አቶ ክርስቲያን ታደለ እና አቶ በለጠ ካሳን ጨምሮ ሌሎች የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) አመራሮችና አባላት ያቀረቡት የዋስትና ጥያቄ ላይ ፍርድ ቤቱ ውድቅ አደረገ

ከሰኔ 15ቱ የአማራ ሕዝብ መሪዎች እና የአገሪቱ ከፍተኛ የጦር መኮነኖች ግድያ ጋር በተያያዘ ጠርጥሬያቸዋለሁ በሚል በፖሊስ ተይዘው ከአራት ወራት በላይ በእስር ላይ የሚገኙትና በሃምሳ አለቃ መሳፍንት ጥጋቡ መዝገብ ስር የቅድመ ክስ ምርመራ ከተከፈተባቸው 13 ተጠርጣሪዎች መካከል የተካተቱት:-

1ኛ) ክርስቲያን ታደለ የአብን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ
2ኛ) በለጠ ካሳ የአብን ፅሕፈት ቤት ኃላፊ
3ኛ) አስጠራው ከበደ የአብን አባል
4ኛ) ሲሳይ አልታሰብ የአብን ብሔራዊ ም/ቤት አባል
5ኛ) ፋንታሁን ሞላ የአብን አባል
6ኛ) አማረ ካሴ የአብን የአዲስ አበባ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ
7ኛ) አየለ አስማረ የአብን አባል

ዛሬ ኅዳር 10 ቀን 2012 ዓ.ም የፌደራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎት ቀርበው ነበር።

ፍርድ ቤቱ ለዛሬ ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቶ የነበረው አቃቢ ሕግ በተጠርጣሪዎቹ ላይ አሉኝ ያላቸውን ምስክሮች ለማሰማት የቅድመ ክስ ምርመራ መዝገብ ከከፈተ በኃላ በተሰጠው 3 የጊዜ ቀጠሮ ምስክሮችን ሳያሰማ ክስ ለመመስረት መዝገቡ ወደ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ይመራልኝ የሚለውን በመቃወም የተጠርጣሪ ጠበቆች ባቀረቡት የዋስትና መብት ይከበርልን ጥያቄ በተጠርጣሪዎቹ ላይ የቀረበውን ክስ ተመልክቶ ውሳኔ ለመስጠት ነበር።

በዛሬው የችሎት ውሎም አቃቤ ሕግ በተጠርጣሪዎቹ ላይ የመሰረተውን ክስ አያይዞ ያቀረበ ሲሆን ፍርድ ቤቱም አቃቤ ሕግ የመሰረተው ክስ ሊያስቀጣ የሚችለው ቅጣት ከባድና ዋስትና የማያሰጥ ነው በሚል ያቀረቡትን የዋስትና ጥያቄ ውድቅ በማድረግ አቃቤ ሕግ በከፍተኛ ፍርድ ቤት ክስ እስኪመሰርት ድረስ ተጠርጣሪዎቹ በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን 3ኛ ፖሊስ ጣቢያ ይቆዩ ሲል ውሳኔ ሰጥቷል፡፡

ፍኖተ አብን

ባሕር ዳር ላይ በተደረገው የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታ ኢትዮጵያ ኮትዲቯርን 2ለ1 አሸንፋለች

ጨዋታውን አስመልክቶ አሰልጣኙ፣ ተጨዋቾች እና ደጋፊዎች አስተያዬታቸውን ሰጥተዋል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ “በሙሉ የጨዋታ ብልጫ እና የኳስ ቁጥጥር ከጥሩ የግብ ሙከራዎች ጋር በማሸነፋችን ደስተኛ ነኝ” ብለዋል። ዋልያዎቹ ጨዋታውን ማሸነፋቸው በአፍሪካ ዋንጫ ውድድር ለመሳተፍ መልካም ጅምር መሆኑን እና ከምድቡ ከባድ ከተባለው ቡድን ሙሉ ሦስት ነጥብ መውሰዳቸው ለቀጣይ ጨዋታ ትልቅ የሞራል ስንቅ እንደሚሆን ነው ኢንስትራክተር አብርሃም የተናገሩት።

የዛሬው ውጤት ለቀጣይ ጨዋታዎች በከፍተኛ የራስ መተማመን እንዲዘጋጁ ትልቅ ሚና እንደሚኖረው አሰልጣኙ ገልጸዋል። ተጨዋቾች በሜዳ ውስጥ የነበራቸው እንቅስቃሴ በተሰጣቸው ትዕዛዝ መሠረት መሆኑን በመጥቀስም አስጣኙ ምሥጋና አቅርበዋል። ከብሔራዊ ቡድኑ ጀርባ ሆነው በጥሩ ሥነ ምግባር ሲደግፉ የነበሩትን የባሕር ዳርና አካባቢው እንዲሁም ከሩቅ ቦታ ወደ ስታዲዮሙ የመጡ የእግር ኳስ አፍቃሪያዎችንም አመሥግነዋል።

የቡድኑ አንበል ሽመልስ በቀለ እና የአማካይ ስፍራ ተጨዋቹ ሱራፌል ዳኛቸው ለውጤቱ መገኘት ኢንስትራክተር አብርሃም ቡድኑን የገነቡበት መንገድና የተከተሉት የእግር ኳስ አጨዋወት ጥበብ መሆኑን ተናግረዋል። በጨዋታው የተሰለፉት ወጣት ተጨዋቾች በሙሉ የራስ መተማመን እና የቡድን መግባባት ስለነበራቸው የተሻለ መጫወታቸውንም ተናግረዋል። ቀጣይ በሚኖራቸው ጨዋታ ኳስን በመቆጣጠር ጥሩ ውጤት ለማምጣት እንደሚጫወቱም ተናግረዋል። ደጋፊዎች በጨዋታው ያሳዩትን ጨዋነት የተሞላበት ድጋፍ ቀጣይም አጠናክረው እንዲቀጥሉም ጠይቀዋል።
ጨዋታውን አስመልክቶ አስተያዬታቸውነ ለአብመድ የሰጡ ደጋፊዎችም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ፍጹም የጨዋታ የበላይነት ወስዶ ያሸነፈበት መሆኑን ነው የተናገሩት። እንዳለ ሙሉ እና ሳለአምላክ ዓለምነው የተባሉ ደጋፊዎች ጨዋታው አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው ኢትዮጵያን ለአፍሪካ ዋንጫ ያሳለፉበትን ጊዜ እንዳስታወሳቸው ተናግረዋል። እንደ ደጋፊዎቹ አስተያዬት ኢትዮጵያ ከኮትዲቯር ያደረጉት ጨዋታ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የበላይነት፣ ጥሩ የኳስ ፍሰት ታይቶበት፣ በሙሉ የራስ መተማመን ስሜት ሙሉ ሦስት ነጥብ መገኘቱ አስደሳች ሆኗል። በእንግሊዝና ሌሎችም የአውሮፓ ሊጎች ዝናን ያተረፉ ተጨዋቾች የተካተቱበትን ስብስብ ማሸነፋቸው ደግሞ ከድልም ከፍ ያለ ድል እንደሆነ አስተያዬት ሰጭዎቹ አመልክተዋል፡፡

