየት ለመመርመርም ሆነ ለመተቸት አልተፈለገም ፡፡ በተቃራኒው የአዲስ አበባ ነዋሪዎችን ጥቅም ለማስጠበቅ በሚንቀሳቀሰው እስክንድር ነጋ ላይ ግልጽ ጦርነት እናውጃለን ተብሏል ፡፡ ሲጠቃለል ዶ/ር አብይ በበቀለ ፣ በኦነግ ፣ በጃዋር ፣ በህገወጥ ፖለቲከኞችም ሆነ በእስክንድር ሀሳብ ላይ ሚዛናዊ መሆን አልቻሉም ፡፡

ለዚህም ነው ማንኛውም ሚዛናዊ ለመሆን የሚጥር ስው ለምን የሚል ቀጥተኛ ጥያቄና እንዴት የሚል የጀርባ ምፀት ለማንሳት የሚገደደው ፡፡ ግዜ የሰጠው ቅል ድንጋይ እንዲሰብር ብሂሉ ስለሚያስገድድ ? ምንም ቢሆን ዘር ክልጓም ስለሚስብ ? … ኢትዮጵያዊነትን መርህ አድርጌያለሁ የሚል መሪ ለጃዋርም ሆነ ለእስክንድር ሀሳቦች እኩል የድጋፍም ሆነ የተግሳጽ መስፈርት ማበጀት ካልቻለ መርሁ ሁሉ Backfire ያደርግበታል ፡፡ ዶ/ር አብይ ከግዜ ወደግዜ እየገረጣ የመጣባቸውን ህዝባዊ እምነት ስር ሳይሰድ ለማከም ከፈለጉ ሚዛናዊነት ከራሳቸው መጀመር ያለባቸው ይመስለኛል ፡፡ ጥሩ መሪ ደግሞ እንደዛ ነው ፡፡ መንገዱን የሚያውቅ ፣ በመንገዱ የሚሄድ እና መንገዱን የሚያሳይ ስለሚሆን ፡፡ ባለግዜ ነን በሚሉ ቡድኖች የሚሰሩ አስከፊና አቀያያሚ ጉዳዮችን አደብ ማስገዛት ፣ አቅም ቢያጥር እንኳን በግልጽ አካፋን አካፋ በማለት ማውገዝ መጀመር አለባቸው ፡፡ ከዚህ ከጀመሩ ሌላኛውን ብልሹ ሀሳብና ተግባር ለማረቅ ምቹ መደላድል ይፈጥራል ፡፡ ይህ አካሄድ ልበ ሙሉነትን በቀላሉ ማትረፍ የሚያስችል ሲሆን ከሁሉም አቅጣጫ በቂ ድጋፍ ያስገኛል ፡፡ አክባቢዋን በሚያውቋቸው ሰዋች መሙላት ብቻ ሳይሆን ገለልተኛና ሚዛናዊ ሀሳብ የሚሰጡትንም አማካሪዋች ቢያበዙ ጭልጥ ብሎ ከመሳሳትም ያድናል ፡፡

ወንጀሉ አይለባበስ! (ሚኪያስ ጥላሁን)

ዛሬ አብይ አህመድ የጌዲኦ ተፈናቃዮችን ጎብኝቷል፤ ከተፈናቃዮቹ ጋርም ወይይት ‹‹አድርጓል!›› ተብሏል፡፡ የተፈናቃዮቹ ችግር ለ8 ወራት ያህል የዘለቀ ቢሆንም፣ ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ ግን አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ አብይ ስለጉዳዩ ባሳዬው ቸልተኝነት ሊወቀስና ሊከሰስ፣ አለፍ ሲልም ሊወገዝ ይገባዋል፡፡ የዛሬው ጉብኝትና ውይይት እርሱና እርሱ የሚመራው ስርዓት ለፈፀማቸው ኢ-ሰብዓዊ ድርጊቶች ማለባበሻ መሆን የለባቸውም፣ አይገባቸውምም፡፡

