የአንድ ሀገር! አንድ ሕዝብ! ኢትዮጵያችን ሕዝባዊ ንቅናቄ (ኢትዮጵያችን) – ልሳን ኢትዮጵያችን ቅጽ 3 ቁጥር 6

ኢትዮጵያችን ቅጽ 3 ቁጥር 6                                                  ሚያዝያ 27 ቀን 2011 ዓ.ም.

በምርጫ ስም ኢትዮጵያችን “አትከፋፈልም”

የድምጽ ቅጂውን ለማድመጥ እዚህ ይጫኑ https://www.youtube.com/watch?v=8tJQcZdGiLY

የኢትዮጵያ ሕዝብ በመረጠው መንግሥት ይተዳደር ዘንድ የነበረው ጥረት እንደ አንድ ተውኔት ሲያስገርም፣ ሲያስደንቅ፣ ሲያስቅ፣ ሲያበግን፣ ተስፋ ሲያስቆርጥ አልፎ ተርፎም ሲያሳስር፣ ሲያስደበድብ፣ አካል ሲያቆስል፣ ሕይወት ሲቀጥፍ አይተናል ታዝበናል። ምርጫ ከአካባቢ፣ ከቀበሌ፣ ከወረዳ እየጀመረ ከፍ ብሎ አውራጃ፣ ክፍለ ሀገርና በሀገር ደረጃ ሲከናወን ተመልክተናል፤ ታዝበናል። ተመራጮች ለሕዝብ፣ ለመረጣቸው ሳይሆን በሕዝብ ላይ፣ ላስመረጣቸው አገልጋይ ሲሆኑ ተመልክተናል። ማ እንደሚመረጥ፣ ለምን እንደሚመረጥ እየታወቀ በውድም ሆነ በግዴታ የተውኔቱ ተካፋይ ከተሆነ በርካታ ዓመታት አስቆጥረዋል።

በዓፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመንም ፓርላማው የተሞላው በየወረዳውና አውራጃው እንዲሁም አዲስ አበባን ጨምሮ በየከተማው በተካሄዱ ምርጫዎች ነበር። ምርጫው ግና የመረጣቸውን ሕዝብና አካባቢያቸውን ለማገልገል ሳይሆን ለንጉሠ ነገሥቱ ያላቸውን ታማኝነት በመግለጽ መንግሥታቸውን ማስጠበቅ፣ “ለሚወደንና ለምንወደው ሕዝባችን” ብለው የለገሱትን ሕገ መንግሥት ማክበር ነበር። “ንጉሥ አይከሰስ ሰማይ አይታረስ” መርሆአቸው አድርገው “ስዩመ እግዚአብሔርን” በመጥራት በተለይ በአማኙ ህብረተሰብ ዘንድ ስነልቦናዊ ስጋት በመፍጠርና “ፀሐዩ ንጉሥ” አስብለው ሰጥ ለጥ አድርጎ ለመግዛት የተደረገ ተውኔት በምርጫ ስም በመጠኑም ቢሆን ሀገራችን እንደ መድረክ ሁና አሳይታናለች። አስተናግዳለች።

አብዮት ፈነዳ፣ ፖለቲካ ጦዘ፣ ብሶት ተቀጣጠለ፣ የመብት ጥያቄ የተጠየቀበት፣ እኩልነት የተጮኸለት፣ ሕዝባዊ መንግሥት ከፍ ያለበት የየካቲት 1966 ዓ.ም. ሕዝባዊ ማዕበል ኢትዮጵያን ለዘመናት ከነበረችበት ሥርዓት ወደ ሌላ ምዕራፍ ለማሸጋገሩ ማንም የማይክደው ሀቅ ነው። የዘመናት የዘውድ አገዛዝ እንዲያበቃ አድርጓል። ቀጥዩ አገዛዝ ምንም ይሁን ምን በቤተሰባዊ ዘር ቆጠራ ላይ መሠረቱን የጣለው ንጉሣዊ አገዛዝ አክትሟል።

ስድስት ወር የዘውድ አገዛዝን ሲረግምና መዋቅሩን ሲገዘግዝ የነበረው ሂደት የንጉሡን ሕገ መንግሥት ሠርዞ፣ ፓርላማቸውን በትኖ በ“ጊዜያዊ የሞግዚት አስተዳደርነት” ወታደራዊ አገዛዝ በሀገሪቷ ላይ አስፍኗል። ከ1967 ዓ.ም. መስከረም 2 ቀን ጀምሮ ደርግ ኢትዮጵያችንን ያለ ሕገ መንግሥት በትንሹ ለ13 ዓመት አስተዳድሯል። በሀገራችን ሕገ መንግሥት ተረቆና በሕዝብ ወሳኝነት ተግባራዊ ሳይደረግ በቆየበት የደርግ አገዛዝ በከተማ ለቀበሌ ማኅበራት፣ በክፍለሀገር በገጠር ገበሬ ማህበራት ምሥረታ ምርጫዎች ሲከናወኑ ሕዝብ እጁን አውጥቷል። የደርግ አገዛዝ አብዮቱን አቅጣጫ እያሳተና ጊዜያዊ አስተዳደሩን ቋሚ ሕይወት ለመስጠት ከጅምሩ በወጠነው ሂደት ከተሸከመው መሣሪያ ባሻገር እንኮኮ ያሉት አድር ባይ ምሁራንን ጨምሮ ቀበሌና ገበሬ ማኅበራት ዋናው የደርግ ዓይንና ጆሮ በመሆን አገልግለዋል። ሕዝብ ለአካባቢው ልማትና እድገት ይሠሩልኛል እያለ ከውስጡ የመረጣቸው በራሱ ላይ ሲዶሉቱበት፣ ልጆቹን መውጫ መግቢያ ሲያሳጡበት አልፎ ተርፎ ሲገድሉበት እንደነበር ታሪክ በማህደሯ ከትባዋለች።

