የፖለቲካ ልምዳችን ከትላንቱ ዛሬ ቁልቁል እንዳይወርድ…… (ጌድዮን በቀለ)

ጌድዮን በቀለ
Gedionbe56@yahoo.com

አመት የሞላው የዶክተር አብይ በዓለ ሲመት ላለፉት ፪፯ ዓመታት ሳይቋረጥ ሲካሄድ ለነበረው የህዝቦች እምቢተኝነት ዓመጽ የለውጥ ሽግግር ምዕራፍ መባቻ መሆኑ ዋና ገጽታው ነው።  ይሄው የሽግግር ንቅናቄ  ስጋት፤ ጥርጣሬና ተስፋ የተቀላቀለ ነፋስ እያናወጠው መጓዙን ቀጥሏል። ከጅምሩ ልክ በሌለሽ የተስፋ ፈንጠዝያ የተሳከረው የህዝብ ስሜትም፤ ከመነሻው በተሳከሩ ህልሞች ታጅቦ ያንንም ያንንም ለመጨበጥ ሲተረማመስ የለውጡ እሳት ይለበልበናል በማለት የሰጉ ቡድኖችና ግለሰቦች ለውጥ መጣልኝ ብሎ እየፈነጠዘ ካለው መንጋ መሀል ተቀላቅለው በመትመም አመች የመሰላቸውን የቅራኔ ክር በመምዘዝ አቅጣጫ የማስቀየስ ስራቸውን በቆራጥነት ይዘው መሳ ለመሳ እንደቀጠሉ ናቸው።  ስካሩ ወደዞረ ድምር ሲሸጋገር ደግሞ  በጅምላ ሲተም የነበረው ኢትዮጵያዊ በይደር አቆይቶት የነበረውን ጫፍና-ጫፍ የረገጡ የአካሄድ አቅጣጫዎቹን ወደመሬት አውርዶ ከመበሻሸቅና ከመሸነቋቆጥ አልፎ ወደለየለት ፍጥጫ እየተሸጋገረ ይገኛል።

ከሁሉ ሁሉ የሚያስደምመው በተለይም ፈንጠዝያው ያስከተለው መደናገር በጅምላ የተጓዝንበት አንድ አመት ለውጥ ነው? ወደለውጥ የሚወስድ ሽግግር ነው? ወይስ ኢህአዴግ ሲለው የነበረው ጥልቅ ተሃድሶ? በሚሉት የቃላት ፍችዎች እንኳ ወጥነት ያለው የትርጓሜ መግባባት ላይ ሳይደረስ እያንዳንዱ ለራሱ የተመቸውን ፍቺ እየሰጠ መቀጠሉ ነው። ጨርሶ ሳይጨልም  በተቻለ መጠን ለነዚህ ቃላት  ምላሽ መስጠት ያለፈውን አንድ ዓመት ጉዞ ለመገምገምና ወዴት እየሄድን ነው? ምንስ ማድረግ አለብን? የሚሉትን ጥያቄዎች ለመመለስ ያግዘናል። የበኩሌን እነሆ።

፩- በተጓዝንበት አንድ ድፍን ዓመት ውስጥ ለውጥ ነበር ወይ? በደምሳሳው መልሳችን — አዎ ለውጥ ነበረ የምንል ብዙዎች ነን። ምክኒያታችንም በሚከተሉት የፖለቲካ እምነት ፤ ወይም ሀይማኖት፤ ወይም ዘር፤ ታስረው የነበሩ ዜጎች ሁሩ ወጥተዋል፤ የህሊና እስረኞች፤ ጋዜጠኞች፤ የሰብ አዊ መብት ተከራካሪዎች ወዘተ ተለቀዋል። ከሀገራቸው የተሳደዱ ፤ በነፍጥ ነጻነታችንን እናስመልሳለን ብለው ለመፋለም በስደት አገር፤የኮበለሉ፤ በኤርትራ የመሸጉ፤ የሞት ፍርድ የተፈረደባቸው የፖለቲካ ቡድን መሪዎችና ድርጅቶች ወደ አገር ገብተዋል፡፤ ከሁሉም በላይ የሚገዟት መሪዎች ባአፋቸው ለመጠራት ሲጠየፏት የነበረችው ኢትዮጵያ ፤ በተወገዘችበት አደባባይ አሻራዋን ለማጥፋት ሌት ተቀን ተግቶ ሲሰራ ከነበረ ድርጅት አብራክ በወጡ መሪዎች አንደበት እጅግ ግርማ ሞገስ ተላብሳ ተነስታለች። ይህንን ተከትሎ ለዘመናት በመቃወምና አቤቱታ በማሰማት የሚታወቀው በውጭ የሚኖር ኢትዮጵያዊ ሳይቀር ከተቃውሞ ወደጅምላ ድጋፍ አልፎ ተርፎም ላምልኮት በቀረበ ፍቅር አዲሶቹን መሪዎች ወደ ማወደስ ተሸጋግሯል።

