በአንድነት መቆም ሲያቅት እጅ ጠምዛዦች ይጠናከራሉ!

በአንድነት መቆም ሲያቅት እጅ ጠምዛዦች ይጠናከራሉ!

ለአንድ አገር የጥንካሬ መሠረቱ የሕዝቡ አንድነት ነው፡፡ ሕዝብ በአገሩ ጉዳይ የጋራ አቋም ኖሮት አንድነቱን በተግባር ማሳየት የሚሳነው ከሆነ፣ በውስጡ መከፋፈልና መለያየት እንዳለ ግልጽ ነው፡፡ ዝነኛው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት አብረሃም ሊንከን፣ ‹‹የተከፋፈለ ቤት ፀንቶ ሊቆም አይችልም፤›› እንዳለው፣ አገርም ልባቸው በከተፋፈለ ዜጎች ምክንያት መቆም ይቸግረዋል፡፡ ምንም እንኳ በሁሉም ነገር መስማማት ባይቻልም፣ ወሳኝ በሚባሉ ብሔራዊ ጉዳዮች ላይ መከፋፈል የአገርን ጥንካሬ ያዳክማል፡፡ ከዚህ ቀደም ኢትዮጵያዊያን የሚታወቁበት ልዩ መለያቸው አገራቸውን መውደዳቸው፣ ለአገራቸው ሲሉ ልዩነቶችን በማስወገድ አንድ ላይ መቆማቸውና ከራሳቸው በፊት የአገራቸውን ጥቅምና ደኅንነት ማስቀደማቸው ነው፡፡ የአገር ህልውና አስተማማኝ የሚሆነው ከራስ ጉዳይ በፊት የአገር ሲቀድም ነው፡፡ በዚህ ዘመን ግን በበርካታ ዘርፈ ብዙ ጉዳዮች ምክንያት በአገር የጋራ ጉዳይ ላይ እንኳን አንድ ላይ ለመቆም፣ ተነጋግሮ መግባባትም በጣም እየከበደ ነው፡፡ ‹‹የጋራ ታሪክ የለንም›› ከሚሉ አላዋቂዎች ጀምሮ በኢትዮጵያዊነት ላይ እስከሚያላግጡ መሰሪዎች ድረስ፣ ለማመን የሚከብዱ ጥልቅ የሆኑ ልዩነቶች እየታዩ ነው፡፡ በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚና በተለያዩ ማኅበራዊ ጉዳዮች ልዩነቶች መኖራቸው የግድ ቢሆንም፣ በጋራ ብሔራዊ ጉዳዮች ላይ መከፋፈል ለጥቃት ያጋልጣል እንጂ ፋይዳ የለውም፡፡ ሰላም፣ ዴሞክራሲና ብልፅግና ዕውን የሚሆኑት በመከፋፈል አይደለም፡፡ መከፋፈል የአጥቂ ሰለባ ያደርጋል፡፡

ኢትዮጵያዊያን የጋራ የሆኑ እሴቶቻቸውን አስጠብቀው ዘመናትን የተሻገሩት፣ ለአገራቸው በነበራቸው ጥልቅ የሆነ ፍቅር እንደነበር አይዘነጋም፡፡ በከባድ የጭቆና ቀንበሮች ውስጥ ሆነው እንኳ አገራቸውን በጋራ ሲጠብቁ ኖሩ እንጂ፣ አገራቸውን አንዴም በጠላት አስደፍረው አያውቁም፡፡ በታላቁ የዓድዋ ድል አከርካሪውን የተመታው ጣሊያን ከ40 ዓመታት በኋላ በሠለጠኑ ተዋጊዎች፣ በዘመናዊ የጦር መሣሪያና ድርጅት ተጠናክሮ መጥቶ ወረራ በፈጸመባቸው አምስት ዓመታት፣ አንድም ቀን ፋታ ሳያገኝ በሽምቅ ውጊያ ጀግኖች አርበኞች እንዳርበደበዱትና በመጨረሻ ተሸንፎ መውጣቱን ታሪክ የመዘገበው ሀቅ ነው፡፡ ይህ ታላቅ የአገር ፍቅር ከጥንት ጀምሮ እስከ ባድመ ጦርነት ድርስ በአንፀባራቂ ድሎች የታጀበ ነበር፡፡ ለኢትዮጵያ ሕዝብ የአንድነቱ ማሳያ ቋሚ ምስክርም ነው፡፡ ይህንን የመሰለ አንፀባራቂ ገድል በተሠራበት አገር ውስጥ ከአንድነት ይልቅ መለያየት፣ ከጋራ ጉዳዮች ይልቅ ቡድን ላይ ማተኮር፣ ኢትዮጵያዊነትን በማጣጣል ብሔርተኝነትን ማሟሟቅ፣ የዘመናት አብሮነትን ወደ ጎን በመግፋት መነጠልን ማበረታታት፣ ወዘተ ከመጠን በላይ እየተለመደ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት አገራዊ አንድነት እየተሸረሸረ ሸብረክ እየተባለ ነው፡፡ ታሪካዊው አንድነት ተሸርሽሮ ልዩነት ሲሰፋ፣ የዘመናት የአገር ባላንጣዎች አንገታቸውን ቀና አድርገው እጅ መጠምዘዝ ጀምረዋል፡፡

