“ስጋት ቢኖርብኝም ጥበቃ እንዲደረግልኝ አልፈልግም!” ~ እስክንድር ነጋ [ ጋዜጠኛ እና የአዲስ አበባ ባለደራ ምክር ቤት ሰብሳቢ]

ጋዜጠኛ እና የአዲስ አበባ ባለደራ ምክር ቤት ሰብሳቢ የሆነው እስክንድር ነጋ ትላንት በበርካታ ወጣቶች ተከቦ እንደነበር ለቢቢሲ አረጋግጧል።

“ትናንት ቅዳሜ ምሽት 1፡00 አካባቢ፤ ፒያሳ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን አካባቢ ከሚገኘው ቢሯችን ስብሰባ ጨርሰን ስንወጣ ነው የተወሰኑ ወጣቶች ናቸው የከበቡን” ይላል እስክንድር።

እስክንድር ቁጥራቸው ከ10 በላይ ይሆናል ያላቸው ሰብሰብ ያሉ ወጣቶች ከቢሮው ውጪ ደጃፍ ላይ ጠብቀው እርሱንና አራት የባልደራስ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላትን እንደከበቧቸው ያስረዳል።

«አልፈናቸው ስንሄድ በከበባ መልክ ተከትለውናል። እንቅስቃሴያቸው አስጊ ስለነበር ወደ ኋላ ተመልሰን ፖሊስ ይዞ እንዲጠይቅልን ሙከራ አድርገናል። ቢሆንም አንዱ ብቻ ነው በፖሊስ ቁጥጥር ሥራ መዋል የቻለው።»

“የለውጥ አመራሩን ሳይረፍድ ከጥፋት መመለስ ይቻላል” እስክንድር ነጋ
ወጣቶቹ ተቃውሞም ሆነ ጥያቄ አቅርበው ነበር ወይ? ሲጠጓችሁ ዓላማቸው ምንድን ነበር? ተብሎ የተጠየቀው እስክንድር ምንም ያሉን ነገር የለም፤ ነገር ግን በከበባው ውስጥ አስገብተው ተከትለውናል ይላል።

«እኛ ላይ ከሚደርስብን የግድያ ዛቻ አንፃር አስጊ ነበር። እንደዚህ ዓይነት ነገር ተፈጥሮ አያውቅም። ይሄ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው። ብዛት ነበራቸው እና አደጋ ለማድረስ በጣም ቀላል ነበር።»

ወጣቶቹ ጥቃት ሊያደርሱብን ይችሉ ነበር የቦታ መረጣ ጉዳይ እንጂ ብሏል እስክንድር ጨምሮ።

«በእኛ ድምዳሜ ለከበቡን ሰዎች ቦታው አመቺ አልነበረም፤ እኛም ተመለስን። ፊት ለፊታችን ጨለማ ነበር። ከጨለማው ወደኋላ ተመልሰን። እንደ አጋጣሚ አንዲት ፖሊስ ስትመጣ አገኘን። አጠራጣሪ ሁኔታ ስላለ ሰዎቹን እንዲያዙልን እንደምንፈልግ አመለክትን። ተጨማሪ ኃይል ፈልጋ ነበር። በዚያ መሃል ነው እንግዲህ ልጆቹ ተሰባስበው ከአከባቢው የሄዱት።»

ከአንድ ወጣት በቀር የተቀሩት በሚኒባስ እንዳመለጡ የሚናገረው እስክንድር ግለሰቡን ወደ ፖሊስ ጣቢያ ሲወስዱት የፖሊስ አባልና ምክትል ሳጅን ሆኖ ተገኝቷል ይላል።

«ፖሊስ ጣቢያው ቃል ሲሰጥ የደረስንበት ነገር ምክትል ሳጅን መሆኑ ነው። መጀመሪያ ላይ በአካባቢው ምን ሲያደርግ እንደነበር ሲጠየቅ ተማሪ ነኝ ብሎ ነበር። በኋላ ፖሊስ ሆኖ ተገኝቷል። እኛ ቃል ሰጥተን ወደየቤታችን ሄደናል እሱ ፖሊስ ጣቢያ እንዲቆይ ተደርጓል። ዛሬ ጠዋት ተመለሱ ተብለን ስንሄድ ነገ ኑ ተብለናል። ልጁ በእሥር ላይ ይሁን ወይም ለቀውት እንደሆነ የምናውቀው ነገር የለም» ብለል እስክንድር።

ጥበቃ ለእስክንድር. . .?
«በርካታ የግድያ ዛቻ እና ማስፈራሪያ ይደርሰኛል» የሚለው እስክንድር ነጋ ምናልባት ከመንግሥት በኩል ጥበቃ እንዲደረግለት ይፈልግ ይሆን?

«የለም! የለም! እኔ ጥበቃ እንዲደረግልኝም አልፈልግም። የሚያስፈልገው አሁን በተያዘው ልጅ ላይ ጥብቅ የሆነ ምርመራ እንዲደረግ፤ ‘ፌር’ [ፍትሃዊ] የሆነ፤ ሳይንሳዊ የሆነ፤ ሕጉ በሚፈቅደው መሠረት ልጁ እንዲመረመር ነው። በተለይ ከእርሱ ጋር አብረውት የነበሩት ልጆችን አፈላልጎ መያዝና ለምን እንዲህ ዓይነት እንቅስቃሴ እንዳደረጉ መጠየቅ እና ጉዳዩን እስከ ሥር ድረስ ሄዶ መመርመር ነው የሚያስፈልገው። ይሄን ብቻ ነው እኔ ከመንግሥት የምፈልገው።»

እስክንድር ወጣቶቹ ተዘጋጅተውበት እና አጥንተው እንደመጡ ይናገራል። የዕለተ’ለት እንቅሰቃሴያችን ከግምት ውስጥ ገብቷል የሚል ጥርጣሬ እንዳለውም ይናገራል።

«ሁልጊዜ በዚህ ሰዓት ነው የምንጨርሰው። ቅዳሜ ማታ ጨርሰን በእግራችን ነው የምንንቀሳቀሰው። ለምሳሌ እኔ ከጊዮርጊስ ተነስቼ ከአንድ ወይም ከሁለት ሰው ጋር እስከ አራት ኪሎ ደረስ እሄዳለሁ። የተጠና ነው የምለው ለዚህ ነው። ለማናቸውም ዝርዝሩ በፖሊስ የሚረጋገጥ ነገር ነው።»

የተቀናጁ እንቅስቃሴዎች እንዳሉ የአከባቢው ሰው ሲከታተል ነበር የሚለው እስክንድር ዛሬ ጠዋት ምስክሮች ይዘው ወደ ፖሊስ ጣብያ እንደሄዱ ያስረዳል።

«ከእኛ ውጭ የሆኑ፤ በአካባቢው የነበሩ፤ ወጣቶቹ ሲመጡ እና እኛ ላይ ሲያደርጉ የነበረውን የተከታተሉ ሰዎችን ምስክር እንዲሆኑ ይዘን ነው የሄድነው። አስፈላጊ ስለሆነ ማለት ነው። ይሄንን መሠረት አድርጎ ከመንግሥት ትክክለኛ የሆነ ምርመራ አድርጎ እርምጃ እንዲወሰድ ነው። ምክንያቱም ከኃይል እርምጃ ኢትዮጵያ አታተርፍም። በኃይል የሚፈታ የፖለቲካ ጥያቄ የለም።»

እነእስክንድር ምናልባት በቁጥጥር ሥር የዋለው ግለሰብ ቢለቀቅ ክስ የመመሥረት ሃሳብ ይኖራቸው ይሆን?

«እንግዲህ ነገ ነው የምናውቀው። ተለቋል ካሉን ወደ አዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ሄደን የነበረውን ሁኔታ እናስረዳለን። ምስክሮች ይዘን ወደላይ አቤት እንላለን ብለን እናስባለን። በዚያም ደረጃ የማይፈታ ከሆነ ከዚያም ወደላይ ሄደን ማሳሰብ እንፈልጋለን። በመንግሥት ውስጥ ሁለት ሃሳብ አለ ብለን እናስባለን። ብጥብጥ የሚፈልግ ኃይልና ብጥብጥ የማይፈልግ ኃይል አለ። ያንን ግምት ውስጥ በማስገባት እስከ ጥግ ድረስ ሄደን አግባብ ያለው ምርመራ እንዲደረግ ነው የምንፈልገው። ይሄ ልጅ ንፁህ ከሆነ እንዲለቀቅ ነው የምንፈልገው። የግድ መታሠር አለበት የሚል አቋም የለንም።»

ስጋት
እስክንድር፤ ይደርስብኛል ከሚለው ዛቻ እና ማስፈራሪያ አንፃር አደጋ ወይም ጥቃት ይደርስብኛል የሚል ስጋት ይኖርበት ይሆን?

«. . .እኔ የሚጠብቀኝ እግዚአብሔር ነው ብዬ ነው የማስበው። ከዚያ ባሻገር እኔ በግሌ ጥበቃ ይገባኛል ብዬ አላስብም። ጉዳዩ ከእኔ ጋር የተያያዘ አይደለም። የተነሳው ጥያቄ እኔ ኖርኩ አልኖርኩ የሚኖር ነው። በዲሞክራሲያዊ መንገድ እልባት እስካላገኘ ድረስ ማለት ነው። መኖር አልፈልግም ማለት ግን አይደለም» ይላል እስክንድር።

• “ከጄ/ል አሳምነው ጋ በምንም ጉዳይ ያወራሁበት አጋጣሚ የለም” እስክንድር ነጋ

አክሎም «ለሚስቴ መኖር እፈልጋለሁ፤ ለልጄ መኖር እፈልጋለሁ። ኖሬም ደግሞ ለሕብረተሰቡ ገንቢ የሆነ አስተዋፅዖ ማድረግ እፈልጋለሁ። ጥበቃ ግን ይከብደኛል። ኅሊናዬም አይፈቅደውም። ካለው ዛቻ አኳያ፤ በተለይ ደግሞ ትላንት በተግባር ስላየነው አያሳስበኝም ማለት ግን አልችልም፤ ያሳስበኛል» ብሏል።

ቢቢሲ ጉዳዩን በተመለከተ ፖሊስ በኩል ያለውን አስተያየት ለማወቅ ያደረገው ጥረት ሳይሳካ ቀርቷል።

– #BBC

ፌዴራላዊ ስርዐቱ የተተገበረበት መንገድ ዜጎችን ለሰብአዊ መብት ጥሰት አጋልጧል ተባለ

Daniel Bekele

Daniel Bekele, Chief Commissioner, Ethiopian Human Rights Commission.

