በአማራው ሞት ላይ የሚቆምሩት እነ ማን ናቸው? (በረራ ጋዜጣ)

የአማራ ክልል ፀጥታ ኃይል ስልጠናዎችን እየሰጠ በነበረበት ወቅት አንድ አነጋጋሪ ጉዳይ ተፈጥሮ ነበር። አሰልጣኝ ተብለው ከተመረጡት ግለሰቦች መካከል አንደኛው የክልሉን መሪዎች እንዲሁም የፀጥታ ኃይሉ አመራሮችን እርስ በእርስ ለማጣላት ሲሰራ እንደተደረሰበት ባሕርዳር አካባቢ ብዙ ተወርቷል። ይህ መሪዎቹን ለማጣለት ሲሰራ የተደረሰበት ግለሰብ እንደተባረረ የተነገረ ሲሆን ላኪዎቹ አዲስ አበባ ያሉ ባለጊዜዎች እንደሆኑ ከወደባሕርዳር ሲወራ ሰንብቷል። ላኪዎቹ አቅም ያላቸው እንደመሆናቸው አመራሮችን እስር በእርስ ለማፋጀት ሲሰራ የነበረ ሰው ተደርሶበት ያለ ምንም ቅጣት ወደ አዲስ አበባ መላኩ በብዙዎቹ ዘንድ ሲነገር የሰማ አማራው የብዙ ቁማርተኞች መነሃሪያ ሆኖ መሰንበቱን ለመረደት አይሳነውም። የአማራ ክልል መሪዎችና የፀጥታ ኃይሉ ኃላፊዎች እርስ በእርስ እንዲፋጁ ሲሰራ ነበር የተባለው “አሰልጣኝ” ጉዳይን ላስታወሰ የሰሞኑን አሳዛኝ ድርጊት በፊትም አማራውን ለማገዳደል ስራዎች ሲሰሩ እንደነበሩ መገንዘብ አያዳግተውም። የሰሞኑ አሳዛኝ ድርጊት በስተጀርባ እነ ማን አሉ የሚለው ወደፊት ይበልጥ ግልፅ የሚሆን ቢሆንም በርካታና በቀላሉ የማይገመቱ ኃይሎች እንዳሉበት ጠቋሚ ምልክቶች ታይተዋል። ከሰሞኑ ክስተት በስተጀርባ እነማን አሉበት የሚለው ቀጣይ ምርመራ በደንብ የሚያረጋግጠው ሆኖ በክስተቱ እጃቸውን ያስገቡ አካላት ላይ ማተኮር የተሻለ ይሆናል።

አማራው በርካታ አወንታዊ አበርክቶዎችን ሲሰጥ ዝምታን ሲመርጥ ባጅቶ ስህተት ፈፀመ ብሎ ሲያምን ከየጎሬው ብቅ የሚለው የፖለቲካ ኃይል ቁጥሩ በርከት ያለ ነው። ለዚህ እንደአብነት ከሰኔ 15ቱ የባሕርዳሩ ክስተት ማግስት በሀዘን ላይ የነበረውን አማራውን ለመርገም ብቅ ብቅ ያለውን የፖለቲካ ኃይል ማየት በቂ ነው። ላለፉት ጥቂት ወራት የአማራው ፖለቲካ ለአማራ ጠል ኃይሎች አስጨናቂ ነበር። በምዕራብ ጎንደር በኩል የጫሩት ሳት ብዙ መስዋዕትነት አስከፍሎም ቢሆን እንዲበርድ ሆኗል። በአካባቢው የመሸገ ፀረ አማራ ኃይል ከመቸውም ጊዜ በላይ ምሽጉን እንዲለቅቅ ተደርጓል። ብዙ ሚስጥሮቹ ተዝረክርከዋል። በምድረገኝ/ከሚሴ፣ አጣዬ፣ ሸንኮራ፣ …አማራውን ለመውረር ጥረት ያደረጉ “ተረኛ” ገዥዎች በኢትዮጵያ ሕዝብ ፊት ተጋልጠው ተመልሰዋል። በተለያዩ ግንባሮች ወደ አማራው የዘመተ ፀረ አማራ ኃይል በአብዛኛው ተጋልጦ ተመልሷል። አማራውን የጦር ቀጠና ለማድረግ ሲሰሩ የነበሩ አካላት በቁጥጥር ስር ሲውሉ ላኪዎቻቸው ቡራ ከረዩ ብለው አልተሳካላቸውም። ለምሳሌ ያህል በምድረገኝ/ ከሚሴ፣ ኤፌሶን/አጣዬና አካባቢው በአማራው ላይ ጥቃት የሰነዘሩት በቁጥጥር ስር ሲውሉ ላኪዎቻቸው የሌላን ክልል መንግስት መዋቅር ተጠቅመው አድማና ብጥብጥ እንዲደረግ ጥረት አድርገዋል። ይሁንና የአማራ የፀጥታ ኃይል ይህን የፀረ አማራዎች ቅስቀሳ ወደተግባር ተቀይሮ ሕዝብ ላይ ችግር እንዳይፈጠር መመከት ችሏል። ይህን የተገነዘቡት ኃይሎች የአማራው መደራጀት ለውጥ ማምጣቱን በመመልከታቸው ከባድ ድንጋጤ ውስጥ ነበሩ። በዚህ ስጋትና ድንጋጤ ውስጥ እያሉ በለስ ቀናቸው። የባሕርዳሩ አሳዛኝ ክስተት ተፈጠረ።

የባሕርዳሩ ክስተት የውስብስብ ጉዳዮች ውጤት ቢሆንም ጉዳዩን በመግፋት ፀረ አማራ ኃይሎች እንዳሉበት የሚያጠራጥር ጉዳይ አይደለም። ለዚህ በዋቢነት ሊጠቀሱ የሚችሉት ጉዳዩ ከተከሰተ ጀምሮ የተሰጠው መግለጫ፣ ፍረጃዎችና እርምጃዎች ናቸው። ጉዳዩ በተፈጠረ በሰዓታት ውስጥ “መፈንቅለ መንግስት” የሚልና የችኮላ ብያኔ ተሰጠው። ምንም አይነት ምርመራ ሳይደረግ አዲስ አበባ ላይ ተፈጠረ ከተባለ ሌላ ክስተት ጋር እንዲያያዝ ተደረገ። ጉዳዩን ፈፅመውታል የተባሉ አካላት ላይ በማስመሰል ወደ ሕዝብ በርካታ የጥላቻ ጠጠሮች ተጣሉ። የመንግስት ስልጣን ላይ ያለ አካል “ፋሽስት” ብሎ አማራው ላይ የተፈጠረውን ክስተት በምን መንገድ እንደሚይዘው ፍንጭ ሲሰጥ በዚህ ጎራ ሳይርቅ ተቃዋሚ ነን ያሉት አማራውን ጨፍጫፊ በማፍረግ ለሌሎችም ተሟጋች በመምሰል አማራው ላይ የሰነበቱ የሀሰት ዶሴዎችን በመምዘዝ አማራው ላይ በተመሳይ የጥላቻ አውደ ግንባር ተሰለፉ። የአማራ ብሔርተኝነትን ከመኮነንና የሕዝብን ስም ከማጥፋት አልፈው የመንፈስ አባታቸው መለስ ዜናዊ እንደሚለው አማራውን አከርካሪውን ለመምታት መልካም አጋጣሚ አድርገው ወሰዱት። በዚህም መሰረት ገቢዎችና ጉምሩክን የአንድ ቋንቋ ተናጋሪ መስርያ ቤት ልታደርጉት ነው ብለው በስም ዝርዝርና በጥሬ ማስረጃ የተሟገቷቸውን ሰዎች አጋጣሚውን ተጠቅመው አሰሩ። ከታሳሪዎቹ መካከል ገቢዎችና ጉምሩክ በተረኞቹ መጥለቅለቁን በሰነድ ያጋለጠውና የተቋሙ ሰራተኛ የነበረው ማስተዋል አረጋ ይገኝበታል።