ኢትዮጵያ በታላቁ የህዳሴ ግድብ የኤሌክትሪክ ኃይል ለማመንጨት የጀመረችው ፕሮጀክት፣ በእልህ አስጨራሽ ውጣ ውረድ ውስጥ ስምንት ዓመታት አስቆጥሯል፡፡ በአምስት ዓመታት ይጠናቀቃል የተባለው ይህ ብሔራዊ ፕሮጀክት ውስጣዊ ችግሮች ቢያጋጥሙትም፣ በተለይ በግብፅ እየተጋረጠበት ያለው መሰናክል እንዲህ በቀላሉ የሚታይ አይደለም፡፡ ግብፅ በቅርቡ የውኃ አሞላሉ የአስዋን ግድብን መጠን ከ165 ሜትር በታች ዝቅ እንዳያደርግ ያቀረበችው አደገኛ ፕሮፖዛል፣ ምን ያህል ነገር ፈላጊነት የሚንፀባረቅበትና የእኛን የእርስ በርስ መከፋፈል አጋጣሚ በመጠቀም የቀረበ እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡ ይህ አልበቃ ብሎ አሜሪካና የዓለም ባንክ ወደ ውይይቱ እንዲመጡ ያደረገችበት እጅ ጥምዘዛም ቀላል አይደለም፡፡ እስካሁን ባለው መረጃ የኢትዮጵያ መንግሥት ቀደም ሲል ከነበረው አቋሙ የተለየ ነገር እንደሌለ ቢያስታውቅም፣ የአሜሪካና የዓለም ባንክ የውይይቱ አካል እንዲሆኑ መደረጉ ይጎረብጣል፡፡ የተፅዕኖው አድማስ እንዴት እየሰፋ መምጣቱንም  ማመላከቻ ነው፡፡ ለዓባይ ውኃ 87 በመቶ የምታበረክተው ኢትዮጵያ፣ ውኃውን በፍትሐዊ መንገድ የመጠቀም መብት ያላት ኢትዮጵያ፣ በግድቡ ላይ የሚነሱ አለመግባባቶች በቴክኒክ ባለሙያዎች ሙያዊ ምክክርና ምክረ ሐሳብ እንደሚፈቱ እምነት ያላት ኢትዮጵያ፣ ለውኃው ምንም ዓይነት አስተዋጽኦ በሌላት ግብፅ እጇ መጠምዘዝ አልነበረበትም፡፡ ይህንን ከበባ እያዩ ኢትዮጵያዊያን ከመቼውም ጊዜ  በላይ በአንድነት መቆም ነበረባቸው፡፡ ይህ ግድብ ተወደደም ተጠላም ብሔራዊ ፕሮጀክታችን ነው፡፡ ይህንን ብሔራዊ ፕሮጀክት በጋራ የመጠበቅ ኃላፊነት የኢትዮጵያዊያን ብቻ ነው፡፡ ይህንን የሚፃረሩ ካሉ በእርግጥም የባዕዳን ተላላኪዎች ናቸው፡፡ በአንድነት አለመቆም መዘዙ የከፋ ነው፡፡