ይህን የመሰለው ከሚገመተው በላይ “ፈጣን” የተባለለት ክንውን ፤ በለውጥነት ተመዝግቦ “ሁላችንም” ሊባል በሚችል ደረጃ ተስማምተንበትና ተቀብለነው እንደቀጠለ ቆይቷል። በዚህም የተነሳ እሱን ተከትሎ በመጣው “ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ፤ የመደራጀት፤ ተደራጅቶ በሰላማዊ ሰልፍ መንግስትንና ተቋማቱን ሳይቀር ያለ ስጋት የመተቸት መብት፤ “ በዚህ አንድ ዓመት ውስጥ ታይቷል። በዚያው መጠን ታይቶ በማይታወቅ ደረጃ አሉታዊ ገጽታዎችም ተስተናግደዋል፤ የዜጎች በነጻነት ወጥቶ መገባት፤ እንደልብ ከቦታ ቦታ ተዘዋውሮ የመስራትና የመኖር መብት አደጋ ላይ ወድቋል። በዘር፤ በሃይማኖትና በሚከተሉት የፖለቲካ አመለካከታቸው የተነሳ  ዜጎች ከትውልድ ቀያቸው የተሳደዱበት፤ የመንጋ ፍርድ እንደዋና የነጻነት መገለጫ የተወሰደበት፤ አጉራጢነኛ የጎበዝ አለቆች የነገሱበት ፤ ስር ዓት አልበኝነት የተበረታታበት፤ የጥፋት ጉዞም እንደለውጡ ትሩፋት የተቆጠረበትም አመት ነበር። እንግዲህ ባንድ በኩል “ሃሳብን በነጻነት መግለጽ ተችሏል” ባልንበት አፋችን “አይደለም መናገር ወይም ልዩነትን በነጻነት መግለጽ የዜጎች ከቦታ-ቦታ ተንቀሳቅሶ የመስራት ነጻነት ከመቸውም በላይ ተገድቧል” ስንል የለውጥ ተብዬውን ምጸት ያሳያል።

በሌላ በኩል የደምሳሳውን የለውጥ መለኪያ መነጽራችንን ስናወልቅ ደግሞ  መልሳችን ይቀየራል። በለውጥነት የተዘረዘሩት ጉዳዮች ሁሉ ፤ ወደለውጥ ለመግባት የተወሰዱ ዋናና አስፈላጊ ቅድመ ሁኔታዎች እንጅ በራሳቸው ለውጥ አይደሉም። ዎያኔ-ኢህአዴግ በራሱ “ህገ-መንግስት” ጽፎ የራሱን ህገመንግስት ጥሶ የገባውን ቃል በማጠፍ ሲረጋግጣቸው የነበሩትን መብቶች  በተራዘመው የህዝብ ትግል ተገዶ እንዲቀበል የመደረጉ ውጤቶች መሆናቸውን እናስተውላለን።

ስለዚህ ለውጡ ለ፪፯ ዓመት ለህዝብ ጩኽትና አቤቱታ ጆሮዳባ ልበስ ብሎ የኖረው ኢሃዴግ የህዝቡን እሮሮና ብሶት ለማዳመጥ ቆርጠው በተነሱ ከራሱ ከድርጅቱ መሃል በወጡ ወጣት ኢህአዴጎች የተሰጠ በጎ ምላሽ ሆኖ እናገኘዋለን። ስለሆነም በግፍ የተነጠቅነውን መብት ማሰመለስ እንጅ ፤ የስርዓት ለውጥ እየተከናወነና እሱም በሰላማዊ መንገድ ተከናወነ እያሉ ማውገርገርና ማስመሰሉ ከባዶ የፖለቲካ ፍጆታ አይዘልም። ባንጻሩ ኢህአዴግ በእምቢተኛነቱ እንደጸና ቢቀጥል ኖሮ አገራችን ኢትዮጵያ ወደከፋ ግጭትና መዳረሻው ወደማይታወቅ የርስ-በርስ መተላለቅ የመግባት መጥፎ አጋጣሚ ይጠብቃት እንደነበር አዋቂ ፍለጋ መዞር አያስፈልገንም።

ስለዚህም ነበር ከችግሩ ጠንሳሽና አሳዳጊ ቡድን መሃል ወደመፍትሄ ለመሄድ ቁርጠኝነታቸውን ያሳዩ  እስከቅርብ ጊዜ “ቲም ለማ “ የሚል ስያሜ የተሰጣቸው ቡድኖች ብቅ በማለታቸው ያለምንም ማንገራገር ተቀብለን ፤ ያለንን አክብሮትና ምስጋና በሙሉ ልብና ድጋፍ ስናሳያቸው የቆየነው። ስለዚህ ለውጡ የስርዓት ለውጥ ሳይሆን የማይሰማ ጆሮ ለመስማት ፈቃደኛ መሆኑን በተግባር ያስመሰከረበት ለውጥ የሚሆነው።

