ባልደራስ ዋና ፀሃፊዬ ኤልያስ ገብሩ ታስረብኝ አለ – ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ (VOA Amharic)


ዋሽንግተን ዲሲ — በቅርቡ የተቋቋመውና የአዲስ አበባ ባለአደራ ምክር ቤት (ባልደራስ) በመባል የሚጠራው ቡድን ዋና ፀሐፊ ኤልያስ ገብሩ በቁጥጥር ስር መዋሉ ተሰምቷል። ዛሬ ፍርድ ቤት በቀረበ ጊዜ የ28 ቀን የጊዜ ቀጠሮ ተጠይቆበታል።የም/ቤቱ ሰብሳቢ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ኤልያስ እና ሌሎች በቁጥጥር ስር የዋሉ አባላት ያሉበት ሁኔታ አስከፊ መሆኑን ለአሜሪካ ድምፅ ራዽዮ ተናግሯል።

ሀብታሙ ስዩም ዝርዝር ጉዳዩን ይነግረናል።

በክልል ሰበብ ደቡብ ኢትዮጵያ ውስጥ ደም እንዳይፈስ (ሰለሞን ምትኩ)

ደቡብ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉት ወደ 13 ዞኖች በሙሉ ማለት በሚቻል ደረጃ ኢትዮጵያ ላለፉት 27 ወያኔ ሲጨቁናት በቆየው ሕገ መንግስት መሰረት የክልልነት ጥያቄ አቅርበዋል።

የደቡብ ኢትዮጵያ ብሄሮች እያነሱት ያሉት የክልልነት ጥያቄዎች ሕጋዊና ፍትሃዊ ናቸው። ሕገመንግስቱ ያስቀመጣቸውን ደረጃዎች እያለፉ መልስ ሊያገኙ ይገባል።

ላለፉት 27 ዓመታት ወያኔ ደቡብ ኢትዮጵያን ይጨቁንበት የነበረው ስርዓት ሕገ መንግስት እያለ በሚንጠራራው መሳሪያው እንኳን በማይፈቅድለት የጭፍለቃ አካሄድ መሆኑ ግልጽ ነው። አሁን ዶክተር አብይ ጠቅላይ ሚኒስትር ከሆኑልን ወዲህ ግን ይህ ኢፍትሃዊነት ይስተካከላል ወይም ለጠቅላላው ኢትዮጵያዊ የማይሰራው ሕገ መንግስት ይለወጣል ብለን ጠብቀናል። ጠቅላዩ ያለባቸው ጫና ሕገ መንግስቱን በዝህች ኣጭር ሰዓት እንዲቀይሩልን ስለማያስችላቸው ባለው ሕገ መንግስት መሰረት ተገቢውን መስፈርት ያሟሉ ጥያቄዎችን ተቀብለው መልስ እንዲሰጡልን ሲል ሕዝቡ በመወትወት ላይ ይገኛል።

መንግስት የሕዝብን ድምጽ እያዳመጠና ወደ ታች ወርዶ እየተወያየ ባለበትና የወሰንና ድምበር ጉዳዮችን እያስጠና ባለበት በዝህ ወቅት ይህንን መብት በጉልበት ለማስፈጸም የሚቸኩሉ አካላት ሃገሪቷ ያለችበትን የሽግግር ሂደት ከግንዛቤ ያስገባ ሊሆን ይገባል። ምርጫ ቦርድ ሕዝበ ውሳኔ ለመጥራት የሰው ሃይሌን እያሟለሁኝ ነው እያለ የሕዝቡን ትዕግስት እየጠየቀ ይገኛል።

ሲዳማ ወላይታ ጉራጌ ሀድያ ጋሞ ብሄረሰቦች ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉትን ብሄሮች ሕዝብ ብዛት ከ1-10ኛ ስናስቀምጥ የምናገኛቸው በኢትዮጵያ የሕዝብ ብዛት እንደ መስፈርት ከታዬ ከፍተኛ ሕዝብ ብዛት ያላቸው የደቡብ ኢትዮጵያ ብሄሮች ናቸው።

እነዝህ ብሄሮች ከጋምቤላ፥ ቤኒሻንጉልና ሕረሪ በላይ የሕዝብ ብዛት እንዳላቸው ማስረጃዎች ያሳያሉ።

የሲዳማ ሕዝብ ብዛት ከፍተኛም ነው። ጥንትም ክፍለሃገር ሁሉ ነበር። አሁን ያለንን ሕገ መንግስት ከተጠቀምን ሲዳማም ሆነ ሌሎቹ የደቡብ ብሄሮች በሙሉ ክልል ከመሆነ የሚከለክላቸው ምንም ምድራዊ ሃይል አይኖርምና ትዕግስት ይኑረን።

ሕጉ የሚፈቅደውን መብት ለማስፈጸም ለምን የአንድ ንጽሁህ ሰው ሕይወት እንኳን አደጋ ውስጥ ይገባል?

የሲዳማ ሕዝብና ኤጄቶ በአጠቃላይ ከፍተኛ ሃላፊነት በሚሰማበት ደረጃ እንዲንቀሳቀሱ እናሳስብ።

ትዕግስት የፍርሃት ምልክት አይደለም። መሬት ላይ በመንግስታችን ላይ ያለውንም ጫና በሚገባ እንረዳ።

ዶክተር አብይ የመላውን ኢትዮጵያ ሕዝብ ጥያቄ የሚሰሙ መሪ በመሆናቸው ከቶውንም Abuse ልናደርጋቸው አይገባም።

በጉልበትም ቢሆን እናስፈጽማለን ያለውን የሶስተኛ አካል ዛቻ በፍጹም ልናስተናግድ አይገባም።

እርስ በራሳችን በመዋደድ በመከባበር እናድርገው። የብዙ ልማት የተፈጥሮ ጸጋ የሃገር ኣስታራቂ ሽማግሌዎችና አኩሪ ባህሎች ባለቤት ብቻም ሳይሆን የወንጌላዊት ቤተክርስቲያናት የሙስሊም እምነቶች ባለቤት የሆነው የሕዝባችን ክፍል ትዕግስት በማጣት አላስፈላጊ ግጭት ውስጥ ገብቶ ክቡር የሰው ልጅ ሕይወት በከንቱ እንዲፈስ መፍቀድ የለብንም።

በአማራው ሞት ላይ የሚቆምሩት እነ ማን ናቸው? (በረራ ጋዜጣ)

የአማራ ክልል ፀጥታ ኃይል ስልጠናዎችን እየሰጠ በነበረበት ወቅት አንድ አነጋጋሪ ጉዳይ ተፈጥሮ ነበር። አሰልጣኝ ተብለው ከተመረጡት ግለሰቦች መካከል አንደኛው የክልሉን መሪዎች እንዲሁም የፀጥታ ኃይሉ አመራሮችን እርስ በእርስ ለማጣላት ሲሰራ እንደተደረሰበት ባሕርዳር አካባቢ ብዙ ተወርቷል። ይህ መሪዎቹን ለማጣለት ሲሰራ የተደረሰበት ግለሰብ እንደተባረረ የተነገረ ሲሆን ላኪዎቹ አዲስ አበባ ያሉ ባለጊዜዎች እንደሆኑ ከወደባሕርዳር ሲወራ ሰንብቷል። ላኪዎቹ አቅም ያላቸው እንደመሆናቸው አመራሮችን እስር በእርስ ለማፋጀት ሲሰራ የነበረ ሰው ተደርሶበት ያለ ምንም ቅጣት ወደ አዲስ አበባ መላኩ በብዙዎቹ ዘንድ ሲነገር የሰማ አማራው የብዙ ቁማርተኞች መነሃሪያ ሆኖ መሰንበቱን ለመረደት አይሳነውም። የአማራ ክልል መሪዎችና የፀጥታ ኃይሉ ኃላፊዎች እርስ በእርስ እንዲፋጁ ሲሰራ ነበር የተባለው “አሰልጣኝ” ጉዳይን ላስታወሰ የሰሞኑን አሳዛኝ ድርጊት በፊትም አማራውን ለማገዳደል ስራዎች ሲሰሩ እንደነበሩ መገንዘብ አያዳግተውም። የሰሞኑ አሳዛኝ ድርጊት በስተጀርባ እነ ማን አሉ የሚለው ወደፊት ይበልጥ ግልፅ የሚሆን ቢሆንም በርካታና በቀላሉ የማይገመቱ ኃይሎች እንዳሉበት ጠቋሚ ምልክቶች ታይተዋል። ከሰሞኑ ክስተት በስተጀርባ እነማን አሉበት የሚለው ቀጣይ ምርመራ በደንብ የሚያረጋግጠው ሆኖ በክስተቱ እጃቸውን ያስገቡ አካላት ላይ ማተኮር የተሻለ ይሆናል።

አማራው በርካታ አወንታዊ አበርክቶዎችን ሲሰጥ ዝምታን ሲመርጥ ባጅቶ ስህተት ፈፀመ ብሎ ሲያምን ከየጎሬው ብቅ የሚለው የፖለቲካ ኃይል ቁጥሩ በርከት ያለ ነው። ለዚህ እንደአብነት ከሰኔ 15ቱ የባሕርዳሩ ክስተት ማግስት በሀዘን ላይ የነበረውን አማራውን ለመርገም ብቅ ብቅ ያለውን የፖለቲካ ኃይል ማየት በቂ ነው። ላለፉት ጥቂት ወራት የአማራው ፖለቲካ ለአማራ ጠል ኃይሎች አስጨናቂ ነበር። በምዕራብ ጎንደር በኩል የጫሩት ሳት ብዙ መስዋዕትነት አስከፍሎም ቢሆን እንዲበርድ ሆኗል። በአካባቢው የመሸገ ፀረ አማራ ኃይል ከመቸውም ጊዜ በላይ ምሽጉን እንዲለቅቅ ተደርጓል። ብዙ ሚስጥሮቹ ተዝረክርከዋል። በምድረገኝ/ከሚሴ፣ አጣዬ፣ ሸንኮራ፣ …አማራውን ለመውረር ጥረት ያደረጉ “ተረኛ” ገዥዎች በኢትዮጵያ ሕዝብ ፊት ተጋልጠው ተመልሰዋል። በተለያዩ ግንባሮች ወደ አማራው የዘመተ ፀረ አማራ ኃይል በአብዛኛው ተጋልጦ ተመልሷል። አማራውን የጦር ቀጠና ለማድረግ ሲሰሩ የነበሩ አካላት በቁጥጥር ስር ሲውሉ ላኪዎቻቸው ቡራ ከረዩ ብለው አልተሳካላቸውም። ለምሳሌ ያህል በምድረገኝ/ ከሚሴ፣ ኤፌሶን/አጣዬና አካባቢው በአማራው ላይ ጥቃት የሰነዘሩት በቁጥጥር ስር ሲውሉ ላኪዎቻቸው የሌላን ክልል መንግስት መዋቅር ተጠቅመው አድማና ብጥብጥ እንዲደረግ ጥረት አድርገዋል። ይሁንና የአማራ የፀጥታ ኃይል ይህን የፀረ አማራዎች ቅስቀሳ ወደተግባር ተቀይሮ ሕዝብ ላይ ችግር እንዳይፈጠር መመከት ችሏል። ይህን የተገነዘቡት ኃይሎች የአማራው መደራጀት ለውጥ ማምጣቱን በመመልከታቸው ከባድ ድንጋጤ ውስጥ ነበሩ። በዚህ ስጋትና ድንጋጤ ውስጥ እያሉ በለስ ቀናቸው። የባሕርዳሩ አሳዛኝ ክስተት ተፈጠረ።

የባሕርዳሩ ክስተት የውስብስብ ጉዳዮች ውጤት ቢሆንም ጉዳዩን በመግፋት ፀረ አማራ ኃይሎች እንዳሉበት የሚያጠራጥር ጉዳይ አይደለም። ለዚህ በዋቢነት ሊጠቀሱ የሚችሉት ጉዳዩ ከተከሰተ ጀምሮ የተሰጠው መግለጫ፣ ፍረጃዎችና እርምጃዎች ናቸው። ጉዳዩ በተፈጠረ በሰዓታት ውስጥ “መፈንቅለ መንግስት” የሚልና የችኮላ ብያኔ ተሰጠው። ምንም አይነት ምርመራ ሳይደረግ አዲስ አበባ ላይ ተፈጠረ ከተባለ ሌላ ክስተት ጋር እንዲያያዝ ተደረገ። ጉዳዩን ፈፅመውታል የተባሉ አካላት ላይ በማስመሰል ወደ ሕዝብ በርካታ የጥላቻ ጠጠሮች ተጣሉ። የመንግስት ስልጣን ላይ ያለ አካል “ፋሽስት” ብሎ አማራው ላይ የተፈጠረውን ክስተት በምን መንገድ እንደሚይዘው ፍንጭ ሲሰጥ በዚህ ጎራ ሳይርቅ ተቃዋሚ ነን ያሉት አማራውን ጨፍጫፊ በማፍረግ ለሌሎችም ተሟጋች በመምሰል አማራው ላይ የሰነበቱ የሀሰት ዶሴዎችን በመምዘዝ አማራው ላይ በተመሳይ የጥላቻ አውደ ግንባር ተሰለፉ። የአማራ ብሔርተኝነትን ከመኮነንና የሕዝብን ስም ከማጥፋት አልፈው የመንፈስ አባታቸው መለስ ዜናዊ እንደሚለው አማራውን አከርካሪውን ለመምታት መልካም አጋጣሚ አድርገው ወሰዱት። በዚህም መሰረት ገቢዎችና ጉምሩክን የአንድ ቋንቋ ተናጋሪ መስርያ ቤት ልታደርጉት ነው ብለው በስም ዝርዝርና በጥሬ ማስረጃ የተሟገቷቸውን ሰዎች አጋጣሚውን ተጠቅመው አሰሩ። ከታሳሪዎቹ መካከል ገቢዎችና ጉምሩክ በተረኞቹ መጥለቅለቁን በሰነድ ያጋለጠውና የተቋሙ ሰራተኛ የነበረው ማስተዋል አረጋ ይገኝበታል።

በየቦታው አማራው ላይ የሚፈፅሙትን በደል፣ ኢትዮጵያ ላይ የሚያሳዩትን ስግብግብ ፖለቲካ የተቹ ማሕበራዊ አንቂዎችን፣ የስግብግብነት ልካቸውን ሳይሸፋፍን የሚሟገታቸውን አብን አባላትን፣ በዜጎች ላይ የሚፈፅሙትን በደል በመዘገብ የሚያጋልጣቸውን አሥራት ሚዲያ ባልደረቦች በማሰር የአማራውን ኃይል ለማዳከም የሚችሉትን ሁሉ አድርገዋል። ባለፉት አስር ወራት ከኦሮሚያና ከአዲስ አበባ በገፍ ካባረሯቸው የተረፉትን አማራዎች በማሳደድና በማሰር የጥላቻ ሰይፋቸውን እንደ አዲስ መዝዘዋል። ሆኖም በአማራው ላይ የተፈጠረው ክፍተት ከዚህም በላይ የጥላቻ አላማቸውን የሚያራምድላቸው መሆኑን ተገንዝበዋል። በዋነኝነት ደግሞ አማራው ባለፉት ጥቂት ወራት የተከላቸውን መልካም ጅምሮች በማፈራረስ አንገቱን አስደፍቶ መግዛትን አላማቸው አድርገዋል። በዚህም መሰረት ልዩ ኃይሉን ትጥቅ ለማስፈታት፣ የፀጥታ ተቋማቱን ለማፈራረስ እቅድ ሰንቀዋል። የአማራ ሕዝብ ደጀን ይሆናል የተባለውን ፋኖን በማሳደድ፣ የገበሬውን መሳርያ በማስፈታት፣ በተለያየ ስራ ላይ የተሰማሩ የፀጥታ አካላትን በመወንጀልና በማሰር አማራውን ማራቆት ላይ ያተኮረ ስራ ለመስራት ተሞክሯል። ሰኔ 15/2011 ዓ/ም ባሕርዳር ላይ ችግር ሲፈጠር የታገቱትንና የግድያ ትዕዛዝ ወጥቶባቸው የነበሩትን ኮ/ል አለበል አማረ፣ ጀኔራል ተፈራ ማሞ ጨምሮ በፀጥታ መዋቅሩ ጉልህ ሚና የነበራቸውን ግለሰቦች የአዴፓን መደናገጥ በመጠቀም ለእስር ዳርገዋል። ወደ አዲስ አበባ ለማምጣትም ጥረት አድርገዋል። እነዚህ ግለሰቦች የኦሮሞ አክራሪዎች በአማራው ላይ ጥቃት ሲፈፅሙ ከፅንፈኞቹ አመራሮችና ላኪዎቻቸው ጋር የተፋጠጡ በመሆናቸው ቂም ተይዞባቸው ቆይቷል። ይህ ክስተት ሲፈጠርም አማራውንና አመራሮችን ለመበቀል ብዙ ርቀት ተሂዷል። በአሁኑ ወቅትም ይህ የጥላቻ እርምጃ ተቀልብሷል ለማለት አያስደፍርም። በእርግጥ የባሕርዳሩን ክስተት አማራውን በማዳከም ብቻ ሳይሆን ራሳቸውን በማጠናከርም ቀላል የማይባል ስራ እየሰሩበት መሆኑን ከቀናት በኋላ የተሰጡት ሹመቶች ማሳያ ናቸው። ኢታማዡር ሹሙ ከተገደሉ በኋላ ከወደ ትግራይም ሆነ ከመሃል ሀገር የፌደራል መንግስቱ ላይ ብዙ አስተያየቶች ተሰጥተዋል። ይህ አስተያየት ይበልጥ ወደራሱ እየተጠጋ እንደሆነ የሰሞኑ የስልጣን ድልድል አይነተኛ ማሳያ ነው። ጀኔራል ሰዓረ መኮንን የኢታማዡር ሹም ናቸው ቢባልም መከላከያውን ሲያዙት የቆዩት ምክትላቸው ብርሃኑ ጁላ ናቸው። የባሕርዳሩን ክስተት አዲስ አበባ ተስቦ መጨረሻው የስልጣን ቁማር ውስጥ ገብቷል። ሰሞኑን ሲሰጡ የሰነበቱት አስተያየቶችን ለማምለጥ ሲቋምጡበት የነበረው ወንበር ላይ አልወጡም። ይልቁንም ሌላ ስሌት ነበር። ጠቅላይ ሚኒስትሩ የጦር ኃይሎች ዋና አዛዥ ናቸው። የመከላከያ ሚኒስትሩ አቶ ለማ መገርሳ ናቸው። ለስም ምክትል ይሁኑ እንጅ ብርሃኑ ጁላ ከኢታማዡር ሹሙ በላይ አዛዥ ናዛዥ ናቸው። በዚህ መሃል ኢታማዡር ሹም መሆን በተረኞቹ ከመጨፍለቅና ከመታዘዝ ያለፈ ሚና የለውም። በአንፃሩ ኦዴፓ ሲቋምጥበት የነበረውን ሌላ ቦታ ለመያዝ ጊዜ አግኝቷል። የብሔራዊ መረጃ ደሕንነት አገልግሎት። ለዚህም ሲባል የብሔራዊ መረጃ ደሕንነት አገልግሎት ዳይሬክተር የነበሩትን ጀኔራል አንስተው ከአብይና ለማ ስር፣ እንዲሁም ለስሙ ከብርሃኑ ጁላና በርካታ የኦሮሞ ጀኔራሎች መሃል አስገቧቸው። የብሔራዊ መረጃ ደሕንነት አገልግሎትን በራሳቸው ሰው ተኩ። ከዚህ ቀደም የኢንፎርሜሽን መረብ ደሕንነት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተርን በቁማር ወደ አዴፓ ማዕከላዊ ኮሚቴ አስጠግተው ተመሳሳይ ቁማር ሰርተዋል። በአሁኑ ወቅት ሁለቱም የመረጃ መስርያ ቤቶች፣ የመከላከያ ሚኒስትርና ሌሎች ቁልፍ ተቋማትን ተቆጣጥረዋል። አብዛኛውን ተቋማት ክስተቶችን ጠብቀው የወረሷቸው ሆነው እናገኛቸዋለን።