በጨዋታው በክረምቱ የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ የዝውውር ወቅት አርሰናልን በክብረ ወሰን ክፍያ የተቀላቀለው ኒኮላስ ፔፔ እና የቶተንሃሙ ኦሬይን የመሳሰሉ ድንቅ ተጨዋቾች እምብዛም እንቅስቃሴ ሲያደርጉ አልተስተዋለም። “በእንግሊዝ ፕሪሜዬር ሊግ አጥቂዎች አልደፈሩትም እየተባለ የተወራለትን የሊሸርፑል ተከላካይ ቨርጅል ቫንዳይክን ለመጀመሪያ ጊዜ የደፈረው ፔፔ አስቻለው ታመነን ማለፍ አቅቶት አምሽቷል” ብሏል እንዳለው።

በአንጻሩ በኢትዮጵያ በኩል እነ ሽመልስ በቀለ፣ ሱራፌል ዳኛቸው፣ አዲስ ግደይ እና ሌሎችም ተጨዋቾች ተስፋ ሰጪ የጨዋታ እንቅስቃሴ አድርገዋል። ‹‹ይህም ኢትዮጵያውያን ተጨዋቾች እድል ቢያገኙ በአውሮፓ ከሚጫወቱ አንዳንድ ተጨዋቾች የተሻሉ እንደሚሆኑ ያሳያል›› ብለዋል አስተያዬት ሰጪዎቹ። በጨዋታው የታየውን ጥሩ እንቅስቃሴ ያደነቁት ደጋፊዎቹ በቀጣይ የአካል ብቃት፣ ሥነ ልቦናዊ ጥንካሬ እና በቡድን መሥራት ላይ በትኩረት መሠራት እንዳለበትም አስተያዬታቸውን ሰጥተዋል። ደጋፊው በባሕር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲዮም ከዚህ በፊት እንደሚያደርገው ሁሉ ጥሩ ድጋፍ ማድረጉ ለውጤቱ መገኘት አስተዋጽኦ እንደነበረውም ነው ደጋፊዎቹ የተናገሩት።

ባሕር ዳር ላይ የሚደረጉ ጨዋታዎች ከገጽታ ግንባታ ጀምሮ ለከተማዋ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ እንክስቃሴዎች ማደግ የሚጫወተው ሚና ከፍተኛ መሆኑን ነው የተናገሩት። እንደ ደጋፊዎቹ አስተያዬት በከተማዋ ዓለም አቀፍ ውድድሮች ሲደረጉ በርካታ ስፖርተኞች እንዲያድጉ እድል ይፈጥራል። በከተማው የእግር ኳስ መሠረተ ልማት በጥሩ ሁኔታ እንዲስፋፋም በር ይከፍታል። በጥቅሉ የሚደረጉ ዓለም አቀፍ ውድድሮች ሁለንተናዊ ስፖርታዊ እድገት እንዲኖረው ያደርጋል። በመሆኑም የከተማዋ ስፖርት አፍቃሪያን ፍጹም ጨዋነት በተሞላው መንገድ የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉም አሳስበዋል።

ኢትዮጵያ በምትገኝበት ምድብ 11 የሚገኙት ኒጀርና ማዳጋስከር ማምሻውን ተጫውተዋል፤ በውጤቱም ማዳጋስከር 6ለ2 አሸንፋለች፡፡ ከቀናት በፊት ኢትዮጵያን ያሸነፈችው ማዳጋስከር በ6 ነጥብና አምስት የግብ ክፍያ ምድቡን ትመራለች፤ ኢትዮጵያና ኮትዲቯር በእኩል 3 ነጥብ ቀጣዩን ደረጃ ይዘዋል፡፡ ኒጀር ያለምንም ግብ ከምድቡ ግርጌ ተቀምጣለች፤ በነሐሴ ወር የመጨረሻ ሳምንት ኢትዮጵያ ከኒጀር ጋር የምትጫወት ይሆናል፡፡

ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ

በአንድነት መቆም ሲያቅት እጅ ጠምዛዦች ይጠናከራሉ!

በአንድነት መቆም ሲያቅት እጅ ጠምዛዦች ይጠናከራሉ!

ለአንድ አገር የጥንካሬ መሠረቱ የሕዝቡ አንድነት ነው፡፡ ሕዝብ በአገሩ ጉዳይ የጋራ አቋም ኖሮት አንድነቱን በተግባር ማሳየት የሚሳነው ከሆነ፣ በውስጡ መከፋፈልና መለያየት እንዳለ ግልጽ ነው፡፡ ዝነኛው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት አብረሃም ሊንከን፣ ‹‹የተከፋፈለ ቤት ፀንቶ ሊቆም አይችልም፤›› እንዳለው፣ አገርም ልባቸው በከተፋፈለ ዜጎች ምክንያት መቆም ይቸግረዋል፡፡ ምንም እንኳ በሁሉም ነገር መስማማት ባይቻልም፣ ወሳኝ በሚባሉ ብሔራዊ ጉዳዮች ላይ መከፋፈል የአገርን ጥንካሬ ያዳክማል፡፡ ከዚህ ቀደም ኢትዮጵያዊያን የሚታወቁበት ልዩ መለያቸው አገራቸውን መውደዳቸው፣ ለአገራቸው ሲሉ ልዩነቶችን በማስወገድ አንድ ላይ መቆማቸውና ከራሳቸው በፊት የአገራቸውን ጥቅምና ደኅንነት ማስቀደማቸው ነው፡፡ የአገር ህልውና አስተማማኝ የሚሆነው ከራስ ጉዳይ በፊት የአገር ሲቀድም ነው፡፡ በዚህ ዘመን ግን በበርካታ ዘርፈ ብዙ ጉዳዮች ምክንያት በአገር የጋራ ጉዳይ ላይ እንኳን አንድ ላይ ለመቆም፣ ተነጋግሮ መግባባትም በጣም እየከበደ ነው፡፡ ‹‹የጋራ ታሪክ የለንም›› ከሚሉ አላዋቂዎች ጀምሮ በኢትዮጵያዊነት ላይ እስከሚያላግጡ መሰሪዎች ድረስ፣ ለማመን የሚከብዱ ጥልቅ የሆኑ ልዩነቶች እየታዩ ነው፡፡ በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚና በተለያዩ ማኅበራዊ ጉዳዮች ልዩነቶች መኖራቸው የግድ ቢሆንም፣ በጋራ ብሔራዊ ጉዳዮች ላይ መከፋፈል ለጥቃት ያጋልጣል እንጂ ፋይዳ የለውም፡፡ ሰላም፣ ዴሞክራሲና ብልፅግና ዕውን የሚሆኑት በመከፋፈል አይደለም፡፡ መከፋፈል የአጥቂ ሰለባ ያደርጋል፡፡

