ባሕር ዳር ላይ በተደረገው የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታ ኢትዮጵያ ኮትዲቯርን 2ለ1 አሸንፋለች

ጨዋታውን አስመልክቶ አሰልጣኙ፣ ተጨዋቾች እና ደጋፊዎች አስተያዬታቸውን ሰጥተዋል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ “በሙሉ የጨዋታ ብልጫ እና የኳስ ቁጥጥር ከጥሩ የግብ ሙከራዎች ጋር በማሸነፋችን ደስተኛ ነኝ” ብለዋል። ዋልያዎቹ ጨዋታውን ማሸነፋቸው በአፍሪካ ዋንጫ ውድድር ለመሳተፍ መልካም ጅምር መሆኑን እና ከምድቡ ከባድ ከተባለው ቡድን ሙሉ ሦስት ነጥብ መውሰዳቸው ለቀጣይ ጨዋታ ትልቅ የሞራል ስንቅ እንደሚሆን ነው ኢንስትራክተር አብርሃም የተናገሩት።

የዛሬው ውጤት ለቀጣይ ጨዋታዎች በከፍተኛ የራስ መተማመን እንዲዘጋጁ ትልቅ ሚና እንደሚኖረው አሰልጣኙ ገልጸዋል። ተጨዋቾች በሜዳ ውስጥ የነበራቸው እንቅስቃሴ በተሰጣቸው ትዕዛዝ መሠረት መሆኑን በመጥቀስም አስጣኙ ምሥጋና አቅርበዋል። ከብሔራዊ ቡድኑ ጀርባ ሆነው በጥሩ ሥነ ምግባር ሲደግፉ የነበሩትን የባሕር ዳርና አካባቢው እንዲሁም ከሩቅ ቦታ ወደ ስታዲዮሙ የመጡ የእግር ኳስ አፍቃሪያዎችንም አመሥግነዋል።

የቡድኑ አንበል ሽመልስ በቀለ እና የአማካይ ስፍራ ተጨዋቹ ሱራፌል ዳኛቸው ለውጤቱ መገኘት ኢንስትራክተር አብርሃም ቡድኑን የገነቡበት መንገድና የተከተሉት የእግር ኳስ አጨዋወት ጥበብ መሆኑን ተናግረዋል። በጨዋታው የተሰለፉት ወጣት ተጨዋቾች በሙሉ የራስ መተማመን እና የቡድን መግባባት ስለነበራቸው የተሻለ መጫወታቸውንም ተናግረዋል። ቀጣይ በሚኖራቸው ጨዋታ ኳስን በመቆጣጠር ጥሩ ውጤት ለማምጣት እንደሚጫወቱም ተናግረዋል። ደጋፊዎች በጨዋታው ያሳዩትን ጨዋነት የተሞላበት ድጋፍ ቀጣይም አጠናክረው እንዲቀጥሉም ጠይቀዋል።
ጨዋታውን አስመልክቶ አስተያዬታቸውነ ለአብመድ የሰጡ ደጋፊዎችም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ፍጹም የጨዋታ የበላይነት ወስዶ ያሸነፈበት መሆኑን ነው የተናገሩት። እንዳለ ሙሉ እና ሳለአምላክ ዓለምነው የተባሉ ደጋፊዎች ጨዋታው አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው ኢትዮጵያን ለአፍሪካ ዋንጫ ያሳለፉበትን ጊዜ እንዳስታወሳቸው ተናግረዋል። እንደ ደጋፊዎቹ አስተያዬት ኢትዮጵያ ከኮትዲቯር ያደረጉት ጨዋታ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የበላይነት፣ ጥሩ የኳስ ፍሰት ታይቶበት፣ በሙሉ የራስ መተማመን ስሜት ሙሉ ሦስት ነጥብ መገኘቱ አስደሳች ሆኗል። በእንግሊዝና ሌሎችም የአውሮፓ ሊጎች ዝናን ያተረፉ ተጨዋቾች የተካተቱበትን ስብስብ ማሸነፋቸው ደግሞ ከድልም ከፍ ያለ ድል እንደሆነ አስተያዬት ሰጭዎቹ አመልክተዋል፡፡

