የጠቅላይ ሚንስትሩ “የሰላም” ሽልማት እና የምዕራባውያን ሴራ – በተመስገን አስጨነቅ ዘለቀ

ተመስገን አስጨነቅ ዘለቀ

ምዕራባውያን ተንኮል ብቻ ሳይሆን ቀልድም በድንብ ይችሉበታል። ሰሞኑን የነገሩን ቀልድ ደግሞ ለሚያውቃቸው ፈገግ ሲያሰኝ ለማያውቃቸው እና ሀገሪቱ ያለችበትን ሁኔታ ለተረዳ ደግሞ ቀንድ ያቆማል ። ጠቅላዩ “የዩኒስኮ የሰላም አዋርድ” ተሸላሚ ሆኑ ይላል። ሀገር በአራቱም አቅጣጫ እንደበሬ ቆዳ ተወጥራ በየቀኑ የምንሰማው ግድያ እና እልቂት ለምዕራባውያን እንደ ሰላም ተቆጥሮ ሽልማት ያሰጣል። እነሱ ምን አሻቸው እጃቸውን የሚያስገባላቸው እና ገብተው የሚፈተፍቱበት መንገድ እስካገኙ ድረሰር አንዳች አይገዳቸውም። በኢ-ሚዛናዊ (stereotype) በተሞሉ ሚዲያዎቻቸው ተጠቅመው ያሞካሹሃል፤ተቋሞቻቸውን ተጠቅመው ይሸልሙሃል፤ የረቀቀ ቴክኖሎጃቸውን ተጠቅመው ስነልቦናህን ይተነትኑልሃል ከዚያም በድክመትህ ይገቡ እና የራሳቸውን አቅጣጫ እና ፖሊሲ አስፈጻሚ ያደርጉሃል። ትንሽ እንደማንገራገር ካልክ አንድ ባላንጣ ያመጡ እና ድምጥማጥህን ያጠፉሃል። ምዕራባውያን እንዲህ ናቸው። እጅ ከሰጠሃቸው ያነግሱሃል፤ ከተቃወምካቸው ደግሞ ፍዳህን ያሳዩሃል።

******

ምዕራባውያንን እምቢኝ ብለው መከራ ከተቀበሉት  አፍሪካውያን ውስጥ ጥቂቱን እንይ፦

******

የኮንጎው ጸረ ኢምፔሪያሊስት እና የነጻነት ታጋይ ፓትሪስ ሉምባ በ1958 የኮንጎ ብሄራዊ ንቅናቄ የተባለውን የፖለቲካ ፓርቲ ከመሰረተ በኋላ በመላው የአህጉሪቱ የተነጻነት ታጋዮችን ማነቃቃት ተያያዘው።ወቅቱ የአፍሪካ ሀገራት ከቅኝ ግዛት ነጻ እየወጡ የነበረ በመሆኑ ቤልጂየም የኮንጎን ነጻ መውጣት ሂደት የሚያመላክት የአምስት አመት ፕሮግራም ነደፈች። የዚህ ጊዜ ፓትሪስ ሉምባ በፍጹም ይህ የአምስት አመት ፕሮግራም የራሳችሁን አሻንጉሊት ለማስቀመጥ የታለመ ነው ሲል ቤልጂየሞችን ሞገተ። በዚህም ጥርስ ውስጥ ገባ የተለያዩ የእስር ጊዜያትንም ማቀቀ። በ1960 ኮንጎ ነጻነቷን ብታገኝም የፓትሪስ መንግስት በቤልጂየሞች የእጅ አዙር ጥምዘዛ ውስጥ ገባ። ካታንጋ የተባለውን እና በማዕድን የበለጸገውን ግዛት የሚያስገነጥል ቡድን አቋቁመው የሉምባን መንግስት እረፍት ነሱት። ፓትሪስ የተባበሩት መንግስታት ድርጅትን ቤልጀየሞች ከተግባራቸው እንዲቆጠቡ ጥሪ አቀረበ በፍጹም አልሆነም።  ይልቁንም መረጃዎች እንደሚያሳዩት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እራሱ ከቤልጂየሞች ጎን ተሰልፎ ድጋፍ ይሰጥ እንደበር ተመልክቷል። በኋላም የኮንጎ ወታደራዊ ሃይል መሪ ጆሴፍ ሞቡቱ የፖለቲካ ሃይሉን ተቆጣጠረ፤ ፓትሪስም በቤልጂየሞች አቀናባሪነት ተገደለ።

