እንዳትታለሉ ሰሙን እያያችሁ – ወርቁን መርምሩ ረጋ ብላችሁ

ይገረም አለሙ

Hailemariam Desalegn

ግድያ እስርና እንግልት በሀገሪቱ የተለያዩ ቦታዎች እዚህም እዛም፤ የፖለቲካና የህሊና እስረኞች መፈታት፣የጠቅላይ ምኒስትሩ ሥልጣን እለቃለሁ ማለት ሰሞነኛ ክስተቶች ናቸው፡፡ በቅድሚያ በደደቢት አውሬዎች ትዕዛዝ ከታጠቁት መሳሪያ በማይሻሉ ሰዎች ትዕዛዝ ፈጻሚነት በየማጎሪያ ስፍራዎች ስትሰቃዩ የከረማችሁ ወገኖቼ ሁሉን እንደፈቃዱ በግዜው የሚያደርገው አንድዬ የማሪያም ልጅ እንኳን ከልጆቻችሁ ከሚስቶቻችሁና ከወዳጅ ዘመድ ለመቀላቀል አበቃችሁ፡፡ ነጻ አወጣችሁ አለማለቴ ነጻነት በሌለበት ሀገር ከእስር መፈታት ነጻ መውጣት አይደለምና ነው፡፡ ለዚህም ይመስለኛል ከጠባቡ እስር ቤት ወደ ሰፊው የሚለው አነጋገር የተለመደ የሆነው፡፡

ሰው ሲታሰር ይበልጥ የሚጎዳው ቤተሰብ ነው፡፡ ታሳሪው አንዴ ለይቶለት በግፈኞች እጅ ወድቋልና “የማይቻለውን እንዳይቻል ችሎ” ( ይህች አባባል የዶ/ር ኃይሉ ዓርአያ ነች) ይኖራል፡፡ ቤተሰብ ግን ምን አደረጉት? ወዴት ወሰዱት? ዛሬ ምን ይፈጠር ይሆን? ወዘተ የሚለው የእለት ተዕለት ጭንቀት፤ ከቦታው ርቀት አንጻር እየተመላለሱ መጠየቁ፣ ቀለብ ማቅረቡ ወዘተ በሚል የሚደርስበትን ስቃይ የሚያውቅ ያውቀዋል፡፡ እናም የታሳሪ ቤተሰቦች የደረሰባችሁን ሁሉ የሚክስ ባይሆንም እንኳን ለዚህ አበቃችሁ እላለሁ፡፡ሌላ ምን ማለትስ ምን ማድረግስ ይቻላል፡፡

አቶ ኃይለማሪያም ከዚህ በላይ አሽከርነት በቃኝ ብለው በራሳቸው ወስነውም ይሁን፣ ጌቶቻቸው ህውኃቶች ሌላ ሴራ አዘጋጅተውልን እሳቸውን ለታይታ ከተቀመጡበት ቦታ ገለል ማድርጉ አስፈልጓቸው ውጣና ልለቅ ነው ብልህ ተናገር ብለዋቸው ለጊዜው ባይታወቅም፤ድርጊቱም በስመ ጠቅላይ ምኒስትርነት ዘመናቸው ለሆነው ከተጠያቂነት ሊያድናቸው ባይችልም የፈጸሙት ተግባር ግን ቀላል ሊባል የሚችል አይደለም፡፡ ነገር ግን ይህን የርሳቸውን መልቀቂያ አቀረብኩ ጥያቄ ለሀገር እንደሚበጅ ትልቅ ፖለቲካዊ ጉዳይ አድርጎ መመልከት ብሎም አጀንዳ አድርጎ በዚህ መጠመድ አንድም ህውኃትን ያለማወቅ ውጤት ሁለትም ጠቅላይ ምኒስትሩ ሥልጣን የለውም የህውኃት አሻንጉሊት ነው ስንል ከነበረው የራሳችን ቃል ጋር መጋጨት ይሆናል፡፡

ህውኃትን ለማወቅ ያለመቻላችን ዋናው ምክንያት ራሳችንን በትክክል ማወቅ ያለመቻላችን ይመስለኛል፡፡ለማናቸውም ነገር ቀዳሚው ራስን ማወቅ ነው፡፡አበው ሲተርቱ “አፍ የሚጎርሰውን እጅ ይመጥነዋል እንዴት ሰው መጠኑ አቅሙ ይጠፋዋል” ይላሉ፡፡እኛ ግን አቅማችንን አላውቅ፣ መጠናችንን አንረዳ ብለን ስሜት ፍላጎታችን የአንደኛችን ከሌላኛችን ብቻ ሳይሆን የእኛው ከእኛው ጋር ጭምር እየተጋጨብን ከመግለጫ የዘለለ ተቃውሞ፣ ከውግዘትና ዋይታ ሊሻገር የቻለ ትግል ማድረግ ተስኖን ሰምና ወርቅ የሆነውን የወያኔ ንግግርና ድርጊት ሰሙን ብቻ እያየንና እየተከተልን ወርቁን ለመመርመር ስክነቱም አስተውሎቱም ርቆን እነርሱ በሚሰጡን አጀንዳ እየተጠመድን በሚወረውሩልን ኳስ እየተጫወትን ብዙ መልካም አጋጣሚዎችን በቀላሉ እንደዘበት አሳልፈናል፡፡

በዚህ ሁኔታ ፖለቲካውን እንተውናለን ያሉት አልሆንላቸው ሲል በእነርሱ ተስፋ የቆረጠውና በወያኔ አገዛዝ የተንገሸገሸው ህዝብ ራስ በራሱ እየተጠራራ ባካሄደው መራር ትግልና በከፈለው መስዋዕትነት እነሆ እስረኞችን ከማስፈታት አልፎ ተራራ እናንቀጠቅጣለን ይሉን የነበሩትን ሰዎች ለማንቀጥቀጥ በቅቶ ጠቅላይ ምኒስትሩ የሥልጣን መልቀቂያ ደብዳቤ አቅርቤአለሁ የለውጡ አካል መሆን እፈልጋለሁ እንዲሉ አብቅቶአቸዋል፡፡አንድም ጋዜጠኛ በጣፈው ነገር አንድም ፖለቲከኛ በአቋሙ ምክንያት አላሰርንም፣ የፖለቲካም ሆነ የህሊና እስረኛ የምትሉት በእኛ ስር ቤቶች የለም እያሉ ሲዘባበቱብን የነበሩት ተንበርክከው ወደው ሳይሆን እንዲፈቱ ስገደድ ችሏል፡፡

ወያኔን ለዚህ ያደረሰው ለውጥ ሽቶ የደደቢት ህልሙን አራግፎ ጥሎ ኢትዮጵያ ወደ ዴሞክራሲ ሽግግር እንድታደርግ የበኩሉን ሊወጣ ተዘጋጅቶ ወዘተ ሳይሆን የህዝቡ አገዛዝ በቃኝ ማለት ለሥልጣኑ አስጊ ስለሆነበት ለመደለያም ቀን ለመግዣም ቢሆነን ብሎ ስለመሆኑ አጠያያቂ አይደለም፡፡ትናንትም ሆነ ዛሬ ለሀያ ሰባት አመታት ከወያኔ ሰፈር በኢህአዴግ ጭንብል በአደባባይ ሲነገሩ የምንሰማቸውም ሆኑ ሲፈጸሙ የምናያቸው ተግባራት በሙሉ እንደ እኔ አረዳድ ሰሞቹ ናቸው፡፡

