### የውጫሌ ውል ከዲፕሎማሲ እይታ አንፃር ### Mes Demoze


· 

የዓድዋ ጦርነት መነሻ የሆነውን የውጫሌን ውል መፈራረም ከኢትዮጵያ አንፃር እንደ ታሪካዊ ስህተት ቢታይም ያመጣብን ችግር በውስጡ ያልታሰበ በረከትም ነበረው፡፡ በዘመናዊው የዓለም ፖለቲካ በውል የተሳሰሩት ሀገራት አንዱ ሀገር ሌላውን እንደ ሀገር መኖር መቀበሉንና እውቅና መስጠቱን ማረጋገጫ ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ የውጫሌው ውል ለኢትዮጵያ እንደ ሀገር የመኖር እውቅናን አትርፏል ማለት ነው፡፡ ይህን በተመለከተ ሬይሞንድ ጆናስ ሲያብራራ “በ19ኛው ክፍለ ዘመን አውሮፓውያን ከአፍሪከ ሀገራት ጋር መዋዋላቸው ያልተለመደ ስለነበር የውሉ 17ኛው አንቀፅ ምንም ችግር ቢኖረውም ጣሊያን ከኢትዮጵያ ውል ማሰሯ በራሱ ጣሊያን ምኒልክ ለሚያስተዳድሯት ኢትዮጵያ አውቅና መስጠቷን ያሳየ ነበር” ሲል ያትታል፡፡ ፀሀፊው ሲቀጥልም “ራስ መኮንንና ቀሪዎቹ የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን አባላት ነሃሴ 27 ቀን 1889 እ.ኤ.አ ሮም ላይ ከባቡር ሲወርዱ ለአፍሪካ ድል ነበር፡፡ ከሰሀራ በታች ባለችው አፍሪካና በአውሮፓ መካከል በሰለጠነው ዘመን የመጀመሪያው የከፍተኛ ደረጃ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙትነት ነበር” ይላል፡፡ የውጫሌ ውል ትርጓሜ ኋላ በጦርነት ቢቋጭም በመነሻው ግን ለኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ እውቅና በር የከፈተ እንደነበር መገንዘብ ይቻላል፡፡

የውጫሌ ውል ቅቡልነት በአውሮፓ ሀገራት

“ጣሊያኖች የውጫሌን ውል አንቀፅ 17 በተመለከተ ለሌሎች መንግስታት ከመናገራቸው በፊት ሁለት ሳምንት ቀደም ብለው ለሩሲያ አሳወቁ” ይላል ሃሮድ ማርከስ “አፄ ምኒሊክ” በሚለው መፅሀፉ፡፡ ይህም መስኮብ የጣሊያን ኢትዮጵያን ለመቆጣጠር እቅድ ላይ እንቅፋት እንዳትፈጥር ለማድረግ ነበር፡፡ የውጫሌን ውል ጣሊያነኛ ትርጉም እንግሊዝና ጀርመን በመቀበላቸው፤ አፄ ምኒሊክ “ንጉሠ ነገሥት መሆኔን እወቁልኝ” በሚል ለላኩት ደብዳቤ የሰጧቸው ምላሽ በሞግዚትዎ በኢጣሊያ በኩል ደብዳቤው ይድረሰን የሚል ነበር፡፡ በሌላ ወገን የፈረንሳይና ሩሲያ መንግስታት ግን የጣሊያንን ሞግዚትነት አለመቀበላቸው ለኢትዮጵያ ነፃነቷን ጠብቃ መቆየት የጎላ ሚና ተጫውቷል፡፡

ፈረንሳይ ፡-

ፈረንሳዮች የጣሊያንን በእንግሊዝ ታግዞ የሚደረገውን ኢትዮጵያን የመቆጣጠር ፍላጎት አልወደዱትም ነበር። ከጦርነቱ አስቀድሞ ኢትዮጵያ ለውጭ ንግድ ግንኙነቷ በፈረንሳይ ስር የሚገኘውን ኦቦክ (ጅቡቲን) ለመጠቀም ስትጠይቅ መፍቀዷ ኋላም ለጦርነት ዝግጅት ሲጀመርም ከጣሊያን እውቅና ውጭ የጦር መሳሪያ ወደ ኢትዮጵያ ለማስገባት ይህንኑ ወደብ አጼ ምኒለክ እንዲጠቀሙ መስማማታቸው ይህን ፍላጎታቸውን የሚያሳይ ነው።

መስኮብ

ተክለጻዲቅ መኩሪያ “አጼ ምኒልክና የኢትዮያ አንድነት” በሚለው መፅሀፋቸው የኢትዮጵያና የመስኮብ መንግስትና ቅድመ ዓድዋ ግንኙነትን ሲገልጹ “የጣሊያኖች አጥቂነት በከፋበት ሰዓት የመስኮብን እርዳታ ማግኘት አስፈላጊ ነበር፡፡ ለዚህም በፊታውራሪ ዳምጠው ከተማ የሚመራ ልዑካን ቡድን ወደ ሩሲያ ሲያመራ በንጉሠ ነገሥቱ ዳግማዊ ኒኮላ የተደረገለት እጅግ የደመቀ የክብር አቀባበል ኢጣሊያኖችን እጅግ እስቆጣ” ሲሉ ይገልፃሉ፡፡

የውጫሌ ውል እንደውል ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ግንኙነት እንደ ነፃ ተዋናይ የመሳተፍ መብቷን በተግባር ያሳየ ሲሆን፤ ከዓድዋ ጦርነት በፊትም የኢትዮጵያን የውጭ ግንኙነት ነፃነት በ17ኛው አንቀጽ ለመገደብ የሞከሩት ኢጣሊያኖች ሀሳባቸው አልሰመረም፡፡ በተቃራኒው ኢትዮጵያ ከአውሮፓ ኃያላን ጋር የሁለትዮሽ ግንኙነት በመፍጠር ለዓድዋ ጦርነት የጦር መሳሪያ በበቂ አቅርቦት እንድታገኝ አድርጓል፡፡ ይህም በዓድዋ ጦርነት ኢትዮጵያ በወራሪዋ ኢጣሊያ ላይ ለተቀዳጀችው የበላይነት መንገዱን አመቻችቷል ፡፡

#የጥቁር_ህዝብ_ኩራት
#ዓድዋ_123 
#የኢትዮጵያውያን_ድል
#VictoryofAdwa
#Ethiopia

Advertisements

የዓድዋ ድልና እቴጌ ጣይቱ Minilik Salsawiየዓድዋ ድልና እቴጌ ጣይቱ

1. ቅድመ ጦርነት

የዓድዋ ጦርነት ከመጀመሩ በፊት ሃገር እስክትረጋና የጦር መሳሪያ እስኪሠበሠብ ድረስ አፄ ምኒልክ ከኢጣልያ ጋር የነበረውን ግንኙነት ፍፁም ብልጠት በተሞላበት ዲፕሎማሲያዊ መንገድ ሲያስኬዱት ነበር። 
እቴጌ ጣይቱ ከእርሳቸው በፊት ከነበሩትም ሆነ ከሳቸው በኋላ ከመጡት እቴጌዎች የሚለዩት በመንግስቱ ሥራዎች ውስጥ እየገቡ ያማክሩ፣ ታላላቅ ሃገራዊ ጉዳዮችንም ከንገሡና ከመኳንንቱ ጋር በመምከር ውሳኔ እንዲተላለፍም ያደርጉ ስለነበር ነው።

ለዓድዋ ጦርነት መነሳት ትልቁን ሚና የተጫወተው የውጫሌን ውል ጉዳይ ሊያስፈፅም የመጣው የአጣልያ ቆንስላ ኮንት አንቶሎኒ በአንቀጽ 17 ተቃውሞውን አሠምቶ ኢጣልያ ጦርነት እንደምታስነሳ በምኒልክ ቤተመንግስት ውስጥ ሲፎክር እቴጌይቱ የመለሱለት እንዲህ በማለት ነበር

“ … የዛሬ ሳምንት አድርገው፡፡ እኔ ሴት ነኝ ጦርነት አልወድም፤ ነገር ግን ሀገሬ እንደዚህ ያለ ክብር የሚነካ ዘለፋ ከምትሸከም ጦርነትን እመርጣለሁ፡፡ ሂድ መንገዱን ጨርቅ ያድርግልህ እግሩን ለጠጠር፤ ደረቱን ለጦር አስጥቶ፤ ደሙን ለሀገሩ ፍቅር አፍስሶ፤ ለአፈሩ ክብር ለብሶ፤ እሱ ወድቆ ሀገሩን የማያቆም እዚህ ያለ እንዳይመስልህ! ሂድ! የኢትዮጵያን ሰው ባታውቀው ነው፡፡ ለሀገሩ መሞት ማለት ለሀበሻ ጌጡ ነው፡፡ ሂድ ባሻህ ግዜ ተመለስ ተሰናድተን እንጠብቅሃለን፡፡ ያንተን ወንድነትና የጣይቱን ሴትነትም ያን ጊዜ እናየዋለን ሂድ መንገዱን ጨርቅ ያድርግልህ፡፡”

ይሄ የእቴጌይቱ ንግግር በወቅቱ ያሳደረው ጫና ቀላል የሚባል አልነበረም ለአብዛኛው ዘማች አርበኛ ” ሴቷ እንኳን ……” የሚል እሳቤን በውስጡ እንዲኖር ሲያደርግ በተጨማሪም ለኢጣልያ ጦር የሠጠው ግምት አናሳ እንዲሆንና ድል ማድረግ እንደሚችልም ውስጡን እንዲያሳምን አድርጎታል። እዚህ ንግግር ላይ ለሃገር ያላቸውን ከፍ ያለ ፍቅር ያሳያል አይደለም የሃገር ዳር ድንበሯ ተነክቶ ይቅርና ዘለፋን እንኳን መቋቋም የማይችል አመለካከት እንደነበራቸውም ያሳያል ……ሃገሬ እንደዚህ ያለክብር የሚነካ ዘለፋ ከምትሸከም ጦርነትን እመርጣለሁ ….

2. ጦርነቱ ላይ

በዓድዋ ጦርነት እቴጌይቱ በራሳቸው በኩል 5,000 ጦር ይዘው የዘመቱ ሲሆን በተጫማሪም ስንቅ በማዘጋጀት፤ የደከመውን በማበርታት፤ የቆሠለውን በማከም፤ የሚሸሸውን በመገሰፅ ታላቅ ተጋድሎን ሲፈፅሙ ውለዋል። 
የዕለቱን የእቴጌይቱን ውሎ ጸሃፌ ትዕዛዝ ገብረሥላሴ እንዲህ ይተርኩታል
……. በዚህ ቀን በዓድዋ በዐይናችንን ያየነውንና በዦሮአችን የሠማነውን ለመጻፍ ችግር ነው። በዚህ ጊዜ እቴጌ ጣይቱ በማጅራታቸው ድንጋይ ተሸክመው በጉልበታቸው ተንበርክክከው በጋለ ፀሎት ወደ እግዚአብሔር ይጸልዩ ነበር። እቴጌ ጣይቱ ጥቁር ጥላ አስይዘው አይነርግባቸውን ገልፀው ወደፊት ጉዟቸውን ቀጠሉ። ወዲያውም የኋላው ወታደር ሲያመነታ አይተው “በርታ ምን ሆነሃል ድሉ የኛ ነው በለው” በማለት ሲያበረቱ ሁሉም ወደፊት ገፋ። እቴጌይቱ በዚህን ቀን የሴትነት ባህሪያቸውን ትተው እንደወንድ ወታደሮቻቸውን በግራና በቀኝ አሠልፈው ወደ ጦርነቱ ገቡ። ቁስለኛና ምርኮ የያዘውም ወደኋላ ሲመለስ ባዩት ጊዜ “ንጉሡ ሳይመለሱ ወዴት ነው የምትመለሱት? ምርኮኞቻችሁንና ቁስለኞቻችሁን ለኔ ስጡኝና ተመለሱ ……. በማለት ጦሩን ያበረቱ ነበር። 
ከውጫሌ ውል ጀምሮ ያልተለዩትና በኢጣልያኖች ሃሳብ ሲናደዱ የቆዩት እቴጌይቱ የቁርጡ ቀን ሲመጣ 
በፈጣሪ በጣም ይታመኑ ስለነበር በፀሎት መጀመራቸውን ጦርነቱ ሲፋፋምም ይዘው የዘመቱትን 5000 ጦር ይዘው መሃል ገብተው ያዋጉ እንደነበር በመጨረሻም ቁስለኛን ሲያክሙ የደከመውንም ሲያበረቱ በመዋል ታላቅ ስራን ፈፅመዋል። ከዚህም በተጨማሪ እቴጌይቱ ለኢትዮጵያው ዘማች ብቻ ሳይሆን ለኢጣልያኖቹም ምን ያህል ሩህሩህ እንደነበሩ ማሳያው ምርኮኞቹን ጥለውላቸው ከሄዱ በኋላ እንደ ኢትዮጵያውያን ሁሉ ጣልያኖቹንም በማከምና ውሃ በመስጠት ሲንከባከቡ እንደነበር ተፅፎ ይገኛል ይሄም ምን ያህል ይቅር ባይ ልብ እንደነበራቸው ያሳያል። ከጦርነቱ ፍፃሜ በኋላ የኢትዮጵያ አርበኛ ሲጨፍር “አዳም አዳምን ገደለና ይሄ ሁሉ ደስታ ለምን ነው?” የሚለው ንግግራቸው ምንም ጠላት ቢሆኑ እንኳን በሠው ልጆች ሞት መደሰት እንደማይገባ የሚያሳይ ነው። 
ሃገር በምን አይነት መስዕዋትነት እንደቆመች አንዘነጋም።

#የጥቁር_ህዝብ_ኩራት
#ዓድዋ_123
#የኢትዮጵያውያን_ድል
#victoryofAdwa
#Ethiopia

### የዓድዋ ጦርነት መነሻ Minilik Salsawi

 

### የዓድዋ ጦርነት መነሻ
(ሥነ ልቦናዊና ማኅበረሰባዊ ዳራ) ### 
ክፍል ሁለት

” ባትዋጋ እንኳን በል እርገፍ እርገፍ
ያባትህ ጋሻ ትኋኑ ይርገፍ”

፪) ከኢትዮጵያ ወገን

ከዓድዋ ጦርነት በፊት በኢትዮጵያ ወገን የነበረው ማኅበረሰባዊ እሳቤና ሥነ ልቦናዊ ቅኝት ከወራሪያቸዉ የኢጣሊያ ጦር የተለየ ነበር፡፡ ። የአሸናፊነትና የልበ ሙሉነት የሆነ ።

ከእግዚአብሔር የተሠጠንን …….

ኢትዮጵያውያን መሪዎችም ሆኑ ተመሪዎቹ ሀገርና ግዛት የፈጣሪ ስጦታ ነው የሚል የፀና እምነት አላቸው፡፡ ኢትዮጵያዊ በርስቱና በሚስት ሲመጡበት አንገትን ለካራ ለመስጠት ያለማመንታቱ ልማድ ለዚህ ጥሩ ማሳያ ነው። ይህን ሳይረዳ መሬትህን እንዲሁ ነጥቄ ልውሰድ ብሎ የመጣን ባላንጣ መመከት ለኢትዮያውያን የመብትና የክብር ጉዳይ ነበር፡፡ ለዚያም ይመስላል ምታ ነጋሪት ክተት ሰራዊት ሲባል ሳያቅማማ ከያለበት ወደ ዓድዋ የዘመተው፡፡

የህልውና ጉዳይ…

ምኒልክ እንደ ንጉሥ ኢትዮጵያ እንደ ሀገር የመዝለቅ ጥያቄ 
በኢትዮጵያ ከዘመነ-መሳፍንት ያልተማከለ አስተዳደር ተወጥቶ እንደሀገር ለመጽናት የተሞከርው ጣሊያን ሀገር ልሁን ብላ በምትታትረበት ዋዜማ እ.ኤ.አ 1855 ዓ.ም ላይ ነበር፡፡ በአጤ ቴድሮስም ይሁን በአጤ ዮሐንስ ዘመነ መንግሥት የሀገሪቱ ወሰን በደቡብ ከሸዋ ለማለፍ አልቻለም ነበር፡፡

የየክፍለ ሀገሩ ገዢዎች (የሸዋው ምኒልክን ጨምሮ) ለማዕከላዊ መንግሥት ማደርን አይሹም ነበር፡፡ ይህም የወጭ ጠላት ሲመጣ ከንጉሠ ነገሥቱ ጋር አብሮ ከመቆም ይልቅ የአካባቢውን ገዢነት ማስጠበቅ ላይ ያተኩሩ ነበር፡፡ ለዚህም እንግሊዞች በአጤ ቴዎድሮስ ደርቡሽ በአጤ ዮሐንስ ላይ ጥቃት ሲያደርሱ የበረታ መከላከል ያልገጠማቸው፡፡፡ ጣሊያን ኢትዮጵያን ሲወር ግን ይህ ተቀይሮ ነበር፡፡ የወስጥ የስልጣን ሽኩቻው ከሞላ ጎደል በመጠቃለሉና ራሶቹም በምንሊክ ስር በመግባታተቸው ኢትዮጵያ ወስጣዊ ሽኩቻዋን አስታርቃ በመገኘቷ በጣሊያን ላይ የሥነ-ልቦና የበላይነት እንዲኖራት አድርጓል፡፡ የቀረ እነኳን ቢኖር ንጉሡ “አመልህን በጉያ ስንቅህን በአህያ” ያሉት ትዕዛዝ የሚገዛው ነበር።

የንጉሡ የስልጣን ቅቡልነት

በአጤ ምኒልክ ጥላ ስር ያደሩት ሀገረ ገዥዎችና ራሶች ለንጉሠ ነገሥቱ ባለ ሙሉ ሥልጣን እውቅና የሰጡ ሲሆን፤ በተማከለው የዘመናዊት ኢትዮጵያ አስተዳደር ውስጥ የየራሳቸውን ግዛት ማስተዳደሩን ብዙሃኑ ተቀብለውት ነበር፡፡ ይህንን አዲስ አሰራር ሊያፋልስ የመጣን ጠላት መመከት አንድም ለንጉሠ ነገሥቱ ያላቸውን ታማኝነት ማሳያ ሁለትም ያሉበትን የየግለ ግዛታቸውን ማጽኛ መንገድ አድርገው ወስደውታል፡፡ ስለዚህም ለሀገርና ለንጉሥ መሞትን ከክብርም በላይ አድርገው በማሰብ አልጋውን ለማቅናት ብዙዎቹ ህይወታቸውን ሰውተዋል፡፡

የንጉሡ ልበ ሙሉነት

አጤ ምኒልክ ጣሊያንን እንደሚያሸንፉት በሙሉ ልባቸው ያምኑ ነበር፡፡ ከክተት አዋጁ ቢጀመር ” ……..ወስልተህ የቀረህ ግን ኋላ ትጣላኛለህ አልተውህም ማሪያምን………” ሲሉ አቅም እያለው አልዋጋም ያለውን ለማስፈራራትና ስለመቅጣት ብቻ አልነበረም፤ ለመቅጣትም ቢሆን እኮ ወደ ርስተ ዙፋናቸው መመለስ አለባቸው፡፡ ታዲያ ጦርነቱን አሸፈው እንደሚመለሱ በማመናቸው ነበር ወስላታውን በኋላ አማላጅ የለኝም ሲሉ ማሳሰባቸው፡፡ ከዚህም ሌላ እነ ካዎ ጦና፣ አባ ጅፋርን ሀገር ጠብቁ ብለው ከጦርነቱ አለመጨመራቸው ለጣሊያን እኛ መች አንሰነው የሚል መልክት ነበረው፡፡

በመጨረሻም የጦርነቱ መነሻ ኢትዮጵያውያን ለራሳቸው ከሚሰጡት ክብር፣ ጭቆናና ሽንፈትን መጠየፍ፣ ሳያደገድጉ በነፃነት ለኖሮ የማለፍ እሳቤ ጋርም ተዛማጅነት አለው፡፡