የኦሮሞ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኦዴፓ) ከሚመራው ቁማርተኛ ኃይል ባሻገር ከዚህ ቡድን ጋር የጦርነት ነጋሪነት ሲጎሳሰም የሚውለው ትህነግ/ሕወሓት መራሹ ቡድንም የባሕርዳሩን ክስተት ተከትሎ የአማራው ውድቀት ላይ እጠቀማለሁ የሚል የቅዠት ፕሮፖጋንዳ ውስጥ ገብቶ ተስተውሏል። ብአዴን/አዴፓ የአማራ ሕዝብ ጥያቄዎች እንዲመለሱ እታገላለሁ ሲል የመጀመርያው ጥያቄ የማንነትና ወሰን ጥያቄ እንደሆነ ሲገልፅ ቆይቷል። ይህም በአዴፓ/ብአዴን እና ትህነግ/ሕወሓት መካከል ትልቅ የልዩነት መስመር ሆኖ ቆይቷል። ትህነግ/ሕወሓት የአዴፓ/ብአዴን አመራሮችን ከተቃዋሚ መሪዎች ባልተናነሰ ሲያወግዛቸው ከርሟል። በሌላ በኩል የአማራን ሕዝብ በውክልና ጦርነት በመወጠር ለማባከን ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል። እንደ ኦሮሞ ፅንፈኞች ሁሉ በአማራ ላይ ሲያሰማራ የነበረው ወኪሎች የተሸነፉበት ትህነግ/ሕወሓት የአማራ ፀጥታ ኃይል ኃላፊዎች ያከናወኗቸውን ስራዎች በስጋትነት ሲመለከት ቆይቷል። የአዴፓ/ብአዴን አመራርን አቋምና ስራዎች በስጋትነት ሲመለከት ቆይቷል። ኦዴፓ በፊት መንገድ እንደሚመራቸው ፅንፈኞች ሁሉ ትህነግ/ሕወሓትም የባሕርዳሩን ክስተት አማራውን አንገት ለማስደፋት ለመጠቀም ጥሯል። የትግራይ ክልል ም/ርዕሰ መስተዳደር በሰጡት መግለጫ በጉዳዩ ኖሩበትም አልኖሩበትም ከፌደራል መንግስቱ ጋር በመተባበር በርካቶችን እንደሚያስሩ በግልፅ ተናግረዋል። ጦር ለመማዘዝ ማዶና ማዶ ሆነው ሲናቆሩ ከሚውሉት የፌደራል መንግስት ጋር አንድ አቋም ያስያዛቸው “ትምክተኛ” የሚሉት የአማራ ጉዳይ ነው። በዚህም መሰረት ትህነግ/ሕወሓት በግድ በያዛቸው የአማራ ግዛቶች ውስጥ አማራዎችን እንደ አዲስ ማሰር ተጀምሯል። የፌደራል መንግስቱ የሚወስደውን አፈናም አብረው እያገዙ መሆኑን ተናግረዋል። የኦሮሞ እና የትግራይ ፅንፈኞችን አንድ ያደረጋቸው በአማራ ላይ የያዙት ክፉ አመለካከት ነው። አማራው ችግር ሲገጥመው ጠብቀው ተቋማቱን በመምታት፣ አመራሩን በማሰር አንገት ለማስደፋት አላማ አድርገው እየሰሩ ነው። ይህ ቁማር ባሕርዳር ላይ የተፈጠረውን ክስተት ተጠቅመው፣ ለተገደሉት ያዘኑ፣ ለሕግ የሚቆሙ መስለው በአማራው ሕዝብ ላይ እየሰሩት ይገኛሉ። ሆኖም እነዚህ በአማራው ሞት የሚቆምሩ አካላት ያልተረዱት አማራው የደረሰበትን የፖለቲካ እርከን ነው። ባለፉት አመታት ኢትዮጵያ እንዳትፈርስ የአማራነት ጎኑ ሲደቃ ዝምታን የመረጠ ሕዝብ ዛሬም በተመሳሳይ የፖለቲካ ሁኔታ ላይ ያለ ይመስላቸዋል። እውነታው ግን ሌላ ነው። አማራው ስለ ኢትዮጵያ ብቻ ሲወገር ተረኞች ተፈራርቀውበታል። ሲቆስልበት የኖረውን ማንነቱን አላስነካም ካለ ጥቂትም ቢሆኑ አመታት እየተቆጠሩ ነው። ዛሬ ላይ ደግሞ በአራቱም አቅጣጫ የሚቃጣበትን ጥቃት ለመመከት ዝግጁ የሆነበት ጊዜ ነው። ስለ ኢትዮጵያ ስለደማ ብቻ የሀገሩን ስም አስር ጊዜ ሲጠራ ለሚውል የሚታለልበት ወቅት አይደለም። ከመቸውም ጊዜ በላይ ጠላቶቹን ለይቶ ያስቀመጠበት ወቅት ነው። ጠላቶቹ ያስቀመጡበትን እንቅፋቶች ለማለፍ አቅም እንዳለው የሰሞኑን ውዥንብርና የጠላቶቹን ቁማር እያለፈበት ያለው መንገድ ሁነኛ ምስክር ነው።

በሌላው እንዴት ሊሆን ነው ?! (ይድነቃቸው ከበደ)

የብ/ጀነራል አሳምነው ጽጌ የባንክ ደብርተር ነው ተብሎ በምርመራ ቡድኑ ለህዝብ የተለቀቀው ይሄ የመስላል ፦

 የባንክ ቅርንጫፍ = M.G (ሜጀር ጀነራል)
 ዜግነት = ጉለሌ
 ስራ = 12 ድጅት ስልክ ቁጥር
******
*ብ/ጀኔራል አሳምነው ፅጌ እራሱን ለመደበቅ በሌላ ክፍለከተማ በስሙ መታወቂያ 17ኛ ቤተሰብ ሆኖ አውጥቷልም ብለውናል። ሰውን እራሱን ለመደበቅ በእራሱ ስም እንዴት ያወጣል???
********
ስለቤቱ ጉዳይ ብሩክ አበጋዝ የሚከተለውን አጣርቻለሁ ብሏል ፦

☞ የቡራዩው ቤት የተባለው የብ/ጀነራል አሳምነው አሁን በእስር ቤት ያለችው ሚስቱ የወ/ሮ ደስታ አሰፋ ቤት ነው። ወ/ሮ ደስታ ላሊበላ ታዋቂ የነበረው የሮሀ ሆቴል ባለቤት የአሰፋ ግርማይ ልጅ ነች።
.
☞ የሰበታው ቤት ዓምና በፍርድ ቤት የተለያዩትና የ3 ልጅ እናት የሆነችው የወ/ሮ አልማዝ አስፋው ቤት ነው።
:
☞ ሃያት የተባለው መኖሪያ ቤቱ፤ ከወ/ሮ አልማዝ ጋር ሲለያዩ ለእሱ የደረሰው መኖሪያ ኮንዶሚኒየም ነው።
:
☞ ጉለሌ በወዳጆ ሞላ ተመዘገበ የተባለው ቤትም ባለቤቱ ወዳጆ ሞላ አሳመነው በእስር እያለ ጠበቃ የነበረው ግለሰብ ቤት ነው፡፡ አቶ ወዳጆ የላስታ ሰው ነው፤ ከእስር እንደተፈታ የቤተሰብ አባል አድርጎ ለአሳምነው መታወቂያ ያወጣለትም እሱ ነው። ይህን ሰውም አስረውታል።

እናም ፤ የምርመራ ቡድኑ ደረስኩበት ካላቸው ወንጀሎች እና ማስረጃዎች መካከል የብ/ጀኔራል አሳምነው ፅጌ ይህ ከሆነ ፣በሌላው እንዴት ሊሆን ነው ?! ኧራ ጎብዝ ወዴት እየሄድን ነው ?! ማለት አሁን ነው።

ከማል ገልቹ በሰላም ሲሸኝ አሳምነው ለምን ሊገደል ቻለ? – ዲጎኔ ሞረቴው ከሚድ ዌስት አሜሪካ

በሃገራችን ኢትዮጲያ ሰዎች በስልጣን ላይ በሚቆዩበት ወቅት ከባልደረቦቻቸው ጋር ባለመስማማት ገሚሶቹ በሰላም ሃላፊነቱን ሲለቁ ሌሎቹ በግድያ ይወገዳሉ ይታሰራሉ:: የታደሉት በጎ ነገር ሰርተው በክብር ሲሸኙ ሲሞገሱ አንዳንዶቹም ክፉ ቢሰሩም በወዳጆቻቸው ጥፋቱ ተሸፍኖ በክብር ሲሰናበቱ በቅርቡ ያየናቸው ብዙዎች  አሉ ; ; በዚህ ክፍል ግን ተመሳሳይ ሃላፊነት የነበራቸው ከተለያይ ብሄር ወይም ክልል ስለሆኑት  ባለስልጣኖች አንተነትናለን::                                                          

በሃገራችን ታሪክ ይህ በስልጣንና በፖለቲካ መገዳደል የታሪካችን ዋና አካል ሆኖ የቆየ ሲሆን በዚህ ወቅት በአለም ዙሪያ በሃይል ስልጣን መያዝ በተወገዘበትና በሃገራችንም ብዙ የሰላም ተስፋ ከገዥዎቹ መንበር ባልተለመደ ሁኔታ በሚነገርበት ወቅት ይህ መከሰቱ በጣም ያሳዝናል ልብንም ይሰብራል ለትውልድም የሚተወው መልክት በጣም ያሳፍራል::

የሰሞኑ የፖለቲካ ውዝግብ መገዳደልን ከመንግስት ጀምሮ ሁሉም ለየራሱ በሚመች መልክ ሲያስፋፋው ደግሞ የበለጠ ያናድ ዳል የሃገርና የወገኖቻችን ጉዳይ ግድ ለሚለው ግን ጉዳዮቹን  ለምን እንዴት በማለት በሚዛናዊነት በማነጻጸር ይህ ድርጊት እንዳይደገም ምክር ይለግሳል በተፈጠረውም ድርጊት የተነሳ ተጨማሪ ጥላቻ መገዳደል እልቂት እንዳይከተል ይመክራል;:

ከዚህ በፊት ተመሳሳይ ሃላፊነት የነበራቸው ጄንራል ከማል ገልቹ ከኦሮሚያ ክልል በሰላም ሲሸኙ ቅሬታ እንደነበረባቸው በክልሉ መሪዎችና በገዥው ፓርቲም ላይ ሃዘናቸውን የገለጹ ሲሆን የጄነራል አሳምነው ግን ወደመገዳደል ማምራቱ ለምን እንዴት ተከሰተ ለወደፊቱስ ቁርሾ እንዳይኖር ምን ማድረግ ይኖርብናል ብለን መጠየቅ በቅን መምከር ይኖርብናል::ከሁሉም በላይ የጄነራል አሳምነው ልጆች ልብ በሚነካ ሁኔታ የአባታቸውን ሞት ከገለጹ በኋላ ያለው መንግስት ጄነራሉ እንደገደሏቸው ለሚያወራው የዶ/ር አምባቸው ልጆች የገለጹት የፍቅር የይቅርታ መልክት የሚያረካ እልቂቱ ቂምና ጥላቻው ይቀጥል ዘንድ ለሚፈልጉ ክፉዎች ደግሞ ጥሩ የመልስ ምት ይሆናል::

በመንግስት ስልጣን ሽኩቻ መገዳደል ሰለባ የሆኑ  ልጆች ከጥንቱም  ጀምሮ የነበሩ ሲሆን  በህይወት የተረፉት የኮሎኔል አጥናፉ አባተ ልጆች ያስሙት የቅርብ ጊዜው ምስክርነት በጣም የሚያሳዝን ነበር:: የታደሉት ደግሞ የጄነራል ደምሴ ቡልቶ ልጆች  አባታቸው ለሃገር መሻሻል ግፈኛውን ለማስወገድ ባደረገው ሙከራ በራሱ ወታደሮች ተገድሎ ክቡር ሰውነቱ በሜዳ ላይ የጎተቱትን ቂም ሳይቆጥሩ ዛሬ በተማሩት እውቀት በተለይ በውጭ ሃገር ሲያገለግሉ ማየቱ ትልቅ ቁም ነገር ነው::

ለማጠቃለል  በምክንያታዊ ትንታኔ በማየት ጄነራል አሳምነው የነበረባቸው ሃላፊነት  በብዙ መፈናቀል በብሀረተኝነት ሳይቀር በወቅቱ መሪ የሚነቀፍ አማራን ክልል ልዩ ሃይልን በሚገባ በማደራጀት በአጣዬ በወልቃይት በከሚሴ በክፉ ሃይሎች የተጨፈጨፉትን ለመጠበቅ በልዩ ሁኔታ ባደራጁት ልዩ ሃይል ሰበብ በሃገሪቱ መሪዎች በክልላቸው መሪ ሳይቀር ጥርስ ውስጥ መግባታቸውን ግምት ውስጥ በማስገባት አድርገውታል የተባለውም መገዳደል ላደረጉት በምክያታዊ ትንታኔ cause and effect ያሉበትን ሁኔታ መረዳት እንጂ የተለመደው የመንግስት የማጥላላት ዘመቻ በአንድ ጄነራል ቤት ቀላል መሳሪያ መገኘትን በልዩ ወንጀል መፈርጅ የቅርብ ባልደረቦቻቸውና  ለክልላቸው የቆሙትን የልዩ ሃይል አባላት ማስረ ማዋከብ  ለነገ የሚያስከትለውን ጠንቅ በማወቅ ማስቆም ሃላፊነት የሚሰማው መንግስት ተግባር መሆን ይኖርበታል::

ከሁሉም በላይ ስለጉዳዩ በጣም ኣወዛጋቢና ጥርጥር ውስጥ የሚያስገቡ መግለጫዎችን ባለው መንግስትና  በተለያዩ የማህበራዊ ዜና ምንጮች ስለሚሰማ ጉዳዩ በገለለተኛ አካል መጣራት ለሃገሪቱ መጻኢ እድል ወሳኝ ነው:: የኣማራ ክልል የሚባለውም የወቅቱ መሪዎች ራሳቸውን ይመርምሩ ዘንድ የዚህ መሰሉ የሃላፊነት ቦታ የነበራቸው የሌላው ክልል ሃላፊ በሰላም መሰናበት የአማራው ክልል ሃላፊ ስንብት በመገዳደል የተቋጨበትን ሁኔታ ከውስጥ ድክመት ከፌደራሉ  መንግስት ጣልቃ ገብነት መሆን ያለመሆኑን ሊመረምሩ ሊስተካከሉ ይገባል:: በሃገር ደረጃም ያለው መንግስት ለውጡን በትክክለኛው መንገድ ለመቀጠል ትልቁን የህዝብ ድጋፍ ለመጠበቅ የበለጠ ግልጽነት ሚዛናዊ አሰራርና የህግ የበላይነትTransparency and rule of law ይከተል ዘንድ ያስፈልጋል ያለበለዚያ በታልቁ መጽሃፍ አባባል ስንነካከስ ኣብረን መፍረስ ይከተላል::

ኢትዮክራሲ፣ የኢትዮጵያ ማኅበራዊ ኃላፊነትን ያነገበ የገበያ ኢኮኖሚ (በአባተ ካሣ)

በአባተ ካሣ     መጋቢት 20, 2011

የዚህ ጽሁፍ ዓላማ የሀገሬ ልጆች ኢትዮጵያውያን የአባቶቻችንን የግዕዝ ፊደላትን የመፍጠር መሰል የቀደምትነት ተመክሮ እንደ አርዓያ በመከተል ሀገር-በቀል የኢትዮጵያ ርዕዮተ-ዓለም ይነድፉ ዘንድ ለማበረታታት ነው። ይህ ማዘዣ አይደለም፤ ለውይይት መነሻ የሚሆን ጥቆማ እንጂ።

አባተ ካሣ

የበለፀጉ እና በማደግ ላይ ያሉ ሀገራት በዓለም ላይ ይገኛሉ። አብዛኛዎቹ በአፍሪካ የሚገኙት በማደግ ላይ ያሉ ሀገራት ነፃነታቸውን የተቀዳጁት ገና በ1953ዎቹ የመጀመሪያ ዓመታት ነበር። ይሁንና ኢትዮጵያ፣ በሺህ ዓመታቶች የተመዘገበ ታሪኳ የምትኮራና ከአምሰት-ዓመት የጣሊያን ወረራ በቀር በዚያ ሁላ ዘመን ሁሌም ነፃነቷን የተጎናጸፈች ሀገር የነበረች ግን በማደግ ላይ ካሉት ሀገራት ጎራ ናት። 1966 በኢትዮጵያ የዘውዳዊ ሥርዓት (monarchy) ፍፃሜን እና የጥቂቶች ሥርዓት (oligarchy) ጅማሬን ያሳየ ዓመት ነበር። ሆኖም ከፖለቲካ ባህሏ አኳያ ዛሬ ላይ ለኢትዮጵያ ይበልጥ ተስማሚ የሚሆነው የፖለቲካ ሥርዓት፣ በተፎካካሪ ወይም ተወዳዳሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ዘንድ ሥልጣን የሚከፋፈልበት የብዙሃን ሥርዓት (polyarchy) ሊሆን ይችላል።

ለአንድ ሀገር ተስማሚ የልማት ሞዴል የማመንጨቱ ኃላፊነት በራሱ በሕብረተሰቡ ላይ ይውላል፤ ከራሱ ታሪክ እና ባህል እንዴት መማር እንደሚችል በመመርመርና በውስጥ እና በውጭ አካባቢ ሁናቴዎች ያሉትን እንቅፋቶች እና እድሎች ሙሉ በሙሉ በመረዳት ይሆናል። ስለሆነም የራሳችን ለሆነ ጉልብትና ስለሚበጅ አዲስ ዓይነት ሞዴል የተወሰኑ ቁልፍ እሳቤዎችን እስቲ እንገምግም።

ብዙዎቹ በማደግ ላይ ያሉ ሀገራት ብሔራዊ ኢኮኖሚያቸውን ለማጎልበት የወሰዱት ሞዴል የበለፀጉ ኅብረተሰቦች የተከተሉትን ካፒታሊስት አልያም ሶሻሊስት ሞዴል ነው። ነገር ግን አብዛኛዎቹ አሁንም ድረስ በአስከፊ ድህነት እና በአሽቆልቋይ ኢኮኖሚ እየተሰቃዩ ይገኛሉ፤ ኢትዮጵያም ከእነርሱ የተለየች አይደለችም።

ይሁንና፣ ካፒታሊዝምም ሆነ ሶሻሊዝም አያሌ ያልተፈቱ ችግሮች አሉባቸው። እውቁ ጣሊያናዊ ጋዜጠኛ አሪጎ ሌቪ፣ እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር ጥቅምት 30/1980 ታይምስ ኦፍ ሎንደን ላይ “Failure Cannot Shatter the Socialist Dream” በተሰኘ ጽሁፉ፣ ጉዳዩን እንደሚከተለው በግልፅ አስቀምጦታል፡-

ሶሻሊስቶች ገነት ስለሆናች አገር ያልማሉ፤ ሁልአቀፍ ብልፅግና ያለውና በዚያ ላይ ደግሞ ለግለሰቦች ፍፁም ነፃነትን የሚያጎናፅፍ መደብ-አልባ የእኩሎች ኅብረተሰብ ይመኛሉ። ይህቺ ገነት የሆነች አገር መቼም እውን ሆና አታውቅም።

የሶሻሊስት ህልም የጠንካራነቱ ኃያልነት እጅግ ምሁር የሆኑ ግን ደግሞ ለሶሻሊዝም የማርክሲስት ኃልዮት አሰቃቂ ውድቀት ፍፁም ጭፍንነትን ያዳበሩ ብዙ ሰዎች መኖራቸው ነው።

