“ቀይ መስመር ተጥሷል…!!!” ፕ/ት ሳህለወርቅ ዘውዴ

ሰሞኑን በአዲስ አበባ እና በተለያዩ የኦሮሚያ ከተሞች ውስጥ በአብዛኛው ዘር እና ሀይማኖትን ኢላማን ያደረገው እና ለበርካታ ዜጎችን ህይወት እንዲቀጥፍ ምክንያት የሆነው ጭፍጨፋ “ቀይ መስመሩን ያለፈ ነው” ሲሉ ፕ/ት ሳህለወርቅ ዘውዴ ድርጊቱን በጽኑ አወገዙ።

ፕ/ት ሳህለወርቅ በወዳጆች መገናኛ መረብ የቲውተር ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት ጽሑፍ” ዘር እና ሀይማኖት ለፖለቲካ ጥቅም እንዲውሉ ሲደረግ፣ንጹሀን እና ሰላማዊ ዜጎቻችን በአሳቃቂ ሁኔታ ሲገደሉ፣ሲፈናቀሉ እና ሲሰደዱ ስናይ ስሜትን ለመግለጽ ቃላት ያጥራል፣ለቅሶ ድንጋጤ እና ስጋት የብዙዎችን በርን አንኳኩቷል።ሀዘናቸው ሀዘኔ ነው”በማለት እጅግ አሳዛኝ እና አሳፋሪ በሆነው ድርጊት መቆጨታቸውን በግላጭ ተናግረዋል።
ወደ ፕ/ትነት ስልጣን ከመምጣታቸው በፊት ኢትዮጵያን እና ህዝቦቿን በመወከል ከሰላሳ አመት በላይ በዲፕሎማትነት ያገለገሉት ፕ/ት ሳህለወርቅ የትዊተር መልክታቸውን ሲቀጥሉ”ለሀገር እና ለህዝብ ጥቅም ሲባል ልናሰምረው እና ልናከብረው የሚገባው ቀይ መስመር ተጥሷል፣ሀገራችን ካንዣበበባት ክፉ አደጋ ለማዳን ሁላችንም ሚና አለን፣የሚመለከታቸው ሁሉ የየበኩላቸውን ሀላፊነትን መጫወት አለባቸው፣ቀዩ መስመር መጣስ የለበትም እንበል”በማለት ስርአት አልበኞችን መዋጋት ለአንድ ተቋም ብቻ የሚሰጥ ሳይሆን በሀገሬ ጉዳይ ያገባኛል የሚል ሰላም ወዳድ ዜጋ ሁሉ እርብርቦሽ እንዲያደርግ ተቃውሞ አዘል ጥሪ አቅርበዋል።

እንደ የኢትዮጵያ የሰብአዊ መብት ኮሚሽን መግለጫ ከሆነ በሰሞኑ ግጭት ከሰማኒያ በላይ ዜጎች ህይወታቸውን ያጡ ሲሆን የአሟሟታቸውንም ሁኔታ በተመለከት ኮሚሽኑ እንደታዘበው አስር የሚሆኑት ብቻ በጥይት ተመትተው የሞቱ ሲሆን የተቀሩት በድንጋይ ተወግረው፣በስለት ተወግተው እና በዱላ ተጨፍጭፈው እንዲሞቱ መደረጉን የኬሚሽኑ መግለጫ ይገልጻል።
ከዚህ በመቀጠልም ከወንጀሉ ጋር በቀጥተኛ ሆነ በተዘዋዋሪ ግንኙነት ያላቸው በሙሉ በህግ እንዲጠየቁ አሳስቧል።
የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን በበኩሉ ከስሞኑ እልቂት ጋር የተጠረጠሩ ወደ ሶስት መቶ ሀምሳ ዘጠኝ ግለሰቦችን በቁጥርጥር ማዋሉን አስታውቋል።

(በታምሩ ገዳ/ህብር ራዲዮ)

ሃሰተኛው ዶክተር (አቶ ጸጋዬ አራርሳ) እና የዘር ጥላቻ ቅስቀሳው – አበበ ገላው

ሃሰተኛው ዶክተር አቶ ጸጋዬ አራርሳ

የጥላቻ ፖለቲካ አቀንቃኝ በመሆን የተዛባና መርዘኛ የሆነ “ትንታኔ” በመስጠት ህዝብን በህዝብ፣ ድሃን በድሃ ላይ በማነሳሳት ላይ ከሚገኙ የጃዋር ጋሻ ጃግሬዎች አንዱ አቶ ጸጋዬ አራርሳ መሆኑ ያደባባይ ሚስጥር ነው። በትናንትናው እለት ባጋጣሚ ፌስቡክ ላይ ላይቭ ወጥቶ ሲዘባርቅ እንደምንም ለትንሽ ደቂቃ ታግሼ እየጎመዘዘኝም ቢሆን ሰማሁት።

አገራችን ላይ የተፈጠረውን ሰቆቃና እየመጣ ያለውን ከባድ የእልቂት ድግስ ባላገናዘበ መልኩ በትንታኔ ስም ያለምንም እፍረት ከፋፋይና ጸረ-ኢትዮጵያ ዲስኩር ሲያሰማ አየሁት። ሃላፊነት ለሚሰማው ማንም ግለሰብ ከባዱ ነገር ያልኖርንበትን ታሪክ ለቁርሾ፣ ለጥላቻና ህዝብ ለማጋጨት መርዝ መርጨት አይደለም። ከባዱ ነገር ካለፈው በጎም ይሁን ክፉ ታሪክ ተምሮ የተሻለና ለሁሉም ዜጋ ፍትሃዊ የሆነ ስርአት መፍጠር ነው። የኢትዮጵያም ትልቁም ፈተና ይሄው ነው። ጥላቻ ለመስበክ ግን ማንም ቀለም መቁጠር አይጠበቅበትም።

ከሁሉ በላይ ያስገረመኝ አቶ ጸጋዬ ያለምንም ሃፍረት አሁንም ዶክተር የሚል የሃሰት ታፔላ ለጥፎ “ተንታኝ” እየተባለ በየመስኮቱ ብቅ ማለቱ ነው። አንድ ሰው እንኳን ህዝብን ተራ ግለሰብን ለማጥላላት አደባባይ ከመውጣቱ በፊት እራሱን በአግባቡ ማወቅ አለበት።

አቶ ጸጋዬ ሆይ! አንተ ያልሆንከውን ሆነህ ሌላውን ለምን ታምታታለህ። ትምርትህን ባግባቡ መከታተል ትተህ ሌት ተቀን ጥላቻ ስትዘራ ያሰናበተህ የሜልበርን ዩኒቨርሲቲ አንተን በተመለከተ አንድ ጊዜ ሳይሆን ሁለት ጊዜ በይፋ መግለጫ አውጥቷል። ሁለቱም መግለጫዎች ተመሳሳይ ናቸው። “ሚስተር ( አቶ) ጸጋዬ አራርሳ የዩኒቨርሲቲው ተቀጣሪ አይደለም። ትምርቱን ስላላጠናቀቀ የዶክትሬት ዲግሪ አልሰጠሁትም” ነው ያለው። ይሄ ሃቅ አሁንም አልተቀየረም።

እኔ በግሌ በዚህ ጉዳይ ከተለያዩ የዩኒቨርሲቲው ሃላፊዎች ጋር መጻጻፍ ብቻ ሳይሆን በስልክም ተነጋግሪያለሁ። የዩኒቨርሲቲው የህግ ትምህርት ዲን ፕሮፌሰር ፒፕ ኒኮልሰንን ጨምሮ አራት በተለያየ ሃላፊነት ላይ ያሉ ሰዎችን በስልክ ያነጋገርኩ ሲሆን በኢሜይልም ተጻጽፍያለሁ። ጊዜ ማበከን ካልሆነብኝ በዝርዝር ሁሉንም ይፋ ላረግልህ እችላለሁ።

ከሁሉም የተረዳሁት ነገር የአንተ ጉዳይ ስመጥር ለሆነው ዩኒቨርሲቲ ግራ የሚያጋባ መሆኑን ነው። አንተ ግን ያልሆንከውን ነኝ በማለት አሁንም በየዋህነት የሚከተሉህን የጥላቻ አብጊዳ ቆጣሪዎች ታደናግራለህ።

እውነቱን ለመናገር ምሁር ለመባል ፒኤችዲ (PhD) ፈጽሞ አያስፈልግህም። ምሁር ለመሆን የሚያስፈልግህ ዋጋ ያለው መልካም ሃሳብና እውቀት ነው። አንተን የጎደለህ ቅንነና እውነተኛ ማንነትህ ላይ የፈጠርከው ብዥታ በመሆኑ ተምታቶብሃል። አንድ ሰው አደባባይ ከመውጣቱ በፊት አቶ ወይንም ዶክተር መሆኑን ለራሱ አጣርቶ ማወቅ ከተሰናው ለሌሎች የሚተርፍ እውነት ይናገራል የሚል እምነት የለኝም።

ማንነት የሚጀምረው ከግለሰብ ነው። ስለዚህም ኢትዮጵያዊ የሚባል ማንነት የለም የሚል ቀሽም ዲስኩር ከማሰማትህ በፊት ለሰው ስትል ሳይሆን ለራስህ “ዶክተር ጸጋዬ አራርሳ” የሚባል ማንነት አለመኖሩን አምነህ መቀበል ይኖርብሃል። አንድ ሰው ለራሱ የትምርት ማእረግ አይሰጥም። እንደተ አይነቱ ግራ የገው “ምሁር” ግን አይኑን በጨው ታጥቦ ድርቅ ካለ ትርፉ “የሌባ አይነ ደረቅ” መባልና እራሱን የሃሰት ዲግሪ ከሚገዙ ሰዎች በታች አሳንሶ መገኘት ብቻ ነው ትርፉ። መማር ቢሳናቸው ከጥቁር ገበያ ዲግሪ የገዙ ሰዎች ቢያንስ ገንዘባቸውን ከፍለዋል።

ለማንኛውም አታምታታ። በሃሰተኛ ዶክተርነት ከመጀቦን በእውነተኛ አቶነህ ኮርተህ ከጥላቻ ሰባኪነት ውጣና መልካም ለመስራት ትጋ። ዛሬ ከእነጃዋር ጋር ወግነህ ህዝብ መከፋፈልና ማባላት ነገ እንደሚያስጠይቅህ አትጠራጠር። በድሃ ህዝብና አገር እጣ ፈንታ ላይ አትቆምሩ። ህዝብም ታሪክም እንደሚፈርድ አትጠራጠር።

አበበ ገላው

ባለቤቷን ከቀናት በፊት ፊቷ ላይ ጭካኔ በተሞላበት መንገድ የገደሉባት የሁለት መንታ ልጆች እናት

ባለቤቷን ከቀናት በፊት ፊቷ ላይ ጭካኔ በተሞላበት መንገድ የገደሉባት የሁለት መንታ ልጆች እናት ስለሁኔታው ይሄንን ብላለች

“ከቀኑ 7 ሰዓት ላይ ቄሮ መጣ እያሉ ሰዎች እየጮኹ ወደየቤታቸው መግባት ጀመሩ። እኛም ቤታችን ገብተን በር ዘግተን ተቀመጥን። ቄሮዎቹም እንደደረሱ የእኛ ቤት ላይ ድንጋይ መወርወር ጀመሩ። እኛ ምንም አላሰብንም፤ ደነገጥን። ከዝያም አጥራችንን አፍርሰው ወደጊቢያችን እንደገቡ በመጀመርያ ስድብ መስደብ ጀመሩ። መሬቱም የኛ ነው፤ መንግስትም የኛ ነው እናንተ ጋሞዎች ኑ ውጡ አሉን። ከነርሱም መካከል ሁለቱ ቤት ገብተው እኔና ባለቤቴን ይዘውን ወጡ። ባለቤቴም ከቄሮዎቹ መካከል የሚያውቀውን አንድ ጋዲሳ የተባለ የሰፈር ልጅን ‘አንተ ጋዲሣ እንዴት እንዲህ አይነት ነገር በእኛ ላይ ታደርጋለህ እባክህን ተው፤ ለነዚህ ህፃናት ስትል ተው ባክህ’ ይለዋል። እነርሱ ግን እንጨርሳለን፤ ገና እንጨርሳቹኋለን እያሉ ባለቤቴን በድንጋይ መደብደብ፣ በስለት መውጋት ጀመሩ። ባለቤቴ ብዙ ከደበደቡት በኋላ ሞተ። እሱ እንደሞተ እኔ መጨው ስጀምር ‘ለምን ትጮዄለሽ አፍሽን ዝጊ እያሉ እኔንም መምታት ጀመሩ። ከዝያንም የሰፈራችን ሰው 5 ሌትር ጅሪካን እና ክብሪት ሲሰጣቸው አየሁ። ‘ጨርሱ ካለቀ እኔ ጨምራለው’ አላቸው። ባመጡት ጋዝ ቤታችንን አቃጠሉ። አብዝቼ ብጮህም የደረሰልኝ የለም። የፖሊስ ልብስ የለበሱ ሰዎችን የባሌን አስክሬን አንሱልኝ ስላቸው እየሳቁ አይተውኝ ሄዱ።”

የዛሬ ዓመት እንደዚህ ወሬ እየሰማን ነበር። ግን የመንግስት ባለሥልጣናት ችግር የለም ሁሉም ተስተካክሏል እያሉ አዘናጉን። ይሄው ዛሬ ግን ቤት ድረስ መተው አጠገቤ ባሌን ቆራርጠው ገደሉብኝ። ለማን አቤት እላለው?የዓለም መንግስት ይድረስልን!

የሙታን ፖለቲካ ያጣመራቸው የዕልቂት መልዕክተኞች!