በልበ-ሙሉነት የተገራው ኢትዮጵያዊው ተክለ-ስብዕና ተናነሶ መኖርን የሚጠየፍ ነበር ስለዚህም ድንበር ጥሶ አጥር አፍርሶ የመጣን ወራሪ ለመመከት አለማመንታት ዛሬም ድረስ የኢትዮጵያ ህዝብ ልዩ መገለጫ ሆኖ ቆይቷል፡፡

የጥቁር_ህዝብ_ኩራት
#ዓድዋ_123 
#የኢትዮጵያውያን_ድል
#VictoryofAdwa
#Ethiopia

በተለይ የኦሮሞ ልሂቃን እንዲያነቡልኝ የምጋብዘው ጽሑፌ (ነፃነት ዘለቀ)

ነፃነት ዘለቀ (netsanetz28@gmail.com)

የኦሮሚያ ክልል ምክር ቤት ሹመታቸውን ያፀደቀላቸው ተሿሚዎች ቃለ መሃላ ሲፈጽሙ

ይህችን ማስታወሻ ጽፌ የላክት ትናንት እሁድ የካቲት 3 ቀን 2011ዓ.ም ነው፡፡ ሆኖም አንዳንድ ስንቅሪጦችን (insertions) ማስገባት እንዳለብኝ ዛሬ ተረዳሁና አስተካክዬ እንደገና ላክኋት፡፡ ባለፈው ሰሞን ስለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አይሆኑ እየሆነ መምጣት መክተቤም ይታወሳል፡፡ ዛሬ ሌሊት በሣተናው ድረገጽ ላይ ሳነብ ደግሞ ያንን መረጃ የሚያጠናክር አዲስ ነገር አየሁ (https://www.satenaw.com/amharic/archives/63435) – ሁኔታዎች አሳሳቢ ደረጃ ላይ ናቸው፤ ያስጨንቃል፡፡ ይህን በሚመለከትም ጉዳዩ የሚመለከታችሁ በተለይም የኦሮሞ አክቲቪስቶችና ምሁራን ሁኔታው በአፋጣኝ እንዲስተካከል የበኩላችሁን ጥረት ታደርጉ ዘንድ የዜግነት ጥሪየን በዚህ አጋጣሚ አቀርባለሁ፡፡ የኔን ጽሑፍ ማንበብ የሚፈልግ “በዘረኝነት ጦስ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክም ባፍጢሙ ሊደፋ ነው!” በሚል ርዕስ ገብቶ ከሁነኛ ድረገፆች ማንበብ ይቻላል፡፡ ማንኛቸው እንደተናገሩት ማስታወስ አልችልም እንጂ ከወያኔዎች አንዱ – ቀደም ሲል – “እኛ ይህችን አገር ማስተዳደር ካልቻልን ለኦሮሞ አሳልፈን እንሰጥና እርስ በርሳቸው (አማራና ኦሮሞን ማለት ነው) አባልተናቸው ወደ ትግራይ እንሄዳለን” ማለቱ ተዘግቧል፡፡ ያ ጊዜ አሁን በትክክል እንደመጣ አፍን ሞልቶ መናገር ይቻላል፡፡ ዋናው መፍትሔ በታቀደልን መሠረት እንባላ ወይንስ ቆም ብለን በማሰብ ለሁላችን የሚሆን የጋራ ምቹ ሁኔታን እንፍጠር የሚለው ነው፡፡ በቀላሉ አትዩት፡፡ እነሱ ባቀዱት መንገድ ወደ ትግራይ መሄድ አለመሄዳቸውን አንድዬ የሚያውቀው ሆኖ ባሰቡትም ሆነ ባላሰቡት መንገድ ትንቢታቸው እየተፈጸመ ይመስላል፡፡ ስለዚህ ይህ አዲሱ የኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ችላ ባይባል መልካም ነው – ለሁላችንም ደኅንነት ሲባል፡፡ የልደት ቀን እንዳለ የሞትም አለ፤ የመደሰት ቀን እንዳለ የማዘንም አለ፤ “የጨው ተራራ ሲናድ ብልኅ ያለቅስ ፣ ሞኝ ይስቅ” እንዲሉ በምናየው ወንዝ የማያሻር አልባሌ ነገር ሁሉ ጥቂት የማንባል ዜጎች ውስጣችን እየደማ እንገኛለን፡፡ ….

የቀደመውን ጽሑፌን ለማየት የሚፈልግ በርዕሱ አጋዥነት እነዚህን ድረገፆች መጎብኘት ይችላል – satenaw.com, welkait.com, ethiolion.com, ethioexplorer.com, ethioreference.com, ethioforum.com.

ይህን ዘመን ዝም ካሉት ሁላችንም በአንድ ወይ በሌላ ምክንያት ተቆራርጠን መቅረታችን ነው፡፡ ለደቂቃዎች ብንጠፋፋ ዓመት የተለያየን የምንመስል የነበርነው የዘሀበሻው ሄኖክ ዓለማየሁና እኔ እንኳን ይሄውና በቁርጥ “ከተጣላን” ድፍን አምስት ወር ተኩል ሊሆነን ምንም አልቀረንም፡፡ ይሄ ዘር የሚሉት የሰይጣን ትክል ለካንስ ይህን ያህል ወራዳና ብስብስ ኖሯል! እደግመዋለሁ – ወራዳና ብስብስ ያለ ብስብስ ነው! ወያኔን ምሥጋን ይንሳውና እንኳንስ በአካል የማንተዋወቅን የአንዲት ሀገር ዜጎች ይቅርና ይህ ዘመን እኮ አባትንና ልጅን፣ እናትንና ልጅን እኮ በዘር ምክንያት አባልቷል፤ አለያይቷል – አሁን እዚህ ማስታወሱ ተገቢና ገምቢ አይደለም እንጂ – ወያኔ በገባ ሰሞን – በዘረኝነት የወረት ፍቅር ያበደች አንዲት ትግሬ ከአንድ ወሎዬ አማራ የወለደችውን ሕጻን ሽንት ቤት ውስጥ ጨምራ ገድላለች – (ቀድሞ ነገር ማን ከርሱ ጋር ተኝ አላት በል)፡፡ ዘረኝነት ማለት ዐይንንም፣ ኅሊናንም፣ አእምሮንም፣ በጥቅሉ ሁለመናን የሚያሣውር መጥፎ በሽታ ነው –  በኔ ግምትና የእስካሁን ግንዛቤ ይህ በሽታ መድኃኒቱ ሞት ወይም በአንዳንዶች ላይ እንዳስተዋልኩት በእርጅና ዘመን አካባቢ ሊመጣ የሚችል ጸጸት ብቻ ነው – የጸጸት ዋጋ ደግሞ ትንሽ ነው ወይም ከናካቴው ምንም ዋጋ ላይኖረውም ይችላል፡፡ “ባልገጨሁት ባልሞተ” ብትል መግጨትህንም ገጭተህ መግደልህንም ስለማያስቀረው ጸጸትህ ከንቱ ነው፡፡ … ፍቅር በበዛበት ጠብም ትበዛለች … ወንድሜ ሄኖክ ወያኔ ትግሬዎችን ጥምብ እርኩሳቸውን ሳወጣ፣ የክት ስድቤንና ትችቴን ከየኮረጆየ ያለአንዳች ስስት እየመዠረጥኩ በነገር ጦር እንዳይሸጡ እንዳይለወጡ አድርጌ ስወርፍ ከአፌ እየነጠቀ በድረገጹ ይለጥፍ እንዳልነበር ዛሬ የነካውን እንጃ እንደ አብርሃ በላይና እንደነስም አይጠሬ አንዳንድ ሞገደኛ “የዴሞክራሲ ጠበቃ ሚዲያዎች” አሽቀንጥሮ ጣለኝ – ስጠረጥር ግን ይህ አዝማሚያ የተከሰተው ከነዚህ አሥርና ዘጠኝ ወራት ወዲህ በመጣብን አዲስ የዘረኝነት ልምሻ መሆን አለበት – ይቺ “ትንሽ ሥጋ እንደመርፌ ትወጋ” የሚሏት ነገር ኢትዮጵያ ላይ ድንኳኗን ደኩና እየተጫወተችብን ናት – ትናንት በውስጥ ተደብቆ የነበረ dormant volcano of racism ዛሬ active volcano ይሆንና በብርቱ ያስቸግረን ይዟል፡፡ በዚህች ደዌ እየተለከፈ ስንቱ ትልቅ ሰው ትንሽ ሆነ መሰላችሁ! የምትገርም ማግኔት ናት ወንድሞቼ፡፡ እኔን ቀልበቢስ ሞነጫጫሪውን ብቻ ሳይሆን ግርማ ካሣንና መስከረም አበራን የመሰሉ ግሩም ጸሐፊዎችን ሁሉ ጥርቅም አድርጎ በ15 ነጥብ 9 ቁጥር ምስማር ዘግቷቸዋል፡፡ እስካሁን ያወጣልን የነበረው እርሱ የሚፈልገው ሀገራዊ ምስል እስኪከሰት እንደመናጆ ቆጥሮን ነበር ማለት ነው፡፡ ይሁን፡፡ ይህም ተራውን ጠብቆ ያልፋል፡፡ “ያልፋል” ብለን ያላለፈ ባለመኖሩ በዚህ አቋምም አናፍርም፡፡ ደግሞም ሰው ነውና አይፈረድበትም፡፡ በወዳጅነታችን የምንቀጥልበት ሌላ አዲስ ዘመን መምጣቱ ስለማይቀር ልፋቱን ሁሉ በነዚህ አሥር ወሮች ምክንያት አንሰርዝም፡፡ የሆነውንና እየሆነ ያለውን መናገር ግን አስፈላጊና ተገቢም ነው፡፡ መተፋፈር የለም፡፡ ለምኑ ተብሎ?

በነገራችን ላይ የአዲሱ የዘረኝነት ቅኝት ጓደኛሞችን ሳይቀር እያናቆረ ነው፡፡ ዛሬ ጧት የሰማሁትን ሹክ ልበላችሁ፡፡ አንድ ሠርግ ላይ ነው፡፡ ትናንትና ማታ፡፡ እሁድ የካቲት 3 ቀን 2011 ዓ.ም፡፡ ልጆቻቸው በአንድ የሚማሩና የሚያጠኑ፣ እነሱም ልጆቻቸውም እንደአህያ ጡት የማይነጣጠሉ አንድ ኦሮሞና አንድ ራያ በሠርጉ ታድመዋል፡፡ ሞቅታ እየጨመረ ሲሄድ ኦሮሞው በራያው ላይ ዘረኝነትን የተንተራሰ የነገር ዶፍ ያወርድበት ገባ፡፡ መብሰልና ማስተዋል ደግ ነውና ያ ራያ በአዲስ የጎሠኝነት ወረት የሚያጓራውን ጓደኛውን ችላ በማለት ወደ ቤቱ ሄደ፡፡ ብዙ ችግር ሊደርስ ሲል ሰዎች ጣልቃ ገብተው ለማብረድ ሞከሩ፡፡ የተነጋሩትን እዚህ መናገር ስላልፈለግሁ ትቸዋለሁ፡፡

እናም እባካችሁን ወገኖቼ ጊዜያችሁ “የመጣ”ም፣ ጊዜያችሁ “ያለፈ”ም፣ ገና ጊዜ ይመጣልናል ብላችሁ በተስፋና በጉጉት የምትጠባበቁም ሁለ ነገራችሁን በአግባቡ ያዙት – ብትችሉ ሰው ሁኑ፤ እንደሰውም ለማሰብ ሞክሩ – በጊዜና በሁኔታ የሚንሸራተት ስብዕና አይኑራችሁ፡፡ ሁሉም ቀሪ ነው፡፡ ይህች ምድር የስደት ሥፍራ እንጂ በአንድ ወይ በሌላ ጠፊ ነገር ልንኮራባትና ልንኮፈስባት የምንችልባት አይደለችም፡፡ ሥልጣን አላፊ ነው፤ መልክና ውበት ረጋፊ ነው፤ ሀብትን የኪሣራና የዕዳ ብል ይበላዋል፡፡ ዕድሜም ያረጃል፤ ሞትንም ተሸክመነው የምንዞረው ወንድማችን ነው፡፡ ለዚህች እንደጤዛ ለምትረግፍና እንደጉም ለምትበን ምድር ብለን ታዲያ በወገናችን ላይ ለምን እንጨክናለን? በጊዜ አመጣሽ ነገሮች ቀላልነታችንን እያወጣን አንዋረድ፡፡ ጥጋብንና ዕብሪትን በቅጡ ያልያዘ ሰው ብዙ ርቀት አይጓዝም፡፡ እንደጎማ ይተነፍሳል፡፡ ይዋረዳል፡፡ ይቀላል፡፡ በቅጡ ያልተያዘ ማግኘትና ማጣት ሰውን ትዝብት ውስጥ ይከታል – በትንሹ ሊያውም፡፡ አለበለዚያ ለጥጋበኛ ጥጋበኛን መላክ የማይሳነው ፈጣሪ ይዋል ይደር እንጂ እርሱንም የሚያንቆራጥጥ ሌላ ጥጋበኛ ወይም ፍርድ አስተካካይ ይልክበታለል፡፡ ከምናየው ካልተማርን በውነቱ ሞኞች ነን፡፡ ከዚህ ነጥብ አኳያ አስተዋይነት የጎደላቸው ብዙ ጥጋበኛ ባለጊዜዎችን እየታዘብን ነውና ለራሳችሁና ለቀሪ ቤተሰባችሁ ስትሉ ጥጋባችሁን በልክ እንድትይዙት አደራ እንላለን፡፡ ሻል ያለ አስተሳሰብ ያላችሁ የየጎሣው ወገኖችም ምከሯቸው – በፍጹም አያዋጣም፡፡ መለስ እንደዚያ በቁሙ ተፈረካክሶ የሞተው በጥጋቡና በዕብሪቱ ሳቢያ መሆኑን አንርሳ፡፡ የበረከት ስምዖን ጥጋብና ዕብሪት ባህር ዳር ላይ “ኢንተርኔት እንዲናፍቀው” አድርጎታል፡፡ ገና ምን ታየና ደግሞስ!

ከፍ ሲል ወደጀመርኩት ተመለስኩ፡፡ እንደአጠቃላይ አውነት ከሆነ ጆሮዋችን መስማት የሚፈልገውን ብቻ እንዲሰማ ካደረግን፣ ዐይናችን ማየት የሚፈልገውን ብቻ እንዲያይ ከፈቀድን፣ አንጎላችን ማሰብ የምንፈልገውን ብቻ እንዲያስብ ካስገደድንና መሬት ላይ የፈጠጠውን እውነት ከካድን የሁለት ጌቶች ባርያ ሆን፡፡ እንደፈረንጆቹም በ double standard አራማጅነት ታወቅን፡፡ ለሆዳችን አደርን፡፡ እውነትን ጠላን፡፡ ለሚጠፋ ነገር ሰገድን፡፡ ስብዕናችንን አጣብቂኝ ውስጥ ከተትን፡፡….

በነገራችን ላይ ዘረኝነትና የፍየል ሥጋ አንድ ናቸው፡፡

የፍየል ሥጋ ሁሉም ሰው እኩል አይመገበውም፡፡ በሽተኞች ይጠነቀቃሉ፡፡ ምክንያቱም የፍየል ሥጋ የሚበላ ሰው የውስጥ ህመሙን ሁሉ ይበረብረውና ገሃድ ያወጣበታል – ፍየል የማትበላው ነገር ስለሌላት – ይገርማችኋል እባብን ጭምር – ይህ ነገር ከዚያ ይመነጫል የሚሉ አሉ – በሌላም በኩል ፍየልን ከሰይጣን ጋር ስለሚያመሳስሏት ከዚያም አኳያ የሚያያይዙት ወገኖች አሉ – ብቻ የፍየል ሥጋ የተደበቀን በሽታ ሳይቀር ይቀሰቅሳል፡፡፡ ስለዚህም የፍየልን ሥጋ የሚበላ ሰው የሠራ አካላቱ ጤና መሆኑን መፈተሸ አለበት፡፡ አለበለዚያ ጠቅሞ ላይጠቅመው ነገረኛ ሥጋ በልቶ ለበሽታ ሊዳረግ ይችላል – እንደኔ አነሳስ ለትዝትብም፡፡ ፖለቲካችንም የፍየል ሥጋ ሆና! ሆ!

አዎ፣ “የዘሬን ብተው ያንዘርዝረኝ” ነው ነገሩ፡፡ አዎ፣ “ያንተ ልጅ የኔን ልጅ መትቶት ከሆነ ምች ይምታው፤ የኔ ልጅ ያንተን ልጅ መትቶት ከሆነ ግን መቼም…” እንዲሉ እየሆነ ነው ነገሩ፡፡ አዎ፣ “ለራስ ሲቆርሱ አያሳንሱ ነው” አካሄዳችን ሁሉ፡፡ አዎ፣ “የኔ ባል ካንቺ ባል ይበልጣልና ሽሮ አበድሪኝ” እንዲሉ ነው እማዎች፡፡ በርግጥ ምን ዓይነት የዘመን ሙጣጭ ውስጥ ገባን? እንዲህ ፍርክስክሳችን የወጣው የዱሮ አባት እናቶቻችን እንዴት አድርገው ፈጣሪን ቢያስቀይሙት ይሆን?…

አብርሃ በላይ ስለትግሬ በጨረፍታም ቢሆን ከነካህ ጽሑፍህን የጎሪጥ ያይብሃል  – መለጠፉ ይቅርና፡፡ ግንቦት ሰባትንና የወቅቱን ፖለቲካ ከነቀፍክ ወይም እየሆነ ያለውን ከተነፈስክ ኢካድፍ ከንፈሩን ይነክስብሃል – መለጠፉን ተወውና፡፡ ኦሮሞንና በፊንፊኔ ፍቅር ያበዱትን እነታከለ ኡማን መንካት አይደለም አሉታዊ በሆነ መንገድ በተዛዋሪም ቢሆን ጠቀስ ካደረግህ ዘሀበሻ ጀርባውን ይሰጥሃል፡፡ አማራን ከነካህ የአማራነት ፍቅር ከኢትዮጵያዊነትና ከሰውነት ደረጃ የሚበልጥባቸው አዲስ ግልብጦች ይፎክሩብሃል (ስላልተነሳሁበት እንጂ አማራን ሊነገር የሚሰቀጥጥ መስዋዕትነት ከከፈለበት ኢትዮጵያዊነት ለመለየት የሚደረገውን ጥረት በአዲስ ወያኔነት እንደምፈርጀው በዚህ አጋጣሚ መግለጽ እወዳለሁ፤ አያዋጣም፤ አማራን የጎሣ ከረጢት ውስጥ መክተት የማይቻል መሆኑን ብረዳም ሙከራው ግን ጥቂቶችንም ቢሆን ማሳቱና ማሳሳቱ አይቀርምና በዚህ ረገድ ጥንቃቄ ይደረግ)፡፡ ሕወሓትን ከነካህ – ያው አንዴውኑ ተነክቶና ተነካክቶ መዘረሩ ወይም የተዘረረ መምሰሉ በጄ እንጂ – ምድረ ወያኔ በየአይጋፎረሙና በየትግራይኦንላይኑ ይንጫጫብሃል፡፡ ሁሉንም በአንዴ ማስደሰት ዶሞ አትችልም፡፡ ጨለማንና ብርሃንን ለማቀላቀል የሞከረችው ብቸኛዋ ፃዲቅ ሴት ክርስቶስ ሠምራ ናት፡፡ ሰይጣንን ከእግዚአብሔር ላስታርቅ ብላ ስትነሳ – እርሱም ሀሰት ይሁን እውነት አላውቅም፡፡ በኛ ሁኔታ ግን አንዱን ስታወደስ ሌላው ያበሻቅጥሃል፤ አንዱን ድርጅት ስትሄስ ነፈዝ ደጋፊው በስድብ ያጥረገርግሃል፡፡ ተቸገርነ፡፡ No politics of any nation on this bloody planet is more polarized than that of ours now. በለበጣ የሚያስቀውና እጅጉን የሚገርመው ደ’ሞ ሁሉም እየተነሣ “ዴሞክራሲ፣ ዴሞክራሲ” እያለ በዴሞክራሲ ስም ሲቀልድ ቅንጣት አያፍርም፡፡ ቃሊቱን የቃቃ መጫወቻ አደረጓት፡፡ ዴሞክራሲ ሲሞቅ በማንኪያ ሲቀዘቅዝ በእጅ እንዳልሆነ የምዕራቡንና የአውሮፓን ዴሞክራሲ በማየት መረዳት ይቻላል፡፡