የማርክሲስት ሶሻሊዝም መትረፍረፍንም ሆነ እኩልነትን አልያም ነፃነትን ማቅረብ እንደማይችል አረጋግጧል። ስልተ-ምርት ሙሉ በሙሉ በመንግስት ቁጥጥር ስር መሆን ለሶሻሊስት ዩቶፕያ መሠረት ሊሆን ይችላል የሚለው ሀሳብ፣ ዛሬ ላይ ታሪካዊ የቁም-ቅዠት ብቻ ስለመሆኑ ገሀድ ወጥቷል።

የታሪክ ተሞክሮ እንዳስተማረን፣ የሶሻሊስት አወቃቀር መሠረት ማበጀት የሚችለው ለየተማከለ፣ አምባገነን ሥርዓት እና የሕዝብን ድምፅ የማያከብር የፖለቲካ ኃይል ብቻ መሆኑን ነው።

ሰርቶ-አደሩን በማኅበር የመደራጀት ነፃነቱን፣ ሸማቹን ደግሞ አማራጭ የማግኘት መብቱን ይነፍጋል።  እጅግ አስከፊ የሆነ የአላቂ ሀብቶች ክፍፍል ሥርዓትን ያቀርባል። ፈጠራን አዝጋሚ ያደርጋል። ተቀዛቅዞ እስኪቆም ድረስ ኢኮኖሚውን ይጫነዋል።

እንደዚህ በግልፅ ስህተት በሆኑ እሳቤዎች ላይ ይህን ዓይነት የከረረ አቋም ሊኖር የቻለው ሌሎች እሳቤዎች በተመሳሳይ አጥጋቢ ሳይሆኑ በመገኘታቸው እውነታ ብቻ ነው።

በርግጥ በምዕራቡ ዓለም በአብላጫነት የሚተገበረው “ቅይጥ ኢኮኖሚ (mixed economy) ፣ የማኅበራዊ ዋስትና መንግስት (welfare state)” ሞዴል፣ ታላላቅ የታሪክ ስኬቶቹ እንዳሉ ሆኖ፣ ታላላቅ ስንክሳሮችን ባለማቋረጥ ያስከስታል፡- ግሽበት እና ሥራ-አጥነት፤ እንዲሁም ቅጥ-ያጣ ኢፍትሃዊነት እና የእኩልነት እጦት፣ ትርፍ አግበስባሽነት፣ እና ስግብግብነት ይገኙበታል።

ስለሆነም፣ ሁለቱም ሶሻሊስቶች እና ካፒታሊስቶች ከመቼውም ጊዜ በበለጠ የተሻለ ቀመር በመፈለግ ላይ ይገኛሉ።

ሪቻርድ ኤል. ስክላር “Beyond Capitalism and Socialism in Africa” በተሰኘ ርዕስ በሞደርን አፍሪካን ስተዲስ ጆርናል (Journal of Modern African Studies, 26 (1988), pp. 14-15, 18) በካፒታሊዝም እና በሶሻሊዝም መካከል ባለው ‹ታላቅ ፉክክር› አስመልክቶ ባቀረበው እይታ ላይ፣ ንፅፅሮሹን እንደሚከተለው ያብራራዋል፡-

ዛሬ ላይ ጥቂት ታዋቂ ሶሻሊስቶች የሶሻሊዝምን “የልማታዊነት ብቃቶች” ከካፒታሊዝም ብቃቶች በላይ አድርገው ይመዝኗቸዋል፤ ጥቂቶቹ ደግሞ በኢንዱስትሪ ጉልብትና የመጀመሪያ ደረጃ ላይ ለሚገኙ ማኅበረሰቦች የካፒታሊዝምን የአጭር-ጊዜ ጠቀሜታ ይሞግታሉ። በምትኩም ሶሻሊዝም እንደ ካፒታሊዝም ባለ የሠራተኛው ሕዝብ ልዩ መብት በተሰጠው መደብ በመጨቆን እና በመበዝበዝ ላይ በሚመረኮዝ የኢኮኖሚ ሥርዓት ላይ የሞራል የበላይነት አለው ብለው ይከራከራሉ። ሶሻሊዝም ክሽፈቶች ቢኖሩትም የርዕዮት እና የፖለቲካ ንቅናቄ እንደሆነ ቀጥሏል፤ ምክንያቱም ካፒታሊዝም በተናጠል ከማኅበራዊ ኢፍትሃዊነት ጋር ተዛምዶ ታይቷል። የግለሰብ የደህንነት ስጋት፣ የማኅበራዊ አደረጃጀት እጦት፣ እንዲሁም የከተማ ሥራ-አጥነት በአፍሪካ ውስጥ ያለው ካፒታሊዝም ህያው አጋላጮች ናቸው።

ለሦስት አስርት ዓመታት በአፍሪካም ሆነ በሌላ ቦታ በሚገኝ የሦስተኛው ዓለም በቆየው የሙከራ ጊዜ የማኅበራዊ ተሟጋቾች የሶሻሊዝም እክሎች ገጥመዋቸዋል። ለሶሻሊስቶች ሊማሩት ዘንድ የከበዳቸው ከባዱ ትምህርት ካርል ማርክስ ከማንም በተሻለ ያስተማረው ነው። በግልፅ ሲቀመጥ፣ ሀብትን (capital) ምንም አይተካውም፤ የኢኮኖሚያዊ ጉልብትና አቀሳቃሽ ኃይል እርሱ ነው። ለሶሻሊስቶች ሁለተኛው ትምህርት፣ ይህም ከማርክስ መማር የማይቻለው ትምህርት፣ ሶሻሊዝም ብቁ የሆነ የማበረታቻ ኃልዮት (theory of incentives) የሌለው ስለመሆኑ ነው።

ሲጠቃለል፣ ሶሻሊዝም ሀብት (capital) ያስፈልገዋል፣ እንዲሁም የማበራቻ ኃልዮት (theory of incentives) ይጎድለዋል፤ በሌላ በኩል ካፒታሊዝም መንግስት ያስፈልገዋል፣ እንዲሁም የማኅበራዊ ኃላፊነት ኃልዮት ይጎድለዋል። የአፍሪካ ሀገራት የኢኮኖሚ ሥርዓቶች ለአጠቃላይ ሚዛናዊ የኑሮ ሁኔታ የግል ሀብት፣ አግባብነት ያለው የመንግስት ተሳትፎ፣ ጠንካራ ማበራቻዎች፣ እንዲሁም ሕዝባዊ ኃላፊነት ያስፈልጓቸዋል። እነዚህ የማኅበራዊ እድገት መደበኛ መመዘኛዎች ሊሟሉ የሚችሉት በካፒታሊዝም እና በሶሻሊዝም ጥንቃቄ የተሞላበት ቅይጥ ብቻ ነው።

ጉዳዩ በማደግ ላይ ያሉ ሀገራት ወይ የካፒታሊስት አልያም የሶሻሊስት ሞዴልን በፍፁምነት እንዲቀበሉ የሚወስናቸውን ገዳቢ የፖለቲካ አስተሳሰብ ትክክለኛነቱን መፈተን ነው። እኔ ኢትዮክራሲ (Ethiocracy) በሚል መጠሪያ የማቀርበው ሀሳበ-ዘ-መፍትሔ (proposal) ከሁለቱ ሞዴሎች ጥንካሬዎቻቸውን ጥቅም ላይ የሚያውል፣ ግን ደግሞ ድክመቶቻቸውን የሚያስወግድ ንፅረታዊ (relativistic) እና ተግባራዊ (pragmatic) አቀራረብን በማስተዋወቅ ያንን አስተሳሰብ ለመተካት ይሞክራል።

ደርግ እውነቱ ሶሻሊዝም ነው አለ። ህወሓት/ኢሕአዴግ ደግሞ የጐሣ ፌደራሊዝምን እንደ እውነት ይመለከታል። ሁለቱም ከግለሰብ ይልቅ ቡድን የሚያስቀድሙ ስርአቶች የተሳሳተ ፍፁምነትን ይከተላሉ። ስቴፈን ሃውኪንግ እንደነገረን ግን፣ “ከህዋ (universe) መሠረታዊ ሕጎች አንደኛው ምንም ፍፁም የሆነ ነገር የለም የሚለው ነው። ፍፁምነት (perfection) ከነጭራሹ የለም። ያለ ፍፁም-አልባነት ደግሞ አንተም ሆንክ እኔ አንኖርም ነበር።” ጽንፋዊ የሆነ የሶሻሊስት ኢኮኖሚ ፖሊሲ እንደ ኢትዮጵያ ላለ ለቅድመ-ኢንዱስትሪያዊ የግብርና ኢኮኖሚ አግባብነት እንዳልነበረው ታዝበናል። ገደብ-አልባ ካፒታሊዝምም ቢሆን አዋጪ አማራጭ ተደርጎ ሊወሰድ አይችልም።

የሶሻሊዝምን ከልማት ኃልዮት ረገድ መውደቅ እና የካፒታሊዝምን ከማኅበራዊ ኃላፊነት አኳያ ውድቀት ከግንዛቤ በማስገባት፣ ጥንካሬዎቹን ውጤታማ የሚያደርግና ድክመቶቹን አላስፈላጊ የሚያደርግ አንድ ተግባራዊነት ያለው የኢኮኖሚ ሥርዓት መምረጥ ይገባናል። የ‘ስልት/ግብ’ (means/end) አመክንዮአዊ መነሻ ንጽጽሮሹን ለማብራራት ይረዳን ይሆናል፡- ካፒታሊስት እንደ ስልት እና ሶሻሊስት እንደ ግብ። ሶሻሊዝም እንደፍልስፍና ‘እዝአዊ/directive’ ነው፤ ድልድዮችን አይገነባም ወይም እንጀራ አይጋግርም። ካፒታሊዝም እንደ ሳይንስ ‘ምርታማ/productive’ ነው፤ የልማት ኃልዮት ነው። የሶሻሊስት ስልተ-ምርት በከፍተኛ መጠን የእዝ ኢኮኖሚን ሲከተል፣ የካፒታሊስት ሞዴል ደግሞ የገበያ ፍላጎቶች ላይ ያተኩራል። የሶሻሊስት መንገድ የቡድናዊነትን (collectivism) ቅርፅ ሲወስድ፣ ካፒታሊስት ግላዊነት (individualism) ላይ አፅዕኖት ያደርጋል። የሶሻሊስት ሥርዓት የስልተ-ምርቱ ሕዝባዊ ባለቤትነትን ለማስፋት ቁርጠኝነት ሲያሳይ፣ ካፒታሊስቱ ሰፊ የግሉ ዘርፍ ባለቤትነትን ይመርጣል።

ኢትዮክራሲ በበኩሉ፣ ሀሳቦች እና ድርጊቶች በቀኖናዊ የርዕዮት ዓለም መስመሮች ሳይሆን፣ በጠቃሚ ውጤቶቻቸው የሚመዘኑበት ተጨባጭነትን (pragmatism) ይከተላል። የነፃ ገበያ ገፅታዎችን ከመንግስት ጣልቃ-ገብነት ጋር እንደወረደ ከሚያጣምረው ከቅይጥ ኢኮኖሚ ሞዴል በተለየ መልኩ፣ ኢትዮክራሲ የሁለቱንም የካፒታሊስት እና ሶሻሊስት እሳቤዎች ያካትታል፤ ነገር ግን እሳቤዎቹ እየተመረጡ የሚካተቱት በሥርዓቱ ክህሎት፣ መሠረተ-ልማትና ቴክኖሎጂ ላይ መዋዕለ ንዋይ በማፍሰስ፣ የቡድን ሥራን በመደገፍ፣ ፉክክር እና ፈጠራን በማበረታታት፣ ዓለማቀፋዊ ትስስሮችን በማሳደግ፣ እንዲሁም የሀገር ውስጥ ቁጠባን እና የሀብት ምስረታን በማስተባበር ምርታማነትን የሚጨምር እድገት-ወዳድ የጋራ አስተሳሰብን (pro-growth mindset) የማስረፅ አቅም ላይ መሠረት በማድረግ ሲሆን፣ በሀቀኛ ዴሞክራሲ፣ በሕግ የበላይነትና ከሞራል አንፃር ትክክል በሆኑ እርምጃዎች ላይ በሚያተኩር በጠቃሚያዊነት (utilitarian) አሰራር የሚታገዝ ነው። ኢትዮክራሲየዜጎችን ምሉዕ ተሳስትፎ ውጤታማ ለማድረግ የኢትዮጵያን ባሕላዊ እሴቶች ያቅፋል፤ ምክንያቱም “ባሕል ስትራቴጂን ቁርስ ስለሚያደርገው።” የፖለቲካ ሥርዓት ባሕልን ሳይሆን በተቃራኒው ባሕል የፖለቲካ ሥርዓትን መወሰን ስላለበትና የፖለቲካ ባሕል በአንድ የፖለቲካ ሥርዓት ውስጥ ለሚከናወን ሁሉም ነገር የመሠረት ድንጋይ በመሆኑ ምክንያት፣ ከኢትዮጵያ የፖለቲካ ባሕል ይኸውም የፖለቲካ እርምጃዎች የሚወሰዱባቸውን ሁናቴዎች ከሚወስኑ መሠረታዊ የእምነቶች ሥርዓት፣ አመለካከቶች፣ እሴቶች እና ገላጭ ምልክቶች ጋር ተዛማጅነት ያለው ሥርዓት መንደፍ የግድ አስፈላጊ ይሆናል። እዚህ ላይ ኢትዮጵያ የፖለቲካ ባሕሏን በማጎልበት ረገድ ሺህ ዓመታቶችን የከፈለች ስለመሆኗ አፅንዖት መስጠት እፈልጋለሁ፣ እናም መሬት ላይ ያሉት እውነታዎች ፍፁም የተለዩ በሆኑባት ሀገር ላይ ፀጉረ-ልውጥ ተመክሮ መጫን አግባብ አይሆንም።

ፒዬሮ ጌሄዶ “Why is the Third World Poor” በተሰኘ መፅሐፉ ላይ እንደሚያስቀምጠው መከራከሪያ፣ መንፈሳዊው የልማት ፅንሰ-ሀሳብ ልማትን እንደ የሰው ልጅ እውነታ፣ ስለሆነም ቴክኒካዊ ወይም ኢኮኖሚያዊ ከመሆኑ በፊት በቀዳሚነት ባሕላዊ እንደሆነ አድርጎ ይመለከተዋል። የሚያድገው እና የሚጎለብተው ሰው በመሆኑም፣ ኢትዮጵያዊው ፈላስፋ ዘርዓ ያዕቆብ (1599-1692) እንዳለው፣ “ሰው የእራሱ ልማት ቀዳሚው አስፈፃሚ ነው።” እናም ልማት እውነተኛ እንዲሆን ከተፈለገ፣ ሕዝቦች መለወጥ እንዲቻላቸውና የተለያዩ የህይወት ሁናቴዎችን ይላመዱ ዘንድ ለሁሉም ሕዝብ ተስማሚ የሆኑ የባሕል እሴቶችን ሊያከብር ይገባዋል። የአንድ ሀገር ቁሳዊ እድገት ማንነቷን የሚወክለውን የቆየ ባሕሏን ለማጣቷ ክፍያ ሊሆን እንደማይችል ጌሄዶ በአፅዕኖት ያስቀምጣል።

የካፒታሊዝም እና የሶሻሊዝም፣ እንዲሁም የሊበራል ዲሞክራሲ እና የሶሻል ዲሞክራሲ መልካም ጎኖችን በማዋሃድ እኔ ኢትዮክራሲ በማለት የጠራሁትን አዲሱን የኢትዮጵያ የማኅበራዊ፣ የኢኮኖሚ፣ እና የፖለቲካ ፖሊሲ ታገኛለህ። ኢትዮክራሲማኅበራዊ ኃላፊነትን ያነገበ የገበያ ኢኮኖሚ፤ ሀገር-በቀል አዲሱ የኢትዮጵያ ርዕዮተ-ዓለም ነው። ኢትዮ የሚለው ኢትዮጵያን የሚወክል ሲሆን፣ –ክራሲ አንድ የመንግሥት ወይም የአገዛዝ ዓይነትን ይጠቁማል። ስለዚህም ኢትዮክራሲ ኢትዮጵያዊ የመንግስት ስርዓት መንገድ ነው፣ ምክንያቱም ሀገራችን የራሷን መቀየስ ይኖርባታልና! ኢትዮክራሲ የኢትዮጵያ እውነተኛ ዲሞክራሲ መገለጫና የሁሉንም ዜጎች እኩልነት፣ የግለሰብ ሰብዓዊ መብቶችን፣ እንዲሁም የሕግን የበላይነት ያገናዘበ በእውቀት ላይ የተመሠረተ ኢኮኖሚ ነው። ኢትዮክራሲ ዲሞክራሲያዊ ላልሆነውና ጐሣን መሠረት ላደረገው የፖለቲካ ኢኮኖሚ፣ለኢትዮዽያ ተስማሚ ላልሆነው የህወሓት/ኢሕአዴግ አብዮታዊ ዲሞክራሲ እና ልማታዊ መንግስት ፖሊሲ በአማራጭነት የቀረበ ነው። ልማታዊ መንግስት ሞዴል ለቻይና እና ለሌሎች የምስራቅ እስያ ሀገራት ሰርቷል፤ ምክንያቱም እነርሱ የጐሣ ፌዴሬሽን ፖሊሲ እራስ ምታት የለባቸውምና። ህወሓት/ኢሕአዴግ የተከተለው የጆሴፍ ስታሊን ጐሠኝነት ሞዴልን እንደመሳሪያ በመጠቀም የእከክልኝ-ልከክልህ ዜሮ-ድምር ፓለቲካ ነው። ጐሠኝነትን የመንግሥት ስልጣንን ለመቆናጠጥና የግል ሀብትን ለማካበት (ዝምደኝነት/cronyism እና ኪራይ-ሰብሳቢነት/rent-seeking) እንደ ስልት ተጠቅሞበታል።

ኢትዮክራሲ የኢኮኖሚ ዘርፉን በአራት ክለስተሮች ይመድባቸዋል፤ በተጠቃሽም በመንግስት ባለቤትነት ስር ያሉ፣ በግሉ ዘርፍ የተያዙ፣ በኅብረት ሥራ ማኅበራት የተያዙ፣ እና ሌሎች ድርጅቶች/ተቋማት።

(ሀ) የመንግሥቱ ዘርፍ እንደ መንገድ፣ ማረሚያ ቤት፣ የአየር ትንበያ፣ ፖሊስ፣ ፓስፖርት፣ ፖስታ ቤት፣ እና የመሳሰሉትን ሕዝባዊ መሠረተ-ልማቶችን ያቀርባል።

(ለ) የግሉ ዘርፍ በቅርበት በተያዘም ሆነ ይፋዊ ገበያ ላይ በሚቀርቡ አክሲዮኖች አማካኝነት በገበያ ኃይላት ቁጥጥር የሚደረግባቸው ምርት እና አገልግሎቶችን ያደርሳል።

(ሐ) በኅብረት ሥራ ማኅበራት የተያዘው የኢኮኖሚ ዘርፍ እንደ የግብርና ኅብረት ሥራ ማኅበራት ባሉ አቅራቢዎች ቁጥጥር ስር የሆኑ ተቋማትን ይመለከታል፤ ወይም በጋራ ባለቤትነት ስር እንዳሉ ኩባንያዎች ሌሎችም በደንበኞች ቁጥጥ ስር የሆኑ ኩባንያዎች፤ እንዲሁም ሌሎች በሠራተኞች ባለቤትነት እና ቁጥጥር ስር የሆኑ ተቋማት።