******

የቡርኪናፋሶው አብዮታዊ መሪ ቶማስ ሳንካራ የአይ ኤም ኤፍ እና አለም ባንክ እንዲሁም የምዕራባውያንን ብድር እና እርዳታ በማሽቀንጠር  “The one who feeds you usually imposes his will upon you.” ሲል ተቃወመ። እጅግ ሰፋፊ ሪፎርሞችን እና ሀገራዊ ትልሞችንም ተለመ። የቀድሞዋን “የላይኛው ቮልታ” የቅኝ ግዛት ስም አንጠቀምም በማለት ቡርኪናፋሶ ብሎም ሰየመ።  ከአይ ኤም ኤፍ እና አለም ባንክ ብድር እና ሪፎርም አልቀበልም ብሎ ዞርበሉልኝ በማለቱ  በአሜሪካው የስለላ ድርጅት ሲ አይ ኤ እና በፈረንሳይ የደህንነት አገልግሎት ጥርስ ውስጥ ገባ። በቅርብ ጓደኞቹ በኩል በተቀነባበረ ሁኔታም አስገደሉት።

******

የጊኒ ቢሳው አብዮተኛ ካብራል ሌላው የምዕራብውያን ስውር ደባ ሰለባ አፍሪካዊ መሪ ነበር። ካብራል የፖለርቱጋልን ቀኝ ገዥ ስርዓት በሽምቅ ውጊያ አርበድብዶ ከቅኝ ግዛት ነጻ አውጥቶ ሀገር ከመሰረተ በኋላ በእነዚሁ መርዘኛ ምዕራባውያን ስውርው እጆች በ1973 ተገድሏል።

******

የሊቢያው ሞሃመድ ጋዳፊም እንዲሁ ዜጎቿ በአለማችን የተንደላቀቀ ሂወይት ከሚመሩ ሀገራት አንዷ የነበረች ሲሆን ዛሬ በአለማችን ላይ ከከሰሙ ሀገራት እንድትመደብ አደርገዋታል። ይህ ብቻ አይደለም ምዕራባውያን በእያንዳንዱ የአፍሪካ መንግስታት ጓዳ ውስጥ አሉ።

******

ምዕራባውያን ከተቃወምካቸው መሪ ወይም ምሁር አይሉም። እንደ ስጋት ካዩህ ባጭሩ ይቀጩሃል። በካሪቢያን በምትገኛው ጉያና የፖለቲካ ምሁር እና በታንዛኒያ ዳሬሰላም ዩኒቨርስቲ ተመራማሪው ዋልተር ሩድኒ ግድያ ለዚህ ማሳያ ነው። ዋልተር “አውሮውያን እንዴት አፍሪካን አቆረቆዙት”  ሲል ከአለማቀፉ ያልተመጣጠነ የንግድ ልውውጥ፣ የኢኮኖሚ ቅርምት እና የፖለቲካ ተጽዕኖን ፍንትው አድርጎ አሳይቷቸዋል። በዚህም ጥርስ ውስጥ ገብቷል። የዝምባብዌን የነጻነት በዓል አክበሮ ወር ሳይሞላው በመኪናው ላይ በተጠመደ ቦንብ በ38 አመቱ አሰናብተውታል።

