ኤች አር 128 በመባል የሚታወቀውና በአሜሪካ ምክር ቤት የወጣው ረቂቅ ሕገ ውሳኔ በምክር ቤቱ ለድምጽ አሰጣጥ እንደሚቀርብ ታወቀ

ኢሳት ዲሲ–ጥር 22/2010) ።

ሕገ ውሳኔው ለድምጽ አሰጣጥ የሚቀርበው በኢትዮጵያ ያለው አገዛዝ የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብት መርማሪዎች በሀገሪቱ እየተፈጸመ ያለውን የሰብአዊ መብት ጥሰት እንዲያጣሩ እስከሚቀጥለው ወር ድረስ የማይፈቅድ ከሆነ ነው። የኢትዮጵያ አሜሪካውያን ሲቪክ ካውንስል ከሌሎች የማህበረሰቡ ተወካዮችና ድርጅቶች ጋር በመሆን ትላንት ከአሜሪካ ምክር ቤት አባላትና ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ተወካይ ጋ ኤች አር 128 ሕገ ውሳኔ ስለሚጸድቅበት መንገድ ተወያይተዋል። ውይይቱ በአሜሪካ የተወካዮች ምክር ቤት የአብላጫ ወንበር ያለው የሪፐብሊካን ፓርቲ መሪ ኬቨን ማካርቲ ከኢትዮጵያውያኑ ተወካዮች ጋር ተገናኝተው ለመነጋገር በጠየቁት መሰረት የተካሄደ መሆኑን ለመረዳት ተችሏል። በቀጣዩ ወር ማለትም እስከ የካቲት 8 ድረስ በኢትዮጵያ ያለው አገዛዝ የተባበሩት መንግስታት አጣሪ ቡድን በሃገሪቱ ገብቶ የተፈጸሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን እንዲያጣራ ፍቃድ እንዲሰጥ ቀነ ገደብ ለማስቀመጥ ስምምነት ላይ መደረሱን የውይይቱ ተሳታፊዎች ከጋዜጠኞች ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ተናግረዋል። አገዛዙ ለዚህ የማይተባበር ከሆነ ግን ኤች አር 128 በመባል የሚታወቀውና በኢትዮጵያ የሰብአዊ መብት እንዲከበርና የመብት ጥሰት የፈጸሙትን በሕግ ተጠያቂ የሚያደርገው ሕግ በአሜሪካ ምክር ቤት እንዲጸድቅ እንደሚደረግ ለማወቅ ተችሏል። የሕገ ውሳኔው ዋና አዘጋጅ የሆኑት የምክር ቤቱና የውጪ ጉዳይ ኮሚቴ አባል ክሪስ ስሚዝ የተባበሩት መንግስታት መርማሪዎች ሙሉ ለሙሉ በፈለጉበት ቦታ ተንቀሳቅሰው የተፈጸሙትን የሰብአዊ መብት ጥሰቶች እንዲያጣሩ አገዛዙ የማይፈቅድ ከሆነ ሕጉ በአስቸኳይ ይጸድቃል ብለዋል። ይህም ብቻ ሳይሆን ክሪስ ስሚዝ እንዳሉት በመብት ጥሰቱ ተሳታፊ የሆኑ ግለሰቦችን በአለም አቀፉ ማግንትስኪ የሰብአዊ መብት ሕግ መሰረት በሕግ እንዲጠየቁ እንደሚደረግ አስታውቀዋል።

ሌላው የምክር ቤት አባል ማይክ ኮፍማን እንዳሉት ደግሞ አሜሪካ ለረጅም ጊዜ ከአገዛዙ ጋር ይላትን የጸጥታ ትብብር ሰበብ በማድረግ እየተፈጸሙ ያሉ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን ችላ ስትል መቆየቷ አግባብ እንዳልነበር ተናግረዋል። አገዛዙ ሕዝቡን እያሸበረ አሜሪካ ትብብሯን መቀጠሏ አግባብ አይደልም ሲሉ ተደምጠዋል። በኢትዮጵያ አሜሪካውያን ሲቪክ ካውንስል ተወካይ ዲያቆን ዮሴፍ ተፈሪ በበኩላቸው በውይይቱ ወቅት በምክር ቤቱ የአብላጫ ወንበር ያለው የሪፐብሊካን ፓርቲ መሪ ኬቨን ማካርቲ እንደተገኙና እሳቸውም በኢትዮጵያ ያለውን የመብት ረገጣ በቅርብ እንደሚከታተሉት ገልጸውላቸዋል። ኬቨን ማካርቲ ሕጉን የማስቆም ፍላጎት እንደሌላቸው ይሁን እንጂ አገዛዙ አንድ እድል እንዲሰጠው እንደሚፈልጉ ተናግረዋል ብለዋል። በዚህም መሰረት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት መርማሪዎች ፍቃድ የማያገኙ ከሆነ ሕጉን ተግባራዊ ለማድረግ ስምምነት ላይ ተደርሷል ብለዋል። በውይይቱ ላይ የተገኙት የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ተወካይም አገዛዙ ለጥያቄው አዎንታዊ መልስ የሚሰጥ ከሆነ የኮሚሽኑ ባለሙያዎች ወዲያውኑ የማጣራት ስራቸውን እንደሚጀምሩ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ህዝብ የሚያደርገው የእምቢተኝነት ትግል ብሄራዊ ቅርጽ እንዲይዝና ከህወሀት ፋሽስታዊ ጭፍጨፋ አራሱን በመከላከል የተቀናጀ ትግል እንዲያደርግ ለማገዝ በጋራ እንቁም!

ቀን፤ ጥር 11 2010

የኢትዮጵያ ህዝብ በተለይ  የኦሮሞና የአማራ ሕዝብ ላለፉት 2 አመታት ዘርና አገር በማጥፋት ላይ የሚገኘውን ዘረኛ አገዛዝ በቃኝ በማለት ባደረገት ተከታታይ ሕዝባዊ እምቢተኝነት ምክንያት  ውጥረት ውስጥ የገባው የህወሀት አመራር ቡድን ለተከታታይ ሳምንታት ዝግ ስብሰባ በማድረግ በግምገማ ውስጣዊ ማሻሻያና ተሃድሶ አድርጊያለሁ በማለት፤ የተለመደ የማዘናጊያ አዋጅ ባወጀ ማግስት፤ በወልዲያ የጥምቀት በዓል በማክበር ታቦት አጅበው በነበሩ ንጹሃን ምመናን ላይ የ 13 አመት ህጻን ልጅን ጨምሮ ባልሞ ተኳሽ የአጋዚ ወታደሮቹ አማካኝነት ሰይጣናዊ ድርጊትና ፋሽስታዊ ጭፍጨፋ ፈጽሟል።  ይህ ጭፍጨፋ በትግራይ ወታደሮች መካሄዱን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የደህነትና የጸጥታ መምሪያ /United Nations Department for Safety and Security/ ለሰራተኞች በላከው የውስጥ መልዕክት ተረጋግጧል።  ተመሳሳይ የዘር ማጥፋት ፋሽስታዊ ጭፍጨፋውን  በቆቦ፣ መርሳና በሌሎች ቦታዎች በመፈጸም ላይ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ብሄራዊ የሽግግር ምክርቤት ይህን የዘር ማጥፋት ጭፍጨፋ በጥብቅ እያወገዘ፤ ይህ አሰቃቂ ድርጊት  ለተፈጸመባቸው ወገኖቻችን ቤተሰብ፤ ዘመድና ወዳጆች መጽናናትና ብረታቱን እንዲሰጣቸው ይመኛል።

ህውሀት ላለፉት 27 አመታት፤ ያፓርታይድ ያገዛዝ ዘዴን በመጠቀም፤ በወልድያ ከተፈጸሙት ፋሽስታዊ ድርጊቶች የከፉ ዘግናኝ ድርጊቶችን በኢትዮጵያውያን ላይ በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች ፈጽሟል። ይህ ዘረኛ አገዛዝ ከጥቂት ወራት በፊት በኦሮሞና የሱማሌ ህዝብ መካከል የተፈጸመ የጎሳ ግጭት በማስመሰል የብዙ ኢትዮጵያውያን ሕይወት እነዲጠፋ ከማስደረጉ በተጨማሪ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ የኦሮሞ ህዝብ ከገዛ አገሩ እንደሌላ አገር ዜጋ እንዲፈናቀል አስደርጓል። በወልድያ የጥምቀት በዓል የተፈጸመው ፋሽስታዊ ጭፍጨፋ ከዚህ በፊት በኢሬቻ በአል ላይ በመቶዎች የሚቆጠሩ የኦሮሞ ወገኖቻችን ላይ ተፈጽሟል።

ካለፈው ሳምንት ጀምሮ በወልድያ፣ ቆቦ፣ መርሳና ሌሎች የኢትዮጵያ ከፍሎች በአጋዚ ጦር እየተፈጸመ ያለውን የተለመደ ፋሽስታዊ ድርጊት ለየት የሚያደርገው፤ 1ኛ/ ህወሃት ለብዙ ሳምንታት የግሉን ውስጣዊ ጉባኤ በማድረግና ከኢህአደግ አባል ድርጅቶች ተመሳሳይ ግምገማ በማድረግ ተሃድሶ አድርገናል የህዝቡን በደል በመረዳት አቅጣጫ አስቀምጠናል በሚል ይፋዊ ጋዜጣዊ መግለጫና ተከታታይ ማብራሪያ መስጠቱና

2ኛ/ ሁሉንም የፖለቲካ እስረኞች በመፍታት ማእከላዊ አስር ቤትን ሙዚየም እናደረጋለን የሚል ይፋዊ መግለጫ ለኢትዮጵያ ህዝብና ለአለም አቀፍ ህብረተሰብ ይፋ ባደረጉ ማግስት መፈጸማቸው ነው።

ይህ የህወሀት የተለመደ አቅጣጫ የማሰቀየሪያ ወይም ሕዝባዊ ትግሉን የማፈኛና ጊዜ የመግዣ ዘዴ ነው። ከ27 አመት በኋላ የህዋትን መሰሪነትና የተለመደ ድራማውን አለመረዳት ከእባብ እንቁላል እርግብ ይፈለፈላል ብሎ እንደመጠበቅ ይቆጠራል።

ለረዢም አመታት ለነጻነት በተደረገው ትግል በኢትዮጵውያን ከፍተኛ መስዋእትነት የተከፈለ ቢሆንም ፋይዳ ያለው ውጤት ላይ ያለመድረሳችን ዋናው ምንጭ ትግሉን በአንድ ማእከል በብሄራዊ ደረጃ የሚመራ፤ ታማኝነትና ተቀባይነት ያለው አንድ የአማራጭ ሃይል ባለመኖሩ ምክንያት ማለቂያ በሌላቸው ከወያኔ ለሚሰጡ የተሸራረፉ አጀንዳዎች ቅጽበታዊና ስሜታዊ ምላሽ ከመስጠት አዙሪት ውስጥ እንዳንወጣ አድርጎናል። ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ዛሬ ላለንበት አደጋና ተደጋጋሚ ብሄራዊ ውርደት ውስጥ መግባት፤ ለዘመናት በአለም አቀፍ ደረጃ የተቀናበረ ድርጊትና ቀጣይ ሂደት ነው። ኢትዮጵያ ወዳጅ እንዴሌላትና ችግራችን ጥልቅና ውስብስብ መሆኑን በመገንዘብ ትግላችንን ዘላቂ ውጤት ላይ ለማድረስ ብቸኛው አማራጭ በራስ መተማመንና የኢትዮጵያን ሕዝብ መሰረት ያደረገ ትግል ከማድረግ ውጭ ሌላ አቋራጭ መንገድ እንደሌለ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ሽግግር ምክርቤት በጽኑ ያምናል።

ሽግግር ምክር ቤቱ ከዚህ ጭብጥ በመነሳት አደጋዎችን ለመከላከል ከምስረታው ወቅት ጀምሮ ስርአቱን በማስወገድና ሁሉን አቀፍ ህዝባዊ የሽግግር መንግስት ምስረታን መሰረት በመጣል ሂደት ዙሪያ ከፍተኛ የሆነ እንቅስቃሴና ዘመቻ ባለምአቀፍ ዙሪያ አካሂዷል። በርካታ የምክክር ጉባኤዎችን በማዘጋጀት የአገራችን ጉዳይ ከሚመለከታቸው የፖለቲካና ሲቪክ ድርጅቶች፤ ምሁራን፤ ታዋቂ ግለሰቦችንና፤ አጠቃላይ የኢትዮጵያን ህዝብ በጉዳዩ ሲያወያይና የምክክር ጉባኤዎችን ሲያከናውን ቆይቷል። እንዲሁም ስርአቱን በማስወገድና በመተካት የትግል ሂደት ላይ ወሳኝ ሚና ሊጫወት የሚያስችለውን የወደፊቱን የመንግስት ቅርጽ የሚያሳይና በሽግግር ወቅት መኖር ስለሚገባው የመተዳደርያ ቻርተር ረቂቅ በማዘጋጀት ለውይይትና ለምክክር በኢትዮጵያና በውጭ ለሚገኘው ህዝብ አሰራጭቷል። ከዚህ በተጨማሪ ምከር ቤቱ ከአንድ አመት በፊት የመሪነት ሚና በመጫወት በጃንዋሪ 13-14 2016 ዓ.ም በዋሺንግተን ዲሲ የተካሄደውን የምክክር ጉባኤ እንዲዘጋጅና የተለያዩ ድርጅቶች እንዲሳተፉ ከፍተኛ ጥረት በማድረግ በ 9 ድርጅቶች መካከል ስምምነት ላይ በመድረስ የኢትዮጵያ አገር-አድን  ኃይል ተመስርቶ ለአንድ አመት ያህል በጋራ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል።

ምክር ቤቱ ከኢትዮጵያ አገር-አድን ኃይል ጋርም ሆነ ከሌሎች ስብስቦችና ድርጅቶች ጋር በሚያደርጋቸው ግንኙነቶች ዘረኛውን የህውሀት አገዛዝ ለማስወገድ እንዲሁም ስርአቱ ሲወገድ ወደፊት በኢትዮጵያ ውስጥ በሁሉ አቀፍ ህዝባዊ የሽግግር መንግስት ለመተካት የሚረዳ እንደድልድይ ወይም ጥንስስ በመሆን መሰረት የሚጥልና የተበታተነውን ትግል ብሄራዊ ቅርጽ እንዲኖረው የሚያግዝ የስደት መንግስት ወይም ያማራጭ ሃይሎች ምክር ቤት እንደአማራጭ ሌሎች ባለድርሻ አካላትን ባሳተፈ መልኩ እንዲቋቋም ጥረት ማድረጉን ይቀጥላል።

 

ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!

የኢትዮጵያ ብሄራዊ የሽግግር ምክርቤት

ግብፃዊያን በህዳሴ ግድቡ ግንባታ ላይ የጋራ አቋም ለመያዝ ውይይት ሊያደርጉ ነው (ዘመኑ ተናኘ)

ግብፃዊያን ኢትዮጵያ እየገነባች ባለው የህዳሴ ግድብ ግንባታ ላይ የተለያየ አመለካከት እንዳላቸው፣ ይህንን አመለካከት ወደ አንድ ሐሳብ ለማምጣትና የጋራ አቋም ለመያዝ ውይይት ሊያደርጉ መሆኑ ታወቀ፡፡

30ኛውን የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ ለመካፈል የመጡና ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ አንድ ከፍተኛ የግብፅ ዲፕሎማት ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ ኢትዮጵያ እየገነባች ባለው የህዳሴ ግድብ ግንባታ ላይ አብዛኛው የግብፅ ሕዝብ ጥያቄ ያነሳል፡፡

የሕዝቡን ጥያቄ ለመመለስና ሁሉም ግብፃውያን የጋራ አቋም እንደሚኖራቸው ለማድረግ በሚቀጥሉት ሁለት ወራት ውስጥ የአገሪቱ ሕዝብ ከመንግሥት አመራሮች ጋር ውይይት እንደሚያደርግ ገልጸዋል፡፡

የግብፅ ፕሬዚዳንት አብዱልፈታህ አልሲሲ በግንባታው ላይ ቅሬታ እንደሌላቸው የጠቆሙት ዲፕሎማቱ፣ ሕዝቡ ግን አሁንም ቅሬታ አለው ብለዋል፡፡ ‹‹

በበረሃ ያለን ሕዝቦች በመሆናችን አንድ ቀን እንኳ የናይል ወንዝ መጠኑ ቢቀንስ ተጎጂዎች እንሆናለን፤›› በማለት ጥያቄ እንደሚያነሳ ጠቁመዋል፡፡

የግብፅን ሕዝብ ጥያቄ ለመመለስ የአብዱልፈታህ አልሲሲ መንግሥት ጠንክሮ እየሠራ መሆኑን የገለጹት ዲፕሎማቱ፣ የውይይቱ አጀንዳና የሚጠበቀው ውጤት የኢትዮጵያን የመልማትና በተፈጠሮ ሀብቷ የመጠቀም መብት የሚጋፋ እንደማይሆን አስረድተዋል፡፡

ከፕሬዚዳንት አብዱልፈታህ አልሲሲ በፊት የነበሩት የግብፅ መሪዎች ኢትዮጵያ የምትገነባውን የህዳሴ ግድብ እንደሚቃወሙና ኢትዮጵያ ግንባታውን የማታቆም ከሆነ የኃይል ዕርምጃ እንወስዳለን የሚል ዛቻ ሲያስተላልፉ እንደነበር የሚታወስ ሲሆን፣ አብዱልፈታህ አልሲሲ ወደ ሥልጣን ከመጡ ወዲህ በአንፃራዊነት ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ጉዳዩን በድርድር ለመፍታት ሙከራ ሲያደርጉ ተስተውሏል፡፡

ዲፕሎማቱ እንደገለጹት፣ የአሁኑ የግብፅ መንግሥት የህዳሴ ግድቡ ግንባታን በተመለከተ ያለውን ችግር ሁለቱ አገሮች በመግባባት ይፈታሉ የሚል እምነት አለ፡፡

በውይይቱ መጨረሻ ላይ የግብፅ ሕዝብ የህዳሴ ግድቡን ግንባታ የሚቃወም ከሆነ ግብፅ ምን ዓይነት አቋም ሊኖራት ይችላል የሚል ጥያቄ ቀርቦላቸው በሰጡት ምላሽ፣ ‹‹መንግሥት ሕዝቡን ለማሳመን ይሞክራል፡፡