(መ) በባለቤትነት ያልተያዙት ሌሎች ደግሞ እንደ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች (NGOs)፣ ለንግድ ያልተቋቋሙ ድርጅቶች (NBOs)፣ እንዲሁም በማኅበራት ያልተያዙ ድርጅቶች (NCOs) ዓይነት የሆኑ ለትርፍ ያልተቋቋሙ ተቋማትን ያካትታል። የሙያ ማኅበራት፣ የንግድ ማኅበራት፣ በጎ አድራጎት ድርጅቶች፣ ዩኒቨርሲቲዎች፣ ሆስፒታሎች፣ እንዲሁም ቀይ መስቀል የመሳሰሉት በዚህ ዘርፍ ውስጥ ይገኛሉ።

ለሶቭየት ሕብረት መፈራረስ መሠረታዊ ምክንያቶች ከነበሩት አንደኛው ሁሉም ነገር በመንግሥት ባለቤትነት መያዙ ነበር። ስኬታማ ለመሆን አራቱንም የባለቤትነት ቅርፆች በስፋት ጥቅም ላይ የማዋል አመዛዛኝ እርምጃ መውሰድን ይጠይቃል። ገበያን ለመተካት ከሚጥሩ መንግሥታት ይልቅ ገበያ የሚፈጥሩ መንግሥታት እድገትን በማፋጠን ረገድ ይበልጥ ስኬታማ ናቸው። በነገራችን ላይ፣ የመንግሥት ተሳትፎ ፈጠራን ያቀጭጫል የሚለው ከፍተኛ ተቀባይነት ያለው የካፒታሊስት ምልከታ ይኑር እንጂ፣ በቻይና የሚታየው ይህ አይደለም።

ማኅበራዊ ኃላፊነትን ባነገበው የኢትዮክራሲ የገበያ ኢኮኖሚ፣ የፍቅር እና እንክብካቤ ፍልስፍናዎች በፉክክራዊ ገበያ ላይ ከተጣበቁት የስግብግብነት እና ራስ-ወዳድነት ፍልስፍናዎች ጋር ይማዘናሉ። አክራሪ የነፃ-ገበያ አቀንቃኞች (Market fundamentalists) የጋራ ጥቅም በተሻለ ሁኔታ እውን የሚሆነው ያለ ምንም ገደብ የራስን ጥቅም በማስጠበቅ ነው የሚል የተሳሳተ እምነት አላቸው። ገበያዎች ፍትሃዊ የሀብት ክፍፍልን (distributive justice) ለማምጣት የተነደፉ አይደሉም። ለምሳሌ፣ የግል ኮርፖሬሽኖች የሥራ ዕድል መፍጠርን ዓላማ አያደርጉም፤ ትርፍ ለማምጣት (በተቻለ መጠን ጥቂት እና በርካሽ ዋጋ) ሰዎችን ይቀጥራሉ። የንግድ ተቋማት የሚፎካከሩት ለማትረፍ ነው፣ ፉክክሩን ለማስቀጠል አይደለም፤ እንዲያውም ቢቻላቸው ሁሉንም ተፎካካሪዎች ከነጭራሹ ያስወግዱ ነበር። ኢትዮክራሲ ከጂዲፒ (GDP) ይበልጥ ስለአዕምሮ ጤና እና ስለሕጻናት ድህነት ይጨነቃል።

ከቀኖናዊ ግትርነት ይልቅ፣ ኢትዮክራሲ ተጨባጭነት ያለው ተለዋዋጭነትን (flexibility) ይከተላል። ኢትዮክራሲ ፍፁማዊውን የመንግሥት ዓይነት እሳቤ ይቃወማል። ፍፁም (perfect) ባልሆነ ዓለም ውስጥ ፍፁም መንግሥት ሊኖር አይችልም፤ ውዳቂውንም (mediocrity) ዝም ብለን መቀበል የለብንም። ኢትዮክራሲ የንግድ ዓይነት ተጨባጭ የኢኮኖሚ አመራር ስልትን ይከተላል። ለዜጎቹ ጥበቃ፣ ፍትሕ እና ምርጥ መንግሥታዊ አገልግሎቶችን በተቻለ መጠን በጣም በዝቅተኛ የሀብት ወጪ ለማቅረብ የሚተጋ እየላቀ የሚሄድ መንግሥት መመዘኛዎችን ነድፎ ያቀርባል። ለለውጥ የተቃኘ ስለሆነና በርዕዮት-ዓለም ስንክሳሮች እንዳይደናቀፍ ዕድል ስለማይሰጥ፣ ኢትዮክራሲ መንግሥታዊ ልህቀትን እውን በማድረግ ጉዞው የተሻሉ መመዘኛዎች በማሳካት ሕዝባዊ አገልግሎት እያሻሻለ ይቀጥላል። ከሃይማኖት በተለየ መልኩ፣ በኢትዮክራሲ የፖለቲካ ኢኮኖሚ እሳቤዎች ምንጊዜም በለውጥ ሂደት ላይ ሲሆኑ፣ ለግትር ርዕዮት ቦታ የለውም። ኢትዮክራሲ ለትግበራ እና ውጤት፣ ለባለሙያ እውቀት፣ እንዲሁም በሁሉም ወገን አሸናፊነት (win-win) ትብብር አማካኝነት እውን ለሚሆን የጋራ ጥቅም አስፈላጊነት ትልቅ ዋጋ ይሰጣል።

ኢትዮክራሲ ከሁለቱም ከካፒታሊዝም እና ከሶሻሊዝም ነቅሰን ብናስቀራቸው ጠቃሚ የሆኑትን ንጥረ-ነገሮች የሚያቅፍ አማራጭ (flexible)፣ ፈጠራዊ፣ እና ኢ-ቀኖናዊ አካሄድን በመከተል የአንዲት ደሃ ሀገርን ‘መሠረታዊ ፍላጎቶች’ ለማሟላት ይጥራል። በዚህም ጥግ-ደረስ የሆነ የካፒታሊዝምም ሆነ የሶሻሊዝም ፖለቲካን ውድቅ ያደርጋል። በሌላ አገላለፅ፣ኢትዮክራሲአንዱን ከሌላው የመምረጥ ቀኖናዊ እና ግትር አካሄድ ለታዳጊ ኅብረተሰብ የማይገባ ወይም ገዳቢ እንደሆነ አድርጎ ይመለከተዋል። በኢትዮክራሲ ፋይዳ ላለው ሥራ ቅድሚያ የሚሰጥ መንግሥት፣ ለልማት የተነሳሳ አስተሳሰብ፣ አሳታፊ ዲሞክራሲ፣ ሕገ-መንግሥታዊ አወቃቀር፣ መልካም አስተዳደር፣ እንዲሁም በምርጫ መሳተፍ የዜጋዊ ኃላፊነት ሆኖ ምርጫዎችም በሳምንቱ መጨራሻ የእረፍት ቀናት የሚካሄዱባቸው ቢሆኑ የሚመርጥ እና እነዚህ ስርዓቶች በኢትዮጵያ ውስጥ የመንግሥት መሠረታዊ ደንቦች ሆነው እንዲያገለግሉ ያሳስባል።

በድሮው የፍፁም ዘውዳዊ አገዛዝ፣ እንዲሁም በዛሬው የአንድ-ፓርቲ የበላይነት ሥርዓት ላይ በፖለቲካ እና በአስተዳደራዊ ተቋማት መካከል የአስተዳደር ጉልብትና አለመመጣጠን ይታያል፤ የአለመመጣጠኑ ሚዛን ለኋለኛው ባደላ መልኩ። ስለሆነም እንደ ሕግ አውጪ እና የፖለቲካ ፓርቲዎች የመሳሰሉትን የመንግሥታዊ አስተዳደር ሥርዓትን ግንባታ ዋና ዋና አካላት ለማጠናከር በአግባቡ የተነደፉ የተቋማት አቅም ግንባታ ፕሮግራሞችን የመጀመሩ አስፈላጊነት ከፍተኛ ነው።

የፋሺስት አምባገነን (የጣሊያኑ)፣ ንጉሣዊ አምባገነን፣ ወታደራዊ አምባገነን፣ የሠርቶ-አደር አምባገነን፣ እንዲሁም የአንድ-ፓርቲ አምባገነን ሥርዓቶች በተከታተል ለኢትዮጵያ ድህነትን እና ስቃይን አትርፈዋል። ኢትዮክራሲ በመባል በቀረበው ማኅበራዊ ኃላፊነትን ባነገበው የገበያ ኢኮኖሚ መንግሥት ሥልጣኑን የሚያገኘው ነፃ በሆነ እና በተደጋጋሚነት በሚካሄዱ ምርጫዎች አማካኝነት ከሕዝቡ በተገኘ ፈቃድ ነው። የመንግሥት ሥልጣን መቆጣጠሪያዎቹ የሦስቱ መንግስት አካላት መዛኙ ቁጥጥር (check-and-balance system) ፣ በነፃ ፕሬስ ልጓም ቁጥጥር፤ እንዲሁም የፖለቲካ አመራር አባላቱ ከተፎካካሪ/ተወዳዳሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል ሲመረጡ ነው። በተጨማሪም አዲሱን ሕገ-መንግሥት የምናውጀውና የምናቋቁመው አንድ አውራ-ፓርት ሳይሆን እኛ ዜጎቹ ስንሆን ብቻ ነው። ከ86 ብሔሮች የተውጣጡትና በግምት 123 የሚሆኑትን ቋንቋዎች የሚናገሩ ግን አንድ የጋራ አማርኛ የሥራ ቋንቋ ያላቸው የዛሬይቱ ኢትዮጵያ 110 ሚሊዮን ሕዝቦች ለረዥም ጊዜ በሕብር ኖረዋል፤ ማለትም እኛ ኢትዮጵያውያን ለዘመናት የመደመር ታሪክ ያለን ሕዝብ ነን። የህወሓት/ኢሕአዴግን የፖለቲካ አጀንዳ ለማስፈፀም የተነደፈው አሁን የሚገኘው ጐሣ-ተኮር ፌደራሊዝም ሕገ-መንግሥት፣ የሰላማዊ አብሮነት የባሕል እሴቶችን ከማበረታታት ይልቅ ‘የእርስ-በርስ ግጭቶችን’ የሚያቀጣጥል መለያየትን እያስፋፋ በመሆኑ፣ ሊሻሻል ወይም በሌላ ሊተካ ይገባል።

የፖለቲካ ለውጥ ያለ የኢኮኖሚ ለውጥ ለሕዝቦች ምንም ማድረግ በማይችሉት ጉዳይ ላይ ቅሬታ የማቅረብ ነፃነት ብቻ ነው የሚሰጠው። ስለዚህም የቀመሩን የኢኮኖሚ ክፍል ይበልጥ እናብራራ። አዲሱ የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ፖሊሲ የምግብ አመራረትን በማሳደግና ርሃብን በማስወገድ ላይ ማነጣጠር ይኖርበታል። ይህን ለማድረግም ማኅበራዊው በጀት ከወታደራዊው በጀት በጉልህ መጠን የበለጠ መሆን አለበት፤ ሆኖም ይህ የሚሆነው የሀገሪቱን ደህንነት አደጋ ላይ በማይጠል መልኩ እንደሆነ ሲረጋገጥ ነው። ይህ ፖሊሲ ግብርናን፣ የጥሬ-እቃ ምርትን፣ እና ቀላል ኢንዱስትሪን በመደገፍ የሚጀምር የተመጣጠነ ልማት (balanced development) ላይ ያተኩራል። አዲስ ትኩረት ሊሰጠው የሚያስፈልገው ወደ ውጭ የመላክ አቅምን አሳድጎ የውጭ ንግድ ገቢን ለማረጋገጥና የውጭ ቴክኖሎጂዎችን ለመግዛት እንዲቻል እንደ ስኳር፣ ጥጥ፣ ቆዳ እና ቡና ኢንዱስትሪዎች ባሉ ፋይዳ ጨማሪና (value-added) ግዙፍ የሰው ኃይል የሚጠቀሙ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ልማት ነው።

የብድር ዕዳ የጂዲፒ 59% መሆን ልማትን ከባድ ያደርገዋል። አዲሱ መንግሥት በውርስ ለሚረከበው ተንጠልጣይ ዕዳ፣ የብድር ማቅለያ ዐቅድ (debt relief scheme) መንደፍ አስፈላጊ ነው። አዲሱ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ሁለተኛው የዓለም ጦርነትን ተከትሎ ከተተገበረው ማርሻል ፕላን ወይም የአውሮፓን ማገገሚያ ፕሮግራም ጋር ተመሳሳይ የሆነ የካፒታል ፍሰትን የሚያመጣ የገንዘብ አቅርቦትን ከወዲሁ ያስብበታል። እንዲህ ያለው የመልሶ-ግንባታ ስትራቴጂ ዛሬ ላይ ለኢትዮጵያ አስፈላጊ ሊሆን ይችላል፤ ምክንያቱም ለዚህ የሚያስፈልጉት አብዛኛዎቹ መዋቅሮች እና ተቋማት እንዳሉ አሉ ወይም ሊጠገኑ/ሊዘጋጁ ይችላሉ።የገበያ ፍላጎትን (demand) እንዲያንሰራራ ለማድረግና በዚህም የኢኮኖሚ ማገገምን ለማሳካት የመንግሥት የግዢ ወጪዎችን መደገፍ እንዲያስችል የገበያ ፍላጎት-ተኮር የሥራ አመራር ስትራቴጂን መንደፍ ያስፈልጋል። እንዲህ ዓይነቱ ስትራቴጂ የተፈለገውን ውጤት እንዲያመጡ የታለሙ የኢኮኖሚ ፖሊሲዎችን ይበልጥ በማጥራት ከማስተካከያ እና ከማስቀጠያ ምልከታዎች መካከል እያማረጠ በሚጓዝ የበጀት ዓመት ፖሊሲ መደገፍ ይኖርበታል። ከዚህ አኳያ ሊተገበሩ የሚገባቸው የአጠቃላዩ የኢኮኖሚ ፖሊሲ መመሪያዎች እነዚህን ያካትታሉ፡- የምርታማነት መጨመርን ለመደገፍ እና የመግዛት አቅምን እውን ለማድረግ በሥራ ቅጥር አልያም ደግሞ ያለሥራ ቁጭ ብሎ የነበረውን የሰው ኃይል በሕዝባዊ የሥራ ፕሮግራሞች ላይ በማሳተፍ የሰው ሀብትን ስምሪት፤ ዘላቂ የቱሪዝም እድገት መገንባት፣ የዘላቂ ውጤት መዋዕለ-ነዋይ ፍሰት (impact investing – ይህም ለሕዝብ መልካም ሁኔታን ለሚያበረክቱ ለማኅበራዊ እና ለአካባቢያዊ ተፅዕኖዎች መጨነቅን የመሳሰሉ ለማኅበረሰቡ በጎ የማድረግ ሥራዎችን በተጓዳኝ እያከናወኑ ዘላቂ የገንዘብ ትርፍን ማሳካት)፤ እና ለጂዲፒ እድገት ወሳኝ የሆነውን ቁጠባን ማበረታታት።

መፃኢ ጊዜያችንን ለመተንበይ የተሻለው መንገድ መፃኢ ጊዜያችንን እራሳችን መፍጠር ነው። አዲሱ በእውቀት ላይ የተመሠረተው የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ፖሊሲ በተግባር ለሚገኙ መሠረታዊ ፍላጎቶች እና ለሕዝቦች ተስፋ ምላሽ መስጠት የሚኖርበት ሲሆን፣ ሀገሪቱ በስፋት የተንሰራፋውን ርሃብ፣ በሽታን፣ እንዲሁም መሃይምነትን በ2031 ዓ.ም. እንደምትቆጣጠር ያቅዳል።

የመሬት ስሪት ማሻሻያ፡ አለምነህ ደጀኔ እንደሚለው፣ በኢትዮጵያ ውስጥ መሬት በአንፃራዊነት በብዛት ይገኛል፤ ከ75 እስከ 85 ሚሊዮን ሄክታር የእርሻ መሬት ኢትዮጵያ አላት። ከአርሲ የተገኙ ጥናቶች ለአብዛኛው ገበሬ ውጤታማ ግብርና ለማካሄድ በነፍስ-ወከፍ 5 ሄክታር መሬት አግባብነት ሊኖረው ይችላል የሚለውን የደሳለኝ ራህማቶን ጥናት ይደግፋሉ። በኢትዮጵያ ለረዥም ዘመን የቆየውን መሬትን በግል ባለቤትነት የመያዝ ባህል ከግምት በማስገባት፣ እንዲሁም የግብርና ዘርፉን ዳግም እንዲያንሰራራ ለማድረግ፣ በግብርና የሚተዳደሩ ቤተሰቦች የእርሻ መሬት የግል ባለቤትነት ሊፈቀድላቸውና ምርታቸውንም በነፃ ገበያ መሸጥ እንዲችሉ ሊደረግ ይገባል። አዲሱ የግብርና ፖሊሲ አዲስ የሆነ የ‘መሬት ለአራሹ’ መርሀ-ግብር እውን በማድረግና በሁሉም ከአጭር-ጊዜ የዝቅተኛ ብድር አቅርቦት ጋር በተያያዙ ዋጋዎች ላይ ቁጥጥርን በማንሳት ላይ ሊያነጣጥር ይገባል። እድገቱ እየጨመረ ያለውን የኢትዮጵያን ሕዝብ ለመመገብ፣ የግብርና ምርታማነት መሻሻልን ይጠይቃል። ስለሆነም ድህነትን ወደሚቀጥለው ትውልድ ላለማስተላለፍ፣ በበሬ ከማረስ ዘመናዊ የግብርና ተስማሚ ቴክኖሎጂን ተቀብሎ ወደመተግበር የሚደረግ ሽግግር ቅድሚያ የሚሰጠው ብሔራዊ እንቅስቃሴ ሊሆን ይገባል።

መንግሥት በሕግ የሚቆጣጠረው ነገር ግን ግለሰቦች በባለቤትነት ይዘውት የሚያንቀሳቅሱት የገበያ ሥርዓት፣ ከሁለቱም ዓለማት ምርጦቹን ተመክሮዎች ያጣመረ ስለመሆኑ እውቅና ሲሰጠው ቆይቷል። ከማትረፍ ዓላማ እና ከፉክክር/ከውድድር አነቃቂነት ጋር በተያያዘ የግሉ ዘርፍ ባለቤትነት ምርታማነትን ሲያበረክት፣ የመንግሥት የገበያ ሕጋዊ ክትትል መኖር ደግሞ ከትርፍ ጎን-ለጎን ለሕዝቡ አገልግሎት እና ደህንነት ተደራሽ ስለመሆናቸው ያረጋግጣል። አንድ ንግድ በኪሣራ መንቀሳቀስ ወይም ትርፍ ባለማስገኘት ቢቀጥል ከነጭራሹ መኖሩን እንደሚያቆም ሁሉ፣ ትርፍ እንደ ወሳኝ መስፈርት ተደርጎ እውቅና ሊሰጠው ይገባል፤ ምክንያቱም የንግድ ብልፅግና ለአንድ ሀገር ህልውና መሠረታዊ ነው። በተጨማሪም የመንግሥትና-የግል ትብብር/ሽርክና (public-private partnership – PPP) ፅንሰ-ሀሳብ በመሠረተ-ልማት ፕሮጀክቶች ይጠቅም እንደሆን የፋይዳ ትንታኔ (value-for-money – VfM) ልዩ ጥናት ማድረግ ተገቢ ይሆናል።