ኢትዮጵያዊያን የጋራ የሆኑ እሴቶቻቸውን አስጠብቀው ዘመናትን የተሻገሩት፣ ለአገራቸው በነበራቸው ጥልቅ የሆነ ፍቅር እንደነበር አይዘነጋም፡፡ በከባድ የጭቆና ቀንበሮች ውስጥ ሆነው እንኳ አገራቸውን በጋራ ሲጠብቁ ኖሩ እንጂ፣ አገራቸውን አንዴም በጠላት አስደፍረው አያውቁም፡፡ በታላቁ የዓድዋ ድል አከርካሪውን የተመታው ጣሊያን ከ40 ዓመታት በኋላ በሠለጠኑ ተዋጊዎች፣ በዘመናዊ የጦር መሣሪያና ድርጅት ተጠናክሮ መጥቶ ወረራ በፈጸመባቸው አምስት ዓመታት፣ አንድም ቀን ፋታ ሳያገኝ በሽምቅ ውጊያ ጀግኖች አርበኞች እንዳርበደበዱትና በመጨረሻ ተሸንፎ መውጣቱን ታሪክ የመዘገበው ሀቅ ነው፡፡ ይህ ታላቅ የአገር ፍቅር ከጥንት ጀምሮ እስከ ባድመ ጦርነት ድርስ በአንፀባራቂ ድሎች የታጀበ ነበር፡፡ ለኢትዮጵያ ሕዝብ የአንድነቱ ማሳያ ቋሚ ምስክርም ነው፡፡ ይህንን የመሰለ አንፀባራቂ ገድል በተሠራበት አገር ውስጥ ከአንድነት ይልቅ መለያየት፣ ከጋራ ጉዳዮች ይልቅ ቡድን ላይ ማተኮር፣ ኢትዮጵያዊነትን በማጣጣል ብሔርተኝነትን ማሟሟቅ፣ የዘመናት አብሮነትን ወደ ጎን በመግፋት መነጠልን ማበረታታት፣ ወዘተ ከመጠን በላይ እየተለመደ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት አገራዊ አንድነት እየተሸረሸረ ሸብረክ እየተባለ ነው፡፡ ታሪካዊው አንድነት ተሸርሽሮ ልዩነት ሲሰፋ፣ የዘመናት የአገር ባላንጣዎች አንገታቸውን ቀና አድርገው እጅ መጠምዘዝ ጀምረዋል፡፡

ኢትዮጵያ በታላቁ የህዳሴ ግድብ የኤሌክትሪክ ኃይል ለማመንጨት የጀመረችው ፕሮጀክት፣ በእልህ አስጨራሽ ውጣ ውረድ ውስጥ ስምንት ዓመታት አስቆጥሯል፡፡ በአምስት ዓመታት ይጠናቀቃል የተባለው ይህ ብሔራዊ ፕሮጀክት ውስጣዊ ችግሮች ቢያጋጥሙትም፣ በተለይ በግብፅ እየተጋረጠበት ያለው መሰናክል እንዲህ በቀላሉ የሚታይ አይደለም፡፡ ግብፅ በቅርቡ የውኃ አሞላሉ የአስዋን ግድብን መጠን ከ165 ሜትር በታች ዝቅ እንዳያደርግ ያቀረበችው አደገኛ ፕሮፖዛል፣ ምን ያህል ነገር ፈላጊነት የሚንፀባረቅበትና የእኛን የእርስ በርስ መከፋፈል አጋጣሚ በመጠቀም የቀረበ እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡ ይህ አልበቃ ብሎ አሜሪካና የዓለም ባንክ ወደ ውይይቱ እንዲመጡ ያደረገችበት እጅ ጥምዘዛም ቀላል አይደለም፡፡ እስካሁን ባለው መረጃ የኢትዮጵያ መንግሥት ቀደም ሲል ከነበረው አቋሙ የተለየ ነገር እንደሌለ ቢያስታውቅም፣ የአሜሪካና የዓለም ባንክ የውይይቱ አካል እንዲሆኑ መደረጉ ይጎረብጣል፡፡ የተፅዕኖው አድማስ እንዴት እየሰፋ መምጣቱንም  ማመላከቻ ነው፡፡ ለዓባይ ውኃ 87 በመቶ የምታበረክተው ኢትዮጵያ፣ ውኃውን በፍትሐዊ መንገድ የመጠቀም መብት ያላት ኢትዮጵያ፣ በግድቡ ላይ የሚነሱ አለመግባባቶች በቴክኒክ ባለሙያዎች ሙያዊ ምክክርና ምክረ ሐሳብ እንደሚፈቱ እምነት ያላት ኢትዮጵያ፣ ለውኃው ምንም ዓይነት አስተዋጽኦ በሌላት ግብፅ እጇ መጠምዘዝ አልነበረበትም፡፡ ይህንን ከበባ እያዩ ኢትዮጵያዊያን ከመቼውም ጊዜ  በላይ በአንድነት መቆም ነበረባቸው፡፡ ይህ ግድብ ተወደደም ተጠላም ብሔራዊ ፕሮጀክታችን ነው፡፡ ይህንን ብሔራዊ ፕሮጀክት በጋራ የመጠበቅ ኃላፊነት የኢትዮጵያዊያን ብቻ ነው፡፡ ይህንን የሚፃረሩ ካሉ በእርግጥም የባዕዳን ተላላኪዎች ናቸው፡፡ በአንድነት አለመቆም መዘዙ የከፋ ነው፡፡

