የአማራ ብሄረተኝነት ትልቅ ስጋት ነው፣ ግን መፍትሄው እነ ዶ/ር አብይ እጅ ውስጥ ነው ያለው #ግርማካሳ

አንዳንድ ሰዎች የአማራ ብሄረተኝነት በጣም አደገኛ ደረጃ ደርሷል ይላሉ። ከነዚህ ሰዎች መካከል ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ይገኙበታል። አንድ ወቅት በሰጡት አስተያየት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፣ “የአማራ ናሽናሊዝም ወደ ሚያስፈራ ደራጃ እያደገ ነው” ብለው ነበር የተናገሩት።

የአማራ ብሄረተኝነት ስጋት ነው ተብሎ ከታሰበ፣ በቀዳሚነት ይሄ ከጥቂት አመታት በፊት ያልነበረ ብሄረተኝነት እንዴት በአጭር ጊዜ   ውስጥ አሁን የደረሰበት ደረጃ መድረስ ቻለ ብለን መመርመር ያለብን መሰለኝ።  መፍትሄ ወደምንለው ከመሄዳችን በፊት የችግሩን ምንጭ መረዳት አስፈላጊ ነው።

የአማራ ብሄረተኝነትን የተወለደው አማራ-ጠል በሆኑ የትግራይና የኦሮሞ ብሄረተኝነት ነው። ስልጣን ላይ የነበሩና አሁንም ያሉ የኦሮሞ(ኦነግ/ኦህዴድ) እና የትግራይ (ሕወሃት) ብሄረተኛ ፖለቲከኞች፣  አሁን ሕግ መንግህስት የሚባለውን ሲያረቁ፣ በዘር ላይ እንዲያተኩር ነው ያደረጉት። ክልል የሚሏቸው የፌዴራል መስተዳድሮች የተዘረጉት በዘር ነው። ከአማራ ክልል ውጭና በአማራ ክልል ውስጥም የኦሮሞ ዞን(ከሚሴ) ውስጥ ፣ አማራዎች እንደ ሁለተኛ ዜጋ እየተቆጠሩ  ከፍተኛ በደልና ግፍ ላለፉት ሃያ ሰምንስት አመታት ሲፈጸምባቸው ነበር። አማራው ኢትዮጵያዊነቴ ይበቃኛል ብሎ ሲቆም፣ ነፍጠኛ፣ ትምክህተኛ ተብሎ ተጠቃ። ተፈናቀለ፣ ተገደለ።

አማራ ተብሎ፣ ተነጥሎ፣ በስርዓቱና በመንግስታዊ አሰራሩ፣ በደልና ግፍ እየደረሰበት ስለሆነም፣ ለሕልውናው ሲል፣ በአማራ ስም መደረጃት ተፈለገ። የአማራ ብሄረተኘነትም አቆጥቁጦ በእግሩ መሄድ ጀመረ።

በዶ/ር አብይ አህመድ የሚመራው የኦዴፓ አገዛዝ፣ ከሰኔ 15ቱ የባህር ዳርና የአዲስ አበባ የባለስልጣናትን መሞትን ተከትሎ፣  “መፈንቀለ መንግስት” ብለው የጠሩትን፣ የራሳቸው የኢሕአዴጎች የርስ በርስ ሽኩቻንና መገዳደልን፣ እንደ ሰበብና መልካም አጋጣሚ በመጠቀም፣ ከነርሱ የተለየ የፖለቲካ አመለካከት ያላቸው የሚባሉትን፣  በዋናነት የባላአደራው ምክር ቤትና የአብን  አባላትንና፣ በኢሕአዴግ/አዴፓ ውስጥ ያሉ ለኦዴፓ ማጎብደድ የለብንም የሚሉ ጠንካራ አመራሮችና አባላትንም  በገፍና በጅምላ፣  “ሽብርተኛ” እያሉ እያሰሩ ነው።