በየቦታው አማራው ላይ የሚፈፅሙትን በደል፣ ኢትዮጵያ ላይ የሚያሳዩትን ስግብግብ ፖለቲካ የተቹ ማሕበራዊ አንቂዎችን፣ የስግብግብነት ልካቸውን ሳይሸፋፍን የሚሟገታቸውን አብን አባላትን፣ በዜጎች ላይ የሚፈፅሙትን በደል በመዘገብ የሚያጋልጣቸውን አሥራት ሚዲያ ባልደረቦች በማሰር የአማራውን ኃይል ለማዳከም የሚችሉትን ሁሉ አድርገዋል። ባለፉት አስር ወራት ከኦሮሚያና ከአዲስ አበባ በገፍ ካባረሯቸው የተረፉትን አማራዎች በማሳደድና በማሰር የጥላቻ ሰይፋቸውን እንደ አዲስ መዝዘዋል። ሆኖም በአማራው ላይ የተፈጠረው ክፍተት ከዚህም በላይ የጥላቻ አላማቸውን የሚያራምድላቸው መሆኑን ተገንዝበዋል። በዋነኝነት ደግሞ አማራው ባለፉት ጥቂት ወራት የተከላቸውን መልካም ጅምሮች በማፈራረስ አንገቱን አስደፍቶ መግዛትን አላማቸው አድርገዋል። በዚህም መሰረት ልዩ ኃይሉን ትጥቅ ለማስፈታት፣ የፀጥታ ተቋማቱን ለማፈራረስ እቅድ ሰንቀዋል። የአማራ ሕዝብ ደጀን ይሆናል የተባለውን ፋኖን በማሳደድ፣ የገበሬውን መሳርያ በማስፈታት፣ በተለያየ ስራ ላይ የተሰማሩ የፀጥታ አካላትን በመወንጀልና በማሰር አማራውን ማራቆት ላይ ያተኮረ ስራ ለመስራት ተሞክሯል። ሰኔ 15/2011 ዓ/ም ባሕርዳር ላይ ችግር ሲፈጠር የታገቱትንና የግድያ ትዕዛዝ ወጥቶባቸው የነበሩትን ኮ/ል አለበል አማረ፣ ጀኔራል ተፈራ ማሞ ጨምሮ በፀጥታ መዋቅሩ ጉልህ ሚና የነበራቸውን ግለሰቦች የአዴፓን መደናገጥ በመጠቀም ለእስር ዳርገዋል። ወደ አዲስ አበባ ለማምጣትም ጥረት አድርገዋል። እነዚህ ግለሰቦች የኦሮሞ አክራሪዎች በአማራው ላይ ጥቃት ሲፈፅሙ ከፅንፈኞቹ አመራሮችና ላኪዎቻቸው ጋር የተፋጠጡ በመሆናቸው ቂም ተይዞባቸው ቆይቷል። ይህ ክስተት ሲፈጠርም አማራውንና አመራሮችን ለመበቀል ብዙ ርቀት ተሂዷል። በአሁኑ ወቅትም ይህ የጥላቻ እርምጃ ተቀልብሷል ለማለት አያስደፍርም። በእርግጥ የባሕርዳሩን ክስተት አማራውን በማዳከም ብቻ ሳይሆን ራሳቸውን በማጠናከርም ቀላል የማይባል ስራ እየሰሩበት መሆኑን ከቀናት በኋላ የተሰጡት ሹመቶች ማሳያ ናቸው። ኢታማዡር ሹሙ ከተገደሉ በኋላ ከወደ ትግራይም ሆነ ከመሃል ሀገር የፌደራል መንግስቱ ላይ ብዙ አስተያየቶች ተሰጥተዋል። ይህ አስተያየት ይበልጥ ወደራሱ እየተጠጋ እንደሆነ የሰሞኑ የስልጣን ድልድል አይነተኛ ማሳያ ነው። ጀኔራል ሰዓረ መኮንን የኢታማዡር ሹም ናቸው ቢባልም መከላከያውን ሲያዙት የቆዩት ምክትላቸው ብርሃኑ ጁላ ናቸው። የባሕርዳሩን ክስተት አዲስ አበባ ተስቦ መጨረሻው የስልጣን ቁማር ውስጥ ገብቷል። ሰሞኑን ሲሰጡ የሰነበቱት አስተያየቶችን ለማምለጥ ሲቋምጡበት የነበረው ወንበር ላይ አልወጡም። ይልቁንም ሌላ ስሌት ነበር። ጠቅላይ ሚኒስትሩ የጦር ኃይሎች ዋና አዛዥ ናቸው። የመከላከያ ሚኒስትሩ አቶ ለማ መገርሳ ናቸው። ለስም ምክትል ይሁኑ እንጅ ብርሃኑ ጁላ ከኢታማዡር ሹሙ በላይ አዛዥ ናዛዥ ናቸው። በዚህ መሃል ኢታማዡር ሹም መሆን በተረኞቹ ከመጨፍለቅና ከመታዘዝ ያለፈ ሚና የለውም። በአንፃሩ ኦዴፓ ሲቋምጥበት የነበረውን ሌላ ቦታ ለመያዝ ጊዜ አግኝቷል። የብሔራዊ መረጃ ደሕንነት አገልግሎት። ለዚህም ሲባል የብሔራዊ መረጃ ደሕንነት አገልግሎት ዳይሬክተር የነበሩትን ጀኔራል አንስተው ከአብይና ለማ ስር፣ እንዲሁም ለስሙ ከብርሃኑ ጁላና በርካታ የኦሮሞ ጀኔራሎች መሃል አስገቧቸው። የብሔራዊ መረጃ ደሕንነት አገልግሎትን በራሳቸው ሰው ተኩ። ከዚህ ቀደም የኢንፎርሜሽን መረብ ደሕንነት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተርን በቁማር ወደ አዴፓ ማዕከላዊ ኮሚቴ አስጠግተው ተመሳሳይ ቁማር ሰርተዋል። በአሁኑ ወቅት ሁለቱም የመረጃ መስርያ ቤቶች፣ የመከላከያ ሚኒስትርና ሌሎች ቁልፍ ተቋማትን ተቆጣጥረዋል። አብዛኛውን ተቋማት ክስተቶችን ጠብቀው የወረሷቸው ሆነው እናገኛቸዋለን።

የኦሮሞ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኦዴፓ) ከሚመራው ቁማርተኛ ኃይል ባሻገር ከዚህ ቡድን ጋር የጦርነት ነጋሪነት ሲጎሳሰም የሚውለው ትህነግ/ሕወሓት መራሹ ቡድንም የባሕርዳሩን ክስተት ተከትሎ የአማራው ውድቀት ላይ እጠቀማለሁ የሚል የቅዠት ፕሮፖጋንዳ ውስጥ ገብቶ ተስተውሏል። ብአዴን/አዴፓ የአማራ ሕዝብ ጥያቄዎች እንዲመለሱ እታገላለሁ ሲል የመጀመርያው ጥያቄ የማንነትና ወሰን ጥያቄ እንደሆነ ሲገልፅ ቆይቷል። ይህም በአዴፓ/ብአዴን እና ትህነግ/ሕወሓት መካከል ትልቅ የልዩነት መስመር ሆኖ ቆይቷል። ትህነግ/ሕወሓት የአዴፓ/ብአዴን አመራሮችን ከተቃዋሚ መሪዎች ባልተናነሰ ሲያወግዛቸው ከርሟል። በሌላ በኩል የአማራን ሕዝብ በውክልና ጦርነት በመወጠር ለማባከን ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል። እንደ ኦሮሞ ፅንፈኞች ሁሉ በአማራ ላይ ሲያሰማራ የነበረው ወኪሎች የተሸነፉበት ትህነግ/ሕወሓት የአማራ ፀጥታ ኃይል ኃላፊዎች ያከናወኗቸውን ስራዎች በስጋትነት ሲመለከት ቆይቷል። የአዴፓ/ብአዴን አመራርን አቋምና ስራዎች በስጋትነት ሲመለከት ቆይቷል። ኦዴፓ በፊት መንገድ እንደሚመራቸው ፅንፈኞች ሁሉ ትህነግ/ሕወሓትም የባሕርዳሩን ክስተት አማራውን አንገት ለማስደፋት ለመጠቀም ጥሯል። የትግራይ ክልል ም/ርዕሰ መስተዳደር በሰጡት መግለጫ በጉዳዩ ኖሩበትም አልኖሩበትም ከፌደራል መንግስቱ ጋር በመተባበር በርካቶችን እንደሚያስሩ በግልፅ ተናግረዋል። ጦር ለመማዘዝ ማዶና ማዶ ሆነው ሲናቆሩ ከሚውሉት የፌደራል መንግስት ጋር አንድ አቋም ያስያዛቸው “ትምክተኛ” የሚሉት የአማራ ጉዳይ ነው። በዚህም መሰረት ትህነግ/ሕወሓት በግድ በያዛቸው የአማራ ግዛቶች ውስጥ አማራዎችን እንደ አዲስ ማሰር ተጀምሯል። የፌደራል መንግስቱ የሚወስደውን አፈናም አብረው እያገዙ መሆኑን ተናግረዋል። የኦሮሞ እና የትግራይ ፅንፈኞችን አንድ ያደረጋቸው በአማራ ላይ የያዙት ክፉ አመለካከት ነው። አማራው ችግር ሲገጥመው ጠብቀው ተቋማቱን በመምታት፣ አመራሩን በማሰር አንገት ለማስደፋት አላማ አድርገው እየሰሩ ነው። ይህ ቁማር ባሕርዳር ላይ የተፈጠረውን ክስተት ተጠቅመው፣ ለተገደሉት ያዘኑ፣ ለሕግ የሚቆሙ መስለው በአማራው ሕዝብ ላይ እየሰሩት ይገኛሉ። ሆኖም እነዚህ በአማራው ሞት የሚቆምሩ አካላት ያልተረዱት አማራው የደረሰበትን የፖለቲካ እርከን ነው። ባለፉት አመታት ኢትዮጵያ እንዳትፈርስ የአማራነት ጎኑ ሲደቃ ዝምታን የመረጠ ሕዝብ ዛሬም በተመሳሳይ የፖለቲካ ሁኔታ ላይ ያለ ይመስላቸዋል። እውነታው ግን ሌላ ነው። አማራው ስለ ኢትዮጵያ ብቻ ሲወገር ተረኞች ተፈራርቀውበታል። ሲቆስልበት የኖረውን ማንነቱን አላስነካም ካለ ጥቂትም ቢሆኑ አመታት እየተቆጠሩ ነው። ዛሬ ላይ ደግሞ በአራቱም አቅጣጫ የሚቃጣበትን ጥቃት ለመመከት ዝግጁ የሆነበት ጊዜ ነው። ስለ ኢትዮጵያ ስለደማ ብቻ የሀገሩን ስም አስር ጊዜ ሲጠራ ለሚውል የሚታለልበት ወቅት አይደለም። ከመቸውም ጊዜ በላይ ጠላቶቹን ለይቶ ያስቀመጠበት ወቅት ነው። ጠላቶቹ ያስቀመጡበትን እንቅፋቶች ለማለፍ አቅም እንዳለው የሰሞኑን ውዥንብርና የጠላቶቹን ቁማር እያለፈበት ያለው መንገድ ሁነኛ ምስክር ነው።

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s