አንድ ሀገር! አንድ ሕዝብ! ኢትዮጵያችን ሕዝባዊ ንቅናቄ (ኢትዮጵያችን) – (ልሳን ኢትዮጵያችን ቅጽ 3 ቁጥር 5)
ሚያዝያ 05 ቀን 2011 ዓ.ም.

ኢሕአዴግና ደጋፊዎቹ የ“ለውጥ” እንቅፋቶች

የድምጽ ቅጂውን ለማድመጥ እዚህ ይጫኑ https://www.youtube.com/watch?v=oRK2p86xt7c

ኢትዮጵያችን እንደ ሀገር ለመኖሯ ጥርጥር የለንም። ትላንትም ዛሬም ነገም ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኖራለች! ይህ ለኢትዮጵያ እንደ ሀገር የህልውናዋ ጉዳይ በበርካታ ሕይወት የተገነባ ነው። ለሀገራችን ልምላሜ ፣ ለዘላለም ሀገር ሆና እንድትኖር የጀግኖች ልጆቿ አጥንትና ደም የዘላለም ሕይወት ሆኗታል ወደፊትም ይሆናታል። በትንሹ የሦስት ሺህ ዘመን ታሪክ ያላት ሀገራችን ወቅትን እየጠበቀ የተፈታተናት የባዕድ ወራሪ በርካታ ልጆቿን ቢነጥቃትም ኢትዮጵያዊ ሀገርነቷን አላጣችም። በነገሥታት ዝና እና የይገባኛል ውጥረት ያሳደገቻቸውን ልጆቿን አጥታለች።  በዘመነ መሳፍንት ሹኩቻ ሁሉም ልንገሥ ባይ የቀሰቀሰው የእርስ በርስ ግጭት ያተረፈው ቢኖር ክቡር ሕይወትን መገበር ነበር። ኢትዮጵያ አንድነቷን አጠናክራ በአንድ ማዕከላዊ አስተዳደር ትተዳደር ዘንድ የተከፈለው መስዋዕትነት ቀላል አልነበረም። በተለይ ከዓፄ ቴዎድሮስ አገዛዝ ወዲህ ሀገራችን እንደገና በአንድ ማዕከላዊ መንግሥት ብትተዳደርም የእርስ በእርስ ፍትጊያውም ጋብ አላለም፤ የባዕዳን ትኩረትም አልቀነሰም። ምስጋና ይግባቸውና ለጀግኖች ልጆቿ ዛሬ አርበኞች ለምንላቸው “ለሀገር መሞት ኩራት” ብለው እኛ እንድንኖር ሞተውልናል። አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ሰንደቅ ዓላማችን ዘላለማዊ መለያችን ይሆን ዘንድ የነፃነት ተምሳሌት አድርገውታል። ዓፄ ቴዎድሮስ በመቅደላ፣ ዓፄ ዮሐንስ በመተማ ሰንደቅ ዓላማችንን በአጽማቸው አውለውልበዋል። አሉላ አባ ነጋ በዶጋሌ ሰንደቅ ዓላማችን ለዘላለም ይውለበለብ ዘንድ ታሪክ ሰርተዋል። ምኒልክ በዐድዋ በሰንደቅ ዓላማችን ወራሪ ጣልያንን ድባቅ መምታት ብቻ ሳይሆን የነፃነት ተምሳሌት፤ የአፍሪካ ኩራት አድርገውታል። በአምስቱ ዓመት የጣሊያን ወረራ አርበኞቻችን በሰንደቅ ዓላማችን አዋጊነት ቅኝ አገዛዝን ከሀገራችን ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካ አርኣያ፣ ተምሳሌት ለነፃነት ይሆን ዘንድ ሕይወት ከፍለውበታል። “ጀግንነት እንደ ኢትዮጵያ!” ብለው የአፍሪካ ሀገሮች ለነፃነት ክብራቸው የእኛን፣ የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ በተለያየ አቀማመጥ አውለብልበው ዘምረዋል። ታሪክ ስንል ትንሽ እውቀት ያለው ዜጋ ይህንን ይገነዘባል። እንጻፍ ብንል የማያልቅ፣ የማያሳፍር፣ ተዓምር የሚያሰኝ ሳይሆን የሆነ ታሪክ አለን። ዓለምና የወረሩን እንኳ ሳይቀሩ እንደ ሀገር ስለ ኢትዮጵያዊነታችንና ስለ ክብራችን፣ ኩራታችን፣ ጀግንነታችን መስክረውልናል።

ኢትዮጵያ ማንም ቅኝ ገዥና ወራሪ ጠፍጥፎ ያልሰራት በመሆኗ ልንኮራ ይገባናል። ኢትዮጵያችን ቅኝ ገዥዎች ሊተክሉባት በአቀዱት ሃይማኖት እጇን ያልሰጠች፣ ለባዕድ ቋንቋ ያልተገዛች የራሷ ቋንቋ ባለቤት እና ሆሄያት ያላት ብቸኛ አፍሪካዊ ሀገር በመሆኗ እንኮራለን። ኢትዮጵያ እስልምና ሃይማኖትን ተቀብላና አማኙንም አክብራ በአንድ ቤት ከክርስትና እምነት ጋር አስተቃቅፋና አቅፋ በኖረች ሀገራችን እንኮራለን። ኢትዮጵያ የመጀመሪያዋ የሰው ልጅ መገኛ ታሪካዊ የድንቅነሽ/ሉሲ እናት መሆኗ ያኮራናል። የታሪካዊ ቅርሶች አክሱም፣ ላሊበላ፣ ፋሲለደስ፣ ሐረር ግምብ ወዘተ. ተጠሪ በመሆናችን እንኮራለን። ኢትዮጵያ በረሃን መጋቢ፤ ምድረበዳን ሀገር ያደረገች የዐባይ ባለቤት መሆኗ ያኮራናል። ኢትዮጵያ ብቸኛዋ የዋልያ/ኒያላ፣ ጭላዳ ዥንዠሮ ዋሻ በመሆኗ እንኮራለን። ኢትዮጵያ ከሰማንያ የማያንሱ የቋንቋ ባለቤትና የጎሳ/ነገዶች እናት በመሆኗ ኑሪልን፣ ክበሪልን እንላለን። የ13 ወር ፀጋ፣ የራሳችን የወራትና ባህላት አቆጣጠር ያለን ብቸኛ የጳጉሜን ባለቤት የመሆናችን ምስጢር ያኮራናል። የትግሬ ጭፈራ፣ የጎጃም እስክስታ፣ የጎንደር አዝማሪ፣ የወሎዬ ከምከም፣ የኦሮሞ ረገዳ፣ የጋምቤላ እምቢልታ፣ የሲዳማ ወላይታ፣ የጉራጌ አሽቃሮ፣ የእስላም ዝያራ፣ የክርስቲያን ሽብሸባ ወዘተ. አድማቂ ባህል ባለቤት ኢትዮጵያችን ታኮራናለች። የገና ጀምበር ቢባልም ቀንና ምሽቱ ያልተዘበራረቀ እኩል አመቻችቶ ለተቸራት ሀገራችን እንኮራለን። መጤነታችን ኢትዮጵያ፣ እድገታችን ኢትዮጵያ፣ ሕይወታችን ኢትዮጵያ፣ ፈጣሪያችን ኢትዮጵያ፣ ሞታችን ኢትዮጵያ በመሆኗ ክብር ይሰማናል።