አዲስ አበባ፤ በኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት ፌዴራላዊ ስርዐቱ የተተገበረበት መንገድ ዜጎችን ለሰብአዊ መብት ተጋላጭ ማድረጉን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽነር ዶክተር ዳንኤል በቀለ ተናገሩ::

ዶክተር ዳንኤል በተለይ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንዳብራሩት፤ ዜጎችን ለሰብአዊ መብት ጥሰት ተጋላጭ ያደረገው ፌዴራላዊ ስርዓቱ የተተገበረበት መንገድና የፌዴራል ስርዓቱ የመንግስት አወቃቀር አንዱ ችግር መሆኑን አሰረድተዋል:: የፖለቲካ ፓርቲ አወቃቀሩም ሌላው ምክንያት ሊሆን እንደሚችልም ጠቁመው በተለየ ማንነት ላይ ትኩረት ተደርጎ መሰራቱም ለግጭት መዳረጉንም ጠቁመዋል፡፡

የፖለቲካ ፓርቲዎች አወቃቀር፣ የመንግስት አወቃቀርና ህገ መንግስታዊ ማዕቀፍ መፈተሽ አለብን፣የፖለቲካ አወቃቀራችን በተፈጥሯቸው የአግላይነት ጸባይ ስላላቸው በውጤታቸው ደግሞ ለግጭት፣ ለብጥብጥና ለእርስ በእርስ አመጽ የሚጋብዙ ሆነው የሚታዩ ስለሚመስሉ ጉዳዩ ሊመረመር፣ ሊጠና እና ሊታይ ይገባዋል ያሉት ኮሚሽነሩ የፖለቲካ መሪዎችም በእዚህ ጉዳይ መወያየት መጀመር የሚገባቸው ይመስለኛል ብለዋል፡፡

በእኔ እምነት ለሰብአዊ መብት ተጋላጭ ያደረገው ራሱ ፌዴራላዊ ስርዓቱ ሳይሆን ፌዴራላዊ ስርዓቱ የተተገበረበት መንገድና የፌዴራል ስርዓቱ የመንግስት አወቃቀር አንዱ ሊሆን ይችላል ያሉት ኮሚሽነሩ፤ የፖለቲካ ፓርቲ አወቃቀሩ፣ በተለየ ማንነት ላይ (የዘር ማንነት፣ የብሄር ብሄረሰብ ማንነት፣ የአካባቢ፣ የሃይማኖት ማንነት ላይ የተመሰረቱ አደረጃጀቶች) የተመሰረተ ፓርቲ ለግጭት ስለሚዳርግ አብዛኞቹ የአፍሪካ አገሮች እንዲህ አይነት የፖለቲካ አደረጃጀት በህጎቻቸው አልፈቀዱም ወይም በግልጽ ከልክለዋል ሲሉም አብራርተዋል፡፡ ‹‹ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲህ አይነት የፖለቲካ አስተዳደር እንዳለን ይታወቃል፡፡ ታሪካዊ መሰረትና ምክንያት አለው›› ሲሉም ጠቁመዋል፡፡

እስካሁን የመጣንበት መንገድ ያስገኘው ውጤትና የፈጠሩት ተግዳሮቶችም አሉት ያሉት ዶክተር ዳንኤል፤ ከተደረሰበት የፖለቲካ ምዕራፍ አንጻር ሂደቱን መርምሮ ችግሮችና ያስገኘውን ውጤት በማስመልከት ግልጽ ውይይት ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ ለሰብአዊ መብት ጥሰት ተጋላጭ ያደረገ የመንግስት አወቃቀር ካለውም አወቃቀሩን መፈተሽ እንደሚያስፈልግም ጠቁመዋል፡፡

‹‹ይህ ማለት ግን የፌዴራላዊ አስተዳደርን ማፍረስ ማለት አይደለም፣ ኢትዮጵያ ካላት ብዝሃነት አንጻር እንደ ኢትዮጵያ በርካታ ብሄር ብሄረሰብ ላላቸው አገራት የፌዴራላዊ አስተዳደር ተገቢ አስተዳደር ነው ሲሉም አብራርተዋል፡፡

ፌዴራላዊ አወቃቀር ህዝቦች፣ ሰዎች፣ ዜጎች በየአካባቢያቸው የራሳቸውን ጉዳይ በእየራሳቸው የሚያስተዳድሩበት መንገድ መሆኑን በመጠቆምም፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ተግባራዊ የሆነው አስተዳደር ግን በተለይ ከብሄር ብሄረሰብ ማንነት ጋር በጣም የተቆራኘ መሆኑን ነው የተናገሩት፡፡ በተለያዩ ክልሎችና በክልሎቹ ውስጥ ባሉ የተለያዩ የማንነት ጥያቄዎች እና የድንበርና የወሰን ልዩነት ላይ እጅግ አወዛጋቢ ክርክር የፈጠረ መሆኑ ለሰብአዊ መብት ጥሰት ተጋላጭ ማድረጉንም አልሸሸጉም፡፡

በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሚታዩ ግጭቶች ከማንነት ጥያቄና ከአካባቢ እና ከድንበር ጉዳይ ጋር ተያይዞ ‹‹ይህ የእኔ አካባቢ ነው፣ ይህ አካባቢ የአንተ አይደለምና ከእዚህ ትወጣለህ፣ የአንተ ድንበር እዛ ጋር ነው›› ከሚሉ ጥያቄዎች ጋር የተያያዘ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

አገራችን ውስጥ በየክልሎቹ ብቻ ሳይሆን በየቀበሌዎቹና በየወረዳዎቹ ደረጃ ያለ የማንነትና የአስተዳደር ወሰን፤ የአስተዳደር ወሰን መሆኑ ቀርቶ ልክ ከአጎራባች አገሮች ጋር እንዳለ አይነት የድንበር ወሰን ጋራ የሚመሳሰል እየሆነ መጥቷል ብለዋል፡፡

አሁን የተፈጠሩት ግጭቶችም በተለያዩ አካባቢዎች ያሉ የአስተዳደር ወሰኖችን እንደ ድንበር በመቁጠር ከሌላ አገር ጋር የተፈጠረ ችግር አይነት አዝማሚያ እንደሚታይበት ኮሚሽነሩ ገልጽው የፌዴራል ስርዓቱን በሚያጠንክር መልኩ የአስተዳደር ወሰኖችና የማንነት ጥያቄዎች በተገቢው መንገድ ተወያይቶ የፖለቲካ መፍትሄ መፈለግ ይሻላል ሲሉ መክረዋል፡፡

አዲስ ዘመን ጥቅምት 22/2012

ዘላለም ግዛው

የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንቷ የት ገባች ??? ምንሊክ ሳልሳዊ

የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንቷ የት ገባች ??? ምንሊክ ሳልሳዊ

ስለፍትሕ ነው እያወራን ያለነው። ስለሕግ የበላይነት ነው እየጮኽን ያለነው። ስለሃገርና ሕዝብ መብት ነው እያወራን ያለነው።ይህ ሁሉ ወንጀል ሲፈፀም ከሕግ አንፃር ያለውን ሁኔታ ተከታትላ ለሕዝብ ማሳወቅ የሚገባትና የሕግ የበላይነት እንዲከበር መታገል የሚገባት ኃላፊነት የተጣለባት የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንቷ የት ገባች ??? ድምጿን ለምን አጠፋች ???

ሕወሓት ላይ ዘራፍ ስትል የነበረች ከደብረዘይት ወደ መቀሌ ተዋጊ ጀቶች ልካ እነጌታቸው አሰፋን ለማስደብደብ የዛተች የአሜሪካንን የሕግ ገጠመኞች ለኢትዮጵያ እጠቀማለሁ ብላ የፎከረችው ወይዘሮ መዓዛ ምን ይዋጣት ምን ይሰልቅጣት ሳይታወቅ ጠፍታለች። ዝምታዋ ወይ የተረኝነቱ አንድ አካል መሆኗን አሊያም ለሕግ የበላነት መከበር ደንታ ቢስ መሆኗን ያሳያል።

ሕግ ሲጣስ፣ ሕግ ሲናድ፣ ሕግ ሲዛባ፣ ሕግ የፖለቲካ መጠቀሚያ ሲሆን፣ ሕግ ንፁሃንን እያሰረ ወንጀለኞችን ሲንከባከብ የሀገሪቱ ትልቁ የሕግ አካል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዝምታ አደገኛ ነው።ይህ ሁሉ መንጋ ድንጋይ፣ አጠናና ስለት ተሸካሚ ጦር በአንድ ግለሰብ መሪነት አገር ሲያምስ፣ ሲገድል፣ ሲያቆስል፣ ንብረት ሲያወድም ዝምታን መምረጧ ኋላፊነቷን በአግባቡ ላለመወጣት ዘገምተኝነት ማሳየቷ ከተጠያቂነት አያድናትም። #MinilikSalsawi ምንሊክ ሳልሳዊ

Image may contain: 1 person, smiling

መንግስት የዜጐችን ደህንነት የማስጠበቅ ኃላፊነቱን ይወጣ!! የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ (ኢሰመጉ)

(ጥቅምት 17 ቀን 2012 ዓ/ም)

የኢፌዲሪ ሕገ-መንግሥት ክፍል አንድ አንቀፅ 14 ማንኛውም ሰው ሰብዓዊ በመሆኑ የማይደፈርና የማይገሠሥ፣ በሕይወት የመኖር፣ የአካል ደኅንነትና የነጻነት መብት እንዳለው ይደነግጋል፡፡ ማንኛውም ሰው በሕይወት የመኖር መብት እንዳለውና በሕግ በተደነገገ ከባድ የወንጀል ቅጣት ካልሆነ በስተቀር ሕይወቱን እንደማያጣ በሕገ መንግሥቱ አንቀፅ 15 ላይ ሠፍሯል፡፡ የሕገ መንግሥቱ አንቀፅ 32(1) ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ወይም በሕጋዊ መንገድ ሐገሪቱ ውስጥ የሚገኝ የውጭ ዜጋ በመረጠው የሐገሪቱ አካባቢ የመዘዋወርና የመኖሪያ ቦታ የመመሥረት መብት እንዳለው በግልጽ አስቀምጧል፡፡ እንደዚሁም፣ አንቀፅ 40 (1) ለማንኛውም ኢትዮጵያዊ ዜጋ የግል ንብረት ባለቤትነት መብት አጎናጽፏል፡፡

ኢትዮጵያ የተቀበለችውና የሕጓ አካል ያደረገችው የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ዓለም ዓቀፍ ቃል ኪዳን በአንቀፅ 2 እያንዳንዱ ይህንን ቃልኪዳን የተቀበለ አገር በግዛቱ ውስጥ ለሚኖርና በሥሩ ለሚተዳደር ማንኛውም ሰው በዘር፣ በቀለም፣ በፆታ፣ በቋንቋ፣ በሃይማኖት፣ በፖለቲካ ወይም ሌላ አመለካከት፣ በብሔራዊም ሆነ ማኅበራዊ አመጣጡ፣ በሀብት፣ በውልደት ወይም በሌላ መለኪያ ምንም ልዩነት ሳያደርግ በዚህ ሕግ ዕውቅና ያገኙትን መብቶችና ነፃነቶች እንዲያስከብር ግዴታ ይጥላል፡፡ በተመሳሳይ፣ ኢትዮጵያ ፈርማ የተቀበለችው የአፍሪካ የግለሰቦችና የሕዝቦች መብቶች ቻርተር አንቀፅ 1 በሠነዱ ውስጥ የተጠቀሱትን መብቶች የማክበር፣ የማስከበርና መብቶቹ የሚከበሩባቸውን ሁኔታዎች የማሟላት ግዴታ፣ በፈራሚ ሐገራት ላይ ይጥላል፡፡