ኢትዮክራሲ የሕዝቡን መሠረታዊ ፍላጎቶች ከመንግሥት በላይ ገበያው በተሻለ መመዘን ይችላል የሚለውን የኢኮኖሚ ንቡር ኃልዮት (classic economic theory) የሚቀበል ሲሆን፣ በተጨማሪም አንዳንድ ነገሮች በጣም ወሳኝ ከመሆናቸው የተነሳ ለማያስተማምነው ለገበያውውሳኔ መተው መልካም እንዳልሆነም ያምናል። ገበያም ሕግ ከሌለ ሌብነትን ይጋብዛል። ስለሆነም የሕዝቡን መሠረታዊ ፍላጎቶች እና የግሉን ዘርፍ የሚያገናኝ አካል ለማቅረብ ከመንግሥት የሆነ ዓይነት ማኅበራዊ ቁጥጥር ይጠበቃል። የግሉ ኢንዱስትሪ ተመጣጣኝ ትርፍ የማግኘት መብት አለው፤ ሆኖም ሠራተኞቹም ጤንነታቸው እና ደህንነታቸው የመጠበቅ መብት አላቸው፤ ሸማቹ አደገኛ ያልሆነ እና በአግባቡ የተመረተ የምርት ዕቃ የማግኘት መብት አለው፤ እንዲሁም ሕዝቡ አየር፣ ውሃ እና ደረጃውን የጠበቀ ሕይወት የመኖር መብቱ የተጠበቀ መሆን አለበት። የማይታየው እጅ የሚባለው የገበያ ኡደት ለሁሉም ነገር መፍትሔ ሊያቀርብ አይችልም፤ መንግሥት ጥያቄ ወይም ክስተት የማይጠብቅ (proactive) እንዲሆን እና ለከተሞች፣ ለአየር ንብረት ለውጥና ለከባቢ ሁናቴ ኃላፊነትን መቀበል ይኖርበታል። ኢትዮጵያ አሁን የምትገኝበትን ሁኔታዎች ከግምት በማስገባት፣ በግራ ከሶሻሊዝም ግድፈቶች እና በስተቀኝ ከልቅ ካፒታሊዝም መሀከል በመሆን የኢትዮክራሲ ተጨባጭ አማራጭ ይበልጥ ተስማሚ ሊሆን ይችላል።

ኢትዮክራሲ የግል ኢንዱስትሪው በተሻለ ሊከውነው የሚችለውን መንግሥት ሊሠራው አይገባም በሚል መርሆ መሠረት የግል እና የመንግሥት ባለቤትነቶች ጎን-ለጎን በሚኖሩባቸው ፖሊሲዎች ላይ የተግባር ሙከራ ማድረግን ይፈቅዳል። የግል ባለሀበቶች መተማመኑ እንዲኖራቸው መንግሥት ቁጥጥር እና የሕግ ማዕከፎችን (frameworks) የማቋቋም ኃላፊነት ሊጣልበት ይገባል። የሚፈለገው የሁለቱም ጤናማ የመንግሥት ዘርፍ እና ጤናማ የግሉ ዘርፍ መኖር ነው። ስለሆነም ኢትዮክራሲ የመንግሥት ባለቤትነትን በሚከተሉት ሁኔታዎች ላይ ይፈቅዳል፡- (ሀ) ለሁሉም አስፈላጊ በሆኑ እንደ ትራንስፖርት እና ውሃ ዓይነት አገልግሎቶች፤ (ለ) ለሌሎች በአግባቡ መንቀሳቀስ አስፈላጊና መሠረታዊ በሆኑ እንደ ኢነርጂ እና ኤሌክትሪክ ያሉ ቁልፍ ኢንዱስትሪዎች፤ (ሐ) አዲስ ኢንዱስትሪ ለማቋቋምም ሆነ የድሮውን ለማዘመን ከፍተኛ ካፒታል የሚጠይቁና መንግሥት በራሱ ካፒታሉን ሊያመነጭ በሚችልባቸው አንዳንድ ትግበራዎች፤ እንዲሁም (መ) ሞኖፖል አግባብ በሚሆንበት ጊዜ፣ ለምሳሌ ኃይል ማመንጨት፤ ምክንያቱም ሕዝቡ በመንግሥት በኩል ባለቤት በመሆን ከፍተኛውን ቁጥጥር ሊይዝ የሚችልበት ዓይነት ዘርፍ በመሆኑ።

ዛሬ በኢትዮጵያ ያለው ገዢ ፓርቲ ፖለቲካውን ከመምራት ባሻገር፣ በቴክኒካዊ እና በኢኮኖሚያዊ የማምረት ሥራ አመራር ላይም በቀጥታ ተጠምዶ ይገኛል። የፖለቲካ ፓርቲ ቢሮክራሲው ቅጥ-ያጣ ጣልቃ-ገብነት በመንግሥት ኤንተርፕራይዞች ከዳይሬክተሮች ቦርድ ጋር እስከሚስተካከል ሚና ድረስ የተለጠጠ ነው። የፓርቲ የበላይነት መተማመንን (confidence) ያከስማል፣ እንዲሁም የመንግሥት ኃላፊዎችን እና የኤንተርፕራይዝ መሪዎችን ተነሳሽነት ይገድባል። ስለዚህም ከሁሉም የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች እና የማምረቻ ተቋማት የፓርቲ ተወካዮች ሊወገዱ ይገባል።

ድህነት የግድ የግል ውድቀት ማሳያ ላይሆን ይችላል። ዝቅተኛ ተከፋይ፣ ሥራ-አጥ፣ ወይም የአካል ጉዳት ያለባቸው ሠራተኞች ከእነርሱ ባልመነጨ ጥፋት የተረጂነት እድል ሊገጥማቸው ይችላል። እንዲህ ላለ ጊዜ ነው መንግሥት ለሠራተኞች ገቢ ድጋፍ የማድረግ ኃላፊነት ያለበት፤ ይህም እንደ ችሮታ ሳይሆን እንደ ማኅበራዊ ፍትሕ መቆጠር ያለበት። ከኢኮኖሚው ደረጃ ጋር ተመጣጣኝ የሆነ ሁል-አቀፍ የማኅበራዊ ዋስትና ሥርዓት ሊዘረጋ ይገባዋል። ኢትዮክራሲ በጠንካራ የሥራ ሥነ-ምግባር እና በኢትዮጵያዊያን የይቻላል መንፈስ ላይ መሠረት ያደረጉ የራስ-አገዝ የገጠር ማኅበረሰብ ልማት ፕሮግራሞችን ያበረታታል።

ከተቋማዊ አቅም ግንባታ ረገድና በተቋማዊ አፈፃፀም ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ ለማሳደር፣ እውቀት እና ክህሎት ለመንግሥትም ሆነ ለኤንተርፕራይዝ ከምንም በላይ ዋጋ ያለቸው እና አስተማማኝ ሀብቶች ናቸው። የአመራር ጉልብትና ለኢትዮጵያ መፃኢ ጊዜ የሚፈስ መዋዕለ-ነዋይ ይሆናል፤ እንዲህ ያለው የሥልጠና ወጪ ለኢትዮጵያ ከፍተኛውን የገንዛብ-ፋይዳ (value-for-money) ትርፍ ማረጋገጥ የሚችል ቀላል የመሠረተ-ልማት መዋዕለ-ነዋይ ፍሰት ነው። ስለዚህ የኢትዮክራሲ አዲሱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ፍልስፍና ሰብዓዊ ካፒታልን የማፍራት አቅም ያለው ሰውን ማዕከል ያደረገ ይሆናል። የማይቋረጥ ማሻሻያ ትግበራ ባህልን (continuous improvement culture) በንግድ ተቋምም ሆነ በመንግሥት ሥራ ላይ አጣጥሞ ተፈፃሚ በማድረግ፣ በኢትዮጵያ በአመራር ቦታ ላይ የሚገኙ ሰዎች ሥራን የተሻለ፣ ፈጣን እና ፋይዳዊ (better, faster, and leaner) በማድረግ ሀብትን በአግባቡ ጥቅም ላይ ማዋል ይቻላቸዋል። እውቀት የኢኮኖሚ እድገትን የሚያሽከረክር ሞተር ሲሆን፣ መንግሥት የጥገኛነት ስሜት አመለካከትን (dependency syndrome mindset) እንዲቀርፍ ያስችለዋል። ኢትዮጵያ በቅድሚያ የእውቀት ሀብቷን ሳታሳድግ እና ሳታበለፅግ ድህነትን ማስወገድ አይቻላትም። ለምሳሌ፣ የሀገራችን ሀብት የሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ መፃኢ እጣ-ፈንታው በሠራተኞቹ እውቀት እና በማሰብ ችሎታቸው ላይ እንጂ በአውሮፕላኖቹ እና በጉዞ ስምሪቱ ላይ የተመረኮዘ አይደለም።

መንግሥታዊ ማሻሻያ፧ ከኢኮኖሚው ሥራ አመራር ጋር በተያያዘ አበክሮ ሊታወቅ የሚያስፈልገው ዋናው ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት የገንዘብ ሚኒስቴር ነው። ይህ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት በብሔራዊ ኢኮኖሚው ላይ ከሚጫወተው ወሳኝ ሚና አኳያ፣ ከፍተኛ የሙያተኝነት ደረጃ ባላቸው ሰዎች የተሞላ ስለመሆኑ መንግሥት ማረጋገጥ ይገባዋል። እንዲሁም (ሀ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የመንግሥት (የአስፈፃሚው) ተፅዕኖ የሌለበትና ተጠሪነቱንም ለፓርላማው (ለሕግ አውጪው) ማድረግ፣ እና (ለ) የፋይናንስ ሥርዓቱን ነፃ (liberalize) ማድረግ ትኩረት ሊሰጣቸው የሚገባቸው ናቸው።

ኢትዮጵያ እንደሚገባት አላደገችም፣ ምክንያቱም እንደሚገባት ስላልተመራች፤ ይህም ድህነትን ከአመራር ግድፈት የመነጨ ችግር ያደርገዋል፣ ምክንያቱም የአመራር ብቃት ዋጋ አለውና። ኢትዮጵያ (አሁንም በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሕዝቦቿ እየተራቡ የሚገኙባት) የኢኮኖሚ ስንኩል (economic basket case) ሀገር የሆነችው በሕዝቦቿ ድክመት ሳይሆን በመሪዎቿ ውድቀት ነው። ኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት የሕዝቦቿን ታልቅነት የሚመጥኑ መሪዎች ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድን እንደ ሀገራዊ መንፈስ አነቃቂና ተስፋ-ሰጪ የኢትዮጵያ መሪ ተቀብዬአቸዋለሁ። አሁን ኢትዮጵያ ከምትገኝበት ወቅታዊ ሁኔታ (Current State) በሽግግር ሂደት አማካኝነት (Transition State) ኢትዮጵያ መድረስ ወዳለባት ወደሚፈለገው መፃኢ ሁኔታ (Desired Future State) የሚደረገውን የለውጥ ሂደት መስመር ማስያዝ እና ማፋጠን የሚችሉ መሪ እንደሆኑ ይሰማኛል። የህወሓት/ኢሕአዴግ ፍፁም አምባገነንነት ተቀባይነት የለውም፤ ምክንያቱም አገዛዙ የጋራ ጠላቶቻችን የሆኑት አምባገነንነት ፣ድህነት፣ በሽታ፣ ሙስና፣ እንዲሁም የውስጥ መፈናቀል ክትትል ማዕከል (Internal Displacement Monitoring Centre) እንዳስቀመጠው በ2011ዓ.ም. ለ1.4 ሚሊዮን ዜጎች በሀገር ውስጥ መፈናቀል ምክንያት የሆነው የጐሣ ግጭት መገለጫ ነውና። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ኢትዮጵያን ከህወሓት/ኢሕአዴግ የማፊያ ኢኮኖሚ እና የጐሣ አፓርታይድ ሥርዓት ሁሉም ዜጎች በሕግ ፊት እኩል ወደሚሆኑበትና የግለሰብ ሰብዓዊ መብቶች ሙሉ በሙሉ ወደሚከበሩበት እውነተኛ ዲሞክራሲ ለማሸጋገር ተፅዕኖ የመፍጠር አቅማቸውን (soft power) መጠቀም ይችላሉ የሚል ተስፋ አለኝ። ኤኤንሲ(African National Congress) ጉዳዩን ነጮች ላይ ሳይሆን ‘አፓርታይድ’ ላይ በማነጣጠር ለሁሉም ደቡብ አፍሪካውያን መብት ባደረገው ትግል ስኬታማ ሆኗል። እኛም የጐሣ አፓርታይድን ለመፈረካከስ ተመሳሳዩን እርምጃ መውሰድ እና ለሁሉም የኢትዮጵያ ዜጎች እኩልነትን የሚሰጥ ዜጋ-ተኮር ስርዓትን ማወጅ፣ በአሳብ ብቻ መወዳደር እንጅ በጐሣ ማንነት ላይ ተመርኩዞ የፖለቲካ ፓርቲዎች መቋቋምን መከልከል ይጠበቅብናል።

“ሁሉም ለአንድ ኢትዮጵያ፣ አንድ ኢትዮጵያ ለሁሉም” በሚለው መንፈስ ተነሳስተው ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ የሽግግር ሂደቱን የሚያስተናብሩበት ትክክለኛ መንገድ በቀዳሚነት ትልቁ እና ደፋሩ እርምጃ ‘የብሔራዊ አንድነት የሽግግር መንግሥት’ ማቋቋም ሊሆን ይገባል። ይህ ካልሆነ ግን የራሳቸውን የ‘መደመር’ መርሆ ተከትለው በአሳታፊ ዴሞክራሲ የኢትዮጵያን ዜጎች ተዋናይ በማድረግ ድልድያችን ሆነው መገኘት ነው። ከዚህ አኳያም (ከሚቀጥለው ምርጫ አስቀድሞ) አሁን በሚገኘው ሕገ-መንግሥት ላይ ከ4 እስከ 5 ወራት በሚደርስ ጊዜ ውስጥ ውይይት ለማድረግና በዜጎች ሕዝበ-ውሳኔ በሌላ ለመተካት ወይም ለማሻሻል የሚሰባሰቡ ከየወረዳው በአብላጫ ድምፅ የተመረጡ ተወካዮችን አስፈላጊው እውቀት ያላቸውን ባለሙያዎች የሚያካትት የብሔራዊ ሕገ-መንግሥት ጉባኤ (National Constitutional Convention) ማዘጋጀት አለባቸው። ጥናታቸውን ለማፋጠን እና ለመነሻነት ዓላማ፣ ቡድኑ ሁሉም የዓለም ሕገ-መንግሥቶች ታትመው የሚገኙበትን ይህንን ድረ-ገጽ ሊጠቀሙ ይችላሉ፡-https://www.constituteproject.org/

በነገራችን ላይ፣ ስለ አዲስ ወይም ስለሚሻሻል ሕገ-መንግሥት ከተነሳ አይቀር፣ “Constitution” ለሚለው ቃል የተሰጠው “ሕገ-መንግሥት” ከሚለው አማርኛ ቃል ጋር ቅራኔ አለኝ፤ ምክንያቱም “የዘውድ ሕገ-መንግሥት”፣ “የደርግ ሕገ-መንግሥት”፣ እና “የኢሕአዴግ ሕገ-መንግሥት” የሚል መጠሪያ ያስታውሰኛልና። “ርዕሰ-ብሔር” እና “ርዕሰ-መስተዳድር” እንደምንለው ሁሉ ለኢትዮጵያ “Constitution”ንም የመንግሥት ሳይሆን የሀገሪቱ ላዕላይ ሕግ እንደመሆኑ“የኢትዮጵያ ርዕሰ-ሕግ” ተብሎ ቢጠራ ይሻል ይመስለኛል። ኢሕአዴግ ሕገ-መንግሥቱን የራሱ የድርጅታዊ ሰነድ ያደረገ፣ ጐሣ-ተኮር መንግሥት የደነገገ ከፋፋይ አምባገነን ነው። ስለመሆኑ ትግላችን ግን ኢትዮዽያዊነትን አስቀድሞ የግለሰብ ዜግነትን ያቀፈ፣ከሥዩመ-እግዚአብሔር ወደ ሥዩመ-ፓርቲ የተሸጋገረውን አሁን ወደ ሥዩመ-ሕዝብ ለማሳደግ፣ከሕዝብ ለሕዝብና በሕዝብ ድምፅ የተመረጠና በሕግ የበላይነት የሚዳኝ ሕገ-ሕዝብ አስተዳደር ለመፍጠር ነው። መንግሥት እና አገርን አንድ አድርጎ የማየት ልማድም ማብቃት አለበት። ሀገር ሉዓላዊነቱን በመንግሥት አማካኝነት የሚያስተገብር ሉዓላዊነት ያለው አካል ነው። ሀገር ኑዋሪ ሲሆን መንግሥት ግን ጊዜያዊ ነው።

ከመንግሥት (ወይም ከሲቪል ማኅበር) አስቀድሞ የተፈጥሮ ሕግ ነበር። ሁሉም ሰው ከመነሻው ራስ-ተኮር በመሆኑም እራሳችንን አንዳችን ከሌላችን ለመጠበቅ መንግሥታትን መሠረትን። ሰዎች እራስን የማቆየት ወይም የማኖር (ተፈጥሯዊ) መብታቸውን ተፈፃሚ ለማድረግ መንግሥታት ላይ ያምፃሉ። ሕግ ሰብዓዊ ተፈጥሮን ያከበረ ሊሆን ይገባል። ስለዚህም የሕግ መነሻ ወይም ምንጭ ሰዎች መሆን ይኖርባቸዋል። ዜጎች ኢ-ፍትሃዊ የሆነን መንግሥት የማውረድ መብት ብቻ ሳይሆን ግዴታም ሊኖርባቸው ይገባል። ቶማስ አክዌነስ እንዳለው፣ “አምባገነናዊ መንግሥትን መቃወም ለፈጣሪ ሕግጋቶች መገዛት ነው።”

በሟቹ በመለስ ዜናዊ ሲቀለድበትና ሲወገዝ የቆየው የኢትዮጵያ ዳያስፖራ፣ አሁን ተሰውሮ እንደቆየ ሐብት (hidden treasure) ተቆጥሮ በሀገር-ግንባታ ሂደቱ እንዲሳተፍ በጋበዙን በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ ተቀባይነት አግኝቷል። በነገራችን ላይ፣ ለሁለቱም ለመንግሥት እና ለኢትዮጵያ ዳያስፖራ የጋራ ጥቅም ሲባል፣ ብሎም የጠቅላይ ሚኒስትር አብይን ድልድይ የመገንባት ጥረት ለማጠናከር፣ የጥምር ዜግነት (dual citizenship) ሕግ የማውጣቱ ሥራ ጉልህ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል። ራዕይ ለማመላከት፣ወደ አሜሪካ በስደት የመጡት እና ትውልደ-አሜሪካ-ቻይናውያን ለየራሳቸው ሀገራት ያሳኩትን ኢትዮጵያም እንዲሁ እንድታሳካ ለዲያስፖራ ኢትዮዽያውያንም ትክክለኛውን ዓይነት ምቹ ሁኔታ በመፍጠር የሰብዓዊ ካፒታልን ፋይዳ ሊጨምር የሚችል ሰውን ማዕከል ያደረገና እውቀት-መር የሆነ መርህ የኢትዮክራሲን ራዕይ ያንጸባርቃል።

ኢትዮጵያ የመደብ ፖለቲካን በደርግ ዘመን፣ እንዲሁም የጐሣ ፖለቲካን በህወሓት/ኢሕአዴግ ዘመን ሞክራለች። አሁን ደግሞ ጊዜው ከፓርቲ በፊት የሀገር ፍቅርን የምናስቀድምበት የብሔራዊ ፖለቲካ ጊዜ ነው። የፖለቲካ ፓርቲዎችም ቢሆኑ ፓርቲያቸውን በተሻለ የሚያገለግሉት በቅድሚያ ሀገራቸውን ሲያገለግሉ ነው። የፖለቲካ ፓርቲዎች እና የሲቪል ማኅበራት፣ እንዲሁም ሀገር-ወዳድ ግለሰቦች ለ“ዛሬ ትብብር፣ ነገ ውድድር” ዝማሬ ሙሉ ምላሽ ይሰጡ ዘንድ ከክፍፍል ፖለቲካ (factional politics) መፋታት ይኖርባቸዋል። ቅድሚያ ኢትዮጵያን ከውስጥ እና ከውጭ ጠላቶችዋ ለመታደግ የመተባበሪያ ጊዜው አሁን ነው። ስለሆነም፣ ለቀጣዩ ነፃ እና ፍትሐዊ ምርጫ በሚደረገው ዝግጅት ተፎካካሪ/ተወዳዳሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች አሸናፊ በሚሆኑበት ትብብር ላይ በመሳተፍና አስተማማኝ እና ኗሪ የህወሓት/ኢሕአዴግ ምትክ አማራጭን ለዜጎች የሚያቀርብ የፓርቲ መርሃ-ግብር ወይም ማኒፌስቶ በማዘጋጀት በትክክለኛው የታሪክ መስመር ላይ እንዲቆሙና ለውጥ እንዲያመጡ ጥሪዬን አቀርባለሁ።