******

እነዚህ እንግዲህ ጥቂት ለማለት ያክል ብቻ ነው። ጎግል ማድረግ ለሚችል ማዓት ነገር ማግኘት ይችላል። ምዕራባውያን በግድያ እና በማጥቃት ብቻ የተወሰኑ አይደሉም። ፖሊሲ ቀርጸው መፈናፈኛ ያሳጡሃል። በቤትህ ገብተው ይፈተፍታሉ፤ በማታውቀው መንገድ ይገቡ እና ወደ ገደል ይጨምሩሃል። ለምሳሌ ታዳጊ ሀገራት ከአይ ኤም ኤፍ እና አለም ባንክ ብድር ለማግኘት መከተል ያለባቸው ቅድመ ሁኔታዎችን አስቀምጦ የተቀረጸው  “Structural Adjustment Programme” ብዙ የአፍሪካ ሃገራትን የቁልቁለት ግስጋሴ አፋጥኗል።ይህንን ካደረግክ ብድር እሰጥሃለሁ የሚል የእጅ ጥምዘዛ ፖሊሲ እና ስትራቴጂ በመከተል የአፍሪካን መከራ እያራዘሙት ይገኛሉ። በተጨማሪም “የዋሽንግተን ስምምነት” ተብሎ የሚታወቀው ታዳጊ ሀገራት “ለመበልጸግ” መከተል ያለባቸው ፍኖተ ካርታ ብለው በኛው መከረኛ የአፍሪካ ሀገራት ውስጥ የተገበሩት ስምምነት ተጠቃሽ ነው።የፊሲካል ፖሊሲ፣የታክስ ክለሳ፣ የከንዘብ ልውውጥ ተመን፣ ፕራይቬታይዜሽን፣ ነጻ የንግድ ልውውጥ ወዘተ የሚሉ 10 ህግጋትን ታዳጊ ሀገራት እንዲተገብሩ የእጅ አዙር ጥምዘዛ በማድረግ የአፍሪካ ሀገራት ገንዘብ እርባና ቢስ እንዲሆን፣ የአፍሪካ መንግስታት ታክስ ሰብስበው መሰረተ ልማት መገንባት የማይችሉ ለማኞች እንዲሆኑ እና የአፍሪካ ሀገራት ገበያዎች የአደጉ ሀገራት ምርት ማራገፊያ ሁነው እንዲቀጥሉ እያደረጉ ይገኛሉ።

******

ምዕራባውያን ሁሉ በእጃቸው ነው፤ የትምህርት እድል ብለው ይሰጡህ እና የተንደላቀቀ ህይወት እያኖሩህ ሀገርህን፣ ወገንህን እረስተህ  በዚያው ጥቁር አሞራ ሁነህ እንድትቀር ያደርጉሃል። ሲፈልጉም በተደራጀ ሚዲያቸው የምዕራባውያንን የመሰረተ ልማት ምናባዊ በሆነ መንገድ ይስሉልሃል። እኛ አፍሪካውያንም 24 ሰዓት የነሱን ምድር ለመርገጥ እናልማለን፣እንተጋለን። ጥገኝነት ይሰጡህ እና ቀለብ እየሰፈሩ እስከ 10 አመት ያኖሩሃል። አምሮህ ላሽቆ ጉልበትህ ሲደክም የስራ እና የመኖሪያ ፈቃድ ይሰጡሃል። ከዚያ በኋላ አማራጭ የለህም ለነሱ የጉልበት ስራ እየሰራህ ቀሪ ህይወትህን ትገፋለህ። በተቃራኒው መርከቦቻቸው 24 ሰዓት የአፍሪካን ጥሬ እቃ ያጓጉዛሉ፤ እንቅልፍ አታይባቸውም። መርከቦቻቸው ጭነው ያመጡትን የአፍሪካ ሃብት ትንሽ እሴት ተጨምሮበት ሱፐር ማርኬቶቻቸውን ይሞላሉ። እኛ አፍሪካውያን የኛኑ ሃብት ባህር አቋርጠን ለመብላት መስዋት ከፍለን  ስደት ስንኳትን ውሃ ይበላናል። አውሮፓውያን አንድ ተክል ለውዝ አያበቅሉም፤ ነገር ግን ሱፐር ማርኬቶቻቸው በቸኮሌት ምርት የሞሉ ናቸው። አንድ የሙዝ ዛፍ የላቸውም ገበያዎቻቸው ግን 24 ሰዓት በሙዝ ፍራፍሬ የጠገቡ ናቸው፤ ሌሎች ምርቶቻቸውም እንደዚሁ ናቸው።