ለነገሩ ዴሞክራሲ ወደ ኢትዮጵያ ሊመጣ አይችልም፡፡ ምን ቅብጥ አድርጎት? ዱሮም ዱሮ ነን – አሁንማ አንድ ሁለት ቃል ከመነጋገራችን “አሃ! ከምዚ ዝብለኒ ዘሎ ትግራዋይ ስለዝሆንኩ እምበር…?”፣ “አሃ፣ እንዲህ የሚለኝ አማራ ስለሆንኩ አይዶል እንዴ…?”፣ “አካሲሚቲ! ሲላ ኦሮሞ ታኤቲ …?” እየተባባልን ከእንስሳትም ባሕርይ በወረደና እጅግ ባፈነገጠ ሁኔታ እየተመነቃቀርን እንገኛለን፡፡ መልካምን ነገር በባዶ መሬት ቢመኙት ጠብ የሚል ነገር የለም፡፡ አታሟርትብን የሚለኝ ካለ እርሱ ማኅበረሰብኣዊ እውነቱን እንዳያይ ሌሎች ሰዎች ጋርደውበት ወይም ቁሣዊ ሕይወቱ በቦሌና በባሌ ተመቻችቶለት በተመሳስሎ የድሎት ግርዶሽ ዐይኑ የተሸፈነበተ ግልብ ወገን ነው፡፡ እንጂ ሀገራችን በአሁኑ ቅጽበት ቤንዚን ተርከፍክፎበት ክብሪት የተጫረበት ደን መሆኗን ለመረዳት ሌላው ቀርቶ የታከለ ኡማ መንግሥት በአሁኑ ወቅት የሚሠራቸውን አዲስ አበባን በአዲሱ ቋንቋ oromize የማድረግ የ24/7 አጣዳፊ ተግባር መታዘብ ከበቂ በላይ ነው፡፡ ደግነቱ ግን ይህም ልክ እንደወያኔዎቹ ሁሉ ብዙ አይዘልቅም፡፡ የነዚህም ዕኩይ ተግባር ወረት በአጭር ጊዜ ይቀጫል፡፡ ኢትዮጵያን እየጠበቃት ያለውን ኃይል ያለመረዳት ችግር ነው ሰዎች ወደዚህ ዓይነት ብልጥነትን ማዕከል ያደረገ ጅልነት እየከተታቸው የሚገኘው – ከወያኔ የማይማር መቼም የመጨረሻው ደንቆሮ መሆን አለበት፡፡ እንጂ መለስ ዜናዊና ስብሃት ነጋ ከዓለም አቀፉ የሤረኞች ኅቡዕ ኃይል ጋር ተባብረው ማጥፋት ያልቻሏትን ሀገር ዛሬ ጃዋርና ታከለ ያጠፏታል ብሎ ማሰብ በትንሹ የዋህነት ነው – ብዙ ቡልሃ አለ – ኢትዮጵያን ከደራጎኑ የወያኔ ፈርዖናዊ አገዛዝ ነፃ ያወጣው ቄሮና አቢይ ወይም እነጃዋር ናቸው ብሎ የሚያምን ብዙ ጅል አለ – ይገርመኛል፡፡ እነዚህ ከማን አንሼዎች የሚከናቱት ክፍተት ያገኙ መስሏቸው ነው፡፡ ወያኔም እኮ ይህን መሰል ክፍተት ነው የተጠቀመችው፡፡ ከላይ የተላከው በአካል እስኪከሰት እንዲህ ያለ የሽግግር ሁከት የሚጠበቅና ያለም ነው፡፡

እርግጥ ነው – እንዲህ ያለው አካሄድ የተወሰነ ጉዳት ላልተወሰነ ጊዜ ማስከተሉ አይቀርም፡፡ ሰዎች መፈናቀላቸውና ሀብትና ንብረት ማጣታቸው የሚጠበቅ ነው፡፡ በሀገረ አሜሪካ – ሰለጠነ በሚባለው ዓለም ውስጥ አምስት ዓመት ተኑሮ ስንትና ስንት ቋሚና ተንቀሳቃሽ ንብረት ማፍራትና ከፕሬዝደንትነት ቦታ ውጪ – እርሱም እዚያው መወለድን ስለሚጠይቅ እንጂ በቀለምና በዘር አይደለም – ከዚህ የኃላፊነት ሥፍራ ውጪ ባሉ የሥልጣን ቦታዎች ተመርጦ ወይ ተመድቦ ማገልገል በሚቻልበት ሁኔታ እኔ 40 ዓመት በኖርኩባት ከተማ መጤ ከተባልኩ በጊነስ ቡክ ኦፍ ሪከርድስ መመዝገብና ለወደፊቷ ዓለማችን መሣቂያነት መብቃት አለበት – አሁንማ መሣቂያ መች ጠፋና – ሞልቶ! … ዶሮ መሬት ስትጭር ብዙ ነገር ታወጣለች – ስለዚህ ብዙ መጫር ላይኖርባት ነው፤ “በቀላሉ ጭራ መኖር ስትችል ለምንስ ብዙ መጫር አስፈለጋት?” ብሎ መጠየቅም ሞኝነት አይደለም፡፡ ለማንኛውም ግን ይቺ የወያኔ አካሄድ ለማንም አትጠቅምም፡፡

“ፍቅር ያዘኝ ብለህ አትበል ደምበር ገተር፤

እኛም አንድ ሰሞን እንዲህ አ’ርጎን ነበር” ብላ አቀንቅናለች ‹አብረኸት ባራኺ› ነፍሷን ይማረውና፡፡ (ሞታለች እንዴ ግን?)

ዴሞክራሲና ሃሳብን በነፃነት መግለጽ እንግዲህ እንደዚህ ነው፡፡ ለራስህ ሲሆን እስከፑንት – ለሌሎች ሲሆን አንድያውን ጥርቅም! ወይም በመለኪያና በመቁነን – እንደገዳም ሬሽን፡፡ አየ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን! ከስደትና በስደት እንኳን ምንም የማንማር ግትሮች፡፡

እኔ ደግሞ እላለሁ – አንድ ሰው የሚናገረው እውነት እስከሆነ ድረስ – እውነት ባይሆን እንኳን በተሳሳተ መረጃ ምክንያት የመሰለውን ግን ለጦርነትና ለዐመፅ የማይጋብዝ ሃሳብ እስከተናገረ ወይ እስከጻፈ ድረስ ሃሳብን በሃሳብ መሞገት እንጂ ማፈን ወይም ባልተመጣጠነ መሣሪያ ወግቶ በሚገኝ ድል መቦረቅ አስፈላጊ አይደለም፡፡ ባደጉ ሀገሮች መሪዎቻቸውን በጦጣና በዝንጀሮ፣ ሲፈልጉ በውሻና በጉማሬ እየመሰሉ ቢያወጡ ማንም ዝምባቸውን እሽ የሚላቸው የለም (እኛ ጋ እኮ ወዲያውኑ ማምለክ ወይም በሰይጣንነት ፈርጆ ማውገዝ እንጂ ማስተዋል ብሎ ነገር አልፈጠረብንም፤ አሁን አቢይን በትችት መልክ ተስቶህ ወይም አምነህበት ትንሽ ብትነካ … ኧሯሯ… ይወርዱብሃልኝ፡፡) ባደጉ ሀገሮች ሰዎች እላፊ ቢናገሩ እንኳን አበዱ ተብለው በአንባቢዎች ይተቻሉ እንጂ እነሱን እየተከተለ ጊዜውን የሚያጠፋ መንግሥታዊም ሆነ ግላዊ አካል ያለ አይመስለኝም፡፡ የኛ ሀገር እኮ የተለዬ ነው፡፡ ሁሉም ስላንተ እርሱ ነው የሚያውቅልህ፡፡ ሁሉም ምርጫህን እርሱ ነው የሚወስንልህ፡፡ የቤቢሲተሩ (babysitter) ብዛት ከቁጥር በላይ ነው፡፡ መንግሥት  ቤቢሲተር ነው፤ ተቃዋሚዎች ቤቢሲተር(ስ?) ናቸው፤ ጋዜጠኞች ቤቢሲተር ናቸው፤ ባለድረገፆች ቤቢሲተር ናቸው፤ ሁሉም እንዳልል ጥቂቶች ስለሚጨፈለቁብኝ ፈርቼ እንጂ አብዛኛው የግልም ሆነ የመንግሥት ሚዲያ ቤቢሲተር ነው፤ ታዋቂ ግለሰቦች ቤቢሲተር ናቸው፤ ነጋዴው ቤቢሰተር ነው፤ ሀኪሙ ቤቢሲተር ነው (ራስህን አሞህ እግርህን ሊያክምህ የሚጎነበስ እኮ አለ – ብትነግረውም በትዕቢት ተወጥሮ የማይሰማህ)፤ … እኛ እንግዲህ የት እንግባ? የዚህ ሁኔታ ምንጭ ሕዝብን መናቅ ነው፤ ሕዝብን ምርጫ እንደሌለው ባዶ ጭንቅላት (ነጮቹ ታቡላ ራዛ የሚሉት) እንደሆነ አድርጎ የመቁጠርና ራስን ሰማየ ሰማያት የመስቀል ልክፍት ነው፡፡ የሚገርም ሀገራዊ ቋሚ ልክፍት፡፡ ሕዝብ አያውቅም ካልን እንዲያውቅ መንገዶችን ማመቻቸት ነው፤ ትምህርትን በጥራት መስጠት ነው፤ የንቃተ ኅሊና ማሳደጊያ ማዕከላትን ማቋቋምና በሁሉም ረገድ መደገፍ ነው፡፡ ሕዝብን የማብቃት ሥራ መሥራት ነው፡፡ ራስንም ከሙስናና ከዘረኝነት ማጽዳት፣ በዕውቀትና ችሎታም ማነጽ ነው፡፡ …. በዚህ መልክ መቀጠሉ ግን ወደ ገደል መጓዝ ነው፡፡

እንግዲህ ስለኛ የሚገርም ጉዳይ ይችን ታህል ከተነፈስኩ በቃኝ፡፡ ግን ከጀርባቸውም ሆነ ከፊት ለፊታቸው ምንም ዓይነት ቁስል የሌለባቸው (የሚመስሉኝ – ቢያንስ)፣ ከፊትም ሆነ ከኋላ ገራፊና ተቆጣጣሪ ያልተመደበባቸው፣ ለእንጀራ ሲሉ የዴሞክራሲን ባህል እንደሸቀጥ ዋጋ የማያወጡና የማያወርዱ፣ በዘር ልክፍትም የማይሰቃዩ፣ ሙያን በእንጀራ የማይለውጡ፣ ዴሞክራሲን ለመተሻሻነትና ለመሞዳሞጃነት ወይም ለመመሳሰል ሲሉ የቃሉን ፍቺ በመዘንጋት ራሳቸውን ለትዝብት የማይዳርጉ እነ እንትናን የመሰሉ ግለሰቦችና ድረገፆች እንዳሉ በዚህ አጋጣሚ መናገር ተገቢ ነው – ማስታወቂያ እንዳይመስልብኝ ለጊዜው ስማቸውን መናገር አልፈለግም፡፡ እንጂ ወላድ በድባብ ትሂድ አሉ፡፡ በነገው ቀን የማያሳፍሩን ለፈይሣ የማይሉ፣ ለአምባቸው የማይሉ፣ ለፍትዊ የማይሉ፣ ዘበርጋ ሲነሳ ወከክ የማይሉ፣ ግምብወግሽ ስትጠራ ፊታቸውን ኮሶ የማያስመሰሉ፣ …. ጥቂትም ቢሆኑ ለኅሊናቸው ያደሩ አሉን – በምድረ በዳው ጉዟችን ጉልበታችን እንዳይዝል የሚያበረታቱንና ተስፋ የሚሆኑን፤ በበረሃማው ጠመዝማዛ መንገዳችን ምንጭ ሆነው የውኃ ጥማታችንን የሚያስታግሱልን – በድቅድቅ ጨለማ ውስጥ የብርሃን መቅረዝ የሚሆኑን እጅግ ጥቂት ሻማዎች አሉን – እግዚአብሔር እነሱን ያብዛልን፤ ከሀሰተኛና አስመሳይ ነቢያት፣ ጊዜ እየጠበቁ በዚህ ወይ በዚያ ሰበብ-አስባብ ከሚከዱን ግን ይጠብቀን፡፡ የዛሬው ማፈሪያ ታሪካችን በነገው ዕለት ሲለወጥ – የድል አጥቢያ አርበኛው ቢበዛና በዚያም ሥርዓት እንደእስስት ዐመልን ቀይሮ ማስቸገሩን ቢቀጥልም – ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ተገቢ ክብራቸውን ያገኛሉ፡፡ ዛሬ የተጎሳቆሉ፣ ኑሮና ሕይወታቸውን ለማሻሻል ሲሉ ሕዝባዊውን የሀገር ትንሣኤ ዓላማና ትግል እንደኢሣው በጭብጥ ምሥር ያልለወጡ ወገኖቻችን ይህችን ሀገር ከፈጣሪ እጅ ተረክበው እንደገና የዓለም ቁንጮ ያደርጓታል፡፡ ከሥር የነበረ ቁንጮ ቢሆን ያስደስታል የፈጣሪን ፍርድ ትክክለኝነትም ያሳያል  እንጂ አያስከፋም፤ ትዕቢተኛና ትምክህተኛም አያስብልም – የቀኝ ኋላ ዙር አንዱ ትርጉምም ይሄው ነውና! መጽሐፉስ “ፊተኞች ኋለኞች፤ ኋለኞችም ፊተኞች ይሆናሉ” ይል የለምን?

የህብረተሰቡ የፀጥታ ስጋቶች እንዲቀረፉ የአካባቢውን የፀጥታ ኃይል በተለየ ሁኔታ የማደራጀት ስራ በትኩረት እየተሰራ ነው

የአማራ ክልል ሰላምና የህዝብ ደህንነት ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ ብርጋዴል ጄኔራል አሳምነው ፅጌ

‹‹የህብረተሰቡ የፀጥታ ስጋቶች እንዲቀረፉ እና ልዩ ተልዕኮ ተሰጥቷቸው የአካባቢውን ሰላም የሚያደፈርሱ አካላትም ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ ለማድረግ የአካባቢውን የፀጥታ ኃይል በተለየ ሁኔታ የማደራጀት ስራ በትኩረት እየተሰራ ነው፡፡›› ብርጋዴር ጄኔራል አሳምነው ጽጌ

• ችግሩን የሚፈጥሩት አካላት በማህበራዊ ሚዲያ የተደራጀ ቡድን ስላላቸው በሚነዙ የሃሰት ወሬዎች መረበሽ እንደሌለበት እና ማጣራት እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

ባሕር ዳር፡ የካቲት 04/2011 ዓ.ም(አብመድ) በአማራ ክልል በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ደምቢያ ወረዳ ሰሞኑን አለመረጋጋት ተፈጥሯል፡፡ በፀጥታ ችግሩም በሰው ህይዎት እና በንብረት ላይ ጉዳት ደርሷል፡፡ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት የክልሉ መንግስት ጥረት እያደረገ ነውም ተብሏል፡፡

የአማራ ክልል ሰላምና የህዝብ ደህንነት ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ ብርጋዴል ጄኔራል አሳምነው ፅጌ ጉዳዩን አስመልክተው ለአማራ ብዙኃን መገናኛ ድርጅት በስልክ ማብራሪያ ሰጥተውናል፡፡ በዞኑ ያለው የፀጥታ አለመረጋጋት ችግር ቆይቷል፡፡ በፀጥታ ችግሩም የዜጎች ህይዎት አልፏል፣ መፈናቀልና ጉዳት ደርሷል፣ መንገዶች በተረጋጋ ሁኔታ ለስራ ምቹ እንዳይሆኑ ተደርጓል እንዲሁም የነዋሪዎቹ ችግር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጎላ እንዲሄድ በጣም የተደራጁ፣ የተቀናጁ እና በስልት የሚመራ የጥፋት ሴራ በአካባቢው በየቀኑ የሚፈጠር ክስተት ሆኗል ብለዋል ጀኔራል አሳምነው፡፡
ይህንን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት ከአካባቢው የፀጥታ ሃይል እና ከመከላከያ ጋር በጋራ እየተሰራ ነው ያሉት ቢሮ ኃላፊው ከዚህ በተጨማሪም በእያንዳንዱ ቀበሌ የአካባቢ ፀጥታ መዋቅሩን በማሰልጠን እና በማደራጀት የአካባቢውን ፀጥታ በአስተማማኝ ሁኔታ ለመቆጣጠር እየተሰራ እንደሆነ ነግረውናል፡፡

የህብረተሰቡ የፀጥታ ስጋቶች እንዲቀረፉ እና ልዩ ተልዕኮ ተሰጥቷቸው የአካባቢውን ሰላም የሚያደፈርሱ አካላትም ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ ለማድረግ የአካባቢውን የፀጥታ ኃይል በተለየ ሁኔታ የማደራጀት ስራ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን እና ይህም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ቢሮ ሃላፊው ተናግረዋል፡፡ አሁን የጀምርናቸውን የፀጥታ ማስከበር ስትራቴጅካዊ ስራዎች ስናጠናቅቅ በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ አሁን ያለው የተደራጀ እና በአግባቡ የታጠቀ የሁከት ኃይል በአጭር ጊዜ የሚታቀብበትና የሚቆምበት ሁኔታ ይፈጠራል ብለን እናስባለን ነው ያሉት ጀኔራል አሳምነው፡፡

ትልቁ የፀጥታ ኃይል ህዝቡ ነው የሚሉት ጀኔራል አሳምነው፤ ህዝቡን የመረጃ ምንጭ እና የእንቅስቃሴው አካል ለማድረግ አቀናጅተን በክልሉ ጫፍ እስከ ጫፍ እንሰራለን፡፡ ምክንያቱም በህዝቡ ላይ እየደረሰ ያለው መፈናቀል እና ጉዳት ቀላል አይደለም ብለዋል፡፡
እስካሁን በተፈጠረው ችግር አጥፊዎችን ለህግ በማቅረብ በኩል ምን እየተሰራ ነው ስንል ላቀረብንላቸው ጥያቄ መልስ የሰጡት ቢሮ ኃላፊው ለህግ መቅረብ ያለበት አካል እየተጣራ ለህግ ይቀርባል ብለዋል፡፡ ክልሉን የለየለት የጦርነት ቀጠና ለማድረግ በመቶዎች የሚቆጠሩ የሽብር ቡድን አባላትን እያስታጠቁ የሚያስገቡ ኃይሎች አሉ የሚሉት ኃላፊው በዚህም ዞኑ አይቶት የማያውቀውን ቀውስ እንዲያስተናግድ ምክንያት ሆነዋል፡፡ የክልሉ የፀጥታ መዋቅር የመጀመሪያ ስራውም እነዚህን የሽብር ኃይሎች በቁጥጥር ስር በማዋል ለህግ ማቅረብ፤ በህዝቡና በፀጥታ ኃይሉ የተቀናጀ ስራ ለመመከት እየተሰራ እንደሆነ ነው የተናገሩት፡፡

እንደ ጀኔራል አሳምነው ገለፃ በህግ ቁጥጥር ስር እንዲውሉ በፍርድ ቤት ማደኛ ወጥቶባቸው ነገር ግን በርሃ የገቡ ሃይሎች አሉ፡፡ እነርሱም ለአካባቢው ሰላም መደፍረስ ምክንያት ናቸው፡፡ እነዚህን አካላት በህግ ቁጥጥር ስር ለማዋል ካልተቻለ ደግሞ በመረጡት አግባብ ምላሽ ለመስጠት ዝግጅት ጨርሰናል ብለዋል፡፡
በሌሎች የክልሉ አካባቢዎች ተመሳሳይ ችግር እንዳይከሰት የጥፋት ኃይሎቹ ለዘመናት በአደረጃጀት ለመረጃ ሲጠቀሙባቸው የቆዩትን የፀጥታ መዋቅር ማረምና ማስተካከል እንዲሁም የፀጥታ ኃይሉን በአዲስ ለማደራጀት እና ስምሪት ለመስጠት እየተሰራ እንደሆነ ነግረውናል፡፡