እነዚህን የዜጎችን የአካል ደኅንነትና ነጻነት እንዲሁም የንብረት ባለቤትነት መብቶች የመጠበቅ ኃላፊነት በግንባር ቀደምትነት የተጣለበት መንግሥት ነው፡፡ ይሁንና እነዚህ ሐገራዊ፣ አሕጉራዊና የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌዎች ባለመከበራቸው እና መንግስት የማስከበር ኃላፊነቱን ባለመወጣቱ ከዚህ በታች የተዘረዘሩት የመብት ጥሰቶች ተፈጽመዋል፡፡

~ ከጥቅምት አንድ ቀን 2012ዓ.ም ከሌሊቱ ዘጠኝ ሰዓት ጀምሮ እስከ ጥቅምት ሁለት ቀን 2012ዓ.ም ከቀኑ 10 ሰዓት ድረስ አፋር ክልል አፋምቦ ወረዳ ‹‹ሰንጋ›› በሚባል መንደር ከሌላ አካባቢ መምጣታቸው በተገለጸ ታጣቂዎች በተፈጸመ ጥቃት የ17 ሰዎች ሕይወት ጠፍቷል፣ በርካታ ሰዎች የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል፤

~ ጥቅምት 11 ቀን 2012ዓ.ም ሌሊት አክቲቪስት ጃዋር መሐመድ በማኅበራዊ ድረ ገጽ ‹‹ጥበቃ እንዲያደርጉልኝ የተመደቡልኝ የጸጥታ ኃይሎች ሊነሱብኝ ነው፡፡ ቤቴም በጸጥታ ኃይሎች ተከብቧል›› የሚል መልዕክት በማስተላለፋቸው መልዕክቱን የተቀበሉ በመቶዎች የሚቆጠሩ ወጣቶች ሌሊቱን ወደ ግለሰቡ መኖሪያ ቤት አምርተዋል፤ በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ አካባቢዎችም የአክቲቪስቱ ደጋፊዎችና ተከታዮች በመሰባሰብ መንገድ ዘግተው የተቃውሞ ሰልፍ አድርገዋል፡፡ ይህ የተቃውሞ ሠልፍ ወደ ግጭት አምርቶ የበርካታ ዜጐች ሕይወት ጠፍቷል፣ በብዙዎች ላይ የአካል ጉዳት ደርሷል፣ ግምቱ ያልታወቀ ከፍተኛ ንብረት ወድሟል፣ የዜጐች ያለሥጋት የመንቀሳቀስ መብታቸው ተገድቧል፣ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ ባንኮች፣ የንግድ ድርጅቶችና ት/ቤቶች ተዘግተዋል፡፡

ይህ አስቸኳይ ጋዜጣዊ መግለጫ ይፋ እስከሚሆንበት ሰዓት ድረስ ኢሰመጉ በተለያዩ አካባቢዎች ከሚገኙ ምንጮቹ በሰበሰበው መረጃ መሠረት ግለሰቡ ያስተላለፉትን መልዕክት ተከትሎ በተነሣው ተቃውሞና በተፈጸመው ብሔርና ሃማኖት ተኮር ጥቃት በምሥራቅ ሐረርጌ ዞን፣ በሐረር ከተማ፣ በአወዳይ ከተማ፣ በድሬዳዋ ከተማ፣ በአዳማ፣ በባሌ ዞን ዶዶላ ወረዳ፣ በአምቦ ከተማ፣ በአርሲ ዞን ኮፈሌ ወረዳ፣ በዝዋይ ከተማ፣ አርሲ ነጌሌ፣ በባሌሮቤ በድምሩ ቁጥራቸው ከ67 በላይ ሰዎች መገደላቸውን፣ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች አካላዊ ጉዳት ደርሶባቸዋል፣ በርካታ የንግድ ድርጅቶች መቃጠላቸውን፣ በብዙ ከተሞች የንግድ እንቅስቃሴና ተቋሞች ተዘግተው መዋላቸውን አረጋግጠናል፡፡ ከሟቾቹ ውስጥ በርካቶቹ ጭካኔ በተሞላበት ሁኔታ በድንጋይ እና በዱላ ተወግረው መገደላቸው ሁኔታውን ይበልጥ አሰቃቂ አድርጐታል።

ኢሰመጉ የቆመው ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መዳበር፣ ለሕግ የበላይነት መስፈንና ለሰብዓዊ መብቶች መከበር ነው! EHRCO stands for Democracy, the rule of Law and the respect of Human Rights. በተጠቀሱት ሥፍራዎች እና በሐገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በተደጋጋሚ ከሚፈጠሩ ሁከቶች ጋር ተያይዞ ብሔርን እና እምነትን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶችና ግጭቶች በዜጎች ላይ ሲፈጸሙ ተስተውለዋል። ይሁን እንጂ ከዚህ በፊት በተደጋጋሚ እንደተስተዋለው ሁሉ የዞንና የወረዳ አስተዳደር አመራሮች እንዲሁም የጸጥታ አካላት በሕግ የተጣለባቸውን ለዜጎች ጥበቃ የማድረግ ግዴታ ባለመወጣታቸውና በፍጥነት ድርጊቶቹን ባለመቆጣጠራቸው ችግሩ በከፍተኛ መጠን ተባብሶ ወደ ከፍተኛ ቀውስ እያመራ ይገኛል። መንግሥት በተለይም ባለፉት ሁለት ዓመታት በተለያዩ አካባቢዎች መሠል ድርጊቶች ሲፈጸሙ በዝምታ መመልከቱ፣ የድርጊቶቹን አነሳሾች እና ፈጻሚዎች በሕግ ፊት ተጠያቂ ባለማድረጉ በመቶዎች የሚቆጠሩ ንጹሃን ክቡር ሕይወታቸውን አጥተዋል፣ አካላቸው ጐድሏል፣ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ከመኖሪያ ቀዬአቸው ተሰድደዋል፣ ዜጐች ለማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ተዳርገዋል፣ የሕዝቡ ተቻችሎ እና ተከባብሮ የመኖር ዕሤቶችን እንዲሸረሸር አድርጓል።

ይህ መግለጫ በሚጠናቀርበት ወቅትም ዜጎችን ብሔርና ሃይማኖትን መሠረት ላደረጉ ጥቃቶችና ግጭቶች ዒላማ የሚያደርጉ መልዕክቶች በማኅበራዊ ድረ ገጾች በስፋት እየተሰራጩ ይገኛሉ።

በተጨማሪም፣ በኦሮሚያ ክልል በባሌ ሮቤ እና በዶዶላ ወረዳዎች ለኢሰመጉ በስልክ በደረሰው መረጃ መሠረት አሁንም ተጨማሪ ጥቃት ለመፈጸም በጥቃት አድራሾቹ እየተዛተባቸው እንደሚገኝ፤ በዚህም ምክንያት ለሕይወታቸው በመሥጋት ከአራት ሺ በላይ የሚሆኑ ሰዎች በሁለት አብያተ ክርስትያናት ተጠልለው እንደሚገኙና በርካቶችም በቤታቸው ውስጥ በፍርኀትና በጭንቀት የድረሱልን ጥሪ እያቀረቡ ይገኛሉ፡፡
እንዲሁም፣ በድሬዳዋ ከተማ በተለያዩ አካባቢዎች ሃይማኖትንና ብሄርን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶች በስፋት እየተፈጸሙ ይገኛሉ፡፡ ይህ መግለጫ በሚጠናቀርበት ወቅትም የከተማዋ ነዋሪዎች በከፍተኛ ሥጋትና ፍርኀት ውስጥ እንደሚገኙ፣ ከሌላ የሐገሪቱ አካባቢዎች የመጡና ጥቃቱን የሚፈጽሙ ወጣቶች የጦር መሣሪያዎች እና ድምፅ አልባ የስለት መሣሪያዎች የታጠቁ እንደሆኑ ከአካባቢው ለኢሰመጉ እየደረሱ ያሉ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ የሐገር መከላከያ ሠራዊትም ግጭቱን ለመቆጣጠር ጥረት በማድረግ ላይ እንደሚገኝ ምንጮቻችን አረጋግጠዋል፡፡

መንግሥት ለእነዚህም ሆነ ለተመሳሳይ ድርጊቶች ሕጋዊ እና የማያወላውል እርምጃ በመውሰድ የዜጐችን በሕይወት የመኖር፣ አካላዊ ደኅንነት እና በፈለጉት የሐገሪቱ አካባቢዎች በነጻነት ተንቀሳቅሰው የመኖር መብታቸውን እንዲያከብር እና እንዲያስከብር ኢሰመጉ በድጋሚ ያሳስባል።

በተጨማሪም መንግሥት፡-
~በተለያዩ የብዙኃን መገናኛ ዘዴዎች አማካይነት ዜጎችን ለጥቃትና ለግጭት የሚያጋልጡ ቀስቃሽ መልዕክቶችን የሚያሠራጩ አካላትን እንዲቆጣጠር፣
~ተገቢውን ማጣራት በማድረግ ድርጊቱን ባነሣሡና የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶችን በፈጸሙ ግለሰቦችና አካላት እንዲሁም ይህንን የመከላከልና የመቆጣጠር በሕግ የተጣለ
ባቸውን ኃላፊነት ሳይወጡ በቀሩ የፀጥታ ኃይሎች እና የመንግሥት ኃላፊዎች ላይ ሕጋዊ እርምጃ እንዲወስድ፣
~ጉዳዩ ተጣርቶ የአካል ጉዳት ለደረሰባቸው፣ ለሟች ቤተሰቦች፣ ቤት ንብረት ለወደመባቸውና ለተፈናቀሉ ዜጎች ካሣ እንዲከፍል እንዲሁም ሰብዓዊ ድጋፍና ርዳታ የሚያገኙበትን መንገድ እንዲያመቻች፣
~በክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች በስፋት የሚስተዋለው የአክራሪ ብሔርተኛነት አስተሳሰብን መሠረት ያደረጉ ኢ-መደበኛ ቡድኖች እያደረሱ ያሉትን ጥፋት ለማስቆም የሚያስችል አስቸኳይ መፍትሄ በመስጠት ሕጋዊ እርምጃ እንዲወሰድ፣
~በፌዴራል መንግሥት አካላትና በክልል መስተዳድሮች መካከል ያለው ግንኙነት ሕግን መሠረት ያደረገና የሕዝቦችን የጋራ ተጠቃሚነት ያስከበረ መሆኑን እንዲያረጋግጥ፣
~በየደረጃው የሚገኙ የመንግሥት አካላት ፖሊቲካዊ ቁርጠኛነቱ ኖሯቸው የዜጎችን ሕይወትና የአገርን ሕልውና አደጋ ላይ የሚጋርጡ የጅምላ የወንጀል ድርጊቶችን እንዲያስቆሙ፣
~ግለሰቦችም በተለያዩ ሚዲያ እየተሠራጩ የሚገኙትንና ሕዝብን ለግጭትና ለጥቃት የሚያነሣሡ ንግግሮችና የሐሰተኛ መረጃ ከመፈብረክና ሳያመዛዝኑ ከማሠራጨት በመቆጠብ የበኩላቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ፣ በየአካባቢው የሚፈጸሙ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶችን እንዲቃወሙና ድርጊቶቹን እንዲከላከሉ ኢሰመጉ ጥሪውን ያቀርባል፡፡

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ /ኢሰመጉ/ ለሕግ ልዕልና፣ ለዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታና ለሰብዓዊ መብቶች መከበር የቆመ ድርጅት ነው፡፡
ሁሉም መብቶች ለሁሉም!!