 1. ስለጌዲኦ ወገኖቻችን ረሃብ በተራድዖ ድርጅቶች በኩል ለበርካታ ሳምንታት ሲነገር ቆይቷል፡፡ ወደ አካባቢው ዕርዳታ ይዘው ለመሄድ የሞከሩ ድርጅቶች፣ መንገድ በመዘጋቱ ምክንያት (ሆነ ተብሎ፣ በስርዓቱ ባለሟሎች የተፈፀመ ነው፡፡) ለተረጂው ህዝብ ተፈላጊውን አገልግሎት ማድረስ አልቻሉም፣ አሁን ከአብይ ጉብኝት በኋላ መንገዱ ሊከፈት ይችላል፡፡ ድርጅቶቹም ገብተው ተልዕኳቸውን መፈፀም ይችላሉ፡፡ ያለፉት የችግር ወራት ግን ከረሃብተኛውና የሰብዓዊ መብት ተቆርቋሪዎች አዕምሮ አይረሱም፡፡
 2. ከረሃቡ ፈቀቅ ሲል፣ የጌዲኦ ወገኖች ላይ ማፈናቀል የተፈፀመው በምዕራብ ጉጂ ዞን አመራሮች ቆስቋሽነትና በኦነግ ሰራዊት አማካይነት ነው፡፡ ስርዓቱ በተፈናቀሉበት ሰሞን መልሶ የማስፈር ሙከራ ቢያደርግም፣ የጌዲኦ ወገኖች የሚፈፀምባቸውን ዛቻ፣ ግድያና ዘረፋ በመሸሽ ወደ ጌዲኦ አካባቢ አምርተዋል፡፡ የማይረሳው ነገር የጌዲኦ ወገኖች ‹‹ሂዱ!›› ወደ ተባሉበት አካባቢ ሲሄዱ፣ የዞኑ አስተዳደር አውቶብስ መድቦ ማጓጓዙ ነው፤ ይህ የተተለመ ዘር-ተኮር ጥቃት ለምን ሚዲያ ላይ እንዳይቀርብ ተለባበሰ? ስርዓቱ እርቃኑን ስለሚቀር!
 3. ትናንትና ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል በተራቡ ወገኖቻችን ላይ ተሳልቃለች፡፡ ‹‹በረሃብ ስለመጎዳታቸው እናጣራለን!›› ብላለች፡፡ ከዚህ በላይ ምኑ ነው የሚጣራው? አንድ ቄስ ለጀርመን ድምፅ ራዲዮ እንደተናገሩት፣ በቀን ከ3 እስከ 4 ሰዎች በምግብ ዕጥረት ይሞታሉ፡፡ ወይዘሮ ሙፈሪያት ደግሞ የይሉኝታ እንጥፍጣፊ በሌለበት አነጋገሯ ስለ‹‹ማጣራት›› ታወራናለች፤ ቅጥ ያጣ ኢ-ሰብዓዊነት!

ለምሳሌ ያህል 3 ነጥቦችን በተርታ ያነሳሁት አብይ አህመድ የስርዓቱ ዘዋሪ ሆኖ ሳለ በማወቅና በቸለልተኝነት ያስፈፀማቸው የህዝብ ክብር ላይ የተሰሩ ደባዎች ናቸው፡፡ ደባ ባይሆኑም እንኳ፣ ስላቅ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ዋናው ነጥቤ ምንድን ነው? አብይ አህመድ ስለሞቱትና ስለተራቡት ወገኖች ተጠያቂ ነውና ዛሬ ባደረገው ጉብኝት ሰበብ እርሱን ማወደስ አያስፈልግም፤ በሰራው ወንጀል ልክ መተቸት አለበት፡፡

በፌደራል መንግሥት የታቀዱ የባቡር መሥመር ፕሮጀክቶች በፍጥነት ሊጀመሩ ይገባል”-የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር

ባህር ዳር መጋቢት 7/2011በአማራ ክልል ይገነባሉ ተብሎ በፌደራል መንግሥት የታቀዱ የባቡር መሥመር ፕሮጀከቶች በፍጥነት እንዲጀመሩ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር አምባቸው መኮንን ጠየቁ።

በደቡብ ጎንደር ዞን ወረታ ከተማ የሚገነባውን የደረቅ ወደብና ተርሚናል ግንባታ የመሠረት ድንጋይ ተቀምጧል፡፡

ዶክተር አምባቸው በዚሁ ወቅት እንዳሉት ባቡር ለአገሪቱ የሚያበረክተውን ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ከግምት በማስገባት የተያዘው ዕቅድ ወደ ተግባር መግባት ይኖርበታል።

መሥመሮቹ ከወልዲያ -ወረታ-ፍኖተ ሰላም እንዲሁም ከወረታ- መተማ-ሱዳን ለመዘርጋት የታቀዱ እንደሆኑም አስታውሰዋል፡፡

በዕቅድ ከተያዙት መሥመሮች አንዱም ሥራ ባለመጀመሩ በሕዝቡ ዘንድ ቅሬታ መፍጠሩን ዶክተር አምባቸው ገልጸዋል።

በወረታ ከተማ በ20 ሄክታር መሬት የሚያርፈው የደረቅ ወደብና ተርሚናል ግንባታም አስፈላጊው የመሠረተ ልማት አቅርቦት ካልተሰራለት ውጤታማ ሊሆን እንደማይችል ተናግረዋል፡፡

በክልሉ ከ420 ሺህ በላይ ሕጋዊ ነጋዴዎች እንዳሉ ያስረዱት ርዕሰ መስተዳድሩ፣ ነጋዴዎቹ ተገቢ የመሠረተ ልማት ባለመኖሩ ወደ ክልሉ የሚያስመጡትንም ሆነ ወደ ውጪ የሚልኩትን ምርት በመንገድ መሠረተ ልማት እጥረት አለመሟላት ችግር እንደሚያጋጥመው ተናግረዋል።

ይህምተገቢ ላልሆነ የጊዜና የገንዘብ ወጪ እንደሚዳርጋቸው ዶክተር አምባቸው አስረድተዋል።

ክልሉ ትርፍ አምራችና የአገሪቱን ኢኮኖሚ ለማሳደግ  ከፍተኛ አስተዋጽኦ ስላለው  የፌዴራል መንግሥት ለክልሉ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ብለዋል።

በመንግሥት ላይ ሙሉ ተስፋ ያለው የክልሉ ሕዝብ ይገነባሉ ተብለው ግንባታውን  በጉጉት እየተጠባበቀ ነው ብለዋል።

የትራንስፖርት ሚኒስትሯ  ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስ በበኩላቸው በክልሉ ለመገንባት የታቀዱትን የባቡር መሥመር ዝርጋታ ለማስጀመር ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን  አስታውቀዋል።

ለዚህም የወረታ-ጎንደር-መተማ 504 ኪሎ ሜትር፣በሱዳን በኩል ጋላባት፣ ገዳሪፍ፣ከሰላና ሃያ ሱዳን ወደብ የሚዘረጋ ደረጃውን የጠበቀ የባቡር መሥመር ፕሮጀክት ግንባታ  እውን ለማድረግ ከሱዳን መንግሥት ጋር ስምምነት ላይ ተደርሷል።

ለፕሮጀክቱ መሳካት አስተዋጽኦ የሚያደርግ  የአዋጪነት ጥናት በአፍሪካ ልማት ባንክ አማካኝነት በቅርቡ  እንደሚጀመርም ተናግረዋል።

የወረታ ደረቅ ወደብ ግንባታም ይህንን የባቡር መሥመር  ግንባታ ግምት ውስጥ በማስገባት እንደሚገነባ ገልጸዋል።

የወረታ የደረቅ ወደብና ተርሚናል ግንባታ በ20 ሄክታር መሬት ላይ የሚያርፍ ሲሆን፣ ለመጀመሪያው ምዕራፍ ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ይደረጋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