በቀጣይ ለምንሰራቸው የሰላምና የፀጥታ ስራዎች የህዝቡ ድጋፍ በርካታ ነው የሚሉት ጀኔራል አሳምነው የመጀመሪያው የአማራ ህዝብ ታሪካዊ ጠላቶች ያላቸውን ሃብትና አቅም ሁሉ ተጠቅመው አካባቢውን የጦርነት ቀጠና ለማድረግ እየሰሩ መሆኑን ማወቅ ይገባል፡፡ ሲቀጥል በአካባቢው እየተፈጠረ የሚሰጠን የጎሳ አጀንዳ ውሸት መሆኑን መረዳት ነው፡፡ ስትራቴጂያዊ በሆነ መንገድ በአማራ ህዝብ መካከል ልዩነት በመፍጠር ሊያተራምሱን ለሚፈልጉን ሰዎች መሳሪያ መሆን የለብንም ብለዋል ጀኔራል አሳምነው፡፡ ችግሮቹን ህዝቡ እንዲያርምና እንዲያስተካክል እድል መስጠት አለበን፡፡ ህብረተሰቡ በየአካባቢው የተለየ እና ለጥርጣሬ የሚዳርግ እንቅስቃሴ ካየ ለፀጥታ ሃይሉ ማሳወቅ እንዳለበት እና ችግሩን የሚፈጥሩት አካላት በማህበራዊ ሚዲያ የተደራጀ ቡድን ስላላቸው በሚነዙ የሃሰት ወሬዎች መረበሽ እንደሌለበት እና ማጣራት እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

የክልሉን ፀጥታ በተጠና እና በተደራጀ ሁኔታ የሚረብሹ አካላት ክልሉ የልማት ስራዎቹን እንዳይሰራ እና ለውጥ እንዳያመጣ፤ ሲቀጥልም የስራ ዕድል ያልተፈጠረለት ወጣት ለውጡን እንዲያማርር ታስቦቦት የቤት ስራ እንደተሰጠን በማወቅ በክልሉ ውስጥ ያለን ማንኛውንም ልማት ከማስተጓጎል በመታቀብ ሊያግዘን ይገባል ብለዋል ጀኔራል አሳምነው፡፡

ዘጋቢ፡-ታዘብ አራጋው

የጎሳ ቅኝት የተቃኜ መተካካት የሚያመጣው ውድመት ። ሂልተን አዲስ አበባን እንደ ምሳሌ። (በዳዊት ሳሙኤል)

ዛሬ ደግሞ ምኑን ከምኑ አገናኜህብን እደምትሉኝ እገምታለሁ። ሰሞኑን በተለያዩ መገናኛ ብዙሀን አዲሱ የለውጥ    አመራር በአዲስ አበባ እና በፌደራን ደረጃ በፊት ወያኔ ያደርገው ነበር ከሚባለው በከፋ ሁኔታ ቦታዎችን፣ ስልጣንንና ኃላፊነትን በአንድ ቋንቋ ተናጋሪዎች እየተሞሉ ነው። የሚል ዜና በሰፊው እየተሰራጨ መሆኑን ስሰማ የዛሬ 20 አመት ሂልተን ሆቴል ለስልጠና ከቱሪዝም ኮሌጅ ተልኬ ያየሁትን የሰማሁት ሁኔታ ጋር ስለተመሳሰለብኝ ለአንባቢ ላጋራ ፈለኩኝ። አይደረግም ብዬ አልከራከርም። ነገር ግን ከላይ ያሉት አመራሮች ግን ሙሉ በሙሉ በእቅድ ይሰሩታል ለማለት ግን አልደፍርም። የሚሾመው በጎሳ ፖለቲካ የሰከረ፣ በመቦጥቦጥ ምኞት የጦዘ ብዙ ከንቱ ግን እንደሚኖር ከሀገሪቱ የፖለቲካል ሂስትሪ የሚጠበቅ ነው። ከአሁኑም ሁላችንም በአንድ ላይ ቁመን ካላወገዝነው መጨረሻው ጥፋት ነው።

እስኪ መጀመሪያ ስለ ሂልተን ትንሽ ልበል። ሂልተን አዲስ አበባ በመሀል አዲስ አበባ ሁለቱን ቤተመንግስቶች አማካኝ በሚያደርግ ስትራቴጅክ ቦታ ላይ በ1961 ዓ ም በግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ስላሴ ዘመን ተመሰረተ። በውስጡ ከ400 በላይ አልጋዎች፣ የመዋኛ ገንዳ፣ የሳውናና ጃኩዊዚ አገልግሎት፣ የሀገር ምርቶች መሸጫ ሱቆች፣ የስፖርት ማዘውተሪያ ቦታዎች( ጎልፍ፣ የሜዳና የጠረንጴዛ ቴንስ፣ ጅም፣ )፣ የስብሰባ አዳራሾች፣ እጅግ የተዋቡ የተለያዩ ሬስቶራንቶችና መጠጥ ቤቶች ያሉት ሲሆን 11ኛ ፎቅ ላይ ሙሉውን አዲስ አበባን እያዩ የሚዝናኑበት ሬስትቶራንት ለከፍተኛ እንግዶች ያለበት፣ በዚሁ ፎቅ ላይ እጅግ የተዋበ ለሀገር መሪዎች ተብሎ ከፊት ለፊት መግቢያው ላይ የንጉሰ ነገስቱ ወርቃማ የአንበሳ ሀውልት ጉብ ያለበት የምኝታ ክፍል አለ። በአጠቃላይ ግቢው በብዙ በተለያዩ ዛፎችና አበቦች የተሞላ እጅግ የተዋበ ግቢ ነበር።

ከ400 የማያንስ ሰራተኛ የሚያስተዳድር፣ ሰራተኞቹ ለድርጅቱ በጣም ታማኞች ነገር ግን በጣም ትንሽ ደመወዝ የሚከፈላቸው ነበሩ። ነበሩ የምለው የዛሬውን ስለማላውቅ ነው። አሰሪዎቹ ትንሽ የውጭ አገር ሰዎች ቢኖሩበትም 90% አበሻ አሰሪዎች ናቸው።
ወደ ተነሳሁበት ርእስ ልምጣና እኔ እዛ በነበርኩ ግዜ ሰራተኞቹ የሚደርስባቸውን ጫና ለመታገል እስከ ስራ ማቆም አድማ እርምጃዎችን ይወስዱ ነበር። እንዳለመታደል ሁኖ አሰሪዎቹ የብዙ አመት ልምድ ስላላቸው የማህበር መሪዎችን በጥቅማ ጥቅም እየያዙ ብዙ ቆራጥ ሰራተኞችን እስከ ስራ ማባረር እና አንዳንዶቹንም እስከ ህይወት መጥፋት ድረስ የደረሱ አሉ ይባላል። በወቅቱም ጸጋየ የሚባል የትግራይ ልጅ ብዙ ሰው ይወደው የነበረ በምግብ ተመርዞ ተገደለ ተብሎ ተጠርጣሪዎችም ታስረው ነበር። የተወሰኑ ሰራተኞችም ከስራ ተባረው በማይሰራው ፍርድ ቤት እየተንከራተቱ ነበር።
በሆቴል ቤት ከፍተኛ ቁልፍ ቦታዎች የሚባሉት የእንግዳ አቀባበል፣ የፋይናንስ ክፍል ፣ የሴኩሪቲ ኃላፊነቶች ፣ የምግብና መጠጥ ክፍል ናቸው። በደርግ ግዜ እና ወያኔ በገባባቸው የመጀመሪያ አመታት ኤርትራውያን በብዛት ቁልፍ ቁልፍ ቦታዎችን ይዘው ነበር ይባላል። በሗላ ግን የነበረው የሀገሪቱ የፖለቲካ ሁኔታን ተገን በማድረግና የኤርትራ ውያን መባረርን ተከትሉ ቁልፍ ቁልፍ ቦታዎች በትግራይ ተወላጆች መያዝ ጀመሩ። በወቅቱ የሴኩሪቲ ሀሌፊ የነበረ ሊላይ የሚባል የትግራይ ሰው ተስፈንጥሮ የእንግዳ አቀባበል ኃላፊ ሆኖ ሰራተኛውን ያም ሰው ነበር። እንደ ስራተኞቹ ትረካ በጠላትነት የታዩትን ሰራተኞች በልብስ ማስቀመጫ ሳጥናቸው ሳይቀር የድርጅቱን ንብረት በድብቅ በማስቀመጥ ድንገት ፍተሻ ተካሄደ በማለት ሰራተኞች ይባረሩ እንደነበር በምሬት ይናገሩ ነበር። ባጠቃላይ እድገት በዝምድና ፣ በታማኝነት ብቻ ነበር የሚሰጠው። አድርባዩ ለሆዱ እያንዳንዷን መረጃ ይዞ በመሮጥ የበቀል እርምጃ ስለሚወሰድበት ሰራተኛው በፍጹም አይተማመንም ነበር። አንድ ሰው በፊት እቃ አጣቢ የነበረ ሰው በዚሁ ስራው ተነስቶ የኮንስያዥ ሀላፊ እስከመሆን እንደደረሰ ሰራተኛው እርስ በእርሱ ይንሾካሾክ ነበር። የድርጅቱ መኪኖች የሚጠገኑት፣ ለሆቴሉ እቃ የሚቀርበው ሁሉ እንዲሁ በዘመድ አዝማድ የተተበተበ ነበር ይላሉ። እንግዲህ በዚህ ሆቴል ሁሉም አልጋ ዎች በሚያዙበት ወቅት በ10 ሽዎች የሚቆጠር ዶላር ገቢ በቀን ከአልጋ ብቻ ይገባል ማለት ነው።
መቼም የሁሉም ነገር መጨረሻ አለውና እነዚህ ማኔጀሮች ህወሀት ሲከፋፈል የነ እሰየ አብርሀ ወገን ነበሩና በተራቸው የዱላ ናዳ ሲወርድባቸው ተበታተኑ። ዋናውም ጠፍቶ ወደ አሜሪካ ኮበለለ። ከዚህ ታሪክ በኋላ ግን እኔም ለትንሽ ግዜ ስልጠናየን ጨርሼ በጊዜያዊ ሰራተኝነት ለአንድ አመት አካባቢ ተቀጥሬ ስለነበር የማቀውን ያየሁትን እጽፋለሁ።
ትግሬዎቹ ሲነቀሉ በፋይናንስ የስራ ክፍል ውስጥ ይሰራ የነበረ መልከ መልካም የአምቦ ሰው አቶ ከበደ ቦረና የሚባል የእውቀት ችግር የሌለበት ሰው የፋይናንስ ሀላፊ ሁኖ ተሾመ ። ወዲያውኑ ሊላይ የተከለው ሁሉ መነቀል ተጀመረ። የእንግዳ አቀባበል ኃላፊው ትንሽ ወንድሙ ሆነ፣ በሁሉም የስራ ክፍሎች የሂሳብ ተቆጣጣሪዎች የእህት ልጅ፣ የአጎት ልጅ ተደረጉ፣ የሾፌሮች አለቃ፣ ከአየር መንገድ እንግዶችን አምጭ ሀላፊ ደግሞ አጎቱ ነው የሚባል ሰው ተሾመ። ባጠቃላይ ያለምንም ሀፍረት ሁሉም ቦታ በሚባል መልኩ ተወረረ።
በወቅቱ ከአስር አመት በላይ በሴኩዩሪቲ የስራ ክፍል በጊዜአዊነት ያገለገሉ ሰራተኞች ቋሚ እንሁን ብለው ወደ ክስ በመሄዳቸው ድርጅቱ ድፖርትመንቱን ሙሉ በሙሉ አፍርሶ ለግል የጥበቃ ድርጅት ኮንትራት ሰጥቶ ከስራ አስወጣቸው። በዚህ ወቅት በሌሎች የስራ ክፍሎች እስከ 19 አመት በጊዜአዊነት የሰሩ ጎስቋላ ሴቶች በድርጅቱ ውስጥ ነበር። ክስ እንደሚመጣባቸው ሲያውቁ ጊዜያዊ ሰራተኞችን ተከታታይ ጊዜ አይሰሩም ለማስባል ሁላችንንም አንድ አንድ ወር እያሳረፉ በማሰራት ሰራተኛው ላይ የጭንቀት ጦርነት ከፈቱበት። በወቅቱም ከነበሩት ለምን? ብለው ከሚጠይቁ ደፋሮች ውስጥ ተፈርጄ አንድ ወር አሳረፉኝ። በዚህ ወቅት 24 ልጆችን አስተባብረን የክስ ወረቀት ይዘን መጥተን ክሱ እስከሚፈረድ ማባረር አትችሉም ተብለው ወደ ስራ መለሱን። የማይነካው የድርጅቱ የጭካኔ ጥግም ተደፈረና ከዚያ በኋላ ሁሉም ወደክስ መሮጥ ተጀመረ። እኔ ሌላ የተሻለ ብየ በወቅቱ ወዳመንኩበት ቦታ ሌላ ስራ በማግኜቴ ሄድኩ እንጅ ጓደኞች ቋሚ እንዲሆኑ የሚል ተፈርዶላቸው ገቡ።
በወቅቱ ቋሚው ሰራተኛ የስራ ማቆም አድማ ሲጠራ የሰራተኛ ማህበር መሪው 5 ደረጃና የደመወዝ ጭማሪ ሲደረግለት የሰራተኛውን ትግል ከማኔጀሮቹ ጋር ተመሳጥሮ አመከነው። ባንድ ወቅትም የኢትዬጵያ ሰራተኞች ስብሰባ ተገናኝተን እንዴት እንዲህ ታደርጋለህ ስለው። ” ወንድሜ እኔ ጡረታ ለመውጣት የቀረኝ ግዜ አምስት አመት አልቀረኝም፣ የሀገሩ ባለስልጣናት መብትህን ብትጠይቅ ጥይት ነው ምላሻቸው፣ 30 አመት ሰርቼ ያላገኜሁትን ገንዘብ ደመውዜ ላይ ሲጨምሩልኝ ለምን ብየ ነው ዝም እምለው?” ብሎ ያለምንም ሀፍረት አመነልኝ። በሗላም ደጋግሞ እንዲመረጥ ይደረግ የነበረውን ሸፍጥ ተረከልኝ።
በወቅቱ የድርጅቱ ማኔጀር አንድ ጀርመናዊ ክላውስ ሻርክ የሚባል እጅግ አምባገነን ከሀበሾቹ ጋር ሁኖ ነበር ይህ ሁሉ ግፍ የሚሰራው። ለሁሉም ግዜ አለው እንደሚባለው እነዚህም በተራቸው ወያኔ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የሚኖሩ በድብቅ ለኦሮሞ ነጻነት ግንባር የገንዘብና የውስጥ ድርጅት ስራ ይሰራሉ ብሎ በርካታ ባለ ሀብቶችን ባሰረ ግዜ ከሀዊ ሆቴል ማኔጀር ጋር ጠራርጎ ዘብጥያ ከተታቸው። በወቅቱ ወያኔ ወለጋ ውስጥ ለገሰ ወጊ የተባለን የኦነግ የሽምቅ መሪ ገደልኩ ብሎ ከበሮ የሚደልቅበት ወቅት ነበር። በወቅቱ ግን የለገሰ ምክትል የነበረው ለገሰ ከመገደሉ በፊት እጁ ንና ሙሉ መረጃዎችን አምስተኛ ፖሊስ ጣብያ አምጥቶ ጓደኞቹን ከድቶ እንዳስጨረሳቸው ውስጥ አዋቂዎች ያወሩ ነበር። ከአስመራም በቀጥታ ከኦነግ አመራሮች ወያያኔ ሙሉ መረጃ ይመጣለት ነበር። እኒህ ሁሉ ሰዎች አሁን የት ሁኑው ይሆን? እያልኩ አሁንም አእምሮየ ይጠይቃል ። አብረውን ተደምረው ደግሞ እያወናበዱን እንደሆነ ባልጠራጠርም።
አሁን መከረኛው ሂልተንና ሰራተኛው ምን ላይ ይሆን? ከአራት አመት በፊት በተደረገ የሆቴሎች ደረጃ ግን ትናንሽ የግል ሆቴሎች በልጠውት እጅግ ዝቅተኛ ደረጃ አግኝቶ አንዱ አወዳዳሪ የነበረ ሰው ” እዚህ ሀገር በስም ብቻ ትልቅ የሚባሉ ብዙ ድርጅቶች አሉ። ከነዚህ ውስጥ 3 ኮኮብ እንኳን ሳይገባው ዝም ብለን የሰጠነው ድርጅት ቢኖር ሂልተን ነው” አለኝ። ለመሆኑ በዚህ ድርጅት ላይ ላለፉት 20 አመታት የወረደበትን መከራ ታውቃለህ? ስለው አላቅም አለኝ። ይህ ምሳሌ ለአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲም የሚሰራ ነው። ወደፊት ግዜ ሲገኝ እመጣበታለሁ። ለአሁኑ ግን ያለውን ሀብት በጋራ እያሳደጉ እያሻሻሉ እንደመጠቀም ብልጣብልጥ ወስላቶች በጎሳ ስም ተደራጅተው ሲያወድሙ የጎሳው አባላት የሁላችንም የጋራ የሆነው ሀገር ና ድርጅት ከመውደሙ ውጭ ምን ጠብ ይልለታል? በዚህ አይነትስ አዙሪት ውስጥ መቀጠሉ አይሰለቼንም ወይ? አሁን በሀገሪቱ ውስጥ የተተፋን የከንቱ ሀሳብ እንደገና መድገም ነገ በሌላ አብዬት መውደቅ እንዳለ መገንዘብ አቃታቸው ወይ? አምስት መቶ የማይሞሉ የወያኔ ወንጀለኞች በዘረፉት የትግራይ ህዝብ ምን ጠብ አለለት? አሁንስ በኦሮሞ ስም የሚራኮቱ ስግብግቦች ለ30 ሚሊዬን ህዝብ ምን ያዘንቡሉታል ሀገርን ከማዳከም ውጭ? ይህ ሁሉ ሲሆን ደህንነቱ፣ ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮው፣ የኢትዬጵያ ሰራተኞች ማህበር መሪዎች ምን እየሰሩ ነበር? በሀጢያቱስ አብረው ተጠያቂ አልነበሩም ወይ? ወዘተ የሚሉ ጥያቄዎች እንደሚመጡባችሁ እገምታለሁ። እኔ ግን እምለው ገና ካሁኑ ይህ ነገር ስር ሳይሰድ ለሁላችንም እኩል የሆነች ሀገርን ለመገንባት ያገባኛል እስካላልን ሀገሩም፣ ለውጡም የትም አይደርስም።
ድል ለኢትዬጵያ ህዝብ!!