ከህዳሴ ግድቡ በተጨማሪ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ደኅንነትና ጥቅም ኢትዮጵያዊያንን ሊያሳስብ ይገባል፡፡ ፖለቲከኞች፣ ምሁራን፣ የሃይማኖት መሪዎች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ አርሶ አደሮች፣ ነጋዴዎች፣ ተማሪዎች፣ ወዘተ አገራቸው ማናቸውም ዓይነት ግጭቶች ውስጥ ሳትገባ በሰላም መኖር እንዳለባት ስምምነት ሊኖራቸው ይገባል፡፡ የትኛውም የፖለቲካ፣ የእምነት፣ የቋንቋ፣ የባህል፣ የብሔርና ሌሎች መሰል ጉዳዮች ላይ ልዩነት ቢኖር፣ ልዩነቱ የአገርን አንድነት የሚያፈርስ ወይም የሚበትን መሆን የለበትም፡፡ ግለሰብ ፖለቲከኞችም ሆኑ ሌሎች ልዩነታቸውን በሠለጠነ መንገድ የሚፈቱበት ሕጋዊና ዴሞራሲያዊ አሠራር እንዲጠናከር መሥራት አለባቸው እንጂ፣ ጥጋባቸው በተነሳ ቁጥር አመፅ እያስነሱ ሕዝብ ማስፈጀት አይኖርባቸውም፡፡ በእነሱ ምክንያት የአገር ሰላም እየተናጋ ንፁኃን ሲገደሉ፣ የአካልና የሥነ ልቦና ጉዳት ሲደርስባቸው፣ ሲፈናቀሉና ንብረታቸው ሲዘረፍ የአገር ሰላም ይቃወሳል፡፡ ግለሰቦች ወይም ቡድኖች ከአገር ህልውና በላይ ሆነው እንደ ፈለጋቸው ሲሆኑ፣ የሕዝቡ የዘመናት የጋራ እሴቶች እየተናዱ እርስ በርስ መጋደል ልማድ ይሆናል፡፡ ይህ አስከፊ ልማድ ሲጠናከር ደግሞ አገር ትዳከማለች፡፡ ለዘመናት የተገነባው ኢትዮጵያዊ ማንነት ይጠፋል፡፡ እንኳንስ ሰላም፣ ዴሞክራሲና ብልፅግና ሊመጡ ዕልቂት የየዕለቱ ዜና ይሆናል፡፡ ይህንን የሚፈልጉ ኃይሎች ደግሞ ከኋላ ሆነው እየቆሰቆሱ አገር ያፈርሳሉ፡፡ ፍላጎታቸው ይኸው ብቻ ነው፡፡ በአንድነት መቆም ካልተቻለ ለተፅዕኖ ፈጣሪዎች መንበርከክ አይቀሬ ነው፡፡

ለኢትዮጵያ የሚበጃት የሕዝቧ አንድነት ነው፡፡ ይህ አንድነት በመፈላለግ፣ በመከባበር፣ በመፈቃቀርና በመተሳሰብ ላይ እንዲገነባ ከጥፋት መንገዶች መታቀብ ተገቢ ነው፡፡ አንዱ የኢትዮጵያዊነት ዋና ባለቤት ሆኖ ዜግነት ሰጪና ከልካይ ሲሆን፣ ሌላው ደግሞ ታሪካዊ ዳራዎችን በሚፈልገው መንገድ እየተረጎመ አገር ለመበተን ሲነሳ በጋራ አይሆንም ማለት ይገባል፡፡ ሁለቱም ጽንፍ የረገጡና አማካይ የሚባል ነገር ስለማያውቁ፣ ከእነሱ ተሽሎ መገኘት የግድ ይሆናል፡፡ የኢትዮጵያ ፖለቲካ አላድግ ያለው የጽንፈኝነት መራቢያ በመሆኑ ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ምድር አሀዳዊ ሥርዓት ተግባራዊ ማድረግ እንደማይቻለው ሁሉ፣ በጽንፈኛ ብሔርተኝነት ትክክለኛ ፌዴራላዊ ሥርዓት መመሥረት አይቻልም፡፡ የሚቻለው ግን ልዩነትን በመያዝ ለጋራ ጉዳዮች አስተዋጽኦ ማበርከት ነው፡፡ ተግባራዊ ሊሆኑ የማይችሉ ጽንፍ የረገጡ አቋሞችን ይዞ ፖለቲካኛ ነኝ ማለት እንደማይቻለው ሁሉ፣ ተግባራዊ መሆን የሚችሉ አጀንዳዎችን በማንቀሳቀስ በጋራ ለመቆም አለመቻልም ፖለቲከኛ አያሰኝም፡፡ ከታሪካዊ ስህተቶች በማመር ኢትዮጵያ የሰላም፣ የነፃነት፣ የፍትሕና የእኩልነት አገር እንድትሆን በአንድነት መቆም የጊዜው ጥያቄ ነው፡፡ ከዚህ ውጪ ያለው ወይ የታሪካዊ ጠላቶች ተላላኪ መሆን ነው፣ ወይም የፖለቲካ ማይምነት አረንቋ ውስጥ መዘፈቅ ነው፡፡ ለኢትዮጵያ ሁለቱም አይበጇትም፡፡ ለኢትዮጵያ የሚበጇት አንድነቷን አጠናክረው ታላቅ የሚያደርጓት ናቸው፡፡ አገር በተከፋፈለ ልብ ፀንታ መቆም መቸገር ብቻ ሳይሆን፣ የእጅ ጠምዛዦች ሰለባ እንደምትሆን ማሰብ ያስፈልጋል፡፡ በአንድነት መቆም ካልተቻለ እጅ ጠምዛዦች መጠናከራቸው አይቀሬ ነው!FacebookTwitterLinkedInShare

በህዳሴ ግድብ ስም ተከፍተው የነበሩ 4000 የገንዘብ አካውንቶች በአንድ ቋት ተጠቃለሉ – በሩብ ዓመት ብቻ 168 ሚሊየን ብር ተሰብስቧል

– በሩብ ዓመት ብቻ 168 ሚሊየን ብር ተሰብስቧል

አዲስ አበባ፡- ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታን ለማፋጠን ሲባል ተከፍተው የነበሩ 4000 የገንዘብ አካውንቶች በአንድ ቋት መካተታቸው ተገለፀ።

ህዝባዊ ተሳትፎ እንደቀጠለ ሲሆን በ2012 ሩብ ዓመት ብቻ 168 ሚሊየን ብር መሰብሰቡ ተጠቆመ።

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ህዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት የህዝብ ግንኙነትና የሚዲያ ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ኃይሉ አብርሃም ትናንት በሰጡት መግለጫ፤ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታን ለማፋጠን ሲባል በድርጅቶች፣ ተቋማትና ግለሰቦች ተከፍተው የነበሩ ከ4000 በላይ አካውንቶች ለሥራ ያመች ዘንድ በአንድ አካውንት ብቻ እንዲስተናገድ ተደርጓል።