በዘመነ ደርግ ጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ እንዴት አድርጎ ወደ የኢትዮጵያ ማርክሲስት ሌኒንስት ድርጅቶች ህብረት (ኢማሌድህ)፣ ቀጥሎ የኢትዮጵያ ሠራተኞች ፓርቲ አደራጅ ኮሚሽን (ኢሠፓአኮ)፣ ከዚያ የኢትዮጵያ ሠራተኞች ፓርቲ (ኢሠፓ)፣ በመጨረሻም መለዮውን አውልቆ ወደ ሲቪል አስተዳደር በመሸጋገር የኢትዮጵያ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊት ሪፐብሊክ (ኢሕዴሪ) እንደተመሠረተ ተከታታይ ተውኔት ኢትዮጵያችን በመድረኳ አስተናገደች። ሌ/ኮ መንግሥቱ ኃይለማርያም ወደ ክቡር ፕሬዘዳንትነት ተቀየሩ፣ ወታደሩ/ደርግ 1967 ዓ.ም. ቃል በገባው መሠረት ሥልጣኑን መለዮአቸውን ላወለቁ የሲቪል አስተዳደር አስረከበ። የዚህ ሁሉ መሸጋገሪያ ድልድይ ታዲያ ምርጫ ነበር። ሕዝባዊ ሽፋን፣ ሕጋዊ ጠለላ፣ ከለላ ለመስጠት የተደረገ ምርጫ።

ደርግ ሕገ መንግሥት አርቅቆ ሕዝባዊ ልባስ ለመስጠት በሀገሪቷ ጫፍ እስከ ጫፍ በትናንሽ ቀጠናዎች ሳይቀር ውይይት እንዲካሄድበት በማድረግ በሕዝብ የፀደቀ ብቻ ሳይሆን የተረቀቀና የፀደቀ እስኪመስል አስካክቶበታል። ሕዝብ መረጠኝ ለማለት ኮሎኔሉ እራሳቸው ሳይቀሩ ቤተመንግሥቱ በሚገኝበት ከፍተኛ 14 ቀበሌ 18 ተገኝተው ለምርጫ ተወዳደሩ። ድራማው/ተውኔቱ ለሕዝብ ቤቴሌቪዥን መስኮት ቀረበ፤ “ሕዝብ የመረጣቸው ቆራጡ መሪ” ተባለላቸው። ተውኔቱ ግና እውን ነበር።

የምርጫ ተውኔቱ አዝናኝና አስቂኝ ምዕራፎችም ነበሩት። ሌሎቹ ተመራጭ እጩዎች ከጓድ ሊቀመንበሩ እኩል ለመወዳደር አንመጥንም ብለው በገዛ ፈቃዳቸው ራሳቸውን ከምርጫው አገለሉ። ጓድ ሊቀመንበሩም ለብቻቸው ሮጠው ለብቻቸው አሸነፉ። በተመሳሳይ በሌሎች የምራጫ ጣቢያዎችም ከጓድ እከሌ ለመወዳደር አልመጥንም እያሉ እጩ ተብዬዎች ራሳቸውን ከምርጫ ያስወግዱ ዘንድ የትዕይንቱ ክፍል ነበር። ሌላው መዝናኛ ደግሞ ለምርጫ እጩዎች የተሰጠው ዓርማና የምርጫው አሸናፊዎችን አስቀድሞ ያስታወቀው አፈትልኮ የወጣው መረጃ የከተማ ወሬ መሆኑ ነው። በየጣቢያው ለተመራጭ እጩዎች የተሰጠው ዓርማ  በሁሉም ዘንድ የጎሽ፣ የአንበሳ፣ የዝሆንና የአውራሪስ ምስል ነበር። ባለዝሆን ዓርማዎች አሽናፊ መሆናቸው አስቀድሞ መታወቁና ይኸውም መፈፀሙ የምርጫውን ቧልትነት ያሳየ ነበር። የቀድሞው የኮሚዩኒስት ሶቪየት ሕብረት መሪ ጆሴፍ እስታሊን በአንድ ወቅት “የምርጫ ውጤትን የሚወስነው ድምፅ የሰጠው ሕዝብ ሳይሆን ድምፁን የሚቆጥረው ነው” ብሎ ነበር። ይህ የሀገራችን የምርጫ ሂደት ደግሞ የእስታሊንን አባባል ወደ ላቀ ደረጃ አሳድጎ ድምፅ ቆጣሪውንም ከምርጫው ጨወታ ውጪ አደረገው። የዚህ ዓይነት ምርጫ እንደ ፍሬ ከርስኪ ጉንጭ አልፋ ወሬና ከንቱ ጊዜና ገንዘብ ማጥፊያ ነው።