ኢትዮጵያ “ዩጎስላቪያ” አይደለችም –ምርጫው ልማት ወይንም እልቂት ነው— (አክሎግ ቢራራ (ዶር)

አክሎግ ቢራራ (ዶ/ር)
አክሎግ ቢራራ (ዶ/ር)

ጠ/ሚንስትር ዶር ዐብይ አህመድ ሥልጣን ከያዙበት ጊዜ ወዲህ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከዚህ በፊት አይቶትና ሰምቶት የማያውቀውን የሰብአዊ መብት መከበር፤ በነጻ የመናገርና የመጻፍ፤ መንግሥትን የመተቸት፤ እንደልብ የመንቀሳቀስና የመደራጀት፤ የመሰብሰብ፤ ከአገር የመውጣትና የመግባት መብቶችን ተቀዳጅቷል። ችግሮችን በጋራና በሰላም የመፍታትና የኢትዮጵያን ጥልቀት ያለው የኋላ ቀርነትና የድህነት ሰቆቃ ለመቅረፍ እድሉ ከፍ ብሏል። ኢትዮጵያን ካስቀደምና ከዘውግ በላይ ለእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ መብትና ደህንነት ለማሰብና ለመስራት ከቻልን፤

 • ኢትዮጵያ በአስርት ዓመታት ረሃብን፤ ፍጹም ድህነትንና ኋላ ቀርነትን ለመቅረፍ ትችላለች፤
 • ኢትዮጵያ ዩጎስላቭያን አትሆንም። ይህን ማድረግ ግን ቀላል አይሆንም፤ ብዙ አስመሳዮችና ጠባብ ብሄርተኞች የከበቡት መንግሥት ሆኗል።

መጀመሪያ የፖለቲካውን ችግር በጋራ፤ በቅንነትና በድፍረት ለመፈታት ፈቃደኛ መሆን አለብን። የመንግሥቱ መሪዎች ደፋር መሆን አለባቸው።

የኢትዮጵያን ረጅም፤ የሚያኮራና የጋራ ታሪክ ሂደት፤ የዘውግን ጠባብ ብሄርተኝነት አደጋነት፤ አድካሚነትና አፍራሽነት፤ የኢትዮጵያዊነትን የዜግነት መለያ ወይንም የኢትዮጵያዊ ብሄርተኝነት አስፈላጊነትና ወሳኝነት፤ ጦርነትን ወደ ጎን ትቶ ኋላ ቀርነትንና ድህነትን የመቅረፍና የማሸነፍ ወሳኝነትን ወዘተ እሴቶች በሚመለከት ብዙ አገር አቀፍና ዓለም አቀፍ ስብሰባዎችና ውይይቶች ሲካሄዱ ቆይተዋል። ይህች የብዙ ሽህዎች ዓመታት ታሪክ ያላት አገር በሃያ አንደኛው መቶ ክፍለ ዘመን ገና ስለ አገር ግንባታ (Nation-building) ጥናት፤ ምርምርና ውይይት ታደርጋለች። ለማስታወስ፤ እኛ ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ምሁራን መናገር፤ መጻፍና መተቻቸት እንወዳለን። በጋራ እሴቶች መስማማት ግን አንችልም። “Quo Vadis Ethiopia (ኢትዮጵያ ወደ የት እየሄደች ነው?”) የሚለውን ጥያቄ ያልፈተሸ ምሁር ወይንም ስብስብ የለም። ይህ ባለፉት አምሳ ዓመታት ሲፈተሽ የቆየ ጥያቄ ሁሉም ምሁራን፤ ልሂቃን፤ የፖለቲካ ስብስቦች፤ መሪዎች የሚጋሩት መልስ አለማግኘቱ ይህች ታላቅ አገር አሁንም በራሷ ዜጎች እየተጎዳች መሆኑን ያሳያል። አገሩን የማያከብርና በማያሻማ ደረጃ የማይቀበል ዜጋ ወይንም ቡድን ሕዝብን ይወዳል፤ ለፍትህ ቆሟል ለማለት አይቻልም፤ የሚወደው ራሱንና የራሱን ዝና ነው። የሚያገለግለው የራሱንና የቡድኑን ጥቅም ነው።

የችግሩ መንስኤ ኢትዮጵያ ወይንም የኢትዮጵያ ሕዝብ አይደሉም። ኢትዮጵያን እንደ ችግር የምናቀርባትና የምነወያይባት እኛው ነን። የቻይና ሕዝብ ቻይናን፤ የአሜሪካ ሕዝብ አሜሪካን፤ የራሽያ ሕዝብ ራሽያን፤ የኢራን ሕዝብ ኢራንን፤ የግብጽ ሕዝብ ግብጽን ወዘተ እንደ ችግር አያይም። የሰለጠነውና አገሩን ዘመናዊ ለማድረግ ቆርጦ የተነሳ የዓለም ሕዝብ፤ የፖለቲካውንና የፓርቲውን ልዩነት ከአገሩ ዘላቂነትና ብሄራዊ ጥቅም ይለያል። አገር እንደ ችግር አይታይም፤ ችግሩ የፖለቲካ ሥልጣን ፈላጊዎች ናቸው ። ዓለም ያደነቃትን አገር ኢትዮጵያን ዛሬም የምናዋርዳት፤ ሌላው ቀርቶ አሁንም በስሟ ፓርቲዎችንና ተቋማትን ለመሰየም የምንቸገረው፤ ባለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት፤ የአገሪቱ አምባሳደሮች አይን ባወጣ ደረጃ የኢትዮጵያን ዘላቂ የንግድ፤ የመዋእለ ንዋይ ፈሰስ አስፈላጊነት ጥቅም፤ የሁሉም ዜጎቿ የመከበርና የመገልገል መብት፤ የአገራችን የመከበርና የዜግነት መለያችን መሆኑን የማስተጋባትን ግዴታቸውን ወደጎን ትተው ኤምባሲዎችን የራሳቸው ዘውግ አባላት መሰብሰቢያና መገልገያ ማድረጋቸው ምን ያህል ይህችን ታላቅ አገር ዝቅ እንዳደረግናት ያሳያሉ። የኢትዮጵያ ዘላቂነት፤ የመላው ሕዝቧ እድገትና በሁለመናዋ ተሳታፊነት የህልውና ጥያቄ መሆኑን “ኢትዮጵያ ወደ የት እየሄደች ነው” በሚሉት ስብሰባዎች ስነወያይባቸው ቆይተናል።

ዛሬ ኢትዮጵያና የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚፈልጉት ተግባር እንጅ ዲስኲር አይደለም። ኢትዮጵያ ፍትሃዊና አስተማማኝ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ማህበረሰብ ለመመስረት የምትችለው የሕግ የበላይነት፤ እውነተኛ እኩልነት፤ በዜግነት መብት የተመሰረተ፤ ብሄርና ቋንቋ ተኮሩን ሕገ መንግሥት የሚተካ ሌላ ሕዝብ ተወያይቶና ተስማምቶ የተቀበለው ሕገ መንግሥት ስኬታማ ሲሆን ነው። ችግሩ ሕገ መንግሥቱ አይደለም፤ አፈጻጸም ነው የሚለውን ብሂል አልቀበልም። በዜጎች መብት ላይ ያልተመሰረተ፤ ሕብረ-ብሄራዊነትን ያዳከመ ሕገ መንግሥት እንዴት አግባብ አለው ለማለት ይቻላል?

ያለውን የአንድ ፓርቲ ስርዓት ለማጠናከርና የጥቂቶችን የፖለቲካና የኢኮኖሚ የበላይነት መልሶ እንዲያንሰራራ ለማድረግ ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር ካልተፈለገ በስተቀር፤ በአሁኑ ወቅት፤ “ሕገ መንግሥቱ ይከበር፤ ምርጫ ለይስሙላ ይካሄድ” ማለቱ ከጥቅሙ ጉዳቱ ሊያመዝን ይችላል። ምክንያቱም፤ የብሄር ጥላቻው ስር እንደሰደደ ነው። ቅደመ ሁኔታዎች አልተመቻቹም። ከአዲስ አበባና ሌሎች ጥቂት ቦታዎች ውጭ ሰላምና እርጋታ፤ የሕግ የበላይነት፤ አስተማማኝ ኑሮ ወዘተ የለም። ከፍተኛ ሌቦችና ነፍሰ ገዳዮች በሃላፊነት ለፍርድ አልቀረቡም።

ለምሳሌ፤ ባለፈው ሳምንት፤ በ February 6, 2019 የመጀመሪያ ቀናት ብቻ በደምቢያ ወረዳ ጎንደር ጦርነት ተካሂዶ ቁጥራቸው ያልተረጋገጠ ዜጎች ህይወት አልፏል፤ ብዙ ኃብት ወድሟል። ዶቸ ቬላ እንዳታወቀው ከሆነ የችግሩ መነሻ በጭልጋ ወረዳ በሚኖሩ “የዐማራና የቅማንት” ወንድማማች ሕዝቦች መካከል በተከሰተ ልዩነት ነው። ይህን ልዩነት በተከትጋታይ እሳት እየጫሩ ያባባሱት ህወሓቶች መሆናቸው የሚከራክር አይመስለኝም። ህወሓት ሥልጣን ከመያዙ በፊት በዚህና በሌሎች የጎንደር አካባቢዎች የተጨፈጨፈው ሕዝብ ብዛት በቅጡ ባይታወቅም፤ በብዙ ሽህዎች ይገመታል። ዛሬም እንደ ትላንቱ፤ የህወሓቶች ዐላማ ጎንደርን ማውደምም ባይችሉ በዘረፉት ኃብትና በገዙት መሳሪያ ጎንደርንና ጎንደሬውን ማድቀቅና ማዳከም ነው።  ይህ ሁኔታ ከቀጠለና ከተስፋፋ የሚካሄደው ጦርነት በመላው ዐማራ ሕዝብ ላይ እንደሚሆን መጠራጠር የለብንም። ችግሩ የጎንደሬው ብቻ አይደለም።

የኢትዮጵያ ሕዝብ አስተማማኝ ኑሮ ለመኖር የሚችለው ሰላምና እርጋታ ሲኖር፤ የስራ እድል በገፍ ሲፈጠር፤ የምርት ኃይሎች ሲስፋፉና አስተማማኝ፤ ጠናካራና ራሱን ችሎ የሚንቀሳቀስ ማህበረሰባዊ ኢኮኖሚ ሲፈጠር ነው። እምቅ ኃብት መኖሩ ብቻ እድልና ምርት ሊፈጥር አይችልም። ሰላም፤ እርጋታና ፍትህ፤ ሙሉ ተሳትፎ አስፈላጊ የሚሆኑት ለዚህ ነው። የርስ በርስ ግጭት ለእነዚህ አስፈላጊ ሁኔታዎች መሰናክል መሆኑን በተደጋጋሚ አሳስቤአለሁ። ጎንደር የጦር አውድማ ሆኖ መቆየቱን ማንም አይዘነጋውም። በቅማንት “ማንነትና የመሬት ይገባኛልነት” ስም ሲነግዱ የቆዩ ኃይሎች አሁንም ችግሩ እንዲፈታ አይፈልጉም። የውስጥ ታዛቢዎች እንደሚሉት ከሆነ በራያና አዘቦም ጦርነት የሚጭሩ ኃይሎች አሉ። በአጠቃላይ ሲገመገም፤ ጨካኙ ህወሓት በጎንደር ዐማራ ሕዝብ ላይ የሚያካሂደው አዲስ “የውክልና ጦርነት (Proxy war) እና እልቂት በዘውግና በቋንቋ ልዩነት ላይ የተመሰረተው ሕገ መንግሥትና የአገዛዝ ስርዓት ውጤት ነው።

በጎንደር ከተማ ዙሪያ፤ በአዘዞ አካባቢ በየካቲት 1, 2011, የተካሄደውን ውንብድና ስመለከት ይህ በደለቡ ከብቶች ላይ የተካሄድ ጭካኔ የተካሄደው ድሃውን የዐማራ ሕዝብ በኢኮኖሚ ለመቅጣት መሆኑ አያከከራክርም። ከአምሳ በላይ የሚሆኑ ከብቶች ተቃጥለው መውደማቸው ብቻ አይደለም። ከዚህ ባሻገር የተከሰተው ሁኔታ፤ የጎንደር ሕዝብ ተቆርቋሪ የክልል ሆነ የፌደራል መንግሥት እንደሌለው ያሳያል። በአንድ በኩል የጠ/ሚንስትር ዶር ዐብይ አህመድ መንግሥት የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን መሪዎች በአዲስ አበባ እያስተናገደ ስለ ስደተኞች ሁኔታ ሲወያይ የጎንደር ዐማራ ሕዝብ ግን ለአደጋ ተጋልጦ ዘላቂ መፍትሄ አላገኘም። በሕዝብ ህይወት ላይ ብቻ ሳይሆን በኢኮኖሚ ላይ የሚካሄድ ጥቃት የህልውና ጥያቄ ነው።

በዚህ አጋጣሚ ላልፈው የማልችለው ሌላው ክስተት፤ የማንነትንና የድንበርን ጉዳይ በሚመለከት ጠ/ሚንስትሩ የሰየሟቸው የኮሚሽን አባላት መስፈርትና ቅይጥ (Composition) አከራካሪ ከመሆን ያለፈ መሆኑ ነው። ችግሩን የፈጠሩ ግለሰቦች የፈጠሩትን ችግር በማይፈታ ሁኔታ ተቋቁሟል፤ በተለይ የዐማራውን ሕዝብ በሚጎዳ ሁኔታ።

መስፈርቱ ምንድን ነው?

ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን፤ ፍትህን፤ የሕግ የበላይነትን፤ እውነተኛ የዜጎች እኩልነትን፤ ዲሞክራሲን፤ ሚዛናዊና ዘላቂ ልማትን፤ ሰላም፤ እርቅና አብሮነትን፤ ብሄራዊ እርጋታን፤ የአካባቢ ጤንነትንና ተመሳሳይ እሴቶችን ተቋማዊ ለማድረግ ከተፈለገ ጠ/ሚንስትሩና ፓርላማው የሚያጸድቋቸው ኮሚሺኖች አባላት መስፈርቶች የማያሻሙና ያለፈውን የማይደግሙ መሆን ይኖርባቸዋል። ከእነዚህ መስፈርቶች መካከል የሚከተሉት አስፈላጊ ናቸው፤

 • ከማንኛውም ወንጀል የጸዱ፤ ሕዝብን ከሕዝብ ጋር ያላጋጩ፤
 • ታሪክን የማያዛቡ፤
 • ለሁሉም ዜጎች እኩልነትና መብት የቆሙ፤
 • የዘውግ ጥላቻ የሌላቸው፤
 • በጠባብ ብሄርተኝነትና በትምክኽተኝነት ያልተበከሉ፤
 • በሃቅኛነትና በህሊና ተገዥነት የሚያምኑ፤
 • ለአጭር ጊዜ ጥቅም ህሊናቸውን የማይሸጡ፤
 • ለሥልጣንና ለግል ዝና የማይሻሙ፤
 • ሃላፊነት የሚሰማቸው፤
 • በአርቆ አስተዋይነት እሴት የሚታወቁ።

በድህረ ገጾችና በማህበረሰባዊ መገናኛዎች የተሰራጨው ቅይጥ እንዳለ ከቀጠለ ግን የወልቃይት- ጥገዴ፤ ጠለምት፤ ሰቲት ሁመራ፤ ራያና አዘቦ ጉዳይ እንዳለቀለት እቆጥረዋለሁ። ግጭትና እልቂት ይከተላል። ህወሓት የፈለፈውን ለመቀዳጀት በሚል ስሌት፤ የዐማራው ሕዝብ መሬቱን ይነጠቃል። በተለይ የሚጎዳ የጎንደር ዐማራ ሕዝብ ነው። ይህ ከሆነ ኢትዮጵያና ኢትዮጱያዊነትም አብረው ይጎዳሉ። ጎንደርን ማጥፋት ኢትዮጵያን እንደማጥፋት ነው!! የዐማራው ክልልና የፌደራሉ መንግሥት ይህን ሁኔታ ማክሸፍ ግዴታቸው ነው።

ወጣቱ ትውልድ ይህን ጉዳት ያውቀዋል፤ ይታገላል።

የዐማራው ሆነ ሌላው ወጣቱ ትውልድ በጉጉት የሚጠብቀውና የሚመኘው ግጭትን፤ ጥላቻን፤ ምዝበራን፤ አፈናን አይደለም። ይህንማ ለምዶታል፤ አልፈልግም ብሏል። የሚመኘውና የሚፈልገው ኑሮውን ማሻሻል ነው። ሆኖም፤ የስራ እድል ወይንም ኑሮን ለማሻሻል የራስን ኩባንያ የመመስረት እድል አሁንም ጠባብ ነው። መሬቱን ከተነጠቀ እድሉም ይጠባል። እድሜው ከአርባ ዓምስት ዓመት በታች የሆነው ወጣት ቢያንስ ሰባ በመቶ ይሆናል የሚለው ዘገባ ምስክር አያስፈልገውም። በያንዳንዱ ከተማና በመላው የአገሪቱ ክፍል ያለውን የወጣት ብዛት፤ በየጠለላው የሚተኛውን ወጣት ትውልድ የኑሮ ሁኔታ ብቻ ማየቱ ይበቃል። በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ ከ 800,000 በላይ የሚገመተው ሕዝብ በጠለላ ይኖራል፤ ይራባል።

በዚህ ዓመት የተባበሩት መንግሥታት የህጻናት ድርጅት (UNICEF) የኦክስፎርድ ዩንቨርስቲን የጥናትና ምርምር መሳሪያ፤ ሁሉን አቀፍ የድህነት መስፈርቶች መሰረት አድርጎ ባደረገው ዘገባ እድሚያቸው ከአስራ ስምንት በታች የሚገመተውን አርባ አንድ ሚሊየን ወጣት ኢትዮጵያዊያን ተመን መሰረት አድርጎ ከእነዚህ መካከል 36 ሚሊየን ወይንም ሰማንያ ስምት በመቶ የሚገመቱት ድሃ ወይንም ፍጹም ድሃ መሆናቸውን አሳይቷል።

ይህ ምን ማለት ነው? ድህነት ወይንም ፍጹም ድህነት ማለት በቂ ምግብ፤ የጤና አገልግሎት፤ መጸዳጃ፤ ንጹህ ውሃ፤ አጥጋቢ መጠለያ፤ የትምህርት እድል፤ አስፈላጊ ዜናና መረጃ ወዘተ የማያገኙ በማህበረሰባዊ፤ በኢኮኖሚና በፖለቲካ ለመሳተፍ እድል የሌላቸው ማለት ነው። በሰለጠነው ዓለም እነዚህ ፍላጎቶች መሰረታዊ ሰብአዊ መብቶች ናቸው። ማንኛውም መንግሥት ባለው ዓቅም መሰረት እነዚህን ፍላጎቶች የማሟላት ግዴታ አለበት። አለያ ወጣቱ በመንግሥቱ ላይ ይነሳል!!