ኢሰመጉ በአፍሪካ የሕዝቦችና የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን የታዛቢነት ቦታ አለው፤ የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ፌዴሬሽን (FIDH) አባል፣ የዓለም ዓቀፍ ጸረ-ሥቃይ ድርጅት (OMCT) አባልና የምሥራቅና የአፍሪካ ቀንድ የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾች ጥበቃ ኅብረት (DefendDefenders) መሥራች አባልም ነው፡፡

ቆንጨራ አከፋፋዩ ማነው!? አብይ ስልጣንዎን ይጠቀሙ ወይ ለሕዝቡ ቁርጡን ይንገሩ!! – ሀብታሙ አሰፋ

የሕወሓት መሪዎች ከስልጣን እንደወረዱ ሰሞን ቆንጨራ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ያከፋፍሉ ነበር። ከዚህ ሁሉ የሚታወሰው አባይ ጸሐይዬ በቤንሻንጉል ድብቅ ስብሰባ አድርጎ በወጡ ማግስት ለዕቅዱ ተግባራዊነት አንድ መኪና ቆንጨራ በክልሉ ፖሊስ ተይዙዋል።ይሄ አብይ ስልጣን ላይ የወጡ ሰሞን የሆነ ነው። ሰሞኑን በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ ከተሞች ፣በድሬዳዋ እና በሐረር ጥቃት አድራሽ አሸባሪዎች በጭካኔ ያጠፉት ሕይወት ሳያንስ ሌላ ንጹሃንን የመቅጠፍ ዓላማ አለ?እነ ከማል ገልቹ እና ብ/ጄ/ል ሀይሉ ጎንፋ አባይ ወልዱ እንዳሉት ጦርነቱን አማራ ክልል ለማስገባት በየበኩላቸው እየሰሩ ነው። ያው ከማል መደበኛ ሰራዊት እስላማዊ መንግስት እስኪመሰረት የቄሮን ብጌግድ ማዘዝ ከጀመሩ ውለው አድረዋል። ሥራ ሳይኖራቸው ከመንግስት ድጎማ በላይ ለቄሮ በጀት ከየት አምጥተው ነው የሚሰጡት!? ስለ ወሎ ሲቃዡ አሩሲንም ማጣት እንዳለ ዘንግተው ይሆን? ሰው እንዴት ይህን ያህል ዓመት የኦሮሞ ፖለቲካ ውስጥ ሲዳክር ኖሮ ያለውን እውነታ መረዳት ያቅተዋል! መጥኔ ነው።

ብ/ጄ/ል ከማል ገልቹ የሚመሩት ፓርቲ ተወካይ አቶ ሊበን ዋቆን ብዙ ሰው ያስታውሳቸዋል።የለንደኑ ኮንፈረንስ ላይ ኢትዮጵያ ካልፈረሰች የኦሮሞ ጥቅም አይከበርም ያሉትን? አሁን እንኩዋን በቅርቡ የጃዋር ቲቪ ላይ እየቀረቡ ኦዴፓን ይዘነጥሉት ነበር ።ልጃቸው ደግሞ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽ/ቤት ቤተኛ የዲሲው ኤምባሲ አፈ ቀላጤ ነች።ጠንቃቃ መንግስት እንዲህ ነው።

የ80ዓመት የአልጋ ቁራኛን በጭካኔ መግደል፣መቆራረጥ፣ህጻናት እና ሴቶችን ሳይቀር በግፍ መግደል አይበቃም!? መንግስት እሹሩሩ ያለው ሀይል በስልጣን ጥቅም የናወዙ አንዳንድ የኦዴፓ አመራሮች፣ጃዋር እና ጋሻ ጃግሬዎቹ ከምንም ጊዜ በላይ ተናበው ይሰራሉ። ሕወሓት ደግሞ አብሮ መሰለፉን ትላንት ስንናገር የነበረው ዛሬ የዶ/ር ደብረጺዮን ኢሜል ሲዘረገፍ እንደ አዲስ እየሰማን ነው።

አብይ ሕወሓትን ሲያሽሞነሙኑ ከፈሰሰው ንጹሃን ደም ይልቅ ያኮረፈውን ጃዋርን ሲያባብሉ ዛሬ አምቦ ላይ ደሞዝ የሚከፍሏቸው ካድሬዎች ጃዋር ከሚያዘው የኢትዮጵያው አይ ሴስ ኔትዎርክ ጋር ተቀናጅተው ተቃወሙዋቸው።ነገሩ ከዚያም የከፋ ግርግር ለመፍጠር ያለመ ነበር ይባላል አዳራሽ መግባት ቄሮ ተከልክሎ ነው ሰንካላ ምክንያት ነው። ምንም ይፈልግ አብይን መቃወም ነው።

የሰው አንገት ቆርጦ፣የሴት ጡት ቆርጠው፣በድንጋይ እና በዱላ ጭካኔ በተሞላበት ሁኔታ ከ70 እስከ 80 ንጹሃንን የጨፈጨፉትን የየአካባቢው ባለስልጣናት እና አንዳንድ ባለሀብቶች ከየት አምጥተው ነው ማበረታቻ የገንዘብ ድጎማ፣ግብዣ የሚያደርጉት? የግድ መንግስት ግብጻዊ ወይ ቱርካዊ ብር ሲያድል ማየት አለበት!?

የሐረሩ ስብሰባ ላይ ከተማው ውስጥ ዋናውን ሽብር ሲያስተባብሩ የነበሩ የሰላም ኮንፈረስን ተሳትፈው፣የጠቅላዩን ስኮርት በጅማ እና በአርሲ ያለውን ፍቺ አብራርተው ጃዋርን ለማጥቃት እንዳልተፈለገ አለሳልሰው ሲናገሩ ተገኝተው አበላቸውን ጭምር በልተው ለምን አምቦ ሲሆን ይከለከላሉ?

በኦሮሚያ የእነ አብይ መንግስት መደበኛውን የአስተዳደር መዋቅር ሲጠቀም ማነው ቄሮ በጎን ራሱን አደራጅቶ፣አብሮ እየተሰበሰብ አብሮ እየወሰነ ብዙ ቦታ የቄሮ ተወካይ ከባለስልጣናቱ የበለጠ ተሰሚ ሆኖ በሚያስተዳድረው ክልል አብይ እንዴት ዘው ብለው ስብሰባ ይሄዳሉ? አንዳንዶች በብሽቀት እንደሚቀልዱት ስብሰባውን ጃዋር ፈቅዶላቸዋል!?

ሰውዬው ስልጣን እና ሀላፊነታቸውን በአግባቡ ባለመወጣት አሁን ጉሮሯቸውን ሊያንቁት ደርሰዋል። የኦዴፓ አመራሮችም ለሁለት ጌታ ከመገዛት ወደ አንዱ ለመጠቃለል ያሰቡ ይመስላል።ያው የድሮ ጌቶቻቸው ይሻሉናል ብለው አራት ኪሎን ይዘው አዲስ አበባን፣ድሬዳዋ፣ሐረር እና ወሎን አጠቃለው ታላቅ የኦሮሞ አገር ሲመሰርቱ እየቃዡ ህልማቸውን መቀሌ ማስፈታት ከጀመሩ ውለው አድረዋል ።ይሄ ሁሉ ኢትዮጵያን አፍርሰው ነው።ይህን የሚያደርጉት ደግሞ በኔትዎርክ ድንጋይ እና ዱላ ይዘህ ውጣ ተብለው የሚታዘዙት ሳይሆን ለሳቸውም ለጃዋርም እኩል መገዛት የሚያምራቸው የኦዴፓ ሰዎች እና መንግስት ቀለብ የሚሰፍርላቸው የኦሮሞ ጎምቱ ፖለቲከኞች ናቸው።

አሁንም አብይ የባከነ ሰዓት አላቸው።ከአራጅ ጋር ለፖለቲካ ትርፍ ያደረጉት መልመጥመጥ እንዳልጠቀማቸው አምቦ ግልጽ አድርጎላቸዋል። ጃዋርን ሳይሆን ክርስቲያን ታደለን እንደ ስጋት ማየታቸው ውርደታቸውን ካልሆነ ማሻገሩ ቀርቶ ውርደት የሚያስቀርላቸው አይመስልም።ምን ችግር አለ ነፍጠኛ እንደሁ ተብለዋል። የጃዋር መንግስት ደግሞ ነፍጠኛ ብሎ ለፈረጀው እንደ ሕወሓት ጥፍር በመንቀል፣ዘር በማኮላሸት የሚወሰን ሳይሆን ሰው በቁሙ የሚያርድ፣ሴትን አይኑዋ እያየ ጡት የሚቆርጥ አገር በቀል አይ ኤስ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ስለዚህ በቀረችዎ ጥቂት ጊዜ እባክዎ ተዋርደው አገሪቱዋን አያዋርዱዋት። ቆንጨራ አከፋፋዮችን እና ጽንፈኛ ሰው አራጆችን በፓርቲው ያሉ እና ለደህንነቱ የሚጨነቁለት የሁለተኛው መንግስት መሪ ስር የተደራጁትን ከቻሉ ቢያንስ ያስታግሱ ካልቻሉም በግልጽ ይናገሩ ።ዋና ዋናዎቹን ለፍርድ ማቅረብ ፍላጎት ከሌለዎ ሕዝቡ የራሱን ውሳኔ ይወስን።ካልሆነም ቢያንስ የሀይለማርያምን ልብ ይስጥዎ።በግልጽ ለአገሪቱ መረጋጋት ሲሉ አስቸኩዋይ መፍትሄ መስጠት ግዴታዎ ነው ።ጨው ለራስህ ስትል ማለት ይሄኔ ነው። ስልጣን ከወጡ ወዲህ የተናገርነውም ይህንኑ ነበር። ጠቅላዩ የባከነ ሰዓታቸውን ተጠቅመው ራሳቸውንም አገሪቱንም ይታደጉዋት ይመስልዎታል የበኩልዎን አስተያየት ይስጡበት። ዝም ከማለት ቢያንስ እያስጠነቀቅን ወይም እየተጠነቀቅን የማይቀረውን ቀን ለማስቀረት በጋራ መቆም ይገባል።