******

እነዚህ በኢትዮጵያ ላይ እያንዣበቡ ያሉ ምዕራባዊ በዝባዥ ተቋማት(exctractive instituions) የቅኝ ግዛት ኢ-ቀጥተኛ በሆነ መልኩ ማስቀጠል አላማቸው ሲሆን እነሱ የገቡበት አፍሪካዊ ሀገር ሁሉ መነሻ የለውም። ልክ ምዕራባውያንን ከ1929 ጀምሮ ለአስር አመታት የመታቸው ከባዱ የኢኮኖሚ ዝቅጠት ወቅት “ገንዘብ በዘንቢል  እቃ በኪስ” እንደነበረበት ወቅት ያደርጉሃል። ለምሳሌ ዩጋንዳ ውስጥ አንድ ኪሎ ቲማቲም 3600 ሽልንግ ትገዛለህ። የመካከለኛዋ አፍሪካ ካሜሩን ውስጥ አንድ እራስ ሽንኩርት 150፣ አንድ ኪሎ ስጋ 5000 ፍራንሴፋ ትገዛለህ። ዚምባብዌ ውስጥ ጭራሽ ገንዘባቸውን ከገብያ ውጭ አድርገው የአሜሪካን ዶላር እና የሌሎች የጎረቤት ሀገራት የገንዘብ ኖት እንድትጠቀም ተገዳለች። በአጠቃላይ እንዚህ ተቋማት የሚጠመዝዟቸው ሀገራት የመከራ ህይወት እንጂ ተስፋ አታይባቸውም።

******

እነዚህ በዝባዥ ተቋማት ታዲያ ኢትዮጵያ ውስጥ እያንዣበቡበት የለው ሁኔታ አንድ ሊባል ይገባል።  በተለይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ወደ ኢትዮጵያ እየገሰገሱ ያለበት ፍጥነት መረን የለቀቀ ይመስለኛል።  በ2017 መጨረሻ አካባቢ የአይ ኤም ኤፍ ዳይሬክተር ክርስቲያን ላጋርድ አዲስ በአበባ ገብተው ሲፈተፍቱ ውለው አድረው ኢከኖሚው ነጻ እንዲሆን መክረ ሃሳባቸውን ሰጥተው ነበር። ሰሞኑን ደግሞ የአለም ባንክ ፕሬዝደንት ጎራ ብለው ሲፈተፍቱ እንደነበር ሰምተናል። የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክም የኢትዮጵያ የብር ምንዛሬ በገበያ አቅርቦት እና ፍላጎት እንዲመራ አቅጣጫ ማስቀመጡን እና ለዚህም የአይ ኤም ኤፍ ባለሙያዎች ድጋፍ እየሰጡ እንደሆነ መረጃዎች አመልክተዋል። ከፈረንሳይ እና ከጣሊያን ጋር ጠቅላይ ሚንስትሩ አደረጉ የተባለው የወታደራዊ ትብብር ስምምነትም ሌላው ምስጢራዊ እንቆቅልሽ ነው። ምዕራባዊያን በጸጥታ እና ደህንነት እንዲሁም ወታደራዊ ጊዳዮች እጃቸውን አስገቡ ማለት ፈርመህ ሀገርህን አስረከብክ ማለት ነው።