አዎ! ስለ ሀገራችን ውብነት እንተርክ ካልን “መኃልዬ ዘማህሌት ኢትዮጵያ” ለእኛ ብቻ ሳይሆን ለዓለምም ከነድህነቷ ውብ ናት። እኛ ሀገር ስንል ከቃላት በላይ እየገለጽናት ነው። እናታችን ናትና ችግራችን ችግሯ፣ ረሃባችን ረሃቧ፣ ልቅሷችን ልቅሶዋ፣ ደስታችን ደስታዋ፣ ሀዘናችን ሀዘኗ መሆኑን በመገንዘብ ነው።

ሀገራችን ኢትዮጵያን ዛሬ ለደረስንበት ያደረሳት በተለይ በአለፉት 50 ዓመታት በገጠሟት ብልሹ አገዛዞች ምክንያት ከዓለም የሥልጣኔና ዕድገት ደረጃ መራመድ አለመቻሏ ነው። በነፃነቷ ያልተደፈረች አፍሪካዊ ሀገር እንደመሆኗ ተፈጥሮ የሰጣትን ሀብት ተጠቅማ ልጆቿን መመገብ አለመቻሏ፤ የእናታችን አለማዘን ሳይሆን ቀፍድደው የያዟት፣ በሀገር ስም የተስገበገቡባት፣ በሀገር ስም ትውልድ የፈጀባት አገዛዞች ኢዴሞክራሲያዊ አካሄድ ያመጣባት ጣጣ ነው። ሲባባስም ሀገር ከሀዲ በዘርና በቋንቋ ከፋፍሎ ለአለፉት 28 ዓመታት ቀፍድዶ መያዝ ብቻ ሳይሆን ሊበጣጥሳት ከአራቱም ማዕዘን እየወጠራት ይገኛል። በብሉሹ አስተዳደር ሥር በመውደቋ ክብሯን ረሃብ፣ ችግር፣ ጉስቁልና፣ ስደት ደፍሯታል። አገዛዞች በተቀያየሩ ቁጥር እድገቷ እስር ቤቶች ሁነዋል። ማንኛውም አገዛዝ ሊመለከተውና ትኩረት ሊሰጠው ያልቻለው የሕዝብ መባዛት፣ መዋለድ እጅጉን እያሻቀበ ዛሬ በመቶ ሚልዮን የሚቆጠር ሕዝብ አቅፋለች። የብልሹ አገዛዝ ያመጣብንን ድህነት፣ ኋላ ቀርነት፣ ድንቁርና፣ በሽታ ተገን በማድረግ የአንድ ዘር የበላይነት እንደነበርና ሀገር እንዳስተዳደረ ዘረኝነትን መለዮው አድርጎ 28 ዓመት የገዛው ኢሕአዴግ በረቀቀ ዘዴ ሀገራችንን ከአስከፊ የእርስ በርስ ግጭት ሊከታት እየተንደረደረ ነው።

ሀገራችን ኢትዮጵያን በአንድነቷና በክብሯ የቀኑባት ከጥንት እስከዛሬ አላረፉላትም። የኦርቶዶክስ እምነቷን ለማጥፋትና ለማሽመሽመድ ባዕዳን ኃይሎች ሀገር በቀል ከሀዲዎችን በእጅ አዙር በመግዛት በግራኝ አሕመድ፣ በዮዲት ጉዲት ዘመን ቢጥሩም በርካታ አብያተ ክርስቲያናትን ከማቃጠልና ከመዝረፍ ባሻገር በተከፈለ ከባድ መስዋዕትነት ሃይማኖቷን አስጠብቃና ድል መትታ ዛሬም አለች፤ ነገም አልፋ ኦሜጋ ትኖራለች።  የድርቡሾች ጥቃት፣ የእንግሊዞች ዝርፊያ፣ የጣሊያን ወረራ በርካታ ቅርሶቻችን እንዲወድሙና እንዲዘረፉ ምክንያት ቢሆኑም ሀገራችን ግና ቀጥላለች። ጥንትም፣ አሁንም፣ ወደፊትም ኢትዮጵያ ነች።

በሀገራችን ታሪክ ግራኝ አሕመድ ለ16 ዓመት፣ ዮዲት ጉዲት ለ40 ዓመት ወያኔ/ኢሕአዴግ ለ28 ዓመት አማራንና ኦርቶዶክስ እምነትን ለማጥፋት ጥረዋል። አልተሳካላቸውም። 28 ዓመት የገዛው ህወሓት/ኢሕአዴግ እራሱ አውጥቶ፣ እራሱ አጽድቆ ሀገርና ሕዝብ ላይ በከመረው ሕገ መንግስት ዛሬ ሀገር ልትበተን፣ ሕዝብን እርስ በእርስ ሊያባላ የጫረው እሳት አድራጊዎችን እንደሚፈጅ በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል። ጥፋት ቢኖርም ኢትዮጵያችን ትኖራለች። ዛሬ በመንግሥት ደረጃና በአንዳንድ የዘር ድርጅቶችና በኢሕአዴግ አገዛዝ የጥቅም ተካፋዮች ተግባር ላይ ሊውል ተቀጣጣይ ፈንጂ የሆነው ሕገ መንግሥት አንቀጽ 39 እና 47 ላይ ተደርሷል። ኢትዮጵያን የመበታተን ፈንጂው የተቀበረባቸው እነኚህ አንቀጾችን ተግባራዊ ለማድረግ “ጊዜው ዛሬ ነው” ብለው ለተነሱ ኃይሎች በሀገራችን ላይ ጉዳት ቢያደርሱም የመጨረሻው ተሸናፊዎች እንደሚሆኑ አንጠራጠርም። ዘርንና/የቋንቋ ተገን ያደረገ የግዛት አከላለል፤ ተዋዶና ተከባብሮ የኖረን ሕዝብ መከፋፈል፤ ከአቀንቃኝ ድርጅቶች፣ አክቲቪስቶችና ዘላለማቸውን ለመጣው ሁሉ አሸርጋጅ ምዑራን በቀር በየትኛውም ዘር ኅብረተሰብ ዘንድ ተቀባይነት የማይኖረው ውሃ በወንፊት ሩጫ ነው።