ህወሓት/ኢሕአዴግ ጐሣን መሠረት ባደረገ የጥላቻ ፖለቲካ ይመራል። እኛን የሚመራን ኃይላችን ለሀገራችን ያለን ፍቅር ነው። ፍቅር በጥላቻ ላይ ይነግሣል። ኢትዮክራሲ መርዛማውን የጐሣ-መር ትርክት አይታገስም። መላው ኢትዮጵያዊያን ኃላፊነት በጎደላቸው፣ ቅቡልነት በሌላቸውና ብቃት በተሳናቸው መሪዎች ስር ሲሰቃይ ቆይቷል። ኢትዮክራሲ በአዲስ ዜጋ-ተኮር ርዕሰ-ሕግ (constitution) እና በላቁ የነፃነት (liberty)፣ የእኩልነት (equality)፣ እና የወንድማማችነት (fraternity) ልዕለ-ሀሳቦች ጥላ ስር አዲሲቷን ኢትዮጵያ ለመገንባት አርቆ ይመለከታል።

ከ123 ዓመታት በፊት በአድዋ ጦርነት፣ ከሁሉም የጐሦች ቡድኖች እና ከሁሉም ሃይማኖቶች የተውጣጡ ሐገር-ወዳድ ኢትዮጵያዊያን፣ ኢትዮጵያ ከክፍሎቿ ድምር በላይ የላቀች ስለመሆኗ አረጋግጠዋል። የብዙሃን-ጐሣ ብሔራዊ ሀገር በመሆናችን፣ የራሳችን የግዕዝ ፊደል ያለን፣ የአድዋ ድል እና የሰው ዘር መገኛነታችን ሁሉም ኢትዮጵያን የተለየንነት (Ethiopian Exceptionalism) ስለመወከላቸው እውቅና የተሰጠን የአኩሪ ታሪክ ባለቤቶች በመሆናችን እድለኞች ነን። ዛሬ ግን የኛ ተግዳሮት የራሳችንን ድል መቀዳጀት ነው። የኢትዮጵያ ስብጥራዊ ውበት በይበልጥ የሚመሰለው ለጋራ መልካምነት በቆመ የብዙሃን አንድነት ነው። አንድ ላይ ስንሆን ጠንካራ ነን። የማንከፋፈል ስንሆን የማንበገር እንሆናለን። ብዙ ሆነን አንድ የሚያደርገን ኢትዮጵያዊነታችን ነው። ለኢትዮጵያውያን ልዩነታችን ጌጣችን እና የፈጠራ ምንጫችን፣ አንድነታችን ኃይላችን ነው።

ለማጠቃለል፣ ኢትዮክራሲ አደገኛ ለሆኑት የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ሀገር-በቀል መፍትሔ ነው። በማያቋርጥ ድህነትና በጐሣ ፖለቲካ ካንሰር አባባሽነት ላለፉት 28 ዓመታት ስንደናቀፍ ቆይተናል። አምባሻውን እንዴት ማተለቅ እንችላለን በሚለው ላይ ከፍተኛ ትኩረት ማድረግ ሲገባን፣ የጐሠኝነት ለያዪው አስተሳሰብ ግን አምባሻውን ይከፋፍለዋል። ኢትዮጵያውነት የልዩነቶች ውኅደት የፈጠረው የወል ማንነት መገለጫ የሆነ እኛነት ነው።ኢትዮጵያ የብዙሀን-ጐሣ ሀገርነቷን ስብጥራዊ ውበት ጎን-ለጎን እያበለፀገች የጐሣ ክፍፍሎሹን (silo syndrome) በመቅረፍ የሀገራዊ አንድነት ስሜት ዳግም እንዲያንሰራራ የመጠቀ ስትራቴጂ ያስፈልጋታል።

ኢትዮክራሲ የፈጠራ ችሎታና ትግበራ የተጎዳኙበትን፣ እንዲሁም ኢትዮጵያ በ2031 ዓ.ም. ሰብዓዊ ካፒታሏን ከታሰረበት ማነቆ አልላቃ የተንሰራፋውን ርሃብ፣ በሽታና መሃይምነት ድል መንሳት የሚያስችላትን ሕዝብን ማዕከል ያደረገና በእውቀት ላይ የተመረኮዘ የኢኮኖሚ ሥርዓት (knowledge based economy) ሥራ ላይ በማዋል የዲሞክራሲ እና የልማት ፍኖተ-ካርታ አስቀምጦ ኢትዮጵያን ከጥገኝነት ስሜት አመለካከት (dependency syndrome mindset) ነፃ ያደርጋታል። ስለ እውቀት ገንቢነት ስናስብ ማንበብ እና መፃፍ የሰብዓዊ ልማት የመጀመሪያ እርምጃዎች መሆናቸውን እያስታውስን፣ የኢትዮጵያን ቋንቋዎች የበለጠ ለማበልፀግና የሁሉንም ሥነ-ጽሑፍ ለማጎልበት የግዕዝን ፊደል ለሁሉም የኢትዮጵያ ቋንቋዎች በትጋት እንድንጠቀም ሀሳብ አቀርባለሁ።

ኢትዮጵያዊያን የበሬ እርሻ እና የሣር ጎጆ ባሕልን በመለወጥ ውድ አገራቸውን ኢትዮጵያን ለማዘመን ይመኛሉ። የሥራ-አጡን ወጣት ስሜት ከከተማ መንገድ ወደ ገጠሩ ልማት ለመለወጥ፣ የሀገሪቱን ከእጅ-ወደ-አፍ አኗኗር ወደ ተደራጀ ንግድ-ተኮር እርሻ (commercial farming) ለማሸጋገር ከግብርናው ዘርፍ በመጀመር በንቃት መሣተፍና በሁል-አቀፍ የሀገር-ግንባታው ጥረትም መርካት ይጠበቅባቸዋል። ሀገሪቱን ከድህነት ውስጥ ጎትቶ ለማውጣት የሥራ-ወዳድነት ሥነ-ምግባር፣ የራስ-አገዝ ባህል፣ እንዲሁም የኅብረት ሥራ የማኅበረሰብ ልማት መርሆዎች በወጣቱ ዓዕምሮ ውስጥ ሊሰርፁ ይገባል።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ የህወሓት/ኢሕአዴግ አያሌ ስህተቶችን በማረሙ ላይ መጠመዳቸውን አያለሁ አደንቃለሁም፤ ነገር ግን አያሌ የኢትዮጵያ ማኅበረሰቦችን ላዳረሰ እጅግ የሚያስጨንቅ የሞት እና የንብረት ውድመት ጉዳይ ቸል ማለታቸውያሳስበኛል። ምክንያቱም የኢትዮጵያን መሠረታዊ ችግር ይህም ማለት በህወሓት/ኢሕአዴግ ሕገ-መንግሥት የታወጀውን አውዳሚ የጐሣ ፌዴራሊዝም (ዜናዊዝም) መፍትሔ ለመስጠት የፖለቲካ ፈቃድም ሆነ ወኔ ያጠረቸው ይመስላል።

ኢትዮጵያ አንድ ወይስ ሁለት የሕግ አውጪ ምክር ቤቶች ሊኖራት ይገባል? ወይም ለኢትዮጵያ የሚስማማው አሃዳዊ ወይስ ፌዴራላዊ ሥርዓት ይሆን? ወይም ለኢትዮጵያ የሚሻለው ፓርላሜንታዊ ወይስ ፕሬዝዴንታዊ ሥርዓት ነው የሚሉት ጉዳዮች በሁሉም የሚመለከታቸው ወገኖች ጤናማ ክርክር እና ሕዝባዊ ውይይት ከተደረገ በኋላ ህገ-መንግሥት መተካት ወይም ማሻሻል እና ከዛ በኋላ ምርጫ ማካሄድ ይቻላል።

ሁላችንንም ሊያኮራ የሚችል የመንግሥት ዓይነት ከሁለት ክፍለ-ዘመናት በፊት በቶማስ ፔይን እንዲህ ተገልፅዋል፡- “በማንኛውም አንድ የዓለም ሀገር እንደዚህ ብሎ መናገር የተቻለ እንደሆን፣ ደሃው ሕዝቤ ደስተኛ ነው፣ አላዋቂም ሆነ ሀዘንተኛ ሰው በመካከላቸው አይገኝም፤ እስር ቤቶቼም እስረኛ ጎዳናዎቼም የኔቢጤ አይታዩባቸውም፤ አረጋዊያን የሰው ፊት አያዩም፤ የሚጣለው ግብር ጨቋኝ አይደለም፤ ይህ እሳቢው ዓለም ባልንጀራዬ ነው፣ ምክንያቱም ደስታው ደስታዬ ነውና። እነዚህ ነገሮች መነገር ከቻሉ፣ እነሆ ያ ሀገር በሕገ-መንግሥቱ እና በመንግሥቱ ሊኮራ ይችላል።”

ኢትዮጵያን ከኢሕአዴግ የአምባገነን አገዛዝ ነፃ ለማውጣት ኢትዮዽያውያን በሀገርቤት በገፍ ሲታሰሩና ብዙዎች ደግሞ በፖለቲካ ትግሉ ህይወታቸውን መስዋዕት ሲከፍሉ ቆይተዋል። በበኩሌ ኢትዮዽያን ከኤስኖክራሲ (ሥልጣን ለጐሠኞች) ወደ ኢትዮክራሲ (ሥልጣን ለኢትዮዽያ ሕዝብ) የሚያሸጋግር መፍትሄ ሀሳብ አቅርቤአለሁ። ለረዥም ጊዜ ሙሉ ለሙሉ ከሽፎ በሥልጣን የቆየ መንግሥት አንድም የለም። ኢትዮጵያ ነፃ ትወጣለች፤ አምባገነንነትም በዲሞክራሲ ይተካል፤ ምክንያቱም እንደ የአፍሪካውያን አባባል “ዝናብን ማንም ሊያቆመው አይችልም!”

አቶ አባተ ካሣ Value Analysis and Engineering Reengineered” እና “የፋይዳ ትንታኔ እና ህንደሳ” መፅሐፎች ደራሲ ነው።

ኢትዮክራሲ ላይ የሚኖራችሁን ምልከታ በደስታ ለመቀበል ዝግጁ ነኝ። አመሰግናለሁ።kassa.abate@gmail.com

በአማራ ሕዝብ ላይ የተከፈተው ዘመቻ በአስቸኳይ ይቁም!!! (ሻለቃ ዳዊት ወልደጊዮርጊስ)

ዳዊት ወልደ ጊዮርጊስ

ኢትዮጵያ ታፍራና ተከብራ በነጻነት እንዳበራች ዛሬ ላይ እንድትደርስ የአማራው ሕዝብ መስፈሪያ የለሽ ዋጋ መክፈሉ ታሪክ ምስክር ነው:: ሃገራችን ተስፋፊና ወራሪ ሃይሎችን መክታ ሉዐላዊነቷ አስጠብቃ እንድትኖር የመላው ዜጎቿ ተጋድሎ ውጤት ቢሆንም አማራው ግንባር ቀደም በመሆኑ ለውጪና ለውስጥ ጠላቶች ኢላማ እንዲሆን አድርጎታል:: በዚህም ባለፉት 50 አመታት ግልጽ ጥቃት ተከፍቶበት ብዙ መከራን ሊያስተናግድ ተገዶ ቆይቷል::

በተለይ ባለፉት 28 አመታት አማራው በግልጽ ማንነቱን መሰረት ያደረገ የጥቃት ዘመቻ ተከፍቶበት ዋጋ ሲከፍል ቢቆይም ከኢትዮጵያዊ ማንነቱ ወርዶ በብሄር ላለመደራጀት በትግዕስት ለመቆየት ሞክሯል:: የመከራው መርግ መክበድ የግፍ መበራከትና የስቃዩ ብዛት ሳይወድ በግድ በብሄር ማንነቱ ተሰባስቦ እንዲመክት ተገዷል::

ሕወሃት ኦነግና ግብረአበሮቻቸው አማራውን ገለን ቀብረነዋል :: አከርካሪው ተሰብሮ እንዳይነሳ አርገን ጥለንዋል:: ቢሉም በማንነቱ መሰባሰብ በጀመረ ማግስት ያሳየው መነሳሳት ጠላቶቹን ከፍተኛ ድንጋጤ ላይ ጥሏቸዋል:: የአማራው መነቃቃትና መደራጀት ለአማራው ብቻ ሳይሆን ጥላቻና የግንጠላ አጀንዳ ያላቸውን የጽንፈኛ ሃይሎችን ሕልም አምክኖ ለመላው ኢትዮጵያዉያን ብሄሮች ሕልውና ጭምር ተስፉ በመሆኑ አደረጃጀቱ እንዲመክን አንድነቱ እንዲበተን በግልጽና በስውር ሰፊ ዘመቻ ተከፍቶበት ቆይቷል::

ይህንንም ተቋቁሞ እራሱን ከማንኛውም ጥቃት ለመከላከል የሚያደርገውን ዝግጅት ለመቀልበስ በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በተቀናበረ ሴራና የፖለቲካ አሻጥር መፈንቅለ መንግስት በሚል ሰበብ በአንድ ቡድን የበላይነት በሚመራ የፌዴራል ጣልቃ ገብ ወታደራዊ ወረራ ስር እንዲውል ተደርጏል:: ይህንን በዓለም ታሪክ ተሠምቶ የማያውቅና ፍጹም ግልጽነት የጎደለው ድርጊት በጽኑ እናወግዛለን:: ለሃገር የማይበጅና ሁሉንም ወገን ዋጋ የሚያስከፍልና መሪውን የሚያስጠይቅ እርምጃ ባስቸኳይ እንዲቆም የሕዝቡን መብትና ነጻነት እንዲያከብሩ በጥብቅ እናሳስባለን::

ጠቅላይ ሚንስትሩ ድርጅታቸውና የፌዴራል ካቢኔያቸው ሃገር ሊያፈርስ ሕዝብን ለአመጽ ከሚጋብዝ ድርጊት ተቆጥበው ዘለቄታዊ አብሮነታችን እንዲቀጥልና ሰላማችን እንዲከበር ግልጽና አፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጡ እንጠይቃለን:: የአማራው ሕዝብ የጀመረውን መብቱን የማስጠበቅና ሕልውናውን የመከላከል ትግል ሳይከፋፈል አንድነቱን አጥብቆና አጠንክሮ እንዲቀጥል ወገናዊ ጥሪያችንን እናቀርባለን::

እንዲሁም :-
1, መፈንቅለ መንግስት በሚል ተራ የቅጥፈት ፖለቲካ ሃገሪቷ ብሄራዊ አደጋ ላይ የወደቀች አስመስሎ በዶር አብይና በመንግስታቸው የቀረበው ዘገባና ፍረጃ አስቸኳይ የሆነ ማብራሪይ እንዲሰጥበት::

2, ከአማራ ክልል ፍቃድና እውቅና ውጪ በጠቅላይ ሚንስትሩ አዝማችንት በፌዴራል ወታደሮች የተደረገው ጣልቃ ገብነት ሕጋዊ አግባብነት የሌለው በመሆኑ ውሳኔውን የሰጠው አካል እንዲጠየቅ የፈጸሙትም ድርጊት በነጻና ገለልተኛ አካል እንዲጣራ

3, በአንድ ቡድንና ብሄር የበላይነት የሚመራው ወታደራዊ ካውንስል የሚወስዳቸው እርምጃዎች ተቀባይነት የሌለው በመሆኑ ባስቸኳይ ከአማራ ክልል ለቆ እንዲወጣ ጸጥታ የማስከበሩን ሃላፊነት ለክልሉ ፀጥታ ሃይል እንዲያስረክብ

4, ከሕግ አግባብና ግልጽ ባልሆነ ምክንያት የታሰሩ የክልሉ አመራሮችና የአማራ ወጣቶች በአስቸኳይ እንዲፈታ ጥፉት አደረሱ የተባሉም ካሉ በግልጽ እንዲዳኙ እንዲደረግ

5, ምንም ባልተጣራ ምክንያት በፌዴራል መንግስት በአማራ ሕዝብና መሪዎች ላይ የተወሰደው እርምጃ : በሃገሪቱ የኢታማጆር ሹምና በጡረተኛው ጀነራል ላይ ምንነቱ ያልታወቀው ግድያ ገለልተኛና እለም ዓቀፍ አጣሪ ኮሚሽን ተቋቁሞ ሂደቱ እንዲጣራ

6, ከሕግ አግባብ ውጪ የአማራውን ሕዝብ ትጥቅ የማስፈታት እንቅስቃሴ በአስቸኳይ እንዲቆም: ሰላም ለማስፈን በሚል ሰበብ በሕዝቡ ላይ የሚደረገው ግድያ በአስቸኳይ እንዲቆም እንጠይቃለን::

7, ኢሳት የተባለው ሚድያ ሕዝባዊ ወገንተኛነቱን ትቶ ለገዥዎች ልሳን በመሆን ያልተጣራ ዘገባና ውንጀላን በስፋት በማናፈስ እውነትን ለማድበስበስ ከሚያደርገው እርካሽ ተግባር እንዲቆጠብ ሕዝባችንም የሚዲያ ተቋሙን ቅጥረኛ ተግባር ተረድቶ እንዳይታለል በጥብቅ እናሳስባለን!

ድል ለሕዝባችን!