(ስዩም ተሾመ)

እስኪ ፖለቲካው ይቆየንና ስለ እውነት እንናገር። ለአንድ አፍታ፤ ሳናዳምጥ አናውራ፣ ሳናውቅ አንቃወም፣ ሳይገባን አንደግፍ። እስኪ ለአፍታ እንኳን ከግብታዊ ስሜት እንውጣ፣ በምክንያት እናስብ። የአንድ ሃሳብ ትክክለኝነት የሚመዘነው በተናጋሪው ስልጣንና ማንነት ሳይሆን በምክንያታዊ ዕውቀት ነው። ምክንያታዊ ዕውቀት የትላንቱን ጠንቅቆ ማወቅ፣ የዛሬን በዝርዝር መገንዘብ፣ የነገን በትክክል መገመት ያስችላል። የትላንቱን ታሪክ እና የወደፊቱን ሁኔታ መሰረት ያደረገ በሰዎች ሕይወት ላይ ተጨባጭ ለውጥና መሻሻል ሊያመጣ የሚችል ሃሳብ ትክክልና አግባብ ነው። እንዲህ ያለ ሃሳብን ላለመቀበል መቃወም ራስን ማታለል፣ ሌሎችን መበደል ነው። ስለዚህ ለራሳችንም ሆነ ለሌሎች ስንል ቆም ብለን ማሰብ፣ በምክንያት መጠየቅና በተግባር መፈተሸ ያስፈልጋል።

እንደ ናጄሪያዊው ሎሬት “Wale Soyinka” አገላለፅ “አክራሪ ብሔርተኝነት አንድ ላይ ያስተሳስራል፤ ግን ደግሞ አንድ ላይ ያውራል!” ይላል። በዋናነት ከ50 አመት በፊት የተጀመረው የብሔርተኝነት ንቅናቄ የመጨረሻው ደረጃ ላይ ደርሷል። ዛሬ ላይ ብሔርተኝነት ህዝባዊ ንቅናቄ ከመፍጠር አልፎ የግጭትና ዕልቂት መሳሪያ ሆኗል። ነገሩ ከራስ ወዳድነትና ወገንተኝነት አልፎ ወደ ጦርነትና ዕልቂት ሊቀየር ጫፍ ላይ ደርሷል። ሁሉም ሰው በየራሱ ብሔር ስር ተወሽቋል። እድሜ ለሕገ መንግስቱ እና ፌደራሊዝም ስርዓት ሁሉም ሰው በየራሱ ብሔር ጉያ ስር ተወሽቋል። ሁሉም ሰው በብሔር ተደራጅቶ አንድነቱን አጠናክሯል። ነገር ግን አንድ ላይ ያስተሳሰረው ነገር አንድ ላይ አውሮታል። ብሔርተኝነት በተንሰራፋው ልክ የሰዎችን እይታ፣ የማስተዋል አቅም እና የግንዛቤ ደረጃ በከፍተኛ ደረጃ ቀንሷል።

አዎ… ብሔርተኝነት አንድ ላይ ያስተሳስራል። የእያንዳንዱን ብሔር አንድነት ያጠናክራል፤ የብሔር መብትና እኩልነት ይከበራል። በብሔር መደራጀት፣ በብሔር መነቃነቅ፣ በብሔር መቃወም፣ በብሔር መጠየቅ፣ በብሔር መንጠቅ፣ በብሔር ማጥፋት፣ በብሔር መግደል ይቻል ይሆናል። ነገር ግን በብሔር ፖለቲካ በራስ ማየት፣ በራስ ማሰብ፣ በራስ ማስተዋል፣ በራስ ፍላጎትና ምርጫ መንቀሳቀስ፣ በራስ አመዛዝኖ መወሰን፣ ራስን በራስ መምራት አይቻልም። ምክንያቱም ብሔርተኝነት አንድ ላይ ያስተሳስራል እንጂ አንድ ዓይን የለውም፤ የሚያስብ አዕምሮ፣ አስተዋይ ልቦና፣ የራሱ ፍላጎትና ምርጫ የለውም። በመሆኑም ብሔር በራሱ አመዛዝኖ መወሰን እና ራሱን በራሱ መምራት አይችልም።

“Wale Soyinka” እንዳለው አንድ ላይ ያስተሳሰረን ብሔርተኝነት እውነታን ከማየት ያግደናል። ነባራዊ እውነታን ማየትና መገንዘብ የማይችል በራሱ ማሰብና ማስተዋል አይችልም፤ በራሱ ፍላጎትና ምርጫ መወሰን፣ ራሱን በራሱ መምራትና መንቀሳቀስ ይሳነዋል። ስለዚህ በብሔርተኝነት አንድ ላይ የታሰረ ህዝብ እውነታን አይቶ የሚገነዘብለት፣ አስቦና አመዛዝኖ የሚወስንለት፣ እንዲሁም ከፊት ሆኖ እየመራ የሚያንቀሳቅሰው መሪ ያስፈልገዋል። አንድ ላይ የተሳሰረን ህዝብ መምራት የሚችለው አንድ ሰው ወይም ቡድን ነው። በመሆኑም አንድ ብሔር ከአንድ በላይ መሪ ሊኖረው አይችልም። ስለዚህ አንድ መሪ በራሱ እውነታን ያያል፣ ያገናዝባል፣ አመዛዝኖ ይወስናል፣ ከፊት ሆኖ ይመራል። የተቀሩት የብሔሩ አባላት በመሪው ዓይን ያያሉ፣ እሱ ያዘዛቸውን ያደርጋሉ፣ እሱ በመራቸው መንገድ ይጓዛሉ።

በዚህ መልኩ አክራሪ ብሔርተኝነት የሰው ልጅን ከምክንያታዊነት ወደ ግዑዝ መንጋነት ይቀይራል። መሪው የተናገረው ውሸት እውነት ይሆናል፣ መሪው የካደው እውነት ወደ ውሸትነት ይቀየራል፣ የመሪው ጥፋት ሁሌም አግባብ ነው፣ የመሪው መንግድ ፍፁም ትክክል ነው። መንገዱ በጠላቶች የተሞላ ነው። በጠላት ላይ ሲሰበክ የኖረ ጥላቻ ሁሌም ጠላት ይፈልጋል። በመሆኑም አንዱ ጠላት ሲወገድ ሌላ መተካት የግድ ይላል። ጉዞው በህልውና ላይ የተጋረጠን አደጋ ለመከላከል የሚካሄድ ትግል ነው። በህልውና ላይ የተጋረጠን አደጋ ለመከላከል የሚደረገው ትግል መስዕዋትነት ይጠይቃል። የትግሉ ዓላማ ነፃነትን መቀዳጀት ነው። በመጨረሻ የትግሉ ውጤት ነፃነትና ሰማዕታት ይሆናሉ።

እንደ ካሜሮናዊው ምሁር አቺሌ ምቤምቤ አገላለፅ መሪው ያለው “የሙታን ኃይል” (Necropower) ነው፣ ፖለቲካውም “የሙታን ፖለቲካ” (Necropolitics” ይባላል። የሙታን ኃይል ማን መኖር፣ ማን መሞት እንዳለበት መወሰን የሚያስችል ስልጣን ነው። በሙታን ፖለቲካ ራስን በመከላከል እና በማጥፋት፣ በመመለስ እና ነመቅረት፣ በነፃነት እና ሰማዓት መካክል ግልፅ የሆነ መስመር የለም። የሙታን መሪዎች በትግል ከተገኘው ድል ይልቅ የተገደሉትን፣ ካገኙት ነፃነት ይልቅ ሰማዕታቱን ማሰብ ይመርጣሉ። ምክንያቱም ቂምና ጥላቻን ማራዘም ይሻሉ። ጠላትና ጦርነት ከሌለ ተከታይ አይኖራቸውም። ስለዚህ ስልጣናቸውን ለማራዘም ጥላቻ እየሰበኩ ጠላት ያፈራሉ፣ ቂም በመቆስቆስ ግጭት ይፈጥራሉ። ይህ ሲሆን ጭፍን ደጋፊዎች የሙታን መንገድን ይከተላሉ። በቂምና ጥላቻ ሌሎችን ይገድላሉ ወይም በሌሎች ይገደላሉ። በዚህ መልኩ የሙታን ኃይል ከሞት ይመነጫል፣ የሙታን ፖለቲካ በፍርሃት መርህ ይመራል።

ባለፉት አራት አስርት አመታት ኢትዮጵያ ውስጥ የነበረው የሙታን ፖለቲካ ነው። የፖለቲካ መሪዎቻችን ስልጣንም ከሞት የመነጨ ኃይል ነው። ከአብዮቱ ጀምሮ የሀገራችን ፖለቲካ በጅምላ መፈራረጅና መገዳደል የተሞላ መሆኑ ለዚህ ጥሩ ማሳያ ነው። በተለይ ባለፈው ግማሽ ክፍለ ዘመን አብዮትና ፀረ አብዮት፣ ነጭ ሽብርና ቀይ ሽብር፤ ኢትዮጵያ ወይም ሞት፣ የአንድነት ወታደር እና ገንጣይ ወንበዴ፤ ሰላምና ፀረ-ሰላም፣ ልማትና ፀረ-ልማት፣ ህገ መንግስትና ፀረ-ህገ መንግስት፣ ሽብርና ፀረ-ሽብር፣… ወዘተ በሚል የጅምላ ፍረጃ የአንድ ዘመን ትውልድ እርስ በእርሱ ለዕልቂት ተዳርጓል። ምክንያቱም ያ ትውልድ አብዮተኛ ነው። “አብዮት” ደግሞ ወረተኛ ነው። ወረቱ ሲያልቅ እርስ በእርስ መፈራረጅና መገዳደል የግድ ነው።

በመሰረቱ አብዮተኛ እና ፀረ-አብዮተኛ በሚል በጅምላ ከመከፋፈል በስተቀር በመካከላቸው መሰረታዊ የሆነ የአቋም ሆነ ርዕዮተ-ዓለም ልዩነት አልነበረውም። ሁሉም አብዮተኛ ሥር ነቀል ለውጥ ያስፈልጋል፣ የዜጎች እኩልነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ ይጠይቃል። ከሞላ ጎደል ሁሉም አብዮተኞች የማርክሲስት/ሌኔኒስት ጥራዝ ነጠቆች ናቸው። ነገር ግን ሁሉም ራሳቸውን “አብዮተኛ” ሌሎችን “ፀረ-አብዮተኛ” ብለው በጅምላ ይፈራረጃሉ። ከጅምላ መፈራረጅ ቀጥሎ በጅምላ መገዳደል ይከተላል። ምክንያቱም የአብዮተኛው ድል የሚረጋገጠው ፀረ-አብዮቶችን በመግደል ነው። በሌላ በኩል አንድ ፀረ-አብዮተኛ የሚኖረው አብዮተኞች በሙሉ ሲወገዱ ነው። የአብዮቱ ስኬት ለፀረ አብዮቱ ሽንፈት ነው።

በሙታን ፖለቲካ የአንዱ ህይወት የሚገኘው በተቀናቃኙ ሞት ነው። ስለዚህ ጎራ ለይቶ መገዳደል የስርዓቱ መገለጫ ነው። ይህ በተለይ ከ1966ቱ አብዮት በኋላ ኢትዮጵያ ስትመራበት የነበረ የፖለቲካ ስርዓት ነው። ለምሳሌ በደርግ የተጠለፈውን የተማሪዎች አብዮት ለማስመለስ የነጭ ሽብር ጥቃት ተፈፀመ። ነጭ ሽብርን ለመመከት ቀይ ሽብር ተፋፋመ። በዚህ ምክንያት አንድ ትውልድ በሙታን ፖለቲካ መከነ። እናት ልጇ ለተገደለበት ጥይት ከፈለች፣ አባት የልጁን ሬሳ ከመንገድ ላይ ማንሳት ተሳነው፣ ወዳጅ ዘመድ ከገዳዮች ፊት ማልቀስ ተከለከለ።

ከነጭ ሽብር ጥቃት የተረፉት ሶሻሊስት አብዮተኞች ደርግ እና መኢሶን በሚል ተከፋፍለው ተገዳደሉ። ደርግ ደግሞ “ቆራጥ አብዮተኛ” እና “ስርጎ-ገብ አድሃሪ” በሚል እርስ በእርስ ተከፋፍሎ ተገዳደለ። በዚህ መልኩ እነ ጄነራል ተፈሪ በንቲ እና ሺ/አለቃ አጥናፉ አባተን የመሳሰሉ ከፍተኛ አመራሮች ተገደሉ። የአብዮታዊ ዴሞክራሲ አቀንቃኞች የነበሩት ኢህአፓ እና ህወሓት ደርግን ለመውጋት በመሸጉበት እርስ በእርስ ተዋጉ። ኢህአፓን ያስወጣው ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) በውስጡ የትግራይ ማርክሲስት ልኔኒስት ሊግ (ትማልሊ) የሚል ድርጅት በመፍጠር ለሁለት ተከፈለ። ይህን ተከትሎ የህወሓት ዋና ሊቀመንበር የነበሩት ዶ/ር አረጋዊ በርሄ እና ምክትል ሊቀመንበር የነበሩት ኢ/ር ግደይ ዘርዓፂዮንን ጨምሮ ሌሎች የድርጅቱ መስራቾች ተሰደዱ።

ደርግ እና ህወሓት በየፊናቸው እርስ በእርስ ተከፋፍለው ከተገዳደሉ በኋላ የሀገር አንድነት እና የብሔር እኩልነት በሚል እርስ በእርስ ውጊያ ገጠሙ። ደርግ ወድቆ ህወሓት ሲመጣ ከስም በቀር የትውልድ አሊያም የስርዓት ለውጥ አልተደረገም። ምክንያቱም ደርግና ህወሓት የ1960ዎቹ አብዮተኛ ትውልድ ናቸው። አብዮተኛ ትውልድ ደግሞ “የፀረ” ፖለቲካ አራማጅ ነው። ስልጣኑም ከሞት የመነጨ ነው። በመሆኑም ህወሓት ወደ ስልጣን በመጣ ማግስት፤ ሰላምና ፀረ-ሰላም፣ ልማትና ፀረ-ልማት፣ ህገ መንግስትና ፀረ-ህገ መንግስት እያለ በጅምላ መፈረጅ፣ በጅምላ ማሰር፣ በጅምላ መግደልና ማሰቃየት ጀመረ። ለዚህ ደግሞ ሁሉንም ነገር በሽብርተኝነት የሚፈርጅ የፀረ-ሽብር አዋጅ አወጣ። በዚህ መልኩ የደርግ ቀይ ሽብር ዘመቻ በፀረ-ሽብር አዋጅ ተተካ።