በጨዋታው በክረምቱ የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ የዝውውር ወቅት አርሰናልን በክብረ ወሰን ክፍያ የተቀላቀለው ኒኮላስ ፔፔ እና የቶተንሃሙ ኦሬይን የመሳሰሉ ድንቅ ተጨዋቾች እምብዛም እንቅስቃሴ ሲያደርጉ አልተስተዋለም። “በእንግሊዝ ፕሪሜዬር ሊግ አጥቂዎች አልደፈሩትም እየተባለ የተወራለትን የሊሸርፑል ተከላካይ ቨርጅል ቫንዳይክን ለመጀመሪያ ጊዜ የደፈረው ፔፔ አስቻለው ታመነን ማለፍ አቅቶት አምሽቷል” ብሏል እንዳለው።

በአንጻሩ በኢትዮጵያ በኩል እነ ሽመልስ በቀለ፣ ሱራፌል ዳኛቸው፣ አዲስ ግደይ እና ሌሎችም ተጨዋቾች ተስፋ ሰጪ የጨዋታ እንቅስቃሴ አድርገዋል። ‹‹ይህም ኢትዮጵያውያን ተጨዋቾች እድል ቢያገኙ በአውሮፓ ከሚጫወቱ አንዳንድ ተጨዋቾች የተሻሉ እንደሚሆኑ ያሳያል›› ብለዋል አስተያዬት ሰጪዎቹ። በጨዋታው የታየውን ጥሩ እንቅስቃሴ ያደነቁት ደጋፊዎቹ በቀጣይ የአካል ብቃት፣ ሥነ ልቦናዊ ጥንካሬ እና በቡድን መሥራት ላይ በትኩረት መሠራት እንዳለበትም አስተያዬታቸውን ሰጥተዋል። ደጋፊው በባሕር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲዮም ከዚህ በፊት እንደሚያደርገው ሁሉ ጥሩ ድጋፍ ማድረጉ ለውጤቱ መገኘት አስተዋጽኦ እንደነበረውም ነው ደጋፊዎቹ የተናገሩት።

ባሕር ዳር ላይ የሚደረጉ ጨዋታዎች ከገጽታ ግንባታ ጀምሮ ለከተማዋ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ እንክስቃሴዎች ማደግ የሚጫወተው ሚና ከፍተኛ መሆኑን ነው የተናገሩት። እንደ ደጋፊዎቹ አስተያዬት በከተማዋ ዓለም አቀፍ ውድድሮች ሲደረጉ በርካታ ስፖርተኞች እንዲያድጉ እድል ይፈጥራል። በከተማው የእግር ኳስ መሠረተ ልማት በጥሩ ሁኔታ እንዲስፋፋም በር ይከፍታል። በጥቅሉ የሚደረጉ ዓለም አቀፍ ውድድሮች ሁለንተናዊ ስፖርታዊ እድገት እንዲኖረው ያደርጋል። በመሆኑም የከተማዋ ስፖርት አፍቃሪያን ፍጹም ጨዋነት በተሞላው መንገድ የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉም አሳስበዋል።

ኢትዮጵያ በምትገኝበት ምድብ 11 የሚገኙት ኒጀርና ማዳጋስከር ማምሻውን ተጫውተዋል፤ በውጤቱም ማዳጋስከር 6ለ2 አሸንፋለች፡፡ ከቀናት በፊት ኢትዮጵያን ያሸነፈችው ማዳጋስከር በ6 ነጥብና አምስት የግብ ክፍያ ምድቡን ትመራለች፤ ኢትዮጵያና ኮትዲቯር በእኩል 3 ነጥብ ቀጣዩን ደረጃ ይዘዋል፡፡ ኒጀር ያለምንም ግብ ከምድቡ ግርጌ ተቀምጣለች፤ በነሐሴ ወር የመጨረሻ ሳምንት ኢትዮጵያ ከኒጀር ጋር የምትጫወት ይሆናል፡፡

ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s