የአማራ ብሄረተኝነት ትልቅ ስጋት ነው፣ ግን መፍትሄው እነ ዶ/ር አብይ እጅ ውስጥ ነው ያለው #ግርማካሳ

አንዳንድ ሰዎች የአማራ ብሄረተኝነት በጣም አደገኛ ደረጃ ደርሷል ይላሉ። ከነዚህ ሰዎች መካከል ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ይገኙበታል። አንድ ወቅት በሰጡት አስተያየት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፣ “የአማራ ናሽናሊዝም ወደ ሚያስፈራ ደራጃ እያደገ ነው” ብለው ነበር የተናገሩት።

የአማራ ብሄረተኝነት ስጋት ነው ተብሎ ከታሰበ፣ በቀዳሚነት ይሄ ከጥቂት አመታት በፊት ያልነበረ ብሄረተኝነት እንዴት በአጭር ጊዜ   ውስጥ አሁን የደረሰበት ደረጃ መድረስ ቻለ ብለን መመርመር ያለብን መሰለኝ።  መፍትሄ ወደምንለው ከመሄዳችን በፊት የችግሩን ምንጭ መረዳት አስፈላጊ ነው።

የአማራ ብሄረተኝነትን የተወለደው አማራ-ጠል በሆኑ የትግራይና የኦሮሞ ብሄረተኝነት ነው። ስልጣን ላይ የነበሩና አሁንም ያሉ የኦሮሞ(ኦነግ/ኦህዴድ) እና የትግራይ (ሕወሃት) ብሄረተኛ ፖለቲከኞች፣  አሁን ሕግ መንግህስት የሚባለውን ሲያረቁ፣ በዘር ላይ እንዲያተኩር ነው ያደረጉት። ክልል የሚሏቸው የፌዴራል መስተዳድሮች የተዘረጉት በዘር ነው። ከአማራ ክልል ውጭና በአማራ ክልል ውስጥም የኦሮሞ ዞን(ከሚሴ) ውስጥ ፣ አማራዎች እንደ ሁለተኛ ዜጋ እየተቆጠሩ  ከፍተኛ በደልና ግፍ ላለፉት ሃያ ሰምንስት አመታት ሲፈጸምባቸው ነበር። አማራው ኢትዮጵያዊነቴ ይበቃኛል ብሎ ሲቆም፣ ነፍጠኛ፣ ትምክህተኛ ተብሎ ተጠቃ። ተፈናቀለ፣ ተገደለ።

አማራ ተብሎ፣ ተነጥሎ፣ በስርዓቱና በመንግስታዊ አሰራሩ፣ በደልና ግፍ እየደረሰበት ስለሆነም፣ ለሕልውናው ሲል፣ በአማራ ስም መደረጃት ተፈለገ። የአማራ ብሄረተኘነትም አቆጥቁጦ በእግሩ መሄድ ጀመረ።

በዶ/ር አብይ አህመድ የሚመራው የኦዴፓ አገዛዝ፣ ከሰኔ 15ቱ የባህር ዳርና የአዲስ አበባ የባለስልጣናትን መሞትን ተከትሎ፣  “መፈንቀለ መንግስት” ብለው የጠሩትን፣ የራሳቸው የኢሕአዴጎች የርስ በርስ ሽኩቻንና መገዳደልን፣ እንደ ሰበብና መልካም አጋጣሚ በመጠቀም፣ ከነርሱ የተለየ የፖለቲካ አመለካከት ያላቸው የሚባሉትን፣  በዋናነት የባላአደራው ምክር ቤትና የአብን  አባላትንና፣ በኢሕአዴግ/አዴፓ ውስጥ ያሉ ለኦዴፓ ማጎብደድ የለብንም የሚሉ ጠንካራ አመራሮችና አባላትንም  በገፍና በጅምላ፣  “ሽብርተኛ” እያሉ እያሰሩ ነው።

እነ ዶ/ር አብይ አህመድማ የኦዴፓ ጓዶቻችው፣  ምን አልባት ይሄንን መስመር የለቀቀ፣ ህወሃት ሲያደርገው የነበረውን አይነት የጡንቻ እርምጃ በመዉሰዳቸው፣ “የአማራ  ብሄረተኝነት እናጠፋለን” ብለው አስበው  ከሆነ በጣም ፣ እጅግ በጣም ተሳስተዋል። እንደው የበለጠ አስር እጥፍ የአማራ ብሄረተኝነት ጥንካሬ እንዲጨምር ነው የሚያደርጉት።

የአማራ ብሄረተኝነትን እድገት ለማቆም ብሎም በሂደት ተዳክሞ  እንዲከስም ማድረግ አስፈላጊ ነው። ያንን ለማድረግ፣የአማራ ብሄረተኝነት እንዲያድግ ingredient የሆነውን ነገር ማራቅና ማስወገድ ያስፈልጋል። በዋናነት የአገሪቷን የፖለቲከ ጨዋታ ህግ መቀየር ያስፍፈልጋል። ጨዋታውን ከጎሳ ፖለቲካ ጨዋታ ማውጣት ያስፈለጋል። ያን ማድረግ ካልተቻለ፣ በጉራጌኛ ዘፈን ትግሪኛ ጨፍሩ፣ ወይም በቅርጫት ኳስ ጨዋታ፣ እግር ኳስ ይመስል፣  አስራ አንድ ተጨዋች አሰልፉ እንደማለት ነው።

  1. የኦሮሞ ፣ የትግሬ፣ የአማራ ..ባህል ማእከላት፣ የተለያዩ የብሄረሰቦች ቅርስና ቋንቋ የሚያሳድቁ የሲቪክ ማህበራትና ተቋማት ሊኖሩ ይችላሉ። ዜጎች አማራ ነን፣ ጉራጌ ነን …ብለው በግለሰብ ደረጃ መናገር፣ መጻፍ ይችላሉ። ነገር ግን በዘርና በጎሳ ላይ የተመሰረቱ የፖለቲካ ድርጅቶች መታገድ አለባቸው።
  2. ኢትዮጵያዊነትን ያላማከለ ዘረኛ ሕግ መንግስትን መቀየር ወይንም በእጅጉ ማሻሻል፣ በተለይም የኢትዮጵያ ባለቤት ብሄር ብሄረሰብና ህዝብ የሚለው ሳይሆን የኢትዮጵያ ሕዝብ ወይን ዜጎች እንዲሆኑ ማድረግ አስፈላጊ ነው።
  3. የጎሳ አወቃቀርን አስወግዶ፣ ምን አልባት የሶማሌ ክልል ርእስ መስተዳደር አቶ ሙስጠፋ እንዳሉት ሰሜን፣ ደቡብ፣ ምስራቅ፣ ምእራብና መሐል ኢትዮጵያ የሚሉ ፣ ወይም ሌላ ግን ዘር ላይ ያላተኮረ፣ የፌዴራል መስተዳድሮችን መዘርጋት አስፈላጊ ነው። አንድም ቦታ፣ አንድም ቀበሌ የአንድ ወይንም የተወሰኑ ጎሳዎች መሬት ተደርጎ መቆጠር የለበትም። ሁሉም የአገሪቷ ግዛት የሁሉም ኢትዮጵያዉያን መሆኑን መረጋገጥ አለበት።  አንድ ኦሮሞ ከጨለንቆ ወይም አንድ ትግሬ ከሸምበቆ አዲስ አበባ  ወይም ጎንደር ቢመጡ፣ በአዲስ አበባና ጎንደር ከተማ ሕግ መሰረት ለተወሰኑ ወራት ከኖሩ በኋላ እዚያ ከተወለዱት ነዋሪዎች እኩል መብታቸው ተከብሮ ካስፈለገም ተወዳድረው፣ ህዝብ ከመረጣቸው ከንቲባ የመሆን መብታቸው መረጋገጥ አለበት። የየደብረ ማርቆስ  ወይም የወላይታ ሶዶ ተወላጆች፣  ነቀምቴ ወይም ደሴ አስተዳዳሪ መሆን መቻል አለባቸው።

አንድ ወቅት ከሞሬሽ፣ በቅርቡ ደግሞ ከአብን አመራሮች ጋር ተነጋግሬ ነበር። ሁለቱም የአማራ ድርጅቶች ከላይ የተጠቀሱት ሃሳቦችን በእጅጉ እንደሚጋሩ ነው ለመረዳት የቻልኩት። ራሳቸውን አክስመው አገር አቀፍ ለመሆን ዝግጁ ናቸው ።

የአማራ ማህበረሰብ መጀመሪያዉኑ አማራ ብሎ የተነሳው ስለተጠቃ ፣ ለሕልውና ብሎ እንጂ ፈልጎ አልነበረም። ውስጡ፣ አጥንቱና ደሙ ኢትዮጵያዊነት ነው። ሁሉም ኢትዮጵያን ካለ፣ በሁሉም ቦታ እንደ ኢትዮጵያዊ መኖር፣ መስራት ከተቻለ፣ መቀሌና ነቀምቴ እንደ ደብረ ማርቆስና ደሴ ከሆኑለት እልልልል ይላል እንጂ በጭራሽ አይከፋውም።

የኢትዮጵያ ጠላት ሄርማን ኮሆን፣ “አማራዎች ስልጣን አጣን፣  የበላይ መሆን አለብን ብለው ፣ የድሮዉን ስርዓት ለመመለስ ነው የሚፈልጉት”  አለ። የዉሸትና የጥላቻ ፕሮፖጋንዳ !!!!ምን አልባት ይህን አይነት አስተያየት ሀርማን ኮሆን የሚናገረው የኦሮሞ ጽንፈኛ ብሄረተኞች ከሚናገሩትና ከሚጽፉት ተነስቶም ሊሆን ይችላል።

ህዝቡ ዘረኛ አይደለም። እኔ ብቻ ልጠቀም፣ እኔ ብቻ ልዩ ጥቅም ላግኝ አላለም። ምነው ኦሮሞዎቹን እነ ዶ/ር አብይን ቀድሞ ሆ ብሎ የደገፈው ማህበረሰብ የአማራው ማህበረሰብ አይደለምን ? ሕዝቡ የሚፈልገው እኩልነት ነው።

ከላይ የተጠቀሱ ነጥቦች ተግባራዊ በማድረግ፣ ሃይልና ጡንቻ ሳያስፈልግ የአማራ ብሄረተኝነትን ራሱ አማራው ጆንያ ውስጥ ያስገባዋል፤ ወደ ጎን ያደርገዋል።

ነገር ግን ጽንፈኛ ኦሮሞዎች አገርን እያመሱ፣ እነ ኦነግና መሰሎቻቸው ሚሊሺያ እያደራጁ፣ የኬኛ ፖለቲካ አየሩን ተቆጣጥሮ፣ በኦሮሞ ክልል ኦሮሞ ያልሆኑ በግፍ መጤ እየተባሉ እየተፈናቀሉ፣ የኦሮሞ ብሄረተኝነት በተለይም አማራ ጠል የኦሮሞ ብሄረተኝነት ከቁጥጥር ውጭ እየሆነ፣ እኛ ልዩ ተጠቃሚ መሆን አለብን በሚል፣ ኦሮሞው ከሌላው እኩል ሆኖ የሚኖርበት ሳይሆን ኦሮሞ የበላይ እንዲሆን እየተፈለገ፣ ተራው የኛ ነው ባዮች ስልጣኑን ጨብጠውና ዜጎች በጅምላ እየታሰሩ ባለበት ሁኔታ፣ አማራውን በአማራነት አትደራጅ ማለት ግብዝነት ካልሆነ ምን ሊባል ይችላል ?

እንደውም ትግሬ በዘሩ፣ ኦሮሞ በዘሩ ሲደራጅ ዝም ተብሎ፣ ከነርሱም ጋር እየተሰራ፣ አማራው ለምን ተደራጀ ማለት ፣ የዘር-ፖለቲካን መቃወምና መጥላትን ሳይሆን፣ አማራውን መጥላት ተደርጎ ነው ሊታይ የሚገባው።

በኢትዮጵያ ውስጥ በተለይም በአማራው ክልልና በአዲስ አበባ ወጣቶችን እያፈኑ ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ በእስር ቤት ማጎር በአስችካይ እንዲቆም ለኢትዮጵያ መንግስት የተላለፈ ጥሪ

ዓለም አቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያውያን መብት
Global Alliance for the Rights of Ethiopians (GARE)

Global Alliance for the Rights of Ethiopians (GARE).

Global Alliance for the Rights of Ethiopians (GARE)

ግሎባል አልያንስ ከተቋቋመበት ግዜ ጀምሮ ለአለም አቀፍ መርሆወችና ለስብአዊ መብቶች መከበር በኢትዮጵያም ውስጥ ይሁን በወጪ አገራት ኢትዮጵያኖች በሚደርስባቸው የስብዓዊ መብት ጥስት በግንባር ቀደምትነት ስብአዊ መብታቸው እንዲከበር ለዓለም አቀፍ የስብአዊ መብት ተቋማትና ለኢትዮጵያ መንግስት ያለምንም ቅደመ ሁኔታ የዜጎቻችን መብት እንዲከበር የራሱን አስተዋጽኦ ሲያደርግ መቆየቱ የሚታወስ ነው። በተለይም ላለፍት 27 ዓመታት በኢትዮጵያ ውስጥ ጋዜጠኞችና የመብት ተማጋቾች በነጻነት ሃሳባቸውን ስለገለጹ ብቻ ያለምንም የፍርድ ቤት ትእዛዝ ሲታስሩ፤ ሲገረፉ፤ ሲገደሉ እና ሲስቃዩ ያሳለፉት ዘመናት ገና ሳይረሳ በተለይም በአሁኑ ስአት በሃገራችን በኢትዮጵያ ውስጥ ለውጥ መጥቷል በሚባልበት ግዜ እና ሃገሪቱን የሚመሩት ጠቅላይ ሚንስትር በኢትዮጵያ ውስጥ ማንም ይሁን ማን አስቀድሞ ማጣራት ሳይደረግና የፍርድ ቤት ትእዛዝ ሳይወጣ አንድም ስው እንዲታስር አንፍቅደም በማለታችው ምክንያት ከአለም አቀፍ ተቋማት አምንስቴ ኢንተርናሽናልና የመሳስሉት ድርጅቶች ሳይቀር እውቅና በተስጣቸው አንድ ወር በማይሞላ ጊዜ ውስጥ ምክንያቱ ባልታወቀ ሁኔታ፤ በተለይ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ያለፍርድ ቤት ትእዛዝ ከሁለት መቶ ሰባ በላይ የሚሆኑ የአዲስ አበባና የሊሎች ነዋሪዎች ታፍነው ወደ እስር ቤት ተወርውረዋል። እየተገረፉ ነው። በሽብርተኛነት እየተከሰሱ ነው። ይህ የህወሓት መራሹን አፋኝና ጨቃኝ መንግስት ስራ የሚያስታውሰንና የሚመስል አድራጎት በአገሪቷ ውስጥ መጥቷል የሚባለውን ለውጥ ተስፋ ስጪ መሆኑ ቀርቶ ኢትዮጵያዊያኖች መጪውን ግዜ በጭንቀትና በፍርሃት እንዲመለከቱት ከማድረጉም ባሻገር ያለፈው የመከራና የአፈና ዘመን መልሶ መምጣቱን ከወዲሁ አመላካች እንደሆነ ያሳያል። በአሁኑ ወቅት በሀገራችን እየታየው ያለው የብሄር ልዩነቶች ከጊዜ ወደጊዜ መጠኑ ስር እየስደደ በመሄዱ መንግስት ለዚህ ትኩረት መስጠት እንዳለበት ለመለፅ እንወዳለን:። በተለይ በዐማራውና ኦሮሞ ባልሆነው ሕዝብ ላይ በቡራዩ፤ በሰሜን ሸዋ፤ በቤኒ ሻንጉል ጉሙዝ፤ በልዩ ልዩ የኦሮሞ ክልል ስፍራዎች ላይን እጅግ የሚዘገንን ብሄር ተኮር እልቂትና አፈና እየተክሄደ ነው።

ይህ አድራጎት ጠቅላይ ሚንስትር ዓቢይ ገና ወደ ስልጣን እንደመጡ ምክንያቱ ባልታወቀ ሁኔታ ከአንድ ሺህ በላይ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች በተለይም ወጣቶች ታፍነው ከተያዙ በኋላ ወደ ጠቅላይ የጦር ማስልጠኛ ካምፕና ወደ ስንዳፋ የጦር ካምፕ ተወስደው ከፍተኛ ድብደባና የስብአዊ መብት ጥስት ከተፈጸመባቸው በኋላ በግድ አጥፈተናል እንዲሉ ከተደረጉ ከወር በኋላ ወደ የቤተስቦቻችው መመለሳቸው የቅርብ ግዜ ትዝታችን ነው። አሁንም ቁጥራቸው የማይታወቅ ወጣቶች ወደ ሰንዳፋ ተወስደው እርህራሄ የጎደለው ግርፋትና እንግልት እየተፈጸመባቸው ነው። የኢትዮጵያ መንግሥት ኢንተርኔት እንዳይተላለፍ ስለከለከለ ሃቁን ለመከታተል አልተቻለም። የኢንተርኔት መገናኛ መቋረጥ ዋናው ዓላማ ለአፈናው አመች እንዲሆን ነው።

ስለዚህ በአሁኑ ስአት በማንኛውም ስልጣን ደረጃ ላይ ያሉ የመንግስት ባለስልጣናት የፍትህ አካላት እና የፓሊስ ሃይል ልብ ሊሉት የሚገባው ያለምንም የፍርድ ቤት ትእዛዝና የወንጀል ድርጊት ማስረጃ ሳይቀርብባቸው ዜጎችን በድንገት አፍኖ እስር ቤት ማጎር አለም አቀፍ ህግጋትን የጣስና የግለሰብን ስብአዊ መብት በእጅጉ የሚጎዳ ከመሆኑ ባሻገር ይህንን ህገወጥ አድራጎት የሚፈጽሙትንም የመንግስት አካላት ተጠያቂ እንደሚያደርግ ከወዲሁ ግሎባል አልያንስ ማሳስብ ይወዳል ።

ይህ ጭፍንና አደገኛ የፌደራል መንግሥት አፈና በአስቸኳይ እንዲቆም እንጠይቃለን። የኢንተርኔት አገልግሎት ያለምንም ገደብ እንዲሰራጭ እንጠይቃለን። በመጨረሻም በአዲስ አበባ ውስጥ ያለምንም የፍርድ ቤት ትዕዛዝ ታፍነው የታስሩ ዜጎቻችን ያለምንም ቅደመ ሁኔታ በአስቸካይ ከእስር እንዲፈቱና ዳግመኛም እንዲህ አይነቱ ህገ ወጥ አስራር የሃገሪቱን ዜጎች እጅግ የሚያሳዝንና ሃገሪቱ የምታደርገውን የለውጥ እንቅስቃሴ ከድጡ ወደ ማጡ እንደሚያሸጋግር እናሳስባለን። በመጨረሻ፤ የኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት፤ የክልል ባለሥልጣናት፤ ተፎካካሪ ፓርቲዎች፤ የማህበረሰብ ድርጅቶች፤ መንፈሳዊ አባቶችና እናቶች፤ ወጣቶች፤ ምሁራንና ሌሎች ባለድርሻዎች በጋራ አስቸኳይ ብሄራዊ ውይይት እንዲያደርጉና ወደማይመለስ ጫፍ የደረሰችውን ኢትዮጵያን ከአደጋ እንዲታደጓት ጥሪ እናደርጋለን።

ሰብአዊ መብቶች ይከበሩ!!
አፈና በአስቸኳይ ይቁም!!

የጠቅላይ ሚኒስትሩ የፓርላማ ውሎ (በመስከረም አበራ)

በመስከረም አበራ

PM Abiy Ahmed in the parliament.

ጠንካራ ነኝ ማለቱ ለበጎ ያልሆነው ህወሃት የማዕከላዊ መንግስቱን መዘወሩን ካቆመ ወዲህ የመጣው የዶክተር አብይ መንግስት የተረከባት ኢትዮጵያ  በጉያ በጀርባዋ፣በእጅ በእግሯ፣በአፍ በሆዷ ውስብስብ ችግር አዝላ የምትጎተት ነች፡፡ይህ ችግር በድንገት በመጣው የዶ/ር አብይ መንግስት ቀርቶ በማኛውም እኔ ነኝ ባይ የምድር ጠቢብብ በአንድ አመት ውስጥ ሊፈታ አይችልም፡፡ዶ/ር አብይን እንደ መልስ ሳጥን ቆጥሮ ሁሉን በአንድ ቀን ፍታ የሚል ጤነኛ ኢትዮጵያዊም የለም፡፡

ሆኖም ከችግሩ ውስብስብነት እና ውዝፍነት የተነሳም ሆነ ከእርሳቸው ሰዋዊ ድክመት የተነሳ ችግር መፍታት ቢያቅታቸው እንኳን እሳቸው የሚያመጡት ተጨማሪ ችግር እንዳይኖር ለሚሰሩት ስራ ሁሉ ተጠያቂነት ሊኖራቸው ግድ ነው፡፡በመንግስታቸው አሰራር ላይ ጥያቄ የሚያነሳው ኢትዮጵያዊ ሁሉ አላማው እሳቸውን ማጣጣል፣የጀመሩትን ጉዞ ማጨናገፍ፣ይበጃል ብለው እየሰሩ ያለውን ነገር ዋጋ ለማሳጣት ሊሆን አይችልም፡፡ይልቅስ ሃገራችን በጣም አሳሳቢ ችግር ውስጥ እንደመሆኗ መንግስታቸው በችግሩ አሳሳቢነት መጠን ያልተራመደ የሚመስለው ዜጋ ሊተቻቸው ይችላል፡፡ይህ አይነቱ ትችት የእሳቸውን ልፋት ገደል ለመክተት የተደረገ ክፉ ነገር አይደለም፡፡

እሳቸው ግን የሚቀርብባቸውን ትችት በበጎ ጎኑ የሚረዱት አልመሰለኝም፡፡ጠቅላይ ሚኒስትሩ በትናንቱ የፓርላማ ውሏቸው ካሳዩት ሁኔታ የተረዳሁት የሃሳብ ልዩነትን እና የመንግስት ተጠያቂነትን እምብዛም እንደማይፈልጉ ብቻ ሳይሆን ስሜታዊ ብስጭት ውስጥ ሊከታቸው እንደሚፈትናቸው ነው፡፡የእርሳቸው ስሜታዊ መሆን ደግሞ የሚያጠፋው ብዙ ነው፡፡ወጣት መሪ መሆናቸው፣ሃገሪቱ ራስ አዟሪ ውስብስብ ችግር ውስጥ በተዘፈቀችበት ጊዜ ወደስልጣን መምጣታቸው ተደማምሮ ብስጭታቸውን ሊያብሰው ይችላል፡፡ሆኖም መንግስትነት ሆደ-ሰፊነት መሆኑን ማሰቡ ለእራሳቸውም ለሃገራችንም በጎ ውጤት ይኖረዋል፡፡

በግሌ ዶ/ር አብይ ውስብስብ ችግር ያዘለችውን ሃገር ሊመሩ መንበር ከጨበጡ ወዲህ ኢህአዴግ ውስጥም ኢትዮጵያ ትታየኛለች፡፡ህወሃት መራሹን ኢህአዴግ በምጠረጥርበት ሃገር የማፍረስ ሴራ የዶ/ር አብይን ኢህአዴግ አልጠራጠውም፡፡ዶ/ር አብይ “በኢትዮጵያ  ህልውና ላይ አንደራደርም” ሲሉ እኔም ስለምሳሳላት ኢትዮጵያ እኔ በሚሰማኝ መጠን እየተሰማቸው እንደሚያወሩ አምናለሁ፡፡ህወሃት ኢትዮጵያ እንዳትፈርስ ሲል ግን ስልጣኑን አጥብቆ እያሰረ እንደሆነ ብቻ እረዳ ነበር!ስለዚህ እኔን ጨምሮ እያንዳንዱ ኢትዮጵያን የሚወድ ዜጋ ከዶ/ር አብይ ጋር የሚያስማማው አንድ ጉዳይ አለ-የኢትዮጵያ ህልውና!