አብዮተኛ ትውልድ የፀረ-ፖለቲካ አቀንቃኝ፣ የሙታን ፖለቲካ አራማጅ ነው። የአንድ ትውልድ አማካይ ዘመን 30 አመት ነው። በዚህ መሰረት የ1960ዎቹ ትውልድ ዘመን ያከተመው በ1990ዎቹ አጋማሽ ላይ ነው። የ1997ቱ ምርጫ የአብዮተኛው ትውልድ ዘመን ማብቂያና የአዲሱ ትውልድ ዘመን መጀመሪያ ነበር። ነገር ግን አዲሱ ትውልድ ሀገሪቱን ለመረከብ ከህወሓት/ኢህአዴግ ጋር ያደረገው ግብግብ በአጋዚ ወታደሮች ተጨናገፈ። ከአስር አመት ትዕግስት በኋላ ለቀጣይ 50 አመታት ኢትዮጵያን ለመግዛት ሲያልሙ የነበሩትን አብዮተኞች በሦስት አመት ህዝባዊ አመፅና ተቃውሞ ከስልጣን አስወገደ።

በአጠቃላይ ከደርግ መምጣት እስከ ህወሓት ውድቀት ድረስ ያለው ሁኔታ አንድና ተመሳሳይ ነው። አብዮተኞች ከሃሳብ የበላይነት ይልቅ በጉልበት የበላይነት፣ ከውይይት ይልቅ በጦርነት፣ ከመነጋገር ይልቅ በመገዳደል የሚያምኑ ስለመሆናቸው ከኢትዮጵያ በላይ እማኝ ምስክር የለም። በዚህ የጥሎ ማለፍ ፖለቲካ ውስጥ የአንዱ ስልጣን ሌላውን በመጣል፣ የአንዱ ድል ሌላውን በመግደል፣ የአንዱ ህይወት በሌላኛው ሞት ላይ የተመሰረተ ነው። በዚህ ምክንያት ሀገሪቱ የተገነባችበት መሰረት ተሸርሽሮ አልቋል።

በእርግጥ የአብዮቱ ፖለቲካ የሚቀጥል ከሆነ በጥቂት አመታት ውስጥ ኢትዮጵያ ትፈርሳለች። ስለዚህ አዲሱ ትውልድ እንኳን የሚመራው መንግስት የሚኖርበት ሀገር አይኖረውም። ኢትዮጵያ ከፈረሰች ደግሞ አሁን በውስጧ ያሉት ብሔሮች፥ ብሔረሰቦች የየራሳቸውን ሀገር መስርተው በጉርብትና የሚኖሩ ከመሰላችሁ ተሳስታችኋል። ከዚያ ይልቅ ሀገሪቱ ከፈረሰች ምስራቅ አፍሪካን የሚያጥለቀልቅ የደም ጎርፍ ይፈስሳል፣ ተቆጥሮ የማያልቅ ሬሳ በየስርቻው ይከመራል። ኢትዮጵያ ወደ ምድራዊ ሲዖል ትቀየራለች። ስለዚህ አዲሱ ትውልድ የትላንቱን ያረጀ የፖለቲካ አመለካከትና ዛሬ ላይ የሚስተዋለውን ጭፍን ብሔርተኝነት ማስወገድ አለበት።

በዚህ መሰረት የወደፊቱን አስከፊ እልቂትና ውድቀት ለማስቀረት አዲሱ ትውልድ አበክሮ ማሰብ፣ መስራትና መተባበር ይጠበቅበታል። ለዚህ ደግሞ ከፊት ለፊቱ ቆመው የዕልቂት ነጋሪት እየጎሰሙ ያሉትን የፖለቲካ ቡድኖች በግልጽ መጋፈጥ አለበት። እነዚህ የሙታን ፖለቲካ ያጣመራቸው የዕልቂት መልዕክተኞች ህወሓት እና ጃዋር (ኦነግ) ናቸው። ለአዲሱ ትውልድ የሁለቱ ጥምረት ትክክለኝነት እና አግባብነት ፍፁም ሊያሳስበው አይገባም። ምክንያቱም የህወሓቶች ዓላማና ግብ ምን እንደሆነ ባለፉት 27 አመታት በተግባር የታየ ነገር ነው። ህወሓቶች በ1997ቱ ምርጫ ደንግጠው ልክ እንደ አሁኑ ወደ መቀሌ ሸሽተው ከተመለሱ በኋላ በአስር አመት ውስጥ በህዝብ ላይ ያደረሱትን ስቃይ እና በሀገር ላይ የፈፀሙትን ዘረፋ ሁላችንም እናውቃለን።

አሁን ደግሞ ተመልሰው ከመጡ በምድር ላይ ታይቶና ተሰምቶ የማያውቅ አሰቃቂ ነገር ሊፈፅሙ እንደሚችሉ ጥርጥር የለኝም። በሌላ በኩል እነ ጃዋር መሃመድ የሚያራግቡት አክራሪ ብሔርተኝነት እነ ሌንጮ ለታ እና ሌንጮ ባቲ እድሜ ልካቸውን ሞክረው እውን ሊሆን እንደማይችል በተግባር ያረጋገጡት ነገር ነው። ህወሓት እና ጃዋር/ኦነግ ጥምረት የፈጠሩበት ምክንያት፤ አንደኛ፡- ሁለቱም ስር የሰደደ የስልጣን ጥማት እና የቁሳዊ ኃብት ፍላጎት ስላላቸው፣ ሁለተኛ፡- ሁለቱም የሙታን ፖለቲካ የሚያራምዱ የአብዮቱ ትውልድ ርዘራዦች በመሆናቸው ነው። በአጠቃላይ የህወሓት እና ጃዋር/ኦነግ ቅንጅት ላለፉት አርባ አመታት የመጣንበትን በጥላቻነ ቂም የታጨቀ፣ በግጭትና ጦርነት፣ እንዲሁም በጅምላ ፍረጃና ግድያ የሚታመስ፣ ያን ያረጀና ያፈጀ የሙታን ፖለቲካ ለማስቀጠል ያለመ ነው። በዚህ ምክንያት ገፈት ቀማሽ የሚሆነው ደግሞ አዲሱ ትውልድ ነው! የሙታን ፖለቲካ ያጣመራቸው የዕልቂት መልዕክተኞች የሁላችንም ስጋት ናቸው!

ሥርዓት አልበኞች ለፍርድ ይቀርባሉ!!! (የግሎባል አልያንስ መግለጫ)

የግሎባል አልያንስ መግለጫ

Global Alliance for the Rights of Ethiopians (GARE).

Global Alliance for the Rights of Ethiopians (GARE)

በቅድሚያ ስሞኑን በኢትዮጵያ ውስጥ በኦሮሚያ ክልል ሃላፊነት በጎደለውና “እኛ የቄሮን ጉልበትና አቅም አሳይተናል” እያለ የሚፈክረው አክትቪስት ነኝ ባዩ  ባስተላለፈው ጥሪ ተነሳስተው አብዛኛውንና ስላማዊውን የኦሮሞ ወጣት የማይወክሉ ሥርአት አልበኞች በስላማዊ ዜጎች ላይ ባደረሱት ብሄርና ሃይማኖት ተኮር ጭፍጨፋ በአስቃቂ ሁኔታ ህይወታቸውን ላጡ ፣ ለቆስሉና ቤት ንብረታቸው ለወደመባቸው ከቄያቸው ለተፈናቀሉ፣ ወገኖቻችን በሙሉ ለደረስባቸው ጥቃት ዘግናኚና ኢስብአዊ ጥቃት የተስማንን ልባዊና ከፍተኛ ሃዘን እየገለጽን ይህንን ከስበዓዊነትና ከኢትዮጵያዊነት ተፃራሪ የሆነ ግፍና አስቃቂ ድርጊት አጥብቀን እናወግዛለን።

ላለፍት 28  አመታት አፋኝና አምባገነናዊ በሆኑ የአገዛዝ ስርዓቶች ውስጥ የቆየችው አገራችን የዛሬ ሁለት አመት በህዝብ፤ በተለይ በወጣት ልጆቿ  ከፍተኛ መስዋእትነት ወደ ሌላ ምእራፍ ተሽጋግራለች። ይህ የሺዎች ህይወት የተገበረበት፣ በአስር ሺዎች የሚቆጥሩ ለእስር እና ለከፍተኛ እንግልት የተዳረጉበት ለውጥ በአገዛዝ ቁንጮ የነበረውን የህወሃት ቡድን ከፖለቲካና ከኢኮኖሚ የበላይነቱ ገሽሽ አድርጎ፤ አገሪቱን ከደም መፋስስ እድኖ ወደ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ጎዳና ይመሩናል በሚል እምነትና ተስፋ፤ አብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ ከገዢው ፓርቲ ከኢህአዴግ አብራክ ለወጡት የለውጥ ሃይሎች ድጋፍ በመስጠት መልካም ውጤቶችን  ሲጠባበቅ ቆይታል ። ለውጡን የሚመሩት ጠቅላይ ሚንስትር ዶ/ር ዐብይ አህመድ የዚህ ተስፋ ተምሳሌት ሆነው የተገኙበት ዋናው ምክንያት ኢትዮጵያዊነትንና ኢትዮጵያን ስላስቀደሙ ነበር። በመጀመርያው ቀን የፓርላማ ንግግራቸውና ከዚያም በኋላ ከኢትዮጵያዊያን ጋር ባደረጓቸው ውይይቶች ሁሉ ባለፋት የጭካኔ፤ የጭቆናና የምዝበራ አመታት ለተፈጸሙት የስብአዊ መብት ጥስቶች ሁሉ መንግስት እና ድርጅታቸው ተጠያቂ መሆናቸውን፤ ከዚህም አልፈው “እኛም ሽብርተኞች ነበርን፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ ይቅርታ ያድርግልን” በማለት ስሜቱ ተጎድቶ ለነበረው ህዝብ ትልቅ መጽናኛ ሆነዋል።

ሕዝቡም የፓለቲካ እስረኞቹ መፈታት፣ የፍትህ ተቋማትን ጨምሮ የሌሎች መንግስታዊ ተቋማት ለማጠናከር የተጀመረውን እንቅስቃሴ ከግምት በማስገባት በለውጡ ላይ እና ለውጡን በሚመሩ ስዎችም ላይ ትልቅ ተስፋ ስንቆ ነበር። ይሁን እንጂ ብዙም ሳይቆይ በቡራዩ ከተማ የተፈጸመው በማንነት ላይ ያነጣጠረ የጅምላ ጭፍጨፋ ለብዙ ዜጎች በአስቃቂ ሁኔታ ሕይወት መጥፋት ምክንያት ሆናል። ብዙዎቹም የአካልና የስነልቡናዊ ቀውስና ጉዳት ደርሶባቸዋል። ከቤትና ከንብረታቸው የተፈናቀሉትም ቁጥራቸው ቀላል አልነበረም። ይህ ግፍና ጭካኔ በቀላሉ የሚታይ አይደለም።  ነገር ግን ጥቃቱን ያቀነባበሩትና የመሩት የፓለቲካ  መሪዎችና ተጽዕኖ ፈጣሪዎች ለፍርድ ይቀርባሉ ተብሎ ቢነገርም ወንጀላቸው እስካሁን ድረስ በገለልተኛ ወገን እንዲጣራ አልተደረገም። ባለሥልጣናትም ሆኑ ጨፍጫፊዎቹ ሊማሩበት አልቻሉም። ወንጀልና ጭካኔ እንደ ልምድና እንደ ተራ ነገር ታለፈ። አሁንም እተደገመ።

እንደውም ይባስ ብለው ከጉዳዩ ጋር ምንም ግንኙነት የሌላቸውን የአዲስ አበባን ወጣቶች በግፍ በማስር ከአንድ ወር እንግልትና ስቃይ በሃላ “ሁለተኛ አይለመደንም ብለው” ከእስር እንዲለቀቁ ተደርገዋል። በጣም የሚያሳዝነው ደግሞ በቡራዩ ብሄር ተኮር ጥቃት ያደረጉት ወንጀለኞች በህግ ባለመጠየቃቸው ባለፋት ሁለት አመታት በርካታ ተመሳሳይ ጥቃቶች ተከስተዋል። በሚሊዮን የሚቆጠሩ ወገኖቻችን ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው ሲንገላቱ የከረሙበት አሳዛኝ ሁኔታ ተፈጥራል። በአገሪታ ውስጥ የታየው ስርአተ አልበኝነት እና የህግ የበላይነት መፋለስ እያደር አድማሱን አስፍቶ እና በተደራጁ አክራሪዎችና ጽንፈኞች እየተገፋ ዛሬ አገሪቱ የተጋረጠባትን ቀውስ ፈጥራል። በስሞኑም ያየነው መንግስት ቀለብ ከሚስፋርላቸውና ጥበቃ ከሚደረግላቸው መካከል አንዱ አክቲቪስት ተብየው  ያስራጨውን ጥሪ ተከትሎ በደብረዘይት፣ በእዳማ፣ በአሪሲ፣ በባሌ ሮቢና በዶዶላ፣ በሃረር፣ በድሬደዋ፣ እና በአዲስ አበባ ዙሪያ ሥርአተ አልበኛ ቡድኖች ባደረሱት ጥቃት ወገኖቻችን በአስቃቂ ሁኔታ የተገደሉና በመቶዎች የሚቆጠሩ ከባድና ቀላል የመቁስል አደጋ የደረስባቸው መሆኑን ቤት ንብረታቸው የተቃጠለባቸው እና በአሁኑ ስአት መውደቂያ የሌላቸው ወገኖቻችን እጅግ በርካታ መሆናቸውን በመገንዘብ አለም አቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያውያን መብት (ግሎባል አልያንስ) እንደተለመደው ዲያስፓራውን አስተባብሮ የወገን አለኝታነታቸውን በተግባር እንዲያሳዩ የሚከተሉት እርምጃዎችን ለመውስድ በቁርጠኝነት መወስኑን ለመላው የኢትዮጵያና ለአለም ህዝብ ይገልጻል ።