በኢሕአዴግ አገዛዝ ዘመን ለሥራ ዋስትናና ለሌላ ጥቅማ ጥቅም አገዛዙን ደግፋችሁ ላላችሁና ዛሬም ኢትዮጵያዊነት ዝማሬ ላስበረገጋችሁ መስመራችሁ ከሀገርና ሕዝብ ጎራ ይሆን ዘንድ ምክራችንን እንለግሳለን።  ለአለፉት 50 ዓመታት የአምባገነኖችና የዘራፊዎች በትር ዘር ሳይመርጥ ሁሉም ላይ ያረፈ የመሆኑ ሀቅ እየታወቀ ሀገር እንደበደለች ታሪክ ሲፈጠር መስማቱ ማብቃት ይኖርበታል። ኢትዮጵያ ክብሯንና ማንነቷን ጠብቃ ትኖር ዘንድ ወደድንም ጠላን ዘርንና ቋንቋን ተገን ያደረገ አከላለል ማብቃት ይኖርበታል። ዘርንና ቋንቋን፣ ሃይማኖትን፣ ፆታን ተገን አድርጎ የሚፈጠር የፖለቲካ ድርጅት ማብቃት ማለት የኢትዮጵያን አንድነት ማስጠበቅ መሆኑን አጥብቀን እናስቀምጣለን። የጎሳዎችንና የነገዶችን መብት ማወቅ ማለት ተካሎና መስመር አስምሮ አትድረሱብኝ የማይሰራ ቅዠት ነው። የዴሞክራሲ መብት ሀገር ለመገነጣጠል፣ አንድ ጎሳ/ነገድ በሌላ ላይ ለማነሳሳት ሊሆን አይገባውም። ይህ እንዲያበቃ “ሀገር የመገነጣጠል” ቁልፉ ኢሕአዴግና ሕገ መንግሥቱ ላይ በመሆኑ ሁለቱም ማብቃት እንዳለባቸው አጠንክረን ስንታገል ኦሮሞ፣ አማራ፣ ትግሬ፣ ጉራጌ፣ ወላይታ፣ ጋምቤላ፣ አፋር፣ ኦጋዴን፣ ሐደሬ፣ ሲዳማ፣ አኝዋክ፣ ሌላም ሌላ ችግር የለባቸውምና ከድሮው በበለጠ የዜግነት መብታቸውን አስከብረው እንደሚነሱ አንጠራጠርም።ችግራቸው የዜግነት መብታቸውን አግኝንተው፣ ጎሳና ነገድ ሳይመርጡ በመረጡት ተመርተው፣ ወሰን ሳይገድባቸው የትም ሠርተው፣ የትም ተምረው፣ የትም ኑረው፣ አንድ ሰንደቅ ዓላማ አውለብልበው፣ ስለ አንድ ሀገር ዘምረው የኢትዮጵያን ትንሳዬ የሚያዩበትን እንጂ የናፈቁት፤ “አውቅልሃለው፣ ወክዬሃለሁ” ባይ ሀገር ተረት ለሆነችባቸው ፖለቲከኞችን አይደለም።

በመገነጣጠል አባዜ በቅዠት ለተዋጡ “ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር” ስንል ጉዟችን ኦሮሞን፣ ትግራይን፣ አማራን እና ሁሉንም የተለያዩ ጎሳና ነገዶች ይዘን እንደሆነ ሊሰመርበት ይገባል። የመጨረሻ ግቡ ኢትዮጵያን ለመበተን ካልሆነ በቀር ኦሮሚያ መንግሥት ሊሆን አይችልም። ትግራይ በህወሓት/ወያኔ ቁጥጥር ሥር ተገንጥላ አትኖርም። የምሥራቅ ኢትዮጵያ ሶማሌ ወገኖቻችን ከኢትዮጵያ ሊለዩ አይታሰብም። ደቡብ ኢትዮጵያውያን፣ ጋምቤላ፣ አፋር ዛሬም ለኢትዮጵያ ዘብ ቋሚዎች ናቸው።  ለዚህም ነው የመገነጣጠል አባዜ ውድቀቱና ጉዳቱ ለሁሉም እንደሚሆንና ማንም ሳያሸንፍ መልሳ ኢትዮጵያ አንድ ሀገር! ሆና እንደምትቀጥል ትንቢት ሳይሆን ሀቅ ነው። ድህነቷ ጠንካራ መሠረቷን አላሳጣትምና።

የአረቃቀቁ ታሪክ አድሎዓዊ፣ አጨቃጫቂና አስቀድሞ በታቀደ ተግባር ስለሆነ የኢሕአዴግ ሕገ መንግሥት ከፀደቀበት ወቅት አንስቶ ለትልልቅ ብሔራዊ ችግሮች መፈጠርና መባባስ ዋነኛው ምክንያት ሆኗል። ይህንን ሕገ መንግሥት መሠረት አድርገው ሥራ ላይ ከዋሉት ዕቅዶች በቁጥር አንደኛው  ዘርንና ቋንቋን መሠረት ያደረገው የፌደራል ሥርዓት ተብዬው ነው።

እንደ ተመሠረተበት ሕገ መንግሥት ሁሉ የፌደራል ሥርዓቱም ከወላጁ ይህንኑ አጨቃጫቂና አድሎአዊ ባህርይ ወርሷል። የኢሕአዴግ ፌደራል ሥርዓት ተብዬው እነዚህ የሕገ መንግሥቱ አስከፊ ገፅታዎች በተግባር በመሬትና በሕዝብ ላይ በሥራ ስለሚተረጎም የሚያደርሳቸው ጥፋቶች ጥልቀትና ስፋት በወረቀት ከሰፈረው ሕገ መንግስት በብዙ እጅ የከፋ ነው።