፪. ኢሃዴግ እንደሚለው “ጥልቅ ተሃድሶ” ነበር ወይ ያካሂያደው? የሚለውን ራሱ ዎያኔ ኢህአዴግ በነገረን መለኪያ ብንሰፍረው እንኳ ሂደቱ የሚያረጋግጥልን እውነት “ግማሽ ልጩ” ሆኖ እናገኘዋለን። አስረጅ፤- “ሰላማዊ “ ከተባለው የስልጣን ሽግግር ማግስት ጀምሮ እንደ… እንትን ዝንጀሮ መቀሌን ምሽጉ አድርጎ የሚገኘው ዎያኔ “እንደ ለውጥ “ በተቆጠሩት ወሳኝ እርምጃዎች ሁሉ ላይ ከማኩረፍ እስከ መቃዎም የደረሰ የልዩነት ጽናቱን በቆራጥነት አሳይቶናል። ይባስ ብሎም በተዘዋዋሪና በይፋ እርምጃዎቹን ለማስቀልበስ በመስራት ላይ ይገኛል። ከዎያኔ ህዋሃት ቀጥሎ ኢህአዴግ በሚባለው ድርጅት ውስጥ የሚገኙ በርካታ የኦዴፓ፤አዴፓ፤ደህዴን ከፍተኛ፤ መሃከለኛና ዝቅተኛ አመራሮች፤ በድርጅታቸው ጀርባ ተጠልለው የክልላቸውን ህዝብ እንዲመሩ ሃላፊነት የተሰጣቸው አያሌ ባለስልጣናት ለጥፋት በታማኝነትና በትጋት ሌት ተቀን የተጀመረውን የለውጥ እንቅስቃሴ ለመግታት ወይም አቅጣጫ ለማስቀየስ እየሰሩ ይገኛሉ።  እንግዲህ በልዩ ልዩ ጥቅማጥቅም ተጋሪ የነበረውንና ባንድ ጀምበር እንደሙጃ የበቀለውን ባለብዙ ቪላ፤ፎቅና ፋብሪካ ባለቤት የሆነውን በለጊዜ ሃብታምን ከጨመርነው ያገራችን አበሳ በዋዛ እንደማይፈታ አረጋጋጭ ነው። ከዚህ አንጻር ኢህአዴግ በጅምላ “ጥልቅ ተሃድሶ ጎዳና ላይ ነው” ከማለት ይልቅ ከላይ በስም ተጠቃሹ “ቲም ለማ” በመባል የሚታወቀው ቡድን ፍልጥ ፍለጥ እስከሆነው ህጸጹ በጥልቅ ከመታደስም አልፎ ለመለወጥ የቆረጠ ሆኖ ታይቷል።

፫.  የሽግግር ለውጥ ውስጥ ገብተናል  ወይ? የሚለውን ደግሞ እንመልከት፤ ሲጀመር በዎያኔ ተጨፍልቀው የነበሩ መብቶችን በመመለስ “ከህዝቡ ጎን ነኝ” ያለው “ለውጥ አራማጅ” ቡድን ባጭር ጊዜ ውስጥ በወሰዳቸው እርምጃዎች የአብዛኛውን ህዝብ ሊባል በሚችል ደረጃ ድጋፍና ተቀባይነት አግኝቶ ቆይቷል። በዚህ የተነሳ  “የሽግግር መንግሥት “ ይቋቋም ለማለት ሲዳዳቸው የነበሩ ወገኖችና የፖለቲካ ቡድኖች ጥያቄ “እኔ አሻግራችኋለሁ” ባሉት በዶክተር አብይ ቃል ተተክቶ፤ ቃሉም የድጋፍም ሆነ ተቃውሞ ድምጽ ሳይሰጥበት በዝምታ ስምምነት የጸና መስሎ ቀጥሏል። ይሁን እንጅ ከመነሻው የሽግግሩ አቅጣጫ በጊዜ ቀመር ተለክቶ፤ ቅደም ተከተል ወጥቶለት በወጣለትም  አቅጣጫ የጋራ መግባባት ላይ ስላልተደረሰ  “ሽግግር” የሚለው ቃል እንደየፊናው አሻሚ ትርጉም ተስጥቶት ቀጥሏል።