እነ ዶ/ር አብይ አህመድማ የኦዴፓ ጓዶቻችው፣  ምን አልባት ይሄንን መስመር የለቀቀ፣ ህወሃት ሲያደርገው የነበረውን አይነት የጡንቻ እርምጃ በመዉሰዳቸው፣ “የአማራ  ብሄረተኝነት እናጠፋለን” ብለው አስበው  ከሆነ በጣም ፣ እጅግ በጣም ተሳስተዋል። እንደው የበለጠ አስር እጥፍ የአማራ ብሄረተኝነት ጥንካሬ እንዲጨምር ነው የሚያደርጉት።

የአማራ ብሄረተኝነትን እድገት ለማቆም ብሎም በሂደት ተዳክሞ  እንዲከስም ማድረግ አስፈላጊ ነው። ያንን ለማድረግ፣የአማራ ብሄረተኝነት እንዲያድግ ingredient የሆነውን ነገር ማራቅና ማስወገድ ያስፈልጋል። በዋናነት የአገሪቷን የፖለቲከ ጨዋታ ህግ መቀየር ያስፍፈልጋል። ጨዋታውን ከጎሳ ፖለቲካ ጨዋታ ማውጣት ያስፈለጋል። ያን ማድረግ ካልተቻለ፣ በጉራጌኛ ዘፈን ትግሪኛ ጨፍሩ፣ ወይም በቅርጫት ኳስ ጨዋታ፣ እግር ኳስ ይመስል፣  አስራ አንድ ተጨዋች አሰልፉ እንደማለት ነው።

  1. የኦሮሞ ፣ የትግሬ፣ የአማራ ..ባህል ማእከላት፣ የተለያዩ የብሄረሰቦች ቅርስና ቋንቋ የሚያሳድቁ የሲቪክ ማህበራትና ተቋማት ሊኖሩ ይችላሉ። ዜጎች አማራ ነን፣ ጉራጌ ነን …ብለው በግለሰብ ደረጃ መናገር፣ መጻፍ ይችላሉ። ነገር ግን በዘርና በጎሳ ላይ የተመሰረቱ የፖለቲካ ድርጅቶች መታገድ አለባቸው።
  2. ኢትዮጵያዊነትን ያላማከለ ዘረኛ ሕግ መንግስትን መቀየር ወይንም በእጅጉ ማሻሻል፣ በተለይም የኢትዮጵያ ባለቤት ብሄር ብሄረሰብና ህዝብ የሚለው ሳይሆን የኢትዮጵያ ሕዝብ ወይን ዜጎች እንዲሆኑ ማድረግ አስፈላጊ ነው።
  3. የጎሳ አወቃቀርን አስወግዶ፣ ምን አልባት የሶማሌ ክልል ርእስ መስተዳደር አቶ ሙስጠፋ እንዳሉት ሰሜን፣ ደቡብ፣ ምስራቅ፣ ምእራብና መሐል ኢትዮጵያ የሚሉ ፣ ወይም ሌላ ግን ዘር ላይ ያላተኮረ፣ የፌዴራል መስተዳድሮችን መዘርጋት አስፈላጊ ነው። አንድም ቦታ፣ አንድም ቀበሌ የአንድ ወይንም የተወሰኑ ጎሳዎች መሬት ተደርጎ መቆጠር የለበትም። ሁሉም የአገሪቷ ግዛት የሁሉም ኢትዮጵያዉያን መሆኑን መረጋገጥ አለበት።  አንድ ኦሮሞ ከጨለንቆ ወይም አንድ ትግሬ ከሸምበቆ አዲስ አበባ  ወይም ጎንደር ቢመጡ፣ በአዲስ አበባና ጎንደር ከተማ ሕግ መሰረት ለተወሰኑ ወራት ከኖሩ በኋላ እዚያ ከተወለዱት ነዋሪዎች እኩል መብታቸው ተከብሮ ካስፈለገም ተወዳድረው፣ ህዝብ ከመረጣቸው ከንቲባ የመሆን መብታቸው መረጋገጥ አለበት። የየደብረ ማርቆስ  ወይም የወላይታ ሶዶ ተወላጆች፣  ነቀምቴ ወይም ደሴ አስተዳዳሪ መሆን መቻል አለባቸው።