ተውኔቱ ቀጠለ፤ በ“ዴሞክራሲያዊ” ምርጫ የሕዝብ ተወካዮች በፓርላማው ተሰባሰቡ፤ ሕዝብ መርጧቸው በሕዝብ ላይ ሊሠሩ “ከጓድ ሊቀመንበራችን ቆራጥ አመራር ጋር ወደፊት” አሉ። ተዘመረ፣ ተጨፈረ፣ ተለፈፈ። 17 ዓመት ሀገር ሠፊ የተውኔት መድረክ ሆነች። ክፍል አንድ ተውኔቱ አለቀ፤ መጋረጃውም ተዘጋ መንግሥቱ ፈረጠጡ፣ ደርግ ኢሠፓ ወደ ከርቼሌ፣ ህወሓት ወደ ቤተ መንግሥት። ሌላ ተውኔት ቀጠለ. . .።

ህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ደርግ ኢሠፓ ከመወገዱ በፊት ትግራይን ለሦስት ዓመት ይዘው ቆይተዋል። የደርግ ሽንፈት የመጀመሪያው መጨረሻ። በመለስ ዜናዊ የሚመራው ህወሓት ጥንስሱ እንደስሙ ትግራይን ነፃ ማውጣት ነበር። እንደ ሻቢያው ሕዝባዊ ግንባር ሓርነት ኤርትራ (ሕግሓኤ) ማለት ነው። ህወሓት ትግራይን ከተቆጣጠረ በኋላ የደርግን በሕዝብ መጠላትና ሕዝባዊ መሠረት የሌለው መሆኑን በመገንዘብ መለስ ዜናዊና ቡድኑ በህወሓት ስም ወደ ሌላው የኢትዮጵያ ግዛት መግባት ስለማይችሉ በአላቸው “ብልጠት” እንደ ዘረኝነታቸው የዘር ድርጅቶችን ማሰባሰብና መፍጠር ጀመሩ። ከኦሮሞ፣ አማራ፣ ደቡብ ያሉትን በማሰባሰብ የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) የሚል ጭምብል በመስጠት በግንቦት 1983 ዓ.ም. የምኒልክን ቤተ መንግሥትን ሊቆጣጠሩ ችለዋል።

ወያኔ/ህወሓትን ማዕከል ያደረገውና በቀጥታ በመለስ ዜናዊና ቡድኖቹ ቁጥጥር ሥር ያለው ኢሕአዴግ ሀገሪቷን እንደፈለጉ ለማተራመስ የዕቅዳቸው ማሳኪያ ሽፋን ሆነላቸው። በፈጣሪያቸው ሻቢያና በራሳቸው አቀነባባሪነት ሜዳ እያሉ የጠነሰሱት ሕገ መንግሥትና ዘረኛ ፖሊሲያቸውን በሀገርና ሕዝብ ላይ ለመጫን የመጀመሪያ ተውኔታቸውን ጀመሩ። ለይስሙላ በተሰባሰቡ የፖለቲካ ድርጅቶችና ለመጣው ሁሉ በሚሰግዱ አድር ባይ ምሁራን እገዛ ሕገ መንግስቱን በሸንጎ አፀደቁ፤ ኢትዮጵያን ዘርንና ቋንቋን ተገን ባደረገ አከላለል ሸነሸኑ።

ኢሕአዴግ በቀጣይነት “አዲሲቷን ኢትዮጵያ” በሚፈልገው አምሳያ ለመፍጠርና ዛሬ ለደረስንበት በዘር ለተቀነቀነ ማንነት ሥልጥኑን ከጨበጠ ጀምሮ ሰርቶበታል። ለዚህም የምርጫ ፖለቲካው ዋነኛ መለያው አድርጎታል። ስለ ኢትዮጵያ አንድነት የሚሞግቱትንና ብሔራዊ አጀንዳ ይዘው የሚንቀሳቀሱትን በማዳከም፣ ከሀገር በማስኮብለል ማንም ሃይ ባይ ሳይኖረው እንደ ደርግ አገዛዝ የምርጫ ተውኔቱን ቀጠለ። በዘር ላይ ለተመሠረተው መንግሥታዊ አስተዳደር በየአካባቢው እጩ የሚሆኑ የኢሕአዴግ ካድሬዎችን በማደራጀት፣ በማሰባሰብ መንግሥታዊ ኃይሉን በገንዘቡ፣ በቅስቀሳው በመያያዝ የምርጫ ትርይቱ ለዓመታት ቀጠለ። ያለምንም ተቀናቃኝ ለ14 ዓመት እራሱ አቅራቢ፣ እራሱ አስመራጭ፣ እራሱ ተመራጭ እየሆነ ገዛ።