ግድቡ በእኛ ላይ ጉልህ ጉዳይ እንደማይኖረውና የኤሌክትሪክ ኃይል ሲያመነጭ የሚኖረውን በጎ ተፅዕኖ ማየት ጥሩ እንደሆነ ገለጻ ይደረጋል፤›› ብለዋል፡፡

ዲፕሎማቱ ኤርትራን በተመለከተ ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፣ ‹‹ከኤርትራ ይልቅ ወዳጃችን ኢትዮጵያ ነች፤›› የሚል አጭር መልስ ሰጥተዋል፡፡ ዲፕሎማቱ ኤርትራን በተመለከተ ከዚህ በላይ ማብራሪያ ለመስጠት አልፈቀዱም፡፡

ኢትዮጵያ የህዳሴ ግድቡን የመሠረት ድንጋይ ከጣለች ሰባተኛ ዓመቱን ያስቆጠረ ሲሆን፣ የግንባታ ሒደቱም ከ60 በመቶ በላይ መድረሱ መዘገቡ አይዘነጋም፡፡

ኢትዮጵያ፣ ግብፅና ሱዳን የህዳሴ ግድቡ በታችኞቹ የተፋሰስ አገሮች ላይ የሚያደርሰውን ተፅዕኖና የውኃውን አሞላልና አለቃቀቅ በተመለከተ ዓለም አቀፍ ተቋም ቀጥረው ለማሠራት ስምምነት ላይ እንደደረሱ ቢታወቅም፣ አጥኚ ቡድኑ በሚሠራበት የመነሻ ሐሳብ ላይ ስምምነት አልደረሱም፡፡

በዋናነት ግብፅ እ.ኤ.አ. የ1959 የውኃ ስምምነት የዚህ ስምምነት አካል ይሁን የሚል ጥያቄ በማቅረቧ በኢትዮጵያ ተቀባይነት አላገኘም፡፡

ከድርድሩ ሱዳን እንድትወጣና በምትኩ የዓለም ባንክ እንዲያደራድራቸው ግብፅ በተደጋጋሚ ጥያቄ ማቅረቧም የሚታወስ ሲሆን፣ ይህንን ሐሳብም ኢትዮጵያ ሳትቀበለው ቀርታለች፡፡

ግብፅና ኢትዮጵያ በግድቡ ግንባታ ላይ የሚያደርጉት ድርድር አጣብቂኝ ውስጥ በገባበት ወቅት፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ በቅርቡ ወደ ግብፅ አቅንተው ከፕሬዚዳንት አብዱልፈታህ አልሲሲ ጋር ውይይት ማድረጋቸው አይዘነጋም፡፡

በተመሳሳይ በ30ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ ለመሳተፍ ኢትዮጵያ መጥተው የነበሩት የግብፅ ፕሬዚዳንት፣ ሰኞ ጥር 21 ቀን 2010 ዓ.ም. ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝና ከሱዳን ፕሬዚዳንት ኦማር ሐሰን አል በሽር ጋር በህዳሴ ግድቡ ላይ ተወያይተዋል፡፡

ሦስቱ አገሮች በህዳሴ ግድቡ ብቻ ሳይሆን በሌሎች የጋራ ጉዳዮች ላይ እንደ ሦስት ሳይሆን አንደ አንድ አገር ተስማምቶ ለመሥራት ከስምምነት ላይ እንደ ደረሱ ተገልጿል፡፡ በዓመት አንድ ጊዜ በመሪዎች ደረጃ እየተገናኙ በጋራ ጉዳዮች ላይ ለመነጋገርና አቅጣጫዎችን ለማስቀመጥ ስምምነት ላይ መድረሳቸው ተሰምቷል፡፡

የሦስቱ አገሮች የውጭ ጉዳይ፣ የውኃ ሀብትና ሌሎች የሚመለከታቸው ሚኒስትሮች ሌሎች ተቋማት በህዳሴ ግድቡ ግንባታ ላይ በሚደረጉ ቀጣይ ውይይቶች በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ለመሪዎች ሪፖርት እንዲያቀርቡ መመርያ መሰጠቱንም ለማወቅ ተችሏል፡፡

በሦስቱ አገሮች መካከል ያለውን የሕዝብ ለሕዝብና የኢኮኖሚ ትስስር ለማጠናከር የሚያስችል የሦስትዮሽ የመሠረተ ልማት ፈንድ ለማቋቋም መስማማታቸው ተገልጿል፡፡ ፈንዱም ሦስቱ አገሮች እኩል የሚያዋጡት እንደሆነ ተጠቁሟል፡፡

ኢንዲፔንደንት የተሰኘው የግብፅ ሚዲያ ሰሞኑን እንደ ዘገበው ፕሬዚዳንት አልሲሲ ኢትዮጵያ፣ ግብፅና ሱዳን በህዳሴ ግድቡ ምክንያት ወደ ግጭት አይገቡም ብለዋል፡፡ ፕሬዚዳንት አልሲሲ፣ ‹‹ለጋዜጠኞች ላረጋግጥላችሁ የምወደው በመካከላችን ግጭት የለም፡፡ ሁላችንም አንድ ነን፡፡ አንዱ በሌላው ላይ ጉዳት አያደርስም፤›› ማለታቸውን ጋዜጣው ዘግቧል፡፡

የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳሜህ ሽኩሪ በበኩላቸው፣ አንደኛው አገር በሌላኛው አገር ላይ ጉዳት ላለማድረስ ስምምነት ላይ ደርሰዋል ማለታቸው በዘገባው ተካቷል፡፡

ሪፖርተር

ህወሓት እና ፍርሃት: ከቀበሌ እስከ መቀሌ! – ከስዩም ተሾመ

የኢትዮጲያ ፖለቲካዊ ሁኔታ አሁን ካለበት ደረጃ ላይ እንዴት ደረሰ? በተለይ ከ1997ቱ ምርጫ በኋላ ያለው ፖለቲካዊ ሁኔታ በጥሞና ለታዘበ ሰው ምክንያቱንና ሂደቱን በቀላሉ መገንዘብ ይችላል። በ1997 ዓ.ም በሃሮማያ ዩኒቨርሲቲ የ4ኛ ዓመት ተማሪ ነበርኩ። በፖለቲካ የመሳተፍ ፍላጎት አልነበረኝም። በዚያ ዓመት በተካሄደው ሀገራዊ ምርጫ በመራጭነት ከመሳተፍ የዘለለ ሚና አልነበረኝም። እስከ ግንቦት7/1997 ዓ.ም ዕለት ድረስ የነበረው አጠቃላይ ፖለቲካዊ ሁኔታ ነፃና አሳታፊ ነበር።

በእርግጥ የ1997ቱ ምርጫ የኢህአዴግ መንግስት ወደ ስልጣን ከመጣ በኋላ ያካሄደው ሦስተኛው ሀገራዊ ምርጫ ነው። ታዲያ በወቅቱ “ይህ ምርጫ ለምን ከ1987ቱ እና 1992ቱ ምርጫዎች ተለየ ሆነ?” የሚል ጥያቄ በአዕምሮዬ ሲመላለስ ነበር። በ2002 እና 2007 ዓ.ም የተካሄደው “ማጭበርበር” – መቼም ያንን ቅሌት “ምርጫ” ብሎ መጥራት ይከብዳል – ከ1997ቱ ጋር ምንም የሚያመሳስለው ነገር የለም። የ1997ቱ ምርጫ በኢትዮጲያ ታሪክ ውስጥ ጉልህ ድርሻ እንዳለው የገባኝ በ2004 ዓ.ም የ2ኛ ድግሪ ትምህርቴን ለመማር መቐለ ዩኒቨርሲቲ በሄድኩበት ወቅት ነው።

መቐለ እንደገባሁ በመጀመሪያ የታዘብኩት ነገር የቤት ኪራይ ርካሽነት ነው። ሻውርና ሽንት ቤት ያለው ፅድት ያለ ክፍል በ400 ብር ተከራየሁ። ዓዲ-ሃቂ እና ዓዲ-ሃውሲ የሚባሉ ሰፈሮችን ውስጥ ለውስጥ እየዞርኩ ስመለከት የመኖሪያ ቤቶቹ እንዳሉ ከቅርብ ግዜ ወዲህ የተገነቡ መሆናቸውን ታዘብኩ። የውስጥ-ለውስጥ መንገድ እንኳን ገና በአግባቡ አልተዘረጋም። ከ1997 ዓ.ም በፊት የከተማዋ ዳርቻ የነበረው የመቐለ ዩኒቨርሲቲ ዓዲ-ሃቂ ካምፓስ በአምስት አመት ውስጥ የከተማዋ መሃል ሆኗል። ከዓዲ-ሃቂ ካምፓስ ጎን ያለው ሰፈር ግን አሁንም “የገጠር ቀበሌ ገበሬ ማህበር” ነው። እስከ 1997 ዓ.ም ድረስ የከተማዋ ዳርቻ የነበረ የገጠር ቀበሌ ከ1997ቱ ምርጫ በኋላ የከተማዋ መሃል ሆኗል።

በአጠቃላይ የመቐለ ከተማ ከ1997ቱ ምርጫ በኋላ ባሉት አምስትና ስድስት አመታት ብቻ በእጥፍ ሰፍታለች። ሁለተኛ አብዛኞቹ መኖሪያ ቤቶች ባለ G+1 እና G+2 ዘመናዊ ቪላዎች ናቸው። ነገር ግን፣ በአብዛኞቹ ቪላዎች ውስጥ የሚኖሩት የግቢው ጠባቂ ዘበኛ እና “እርግቦች” ናቸው። ምክንያቱም የቪላዎቹ ባለቤቶች በአብዛኛው የሚኖሩት በዋናነት በአዲስ አበባ እና ሌሎች የመሃል ሀገር ከተሞች፣ እንዲሁም ውጪ ሀገር የሚኖሩ ዲያስፖራዎች ናቸው።

ከላይ የተጠቀሱትንና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮችን በጥሞና ለሚያጤን ሰው በ1997ቱ ምርጫ ወቅት አንዳንድ የቅንጅት ደጋፊዎች እንደዋዛ “ንብረት ወደ ቀበሌ፣ ትግሬ ወደ መቀሌ” በማለት ያሰሙት መፈክር በህወሓት አባላትና ደጋፊዎች ስነ-ልቦና ላይ ያሳረፈውን ጠባሳ መገንዘብ ይችላል። ከዚህ በተጨማሪ፣ በህወሓት መሪነት የተዘረጋው መንግስታዊ ስርዓት ሙሉ በሙሉ ፍፁም አምባገነን የሆነበትን መሰረታዊ ምክንያት በግልፅ ለመረዳት ያስችላል።

የ1997ቱ ምርጫ ከእሱ በፊት እና በኋላ ከተካሄዱት ሀገራዊ ምርጫዎች ፍፁም የተለየ ነው። በወቅቱ የነበረው ፖለቲካዊ ሁኔታ በሁሉም የፖለቲካ ኃይሎች ዘንድ እንደ ልዩ አጋጣሚ ሊጠቀስ የሚችል ነው። ከተወሰኑ የህወሓት/ኢህአዴግ አመራሮች በስተቀር በተቀሩት የፖለቲካ ኃይሎች ዘንድ የ1997ቱ ምርጫ በሀገሪቱ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ለመገንባት ጥሩ አጋጣሚ እንደነበር ይጠቀሳል። ለተወሰኑ የህወሓት/ኢህአዴግ አመራሮችና ደጋፊ ልሂቃን ግን በትጥቅ ትግል የያዙትን የፖለቲካ ስልጣን ለማጠናከር ያደረጉት ሙከራ ራሳቸውን ሊያጠፋቸው ተቃርቦ የነበረበት መጥፎ አጋጣሚ ነበር።

እስከ 1997 ዓ.ም ድረስ ባሉት ዓመታት ህወሓት/ኢህአዴግ የመንግስታዊ ስርዓቱን ሕልውና ለማረጋገጥ ያለመታከት ጥረት ሲያደርግ ነበር። የኦነግ ከሽግግሩ መንግስት ጥሎ መውጣት፣ የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት፣ የህወሓት መሰንጠቅ፣… ወዘተ የመሳሰሉት ክስተቶች በመንግስታዊ ስርዓቱ ላይ ቀጥተኛ የሆነ የሕልውና አደጋ ፈጥረዋል። ከ1995 ዓ.ም ጀምሮ ሀገራዊ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች እንደ አዲስ ተቀርፀው ተግባራዊ ተደረጉ፣ በማህበራዊ ዘርፊ የኮንዶሚኒዬም ግንባታ መጀመር፣ በኦኮኖሚ ረገድ አንዳንድ እድገቶች መታየት ጀመሩ።

ይህን አጋጣሚ በመጠቀም ህወሓት/ኢህአዴግ በጦርነት የያዘውን ስልጣን በሕዝብ ምርጫ ለማጠናከር የ1997ቱም ምርጫ አቅዶ መንቀሳቀስ ጀመረ። የምርጫው ዕለት እየተቃረበ እስኪመጣ ድረስ ድርጅቱ ነፃና ገለልተኛ ምርጫ ለማድረግ እየተንቀሳቀሰ እንደ ነበር ይታወሳል። በዚህ መሰረት፣ ከ1997ቱ ምርጫ በፊትና በኋላ የተካሄዱትን አራት ምርጫዎች በተመሳሳይ ነፃና ገለልተኛ ማድረግ ይችል ነበር።በአጠቃላይ፣ ነፃና ገለልተኛ ምርጫ ማድረግና አለማድረግ በህወሓት/ኢህአዴግ ምርጫና ፍላጎት ላይ የተመሰረተ እንደሆነ መገንዘብ ይችላል።

በዚህ መሰረት፣ በ1987ና 1992 ዓ.ም የተካሄደው ምርጫ ነፃና ገለልተኛ ያልሆነበት መሰረታዊ ምክንያት የህወሓት/ኢህአዴግ የፖለቲካ አቋምና አመለካከት በብዙሃኑ ዘንድ ተቀባይነት ስላልነበረው ነው። በአጠቃላይ በ1997ቱ ምርጫ የተረጋገጡ ሃቆች ምንድን ናቸው?

አንደኛ፡- በህወሓት የፖለቲካ አቋምና አመለካከት ላይ የተመሰረተው መንግስታዊ ስርዓት በብዙሃኑ የኢትዮጲያ ሕዝብ ዘንድ ፍፁም ተቀባይነትና ድጋፍ እንዳልነበረው፥ እንደሌለው፥ ወደፊትም እንደማይኖረው ነው። በመሆኑም የ1997ቱ ምርጫ ውጤት ህወሃት/ኢህአዴግ በስልጣን ላይ እያለ ዴሞክራሲያዊ ምርጫና ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር የሚባል ነገር ከቶ እንዳያስብ አድርጎታል።በዚህ ፅሁፍ “የኢህአዴግ መንግስት” ከሚለው ይልቅ “ህወሓት/ኢህአዴግ” የሚለውን ቃል የምጠቀምበት ምክንያት መንግስታዊ ስርዓቱ በህወሓት/ኢህአዴግ የፖለቲካ አቋምና አመለካከት ላይ የተመሰረተ ስለሆነ ነው።

ሁለተኛ፡- ደግሞ ከምርጫ ማግስት ጀምሮ ህወሓት/ኢህአዴግ እየደጋገመ ሲያራግባት የነበረችውን “ንብረት ወደ ቀበሌ፣ ትግሬ ወደ መቀሌ” የምትለዋ መፈክርና የፈጠረችው ተፅዕኖ ነው። በ1997ቱ ምርጫ ወቅት በነበረው ፖለቲካዊ ሁኔታ ተደናብሮ በመሃል ሀገር ያፈረናውን ሆነ የዘረፈውን ሃብት ይዘው ወደ መቐለ በመሄድ ዛሬ ላይ የእርግቦች መኖሪያ የሆኑ ቪላዎች የገነቡት የህወሓት ልሂቃን ናቸው። በእርግጥ እኔ “ንብረት ወደ ቀበሌ፣ ትግሬ ወደ መቀሌ” የሚለው አባባል ልክ “በባሌ ወይም በቦሌ…” እንደሚባለው ዓይነት ነው። የመጨረሻዎቹ ፊደላት “ሌ” ከመሆኑ በስተቀር እዚህ ግባ የሚባል ትርጉም የለውም። ለህወሓት ልሂቃን ግን በጣም አስደንጋጭ አጋጣሚ ነበር። ከኢህአዴግ አባል ድርጅቶች ውስጥ የደህዴንና ብአዴን ልሂቃን ወደ ባህር ዳር እና ሐዋሳ በመሄድ የወደፊት መሸሸጊያቸውን ሲገነቡ አልታየም። ኦህዴድ ደግሞ ጭርሽ ከአዳማ ወደ አዲስ አበባ የተመለሰው።

የ1997ቱ ምርጫ በህወሓት መሪነት የተዘረጋው መንግስታዊ ስርዓት በትጥቅ ትግል የተቆጣጠረውን የፖለቲካ ስልጣን በሕዝብ ምርጫ ለማጠናከር ያደረገው ሙከራ የፈጠረው ድንጋጤ መቼም ቢሆን ከህወሓቶች ውስጥ ሊወጣ አይችልም። ምክንያቱም ሥልጣናቸውን ለማጠናከር ያደረጉት ሙከራ በኢትዮጲያ ሕዝብ ዘንድ ምን ያህል ተቀባይነት እንደሌላቸው በግልፅ አሳያቸው። ከዚያን ግዜ በኋላ፣ ተግባራዊ እንቅስቃሴያቸው የሚመራው፣ የወደፊት አቅጣጫቸውን የሚወሰነው፣ “የቀድሞው ስርዓት ተመልሶ ይመጣል” በሚል ፍርሃት ነው።

አንድ የፖለቲካ ቡድን ስለ ቀድሞ ስርዓት በደልና ጭቆና ብቻ እያሰበ፥ ወደኋላ እያየ የሚጓዝ ከሆነ ከፊት ለፊቱ ያለውን ነባራዊ እውነታን በቅጡ መገንዘብ አይችልም። በዚህ መልኩ፣ በድንጋጤና ፍርሃት የሚደረግ ነገር የብዙሃኑን መብትና ነፃነት ይገድባል። “የቀድሞ ስርዓት ተመልሶ እንዳይመጣ” በሚል ፍርሃት ሲታትሩ በሕዝብ ላይ ከቀድሞ ስርዓት የባሰ በደልና ጭቆና መፈፀም ጀመሩ።