አንድ ወቅት ከሞሬሽ፣ በቅርቡ ደግሞ ከአብን አመራሮች ጋር ተነጋግሬ ነበር። ሁለቱም የአማራ ድርጅቶች ከላይ የተጠቀሱት ሃሳቦችን በእጅጉ እንደሚጋሩ ነው ለመረዳት የቻልኩት። ራሳቸውን አክስመው አገር አቀፍ ለመሆን ዝግጁ ናቸው ።

የአማራ ማህበረሰብ መጀመሪያዉኑ አማራ ብሎ የተነሳው ስለተጠቃ ፣ ለሕልውና ብሎ እንጂ ፈልጎ አልነበረም። ውስጡ፣ አጥንቱና ደሙ ኢትዮጵያዊነት ነው። ሁሉም ኢትዮጵያን ካለ፣ በሁሉም ቦታ እንደ ኢትዮጵያዊ መኖር፣ መስራት ከተቻለ፣ መቀሌና ነቀምቴ እንደ ደብረ ማርቆስና ደሴ ከሆኑለት እልልልል ይላል እንጂ በጭራሽ አይከፋውም።

የኢትዮጵያ ጠላት ሄርማን ኮሆን፣ “አማራዎች ስልጣን አጣን፣  የበላይ መሆን አለብን ብለው ፣ የድሮዉን ስርዓት ለመመለስ ነው የሚፈልጉት”  አለ። የዉሸትና የጥላቻ ፕሮፖጋንዳ !!!!ምን አልባት ይህን አይነት አስተያየት ሀርማን ኮሆን የሚናገረው የኦሮሞ ጽንፈኛ ብሄረተኞች ከሚናገሩትና ከሚጽፉት ተነስቶም ሊሆን ይችላል።

ህዝቡ ዘረኛ አይደለም። እኔ ብቻ ልጠቀም፣ እኔ ብቻ ልዩ ጥቅም ላግኝ አላለም። ምነው ኦሮሞዎቹን እነ ዶ/ር አብይን ቀድሞ ሆ ብሎ የደገፈው ማህበረሰብ የአማራው ማህበረሰብ አይደለምን ? ሕዝቡ የሚፈልገው እኩልነት ነው።

ከላይ የተጠቀሱ ነጥቦች ተግባራዊ በማድረግ፣ ሃይልና ጡንቻ ሳያስፈልግ የአማራ ብሄረተኝነትን ራሱ አማራው ጆንያ ውስጥ ያስገባዋል፤ ወደ ጎን ያደርገዋል።

ነገር ግን ጽንፈኛ ኦሮሞዎች አገርን እያመሱ፣ እነ ኦነግና መሰሎቻቸው ሚሊሺያ እያደራጁ፣ የኬኛ ፖለቲካ አየሩን ተቆጣጥሮ፣ በኦሮሞ ክልል ኦሮሞ ያልሆኑ በግፍ መጤ እየተባሉ እየተፈናቀሉ፣ የኦሮሞ ብሄረተኝነት በተለይም አማራ ጠል የኦሮሞ ብሄረተኝነት ከቁጥጥር ውጭ እየሆነ፣ እኛ ልዩ ተጠቃሚ መሆን አለብን በሚል፣ ኦሮሞው ከሌላው እኩል ሆኖ የሚኖርበት ሳይሆን ኦሮሞ የበላይ እንዲሆን እየተፈለገ፣ ተራው የኛ ነው ባዮች ስልጣኑን ጨብጠውና ዜጎች በጅምላ እየታሰሩ ባለበት ሁኔታ፣ አማራውን በአማራነት አትደራጅ ማለት ግብዝነት ካልሆነ ምን ሊባል ይችላል ?

እንደውም ትግሬ በዘሩ፣ ኦሮሞ በዘሩ ሲደራጅ ዝም ተብሎ፣ ከነርሱም ጋር እየተሰራ፣ አማራው ለምን ተደራጀ ማለት ፣ የዘር-ፖለቲካን መቃወምና መጥላትን ሳይሆን፣ አማራውን መጥላት ተደርጎ ነው ሊታይ የሚገባው።

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s