ኢሕአዴግም የማስመስል ምርጫው ተሳካልኝ ብሎ “የለመደች ጦጣ ሁልጊዜ ሸምጣጣ” ሆነ። ሕዝብ ይደግፈኛል የሚል የዕውነታ ስቅታ (Reality Hiccup) ያዘው። ተበተ። “እንከን የሌለው ምርጫ አደርጋለሁ፣ ጠንካራ ተቃዋሚ ከመጣ ግማሽ መንገድ ሄጄ እቀበለዋለሁ፣ ምርጫን ለማሸነፍ ማታለል አያስፈልገኝም” አለ። ወደ ምርጫው ቀን በሚወስዱት ወራትና ሳምንታት ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር በሕዝብ ፊትና በመገናኛ ብዙሃን በሚተላለፉ ሙግቶች ለመካፈል ባልተለመደ ሁኔታ ፈቃደኛ ሆነ። በነዚህም ግልጽ የሙጉት መድረኮች እንዲሳተፉ ኢሕአዴግ “ከባድ ሚዛን” የሚባሉትን ፖለቲከኞችና አመራሮቹን አሰለፈ። በየሙግት መድረክ ከተቃዋሚ ፓርቲዎች በተደረጉ ክርክሮች የኢሕአዴግ የፖለቲካ መስመር፣ የኢኮኖሚና የመሬት ፖሊሲዎች፣ የፌደራል ሥርዓትና መነሻው ሕገ መንግስቱ፣ የሰበዓዊ መብቶች ጉዳይ፣ የሚዲያ ነፃነት ፖሊሲዎቹና ራሱም የኢሕአዴግ ፓርቲና መንግሥት ተገላልበው እርቃናቸውን ቀሩ። የምርጫው ቀናት እየቀረበ ሲመጣ ኢሕአዴግ ማንገራገር ጀመረ፡፡ “ሕዝብ በሙግት አዳራሽ አይገባም፣ ሙግቱ በቀጥታ ስርጭት መተላለፍ የለበትም” የሚሉ ሰበባ ሰበቦች ማንሳት ጀመረ። አየር ከበደው። ራሱ በሚቆጣጠረው ሬዲዮና ቴሌቭዥን ለወትሮም ያልተሸፈነውን ገበናውን ሕዝብ በትዝብት አየው። “የትም ፍጪው ዱቄቱን አምጪው” የሆኑ ፖሊሲዎችና አሠራሮችን ማስረዳት አወከው። በደደቢት በረሃ “በሰማይ ቅርቡና አዋቂ ነን” ባይ መሪዎቹ የደረቱት ፖለቲካና አስተዳደር ሀገርን ቀርቶ ወረዳም ለማስትዳደር ጉልድፍ መሆኑ ታወቀበት። ይህም ሆኖ ግን ከአፈርኩ አይመልሰኝ ያለው ኢሕአዴግ የቀን አበል እየከፈልና ትራንስፖርት እያዘጋጀ ሕዝብን መስቀል አደባባይ ሰብስቦ እራሱን በግብዝነት አስደስተ፤ አዋደደ። በማግስቱ በሙሉ ፈቃደኝነት እዛው መስቀል አደባባይ በተቃዋሚዎች የተደረገው ሕዝባዊ ስብሰባ በቁጥርም በትዕይንትም የምርጫው ውጤት አመላካች ነበር። “ትላንት ለገንዘባችን ዛሬ ለሀገራችን” ተባለበት። ለናሙና ያህል በአዲስ አበባ ኢሕአዴግ ለመግደርደርያ እንኳ አንዲት መቀመጫ አጥቶ ዛፍ ያጣች ጉሬዛ ሆነ።

ሲፈጠርም ሕዝብ የጠላው፣ ሀገር የረገመችው አገዛዝ ነበርና ያለውን የገንዘብ፣ የቅስቀሳ፣ የማስፈራራት ኃይሉን ቢጠቀምም ሕዝብ እምቢኝ ወያኔ፣ በቃኝ ኢሕአዴግ ያለበት ወቅት ቢኖር ምርጫ 1997 ዓ.ም. ነበር። መለስ ዜናዊና አገዛዙ በውናቸው አይደለም አልመውት ያልነበረ ዱብ እዳ ከፊታቸው ቢደቀንም ሊከናነቡት የሞከሩትን ገዳይነታቸውን አደባባይ አወጡት። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታውጆ መለስ ዜናዊ ሁሉንም የሠራዊት ክፍልና የስለላ መረቡን በቁጥጥር ሥር አዋለ። ኢንተርሃሞይ ተሰበከ፣ ሁለት ጣት ብቅ የሚያደርግ እንደሚቆረጥ በድፍረት ተለፈፈ። ምርጫውን በሕፃናት፣ በወጣቶች፣ በአዛውንት እናትና አባቶች ጭካኔ በተሞላበት ደምና ሕይወት እንደተቀለበሰ የትላንት ሀቅ እንደነበር ሀገራችን በመድረኳ አሳይታናለች።

ከ1997 ዓ.ም. ምርጫ ወዲህ ተቃዋሚ ኃይሉም የኢሕአዴግ አጨብጫቢና አጃቢ ከመሆን የዘለለ ሚና ሳይኖረው በተካሄዱ ሁለት የምርጫ ተውኔቶች አንዴ 99.6 ከመቶ፣ በቀጣይነት የሌባ ዓይነደረቁ ኢሕአዴግ 100 በመቶ አሸነፈ።

