ዛሬም የሀገር ያለህ! የሕዝብ ያለህ! – (ኢትዮጵያችን) ልሳን

የአንድ ሀገር! አንድ ሕዝብ! ኢትዮጵያችን ሕዝባዊ ንቅናቄ (ኢትዮጵያችን) ልሳን

ኢትዮጵያችን ቅጽ 4 ቁጥር 1                                                     ጥቅምት 17 ቀን 2012 ዓ.ም.

ዛሬም የሀገር ያለህ! የሕዝብ ያለህ!

የድምጽ ቅጂውን ለማድመጥ እዚህ ይጫኑ https://www.youtube.com/watch?v=0LGrl5BLR2s )

“ፍቅር ያስታግሣል፣ ፍቅር ያስተዛዝናል፣ ፍቅር አያቀናናም፣ ፍቅር አያስመካም፣ ፍቅር አያስታብይም፣ ብቻዬን ይድላኝ አያሰኝም፣ አያበሳጭም ክፉ ነገር አያሳስብም፤ ከእውነት ጋር ደስ ይለዋል፤ እንጂ ስለ አመፃ ደስ አይለውም፤ ሁሉን ይታገሳል፣ ሁሉን ያምናል፣ ሁሉን ተስፋ ያደርጋል፣ በሁሉ ይጸናል።” የመጀመሪያይቱ የሐዋርያው የጳውሎስ መልእክት ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች ምዕ. ፲፫ ቁ. ፬-፯

በቅድሚያ በመላው ሀገራችን የተለያዩ አካባቢዎች በቅርቡ በተነሳው የጀዋር መሀመድ ቄሮዎችና ዘረኞች ዱላ ሕይወታቸውን ላጡ ወገኖቻችን የተሰማንን እጅግ ጥልቅ ሀዘን እንገልጻለን፡፡ ቤተሰቦቻቸው፣ ወዳጅ ዘመዶቻቸው፣ እንዲሁም መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ በዚህ ዘግናኝና አሳፋሪ ድርጊት ሳትደናገጡ እምነት፣ ተስፋና ጽናት ተላብሳችሁ ሀገርና ሕዝብ ለማዳን “የሀገር ያለህ! የሕዝብ ያለህ!” እንባባል፡፡

ሀገራችንን የተለያዩ ቋንቋ ተናጋሪ ጎሳዎች/ነገዶች ስብስብነቷ ነው ኢትዮጵያ ያሰኛት። አማራ  እኔ ኦሮሞ አይደለሁምና የኢትዮጵያ ክፍል አይደለሁም ቢል ይህን በማለቱ የኢትዮጵያችን ግዛት መሆኑ ይቀራልን? ኦሮሞ እኔ ትግሬ አይደለሁምና የኢትዮጵያ ግዛት አይደለሁም ቢል ይህን በማለቱ የኢትዮጵያ ግዛት መሆኑ ይቀራልን? ሀገር ሁሉ ትግራይ ቢሆን አፋር ወዴት በተገኘ? ሁሉም አፋር ቢሆን ሲዳማ ወዴት በተገኘ? ይሁን እንጂ የተለያዩ ቋንቋ ተናጋሪዎች ጎሳ/ነገዶችን ኢትዮጵያ ሀገራችን አንድ አድርጋ ይዛለች። ሁሉም አንድ ብሄር/ነገድ/ጎሳ ቢሆኑስ ኢትዮጵያችን ወዴት በሆነች? ዳሩ ግን ጎሳ/ነገዶች ብዙዎች ናቸው ሀገር ግን አንድ ናት፤ ኢትዮጵያ። ትግሬ ቤኒ ሻንጉልን አታስፈልገኝም ሊለው አይችልም ወይም ኦሮሞ ደግሞ ደቡብ ህዝብን አታስፈልጉኝም ሊላቸው አይችልም። እንደውም ጎልተው ያልታዩ “ደካሞች” የሚመስሉ  የኢትዮጵያችን ጎሳ/ነገዶች ይልቁን የሚያስፈልጉ ናቸው። ከሀገራችን ጎሳ/ነገዶች ያልከበሩ ሆነው የሚመስሉን በሚበዛ ክብር ልናለብሳቸው ይገባል። በሁሉም ጎሳ/ነገዶች ከቶም ልንኮራና  ክብር ልንሰጥ እያንዳንዱ ጎሳ/ነገድ ሃላፊነት ሊኖረው ይገባል። ጎሳ/ነገዶች እርስ በርሳቸው በትክክል ይተሳሰቡ ዘንድ እንጂ በዘርና ቋንቋ መለያየት፣ ድንበር ማስመር እንዳይሆን ለተጎዳው ጎሳ/ነገድ የሚበልጥ ክብር፣ ትኩረት እየተሰጠ ሁሉንም አገጣጥመን በአንድ ኢትዮጵያ! በአንድ ሀገር! በአንድ ሕዝብ! ተጋግዘን መኖር ይገባናል፡፡ አንዱ ጎሳ/ነገድ ቢሰቃይ ሁሉም ጎሳ/ነገዶች ሁሉ ከእርሱ ጋር ይሰቃያሉ፣ አንድ ነገድ/ጎሳ ቢከበር ሁሉም ጎሳ/ነገዶች ሁሉ ከእርሱ ጋር ደስ ይላቸዋል።  ሁላችንም የኢትዮጵያ ልጆች ነንና የዚህ ጊዜ ኢትዮጵያችን ትበለጽጋለች፣ ታብባለች። ሁሉም ተደጋግፈው ያሉ ናቸውና አንዱን ከሌላው ገንጥሎ ሀገርም አይኮን፤ ኢትዮጵያም አይባል፤ አብሮ መውደቅ እንጂ።