እንደ አቶ ኃይሉ ገለፃ፤ የግድቡ ግንባታ በተፋጠነ ሁኔታ የቀጠለ ሲሆን ህዝባዊ ተሳትፎውም አሁንም ተጠናክሮ ቀጥሏል። በ2011 በጀት ዓመት 970 ሚሊየን ብር የተሰበሰበ ሲሆን በ2012 ሩብ ዓመት ደግሞ 168 ሚሊየን 953 ሺህ ብር ገቢ ተገኝቷል። በተለይም በመስከረም 2012 ዓ.ም 82 ሚሊየን ብር ተሰብስቧል። በቀጣይም በአማካይ በየወሩ 100 ሚሊየን ብር የመሰብሰብ ውጥን መኖሩን አመልክተዋል። ቀደም ባሉት ዓመታትም ህዝባዊ ተሳትፎ በነበረበት ወቅትም እስከ 100 ሚሊየን ብር ይሰበሰብ ነበር።

ከገንዘብ ተቋማት ጋር በመሆን ጽሕፈት ቤቱ በስፋት እየሠራና ቃል የተገቡ ሀብቶች ተሸጠው ብሩ እንዲገባ እየተደረገ ነው። ለህዝብ መረጃ በመስጠት ረገድ ክፍተት መኖሩንም በመጠቆም፣ በዚህ ረገድ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች በስፋት እንዲሠሩ ጥሪ ቀርቧል። መሥሪያ ቤቶች ተከታትለው ቦንድ ለገዙ ዜጎች ኩፖን አለመስጠታቸው ሌላው ችግር እንደነበር አስታውሰዋል። የቦንድ ግዥ በተመለከተም በርካታ ቅሬታዎች ነበሩ። በአሁኑ ወቅት ግን ሰባት ማይክሮ ፋይናንስ፣ ልማት ባንክ እና ንግድ ባንክ ጋር በመነጋገር አሠራሩ ፈር እንዲይዝ ተደርጓል። እስከ አሁን ቦንድ ለገዙ ዜጎች ስድስት ቢሊዮን ብር ተመላሽ ሆኗል።

እንደ ዳይሬክተሩ ገለፃ፤ በግድቡ ግንባታ ዙሪያ የኢትዮጵያ አካሄድ ሳይንሳዊና የወንዙን የ100 ዓመት ፍሰትን መሰረት በማድረግ የውሃ ሙሌቱን ታሳቢ አድርጋ እየሠራች ነው። ግብፅ ከዲፕሎማሲ ስትወጣ መስመር እንድትይዝ እየተደረገ መሆኑንም አብራርተዋል። ‹‹እየገነባን ያለነው ግድብ እንጂ ስታዲየም አይደለም›› ለዚህም ግድቡ ውሃ እንዲይዝ በሳይንሳዊ መንገድ እንሠራለን ብለዋል።

ግብፅ በአባይ ላይ እምነት በማጣቷም ሦስተኛ አደራዳሪ መፈለጓንም ጠቁመዋል። ይሁንና የሚደራደሩት ባለሙያዎች በመሆናቸው ኢትዮጵያ አሁንም በፍትህ አደባባይ አሸናፊ ትሆናለች፤ ብሔራዊ ጥቅሟንም አሳልፋ አትሰጥም ነው ያሉት።

ግብፅ ጉዳዩን በፖለቲካ ዓይን ከማየት በዘለለ ሌላ እይታ እንዲኖረው አትፈልግም። ይሁንና ግድቡ እውን እንዲሆንም የኢትዮጵያም ህዝብና መንግሥት ወሳኝ ሚና እንዳላቸው አብራርተዋል።

መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፤ የግድቡ መሰረተ ድንጋይ ሲቀመጥ በ80 ቢሊዮን ብር

ለማጠናቀቅ ታስቦ የነበረ ሲሆን፤ እስካሁን 99 ቢሊዮን ብር ወጪ ተደርጓል። ግድቡን ለማጠናቀቅ ደግሞ 40 ቢሊዮን ብር ተጨማሪ ወጪ ይጠይቃል። ለግድቡ ግንባታ 15 ከመቶ የሚሆነውን ገንዘብ ከህዝቡ ለመሰብሰብ የታቀደ ሲሆን እስካሁን 13 ቢሊዮን ብር ከህዝቡ መሰብሰቡ ይታወቃል።

አዲስ ዘመን ጥቅምት 29/2012

ክፍለዮሐንስ አንበርብር

(ኢ.ፕ.ድ)

ኦዴፓ ሕወሓት የሔደበትን ቁልቁለት ባይጀምረው መልካም ነው! – በያሬድ ኃይለማርያም

በኦዴፓ የሚመራው የለውጥ ኃይል ህውሃት ያሰመረለትን የቁልቁለት መንገድ መመለሻው እሩቅ ስለሆነ ባይጀምረው መልካም ነው። ህውሃት ያሽመደመዳት ኢትዮጵያ ሌላ አሽመድማጅ ወይም አፋኝ ወይም የመድሎ ሥርዓት የምትሸከምበት ጫንቃ የላትም። በተወሰነ ደረጃ በተግባር፤ በብዛት ደግሞ በንግግር የታጀበው የዶ/ር አብይ ኢትዮጵያን የመታደግ ህልም እና ምኞት በድርጅታዊ ቅዠት እና በፓርቲዎች መካከል በሚታየው ፉክክር እየተደነቃቀፈ መንገዱን ሊስት የሚችልበት እድል እሩቅ አይደለም።

የለውጥ ኃይሉ በአንድ አመት ውስጥ ያከናወናቸው ብዙ መልካም ነገሮች በየቀኑ በሚፈጠሩና ልብ በሚሰብሩ አሳዛኝ ክስተቶች እና በመንግስት አካላት በሚፈጸሙ ጉልህ ስህተቶች ከወዲሁ ጥቁር ጥላ እያጠላበት ይመስላል። እርግጥ ነው ብዙ የተወሳሰቡ ችግሮች ባሉባት እና ብሔረተኝነት ከፖለቲካ መድረክ መነታረኪያነት አልፎ የእርስ በርስ ግጭቶችን፣ የሚሊዮኖች መፈናቀልን እና ወከባን እያስከተለ ባለበት አገር ሁሉንም ሰው ሊያስደስት የሚችል ሥራ መስራት እጅግ ከባድ ነው።

በዛሬዋ ኢትዮጵያ የመንግስት ስኬት እና ውድቀት ብቻ ሳይሆን እያንዳንዱ እርምጃ የሚለካው በብሔር ሚዛን ስለሆነ ሁሉም ለእኔ ምን ተደረገ እንጂ ከእኔ ምን ይጠበቃል አይልም። ሌላው ሲያገኝ ለእኔም ይበጃል ብሎ የማሰብ ነገር የለም። ሹመትም ሆነ ሽረት፣ እስርም ሆነ ፍቺ፣ ልማትም ሆነ ጥፋት የሚለኩት በአገራዊ ሚዛን ሳይሆን በብሄር ሚዛን ሆኗል።