ስለ ምርጫ በሀገራችን በተለይ አሁን በአለው የኢሕአዴግ አገዛዝ ስናወሳ በሀገሪቷ ያሉትን ነባራዊ ኩነቶች መቃኘት አግባብነት ይኖረዋል። ከአንድ ዓመት በፊት የጠቅላይ ሚንስትርነቱን ቦታ የተረከቡት ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ኢትዮጵያ በኢሕአዴግ/ህወሓት አገዛዝ ዘመን የገጠማትን አሳሳቢና አደገኛ ሁኔታዎች ለማስተካከል በኢትዮጵያዊነት ብሔራዊ ስሜት በአደረጉት የመጀመሪያ ቀን ንግግራቸው ሕዝባችን የራቀውንና የናፈቀውን የልብ ትርታ በመቀስቀሳቸው ጭብጨባ፣ እልልታ፣ ድጋፍ ጎረፈላቸው። ጠ/ሚኒስትሩ በያዙት ሥልጣን ኢሕአዴግንና ሕገ መንግሥቱን ተገን አድርገው እንደሚጓዙ ፍንጭ ሲሰጡ እንዲህ ሲሉ ነበር የካቡት “መሪ ድርጅታችን ኢሕአዴግ ልማታዊ ዴሞክራሲያዊ መሥመሩን አጥብቆ በመያዝ ሀገራችንን ከሁለት አሥርተ ዓመታት በላይ ባስተዳደረበት ወቅት በሁሉም መስክ መሠረታዊ ለውጥ ያመጣ ሕገ መንግሥታዊና ፌደራላዊ ሥርዓት ገንብቷል”። ችግሩ ያለው ከሕገ መንግሥቱ መሆኑን እያወቅን፣ ችግሩ ያለው ከኢሕአዴግ መሆኑን እያወቅን አጣብቂኝ አማራጭ የገባው ፖለቲከኛ “እስቲ እንያቸው” ማለት ሳይሆን ዳር እስከዳር ከደገፋቸው ሕዝብ ጋር ከመጋጨት ሌላ የሚያመጣው ፋይዳ ባለመኖሩ ለጥሪያቸው ቀና ምላሽ ተችሯቸዋል።

“እህልም ከሆነ ይጠፋል ሽልም ከሆነ ይለያል” እንዲሉ እቅዳቸው፣ አካሄዳቸው ጥርጣሬን ሲጭር ዓመት አልሞላውም። በአራቱም የሀገሪቷ ማዕዘን ያላቋረጠ ግጭት፣ ግድያ፣ መፈናቀል የለት ተለት ዜና እየሆነ መጣ። ሕገ መንግሥቱ በሠጣቸው መብት መሠረት “የራሳችን ክልል ይሠጠን፣ ማንነታችን ይከለል” ጥያቄዎች ሀገራችን አስቸጋሪ መንገድ ላይ መሆኗን የዓመት ጉዞው ጠቋሚ ሆነ። የዘር ድርጅትና እንቅስቃሴው ይበልጥ ሕጋዊነትን አግኝቶ “ያዙኝ ልቀቁኝ” መብቱን ተቀዳጀ። የኢትዮጵያ ጥላቻ የተጠናወታቸው ወከልን ያሉት ምስኪን ሕዝብ እስኪያዝንባቸው የዘር ጥላቻውን አራገቡት፣ ሰንደቅ ዓላማዋን አቃጠሉት፣ “ጊዜው አሁን ነው” ጭፈራቸውን በዱላና በገጀራ አደመቁት። እውነትም የመጨረሻው መጀመሪያ ለውጥ! ዝምታው ፍርሃት እየመሰላቸው የቀራቸውን አዲስ አበባ እንደ ናዝሬቱ አዳማ፣ እንደ ደብረዘይቱ ቢሾፍቱ፣ ፊንፊኔ በማለት የጥቃቱ ሙከራ ቡራዮ ላይ ተጀመረ። ሁኔታውን ለማርገብ በተወሰደ የፖሊስ እርምጃ “ይህንን መመከት ያቃታችሁ ሰነፎች!” ተብለው ይመስል ተጠቂ ወጣቶች ለእሥር ተዳረጉ። “ሀገሪቷ እውን መንግሥት አላትን?” ጥያቄ ውስጥ ገባ። ወከባውና ማፈናቀሉ እንደቀጠለ በለገጣፎ አካባቢ አሳዛኝ ድርጊት ተፈጸመ። የጠ/ሚሩ “አልሰማሁም! አላየሁም!” ምላሽ የሂደቱን ሽልነት አመላከተ።