ዘርንና ቋንቋን ተገን ያደረገው ፌደራል ክልሎችና እነዚህን የሚያስተዳድሩት መንግሥታት ለአለፉት ሁለት አሥርተ ዓመታት በላይ ህወሓት መር የነበረው የፌደራል ሥርዓት ዓይነተኛው መገለጫ  ናቸው። እነዚህ የፌደራል ክልሎች የተመሠረቱት ወይም በተገቢው አነጋገር ኢትዮጵያን የሸነሽኑት ከብዙ ዓመታት ቀደም ብሎ በረሃ በታቀዱ ለም መሬት የመያዝ ውጥኖች፣ በመናኛ የ“ታሪክ” ማስረጃዎች፣ ቋንቋዬ የተነገረበት ሁሉ የክልሌ አካል ነው ወዘተ. በሚሉ አደናጋሪ ምክንያቶች ነበር።

እነዚህ ክልሎች የተመሰረቱባቸው ምክንያቶችና የተካሄደው ሽንሸና፡ በሕገ መንግሥቱ የተቀመጡት አንቀጾች በሥራ ላይ መዋል ጋር እየተዳመረ በጥቂት ጊዜያት ውስጥ ችግሮች ይከሰቱ ጀመር። ከክልሌ ውጣ፡ “ማንነቴ” ይከበር፣ ቋንቋዬ ይከበር፣ የራሴ ክልል ልሁን ወዘተ የሚሉ ለመፍትሔ ቀርቶ ለማስተናገድም፣ ለማጥናትም የሚያውኩ ጉዳዮች በየክልሎቹ ይነሱ ጀመር፡ አሁንም እየተንሱ ነው።

እነዚህ ከውሽልሽሉ ሕገ መንግሥት አረቃቀና ከእሱው የእንግዴ ልጅ የፌደራል ሥርዓቱ አመሠራረት የፈለቁት አይቀሬና በተፈጠሩበት አሠራር መላ የማይገኝላቸው ችግሮች የሕዝብ ሰላም ከማደፍረስና ውጥረት ከማንገስ አልፈው ወደ ጎሳ/ዘር ግጭቶች፣ በሺዎች፣ በአሥር ሺዎችና በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ የማህረሰብ አባላት መፈናቅልና የንብረትና ሕይወት መጥፋት ዳፋ ሆኑ። እየሆኑም ነው። ይኸው የሀገር ውስጥ መፈናቀል በአሁኑ ወቅት ከ 3 ሚሊዮን የሚበልጡ ዜጎችን ሰለባ አድርጓል። ቋንቋንና ዘርን ያማከለው ፌደራል ክልላዊ ሥርዓት ሲጸንስም፣ ሲወለድም፣ ሲድህም፣ ጥርስ ሲያወጣም፣ ወፌ ቆመችሲባልም እንደጥላ የተከተለው በሰላም ይኖሩ በነበሩ ጎሳዎች/ነገዶች መሃል መፈራራት፣ መጠራጠር፣ ስጋት፣ ግጭትናመፈናቅል ነው። በድሃ ሀገራችንና ሕዝብ ላይ ይህንን ችግር ጨምሮላታል። የፌደራል ክልል ሥርዓቱ ከሃያ ስምንት ዓመት ዕድሜው በኋላ መገለጫው ወይም አሻራው ይኸው በየክልሉ ውስጥ እርስ በእራስ፣ በክልልና-ክልል መሃል ባሉ ጎሳዎች/ነገዶች መሃል መቃቃርና በሰላም ተረጋግቶ አለመኖር በተጨማሪ የወሰን ነጠቃም አይዘነጋም። ሰሞኑንም አድማሱን አስፍቶ የተወሰኑ ዘሮች በተለይ አማራው፣ ጉራጌው  ላይ ያነጣጠረ የጅምላ ጭፍጨፋ፣ ንብረት ማውደም፣ ሴቶችን መድፈር የመጨረሻው መጀመሪያው በሰሜን ሸዋ የተለያዩ ወረዳዎች ተጀምሯል።

በአጭሩ ሕገ መንግሥቱ፡ ፌደራል የክልል ሥርዓትን አስከተለ፡  የፌደራል የክልል ሥርዓት ደግሞ በበኩሉ በሕዝብ  መሃል መፈራርትና መፈናቀልን አመጣ። ይህ ጉዳዩ በተለይ በአሁኑ “የለውጥ” ጊዜ በኢትዮጵያችን ላይ እያደረሰ ካለው ከፍተኛ የሰላምና የፀጥታ ስጋት ምክንያት ዘላቂ ፈውስ እስኪገኝለት ማስታገሻ መፍትሔ እንደሚያስፈልገው ግልፅ ነው። ነገር ግን ከላይ በአጭሩ እንዳየነው በህወሓት መሩ ኢሕአዴግ በሥራ ላይ የዋለው ሕገ መንግሥትና መዘዙ የሆነው የፌደራል ሥርዓት ያደረሰውና እያደረሰ ያለው ችግር “የማይታያቸው” እና ምንም ዓይነት መፍትሔ ቀርቶ መሻሻልም አያስፈልግወም የሚሉ አክራሪ ሃይሎች አሉ።

የፓርቲና የመንግሥት መዋቅር

የኢሕአዴግ አገዛዝ ዓይነተኛ መገለጫው የፓርቲና የመንግሥት ድንበር አለመለየቱ ነው። ከመንግሥት ከፍተኛ የበላይ አመራር ጀምሮ እስከታች በወረደው የዕዝ ሰንሰለት ማለትም ከምኒስትሮች እስከ ዝቅተኛ እርከን ባለው የመንግሥት መዋቅር ያሉ መንግሥተኞች በአብዛኛው የኢሕአዴግም አባላት ናቸው። ስለሆነም በፓርቲና በመንግሥት መሃል የሚኖረው ግንኙነት ተምታቶ የፓርቲ የፖለቲካ ሥራና የመንግሥት የሕዝብ አገልግሎት ተግባራት በአብዛኛው በተለይ በክልል መንግሥታት ውስጥ ልዩነት አይታይባቸውም። በተጨማሪም የመንግሥት ሠራተኞች የኢሕአዴግ ፓርቲ አባላት የሆኑት በሚሰሩበት መደበኛ ሥራ ላይ እያሉ ነው። በሀገራችን በተለይ ሥልጣን በያዘ ፓርቲ ውስጥ በአባልነት የሚገባው በአብዛኛው የመንግሥት ዝቅተኛና መካከለኛ እርከን ሠራተኞች ለሕዝብና ሀገር አገልግሎት ሳይሆን የሥራ ዋስትናና ዕድገት ይገኝበታል በሚል እሳቤ ነው።