በመሆኑም ከሰሞነኛው እየተነገረም እየተደረገም ካለው በስተጀርባ በስውር የሚካሄድ ሊካሄድም የታቀደ እነዚህን እንደመንደርደሪያም እንደ ግዜ መግዣም የሚጠቀም የነገሩ ወርቁ የሆነው ስራም ሴራም የለም የሚል ካለ ወያኔን አለማወቅ ብቻ ሳይሆን የመጣንበትን ሀያ ሰባት አመታት ፈጽሞ መዘንጋት ይሆናል፡፡ ለዚህ ደግሞ እስረኛ በፈቱና ስመ ጠቅላይ ምኒስትሩ ወደ ዴሞክራሲ ሽግግር ያፈልጋል እኔም የዚህ ለውጥ አካል መሆን እሻለሁ ባሉን ማግስት የደደቢቶቹ በጉልበት የመግዛት ቅዠት የታየበት የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ በቂ ማረጋገጫ ነው፡፡ እኛ ትናንትን በመርሳት ልክፍት የተያዝን ሆነን እንጂ ወያኔ ያው ወያኔ ነው፡፡ በመሆኑም ከ ማእከላዊ በፊት የደደቢት አመለካከት በምትለው ጽሁፌ ለማለት እንደሞከርኩት የደደቢት እምነትና አመለካከት ከመሰረቱ እስከአልተናደ ድረስ ከዛ በመለስ የሚደረጉ ማናቸውም ነገሮች የድርጊቱ ሰሙ እንጂ ወርቁ አይደሉምና ለለውጥ አያበቁንም፡፡ስለሆነም ሰሙን ሳይሆን ወርቁን መፈለጉ መፈተሹ ነው ተገቢው ነገር፡፡

በደንባራ በቅሎ ቃጭል ተጨምሮ እንዲሉ እንኳን የሥልጣን መልቀቅ ነገር ተጭኖባቸው እንኳንም ሀገራዊ ቀውስ አጥለቅልቋቸው ወትሮም ንግግር የማይሆንላቸው የስም ጠቅላይ ምኒስትር የምለቀው ለውጥ ስለሚያስፈልግና የለውጡ አካል መሆን አለብኝ ብዬ ስላመንኩ ነው፡፡ በግለሰብ ደረጃም በድርጅትም የሥልጣን ሽግግር አስፈላጊ ነው፡ ወዘተ ማለታቸውን ሰምተን ብዙም ሳይቆይ የወሬ ምኒስትሩ ነገረ ሌንጮ የጠቅላይ ምኒስትሩ ሥልጣን የመልቀቅ ጥያቄ እንግዳ ደራሽ ክስተት አለመሆኑን ተናግረው ጉዳዩ ርሳቸውን ግለሰቡን አቶ ኃይለማሪያምን እንጂ ካቢኔያቸውን አይመለከትም አሉን፡፡ ጠቅላይ ምኒስትሩ ያቋቋመው የምኒስትሮች ምክር ቤት እሱ ሥልጣን ሲለቅ ባለበት የሚቀጥልበት አሰራር ህገ መንግሥታዊ ይሁን ደደቢታዊ ጋዜጠኞች ቢጠይቁልን መልካም ነበር፡፡ አቶ ሽፈራው ሽጉጤ ደግሞ በተራቸው የደኢህዴንም የኢህአዴግም አፍ ሆነው ብቅ አሉና ከአንጀት አለመሆኑን አነጋገራቸው እያሳበቀባቸው አቶ ኃይለማሪያምን አንቆለጳጰሱና ስለ ኢህአዴግና ስለሚመራው መንግሥት ጠንካራነት ነገሩን፡፡ ልብ በሉ በጥልቅ ታደስን ብለው ሀገሪቱ ለዚህ ደረጃ የደረሰችው በእኛ የአመራር ድክመት ነው ያሉን ሰዎች ወራት ሳይቆጠር ድርጅታችንም መንግሥታችንም ጠንካራ ነው ሁሉን መቆጣጠር ችግሮችን ሁሉ መፍታት ይችላል ሲሉን ተሀድሶ ሲባል የነበረው ዝባዝንኬና እሱን ተከትሎ ሲነገር የሰነበተው ዲስኩር የነገሩ ሰም እንጂ ወርቁ አለመሆኑን ይህም ይጠቁማል፡፡ እናም ከወያኔ ሰፈር የሚነገር የሚሰራውን እንቆቅልሹን መፈተሽ፣ ሰምና ወርቁን መፈለግ፣ መረዳትና መላ መመምታት ካልተቻለ ዛሬም እንደትናንቱ ህዝብ በመስዋዕትነት የደረሰበት የትግል ጫፍ መልሶ መቀመቅ ይወርዳል፣ወያኔም ተንሰራፍቶ ይቀጥላል፡፡

አቶ ኃይለማሪያምን የጭዳ ዶሮ የሚሉት አይነት ማድረግ ካልሆነ በስተቀር እስካሁን የሆነውና እየሆነም ያለው በአቶ ኃይለማሪያም ድክመት ጥንካሬ የሚመዘን አይደለም፡፡ምን አልባት ከዚህ በኋላ ምን ሊቀርብኝ ብለው ትንሽ ወኔ አግኝተው፣ የሚያመልኩት አምላክም ረድቶአቸው፣ የልጆቻቸውና የባለቤታቸው ጸሎትም ድፍረት ሰጥቶአቸው እኔ ስሙ እንጂ ሥልጣኑ አልነበረኝም ብለው የጓዳውን ምስጢር ይነግሩን ይሆን! ምንም ተባለ ምን ግን ከወያኔ በተጓዳኝ ያለን ሰዎች በማንም ተነገረ በማንም ተሰራ ምንጩ የደደቢት ወያኔዎች መሆናቸውን በመረዳት ፊት ለፊት ከምንሰማውና ከምናየው ከሰሙ በስተጀርባ ወርቁን መፈለግ ያለብን ይመስለኛል፡፡

ጅብን ሲወጉ በአህያ ተከልሎ ነው እንዲሉ በአቶ ኃይለማሪያም ተከልለው እዚህ ያደረሱን ሰዎች ባሉበት ተቀምጠው የኃይለማሪያም መነሳት የሚያመጣው ፋይዳ አለመኖሩን፡፡ የጉልቻ መለዋወጥ ወጥ አለማጣፈጡን መረዳትና ከእንግዱህ በኢትዮጵያ አዲስ ንጉስ እንጂ ለውጥ መቼ መጣ የሚባልበት ክስተት መደገም እንደሌለበት እና የትግሉ የመጨረሻ ምዕራፍ እስረኛ ማስፈታት፣ የኃይለማሪያም ሥልጣን መልቀቅ፤ ወያኔን በወያኔ መተካት ወዘተ ሳይሆን የህዝብን የሥልጣን ባለቤትነት የሚያረጋገጥ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እውን ለማድረግ የሚያስችል የመሰረት ድንጋይ የሚያስቀመጥ መሆን አለበት፡፡ አያሌ መስዋዕትነት የተከፈለበት ትግል ባለጠመንጃ የማይገፋው፣ ሴረኛ ሸውዶ የማይልፈው፣ አንባገነንነትን ሊያበቀል ፣ ሥርዓት አልበኝነትን ሊሸከም፣ ዘረኝነትን ሊያስተናግድ ወዘተ የማይችል ሥርዓት መፍጠር መቻል መሆን ይኖርበታል፡፡

