ቆንጨራ አከፋፋዩ ማነው!? አብይ ስልጣንዎን ይጠቀሙ ወይ ለሕዝቡ ቁርጡን ይንገሩ!! – ሀብታሙ አሰፋ

የሕወሓት መሪዎች ከስልጣን እንደወረዱ ሰሞን ቆንጨራ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ያከፋፍሉ ነበር። ከዚህ ሁሉ የሚታወሰው አባይ ጸሐይዬ በቤንሻንጉል ድብቅ ስብሰባ አድርጎ በወጡ ማግስት ለዕቅዱ ተግባራዊነት አንድ መኪና ቆንጨራ በክልሉ ፖሊስ ተይዙዋል።ይሄ አብይ ስልጣን ላይ የወጡ ሰሞን የሆነ ነው። ሰሞኑን በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ ከተሞች ፣በድሬዳዋ እና በሐረር ጥቃት አድራሽ አሸባሪዎች በጭካኔ ያጠፉት ሕይወት ሳያንስ ሌላ ንጹሃንን የመቅጠፍ ዓላማ አለ?እነ ከማል ገልቹ እና ብ/ጄ/ል ሀይሉ ጎንፋ አባይ ወልዱ እንዳሉት ጦርነቱን አማራ ክልል ለማስገባት በየበኩላቸው እየሰሩ ነው። ያው ከማል መደበኛ ሰራዊት እስላማዊ መንግስት እስኪመሰረት የቄሮን ብጌግድ ማዘዝ ከጀመሩ ውለው አድረዋል። ሥራ ሳይኖራቸው ከመንግስት ድጎማ በላይ ለቄሮ በጀት ከየት አምጥተው ነው የሚሰጡት!? ስለ ወሎ ሲቃዡ አሩሲንም ማጣት እንዳለ ዘንግተው ይሆን? ሰው እንዴት ይህን ያህል ዓመት የኦሮሞ ፖለቲካ ውስጥ ሲዳክር ኖሮ ያለውን እውነታ መረዳት ያቅተዋል! መጥኔ ነው።

ብ/ጄ/ል ከማል ገልቹ የሚመሩት ፓርቲ ተወካይ አቶ ሊበን ዋቆን ብዙ ሰው ያስታውሳቸዋል።የለንደኑ ኮንፈረንስ ላይ ኢትዮጵያ ካልፈረሰች የኦሮሞ ጥቅም አይከበርም ያሉትን? አሁን እንኩዋን በቅርቡ የጃዋር ቲቪ ላይ እየቀረቡ ኦዴፓን ይዘነጥሉት ነበር ።ልጃቸው ደግሞ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽ/ቤት ቤተኛ የዲሲው ኤምባሲ አፈ ቀላጤ ነች።ጠንቃቃ መንግስት እንዲህ ነው።

የ80ዓመት የአልጋ ቁራኛን በጭካኔ መግደል፣መቆራረጥ፣ህጻናት እና ሴቶችን ሳይቀር በግፍ መግደል አይበቃም!? መንግስት እሹሩሩ ያለው ሀይል በስልጣን ጥቅም የናወዙ አንዳንድ የኦዴፓ አመራሮች፣ጃዋር እና ጋሻ ጃግሬዎቹ ከምንም ጊዜ በላይ ተናበው ይሰራሉ። ሕወሓት ደግሞ አብሮ መሰለፉን ትላንት ስንናገር የነበረው ዛሬ የዶ/ር ደብረጺዮን ኢሜል ሲዘረገፍ እንደ አዲስ እየሰማን ነው።

አብይ ሕወሓትን ሲያሽሞነሙኑ ከፈሰሰው ንጹሃን ደም ይልቅ ያኮረፈውን ጃዋርን ሲያባብሉ ዛሬ አምቦ ላይ ደሞዝ የሚከፍሏቸው ካድሬዎች ጃዋር ከሚያዘው የኢትዮጵያው አይ ሴስ ኔትዎርክ ጋር ተቀናጅተው ተቃወሙዋቸው።ነገሩ ከዚያም የከፋ ግርግር ለመፍጠር ያለመ ነበር ይባላል አዳራሽ መግባት ቄሮ ተከልክሎ ነው ሰንካላ ምክንያት ነው። ምንም ይፈልግ አብይን መቃወም ነው።

የሰው አንገት ቆርጦ፣የሴት ጡት ቆርጠው፣በድንጋይ እና በዱላ ጭካኔ በተሞላበት ሁኔታ ከ70 እስከ 80 ንጹሃንን የጨፈጨፉትን የየአካባቢው ባለስልጣናት እና አንዳንድ ባለሀብቶች ከየት አምጥተው ነው ማበረታቻ የገንዘብ ድጎማ፣ግብዣ የሚያደርጉት? የግድ መንግስት ግብጻዊ ወይ ቱርካዊ ብር ሲያድል ማየት አለበት!?