መንግሥት የዜጎችን፤ በተለይ የወጣቶችን የኢኮኖሚ መብት ካላስከበረና ፍላጎታቸውን ለማሟላት በቂ ጥረት ካላደረግ ግን በተከታታይ ትውልድ የሚከሰተው ተከታታይ ረሃብ፤ ድህነት፤ ስደት፤ ግጭት፤ የእርጋታና የሰላም አለመኖር ይሆናል። ይህ ሁኔታ ከቀጠለ ደሞ፤ ማንኛውም አገር ከድህነትና ከኋላ ቀርነት አሮንቃ ራሱን ነጻ ለማውጣት አይችልም። የኢትዮጵያ ዘገባ የሚያሳየው በክልሎች መካከል እጅግ የሚያስፈራ የሕጻናት የድህነት ልዩነት መኖሩን ጭምር ነው። በተለይ ተጎድተው የሚገኙት ክልሎች አፋር፤ አማራ፤ ደቡብና ኦሮምያ ናቸው። ሰላሳ አራት ሚሊየን የሚገመቱት ድሃ ህጻናት የሚኖሩት “በኦሮምያ፤ በአማራና በደቡብ ክልሎች” ነው።

ሁሉን አቀፍ የሆነ ድህነት ከተከሰተ ቆይቷል። “አስደናቂ ልማት ይታይባታል” በምትባለው ኢትዮጵያ 95 በመቶ የሚገመተው የወጣቶች ወይንም የህጻናት ክፍል ፍጹም ድሃ ነው። ይህ ሁኔታ የሚያሳየው ለወጣቱ ትውልድ የተለየ ትኩረት፤ የተለየ ኢንቬስትመንት፤ የተለየ ፍትሃዊ የባጀትና የገቢ ስርጭት አለመደረጉን ነው። በጥቂቶች ለጥቂቶች ሰማይ ጠቀስ ፎቅ ሲሰራ በሰማይ ጠቀሱ ሱቁ ዙሪያ የሚኖረው የድሃ ሕዝብ ብዛትና ጭንቀት ምን ይሆን? ብሎ የሚጠይቅ አዲስ ባለኃብትና ባለሥልጣን ብዙም አልታየም። ዛሬ በአዲስ አበባና በሌሎች ከተሞች የለማኙ ብዛት እየጨመረ እንጅ እየቀነሰ አልሄደም። የኢኮኖሚው መዋቅር መለወጥ አለበት። ግዙፍ ኢንቬስትመንት (የመዋእለንዋይ ፈሰስ) መደረግ አለበት።

ከሁከት ወደ ኢንቨስትመንት መሸጋገር የህልውና ጥያቄ ነው።

ሰላም፤ እርጋታ፤ አብሮነት፤ ፍትህ፤ መልካም አስተዳደር ካለ ኢትዮጵያ ሌሎች አገሮች ከደረሱበት ልማት ለመድረስ ትችላለች የሚል እምነቴ አሁንም ጠንካራ ነው። ወጣቱ ትውልድ ግዙፍ ነው (The Youth Buldge) በሚባልበት ጊዜ፤ ይህ ትውልድ ራሱንና አገሩን ዘመናዊ ለማድረግ እምቅ ችሎታ አለው ማለት ነው። የመከከለኛ መደቡን ለመጨመርና ለማስፋት ይህ ትውልድ ወሳኝ ሚና አለው። አመቻችና ችሎታ ያለው መንግሥትና አመራር (Enabling and competent government leadership) ያስፈልጋል።

ግጭት፤ ሁከትና ሌብነት ኃብት ያመክናል። መንግሥት ያለውን ባጀት ማህበረሰባዊ ጭንቀትን ለመፍታት፤ ሰላምንና እርጋታን ለማስጠበቅ ፈሰስ ካደረገው ህጻናትንና ሌሎችን ከድህነት ነጻ ለማውጣት፤ የአገሪቱን የምርት ኃይሎች ለማጠናከር ፈሰስ የሚያደርገው ባጀት ይባክናል ወይንም ይቀንሳል። የፖለቲካ ሥልጣንን እንደ ራሳቸው ርስትና ጉልት የሚያዩት ህወሓቶች፤ ኦነጎችና ሌሎች በመሳሪያ ኃይል ስልጣን መያዝ ያስፈልጋል የሚሉት ሁሉ ማሰብና ትኩረት መስጠት የሚኖርባቸው የሕጻናትና የሌላው ሕዝብ ኑሮ ካልተሻሻለ የፖለቲካው ስልጣን ግብግብ የትም እንደማያደርስ ነው። ይመስላል እንጅ፤ ሁከት፤ የርስ በርስ ግጭት፤ ማህበረሰባዊ ጭንቀት የማንንም ኑሮ አያሻሽልም። የሩዋንዳን፤ የቦስንያንና የሌሎችን በግጭት የተበከሉ አገሮችን የውድመት ምሳሌነት ማጥናቱ የሚረዳው ከልምዳቸው ለመማር ነው።

ምርጫችን ግጭት ሊሆን አይችልም። ምርጫችን ልማት ነው። የውጭ መንግሥታት፤ በተለይ የምእራቡ ዓለም ኢትዮጵያ የአፍሪካ ቀንድ ብቻ ሳይሆን፤ የመላው አፍሪካ ተስፋ አገር ናት የሚል ግንዛቤ ስላላቸው ዛሬ የሚካሄደውን ሰላማዊና መሰረታዊ ለውጥ የሚቃወሙ ኃይሎችን አይደግፉም። የውስጥ ጥናቶችና ምርምሮች፤ እውቅና ያላቸው የምእራብ አገሮች ምሁራንና ተመራማሪዎች፤ በተለይ አሜሪካኖች የሚሉት “ኢትዮጵያ ዩጎስላቭያ እንድትሆን አንፈልግም” ነው። የሚመኙት “ይህች ጥንታዊ አገር የደቡብ ኮሪያን ኢኮኖሚ አይነት ውጤት እንድትቀዳጅ ነው” የሚሉ ታዛቢዎች ብዙ ናቸው። በአንድ በኩል በአሜሪካ፤ በሌላ በኩል በቻይና፤ በራሽያ፤ በኢራንና በሌልች ኃይሎች መካከል ያለው የኃይል፤ የንግድ፤ የዲፕሎማሲና የስትራተጂክ ፉክክር እየሰፋና ጥልቀት እየያዘ ስለሄደ ኢትዮጵያ ጠንካራ፤ ሃብታምና ዘመናዊ አገር እንድትሆን የሚፈልጉ ምእራባዊያን ብዙ ናቸው። ወሳኙ ግን የኢትዮጵያ ሕዝብ፤ በተለይ ወጣቱ ትውልድ ነው። ይህ ዘገባ የሚያሳየው ክስተት፤ የወደፊቷ ጠንካራ ኢትዮጵያ መላውን ከሳሃራ በታች የሚገኘውን ጥቁር ሕዝብ ሁሉ በሚያጠናክር ሁኔታ ከፍተኛ ሚና ትጫወታለች ወደሚል ድምዳሜ እያመራ ነው።

አሜሪካኖች የቀይ ባህርና የአፍሪካ ቀንድ አገሮች ለሌሎች መንግሥታት መገልገያ እንዳይሆኑ የተቻላቸውን እንደሚያደርጉ ብዙ ዘገባዎች ይጠቁማሉ። ለማጠናከር የምፈልገው ሃሳብ፤ የአሜሪካ መንግሥት ባለሥልጣናት የቻይናን፤ የራሽያን፤ የኢራንንና የሌሎችን መንግሥታት ስትራተጂክ ጥቅም ለማዳከምና የራሳቸውን ብሄራዊ ጥቅም ለማጠናከር ኢትዮጵያና ኤርትራ፤ ኢትዮጵያና ሌሎች የአፍሪካ አገሮች እንዲጠናከሩ ማድረጋቸውን ይቀጥላሉ። ይህን ስል ግን የማሳስበው ኢትዮጵያ የራሷን ጥቅም ለማስከበር የራሷን መርሆዎች መከተልና፤ በተለይ የራሷን የውጭ ግንኙነት ማጠናከር ይኖርባታል። ግጭት ግን ይህን እድል ያማክናል።

የምእራብ አገሮች፤ ለመገንጠል ወይንም የኢትዮጵያን መንግሥት ለማዳከም የሚሞክሩ ኃይሎችን፤ በተለይ መሪዎችን ክትትል እንደሚያደርጉባቸው የውስጥ አዋቂዎች ይጠቁማሉ። ኤርትራና ኢትትዮጵያ የጀመሩት ወዳጅነት ደጋፊነት ያገኘበትም ምክንያት ከዚህ የአሜሪካኖች ስትራተጂክ ግንዛቤና ድምዳሜ ጋር አብሮ የተያያዘ መሆኑን እገምታለሁ። የጣሊያን መንግሥት በኤርትራና በኢትዮጵያ ወንድማማች ሕዝቦች መካከል ያለውን ጥንታዊ ግንኙነት ለማጠናከር በሚል ስሌት፤ የሃዲድ መንገድ ጥናት (Rail feasibility studies) ለማድረግ ቃል መግባቱ ጠቃሚና ወቅታዊ ነው።

ቻይናም በበኩሏ ከኢትዮጵያና ከሌሎች የአፍሪካ አገሮች ጋር ያላትን የንግድና የኢንቬስትመንት ፍላጎቶች ለመቀጠል ውሳኔ ማድረጓን በግልጽ አስታውቃለⶭ። ኢትዮጵያ፤ የራሷን ጥቅም ለማስከበር ከቻይና የምትፈልገውን ከራሷ ጥቅም አንጻር ማየት አለባት። መጠንቀቅ ያለባት ግን፤ ለውጭ ምንዛሬ ሲባል የውጭ ኃይሎችን ማባበል አደገኛ  መሆኑን ነው። የአረብ አገሮች ታላቁን የዓባይን ግድብ እንደማይደግፉ በተደጋጋሚ ጽሁፎቸ አሳይቻለሁ። እነሱ የሚፈልጉት ታላቁ ግድብ ትንሽ እንዲሆንና ለግብጽ የሚደርሳት ውሃ እንዳይቀንስ፤ ኢትዮጵያ ጠንካራና ራሱን የቻለ ኢኮኖሚ እንዳትፈጥር ነው።

ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት የሚታየውን የአካባቢና የዓለም አቀፍ ሁኔት በጥንቃቄ መጠቀም አለባት። ይህ የአካባቢና የዓለም አቀፍ ሁኔታ እንዳለ ሆኖ፤ የኢትዮጵያ የውስጥ የፖለቲካ አጣብቂኝ በቀላሉ እንዳይፈታ የሚፈልጉ ኃይሎች ግትርነትና አጥፊነት ለተወሰነ ጊዜ የሚቀጥል ይመስለኛል። ውጣ ውረድም ቢኖር፤ ከአሁን በኋላ ኢትዮጵያ በምንም አትፈርስም። የአሁኑን በያካባቢው በየቀኑ የሚከሰት ግጭትና ሁከት የፈጠሩት ኃይሎች ቀደም ሲል አስበውበት ነው። ህወሓትና አጋሮቹ ባለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት የፈጠሩትና ያስፋፉት የብሄር ጥላቻ፤ ልዩነትና የጥቅም ሰንሰለት በቀላሉ የሚፈታ ያልሆነበት መሰረታዊ ምክንያት ብዙ ገበያተኞች ወይንም የፖለቲካ አትራፊ ሸማቾች ስለተፈጠሩ ነው። ህወሓቶችና ሌሎች የዘረፉት  ኃብት ብቻ ይህን ጥላቻና ልዩነት፤ ቂም በቀልነትና የመገንጠል ዝንባሌ ሊያስቀጥል ይችላል።

ሌቦችና አጥፊዎች በሃላፊነት የሚጠይቁበት ወቅት አሁን ነው።

ደፋር አመራር አስፈላጊ መሆኑን አሳስባለሁ። ከፍተኛ ሌቦችንና ሃብት ያሸሹትን፤ ነፍሰ ገዳዮችንና ሽብርተኞችን ለሕግ ያለማቅረቡ ችግር ውጤቱ ግጭት ነው። ዘራፊዎችና ነፍሰ ገዳዮች በሃላፊነት ካልተጠየቁ የሕግ የበላይነት አይመለከተንም ወደሚል የተሳሳተ ድምዳሜ ስለሚደርሱ ሰላምና እርጋታ እንዲፈጠር አይፈቅዱም። እኔ እስከማውቀው ድረስ ህወሓትና ኦነግ ከሌሎች የፖለቲካ ፓርቲዎች የተለየ መብት የላቸውም።  የተለየ መሳሪያ የመያዝ፤ ጦር የማንቀሳቀስ፤ ሽብርተኝነት የመጫር መብት አልተሰጣቸውም። ኦነግ እንደ ሌላው ውጭ እንደነበረ ኃይል ወደ አገር ቤት ገብቶ በሰላም እንዲንቀሳቀስና እንዲወዳደር ጥሪ ተደረገለት እንጅ ብዙ ሽህ የታጠቀ ወታደር እንዲያንቀሳቅስ፤ ባንኮችን እንዲዘርፍ ፈቃድና መብት አልተሰጠውም።

የደርግ መንግሥት ስልጣን ላይ በነበረበት ጊዜ የማስታውሰው ህወሓትና ሌሎች የታጠቁ ኃይሎች የንግድ ባንክ ቅርንጫፎችን እየዘረፉ ማራቆታቸውን ነው። በተመሳሳይ፤ በ January 2019, ኦነግ የዐብይ መንግሥት የሰጠውን የነጻነት መብት ጥሶ ባንኮችን ዘረፈ፤ ንጹሃን እንዲሞቱና ብዙ ወገኖⶫችን ከቀያቸው እንዲባረሩ አደረገ። ይህ ለምን ሆነ፤ ለምን ዘላቂ ዓላማ? የሚለውን የሚጠይቁ ታዛቢዎች ያገኙት መልስ አንድ ነው። በጥቂት ወራቶች ለብዙ ዓመታት ያላገኘውን የፖለቲካ ስልጣን ለማግኘት የሚለው አንዱ መልስ ነው።

ይህ ከሆነ በህወሓትና በኦነግ መካከል ልዩነት የለም። ሁለቱም የቋንቋና የዘውግ ፌደራሊዝም ዘላቂ አላማው እያንዳንዱ ዘውግ የፖለቲካ ሥልጣን ለመያዝ ካልቻለ የመገንጠል መብቱን ስኬታማ የማድረግ መብቱ የተጠበቀ ይሆናል ማለት ነው። ዩጎስላቭያን መጥቀሱ አግባብ የሚኖረው ለዚህ ነው።

ግን፤ ኢትዮጵያና ዩግስላቭያ የተለያየ የታሪክ ሂደት ያላቸው አገሮች ናቸው። ኢትዮጵያ ዩጎስላቭያ አይደለችም። አለመሆኗን የሚያሳዩ ብዙ ምሳሌዎች አሉ። ኢትዮጵያ ነጻነቷን ያስከበረችው በሁሉም ዜጎቿ ተጋድሎና መስዋእት ነው። ይህ አብሮነት በብዙ ሁኔታዎች ተሰምሮበታል። ለምሳሌ፤ የዚህ ዓመት የጥምቀት በዓል በደመቀና አገር አቀፍ በሆነ ሁኔታ ተከብሯል። በበዓሉ ዙሪያ፤ የእስልምናና የክርስትና ኃይማኖት ተከታዮች ህብረትና አብሮነት ያሳየው ኢትዮጵያ የጋራ አገር እንደሆነች፤ ሕዝቡ በኃይማኖት ልዩነት የማይከፋፈል መሆኑን ነው። ኢትዮጵያዊያንን  የተለዩ ከሚያደርጓቸው እሴቶች መካከል በኃይማኖቶችና በዘውጎች መካከል ያለው የሚያኮራ ግንኙነት ነው። ይጋባሉ፤ ይጎራበታሉ፤ በክፉውም በደጉም ጊዜ ይገናኛሉ። አብረው አገራቸውን ከጠላት ይከላከላሉ።

በሶማልያና በኬንያ በተከታታይ የተካሄዱ የአልሸባብ እልቂቶች በኢትዮጵያ አልተከሰቱም። የኢትዮጵያ እስልምና ኢትዮጵያዊ ከሆነ ቆይቷል።

ኢትዮጵያ ሁሉም ኢትዮጵያዊያን የሚነከባከቧት አገር ናት።

ጠ/ሚንስትር ዶር ዐብይ በኃይማኖቱም ሆነ በዘውጉ፤ በቋንቋው ሆነ በአመለካከቱ ሁሉንም ኢትዮጵያዊያን የሚወክል እትዮጵያዊ መሪ ነው።

ማህበረሰባዊ ጭንቀትን ያባባሰው ምንድን ነው?

የጠ/ሚንስትር ዶር ዐብይ አህመድ መልካም ምኞትና ጥረት፤ የአካባቢውና የዓለም ሁኔታ እንዳለ ሆኖ፤ የአገሪቱን መሰረታዊ የስርዓት ችግር በሃቅ አቅርቦ መፍትሄውን የማቅረብ ደፋርነቱና ተከታታይነቱ ገና ስፋትና ጥልቀት አልያዘም። ለምሳሌ፤ አሁንም በቋንቋና በዘውግ የተመሰረተው የመለያያ ሕገ መንግሥት እንዳለ ነው። “የአፈጻጸም እንጅ የመርህ ችግር የለበትም” የሚሉ አሉ፤ የኢህአዴግ አባል ድርጅቶችን ጨምሮ። በኔ እምነት፤ ይህ ሕገ መንግሥት የችግሩ እምብርትና መሰረት ነው።

ነጻነት ከፍተኛ እሴት መሆኑ አያከራክርም። የማይካደው ክስተት፤ ቅድመ “ዐብይ” ፖለቲካ “ኮረንቲ ነው” ይሉ የነበሩና  ድምጻቸውንና አቋማቸውን አሰምተው የማያውቁ ግለሰቦችና ስብስቦች ጭምር ከተደበቁበት ዓለም እየወጡ ተቆርቋሪነትና ወገንተኝነት ማሰማት ጀምረዋል። በኢትዮጵያዊነት የሚያምኑት ጭምር። ግን ኃይላቸው የተበታተነ ሆኖ ይታያል። በተጨማሪ፤ ከዚህ በፊት ለማንነት ጥያቄ ትኩረት ያልሰጡ ኃይሎች “ነጻነት” አለን በሚል እምነት፤ ብቅ ብቅ ማለት ጀምረዋል። እኔም ክልል ይገባኛል ባዮች  እየበዙ ሲሄዱ ይህ ሁኔታ የአማራውን፤ የኦሮሞውን፤ የደቡቡንና የሌላውን ክልል ሁሉ ይመለከተዋል። ይህ ከቀጠለ የክልሎች ብዛት ከአቅም በላይ ይሆናል፤ ኢትዮጵያ ዩግስላቪያ የመሆን እድሏ ይጠነክራል። እኔ ቀረብ ብየ ስመራመረው፤ ጫፍ ላይ የደረሰውና በማህበረሰባዊ ሜድያ የሚለፈፈው ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነትሳይሆን አሁንም ዘውግ ተኮር ብሄርተኝነት፤ ባልካናይዜሽንነት (Balkanization)፤ ክልላዊነትና ራስን አገልጋይነት ነው። በጎንደር የሚካሄደው ግጭት የዚህ አካል ነው፤ ሆነ ተብሎ የሚካሄድ ሴራ!!