1- የጠ/ሚንስትር ዶ/ር አቢይ አህመድ መንግስት ዋንኛው ተቀዳሚ ተግባሩ የህግ የበላይነት ማረጋገጥ የዜጎችን ህልውና በስላም የመኖር ዋስትና ማረጋገጥ ሊሆን ይገባል ሆኖም እስካሁን በተከታታይ እየታየ ያለው ሁኔታ የተለየ ገጽ ያሳያል። ለምሳሌ ወንጀለኞች፣ ነፍስ ገዳዮች፣ ደብዳቢዎች፣ ብሄርና ሃይማኖት እየለዩ ግጭት የሚፈጥሩ ጠብ አጫሪዎችና ሚዲያ እየተጠቀሙ ግጭቶች እንዲከስቱ፣ ባንኮች እንዲዘረፋ የሚቀስቅሱ ግለስቦችና ቡድኖች ተጠያቂ አልሆኑም። በተገላቢጦሽ አንዳንድ የፌዴራልና የክልል ባለስልጣናት “እንክብካቤም” ሲያደርጉም ይስተዋላል የተጎዱት ወገኖች አድላዊ በሆነ ደረጃ ግፍና በደል ሲደርስባቸው ይታያሉ ። ይህ ዘውጋዊና ፓለቲካዊ አድልዎ በአስቸካይ እንዲቆምና የሁሉም ዜጎች መብት በእኩልነት እንዲጠበቅ እንጠይቃለን ። ጠ/ሚንስትሩ መንግስትና የሚመሩት ገዢ ፓርቲ ማንኛውንም የመንግስት ባለስልጣን በአደባባይ ቦታዎች ሃላፊነት የጎደላቸውን ንግግሮችን ዛቻዎች ከማድረግና ያልተናበቡ መግለጫዎችን በመስጠት የህዝቡ ስጋትና ጥርጣሬ እንዲጨምር ከማድረግ እንዲቆጠቡና የተጣለባቸውን ሃላፊነት በብቃት ባለመወጣታቸው ተጠያቂ እንዲሆኑ አበክረን እናሳስባለን።

2- በመንግስት የሚወስደው እርምጃ እንደተጠበቀ ሆኖ በኛ በኩል ማንኛውም ግለሰብ፣ ምሁር፣ ቡድን፣ ወጣቶች፣ በግል ሆነ በጋራ በብሄራቸው ተደራጅተው የሌሎች ብሄር ተወላጆች በሚኖሩበት አካባቢ በመሄድ ብሄርና ሃይማኖት ተኮር ግጭት በማስነሳት ዜጎች ሃብትና ንብረት አፍርተው ከሚኖሩበት ቦታ በመሳሪያ፣ በዱላ፣ በገጀራ፣ እና በድንጋይ የዜጎችን ህይወት ያጠፋትን፣ ያቆስሉትን፣ ያፈናቀሉትን፣ ቤት ንብረታቸውን ያቃጠሉትን ግለሰቦች በደረስን መረጃ መስረት በማድረግ አለም አቀፍ ጠበቆችን በማስባስብ ለአገር ውስጥና ለዓለም አቀፍ ፍርድ ለማቅረብ መወስናችንና በዝግጅት ላይ መሆናችንን ማሳወቅ እንወዳለን።

3- ማንኛውም ግለሰብ የፈለገውን እምነት የመከተል መብቱ በአለም አቀፍ ህግ የተጠበቀ ቢሆንም ከ50 ሚሊዮን በላይ ተከታዮች ያሉት የኢትዮጵያን ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አገልጋዮች ያረዱትንና አብያተክርስቲያናትን ያቃጠሉትን፣ ምእመናን አስገድደው የደፈሩትን እና በአንዳንድ መስጊዶችም ላይ ጉዳት ያደረሱትን ወንጀለኞች ለፍርድ እንዲቀርቡ ጥረት እናደርጋለን።

4- ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት እንደተጠበቀ ሆኖ ሃላፊነት በማይስማቸውና ሚዛናዊነት የጎደለው የሃስት ወሬ በሚያስራጩ ሚዲያዎች በተለይም ብሄር ከብሄር፣ ሃይማኖት ከሃይማኖት እንዲጋጩ ቅስቀሳ በሚያደርጉ የሚዲያ ተቃማት ሃላፊዎችና ባለሙያዎች አስራራቸውን እንዲመረምሩና እንዲያስተካክሉ እያስገንዘብን በፌስቡክ፣ በቲውተር፣ በዩቲዩብና በመሳስሉት ሚዲያዎች ተጠቅመው ህዝብን የሚያውክ ስራ የሚስሩትን በመከታተልና በማጋለጥ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ጋር በመተባበር ተገቢ እርምጃ እንዲወስድባቸው ተግተን እንስራለን።

5- በቅርቡ በተቀስቀሱ ብሄር ተኮር ጥቃቶች ለሞቱት ቤተስቦች፣ ለቆስሉትና ለተፈናቀሉት ወገኖቻችን እርዳታ የሚውል የጎ ፈንድ ሚ (gofundme) አካውንት ስለከፈትን ከዚህ በፊት በቡራዩና በጌዲኦ የተባበራችሁን ኢትዮጵያውያንና ትውልድ ኢትዮጵያውያን ሁሉ በአፋጣኝ ወገኖቻችሁን ለመርዳት እንድትረባረቡ በእግዚአብሔር ስም ጥሪያችንን እናቀርባለን። ለወገን ደራሽ ወገን ነውና ለጥሪው አፋጣኝ ምላሽ እንደምትስጡን እንተማመናለን።

በመጨረሻም ለምንወዳችሁ እና ለምናከብራችሁ አዋቂና ታጋሽ ለሆናችሁ ኢትዮጵያውያን በሙሉ “ሊነጋ ሲል ይጨልማል” እንደሚባለው እስካሁን ድረስ ያንን አስከፊ ግፍና መከራ በልበ ስፊነት፣ በተስፋና፣ በእምነት እንዲሁም በጽናት ታግስህ እንዳሳለፍከው ሁሉ ዛሬም መከራው ቢበዛም፣ ችግሩ የከፋም ቢሆንም የኢትዮጵያ አምላክ አይተዋትምና አይዛችሁ፣ በርቱ እኛ በውጪ ብንኖርም በመንፈስ ሁል ጊዜም ከናንተው ጋር ነን።

ከታገስነው ሁሉም ስለሚያልፍ ግሎባል አልያንስ ባለው አቅም ሁሉ ለወገኖቻችን ተስፋ ለመሆን የሚቻለውን ሁሉ ለማድረግ ያላስለስ ጥረት እንደሚያደርግ ልናረጋግጥላችሁ እንወዳለን የዜጎች ሕልውና እንዲረጋገጥና የሁሉም መብት እንዲከበር በመተባበርና በአንድነትና በቆራጥነት ዘብ መቆም የሁላችንም ግዴታና ሃላፊነት ነው።

ኢትዮጵያ በዜጎቻ ተከብራና በአንድነት ፅንታ ለዘላለም ትኑር!!!

ለበለጠ መረጃ፣ አለም አቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያውያን መብት (ግሎባል አልያንስ) ድህረ ገፅን ይከታተሉ
http://www.gofundme.com/RescueEthiopians

ከታላቅ አክብሮት ጋር
ታማኝ በየነ  ሊቀመንበር

ዛሬም የሀገር ያለህ! የሕዝብ ያለህ! – (ኢትዮጵያችን) ልሳን

የአንድ ሀገር! አንድ ሕዝብ! ኢትዮጵያችን ሕዝባዊ ንቅናቄ (ኢትዮጵያችን) ልሳን

ኢትዮጵያችን ቅጽ 4 ቁጥር 1                                                     ጥቅምት 17 ቀን 2012 ዓ.ም.

ዛሬም የሀገር ያለህ! የሕዝብ ያለህ!

የድምጽ ቅጂውን ለማድመጥ እዚህ ይጫኑ https://www.youtube.com/watch?v=0LGrl5BLR2s )

“ፍቅር ያስታግሣል፣ ፍቅር ያስተዛዝናል፣ ፍቅር አያቀናናም፣ ፍቅር አያስመካም፣ ፍቅር አያስታብይም፣ ብቻዬን ይድላኝ አያሰኝም፣ አያበሳጭም ክፉ ነገር አያሳስብም፤ ከእውነት ጋር ደስ ይለዋል፤ እንጂ ስለ አመፃ ደስ አይለውም፤ ሁሉን ይታገሳል፣ ሁሉን ያምናል፣ ሁሉን ተስፋ ያደርጋል፣ በሁሉ ይጸናል።” የመጀመሪያይቱ የሐዋርያው የጳውሎስ መልእክት ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች ምዕ. ፲፫ ቁ. ፬-፯

በቅድሚያ በመላው ሀገራችን የተለያዩ አካባቢዎች በቅርቡ በተነሳው የጀዋር መሀመድ ቄሮዎችና ዘረኞች ዱላ ሕይወታቸውን ላጡ ወገኖቻችን የተሰማንን እጅግ ጥልቅ ሀዘን እንገልጻለን፡፡ ቤተሰቦቻቸው፣ ወዳጅ ዘመዶቻቸው፣ እንዲሁም መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ በዚህ ዘግናኝና አሳፋሪ ድርጊት ሳትደናገጡ እምነት፣ ተስፋና ጽናት ተላብሳችሁ ሀገርና ሕዝብ ለማዳን “የሀገር ያለህ! የሕዝብ ያለህ!” እንባባል፡፡

ሀገራችንን የተለያዩ ቋንቋ ተናጋሪ ጎሳዎች/ነገዶች ስብስብነቷ ነው ኢትዮጵያ ያሰኛት። አማራ  እኔ ኦሮሞ አይደለሁምና የኢትዮጵያ ክፍል አይደለሁም ቢል ይህን በማለቱ የኢትዮጵያችን ግዛት መሆኑ ይቀራልን? ኦሮሞ እኔ ትግሬ አይደለሁምና የኢትዮጵያ ግዛት አይደለሁም ቢል ይህን በማለቱ የኢትዮጵያ ግዛት መሆኑ ይቀራልን? ሀገር ሁሉ ትግራይ ቢሆን አፋር ወዴት በተገኘ? ሁሉም አፋር ቢሆን ሲዳማ ወዴት በተገኘ? ይሁን እንጂ የተለያዩ ቋንቋ ተናጋሪዎች ጎሳ/ነገዶችን ኢትዮጵያ ሀገራችን አንድ አድርጋ ይዛለች። ሁሉም አንድ ብሄር/ነገድ/ጎሳ ቢሆኑስ ኢትዮጵያችን ወዴት በሆነች? ዳሩ ግን ጎሳ/ነገዶች ብዙዎች ናቸው ሀገር ግን አንድ ናት፤ ኢትዮጵያ። ትግሬ ቤኒ ሻንጉልን አታስፈልገኝም ሊለው አይችልም ወይም ኦሮሞ ደግሞ ደቡብ ህዝብን አታስፈልጉኝም ሊላቸው አይችልም። እንደውም ጎልተው ያልታዩ “ደካሞች” የሚመስሉ  የኢትዮጵያችን ጎሳ/ነገዶች ይልቁን የሚያስፈልጉ ናቸው። ከሀገራችን ጎሳ/ነገዶች ያልከበሩ ሆነው የሚመስሉን በሚበዛ ክብር ልናለብሳቸው ይገባል። በሁሉም ጎሳ/ነገዶች ከቶም ልንኮራና  ክብር ልንሰጥ እያንዳንዱ ጎሳ/ነገድ ሃላፊነት ሊኖረው ይገባል። ጎሳ/ነገዶች እርስ በርሳቸው በትክክል ይተሳሰቡ ዘንድ እንጂ በዘርና ቋንቋ መለያየት፣ ድንበር ማስመር እንዳይሆን ለተጎዳው ጎሳ/ነገድ የሚበልጥ ክብር፣ ትኩረት እየተሰጠ ሁሉንም አገጣጥመን በአንድ ኢትዮጵያ! በአንድ ሀገር! በአንድ ሕዝብ! ተጋግዘን መኖር ይገባናል፡፡ አንዱ ጎሳ/ነገድ ቢሰቃይ ሁሉም ጎሳ/ነገዶች ሁሉ ከእርሱ ጋር ይሰቃያሉ፣ አንድ ነገድ/ጎሳ ቢከበር ሁሉም ጎሳ/ነገዶች ሁሉ ከእርሱ ጋር ደስ ይላቸዋል።  ሁላችንም የኢትዮጵያ ልጆች ነንና የዚህ ጊዜ ኢትዮጵያችን ትበለጽጋለች፣ ታብባለች። ሁሉም ተደጋግፈው ያሉ ናቸውና አንዱን ከሌላው ገንጥሎ ሀገርም አይኮን፤ ኢትዮጵያም አይባል፤ አብሮ መውደቅ እንጂ።