ከህዳሴ ግድቡ በተጨማሪ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ደኅንነትና ጥቅም ኢትዮጵያዊያንን ሊያሳስብ ይገባል፡፡ ፖለቲከኞች፣ ምሁራን፣ የሃይማኖት መሪዎች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ አርሶ አደሮች፣ ነጋዴዎች፣ ተማሪዎች፣ ወዘተ አገራቸው ማናቸውም ዓይነት ግጭቶች ውስጥ ሳትገባ በሰላም መኖር እንዳለባት ስምምነት ሊኖራቸው ይገባል፡፡ የትኛውም የፖለቲካ፣ የእምነት፣ የቋንቋ፣ የባህል፣ የብሔርና ሌሎች መሰል ጉዳዮች ላይ ልዩነት ቢኖር፣ ልዩነቱ የአገርን አንድነት የሚያፈርስ ወይም የሚበትን መሆን የለበትም፡፡ ግለሰብ ፖለቲከኞችም ሆኑ ሌሎች ልዩነታቸውን በሠለጠነ መንገድ የሚፈቱበት ሕጋዊና ዴሞራሲያዊ አሠራር እንዲጠናከር መሥራት አለባቸው እንጂ፣ ጥጋባቸው በተነሳ ቁጥር አመፅ እያስነሱ ሕዝብ ማስፈጀት አይኖርባቸውም፡፡ በእነሱ ምክንያት የአገር ሰላም እየተናጋ ንፁኃን ሲገደሉ፣ የአካልና የሥነ ልቦና ጉዳት ሲደርስባቸው፣ ሲፈናቀሉና ንብረታቸው ሲዘረፍ የአገር ሰላም ይቃወሳል፡፡ ግለሰቦች ወይም ቡድኖች ከአገር ህልውና በላይ ሆነው እንደ ፈለጋቸው ሲሆኑ፣ የሕዝቡ የዘመናት የጋራ እሴቶች እየተናዱ እርስ በርስ መጋደል ልማድ ይሆናል፡፡ ይህ አስከፊ ልማድ ሲጠናከር ደግሞ አገር ትዳከማለች፡፡ ለዘመናት የተገነባው ኢትዮጵያዊ ማንነት ይጠፋል፡፡ እንኳንስ ሰላም፣ ዴሞክራሲና ብልፅግና ሊመጡ ዕልቂት የየዕለቱ ዜና ይሆናል፡፡ ይህንን የሚፈልጉ ኃይሎች ደግሞ ከኋላ ሆነው እየቆሰቆሱ አገር ያፈርሳሉ፡፡ ፍላጎታቸው ይኸው ብቻ ነው፡፡ በአንድነት መቆም ካልተቻለ ለተፅዕኖ ፈጣሪዎች መንበርከክ አይቀሬ ነው፡፡

ለኢትዮጵያ የሚበጃት የሕዝቧ አንድነት ነው፡፡ ይህ አንድነት በመፈላለግ፣ በመከባበር፣ በመፈቃቀርና በመተሳሰብ ላይ እንዲገነባ ከጥፋት መንገዶች መታቀብ ተገቢ ነው፡፡ አንዱ የኢትዮጵያዊነት ዋና ባለቤት ሆኖ ዜግነት ሰጪና ከልካይ ሲሆን፣ ሌላው ደግሞ ታሪካዊ ዳራዎችን በሚፈልገው መንገድ እየተረጎመ አገር ለመበተን ሲነሳ በጋራ አይሆንም ማለት ይገባል፡፡ ሁለቱም ጽንፍ የረገጡና አማካይ የሚባል ነገር ስለማያውቁ፣ ከእነሱ ተሽሎ መገኘት የግድ ይሆናል፡፡ የኢትዮጵያ ፖለቲካ አላድግ ያለው የጽንፈኝነት መራቢያ በመሆኑ ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ምድር አሀዳዊ ሥርዓት ተግባራዊ ማድረግ እንደማይቻለው ሁሉ፣ በጽንፈኛ ብሔርተኝነት ትክክለኛ ፌዴራላዊ ሥርዓት መመሥረት አይቻልም፡፡ የሚቻለው ግን ልዩነትን በመያዝ ለጋራ ጉዳዮች አስተዋጽኦ ማበርከት ነው፡፡ ተግባራዊ ሊሆኑ የማይችሉ ጽንፍ የረገጡ አቋሞችን ይዞ ፖለቲካኛ ነኝ ማለት እንደማይቻለው ሁሉ፣ ተግባራዊ መሆን የሚችሉ አጀንዳዎችን በማንቀሳቀስ በጋራ ለመቆም አለመቻልም ፖለቲከኛ አያሰኝም፡፡ ከታሪካዊ ስህተቶች በማመር ኢትዮጵያ የሰላም፣ የነፃነት፣ የፍትሕና የእኩልነት አገር እንድትሆን በአንድነት መቆም የጊዜው ጥያቄ ነው፡፡ ከዚህ ውጪ ያለው ወይ የታሪካዊ ጠላቶች ተላላኪ መሆን ነው፣ ወይም የፖለቲካ ማይምነት አረንቋ ውስጥ መዘፈቅ ነው፡፡ ለኢትዮጵያ ሁለቱም አይበጇትም፡፡ ለኢትዮጵያ የሚበጇት አንድነቷን አጠናክረው ታላቅ የሚያደርጓት ናቸው፡፡ አገር በተከፋፈለ ልብ ፀንታ መቆም መቸገር ብቻ ሳይሆን፣ የእጅ ጠምዛዦች ሰለባ እንደምትሆን ማሰብ ያስፈልጋል፡፡ በአንድነት መቆም ካልተቻለ እጅ ጠምዛዦች መጠናከራቸው አይቀሬ ነው!FacebookTwitterLinkedInShare

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s