ስለሆነም በወያኔ ከሚነገር ከሚፈጸመው ውስጥ በግልጽ የሚታየንንና ፈጥኖ የሚረዳንን ሰሙን ብቻ አፈፍ በማድረግ አስተያየት ለመጻፍም ሆነ ለመናገር ሳንቸኩል፣በሌሎች መስዋዕትነት እየተገኘ ባለው ድል ፊታውራሪ ለመሆን ሳይቃጣንም ሰከን ብለን ወርቁን መመርመር ያስፈልጋል፡፡በተለይ ደግሞ የፖለቲካው ተዋናይ ነን የሚሉቱ ወገኖች የምንይልክን ቤተ መንግሥት ከቅርብም ከሩቅም እያዩ ሆድና ጀርባ ከመሆን ወጥተው የህዝብ የሥልጣን ባለቤትነት የሚረጋገጥበት እነርሱም በብቃታቸው ተመዝነው በህዝብ ድምጽ ተመርጠው ሊሚመኙት ሥልጣን የሚበቁበት አለያም የሚያጡበት አስተማማኝ ሥርዓት ለመገንባት የሚያስችል መሰረት በሚጣልበት ሁኔታ ላይ ነገ ሳይሆን ዛሬ ሥራ መጀመር ይኖርባቸዋል፡፡ ይህ የህዝብ ትግል ቢከሽፍና ቢመክን ዋንኛዎቹ የታሪክ ተጠያቂዎች እነርሱ ይሆናሉ፡፡መምራቱ አልሆነላቸውም ህዝብን ተከትሎ ትግሉን አቅጣጫ ለማስያዝ ለመጪው ስትራቴጂ ለመንደፍ አለመቻል ግን….?

በሌላ በኩል ኃይለማሪያምን የሚተካው እገሌ ይሁን እገሌ በሚል በተለያየ መንገድ የሚንጸባረቀው አስተያየትም የትግሉን ግብ ሳይሆን የወያኔን ፍላጎትና መንገድ የተከተለ ነው፡፡ ይህ ሁሉ መስዋዕትነት የተከፈለውና አሁንም እየተከፈለ ያለው የሰው ለውጥ በመሻት አይመስለኝም፡፡የሥርዓት ለውጥ እንጂ፣ከደደቢት ትልም ከህውኃት አገዛዝ የመገላገል እንጂ፡፡የደደቢቱ የቅዠት ትልም ለአንዴና ለመጨረሻ ግዜ ከኢትዮጵያ የፖለቲካ ምህዳር እስካልተወገደ ድረስ በዚህ ማዕቀፍ ውስጥ ተኩኖ አይደለም ሰው መልአክ እንኳን ጠቅላይ ምኒስትር ለመሆን ቢበቃ ወደ ዴሞክራሲ ሽግግር ማድረግ አይቻልም፡፡ ምክንያቱ ግልጽ ነው፣በዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ ደደቢቶች በሥልጣናቸው መቀጠል አይችሉም፤ ወርደውም ዳግም ተወዳድረው ማሸነፍ አይሆንላቸውም፡፡ሥልጣን አጡ ማለት ደግሞ የሚያስከትለውን መዘዝ ከእኛ በላይ እነርሱ ያውቁታል፡፡ደደቢት እስከ ምንይልክ ቤተ መንግሥት ምን እየሰሩ እንደደረሱ ቤተ መንግሥት ተቀምጠው ሀያ ሰባ አመታት ምን አንደፈጸሙ እኛ የማናውቀው እነርሱ ኮሽ ባለ ቁጥር የሚርዱበት ብዙ ጉዳጉድ እንዳላቸው መገመት አይከብድም፡፡

ስለሆነም ብረት የሚቀጠቀጠው እንደ ጋለ ነው እንዲሉ ከወያኔ ሰፈር በሚሰሙ በሚደረጉ ግዜ መግዣ ማዘናጊያ ድርጊቶች ሳይዘናጉ ይህ ውጤት እያስመዘገበና ያለ መስዋዕትነት እየተከፈለበት ያለ ትግል መዳረሻ ግቡ ፍላጎትና ዓላማው የሥርዓት ለውጥ መሆኑ በግልጽ ተቀምጦ መተማመን በመፍጠር የጋለውን ብረት የሚፈለገውን ቅርጽ ለማስያዝ በአንድ ልብና መንፈስ እንዲህ ፍም መስሎ እንደ ጋለ መቀጥቀጥ ነው የሚበጀው፡፡

ሌላው ከታውሞው ጎራ በእጅጉ የሚፈለግ ነገር ቢኖር ከትናንት መማር ነው፡፡ ፖለቲከኞቹ የየግል ፍላጎትና ህልማቸውን ወደ ጎን አድርገው ጠረጴዛቸው ላይ ሀገርና ህዝብን አሰቀምጠው መምከር ይኖርባቸዋል፡፡ደርግ ለ17 አመታት ገዥነት የበቃው ተቃዋሚዎቹ እኛ ብለው ከመስራት እኔ እኔ በሚል ሽኩቻ በመጠመዳቸውና በመተላለቃቸው ነው፡፡ ወያኔም ሀያ ሰባት አመታት ሊገዛን የቻለው በተቀዋሚው አይንና ናጫ መሆንና ሆድና ጀርባ ሆኖ መቀመጥ መሆኑ አሌ የሚባል አይመስለኝም፡፡ ዛሬም ቢሆን የህዝቡን ትግልና ድል የራስ ለማድረግ የሚታዩ አዝማሚያዎች ወደ ምኒልክ ቤተ መንግሥት የሚያስገባ ቀዳዳ ከተገኘ ብሎ አድፍጦ ማድባትና ሌላውን ጠልፎ ለመጣል ማሴርና መዶለት፣ህዝብ ለመሰረታዊ የሥርዓት ለውጥ መስዋዕትነት እየከፈለ የሥልጣን ፍርፋሪ በመሻት ለጥገናዊ ለውጥ ጎንበስ ቀና ማለት ወዘተ ሁሉም ከትናንት አለመማርን የሚያሳዩ እየወደቀ እየተነሳ ወያኔ በገዛዙ እንዲቀጥል የሚያግዙ አድራጎቶች ናቸውና ፈጻሚዎቹ ቆም ብለው ሊያስቡ፣ሌላውም ወገን ሀይ ሊላቸው ይገባል፡፡

Advertisements

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ከህወሓት ውጭ ሌሎች የኢህአዴግ ድርጅቶች አልተስማሙበትም።ህወሓት በለየለት የዕብደት ሥራ ውስጥ ገብቷል። (ጉዳያችን አጭር ዘገባ)