በዚህ መሰረታዊ ነገር የተስማማን ሁሉ ግን ዶ/ር አብይ ኢትዮጵያን ለማዳን እርሳቸው ትክክል ነው ብለው አምነውበት በሚሄዱበት አካሄድ ሁሉ እንስማማለን ማለት አይደለም፡፡ይህ መሰረታዊ አንድነት ሳይረሳ ጥፋት የጠፋ ሲመስለው የተቸ ቢያንስ ኢትዮጵያን በማለቱ ላይ ያለው ተመሳሳይ ምኞት ተረስቶ ለጥፋት የቆመ፣መተቸት ብቻ የሚያስደስተው፣የአሉባታ ሱስ ብቻ የሚያናገረው ተደርጎ በመንግስት ዘንድ የሚታሰብ ከሆነ ቀጣዩ ትዕይንት ጋዜጠኛን እና ተችን እያሳደዱ መሰር ነው የሚሆነው፡፡

ጠ/ሚ አብይ በሰሞኑ የፓርላማ ውሏቸው ከተነሱ ጥያቄዎች ውስጥ ገሚሶቹ ስሜታዊ አድርገዋቸው ተችዎችን “እኛ የያዝነው እውነት ነውና ማሸነፋችን አይቀርም፤እናንተ ግን እግዚአብሄር ይፍረድባችሁ” እስከማለት አድርሷቸዋል፡፡ይህን ንግግራቸውን ስሰማ ዶ/ር አብይ ለትችት ያላቸውን ስስ ስሜት በደንብ ተረድቻለሁ፤ብዙ ነገርም ወደ ህሊናየ መጥቷል-ጭንቀት ጭምር! ዶ/ር አብይ የእግዚአብሄር ፍርድ እንዲያገኛቸው ለፈጣሪ አሳልፈው የሰጧቸው ሚዲያዎች በውጭ ሃገር የሚገኙ፣በዩቱብ የሚሰራጩ እንደሆኑ አብረው ገልፀዋል፡፡ “ባህር ማዶ ስላላችሁ እኔ ምንም ላደርጋችሁ አልችልም” ሲሉም አክለዋል፡፡

አብይ በተችዎቻቸው ላይ የመለኮት ፍርድ እንድትመጣ የፈለጉት እነዚህ ሚዲያዎች ከእርሳቸው ግዛት ውጭ ስለሆኑም ጭምር ነው፡፡ይህ ንግግራቸው እና ብስጭታቸው ሚዲያዎቹ በአብይ ግዛት ቢሆኑስ ኖሮ ማስባሉ አይቀርም፡፡ከዚህመረዳት የሚቻለው ነገር በዶ/ር አብይ ግዛት ሆኖ መንግስታቸውን መተቸት እምብዛም እድሜ ያለው ፈለግ ላይሆን እንደሚችል ነው፡፡

ጠ/ሚው እያደር ስሜታዊነት እየታየባቸው መምጣቱ ሁለት አደጋ አዝሎ ይታየኛል፡፡ አንደኛው የአምባገነንነት ዋዜማ ሁለተኛው በዶ/ር አብይ ዘንድ እየተተከለ የመጣ የተጠልቻለሁ ስጋት፡፡ሁለቱም አሳሳቢ ናቸው፡፡አብይ ወደ አምባገነንነት እያዘነበሉ ከሄዱ የኢትዮጵያ ህዝብ ደግሞ አምባገነንነትን የመሸከም ትዕግስቱ ስለተመናመነ ሃገርን ክፉ ችግር ውስጥ የሚከት፣የመንን እና ሶሪያን የሚመስል የመንግስት እና የህዝብ አምባጓሮ ሊመጣ ይችላል፡፡ አብይ የተቻቸው ሁሉ የጠላቸው አድርገው የማሰባቸው ሁለተኛው ችግር ሰውየው የስነልቦና መረጋጋት እንዳይኖራቸውና የሃገሪቱን ችግር ሰከን ባለ ልቦና እንዳይፈቱ ያደርጋል፣ለህዝብ የመስራት ተነሳሽነታቸውንም ይቀንሳል፣በስነልቦና አለመረጋጋት እና ግራ መጋባት ውስጥም ሊከታቸው ይችላል፡፡ይህም ሃገሪቱን ወደ ቀውስ ሊመራ የሚችል ነገር ነው፡፡ይህ ደግሞ አሳሳቢ ነው፡፡

በበኩሌ በብዙ ችግር ተቀስፋ የተያዘቸው ሃገሬ በከፍተኛ ጥንቃቄ መያዝ ያለባት ተሰባሪ እቃ እየመሰለችኝ ከመጣች ዋል አደር ብያለሁ፡፡አሁን የቀድሞዋ የምትባለው ይጎዝላቪያ ከመፈራረሷ አንድ አመት በፊት የመፍረስ ምልክት ያልነበረባት መሆኗን የሰማሁ ነኝና “እንዴትም አድርገን ብንይዛት ኢትዮጵያ አትፈራርስም” ከሚሉት ወገን አይደለሁም፡፡ ይልቅስ “ከአያያዝ ይቀደዳል” ባይ ነኝ! በተለይ የዘር ፖለቲካ የበላት ሃገር አትፈርስም ብሎ ከመተማመን ይልቅ ተቃራኒውን አስቦ አያያዙ ላይ ጠንክሮ መስራቱ የበለጠ ትርጉም ይሰጠኛል፡፡አያያዙን ማሳመሩ የሁላችንም ሃላፊነት ቢሆንም መንግስትን የሚዘውሩት ዶ/ር አብይ ፖለቲካዊ እና ስነልቦናዊ አቋቋም ደግሞ ይበልጥ አስፈላጊ ይመስለኛል፡፡

አብይ በቋፍ ያለችውን ሃገሬን በመሃል እጃቸው ይዘው የቆሙ ሰው ይመስሉኛል፤ሃገርን ያህክል ውድ ነገር እጃቸው ላይ ያስቀመጥንባቸውን ሰው በከንቱ ሊያስመርር ትችት ይዞ የሚመጣ አለመኖሩን ቢረዱ መልካም ነው፡፡እንዲህ ያለ ሰው አይጠፋም ከተባለም ነገሩን ንቆ የተሻለ ነገር ወደመስራቱ ማዘንበሉ ይመረጣል፡፡የጠሚው ስነ-ልቦናዊ ብርታት፣ የአስተሳሰብ ከፍታ፣እንደሚያወሩት የይቅርታ ሰውነት፣በሌላው ጫማ ገብቶ የማሰብ ነገር፣ፖለቲካዊ ግንዛቤ እና ቁርጠኝነት፣አለማዳላት፣የሚናገሩትን ሆኖ መገኘት በሃገሬ ፖለቲካዊ እጣ ፋንታ ላይ የማይተካ ሚና ያለው እንደሆነ አስባለሁ፡፡የተሳሳቱ ሲመስለኝ አካሄዳቸውን ብተችም ያሉበትን አስቸጋሪ ሁኔታም እረዳለሁ፡፡በአንፃሩ ያሉበት አስቸጋሪ ሁኔታ የማይከለክላቸው ሊያደርጉ ሲገባ ያላደረጉት፣ አለማድረግ ሲገባቸው ያደረጉት ነገር እንዳለም ይሰማኛል፡፡

ባፈው አንድ አመት የኦሮሞ ብሄርተኞች በሚዲያቸውም ሆነ በጠመንጃቸው ያጠፉትን ጥፋት ሃይ አለማለታቸው ሊያደርጉ ሲገባ ያላደረጉት ነገር ነው ብየ አስባለሁ፡፡ የሚመሩት ፓርቲ ኦዴፓ ካድሬዎች የምስኪኖችን ቤት ያውም በክረምት እያፈረሱ ማባረራቸው እና እሳቸውም አልሰማሁም ማለታቸው ባያደርጉት ምንም የማይጎዳቸው ግን ወገባቸውን ታጥቀው የሰሩት ጥፋት ይመስለኛል፡፡ ይህን ከባድ ጥፋት በሪፖርታቸው በአብዛኛው ሳይነኩት ከነኩትም አድበስብሰውት አልፈዋል፡፡

በሰፊው እያነጋጋረ ያለው የኦሮሞ ባለስልጣናት በርከት ብሎ መሾምን በተመለከተ ሳይጠየቁ ራሳቸው አንስተውት “ኦሮሞ ያለአግባብ፣በማይገባው ሁኔታ ስልጣን ይዞ ከሆነ ከእኔ ጀምሮ ተጠያቂ እንደረግ” ብለዋል::መልሳቸው ሁለት ትርጉም አለው፡፡ አንደኛው ኦሮሞ በዛ ብሎ ተሹሞ ከሆነም የሚገባውን ቦታ ነው የያዘው አይነት ሲሆን ሁለተኛው ኦሮሞ በዝቷል እየተባለ የሚባለው ነገር ከነአካቴው ውሸት ነው የሚል አንድምታ አለው፡፡ አባባላቸው ኦሮሞ ብዙ ሆኖ መሾሙ ያለ አግባብ አይደለም ሲለሚገባው ነው የሚል ከሆነ የህወሃትን መጨረሻ እንዲያስቡ ከመምከር ውጭ ምንም የሚባል ነገር የለም፡፡

ኦሮሞ ስልጣን ላይ በርከት ብሎ ተሹሟል የሚለው ነገር እውነት አይደለም የሚሉ ከሆነም በንግድ ባንክ የተሰገሰጉት፣በኢትዮጵያ ጉምሩክ ባለስልጣን ላይ የበዙት፣በውትድርናው መስክም ቢሆን በስመ ምክትል ኢታማጆር ሹምነት ይዝ መምሪያዎችን ሁሉ ለጠቅልሎ መያዙን  አየር ሃይሉን፣የመከላከያ ሚኒስትርነቱን፣የሃገር ውስጥ ደህንነቱን፣የጠቅላይ አቃቤህግነቱን  ኦሮሞ የያዘ መሆኑ እየታወቀ ይህ ምንም ችግር የለውም ብየ ስናገር መታመንን አገኛለሁ ብለው ከሆነ ይህ ከህዝብ የሚያርቅ እንጅ የሚያቀርብ ነገር አይደለም፡፡ከሁሉም በላይ የአዲስ አበባ ከንቲባ የሆኑትን አቶ ታከለ ዑማን የሾሙበት መንገድ ኦሮሞን ያለ አግባብ የመሾሙ ምልክት አይደለም ተብሎ ከሆነ የነገውን መፍራት ሊኖርብን ነው፡፡

በመንግስታዊ መዋቅሩ ላይ የኦሮሞ ባለስልጣናት በርከት ብለው ከመታየታቸው ባሻገር በመደበኛው የመንግስት መዋቅር ላይ ምንም ስልጣን የሌላቸው እንደ ጃዋር ያሉ ኦሮሞዎች ሁሉን ማድረግ እንደሚችሉ የሚናገሩት፣የባሰባቸው ደግሞ በቪዲዮ ምስላቸውን እያሳዩ የሰው ህይወት እንሚያጠፉ የሚዝቱት እና ደግሞ ምንም የማይደረጉት፣ወደ ሃያ የሚጠጉ በንኮችን የዘረፈው የኦሮሞ ድርጅት ምንም አለመባሉ  ኦሮሞ ያለ አግባብ መብት እያገኘ ስላልሆነ ከሆነ ትርጉሙ ምን ሊሆን ይችላል?

የህገ-መንግስት መሻሻልን በተመለከተ የተነሳውን ጥያቄ የመለሱበት መንገድ አንድም ቅንነት በጎደለው ሁለትም የችግሩን አንገብጋቢነት በማይመጥን መልኩ የተመለሰ ሆኖ አግኝቸዋለሁ፡፡ጠ/ሚ አብይ መልሳቸውን የጀመሩት “ህገ-መንግስቱ አይወክለንም የሚሉ ሰዎች ህገ-መንግስቱ ከሚሰጣቸው መብት  መጠቀማቸውን አልተውም” በሚል ንግግር ነው፡፡

በመጀመሪያ ህገ-መንግስትም ሆነ ሌላ ህግ እንዲቀየርለት የሚጠይቅ አካል ጥያቄው ተሰምቶ ህጉ እስኪቀየር ድረስ ባለው ህግ የመገዛት ግዴታ አለበት፡፡ የማይፈልጉትን ህገ-መንግስት አክብረው መብቱንም የሚጠቀሙ ግዴታውንም የሚያደርጉ ሰዎች ሊመሰገኑ እንጅ ሊወቀሱ አይገባም፡፡አብይም መብትን ይጠቀማሉ ብለው ከሰሷቸው እንጅ ጠያቂዎቹ ህገመንግስቱ የጣለባቸውን ግዴታም እየተወጡ ነው፡፡ሁለተኛው እና ዋናው ነገር ህገመንግስቱ እንዲቀየር የሚጠይቁ ሰዎች ህገ-መንግሰቱ ሲረቀቅ አብረው ያላረቀቁ፣ባልተስማሙበት ህግ እንዲገዙ የተፈረደባቸው የዘር ፖለቲካው ባይትዋሮች  ናቸው፡፡

እነዚህ አካላት አብይ እንደሚያስቡት የአማራ ክልል ነዋሪዎች ብቻ አይደሉም፡፡ይልቅስ ከአማራ ክልል ህዝብ በተጨማሪ ህገ-መንግስቱ የማያውቃቸው የኢትዮጵያ የከተማ ነዋሪዎች በአብዛኛው፣ከሁለት እና በላይ ብሄሮች የሚወለዱ ሰዎች በአጠቃላይ ናቸው፡፡ እነዚህ ሰዎች ባልተስማሙበት ህግ ይገዙ ዘንድ የሚጣልባቸው ዕዳ ከየት እንደመጣ ህገ-‘መንግስቱ ጫፉ አይነካ’ የሚሉ አካላት እንዲያስረዷቸው ሁኔታዎችን ማመቻቸት የአብይ መንግስት ሃላፊነት ነው፡፡በተረፈ ‘ህገ-መንግስቱ እኔን እና ቤቴን ስለሚያረካ አናንተ እና ቤታችሁ እኛ ባወጣነው ህገ-መንግስት ትገዙ ዘንድ የተገባ ነው’ የሚሉ አካላትን እና  ከህገ-መንግስቱ አንቀፆች ውስጥ በአንዱ ንዑስ አንቀፅ ውስጥ እንኳን ፍላጎታቸውን እንዳያካትቱ የተፈረደባቸውን ዜጎች እኩል “ዋልታ ረገጥ” ብሎ መሰየም ቅንነት አይደለም፤ሚዛንንም ሰባራ ያደርጋል፡፡

ከሰሞኑ የሞት አጀብ አስከትሎ የመጣውን ፖለቲካዊ ቀውስ አስመልክቶ የተነሳውን ጥያቄ ሲመልሱ ጠ/ሚው ስሜታዊነታቸው በርትቶ፣እርግማናቸው በዝቶ አንድ ወገንን መልኣክ ሌላውን ሰይጣን የማድረግ መዛመም ታይቶባቸዋል፡፡ ወደ መልዓክት ወገን ሊያስጠጓቸው የከጀላቸውን፣በስም የጠሯቸውን ሟቾች(ዶ/ር አምባቸው እና ጀነራል ሰዓረን) የገደለውን  አካል እስከመግደል ያደረሰውን ምክንያት ሁሉ በፓርላማ ውሏቸው እንዲነግሩን አይጠበቅባቸውም፡፡ሆኖም ቢያንስ ገዳዮቹን ለዚህ እርምጃ ያበቃቸው አብይ የሚሉት ክፋት፣እርኩስነት፣ፍልቅልቅ ሰው ላይ የመጨከን እርኩሰት፣ያጎረሰ እጅን የመንከስ ውለታ ቢስነት ብቻ እንደማይሆን አውቆ ላልተኛ ሁሉ የሚሰወር ነገር አይደለም፡፡በአዴፓ መሪዎች መሃል ለተከሰተው መጋደል የፌደራል መንግስቱ እጅ የለበትም ማለትም የኢህአዴግን የፓርቲ ባህል አለማወቅ ነው፡፡

በተለይ አሁን አዴፓ ሆኛለሁ ያለው ብአዴን ለንጉስ የማጎንበስን የረዥም ዘመን ታሪክን ለሚያውቅ የገዳይ እውነት አብይ ከሚሉት እጅግ የተለየ ሌላ ሊሆን እንሚችል፤ፅድቃቸው በፌደራል መንግስት በጣም የተወራላቸው ሟቾችም መታዘዛቸው ፅድቅ ሆኖ የተቆጠረላቸው ሊሆኑ እንደሚችሉ መጠርጠር አይከፋም፡፡በተረፈ ገዳይ ተብሎ የተብጠለጠለው ቡድንም የራሱ ቤተሰብ፣ደጋፊ ያለው ለሃገርም ይበጃል ያለውን ሊሰራ የሞከረ በመሆኑ ቢያንስ ቀብሩ መዘገብ እንደነበረበት ለፍቅር እና ይቅርታ ሰባኪው ጠ/ሚ አብይ ማሳሰብ እወዳለሁ፡፡

በአንፃሩ በዓብይ መንግስት ድርጎ የሚሰፈርላቸው የሃገር ውስጥ ሚዲያዎችም ሆኑ የአብይ መንግስት ፍቅር ያነሆለላቸው ወዶ ገባ የባሕር ማዶ ሚዲያዎች አስር ሰኮንድ ወስደው አብይ አምርረው የጠሏቸውን የብርጋዴር ጀነራል አሳምነው ፅጌን ቀብር መዘገብ አልፈለጉም፡፡ይህ የመረረ ጥላቻ አብይንም ሆነ ለአብይ መንግስት የሚያሸበሽቡ ሚዲያዎችን ትዝብት ላይ የሚጥል ብቻ ሳይሆን በፖለቲካዊ ድራማው ላይ ግድያውን የጀመረው ማን ነው? በዚህ ውስጥ የፌደራሉ መንግስት እጅስ የለበትም ወይ?የሚለውን ጥያቄ ያጠናክራል፡፡