በተፈጠረውም ድንግርግር የተጀመረው ውዝግብ ዜጎች በጋራ ባልተስማሙበትና ባልመከሩበት ጉዳይ እንደተነጋገሩበትና እንደተስማሙበት ሁሉ እጅ-እግር የሌለው መካሰስ ውስጥ ገብተው ይገኛሉ። ይህንኑ ተከትሎ ለተፈጠረው አልተገባብቶ ጉዞ ለደቂቃም እንኳ ቢሆን ቆም ብሎ ለማስተዋልና ለማዳመጥ የከጀለ ወገን ባለመገኘቱ “ሽግግር” የተባለው እሳቤ ከተጸነሰበት አዕምሮ ስዕል የዘለለ ህልውና ሳይኖረው፤ ሳይጀመርና፤ ሳይወለድ ስለመቀልበሱ መወራት መጀመሩ ሌላው የእኛ አገር ፖለቲካ ልዩ ባህሪ ተደርጎ ሊወሰድ ይቻላል። እዚህ ላይ መንግስት እየወሰዳቸው ያሉትን የህግ ማሻሻያ እርምጃዎች፤ የመከላከያና የደህንነት ተቋማት ማስተካከያ እርምጃዎች፤ ወዘተ የሽግግሩ አካል አድርጎ እየተቆጠረ ከሆነ አሁንም የተዛባው መመዘኛ መነጽራችን ቀጣይ ችግር እንዳይሆን ያሰጋኛል።

ምክንያቱም ለማሻገሪያነት ይጠቅማሉ ተብለው እየተሻሻሉ ያሉ ህጎች” የፍትህ ስርዓት፤ የምርጫ ቦርድ፤ የሰላምና ብሄራዊ እርቅ ጉባኤና፤ የድንበር አከላለል አጥኝ ኮሚቴዎች እንቅስቃሴ በዋነኛነት የ፪፯ዓመቱን ኢህአዴጋዊ ጥፋት የማረሚያ እርምጃዎች ሲሆኑ እነሱም ቢሆኑ ከመሬት ከፍ እንዳይሉ ዋና ደንቀራ ሆኖ የተገኘው የጎሳ ፖለቲካ ልምሻ፤ ስርአት አልበኝነትና ህገወጥ እንቅስቃሴዎችን ለመግታት የተወሰደው እርምጃ አናሳነት በድፍን ሀገሪቱ የተፈጠረው የሰላም መደፍረስ ሽግግሩን ሳይወለድ ሊያመክኑት በመቃረባቸው ነው። ለዚህም ነው  በድፍረት “ ሽግግር ውስጥ ነን”  ማለት ሊያሽኮረምም የሚችለው።እንግዲህ በእኔ እይታ ያለፈውን አንድ ዓመት የምመዝንበት መለኪያ የሚመነጨው ከእነዚህ አሉ ሲባሉ ከሌሉ ፫ የመስፈሪያ ቁናዎች ነው።

የዚህ ውጤት ምን እያሳየን፤ ምንስ እያስተማረን ይገኛል?

ከላይ እንደጠቆምኩት በመጀመሪያው ረድፍ ተሰልፎ የሚገኘው አፋኝ የነበረው ኢህአዴጋዊው መንግስትና መዋቅሩ በቅጡ ሳይፈራርሱ፤ ወይም ተቋማቱን የሚዘውሩት ሰዎች ያለምንም የመመሪያና ያመለካከት ለውጥ፤ (አብዮታዊ ዴሞክራሲ ፍልስፍናን) ሙጥኝ እንዳሉ የተሰለፉበት፤ በሌላ በኩል እንደአሜባ እየተራቡ የሄዱት ፤ በዘር ተደራጅተው እንወክለዋለን ለሚሉት ጎሳ፤ ከመብት – እስከነጻነት ለማጎናጸፍ ተግተው የቆሙ ቡድኖች ከመቸውም ጊዜ በላይ “ከኛ ያልሆነ -ከነሱ ነው” በሚል ዘረኛ መለኪያ የራሳቸውን ወገን ሳይቀር በጭካኔ ለመጨፍጨፍ የተነሳሱ በሁለተኛ ዘርፍ፤ ፫ኛ ኢትዮጵያ እንደ ሃገር እንድትቀጥል መፍትሄው በዜግነት ላይ የተመሰረተ ስርዓት ሲመሰረት ነው የሚሉ  ወገኖችና በ፬ኛነት የፌስ ቡክና የሶሻል ሚዲያ አርበኞች የሚረጩላቸውን መርዝና መፍትሄ ገዳይ ወሬዎችን ተከትለው እንዳየሩ ጸባይ የሚናጡ ሰፊ ወግ ቃራሚ ትውልዶች በጅምላ ተቀላቅለው ለውጥ ፤ ወይም የለውጥ ሽግግር ፤ ወይም ተሃድሶ መሆኑ ባለየለት ጎዳና ውስጥ እየተጎናተሉ መትመማቸውን ቀጥለዋል።