በተጨማሪም የኢሕአዴግ ፓርቲ አባልነትና ደጋፊነት የሚያስገኘው ዘርፈ ብዙ ጥቅም ለመንግሥት ሠራተኞች ብቻ ተወስኖ አልቀረም። ተማሪዎችና ወጣቶች የሥራ ዕድል ለማግኘት፣ በአነስተኛ ንግድ ለመቋቋምና የመነሻ ብድር ለማግኘት፣ ነጋዴዎች ከሚደርስባቸው የግብርና የተለያዩ ተፅዕኖዎች ከለላ ለማግኘት፣ ሌሎችም የሕብረተስብ ክፍሎች ኑሮን ለማቃናት ወዘተ ሲሉ የፓርቲው አባላትና ደጋፊዎች ሆነዋል። “ወይን ለኑሮ” በሠፊው ሲባል የነበረው ይህንን ቁልጭ አድርጎ ይገልፀዋል። የፖለቲካ እምነት ወይም ሕዝብ ለማገልገል ሳይሆን ኑሮን ለማሳካት ዋስትናና የጥቅም ተጋሪ ለመሆን ሲባል ብዙዎች ፓርቲውን ተቀላቅለዋል። በአንድ ወቅት በኢሕአዴግ ራሱ እንደተገለፀው 4.5 ሚሊዮን ያህል አባላት አሉት።

ይህ የፓርቲ አባላት 4.5 ሚሊዮን አሃዝ ማለት ከ100 ሚሊዮን ሕዝብ ከአምስቱ ኣንዱ የኢሕአዴግ ሰው ነው ማለት ነው። ከዚህ የአባላት ቁጥር ጋር በገንዘብም የሚረዱትን፣ በተስፈኝነት የሚደግፉትንና ከላይ እንደተገለፀው ለኑሮም፣ ለንግድም፣ ለሥራ ዋስትናም ሲባል በኢሕአዴግ እረጅም እጅና መረብ የተያዙት ዜጎች ቁጥር ከፍተኛ ነው። ይህ የሚያሳየው “ኢሕአዴግ”ነት ባለፉት 28 ዓመታት ውስጥ የኑሮ ዘይቤ እየሆነ መምጣቱን ነው። ይህ ጤናማ ያልሆነ ማህበረሰባዊ ግብረገብነት የሌለው ኑሮን ለማሳካትና ጥቅም ለማግኘት የሚደረግ አባልነት እና ደጋፊነት አደገኝነቱና ደንቃራነቱ የሚወጣው አሁን ኢትዮጵያችን እንደምትገኝበት ዓይነት የጥገና ለውጥ ጊዜ ውስጥ ነው። ኢሕአዴግ እንደ ፖለቲካ ፓርቲ፣ እንደ መንግሥት ባላቤትነቱ ማሕበራዊ ግብረገብነትን ከማስጠበቅና ዜጎች ኑሯቸውን ከመንግሥትና ፖለቲካ ነፃ ሆነው በሃቀኝነትና በቀጥተኛነት መኖርን አርኣያም፣ አስተማሪም መሆን ሲገባው ድርጊቶቹና የፖሊሲ አፈጻጸሞቹ ሁሉ የዚህ ቀጥተኛ ተቃራኒ ናቸው። አባላትና ደጋፊዎቹም እንደዛው።

ሥራውን፣ ንግዱን፣ ጥቅሙን ወዘተ በአጠቃላይ ኑሮውን ከኢሕአዴግ በሥልጣን መቆየት ጋር ያቆራኘው አባልና ደጋፊ ሁኔታዎች ሲቀየሩ መስጋቱና ለተቃውሞ መነሳቱ የሚገርም አይደለም – የሥራ፣ የንግድ የጥቅምና የኑሮ ዋስትናው ከገዢው የኢሕአዴግ ሥልጣን ጋር ስለተሳሰረ! ይህ የጥገና ለውጥ ስጋትና ተቃውሞ ይበልጥ ተጠናክሮ የሚታየውና ለሀገርና ሕዝብ አደገኛ ችግር የሚሆነው በከፍተኛ የመንግሥትና የኢሕአዴግ የፖለቲካ ሹመኞች ሲካሄድ ነው። እነዚህ ኀይሎች ካላቸው የፓርቲና የመንግሥት የሥልጣን እርከን፣ በሚያዙት የድርጅትና የፓርቲ መዋቅርና የዕዝ ሰንሰለት፣ ማሕበረሰባዊ መረብና ግንኙነት በሌሎች በበርካታ መንገዶች ለውጥን የማደናቀፍና የመቅልበስ ፍላጎታቸው ይስተዋላል። ዋና ዋናዎቹን ለማቅረብ፡-

  1. ክልል መስተዳድሮች

የክልል መስተዳድሮች አብዛኛዎቹ ለይስሙላ በሚደረገው ምርጫና የሕዝብ ድጋፍና ተቀባይነት አግኝተው ሳይሆን በቀጥተኛ የፓርቲና የመንግሥት አካላት የተመረጡ የፖለቲካ ሹመኞች ናቸው። በአውራጃ፣ ወረዳ፣ ዞንና ክልል፣ ፌደራል ምክር ቤት ወዘተ የሚመደቡት ለኢሕአዴግ ባላቸው ታማኝነት ነው። ሟቹ ጠቅላይ ሚ/ር በፓርላማ እንደተናገሩት “ለኢሕአዴግ ታማኝ ከሆነ ማንንም እንሾማለን” ማለት ሁኔታውን ግልፅ ያደርገዋል። ሁለት ጉዳዮች የዚህ የኢሕአዴጋዊ ስንኩል አሠራርና አስተሳሰብ ቀጥተኛ መዘዝ ናቸው። አንደኛው በሃላፊነት ቦታ ላይ የሚታጩትም ሆነ የሚቀመጡት ሰዎች ለሥራው የሚያስፈልግ የትምህርት ልምድ፣ ባህርይና ሥነምግባር ለመመዘኛነት አለመዋሉ ነው። ይህም ሰዎቹን በሥራና ሃላፊነታቸው ብቁነትና መተማመን የሌላቸውና የተቀባይነት ችግር የሌላቸው ይሆናል። ለነገሩ ይህ የተቀባይነት ችግር ከፍተኛ የኢሕአዴግ መንግሥትና ፓርቲ ባለሥልጣናትም ያለባቸው ሲሆን በዚህም ምክንያት መንግሥት ራሱ የዚህ ሰለባ ነው። ሁለተኛው ደግሞ በሁሉም በተለይ ግን “ጥቅም” ገንዘብና ምቾት ያስገኛሉ በሚባሉ ነገር ግን ብዙ የትምህርትና የሥራ ልምድና ሌሎችም አስፈላጊ ብቃቶች በሚጠይቁ ቦታዎች ሳይቀር የማይመጥኑ ሰዎች ሲመረጡ በዕውቀት ሥራውን ማስኬድ የሚችሉት ይታለፋሉ። ይህ ሞራል ይነካል፣ አገልግሎትና  ሥራ ይበድላል፣ ችሎታው ያላቸው መገለልና ወደ ግል ሥራ ወይም ወደ ውጪ እንዲመለከቱ ያደርጋል።