ዘውግ ተኮር አደረጃጀቱና ፉክክሩ፤ እኔም ክልል ያስፈልገኛል ባዩ እየጨመረ ሂዷል። አንዳንድ ታዛቢዎች እንደሚሉት ከሆነ፤ “ሃላፊነት የጎደለው ነጻነት እየተስፋፋ ሄዷል” በሚያስብል ደረጃ፤ መንደርተኛነት፤ ወገንተኛነት፤ ክልላዊነት ጥልቀትና ስፋት እየያዙ ነው። ይህን ችግር ብቻ ለማስታረቅና ለመፍታት የሚፈሰው ባጀት፤ ጉልበትና አቅም ግዙፍ ይሆናል። ለኢንቨስትመንት የሚውለው ባጀት እርጋታን ለመከባከብ ይውላል። የውጭ ምንዛሬ ይባክናል።

ላወቀበት ከነጻነት የበለጠ እሴት የለም። ሆኖም፤ ነጻነት ልክ እንደ እንቁላል በጥንቃቄ መያዝ አለበት። ካለተያዘ ተሰብሮ ሌላውን ይሰብራል። ጠፍቶ ሌላውን ያጠፋል። የማካይካደው ሃቅ፤ ከአንድ ዓመት በፊት ይሆናል ተብሎ ያልታሰበው ነጻነት ግን ከሃላፊነት ጋር ሊቆራኝ አልቻለም። እያንዳንዱ በየፊናው፤ የእኔ መብት ይከበር እንጅ የሁሉም ኢትዮጵያዊያን መብት ይከበር ለማለት ካልደፈረ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ወደ የባሰ አደጋ ሊሸጋገሩ ይችልላሉ። ያ ከሆነ የማንም መብት አይከበርም፤ መሳሪያ የያዘ አለቃ ይሆናል።

አንዳንድ በሕዝብ ፈቃድ፤ ፍላጎትና ምርጫ ሳይሆን፤ በትጥቅ ትግል ስልጣንን የመያዝና በጭካኔ የመግዛት ልምድ ያላቸው ክፍሎች አሁንም ከዚህ ኋላ ቀርና አጥፊ ልምዳቸው ራሳቸውን ነጻ አላወጡም። የነጻነትን ትርጉም ፋይዳ ቢስ ከማድረጋቸው ሌላ፤ ለእነዚህ ክፍሎች ሰርቶና አምርቶ፤ ተደጋግፎና አንዱ ለሌላው አስቦ መኖርና መብላት አዲስ ነገር ሆኖባቸዋል። የአገርን ኃብት መዝረፍና የዘረፉትን ግዙፍ ኃብት ለእልቂት፤ ለግጭት፤ ለርስ በርስ ጦርነት ማዋል መብታችን ነው የሚል ብሂል የሚከተሉ ኃይሎች ጥቂት አይደሉም። ከላይ እንዳቀርብኩት፤ ሁኔታውን ያባባሱትና የሚያባብሱት፤ ሌቦችና ነፍሰ ገዳዮች በሃላፊነት አለመከሳሰቸውና የኢትዮጵያ የውጭ ጠላቶች ጭምር ናቸው። አሁንም ቢሆን የማያርፍ ጠላቶች፤ አገር ውስጥ ለሚገኙ አጥፊና አድካሚ ኃይሎች መሳሪያ በገፍ ይሸጣሉ። መሳርያ ለመግዛት የገንዘብ አቅም መኖር አለበት። ከእለት ጉርሱ ውጭ፤ ድሃው ሕዝብ መሳሪያ የመግዛት አቅምም፤ ፍላጎትም የለውም። የመግዛት ፍላጎትና አቅም ያለው፤ በአብዛኛው፤ ሳይሰራ ገንዘብ ያካበተው፤ ሰላማዊ ለውጥ የማይፈልገው ክፍል ነው።

ሰላምና እርጋታ ለፍትሃዊና ለዘላቂ ልማት ወሳኝ መሆናቸውን ምርምሮችና ጥናቶች በተደጋጋሚ አሳይተዋል። ለውጥን የማይፍልጉ ኃይሎች ግን የሚያስተጋቡት መልእክት “እኛ ስልጣኑን እስካልያዝን ድረስ” ሕግ አይከበርም። “ዐብይ የሚመራው መንግሥት ሕገ መንግሥቱን ጥሷል” የሚል ነው። ሕግ ካልተከበረ ሕገ-ወጥነት አግባብ አለው ማለታቸው ነው። ይህ ከሽፍታነት በምን ይለያል? ብየ ራሴን ስጠይቅ በምንም አይለይም የሚል መልስ አገኛለሁ። ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያ ሕዝብ ያለው አማራጭ አንድ ነው። ማንኛውም ኃይል፤ ማንኛውም ዘውግ፤ ማንኛውም ድርጅት፤ ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ሕግን ማክበር አለበት።

መብት ሲባል፤ የትም ቦታ ይኑር የትም፤ የእያንዳንዱ ግለሰብ መብት ማለት መሆን መለመድ አለበት። በዚህ ጉዳይ ላይ ድርድር አያስፈልግም። አለያ፤ ፍትሃዊና ዘላቂ ልማትና ዲሞክራሲ አይቻልም።

የሕግ የበላይነትና የእያንዳንዱ መብት ካልተከበረ፤ ኢንቬስተሮች ኃብታቸውን ያሸሻሉ እንጅ፤ ምርትን ለማሳደግ የመዋእለ ንዋይ ፈሰስ አያደርጉም። የግልክፍሉና የግል ጥረት እንደ ጫጩ ይቆያሉ። የስራ እድል አይፋፋም። የምርት ኃይሎች በተፈለገው ደረጃ አያብቡም። የኢትዮጵያ ሕዝብ በኑሮ የዋጋ ግሽፈት ይሰቃያል። ወጣቱ ትውልድ ወደ እምቢተኛነት ይሸጋገራል!! መሰደዱ ይቀጥላል!! በዘውግ መብት እየተመኻኘ፤ ዜጎች ከቀያቸው መባረራቸው ይቀጥላል

ከዚህ ላይ ሳልጠቅሰው የማላልፍ የቅርብ ክስተት አለ። ይኼውም የዐማራ ብሄር አባላት የዩንቨርስቲ ተማሪዎች፤ በብሄራቸው መለያ ብቻ ከሚማሩበት ተቋም በገፍ ሲደበደቡ፤ ሴቶቹ ሲዋረዱ፤ ሁለት ሽህ አምስት መቶ የሚሆኑት ከትምህርት ገበታቸው ሲባረሩና ወደ ባህር ዳር ሸሽተው ሲሄዱ የተሰጠው መልስ ያሳፍራል። የፌደራሉ መንግሥት ሁኔታው ተቀባይነት የለውም የሚል መግለጫና ማስጠንቀቂያ አልሰጠም። የዐማራው ክልል መንግሥት ተማሪዎቹ ተመለሰው እንዲሄዱ መከረ እንጅ እነሱ “ለህይወታቸው አስጊ ሁኔታ” መኖሩን ገልጸው በአማራው ክልል በሚገኙ ዩንቨርስቲዎች ትምህርታቸውን እንዲቀጥሉ ያቀረቡትን አቤቱታ አልተቀበለውም። ለእነዚህ ተማሪዎች ተቆርቋሪው የበላይ አካል ማነው? የክልል ስርአቱ አደገኛና አግላይ፤ ኢሰሰብአዊ፤ ጸረ-ኢትዮጵያዊነት መሆኑን በዚህ የቅርብ ምሳሌም ለማሳየት ይቻላል። ታዲያ ሕገ መንግሥቱ ችግር አይደለም የሚያስብለው መስፈርት የት ላይ ነው?

የለንደኑ አይነት ጉባኤ እንዳይደገም የማድረግ ግዴታ

የዘውግ ፖለቲካ ልሂቃን ራሳቸው ሁከትና ብጥብጥ እየፈጠሩ መንግሥት የለም ይላሉ!! በአብዛኛው መስፈርቶች ሳመዛዝናው፤ ምንም እንኳን ሙሉ በሙሉ ሰላምና እርጋታ አለ ባይባልም፤ ኢትዮጵያ “መንግሥት የላትም” የሚለው ብሂል ትክክል አይደለም። እርጋታና አስተማማኝ የሆነ የአገር ቀጣይነት ሁኔታ አለ ማለት አይደለም። እምቢ አልገዛም የሚሉ ኃይሎች፤ በተለይ ህወሃትና ኦነግ የሚያምኑበት ርእይቶና የሚከተሉት ዓላማ ስኬታማ ስላልሆነላቸው፤ ህወሓትና አጋሮቹ የፖለቲካ ሥልጣኑን ስለተነጠቁ፤ ኢህአዴግ የፖለቲካ ስልጣን ሲይዝ የመሰረቱት ዘውግንና ቋንቋን መሰረት ያደረገው ህገመንግሥት ፈተና ገጥሞታል ይሉናል። ህወሓት መራሹ ቡድን ባለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት የራሱን ሕገ መንግሥት ያከበረበት ወቅት ትዝ አይለኝም።

ህወሓቶና አጋሮቹ የፈጠሩትን ችግር ራሳቸው ሊፈቱት አይችሉም። ሊፈቱት ቢችሉ ኖሮ ብዙ እድል ነበራቸው። ምርጫ ዘጠና ሰባት የእድል ተምሳሌት ነው። እነ በረከት ሰምዖን ያደረጉት ግን የባሰ ድርጅታዊ ምዝበራ፤ የባሰ እልቂትና ስደት፤ የባሰ ተከታታይ ቀውስ እንዲከሰትና ኢትዮጵያ አምባገነናዊ አገዛዝ ስር እንዲሰድባት ነው። የለንደን ጉባኤ ስምምነት የዛሬው የስርዓት ችግር መነሻ ነው።

በሎንዶን ከተማ በ1991 ዓ.ም. የተካሄደው ጉባዔ አገር ወዳድ ግለሰቦችንና ህብረብሄር ፓርቲዎችን ያገለለ ነበር። ህወሓት በበላይነት፤ ኦነግና ሌሎች የዘውግ ፖለቲካ ፓርቲዎች በአጋርነት የመሰረቱት የመንግሥት አገዛዝ ስልትና የተስማሙበት ሕገ መንግሥት በዘውግ ልዩነትና በመለያየት መብትና አስፈላጊነት የተመሰረተ ነው። ክልል የመለያ ስያሜ እንጅ የአብሮነትና የህብረት ስያሜ አይደለም። ኢትዮጵያንና የኢትዮጵያን ሕዝብ አይወክልም። ሌሎች የአፍሪካ አገሮች አደገኛና አፍራሽ መሆኑን አውቀው ያልተቀበሉት ሕገ መንግሥት መለወጥ አለበት የሚል እምነቴ አሁንም ጠንካራ ነው።

ከላይ እንዳሳሰብኩት፤ ጠ/ሚንስትሩ የሰየሙት የማንነነትና የድንበር ጉዳይ ኮሚሽን፤ በሃቀኛ መስፈርቶች ተመዛዝኖ፤ የክልል አስተዳደሮች፤ ባለሞያዎች፤ ምሁራን፤ አባቶች፤ እናቶችና ሌሎች ተቆርቋሪዎች በሕዝብ ውይይትና ግብዓት ያልተሰየሙበት ስለሆነ፤ በአብዛኛው ከጅምሩ አከራካሪና ውጤቱ አስቀድሞ የሚታወቅ ነው፤ እንደ ገና ቢታሰብበት ይሻላል የሚል ምክር እሰጣለሁ።

January 15, 2019, Foreign Policy “Don’t Let Ethiopia Become the Next Yugoslavia”በሚል አርእስት Florian Biber and Wondemagegn Tadesse Goshu ያቀረቡት ዘገባ እንዲህ ይላል። “Federations of ethnonational states can become explosive during moments of political liberalization, and Abiy must tread carefully to avoid a Balkan nightmare.” የችግሩ መንስኤ የለውጡ ሂደት ብቻ አይደለም። መሰረታዊ ለውጡን ፍጹም በሆነ ደረጃ አንቀበልም የሚሉ ኃይሎች መኖራቸው ጭምር ነው። የጠ/ሚንስትር ዐብይ መንግሥት ይህን ሁኔታ የማሻሻል ግዴታ አለበት። ለምሳሌ፤ ህወሓቶች በተደጋጋሚ  “ሕገ መንግሥቱ ተጣሰ፤ የተገኘው የልማት ድል ሁሉ ተቀለበሰ” እያሉ ይጮሃሉ። የድብቅ ህወሓቶችና ኦነጎች ያሉበት ተቋም ሁሉ ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል። አብዛኛው የኢትዮያ ሕዝብ ሰላምና እርጋታ አለ እያለ ሲያስተጋባ፤ ህወሓቶችና ደጋፊዎቻቸው በአንድ ድምጽ “መንግሥት የለም፤ ሰላምና እርጋታ የለም፤ ነጻነት የለም” ይላሉ። የነሱ ደጋፊዎች የሆኑትን ማህበረሰባዊ ሚዲያዎች ይኼን ሃሰት እንዲያራምድ ጥረት ያደርጋሉ።

ለምሳሌ፤ በቅርቡ አገር ጎብኝተው የተመለሱ ግለስቦችና ቤተሰቦች ወደ ዐማራው ክልል፤ ወደ አዋሳና ሌሎች ቦታዎች ሂደው ሰላምና እርጋታ መኖሩን ይናገራሉ። በዚህ ዓመት የጥምቀት በዓል በጎንደርና በሌሎች ከተማዎች ሲከበር የፌደራሉ ኃይል ከሕዝቡ ጎን ቁሞ ሰላም አስከባሪ ከመሆን ሌላ አብሮ በዓሉን አክብሯል። የጎንደር ከተማ እንደዚህ ያለ ሰላምና እርጋታ አይታ አታውቅም የሚሉ ታዛቢዎች ብዙ ናቸው። በ2015 የተካሄደውን የሚዘገንን እልቂት ማስታወስ ጥሩ ነው። የዛሬ ዓመት የመከላከያ ኃይሉ በያካባቢው ዜጎችን ያስር፤ ያቆስል፤ በጎንደር፤ በባህር ዳር፤ በደብረ ታቦርና ሌሎች ቦታዎች ይገድል ነበር። ህወሓቶች የሚፈልጉት ወንጀሉን፤ ግፉን፤ ግድያውን፤ ዘረፋውን አሁንም መቀጠል ነው። ላለፈው ግፍና በደል በሃላፊነት ያልተጠየቀ ኃይል (Immunity from being held accountable for past crimes and theft) የሚያስከትለው ሌላ ተከታታይ ወንጀል ነው። ማንም አይደፍረኝም ባይነት መቆም አለበት!!

ማንም አይደፍረኝም በሚል ድፍረት የሚሰማው ለፈፋና ጭካኔ መቀጠሉ ለኢትዮጵያዊያን ያሳፍራል እንጅ አያኮራም። ለውጥ መካሄዱ፤ ነጻነት መኖሩ ያኮራል እንጅ አያሳፍርም። ከዚህ በፊት በተደጋጋሚ እንደተከራከርኩት ሁሉ፤ ጠ/ሚንስትር ዶር ዐብይ ሥልጣን ከያዙበት ወዲህ ኢትዮጵያ፤

 1. ብዙ ሽህዎች የፖለቲካ እስረኞችን ፈታለች፤ አንድም የታሰረ ጋዜጠኛ የለም፤
 2. ሁሉም “ተፎካካሪ ፓርቲዎች” መሳሪያቸውን ፈተው ወደ አገር ቤት እንዲገቡ ተደርጓል፤
 3. ጠ/ሚንስትሩ በሚለያዩን እሴቶች ሳይሆን በምንጋራቸው የጋራ እሴቶች ዙሪያ እንድንነጋገርና እንድንወያይ ጠይቀዋል፤
 4. የወደፊቷ ኢትዮጵያ በእርቅ፤ በሰላም፤ በፍቅር፤ በአብሮነት፤ በፍትህ፤ በእርጋታ፤ በተሳትፎ፤ በፍትሃዊ አገዛዝና በእውነተኛ ዲሞክራሲ እንድትመሰረት እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ የድርሻውን እንዲያበረክት ጥሪ ተደርጓል፤
 5. ከዚህ በፊት ባልተለመደ ደረጃ የጠ/ሚንስትሩ ካቢኔ ስርጭት ሴቶችን እንዲያስትፍ ተደርጓል፤
 6. የአፍሪካ ቀንድ ሰላም ለኢትዮጵያ እድገት ወሳኝ በመሆኑ በኤርትራና በኢትዮጵያ መካከል ያለው የወንድማማች/እህትማማች ግንኙነት እንደ ገና እንዲታደስ ተደርጓል፤ የጋራ ግንኙነቱ ለሕዝቡ በሚጠቅም ሁኔታ እየተጠናከረ እንደሚሄድ ይገመታል፤
 7. በህወሓት መራሹ መንግሥት የተከሰተው አይን ያወጣ የዘውግ አድልዎ፤ ሌብነት፤ ሙስና፤ ኃብት ማሸሽ፤ ግፍና በደል መፍትሄ እንዲያገኝ እንቅስቃሴ ተጀምሯል፤ ተቋማት ብሄራዊ እንዲሆኑ ጥረት እየተደረገ ነው፤
 8. ሕዝቡ በመንግሥት ላይ ያለው እምነት እንዲጠናከር አገልግሎት እንዲሻሻል ጥረት እየተደረገ ነው፤
 9. የኢትዮጵያ አምባሳደሮችና ኤምባሲዎች ዋናው ተልኳቸው አገሪቱንና መላውን ዜጋ ማገልገል መሆኑ በማያሻማ ደረጃ ተገልጿል ወዘተ።

ይህም ሆኖ፤ የኢትዮጵያ 110 ሚሊየን የሚገመት ሕዝብ በያካባቢው በግጭት፤ በግድያ፤ በዝርፊያና በሌላ ህውከት ተበክሏል። ዘውግ ተኮር ግጭት ተስፋፍቷል። የፌደራሉ መንግሥት የሚመራበት መርሆና የክልል ፖለቲካ ልሂቃን የሚመሩበት መርህ ሊታረቅና ሊጣጣም አልቻለም። ምክንያቱም፤ ባለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት ሆነ ተብሎ የተሰበከውና ወጣቱ ትውልድ እንዲማር የተደረገው ባህል የመለያየት፤ የጥላቻና ራስን የማገልገል ባህል ነው። የተወሰኑም ቢሆን፤ ለሰላም ቆመናል ብለው ቃል የገቡ ኃይሎች ሳይቀሩ፤ የተገኘውን ነጻነት ተጠቅመው ከዚህ በፊት ታይቶና ተሰምቶ በማይታወቅ ደረጃ ቡድኖቻቸው የገቡትን ቃል ጥሰው እንዲታጠቁ፤ እንዲዘርፉ፤ እንዲገድሉ፤ ኢትዮጵያ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለህገወጥነት እንድትጋለጥ፤ የርስ በርስ ጦርነት እንዲጀመርና አገሪቱ እንደ ዩጎስላቭያ እንድትበታተን ሞክረዋል ወይንም እየሞከሩ ነው።

“These conflicts in turn precipitate ill-conceived moves, including secession, which could have deadly consequences where violence has been the principal means of settling communal disputes.” የኢትዮጵያ ፖለቲካ ልሂቃንና ቡድኖች የለመዱት ሥልጣንን በኃይል ብቻ መያዝ ስለሆነ አሁን የሚካሄዱት ግጭቶች የተለመዱ ናቸው።

የዚህን ማህበረሰባዊ ጉዳት ለማጤን፤ አብዛኛው የዓለም ሕዝብ ምን አይነት ኑሮ ለመኖር እንደሚፈልግና ኑሮው ስኬታማ ለማድረገ ምን አይነት የፖለቲካ ኢኮኖሚ ቅድመ ሁኔዎችን እንደሚፈጥር መመራመር ያስፈልጋል። የልማት ጥናቶች እንዲህ ይላሉ። የመካከለኛውን መደብ ለማስፋት ፖለቲካዊና ማህበረሰባዊ ሰላም፤ የአቅምና የስራ አፈጻጸም ጠንካራነት፤ ጥራት ያለው ትምህርት፤ ጠንካራ ብሄራዊ ተቋማት፤ የዜጎች ተሳትፎ፤ የመፍጠርና የማምረት ሙሉ ተሳትፎ፤ የሕግ የበላይነት ወሳኝ ናቸው። በእነዚህ አገሮች ወጣቶችና ሴቶች ከፍተኛ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴና ተሳትፎ አላቸው። በተለይ አስደናቂ እድገትና የመካለኛ መደብ እድገት የታየው በምስራቅ ኤዢያ ፓሲፊክ፤ በቻይናና በህንድ አገሮች ነው። ዝቅተኛ ተሳፎና እድገት የሚታየው ከሳሃራ በታች ባሉ አገሮች ነው።

በ 2000 ሃያ አምስት በመቶ የሚገመተው የዓለም ሕዝብ መካከለኛ መደብ ነበር። በ2019 በግምት 3.8 ቢሊየን ሕዝብ (የዓለም ሕዝብ ግማሽ) መካከለኛ መደብ ሆኗል። ይህ የሕዝብ አካል የኢኮኖሚ እድገት ሞተር ሆኗል ማለት ነው። ወደ ኋላ የቀሩ አገሮች በግጭት፤ በኑሮ ውድነት፤ በስደት፤ በአካባቢ ውድመት፤ በአድልዎና በሙስና የተበከሉ ናቸው።

የኢትዮጵያን ፖለቲካ ኢኮኖሚ ሁኔታ ቀረብ ብየ ስመራመረው ባለፉት አምሳ ዓመታት የተከተልነው የፖለቲካ መርሆ ግጭትና ንትርክ፤ እልቂትና የኃብት ውድመት ነው። እድገት አለ ቢባልም በዜጎች መካከል የተከሰተው የኑሮና የገቢ ልዩነት እጅግ በጣም አደገኛ ነው። የመካከለኛውን መደብ ስፋት፤ ጥልቀት፤ ማንሰራራትና መጨመር እድል አግዶታል። ሁኔታውን ያባባሱት ብዙ ሰው ሰራሽ ችግሮች አሉ።

ከእነዚህ መካከል፤ ኢትዮጵያ በቋንቋና በብሄር እንድትከፋፈልና ክልሎች የተለያዩ የእድገት እድሎች እንዲኖራቸው፤ ይህች ታሪካዊ አገር ልክ እንደ ቀድሞዋ ዩጎስላቭያ እንድትሆን መደረጉ አንዱና ዋናው ነው።