እየጦዘ ያለው ልዩነት ዛሬም ባንድ ነገር ውሉን አልሳተም። የፖለቲካው አየር ቢያንስ ቢያንስ ልዩነቱን በጥሞና ከማስተናገድ ይልቅ እንደትናንቱ ለመደማመጥ ፈቃድ የማሳየት ባህሪ የፈጠረበት አይመስለም። ልክ እንደትናንቱ ሁለቱም ወገን በራሱ ልክ የሰፈረውንና፤ በራሱ ቁመት የለካውን ፤ መድሀኒት ለማስዋጥ በልህና በቁጣ አረፋ እየደፈቀ ለመጋት ከመውተርተር በስተቀር ላንድ አፍታም እንኳ ረጋ ብሎ ለመጠያየቅ አቅል እያጣ ነው። ዛሬም እንደትላንቱ በሀሳብና ባመለካከት የተለየውን ሁሉ በጠላትነት በመፈረጅ ሃሳቡን በሃሳብ ከመተቸት ይልቅ በግለሰብ ሰብእናና በቡድን ማንነት ፤ ወይም ያለፈ ታሪክ፤ ወይም ሀይማኖት፤ ዘር፤ቀለም፤ የተፈጥሮ ገጽታ እና በመሳሰሉት ከተነሳው ሃሳብ ጋር የረባ ቁርኝት በሌላቸው ቁጭት ፈጣሪ ጉዳዮች ላይ በቀጥታና በተዘዋዋሪ በመዝመት፡ በዝርጠጣ የማሸነፍ እቡይነት ተዘፍቆ በሃገርና ህዝብ ህልውና ላይ የምንግዴ ቁማር እየተስፋፋ መሄዱን እያስተዋልን ነው። ከሁሉ ሁሉ የሚከፋው ደግሞ ፤ ድርጊቱን እየፈጸሙ የሚገኙት በግራ-ቀኙ ያሉ ራሳቸውን “የዴሞክራሲና ሰብዓዊ መብቶች” ጠበቃ የሚቆጥሩ ወይም በዙሪያ-ገባቸው ያጀባቸው የኔ ቢጤ ህዝብ ባለዝና ያደረጋቸውና ቅድስና የሰጣቸው ፤ ከመግነናቸውም የተነሳ ለትችትም የሚከብዱ መሆናቸው ይበልጥ መከራችንን እያባባሰው ይገኛል።

ሌላው የዘመናችን ታላቁ ምጸት ደግሞ እነዚህ ራሳቸውን ባለም አንደኛ የዲሞክራሲ ጠበቃ ያደረጉ ግለሰቦችና ቡድኖች፤ የ፷ዎቹን ፖለቲከኞች “በእናቸንፋለንና-እናሸንፋለን” ተጫረሱ ፤ ጦሳቸውም እስከዛሬ ለኛ ተርፎናል “ በማለት እንዳላበሻቀጡ ሁሉ እነሱ ከነዚያ “የኮሙኒስት አርበኞች” በላቀ የቃላት ሽኩቻን እንደ ዋና የመፋጠጫና የመናቆሪያ ኳስ አድርገውት ማረፋቸው ነው። ፊንፊኔ፤ሸገር፤በረራ፤ ወዘተ…የሚሉት ቃላትን ማንሳት ለማሳያነት በቂ ናቸው።

ከሁሉ ሁሉ የሚያሳቅቀው ደግሞ ከዚያ ትውልድ የወረሱት  የዓላማ ጽናትን፤ ቁርጠኛነትንና ከራስ ይልቅ ለተገፉ ህዝቦች መስዋእት መሆንን የመሳሰሉ መልካም፤መልካም ልምዶችን ሳይሆን፤ ትውልዱንና ሃገሪቷን አሁን ለገባችበት ቀውስ ምክንያት በመሆኑ የተወገዘውን፤ ብሽሽቁን፤ ጥላቻውን፤ እርስ-በርስ መፈራረጁንና ለመጠፋፋት መጣደፍን በመሆኑ  ሸህ ጊዜ የሚደሰኩሩለትንና የሚናገሩለትን ዴሞክራሲ፤ የሚበቅልበትን ማሳ ከእህል ይልቅ ያራሙቻ ማራቢያ ማድረጋቸው ነው። ከዚህ የበለጠ በገዛ ራስ ላይ መዝመት ፤ ከዚህ የከፋ እንወደዋለንና እናከብረዋለን በሚሉት ህዝብና ሃገር ላይ መሳለቅ ከየትም ሊመጣ አይችልም።