በመሰረቱ ፍርሃት (fear) ጨቋኛ የሆነ አምባገነናዊ (Totalitarian) መንግስት የተግባር መርህና መመሪያ ነው። መንግስት ይፈጠራል። የኢትዮጲያ ፖለቲካዊ ሁኔታ አሁን ካለበት ደረጃ የደረሰው የ1997ቱ ምርጫ በህወሓቶች ላይ ባስከተለው ድንጋጤና ፍርሃት ምክንያት የኢህአዴግ መንግስት ወደ ፍፁም አምባገነንነት በመቀየሩ ነው። በመሰረቱ “Totalitarian” ማለት “የአንድ ፓርቲ መንግስት” ማለት ነው። ኢህአዴግ በ2002 እና 2007 ዓ.ም ባካሄደው ሀገራዊ “ማጭበርበር” 99.6% እና 100% “አሸነፍኩ” ፍፁም አምባገነናዊ መንግስት የመሆኑን ያረጋግጣል።

ከዚህ በተጨማሪ፣ የህወሓት/ኢህአዴግ መንግስት ፍፁም አምባገነን የሆነበት ሁኔታ ከስርዓቱ አፈጣጠር ጋር አንድና ተመሳሳይ ነው። “በፍርሃት መርህ የሚመራ አምባገነናዊ መንግስት መቼና እንዴት ይፈጠራል?” ለሚለው፣ “Hanna Arendt” አብዮተዊ ደረጃውን (revolutionary phase) ጨርሶ በሕዝብ ዘንድ ተቀባይነት ለማግኘትና ስልጣኑን ለማጠናከር ጥረት በሚያደርግበት ወቅት እንደሆነ እንዲህ ትገልፃለች፡-

“Regimes become truly totalitarian only when they have left behind their revolutionary phase and the techniques needed for the seizure and the consolidation of power—without of course ever abandoning them, should the need arise again.” On the Nature of Totalitarianism: An Essay in Understanding: 329-360

ባለፉት አስር አመታት ህወሓት/ኢህአዴግ ፍፁም አምባገነን እየሆነ የመጣበት ሂደት ከላይ ከተጠቀሰው ጋር አንድና ተመሳሳይ እንደሆነ መገንዘብ ይቻላል። እንደ “Hanna Arendt” አገላለፅ፣ ህወሓት/ኢህአዴግ አብዮታዊ ደረጃውን ጨርሶ በዴሞክራሲያዊ ምርጫ ስልጣኑን ለማጠናከር ሙከራ ያደረገው ወደ ስልጣን የመጣበትን ዘዴ ይዞ ነው። ይህ የፖለቲካ ቡድን ወደ ስልጣን የመጣው በትጥቅ ትግል ሲሆን በምርጫው ማግስት ተመሳሳይ ስልት በመጠቀም ራሱን ከውድቀት ታድጓል። በዚህ ረገድ፣ የ1997ቱን ምርጫ ተከትሎ “አጋዚ” የተባለውን ልዩ ኃይል በአዲስ አበባ ነዋሪዎች ያደረሰው የሞትና አካል ጉዳት እንደ ማሳያ ሊጠቀስ ይችላል።

እስካሁን ድረስ የ1997ቱን ምርጫ ተከትሎ በፍርሃት መርህ የሚመራ ፍፁም ጨካኝ የሆነ አምባገነናዊ ስርዓት እንደተፈጠረ ተመልክተናል። አሁን ያለው ፖለቲካዊ ቀውስ የተፈጠረው ይህ ቡድን በፍርሃት እየተመራ በዜጎች ላይ በሚፈፅመው በደልና ጭቆና ምክንያት ነው። በዚህ ፅሁፍ፣ የኢትዮጲያ ፖለቲካ ችግር ህወሓትና ፍርሃት እንደሆኑ ተመልክተናል። “ህወሓትና ፍርሃትን እንዴት ማስወገድ ይቻላል?” የሚለውን በሌላ ፅሁፍ ይዘን እንቀርባለን።

“የወንድምህ ደም ከምድር ወደ እኔ ይጮኃል” | ሊቀ ማእመራን ቀሲስ ዶክተር አማረ ካሣዬ

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን።

“የወንድምህ ደም ከምድር ወደ እኔ ይጮኃ 

፩.     ቃየልን ለግድያ ያበቃው፤ ምንድነው? እራስ ወደድነት ፤ ቅናት ፤ ቁጣ ፤ ጥላቻ ፤ ንዴትና ምቀኝነት ናቸው።

“ለምንስ ተናደድክ? ለምንስ ፊትህ ጠቆረ? መልካም ብታደርግ ተቀባይነትን አታገኘምን? መልካም ባታደርግ ግን ኃጢአት በድጅህ እያደባች ነው”

ይህ ኃይለ ቃል መጀመሪያ የቃየል አስተሳሰብ መበላሸቱን ነው የሚያረጋግጠው ። የስው ልጅ መጀመርያ ልቡ (አስተሳሰቡ) ነው የሚታየው። ንግግሩ ወይንም ተግባሩ አይደለም።“እግዚአብሔርሰ ልበ ይሬኢ ወሰብሰ ገጸ ይሬኢ ሰው ፊትን ያያል  እግዚአብሔር ግን ልብን (አስተሳሰብን) ይመለከታል” ስንቶቻችን ዛሬ በልባችን አስበን እኔነትን አንግሠን ቅናትን ፣ ቁጣን ፣ ጥላቻን ፣ ምቀኝነትን አንግበን ፣ የወንድሞቻችንን ሚስቶች ፣ የእህቶቻንን ባሎች የተመኘን ፣ የቀማን? ወንድማችንን ፣ እህታችንን አንድ ጊዜ የአጠቃን፤ እራሳችንን ደጋግመን የምናጠቃ? በቁጣ ፣ በጥላቻ ፣ በንዴት ፣ በምቀኝነት በመነሳሳት ወንድሞቻችንን ፣ እህቶቻችንን የገደልን፤ እራሳችንን ግን ደጋግመን የምንገድል አይደለንም እንዴ’? መንግሥትም የዚሁ ኅብረተሰብ ውጤት በመሆኑ ሌላ ሊሆን አይችልም። 

፪. ቃየል አቤልን ለመግደል የተጠቀመበት ስልት ምን ነበር? በማታለል ፣ በመዋሸትና በማስመሰል ነበር። “እስቲ ና ወደ መስክ እንውጣ አለው በመስክም ሳሉ ወንድሙ አቤልን አጠቃው ገደለውም”። ይህ መጀመሪያው ነፍሰ ገዳይ ነው። “እስኪ ና ወደ መስክ እንውጣ” ዐይን ባወጣ ማታለል በወንድሙ ላይ እና በጻድቅ ሰው ላይ ተፈጸመ አረመኔያዊ ድርጊት ነው። የሰው ልጅ ከአራዊት የባሰ መሆኑን ያረጋግጣል። ዛሬስ በሀገራችን በማታለል ፣በመዋሽት ፣ በማስመስል «ዲሞክራሲ አስፈንኩልህ ፤ በነፃነት የማምለክ ፣ የመናገርና የመጻፍ የተፈጥሮ መብትህን አስከብርኩልህ» እያለ፣ በወልድያ አምልኮታቸውን በሚፈጽሙበት ወቅት በደም የተጥመቁ የአቤል እድል ፈንታ የገጠማቸውን ስማእታተ-ወልድያን እናስባቸዋለን፤ ለዘለዓለም ታሪክ ሲያስትውሳቸውም ይኖራል። ቃየላዊ ተግባር የፈጸመውንና የሚፈጽመውን መንግሥት በእግዚአብሔር ስም እናውግዛለን። ከእንደዚህ ያለው እኩይ ተግባር እንዲርቅና እንዲያቆም በእግዚአብሔር ስም እናስጠነቅቃለን። በውስጥና በውጭ የአላችሁ ከሕዝብ ጎን ቆመናል የምትሉ ወታደሮች ፣ አርበኞች ፣ ምሁራን ፣ የሀገር ሽማግሌዎችና የፖለቲካ ሰዎች፣ ከቃየላዊ ባሕርይና ግብር የተላቀቃችሁ እንድትሆኑ በእግዚአብሔር ስም አደራ እንላለን።

፫/ ከግድያ በኋላ እግዚአብሔርስ ለገዳዩ ምን  አለው? ገዳዩስ ምን መልስ ሰጠ?

“እግዚአብሔር ቃየልን ወንድምህ አቤል የት ነው ? አለው። ቃየልም አላውቅም ፤ እኔ የወንድሜ ጠባቂ ነኝን? ሲል መለሰ።” ወንድሙን የእናቱን ልጅ አንድ ቀን ተጸንሰው አንድ ቀን የተወለዱ ሆኖ እያለ “አላውቅም” ማለት ዓይን ያወጣ ውሽት ፣ ክህደትና ሽፍጥ ነው። ከጭካኔ የመነጨ የግዴለሽነትና «ማን አለብኝ» የሚል የድፍረትና የትዕቢት አባባል ነው። የቃየልን አባባል ዛሬ ሥልጣንን ሙጥኝ ያለው መንግሥት ፣ እንዲጠብቅ የተሰጠውን መንጋና የገዛ ወገኑን በጭካኔ ሲገርፍ ፣ ሲያስርና ሲገድል፣ እኩይ ግብሩ እንደማያውቀው ቃየላዊ ድርጊቱ ያረጋግጣል። ከጥቂቶቻችን በቀር የእያንዳዳችን ልብ(ኃሣብ) ቢመዘንና ተከፍቶ ቢታይ ቃየላዊ ልብ(ኃብ) ነው የሚታየው

፬. እግዚአብሔር ገዳዩ ላይ ምን አደረገ?

“እግዚአብሔር እንዲህ አለ ምንድን ነው ያድረከው? የወንድምህ ደም ወደ እኔ ይጮኃል።እንግዲህ የተረገምክ ነህ። የወንድምህን ደም ከእጅህ ለመቀበል አፏን ከከፈተችው መሬት ትሰደዳለህ … በምድር ላይ ኮብላይ ተቅብዝባዥ ትሆናለህ።” አቤል በወንድሙ በግፍ ቢገደልም እንኳን እስከ አሁን እምነቱ ጽድቅ ሆኖ ሲነገር ይኖራል። ምክንያቱም በወንድሞቻቸው ላይ ክፉ በሚያደርጉ ሰዎች ምክንያት ደማቸው የፈሰሰው ፣ ወደ እግዚአብሔር ከመጮህ አያቋርጥም። እርግማኑ በበዳዩና ክፉ አድራጊው ላይ ብቻ ሳይሆን ፣ በዘሩ ፣ በማንዘሩ ፣ በከብቱ ፣ በሀብቱ ፣ በሚያርሰው ምድር ሳይቀር የሚፈጸም ነው። ገበሬ የሚዘራውን ያጭዳል። መከሩም ደርሷል። ኮርቻውም ዘሟል። ከመውደቁ በፊት አስተካክለው። ኮቻቸው ዘሞ ሳስተካክሉ የደቁትን እነሳዳም እነሙባርቅ ፣ እነጋዳፊ ምሳሌ ይሁኑህ። ንስሐ ግባ፤ ዚያ ቶሎ እመጣብኃለሁ ፤ በአፌም ሰይፍ እዋሁ” ይላል የሠራዊት አምላክ እግዚአብሔር።

/ ገዳዩ ቃየል ከእግዚአብሔር ፍርድ በኋላ፤ ምን አለ?

“ቃየልም እግዚአብሔርን እንዲህ አለው ፥ ቅጣቴ ከምሸከመው በላይ ነው። እነሆ ዛሬ ክምድሪቱ አሳደድከኝ፤ ከፊትሕም እሸሻለሁ ፤ በምድር ላይ ኮብላይና ተቅበዝባሽ እሆናለሁ፤የሚያገኘኝ ሁሉ ይገለኛል።” ቃየል ከፈጸመው በደል የተነሣ በደረሰበት የእርግማን ምት ለራሱ አዘነ እንጂ ኃጢአቱን አስቦ ፤ ጸጸቱ የንስሐ ፀፀት አልነበረም። ይባስ ብሎ ኃጢአትን በኃጢአት ላይ እየደራረበ ይፈጽም ነበር። ለምሳሌ በምንባቡ እንደተገለጸው፤ እግዚአብሔርን ናቀ፤ ናተኛና ነፍሰ ገዳይ ሆነ፤ ዋሾና እራስ ወዳድነቱን አጠነክረ፤ የዚህ ሁሉ ውጤት ከእግዚአብሔር እንዲለይ አድረገው። የዚህ ዓይነቱን ጸጸት በሐዲስ ኪዳን ይሁዳም ደግሞታል። የኢትጵያ መንግሥት ገና ከጅምሩ እያቃጠለ እያፍረሰ እየገደለ እንደመጣ የቅርብ ጊዜ ተውስታ ነው። ኦርቶዶክሱንና አማራውን ለማዳክምና ብሎም ለማውደም የቤት ሥራ ተስጥቶት በደደቢት የተቀለው  የጥፋት ወንጌል ነው። በትረመንግሥቱን ከጨበጠም በኋላ በጎንደር መካነ ኢየሱስ አባባይ፣ በአዲስ አበባ እስጢፋኖስ ቤተ ክርስቲያን ፣ ቃየላዊ ግድያን ፈጽሟል። የዋልድባ ገዳማትን መዝብሯል። መነኮስቱ ታሥረዋል ፤ መነኮሳይያቱም ተደፍረዋል። እስከ አሁን በአደገው ወንጀል እንዲጸጸትና ንስሐ እንዲገባ ጊዜ ተሰጠው፤ ብሔራዊ እርቅና ይቅርታ እንዲያመጣ ተነገረው፤ ይባስ ብሎ ጸጸቱን ወደ ቁጭትና ጭካኔ በመለወጥ በአለፈው ሳምንት በወልድያ የጥምቀትን በዓል በማክበር ላይ ባሉ ክርስቲያኖች ላይ ጭፍጨፋ እንዲፈጸምባቸው ተደረገ። በሃያ አንኛው መቶ ክፍለ ዘመን በጅማ ክፍለ ሀገር በሻ አቡነ አረጋዊ ቀበሌ በአረማውያን የታረዱ የመጀያዎቹ ሰማዕታት ሲሆኑ ፣ ብያ በውቅያኖስ ዳርቻ በአይሲሲ የታረዱና የተረሸኑ ሁለተኛው ሰማዕታተኢትዮጵያን እናስታውሳቸዋለን። የኢትዮጵያ ሥርወመንግሥት መጀመያ የብሉይ ኪዳን መሠረቱ የክርስትና ምንጩ በአኩስምና በአዋ ተወላጆች ክርስቲያኖች በክርስቲያኖች የተሰዉ ሦስኞቹ ሰማዕታተወልድያ በመባል ሲታሰቡ ይኖራሉ።

በመጨረሻ

ይድረስ ለኢትዮጵያ መንግሥት፥

ሀ/      ለሃያ ዓመታት ያህል መንጋውን እንድትመራ ሥልጣኑ ተሰጠህ ያከበረህን እግዚአብሔርን ናቅኸው፤ እሱም የሰጠህን የመሪነት ሥልጣኑን ከአንተ ወስዶታል። በሌለህ ሥልጣን ሕዝብ አታስፈጅ ፣ ንብረት አታውድም “ክወደቁ በኋላ መንፈራገጥ ለ….” እንደተባለው ይሆንብኃል።

ለ/      አሁንም ጀንበሯ ለመጥለቅ እየፈጠነች ነውና ጨርሳ ከመጥለቋ በፊት የናቅኸውን ፈጣሪህን ተማለለው ፤ ንስሐ ግባ ፤ ሕዝብን ይቅርታ ጠይቅ።

ሐ/     “ሰው ሌላውን ቢበድል  እግዚአብሔር ጣልቃ ገብቶ ይፈርዳል ፤ ሰው እግዚአብሔርን ቢበድል ማን ይማልድለታል?” የተባለው በአንተ እየተፈጸመ ነውና የአለህበትን ጊዜ ፣የቆምክበትን ሥፍራ ተመልከት።

መ/     ለአሥራ ሰባት ዓመታት በበረሃ የተንክራተትከው ፣ የተገርፍከው ፣ የሞትከው ፣ ከደርግ ጋር የተፋለምከው ፣ ደርግን ተክተህ በቀልህን በመውጣት ወንድምህን (ወገንህን) ለማሠር ፣ ለመግረፍ ፣ ለማሰቃየትና  ለመግደል ነበርን? የነበርክበትን አስብ። ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወ/ሥላሴ በንጉሠ ነገሥቱ ጊዜ የውጪ ጉዳይ ሚኒስተር ነበሩ፤ የአብነት ተማሪ  በነበሩ ጊዜ ይለብሷት የነበርችውን ደበሎ ሳሎን በክብር ቦታ አስቀምጥዋት ነበር ይባላል፤ «ምነው ?» ተብለው ለተጠየቁት ጥያቄ «የነበርኩበትን እንዳልረሳ» አሉ ይባላል።

ሠ/    ይድረስ ለቤተ ክርስቲያን መሪዎች ፥ ቤተ ክርስቲያኒቱን እንደጥገት የምታልቧት ፤ በዚህ ዘመን ያላችሁ ከጥቂቶች በቀር ጳጳሳት ፣ መነኮሳት ፣ ቆሞሳት ፣ ቀሳውስት ፣ ሰባክያን ፣መዘምራንና የማኅበራት አባላት ፤ እንዲሁም በክርስትና ስም የምትነግዱ ፓስተሮች ፤ በኢትዮጵያ ለፈሰሰውና ለሚፈሰው ደም ተጠያቂዎች ናችሁ(ነን)። ለምን እንደሆነ እናንተም ታውቁታላችሁ ፤ ለሚጠይቀኝ መልስ አለኝ።

