የኢትዮጵያ ልሂቅ Vs እስክንድር (አቤል ዋቤላ)

አቤል ዋቤላ

የኢትዮጵያ ልሂቅ የፖለቲካ ስልጣንን በመግራት ሂደት ውስጥ ከህዝብ ጎን ቆሞ አያውቅም። የፓሊቲካ ፓወርን ከተጋጨም የሚጋጨው በመንበሩ መቀመጥ ሲፈልግ ብቻ ነው። ከዚያ ውጭ መንግስት ጨቋኝ እና አምባገነን ሆኖ ዜጎችን እንዲረግጥ እጀታ (enabler) በመሆን ሲያገለግል ነው የኖረው። አጭበርብሮ ያገኛትን እፍኝ የማትሞላ እውቀት ያለ ልክ አጋኖ እና አሽሞንሙኖ ወደ ባለጊዜው በመጠጋት፣ ባለጊዜው በድፍረት እና በእብሪት ለሚወስደው እርምጃ አፕሩቫል በመስጠት እንጀራውን የሚያበስል ነው።

እስክንድር እድገቱ እና ትምህርቱ ከየትኛው ደጅ ጠኚ ልሂቅ በተሻለ ወደስልጣን ሊያቀርበው የሚችል ነበር። ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በስታንፎርድ የተማረ እና በአሜርካን ሀገር ፖለቲካን ያጠና ሆኖ ሳለ ህዝብን በመምረጡ ህዝብን በጋዜጠኝነት ማገልገል ከጀመረ ሰነባብቷል። ከህዝብ ጋር ያለውን ህብረት ፖለቲካል ስልጣንን ፊትለፊት በመጋፈጥ ጭቆናን በመቃወም አረጋግጧል። እስር፣ ግርፋት፣ እንግልት የፖለቲካ ስልጣን በኢትዮጵያ ስርዓት እንዲይዝ የሚያደርገውን ጥረት አልገቱትም።

አሁንም እየሆነ ያለው ይሄ ነው። ከሰባት ዓመታት እስር በኋላም እስክንድር ደከመኝ ብሎ የኢትዮጵያ ህዝብን ለጅብ አሳልፎ እንዲሰጥ አላደረገውም።

በህዝባዊ አመፅ ይቅርታ ጠይቆ ፍትሃዊ ምርጫ እስኪካሄድ ስልጣን የያዘው የአብይ አህመድ መንግስት ከምርጫ በፊት፣ አሁን ያለው ፓርላማ ፊት እንኳን ከመቅረባቸው በፊት መሰሪ የሆኑ አረመኔያዊ ተግባሮች እየፈፀመ ይገኛል። ከዚህ ውስጥ አንዱ የአዲስ አበባ ጉዳይ ነው። መንግስት ላጠፋው ጥፋት ይቅርታ ጠይቆ ለሽግግር ሲባል ብቻ የቆመ መሆኑን ዘንግቶት አውሬነት በተሞላ መልኩ ከተማዋን ስሪት እየሰራ ይገኛል። ይህንን ተግባሩን ልክ አይደለም የሚል የፖለቲካ ማኀበርም ሆነ ግለሰብ በጠፋበት ሰዓት የህዝብ ልጅ እስክንድር ነጋ እኔ አለኹ ብሏል።

ይህ በአርያነት ሁሉም ዜጋ ሊከተለው የሚገባ ተግባር ሆኖ ሳለ ልሂቁ የተለመደ የአድርባይነት እና እበላባይነት እድሉን የሚጨናግፍበት እየመሰለው ይቃዥ ጀምሯል። እስክንድርን ካልሰለጠነ የሞብ መሪ በማስተካከል ይተች ጀምሯል። የእስክንድርን የጋዜጠኝነት ስልት እና አክቲቪዝም መተቸት በራሱ ችግር የለውም። በዚህ ላይ ውይይት ማካሄድ ይቻላል። እንደኔ እንደኔ ይህ ዝንባሌ የልሂቁ የተለመደ ወራዳነት መገለጫ ነው። ከአውራ ሆድ አደር ልሂቃን እስከ አፍላ አንበጣ ልሂቃን(በወያኔ እስከ እስር፣ ስደት የሚደርስ ስቃይ የደረሰባቸው እና የአምናውን ባለጊዜ አበርቺ ልሂቅን አብዝተው ይተቹ የነበሩ) ሀገርን የመዝረፍ እቅዳቸው እንዳይፈርስ ሲሉ የሚያደርጉት ነው።

ይህ የልሂቃን መርከብ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ተለዋዋጭ እና አታላይ የአደባባይ ገፅታ ምክንያት በርካታ ባለሙያዎች እና እንደብርቱካን ሚደቅሳ ያሉ በቀድሞ ጊዜ የህዝብ ልጅነታቸውን ያስመሰከሩ ሰዎችን/ ልሂቃንን ጭኗል። ይህ የጎራ መደበላለቅ ፈጥሯል። እንደኔ እንደኔ አዲሱ አስተዳደር ምንም አይነት እገዛ የማያስፈልገው መፍረስ ያለበት መንግስት ነው የሚል ድምዳሜ ላይ አልደረስኩም። ከዚህ በመነሳት በሀገር ግንባታ ሂደት ውስጥ በባለሙያነት እና ከፍተኛም ሆነ ዝቅተኛ ኃላፊነቶችን በመውሰድ ሀገርን እና ለህዝብ የሚሰራ መንግስትን ማገልገል ተገቢ ነው ብዬ አምናለኹ። ይሁንና የጋራ ቤትን አብረው እየሰሩ ሳሉ በመንግስት የሚፈፀሙ ከባድ ጥፋቶችን ባላየ ባልሰማ ማለፍ አይገባም። ከቀድሞ የሀገሪቱ የቆየ ልማድ እና ባለፉት ወራት እንዳየነው ልሂቁ ከዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት በበረታ ዝምታ እና ክህደት ላይ ይገኛል።

ይህ የአድርባይነት እና አስመሳይነት ባህል ካልተሰበረ መቼም ቢሆን የፖለቲካ ስልጣንን መግራት አንችልም። ስለዚህ የእስክንድር ፈለግ ተከተለን እርሱን በርታ እያልን ሌሎች በመንግስት ውስጥ የሚገኙ እና ከመንግስት ውጭ ያሉ ሁሉንም አይነት ልሂቃንን በስም በመጥራት ማንቃት ይገባናል። እስክንድር የዚህ የሰለጠነ ማኀበረሰብ እሴት(የፖለቲካ ስልጣንን መግራት) መተከል ሂደት ምልክታችን እና የልሂቅነት ሞዴል ነው።

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s