ያለመደማመጡና  ወይም አውቆ የማደናቆሩ በሽታ እከሌ-ከእከሌ ብሎ ለመለየት ቢያዳግትም በይበልጥ ደግሞ ከተጨበጨበላቸው የሀገርና የድርጅት መሪዎች  አቅጣጫ ሲመነጭ በማሸማቀቅ አንገት ያስደፋል።  አሁን ባባታችሁ “አዲስ አበባ ያዲስ አበቦችና የሁሉም ኢትዮጵያውያን ነች” በማለት በግልጽ የሰፈረ “ባለ አራት ነጥብ ጥያቄ ለማስፈጸም “ ተነስተናል ያለን ሰላማዊ እንቅስቃሴ  “በመንግስት ላይ መንግስት “ለመተካት የታለመ ነው ብሎ ጥያቄውን ሆን ብሎ በማንሻፈፍ ማጦዝ ማንን ይጠቅማል?  በሌላ በኩል መንግስት ባለበት ሀገር አያሌ ባንኮች በጠራራ ፀሐይ ሲዘረፉ፤ የሰው ልጅ በደቦ ፍርድ ባደባባይ ተዘቅዝቆ ሲሰቀል፤ በይፋ የዛፍ ዝንጣይና ገጀራ የያዙ ቡድኖች በሰላማዊ ዜጎች ላይ ያነጣጠረ ዛቻና ማስፈራሪያ የታከለበት ሰልፍ ሲያደርጉ በጥሞና ያስተናገደና ዝምታን የመረጠ መንግስት በሚዛናዊነቱና በተአማኒነቱ ላይ ጥያቄ ቢነሳበት አያስደንቅም። ለቃሉ እጅግ አክብሮታችንንና እምነታችንን ከጣልንበት ጠቅላይ ሚንስትር አንደበት  ሲወጣ መስማታችን ደግሞ አንገታችንን አስቀረቀረን። ቀጥለንም እርስዎንና ቃልዎን አምነን እስከዛሬ ደርሰን ነበርና እንግዲህ ያመነው ቃልዎ ከሚዛን ጎሎ ስናገኘው ብንጠረጥረዎ በኛ ይፈረዳል? ያሁኑ ይባስ ቢባልስ ምን ሃሰት አለው? በማለት የድፍረት መልስ ለመስጠት ተገደድን።

አመቱን ያባተው በዶክተር አብይ መንግስት እየተመራ ያለው እንቅስቃሴ ሌላም የተፋለሰ ያስተሳሰብ ግጭትም አስተናግዷል። ድንግርግሩም ጥቂት የማይባል ወገን፤ ሊሆን የማይችል ወይም እንዲሆን በማይጠበቅ ምኞት መሰል ተስፋ የመንተክተክና የመብተክተክ፤ ቃል ካልተገባበት ቃልን የመጠበቅ አዝማሚያ ማሳየቱ ነው። ይበልጥ ግልጽ ለማድረግ ፡ ባለፈው አንድ አመት እየመራን ያለው “የተጨበጨበለት ለውጥ አራማጅ” ቡድን እጅግ አብዝቶ በግፈኛነቱና ባፋኝነቱ የሚታወቀውን የራሱን ቡድን አውግዞና ኮንኖ ብቅ በማለቱና ፤ ከላይ የጠቀስኳቸውን በለውጥነት የተፈረጁ እርምጃዎችን በመውሰድና ከሁሉም በላይ ሊረሳ ተቃርቦ የነበረውን “ኢትዮጵያዊነት” ከፍ አድርጎ በመዘመር መጣ እንጅ አንዴም እንኳ ተሳስቶ “ኢሃአዴግ ፈርሷል” አላለንም ወይም የምከተለውን “አብዮታዊ ዴሞክራሲ “ መስመር እቀይራለሁ የሚል ቃል አልሰጠንም።

ውነታው ይሄ ሆኖ እያለ ላለፉት ፪፯ ዓመታት የምናውቀው ዎያኔ ኢህአዴግ ካስለመደን ባህሪው የተለየ በማሳየቱ ብቻ ላይ ተመስርተን የየራሳችንን ትንበያ ማድረጋችን እርግጥ ነው። ይሁንና ከትንበያ አልፈው ተርፈው ምኞታቸውን እንደ እውነት ቃል የወሰዱ ወገኖች ኢሃዴግ “ አብዮታዊ ዴሞክራሲን” ትቻለሁ ብሎ ካላረጋገጠልን ለውጥ የለም፤  የሚል አጠቃላይ ለለውጥ የተደረገውን እልህ አስጨራሽ ትግል የዎያኔ-ኢሃዴግን መስመር ለማስቀየር እንደተደረገ በሚያስመስል  የማይረባ አተካራ ውስጥ ቀስ በቀስ እየገቡ በመሄድ እየዋለ ሲያድር ደግሞ ዋናው የትግል አቅጣጫና የመታገያ መሳሪያ ለማድረግ ተግተው ወደመስራቱ እየተሸጋገሩ ነው። በበኩሌ ከዚህ የበለጠ ያስተሳሰብ ስካር ወይም መደናበር ታይቶም ተሰምቶም አይታወቅም ባይ ነኝ።

በመጀመሪያ ስለዎያኔ ኢሃዴግ የፖለቲካ መስመር መጨነቅ ያለበት የድርጅቱ አባልና ደጋፊ እንጅ ሌላው ከኢሃዴግ ውጭ ያለ ህዝብ ሊሆን አይገባውም፤ ከሁሉ ሁሉ ደግሞ ከትከት አርጎ የሚያስቀው ጥያቄው “በዜግነት ላይ የተመሰረተ የፖለቲካ አራማጅና ደጋፊዎች ነን”  ከሚሉ ወገኖች ጎልቶ መደመጡ ነው። ዾር አብይና ቡድናቸው የሚያደርጉትን የለውጥ እንቅስቃሴና አቅጣጫ ለመመዘንና ለመተቸት የሚቃጣቸውም ለ፪፯ዓምታት በተጠራቀመ የህዝብ ትግል የተገኘውን ለውጥ ለማስፈጸም በሚያደርጉት ደፋ ቀና ሳይሆን ለ፵ ዓመታት የዘለቀ ትግል መነሻው አድርጎ የተነሳን ይፖለቲካ ቡድን መስመር በማስቀየር ላይ ማተኮራቸው ነው።