ለሁላችንም ዋልታና ምሰሶ ኢትዮጵያችን ብትሆንም ኦሮሞ ያለ አማራ ቅጠሉ የረገፈ ተክል ነው፣ ትግሬ ያለ ኦሮሞ መሠረቱ ይናጋል፣ አማራ ያለ ሁሉም ጉራ ብቻ ነው፡፡ ኢትዮጵያ እንደ ሀገር ለዘላለም ትኑር! ስንል ኦሮሞን አሻም አሰኝታ፣ አማራን አስፎክራ፣ ትግሬን አስጨፍራ፣ ጉራጌን ቆጮ ብላ፣ በባሌ ሶፎሞር ኮርታ፣ ሐረር ግምብን አጠንክራ፣ ግመሏን ለአፋር አደራ ሰጥታ፣ አዲስ አቤን እምብርቷ አርጋ፣ በእስላምና ክርስቲያኑ ፀሎት ተጠብቃ ሌላም ሌላ እንደሚሆን ልንረዳ ይገባናል።

በኢትዮጵያ ሀገራችን የነፃነት ጮራ ይፈነጥቅ ዘንድ፣ ሕዝብ የሰውነት መብቱ ይከበርለት፣ በጥቂቶች ስግብግብነት በረሀብ እንዳይቀጣ፣ እንደ ቅደም ተከተላቸው በትምህርት፣ በሥራ፣ በህክምና እጦት እንዳይደነቁር፣ እንዳይቦዝን፣ ለበሽታ እንዳይዳረግ ሕዝብና ወጣቱ በትንሹ ለግማሽ ምዕተ ዓመት ታግለዋል። እጅግ ጎልቶ የወጣው የወሎ ረሃብ ለዘውድ ሥርዓት መውደቅ የደመቀ ምክንያት ሆኖ ዑ! ዑ! ያሰኘውን ደርግ አስከትሎ ሀገራችን አንድ ትውልዷን አጣች። ለትሻል የታገለን ትውልድ ትብስ ክላሿን አቀባብላ ለቀመችው። የደርግ ልቅ ያጣ ጭፍጨፋና ጦረኝነት ያስመረረው ሕዝብ ዕድሜውን አሳጥሮት ተገላገልኩ ሳይል ሕዝብን በቋንቋና በዘር ከፋፍሎ የሚያባላ፣ የሀገር አንድነት ተረት የሆነበት፣ የሀገር ያለህ! የሕዝብ ያለህ!” የሚያሰኝ ትባባስ ዘረኛ አገዛዝ ሀገር እያመሰ ይገኛል።

መጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ.ም. በተሃድሶ “ለውጥ” ስም ኢሕአዴግን ሊያስቀጥሉ የጠቅላይ ምኒሥትርነቱን ቦታ የተረከቡት ዶክተር ዐቢይ አሕመድ የህወሓት/ኢሕአዴግን የመጨረሻ ምዕራፍ አስፈፃሚ እንዳይሆኑ ልናስገነዝብ እንወዳለን። ጠ/ሚሩ እሰየው ተብለው ያልተጨበጨበላቸውን ያህል “ይህችን ሀገር ወዴት እየወሰዷት ነው?” ጥያቄ እያጫሩ እንደሆን ማስገንዘብ እንወዳለን። ይህንን ስንል አየር የሞቀውን፣ የቤተ መንግሥት ሳይሆን የአደባባይ ምስጢር፣ በመላ ሀገሪቷ እያንኳኳ ያለውን ዱላ ለተመለከተ፤ መንግሥት እራሱ የዱላው አቀባይ መሆኑን ቢጠቁም አያስደንቅም። ንብረት ሲዘረፍ፣ ሲቃጠል፣ የሰው ልጅ ሲታረድ፣ ሲሰቀል፣ አብያተ ክርስቲያን ሲቃጠሉ፣ መንገድ ሲዘጋጋ፣ ምስማርና ዱላ ሲውለበለብ የአገዛዙ ፌደራል ይባል ልዩ ኃይል ዳር ቆሞ ሲታዘብ ላየ ለውጡ ለካ ሥርነቀልነቱ ሀገር ለመበተን እንደሆነ ቢጽፍ፣ ቢናገር ምን ያስደንቃል? አዎ! ሲጀመርም የኢሕአዴግን ሕገ መንግሥት ይዞ ለውጥ ሊያመጣ ለተነሳ ቡድን፤ አንቀጽ 39ን  ተግባራዊ ለማድረግ ቢሠራ ማድመጥ ያቃተን እኛው ነንና ወደ ተግባራዊነቱ ፍፃሜ ላይ ሲንደረደር ሀገር እንዳትፈርስ፣ ሕዝብ እንዳያልቅ ከተፈለገ፤ በኋላ ሳይሆን ዛሬውኑ “የሀገር ያለህ! የሕዝብ ያለህ!” እምንልበት የመጨረሻው ሰዓት ላይ እንገኛለን።