ህወሓትን ማዕከል ያደረገው ኢሕአዴግ ተረኛ ምሰሶው ከኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት ወደ ፓርቲነት ያደገው ኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኦዴፓ) መሆኑን አረጋገጠ። ሀገር ከአንድ ዘረኛ አገዛዝ ወደ ሌላ እየተሸጋገረች ብቻ ሳይሆን መበታተኗን የናፈቁ “ፊንፊኔ ኬኛ” በሚል አዲስ አበባ የይገባኛል ጥያቄ ላይ ዱላቸውን ላነሱ “እኛም አለን” ተከላካይ ግድ ነውና ብቅ አለባቸው። የጠ/ሚሩ ቀና ምላሽ “ጦርነት አውጃለሁ” ሆነ። ምን አሉ? ተብሎ በሦስተኛ ወገን ሳይሆን በአደባባይ እራሳቸው ዘረገፉት። ደጋፊዎቻቸውን አስኮረፉ፣ ሕዝብን አሳዘኑ። ከዳር እስከዳር የነበራቸውን እልልታ ዝምታ አስዋጡት። ሽሽት ይመስል ሕዝብ እየተፈናቀለና እየተጎሳቆለ ውጭ ውጭው አሰኛቸው። ዛሬ በሀገራችን የተፈናቀለውን የህብረተሰብ ክፍል ማነው እየረዳው፣ የምግብ፣ የመጠጥ ውሃ፣ አልባሳት፣ ሕክምና እያደረገለት ያለው? የማፈናቀል፣ ቤት በላያቸው ላይ የመናድ፣ ሂደት አንሶ ለበሽታና ለሞት ምስኪን ዜጎቻችን በየቦታው ተወርውረው መንግሥት ድምጹን ሲያጠፋ እውን ያሳዝናል። ዛሬ ቤታቸውን ያጡ ቤተሰቦች ሕፃናት ከትምህርታቸው ተስተጓግለው የረሃብ ያለ፣ ድረሱልን ቁልጭልጭ ዓይናቸውን በዩ ቲዩቡና ፌስ ቡክ መመልከቱ እሊናን ያቆስላል፣ ስሜትን ይነካል።

በአንድ ዓመት ውስጥ ወደ 13 ቢሊዮን ዶላር አስገብተናል ያለው “ለውጥ” አራማጁ አገዛዝ ምነዋ ዳቦ ከእጥፍ በላይ አስጨመረብን? ምነዋ የኤሌክትሪክ ታሪፍ ዘግናኝ ጭማሪ የአዲስ አበባን ነዋሪ አሰቃየ? ሰው የዕለት ጉርሱን ማግኘት እተቸገረበት ላይ ምነዋ ሀገሪቷ ወደቀች? በአጭሩ እንግዲህ ሀገራችን ኢትዮጵያ እዚህ ዓይነት ውጥንቅጥና የተዘበራረቀ ወቅት ላይ ነው ያለችው። የነገ እልውናችን አስተማማኝ አልሆነበት ደረጃ ምነዋ ምርጫው ተፈላጊ ሆነ?

ጠ/ሚር ዶር ዐቢይ አሕመድ የኢሕአዴግን ሕገ መንግሥት እንደ መጽሐፍ ቅዱስ ወይም እንደ ቁራን ሙጭጭ እንዳሉበት ሌላው የሚታይባቸው አካሄድ ቀጣዩ ምርጫ እንዳይራዘም ያላቸው ፍላጎት ነው። እውን ኢሕአዴግ ያቦካውንና ያበላሸው ውጥንቅጥ የሀገሪቷ ችግሮችን በመጠኑ ከመቅረፍ ይልቅ እየተባባሰ በአለበት ሁኔታ ይህ ምርጫ የተፈለገበት ምክንያት ለመተንበይ ትንቢተኛ መሆን አያስፈልግም። በሀገራችን በአሁኑ ወቅት ያለው ዋናው ችግር ኦሮሚያ እራሱን መንግሥት ለማድረግ የሚደረገው ቅድመ ዝግጅት ነው። ለኦሮሞ ሕዝብ ኢትዮጵያዊነት፣ እንግዳ ተቀባይነት፣ ተዋዶና ተከባብሮ ከሁሉም ኢትዮጵያዊ ወገኖቹ የመኖር ፍላጎት እራሱ ብሔረሰቡ መስካሪ ነው። አዎ! የማይካደው ሀቅ ወያኔ/ህወሓት በ28 ዓመት አገዛዙ በዘረጋው ፖሊሲ የኦሮሞ ሕፃናት ላይ ከትምህርት ቤት ጀምሮ በየሚኖሩበት ቀዬ በዘራው ከፍተኛ የጥላቻ ፖለቲካ በተለይ አማራው፣ ምኒሊክ እና ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንን ለማዳከም ያለማቋረጥ የረጨው መርዝ ዛሬ በ30 ዕድሜዎቹ የሚቆጠሩ አንዳንድ የኦሮሞ ልጆች አካሄድ ላይ ሲንፀባረቅ ይታያል። የዚህ አደገኛ ቅስቀሳ ውጤት ምኒልክን በጡት ቆራጭነት፣ አማራን በጠላትነት አስፈርጆ ሀውልት አስቁሟል። ሀገሪቷን ለመበታተን ለማፍረስ ላላቸው ዕቅድ ዛሬ በመንግሥት ደረጃ ትብብር ሳይሆን በውስጠ ታዋቂ መንግሥት ሁነዋል። ዛሬ በጠ/ሚሩ ሹም ሽረት አብዛኛውን ቦታ የያዙት ከየትኛው ዘር እንደሆነ መሟገቱ ለዘረኝነቱ አራጋቢ መሆኑን ብናምንም ዓይን ያወጣ መሆኑ የሁኔታዎች አካሄድ እንድንመረምረው ያደርገናል።