“የኢትዮጵያን አንድነት እናስከብራለን” የሚለውን ወገን እንመራለን ያሉና ፤ እነሱን ተከትሎ ባጃቢነትና በወገንተኛነት ለተሰለፈውም ወገን ሌላም ጥያቄ አለኝ፤  ካንድ አመት በፊት ሲጠይቀውና ሲታገልበት የነበረው “ወደሰላማዊ ትግል ለመግባት” ኢህ አዴግ እንዲያከብር የጠየቀው ከላይ “የለውጡ ትሩፋት” እየተባሉ የተወደሱትን እርምጃዎች እንደነበር ለመዘንጋት ገና አልረፈደም። ይሁንና ቅድመሁኔታዎቹ እንደግብ ተቆጥረው ይሁን ወይም በሌላ በሃገሪቱ ላይ ታይቶ ተሰምቶ የማይታወቅ አበሳ በዜጎች ላይ እየወረደ እያዩ ድምጻቸው የሰለለው ከምን የተነሳ ይሆን? የግፍ ትልቅና ትንሽ የለውም፤ ፍርደ ገምድልነትም፤ ሚዛን አልባነትም፤ አልጠግብ ባይነትም ፤ ሁሉም ካንድ የዘርኝነትና ፋሽስትነት ግፍ ቋት  የተጨለፉ ናቸው። በምንም መለኪያ የሚያለቅሱ ህጻናትና አቅመ ደካማ ምንዱባን በበዙባት ምድር ማንም ተነጥሎ ነጻ፤ ተነጥሎ ፍትህ ሊያገኝ እንደማይችል ኢትዮጵያን እንወዳለን ካሉ መብት ታጋዮች የበለጠ መገንዘብ የሚችል አይኖርም።  ቢያንስ ቢያንስ ባለጊዜ ወዳጆቻቸውን እየተስተዋለ ማለትን ማንን ገደለ?

ምን ተሻለን? እንደኔ እንደኔ የነዶ/ር አብይን ቡድን ከአሸጋጋሪነት ያለፈ ፤ የህዝብንና የሃገርን ሰላም አስጠብቆ ወደ ፍትሃዊና ዴሞክራሲያዊ ስርአት የሚወስዱንንን ተቋማት በነጻነትና በፍትሃዊነት እንዲደራጁ ከማገዝና ከማመቻቸት የዘለለ ፤ ተልእኮ እንዲኖራቸው አልጠብቅም። ስለዚህም ነው ለምን ከዘር ድርጅት አልወጡም፤ ምንትስዮ የሚባል ፍሬ የለሽ እሰጥ-አገባ ውስጥ መግባት ከኳሷ ላይ አይናችንን የሚያሸሽ ነው የምለው። ምክንያቱም እኔ ኢሃዴግ ወይም ደጋፊ አይደለሁምና። እንደ እኔ የኢሃዴግ ደጋፊም፤አባልም ያልሆኑ ማተኮር የሚገባቸው ከነግድፈቱ የተጀመረው በነጻ ሃሳብን የማንሸራሸሪያ በር ወለል ብሎ ተበርግዶ ባለበት በዚህ አጋጣሚ እድሉንና ህጋዊ የዲሞክራሲና የሰባዊ መብቱን በመጠቀም ቶሎ ብሎ የዜግነት የኢኮኖሚ፤የፖለቲካና ማህበራዊ መብቱን የሚያስከብር ቡድን እንዲቋቋምና እንዲጠናከር የሚጠበቅበትን አስተውጽኦ ማድረግ ነው።

ክርክራችንና ትኩረታችንም ሊሆን የሚገባው የዶክተር አብይ መንግስት ከማንኛውም ጉዳይ በላይ ቅድሚያ ሰጥተው ህግና ስራትን የማስከበር፤ ባስቸኳይና በከፍተኛ ፍጥነት የሽግግሩ ዋና ዋና ምሰሶዎች የሆኑት፤የብሔራዊ እርቅ፤ የፍትህ ስራት በቅጡ ተደራጅተው ወደ ስራ እንዲገቡ የማስደረግ፤ የምርጫ ቦርድ፡ የሲቪል ማህበራት ማደራጃ ህግ፤ የሚዲያና ብሮድካስቲንግ ወዘተ የመሳሰሉት ተቋማት በቶሎ ተደራጅተው ወደ ስራ እንዲገቡ ጫና ማሳደሩ ላይ ማተኮሩ ወሳኝ ይመስለኛል;። ከዚሁ በተጓዳኝ እነስክንድር የጀመሩት አይነት ይሲቪል መብቶች ላይ የሚሰሩ ተቋሞችን በማበራከት በሃይል ስልጣኑን ከህዝብ ሊነጥቁ የሚዳዱ ቡድኖችንና መንግስትን መገዳደር፤ የህዝብን መብት ማስከበሪያ መሳሪያ አድርጎ መዘጋጀት እጅግ እጅግ ወሳኝ ነው።