ለሁላችንም ዋልታና ምሰሶ ኢትዮጵያችን ብትሆንም ኦሮሞ ያለ አማራ ቅጠሉ የረገፈ ተክል ነው፣ ትግሬ ያለ ኦሮሞ መሠረቱ ይናጋል፣ አማራ ያለ ሁሉም ጉራ ብቻ ነው፡፡ ኢትዮጵያ እንደ ሀገር ለዘላለም ትኑር! ስንል ኦሮሞን አሻም አሰኝታ፣ አማራን አስፎክራ፣ ትግሬን አስጨፍራ፣ ጉራጌን ቆጮ ብላ፣ በባሌ ሶፎሞር ኮርታ፣ ሐረር ግምብን አጠንክራ፣ ግመሏን ለአፋር አደራ ሰጥታ፣ አዲስ አቤን እምብርቷ አርጋ፣ በእስላምና ክርስቲያኑ ፀሎት ተጠብቃ ሌላም ሌላ እንደሚሆን ልንረዳ ይገባናል።

በኢትዮጵያ ሀገራችን የነፃነት ጮራ ይፈነጥቅ ዘንድ፣ ሕዝብ የሰውነት መብቱ ይከበርለት፣ በጥቂቶች ስግብግብነት በረሀብ እንዳይቀጣ፣ እንደ ቅደም ተከተላቸው በትምህርት፣ በሥራ፣ በህክምና እጦት እንዳይደነቁር፣ እንዳይቦዝን፣ ለበሽታ እንዳይዳረግ ሕዝብና ወጣቱ በትንሹ ለግማሽ ምዕተ ዓመት ታግለዋል። እጅግ ጎልቶ የወጣው የወሎ ረሃብ ለዘውድ ሥርዓት መውደቅ የደመቀ ምክንያት ሆኖ ዑ! ዑ! ያሰኘውን ደርግ አስከትሎ ሀገራችን አንድ ትውልዷን አጣች። ለትሻል የታገለን ትውልድ ትብስ ክላሿን አቀባብላ ለቀመችው። የደርግ ልቅ ያጣ ጭፍጨፋና ጦረኝነት ያስመረረው ሕዝብ ዕድሜውን አሳጥሮት ተገላገልኩ ሳይል ሕዝብን በቋንቋና በዘር ከፋፍሎ የሚያባላ፣ የሀገር አንድነት ተረት የሆነበት፣ የሀገር ያለህ! የሕዝብ ያለህ!” የሚያሰኝ ትባባስ ዘረኛ አገዛዝ ሀገር እያመሰ ይገኛል።

መጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ.ም. በተሃድሶ “ለውጥ” ስም ኢሕአዴግን ሊያስቀጥሉ የጠቅላይ ምኒሥትርነቱን ቦታ የተረከቡት ዶክተር ዐቢይ አሕመድ የህወሓት/ኢሕአዴግን የመጨረሻ ምዕራፍ አስፈፃሚ እንዳይሆኑ ልናስገነዝብ እንወዳለን። ጠ/ሚሩ እሰየው ተብለው ያልተጨበጨበላቸውን ያህል “ይህችን ሀገር ወዴት እየወሰዷት ነው?” ጥያቄ እያጫሩ እንደሆን ማስገንዘብ እንወዳለን። ይህንን ስንል አየር የሞቀውን፣ የቤተ መንግሥት ሳይሆን የአደባባይ ምስጢር፣ በመላ ሀገሪቷ እያንኳኳ ያለውን ዱላ ለተመለከተ፤ መንግሥት እራሱ የዱላው አቀባይ መሆኑን ቢጠቁም አያስደንቅም። ንብረት ሲዘረፍ፣ ሲቃጠል፣ የሰው ልጅ ሲታረድ፣ ሲሰቀል፣ አብያተ ክርስቲያን ሲቃጠሉ፣ መንገድ ሲዘጋጋ፣ ምስማርና ዱላ ሲውለበለብ የአገዛዙ ፌደራል ይባል ልዩ ኃይል ዳር ቆሞ ሲታዘብ ላየ ለውጡ ለካ ሥርነቀልነቱ ሀገር ለመበተን እንደሆነ ቢጽፍ፣ ቢናገር ምን ያስደንቃል? አዎ! ሲጀመርም የኢሕአዴግን ሕገ መንግሥት ይዞ ለውጥ ሊያመጣ ለተነሳ ቡድን፤ አንቀጽ 39ን  ተግባራዊ ለማድረግ ቢሠራ ማድመጥ ያቃተን እኛው ነንና ወደ ተግባራዊነቱ ፍፃሜ ላይ ሲንደረደር ሀገር እንዳትፈርስ፣ ሕዝብ እንዳያልቅ ከተፈለገ፤ በኋላ ሳይሆን ዛሬውኑ “የሀገር ያለህ! የሕዝብ ያለህ!” እምንልበት የመጨረሻው ሰዓት ላይ እንገኛለን።

“የምትፈልጉትን ነገር ለማግኘት ድንጋይ መወርወር አያስፈልግም፣ በእርጋታና በትዕግሥት ከሄዳችሁ አያቅታችሁም” የተባለላቸው ዘረኞች ሰንደቅ ዓላማ ሲያቃጥሉ፣ የእኛ አይደላችሁም እየተባሉ ዜጎች ከቄያቸው ሲፈናቀሉ፣ የታዘበ መንግሥት “ኢትዮጵያ አትፈርስም” እያለ ሕዝብና ልጆቹ በየቀኑ ሲፈጁ እየሰማን፣ እያየን እንዴት “ግዴላችሁም” እንባላለን? እውን የኢሕአዴግ ውስኪ ጠጭዎች ከሆኑ ይህን የሚያስደርጉት አሁንም የመንግሥት አውታር በእጃቸው ነውና ለውጡ ከሰንደቅ ዓላማ አልፎ ሀገርና ሕዝብ ሊያቃጥል አኮብኩቧልና “የሀገር ያለህ! የሕዝብ ያለህ!” እንላለን።

ኢትዮጵያ ሀገራችን ዛሬ ወደ እርስ በርስ መተላለቅ እንዳትገባ እጅጉን የሰጋንበት ወቅት ነው። የእርስ በእርስ አልነው እንጂ በቀጥታ ለመናገር የእልቂቱ ጅራፍ ከአንድ ወገን እየጮኸ እንደሆነ በዚህ አንድ ዓመት ተኩል ጉዞ በተለይ ደግሞ ከሰሞኑ የሀገሪቷ ሁኔታ መረዳት ያቃተው ጠ/ሚሩ እንዳሉት ቃሉን እንድገመውና “የደነቆረው” ኢሕአዴግና ዘረኛው ቡድን ብቻ ነው። በግልጽ ለመናገር ኦርቶዶክስ ሃይማኖት፣ አማራና ምኒልክ ታሪክ ላይ ያነጣጠረው ኢትዮጵያን የመበታተን ዘመቻ ሀገር ላይ እየጨፈረ፣ ሕዝብን እግዚዮ እያሰኘ በአለበት ወቅት የመደመር ፍልስፍና ሀገርና ሕዝብ እየቀነሰ መሆኑን ልንገነዘብ ይገባናል።

ኤርትራና ኢትዮጵያን አስታርቀው የኖቤል ተሸላሚ የሆኑት ጠ/ሚር ምነዋ ኦሮሞን፣ አማራ፣ ትግሬን፣ ምሥራቁን፣ ደቡቡን፣ አዲስ አበቤውን አንድ የማድረግ ጥበቡ ተሳናቸው? ሥልጣን እንደጨበጡ የጎረፈላቸው ከኖቤልም ኖቤል የሆነ የዕልልታና የጭብጨባ ሽልማት ለሀገር አንድነት ለሕዝብ ደህንነት እንደነበር ምነዋ አልሰማ አላቸው? ይህን ሕዝባዊ ሽልማት ወዲያውኑ ተጠቅመው ዘረኝነት ላይ አነጣጥረው፣ አንቀጽ 39ን ቀደው ቢሆን አክሊላቸው እምዬ ኢትዮጵያ ነበረች። “እናንት ውስኪ ጠጪ ኢሕአዴጎች የተራቡ ሕፃናት እንዳሉ አትዘንጉ” ያሉት ጠ/ሚር አገዛዞ ፈቃድ ሳይኖረው ዱላ በምስማር ይዞ ሰልፍ ለሚወጣው፣ ብሎም ባንክ ሲዘረፍ፣ ንብረት ለሚያቃጥለው፣ ነዋሪ ለሚገድለው ዝምታ ሲለገሰው ምነዋ በሥነ ሥርዓትና በአግባቡ ለጥቅምት 2 ቀን 2012 ዓ.ም. ለሰልፍ አቤቱታ ያቀረበውን የአዲስ አበባ ሕዝብ አስራቡት ቢባሉ ምላሾ ምን ይሆን?

“አዲስ አበባ ኬኛ” በሚልና በማስፈራራት የ“ኦሮሚያ” ለማድረግ የሞከረውን ኃይል “ባልደራስ” ከአዲስ አበባ ሕዝብ ጋር ባይጋፈጥ ዛሬ ሌላ አፀያፊ ታሪክ በተሠራ። “ባልደራስ” ላይ ጦርነት ታወጀ። ቀጠለ በመፈንቅለ መንግሥት ተውኔት በባህርዳርና አዲስ አበባ ካለቁት ወገኖች በቀጣይነት አማራው ላይ ያነጣጠረ እስርና ፍጅት እውን ሕዝብ እያደመጠው፣ እየታዘበው እንደሆን ከተረዳነው ለውጥ አራማጁ ሕዝብን ለቂምና ተቃውሞ እየጋበዘ እንደሆነ ሊረዳው ይገባል። የአዲስ አበባውን የ “ባልደራስ” አመራርንና አባላትን ማዋከብ፣ ማሠር በአዲስ አበባ ሕዝብ ብቻ ሳይሆን በሀገር ወዳዱ የኢትዮጵያ ሕዝብ ዘንድ እየተሰማ፣ እየታየ ያለ የየዕለት መነጋገሪያ እንደሆነ ለውጥ አራማጆች ሰምታችኋልን? እውን ለውጥ ማራመድ ኢሕአዴግ/ህወሓት ያሠረውን ፈትቶ ሥልጣን ሲደላደል አትቃወሙኝ ብሎ ሙዚየም ሊሆኑ የታሰቡ እስር ቤቶችን ሥራ አለማስፈታት ከሆነ ትርግሙ አዬ! ዴሞክራሲ፣ ድንቄም ለውጥ ያሰኛል።

ደርግ እርጉዝ ማሠር ብቻ ሳይሆን ለመግደሉ ዳሮ ነጋሽ ምስክር ናት፣ የኢሕአፓው ብርሃነ መስቀል ረዳ ባለቤት ታደለች ኃይለሚካኤል ነፍሰ ጡር ሁና እስር ቤት መገላገሏ ከታሪክ ማህደር ይገኛል። ወያኔም የእስክንድር ነጋን ባለቤት ሰርካለም ፋሲል በነፍሰ ጡርነቷ ሳያዝን እስር ቤት እንድትገላገል ፈርዶባታል። እና! እናማ ታሪክ ሲደጋገም ዛሬም የጄነራል አሳምነው ጽጌ ባለቤት ወ/ሮ ደስታ አሰፋ ነፍሰጡርነታቸው እየታወቀ በእሥር ይማቅቃሉ። አይ! የሴቶች መብት አስጠባቂ ለውጥ አራማጅ ቢባል “ሃቅ አያንቅ” ካልሆነ በቀር እውነቱ ይህ ነው።

ውድ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሆይ!

የዛሬ 123 ዓመት ኢጣሊያን ኢትዮጵያን ሊወር ሲነሳ እምዬ ዓፄ ምኒልክ ይህን ብለው ነበር

እግዚአብ በቸርነቱ እስካሁን ጠላት አጥፍቶ አገር አስፍቶ አኖረኝ፤ እኔም እስካሁን በእግዚአብሔር ቸርነት ገዛሁ፡፡ ከእንግዲህ ብሞትም ሞት የሁሉም ነውና ስለእኔ ሞት አላዝንም፡፡ ደግሞ እግዚአብሔር አሳፍሮኝ አያውቅም፤ ወደፊትም ያሳፍረኛል ብዬ አልጠራጠርም፡፡ አሁንም አገር የሚያጠፋ፤ ሃይማኖትን የሚለውጥ፣ በፊት እግዚአብሔር የወሰነልንን ባህር አልፎ መጥቷል፡፡ እኔም የአገሬን ከብት ማለቅ፤ የሰውን መድከም አይቼ እስካሁን ዝም ብለው ደግሞ እያለፈ እንደፍልፈል መሬት ይቆፍር ጀመር፡፡ አሁን ግን በእግዚአብሔር ረዳትነት አገሬን አሳልፌ አልሰጠውም፡፡ የአገሬ ሰው ከአሁን ቀደም የበደልሁህ አይመስለኝም፡፡ አንተም እስካሁን አላስቀየምኸኝም፡፡ ጉልበት ያለህ በጉልበትህ እርዳኝ። ጉልበት የሌለህ ለልጅህ፣ ለምሽትህ፣ ለሃይማኖትህ ስትል በሃዘንህ እርዳኝ፡፡ ወስልተህ የቀረህ ግን ኋላ ትጣላኛለህ፡፡ አልምርህም፡፡ ማርያምን ለዚህ አማላጅ የለኝም። ዘመቻዬ በጥቅምት ነውና የሸዋ ሰው እስከ ጥቅምት እኹሌታ ወረይሉ ከተህ ላግኝህ።

ይህ መልዕክት አሁን ኢትዮጵያችን ባለችበት ወቅታዊ ሁኔታ ወደ አላስፈላጊ እልቂት እንዳታመራ ካስፈለገ ድጋሚ ሊያቃጭልብን ይገባል። የጥንቱ ባህር አልፎ የመጣ ሲሆን የአሁኑ በሀገር በቀልና በባዕዳን ጥምር ተልዕኮ የተቀነባበረ መሆኑ ነው። ዛሬ ሀገር ሊያፈርስ፣ አረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀይ ሰንደቅ አላማችንን እያቃጠለ የመጣው ኃይል፣ ቤትና ንብረት ሲያቃጥል እያየን ነው፣ ዱላና ሜንጫ የንፁሐንን ሕይወት እየቀጠፈ ነው። ሕዝብ ላይ የተሠነዘረው ጥቃት ተጀምሯል። በመላው ሀገሪቷ ይህ ዕልቂት እንዳይዛመትና ሙሉ በሙሉ ይቆም ዘንድ፣ እጅግ ዘግናኝና አሳዛኝ ፍጅት በኢትዮጵያችን እንዳይከሰት የሃይማኖት አባቶችና አማኞች በፀሎት፣ የብዙሃን ማህበራትንና ፖለቲከኞች በአንድነት፣ መላው ሕዝብ በጋራ ለእራሱና ለሀገሩ ሲል ነቅቶ መጠበቅ የሚገባው ወቅት ላይ ደርሰናልና “የሀገር ያለህ! የሕዝብ ያለህ!” እንባባል።

ሁኔታዎች ከቁጥጥር ውጭ ሁነው ዘግናኝ እልቂት በሀገራችን ላይ ከተከሰተ በኋላ “ይህ ቢሆን ኑሮ” አዋጭ አይደለም፡፡ ንፁሓን ወገኖቻችን እያለቁ የምናበቅለው ፀፀት እጅጉን ከባድ ነውና አሁኑኑ ሀገርና ሕዝብ ለማዳን እንዘጋጅ።

ህወሓት ለ28 ዓመት የተከለው የዘረኝነት ችግኝ ዛሬ ፍሬ አፍርቶ በተለይ የኦሮሞን ጥያቄ የትውልዱ አስመስሎታል ቢባል ሚዛን ይደፋል። ይህ የሀገርና ሰንደቅ ዓላማ ጥላቻ ገና ከጥንስሡ በተለይ በየትምህርት ቤቱ፣ በየመንደሩ ብሎም በቤተሰብ ደረጃ የተካሄደው ወያኔያዊ ዘመቻ ዛሬ የኦሮሞ ወጣቶችና ጎልማሶች ወገኖቻችንን ያሳተ ቢመስልም የአንድነት ኃይሉና የኢትዮጵያ ሕዝብ “የሀገር ያለህ! የሕዝብ ያለህ!” ተባብሎ ከተነሳ ዘረኝነትን አምክኖ ከኦሮሞ፣ ከትግራይ፣ ከአማራ በጥቅሉ ከደቡብ፣ ከምሥራቅ፣ ከምዕራብ፣ ከሰሜን፣ ከአዲስ አበባ ሕዝባችን ጋር ተቃቅፈን ዘመቻችን ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን ለተላበሰች ኢትዮጵያ፣ ሁሉንም ልጆቿን በአንድነትና በጋራ ለምትቃኝ ሀገራችን ዕድገትና ብልጽግና እንደሚሆን ጥርጣሬ አይግባን። እኛ፣ ሁላችን አንድ ከሆንን ኃይልና ሥልጣን የሠፊው ሕዝብ መሆኑን እናሳያለንና ዛሬም “የሀገር ያለህ! የሕዝብ ያለህ!” እንባባል።

ለተከበሩ ጠ/ሚር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ

በቅድሚያ በቅርቡ የ 2012 ዓ.ም. የኖቤል ተሸላሚ በመሆኖ እንኳን ደስ አሎት እንላለን። ሽልማቱን የሠጠው አካል ምክንያቱን የኤርትራና ኢትዮጵያ ሀገሮችን ከማቀራረብ ጋር ማያያዙን አድምጠናል። በአንድ ዓመት ከስድስት ወር በኢሕአዴግ አባልነቶና የሀገሪቷ ጠቅላይ ሚንስትርነት ያበረከቷቸው በጎ ጎኖች ቢኖሩም ሀገራችንና ሕዝባችን በየቀኑ እያጋጠማቸው ካለው ሰቆቃ፣ የፍርሃት ኑሮ፣ የኑሮ ውድነት፣ ወዘተ አንፃር እጅጉን እያዘንን ነው።

አሁን ሀገራችን ያለችበትን ተጨባጭ ፖለቲካዊ ሁኔታ ስንመለከተው እውን የመንግሥት ኃይልና ሥልጣን ካለዎት ዝምታ አዋጭ አይደለም፡፡ ሰሞኑን በጀዋር መሀመድ አስተባባሪነት ቄሮ በሚባሉ ዘረኛ ቡድኖች በተለይ አማራውና ቤተ ክርስቲያን ላይ ያነጣጠረ ፍጅትና ቃጠሎ ሲካሄድ ዝምታዎ አስገራሚና አስተዛዛቢ ነው፡፡

ከዓመት በፊት በአዲስ አበባ ዙሪያ ለገጣፎ በተነሳው ዕልቂት አልሰማሁም ያሉትን በቀጣይነት እየደጋገሙት በሚመስል ደረጃ የሕዝብና የልጆቹ እልቂት ከወሬ በዘለለ የወሰዱት መንግሥታዊ እርምጃ አልታየም፡፡ ሕዝብ እየታረደ ምላሹ “ኢትዮጵያ ታላቅ ሀገር ነች” ሳይሆን ለታላቅነቷ አጥፊዎችን፣ አሸባሪዎችንና ገዳዮችን ወደ ፍርድ ማቅረብ ነው፡፡ ከመንግሥት በላይ ሀገር እያመሰና ማን ተናግሮኝ ባዩ ጀዋር መሀመድን ከለላና ጥበቃ ሰጥቶ ደም ማፍሰስ እጅጉን አሳፋሪ ነው፡፡

በተጨማሪ፦

  • በሩሲያ ጉብኝቶ ወቅት በሀገራችን በተለያዩ አካባቢዎች የደረሰውን እልቂት ሲሰሙ በአፋጣኝ ጉብኝትዎን አቋርጠው አፋጣኝ አመራር መስጠት ሲገባዎ ምንም እንዳልተፈጠረ ጉብኝቶን ቀጥለዋል፣
  • ኢትዮጵያም ከተመለሱ በኋላ ይህንን በርካታ ቤተሰቦችንና ሕዝብን ያስተከዘ ሀዘን በቴሌቪዥን መስኮት ቀርበው ሀዘኔታዎን መግለጽ ብቻ ሳይሆን መንግሥት ሊወስድ የሚገባውን አፋጣኝ እርምጃ ሊያሳውቁ አልደፈሩም፣
  • የቄሮ መሪ ጀዋር መሀመድ በሀገሪቱ ያለው መንግሥት ሁለት ነው ከማለት አልፎ ሀገሪቱን ለእርስ በርስ ዕልቂት እያዘጋጀና የኦሮሞ ወጣቶችን በዘረኝነት የጥፋት ዘመቻ ሲቀሰቅስ ቤትና ጥበቃ ሰጥተው ይንከባከቡታል፣
  • ጅዋር መሀመድ በድምጽ የተቀዳ መንግሥታዊ መረጃ አለኝ ሲል ከመንግሥት አካላት ጋር እየተመሳጠረ የሚያገኛቸው መረጃዎች እንዳሉ በአደባባይ እራሱ ላይ ሲመሰክር ድርጊቱ ሊታይ የሚገባው ወንጀል መሆኑን ሊገነዘቡት በተገባ፣
  • የአዲስ አበባ ወጣቶች ሲዋከቡ፣ እነ እስክንድር ነጋና የ“ባልደራስ” አባላት በሰላማዊ መንገድ ለጠየቁት ሰላማዊ ሰልፍ ክልከላ፣ በሚያደርጉት ስብሰባ በቄሮ ቡድኖች ወከባ ሲደርስባቸው እየሰሙ ዝምታን መርጠዋል፣

ብዙ መዘርዘር ይቻላል፡፡

አንድ ሀገር! አንድ ሕዝብ! ኢትዮጵያችን ሕዝባዊ ንቅናቄ” ሥልጣን እንደያዙ ድጋፋችንን ብንሰጥዎም “የቀን ጅብ በግ ላይሆን” ብለን ከጠቆምኖት ኢትዮጵያችን ቅጽ 3 ቁጥር 1 ልሳናችን (http://www.ethiopiachen.org/images/pdf/020511_1H1H-Ethiopiachin-Vol-3-No-1.pdf) ጀምሮ ድጋፋችንና ትችታችን ማድረግ ያለቦትንና ሊያጋጥሙ የሚችሉ ጥፋቶችን በመጠቆምና ያላመንበትንም በመቃወም ነበር። አንዳንድ ሰዎችና በተለይ እንደ ምሁርነታቸው ለትንሽ ጉዳይ የሚፈነጥዙ እስቲ እንያቸው፣ ጊዜ ስጧቸው፣ አትቃወሟቸው አባባል ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሳየን ያለው አዛውንትን፣ ህጻናትን፣ ወጣቶችን በጥቅሉ ዜጎችን እየቀጠፈና አውላላ ሜዳ ላይ እየበተነ ለመሆኑ እማኝ አያስፈልገውም፡፡ ግራና ቀኙን ማየት የተሳናቸው አንዳንድ ምሁራን ከሙያቸው ባሻገር በፖለቲካው መስክ እንደ ትላንቱ ዛሬም ሲያበላሹ ይታያሉ። ዛሬ ጎልቶ ለወጣው አስከፊ ዘረኝነት በአለፈው 28 ዓመት የብዕራቸው አሻራና የማጋጋል ድምፃቸው አስተዋጽዖ እንዳለው ዕድሜ ለሥልጣኔ በኮምፒዩተር መረጃ ለወደፊት አጥኝዎች “እነማን ነበሩ” ዝግጅትና የታሪክ ተመራማሪዎች የደለበ ሠነድ ነው።

ክቡር ጠ/ሚር የኢትዮጵያን አንድነት ለማስጠበቅ እጅግ ብዙ ብለዋል። እኛም ስለ ሀገር አንድነት፣ ዘርንና ቋንቋን ተገን ስለ አደረገ አከላለል አደገኝነት፣ ስለ ኢሕአዴግ ሕገ መንግሥት ማብቃት፣ ወዘተ ብዙ ብለናል፡፡ ይህ በቀደምት ትንታኔያችን እንደተጠበቀ አሁን ይችን ሀገር በአግባቡ እንደ መንግሥትነትዎ ያድኑ አለበለዚያ ለተማረረው ሕዝብ ይተዉለት፡፡ ሕዝባችን እንኳን ለሀገር ውስጥ አሸባሪ አይደለም በታንክና በአየር የመጣበትን ወራሪ ያሳፈረ እንደመሆኑ የሠራውን አኩሪ ታሪክ ዛሬም እንደሚደግመው ጥርጥር የለንም፡፡

የእርሶ “ኢትዮጵያ” ፉከራ ጉያዎ የወሸቁትን ጀዋር መሀመድና ሌሎች ሀገር በታኝ ዘረኞችን ካልተመለከተ ምኑን ሀገር ተኮነ? ምድር ላይ የምናየው ለእኛም ሆነ ለኢትዮጵያ ሕዝብ የተለየ ነው። ገና ሥልጣን እንደጨበጡ ኢትዮጵያን በ10 ዓመት ከአፍሪካ በዕድገትና በሥልጣኔ አውራ እናደርጋታለን ብለዋል፡፡ ዛሬም ዓመት ከስድስት ወር ቢቀነስለትም፤ ነገም አሥር ዓመት እየተባለ እንደማይቀጥል እርግጠኞች ነን። ይህ የዕድገት ትልሞ እሰየው ቢያሰኝም ዛሬ መብላት ያቃተው ቤተሰብ፣ ከምግብ እጦት የተነሳ ትምህርት መማር ያቃታቸው ሕፃናት፣ እጅግ የናረው የኑሮ ውድነት አይዘገንኖትም? እስቲ ልጆቾን አንድ ቀን ምሳ እንዳይበሉ ያርጓቸውና ስሜቱን ያስቡት።

በቅርቡ ከአወጡት የመደመር ፍልስፍና ጋር ለ10 ዓመት እንደሚገዙ እርግጠኛ የሆኑ ይመስላል። መጪውን ምርጫ ሳይዘነጉት መደመር ፍልስፍናን ዘላለማዊ ሕይወት ሊላበስ የተፈለገ ይመስላል።  ተቀበሉትም አልተቀበሉት ዛሬ ኢትዮጵያችን የሚያሳስባት ከፊቷ የተደቀነባት የዘረኝነት አደጋ ነው። ሕዝባችን በቅድሚያ ውሎ ማደሪያ ሀገሩን ይፈልጋል፡፡ የአዲስ አበባን ነዋሪ ጨምሮ በመላው ሀገራችን የስጋትና የፍርሃት ኑሮ ሕዝቡን እያሳሰበ ነው። በየቦታው የሚፈናቀሉ፣ የሚገደሉ ቁጥራቸው እየጨመረ ነው። በእርሶ አገዛዝ ሰንደቅ ዓላማችን እየተረገጠና እየተቃጠለ ይገኛል። አብያተ ክርስቲያናት እየተቃጠሉ፣ ምህመናን እየተገደሉ ነው። “ከእንግዲህ በፖለቲካ አቋሙ የሚታሠር የለም” ያሉትን ዘንግተው ዛሬም ያለ ፍርድ በርካታ ዜጎች ቤታቸው እስር ቤት ሁኗል። ወደ የትኛውም የሀገሪቷ አካባቢ ለመንቀሳቀስ በስጋት በመሆኑ የሀገር ውስጥ የንግድ እንቅስቃሴ እየተዳከመ ለመሄዱ የሚታየው የኑሮ ውድነት ምስክር ነው። በጀዋር የሚመራው የቄሮ ቡድን ያለፍቃድ እንዳሻው ሰልፍና ስብሰባ ያደርጋል፤ በሌላ በኩል ደንብና ሥርዓት ተከትሎ ሠላማዊ ሰልፍ የሚጠይቁ “ባልደራሶች” ይከለከላሉ፣ መንገድ ይዘጋባቸዋል፣ በስብሰባቸው ላይም ይወረራሉ፤ እውን ይህ እንቅልፍ ይሆኖታል?