የሐረሩ ስብሰባ ላይ ከተማው ውስጥ ዋናውን ሽብር ሲያስተባብሩ የነበሩ የሰላም ኮንፈረስን ተሳትፈው፣የጠቅላዩን ስኮርት በጅማ እና በአርሲ ያለውን ፍቺ አብራርተው ጃዋርን ለማጥቃት እንዳልተፈለገ አለሳልሰው ሲናገሩ ተገኝተው አበላቸውን ጭምር በልተው ለምን አምቦ ሲሆን ይከለከላሉ?

በኦሮሚያ የእነ አብይ መንግስት መደበኛውን የአስተዳደር መዋቅር ሲጠቀም ማነው ቄሮ በጎን ራሱን አደራጅቶ፣አብሮ እየተሰበሰብ አብሮ እየወሰነ ብዙ ቦታ የቄሮ ተወካይ ከባለስልጣናቱ የበለጠ ተሰሚ ሆኖ በሚያስተዳድረው ክልል አብይ እንዴት ዘው ብለው ስብሰባ ይሄዳሉ? አንዳንዶች በብሽቀት እንደሚቀልዱት ስብሰባውን ጃዋር ፈቅዶላቸዋል!?

ሰውዬው ስልጣን እና ሀላፊነታቸውን በአግባቡ ባለመወጣት አሁን ጉሮሯቸውን ሊያንቁት ደርሰዋል። የኦዴፓ አመራሮችም ለሁለት ጌታ ከመገዛት ወደ አንዱ ለመጠቃለል ያሰቡ ይመስላል።ያው የድሮ ጌቶቻቸው ይሻሉናል ብለው አራት ኪሎን ይዘው አዲስ አበባን፣ድሬዳዋ፣ሐረር እና ወሎን አጠቃለው ታላቅ የኦሮሞ አገር ሲመሰርቱ እየቃዡ ህልማቸውን መቀሌ ማስፈታት ከጀመሩ ውለው አድረዋል ።ይሄ ሁሉ ኢትዮጵያን አፍርሰው ነው።ይህን የሚያደርጉት ደግሞ በኔትዎርክ ድንጋይ እና ዱላ ይዘህ ውጣ ተብለው የሚታዘዙት ሳይሆን ለሳቸውም ለጃዋርም እኩል መገዛት የሚያምራቸው የኦዴፓ ሰዎች እና መንግስት ቀለብ የሚሰፍርላቸው የኦሮሞ ጎምቱ ፖለቲከኞች ናቸው።

አሁንም አብይ የባከነ ሰዓት አላቸው።ከአራጅ ጋር ለፖለቲካ ትርፍ ያደረጉት መልመጥመጥ እንዳልጠቀማቸው አምቦ ግልጽ አድርጎላቸዋል። ጃዋርን ሳይሆን ክርስቲያን ታደለን እንደ ስጋት ማየታቸው ውርደታቸውን ካልሆነ ማሻገሩ ቀርቶ ውርደት የሚያስቀርላቸው አይመስልም።ምን ችግር አለ ነፍጠኛ እንደሁ ተብለዋል። የጃዋር መንግስት ደግሞ ነፍጠኛ ብሎ ለፈረጀው እንደ ሕወሓት ጥፍር በመንቀል፣ዘር በማኮላሸት የሚወሰን ሳይሆን ሰው በቁሙ የሚያርድ፣ሴትን አይኑዋ እያየ ጡት የሚቆርጥ አገር በቀል አይ ኤስ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ስለዚህ በቀረችዎ ጥቂት ጊዜ እባክዎ ተዋርደው አገሪቱዋን አያዋርዱዋት። ቆንጨራ አከፋፋዮችን እና ጽንፈኛ ሰው አራጆችን በፓርቲው ያሉ እና ለደህንነቱ የሚጨነቁለት የሁለተኛው መንግስት መሪ ስር የተደራጁትን ከቻሉ ቢያንስ ያስታግሱ ካልቻሉም በግልጽ ይናገሩ ።ዋና ዋናዎቹን ለፍርድ ማቅረብ ፍላጎት ከሌለዎ ሕዝቡ የራሱን ውሳኔ ይወስን።ካልሆነም ቢያንስ የሀይለማርያምን ልብ ይስጥዎ።በግልጽ ለአገሪቱ መረጋጋት ሲሉ አስቸኩዋይ መፍትሄ መስጠት ግዴታዎ ነው ።ጨው ለራስህ ስትል ማለት ይሄኔ ነው። ስልጣን ከወጡ ወዲህ የተናገርነውም ይህንኑ ነበር። ጠቅላዩ የባከነ ሰዓታቸውን ተጠቅመው ራሳቸውንም አገሪቱንም ይታደጉዋት ይመስልዎታል የበኩልዎን አስተያየት ይስጡበት። ዝም ከማለት ቢያንስ እያስጠነቀቅን ወይም እየተጠነቀቅን የማይቀረውን ቀን ለማስቀረት በጋራ መቆም ይገባል።