ረ/    ይድረስ ለኢትዮጵያ ተቃዋሚ ኃይሎች፥ በውስጥም ፣ በውጪም የአላችሁ “ጨቋኝ ለመሆን ጭቆናን መቃወሙን አቁሙ(እናቁም)። ደርግና ወያኔ አንግበው የመጡት ምን እንደነበር ፣ ምን ሠርተው እንደአለፉ ፣ ምን እየሠሩ እንደሆነ ትምህርት ይሁናችሁ(ይሁነን)። ኢትዮጵያ ሀገረ-እግዚአብሔር እንደሆነች በመጽሐፍ ቅዱስም ሆነ በቁራኑ ይነበባል፤ ሕዝቧም እድሉ እግዚአብሔር ነው። እምነቱን ለፖለቲካ ግባት አናድርገው(አታድርጉት)። እግዚአብሔር እውነት ፣ ቅን ፣ ፍቅር ነው። በእውነት ፣ በቅንነትና በፍቅር ላይ የተመሠረት የፖለቲካ ዓላማና ግባት ይኑረን (ይኑራችሁ)።

ሰ/    ይድረስ ለኢትዮጵያ ሕዝብ፥ የአርባ ዓመታት የፖለቲካ ፣ የንውውጽታ ዘመን አሳልፈሐል ፤ የአለፉት የመክራና የስቃይ ዘመናት ትምህርት ሊሆኑህ ይገባል። ደግመህ ያለፈውን ስሕተት እንዳትፈጽም ተጠንቀቅ። በእሳት አትጫወት  ተቃውሞህ በጥበብና በማስተዋል ይሁን። ጠላት በአንተ ሊጠቀም ያስታጠቀህን የዘር ትጥቅህን ፈትተህ ጣለው።ዘርህ ኢትዮጵያዊነት ነው። ኢትዮጵያዊነትህ ደግሞ መታወቂያህ ፣ ክብርህ ፣ ሞገስህ ፣ ድልህ ፣ ሐብትህ ፣ ንብረትህና ሕይወትህም ነው።

ሸ/      ሀገር የምትመራው የመምራት ጸጋው (ክራዝማው) የተሰጣቸው እንደነ ሙሴ ፣ ዳዊት ሰሎሞንና ጌድዮን ያሉ በፖለቲካ ሰዎች(ምሁራን) ነው። እግዚአብሔርን የሚያስቀድሙ ፣ሕዝብን የሚያከብሩ (ፍቅረ እግዛብሔርና ፍቅረ ቢጽ የአላቸውን) መሪዎችህን ምረጥ።”ተከትል አለቃህን ፣ ተመልከት ዓላመህን” እንደሚባለው ፣ የመረጥካቸውን መሪዎችህን ተከትል ፤ ዓላማህን የኢትዮጵያን አንድነት ተመልከት።

ቀ/    ይድረስ ለዲስና ለአካባቢው ማኅበረ ምዕመናን

በዲሲ በአካባቢውና በዝርወት ለአላችሁ ማኅበረ ምዕመናን ፥ በሀገራችን ለተከሰተው ፣ እየተከሰተ ለአለው ግድያ ፣ ንውውጽታ ግድ ይለናል። አፍ ላጣው አፍ ፣ ምግብ ለአጣው ዳቦ ፣ ቤት ለአጣው መጠለያ ፣ ጤና ላጣው ህክምና ፣ ለተራቆመተው ልብስ ልንሆነው ይገባል። እንደየአቅማችን ፣ እንደ ችሎታችን ፣በሁሉም አቅጣጫ ልናደርግ የሚገባንን እናድርግላቸው። ልቁና መልስ የናገኝበት ወደ እግዚአብሔር በጸሎትና በምልጃ መቅረብ ነው። ሀገራችንን ክፍርስራሽ ክምር ፣ ከእሳት ቃጥሎ ፣ ከሙታን ከተማ ፣ ከተቃጣው ሠይፍ ፣ ክተወረወረው ጦር ፣ ማዳን የሚችል እግዚአብሔር ብቻ ነው። ቅንቅን ከሆነብን ቅናትና ምቀኝነት ፣ እንደ ጦር ከሚወጋን ቂም ፣ እንደ ሰይፍ ከሚቆራርጠን በቀልና ጥላቻ እንላቀቅ። እርስ በርሳችን ክልብ ይቅር እንባባል። የመምሰልና የማስመሰልን ይቅርታ እግዚአብሔር ይጸየፈዋልና ከዚህ እንራቅ። በአለፈው የልደት ማግሥት ጀምረን ለአምስት ቀናት እንደአደረግነው ፣ ዛሬም ከነገ ጥር ፳፩ ቀን ጀምሮ እስክ ጥር ፳፭ ቀን ድረስ ሦስቱን የነነዌ ጾም ቀናት እስከ ሠርክ በመጸም ፤ የሠርክ ጸሎት በሚካሄድባቸው አብያተ ክርስቲያናት በመገኘት ፣ የምኅላ ጸሎት ማድረስና ምንባባቱ ሰቆቃው ኤርምያስ ከምዕራፍ አንድ እስክ አምስት በተመቸ ጊዜያት ፣ በግልም ፣ በኅብረትም በአንብአ ንስሐ ሆነን እንድናነበውና እንድንጸልይ ፣ በእግዚአብሔር ስም የአደራ መልዕክቴን በአክብሮት አስተላልፋለሁ።

እግዚአብሔር ሀገራችንንና ሕዝባችንን ከተቃጣው ሠይፍ ክተወረወረው ጦር ይታደግልን።

                                         አሜን።

ሊቀ ማእመራን ቀሲስ ዶክተር አማረ ካሣዬ (amare.kassaye @gmail.com)

በዝርወት ላይ ያለችው የርእሰ አድባራት ደብረ ሰላም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አስተዳዳሪ

ዋሽንግተን ፣ ዲሲ

እሑድ ጥር ፳ ቀን ፳፲ ዓ.ም (01/28/18)                                                    ከአ/ካ

የማያባራውን ስርዓት ወለድ የእልቂት ዘመቻ በህብረት እንቅረፈው ( በ ዶ/ር አክሎግ ቢራራ)

አክሎግ ቢራራ (ዶር)
አክሎግ ቢራራ (ዶር)

እረጋ ብለን ብናጤነው፤ እኛ ኢትዮጵያዊያን ከሚለያዩን ሁኔታዎች በላቀ ደረጃ የምንጋራቸው ጥሪቶች፤ የታሪክ ሂደቶች፤ ልምዶች፤ የጋራ መነሻዎችና ብናውቅበት፤ የጋራ መድረሻዎች አሉን። ብናውቅበት፤ የተፈጥሮ ኃብታችን ለአገራችን ሕዝብ ፍላጎት ይበቃል፤ ለሌችም ሊተርፍ ይችላል። በዚህ ወር ብቻ ኢትዮጵያ በዓለም ደረጃ ከፍተኛ ገቢ የሚያስገኝ የወርቅ ኃብት ሊመረትባት የምትችል አገር መሆኗ በሰፊው ተወርቷል። የውሃ ኃብቷ ዝነኛና አኩሪ መሆኑ ከተወራ ቆይቷል። የተፈጥሮ ኃብት እርግማን ወይንም ምርቃን ሊሆን ይችላል። ጥያቄው፤ እነዚህንና ሌሎችን የተፈጥሮ ኃብቶች ማን ይጠቀምባቸው ይሆን? የሚለው ነው።

ቢያንስ ቢያንስ፤ የኢትዮጵያ ህጻናት በቋንቋና በጎሳ ልዩነቶች ላይ በተመሰረተው የህወሕት/ኢህአዴግ አገዛዝ ሊጨፈጨፉ አይገባም ነበር;፡ እነዚህ ለጋውዎችና ጮርቃዎች ምን ወንጀል ሰርተው ነው በዚህ አገዛዝ በተደጋጋሚ፤ በጭካኔና ታይቶና ተሰምቶ በማይታወቅ ደረጃ የሚጨፈጨፉት? በቆቦ የሰባት ዓመት ልጅ፤ በወልድያ የአስራ ሶስት ዓመት ወጣት፤ ቀደም ሲል በቡኖ በደሌ የሶስት ወር ህጻን ሴት ልጅ ተረሸነች፤ የስድስት ወር ሕጻን ሴት ልጅ ወደ ጉድጓድ ተወርውራ ተገደለች። ይህን ጭካኔ የሚፈጽመው የህወሓት አጋዚና በህወሓት የሚመሩ የፌደራልና ሌሎች ኃሎች ናቸው። ከመቀሌ የበረረው “የትግራይ”  ሄሊኮፕተር በንጹሃን አማራዎች ላይ ጭካኔ ሲፈጽም ከዚህ የባሰ የዘር ማጥፋት ዘመቻ ሊጠበቅ አይችልም። የተቀነባበረው የአማራን ብሄር የማጥፋት እርምጃው ዛሬ ሳይሆን የተጀመረው ህወሓት ሥልጣን ከመያዙ በፊት ነው—ወልቃይት-ጠገዴ። የአማራው ብሄር ተተኪ መሪዎችና ተተኪ ትውልድ እንዳይኖረው የአማራ ህጻናትም ጭምር እየተጨፈጨፉ ነው።

ይህ በቋንቋና በጎሳ ለይቶ ህጻናትን ጭምር የመረሸን በሽታ ከየትና ለምን ተከሰተ? የሚለውን፤ እርህራሄ የሌለው የተደጋገመ ወንጀል መጠየቅና ለዚህ ኢ-ስብአዊ ወንጀል መፍትሄ መፈለግ ያለበት ለሂሊናው የሚገዛ ግለሰብ ሁሉ ነው። በመጀመሪያ ደረጃ ራሱን ከዚህ እልቂት ማዳን ያለበት አማራውና ኦሮሞው ነው። ኢትዮጵያ ህጻናቶቿንና ሌሎች ልጆቿን እያስጨፈጨፈች ልትቀጥል አትችልም። የህወሓት ኢላማ የሆነው የኦሮሞውን የአማራው ሕዝብ በተለይ፤ ራሱን ከጭፍጨፋና ከውርደት ለማዳን ቆርጦና ተባብሮ ጨካኙን የህወሓትን ነፍሰ-ገዳይ ቡድን በጋራ መታገል አለበት። ይህ ግዙፍና እምቅ ኃይል ያለው ሕዝብ፤ ከአሁን በኋላ ህወሕት ህጻናትን እንዲጨፈጭፍና ኢትዮጵያን እንዲገዛ መፍቀድ የለበትም።

ከላይ ተገኘ የተባለው የወርቅ ኃብትና ሌሎች ግዙፍ የተፈጥሮ ኃብቶች፤ ለህወሓቶችና ለሌሎች ኪራይ ሰብሳቢዎች ሳይሆን፤ ለአገርና ለዜጎች ጥቅም ከዋሉ፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከድህነት ሰቆቃ ነጻ እንደሚወጣ አልጠራጠርም። ኢትዮጵያ ከውጭ እርዳታ ነጻ ወጥታ ኃብታምና ጠንካራ አገር ልትሆን ትችላለች። ይኼ ስኬታማ ሊሆን የሚችለው ግን ጭፍጨፋው በአስቸኳይ ሲቆም፤ ወንጀለኞቹ ለፍርድ ሲቀርቡ፤ ብሄራዊ መግባባት ሲኖርና ሕዝቡ የፖለቲካ ሥልጣኑ ባለቤት ሲሆን ነው። ሕዝብ የፖለቲካ ሥልጣኑ ባለቤት የሚሆነው በምኞት አይደለም። በፖለቲካ ልሂቃን ጥረት ብቻ ሊሆንም አይችልም። ሕዝብ የፖለቲካ ሥልጣኑ ባለቤት የሚሆነው እውነተኛ ዲሞክራሳዊ ሥርዓት ሲመሰረት ብቻ ነው።

እኛ የሚጎድለን ለጋራ አገር ክብርና ለአንድ ህብረ-ሕዝብ የጋራ ጥቅምና የፍላጎት ማሟላት ጥረት የጋራ ዓላማ አለመኖሩ፤ ጭካኔዎችን በጋራ ተታግለን ለማቆም አለመቻላችን ነው። አንዱ ሲጨፈጨፍ ሌላው በፍጥነት አለመነሳቱ ነው። ባለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት በሚዘገንንና በሚጎዳ ሁኔታ የታየውና የተከሰተው እንደምታ፤ የራስን ወይንም የግልን ወይንም የብሄርን/የጎሳን ጥቅም ከአገርና ከሕዝብ ጥቅም በላይ መተግበራችን ነው። በቋንቋና በጎሳ ልዩነቶች ላይ የተመሰረተው ‘የፌደራል” አገዛዝ ለጋራ ብሄራዊ ዓላማ፤ ለአገር አንድነት፤ ሉዓላዊነትና ለጋራ የሕዝብ ኑሮ መሻሻል ጸር ሆኗል። የማንነት ጥያቄ በተሳሳተና አደገኛ በሆነ መንገድ እንዲተገበር ተደርጓል። ህጻናትን ለይቶ መግደል ከዚህ የማንነት ጥያቄ ጋር የተያያዘ ነው። የጋራ አገር የጋራን መብትን የጋራን ጥቅም ማስከበር አለበት። “ተባበሩ ውይንም ተሰባበሩ” ይላሉ አበው።

የማናኛውም ኢትዮጵያዊ የቋንቋ፤ የባህል፤ የኃይማኖት፤ የታሪክና ሌሎች መለያዎቹ ሕጋዊ እውቅና እንዲኖራቸውና እንዲከበሩ እፈልጋለሁ። በተመሳሳይ ደረጃ ዋናው የዜግነት መለያችን ኢትዮጵያዊነት ሕጋዊና ብሄራዊ ተቀዳሚነት እንዲኖረው ሁላችንም መረባረብ አለብን። የተጨፈጨፉትና በእስር ቤቶች የሚሰቃዩት ወንድሞቻችን፤ እህቶቻችን ዋናው መለያቸው ሰብእነታቸው፤ ኢትዮጵያዊነታቸው ነው። አማራው ኢትዮጵያዊ፤ ኦሮሞው ኢትዮጵያዊ፤ አኟኩ ኢትዮጵያዊ ወዘተ ተጨፍጭፏል፤ ይጨፈጨፋል። በተለየና በባሰ ደረጃ የሚጨፈጨፈው በኢትዮጵያዊነቱ የሚያምነውና የሚኮራው፤ ለሁሉም ኢትዮጵያዊያን የሚታገለው፤ ለዲሞክራሲና ለሕግ የበላይነት የሚከራከረው ክፍል አባል መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ።

ቁም ነገሩ ኦሮሞው ሆነ፤ አማራው፤ አኟኩ ሆነ ሌላው ሲጨፈጨፍ በአንድ ድምጽ፤ በአንድነት መቆም ወሳኝ መሆኑ ነው። ይህን አላደረግንም። የእያንዳዱ ኢትዮጵያዊ ሞት የራሳችን ሞት መሆኑን መቀበል ግዴታችን ነው። “የኦሮሞው ሞት የእኔም ሞት ነው፤ የአማራው ሞት የእኔም ሞት ነው” የምንልበት ጊዜ ዛሬ ነው። ይህ መፈክር መተግበር አለበት።

በማንነት ጥያቄ ዙሪያ የሚደረገው የፖለቲካ ንግድ ለኢትዮጵያ አደገኛ መሆኑን፤ ለሚደረገው እልቂት መንስኤና ምክንያት መሆኑን በተደጋጋሚ አይተናል፤ ተጨማሪ መረጃ አያስፍልገንም። በአንድ ድምጽ እልቂቱን ማውገዝና እልቂት እንዳይደገም ማድረግ ወሳኝ ሆኗል። ጭፍጨፋ የህወሓት ሥልጣን ማቆያ መሳሪያ እንዲሆን መፍቀድ የለብንም። እልቂት እየተካሄደ እድገት አለ፤ የውጭ መዋእለንዋይ “በሽ በሽ ነው” የሚሉ አፈቀላጢዎች እድገቱንና ፈሰሱን ከእልቂቱ ጋር አጣምረው ተናግረው አያውቁም። ፈሰሱ ለጥቂቶች መሳለቂያና መዝናኛ ከሆነ ማህበረሰባዊው ፋይዳው የት ላይ? ነው።

ለእኔ ገዢና ወሳኝ መመሪያየ ጎንደር መወለዴና የአማራ ብሄር አባል መሆኔ አይደለም። ይኼን ማንነቴን ማንም ኃይል ሊነጥቀኝ ወይንም ሊያስተምረኝ አይችልም። ዋናው መለያየ ኢትዮጵያዊነቴ ነው።  ሰብእነቴ ነው። ጎንደሬው “የኦሮሞው ደም ደማችን ነው” ሲል እምነቴ በኢትዮጵያዊነቴ ነው ማለት ነው። ይህ የጋራ መለያችን ሊሰብስበን ይገባል።

እኔ ክልል (መለያ) የሚለውን የመለያያ ቃል አልቀበልም። መለያየት ስለሆነ። “የክልሉ” ስርዓት የኢትዮጵያን ዘላቂ ጥቅም ለማስከበር፤ ኢትዮጵያዊነትን ለማጠናከር፤ የዜጎችን የኑሮ ፍላጎት ለማሟላት፤ የኢትዮጵያዊያንን ትሥስር መሰረት ለማጠናከር አላስቻለም። “የክልል” ምሁራን፤ ልሂቃንና ሌሎች የጋራ ወይንም ኢትዮጵያዊ የሆነ ዓላማ አይጋሩም። ዛሬ አገራችን ለጥቃት ካጋለጧት እንደምታዎች መካከል አንዱ እኛ ኢትዮጵያዊያን ለጋራ አገር፤ ለጋርዮሽ ጥቅም በጋራ ለመወያየትና መፍትሄዎችን ለመፈለግ ፈቃደኛ አለመሆናችን ነው። “እኔ ያልኩት ብቻ” የሚል የትእቢተኞች ብሂል የትም አላደረሰንም፤ አያደርሰንም። ይህ በብሄርና በቡድን ዙሪያ መበታተን ለገዢው ፓርቲና ለውጭ ጠላቶች መሳሪያ ሆኗል።

ዛሬ፤ ለመሬትና ለሌላ የተፈጥሮ ኃብት የበላይነት የሚደረገው የጦፈ ትግል በብሄር ማንነትና ጥቅም ዙሪያ ሲሆን፤ ተጠቃሚው ተራው ሕዝብ ሳይሆን በአብዛኛው ጠባብ ብሄርተኞችና እነሱ የፈጠሯቸው ኪራይ ሰብሳቢዎች የሚባሉት ናቸው። የክልሉ ስርዓት ጠባብ ብሄርተኝነትን፤ የግል/የቤተስብንና የቡድንን ጥቅሞች አጠናክሯል፤ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን አዳክሟል። ለጭፍጨፋው መሰረታዊ ምክንያት ይኼ በጥቅም ዙርያ የተቀናጀ፤ “እኛና እነሱ” የሚል የማይታረቅ ልዩነት እየሆነ መሄዱ ያሳፍራል። “እኛ ኢትዮጵያዊያን” የሚለው ብሄራዊ መፈክር ለምን ተናቀ?