ሀብታሙ አሰፋ

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይፈቱ! – ያሬድ ኃይለማርያም

መቼም ይህ ሁሉ ውርጅብኝ በአገር እና በሕዝብ ላይ እንደማያባራ ዝናብ ሲወርድ ዝም ማለትዎ አንድም አቅም ማጣት፣ አንድም በፓርቲ ሰንሰለት ተጠርንፈው፣ አንድም ከብሽቀት፣ አለያም ምን ይዤ ነው ሕዝብ ፊት የምቀርበው ከሚል በሰዋዊ ስሜት ተውጠው ይሆናል። ወይም እኛ ልንገምተው ያልቻልነው ሌላ ችግር ገጥሞዎት ይሆናል።
ለማንኛውም ግን ዝምታዎ እስከ አሁን ግርምታን ፈጥሯል። ከዚህ ካለፈም እና በዚሁ ከዘለቁም ውስጣችን ሌላ ጥርጣሬን ይጭራል።

በእኔ በኩል የፖለቲካ እስረኛ የሆኑ ስለመሰለኝ እነ ኤሊያስ ገብሩ እንደተፈቱት ጠቅላይ ሚኒስትሩም፤ በዋስም እንኳ ቢሆን ይፈቱልን ልል ትንሽ ነው የቀረኝ። አዎ በድርጅታዊ ትብታብ እና በመንጋዎቹ ማስፈራሪያ ተጠርንፈው የህሊና እስረኛ ሆነዋል ብዮ ባስብ ይቀለኛ እርሶን ከበዳዮች ጋር አብረዋል ወይም ከበዳዮች ተርታ ተሰልፈዋል ከማለት።

አዎ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይፈቱ!

ይፈቱ እና ለቅሶ ይድረሱ፤ ይፈቱና የድረሱን ጣር ድምጽ እያሰሙ ላሉት ወገኖች አጋርነትዎትን አሳዩ፣ ይፈቱና በዳዮችን በስም እየጠሩ ያውግዙ፣ ለፍርድ ያቅርቡ፤ ይፈቱና የደረሰውን ጉዳት ልክ ቡራዩና ጌዲዮ ሄደው እንዳደረጉት ይጎብኙ፤ ይፈቱና የጠቅላይ ሚኒስትርነት ስራዎትን በአግባቡ ይሥሩ፤
አዎ ጠቅላይ ሚንስትሩ ከተተበተቡበት ድርጅታዊ ማነቆ፣ ለሕግ የበላይነት ካላቸው የተዛባ ግንዛቤ፣ ከገጽታ ግንባታ እና ድራማ ከሚመስሉ ሥራዎች ይፈቱ! ይፈቱ! ይፈቱ!

እኛና ይፈቱ የምትለዋ ቃል ለአሥርት አመታት አብረን እንዳለን አለን፤ ትላንት እስክንድር ይፈታ፣ በቀለ ይፈታ፣ መራራ ይፈታ፣ ኤሊያስ ይፈታ፣ እገሌ ይፈታ ስልንል ቆይተናል። ዛሬ ዘቅጠን ይሁን ወግ ደርሶን ጠቅላይ ሚኒስትሩም ይፈቱ ለማለት በቅተናል። አዎ ከተተበተቡበት የኢህአዴግ ፖለቲካ ይፈቱ ወይም ይፋቱ እና ይችን አገር ይታደጓት። ካለዛ ከሕዝብ ጋር መፋታትም አለ። ያኔ ቅጣምባራችን ይጠፋል። ይች አገር አሁን ያለችበት ሁኔታ ሌላ አቢዮት ወይም የመንግስት ስር ነቀል ለውጥ እንድታስተናግድ የሚፈቅድ አይደለም። እንኳንም ዘንቦብሽ ነው ነገሩ። እንኳን መንግስት ተፈንቅሎ ገና በመንገዳገዱ ብቻ ንጹሃን በጠራራ ጸሃይ እየታረዱ አስከሬናቸው በአደባባይ በገመድ ሲጎተት እያየን ነው። ኢትዮጵያ እንዲህ አስነዋሪ፣ አዋራጅ እና አንገት የሚያስደፋ ነገር ገጥሟት የሚያቅ አይመስለኝም።

ከለየለት አንባገነናዊ ሥርዓት ጋር መታገል ወግ ነው። ትግሉም መልክ ይኖረዋል። የገዛ ወገኑን፣ ሕጻናትን፣ አዛውንትን፣ ህሙማንን፣ ሴቶችን በእሳት እያቃጠለ፣ ሰውነት እየቆራረጠ በጅምላ የሚጨፈጭፍ መንጋ ገጥሟት አያውቅም ብል ማጋነን አይሆንም።

ለማንኛውም የኢትዮጵያ ሕዝብ ዛሬ ለእርሶ ደብዳቤ ጻፍ ቢባል ይህን የሚል ይመስለኛል፤

ይድረስ ለዶ/ር አብይ፤ እርሶ እንደምን አሉ? እኛ እንዳለን አለን፤ እንደተሸበርን፣ እንደተሳቀቅን፣ ፍርሃት እንደዋጠን፣ የገዛ ጥላችን ከመንጋዎቹ ውስጥ አንዱ እየመሰለን እየተገላመጥን፣ ወጥተን እስክንገባ ምን ይገጥመን ይሆን የሚል ስጋት ይዞን እግዚያ ማህረነ አስራ ሁለት ጊዜ እያል፣ እረ የመንግስት ያለህ አስራው ሁለት ጊዜ ደጋግመን እየቆጠርን እኛ እንዳለን አለን፤

+ አገር በመንጋዎች ሲታመስ፣ የንጹሃን ዜጎች ደም በግፈኞች በትር ሲፈስ እርሶ እንደምን አሉ?
+ ክቡሩ የሰው ገለ በሜንጫ፣ በዱላ፣ በጥይት ሲወቃ፣ ሲደቃ፤ ሃዘን በየቤቱ ጉዋዙን ይዞ ገብቶ እንባ እያራጨ ሕዝብ ደረት ሲደቃ እርሶ እንደምን አሉ?
+ እልጆቻቸው ፊት ባሎቻቸውን መንጋ የነጠቃቸው ኢትዮጵያዊ እናቶች በየመጠለያው ታጉረው፣ ታርዘው የመንግስትዎ ያለህ እያሉ ሲጮሁ እርሶ እንደምን አሉ?
+ ስንት ጀግኖች ወድቀው ያቆያቱን አገር በመንጋዎቹ ሰልፍ በታበየ አንድ ቀልብ የራቀው ጎረምሳ ስትታመስ፣ እኛም አብረን እንደ ገብስ ቆሎ ስንታመስ፣ ስንወቀጥ፣ ስንታኘክ እርሶ እንደምን አሉ?
+ በዛ ውብ ቃልዎ ያጽናኑናል ብለን፣ በዛ እሩህሩ ልብዎ፣ አዛኝ ስበዕናዎ አደባባይ ወጥተው አይዟቹ ይሉናል ብለን ብንጠብቅ የውሃ ሽታ መሆንዎ ምነው? እርሶ እንደምን አሉ?
+ ፍቅር ያሸንፋል በሚል መርህዎ ጽናትን ሊያሰርጹ የጀመሩት ጎዞ እንዲህ ያለ የግፍ ናዳ ሲወርድበት እያዩ ምነው መጥፋትዎ? እርሶ እንደምን አሉ?
+ ማቅ ለብሰን ማቅ ወርሰን አንድም እንዲያጽናኑን፣ አንድም በዳዮቻንን ለፍርድ በማቅረብ ፍትሕ አንግሰው እኛን እንዲክሱን ደጅ ደጁን እያየን ስንጠብቅዎ አንዴ ወደ ሐረር፣ አንዴ ወደ አንቦ እየገሰገሱ ግራ እንደገባው ሰው ክው ከው ማለትዎ? ከግፉዋን ጩኸት ይልቅ የመጋው ቁጣ ያስደነበርዎ? እርሶ እንደምን አሉ?

ቅዱስ መጽሃፉ በሆነ ገጹ እና በሆነ ምእራፉ ላይ “የግፉዋን አፍ ጥልቅ ጉድጓድ ነው” ይላል። ይህ ጉርጓድ ብዙዎችን ውጧል። የዛሬዎቹን በመንጋ የተደራጁ ግፈኞችም እንደሚጥ አንጠራጠርም። አብሮ እንደ እርሶ ያሉ ደግ ሰዎችን እንዳይውጥብን ግን አጥብቀን እንሰጋለን።

በየአደባባዩ ምስልዎትን ለብሶ ድጋፉን ካሳየዎት እና የመንጋ ሰለባ ከሆነው ሕዝቦ የተጻፈ።

ያሬድ ኃይለማርያም

“ቀይ መስመር ተጥሷል…!!!” ፕ/ት ሳህለወርቅ ዘውዴ

ሰሞኑን በአዲስ አበባ እና በተለያዩ የኦሮሚያ ከተሞች ውስጥ በአብዛኛው ዘር እና ሀይማኖትን ኢላማን ያደረገው እና ለበርካታ ዜጎችን ህይወት እንዲቀጥፍ ምክንያት የሆነው ጭፍጨፋ “ቀይ መስመሩን ያለፈ ነው” ሲሉ ፕ/ት ሳህለወርቅ ዘውዴ ድርጊቱን በጽኑ አወገዙ።

ፕ/ት ሳህለወርቅ በወዳጆች መገናኛ መረብ የቲውተር ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት ጽሑፍ” ዘር እና ሀይማኖት ለፖለቲካ ጥቅም እንዲውሉ ሲደረግ፣ንጹሀን እና ሰላማዊ ዜጎቻችን በአሳቃቂ ሁኔታ ሲገደሉ፣ሲፈናቀሉ እና ሲሰደዱ ስናይ ስሜትን ለመግለጽ ቃላት ያጥራል፣ለቅሶ ድንጋጤ እና ስጋት የብዙዎችን በርን አንኳኩቷል።ሀዘናቸው ሀዘኔ ነው”በማለት እጅግ አሳዛኝ እና አሳፋሪ በሆነው ድርጊት መቆጨታቸውን በግላጭ ተናግረዋል።
ወደ ፕ/ትነት ስልጣን ከመምጣታቸው በፊት ኢትዮጵያን እና ህዝቦቿን በመወከል ከሰላሳ አመት በላይ በዲፕሎማትነት ያገለገሉት ፕ/ት ሳህለወርቅ የትዊተር መልክታቸውን ሲቀጥሉ”ለሀገር እና ለህዝብ ጥቅም ሲባል ልናሰምረው እና ልናከብረው የሚገባው ቀይ መስመር ተጥሷል፣ሀገራችን ካንዣበበባት ክፉ አደጋ ለማዳን ሁላችንም ሚና አለን፣የሚመለከታቸው ሁሉ የየበኩላቸውን ሀላፊነትን መጫወት አለባቸው፣ቀዩ መስመር መጣስ የለበትም እንበል”በማለት ስርአት አልበኞችን መዋጋት ለአንድ ተቋም ብቻ የሚሰጥ ሳይሆን በሀገሬ ጉዳይ ያገባኛል የሚል ሰላም ወዳድ ዜጋ ሁሉ እርብርቦሽ እንዲያደርግ ተቃውሞ አዘል ጥሪ አቅርበዋል።