ከዚህ እውነታ ባሻገር ግን ለውጡን በሚመራው በኦዴፓ በኩል ከወዲሁ እየታዩ ያሉት ችግሮች ህውሃት አገሪቱን ከተቆጣጠረ በኋላ የመጣበትን መንገድ እንድናስታውስ እያደረገን ነው። በሽግግር ወቅት የነበው ህውሃት/ወያኔ በተወሰነ ደረጃ ከሽግግሩ በኋላ ከነበረው ወያኔ ይሻል ነበር። ከምርጫ 1997 በፊት የነበረው ወያኔ በብዙ መልኩ ከምርጫው በኋላ ከነበረው የወያኔ አስተዳደር ይሻል ነበር። ሌላው ቀርቶ ከምርጫ 2007 በፊት የነበረው የኃይለማርም አስተዳደር ከምርጫው በኋላ የለየለት ጨፍጫፊ ሆኖ ለብዙ ወጣቶች ህልፈት እና ስቃይም ምክንያት ከሆነው የወያኔ መንግስት ይሻል ነበር።

ህውሃት/ወያኔ ከለውጥ ኃይል ወደ ከፊል አንባገነን፣ ከከፊል አንባገኔን ወደ ለየለት አንባገነናዊ ሥርዓት፣ ከዚያም በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፍኖ ወደሚገዛ ጨፍላቂ ኃይል የተቀየረው በሂደት ነው። ከመሰረቱም የዲሞክራሲ ባህል የሌለው ቡድን ስለነበር በሃሳብ ልዩነት በተገፋ ቁጥር የአፈና ማነቆውን እያጠበቀ ሄዶ ነው በስተመጨረሻ የለየለት 100% ጠርናፊ የሆነው። ኦዴፓ መራሹም የለውጥ ኃይል ይህን የቁልቁለት የአፈና መንገድ እንዳይጀምረው ማሳሰብም ሆነ ስጋታችንን መገለጽ ካለብን ጊዜው አሁን ይመስለኛል። የቁልቁለቱ መንገድ ከተጀመረ መመለሻ የለውም።

ድርጅቱን ወይም የለውጥ ኃይሉን ወደዚህ አቅጣጫ ሊገፉት የሚችሉ በርካታ ኃይሎች ዙሪያውን ያሉ ይመስላል። አንዳንድ ምልክቶችም ከወዲሁ እየታዩ መሆኑ የአደባባይ መወያያ ሆኗል። በጥቂቱ፤

+ የድርጅቱ እና አንዳንድ ባለሥልጣናቱ በተደጋጋሚ ወሳኝ በሁኑ አገራዊ ጉዳዮች ላይ የሚሰጧቸው እብሪት የተቀላቀለባቸው መግለጫዎች፤

+ በክልሉ ውስጥ በሚኖሩ የሌሎች ብሔር ተወላጆች ላይ እየደረሰ ያለውን መፈናቀል እና ወከባ ማስቆም አለመቻላቸው፤

+ ቁልፍ በሆኑ የመንግስት የኃላፊነት ቦታዎች ምደባ ላይ ግልጽነት የጎደለው አካሄድ ከወዲሁ መታየቱ እና መድልዎ እየታየ መሆኑ አጋር ድርጅቶች ሳይቀሩ በገደምዳሜ መናገር መጀመራቸው፤

+ አንገብጋቢ የሆኑ እና ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገቡ አገራዊ ጉዳዮችን ችላ ማለት ወይም አቃሎ የማየት ዝንባሌ ተደጋግሞ መስተዋሉ፤

+ በክልሉ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ታጣቂ ኃይሎች የሚፈጽሟቸውን የወንጀል ተግባራት በይፋ ከማጋለጥና አጥፊዎቹንም ለፍርድ ከማቅረብ ይልቅ የመሸፋፈን እና ተጠያቂ እንዳይሆኑ ከለላ የመስጠት፤

+ በተቃራኒው በሰላማዊ መንገድ የድርጅቱን አካሄድ የሚቃወሙ አካላት ላይ ዛቻ መሰንዘር፣ ሃሳባቸውን የመገልጽ እና የመሰብሰብ መብታቸውን እንዳይጠቀሙ እንቅፋት መፍጠር እና በክልሉ የሚንቀሳቀሱ ኃይሎች ችግር ሲፈጥሩ ችላ ብሎ ማየት፣

+ ፍትሕን ለፖለቲካ በቀል ከማዋል ባለፈ የመብት ጥሰት የፈጸሙ እና ተባባሪ በነበሩ ሰዎች ላይ ግልጽ የሆነ አቋም አለመወሰዱ። ከዚያም አልፎ ባለፉት አንድ አመት ውስጥ የተፈጸሙ የመብት ጥሰቶችን ችላ በማለት አገሪቱ በመብት ጥበቃ ወደር ያልተገኘላት አስመስሎ ማቅረብ። ለዚህም በቅርቡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ኢትዮጵያ በመብት ጥሰት ስሟ አልተነሳም ብሎ በቡራዩ እና በሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች የተፈጸሙ የመብት ጥሰቶችን መሸፋፈን፤

+ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች በደህንነት ስጋት እና መኖሪያቸው ፈርሶ በየጫካው እና በየሜዳው ፈሰው ለእርሃብ እና እንግልት በተዳረጉበት፣ በዚህም የተነሳ ከፍተኛ ሰብአዊ ቀውስ በአገሪቱ በርካታ ክፍሎች ተከስተው ዜጎች የመንግስት ያለህ እያሉ በሚማጸኑበት ወቅት ከመንግስት በኩል ተገቢውን ምላሽ በወቅቱ አለማግኝት እና መንግስት በሌሎች ግዙፍ የአገር ሃብት በሚጠይቁ የገጽታ ግንባታ ፕሮጀክቶች ላይ ማተኮሩ፤

እና ሌሎች በርካታና ተመሳሳይ ባህሪ ያላቸው ችግሮችን ለመጥቀስ ይቻላል።

ኦዴፓም ሆነ ሌሎቹ አጋር የለውጥ ኃይሎች የአንድ አመት ቆይታቸውን በመሞጋገስ እና በየአዳራሹ ከመጨፈር ባለፈ የመጡበት መስመር ህውሃት ካሰመረው እና ከመጣበት የቁልቁለት ጉዞ የራቀ መሆኑን አጽንተው ቀጣዩ ጉዟቸውን ከወዲሁ ቢያቀኑም መልካም ነው። እንደ እኔ እምነት አሁንም ይችን አገር ለመታደግ ኦዴፓ እንደ መሪ ድርጅት እና ሌሎቹም እንደ አጋር ድርጅት እድሉ በጃቸው ነው። የአገሪቱን ፖለቲካ በጥንቃቄ ከያዙት እና የህውሃትን ስህተት ላለመድገም ከተጠነቀቁ ያሻግሩናል፤ ህውሃት ያራባውን የስግብግብነት እና የጥበት ልክፍት ተሸክመው ወደፊት ለመቀጠል ካለሙ ግን አዘቀት ውስጥ ተሰንቅረን እንቀራለን።

መልካሙን ሁሉ ለኦዲፓ እና ለለውጥ ኃይሉ እመኛለሁ!