እጅግ በርካታ ጉዳዮችን ማንሳት ቢቻልም እውን ለእናት ሀገራችን ኢትዮጵያ ቅን ሀሳቢ እስከሆኑ ከማንም በላይ የሕዝብ ሀብት አሎትና ከግብጽ ሳይሆን ከዘረኝነት ጋር ፍልሚያ ለመግጠም ይጠቀሙበት ብለን ቀደም ሲል አሳስበናል ዛሬም እንላለን። አልተጠቀሙበትም እንጂ የኦሮሞ ህብረተሰብ አንድነቱን ፈላጊ ነው፣ የትግራይ ሕዝብ በኢትዮጵያዊነቱ ኩሩ ነው፣ ደቡብ ለሰንደቅ ዓላማው በአንድነት ይጠብቆታል፣ ሐረሬው፣ አፋሩ፣ ጋምቤላው፣ አማራው ዴሞክራሲያዊ መብቱን አይንፈጉት፣ ከረሃብ ያላቁት እንጂ በሀገሩና በአንድነቱ አይደራደርምና “የሀገር ያለህ! የሕዝብ ያለህ!” ብለው ኢትዮጵያና ሕዝቧ ከተደቀነባቸው አደጋ ያላቅቁ ዘንድ ለማሳሰብ እንወዳለን። ጊዜ ቆሞ አይጠብቅምና ተሽቀዳድመው ይሳፈሩበት። የመንግሥትነቱን ሥልጣን የመጠቀም ችግር ካለብዎትም በአፋጣኝ ለሕዝባችን ግልጽ ያድርጉለትና አሁንም በግል እያደረገ ያለውን መሰባሰብና መደራጀት አጠናክሮ ሀገርና ሕዝቡን ከእልቂትና ከጥፋት ያድን ዘንድ ይተባበሩት፡፡ ይህ ተግባራዊ ካልሆነ የአዲስ አበባ ወጣትም ሆነ በየአካባቢው ያለው ወጣትና ሕዝብ አቃጣዮችን፣ በድንጋይ፣ ሜጫና፣ ዱላ ገዳዮችን የመመከትና የመቋቋም ብሎም የማሸነፍ ታሪክ እንደሚሠራ በእርግጠኝነት ልንገልጽልዎ እንወዳለን፡፡ ያለውንና ያንዣበበውን አደጋ ተቀብሎና ለሕዝብ ይፋ አውጥቶ የሀገሪቷ አንድነት የሕዝባችን ደህንነት ቅድሚያ ይሰጠው ዘንድ “አንድ ሀገር! አንድ ሕዝብ! ኢትዮጵያችን ሕዝባዊ ንቅናቄ” ድምጻችንን እናሰማለን።

ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!!!

ፈጣሪ ኢትዮጵያን ይባርክ!!!

“አንድ ሀገር! አንድ ሕዝብ! ኢትዮጵያችን ሕዝባዊ ንቅናቄ”

ጥቅምት 17 ቀን 2012 ዓ.ም. (October 28, 2019)

ማሳሰቢያ ፡

  • ውድ ወገኖቻችን ይህንን «አንድ ሀገር! አንድ ሕዝብ! ኢትዮጵያችን ሕዝባዊ ንቅናቄ» «ኢትዮጵያችን» ልሳን በተለይ በሀገር ቤት ኮምፒዩተር የማግኘት ዕድል ለሌላቸው በማባዛት ታሰራጩት ዘንድ ቀና ትብብራችሁን በትህትና እንጠይቃለን።
  • «አንድ ሀገር! አንድ ሕዝብ! ኢትዮጵያችን ሕዝባዊ ንቅናቄ» መስከረም 8 ቀን 2009 ዓ.ም. እራሱን ይፋ ያደረገ ሕዝባዊ ድርጅት ሲሆን የንቅናቄውን ማንፌስቶና ፕሮግራም ethiopiachen.org ከሚለው ድረ ገጻችን ማግኘት ትችላላችሁ።

ስልክ ፡ 703 300 4302

ኢሜል ፡ ethiopiachen2009@gmail.com

ድረ ገጽ ፡ www.ethiopiachen.org , www.ethiopiachen.com

ምሥለ ገጽ ፡ 1H1H Ethiopiachin

ከእውነት የበለጠ እውነት ኢትዮጵያን ያሻግራል – ዶ/ር ዘላለም እሸቴ

ኢትዮጵያን እንበታትናለን ብሎ ሲሰራ የነበረው ዕብሪተኛ ሰው ባለጊዜ ሆነና፥ ራሱ ብቻውን መንግስት ሆኖ መላውን ኢትዮጵያ እንደ ጎልያድ በማን አለብኝነት ሲያስጨንቅ የሚታይባት ምድር ኢትዮጵያ ናት።

አንድ ቤተሰብ የሆነውን የኢትዮጵያ ሕዝብ በክልል እያጠሩ ባላንጣ መንግስታትን ፈጥረው፥ ጨለማውን ብርሃን እያሉ ሲጠሩ የማይታፈርበት ምድር ኢትዮጵያ ናት።

ከነገድ ከቋንቋ ዋጅቶ በክርስቶስ ፍቅር አንድ ስለመሆን የሚሰብከው ሃይማኖት ተከታይ ነኝ እያሉ፥ በወንድማማች መካከል ጠብ የሚዘሩ ጉደኞች የሞሉባት ምድር ኢትዮጵያ ናት።

በመርህ ላይ ሳይሆን በዘረኝነት ላይ ብቻ ተመስርቶ የመንጋ አንድነት ያለው ፓርቲ፥ መላውን ኢትዮጵያ አንድ የሚያደርግበት ምሪት ይሰጣል ተብሎ ጉም የሚጨበጥበት ምድር ኢትዮጵያ ናት።

ወዶም ሆነ ተገዶ ሁሉም በየጎሳው ዙሪያ አንድነቱን አጠናክሮ እየተደራጀ ራሱን ለማዳን ሲዳክር፥ ራሱን ለእርስ በርስ ዕልቂት እያመቻቸ መሆኑ እየታወቀ፥ የ “ሰው” ነት ፖለቲካ ቦታ የማይሰጠው ምድር ኢትዮጵያ ናት።

እኩይ የሆነው ዘረኝነት ኢትዮጵያን ሊያሰጥም ጫፍ የደረሰበት ጊዜ ሆኖ ሳለ፥ ሩዋንዳ ልንሆን ነው ብሎ ከመፍራት ያለፈ፥ በማስተዋል ለመጠበቅ ምንም እርምጃ የማይወሰድባት ምድር ኢትዮጵያ ናት።

ይህ ሁሉ እውነት ነው። ግን ከዚህ እውነት የሚበልጥ ሌላ እውነት ደግሞ አለ።

የኢትዮጵያ መዳን ከእግዚአብሔር ዘንድ ነው!

ዕድሜ ልካችንን በመከራ ውስጥ አልፈን ስናበቃ፥ የብርሃን ጭላንጭል አሳይቶ እንቁልጭልጭ የሚጫወትብን ጨካኝ አምላክ የለንም። እግዚአብሔር በምድራችን የጀመረውን መልካም ሥራ ዳር ሳያደርስ መንገድ ላይ አይጥለንም።

እግዚአብሔር ያያል።
እግዚአብሔር ይፈርዳል።
ፈጥኖ ይፈርዳል።
በቀናት ውስጥ ክብሩን ይገልጣል።

ዲያብሎስ የደገሰልን የዕልቂት እኩይ ሤራ ይገለበጣል። ኢትዮጵያ ወጀቡን አልፋ ትሻገራለች። ታበራለች።

መከራ ያየነው ከዓለም በኃጢአት አንደኛ ስለሆንን አይደለም። የቃል ኪዳን ሀገር የሆንነው ከዓለም በፅድቅ አንደኛ ስለሆንን አይደለም። ያለፈው መከራችንም ሆነ የሚመጣው ጉብኝታችን ምክንያቱ የኢትዮጵያ አምላክ ክብር እንዲገለጥብን ብቻ ነው።

ጠላት ለኢትዮጵያ መበታተን ያጠመደው ክፉ ወጥመድ ለእኛ ጭንቀት ቢሆንብንም፥ ለፈጣሪ ክብሩን እንዲገልጥ ጥሩ አጋጣሚ ነው። ምድር ሁሉ በኢትዮጵያ አምላክ አለ እስኪል ድረስ ሥራውን ሊሰራ ፈጣሪ ራሱ ይወርዳል።
ወጥመዱን ይሰብራል።
ኢትዮጵያንም ያስመልጣል።

ከቅዱስ ቃሉ የተወሰደ፡
• የኢትዮጵያ ድንኳኖች ሲጨነቁ አየሁ
• አንተም የዘንዶውን ራሶች ቀጠቀጥህ፤ ለኢትዮጵያ ሰዎችም ምግባቸውን ሰጠሃቸው።
• ኢትዮጵያ እጆችዋን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች።

አጋጥሞ በነበረው የፀጥታ ችግር እጃቸውን ያስገቡ አካላት በህግ ሊጠየቁ ይገባል – የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ

ባሳለፍነው ሳምንት በሀገሪቱ አጋጥሞ በነበረው የፀጥታ ችግር እጃቸውን ያስገቡ አካላት በህግ ሊጠየቁ እንደሚገባ የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የበላይ ጠባቂ አሳሰበ።
የኢትዮጵያ የሀይማኖት ተቋማት ጉባኤ የበላይ ጠባቂ አባቶች ወቅታዊ ጉዳዮችን አስመልክቶ በዛሬው እለት መግለጫ ሰጥቷል።

በመግለጫቸውን ባሳለፍነው ሳምንት በሀገሪቱ ተፈጥሮ በነበረው አለመረጋጋት በሰው ህይወት እና በንብረት ላይ የደረሰው ጉዳት በምንም መመዘኛ ተቀባይነት የሌለው መሆኑን አስታውቋል።

ግጭቶቹ ከሰብአዊ ፍጡር በማይጠበቁ ድርጊቶች የዜጎች ህይወት እያለፈ ንብረትም እየወደመ መሆኑንም በመጥቃስ ጉባዔው፥ ተግባሩ በየትኛውም ሀይማኖት የተወገዘ እና የተጠላ መሆኑን ገልጿል።

የፀጥታ ችግሩን ሽፋን በማድረግ ግጭቱን ወደ ሀይማኖት ግጭት ለመቀየር የተደረገው ጥረትም በየትኛውም ሀይማኖት ዘንድ ተቀባይነት የሌለው መሆኑንም ጉባዔው አስታውቋል።

የፀጥታ ችግሩ ሃይማኖታዊ ገጽታ እንዲላበስ በማድረግ የሃይማኖት ተቋማትን እና የሃይማኖት መሪዎች ከጉዳዩ ጋር ግንኙነት የሌላቸው ንፁሐን ወገኖች በተለይም ሕፃናትና ሴቶች ፣እናቶች እንዲሁም አረጋውያንን ሠለባ ያደረገ
ጥቃት መፈፀሙም በመግለጫው ተነስቷል።

ሃይማኖታዊ ገጽታ እንዲላበስ በማድረግ እየተካሔደ ያለው ዘመቻ በሁሉም ሃይማኖቶች ተቀባይነት የሌለው ከመሆኑም በላይ ፍፁም ወንጀል በመሆኑ ሃሳቡና ተግባሩን እንደሚያወግዙት አስታውቀዋል።

በዚህ መሠሉ ተግባር ላይ የተሠማሩ ግለሰቦችም ሆኑ ቡድኖች ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ ያሳሰበው የበላይ ጠባቂው፥ በሰላም መደፍረሱ እጃቸውን ያስገቡ አካላት የሚመለከተው የፍትህ አካል በህግ ተጠያቂ ሊያደርጋቸው እንደሚገባም አሳስቧል።

መግለጫው አክሎም፥ የክርስትና እና የእስልምና ሃይማኖቶች በኢትዮጵያ ለዘመናት በመከባበርና በሰላም አብረው የኖሩ ወገኖች መሆኑን በመጥቀስ፥ የየሃይማኖቶቹ አስተምህሮም ሰላምን፣ መከባበርን፣ ፍቅርን እና በማኅበራዊ ትስስራችን ወንድማማችነትን እንድናፀና ያስተምራል፤ በአንፃሩ ጥላቻና ግጭት በሁሉም ሃይማኖቶች የተወገዙ ናቸው፤ በመሆኑም አሁን አሁን የሚታየውን ሀገራዊ ውጥረት ከሃይማኖት ጋር ለማያያዝና ሽፋን ለማድረግ የሚደረገው ሙከራ የየሃይማኖቶችን መሠረታዊ አስተምህሮ ካለመገንዘብ ወይም ከጭፍን ወገንተኛነት የመነጨ ስሜት መሆኑን በመረዳት ክርስቲያኖችም ሆኑ ሙስሊሞች እርስ በርስ በመደጋገፍ የሀገራቸውንና የየአካባቢያቸውን ሰላም በጋራ ነቅተው እንድትጠብቁም ጠይቋል።

የሀገሪቱ ብሄር ብሄረሰቦች እና ህዝቦች የረጅም ዓመታት አብሮ የመኖር እሴት ለጥፋት ሳይሆን ለፍቅር እና ለወንድማማችነት መንገድ የሚከፍት መሆኑንም ገልጿል።

በኢትዮጵያውያን መካከል መጥፎ ጠባሳ እየጣለ ያለው ሰሞናዊ ግጭት ከእምነትም ሆነ ከአብሮ የመኖር እሴቶች እና እሳቤዎች ጋር በእጅጉ የሚቃረን በመሆኑ ሁሉም ኢትዮጵያውያን እና አማኞች ለሰላም እና ለአንድነት ሊተጉ እንደሚገባ ጠይቋል።