******

ታዲያ ይህ ሁሉ ማንዣበብ ዝም ብሎ የመጣ አይደለም። ለውጥ እያደረግኩ ነው የሚለው የለውጥን ፊት እና ኋላ ለይቶ የማያውቅ፣ የፖለቲካም ሆነ የኢኮኖሚ ፍኖተ ካርታ የሌለው የለውጥ ቡድን ወደ ስልጣን ለመውጣት የተደረገለት ድጋፍ እንዳለው እና ለዚህም የገባው የብድር ምለሳ ቃል ኪዳን እንዳለው ጥርጥር የለውም።  ምዕራባዊያን በኢንተለጀንስ ባለሙያዎቻቸው የስነልቦናዊ አቋምህን (psycho personality) ጥንቅቅ አድርገው ያውቃሉ። ጠቅላይ ሚንስትሩ ምን አይነት ሰው እና በየትኛው የስነልቦና አይነት እንደሚመደቡ ጠንቅቀው ስለሚያውቁ አንዴ የአመቱ ምርጥ ሰው ይሏቸዋል፤ ቀጥለውም የሰላም ኖቤል ተሸላሚ እጩ ይሏቸዋል፤ ሲፈልጉም እንዲሁ በሁለት ክልሎች መካከል ያለን መንገድ ማስከፈት አና ወንጀለኛን ለህግ ማቅረብ ያልቻለ ሰው የሰላም አዋርድ ተሸላሚ ብለው ያሞካሿቸዋል።  ይህ ሁሉ ጋጋታ “ሊበሏት ያሰቧትን አሞራ ስሟን ጅግራ ይሏታል” እንደሚባለው የሀገራችን ብሂል የእጅ አዙር ጥምዘዛን ለማመቻቸት እንጂ እውነታው ጠፍቷቸው አይደለም።  በእርግጥም የእጅ ጥምዘዛ ዲፕሎማሲውን በትክክል እየተገበሩት ነው። ለምሳሌ ብንወስድ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች መተዳደሪያ አዋጅን ከብርሃን ፍጥነት በቀደመ ሁኔታ እንዲሻሻል ተደጓል። ዜጎችን በጥላቻ የፈረጀ ህገ-መንግስት፣ የምርጫ ስርዓት፣ የጸረ ሽብር ህግ ወዘተ  ሳይሻሻል 10 ሰዎች ሳይቀጥር የራሱን ተልዕኮ ለሚወጣ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት አዋጅ ቀድሞ ማሻሻል ያስፈለገው ለዚህ ነው።  በስልጣን ላይ ያለው ቡድንም ሁኔታዎችን ከውስጥ ወደ ውጭ የሚያይ ሳይሆን እጁን ዘርግቶ የውጭ ሃይሎችን የሚያስተናግድ  አቅመ ቢስ ቡድን እንደሆነ ማሳያ ነው። ከዚህ በኋላ እየገቡ ቢሻው በስነ ጾታ፣ ቢሻው በትምህርት፣ ቢሻው በሰብአዊ መብት እያሉ ስልጣን ላይ ያለውን ቡድን የአራት ማዕዘን ድጋፍ እየሰጡ የኢትዮጵያውያንን ባርነት እና ግድያ ማራዘማቸውን ይቀጥላሉ። በጥቅሉ ሲታይ ይህ ጨቅላ የሆነ ጠቅላይ ሚንስትር የውስጥ ችግር ላይ ብቻ ሳይሆን በዲፕሎማሲው መስክም ሙሉ በሙሉ ሀገሪቱን የሚያከስም ደረጃ ላይ ደርሷል ማለት ይቻላል።

ማስታወሻ፦ሁሉም በጽሁፉ ያሉ አመተ ምህረቶች በአውሮፓውያን አቆጣጠር ናቸው።

በተመስገን አስጨነቅ ዘለቀ

taschenek@gmail.com

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s