ኦሮሚያ ለሚባል ምናባዊ አገር ምስረታና ኦሮሞ ለሚባል ማንነት ፈጠራ እረፍት የሚያጡ ኦሮሞ ወገኖቼ ጉዳይ

ኦሮሚያ ለሚባል ምናባዊ አገር ምስረታና ኦሮሞ ለሚባል ማንነት ፈጠራ እረፍት የሚያጡ ኦሮሞ ወገኖቼ ጉዳይ በየቀኑ እንደ ኣዲስ ይገርመኛል። የሰው ልጅ አእምሮ ምጥቀት በባህርና በየብስ በብዙ ማይልስ ተራርቆ የሚኖሩ የአለም አገሮችን አቀራርቦ አንድ ድንበር አልባ መንደር ባደረገበትና ሰው እንደልቡ ተዘዋውሮ በመረጠው አገር ሰርቶ የመኖር መብቱ ከምንጊዜውም በላይ እያደገ በመጣበት 21ኛው ክፍለዘመን ላይ እንዲህ አይነት አስተሳሰ ከእርግማን ወይስ ከአእምሮ መላሸቅ እንደሚመጣ አልገባ ብሎኛል።
ከሁሉም የሚደንቀኝ ደግሞ የዚህ ሃሳብ ዋና ኣቀንቃኞች የሥልጣኔ፣ የሰላምና ብልጽግና ማእከል በሆኑት ምእራብ አገሮች የኖሩ፣ የሚኖሩ ወይም ተምረው የተመለሱ መሆናቸው ነው።
ታሪክ እንደሚመሰክረው አንድ ወቅት ከቦረና ወደ አራቱም የአገሪቱ ማእዘን የተንቀሳቀሰው ኦሮሞ በየደረሰበት
እየተጋባ፣ እየተዋለደና በአምቻ ጋብቻ እየተዛመደ የመጣ ሌላው ቀርቶ በጦርነት ወቅትም የማርከውን
በሞጋፋቻና በጉዲፈቻ ባህሉ ጭምር
የራሱ ወገን እያደረገ አሁን ለምናውቃት ኢትዮጵያ የመሰረት ድንጋይ የሆነ ህዝብ ነው።
እና የኦሮሚያና የኦሮሞ ጉዳይ እረፍት
የሚነሳችሁ ወገኖቼ የናንተ ኦሮሚያና ኦሮሞ የምትሉት ያልተከለሰ ያልተበረዘ ማህበረሰብ ከወዴት ይምጣላችሁ? ወይስ political Oromoን ብቻ ኦሮሞ እያላችሁ ከሁሉም ጋር ስትላተሙ ለትኖሩ?

ተወደደም ተጠላ የአገራችን እውነታ አብላጫው ህዝብ እንደ ብራዚል ህዝብ mixed (በደምና በሥጋ የተቀላቀለ ) ህዝብ መሆኑ ነው ።
ህዝባችንን በቋንቋና በሃይማኖት ከፋፍሎ ቅኝ ለመግዛት ሞክረው ያልተሳካላቸው አውሮጳዊያን ጥለውት የሄዱትን የአማራና የኦርቶዶክስ ጥላቻ Internalize አድርጋችሁ ኢትዮጵያዊነት ላይ ክህደት መፈጸም ኦሮሚያ የተባለ ነጻ አገርና ኦሮሞ የተባለ አንድ ወጥ ህዝብ አይፈጥርምና እባካችሁን አትጃጃሉ ።
ሁሌም የተበዳይነት ፣ የተጨቋኝነትና የእንናቃለን ባይነት ስሜት ሰለባ አንሁን !
እራሳችንን የታሪክ ተበዳይ አድርገን ከመቁጠር ነጻ እንወጣ ዘንድም ምናልባት በፕሮፈሰር ጌታቸው ሃይሌ የተተረጎመውን የኣባ ባህሪን ዘናሁ ዘጋላንና ፕሮፌሰር መሃመድ ሃሰን The Oromo and the Christian kingdom of Ethiopia 1300 – 1700 ብለው ያሳተሙትን መጻህፍት ማንበብ ሳይጠቅም አይቀርምና እይት አድርጉት ።
በጎ በጎውን ያሳያችሁ ዘንድ የዘወትር ጸሎቴ ነው።

አበበ ቦጋለ

“ስጋት ቢኖርብኝም ጥበቃ እንዲደረግልኝ አልፈልግም!” ~ እስክንድር ነጋ [ ጋዜጠኛ እና የአዲስ አበባ ባለደራ ምክር ቤት ሰብሳቢ]

ጋዜጠኛ እና የአዲስ አበባ ባለደራ ምክር ቤት ሰብሳቢ የሆነው እስክንድር ነጋ ትላንት በበርካታ ወጣቶች ተከቦ እንደነበር ለቢቢሲ አረጋግጧል።

“ትናንት ቅዳሜ ምሽት 1፡00 አካባቢ፤ ፒያሳ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን አካባቢ ከሚገኘው ቢሯችን ስብሰባ ጨርሰን ስንወጣ ነው የተወሰኑ ወጣቶች ናቸው የከበቡን” ይላል እስክንድር።

እስክንድር ቁጥራቸው ከ10 በላይ ይሆናል ያላቸው ሰብሰብ ያሉ ወጣቶች ከቢሮው ውጪ ደጃፍ ላይ ጠብቀው እርሱንና አራት የባልደራስ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላትን እንደከበቧቸው ያስረዳል።

«አልፈናቸው ስንሄድ በከበባ መልክ ተከትለውናል። እንቅስቃሴያቸው አስጊ ስለነበር ወደ ኋላ ተመልሰን ፖሊስ ይዞ እንዲጠይቅልን ሙከራ አድርገናል። ቢሆንም አንዱ ብቻ ነው በፖሊስ ቁጥጥር ሥራ መዋል የቻለው።»