እንደ የኢትዮጵያ የሰብአዊ መብት ኮሚሽን መግለጫ ከሆነ በሰሞኑ ግጭት ከሰማኒያ በላይ ዜጎች ህይወታቸውን ያጡ ሲሆን የአሟሟታቸውንም ሁኔታ በተመለከት ኮሚሽኑ እንደታዘበው አስር የሚሆኑት ብቻ በጥይት ተመትተው የሞቱ ሲሆን የተቀሩት በድንጋይ ተወግረው፣በስለት ተወግተው እና በዱላ ተጨፍጭፈው እንዲሞቱ መደረጉን የኬሚሽኑ መግለጫ ይገልጻል።
ከዚህ በመቀጠልም ከወንጀሉ ጋር በቀጥተኛ ሆነ በተዘዋዋሪ ግንኙነት ያላቸው በሙሉ በህግ እንዲጠየቁ አሳስቧል።
የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን በበኩሉ ከስሞኑ እልቂት ጋር የተጠረጠሩ ወደ ሶስት መቶ ሀምሳ ዘጠኝ ግለሰቦችን በቁጥርጥር ማዋሉን አስታውቋል።

(በታምሩ ገዳ/ህብር ራዲዮ)

ሃሰተኛው ዶክተር (አቶ ጸጋዬ አራርሳ) እና የዘር ጥላቻ ቅስቀሳው – አበበ ገላው

ሃሰተኛው ዶክተር አቶ ጸጋዬ አራርሳ

የጥላቻ ፖለቲካ አቀንቃኝ በመሆን የተዛባና መርዘኛ የሆነ “ትንታኔ” በመስጠት ህዝብን በህዝብ፣ ድሃን በድሃ ላይ በማነሳሳት ላይ ከሚገኙ የጃዋር ጋሻ ጃግሬዎች አንዱ አቶ ጸጋዬ አራርሳ መሆኑ ያደባባይ ሚስጥር ነው። በትናንትናው እለት ባጋጣሚ ፌስቡክ ላይ ላይቭ ወጥቶ ሲዘባርቅ እንደምንም ለትንሽ ደቂቃ ታግሼ እየጎመዘዘኝም ቢሆን ሰማሁት።

አገራችን ላይ የተፈጠረውን ሰቆቃና እየመጣ ያለውን ከባድ የእልቂት ድግስ ባላገናዘበ መልኩ በትንታኔ ስም ያለምንም እፍረት ከፋፋይና ጸረ-ኢትዮጵያ ዲስኩር ሲያሰማ አየሁት። ሃላፊነት ለሚሰማው ማንም ግለሰብ ከባዱ ነገር ያልኖርንበትን ታሪክ ለቁርሾ፣ ለጥላቻና ህዝብ ለማጋጨት መርዝ መርጨት አይደለም። ከባዱ ነገር ካለፈው በጎም ይሁን ክፉ ታሪክ ተምሮ የተሻለና ለሁሉም ዜጋ ፍትሃዊ የሆነ ስርአት መፍጠር ነው። የኢትዮጵያም ትልቁም ፈተና ይሄው ነው። ጥላቻ ለመስበክ ግን ማንም ቀለም መቁጠር አይጠበቅበትም።

ከሁሉ በላይ ያስገረመኝ አቶ ጸጋዬ ያለምንም ሃፍረት አሁንም ዶክተር የሚል የሃሰት ታፔላ ለጥፎ “ተንታኝ” እየተባለ በየመስኮቱ ብቅ ማለቱ ነው። አንድ ሰው እንኳን ህዝብን ተራ ግለሰብን ለማጥላላት አደባባይ ከመውጣቱ በፊት እራሱን በአግባቡ ማወቅ አለበት።

አቶ ጸጋዬ ሆይ! አንተ ያልሆንከውን ሆነህ ሌላውን ለምን ታምታታለህ። ትምርትህን ባግባቡ መከታተል ትተህ ሌት ተቀን ጥላቻ ስትዘራ ያሰናበተህ የሜልበርን ዩኒቨርሲቲ አንተን በተመለከተ አንድ ጊዜ ሳይሆን ሁለት ጊዜ በይፋ መግለጫ አውጥቷል። ሁለቱም መግለጫዎች ተመሳሳይ ናቸው። “ሚስተር ( አቶ) ጸጋዬ አራርሳ የዩኒቨርሲቲው ተቀጣሪ አይደለም። ትምርቱን ስላላጠናቀቀ የዶክትሬት ዲግሪ አልሰጠሁትም” ነው ያለው። ይሄ ሃቅ አሁንም አልተቀየረም።

እኔ በግሌ በዚህ ጉዳይ ከተለያዩ የዩኒቨርሲቲው ሃላፊዎች ጋር መጻጻፍ ብቻ ሳይሆን በስልክም ተነጋግሪያለሁ። የዩኒቨርሲቲው የህግ ትምህርት ዲን ፕሮፌሰር ፒፕ ኒኮልሰንን ጨምሮ አራት በተለያየ ሃላፊነት ላይ ያሉ ሰዎችን በስልክ ያነጋገርኩ ሲሆን በኢሜይልም ተጻጽፍያለሁ። ጊዜ ማበከን ካልሆነብኝ በዝርዝር ሁሉንም ይፋ ላረግልህ እችላለሁ።

ከሁሉም የተረዳሁት ነገር የአንተ ጉዳይ ስመጥር ለሆነው ዩኒቨርሲቲ ግራ የሚያጋባ መሆኑን ነው። አንተ ግን ያልሆንከውን ነኝ በማለት አሁንም በየዋህነት የሚከተሉህን የጥላቻ አብጊዳ ቆጣሪዎች ታደናግራለህ።

እውነቱን ለመናገር ምሁር ለመባል ፒኤችዲ (PhD) ፈጽሞ አያስፈልግህም። ምሁር ለመሆን የሚያስፈልግህ ዋጋ ያለው መልካም ሃሳብና እውቀት ነው። አንተን የጎደለህ ቅንነና እውነተኛ ማንነትህ ላይ የፈጠርከው ብዥታ በመሆኑ ተምታቶብሃል። አንድ ሰው አደባባይ ከመውጣቱ በፊት አቶ ወይንም ዶክተር መሆኑን ለራሱ አጣርቶ ማወቅ ከተሰናው ለሌሎች የሚተርፍ እውነት ይናገራል የሚል እምነት የለኝም።

ማንነት የሚጀምረው ከግለሰብ ነው። ስለዚህም ኢትዮጵያዊ የሚባል ማንነት የለም የሚል ቀሽም ዲስኩር ከማሰማትህ በፊት ለሰው ስትል ሳይሆን ለራስህ “ዶክተር ጸጋዬ አራርሳ” የሚባል ማንነት አለመኖሩን አምነህ መቀበል ይኖርብሃል። አንድ ሰው ለራሱ የትምርት ማእረግ አይሰጥም። እንደተ አይነቱ ግራ የገው “ምሁር” ግን አይኑን በጨው ታጥቦ ድርቅ ካለ ትርፉ “የሌባ አይነ ደረቅ” መባልና እራሱን የሃሰት ዲግሪ ከሚገዙ ሰዎች በታች አሳንሶ መገኘት ብቻ ነው ትርፉ። መማር ቢሳናቸው ከጥቁር ገበያ ዲግሪ የገዙ ሰዎች ቢያንስ ገንዘባቸውን ከፍለዋል።

ለማንኛውም አታምታታ። በሃሰተኛ ዶክተርነት ከመጀቦን በእውነተኛ አቶነህ ኮርተህ ከጥላቻ ሰባኪነት ውጣና መልካም ለመስራት ትጋ። ዛሬ ከእነጃዋር ጋር ወግነህ ህዝብ መከፋፈልና ማባላት ነገ እንደሚያስጠይቅህ አትጠራጠር። በድሃ ህዝብና አገር እጣ ፈንታ ላይ አትቆምሩ። ህዝብም ታሪክም እንደሚፈርድ አትጠራጠር።

አበበ ገላው

ባለቤቷን ከቀናት በፊት ፊቷ ላይ ጭካኔ በተሞላበት መንገድ የገደሉባት የሁለት መንታ ልጆች እናት

ባለቤቷን ከቀናት በፊት ፊቷ ላይ ጭካኔ በተሞላበት መንገድ የገደሉባት የሁለት መንታ ልጆች እናት ስለሁኔታው ይሄንን ብላለች

“ከቀኑ 7 ሰዓት ላይ ቄሮ መጣ እያሉ ሰዎች እየጮኹ ወደየቤታቸው መግባት ጀመሩ። እኛም ቤታችን ገብተን በር ዘግተን ተቀመጥን። ቄሮዎቹም እንደደረሱ የእኛ ቤት ላይ ድንጋይ መወርወር ጀመሩ። እኛ ምንም አላሰብንም፤ ደነገጥን። ከዝያም አጥራችንን አፍርሰው ወደጊቢያችን እንደገቡ በመጀመርያ ስድብ መስደብ ጀመሩ። መሬቱም የኛ ነው፤ መንግስትም የኛ ነው እናንተ ጋሞዎች ኑ ውጡ አሉን። ከነርሱም መካከል ሁለቱ ቤት ገብተው እኔና ባለቤቴን ይዘውን ወጡ። ባለቤቴም ከቄሮዎቹ መካከል የሚያውቀውን አንድ ጋዲሳ የተባለ የሰፈር ልጅን ‘አንተ ጋዲሣ እንዴት እንዲህ አይነት ነገር በእኛ ላይ ታደርጋለህ እባክህን ተው፤ ለነዚህ ህፃናት ስትል ተው ባክህ’ ይለዋል። እነርሱ ግን እንጨርሳለን፤ ገና እንጨርሳቹኋለን እያሉ ባለቤቴን በድንጋይ መደብደብ፣ በስለት መውጋት ጀመሩ። ባለቤቴ ብዙ ከደበደቡት በኋላ ሞተ። እሱ እንደሞተ እኔ መጨው ስጀምር ‘ለምን ትጮዄለሽ አፍሽን ዝጊ እያሉ እኔንም መምታት ጀመሩ። ከዝያንም የሰፈራችን ሰው 5 ሌትር ጅሪካን እና ክብሪት ሲሰጣቸው አየሁ። ‘ጨርሱ ካለቀ እኔ ጨምራለው’ አላቸው። ባመጡት ጋዝ ቤታችንን አቃጠሉ። አብዝቼ ብጮህም የደረሰልኝ የለም። የፖሊስ ልብስ የለበሱ ሰዎችን የባሌን አስክሬን አንሱልኝ ስላቸው እየሳቁ አይተውኝ ሄዱ።”

የዛሬ ዓመት እንደዚህ ወሬ እየሰማን ነበር። ግን የመንግስት ባለሥልጣናት ችግር የለም ሁሉም ተስተካክሏል እያሉ አዘናጉን። ይሄው ዛሬ ግን ቤት ድረስ መተው አጠገቤ ባሌን ቆራርጠው ገደሉብኝ። ለማን አቤት እላለው?የዓለም መንግስት ይድረስልን!