ጉዳያችን / Gudayachn
  የካቲት 10/2010 ዓም (ፈብሯሪ 16/2018 ዓም) 
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የመታወጁ ጉዳይ የህወሓት እና የህወሓት ፍላጎት ብቻ እንደሆነ መረጃዎች ከአዲስ አበባ ይሰማሉ።ባለፈው ዓመት በነበረው አዋጅ መነሳት ላይ በከፍተኛ ደረጃ አዋጁ መነሳቱን ሲቃወሙ የነበሩት የህወሓት ጎራ የሚገኙ ከፍተኛ ባለ ሀብቶች፣የወታደራዊ እና ጥቂት የኤሊቱ ወገን እንደነበር እና ጉዳዩ ዓለም አቀፍ ጫና እና የውጭ ምንዛሪ ላይ ተፅኖ በመፍጠሩ መነሳቱ ይታወቃል።ሆኖም ግን አሜሪካ፣አውሮፓ እና ቦሌ ቅምጥል ህንፃዎች ውስጥ ተቀምጠው የሚሞተው ሕዝብ የማይገዳቸው “አዋጅ ነው ለእዚህ ሕዝብ መድሃኒቱ” በሚል ስላቅ የአሁኑ አዋጅም እንዲታወጅ አዋጁ ከመነገሩ አርባ ስምንት ሰዓታት በፊት በትግራይ ኦን ላይን ድረ ገፅ እና በፌስ ቡክ ሰራዊታቸው አማካይነት ማሰራጨት ጀምረው ነበር። ዛሬ የካቲት 9/2010 ዓም የሚኒስትሮች ምክር ቤት ከቀኑ ሰባት ሰዓት ላይ ለጋዜጠኞች ወቅታዊ ሁኔታ አስመልክቶ መግለጫ እንደሚሰጥ ገልጦ ጋዜጠኞችን እስከ ምሽት ድረስ አስቀምጦ አዋጁ መውጣት እና አለመውጣት ላይ ሲከራከሩ ያመሸው ህወሓት መሩ ስብሰባ ያለውጤት በመቆየቱ ጋዜጠኞች እንዲመለሱ መልዕክት ከተነገረ በኃላ ምሽት ላይ በኢትዮጵያ ቴሌቭዥን እና ራድዮ አዋጁ እንደወጣ ተነገረ።የሆነው ይሄው ነው።በእዚህ ላይ ኦህዴድም ሆነ ብአዴን ያሉት ነገር እየቆየ የሚታይ ጉዳይ ነው የሚሆነው።ጉዳዩ ግን የሚያመለክተው አሁንም የኢትዮጵያ ችግር እያጠነጠነ ያለው በህወሓት አጉል ጀብደኝነት እና ትዕቢት ዙርያ መሆኑን መረዳት ይቻላል።
ህወሓት ኢትዮጵያን ከቀውስ ወደ ቀውስ እየወሰዳት ነው።የእዚህ አይነት አዋጅ ትናንት ከስልጣን ለቅቅያለሁ አንዳንድ ስራዎች እንዳይቆሙ እስካስረክብ ብቻ ኃላፊነት እወጣለሁ ያለ ጠቅላይ ሚኒስትር ያለው እና ከኃላፊነት የወረዱበት ካቢኔ የእዚህ አይነት አዋጅ ያውም ምክር ቤቱ ባልተወያየበት ደረጃ ማውጣት ይችላል ወይ? ይህ ጥያቄ ለጦር ሰራዊቱ ፊደል ቆጥረናል ለሚሉ ይቅረብልኝ።
 የዛሬ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ውሎ ብቻ የሚያሳየው ህወሓት  የትግራይ ኦን ላይን የመሰሉ ድረ ገፆችን  እና ጥቂት በስልጣን እና ሙስና ያበዱ ግለሰቦችን ይዞ የለየለት የእብደት ሥራ ውስጥ እንደገባ  እየታየ ነው።ሌላው ቀርቶ ከአሁን በኃላ በህወሓት አፈቀላጤ የሆኑ ድረ ገፆች እና ማኅበራዊ ሚድያ ላይ የሚተላለፉት መልክቶች የእራሱ የህወሓት ሙሉ ስምምነት ላይ ያልተደረሰባቸው ይልቁንም ጥቂት ደፋር ነን ባዮች በፈጠሩት የአናርኪ ቡድን የሚንቀሳቀስ መሆኑን ማወቅ ይቻላል።ይህ ማለት ካለው ህወሓት ውስጥ እራሱ ሌላ ጀብደኛ ነኝ ባይ ትንሽ ህወሓት እንደፈጠረ አመላካች ነው።በሌላ በኩል አቶ ገዱ ከስልጣን ወርደዋል የሚለውን ዜና እራሱ ሐሰት መሆኑን አሁንም ከሀገር ቤት የሚመጡ ያልተረጋገጡ ዜናዎች ይጠቁማሉ።ዜናው ግን ከቀትር በኃላ ጀምሮ ሲሰራጭ ነበር።
ባጠቃላይ ህወሓት አሁንም ኃላፊነት የተሰማው ተግባር እየፈፀመ አይደለም።ይህ ደግሞ ኢትዮጵያን እንደ ሀገር እጅግ የሚጎዳት ነው።አሁን ሁለተኛው ምዕራፍ የነፃነት ትግል እንደተጀመረ አመላካች ሁኔታዎች አሉ። የመጀመርያውን ምዕራፍ ሕዝብ አይኑን እንዲገልጥ ለነፃነቱ እንዲናገር እንዲደፍር ጥቂቶች እነ እስክንድር ነጋ፣በቀለ ገርባ፣ እና ሌሎች በፈንጅ ላይ የመራመድ ያህል ተረማምደው የህዝብ ልቦና አንቅተዋል።አሁን ሁለተኛው ምዕራፍ ላይ በአንደኛው ምዕራፍ ላይ ዝም ያልን በሙያችን እና ባለን አቅም ሁሉ ለኢትዮጵያ አንድነት፣ፍቅር፣እና ሰላማዊ ሽግግር እንነሳ።ኢትዮጵያን እንደ ሀገር መልሰን እናቁማት።ህወሓት ከጋረጠባት አደጋ እንታደጋት።
ኢትዮጵያ ሀገሬ

ጉዳያችን GUDAYACHN
http://www.gudayachn.com

“መታገስ” ለእኛ እና ለእነርሱ… (በፍቃዱ ኃይሉ)

በፍቃዱ ኃይሉ (ዞን ዘጠኝ ጦማሪ)

Befeqadu Hailu Techanie is an Ethiopian writer, activist, and blogger.

“አድማው የተጠራው መጥፎ ሰዐት ላይ ነው”፣ ወይም ደግሞ “ትንሽ ለምን አይታገሱም?” የሚሉ አስተያየቶች ሲሰነዘሩ ደጋግመን እንሰማለን። ብዙ ግዜ በጭቆና እና በትዕግስት ላሳለፍነው ሕዝቦች ‘ታገሱ’ የሚለው ቃል ምን ያህል አሳማኝ ነው? የኢሕአዴግ ሹማምንት “ዴሞክራሲያዊ ስርዓት መገንባት ግዜ ይወስዳል” ሲሉ እንዲሁ ‘ስንጨቁናችሁ ታገሱን’ ማለታቸው ነው። “ታገሱ” ወይም “ለመቃወም አሁን ግዜው አይደለም” ማለት ማታለል ነው። አሁን ደግሞ በጣም እያሳዘነኝ ያለው ይህ ንግግር ከተቃዋሚው ወገን ወይም ከሕዝቡ ወገን ከሆኑት ሳይቀር መምጣቱ ነው።

“ታገሱ” ወይም “ግዜው አይደለም” የሚለው አስተያየት “ምክር እና ቡጢ ለሰጪው ቀላል ነው” እንደሚሉት ነው እንጂ ይህ ሳይታሰብበት ቀርቶ አይደለም። ንግግሩ የማርቲን ሉተር ኪንግ (ትንሹን) “Why We Can’t Wait” የሚል ጽሑፍ ያስታውሰኛል።

