አጋጥሞ በነበረው የፀጥታ ችግር እጃቸውን ያስገቡ አካላት በህግ ሊጠየቁ ይገባል – የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ

ባሳለፍነው ሳምንት በሀገሪቱ አጋጥሞ በነበረው የፀጥታ ችግር እጃቸውን ያስገቡ አካላት በህግ ሊጠየቁ እንደሚገባ የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የበላይ ጠባቂ አሳሰበ።
የኢትዮጵያ የሀይማኖት ተቋማት ጉባኤ የበላይ ጠባቂ አባቶች ወቅታዊ ጉዳዮችን አስመልክቶ በዛሬው እለት መግለጫ ሰጥቷል።

በመግለጫቸውን ባሳለፍነው ሳምንት በሀገሪቱ ተፈጥሮ በነበረው አለመረጋጋት በሰው ህይወት እና በንብረት ላይ የደረሰው ጉዳት በምንም መመዘኛ ተቀባይነት የሌለው መሆኑን አስታውቋል።

ግጭቶቹ ከሰብአዊ ፍጡር በማይጠበቁ ድርጊቶች የዜጎች ህይወት እያለፈ ንብረትም እየወደመ መሆኑንም በመጥቃስ ጉባዔው፥ ተግባሩ በየትኛውም ሀይማኖት የተወገዘ እና የተጠላ መሆኑን ገልጿል።

የፀጥታ ችግሩን ሽፋን በማድረግ ግጭቱን ወደ ሀይማኖት ግጭት ለመቀየር የተደረገው ጥረትም በየትኛውም ሀይማኖት ዘንድ ተቀባይነት የሌለው መሆኑንም ጉባዔው አስታውቋል።

የፀጥታ ችግሩ ሃይማኖታዊ ገጽታ እንዲላበስ በማድረግ የሃይማኖት ተቋማትን እና የሃይማኖት መሪዎች ከጉዳዩ ጋር ግንኙነት የሌላቸው ንፁሐን ወገኖች በተለይም ሕፃናትና ሴቶች ፣እናቶች እንዲሁም አረጋውያንን ሠለባ ያደረገ
ጥቃት መፈፀሙም በመግለጫው ተነስቷል።

ሃይማኖታዊ ገጽታ እንዲላበስ በማድረግ እየተካሔደ ያለው ዘመቻ በሁሉም ሃይማኖቶች ተቀባይነት የሌለው ከመሆኑም በላይ ፍፁም ወንጀል በመሆኑ ሃሳቡና ተግባሩን እንደሚያወግዙት አስታውቀዋል።

በዚህ መሠሉ ተግባር ላይ የተሠማሩ ግለሰቦችም ሆኑ ቡድኖች ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ ያሳሰበው የበላይ ጠባቂው፥ በሰላም መደፍረሱ እጃቸውን ያስገቡ አካላት የሚመለከተው የፍትህ አካል በህግ ተጠያቂ ሊያደርጋቸው እንደሚገባም አሳስቧል።

መግለጫው አክሎም፥ የክርስትና እና የእስልምና ሃይማኖቶች በኢትዮጵያ ለዘመናት በመከባበርና በሰላም አብረው የኖሩ ወገኖች መሆኑን በመጥቀስ፥ የየሃይማኖቶቹ አስተምህሮም ሰላምን፣ መከባበርን፣ ፍቅርን እና በማኅበራዊ ትስስራችን ወንድማማችነትን እንድናፀና ያስተምራል፤ በአንፃሩ ጥላቻና ግጭት በሁሉም ሃይማኖቶች የተወገዙ ናቸው፤ በመሆኑም አሁን አሁን የሚታየውን ሀገራዊ ውጥረት ከሃይማኖት ጋር ለማያያዝና ሽፋን ለማድረግ የሚደረገው ሙከራ የየሃይማኖቶችን መሠረታዊ አስተምህሮ ካለመገንዘብ ወይም ከጭፍን ወገንተኛነት የመነጨ ስሜት መሆኑን በመረዳት ክርስቲያኖችም ሆኑ ሙስሊሞች እርስ በርስ በመደጋገፍ የሀገራቸውንና የየአካባቢያቸውን ሰላም በጋራ ነቅተው እንድትጠብቁም ጠይቋል።

የሀገሪቱ ብሄር ብሄረሰቦች እና ህዝቦች የረጅም ዓመታት አብሮ የመኖር እሴት ለጥፋት ሳይሆን ለፍቅር እና ለወንድማማችነት መንገድ የሚከፍት መሆኑንም ገልጿል።

በኢትዮጵያውያን መካከል መጥፎ ጠባሳ እየጣለ ያለው ሰሞናዊ ግጭት ከእምነትም ሆነ ከአብሮ የመኖር እሴቶች እና እሳቤዎች ጋር በእጅጉ የሚቃረን በመሆኑ ሁሉም ኢትዮጵያውያን እና አማኞች ለሰላም እና ለአንድነት ሊተጉ እንደሚገባ ጠይቋል።

የሁሉም ሀይማኖት ተከታዮች ፊታቸውን ወደፈጣሪያቸው በማዞር በሀገሪቱ ሰላም እንዲሰፍን ፀሎት እንዲያደርጉም የሀይማኖት ተቋማት ጉባዔ ጥሪ አቅርቧል።

የፌዴራልና የክልሎች መንግስታት ሀገርንና ሕዝብን ለመምራትና ለማስተዳደር የሚጠይቀውን ከፍተኛ ኃላፊነትና አደራ ተቀብላችሁ ሀገራችሁንና ወገናችሁን እያገለገላችሁ መሆኑ ይታወቃል ያለው ጉባዔው፥ ዘላቂ ሰላምንና ብሔራዊ መግባባትን በማጠናከር እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የበላይ ጠባቂ አባቶች በተፈጥሮ በነበረው አለመረጋጋት እና ግጭት ምክንያት የሰዎች ህይወት በማለፉ የተሰማቸን ሀዘን የገለጹ ሲሆን፥ ለሟቾች ቤተሠቦች፣ ወዳጅ ዘመዶች በሙሉ መጽናናትን ተመኝተዋል።

እንደሀገር እየታየ ያለው ያለመረጋጋት እና የግጭት አዝማሚያ ተወግዶ ችግሩ በዘላቂነት እንዲፈታና ወደሰላማዊ ሁኔታ እንዲመለስ፣ ሁከትንና ግጭትን ከሚያባብሱ ሀሳቦችና ድርጊቶች በመታቀብ ሁሉም የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲወጣም ጠይቀዋል።

ኤፍ.ቢ.ሲ

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s