የሙታን ፖለቲካ ያጣመራቸው የዕልቂት መልዕክተኞች!

(ስዩም ተሾመ)

እስኪ ፖለቲካው ይቆየንና ስለ እውነት እንናገር። ለአንድ አፍታ፤ ሳናዳምጥ አናውራ፣ ሳናውቅ አንቃወም፣ ሳይገባን አንደግፍ። እስኪ ለአፍታ እንኳን ከግብታዊ ስሜት እንውጣ፣ በምክንያት እናስብ። የአንድ ሃሳብ ትክክለኝነት የሚመዘነው በተናጋሪው ስልጣንና ማንነት ሳይሆን በምክንያታዊ ዕውቀት ነው። ምክንያታዊ ዕውቀት የትላንቱን ጠንቅቆ ማወቅ፣ የዛሬን በዝርዝር መገንዘብ፣ የነገን በትክክል መገመት ያስችላል። የትላንቱን ታሪክ እና የወደፊቱን ሁኔታ መሰረት ያደረገ በሰዎች ሕይወት ላይ ተጨባጭ ለውጥና መሻሻል ሊያመጣ የሚችል ሃሳብ ትክክልና አግባብ ነው። እንዲህ ያለ ሃሳብን ላለመቀበል መቃወም ራስን ማታለል፣ ሌሎችን መበደል ነው። ስለዚህ ለራሳችንም ሆነ ለሌሎች ስንል ቆም ብለን ማሰብ፣ በምክንያት መጠየቅና በተግባር መፈተሸ ያስፈልጋል።

እንደ ናጄሪያዊው ሎሬት “Wale Soyinka” አገላለፅ “አክራሪ ብሔርተኝነት አንድ ላይ ያስተሳስራል፤ ግን ደግሞ አንድ ላይ ያውራል!” ይላል። በዋናነት ከ50 አመት በፊት የተጀመረው የብሔርተኝነት ንቅናቄ የመጨረሻው ደረጃ ላይ ደርሷል። ዛሬ ላይ ብሔርተኝነት ህዝባዊ ንቅናቄ ከመፍጠር አልፎ የግጭትና ዕልቂት መሳሪያ ሆኗል። ነገሩ ከራስ ወዳድነትና ወገንተኝነት አልፎ ወደ ጦርነትና ዕልቂት ሊቀየር ጫፍ ላይ ደርሷል። ሁሉም ሰው በየራሱ ብሔር ስር ተወሽቋል። እድሜ ለሕገ መንግስቱ እና ፌደራሊዝም ስርዓት ሁሉም ሰው በየራሱ ብሔር ጉያ ስር ተወሽቋል። ሁሉም ሰው በብሔር ተደራጅቶ አንድነቱን አጠናክሯል። ነገር ግን አንድ ላይ ያስተሳሰረው ነገር አንድ ላይ አውሮታል። ብሔርተኝነት በተንሰራፋው ልክ የሰዎችን እይታ፣ የማስተዋል አቅም እና የግንዛቤ ደረጃ በከፍተኛ ደረጃ ቀንሷል።

አዎ… ብሔርተኝነት አንድ ላይ ያስተሳስራል። የእያንዳንዱን ብሔር አንድነት ያጠናክራል፤ የብሔር መብትና እኩልነት ይከበራል። በብሔር መደራጀት፣ በብሔር መነቃነቅ፣ በብሔር መቃወም፣ በብሔር መጠየቅ፣ በብሔር መንጠቅ፣ በብሔር ማጥፋት፣ በብሔር መግደል ይቻል ይሆናል። ነገር ግን በብሔር ፖለቲካ በራስ ማየት፣ በራስ ማሰብ፣ በራስ ማስተዋል፣ በራስ ፍላጎትና ምርጫ መንቀሳቀስ፣ በራስ አመዛዝኖ መወሰን፣ ራስን በራስ መምራት አይቻልም። ምክንያቱም ብሔርተኝነት አንድ ላይ ያስተሳስራል እንጂ አንድ ዓይን የለውም፤ የሚያስብ አዕምሮ፣ አስተዋይ ልቦና፣ የራሱ ፍላጎትና ምርጫ የለውም። በመሆኑም ብሔር በራሱ አመዛዝኖ መወሰን እና ራሱን በራሱ መምራት አይችልም።

“Wale Soyinka” እንዳለው አንድ ላይ ያስተሳሰረን ብሔርተኝነት እውነታን ከማየት ያግደናል። ነባራዊ እውነታን ማየትና መገንዘብ የማይችል በራሱ ማሰብና ማስተዋል አይችልም፤ በራሱ ፍላጎትና ምርጫ መወሰን፣ ራሱን በራሱ መምራትና መንቀሳቀስ ይሳነዋል። ስለዚህ በብሔርተኝነት አንድ ላይ የታሰረ ህዝብ እውነታን አይቶ የሚገነዘብለት፣ አስቦና አመዛዝኖ የሚወስንለት፣ እንዲሁም ከፊት ሆኖ እየመራ የሚያንቀሳቅሰው መሪ ያስፈልገዋል። አንድ ላይ የተሳሰረን ህዝብ መምራት የሚችለው አንድ ሰው ወይም ቡድን ነው። በመሆኑም አንድ ብሔር ከአንድ በላይ መሪ ሊኖረው አይችልም። ስለዚህ አንድ መሪ በራሱ እውነታን ያያል፣ ያገናዝባል፣ አመዛዝኖ ይወስናል፣ ከፊት ሆኖ ይመራል። የተቀሩት የብሔሩ አባላት በመሪው ዓይን ያያሉ፣ እሱ ያዘዛቸውን ያደርጋሉ፣ እሱ በመራቸው መንገድ ይጓዛሉ።

በዚህ መልኩ አክራሪ ብሔርተኝነት የሰው ልጅን ከምክንያታዊነት ወደ ግዑዝ መንጋነት ይቀይራል። መሪው የተናገረው ውሸት እውነት ይሆናል፣ መሪው የካደው እውነት ወደ ውሸትነት ይቀየራል፣ የመሪው ጥፋት ሁሌም አግባብ ነው፣ የመሪው መንግድ ፍፁም ትክክል ነው። መንገዱ በጠላቶች የተሞላ ነው። በጠላት ላይ ሲሰበክ የኖረ ጥላቻ ሁሌም ጠላት ይፈልጋል። በመሆኑም አንዱ ጠላት ሲወገድ ሌላ መተካት የግድ ይላል። ጉዞው በህልውና ላይ የተጋረጠን አደጋ ለመከላከል የሚካሄድ ትግል ነው። በህልውና ላይ የተጋረጠን አደጋ ለመከላከል የሚደረገው ትግል መስዕዋትነት ይጠይቃል። የትግሉ ዓላማ ነፃነትን መቀዳጀት ነው። በመጨረሻ የትግሉ ውጤት ነፃነትና ሰማዕታት ይሆናሉ።

እንደ ካሜሮናዊው ምሁር አቺሌ ምቤምቤ አገላለፅ መሪው ያለው “የሙታን ኃይል” (Necropower) ነው፣ ፖለቲካውም “የሙታን ፖለቲካ” (Necropolitics” ይባላል። የሙታን ኃይል ማን መኖር፣ ማን መሞት እንዳለበት መወሰን የሚያስችል ስልጣን ነው። በሙታን ፖለቲካ ራስን በመከላከል እና በማጥፋት፣ በመመለስ እና ነመቅረት፣ በነፃነት እና ሰማዓት መካክል ግልፅ የሆነ መስመር የለም። የሙታን መሪዎች በትግል ከተገኘው ድል ይልቅ የተገደሉትን፣ ካገኙት ነፃነት ይልቅ ሰማዕታቱን ማሰብ ይመርጣሉ። ምክንያቱም ቂምና ጥላቻን ማራዘም ይሻሉ። ጠላትና ጦርነት ከሌለ ተከታይ አይኖራቸውም። ስለዚህ ስልጣናቸውን ለማራዘም ጥላቻ እየሰበኩ ጠላት ያፈራሉ፣ ቂም በመቆስቆስ ግጭት ይፈጥራሉ። ይህ ሲሆን ጭፍን ደጋፊዎች የሙታን መንገድን ይከተላሉ። በቂምና ጥላቻ ሌሎችን ይገድላሉ ወይም በሌሎች ይገደላሉ። በዚህ መልኩ የሙታን ኃይል ከሞት ይመነጫል፣ የሙታን ፖለቲካ በፍርሃት መርህ ይመራል።

ባለፉት አራት አስርት አመታት ኢትዮጵያ ውስጥ የነበረው የሙታን ፖለቲካ ነው። የፖለቲካ መሪዎቻችን ስልጣንም ከሞት የመነጨ ኃይል ነው። ከአብዮቱ ጀምሮ የሀገራችን ፖለቲካ በጅምላ መፈራረጅና መገዳደል የተሞላ መሆኑ ለዚህ ጥሩ ማሳያ ነው። በተለይ ባለፈው ግማሽ ክፍለ ዘመን አብዮትና ፀረ አብዮት፣ ነጭ ሽብርና ቀይ ሽብር፤ ኢትዮጵያ ወይም ሞት፣ የአንድነት ወታደር እና ገንጣይ ወንበዴ፤ ሰላምና ፀረ-ሰላም፣ ልማትና ፀረ-ልማት፣ ህገ መንግስትና ፀረ-ህገ መንግስት፣ ሽብርና ፀረ-ሽብር፣… ወዘተ በሚል የጅምላ ፍረጃ የአንድ ዘመን ትውልድ እርስ በእርሱ ለዕልቂት ተዳርጓል። ምክንያቱም ያ ትውልድ አብዮተኛ ነው። “አብዮት” ደግሞ ወረተኛ ነው። ወረቱ ሲያልቅ እርስ በእርስ መፈራረጅና መገዳደል የግድ ነው።