ማርቲን ሉተር ኪንግ “የሚያሳዝነው” ይላል፤ “የሚያሳዝነው ተጠቃሚ ቡድኖች ጥቅማቸውን በገዛ ፈቃዳቸው አሳልፈው የማይሰጡ መሆናቸው ታሪካዊ ጥሬ ሐቅ መሆኑ ነው። አንዳንድ ግለሰቦች ትክክለኛው ነገር ታይቷቸው ኢፍትሐዊነትን እምቢ ሊሉ ይችላሉ። … ቡድኖች ግን ከግለሰቦች የበለጠ ክፉ ናቸው።” ይህን አያደርጉም። ባለፈው ሳምንት እነበቀለ ገርባ የፍቺ ዝርዝር ውስጥ አልነበሩም። ሥማቸው የተጠቀሰው በኦሮሚያ ከሰኞ እስከ ረቡዕ የተጠራው አድማ መጀመሩ እንደማይቀር ቁርጡ ሲታወቅ ነው። ረቡዕ ይፈታሉ ከተባለ በኋላ ማክሰኞ ከሰዐት በኋላ የተፈቱት አድማው እና ተቃውሞ ዋና ከተማዋን ያንኳኳል በሚል ድንጋጤ እንደሆነ እናውቃለን። አሁንም የእነኮሎኔል ደመቀ ፍቺ ዜና የመጣው በአማራ ክልል ሰኞ ጀምሮ አድማ ሊካሔድ ይችላል በሚል ስጋት ነው። የኦሕዴድ መለወጥ፣ የብአዴን መግደርደር፣ የኢሕአዴግ መልመጥመጥ ሁሉም በሕዝባዊ ጫና የመጣ እንጂ በፈቃደኝነት የሆነ አንድም ነገር የለም።

ኪንግ ቀጥሎም እንዲህ ይላል፣ “ግዜ በራሱ ገለልተኛ ነው። ለጥፋትም ለመልካምም ነገር ሊውል ይችላል። አሁን አሁን ግን ግዜን ከደጋጎች ይልቅ ክፉዎች በአግባቡ ይጠቀሙበታል ብዬ ማሰብ ጀምሬያለሁ”። አባባሉ የተሳሳተ አይመስለኝም። ክፉዎች ሁሌም ሴራቸውን ለመጎንጎን፣ ከወደቁበት ለመነሳት ግዜ መግዛት ይፈልጋሉ። ታገሱ ይሉናል። ቅኖች ትግስትን በቅንነት ሲቀበሉ ክፉዎች ግዜውን ለክፋታቸው በአግባቡ ይጠቀሙበታል። ለኪንግ “…የሰው ልጅ ስኬት መሽከርከሩ የማይቆም ጎማ አይደለም።” ‘ደከመኝ በማያውቁ ሰዎች ጥረት የሚጨበጥ ነገር ነው’። እናም ‘ጊዜ፣ ትክክለኛውን ነገር ለማድረግ ሁሌም በስሎ የሚጠብቀን ፍሬ ነው’ ይላል።

ትዕግስት መልካም ነገር ሆኖ ሳለ የጨቋኞች ግዜ መግዣ እንዲሆን መፍቀድ ግን ብዙ መስዋዕትነት ለከፈሉ ሕዝቦች አዋጭ አይደለም።

ይህንን ስል አመፅን የደገፍኩ ሊመስል ይችላል። በፍፁም። እንዲያውም ኪንግ በዚያው ጽሑፉ ላይ “በአመፅ ሁሉንም ነገር እናጥረግርገው” የሚሉ እና “እንታገስ ሁሉም በግዜው ይሆናል” የሚሉት ሁለቱም አንድ ናቸው ይላል። እኔም ስለምስማማበት ነው እዚህ የምጠቅሰው። ምክንያቱም ሁለቱም ምንም ለውጥ አያመጡም። ነገር ግን አመፅ አልባ አድማዎች እና ማስተጓጎሎች የታወቁ የሠላማዊ ትግል መርሕዎች ናቸው። መንገድ በመዝጋት የሚሰቃዩ የማኅበረሰብ ክፍሎችን ዘንግተው የራሳቸውን ቢዝነስ የሚያሳድዱ ግለሰቦች ለአጭር ግዜም ቢሆን የወገኖቻቸውን ጉዳት እንዲረዱት የማስገደጃ ቅዱስ ተግባር ነው። በተጨማሪም ለቢዝነሳቸው አለመስተጓጎል ሲሉ የተበዳዮችን ጉዳይ መፍትሔ እንዲያገኝ የበኩላቸውን እንዲያዋጡ የማስገደጃ ቅዱስ ተግባር ነው።

ትግሉ ይቀጥላል!
Qabsoon itti fufaa!

ሰበር ዜና …. የአማራ ትግል ምልክት ከሆኑት አንዱ ኮ/ል ደመቀ ዘውዱ እንዲፈታ ውሳኔ ተላለፈ!

ሰበር ዜና፤ ኮ/ል ደመቀ ዘውዱ እንዲፈታ ውሳኔ ተላለፈ!

ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ

የወልቃይት ዐማራ ማንነት ጥያቄ አስተባባሪና የዐማራ ተጋድሎ መሪው የኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ ክስ ተቋርጦ ከእስር ሊፈታ መሆኑን ዛሬ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡ ኮ/ል ደመቀ በጎንደር ከፍተኛ ፍርድ ቤት በዋለው ችሎት ለየካቲት 22 ቀን 2010 ዓም ቀጠሮ የተሰጠ ቢሆን ክሱ ተቋርጦ እንዲፈታ ተወስኗል፡፡

ፋራ ራዴዮ ደግሞ የሚከተለውን ዘግቧል
***********
FBC (Fana Broadcasting Corporate S.C.)

በአማራ ክልል በጎንደርና ጭልጋ ማረሚያ ቤቶች የሚገኙ 224 ተጠርጣሪዎች ክስ ተቋረጠ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 9፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በቀድሞ ሰሜን ጎንደር ዞን በተለያዩ የወንጀል ድርጊቶች ተጠርጥረው ክስ የተመሰረተባቸው 224 ተጠርጣሪዎች ክስ ተቋረጠ።

ከእነዚህም በተጨማሪ ውሳኔ አግኝተው በጎንደር እና በጭልጋ ማረሚያ ቤቶች የሚገኙ 55 ፍርደኞች በይቅርታ ከእስር እንዲለቀቁ ተወስኗል።

የአማራ ክልል ፍትህ ቢሮ የጎንደር ቋሚ ምድብ አስተባባሪ አቶ ብስራት አበራ በተለይም ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደተናገሩት፥ ክሳቸው የተቋረጠውና በይቅርታ የሚፈቱት ተጠርጣሪዎች እና ፍርደኞች ባለፉት ጊዜያት በሽብር፣ ሁከትና አመፅ ተሳትፎ ተጠርጥረው እና ተከሰው የነበሩ ናቸው።

በክስ ሂደት ላይም ያሉ አብዛኛዎቹ በዋስትና መብት ላይ ያሉ ሲሆን፥ ተጠርተው የተሃድሶ ስልጠና ከወሰዱ በኋላ ከክሳቸው ነፃ ይሆናሉ ብለዋል።