ኢሳትም ሰሞኑን ካሳየን እንካስላንቲያ የመሰለ ጨዋታና ብሽሽቅ ወጥቶ እንዳለፉት ጊዜያት ሁሉ ባደገኛ የዝቅጠት ቁልቁለት ላይ እይተንደረደርች ያለችውን አገራችንን ለመታደግ የሚያስችሉ በምክንያትና በእውቀት የተመሰረቱ መረጃዎችን ወደማቀበሉ ሊመለስ ይገባዋል ። ባብላጫው እንቶ-ፈንቶ በማውራት እሳት እያነደደ ያለውን ሶሻል ሚዲያ ቁጥር ከፍ ማድረግ ለጊዜው የተወሰኑ ሰዎችን ስሜት ይይዝ እንደሆነ እንጅ በረጅም ርቀት ከጥቅሙ ጉዳቱ ሊያመዝን እንደሚችል  መታዘቤ ሰላም ነስቶኛል። ለምን ይበጃል? ማንንስ ይጠቅማል? ጎበዝ ወዴት እየሄድን ነው?

እስኪ ትንሽ ሰከን ብለን፤ ከስሜትና ግለ-ትምክህት ወጣ ብለን እየሰራነው ያለውን እናስተውል። በተግባር እየከወነው ያለው ድርጊት የተቋቋምንበትንና የተነሳንበትን ኢትዮጵያን ወደ ነጻና ዴሞክራሲያዊ ስርዓት የማሸጋገር ህልማችንን እውን ለማድረግ የሚጠቅም ወይስ የሚጎዳ ነው ብለን እንመዝን። ያልነው ሁሉ እውነት እንኳን ቢሆን እስኪ ከፊታችን የተደቀነውን አገራችንን የመበታተንና እርስ-በርስ የመተላለቅ አደጋ ከመቀነስ አኳያ ሊኖረው የሚችለውን በጎ አስተዋጽኦ እንመዝነው።  የምናደርገውና ካንደበታችን የምናወጣቸው ለተሸካሚ አይደለም ለሰሚ የሚከብዱ ዘለፋዎችና ሽሙጦችስ እንደኔ ትውልድ “ፖለቲከኛ” “ልክ-ልኩን ነገረው፤ አገባለት፤ …” ከማለት የዘለለ የሚሊዮኖችን ሬሳ ደርድሮ ነጥብ የማስቆጠር ጨዋታ ምን የሚሉት አዋቂነት፤ አሳቢነትና ተቆርቋሪነት ነው? የኋላ ኋላ ያልተጠበቀ ጉዳት ቢደርስ በሌላ ላይ ጣትን መጠቆም ወደራስ የሚያጮልቁትን ጣቶች እረፍት መንሳት እንዳይሆን፤ “ከእናንተ መሃል አንድም ሃጢያት ያልሰራ ይውገራት…” እንዳለ ክርስቶስ።

ከሁሉም በላይ እያንዳንዳችን በግልም ሆነ በጋራ የምናደርገው ድርጊት ያለማቋረጥ ደሙ እየፈሰሰ በርሃብ አለንጋ መጠበሱ ሳያንሰው በአጉራ ጢነኞች ቡጢ ለስደትና ለርሃብ ተጋልጦ ላለው ኢትዮጵያዊ ምኑ ነው? አይናችንን ከኳስዋ ላይ እንደናነሳ ከማድረግ የዘለለ፤ ኢትዮጵያን አድነን ወደ ዘላቂ ሰላምና ዲሞክራሲያዊ ሽግግር የተጀመረውን ጉዞ አቅጣጫ ከማስቀየስ የዘለለ፤ የትኛውን እንባ ይጠርግለታል? የትኛውንስ በደል ያጸዳለታል? በዚህስ ይበልጥ ተጠቃሚ የሚሆነው ማን ነው?

እንደኔ እንደኔ አገሩን የሚወድ፤ የኢትዮጵያን ደህንነት የሚሻ ዜጋ ከመቸውም ጊዜ የበለጠ አስተውሎ የሚራመድበት፤ ካንደበቱ የሚያወጣቸው ቃላቶች የመረጠውን አገር የማዳን ጎዳና የሚያለሰልሱ እንጅ ኮረኮንች የማያደርጉ መሆናቸውን መመርመር ይኖርበታል።

ይህን ማድረግ ግድ የሚለን ኢትዮጵያ ከማናችንም ግለሰባዊ ስምና ክብር ወይም ዝና በላይ ስለሆነች ነው።

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s