በመሰረቱ አብዮተኛ እና ፀረ-አብዮተኛ በሚል በጅምላ ከመከፋፈል በስተቀር በመካከላቸው መሰረታዊ የሆነ የአቋም ሆነ ርዕዮተ-ዓለም ልዩነት አልነበረውም። ሁሉም አብዮተኛ ሥር ነቀል ለውጥ ያስፈልጋል፣ የዜጎች እኩልነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ ይጠይቃል። ከሞላ ጎደል ሁሉም አብዮተኞች የማርክሲስት/ሌኔኒስት ጥራዝ ነጠቆች ናቸው። ነገር ግን ሁሉም ራሳቸውን “አብዮተኛ” ሌሎችን “ፀረ-አብዮተኛ” ብለው በጅምላ ይፈራረጃሉ። ከጅምላ መፈራረጅ ቀጥሎ በጅምላ መገዳደል ይከተላል። ምክንያቱም የአብዮተኛው ድል የሚረጋገጠው ፀረ-አብዮቶችን በመግደል ነው። በሌላ በኩል አንድ ፀረ-አብዮተኛ የሚኖረው አብዮተኞች በሙሉ ሲወገዱ ነው። የአብዮቱ ስኬት ለፀረ አብዮቱ ሽንፈት ነው።

በሙታን ፖለቲካ የአንዱ ህይወት የሚገኘው በተቀናቃኙ ሞት ነው። ስለዚህ ጎራ ለይቶ መገዳደል የስርዓቱ መገለጫ ነው። ይህ በተለይ ከ1966ቱ አብዮት በኋላ ኢትዮጵያ ስትመራበት የነበረ የፖለቲካ ስርዓት ነው። ለምሳሌ በደርግ የተጠለፈውን የተማሪዎች አብዮት ለማስመለስ የነጭ ሽብር ጥቃት ተፈፀመ። ነጭ ሽብርን ለመመከት ቀይ ሽብር ተፋፋመ። በዚህ ምክንያት አንድ ትውልድ በሙታን ፖለቲካ መከነ። እናት ልጇ ለተገደለበት ጥይት ከፈለች፣ አባት የልጁን ሬሳ ከመንገድ ላይ ማንሳት ተሳነው፣ ወዳጅ ዘመድ ከገዳዮች ፊት ማልቀስ ተከለከለ።

ከነጭ ሽብር ጥቃት የተረፉት ሶሻሊስት አብዮተኞች ደርግ እና መኢሶን በሚል ተከፋፍለው ተገዳደሉ። ደርግ ደግሞ “ቆራጥ አብዮተኛ” እና “ስርጎ-ገብ አድሃሪ” በሚል እርስ በእርስ ተከፋፍሎ ተገዳደለ። በዚህ መልኩ እነ ጄነራል ተፈሪ በንቲ እና ሺ/አለቃ አጥናፉ አባተን የመሳሰሉ ከፍተኛ አመራሮች ተገደሉ። የአብዮታዊ ዴሞክራሲ አቀንቃኞች የነበሩት ኢህአፓ እና ህወሓት ደርግን ለመውጋት በመሸጉበት እርስ በእርስ ተዋጉ። ኢህአፓን ያስወጣው ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) በውስጡ የትግራይ ማርክሲስት ልኔኒስት ሊግ (ትማልሊ) የሚል ድርጅት በመፍጠር ለሁለት ተከፈለ። ይህን ተከትሎ የህወሓት ዋና ሊቀመንበር የነበሩት ዶ/ር አረጋዊ በርሄ እና ምክትል ሊቀመንበር የነበሩት ኢ/ር ግደይ ዘርዓፂዮንን ጨምሮ ሌሎች የድርጅቱ መስራቾች ተሰደዱ።

ደርግ እና ህወሓት በየፊናቸው እርስ በእርስ ተከፋፍለው ከተገዳደሉ በኋላ የሀገር አንድነት እና የብሔር እኩልነት በሚል እርስ በእርስ ውጊያ ገጠሙ። ደርግ ወድቆ ህወሓት ሲመጣ ከስም በቀር የትውልድ አሊያም የስርዓት ለውጥ አልተደረገም። ምክንያቱም ደርግና ህወሓት የ1960ዎቹ አብዮተኛ ትውልድ ናቸው። አብዮተኛ ትውልድ ደግሞ “የፀረ” ፖለቲካ አራማጅ ነው። ስልጣኑም ከሞት የመነጨ ነው። በመሆኑም ህወሓት ወደ ስልጣን በመጣ ማግስት፤ ሰላምና ፀረ-ሰላም፣ ልማትና ፀረ-ልማት፣ ህገ መንግስትና ፀረ-ህገ መንግስት እያለ በጅምላ መፈረጅ፣ በጅምላ ማሰር፣ በጅምላ መግደልና ማሰቃየት ጀመረ። ለዚህ ደግሞ ሁሉንም ነገር በሽብርተኝነት የሚፈርጅ የፀረ-ሽብር አዋጅ አወጣ። በዚህ መልኩ የደርግ ቀይ ሽብር ዘመቻ በፀረ-ሽብር አዋጅ ተተካ።

አብዮተኛ ትውልድ የፀረ-ፖለቲካ አቀንቃኝ፣ የሙታን ፖለቲካ አራማጅ ነው። የአንድ ትውልድ አማካይ ዘመን 30 አመት ነው። በዚህ መሰረት የ1960ዎቹ ትውልድ ዘመን ያከተመው በ1990ዎቹ አጋማሽ ላይ ነው። የ1997ቱ ምርጫ የአብዮተኛው ትውልድ ዘመን ማብቂያና የአዲሱ ትውልድ ዘመን መጀመሪያ ነበር። ነገር ግን አዲሱ ትውልድ ሀገሪቱን ለመረከብ ከህወሓት/ኢህአዴግ ጋር ያደረገው ግብግብ በአጋዚ ወታደሮች ተጨናገፈ። ከአስር አመት ትዕግስት በኋላ ለቀጣይ 50 አመታት ኢትዮጵያን ለመግዛት ሲያልሙ የነበሩትን አብዮተኞች በሦስት አመት ህዝባዊ አመፅና ተቃውሞ ከስልጣን አስወገደ።

በአጠቃላይ ከደርግ መምጣት እስከ ህወሓት ውድቀት ድረስ ያለው ሁኔታ አንድና ተመሳሳይ ነው። አብዮተኞች ከሃሳብ የበላይነት ይልቅ በጉልበት የበላይነት፣ ከውይይት ይልቅ በጦርነት፣ ከመነጋገር ይልቅ በመገዳደል የሚያምኑ ስለመሆናቸው ከኢትዮጵያ በላይ እማኝ ምስክር የለም። በዚህ የጥሎ ማለፍ ፖለቲካ ውስጥ የአንዱ ስልጣን ሌላውን በመጣል፣ የአንዱ ድል ሌላውን በመግደል፣ የአንዱ ህይወት በሌላኛው ሞት ላይ የተመሰረተ ነው። በዚህ ምክንያት ሀገሪቱ የተገነባችበት መሰረት ተሸርሽሮ አልቋል።

በእርግጥ የአብዮቱ ፖለቲካ የሚቀጥል ከሆነ በጥቂት አመታት ውስጥ ኢትዮጵያ ትፈርሳለች። ስለዚህ አዲሱ ትውልድ እንኳን የሚመራው መንግስት የሚኖርበት ሀገር አይኖረውም። ኢትዮጵያ ከፈረሰች ደግሞ አሁን በውስጧ ያሉት ብሔሮች፥ ብሔረሰቦች የየራሳቸውን ሀገር መስርተው በጉርብትና የሚኖሩ ከመሰላችሁ ተሳስታችኋል። ከዚያ ይልቅ ሀገሪቱ ከፈረሰች ምስራቅ አፍሪካን የሚያጥለቀልቅ የደም ጎርፍ ይፈስሳል፣ ተቆጥሮ የማያልቅ ሬሳ በየስርቻው ይከመራል። ኢትዮጵያ ወደ ምድራዊ ሲዖል ትቀየራለች። ስለዚህ አዲሱ ትውልድ የትላንቱን ያረጀ የፖለቲካ አመለካከትና ዛሬ ላይ የሚስተዋለውን ጭፍን ብሔርተኝነት ማስወገድ አለበት።

በዚህ መሰረት የወደፊቱን አስከፊ እልቂትና ውድቀት ለማስቀረት አዲሱ ትውልድ አበክሮ ማሰብ፣ መስራትና መተባበር ይጠበቅበታል። ለዚህ ደግሞ ከፊት ለፊቱ ቆመው የዕልቂት ነጋሪት እየጎሰሙ ያሉትን የፖለቲካ ቡድኖች በግልጽ መጋፈጥ አለበት። እነዚህ የሙታን ፖለቲካ ያጣመራቸው የዕልቂት መልዕክተኞች ህወሓት እና ጃዋር (ኦነግ) ናቸው። ለአዲሱ ትውልድ የሁለቱ ጥምረት ትክክለኝነት እና አግባብነት ፍፁም ሊያሳስበው አይገባም። ምክንያቱም የህወሓቶች ዓላማና ግብ ምን እንደሆነ ባለፉት 27 አመታት በተግባር የታየ ነገር ነው። ህወሓቶች በ1997ቱ ምርጫ ደንግጠው ልክ እንደ አሁኑ ወደ መቀሌ ሸሽተው ከተመለሱ በኋላ በአስር አመት ውስጥ በህዝብ ላይ ያደረሱትን ስቃይ እና በሀገር ላይ የፈፀሙትን ዘረፋ ሁላችንም እናውቃለን።

አሁን ደግሞ ተመልሰው ከመጡ በምድር ላይ ታይቶና ተሰምቶ የማያውቅ አሰቃቂ ነገር ሊፈፅሙ እንደሚችሉ ጥርጥር የለኝም። በሌላ በኩል እነ ጃዋር መሃመድ የሚያራግቡት አክራሪ ብሔርተኝነት እነ ሌንጮ ለታ እና ሌንጮ ባቲ እድሜ ልካቸውን ሞክረው እውን ሊሆን እንደማይችል በተግባር ያረጋገጡት ነገር ነው። ህወሓት እና ጃዋር/ኦነግ ጥምረት የፈጠሩበት ምክንያት፤ አንደኛ፡- ሁለቱም ስር የሰደደ የስልጣን ጥማት እና የቁሳዊ ኃብት ፍላጎት ስላላቸው፣ ሁለተኛ፡- ሁለቱም የሙታን ፖለቲካ የሚያራምዱ የአብዮቱ ትውልድ ርዘራዦች በመሆናቸው ነው። በአጠቃላይ የህወሓት እና ጃዋር/ኦነግ ቅንጅት ላለፉት አርባ አመታት የመጣንበትን በጥላቻነ ቂም የታጨቀ፣ በግጭትና ጦርነት፣ እንዲሁም በጅምላ ፍረጃና ግድያ የሚታመስ፣ ያን ያረጀና ያፈጀ የሙታን ፖለቲካ ለማስቀጠል ያለመ ነው። በዚህ ምክንያት ገፈት ቀማሽ የሚሆነው ደግሞ አዲሱ ትውልድ ነው! የሙታን ፖለቲካ ያጣመራቸው የዕልቂት መልዕክተኞች የሁላችንም ስጋት ናቸው!