እንግዲህ በክልል የሥልጣን እርከኖች ከላይ እስከታች የተሰገሰጉት “በኢሕአዴጋዊ ታማኝነት” የተመረጡ፣ ያለአንዳች ማመንታትና መጠየቅ የተነገራቸውን የሚፈፅሙ የፓርቲ “ሎሌዎች” ናቸው። ከዚህ አልፎ ግን ሊሠመርበት የሚገባው ጉዳይ እነዚህ ሰዎች ሥልጣናቸው ብቻ ሳይሆን ጠቅላላ ሕልውናቸው ከኢሕአዴግ ሥልጣን ላይ መቆየት ጋር የተቆራኘ ነው። የሚይዙት መኪና፣ የሚያገኙት የገንዘብ ገቢ፣ በንግድ፣ በመሬት ይዞታ በሌላውም ማሕበረሰባዊ ኑሮ ዘርፍ ያላቸውን ተፅዕኖ ወዘተ የሚያሳጣ ለውጥ ደመኛ ጠላታቸው ነው። በሥልጣን የባለጉበት ጉድና የሠሩትም ወንጀሎችን የሚያጋልጥ ለውጥን አሁንም በእጃቸው ባለው ሥልጣንና ከመሰሎቻቸው ጋር በመተባበር ለውጥን ማስቆምና ማደናቀፍ ዋና ሥራቸው ነው። በተጨማሪም ለውጡ ከተሳካ ከተጠያቂነት ቢተርፉም እንኳ ፈፅሞ ያልጠበቁት ከዓመታት በፊት እንደነበሩት “ተራ” ዜጋ ወደመሆን መመለሳቸው ማለትም ወደ ሥራ ፈትነት፣ የአንደኛ ደረጃ መምህርነት፣ አነስተኛ ነጋዴነት፡ ዝቅተኛ እርከን የመንግሥት ተቀጣሪነት ወዘተ ከዕንቅልፍ እያባነነ ያሰቃያቸዋል።  ስለሆነም በሕገ ወጥ መንገድ የጦር መሣሪያ ማዘዋወር፣ የመንግሥት ሥራና መመርያ ላይ መለገምና አለመፈፀም፡ ዘርን ከዘር ማጋጨት እና ሕዝብ የሚያቆስል፣ የሚያበሳጭና የሚያስቆጣ ተግባራት በራሱ በመንግሥትና በሕዝብ ቢሮ ሆነው ያሤራሉ፣ ያስፈፅማሉ። ለዚህም ነው የኢሕአዴግ ሥርዓት ከነግሳንግሱ ማብቃት ስንል ይህ በመንግሥታዊ አካል ውስጥ የተሰገሰጉ የጥቅም ተካፋዮችን አቅፎ መሠረታዊ ለውጥ በሀገራችን አይመጣምና ነው።

  1. “ልዩ” ፖሊስ

የክልል “ልዩ” ፖሊስ ሃይል በቀጥታ በክልል ሹመኞችና ካድሬዎች የሚታዘዝ የታጠቀ ሃይል ነው። በምሥራቅ ኢትዮጵያ “ሶማሌ ክልል” እንደታየው ይህ ሃይል የሕዝብ ሰላምና ደህንነት ለመጠበቅ ሳይሆን በስሙ “ፖሊስ” ይባል እንጂ የሚጠብቀውና የሚከላከለው የክልል ባለሥልጣናትን ደህንነትና ትዕዛዛቸውን ነው። “ልዩ” ፖሊስ ሃይል ለፌደራል መንግሥትና ፖሊስ የማይታዘዝ ተጠሪነቱ በተግባር በክልል፣ አውራጃ፣ ወረዳ፣ ዞን ለተዋቀረው የክልል “መንግሥት” የኢሕአዴግ ፖለቲካ ሹሞችና ካድሬዎች ነው።

መሠረታዊ የፖሊስ ተግባር ሕግ ማስከበርና ማስፈፀም የሕብረተሰቡን ሰላም መጠበቅ ነው። ለዚህም የሚሰጠው የሙያ ሥልጠና አደረጃጀቱና የሚሠማራበት ግዳጅ ይህንን መሠረታዊ ተግባሩን በብቃት እንዲወጣ ነው። “ልዩ” ፖሊስ በስሙ ፖሊስ ከመባሉ በቀር የሚሰጠው ሥልጠና በየክልሉና በየጊዜው የተለያየ ነው። በኢትዮጵያችን በጠቅላላው ያለው አንድ ሕገ መንግሥት (የተንሸዋረረ ቢሆንም)፣ ከረጅም ዓመታት ጀምሮ እየተሻሻለ አሁንም በሥራ ላይ ያለው አንድ ወንጀለኛ መቅጫ ሕግና አንድ የፍትሐብሔር ሕግ ነው። የፖሊስ ተግባር እነዚህን የሀገሪቱን ሕግጋት ማስጠበቅና የጣሱትን ሕግ ፊት ማቅረብ፣ ፍርዱንም ተከታትሎ ማስፈፀም ነው። ይህም ማለት እነዚህን ለማስከበርና ለማስፈፀም የሚሰጠው የፖሊስ ሥልጠና ተመሳሳይነት ሊኖረው ይገባል – በሥራም በቤተሰብ ጉዳይም የፖሊስ አባላት በሀገሪቱ ተዘዋውረው መሥራት እንዲችሉ። “ልዩ” ፖሊስ ግን “ልዩ” የሚለው የስሙ ቅጥያ እንድሚያመለክተው የሀገሪቱን ሕግጋት ማስከበር ሳይሆን የክልል ሹመኞችን ፍላጎትና ትዕዛዝ እንዲያስፈፅም የተዋቀረ ነው።