“የምትፈልጉትን ነገር ለማግኘት ድንጋይ መወርወር አያስፈልግም፣ በእርጋታና በትዕግሥት ከሄዳችሁ አያቅታችሁም” የተባለላቸው ዘረኞች ሰንደቅ ዓላማ ሲያቃጥሉ፣ የእኛ አይደላችሁም እየተባሉ ዜጎች ከቄያቸው ሲፈናቀሉ፣ የታዘበ መንግሥት “ኢትዮጵያ አትፈርስም” እያለ ሕዝብና ልጆቹ በየቀኑ ሲፈጁ እየሰማን፣ እያየን እንዴት “ግዴላችሁም” እንባላለን? እውን የኢሕአዴግ ውስኪ ጠጭዎች ከሆኑ ይህን የሚያስደርጉት አሁንም የመንግሥት አውታር በእጃቸው ነውና ለውጡ ከሰንደቅ ዓላማ አልፎ ሀገርና ሕዝብ ሊያቃጥል አኮብኩቧልና “የሀገር ያለህ! የሕዝብ ያለህ!” እንላለን።

ኢትዮጵያ ሀገራችን ዛሬ ወደ እርስ በርስ መተላለቅ እንዳትገባ እጅጉን የሰጋንበት ወቅት ነው። የእርስ በእርስ አልነው እንጂ በቀጥታ ለመናገር የእልቂቱ ጅራፍ ከአንድ ወገን እየጮኸ እንደሆነ በዚህ አንድ ዓመት ተኩል ጉዞ በተለይ ደግሞ ከሰሞኑ የሀገሪቷ ሁኔታ መረዳት ያቃተው ጠ/ሚሩ እንዳሉት ቃሉን እንድገመውና “የደነቆረው” ኢሕአዴግና ዘረኛው ቡድን ብቻ ነው። በግልጽ ለመናገር ኦርቶዶክስ ሃይማኖት፣ አማራና ምኒልክ ታሪክ ላይ ያነጣጠረው ኢትዮጵያን የመበታተን ዘመቻ ሀገር ላይ እየጨፈረ፣ ሕዝብን እግዚዮ እያሰኘ በአለበት ወቅት የመደመር ፍልስፍና ሀገርና ሕዝብ እየቀነሰ መሆኑን ልንገነዘብ ይገባናል።

ኤርትራና ኢትዮጵያን አስታርቀው የኖቤል ተሸላሚ የሆኑት ጠ/ሚር ምነዋ ኦሮሞን፣ አማራ፣ ትግሬን፣ ምሥራቁን፣ ደቡቡን፣ አዲስ አበቤውን አንድ የማድረግ ጥበቡ ተሳናቸው? ሥልጣን እንደጨበጡ የጎረፈላቸው ከኖቤልም ኖቤል የሆነ የዕልልታና የጭብጨባ ሽልማት ለሀገር አንድነት ለሕዝብ ደህንነት እንደነበር ምነዋ አልሰማ አላቸው? ይህን ሕዝባዊ ሽልማት ወዲያውኑ ተጠቅመው ዘረኝነት ላይ አነጣጥረው፣ አንቀጽ 39ን ቀደው ቢሆን አክሊላቸው እምዬ ኢትዮጵያ ነበረች። “እናንት ውስኪ ጠጪ ኢሕአዴጎች የተራቡ ሕፃናት እንዳሉ አትዘንጉ” ያሉት ጠ/ሚር አገዛዞ ፈቃድ ሳይኖረው ዱላ በምስማር ይዞ ሰልፍ ለሚወጣው፣ ብሎም ባንክ ሲዘረፍ፣ ንብረት ለሚያቃጥለው፣ ነዋሪ ለሚገድለው ዝምታ ሲለገሰው ምነዋ በሥነ ሥርዓትና በአግባቡ ለጥቅምት 2 ቀን 2012 ዓ.ም. ለሰልፍ አቤቱታ ያቀረበውን የአዲስ አበባ ሕዝብ አስራቡት ቢባሉ ምላሾ ምን ይሆን?