በማንነት ስም የግልና የቤተሰብ ጥቅም፤ የብሄርና የአካባቢ ጥቅም የበላይ በሚሆንበት ጊዜ ትግሉና ትኩረቱ ለጋራ ዓላማ ሊሆን አይችልም። የኢትዮጵያ የውጭ ጠላቶች እኛን የሚያጠቁን በራሳችን ስግብግብነት፤ በራሳችን ጉራ፤ በራሳችን አለመግባባት ወዘተ ነው። ኢትዮጵያዊነትን የዜግነት መለያችን አለማድረግ ለውጭ ጠላቶቻችንም መሳሪያ ነው።

ገዢው ቡድን ትላንት የኦሮሞውን ወጣት፤ ዛሬ የአማራውን ወጣት፤ ነገ የአኟኩን ወዘተ እየለየና እየከፋፈለ የሚጨፈጨፈው፤ በህወሓት የበላይነት የሚመራው አገዛዝ በምንም መስፈርት ቢገመገም፤ ራሱን ተችቶና አርሞ ለኢትዮጵያ ዘላቂነት፤ ለሕዝቧ፤ በተለይ ለወጣቱ ትውልድ ህይዎት ፋይዳ ያለው ለውጥ ያመጣል ብሎ መናገርና ማሰብ ሕዝብን ያስጠቃል፤ አገርን ያጠፋል። ህወሓት የሕዝብን መዋእለንዋይ ፈሰስ እያደረገ ራሱን እገመግማለሁ ሲል፤ መፍትሄ የሚፈልገው እንዴት አድርጌ የበላይነቴንና ስልጣኔን ልቀጥል በሚል ስልት እንጅ፤ ሕዝብ ስለጠላኝና ስለማይፈልገኝ፤ ስልጣኔን ለሕዝብ ላስረክብ፤ ሕዝቡ የፖለቲካ ስልጣኑ ባለቤት ይሁን፤ ሕዝቡ የተፈጥሮ ኃብቱ ተጠቃሚ የመሆን መብት አለው በሚል እምነት አይደለም። ገዢው ቡድን የሚፈራው ሕዝቡን ነው። ሕዝቡን ከፈራው፤ እየለየ የሚገድለው ለሕዝቡ መብት የቆመውን ግለሰብ ነው። ይህ እየለዩ ማጥቃት አገር ውስጥና አገር ውጭ ያለውን አይለይም።

አገዛዙ ፍትህና ነጻነት ለሚፈልገውና በሰላም ድምጹን ለሚያሰማው ዜጋ ሁሉ የሚሰጠው መልስ አንድ ብቻ ነው–ጭካኔና ግድያ። ይህ የማያባራ ጭካኔ ሊቆም የሚችለው አገዛዙ ተወግዶ ሕዝብ የፖለቲካ ሥልጣኑ ባለቤት ሲሆን ብቻ ነው። ሕዝብ የፖለቲካ ሥልጣኑ ባለቤት የሚሆነው ዲሞክራሳዊ ስርዓት ሲመሰረት ብቻ ነው።  “ዲሞክራሲን” መነገጃ ያደረገው፤የህወሓት ባህርይና ተልእኮ ይለወጣል ብሎ ማሰብ ራስን እየሸነገሉ፤ ሕዝብን ለእልቂት ማጋለጥ ነው። ሽንገላው በልዩ ልዩ መልኮች ይታያል። ለምሳሌ፤ ገዢው ቡድን “በኢትዮጵያ አንድም የፖለቲካ እስረኛ የለም” ካለ በኋላ ሁሉንም የፖለቲካ እስረኞች እፈታለሁ ብሎ ማለ፤ ተገዘተ። የታወቀውን የፍትህ፤ የነጻነትና የዲሞክራሲ ጠበቃ፤ ከጅምሩም መታሰር የሌለበትን ፕሮፌሰር መረራ ጉዲናን ፈታ።

ይህ ጥሩ ውሳኔ ነው። በመቶ የሚቆጠሩ የታሰሩበት ምክንያት ግልጽ ያልሆነ ዜጋዎችንም ፈታ። ሆኖም፤ በብዙ ሽህ የሚገመተውን፤ ከእነዚህ መካከል ዓለም የሚያውቃቸውን የፖለቲካ እስረኞች (እስክንድር ነጋን፤ አንዱዓለም አራጌን፤  አንዳርጋቸው ጽጌን ወዘተ፤ ወዘተ) አልፈታም። የኢትዮጵያንና የዓለምን ሕዝብ ለመሸንገል የተደረገው እርምጃ ትዝብትን አስከትሏል። ዛሬ ፈታሁ ብሎ ነገ ያስራል። የተባበሩት መንግሥታትና ሌሎች ዓለም አቀፍ ድርጅቶችና መንግሥታት “የኢትዮጵያ መንግሥት ያልተፈቱትን የፖለቲካና የህሊና እስረኞች በአስቸኳይ እንዲፈታ” የጠየቁበት ዋና ምክንያት ገዢው ቡድን በኢትዮጵያዊያን ህይወት መነገዱኑና መቀለዱን ስለቀጠለ ነው። ሁሉም የፖለቲካ እስረኞች እንዲፈቱ ተከታታይ ትግልና ጥረት ማድረግ ግዴታችን ነው። ከዚህ በበለጠ ግን አገር ቤት የሚታገሉትን ወገኖቻችን መደገፍ ወሳኝ ነው።

የታወቁ የፖለቲካ እስረኞችን የማይፈታበት ምክንያት ተቀናቃኝ ስለማይፈልግ ነው። ገዢው ቡድን ሰላምንና መግባባትን አይወድም። እንደራደር ሲል ማዘናጊያ ነው። ልዩነቶችን ማስተናገድን አይፈቅድም። ሌላው ቀርቶ ለኃይማኖትና ለእምነት ተከታዮች ደንታ የለውም። እንዲያውም ስለማያከብራቸው እያጠፋቸው ነው።

ህወሓት በበላይነት የሚያሽከረከረው አገዛዝ ማንኛውንም “ተቃዋሚ” አይምርም። በሰላም የሚታገል ግለሰብ፤ ልዩነቱን በሰላማዊ መንገድ ሲገልጽ አይምረውም። አንድ ኢትዮጵያዊ፤ ነጻነቱን መሰረት አድርጎ፤ ሕገመንግሥቱ የሚሰጠውን ሰብአዊ መብት ተጠቅሞ በሰላማዊ መንገድ ሃሳቡን በጽሁፍ ሆነ በአካል ቢገልጽ ልክ መሳሪያ ይዞ ከሚታገል ግለሰብ አይለየውም። ለገዢው ፓርቲ ተቃዋሚ ማለት “ጸረ-ሕገመንግሥት፤ ጸረ-ሰላምና እርጋታ፤ ጸረ-ዲሞክራሲ” ነው። መስፈርቱን ያወጣው ራሱ ነው፤ ትርጉሙን የሚሰጠን ራሱ ነው። ፈራጁ ራሱ ስለሆነ፤ በሰላም ተቃውሞውን የሚያሰማ ግለሰብ “ጠላት” ነው። ዲሞክራሲን አከብራለሁ በሚል ማባበያ ጸረ-ዲሞክራሳዊ ስራዎችን ሲተገብር የቆየን ቡድን ዛሬ፤ ነገ ይለወጣል ብሎ ማመን ራስን ማታለል ነው። በአጭሩ፤ በጠላትነት የተፈረጀ ስርዓት ዲሞክራሳዊ ሊሆን አይችልም።

የዚህ ትንተና መሰረታዊ ሃሳብ፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ እና “አማራጭ ኃይሎች” ከአሁን በኋላ እናቶች፤ በህወሓት የበላዮችና አለቃዎች አልሞ ተኳሽዎችና በሌሎች ለሕዝብ ህይወት ደንታ የሌላቸው ጨካኞች የሚገደሉትን ልጆቻቸውን እያለቀሱ ከመቅበር ባሻገር ዘላቂ መፍትሄ መፈለግ ታሪካዊ ግዴታችን ነው የሚል ሃሳብና ምክር ነው። “ነገ ባለተራው ማን ይሆን?” እያልን ሃያ ሰባት የስቃይ ዓመታትን አሳልፈናል። ከግል ጥቅምና ከግል ዝና ውጭ፤ ይህ ሊቀጥል አይችልም ብለን ለመነሳት የማያስችለን ሁኔታ የለም። ምክንያቱም፤ ገዢው ቡድን ጥቂት ግለሰቦችን ስለፈታ ይኼን እንደ መልካም እርምጃ የምናስተጋባ አለን። ገዢው ቡድን መልካም እርምጃ አካሂዷል ለማለት የምንችለው ሁሉም የፖለቲካ እስረኞች ሲፈቱ፤ ጭፍጨፋው ሲያቆምና የነጻነት ጮራ ሲታይ ነው። ማባበያውን እንደ መሰረታዊ ለውጥ ካስተጋባን ግን አቋማችን የሚያጠናክረው የገዢውን ፓርቲ እጅ ነው። የህወሓት አጋፋሪዎች የሚሰብኩት ሁሉም ነገር “አማን” እያሉ ነው። ህጻናትን እየጨፈጨፉና እያፈኑ አማን! እየሰረቁ አማን” የማታለያ መሳሪያ ነው።

ገዢው ቡድን አሁንም በመርሆዎች ይነግዳል። “ዲሞክራሲ” እየተስፋፋ ነው! እድገቱ በአዲስ “የተሃድሶ መርህ” ይቀጥላል ወዘተ፤ ወዘተ የሚለው ማሳሳቻ እንጅ ሃቁን በግልጽ የሚያቀርብ ትንተና አይደለም። የዲሞክራሲው ምህዳር እየጠበበ እንጅ እየተስፋፋ አልሄደም። አፈናው፤ ጭካኔውና ግድያው እየተባባሰ እንጅ እየተሻሻለ አልሄደም። ቢሻሻል ኖሮ “የወልድያው ጭፍጨፋ” አይካሄድም ነበር። የሰባት፤ የዘጠኝ ዓመት ወጣት የሚገድለው ህወሓት ከፋሽስቶች በምን ይለያል? “ነብር ቆዳውን እንደማይቀይር ሁሉ” ህወሓት ርእዮቱን፤ ዓላማውንና ተልእኮውን አልቀየረም።

All Africa and Ethiopian Herald በየቀኑ የሚያቀርቡት ዘገባ ሰላምና እርጋታ እንዳለ፤ እደገቱ ሳያቋርጥ እንደሚካሄድ፤ የውጭ መዋእለንዋይ እንደቀጠለ፤ የውጭ ምንዛሬ ችግር እንደሌለ አድርገው ነው። እልቂት እንደሚካሄድ አይናገሩም። የእድገቱ ውጤት የዚህን ያክል የሚያኮራና ፍትሃዊ አለመሆኑን አያወሱም።

የህወሓት ርእዮት፤ ተልእኮና መመሪያ የብሄር ጥላቻንና የጥቂት የትግራይ ተወላጆችንና ታማኞችን የፖለቲካና የኢኮኖሚ የበላይነት የሚያስተናግድ የአመራር ስልት ነው። ለሰው ኑሮና ህይወት እርህራሄና ምህረት አያሳይም። እንዲያውም፤ በአገርና በሕዝብ ጥቅም ላይ አቋም በመውሰድ፤ ማንኛውንም ወቅትና እድል ተጠቅመው ሰላማዊ ድምጽ የሚያሰሙትን ግለሰቦች ሁሉ እየለየ በአልሞ ተኳሾች መግደሉን የማያቆም ቡድን መሆኑ በተደጋጋሚ ታይቷል። ወገንን ከወገን እየለየ፤ ሌሎችን እየተጠቀመና መሳሪያ እያደረገ አፈናውንና ማሳደዱን ቀጥሏል። የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን “የኢትዮጵያ ሁኔታ በጣም ያሳስበናል” ያለበት ዋና ምክንያት ጭካኔው ተቀባይነት እንደሌለውና በዓለም ሕግ እንደሚያስከስስ ስላመነበት ነው። ይህም የጋራ ጥረትን ይጠይቃል፤ መጮህ ብቻ በቂ አይደለም።

በዚህ በያዝነው የኢትዮጵያ አዲስ ዓመት በኦሮሞው ሕዝብ ላይ የተካሄደው ጭካኔ ዛሬ ደሞ በአማራው ሕዝብ ላይ ተካሂዷል። ሁለቱ የሕዝብ አካሎች ዋና ኢላማ መሆናቸው የሚቆም አይመስለኝም። የሚያዋጣው፤ ኦሮሞው፤ አማራውና ሌላው፤ ኢትዮጵያዊነቱን ተቀብሎና በአንድነት ሆኖ ጨካኙን አገዛዝ ማስወገድ ብቻ ነው። ህወሓት ራሱን በሰላም ይለውጣል ብሎ ማስተናገድ፤ ራስን ማታለልና ወጣቱን ትውልድ ለባሰ ተከታታይ እልቂት ማጋለጥ ነው።

በዚህ ትንተና፤ በመጀመሪያ፤ በወልድያ ንጹሃን ላይ፤ በተለይ በህጻናት ላይ የተደረገውን ጭፍጨፋ እኔም በዜግነቴ አወግዛለሁ፤ ያወገዙትን ሁሉ አደንቃለሁ። መስዋእት ለሆኑት “ሰማእታት” ቤተሰቦች ሁሉ ሃዘኔን እገልጻለሁ። በወልድያ ወጣት ወንድሞቻችን፤ በተለይ በህጻናት ላይ የተካሄደው እልቂት ታሪክ የመዘገበው፤ ምንም ይቅርታ የማይደረግበት እልቂት (Selective and deliberate ethnic genocide) ነው። በዓለም ፍርድ ቤት ክትትል ሊደረግበት የሚገባ ወንጀል ነው እላለሁ። ግድያውን የፈጸሙት ባለሥልጣናትና ገዳዮቹ ለፍርድ እንዲቀርቡ እንረባረብ እላለሁ።

በዓልን ማክበርና ድምጽን ማሰማት መብት ነው

እኔ ስንት ሰው በእልቂት እስኪሞት ድረስ እያዘንን እንደምንቆይ አልገባኝም። ሕዝቡ ብሶቱና ጭካኔው ስላየለበት፤ ሞትን ንቆታል፤ ለመሞት ቆርጧል። መጥረቢያ ይዠ እዋጋለሁ እያለ ነው። የወልድያ ወጣቶች በቃና ዘገሊላ በዓል ሲያከብሩ፤ በህወሓት የበላይነት በሚታዘዘው ኃይል ሲጨፈጨፉ ከጀርባ ሆኖ ያስጨፈጨፋቸው ኃይል እንዳለ ማወቅ ይኖርብናል። ህወሓት የመሬት ነጠቃንና መስፋፋትን ከሚያካሂድባቸው አካባቢዎች መካከል አንዱ ወልድያ ነው። የመሬት ነጠቃና ጭካኔ አብረው የሚሄዱ መሆናቸውን ከዚህ በፊት ስለ ጋምቤላ፤ ስለ ወልቃይትና ስለ ሌሎች የመሬት ነጠቃዎች፤ የህወሓት መስፋፋቶችና የሕዝብ ፍልሰቶች ጉዳቶች በሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ፤ በመረጃ የተደገፉ ትንተናዎችን አቅርቤአለሁ።

በኦሮሞው ሕዝብ ላይም የተካሄደው ጭፍጨፋ በተመሳሳይ የውስጥ ሴራና ትእዛዝ የተካሄደ ነው። ስለሆነም፤ አዛዡና ወንጀለኛው ማነው ብለን የመጠየቅ ግዴታ አለብን። በአማራውም ሆነ በኦሮሞው ክልል “ለሕዝብ ታዛዢዎችና ተገዢዎች ነን” የሚሉ የክልል ባለሥልጣናት ደፍረውና ቆርጠው ነፈሰ ገዳዮች በአስቸኳይ ለፍርድ ይቅረቡ የሚሉበት ወቅት አሁን ነው። ህወሓት በመሬቶቻቸው ላይ ሚና እንዳይኖረው ማድረግ ግድ ይላል። አለያ፤ እነሱም ከህወሓት ሊለዩ አይችሉም።

ልክ እንደ ኦሮሞ ወንድሞቻቸና እህቶቻቸው፤ የወልድያ ወጣቶች ድምጻቸውን፤ ጸሎታቸውን፤ አቤቱታቸውን ከማሰማት ባለፈ መንገድ ማንንም ድንጋይ ወርውረው አልጎዱም፤ የማንንም ንብረት አላወደሙም። የማንንም ብሄር አባል ኢላማ አላደረጉም። ሌላው ቀርቶ፤ በበዓል ቀን ድምጽንና ልዩነትን ማሰማት ወንጀል የሆነባት አገር ኢትዮጵያ መሆኗ በተደጋጋሚ ታይቷል። ነፍሰ ገዳዮችና ወንጀለኞች ለፍርድ ካልቀረቡ በስተቀር ሌላው ነገ ባለተራ መሆኑ አይቀርም።

አገዛዙ ካልተለወጠ ይህን የመሰለው ጭካኔና ግድያ ሊያቆም አይችልም የምልበት መሰረታዊ ምክንያት ጭካኔውና ግድያው የተጀመረው ዛሬ ስላልሆነ ነው። አፈናና ጭፍጨፋ የአገዛዙ ዋና መሳሪያዎች በመሆናቸው ነው። ከምርጫ ዘጠና ሰባት ውጭ፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ አንድም ቀን በሰላም አድሮ፤ በሰላም ድምጹንና መብቱን አስተላልፎና አስከብሮ አያውቅም። መሰረታዊ ለውጥ ወሳኝ ነው የምልበትም ምክንያት ይኼው ነው።