በምልመላውም በኩል እንደ ሌላው ዓለም ሁሉ የወንጀል ተግባር ያልፈፀመ፣ መልካም ሥነምግባር ያለው፡ ያለአድሎ ግዴታውን መወጣት የሚችል ወዘተ የሚሉ ሙያዊና ግለሰባዊ መስፈረቶችን ማሟላት ይጠበቅባቸዋል። ይህ ሙያዊ መሥፈርት ደግሞ ለተራ ፖሊስ ብቻ ሳይሆን ለኦፊሰርነት ወይም ለአዛዥነት የሚመለመሉትንም ይጨምራል። ይህም ሙያዊ መሥፈርት በፖሊስ አባላት ተጠብቆ መቆየቱ በየጊዜው በፖሊስ ሠራዊት የዕዝ ሰንሰለት ይመረመራል። የፖሊስ አባላት በተዋረድ ትዕዛዝ ማክበር፣ ግዴታን መወጣት፣ የሥራ አፈፃፀም ንቃት ወዘተ ይመዘናል፡፡ የእርማት እርምጃ ሲያስፈልግ የሥነሥርዓት ቅጣትም ይደረጋል። “ልዩ” ፖሊስ ግን እንደ ኢሕአዴግ ባለሥልጣናት ሁሉ በታማኝነትና በተለይም በነገድ ወይም በዘር መስፈረት ስለሚመለመል ታማኝነቱና የሚቀበለውም፣ የሚያስፈፅመውም ትዕዛዛት የክልል መስተዳድር ታማኝ ሹመኞችና የፖለቲካ ካድሬዎች የሚነግሩትን ያለመጠየቅ ነው። ለዚህም አንድ ማሳያ ከአዲስ አበባ ወጣቶች ፖሊስ እንዳይመለመል ለረጅም ጊዜ በህወሓት መሩ ኢሕአዴግ የነበረው አሠራር ነው። ከሕብረተሰቡ መሃል የወጡ የፖሊስ አባላት ጉዳቱ ጉዳታቸው ሆኖ የሚታያቸው ዜጎች ለ”ልዩ” ፖሊስነት አይመለመሉም።

“ልዩ” የፖሊስ ሃይል በፌደራል መንግሥት አለመታዘዙ፣ በነገድና ታማኝነት መመልመሉ ወዘተ ጋር ተዳምሮ በሥራው የሚያገኛቸው ጥቅማ ጥቅሞችና “ተፈሪነት” “ልዩ” ፖሊስ ሃይል የፈጠረውን፣ ያሰለጠነውን፣ የሥራና የጥቅም መስክ የከፈተለትን የክልል አስተዳደር ሥልጣን ላይ እንዲቆይ፣ ተቃዋሚ ንቅናቄ ከተነሳበትም በሃይል ለመደፍጠጥ የተዘጋጀ “ልዩ” ሃይል ነው። በአንዳንድ ክልሎች እንደታየው የ“ልዩ” ፖሊስ ሃይል መለዮውን አውልቆ እንደ ሲቪል ተላብሶ ረብሻ ሲመራና በጦር መሣሪያ እየታገዘ የዘርና የሃይማኖት ግጭቶችን ሲመራ ነው። በቅርቡ አዲስ መመርያ ይወጣል የተባለው የ“ልዩ” ፖሊስ ሃይል የመሣሪያ ትጥቅ “ሚያስተካክል” ነው። መደበኛ ፖሊስ ሕግ ለማስከበርና የሕዝቡን ሰላምና ደህንነት ለማስከበር ከሚያስፈልገው እጅግ የላቀ ከጦር ሠራዊት የማይተናነስ ትጥቅ ነው “ልዩ” የፖሊስ ሃይል ያለው።

ይህ “ልዩ” ፖሊስ ሃይል አሁን ኢትዮጵያችን ባላችበት የ“ለውጥ” ጊዜ ከታማኝ የክልል መስተዳድር ሹመኞችና ካድሬዎች ጋር እጅና ጓንት በመሆን በመሣሪያ ዝውውር፡ የሃሰት መታውቂያ ይዞ የዘር ግጭት በመቀስቀስና ሌሎችም ለውጡን በሚያደናቅፉ ሤራዎች ቀንደኛ ተሳታፊ ነው። እንደ ሕገ መንግሥቱ ድንጋጌም ፖሊስ ከፓርቲና ሌላም ወገንተኛ ፖለቲካ ነፃ ወይም ገለልተኛ መሆን ሲግባው አመላመሉም፣ አሰላጣጠኑም፣ የሥራ መመሪያና የሚሰጠው ተልዕኮም ከዚህ ተቃራኒ ነው።

  1. ደህንነትና ስለላ

የደህንነትና የስለላ መዋቅሩ በክልል መስተዳድሩ፣ በ“ልዩ” ፖሊስ፣ በፓርቲ አባላትና ካድሬዎች እየታገዘ የገዛ ራሱን ዜጎች በመሰለል የሚታወቅ ነው። ሁሉም የክልልና ፌደራል መንግሥት ቅርንጫፎች ለዚህ የስለላ ሃይል ታዛዥ ናቸው። የተቃወሙትን ብቻ ሳይሆን ይቃወሙኝ ይሆናል “በሆዳቸው ይሰድቡኛል” ብሎ የገመታቸውን ግለሰብ ዜጎች ለመከታተል፣ ስልካቸውን ለመጥለፍ፣ ቤታቸውን ለመበርበር፣ ዓይን ሲያወጣም ማስፈራራትና ያለአግባብ ማሠር የሚያደርግ ሕገ መንግሥቱንም ሆነ ሌሎች የሀገሪቱ ሕግጋትን የማያከብር ስውር ሃይል ነው።

በሰለጠኑ ሀገራትም እንደሚስተዋለው የደህንነት ሃይል የሀገርና ሕዝብን ሰላምና ሉዓላዊነትን የሚቀናቀኑ ሃይሎችን በፖሊስና በጦር ሠራዊት ብቻ መቋቋም ስለማይቻል የሚመሠረት ነው። የመንግሥት አስተዳደር (Government) እና የመንግሥት መዋቅር (The State) የተለያዩ ናቸው። መንግሥትን የሚመሠርቱት ፓርቲዎች፣ ፕሬዚዳንቶች፣ ጠቅላይና ሌሎች ሚንስትሮችና የአስተዳደር ባላሥልጣኖች በሕዝብ ምርጫም፣ በሕዝባዊ ንቅናቄም ይለወጣሉ። የመንግሥት መዋቅር ግን በዘላቂነት የሀገርን፤ ሲቪልም ሆነ ወታደራዊ ጉዳዮችና ሌሎችንም እንደ ትምህርት፣ ጤና፣ ንግድ፣ የገንዘብ ተቋማት ወዘተ ያሉ ቋሚ የሀገርና ሕዝብ ሕልውናን የሚመራ ነው። የደህንነት ዋና ተግባርም ይህን ቋሚ የመንግሥት መዋቅርን ደህንነት የመጠበቅና ይህንንም ለሚረከቡት አስተዳደሮች መተላለፉን መጠበቅ ነው። የመንግሥት መዋቅር (The State) የሀገር መሠረት ነውና።

