
ዛሬ አብይ አህመድ የጌዲኦ ተፈናቃዮችን ጎብኝቷል፤ ከተፈናቃዮቹ ጋርም ወይይት ‹‹አድርጓል!›› ተብሏል፡፡ የተፈናቃዮቹ ችግር ለ8 ወራት ያህል የዘለቀ ቢሆንም፣ ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ ግን አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ አብይ ስለጉዳዩ ባሳዬው ቸልተኝነት ሊወቀስና ሊከሰስ፣ አለፍ ሲልም ሊወገዝ ይገባዋል፡፡ የዛሬው ጉብኝትና ውይይት እርሱና እርሱ የሚመራው ስርዓት ለፈፀማቸው ኢ-ሰብዓዊ ድርጊቶች ማለባበሻ መሆን የለባቸውም፣ አይገባቸውምም፡፡
- ስለጌዲኦ ወገኖቻችን ረሃብ በተራድዖ ድርጅቶች በኩል ለበርካታ ሳምንታት ሲነገር ቆይቷል፡፡ ወደ አካባቢው ዕርዳታ ይዘው ለመሄድ የሞከሩ ድርጅቶች፣ መንገድ በመዘጋቱ ምክንያት (ሆነ ተብሎ፣ በስርዓቱ ባለሟሎች የተፈፀመ ነው፡፡) ለተረጂው ህዝብ ተፈላጊውን አገልግሎት ማድረስ አልቻሉም፣ አሁን ከአብይ ጉብኝት በኋላ መንገዱ ሊከፈት ይችላል፡፡ ድርጅቶቹም ገብተው ተልዕኳቸውን መፈፀም ይችላሉ፡፡ ያለፉት የችግር ወራት ግን ከረሃብተኛውና የሰብዓዊ መብት ተቆርቋሪዎች አዕምሮ አይረሱም፡፡
- ከረሃቡ ፈቀቅ ሲል፣ የጌዲኦ ወገኖች ላይ ማፈናቀል የተፈፀመው በምዕራብ ጉጂ ዞን አመራሮች ቆስቋሽነትና በኦነግ ሰራዊት አማካይነት ነው፡፡ ስርዓቱ በተፈናቀሉበት ሰሞን መልሶ የማስፈር ሙከራ ቢያደርግም፣ የጌዲኦ ወገኖች የሚፈፀምባቸውን ዛቻ፣ ግድያና ዘረፋ በመሸሽ ወደ ጌዲኦ አካባቢ አምርተዋል፡፡ የማይረሳው ነገር የጌዲኦ ወገኖች ‹‹ሂዱ!›› ወደ ተባሉበት አካባቢ ሲሄዱ፣ የዞኑ አስተዳደር አውቶብስ መድቦ ማጓጓዙ ነው፤ ይህ የተተለመ ዘር-ተኮር ጥቃት ለምን ሚዲያ ላይ እንዳይቀርብ ተለባበሰ? ስርዓቱ እርቃኑን ስለሚቀር!
- ትናንትና ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል በተራቡ ወገኖቻችን ላይ ተሳልቃለች፡፡ ‹‹በረሃብ ስለመጎዳታቸው እናጣራለን!›› ብላለች፡፡ ከዚህ በላይ ምኑ ነው የሚጣራው? አንድ ቄስ ለጀርመን ድምፅ ራዲዮ እንደተናገሩት፣ በቀን ከ3 እስከ 4 ሰዎች በምግብ ዕጥረት ይሞታሉ፡፡ ወይዘሮ ሙፈሪያት ደግሞ የይሉኝታ እንጥፍጣፊ በሌለበት አነጋገሯ ስለ‹‹ማጣራት›› ታወራናለች፤ ቅጥ ያጣ ኢ-ሰብዓዊነት!
ለምሳሌ ያህል 3 ነጥቦችን በተርታ ያነሳሁት አብይ አህመድ የስርዓቱ ዘዋሪ ሆኖ ሳለ በማወቅና በቸለልተኝነት ያስፈፀማቸው የህዝብ ክብር ላይ የተሰሩ ደባዎች ናቸው፡፡ ደባ ባይሆኑም እንኳ፣ ስላቅ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ዋናው ነጥቤ ምንድን ነው? አብይ አህመድ ስለሞቱትና ስለተራቡት ወገኖች ተጠያቂ ነውና ዛሬ ባደረገው ጉብኝት ሰበብ እርሱን ማወደስ አያስፈልግም፤ በሰራው ወንጀል ልክ መተቸት አለበት፡፡