ይህ ሁላ ገለፃ ዛሬ በኦዴፓና በኦነግ ያንዣበበው ኦሮሚያን ሀገር የማድረግ የእልም ሩጫ ነው። አዲስ አበባን በምርጫ ስም ለመጠቅለል በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ የኦሮሞ ተወላጆች የአዲስ አበባ መታወቂያ መሰጠቱ ሲጋለጥ ድንፋታ መልስ አይሆንም።

“ግርግር ለገንጣይ ያመቻል” እንዲሉ በቀጣዩ ምርጫ ማን ከማን እንደሚወዳደር ማየት በቀላሉ ይቻላል፡፡ ኅብረ ብሔር የሆኑ ድርጅቶች በየትኛውም አካባቢ መንቀሳቀስና መቀስቀስ በማይችሉበት ሂደት እውን ቀጣዩ ምርጫ ለማን ነው የተመቻቸው? በኢሕአዴግ አጠራር ኦሮሚያ ክልል ኦዴፓ ከኦነግ፣ በትግራይ ህወሓት ከአረና፣ በምሥራቅ ኢትዮጵያ ኦብነግ፣ በአማራ ብአዴን ከአብን፣ መአሕድ… ይህ ነው እንግዲህ የዘረኛ ድርጅት የእርስ በርስ ውድድር። የዚህ ሂደት ውጤት መጪውን ምርጫ እና የሕገ መንግሥቱን አንቀጽ 39 ተገን በማድረግ ትግራይን ለህወሓት፣ ኦሮሚያን ለኦነግ፣ ምሥራቁን የሀገራችንን ክፍል ለኦብነግ የማከፋፈልና “ሕጋዊነት” የመስጠት ተውኔት እንደሚሆን ያለጥርጥር መናገር ይቻላል። እውን ለመናገር ከየትኛውም የሀገሪቷ ክልል ተለይቼ ሀገር እሆናለሁ ባይ ክልል ከኢትዮጵያ ይልቅ ጉዳቱ ለራሱ እንደሚሆን መናገር ይቻላል። ለዚህ ምክንያቱ ይህ አካሄድ የኦሮሞም ሆነ የትግራይ እንዲሁም የምሥራቅ ኢትዮጵያ ወገኖቻችን ጥያቄ ሳይሆን ወከልን ያሉ የፖለቲካ ድርጅቶችና አንዳንንድ አጨብጫቢ ምሁራን ግፊት ነውና። ድርጅት፣ ጉልበትና መሣሪያ ለጊዜው አሸናፊ ቢመስልም በንፁሐንና በዜጎች ላይ ቁስሉ የማይሽር እልቂት ያስከትል ይሆናል እንጂ በምርጫ ስም ኢትዮጵያ አትከፋፈልም።

በጠ/ሚር ዶክተር ዐቢይ አካሄድ ቀጣዩ ምርጫ ከሀገሪቷ ተጨባጭና ነባራዊ ሁኔታ አንፃር አንድ የዘር ድርጅትን ከሌላው ለማወዳደር የታቀደ ሂደት ስላለው መጪው ምርጫ የዜጎች ድምፃቸውን ማሰሚያ መሆኑ ቀርቶ መከፋፈልን በማስፋትና መገለልንም በማስከተል የግጭት መነሻ በመሆን ሀገራችንን የእርስ በእርስ ትርምስ ውስጥ እንዳይከታት ያለንን ስጋት እንገልጻለን። ለሀገራችንና ለሕዝባችን እውነት ቀና አመለካከት ካለ ምርጫ መቼና እንዴት እንደሚካሄድ ማወቁ ጠቀሜታው የጎላ ነው።

ከላይ በጠቀስናቸው የሀገሪቱ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና ማህበረሰባዊ ቀውስ ውስጥ ምርጫን ማካሄድ በመራጩ ሕዝባችን ተአማኝነት አለመኖር ብቻ ሳይሆን ሊመርጠው የሚቀርብለትም አማራጭ እንደየክልሉ የዘር ድርጅት በመሆኑ ዝምታውን ሊመርጥ ይችላል። ይህ ደግሞ ለጊዜው ዘረኞች በሩን በመክፈት ሀገርን ለጉዳት ይዳርጋል። የኢትዮጵያ ሕዝብ በየትኛውም አቅጣጫ ዘር ሳይለይ አንድነቱን ፈላጊ፣ ሀገሩን ወዳድ ለመሆኑ ዞር ብለው ካዩት ጠ/ሚር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ በየሄዱበት አካባቢ ስለ ኢትዮጵያ አድምቀው ሲናገሩ ያለው ምላሽ በቂ ምስክር ነው። ከነድህነታቸው ሀገራቸውን ወዳድ ብቻ ሳይሆን ለሀገራቸው ሟች ኢትዮጵያዊ ዜጎች፤ አብሮ የመኖር ባህላቸው፣ አንድነታቸው፣ እምነታቸው ይዳብር ዘንድ መሥራት ሲገባ ቀጥዩ ምርጫ፤ በምርጫ ስም መገነጣጠልን ሕጋዊ ልባስ ለመስጠት የሚደረግ የጠባቦች አስተሳሰብ በመሆኑ ድጋፍ ሊቸረው አይገባም ስንል “አንድ ሀገር! አንድ ሕዝብ! ኢትዮጵያችን ሕዝባዊ ንቅናቄ” አቋማችንን ግልጽ እናደርጋለን።