ለማታወስ ያህል፤ የኢትዮጵያ ቅርብ ወዳጅ አገር የነበረችው (በአጼ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት) ዩጎስላቭያ፤ ችግሮቿን በብሄራዊ ውይይት፤ በሰላም፤ በፍቅር፤ በአብሮነትና በፍትህ ለመፍታት ባለመቻሏ ብዙ ህይወት ጠፍቷል፤ ብዙ ቢሊየን ዶላር ኢንቨስትመንት ባክኗል፤ ታላቋ አገር፤ ቦስንያ-ሄርዘጎቪና፤ ክሮሽያ፤ ሜሶደንያ፤ ሞንቴኔግሮ፤ ሰርብያ፤ ስሎቫንያ፤ ኮሶቮና ራሷን እንድትችል የሆነችው ቮጀቮዲና ወደ ተባሉ ስምነት አገሮች ተከፋፈለች። ዛሬ የዓለም ሕዝብ “ሞንትኔግሮ” የምትባለው አገር የት ናት ቢባል አያውቃትም። ዩጎስላቭያ ግን ዘመናዊ ኢንዱስትሪና የመካከለኛ ገቢ ያሏት ዜጎቿ ከሶቭየት ሕብረት አገሮች የተሻለ ኑሮ የሚኖሩባት አገር ነበረች። የዘውግ ፖለቲካ፤ በቋንቋና በዘውግ የተመሰረተ አገር ሁሌም ግጭቶች ይገጥሙታል። ግጭቶቹ በሰላም ውይይት መፍትሄ ካላገኙ መገንጠል የመጨረሻው አማራጭ ይሆንና ራሳቸውን የማይቹ ትንንሽ አገሮ ይፈጠራሉ። ጠ/ሚንስትር ዶር ዐብይ ይህን ሁኔታ ቢያስቡበት መልካም ነው።

በህወሓት መራሹ የኢህአዴግ መንግሥት ያደገውና የተወለደው ትውልድ (ማለትም አብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ ማለት ነው)፤ እንዲያምን የተገደደው በኢትዮጵያና በኢትዮጵያዊነት ሳይሆን በራሱ ዘውግ፤ በራሱ የዘውግ ፖለቲካ ፓርቲ፤ በራሱ ማንነትና በራሱ ጥቅም ነው። ለማነጻጸር፤ ከላይ የጠቅስኳቸው መካከለኛ መደባቸውን የልማት ሞተር ያደረጉት አገሮች ግን የሚያምኑት በአንድ አገርና በብሄራዊ ብሄርተኝነት ነው። ለምሳሌ፤ ቻይናን እንደ አገር፤ ቻይናዊነትን እንደ ዜግነት መለያ መቀበል ማለቴ ነው። ቬትናም፤ ኢንዶኔዢያ፤ የህንድ አገር፤ አሜሪካር ወዘተ የሚከተሉት ተመሳሳይ ሞዴል ነው። ከኢትዮጵያ ውጭ ከሳሃራ በታች የሚገኙ አገሮችም የሚከተሉት ተመሳሳይ መርህ ነው።

በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ የሚታየው አደገኛ የፖለቲካ ሂደት 9 ወይንም ከዘጠኝ በላይ የሆኑ የክልል መንግሥታት ስር እንዲሰዱ የሚገፉ የድብቅ ኃይሎች መኖራቸው ነው። “Similar to the former Yugoslavia, Ethiopia is a federal state with nine units organized along ethnic lines….The Tigray, Amhara and Oromo regions (around 80 percent of Ethiopia) have their names from their dominant ethnic groups.” ከመሰረቱና ከጽንሰ ሃሳቡ፤ ህወሓት፤ ብአዴን፤ ኦነግና ሌሎች የዘውግ ፖለቲካ ፓርቲዎች የተጠቀሙት ሕገ መንግሥት ህብረ-ብሄራዊነትን የሚጻረር፤ ዘውጋዊነትንና ልዩነትን የሚያጠናክር ነው። ህወሓት ብአዴንን ፈጥሮ የዓማራውን ሕዝብ ትወክላለህ ብሎ ፈረደበት። በረከት ሰምዖን በሙስና መከሰሱ መልካም ዜና ቢሆንም፤ ይህ ድርጅት እስካሁን ድረስ ራሱን ከህወሓቶች አላጸዳም።

በቅርቡ አስደናቂ መሰረታዊ ለውጥ እየተካሄድ ነው የሚለውን ብቀበልም፤ አሁንም ቢሆን ይህ ዘውጋዊነትና ጠባብ ብሄርተኝነት ስር እየሰደድ መሄዱ ለኢትዮጵያና ለመላው ሕዝቧ አደገኛ ነው። “Ethiopia has been ruled for decades by the Ethiopian Peoples’ Revolutionary Democratic Front (EPRDF), a coalition of mostly ethno-regional political parties, dominated by the Socialist Tigray People’s Liberation Front (TPLF). Both combined nondemocratic traits with ethno-federalism.” ህወሓትም ሆነ ኢህአዴግ ብሄራዊና ዲሞክራሳዊ ፓርቲዎች አይደሉም። ባለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት የተፈጠረውና ስር የሰደደው የፖለቲካና የኢኮኖሚ ባህል ኢትዮጵያዊነትን፤ አብሮነትን፤ ሰብእነትንና ሰብአዊ መብትን፤ ፍትህንና ዲሞክራሲን፤ የግል ክፍል ልማትን ሙሉ በሙሉ በሚያስብል ደረጃ የበከለና ያጠፋ ስርዓት ነው።

ዛሬ ህወሓትና መሰል ኃይሎች የሚያደርጉት ጥረት ህወሓትን ህወሓት መሰል በሆነ ሌላ ጨካኝ ፓርቲ መተካት ነው። በኔ ግምገማና እምነት፤ ዳግማዊ ህወሓት ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያዊነት አጥፊ ነው፤ ሁሉም መረባረብ አለበት። ኢህአዴግም ቢሆን በብቸኛነት ኢትዮጵያን ዘመናዊ፤ ፍትሃዊና ዲሞክራሳዊ ለማድረግ አይችልም። ህብረ-ብሄራዊነት ማበብና ቦታውን መያዝ አለበት።

የፈለገውን ያህል ተሻሻለ ቢባልም፤ አንድ ፓርቲ ዲሞክራሳዊ አገዛዝና ሰፊ የመካከለኛ መደብ ሊፈጥር አይችልም። ውድድር መኖር አለበት። በተጨማሪ፤ “አብዮታዊ ዲሞክራሲና” ተወዳዳሪ ኢኰኖሚ፤ ‘ሊበራል ዲሞክራሲ” ተጻራሪ መርሆዎች ናቸው። ሊበራል ዲሞክራሲን ቢሆን መፈተሽና ከአገራችን ሁኔታ ጋር መጣጣም አለበት። መኮረጅ ይቁም።

ይህን ከዲሞክራሲ፤ ከፍትህ፤ ከእውነተኛ እኩልነት ወዘተ ጋር የሚጻረር የጥቂቶች ለጥቂቶች የፖለቲካ ኢኮኖሚ ባህል ከህብረተሰቡ ለማጽዳት ገና ብዙ መሰረታዊ፤ መዋቅራዊ፤ ባህላዊና የተቋማት ለውጥ ያስፈልጋል። ዘውግ ተኮር ፌደራሊዝም ቀስ በቀስ የፈጠረውና ያመረተው ዘጠኝ የተለያዩና የማይደጋገፉ የክልል መንግሥታትን ነው።

የወደፊቷ ኢትዮጵያ ዩጎስላቪያ እንዳትሆን ከተፈለገ ምን አይነት የመንግሥት፤ የፖለቲካ፤ የማህበረሰብና የኢኮኖሚ አገዛዝ (Governance) ያስፈልጋታል? ብየ ራሴን ስጠይቅ አሁን ያለው ዘውግ ተኮር ፌደራሊዝም አለመሆኑን በማያሻማ ደረጃ እጠቁማለሁ። ይህ ሃቅ ብዙ ትንተና፤ ጥናት፤ ውይይትና ጉባኤ አያስፈልገውም። ኢትዮጵያ የዩጎስላቭያ እድል እንዳይገጥማት ከተፈለገ መሰረታዊና ስር ነቀል የሆነ ዲሞክራሳዊ ለውጥ መቀጠል አለበት።

ሕገ መንግሥቱ በአስቸኳይ መለወጥ አለበት። የሕገ መንግሥቱ መሰረት የእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ዜጋ ሁለመናዊ መብት የሚከበርበት መሆን አለበት። በአንድ አገር የተለያዩ “መንግሥታት” ስልጣን ይዘው ሊቆዩ አይችሉም። ይህ ከሆነ ሌሎች አገሮች ከደረሱበት የልማት ደረጃ ለመድረስ አይቻልም። “Without careful management of the delicate transition, Ethiopia risks a dangerous fragmentation along ethnic lines.” የነገዋ ዩጎስላቭያ የመሆን አደጋ ይደርስባታል የሚለውን አልቀበልም። እንጠንቀቅ ግን እላለሁ።

አደጋውን ለመፍጠር የሚፈልጉን ኃይሎች በማባበል ብቻ ለመቋቋም እንደማይቻል አምናለሁ። ለዚህ አደጋ ዋናው ምክንያት “ተገንጣይ” ኃይሎች ብቻ አይደሉም። የኢህአዴግ አባል ድርጅቶችና “ተፎካካሪ” ፓርቲዎች የሚከተሏቸው ፍኖተ ካርታዎች (Road maps) ሊጣጣሙ አለመቻላቸው ጭምር ነው። ለምሳሌ፤ በቅርቡ ስማቸውን የቀየሩት ብአዴን ወደ ዐማራ ዲሞክራቲክ ፓርቲ፤ ኦህዴድ ወደ ኦሮሞ ዲሞክራቲክ ፓርቲ ስማቸውን መቀየራቸው እመርታዊ ለውጥ ሆኖ አላገኘሁትም። አሁንም የያዙት በዘውግ የሚለዩበትን ስም እንጅ በኢትዮጵያዊነታቸው የቆሙበትን እመርታዊ ለውጥ አያሳይም። ሁለቱ ፓርቲዎች የኢትዮጵያን መለያ ስማቸው ይዘው ህብረብሄራዊ ፓርቲ የማይሆኑበት ምን ምክንያት አላቸው?

በኢትዮጵያና በኢትዮጵያዊነት እናምናለን ያሉትንና የሚሉትን እየተቀበልኩ፤ ሁለቱ ፓርቲዎች ውህደት ለመፍጠር የማይችሉበት መሰረታዊ ምክንያት ምንድን ነው? የሚለውን መሰረታዊ ጥያቄ አቀርብላቸዋለሁ። ይህ ካልሆነ አንዱ ሌላውን ለማጥቃት የሚደረገው የፖለቲካ ትግል ይቀጥላል፤ ህወሓትን አስወግዶ ሌላ ህወሓት መተካት ማለት ነው። በዐማራው ዲሞክራሳዊ ፓርቲና በዖሮሞው ዲሞክራሳዊ ፓርቲ መካከል ያለው ግንኙነት እየጠነከረና ህብረ ብሄራዊ እየሆነ ካልሄደ ህወሓት ያለውን ልዩነት ይጠቀምበታል። ከፋፍለህ ግዛውና መዝብረው ይቀጥላል።

በቲቶ ዘመን ዩጎስላቭያ “የክልሎቿ ሕዝቦች ሰብአዊ መብቶች እንዲከበሩ” አድርጋ ነበር። በተመሳሳይ፤ ጠ/ሚንስትር ዶር ዐብይ ሰብአዊ መብቶች እንዲከበሩና የነጻነት ጮራ ስፋትና ጥልቀት እንዲኖረው የማድረጋቸውን ቅንነት የዘውግ ልሂቃንና ፓርቲዎች የራሳቸውን ጠባብ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ጥቅም እያስፋፉበት ይገኛሉ። አድር ባይብነት ጎልቶ ይታያል። እያንዳንዱ የዘውግ ፓርቲ የራሱን ክልል መሬትና ሕዝብ ለራሱ ጥቅም ብቻ እንዲወክል በማድረግ ላይ ይገኛል። ህወሓት የትግራይን ክልል “መንግሥት” የሌቦችና የጨካኞች ምሽግ ሲያደርግ፤ በተመሳሳይም ባይሆን በመጠኑ፤ ኦነግም እድሉን ተጠቅሞ አስራ ሰባት የሚሆኑ የባንክ ቅርንጫፎችን ዘርፏል ወይንም እንዲዘረፉ አድርጓል። በንጹህ ሕዝብ ላይ እልቂት አካሂዷል ወይንም እንዲካሄድ አመቻችቷል።

የዩጎስላቭያን ምሳሌ በመጥቀስ ተመራማሪዎቹ እንዲህ ይላሉ። “Thus, nationalists could easily capture the republics (እኛ ክልል የምንላቸውን ማለት ነው), leading to secession, ethnic cleansing and wars). ቦዝንያና ሌሎች የዩጎስላቭያ ክፍለ ሃገሮች እንደሆነው ማለት ነው። ለምርኮ የሚዳረጉት ክልሎች ብቻ አይሆኑም፤ ኢትዮጵያም ናት!!

ተከታታይ የርስ በርስ ግጭት የሚያስከትለው ጠንቅ ምንድን ነው?

የመዋእለንዋይ ፈሰስ መቀነስ፤ የኑሮ ውድነት፤ የጥቁር ገበያ መስፋፋት፤ የመሳሪያ ሸቀጥ መስፋፋት፤ የውጭ ምንዛሬ እጥረት፤ የኃብት ሽሽት፤ የስራ እድል መጥፋት ወይንም መቀነስ፤ ሕዝቡ በፌደራል መንግሥቱ ላይ ያለው እምነት መቀነስ፤ ሰላምና እርጋታ እየተበከለ መሄድና ሌሎች አስጊ ሁኔታዎች መከሰታቸው ሊካድ አይችልም።

እንዚህ ሁኔታዎች አሉ ቢባልም ኢትዮጵያ “ዩጎስላቭያ” አይደለችም፤ አትሆንም የምልበትን ምክንያት እንደሚከተለው አቀርባለሁ፤

 1. የኢትዮጵያ ሕዝብ አብሮና ተቻችሎ የመኖር ባህሉ ተከታታይና ጠንካራ ነው፤ ተጋብቷል፤ ተዋልዷል፤ ተዛምዷል፤
 1. የኢትዮጵያ ሕዝብ የውጭ ጠላቶቹን በጋራ ሆኖ የመቋቋም ልምድና ባህል አለው፤ ኋላ ቀርነትንና ድህነትንም አብሮ ለመቅረፍ እድሉ ከፍተኛ ነው፤
 1. ኢትዮጵያ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት መስራችና መዲና ናት፤ ይህ ለሁሉም ኢትዮጵያዊያን የሚኮራ ነው፤
 1. አብዛኛው ወጣት ትውልድ የህወሓትንና የአጋሮቹን ግፍና በደል፤ አድሏዊነት፤ ጠባብ ዘረኛነት፤ መዝባሪነት ተቃዋሚ ነው፤ የዐብይን ለውጥ አድናቂና ደጋፊ ነው፤
 1. የዐማራውና የኦሮሞው ዲሞክራቲክ ፓርቲዎች፤ የደቡብ ሕዝብ ፓርቲ የኢትዮጵያን ግዛታዊ አንድነት፤ ሉዐላዊነት፤ ነጻነትና የሕዝቧን አብሮነት በማያሻማ ደረጃ ደጋፊዎች ናቸው፤
 1. የዐብይ መንግሥት መሰረታዊ የሆኑትን ብሄራዊ ተቋማት (የምርጫ ቦርድ፤ የፍትህ፤ የመከላከያ፤ የደህንነትና ሌሎችን) ተቋማት በማሻሻልና በማጠናከር ላይ ነው፤
 1. የዓለም ሕብረተሰብ፤ በተለይ የአሜሪካ፤ የአውሮፓ፤ የጃፓን፤ የቻይናና ሌሎች መንግሥታት የኢትዮጵያን መንግሥትና መሰረታዊ ለውጥ እየደገፉ መታየታቸው፤
 1. ዓለም ባንክ፤ አይ ኤም ኤፍና ሌሎች ግዙፍ የልማትና የገንዘብ ድርጅቶች በኢትዮጵያ የወደፊት ልማት ላይ እምነት ያላቸው መሆኑን በተደጋጋሚ መጠቆማቸው፤ ዓለም ባንክ ግዙፍ ድጋፍ መስጠቱ፤
 1. አብዛኛው የዲያስፖራ አካል የዐብይን መንግሥት ደጋፊ መሆኑ፤
 1. የዐብይ መንግሥት ፍትሃዊ ልማትና ዘላቂ እድገት እንዲመሰረት ማስተጋባቱና ለኢትዮጵያ ዘላቂነትና ለኢትዮጵያዊነት ተቀዳሚነት ያለውን ቆራጥነት በተደጋጋሚ ለኢትዮጵያና ለዓለም ሕዝብ ማስታወቁ ይገኙበታል።

ይህ ለልማት አስፈላጊ ቅድመ ሁኔታ እንዳለ ሆኖ፤ የህወሓትና የኦነግ አክራሪነት፤ የማህበረሰባዊ ሜድያ መረን የለቀቀ አጥፊነትና የብሄራዊ ተቋማት ደካማነት የሚካሄደው መሰረታዊ ለውጥ ረዢም ጊዜ የሚጠይቅና በብልሃትና በጥበብ መመራት እንዳለበት ያሳያል።

የኢትዮጵያ “ተፎካካሪ ፓርቲዎች” ከመቸውም በበለጠ ደረጃ ወደ ውህደት መሸጋገር ያስፈልጋቸዋል።

በተመሳሳይ፤ ኢህአዴግም በዘውግ የተመሰረተውን የፖለቲካ ባህሉን ለመቀየር መድፈር አለበት። ለምሳሌ፤ የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች ከዱሮው ስርዓት የወረሱትን አደረጃጀት ለውጠው ወደ ሕብረብሄራዊ ፓርቲነት የሚቀየሩበት ወቅት ዛሬ እንጅ ኢትዮጵያ የቀድሞዋን ዩጎስላቭያ ከሆነች በኋላ አይደለም። ኢትዮጵያ ሶሪያን እንድትሆንም መፍቀድ የለባቸውም፤ ሕብረብሄራዊነት ለዚህ ይጠቅማል (It is a mitigating factor). “Ethnic parties usually maximize their support not by moderation but by polarization.”

የኢህአዴግ አባል ፓርቲዎች በዘውግ ተደራጅተውና ተሰይመው ሌሎችን ለምን “ጠባብ ብሄርተኛና ጸረ-ኢትዮጵያና ጸረ-ኢትዮጵያዊነት፤ ጸረ-ዲሞክራሲ ትሆናላችሁ” ሊሉ አይችሉም፤ የሞራል ብቃት አይኖራቸውም።

የዐብይ መንግሥት በጥናትና በምርምር ተደግፎ፤ ሕዝብን አሳትፎ በአስቸኳይ ሕገ መንግሥቱን መለወጥ አለበት።

የኔ ምኞትና ተስፋ ኢትዮጵያ አሁን ካለችበት ዘውጋዊ ጥላቻ፤ አድካሚና ሃብትን፤ ጉልበትን፤ እውቀትን፤ ህይወትን፤ የሚያመክን ግጭት ተላቃ ሌሎች ከደረሱበት የመካከለኛ መደብ ደረጃ እንድትደርስ ነው። የኔ ምኞትና ተስፋ፤ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ የዜግነቱን መብት ተጠቅሞ፤ በማንኛውም ኢትዮጵያ ለመኖር፤ ኃብት ለማካበት፤ ለመምረጥና ለመመረጥ የሚችልበት ሁኔታ እንዲፈጠር ነው።

ችግሯ አገሪቱ ወይንም ሕዝቡ አይደለም። መሰረታዊ ችግራችን፤ ጠባብ ብሄርተኝነት፤ ትምክኸተኛነት፤ የስልጣን ፉክክርና የኢኮኖሚ ስግብግብነት ነው። እነዚህ ችግሮች በማባበል አይፈቱም፤ የሚፈታቸው የሕዝብ የፖለቲካ ሥልጣን ስኬታማ ሲሆን ነው። ሕዝቡ የኃብቱ ባለቤት ሲሆን ነው።

Revised slightly from a version of January 23, 2019 published in Ethiopia.

አ/ቢ February 9, 2019