በማረሚያ ቤት የሚገኙ ፍርደኞች እና ተጠርጣሪዎች ከነገ ጀምሮ እንደሚለቀቁ የገለፁት አቶ ብስራት፥ እስካሁንም አምስት ፍርደኞች ተገቢውን የይቅርታ ሂደት አልፈው መለቀቃቸውን አስታውቀዋል።

በነብዩ ዮሃንስ

ጀግናው ወንድማችን ኮ/ል ደመቀ ዘውዱ እ.አ.አ በ2016 ዓ.ም ለህዝብ ያደረጉት ንግግር

ኢትዮጵያ አሁን ላለችበት ሁኔታ ስልጣን በእጁ ያለው ህወሓት በፍጥነት እና በድፍረት መውሰድ ያለበት አስራ ስድስት ቁልፍ እርምጃዎች ( ጉዳያችን)

አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ጥይቄ የህወሓት ከስልጣን የመውረድ ብቻ አይደለም።የኢትዮጵያ የግዛት እና የሕዝብ አንድነት ጥያቄም ጭምር ነው።ስለ አቶ ኃይለማርያም ቀደም ብሎ የወጣውን ፅሁፍ ከፃፍኩ ከተኛሁ በኃላ ስለ ኢትዮጵያ ተጋድሜ ማሰላሰል ጀመርኩ።እንቅልፍ በአይኔ አልዞረም።ሰዓቱ ሌሊቱ አልቆ ሊነጋ ነው።ኢትዮጵያ አደጋ ላይ ነች።ስለ ህወሓት ከስልጣን አለመልቀቅ ስላስከተለው ምስቅልቅል ሁኔታ ብዙ ተፅፏል።ህወሓት የሰራው ስህተት እዚህ አድርሶናል።አሁን ጥያቄው ግን የአንድነት አደጋም ጭምር ነው።

ስለሆነም እንደ ሀገር የተደቀነውን አደጋ ለማስወገድ ለጊዜው ወታደራዊ እና ምጣኔ ሃብታዊ ስልጣኑ በህወሓት ስር እስካለ ድረስ ህወሓት የብዙሃኑን የኢትዮጵያ ሕዝብ አዎንታ ያስገኘ ለውጥ ለመጀመር የሚችለው በመጀመርያ ያለፈ የጎሳ ፖለቲካው ስህተት መሆኑን በግልጥ አምኖ የሚከተሉትን አስራ ስድስት ነጥቦች በድፍረት መተግበር ከቻለ ነው።

1/ በጎሳ ስም የፖለቲካ ድርጅት መመስረት በመላ ሀገሪቱ መከልከል አለበት፣

2/ ከእዚህ በፊት በጎሳ ስም የተደረጁ ጥምረት ፈጥረው ወይንም ለብቻቸው ሃገራዊ ስም ወይንም የቃላት ሐረግ መርጠው እንዲሰየሙ መታዘዝ አለባቸው ፣

3/ ህወሓት ስሙን በፍጥነት ሃገራዊ ስም መስጠት አለበት ማንም ኢትዮጵያዊ ከየትኛውም የኢትዮጵያ ክፍል ትግሪኛ ተናገረም አልተናገረ አባል መሆን መቻል አለበት፣

4/ ጊዜያዊ የሽግግር መንግስት መመስረት እና ህገ መንግስቱን ማሽሻል፣

5/ የብሔራዊ ዕርቅ ኮሚሽን ከሀገር ሽማግሌዎች፣ወጣቶች እና ሴቶች የተውጣጣ ካለ ምንም የፖለቲካ ተፅኖ መመስረት እና ሥራ ማስጀመር፣

6/ ለዲሞክራሲ ሂደቱ ዋስትና የሚሆኑትን ሚድያ በነፃ እንዲዘግቡ ማድረግ፣

7/ የፍትህ ስርዓቱን በገለልተኛ ባለሙያዎች እንዲመራ ማድረግ 

8/ የሃማኖት አካላት በሙሉ ነፃነት እንዲሰሩ መፍቀድ በውስጣቸው ያለውን ንቅዘት እንዲነቀል ከሕዝቡ ጋር በቅንነት መስራት፣

9/ በውጭ ያሉ ኢትዮጵያውያን በሙሉ ወደ ሀገር በነፃነት የመግባት ፍቃድ መስጠት።ከእዚህ በፊት በፖለቲካ የተከሰሱት ሁሉ ነፃነት ማወጅ 

10/ የጦር ኃይሉን እና የደህንነት መዋቅሩን ሁሉን አቀፍ ማድረግ ይህንንም የሚያረጋግጥ ልዩ የህዝብ ኮሚሽን መሰየም፣

11/በሙስና ያጠፉ፣በሰብዓዊ መብት ረገጣ እና በልዩ ልዩ ወንጀል የሚጠየቁ አካላትን በሙሉ ለፍትህ ማ1ቅረብ ህዝብን እና ትውልድን አስተማሪ በሆነ መልኩ ይያለፈ ስህተትን ማረም፣

12/ የሰማዕታት ሃውልት በማለት የተሰሩት ሐውልቶች ሙሉ በሙሉ የቅርፅም ሆነ የይዘት ለውጥ ተደርጎባቸው በሃያኛው ክፍለ ዘመን በደርግም ሆነ በህወሓት ወይንም በኢህአፓም ሆነ በኢድዩ ወይንም በኦነግ ስር ሆነው  ለሞቱት የሃውልቱ ሁሉ የጋራ መታሰቢያ እንዲሁን አዲስ ስያሜ ለምሳሌ  በእርስ በርስ ጦርነት ህይወታቸውን ላጡ ወይንም ሌላ የወል ስም ተፈልጎ እንዲሰየም ፣

13/ ኢትዮጵያ አንድ የብሔራዊ ክብር ቀን እንዲኖራት በእዚህም ቀን ያለፈ የእርስ በርስ ጦርነት ምዕራፍ መዝጊያ መታሰቢያ ቀን ሆኖ ቀኑ የዕርቅ እና የአንድነት ቀን ሆኖ እንዲታስብ እንዲታወጅ ፣

14/ ህወሓት በስሩ ያሉትን የኤፈርት ንብረቶች ወደ ሕዝብ ንብረትነት እንዲቀየሩ እንዲያደርግ ፓርቲዎች የሚኖራቸው ሀብት በሕግ እንዲወሰን  

15/ ኢትዮጵያ የምርጫ ቦርድ ፍትሃዊ የሆነ እንዲሆን እና ኢትዮጵያ የፕረዝዳንታዊ ሀገር እንጂ በጠቅላይ ሚኒስትር የምትመራ ሀገር መሆኗ እንዲቆም ቢደረግ እና 

16/ አሁን ያለው የጎሳ አከላለል ስርዓት ጎሳን ሳይሆን  በጅኦግራፍ፣ታሪክ እና ባህልን መሰረት ያደረገ የፌድራል አከላል ስርዓት እንዲዘረጋ እንዲያደርግ የሚሉት ናቸው።

ከላይ የተጠቀሱትን ተግባራት ለመከወን ህወሓት አሁን ባለው የሰው ኃይል ወይንም ሕዝቡን ደጋግመው ሲዋሹ በተያዙ ባለስልጣናቱ  ማከናወን አይችልም።ስለሆነም አዲሱ ትውልድ ሙሉ በሙሉ ኃላፊነቱን መውሰድ አለበት።ይህንን ማድረግ ካልተቻለ ህወሓት እራሱን ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያን አደጋ ላይ እንደሚጥላት ሳይታለም የተፈታ ነው።