ሀብታሙ አሰፋ

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይፈቱ! – ያሬድ ኃይለማርያም

መቼም ይህ ሁሉ ውርጅብኝ በአገር እና በሕዝብ ላይ እንደማያባራ ዝናብ ሲወርድ ዝም ማለትዎ አንድም አቅም ማጣት፣ አንድም በፓርቲ ሰንሰለት ተጠርንፈው፣ አንድም ከብሽቀት፣ አለያም ምን ይዤ ነው ሕዝብ ፊት የምቀርበው ከሚል በሰዋዊ ስሜት ተውጠው ይሆናል። ወይም እኛ ልንገምተው ያልቻልነው ሌላ ችግር ገጥሞዎት ይሆናል።
ለማንኛውም ግን ዝምታዎ እስከ አሁን ግርምታን ፈጥሯል። ከዚህ ካለፈም እና በዚሁ ከዘለቁም ውስጣችን ሌላ ጥርጣሬን ይጭራል።

በእኔ በኩል የፖለቲካ እስረኛ የሆኑ ስለመሰለኝ እነ ኤሊያስ ገብሩ እንደተፈቱት ጠቅላይ ሚኒስትሩም፤ በዋስም እንኳ ቢሆን ይፈቱልን ልል ትንሽ ነው የቀረኝ። አዎ በድርጅታዊ ትብታብ እና በመንጋዎቹ ማስፈራሪያ ተጠርንፈው የህሊና እስረኛ ሆነዋል ብዮ ባስብ ይቀለኛ እርሶን ከበዳዮች ጋር አብረዋል ወይም ከበዳዮች ተርታ ተሰልፈዋል ከማለት።

አዎ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይፈቱ!

ይፈቱ እና ለቅሶ ይድረሱ፤ ይፈቱና የድረሱን ጣር ድምጽ እያሰሙ ላሉት ወገኖች አጋርነትዎትን አሳዩ፣ ይፈቱና በዳዮችን በስም እየጠሩ ያውግዙ፣ ለፍርድ ያቅርቡ፤ ይፈቱና የደረሰውን ጉዳት ልክ ቡራዩና ጌዲዮ ሄደው እንዳደረጉት ይጎብኙ፤ ይፈቱና የጠቅላይ ሚኒስትርነት ስራዎትን በአግባቡ ይሥሩ፤
አዎ ጠቅላይ ሚንስትሩ ከተተበተቡበት ድርጅታዊ ማነቆ፣ ለሕግ የበላይነት ካላቸው የተዛባ ግንዛቤ፣ ከገጽታ ግንባታ እና ድራማ ከሚመስሉ ሥራዎች ይፈቱ! ይፈቱ! ይፈቱ!

እኛና ይፈቱ የምትለዋ ቃል ለአሥርት አመታት አብረን እንዳለን አለን፤ ትላንት እስክንድር ይፈታ፣ በቀለ ይፈታ፣ መራራ ይፈታ፣ ኤሊያስ ይፈታ፣ እገሌ ይፈታ ስልንል ቆይተናል። ዛሬ ዘቅጠን ይሁን ወግ ደርሶን ጠቅላይ ሚኒስትሩም ይፈቱ ለማለት በቅተናል። አዎ ከተተበተቡበት የኢህአዴግ ፖለቲካ ይፈቱ ወይም ይፋቱ እና ይችን አገር ይታደጓት። ካለዛ ከሕዝብ ጋር መፋታትም አለ። ያኔ ቅጣምባራችን ይጠፋል። ይች አገር አሁን ያለችበት ሁኔታ ሌላ አቢዮት ወይም የመንግስት ስር ነቀል ለውጥ እንድታስተናግድ የሚፈቅድ አይደለም። እንኳንም ዘንቦብሽ ነው ነገሩ። እንኳን መንግስት ተፈንቅሎ ገና በመንገዳገዱ ብቻ ንጹሃን በጠራራ ጸሃይ እየታረዱ አስከሬናቸው በአደባባይ በገመድ ሲጎተት እያየን ነው። ኢትዮጵያ እንዲህ አስነዋሪ፣ አዋራጅ እና አንገት የሚያስደፋ ነገር ገጥሟት የሚያቅ አይመስለኝም።