ወልዲያ ከተማ የመንግሥት ታጣቂዎች ፈፅመውታል ያሉትን የግፍ ግድያ የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) እና ሰማያዊ ፓርቲ፤ የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብት ኮሚሽንና ሌሎች ማውገዛቸው አግባብ አለው። ህወሓቶች ማውገዝን እንደተራና እንደ ተለመደ ነገር ያዩታል። ስለዚህ፤ ወሳኙ አቋምና ሂደት፤ ግድያውን የፈጸሙት ግለሰቦች ለፍርድ እንዲቀርቡ ያልተቆጠበ ትግልና ድምጽ ከማሰማቱና አገዛዙን ከመለወጡ ላይ ነው። ሕዝቡ እምቢተኛነቱን እንዲቀጥል ከማስተጋባቱ ላይ ነው። ስርነቀል ለውጥ እንዲካሄድ ከመደጋገፉ ላይ ነው።

ህወሓት ግድያውን የፈጸመው “ዘርፈ ብዙ ማሻሻዮችን አደርጋለሁ” ብሎ የኢትዮጵያንና የዓለምን ሕዝብ ለማሳመን መግለጫ ባወጣ በማግሥቱ ነው። ከዚህ በፊት ገዢው ቡድን የሚያወጣቸውን ማዘናጊያዎች ለይተን እንድናያቸው፤ እንዳንታለል የሚል ትንተና አቅርቤ ነበር። ማዘናጊያዎችን በተከታታይ ማውጣት የገዢዎቹ የተለመደ ራስን የማቆየት ስልት ሆኗል። ታዲያ፤ ይህ “እየማለ” የሚገድል ገዢ ቡድን እንዴት ሊታመን ይችላል? ገዢው ቡድን ሊታመን የሚችልበት መስፈርት ፈልጌ ላገኝ አልቻልኩም። እንዲያውም የአፈናውና የጭካኔው ሁኔታ እየተባባሰ ቢሄድ አያስገርምም።

በቅርቡ ከህወሓት እጅ አምልጦ ለጥቂት ግለሰቦች የተላከ የምስጢር ሰነድ የማህበረሰባዊ ሜድያን እንዴት ለመቆጣጠር እንደሚቻል ጥናትና ምክር ያቀርባል። የፖለቲካ ንግድና የበላይነት የሚካሄድባቸውን ቁልፍ ዘርፎች የሚጠቁመው ሰነድ የገመገማቸውን አራት አስኳል ስልቶች በአጭሩ ላቅርባቸው።

  1. እድገት መጠን ላይ የሚደረገው ንግድ

ህወሓት እድገትንና ልማትን በራሱ ቋንቋ ገልብጦ የተለየ ትርጉም እንደሰጣቸው ጥናቶችና ትንተናዎች ያሳያሉ። ለምሳሌ፤ በቅርቡ Axios የተባለው የአሜሪካ ተቋም “The world’s fastest growing economy, is one of its poorest nations” በሚል ርእስ እንዲህ ብሏል። “The world’s fastest growing economy is not India (6.7% in 2017) or China (6.8%), but Ethiopia, according to a World Bank estimate that puts the East African country’s 2017 growth at 8.5% and projects 8.2% growth in 2018, ranking second only to Ghana (8.3%).”

ሰላምና እርጋታ በሌለባት ኢትዮጵያ “ፈጣን እድገት” ተከታታይ ሆኗል ሲባል ለህሊና ይቀፋል። እኔ ዓለም ባንክ የሚለውን የተሳሳተ የእድገት እርከን እንደማልጋራ በጥናቶቸ አሳይቻለሁ። ምክንያቱም፤ ዓለም ባንክ የገዢውን ፓርቲ ሰነዶችና መረጃዎች ተጠቅሞ የሚናገረውና የሚያስተጋባው እርከን፤ በመሬት ላይ ከሚታየው የእድገት ውጤት ጋር ግንኙነት የለውም። የኑሮውን ሁኔታ የሚያውቀው ተራው ኢትዮጱያዊ ስለሆነ፤ ከተራው ኢትዮጵያዊ ግብዓት የሚጠይቅ አካል የለም። ዓለም ባንክ የሚሰራውና የሚነጋገረው ከባለሥልጣናት ጋር እንጅ ከተራው ሕዝብ ጋር አይደለም፤ ሆኖም አያውቅም። አክሲዎስ የሚለውና እኔ የምከራከርባቸው ጉዳዮች ተመሳሳይነት አላቸው።

ታላቁን ስእል እንየው ይላል ድርጅቱ። “ With 102 million people, Ethiopia is the 2nd most populous country in Africa and the 12th most populous on earth. It’s also one of the world’s poorest countries —sitting just above Haiti and below Afghanistan in terms of GDP per capita — and its rapid growth has brought millions out of extreme poverty. But ethnic violence, a government crackdown and high unemployment are putting “one of Africa’s brightest success stories” at risk, per Eurasia Group’s Signal newsletter.” በመሬት ላይ የሚታየው ሃቅ የስራ እድል እንደሌለ፤ የኑሮ ውድነት፤ ጉቦ፤ ሙስና፤ የአስተዳደር ብልግናና ጭካኔ እንደቀጠለ። በልቶ ማደር ብርቅ እንደሆነ፤ ስደት እንደቀጠለ፤ አፈናው፤ ጭካኔውና ግድያው የተለመደ እንደሆነ፤ የዲሞክራሲ ጭላንጭል እንደሌለ ወዘተ ያሳያል።

እድገትና የእድገት ውጤት ከሰብአዊ መብት መከበር፤ ከነጻነት፤ ከፍትህ፤ ከሕዝብ ተሳትፎና ከዲሞክራሲ ጋር ቀጥተኛ የሆነ ግንኙነት አላቸው። ዓለም ባንክ ተሳስቷል የምልበትን ምክንያት The Economist, January 25, 2018 የባንኩን ከፍተኛ ኢኮኖሚስት ፓል ሮመርን በሚመለከት ያቀረበው ዘገባ ፍንጭ ይሰጠዋል። ልክ እንደማንኛውም በምእራብ መንግሥታት የበላይነት የሚመራ ድርጅት፤ ዓለም ባንክ ከፖለቲካ ዝንባሌ ውጭ አይሰራም ለማለት መረጃ የለንም። ለምሳሌ፤ ዓለም ባንክ የእያንዳንዱን አገር የፖለቲካ ኢኮኖሚ አመራር ሁኔታዎች የሚያይበት መነጽር ከራሱና ከሚደጉሙት አገሮች የኢንቬስትመንትና የንግድ ጥቅሞች አንጻር መሆኑን ለማጤን ባንኩ ለደርግ መንግሥት ግዙፍ ብድር አይሰጥም ነበር፤ ለሰሜን ኮሪያና ለኩባ አያበድርም። የፖለቲካና የርእዮት ውሳኔ እንጅ ድህነትን ለማጥፋትና የአገርን የምርቶች ኃይል ለማዳበር የተደረገ ውሳኔ አይደለም።

በዓለም የታወቀው የዓለም ባንክ ዋና ኢኮኖሚስት ፖል ሮመር፤ የባንኩን ጥናትና ምርምር ክፍሎች በመተቸት፤ ድፍረት ያለው ወቀሳ ሰንዝሯል። “In an e-mail to several bank economists, sent last October and reported today in the Financial Times, Mr Romer was scathing about the bank’s “diagnostic” reports on individual countries and its broader intellectual culture.” ቀጥተኛ ትችቱ እንዲህ የሚል ነው። “I’ve never in my professional life encountered professional economists who say so many things that are easy to check and turn out not to be true…Imagine a field of science in which people publish research papers with data that are obviously fabricated. When someone points this out, the Internal Justice Bureau steps in [and] says that the concerns do not meet the burden of proof required for them to take action. Nothing happens.” እኔ የምለውን ወደ ጎን ትታችሁ እሱ የተቸውን ትኩረት ስጡት!!

ይህ አባባል ህወሓት ከሚፈበርከው የእድገትና የልማት እርከኖች ጋር ይዛመዳል። ስለሚዛመድ፤ ዓለም ባንክ ስለ ኢትዮጵያ አስደናቂ እድገት የሚሰጠን መረጃ የፈጠራ መረጃ ይሆናል ማለት ነው። ስለሆነም፤ ሃቀኝነት ያለው የእድገት መረጃ ለማግኘት አይቻልም። ፓል ሮመር የዓለም ባንክ ኢኮኖሚስቶች የሚያቀርቡት ዘገባና መረጃ የትንተና ሃቀኝነት  “intellectual integrity” የለውም ማለት ነው።

ይህን ስል ትክክለኛ መረጃ ማግኘት ቀላል ነው ማለቴ አይደለም፤ አስቸጋሪ ነው። ኢኮኖሚስት እንደሚለው “The researcher’s findings may need to be replicable by another scientist. And they may need to show that their method was not reverse-engineered to produce a desired result. Research does not benefit from any presumption of methodological innocence. It has to prove its intellectual honesty and credibility.” የመረጃ ስህተት ወይንም ፖለቲካዊ የሆነ አድልዎ አለ ከተባለ ማን ያጣራዋል የሚል ጥያቄ ማቅረብ ይኖርብናል ማለት ነው። “When a researcher is accused of political bias or malpractice, the burden of proof falls not on the researcher but on the accuser. Reputations and livelihoods are at stake. There is a big difference between rejecting a proposition and repudiating a person…..Mr Romer clearly seems to believe that some of the bank’s economics is sloppy and intellectually dishonest. It cannot, in his view, meet anything like the heavy probative burden required of credible research.”

የኢትዮጵያን እድገት በሚመለከት ስመለከተው፤ የዓለም ባንክ የተዛባ መረጃ ጉዳቱ ለተጠቃሚው ድሃ የኢትዮጵያ ሕዝብ ጠበቃ አለመኖሩ ነው። አገር ቤት የሚኖሩ ምሁራንና ሳይንቲሶቶች በነጻነት ለመንቀሳቀስ፤ ጥናትና ምርምር ለማካሄድ አይችሉም። ማህበረሰባዊ ድርጅቶች እንዲፈርሱ ተደርጓል። ድንቁርና የሚረዳው ገዢውን ቡድን ነው።

የእድገቱ ውጤት ተማርኳል፤ ማራኪው የህወሓት ኃይል ስልጣኑን ለመቀጠል ቆርጦ ተነስቷል። ስልጣኑን ለማራዘም ተቃዋሚ ነው ብሎ የሚጠረጥረውን ሁሉ ማሳደድ፤ ማንበርከክ፤ ማፈን፤ ማሰር፤ መግደል፤ እንዲሰወር ማድረግ ስልቱ ሆኗል። የተቃዋሚው ክፍል መከፋፈል፤ በጥቃቅን ጉዳዮች ላይ ጊዜንና ኃብትን ማቃጠልና ማባከን ለአፋኙ አገዛዝ ግብዓት ሆኗል።

  1. በዲሞክራሲ ላይ የሚደረገው ንግድ

ህወሓት ጸረ-ዲሞክራሲ ነኝ ሊል አይችልም፤ የሚለው “የዲሞክራሲ ተቋም” ነኝ ነው። የራሳችን መስፈርቶች ብንጠቀም፤ እውነተኛ ዲሞክራሲ ማለት፤ የሕዝብ፤ በሕዝብና ለሕዝብ ተገዢ የሆነ የመንግሥት አገዛዝ ነው። ዲሞክራሲ አለ ከተባለ ሁለ ዘርፍ ችግሮች እየተፈቱ ሕዝቡ ፍላጎቱን የሚያሟላበት ሁኔታ ተፈጥሯል ማለት ነው። የስራ መስኮች እየተስፋፉና ምርት እየጨመረ፤ የነፍስ ወከፍ ገቢ እያደገ ይሄዳል ማለት ነው። እውነተኛ ዲሞክራሲ ለፍትሃዊና ለዘላቂ እድገት ወሳኝ ነው። ጭካኔና አፈና ግን የዲሞክራሲና የእድገት ጸር ወይንም ማነቆ ነው። ኢትዮጵያ ከሄይቲና ከአፍጋኒስታን ጋር እንጅ ከቦትስዋና ወይንም ከጋና ወይንም ከቬትናም ጋር ለመነጻጸር ያልቻለችበት መሰረታዊ ምክንያት አገዛዙና ፖሊሲው አፋኝ ስለሆኑ ነው። አፋኝ አገዛዝ የታፈነ ኢኮኖሚ ይፈጥራል፤ የገቢና የኑሮ ልዩነቶችን ያባብሳል ማለት ነው። ተደማምረው እርጋታን፤ ሰላምን፤ አብሮ መኖርን ይበክላሉ።

ሰነዱ እንዲህ ይላል። “የዲሞክራሲ አንዱ መገለጫ የሆነው ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ እና የማስተላለፍ ጉዳይ ሰዎች ሀሳባቸውን እንዲገልጹ ተብሎ የሚተገበር ብቻ ሳይሆን ራሱ የልማት መሳሪያ ነው፡፡” ይህን ማለት ቀላል ነው። በገቢር ምን ይታያል የሚለው ነው ወሳኙ። “ይህን በተመለከተ የዲሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ትግል እና አብዮታዊ ዲሞክራሲ የሚለው የድርጅታችን ሰነድ እንዲህ ይላል፡-

የሕዝቡን ሁኔታ፤ ስሜቱንና ፍላጎቱን አስተሳሰቡን በእርግጠኛነት አውቆ ትክክለኛ ስልት ለመንደፍ በግብአትነት ለመጠቀም የሚቻለው በስልቱ አፈጻጸም ሂደት የመጡ የአስተሳሰብ ለውጦችን በትክክለኛነት ተገንዝቦ ተፈላጊውን ማስተካከያ ማድረግ የሚቻለው ህዝቡ በማንኛውም ጊዜ ሀሳቡን ሳይሸማቀቅ፤በግልጽና በተሟላ ሁኔታ ማቅረብ ሲችል ነው፡፡ህዝቡ በማንኛውም ግዜ ሀሳቡን ሳይሸማቀቅ በግልጽና በተሟላ ሁኔታ መገልጽ የሚችለው ደግሞ ዲሞክራሲ ሲኖር ነው።” “ሕገመንግሥቱና አመራሩ” እንደዚህ ይላሉ የሚለው ብሂል በድርጊት ሲተረጎም ተጻራሪውን ያሳያል። ህጻናትን እየገደሉ “የመናገር ነጻነት” አለ ማለት ፍጹም ውሸት ነው። ይህን ነው የፖለቲካ ንግድ ጨዋታ የምለው።

“በማንኛውም ጊዜ ሃሳቡን ሳይሸማቀቅ ማቅረብ ይችላል” ከተባለ በሰላም ሃሳባቸውን የሚገልጹት የኦሮሞና የአማራ ወገኖቻችን ለምን ተገደሉ፤ ለምን ታሰሩ፤ ለምን እንዲሰወሩ ተደረጉ? ህወሓት/ኢህአዴግ የሚናገረው፤ የሚደሰኩረውና ለዓለም የሚያቀርበው የመብቶች መከበር ከሚሰራው ጋር ምንም ግንኙነት የላቸውም። ቢኖራቸው፤ ሕዝብ አይጨፈጨፍም ነበር፤ ሁሉም የፖለቲካ እስረኞች ይፈቱ ነበር። በህወሓቷ ኢትዮጵዩያ “ሃሳብን ሳይሸማቀቁ” መግለጽ ወንጀል ሆኗል።

በአጭሩ፤ ሕዝብ በነጻነት ድምጹን ሲያሰማ በተከታታይ የተከሰተው ውጤት ጭካኔና ግድያ ነው። ሰነዱን ቀረብ ብየ ስመለከተው ችግሩ አይኑን አፍጥጦ ይታያል። “ህወሓት/ኢህአዴግ ዲሞክራሲ ለልማት ያለው ፋይዳ ከፍተኛ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ ዲሞክራሲን በመጠቀም ጉዳት ለማድረስ የሚፈልጉ አካላትን በተመለከተ ያለው አማራጭ አንድም ጉዳት ማድረስ የሚፈልጉ አካላት ሀሳባቸውን እንዳይገልጹ ማድረግ አልያም ሀሳባቸውን እንዲገልጹና ሀሳባቸው አንዲሸነፍ ማድረግ ነው” ይላል። ሃሳቦች ከሃሳቦች ጋር ተወዳድረው ሕዝብ የራሱን ውሳኔ ያድርግ የሚል አማራጭ አልቀረበም። የቀረቡት የህወሓት አማራጮች እንዲህ የሚሉት ናቸው።

  1. “የሶሻል ሚዲያ አርበኞችን ማንነት ማጋለጥ

“በሶሻል ሚዲያ በመጠቀም የህዝቡን ሰላማዊ ኑሮ፤ የስርዓቱን ህልውና ለመፈታተን የሚሞክሩ ግለሰቦች አብዛኞቹ በውጪ ሀገራት በመሆን የሚሰሩ ሲሆን በሀገር ውስጥ የነሱን ተልዕኮ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ የሚተገብሩም አሉ፡፡ የሶሻል ሚዲያ አርበኞች የሚያስተላልፉቸው እያንዳንዱን መልዕክቶች ካላቸው ፓለቲካዊ፤ ኢኮኖሚያዊ፤ ማህበራዊ እና ህገ-መንግስታዊ ስርዓት ላይ ከሚያስከትለው እንድምታ አንጻር በመተንተን አጸፋዊ ምላሽ ሊሰጥ ይገባል፡፡” ሕዝቡን ያፈነውና የሚያሰቃየው ቡድን ውጭ ያለውንም ለህዝብ መብቶች የሚታገለውን ተቆርቋሪ ኢትዮጵያዊ ለማፈን ዘመቻ እያካሄደ መሆኑ ነው።

ይህን ብዙ የታሰበበትን እርምጃ ለመውሰድ በሚል ስሌት፤ ህወሓት በመመሪያው ላይ እንዲህ የሚል ድምዳሜ አቅርቧል። “የሚሰጠው ምላሽ ስሜታዊነት የሚንጸባርቀበት ወይም የድርጅቱን መስመር የማይስት እንዲሆን በማዕከል ደረጃ ይህን ስራ የሚያከናውን አሰራር መዘርጋት ይኖርበታል፡፡