ጉዳያችን GUDAYACHN
http://www.gudayachn.com

ኃይለማርያም ደሳለኝ  ለምን ለቀቁ? (ክንፉ አሰፋ)

ክንፉ አሰፋ

Hailemariam Desalegn in the TPLF parliament

ኢ.ቢ.ሲ. በሰበር ያስተናግደውን የኃይለማርያም ደሳለኝ መግለጫ፤ ዞምቢዎቹ ተሯሩጠው ለማጽደቅ ግዜ አልወሰደባቸውም። እሳቸውም ልክ ስልጣን እንደነበረው ጠቅላይ ሚኒስቴር “ስልጣን አስረክቢያለሁ” ሲሉ እፍረት የሚባል ነገር ፊታቸው ላይ አይታይባቸውም ነበር።  ሹመት እንጂ ሕገ-መንግስቱ የሚፈቅደው ስልጣን እጃቸው ላይ እንዳልነበር ሕጻናትም ያውቁታል።   የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ መልቀቅያቸውን በብርሃን ፍጥነት ሲያጸድቀው፤ ድርጊትዋን  ከደቡብ አፍሪካው ጃኮብ ዙማ ክስተት ጋር ለማመሳሰል የተተወነች ድራማም አስመስሏታል።  ስልጣን ሳይኖር “ሰላማዊ ሽግግር” የሚሏት ፌዝ …

ኃይለማርያም ደሳለኝ ተሸክመውት የነበረው ሹመት ይሁን ስልጣን  ሲለቅቁ፤  “ከደሙ ነጻ ነኝ”  ብለው ለተሰራው ወንጀል ሁሉ እንደ ጲላጦስ  እጁቸውን ሊታጠቡ እንደማይችሉ ግን እርግጥ ነው።  ከዚህ ባለፈ ግን የእሳቸው መውረድ  በሃገሪቱ ላይ ሊያመጣ የሚችለው ለውጥ ከቅርብም ይሁን ከሩቅ አይታይም። እንደማንኛውም የድል አጥቢያ ካድሬ፤  ቆሻሻውን እና የሸክሙን ስራ ሲሰሩ የሰነበቱ ሰው ነበሩ።

ሰውየው ለጥፋቱ ሁሉ ጠጠያቂ የሚያደርገው ሃላፊነት ቦታ ላይ ይቀመጡ እንጂ፣  በኢትዮጵያ ታሪክ እንደ እሳቸው መሳለቅያ የሆን መሪ አልነበረም። ተጠያቂነቱ እንዳለ ሆኖ ግና  የራሳቸው ራዕይ እና  አንዲት ቀን እንኳ  የራሳቸው አቋም ያልነበራቸው አሸንጉሊት ነበሩ።   “የፖለቲካ እስረኞች በሙሉ ይለቀቃሉ!” ብለው በገዛ ገጻቸው የጻፏት መግለጫ እንኳን በዞምቢዎቹ  ስምንት ግዜ ተሰርዛ – ስምንት ግዜ ተደልዛለች።  ኃይለማርያም በዚህ ደረጃ ለመዋረድ ራሳቸውን ስላዘጋጁ፤  ይህ  ድርጊት ለሳቸው አዲስ ነገር አይደለም። “መረጃ አይሰጡኝም።  ስራዬን የማከናውነው ያለመረጃ ነው።”  እያሉ አንዳንዴ ጣል የሚያደርጓቸው እውነታዎች  “ጉድ ነው” ቢያስብሉም፤  አጃኢብ የሚያሰኙ ንግግሮችንም በአደባባይ ይለቅቃሉ።  ኢትዮጵያ፤  አንድ በመንገደኛ  ፌደራል ፖሊስን በጥፊ የሚመታበት ሃገር እንደሆነች በቴሌቭዥን ቀርበው የሚናገሩ ሰው ናቸው።  ለንግድ የሚነሳ ማንም ሰው ሰፌድ ብቻ ይዞ ትግራይ እና ደቡብ በመሄድ ወርቅ ማፈስ እንደሚችልም በብሄራዊ ቴሌቭዥን ተናግረዋል። “ኮብልስቶን” ድንጋይ ማንጠፍ  እጅግ የሚያዋጣ ስራ እንደሆነ  ለዩኒቨርሲቲ ምሩቃን ሲመክሩም ተደምጠዋል።

ስልጣን የለቀቁበት ምክንያት ግን ግራ ሳያጋባ አልቀረም። “ሃገሪቱ አሁን ያለችበት ሁኔታ  እጅግ አሳሳቢ ነው። ከፍተኛ የሆነ ያለመረጋጋት እና ችግር አለ።  በርካታ ህይወት ጠፍቷል።  በርካታ ሰዎች ተፈናቅለዋል…  ” ብለውናል ኃይሌ። ችግሩ ይህ ሆኖ ሳለ ለችግሩ መፍትሄ ለመሆን እንዲያስችላቸው እሳቸው መውረድ እንዳለባቸው ነው የገለጹት።   ከፍተኛው የመንግስት ስልጣን ላይ እያሉ ያልፈቱትን ችግር – ከዚያ በመውረድ የሚፈቱበትን ፎርሙላም በመግለጫቸው ጀባ ቢሉ ጥሩ ነበር።   ሕዝቡ ለሚያነሳቸው በርካታ ጥያቄዎች የጥይት  ምላሽ  ሲሰጡ  እንዳልነበረ።   ሕዝብ ላይ ሲተኩሱ ለነበሩ ወታደሮች ማዕረግ ሲያንበሻብሹ እንዳልነበር – ይህንን ደፍረው ተናገሩ። ሹመቱ ወር እንኳ መች ሞላው?

ከምህንድስና ሰራቸው አንስቶ የተዋጣለት ካድሬ ያደረጋቸውው የስልጣን ፍቅር ይሁን የበታችነት ስሜት  – ብቻ  አሁን ላይ ደርሰው በራስ መተማመንን ሳይቀር እንዳሳጣቸው ከንግግራቸው መገንዘብ አይከብድም።  እንደ ጠቅላይ ሚኒስትር ሳይሆን ይልቁንም እንደ ተላላኪ ሆነው ለማገልገል ሙሉ ፈቃዳቸውን ባይሰጡ እነሱም እንደ ጅሉ ሞሮ አይቀልዱባቸውም ነበር። ከተራው ሕዝብ ርቀው ጫፍ ላይ በመቀመጥ  ሀገራዊ መርዶ ሲጋቱ ከከረሙ በኋላ ማልቀስ እና ማላዘን ምንም ትርጉም አይሰጥም።

በቅርቡ አሜሪካ የገባው የሳቸው ፕሮቶኮል ኃይሌ በግዞት ውስጥ ያሉ እስረኛ እንደሆኑ ቢናገርም  እሳቸው  ግን አንዲት ቃል እንኳ አልተነፈሱም ነበር። እንዲያውም በቅርቡ ሰጥጠውት በነበረው ጋዜጣዊ መግለጫ የሃገሪቱ እድገት  “የሚያስጎመጅ”  በመሆኑ ሁሉም እንደሚመኙት  በመናገር  ትንሽ ፈገግ አድርገውናል። ይህንን ፈገግታችንን ሳንጨርስ ትላንት በ ኢ.ቢ.ሲ. ቀርበው ኢትዮጵያ በገባችበት አስከፊ ችግር ሳብያ ኢንቨስተሮች ሳይቀሩ ሃገሪቷን እየለቀቁ እንደወጡ አፈረጡት።