“አዲስ አበባ ኬኛ” በሚልና በማስፈራራት የ“ኦሮሚያ” ለማድረግ የሞከረውን ኃይል “ባልደራስ” ከአዲስ አበባ ሕዝብ ጋር ባይጋፈጥ ዛሬ ሌላ አፀያፊ ታሪክ በተሠራ። “ባልደራስ” ላይ ጦርነት ታወጀ። ቀጠለ በመፈንቅለ መንግሥት ተውኔት በባህርዳርና አዲስ አበባ ካለቁት ወገኖች በቀጣይነት አማራው ላይ ያነጣጠረ እስርና ፍጅት እውን ሕዝብ እያደመጠው፣ እየታዘበው እንደሆን ከተረዳነው ለውጥ አራማጁ ሕዝብን ለቂምና ተቃውሞ እየጋበዘ እንደሆነ ሊረዳው ይገባል። የአዲስ አበባውን የ “ባልደራስ” አመራርንና አባላትን ማዋከብ፣ ማሠር በአዲስ አበባ ሕዝብ ብቻ ሳይሆን በሀገር ወዳዱ የኢትዮጵያ ሕዝብ ዘንድ እየተሰማ፣ እየታየ ያለ የየዕለት መነጋገሪያ እንደሆነ ለውጥ አራማጆች ሰምታችኋልን? እውን ለውጥ ማራመድ ኢሕአዴግ/ህወሓት ያሠረውን ፈትቶ ሥልጣን ሲደላደል አትቃወሙኝ ብሎ ሙዚየም ሊሆኑ የታሰቡ እስር ቤቶችን ሥራ አለማስፈታት ከሆነ ትርግሙ አዬ! ዴሞክራሲ፣ ድንቄም ለውጥ ያሰኛል።

ደርግ እርጉዝ ማሠር ብቻ ሳይሆን ለመግደሉ ዳሮ ነጋሽ ምስክር ናት፣ የኢሕአፓው ብርሃነ መስቀል ረዳ ባለቤት ታደለች ኃይለሚካኤል ነፍሰ ጡር ሁና እስር ቤት መገላገሏ ከታሪክ ማህደር ይገኛል። ወያኔም የእስክንድር ነጋን ባለቤት ሰርካለም ፋሲል በነፍሰ ጡርነቷ ሳያዝን እስር ቤት እንድትገላገል ፈርዶባታል። እና! እናማ ታሪክ ሲደጋገም ዛሬም የጄነራል አሳምነው ጽጌ ባለቤት ወ/ሮ ደስታ አሰፋ ነፍሰጡርነታቸው እየታወቀ በእሥር ይማቅቃሉ። አይ! የሴቶች መብት አስጠባቂ ለውጥ አራማጅ ቢባል “ሃቅ አያንቅ” ካልሆነ በቀር እውነቱ ይህ ነው።

ውድ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሆይ!

የዛሬ 123 ዓመት ኢጣሊያን ኢትዮጵያን ሊወር ሲነሳ እምዬ ዓፄ ምኒልክ ይህን ብለው ነበር

እግዚአብ በቸርነቱ እስካሁን ጠላት አጥፍቶ አገር አስፍቶ አኖረኝ፤ እኔም እስካሁን በእግዚአብሔር ቸርነት ገዛሁ፡፡ ከእንግዲህ ብሞትም ሞት የሁሉም ነውና ስለእኔ ሞት አላዝንም፡፡ ደግሞ እግዚአብሔር አሳፍሮኝ አያውቅም፤ ወደፊትም ያሳፍረኛል ብዬ አልጠራጠርም፡፡ አሁንም አገር የሚያጠፋ፤ ሃይማኖትን የሚለውጥ፣ በፊት እግዚአብሔር የወሰነልንን ባህር አልፎ መጥቷል፡፡ እኔም የአገሬን ከብት ማለቅ፤ የሰውን መድከም አይቼ እስካሁን ዝም ብለው ደግሞ እያለፈ እንደፍልፈል መሬት ይቆፍር ጀመር፡፡ አሁን ግን በእግዚአብሔር ረዳትነት አገሬን አሳልፌ አልሰጠውም፡፡ የአገሬ ሰው ከአሁን ቀደም የበደልሁህ አይመስለኝም፡፡ አንተም እስካሁን አላስቀየምኸኝም፡፡ ጉልበት ያለህ በጉልበትህ እርዳኝ። ጉልበት የሌለህ ለልጅህ፣ ለምሽትህ፣ ለሃይማኖትህ ስትል በሃዘንህ እርዳኝ፡፡ ወስልተህ የቀረህ ግን ኋላ ትጣላኛለህ፡፡ አልምርህም፡፡ ማርያምን ለዚህ አማላጅ የለኝም። ዘመቻዬ በጥቅምት ነውና የሸዋ ሰው እስከ ጥቅምት እኹሌታ ወረይሉ ከተህ ላግኝህ።