ደጋግመን እንዳልነው የሀገራችን ዋናው ችግር ኢሕአዴግና ሕገ መንግሥቱ በመሆኑ ቅድሚያ ትኩረት መሠጠት ያለበት ይህ ሕገ መንግሥት እንዴት ይቀየር? 28 ዓመት ያለ ተቀናቃኝ የገዛውና አሁንም “በቀን ጅቦች” መናኸሪያነት ያለው ኢሕአዴግ ሥልጣኑን በቅድሚያ ለሽግግር መንግሥት ማስረከብ ይኖርበታል። ይህ አቋማችን ወደድንም ጠላንም ከታሪክ እንደምንማረው ባላባትን ይዞ መሬት ለአራሹ፣ ደርግ/ኢሠፓን ይዞ ዴሞክራሲያ፣ ኢሕአዴግ/ህወሓትን ይዞ አንድነትን መጠበቅ “ከእባብ ዕንቁላል እርግብ መጠበቅ” መሆኑን አስረግጠን እንናገራለን።

አንድ ዓመት ግድም የቀረውን ቀጣዩን ምርጫ በተመለከተ ስለ ምርጫ ቦርድ አሠራርና አወቃቀር፣ ተአማኝነት ስላለው ምርጫ ሂደት፣ ስለ ፖለቲካ ድርጅቶች እውቅናና ሚና፣ ስለ ነፃ ሚድያና መነጋገሪያ መድረኮች ፣ ስለ ነፃ ታዛቢዎች፣ ስለ ድምጽ ቆጠራ ወዘተ ብዙ የተባሉና የተፃፉ ጥናታዊ ጽሁፎችን በመመልከትና ከሌሎች ሀገሮች ትምህርት በመቅሰም ለሀገራችን ተስማሚ የሆነውን የምርጫ አካሄድ መንደፍ ተገቢነት ይኖረዋል።

ኢትዮጵያችንን በዘርና በቋንቋ ከልሎ የሚደረግ ምርጫ ውጤቱ አንድነት ሳይሆን መከፋፈል፣ ልማት ሳይሆን ጥፋት፣ እድገት ሳይሆን ውድቀት መሆኑን ከ28 ዓመት የኢሕአዴግ አገዛዝ አየን። እና? እናማ ዘርንና ቋንቋን ምሰሶው አድርጎ የተቀረጸው የኢሕአዴግ ሕገ መንግሥትን ሀገራዊ አንድነትንና ኢትዮጵያዊ ብሔራዊ ስሜትን ዋልታና ምሰሶ አድርጎ እንደገና መቅረጽ። ለዚህ ደግሞ አቅሙም ችሎታውም ያላቸው ቅን ወጎኖቻችንን ማሰለፍ ይቻላል። ለዚህ ሂደት ስኬታማነት ቅድሚያ በዘር የተደራጁ የፖለቲካ ድርጅቶች ወደ ኢትዮጵያዊነት ያተኩሩ ዘንድ ቀናና መግባባትን ለተላበሰ የውይይት መድረክ በሩን ክፍት ማድረግ። ጠ/ሚሩ “የምትፈልጉትን ነገር ለማግኘት ድንጋይ መወርወር አያስፈልግም” ብለው በሕዝብ ላይ ጥይት እየተወረወረ መሆኑን ሊስሙ፣ ሊገነዘቡ ይገባል እንላለን። የሚፈለገው ነገርም በምርጫ ስም መገነጣጠልን ለማብሰር ከሆነ ለማንም እንደማይበጅ አድማጭ ካለ አስነብበናል።

ምርጫ ለኢትዮጵያ አንድነት!

ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!

ፈጣሪ ኢትዮጵያን ይባርክ!

“አንድ ሀገር! አንድ ሕዝብ! ኢትዮጵያችን ሕዝባዊ ንቅናቄ”

ሚያዝያ 27 ቀን 2011 ዓ.ም. (May 04, 2019)

ማሳሰቢያ ፡

  • ውድ ወገኖቻችን ይህንን «አንድ ሀገር! አንድ ሕዝብ! ኢትዮጵያችን ሕዝባዊ ንቅናቄ» «ኢትዮጵያችን» ልሳን በተለይ በሀገር ቤት ኮምፒዩተር የማግኘት ዕድል ለሌላቸው በማባዛት ታሰራጩት ዘንድ ቀና ትብብራችሁን በትህትና እንጠይቃለን።
  • «አንድ ሀገር! አንድ ሕዝብ! ኢትዮጵያችን ሕዝባዊ ንቅናቄ» መስከረም 8 ቀን 2009 ዓ.ም. እራሱን ይፋ ያደረገ ሕዝባዊ ድርጅት ሲሆን የንቅናቄውን ማንፌስቶና ፕሮግራም ethiopiachen.org ከሚለው ድረ ገጻችን ማግኘት ትችላላችሁ።

ስልክ፡  703 300 4302

ኢሜል ፡ ethiopiachen2009@gmail.com

ድረ ገጽ ፡ www.ethiopiachen.org , www.ethiopiachen.com

ምሥለ ገጽ ፡ 1H1H Ethiopiachin

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s