“በደርግ ዘመን ማሰቃያ የነበረው ማእከላዊ እንዲዘጋ እና ሙዚየም እንዲሆን” መወሰኑን  ቢነግሩንም ይህንን ሚዚየም ሳያስመርቁ  መሰናበታቸው ግን ቅር ያሰኛል።    ይህንን መናገራቸው ባልከፋ ነበር ግና ጽድቁ ቀርቶ እንዲሉ መንግስት የጀመራቸውን እቅዶች ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለባቸው በስንብታቸውም ሳይጠቅሱ አላለፉም።  የእስካሁኞቹ  የመንግስት  እቅዶችም ያየናቸው ናቸው። መብቱን ያወቀ እና መብቱን የጠየቀ ዜጋን ማሰር – ማፈናቀል – መግደል…. ናቸው።

ባለ ሙሉ ስልጣን ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ቃለ ምህላ ሲያደርጉ፤  “እዚህ ያለሁት የመለስን ራዕይ ለማስፈጸም ነው።” ብለው ነበር። ያን ለማድረግ ደግሞ የበላዮቼ እና የበታቾቼ የሚያዙኝን ሁሉ አደርጋለሁ ሲሉ ቃል መግባታቸው ይታወሳል።  የበላዮቼ ያሉት ምክትል ሆነው የተሾሙ እነ ደብረ ጽዮንን  መሆናቸው ነው።  አድፍጠው ይህችን ወቅት ይጠብቁ የነበሩ እነ አቦይ ስብሃት ዛሬ አደባባይ ወጥተው፣   “የመለስ ራዕይ የሚባል ነገር የለም” ማለት ሲጀምሩ  “ታላቁ መሪ” ን የተኩት “ታዛዡ መሪ” አይናቸው ፈጠጠ። መለስ የጀመረውን ለመጨረስ ቢፍጨረጨሩም ዳር አላደረሱትም። የመልሰ  “ዜጎችን በዘር ከፋፍሎ 100 አመት የመግዛት” ስትራቴጂ በነቄው ትውልድ ሲከሽፍ – እጅ መስጠት ግድ ይላል። እኚህ ሰው ነጸ አልነበሩም።  ነጻ  ሆነው ሲናገሩ የምንሰማቸው ጠቃዋሚ ሃይሎችን እና ጋዜጠኞችን ሲሳደቡ ብቻ ነው።

ዛሬ ኳሷ ሕዝብ እጅ ላይ ስትወድቅ እሳቸውም ም ባነኑ።  ከመለስ ወርሰው የተሸከሙት ነገር ራዕይ ሳይሆን  – ቅዠት እንደሆነ የተረዱት በዚህ ሰዓት ይመስላል።  ይህንን እስኪረዱት ግን ሕዝብ ማለቅ ነበረበት።  መለስ የጀመረው ለእልቂት የተጠነሰሰ የፌዝ ፌደራሊዝም እጨርሳለሁ እንዳሉት ከግብ ባያደርሱትም፣ ብዙ ገፍተውታል።

የፖለቲካ አክሮባቱን ተስተምረው –  የሃይል ሚዛን እያዩ የመገለባባጥ አባዜ ከልሆነ በስተቀር ሃገሪቱ 27 አመት ሙሉ ችግር ላይ ናት።  የሕዝብ ድምጽ ሲዘረፍ አብረው ዘርፈዋል፤ መቶ ሺህ የኦሮሞ ወገናችን ከሃረር ሲፈናቀል አብረው ነበሩ። ኮንሶ ላይ ወገኖች እንደ ባርያ አሳዳሪ በሰንሰለት ሲጠፈሩ አልሰማሁም አይሉንም። ጉራ ፈርዳ ላይ በአማራ ወገናችን የዘር ማጥፋት ወንጀል ሲፈጸምበት አንዲት ነገር አልተነፈሱም። እሬቻ ለበዓል የወጣ ከሺህ በላይ ሰው ሲያልቅ ሰራዊታችን አንድም ጥይት አልተኮሰም ነበር ያሉት። የጎንደር እና የባህርዳር ወጣቶች እንደቅጠል ያረግፍ የነበረው እሳቸው የሚተዳደረው ሰራዊት ነበር። በወልድያ እና በቆቦ ግድያን ሲቃወሙት አልሰማንም።   መግለጫቸውን እያነበቡ በነበሩበት ቅጽበት  እንኳን በ እሳቸው  ጠቅላይ አዛዥነት የሚመራው ሰራዊት ሶስት ሰዎችን ገድሏል።

ልብ ያለው ሰው ሁሉ  ወቅቱ የሚናገረውን ድምጽ ያደምጣል።  የ”ታህሳሱ ግርግር”  ለሃይለስላሴ መንግስት ምልክትን አሳይቶ ነበር።  እሳቸው ግን አይተው እንዳላዩ አለፉት።  የህዝብን ቁጣ በንቀት ከማለፍ ይልቅ በአግባቡ ቢያስተናግዱት ኖሮ ቀዳማዊ ኃይለ ስላሴ  ከመዋረድ ይድኑ ነበር።  ደርግም ቢሆን የሕዝብ ጥያቄን በጥይት ለመፍታት ሲጥር የተሞከረበትን መፈንቅለ መንግስ በ “ጥቂት ጀነራሎች” ስም ከሚያጣጥለው ይልቅ ብሄራዊ እርቅ  ቢያደርግ ኖሮ የሃገሪቱ ችግር መፍትሄ ያገኝ ነበር።

ዛሬም የመውረድ ወይንም  የመዋረድ ደወል እያቃጨለ ነው። ገዢው ፓርቲ  ሁሉንም የፖለቲካ እስረኞች ፈትቶ፤   ከእውነተኛ  ተቃዋሚዎች ጋር  ወደ ብሄራዊ እርቅ መጓዝ ሲችል ችግሩን ይፈታዋል።    በአንድ ነገር እርግጠኛ እንሁን።  ሕዝብን በጠመንጃ ያሸነፈ ሃይል በታሪክ ኖሮ አያውቅም።

ብሄራዊ ቀውስ – ችግር ብቻ አይደለም።  ቀውስ እድልም  ነው። ወያኔ  ይህንን  እድል ለእውነተኛ ብሄራዊ መግባባት ቢጠቀምባት ለራሱም ይበጀዋል።  ይህ ዕድል ካመለጠው ግን ተዋርዶ ፤ ይወርዳል።

የሃይለማርያም ደሳለኝ መልቀቅና ፋይዳው: (ልዩ ውይይት) ዶ/ር መረራ ጉዲና፣ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ፣ አቶ ገብሩ አስራትና አቶ ልደቱ አያሌው | ሊያዩት የሚገባ


የሃይለማርያም ደሳለኝ መልቀቅና ፋይዳው: (ልዩ ውይይት) ዶ/ር መረራ ጉዲና፣ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ፣ አቶ ገብሩ አስራትና አቶ ልደቱ አያሌው | ሊያዩት የሚገባ