ይህ መልዕክት አሁን ኢትዮጵያችን ባለችበት ወቅታዊ ሁኔታ ወደ አላስፈላጊ እልቂት እንዳታመራ ካስፈለገ ድጋሚ ሊያቃጭልብን ይገባል። የጥንቱ ባህር አልፎ የመጣ ሲሆን የአሁኑ በሀገር በቀልና በባዕዳን ጥምር ተልዕኮ የተቀነባበረ መሆኑ ነው። ዛሬ ሀገር ሊያፈርስ፣ አረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀይ ሰንደቅ አላማችንን እያቃጠለ የመጣው ኃይል፣ ቤትና ንብረት ሲያቃጥል እያየን ነው፣ ዱላና ሜንጫ የንፁሐንን ሕይወት እየቀጠፈ ነው። ሕዝብ ላይ የተሠነዘረው ጥቃት ተጀምሯል። በመላው ሀገሪቷ ይህ ዕልቂት እንዳይዛመትና ሙሉ በሙሉ ይቆም ዘንድ፣ እጅግ ዘግናኝና አሳዛኝ ፍጅት በኢትዮጵያችን እንዳይከሰት የሃይማኖት አባቶችና አማኞች በፀሎት፣ የብዙሃን ማህበራትንና ፖለቲከኞች በአንድነት፣ መላው ሕዝብ በጋራ ለእራሱና ለሀገሩ ሲል ነቅቶ መጠበቅ የሚገባው ወቅት ላይ ደርሰናልና “የሀገር ያለህ! የሕዝብ ያለህ!” እንባባል።

ሁኔታዎች ከቁጥጥር ውጭ ሁነው ዘግናኝ እልቂት በሀገራችን ላይ ከተከሰተ በኋላ “ይህ ቢሆን ኑሮ” አዋጭ አይደለም፡፡ ንፁሓን ወገኖቻችን እያለቁ የምናበቅለው ፀፀት እጅጉን ከባድ ነውና አሁኑኑ ሀገርና ሕዝብ ለማዳን እንዘጋጅ።

ህወሓት ለ28 ዓመት የተከለው የዘረኝነት ችግኝ ዛሬ ፍሬ አፍርቶ በተለይ የኦሮሞን ጥያቄ የትውልዱ አስመስሎታል ቢባል ሚዛን ይደፋል። ይህ የሀገርና ሰንደቅ ዓላማ ጥላቻ ገና ከጥንስሡ በተለይ በየትምህርት ቤቱ፣ በየመንደሩ ብሎም በቤተሰብ ደረጃ የተካሄደው ወያኔያዊ ዘመቻ ዛሬ የኦሮሞ ወጣቶችና ጎልማሶች ወገኖቻችንን ያሳተ ቢመስልም የአንድነት ኃይሉና የኢትዮጵያ ሕዝብ “የሀገር ያለህ! የሕዝብ ያለህ!” ተባብሎ ከተነሳ ዘረኝነትን አምክኖ ከኦሮሞ፣ ከትግራይ፣ ከአማራ በጥቅሉ ከደቡብ፣ ከምሥራቅ፣ ከምዕራብ፣ ከሰሜን፣ ከአዲስ አበባ ሕዝባችን ጋር ተቃቅፈን ዘመቻችን ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን ለተላበሰች ኢትዮጵያ፣ ሁሉንም ልጆቿን በአንድነትና በጋራ ለምትቃኝ ሀገራችን ዕድገትና ብልጽግና እንደሚሆን ጥርጣሬ አይግባን። እኛ፣ ሁላችን አንድ ከሆንን ኃይልና ሥልጣን የሠፊው ሕዝብ መሆኑን እናሳያለንና ዛሬም “የሀገር ያለህ! የሕዝብ ያለህ!” እንባባል።

ለተከበሩ ጠ/ሚር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ

በቅድሚያ በቅርቡ የ 2012 ዓ.ም. የኖቤል ተሸላሚ በመሆኖ እንኳን ደስ አሎት እንላለን። ሽልማቱን የሠጠው አካል ምክንያቱን የኤርትራና ኢትዮጵያ ሀገሮችን ከማቀራረብ ጋር ማያያዙን አድምጠናል። በአንድ ዓመት ከስድስት ወር በኢሕአዴግ አባልነቶና የሀገሪቷ ጠቅላይ ሚንስትርነት ያበረከቷቸው በጎ ጎኖች ቢኖሩም ሀገራችንና ሕዝባችን በየቀኑ እያጋጠማቸው ካለው ሰቆቃ፣ የፍርሃት ኑሮ፣ የኑሮ ውድነት፣ ወዘተ አንፃር እጅጉን እያዘንን ነው።