በየክልሉና በሀገር ደረጃ የተዘረጋው የደህንነትና ስለላ ተቋም ግን ሥልጣን ላይ ያለው መንግሥትና ፓርቲ በያዙት ሥልጣን የመቆየት ዓላማቸውን ይፈታተናሉ የተባሉ ዜጎችንና ተቃዋሚ ፓርትዎችን መሰለል፣ ማስጨነቅና ማዋከብ ሲበዛም ማሠርና ማሰቃየት ነው። የሚያሳዝነው ደግሞ በኢሕአዴግ ዘመን የሚታየው የመንግሥትና የፓርቲ “ቅልቅል” በስለላ መርቡ መደረጉም ነው። በሀገር ውስጥ ያሉ ካድሬዎችና የፓርቲ አባላት የስለላ መዋቅሩ አስፈፃሚ ናቸው መሆንም ይጠበቅባቸዋል። በውጭ ሀገራት ያሉ በየኤንባሲውና ቆንስላዎች ውስጥ የተሰገሰጉ የዘር ተዋጽዖ ምድብተኞች በዲፕሎማቲክ ስም የሚዘዋወሩ ካድሬዎች ሳይቀሩ ተቃዋሚ የሚባሉ ዜጎችን ስምና ፎቶ ወደ ዋናው የስለላ መ/ቤት ያስተላልፋሉ – ቦሌ ላይ የሚደረገው የ“ኢምግሬሽን” ማጣራት ይህን የተላለፈ ዝርዝር ማጣራት ይጨምራል። የስለላ ድርጅቱ ከዚህም አልፎ ዜጎችን ለአጎራባች ሀገሮች እያፈኑ መውሰድንም ያከናውናል። ወደ 5 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር በመክፈል ከየመን የተደረገው የግንቦት 7 ፀሃፊ ድርጊት የሚያሳየው ይህንን የሥርዓቱን ዕድሜ ለማቆየት የሚደረግው ጥረት ወሰን እንደሌለው ነው።

የዚሁ የስለላና የመንግሥት ደህንነት አካል የሆነው በየክልሎቹ የተዘረጋው መረብ እንደ “ልዩ” ፖሊስ ሃይል ሁሉ በየቤተሰቡ ደረጃ ከሚደረግው የአንድ-ለ-አምስት ጥርነፋ ጃምሮ ባለው መዋቅሩ ጥቅም ያስገኘለትን መንግሥት፣ ፓርቲና ሥርዓትን የሚቀይር ባለው አቅም ሁሉ ለውጥን ከማደናቀፍና ከመቀልበስ አያርፍም።

በጥቅሉ ዘርዘር አድርገን ከላይ ያስቀመጥናቸው መታየት ያለባቸው ውስብስብ ጉዳዮች  እንደ መንግሥት ኢሕአዴግ፣ እንደ ፓርቲ ኢሕአዴግ፣ እንደ ስለላ ኢሕአዴግ እየመራት በአለው ብቸኛ የ28 ዓመት አገዛዙ ኢትዮጵያ ወደ ተፈላጊው ሀገራዊና ሕዝባዊ ሥርነቀል አይደለም አዝጋሚ ለውጥ እንደማታመራ እኛ ሳንሆን ምድር ላይ ያለው ዋይታና ልቅሶ መስካሪ ነው። ዛሬ የ28 ዓመቱ የዘረኛ አገዛዝ ኢሕአዴግ ወደ ዘር እልቂት እየተሸጋገረ ነው። እስከ አፍንጫው በታጠቀ ሃይል ሕፃናት፣ አዛውንት እናትና አባቶች እየተገደሉ፣ እየተጋዙ፣ ሴቶች እየተደፈሩ፣ ወጣቶች እያለቁ፣ ባለንበት ሀገር ኢሕአዴግ ድረስልን ሳይሆን ከዘረኛ ኩታንኩቱ ጋር ያበቃ ዘንድ መነሳሳት ዋነኛው አማራጭ መሆኑን “አንድ ሀገር! አንድ ሕዝብ! ኢትዮጵያችን ሕዝባዊ ንቅናቄ” አበክረን እናስገነዝባለን። ሀገራችን ኢትዮጵያ ወደ እርስ በእርስ ግጭት እንዳታመራ፣ ኢትዮጵያ እንደ ሀገር እንድትቀጥል፣ ዘርንና/ቋንቋን ተገን ያደረገ ከፋፋይ ሥርዓት እንዲያበቃ፣ ከፊታችን የተጋረጠውን ዋይታና ሰቆቃ ለመመከት ልንደፍር የሚያስፈልገው የኢሕአዴግ አገዛዝ እጁን ለሀገር አድን የሽግግር መንግሥት እንዲያነሳ ነው።

ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!

ፈጣሪ ኢትዮጵያን ይባርክ!

አንድ ሀገር! አንድ ሕዝብ! ኢትዮጵያችን ሕዝባዊ ንቅናቄ

ሚያዝያ 05 ቀን 2011 ዓ.ም. (April 12, 2019)

ማሳሰቢያ ፡

  • ውድ ወገኖቻችን ይህንን “አንድ ሀገር! አንድ ሕዝብ! ኢትዮጵያችን ሕዝባዊ ንቅናቄ” «ኢትዮጵያችን» ዕትም በተለይ በሀገር ቤት ኮምፒዩተር የማግኘት ዕድል ለሌላቸው በማባዛት ታሰራጩት ዘንድ ቀና ትብብራችሁን በትህትና እንጠይቃለን።
  • “አንድ ሀገር! አንድ ሕዝብ! ኢትዮጵያችን ሕዝባዊ ንቅናቄ” መስከረም 8 ቀን 2009 ዓ.ም. እራሱን ይፋ ያደረገ ሕዝባዊ ድርጅት ሲሆን የንቅናቄውን ማንፌስቶና ፕሮግራም ethiopiachen.org ከሚለው ድረ ገጻችን ማግኘት ትችላላችሁ።

ስልክ፡  703 300 4302

ኢሜል ፡ ethiopiachen2009@gmail.com

ድረ ገጽ ፡ www.ethiopiachen.org , www.ethiopiachen.com

ምሥለ ገጽ ፡ 1H1H Ethiopiachin

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s