የሁሉም ሀይማኖት ተከታዮች ፊታቸውን ወደፈጣሪያቸው በማዞር በሀገሪቱ ሰላም እንዲሰፍን ፀሎት እንዲያደርጉም የሀይማኖት ተቋማት ጉባዔ ጥሪ አቅርቧል።

የፌዴራልና የክልሎች መንግስታት ሀገርንና ሕዝብን ለመምራትና ለማስተዳደር የሚጠይቀውን ከፍተኛ ኃላፊነትና አደራ ተቀብላችሁ ሀገራችሁንና ወገናችሁን እያገለገላችሁ መሆኑ ይታወቃል ያለው ጉባዔው፥ ዘላቂ ሰላምንና ብሔራዊ መግባባትን በማጠናከር እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የበላይ ጠባቂ አባቶች በተፈጥሮ በነበረው አለመረጋጋት እና ግጭት ምክንያት የሰዎች ህይወት በማለፉ የተሰማቸን ሀዘን የገለጹ ሲሆን፥ ለሟቾች ቤተሠቦች፣ ወዳጅ ዘመዶች በሙሉ መጽናናትን ተመኝተዋል።

እንደሀገር እየታየ ያለው ያለመረጋጋት እና የግጭት አዝማሚያ ተወግዶ ችግሩ በዘላቂነት እንዲፈታና ወደሰላማዊ ሁኔታ እንዲመለስ፣ ሁከትንና ግጭትን ከሚያባብሱ ሀሳቦችና ድርጊቶች በመታቀብ ሁሉም የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲወጣም ጠይቀዋል።

ኤፍ.ቢ.ሲ

“ተከብቤያለሁ ብሎ ወደ ሕዝብ ከረጬው ግለሰብ ጀምሮ ጥፋተኞች ለፍርድ እእዲቀርቡ…” ከ ኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) የተሠጠ መግለጫ

የኢትዮጵያ ህዝብ ለቀረበለት አገርን የማዳን ጥሪ በሕብረት መልስ መስጠት የሚገባው ወቅት ዛሬ ነው!

ለኢትዮጵያዊያን የነፃነት፣ እኩልነትና የዴሞክራሲ ጥያቄ የህይወታቸው አካል ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ ከውጭ ወራሪም ሆነ ከውስጥ አምባገነን አገዛዝ ጋር የሚያደርጉት ትንቅንቅ ዛሬም መቋጫ አላገኘም፡፡ በየምዕራፉ ግን የለውጥ ጮራዎች ብልጭ ድርግም ማለታቸው ህዝባችንን ለሠቀቀን ዳርገውታል፡፡

በዘመናዊት ኢትዮጵያ እንኳን ከአራት በላይ የለውጥ ብልጭታዎች ታሪክ ሆነው አልፈዋል፡፡ በሚያሳዝን ሁኔታ ለውጥን ማስተዳደር አለመቻል ዛሬም ትልቁ ፈተናችን ሆኗል፡፡

በሁሉም ዜጎች መስዋዕትነት የተገኙ ድሎችን ወደ ራስ የመጠቅለልና የፖለቲካ ፍላጎትን በኃይል በሌሎች ወገኖች ላይ የመጫን ጉዳይ ዛሬም አይኑን አፍጥጦ እየመጣ ነው፡፡
በርግጥ የአሁኑ አጅግ ዘግናኝ ድርጊት መነሻ ኢትዮጵያዊያን ከተዘራባቸው የዘረኝነት እና የአግላይነት ፖለቲካ ለመላቀቅ የነቁበት እና ወደዜግነት ክብር ለመመለስ አበረታች ርምጃዎችን መውሰድ በመጀመራቸው የተነሳ መሆኑን እንገነዘባለን፡፡

በተለይም ዜጎች በእኩልነትና በወንድማማችነት መንፈስ መቆማቸውን የተመለከቱ የዘውግ ፖለቲካ ነጋዴዎች ጣዕረ-ሞት ላይ መሆናቸውን በሚያሳይ ሁኔታ ተንፈራግጠዋል፡፡ የዚህም የመጨረሻ ማሳያዎች ለችግሩ የዘርና የእምነት ይዘት ለመስጠት መታተራቸው ነው፡፡
ከነዚህም ጋር የሕዝባቸውን የመልካም አስተዳደር፣ የመሠረተ ልማትና የሥራ ዕድል ጥያቄዎችን መመለስ ያልቻሉ የመንግሥት ሹመኞች ጭምር ይህን የዘር በሽታ እያራገቡ መሆናቸውን እየታዘብን ነው፡፡ እነዚህ ወገኖች ያልተረዱት ዛሬ ደም መፋሰስን ያለማመዱት ወጣት ጥያቄው እስካልተመለሰለት ድረስ ነገም እነሱንም በዚሁ ሁኔታ እንደሚያጠፋቸው ነው፡፡ ዘውግን መሠረት ባደረገ የፖለቲካ ሥርዓት በስሙ የያዙትን ሥልጣን ተጠቅመው ቆምንለት የሚሉትን ማኅበረሰብ ከኖረበት ሲያፈናቅሉት እና ሲዘርፉት እንደቆዩ ጸሐይ የሞቀው ሀቅ ነው፡፡

የሕዝብን በተለይም የወጣቱን ሁለንተናዊ ደኅንነት እና የኢኮኖሚ ጥያቄዎች በዘላቂነት ለመመለስ የሚቻለው ከቀበሌ ጀምሮ፣ በወረዳ፣ በዞንና በክልል እንዲሁም በሀገር አቀፍ በየደረጃው ሕዝብ በነጻነት በመረጣቸውና የተሻለ ሀሳብ ባላቸው መሪዎቹ ሲተዳደርና እውነተኛ ፌደራላዊ የአስተዳደር ሥርዓት ሲሰፍን ብቻ መሆኑን እናምናለን፡፡ ይህ እንዳይሆን የሚኳትኑ ግለሰቦች ባሳለፍነው ሳምንት በሁለት ቀናት ብቻ ባደረሱት የዜጎችን ሕይወት መቀጠፍ፣ የአካል መጉደልና የንብረት መውደም ተሠማንን የልብ ስብራትና ጥልቅ ሀዘን እየገለፅን በሚከተሉት ነጥቦች ላይ ያለንን አቋም እናሳውቃለን፡-

1. በተለይም ጥቅምት 13 እና 14 ለደረሰው ጥፋት መነሻ ከሆነው ‹‹ተከብቤያለሁ›› በሚል ለመንግስት አካል ማሳወቅ ሲገባው ወደ ህዝቡ ከረጨው ግለሰብ ጀምሮ በየደረጃው በሰው ሕይወት እና ንብረት ላይ አደጋ ያደረሱ ሰዎች በሙሉ ለፍርድ እንዲቀርቡ፣

2. ለዜጎች ሞት ደንታ የሌላቸውና በግጭት የሚነግዱ የማኅበራዊ ድረ-ገፅና የተለያዩ የብዙኃን መገናኛዎች ሕዝባችንን ለሌላ ተከታታይ ግጭቶች ከመዳረጋቸው በፊት ሥልጣን በተሠጠው አካል የማስተካከያ ርምጃ እንዲወሰድ፤

3. በችግሩ ምክንያት በየአካባቢው በአሰቃቂ ሁኔታ የተጨፈጨፉ፣ ከቤት ንበረታቸው የተፈናቀሉና ንብረታቸው የወደመባቸው ዜጎች ተገቢውን ካሳ እንዲያገኙና በአስቸኳይ ተመልሰው እንዲቋቋሙ፣

4. በአጥፊዎች ላይ የሚወሰደው ርምጃ ፈፅሞ ከፖለቲካዊ ወገንተኝነት የፀዳ፣ የፀጥታ ኃይሉን ሕዝባዊ ወገንተኝነት ባረጋገጠ መልኩ እንዲሆንና መበቃቀያ እንዳይሆን ጥንቃቄ እንዲደረግ፤ከዚህ ጋር በተያያዘ መንግስትን መቃወምና በህዝብ ድምፅ መቀየር ህጋዊና ተገቢ ተግባር ሲሆን አገርን የማዋረድና የማፍረስ ተግባር ግን ፈፅሞ የተከለከለና የአገር ክህደት ወንጀል በመሆኑ ይህን በሚፈፅሙት ላይ እርምጃ መውሰድ ተገቢ መሆኑን፤

5. እስካሁን ለተፈፀሙት ሕገ ወጥ ተግባራት መንግሥት አስተማሪ ርምጃ ባለመውሰዱ ሕዝብ መንግሥትን ተጠያቂ እያደረገ ይገኛል፡፡ የመንግሥት ኃላፊነቱን አለመወጣት ደግሞ ሕዝቡ ተደራጅቶ ራስን ወደ መከላከል ደመነፍሳዊ ሁኔታ ይገፋዋል፡፡ ይህም ማንም አሸናፊ ወደማይሆንበት እርስበርስ እልቂት ይከተናል፡፡ ይህንን ለመከላከል እንደ ማህበረሰብ አቀፍ ፖሊስ የመሳሰሉ ሕጋዊ አረጃጀቶች በአስቸኳይ ማጠናከር እና ሥራ ላይ ማዋል የሚገባ መሆኑን፣

6. በአዳማ፣ በባሌ፣ በምዕራብ አርሲ ዶዶላ፣ በምስራቅ አርሲ፣ በባቱ (ዝዋይ)፣ በኮፈሌ፣ በቢሾፍቱ፣ በሰበታ፣ በአምቦ፣ በሐረርና በሌሎችም የኦሮሚያ ክልል የተፈፀሙ እኩይ ተግባራት ፈፅሞ የኦሮሞን ሕዝብ የማይወክሉና እንዲያውም ሕዝቡ እንዲከፋፈል፣ የሥራ እድል እንዲጠፋና የልማት እንቅስቃሴዎች እንዲስተጓጎሉ በማድረግ ክልሉ ብሎም ሀገር እንዲዳከም ተግተው የሚሰሩ እኩይ ዓላማ ያነገቡ ግለሰቦች አጀንዳ መሆኑን ሁሉም እንዲረዳው፡፡

7. በአጠቃላይ የሀገር መረጋጋት እና ሰላም እንዲሁም ከቀጣዩ ሀገራዊ ምርጫ ጋር ተያይዞ ባሉ አንገብጋቢ ጉዳዮች ላይ ሁሉንም ባለድርሻ አካላት ያሳተፈ ውይይት በፍጥነት መጀመር እንዳለበት እናምናለን፡፡ ለዚህም መንግስት ግንባር ቀደሙን ሚና እንዲወጣ እየጠየቅን በእኛ በኩል ለውይይቱ ያለንን ከፍተኛ ተነሳሽነት እና ቁርጠኝነት እንገልጻለን፡፡

8. በዚህ አጋጣሚ በመፈናቀል፣ በድርቅ እና በአንበጣ መንጋ በመመታትና በልዩ ልዩ ችግሮች የተከበቡ ወገኖችን በሌሎች ወቅታዊ ጉዳዮች ተጠምደን እንዳንዘነጋቸው የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት በፍጥነት እንዲደርሱላቸው ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡

በመጨረሻም ሕዝቡ በደረሱት ጥቃቶች ማዘኑን፣ መበሳጨቱንና ይህን የሞራል ስብራት ተቀብሎ በዝምታ ለመቀመጥ መቸገሩን ተረድተናል፡፡ ሆኖም በዚህ ዓይነት ሁኔታ መረጋጋትና አስተውሎ መንቀሳቀስ ወሳኝ መሆኑን ለፓርቲያችን አመራር፣ አባላት፣ ደጋፊዎችና ለሕዝብ አደራ በማለት ከአምባገነናዊ ሥርዓት ለመውጣትና ኢትዮጵያን ዴሞክራሲያዊ ሀገር አድርጎ ለማስቀጠል ከሚሹ ወገኖች ሁሉ ጋር በጋራ ለመሥራት ያለንን ዝግጁነት እንገልጻለን፡፡ ለፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ለግብረ ሰናይ ድርጅቶች፣ ለሀገር በቀል ማኅበራት፣ ለሀገር ሽማግሌዎች፣ ለሃይማኖት አባቶችና ለሌሎችም የማኅበረሰብ መሪዎች የጋራ ሀገር አድን ጥሪ እናቀርባለን፡፡

ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር!

ጥቅምት 18 ቀን 2012 ዓ.ም
አዲስ አበባ

ብዙ ደጋፊ ስላለው አይነካም የሚል ክርክር አይሰራም። የጥላቻና የጥፋት ሰባኪዎች ደጋፊ አጥተው አያውቁም። ከጃዋር የበለጠ ሂትለርም፣ ሞሶሎኒም፣ ሚሎሶቪችም፣ ቢን ላደንም ደጋፊ ነበራቸው

የዘር ማጽዳት (ethnic cleansing) እንኳን ከ80 በላይ ብሄረሰቦች በሚኖሩባት ኢትዮጵያ ይቅርና ሁለት ብሄረሰቦች ለሚኖሩባት ሩዋንዳም አላዋጣም። አይናችን እያየ በአገራችን ጄኖሳይድ እንዲፈጸም ፈጽሞ አንፈቅድም። ስለዚህም ነው ጃዋር መሃመድ ለሰራው አሰቃቂ ወንጀል በህግ ተጠያቂ መሆን የሚገባው።
ብዙ ደጋፊ ስላለው አይነካም የሚል ክርክር አይሰራም። የጥላቻና የጥፋት ሰባኪዎች ደጋፊ አጥተው አያውቁም። ከጃዋር የበለጠ ሂትለርም፣ ሞሶሎኒም፣ ሚሎሶቪችም፣ ቢን ላደንም ደጋፊ ነበራቸው