አሁን ሀገራችን ያለችበትን ተጨባጭ ፖለቲካዊ ሁኔታ ስንመለከተው እውን የመንግሥት ኃይልና ሥልጣን ካለዎት ዝምታ አዋጭ አይደለም፡፡ ሰሞኑን በጀዋር መሀመድ አስተባባሪነት ቄሮ በሚባሉ ዘረኛ ቡድኖች በተለይ አማራውና ቤተ ክርስቲያን ላይ ያነጣጠረ ፍጅትና ቃጠሎ ሲካሄድ ዝምታዎ አስገራሚና አስተዛዛቢ ነው፡፡

ከዓመት በፊት በአዲስ አበባ ዙሪያ ለገጣፎ በተነሳው ዕልቂት አልሰማሁም ያሉትን በቀጣይነት እየደጋገሙት በሚመስል ደረጃ የሕዝብና የልጆቹ እልቂት ከወሬ በዘለለ የወሰዱት መንግሥታዊ እርምጃ አልታየም፡፡ ሕዝብ እየታረደ ምላሹ “ኢትዮጵያ ታላቅ ሀገር ነች” ሳይሆን ለታላቅነቷ አጥፊዎችን፣ አሸባሪዎችንና ገዳዮችን ወደ ፍርድ ማቅረብ ነው፡፡ ከመንግሥት በላይ ሀገር እያመሰና ማን ተናግሮኝ ባዩ ጀዋር መሀመድን ከለላና ጥበቃ ሰጥቶ ደም ማፍሰስ እጅጉን አሳፋሪ ነው፡፡

በተጨማሪ፦

  • በሩሲያ ጉብኝቶ ወቅት በሀገራችን በተለያዩ አካባቢዎች የደረሰውን እልቂት ሲሰሙ በአፋጣኝ ጉብኝትዎን አቋርጠው አፋጣኝ አመራር መስጠት ሲገባዎ ምንም እንዳልተፈጠረ ጉብኝቶን ቀጥለዋል፣
  • ኢትዮጵያም ከተመለሱ በኋላ ይህንን በርካታ ቤተሰቦችንና ሕዝብን ያስተከዘ ሀዘን በቴሌቪዥን መስኮት ቀርበው ሀዘኔታዎን መግለጽ ብቻ ሳይሆን መንግሥት ሊወስድ የሚገባውን አፋጣኝ እርምጃ ሊያሳውቁ አልደፈሩም፣
  • የቄሮ መሪ ጀዋር መሀመድ በሀገሪቱ ያለው መንግሥት ሁለት ነው ከማለት አልፎ ሀገሪቱን ለእርስ በርስ ዕልቂት እያዘጋጀና የኦሮሞ ወጣቶችን በዘረኝነት የጥፋት ዘመቻ ሲቀሰቅስ ቤትና ጥበቃ ሰጥተው ይንከባከቡታል፣
  • ጅዋር መሀመድ በድምጽ የተቀዳ መንግሥታዊ መረጃ አለኝ ሲል ከመንግሥት አካላት ጋር እየተመሳጠረ የሚያገኛቸው መረጃዎች እንዳሉ በአደባባይ እራሱ ላይ ሲመሰክር ድርጊቱ ሊታይ የሚገባው ወንጀል መሆኑን ሊገነዘቡት በተገባ፣
  • የአዲስ አበባ ወጣቶች ሲዋከቡ፣ እነ እስክንድር ነጋና የ“ባልደራስ” አባላት በሰላማዊ መንገድ ለጠየቁት ሰላማዊ ሰልፍ ክልከላ፣ በሚያደርጉት ስብሰባ በቄሮ ቡድኖች ወከባ ሲደርስባቸው እየሰሙ ዝምታን መርጠዋል፣

ብዙ መዘርዘር ይቻላል፡፡

አንድ ሀገር! አንድ ሕዝብ! ኢትዮጵያችን ሕዝባዊ ንቅናቄ” ሥልጣን እንደያዙ ድጋፋችንን ብንሰጥዎም “የቀን ጅብ በግ ላይሆን” ብለን ከጠቆምኖት ኢትዮጵያችን ቅጽ 3 ቁጥር 1 ልሳናችን (http://www.ethiopiachen.org/images/pdf/020511_1H1H-Ethiopiachin-Vol-3-No-1.pdf) ጀምሮ ድጋፋችንና ትችታችን ማድረግ ያለቦትንና ሊያጋጥሙ የሚችሉ ጥፋቶችን በመጠቆምና ያላመንበትንም በመቃወም ነበር። አንዳንድ ሰዎችና በተለይ እንደ ምሁርነታቸው ለትንሽ ጉዳይ የሚፈነጥዙ እስቲ እንያቸው፣ ጊዜ ስጧቸው፣ አትቃወሟቸው አባባል ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሳየን ያለው አዛውንትን፣ ህጻናትን፣ ወጣቶችን በጥቅሉ ዜጎችን እየቀጠፈና አውላላ ሜዳ ላይ እየበተነ ለመሆኑ እማኝ አያስፈልገውም፡፡ ግራና ቀኙን ማየት የተሳናቸው አንዳንድ ምሁራን ከሙያቸው ባሻገር በፖለቲካው መስክ እንደ ትላንቱ ዛሬም ሲያበላሹ ይታያሉ። ዛሬ ጎልቶ ለወጣው አስከፊ ዘረኝነት በአለፈው 28 ዓመት የብዕራቸው አሻራና የማጋጋል ድምፃቸው አስተዋጽዖ እንዳለው ዕድሜ ለሥልጣኔ በኮምፒዩተር መረጃ ለወደፊት አጥኝዎች “እነማን ነበሩ” ዝግጅትና የታሪክ ተመራማሪዎች የደለበ ሠነድ ነው።

ክቡር ጠ/ሚር የኢትዮጵያን አንድነት ለማስጠበቅ እጅግ ብዙ ብለዋል። እኛም ስለ ሀገር አንድነት፣ ዘርንና ቋንቋን ተገን ስለ አደረገ አከላለል አደገኝነት፣ ስለ ኢሕአዴግ ሕገ መንግሥት ማብቃት፣ ወዘተ ብዙ ብለናል፡፡ ይህ በቀደምት ትንታኔያችን እንደተጠበቀ አሁን ይችን ሀገር በአግባቡ እንደ መንግሥትነትዎ ያድኑ አለበለዚያ ለተማረረው ሕዝብ ይተዉለት፡፡ ሕዝባችን እንኳን ለሀገር ውስጥ አሸባሪ አይደለም በታንክና በአየር የመጣበትን ወራሪ ያሳፈረ እንደመሆኑ የሠራውን አኩሪ ታሪክ ዛሬም እንደሚደግመው ጥርጥር የለንም፡፡

የእርሶ “ኢትዮጵያ” ፉከራ ጉያዎ የወሸቁትን ጀዋር መሀመድና ሌሎች ሀገር በታኝ ዘረኞችን ካልተመለከተ ምኑን ሀገር ተኮነ? ምድር ላይ የምናየው ለእኛም ሆነ ለኢትዮጵያ ሕዝብ የተለየ ነው። ገና ሥልጣን እንደጨበጡ ኢትዮጵያን በ10 ዓመት ከአፍሪካ በዕድገትና በሥልጣኔ አውራ እናደርጋታለን ብለዋል፡፡ ዛሬም ዓመት ከስድስት ወር ቢቀነስለትም፤ ነገም አሥር ዓመት እየተባለ እንደማይቀጥል እርግጠኞች ነን። ይህ የዕድገት ትልሞ እሰየው ቢያሰኝም ዛሬ መብላት ያቃተው ቤተሰብ፣ ከምግብ እጦት የተነሳ ትምህርት መማር ያቃታቸው ሕፃናት፣ እጅግ የናረው የኑሮ ውድነት አይዘገንኖትም? እስቲ ልጆቾን አንድ ቀን ምሳ እንዳይበሉ ያርጓቸውና ስሜቱን ያስቡት።

በቅርቡ ከአወጡት የመደመር ፍልስፍና ጋር ለ10 ዓመት እንደሚገዙ እርግጠኛ የሆኑ ይመስላል። መጪውን ምርጫ ሳይዘነጉት መደመር ፍልስፍናን ዘላለማዊ ሕይወት ሊላበስ የተፈለገ ይመስላል።  ተቀበሉትም አልተቀበሉት ዛሬ ኢትዮጵያችን የሚያሳስባት ከፊቷ የተደቀነባት የዘረኝነት አደጋ ነው። ሕዝባችን በቅድሚያ ውሎ ማደሪያ ሀገሩን ይፈልጋል፡፡ የአዲስ አበባን ነዋሪ ጨምሮ በመላው ሀገራችን የስጋትና የፍርሃት ኑሮ ሕዝቡን እያሳሰበ ነው። በየቦታው የሚፈናቀሉ፣ የሚገደሉ ቁጥራቸው እየጨመረ ነው። በእርሶ አገዛዝ ሰንደቅ ዓላማችን እየተረገጠና እየተቃጠለ ይገኛል። አብያተ ክርስቲያናት እየተቃጠሉ፣ ምህመናን እየተገደሉ ነው። “ከእንግዲህ በፖለቲካ አቋሙ የሚታሠር የለም” ያሉትን ዘንግተው ዛሬም ያለ ፍርድ በርካታ ዜጎች ቤታቸው እስር ቤት ሁኗል። ወደ የትኛውም የሀገሪቷ አካባቢ ለመንቀሳቀስ በስጋት በመሆኑ የሀገር ውስጥ የንግድ እንቅስቃሴ እየተዳከመ ለመሄዱ የሚታየው የኑሮ ውድነት ምስክር ነው። በጀዋር የሚመራው የቄሮ ቡድን ያለፍቃድ እንዳሻው ሰልፍና ስብሰባ ያደርጋል፤ በሌላ በኩል ደንብና ሥርዓት ተከትሎ ሠላማዊ ሰልፍ የሚጠይቁ “ባልደራሶች” ይከለከላሉ፣ መንገድ ይዘጋባቸዋል፣ በስብሰባቸው ላይም ይወረራሉ፤ እውን ይህ እንቅልፍ ይሆኖታል?