ከለየለት አንባገነናዊ ሥርዓት ጋር መታገል ወግ ነው። ትግሉም መልክ ይኖረዋል። የገዛ ወገኑን፣ ሕጻናትን፣ አዛውንትን፣ ህሙማንን፣ ሴቶችን በእሳት እያቃጠለ፣ ሰውነት እየቆራረጠ በጅምላ የሚጨፈጭፍ መንጋ ገጥሟት አያውቅም ብል ማጋነን አይሆንም።

ለማንኛውም የኢትዮጵያ ሕዝብ ዛሬ ለእርሶ ደብዳቤ ጻፍ ቢባል ይህን የሚል ይመስለኛል፤

ይድረስ ለዶ/ር አብይ፤ እርሶ እንደምን አሉ? እኛ እንዳለን አለን፤ እንደተሸበርን፣ እንደተሳቀቅን፣ ፍርሃት እንደዋጠን፣ የገዛ ጥላችን ከመንጋዎቹ ውስጥ አንዱ እየመሰለን እየተገላመጥን፣ ወጥተን እስክንገባ ምን ይገጥመን ይሆን የሚል ስጋት ይዞን እግዚያ ማህረነ አስራ ሁለት ጊዜ እያል፣ እረ የመንግስት ያለህ አስራው ሁለት ጊዜ ደጋግመን እየቆጠርን እኛ እንዳለን አለን፤

+ አገር በመንጋዎች ሲታመስ፣ የንጹሃን ዜጎች ደም በግፈኞች በትር ሲፈስ እርሶ እንደምን አሉ?
+ ክቡሩ የሰው ገለ በሜንጫ፣ በዱላ፣ በጥይት ሲወቃ፣ ሲደቃ፤ ሃዘን በየቤቱ ጉዋዙን ይዞ ገብቶ እንባ እያራጨ ሕዝብ ደረት ሲደቃ እርሶ እንደምን አሉ?
+ እልጆቻቸው ፊት ባሎቻቸውን መንጋ የነጠቃቸው ኢትዮጵያዊ እናቶች በየመጠለያው ታጉረው፣ ታርዘው የመንግስትዎ ያለህ እያሉ ሲጮሁ እርሶ እንደምን አሉ?
+ ስንት ጀግኖች ወድቀው ያቆያቱን አገር በመንጋዎቹ ሰልፍ በታበየ አንድ ቀልብ የራቀው ጎረምሳ ስትታመስ፣ እኛም አብረን እንደ ገብስ ቆሎ ስንታመስ፣ ስንወቀጥ፣ ስንታኘክ እርሶ እንደምን አሉ?
+ በዛ ውብ ቃልዎ ያጽናኑናል ብለን፣ በዛ እሩህሩ ልብዎ፣ አዛኝ ስበዕናዎ አደባባይ ወጥተው አይዟቹ ይሉናል ብለን ብንጠብቅ የውሃ ሽታ መሆንዎ ምነው? እርሶ እንደምን አሉ?
+ ፍቅር ያሸንፋል በሚል መርህዎ ጽናትን ሊያሰርጹ የጀመሩት ጎዞ እንዲህ ያለ የግፍ ናዳ ሲወርድበት እያዩ ምነው መጥፋትዎ? እርሶ እንደምን አሉ?
+ ማቅ ለብሰን ማቅ ወርሰን አንድም እንዲያጽናኑን፣ አንድም በዳዮቻንን ለፍርድ በማቅረብ ፍትሕ አንግሰው እኛን እንዲክሱን ደጅ ደጁን እያየን ስንጠብቅዎ አንዴ ወደ ሐረር፣ አንዴ ወደ አንቦ እየገሰገሱ ግራ እንደገባው ሰው ክው ከው ማለትዎ? ከግፉዋን ጩኸት ይልቅ የመጋው ቁጣ ያስደነበርዎ? እርሶ እንደምን አሉ?

ቅዱስ መጽሃፉ በሆነ ገጹ እና በሆነ ምእራፉ ላይ “የግፉዋን አፍ ጥልቅ ጉድጓድ ነው” ይላል። ይህ ጉርጓድ ብዙዎችን ውጧል። የዛሬዎቹን በመንጋ የተደራጁ ግፈኞችም እንደሚጥ አንጠራጠርም። አብሮ እንደ እርሶ ያሉ ደግ ሰዎችን እንዳይውጥብን ግን አጥብቀን እንሰጋለን።

በየአደባባዩ ምስልዎትን ለብሶ ድጋፉን ካሳየዎት እና የመንጋ ሰለባ ከሆነው ሕዝቦ የተጻፈ።

ያሬድ ኃይለማርያም