  • በጥቅሉ ሲታይ በሶሻል ሚዲያ በመጠቀም ችግሮች ለመፍጠር የሚታትሩ ሃይሎች በሁለት ተከፍለው ሊታዩ የሚችሉ ሲሆን አንደኛው የጠባቡ ሃይልሲሆን ሁለተኛው ደግሞ የትምክህት ሃይል ነው፡፡ እነዚህን ሃይሎች በዘርፋቸው በማስቀመጥ በእያንዳንዱ ሃይል ስር የተሰለፉትን ግለሰቦች እንዳላቸው የተከታይ ብዛት፤ የመልዕክታቸው አፍራሽነት ደረጃ በመለየት እጅግ አጥፊ ከሆኑት በመነሳት እስከ ዘገምተኛው ሃይል ያለውን መለየት ይገባል፡፡ ይህንንም መነሻ በማድረግ ግለሰቦች የሚያሰራጩዋቸውን መልዕክቶች ከስር ከስር በመከታተል የማጋለጥ ስራ ሊከናወን ይገባል፡፡
  • በተጨማሪነት ግለሰቦች በግለሰብ ደረጃ የሚያሰዩዋቸው ባህሪያቶች የራሳቸው ቤተሰባዊ፤ ማህበረሰባዊ መነሻ ሊኖራቸው የሚችል በመሆኑ እነዚህን ጉዳዮች በጥልቀት በማጥናት ግለሰቦች ፍሪዚ ሊያደርጉ የሚችሉበትን ስራዎች ማከናወን ተገቢ ይሆናል፡፡”

በአገር ቤት ተቃዋሚ የሆኑ ግለሰቦችንና ስብስቦችን ማፈን፤ ማሳደድ፤ መግደልና ማሰር እንዲጠናከሩ እያደረገ፤ በውጭ ያለውን ተቃዋሚ “ጠባብና ትምክህተኛ” ኃሎች ናቸው ብሎ በመሰየም፤ “በአጥፊዎቹ ላይ” የተለየ ትኩረትና ክትትል እንዲደረግ ወስኗል። “ጠባብና ትምክህተኛ” ተብለው የተበየነባቸውን ክፍሎች ለመለየት አስቸጋሪ አይደለም። ቁም ነገሩ ግን፤ እነዚህ የውጭ ተቃዋሚ ኃይሎች የሚጠቀሙባቸው የሜድያ መሳሪያዎች ፌስቡክ፤ ትዊተር፤ ሊንድኪንና ተመሳሳዮቹ ከፍተኛ ክትትል እየተደረገባቸው መሆኑ ነው። ለዚህ አዲስ የተቀነባበረ ዘመቻ የሚያዋጣው፤ ከብሄር፤ ከግል ጥቅም፤ ከጉራ፤ ከቡድንና ከሌላ መለያ ባሻገር እየተረባረቡ፤ በአንድነትና በኢትዮጵያዊነት ዙሪያ እየተሰበሰቡና እየተደጋገፉ ገዢውን ፓርቲና በዲያስፖራው ዓለም ውስጥ በሰላይነትና በአጥፊነት የተሰማሩትን ተባባሪዎች ማጋለጥና በሕግ እንዲጠየቁ ማድረግ ይሆናል። የህወሕትን የጭካኔ ግድያዎች በአንድ ላይ ወደ ፍርድ ቤት የምናቀርብበት ወቅት አሁን ነው።

  1. “በሕገመንግሥቱ” የሚደረገው ንግድ

የማንኛውም መንግሥት የመጀመሪያ ስራው የዜጎችን ምኞት፤ ተስፋና ፍላጎት ለማሟላት መሞከር ነው። ምን አይነት መንግሥት ያስፈልጋል የሚለው ጥያቄ መመለስ ያለበት በጥናትና በሕዝብ ተሳትፎ እንጅ በጥቂቶች ስሌት ሊሆን አይችልም።  የህወሓት የውስጥ ጥናትና ድምዳሜ እንዲህ ይላል።

  • “የሀገራችን ህገ መንግስት በአንድ በኩል ሀገራችን የነበረችበትን መሰረታዊ ችግር የማንነት እውቅና ያለማግኘት መሆኑን በጽኑ በማመን፤ በሌላ በኩል ይህን ችግር ለመፍታት የማንነት መገለጫዎች ህገ-መንግስታዊ ዕወቅና እንዲያገኙ ያደረገ በሌሎች ሀገራት የማይገኙ ተራማጅ የሆኑ ድንጋጌዎችን የያዘ ህገ-መንግስት ነው፡፡ህገ-መንግስት የግለሰቦችና የቡድን መብቶችና በእኩልነት እና ሳይነጣጥል መተግበር አለባቸው የሚል እና ይህንንም ለመተግበር የሚያስችሉ ዲሞክራሲያው የመንግስት አወቃቀር የያዘ ነው፡፡
  • ሕገ መንግስቱ ይህን ያህል ጠቀሜታ ያለው ሰነድ ቢሆንም ይህን ሰነድ በእያንዳንዱ የማህበረሰብ ክፍል ማስረጽ ላይ የተሰራው ስራ ከህገመንግስቱ ዋጋ አንጻር ሲታይ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም፡፡አሁንም ቢሆን በህገ-መንግስቱ ላይ የተቀመጡት ድንጋጌዎች፤ ከድንጋጌዎች ጀርባ ያሉ የህዝብ ትግል የፈጠራቸው አስተሳሰቦች ይዘት እና ጥልቀት ላይ በቂ የሆነ ግንዛቤ ሊሰጥ የሚችል ሃይል መፍጠር አልተቻለም፤ ግንዛቤው ያለውም ሃይል ይህን እንዲያስተላልፍ በቂ መድረክ አልተዘጋጀለትም፡፡
  • እንዲያውም ባንዳንድ ቦታዎች ሕገ-መንግስት አከራካሪ ሰነድ መሆኑን ማሳየት እና ከዛ ውስጥ ህገ-መንግስቱን ያለመቀበል አዝማሚያን የሚያመለክት ሀሳብ እንዲንሸራሸር የሚደረግበት ሁኔታ ይታያል፡፡”

ችግሩ የአፈጻጸም ብቻ አይደለም። በብሄር/ቋንቋ የማይታረቁ ልዩነቶች ላይ የተመሰረተ “ክልላዊ ስርዓት” ስለሆነ ሊፈቱ የማይችሉ ሁኔታዎችን አስከትሏል። ሰው ሰራሽ ችግር የአስተሳሰብ ለውጥን ይጠይቃል።

ችግሩ ፌደራል መሆኑ አይደለም፤ የማንነት ጥያቄም አይደለም። ችግሩ ኢትዮጵያና የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚስፈልጋቸው ምን አይነት መንግሥትና የፌደራል ስርዓት ይሆን? የሚለው በአግባቡ ያልተወሰነ፤ ሕዝቡ ያልተወያየበትና በባለቤትነት ያልተጋራው መሆኑ ነው። የህወሓት/ኢህአዴግ አገዛዝ ከላይ የተጫነ እንጅ በሕዝብ ፈቃደኛነት የተመሰረተ አይደለም።

ስለዚህ፤ ችግሩን የፈጠረው ገዢው ፓርቲ ችግር መኖሩን ቢያምንና ቢቀበልም፤ መፍትሄውን የማቅረብ ብቃት፤ ጥራትና ችሎታ የለውም። ውሳኔ መስጠት ያለበት የኢትዮጵያ ሕዝብ እንጅ ጥቂት የጠባብ ብሄርተኞች ምሁራንና ልሂቃን ሊሆኑ አይችሉም። “በሌሎች አገሮች ያልተደረጉ ተራማጅ ድንጋጌዎች” የሚለው ብሂል ሌላ ማዘናጊያ ነው እንጅ የአሁኑ የጎሳ ፌደራል አገዛዝ ለአኟኩ፤ ለኦሞ ሽለቆውና ለሌላው ጭቁን ሕዝብ ምን ጥቅም አምጥቶለታል? በሕዝብ ስም የፖለቲካ ንግድ እየተካሄደ ነው የምለው ለዚህ ነው። ሌሎች የአፍሪካ መንግሥታት የናቁትን ህወሓት ለስልጣኑና ለጥቅሙ ሲል ያመልክበታል!

“የክልል” ነጻነትና የራስን ክልል የማስተዳደር መብት አለ የሚባለው ከእውነቱ የራቀ ነው። ለምሳሌ፤ የአማራውን ክልል በበላይነት የሚመራው የአማራው ህወሓት የመረጣቸውና እንዲወክሉት ስልጣን የሰጣቸው እንጅ የራሱ ተቆርቋሪዎች አይደሉም። የሚያዙትና የሚያስተዳድሩት ህወሓትና ህወሓት የፈለፈላቸው የአማራ ብሄር አባላት ናቸው። ይህ ባይሆን ኖሮ፤ የአማራው ፖሊስ ወይንም ሚሊሽያ የራሱን ወገኖች፤ በወልዲያም ሆነ በወልቃይት፤ በባህር ዳር ሆነ በጎንደር አይጨፈጭፍም ነበር። የፈረሰውና መተካት ያለበት የኢትዮጵያ የመከላከያ ኃይል የሚያኮራ ታሪክ አለው። ሕጻናትና ሴቶችን አይገድል፤ አይጨፈጭፍም።

የአሁኑ “የመከላካያ ኃይል” የበላይ አዛዡና አስተዳዳሪው ህወሓትና የፈጠራችው ግለሰቦች መሆኑ አያከራክርም። ይህ ኃይል የህወሓት መሳሪያ ነው። በዚህ ምክንያት ነው፤ የአማራው ሕዝብ በአዴንን እስከሚሰለቸው ድረስ የተቸውና አንተ ልትወክለን አትችልም ያለው።

ለማጠቃለል፤ ታሪክ ያላትን ኢትዮጵያን ለመታደግ የምንችለው በአገራችን ዘላቂ ጥቅም ላይ የማያወላዳ አቋም ወስደን፤ ኢትዮጵያዊነት የዜግነት መለያችን ነው የሚል መርሆን ተቀብለን፤ በአንድነት፤ ለአንድ አገር ግዛታዊ አንድነትና ሉዐላዊነት፤ ለአንድና ለተሳሰረ ሕዝብ ደህንነት፤ መብትና የኑሮ መሻሻል ተደጋግፈን ለመስራት ስንወስን ነው።

የኢትዮጵያ ሕዝብ የፖለቲካ ሥልጣኑ ባለቤት ከሆነ ህይወቱንና ኑሮውን ለማሻሻል የሚችልበት የተፈጥሮ ኃብቱ ግዙፍ ነው። መስረታዊ ፍላጎቱን– በቂ ምግብ፤ ትምህርት፤ የጤና አገልግሎት፤ ዘመናዊ መጸዳጃ፤ ንጹህ ውሃ፤ መጠለያ ወዘተ– ለማሟላት የሚችል ሕዝብ ነው። አንድ አገር፤ አንድ ሕዝብ ስል ብርቃማ የሆኑትን የልዩ ልዩ ብሄረሰቦች እሴቶች ወደ ጎን እንተው ማለቴ አይደለም። እነዚህ እሴቶች ለኢትዮጵያዊያን ሁሉ የጋራ ጥሪቶች ናቸው፤ ከኢትዮጵያዊነት ጋር አይጋጩም።

ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!!

January 30, 2018

የራስን ዕድል በፍቅር መወሰን (ተስፋዬ ዋቅቶላ)

ባህር ዳር ወደ ፍቅር

በቅርቡ ቴዲ አፍሮ ባህር ዳር ላይ ፈተና ገጥሞት ነበር፡፡” ጃ ያስተሰርልን” ዝፈን ተብሎ፡፡ በ17መርፌ እንዲል፡፡ ለውጥ መቼ መጣ እነዲል፡፡ ንግስና በዘረ ነው ስለዚህ አዲስ ንጉስ እንጂ… ሊልላቸው ፈልገው ነበር፡፡ ቴዲሾ ግን አንዲት መልስ ብቻ ነበረችው፡፡ ሁሉንም በፍቅር እናሸንፋለን ፡፡ የምትል፡፡ አንዳንድ አክቲቪስቶች ግን ተቃውመውታል፡፡ “ከመቼ ወዲህ ነው ሴጣን በፍቅር የተሸነፈው “ ብለው፡፡ ነው እንዴ…. ነገርየዋ ካልተካረርን አንፋታም አይነት ነው፡፡ ቴዲ ጥበቡን ይጨምርልህ!

ቤተሰብ ወደ ፍቅር

ለመፋታት ቅድሚያ መጋባት ያስፈልጋል፡፡ ለመጋባት ደግሞ ቀድሞውኑ ሁለት የተለያየን አካላት መሆናችንን ማክበር አለብን፡፡ ከዚያ “እሱ አንድ ያደረገውን …. “ ብለን ብንፎክር ያስኬዳል፡፡ አንድ መንግስት የራስን ዕድል በራስ ለመወሰን መጀመሪያ የግለሰብ መብትን ያለገደብ ያክብር፡፡ ዲሞክራሲን ያለ ገደብ ከሕዝቡ ለሕዝቡ በህዝቡ ያክብር፡፡ ከዚያ ማንም በሌላው አይፈርድም፡፡ መብቱ ተከብሮለታልና፡፡ ለይስሙላና በማጭበርበር ሳይሆን ማንም የማንንም መላጣ እማይነካ ጨዋ ስልጡንና ሥርዓትና ባህል ያለው ሕዝብ እንዳለን አንዘንጋ፡፡ ይህ ህዝብ ለዕድገታችን ቅራኔዎች ያሉትን የቡድን መብት ከግለሰብ መብት እኩል ማክበርንም ያውቅበታል፡፡ ብቻ ቅድሚያ የግለሰብ መብት ይከበርልንማ፡፡ “ከሩቅ ዘመድ የቅረብ ጎረቤት” እንጂ “ዘር ከልጓም ይስባል” የሚለው አይቀድመውምና፡፡ “ሀ ራስህን አድን” ብሏል ያራዳ ልጅ፡፡ ፍሬንዶች በግል እየወጣችሁ ከፒፕሉ ጋር “ተዛረቡ”፡፡ ከዚያ አዳሜ ነቄ ነው፤ ነጥሎ ከምቹን አስሊዋ ላይ ማሳረፍ ይችልበታል፡፡ ይህ ነው እንግዲህ በቅድሚያ የራስን እድል በራስ መወሰን ሲባል፡፡ ቡድኑ ያከብርልኛል ብለህ ግነ እንዳትጠገረር ጀለስ፡፡

ሕዝብ ወደ ፍቅር

ማንም ሕዝብ “በራሱ ጉዳይ ራሱ ወሰነ” ማለት ቀላል ነገር አይደለም፡፡ ትልቅ የመብት ማስከበር ስርዓት ተከናወነ ማለት ነው፡፡ ይህ መብት ግን የቡድንን መብት ሊያስገኝ እንዳይችል ልናውቅ ግድ ይለናል፡፡ ክሪሚያ ውስጥ በድምፅ ተበልጠው ከዩክሬይን የተለዩ እንዳሉና ድምፃቸውን አጥፍተው እንደሚኖሩ አንርሳ፡፡ ያቺ “የግለሰብ መብት” በድንገተኛው የዩክሬንና ሩሲያ ግጭት እንደቁማር ተበላች፡፡ ግና ቀድማ በዩክሬን ሳለች ተከብራለት ቢሆን ኖሮ ቀድሞውኑ ራሱ፤“የራሱን እድል የመወሰን መብት” ያለው አካል አባል በሆነ ነበር፡፡ በፍቅሩ ጊዜ፡፡

የሪፈረንደም ሪፌሪዎች(ዳኞች)

ብዙ ጊዜ የራስን ዕድል በራስ መወሰን ወይም (ሪፈረንደም) የሚካሄደው ችግሮች ከተፈጠሩ በኋላ ነው፡፡ ችግሮቹም ሰው ሰራሽ ናቸው፡፡ ችግሮቹን የሚያባበሱአቸው እነዚያው ያቺን ከመለያየት የምትገኝ ትርፍ ለማፈስ የተዘጋጁ አካላት ናቸው- ሪፌሪዎች፡፡ በኤርትራ ከ30ዓመታት ጦርነት በኋላ ማንም በእንባ እየተራጨ የማይለይ አካል አይኖርም፡፡ “….ሀዘንሽ ቅጥ አጣ” ነዋ ነገሩ፡፡ እንጠቅሳለን ፡ – የሎንዶን አደራዳሪው ኸርማን ኮኸን፡፡ ዛሬም አንቀፅ 39ን ተግብሩ ይላል አሉ፡፡ (ተስፋ ኒውስ)በቅድሚያ መላው ስላንተ መጨነቅ እንዲችል ሰላም ያስፈልጋል ለሀገሩ፡፡ ሰላም የህሊና ሰላም ያስፈልገዋል ለግለሰቡ ህሊና፡፡ አንድነትም እንዲኖር ሰላም ያስፈልጋል፡፡ ለመተካከም ሰላም ያስፈልጋል፡፡ ሰላም እንዳይኖር የሚሻው ያው የታወቀ ነው – ዓላማውና ዒላማው፡፡ ትናንሽ መንግስታትና የአንድነት ሐይሎች ናቸው፡፡ መንግስታቱን አግኝቶም ጭዳ የሚያደርጋቸው በፍቅር ሰለባነት የአንድነት ተጓዦቹን ነው፡፡ለዚህ ሁሉ ሪፌሪ ዳኛ የሚሆኑት ጥቅመኛና ስግብግብ ብሎም የፍቅር ጠላቶች ናቸው የሪፈረንደም አጋፋሪዎቹ፡፡ የዳኛ ተጫዋቾች እንዲል አንድ ገጣሚ ወዳጄ፡፡

የራስን ዕድል በፍቅር መወሰን እንዴትነት

ፍቅር ያለ አንድነት፤ አንድነትም ያለ ፍቅር አይኖሩም፡፡ ሰላም የምንለውም የሁለቱን ስምረት ነው፡፡ በዚህ አንፃር አሻግረን ስንመለከት ለፍቅር የግለሰብ መብት መከበር ግዴታ ይሆናል፡፡ ፍቅር ያለ ነፃነት አይገኝም፡፡ነፃነት ያለው ፍቅር ካለንና ከተዋደድን ሰላምም ሆነ አንድነት አለን፡፡ አንድነታችን በፍቅር ላይ ከተገነባ ደግሞ መለያየት አንፈልግም፤ የራስን ዕድል በራስ መወሰን አያስፈልገንም፡፡ ፍቅር ሁሉንም ወስኖልናልና፡፡ ያንንም የራስን ዕድል በፍቅር መወሰን ብንለውሳ፡፡ እኛው እንታረቅ እኛው እንፋቀር፡፡