እጅግ በርካታ ጉዳዮችን ማንሳት ቢቻልም እውን ለእናት ሀገራችን ኢትዮጵያ ቅን ሀሳቢ እስከሆኑ ከማንም በላይ የሕዝብ ሀብት አሎትና ከግብጽ ሳይሆን ከዘረኝነት ጋር ፍልሚያ ለመግጠም ይጠቀሙበት ብለን ቀደም ሲል አሳስበናል ዛሬም እንላለን። አልተጠቀሙበትም እንጂ የኦሮሞ ህብረተሰብ አንድነቱን ፈላጊ ነው፣ የትግራይ ሕዝብ በኢትዮጵያዊነቱ ኩሩ ነው፣ ደቡብ ለሰንደቅ ዓላማው በአንድነት ይጠብቆታል፣ ሐረሬው፣ አፋሩ፣ ጋምቤላው፣ አማራው ዴሞክራሲያዊ መብቱን አይንፈጉት፣ ከረሃብ ያላቁት እንጂ በሀገሩና በአንድነቱ አይደራደርምና “የሀገር ያለህ! የሕዝብ ያለህ!” ብለው ኢትዮጵያና ሕዝቧ ከተደቀነባቸው አደጋ ያላቅቁ ዘንድ ለማሳሰብ እንወዳለን። ጊዜ ቆሞ አይጠብቅምና ተሽቀዳድመው ይሳፈሩበት። የመንግሥትነቱን ሥልጣን የመጠቀም ችግር ካለብዎትም በአፋጣኝ ለሕዝባችን ግልጽ ያድርጉለትና አሁንም በግል እያደረገ ያለውን መሰባሰብና መደራጀት አጠናክሮ ሀገርና ሕዝቡን ከእልቂትና ከጥፋት ያድን ዘንድ ይተባበሩት፡፡ ይህ ተግባራዊ ካልሆነ የአዲስ አበባ ወጣትም ሆነ በየአካባቢው ያለው ወጣትና ሕዝብ አቃጣዮችን፣ በድንጋይ፣ ሜጫና፣ ዱላ ገዳዮችን የመመከትና የመቋቋም ብሎም የማሸነፍ ታሪክ እንደሚሠራ በእርግጠኝነት ልንገልጽልዎ እንወዳለን፡፡ ያለውንና ያንዣበበውን አደጋ ተቀብሎና ለሕዝብ ይፋ አውጥቶ የሀገሪቷ አንድነት የሕዝባችን ደህንነት ቅድሚያ ይሰጠው ዘንድ “አንድ ሀገር! አንድ ሕዝብ! ኢትዮጵያችን ሕዝባዊ ንቅናቄ” ድምጻችንን እናሰማለን።

ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!!!

ፈጣሪ ኢትዮጵያን ይባርክ!!!

“አንድ ሀገር! አንድ ሕዝብ! ኢትዮጵያችን ሕዝባዊ ንቅናቄ”

ጥቅምት 17 ቀን 2012 ዓ.ም. (October 28, 2019)

ማሳሰቢያ ፡

  • ውድ ወገኖቻችን ይህንን «አንድ ሀገር! አንድ ሕዝብ! ኢትዮጵያችን ሕዝባዊ ንቅናቄ» «ኢትዮጵያችን» ልሳን በተለይ በሀገር ቤት ኮምፒዩተር የማግኘት ዕድል ለሌላቸው በማባዛት ታሰራጩት ዘንድ ቀና ትብብራችሁን በትህትና እንጠይቃለን።
  • «አንድ ሀገር! አንድ ሕዝብ! ኢትዮጵያችን ሕዝባዊ ንቅናቄ» መስከረም 8 ቀን 2009 ዓ.ም. እራሱን ይፋ ያደረገ ሕዝባዊ ድርጅት ሲሆን የንቅናቄውን ማንፌስቶና ፕሮግራም ethiopiachen.org ከሚለው ድረ ገጻችን ማግኘት ትችላላችሁ።

ስልክ ፡ 703 300 4302

ኢሜል ፡ ethiopiachen2009@gmail.com

ድረ ገጽ ፡ www.ethiopiachen.org , www.ethiopiachen.com

ምሥለ ገጽ ፡ 1H1H Ethiopiachin

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s