ማንም በማንም ላይ አይወስንም (ማንዴቴ)

በፖለቲካ ከምንም ነገር በላይ የሕዝብን ይሁንታ ወይም ማንዴት በሕጋዊ መንገድ መቀበል የሥርዓቶች ሁሉ መጀመሪያ ነው፡፡ ፖለቲከኞች ያለ ሕዝባዊ ማንዴት ሕዝብ ላይ ቂጥ ብለው ሕዝብን ሲያሸማቅቁ ይታያሉ፡፡ ዘመናችን የማንዴት አልባ ፖለቲካ ወደ ሽብር ያደገበት ሆኖ በየእጣጫው ይስተዋላል፡፡ “እስላማዊ መንግስት ነኝ” የሚል አካል የሙስሊሞችን ታሪካዊ ቅርሶች እንዴት ሊያጠፋ ይችላል፡፡ በቺቦክ ልጃገረዶችን ያፈነው ለእነዚያው ልጆች ነፃነት የምታገል አካል ነኝ ቢል ማን መብትህ ነው ብሎ ይቀበለዋል፡፡ ያ ህዝብ ትወክለኛለህ ሳይለው እንዴት በራሱ በህዝቡ ላይ መልሶ ጥቃት ይፈፅማል፡፡ የግለሰብን መብት የማያከብር የነፃነት ትግል ነፃነትን የማያውቅ መሆኑን ማወቅ በራሱ ላይ እንድትነሳ ያደርግሃል፡፡ ለዚህ መሰረቱ “ታግለህ አታግለኝ” የሚል ማንዴትን ከሕዝቡ የሚቀበል ሐይል መኖር አለበት፡፡ ያለማንዴት ሕገመንግስት አይደለም አንድ ረቂቅ ህግ ማውጣት ከንቱ ነው፡፡ ሕዝብን የሚያከብር ማንዴቱን ያከብራል፡፡ በተሰጠው ህዝባዊ ማንዴት ሥራውን ይሰራል እንጂ ከማንዴቱ በፊት አዋጅ አያወጣም፡፡

መሪ ግብዝ አይደለም አፍቃሪ ንጂ

“ተናገር በከንፈሬ ተቀመጥ በወንበሬ” ሳይባል መባተት እንደ ሰርቫንቲስ ዶን ኪሆቴ ግብዝነትን ያላብሣል፡፡ ብኩን ያደርጋል፡፡ ስትወዳት ስትወድህ ነው እንጂ አንተ ብቻ መውደድህ ከንቱ ነው፡፡ የራሷን አድል በራሷ ወስና የምታገባህ ሚስት እንጂ እንደጥንቱ ጋብቻ ቤተሰብ የመረጠላትን የምታገባ ሴት ምን ትረባሃለች፡፡ ላትወድህ ላታፈቅርህ ትችላለችና፡፡የልምዣትን ያነቧል፡፡ ሕፃናትም ከማን ጋር ማደግ እንዳለባቸው የሚወስኑበት እድሜ አለ፡፡ ለዚህ ሁሉ ፍቅር ወሳኝ ነው፡፡ አግቢዋም ህፃኑም ፍቅር ወዳላቸው መሰብሰባቸው ተፈጥሮአዊ ነው፡፡ ፍቅር ካለ ሰላም አለ፤ ሰላም ካለ በልዩነት ውስጥ አንድነት አለ፡፡

መደምደሚያ

አይዞን ወገኔ ፤ፍቅር ነው መድኔ
ተባባል ወገኔ፤ ተባበር ወገኔ፡፡

በ”የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት” ስበብ ፤ ሕዝብ ቢለያይ አንድ ተስፋ አለው፡፡ ያም ተስፋ ቀድሞውኑ ያ ህዝብ የግለሰብ መብቱ የተከበረለት ህዝብ የሆነ እንደሆነ ብቻ ነው፡፡ ያ ከሆነ ምርጫውን ያውቃል፡፡ በድገተኛና ሰውሰራሽ ሁኔታዎች በጥድፊያ በሚደረግ ሪፈረንደም ዋና ምርጫውን እንዳይስት ልቦና ይኖረዋልና፡፡ አምባገነኖች ግን የራሰን ዕድል በራስ መወሰንን ተጠቅመው ሕገወጥ መለያየት ቢፈጥሩ እንኳን አሁንም ሌላ አንድ ተስፋ አለን፡፡ ልብ እንበል፡፡ ያለስልት በመታገል ሣይሆን፤ ከተለያዩ በኋላም ቢሆን፤ በፍቅር በመተሳሳብ ያን የተለዩበትን ሀገር መልሶ በአንድ የተባበረ ሀገርነት መመስረት ይቻላል፡፡ ይህ በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ያለ ሕጋዊ የተባበረ መንግስት ምሰረታ ቅርፅ ነው፡፡ የተባበረች አሜሪካ መንግስታትም የዚሁ ዓይነት ትግል ውጤት ናት፡፡ ሊያውም የእሷ ፍጹም የተለያዩ ሀገር ዜጎችን አሰባስባ የምትኖር የታባበረች ሀገር፡፡ ስለተባበረችም የተከበረች፡፡ ለዚህ ደግሞ ዋናው ዋስትና የሕግ የበላይነት መከበር ነው፡፡ ሕግ በእኩል በሚከበርበት፤ ፍትሕ ርትዕ ባለበት፤ ዜጎች በግል ሆነ በቡድን መለያየትን ሳይሆን የአንድነትን ፍሬ ነው ማጣጣም የሚሹት፡፡ አንድነት እና ሕብረት የፍቅር መግለጫዎች ናቸው፡፡ ለዚህም ነው ለእኛ ለኢትዮጵያውያን ክቡር ዶ/ር ጥላሁን እንዳቀነቀነው “መለያየት ሞት” የሚሆነው፡፡ አንለያይም ሳይሆን እንተባበራለን፡፡ ተስፋ አንቆርጥም እንገናኛለን፡፡

የራሣችንን ዕድል በፍቅር በመወሰን የዘረኞችን ሴራ እናከሽፋል!

ዛሬም ነገም – አብረን ነን!!!

“ወያኔ የጀመረው ለትግራይ ሕዝብ ጠላትን የማራባት ዘመቻ የትግራይን ሕዝብ ያጠፋዋል፤ ይህንን ሳንጠራጠር ልንቀበለው ይገባናል (ፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማርያም)

ፕሮፌስር መስፍን
ፕሮፌስር መስፍን

ብንደብቀው አይጠቅመንም፤ ስለዚህ የመጀመሪያው ደረጃ መፍትሔ የጠላትነት እሳት እንዳይቀጣጠልና ትግራይን እንዳይበላ መከላከል ነው፤ ይህንን የመጀመሪያ ደረጃ መፍትሔ ለመጀመር የትግራይ ሕዝብ ግምባር ቀዳሚ መሆን ያለበት ይመስለኛል፤ የገጠመውን የተቆላለፈ ችግር የትግራይ ሕዝብ በትግሬነት እፈታዋለሁ ብሎ ከተነሣ ያባብሰዋል እንጂ በጭራሽ ሊፈታው እንደማይችል መቀበል የትግሉ መነሻ ይሆናል፤ ከዚህም ጋር ወያኔ ትግራይን ድሪቶ በማድረግ ከዚያም ከዚህም መሬት እየቀነጫጨበ በማስገባት ትግራይን አሳብጦ ከጎረቤቶች ሁሉ ጋር ለማጣላት የሚያደርገውን አጉል ቂልነት መቃወም ግዴታቸው እንዲሆን በበጎ ፈቃድ ቢወስኑ ከብዙ ችግሮች የሚድኑ ያመስለኛል፤ ወደትግራይ እሳቱ ሳይቀጣጠል የትግራይ ሕዝብ ነቅቶ እሳቱን ለማዳፈን መዘጋጀት ያስፈልገዋል፤ ለዚህ ሁለት ምክንያቶች አሉ፤ አንደኛ የችግሩ ፈጣሪ የሆነው ወያኔ ቤቱና ምሽጉ ያደረገው ትግራይን ስለሆነ ለወያኔ የተቃጣው ሁሉ ትግራይ ላይ የሚያርፍ ነው፤ ስለዚህም የሚቀጣጠለው እሳት በቅድሚያ የሚበላው የትግራይን ሕዝብን መሆኑ ሁለተኛው ምክንያት ይሆናል፤ ወያኔ ሆነ ብሎ በትግሬነትና በወያኔነት መሀከል ያለውን ልዩነት አፍርሶ ትግሬንና ወያኔን አንድ አድርጎ በማቅረብ የችግሩን ፈጣሪና የችግሩን ገፈት ቀማሽ አንድ ለማድረግ እየሞከረ መሆኑ ነው፤ ይህንን ሀሳብ የትግራይን ሕዝብ ለመከፋፈል የታቀደ የፖሊቲካ ስልት አድርጎ ለመውሰድ ይቻላል፤ ግን የትግራይን ሕዝብ መከፋፈል ለኢትዮጵያ ምን የፖሊቲካ ትርፍ ያስገኛል?”

ፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማርያም

“ኃላፊነቱን እንወስዳለን!” እያሉ እንደገና ጭፍጨፋ ውስጥ መግባት ብልጠት ወይስ ድንቁርና? (ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው)

“ኃላፊነቱን እንወስዳለን!” ወያኔ ወንጀሎቹን የመካጃ፣ የማስተባበያ፣ የመዋሻ፣ የማምለጫ፣ የማወናበጃ፣ የጊዜ መግዣ ምክንያቶቹን ሁሉ ሲጨርስ እንዲሁም የሚፈጽማቸው ግፎች በበቂ ማስረጃ የተያዙና ማስተባበል፣ መዋሸት፣ መካድ የማይችለው ነገር እንደሆነ ሲረዳ አሁን በመጨረሻ ላይ ያመጣት የማታለያ፣ የማጃጃያ፣ የጊዜ መግዣ ቃል መሆኗ ነው፡፡

ወያኔ/ኢሕአዴግ “ኃላፊነቱን እንወስዳለን!” በማለት ሙሉ ለሙሉ እራሱን ተጠያቂ ሲያደርግ ይሄ የመጀመሪያ ጊዜው ነው፡፡ ከዚህ ቀደም ግን ጥፋት የፈጸሙ አንዳንድ ኪራይ ሰብሳቢዎች ከመሀሉ እንዳሉ ይገልጽና፣ በስብሰናል ገምተናል ምንትስ ይልና ሕዝብን ለማታለል፣ ለመደለል፣ ጊዜ ለመግዛት ተሐድሶ፣ ጥልቅ ተሐድሶ፣ በጣም ጥልቅ ተሐድሶ በማለት ነበረ ለማሞኘት ሲሞክር የነበረው፡፡አስገራሚው ነገር ግን ወያኔ እንደ ዘውዳዊ አገዛዝ ሥልጣኑን የያዝኩት በዐፅመ ርስትነት ነው ብሎ ያምናል መሰለኝ መግማቱን፣ መበስበሱን፣ በጥፋት ማጥ ውስጥ መስጠሙን አምኖ እየተናገረም “ብበሰብስም፣ ብገማም፣ ብከረፋም፣ ጥፋት በጥፋት ብሆንም እኔው ብቻ እገዛለሁ እንጅ!” ብሎ በሕገ መንግሥቱ የሥልጣን ባለቤት ነው ያለውን የኢትዮጵያን ሕዝብ ሌላ መንግሥት እንዳይመሠርት ፈጽሞ አለመፍቀዱ ነው፡፡ እንዲህ እያደረገም ደግሞ ሳያፍር ዲሞክራሲያዊ (መስፍነ ሕዝባዊ) ነኝ ይላል፡፡

“ኃላፊነቱን እንወስዳለን!” የሚለው ቃል መጀመሪያ ላይ የተሰማው ወያኔ/ኢሕአዴግ የ17 ቀናት ግምገማ ካደረገ በኋላ ባወጣው መግለጫ ላይ “በሀገሪቱ ለደረሰው ጥፋት ሁሉ ተጠያቂዎቹ እኛ ነን ይቅርታ እንጠይቃለን!” በማለት ሲናገሩና ኃላፊነቱንም እንደሚወስዱ ሲገልጹ ነበር የተሰማው፡፡

ከዚያ በኋላ ደግሞ ሰሞኑን ከወልዲያው፣ ከቆቦው የግፍ ግድያዎች በኋላ ሕዝቡ እራስን የመከላከል እርምጃ መውሰድ በጀመረ ማግሥት አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ችግሩን አስመልክቶ በሰጠው መግለጫ “ለተፈጸመው ጥፋት ኃላፊነቱን እንወስዳለን!” ሲል ቃሉን ደግሞ አንሥቶታል፡፡ ይሁን እንጅ እያሉት እንዳሉት ሁሉ እንኳንና ኃላፊነት ወስደው ቀጥለው መውሰድ ያለባቸውን እርምጃ ሊወስዱ ቀርቶ ከወትሮው በባሰ ኃላፊነትና ተጠያቂነት የሚባል ነገር ጨርሶ በሌለበት መልኩ በሕዝብ ላይ ግፍ በመፈጸም የሕዝብ ደም እያፈሰሱ ይገኛሉ፡፡

ለመሆኑ ኃላፊነትን መውሰድ ማለት ምን ማለት ነው? ኃላፊነትን መውሰድ ማለት ጥፋትን ማመንና ለተፈጸመው ጥፋትም ተጠያቂ በመሆን በተፈጸመው ጥፋት ልክ ፍትሐዊ ቅጣትን በመውሰድ የሕዝብን ጥያቄ ተቀብሎ መቃናት፣ መታረም፣ መስተካከል ማለት ነው፡፡ ከዚህ ውጭ ሌላ ትርጉም የለውም፡፡ የቃሉን አጠቃቀም በአሸባሪዎች ዐውድ ያየነው ከሆነ ትርጉሙ “አደጋውን ያደረስነው እኛ ነን!” ማለት ነው፡፡

ወያኔ በቃል “ኃላፊነትን እወስዳለሁ ለተፈጸመው ጥፋት ሁሉ ይቅርታ እጠይቃለሁ!” አለ እንጅ እስከአሁን ድረስ ለደረሰው ጥፋት ተጠያቂ የሆኑና ፍትሐዊ ቅጣት እንዲያገኙ የተደረጉ አንድም የጥፋት እርምጃዎቹ እንዲወሰዱ ትዕዛዝ ያስተላለፈ ባለሥልጣንና ነፍሰ ገዳይ ወታደር የለም፡፡ ወደፊትም ይኖራል ተብሎ አይታሰብም፡፡

ወያኔ ሌሎች የማጭበርበሪያ የማወናበጃ ዘዴዎችን ስለጨረሰ ለማጭበርበር ያህል ይሄንን ቃል ተናገረ እንጅ ኃላፊነትን ከመውሰድ ጋር ተያይዘው ያሉ እርምጃዎችን ለመውሰድ ፈልጎ ፈቅዶና ተዘጋጅቶ የተናገረው ቃል አይደለም፡፡ ወያኔ እንዲህ ላድርግ ቢል ሕዝባዊ ዐመፁ ለመቀስቀሱና ዐመፁን ተከትሎ ለተወሰደው ግፍ የተሞላበት አረመኔያዊ እርምጃ ተጠያቂ የማይሆን አንድም የወያኔ ባለሥልጣን አይኖርምና ነው፡፡ ከዚህ የተነሣ የዋሃን ተላሎች ካልሆኑ በስተቀር ይሄንን “ኃላፊነቱን እንወስዳለን!” የሚለውን የወያኔን ቃል ከልብ የተባለና የሚፈጸም አድርጎ ያሰበ ኢትዮጵያዊ ይኖራል ብየ አላስብም፡፡

እናም ወያኔ ቃሉን የተጠቀመው እንደለመደው ሕዝብን ለማታለያነት፣ ለማወናበጃነት፣ ለጊዜ መግዣነት ብቻ ነው ማለት ነው፡፡ ይሄ ለመሆኑ አንዱ ማረጋገጫው ደግሞ ሰሞኑን አስቀድሞ ያሰበበትንና የተዘጋጀበትን የግፍ ግድያ ወልዲያ ላይ ሃይማኖታዊ ሥርዓት በመፈጸም ላይ ባሉ ምእመናን ላይ ከፈጸመ በኋላ በላኮመልዛ (ወሎ) ከሰባት በላይ ከተሞች ሕዝብ ላይ እየወሰደው ያለው ግፍ የተሞላበት፣ ፈጽሞ ኃላፊነትና ተጠያቂነት የሚባል ነገር የሌለበት አረመኔያዊ እርምጃ እየወሰደ ያለ መሆኑ ነው፡፡

ይሁን እንጅ ይህ የወያኔ/ኢሕአዴግ ባለሥልጣናት በገዛ አንደበታቸው ጥፋቱ የራሳቸው መሆኑን አምነው የተናገሩት ቃል ወንጀለኝነታቸውን፣ ተጠያቂነታቸውን ኦፊሴላዊ (ይፋዊ) በሆነ መንገድ በራሳቸው ላይ በመመስከር ያረጋገጡበት ቃል በመሆኑ ይህ መግለጫ ወደፊት አንዳችም ምስክርና ማስረጃ ሳያስፈልግ ወንጀለኝነታቸውን አረጋግጦ ተገቢውን ፍርድ የሚያሰጣቸው የራስ የምስክርነት ቃል በመሆኑ ለወደፊቱ ጠቀሜታው እጅግ የጎላ ነው፡፡ እነኝህ የወያኔ/ኢሕአዴግና የአቶ ገዱ መግለጫዎች ተጠብቀው መያዝ ይኖርባቸዋል፡፡ በመሆኑም “ኃላፊነቱን እንወስዳለን!” እያሉ እንደገና ጭፍጨፋ ውስጥ መግባት ብልጠት ሳይሆን እጅግ የከፋና ከባድ ዋጋ የሚያስከፍል ድንቁርና ነው!!!

ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!! ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!!
ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው
amsalugkidan@gmail.com