“የለውጥ አመራሩን ሳይረፍድ ከጥፋት መመለስ ይቻላል” እስክንድር ነጋ
ወጣቶቹ ተቃውሞም ሆነ ጥያቄ አቅርበው ነበር ወይ? ሲጠጓችሁ ዓላማቸው ምንድን ነበር? ተብሎ የተጠየቀው እስክንድር ምንም ያሉን ነገር የለም፤ ነገር ግን በከበባው ውስጥ አስገብተው ተከትለውናል ይላል።

«እኛ ላይ ከሚደርስብን የግድያ ዛቻ አንፃር አስጊ ነበር። እንደዚህ ዓይነት ነገር ተፈጥሮ አያውቅም። ይሄ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው። ብዛት ነበራቸው እና አደጋ ለማድረስ በጣም ቀላል ነበር።»

ወጣቶቹ ጥቃት ሊያደርሱብን ይችሉ ነበር የቦታ መረጣ ጉዳይ እንጂ ብሏል እስክንድር ጨምሮ።

«በእኛ ድምዳሜ ለከበቡን ሰዎች ቦታው አመቺ አልነበረም፤ እኛም ተመለስን። ፊት ለፊታችን ጨለማ ነበር። ከጨለማው ወደኋላ ተመልሰን። እንደ አጋጣሚ አንዲት ፖሊስ ስትመጣ አገኘን። አጠራጣሪ ሁኔታ ስላለ ሰዎቹን እንዲያዙልን እንደምንፈልግ አመለክትን። ተጨማሪ ኃይል ፈልጋ ነበር። በዚያ መሃል ነው እንግዲህ ልጆቹ ተሰባስበው ከአከባቢው የሄዱት።»

ከአንድ ወጣት በቀር የተቀሩት በሚኒባስ እንዳመለጡ የሚናገረው እስክንድር ግለሰቡን ወደ ፖሊስ ጣቢያ ሲወስዱት የፖሊስ አባልና ምክትል ሳጅን ሆኖ ተገኝቷል ይላል።

«ፖሊስ ጣቢያው ቃል ሲሰጥ የደረስንበት ነገር ምክትል ሳጅን መሆኑ ነው። መጀመሪያ ላይ በአካባቢው ምን ሲያደርግ እንደነበር ሲጠየቅ ተማሪ ነኝ ብሎ ነበር። በኋላ ፖሊስ ሆኖ ተገኝቷል። እኛ ቃል ሰጥተን ወደየቤታችን ሄደናል እሱ ፖሊስ ጣቢያ እንዲቆይ ተደርጓል። ዛሬ ጠዋት ተመለሱ ተብለን ስንሄድ ነገ ኑ ተብለናል። ልጁ በእሥር ላይ ይሁን ወይም ለቀውት እንደሆነ የምናውቀው ነገር የለም» ብለል እስክንድር።

ጥበቃ ለእስክንድር. . .?
«በርካታ የግድያ ዛቻ እና ማስፈራሪያ ይደርሰኛል» የሚለው እስክንድር ነጋ ምናልባት ከመንግሥት በኩል ጥበቃ እንዲደረግለት ይፈልግ ይሆን?

«የለም! የለም! እኔ ጥበቃ እንዲደረግልኝም አልፈልግም። የሚያስፈልገው አሁን በተያዘው ልጅ ላይ ጥብቅ የሆነ ምርመራ እንዲደረግ፤ ‘ፌር’ [ፍትሃዊ] የሆነ፤ ሳይንሳዊ የሆነ፤ ሕጉ በሚፈቅደው መሠረት ልጁ እንዲመረመር ነው። በተለይ ከእርሱ ጋር አብረውት የነበሩት ልጆችን አፈላልጎ መያዝና ለምን እንዲህ ዓይነት እንቅስቃሴ እንዳደረጉ መጠየቅ እና ጉዳዩን እስከ ሥር ድረስ ሄዶ መመርመር ነው የሚያስፈልገው። ይሄን ብቻ ነው እኔ ከመንግሥት የምፈልገው።»

እስክንድር ወጣቶቹ ተዘጋጅተውበት እና አጥንተው እንደመጡ ይናገራል። የዕለተ’ለት እንቅሰቃሴያችን ከግምት ውስጥ ገብቷል የሚል ጥርጣሬ እንዳለውም ይናገራል።

«ሁልጊዜ በዚህ ሰዓት ነው የምንጨርሰው። ቅዳሜ ማታ ጨርሰን በእግራችን ነው የምንንቀሳቀሰው። ለምሳሌ እኔ ከጊዮርጊስ ተነስቼ ከአንድ ወይም ከሁለት ሰው ጋር እስከ አራት ኪሎ ደረስ እሄዳለሁ። የተጠና ነው የምለው ለዚህ ነው። ለማናቸውም ዝርዝሩ በፖሊስ የሚረጋገጥ ነገር ነው።»

የተቀናጁ እንቅስቃሴዎች እንዳሉ የአከባቢው ሰው ሲከታተል ነበር የሚለው እስክንድር ዛሬ ጠዋት ምስክሮች ይዘው ወደ ፖሊስ ጣብያ እንደሄዱ ያስረዳል።

«ከእኛ ውጭ የሆኑ፤ በአካባቢው የነበሩ፤ ወጣቶቹ ሲመጡ እና እኛ ላይ ሲያደርጉ የነበረውን የተከታተሉ ሰዎችን ምስክር እንዲሆኑ ይዘን ነው የሄድነው። አስፈላጊ ስለሆነ ማለት ነው። ይሄንን መሠረት አድርጎ ከመንግሥት ትክክለኛ የሆነ ምርመራ አድርጎ እርምጃ እንዲወሰድ ነው። ምክንያቱም ከኃይል እርምጃ ኢትዮጵያ አታተርፍም። በኃይል የሚፈታ የፖለቲካ ጥያቄ የለም።»

እነእስክንድር ምናልባት በቁጥጥር ሥር የዋለው ግለሰብ ቢለቀቅ ክስ የመመሥረት ሃሳብ ይኖራቸው ይሆን?

«እንግዲህ ነገ ነው የምናውቀው። ተለቋል ካሉን ወደ አዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ሄደን የነበረውን ሁኔታ እናስረዳለን። ምስክሮች ይዘን ወደላይ አቤት እንላለን ብለን እናስባለን። በዚያም ደረጃ የማይፈታ ከሆነ ከዚያም ወደላይ ሄደን ማሳሰብ እንፈልጋለን። በመንግሥት ውስጥ ሁለት ሃሳብ አለ ብለን እናስባለን። ብጥብጥ የሚፈልግ ኃይልና ብጥብጥ የማይፈልግ ኃይል አለ። ያንን ግምት ውስጥ በማስገባት እስከ ጥግ ድረስ ሄደን አግባብ ያለው ምርመራ እንዲደረግ ነው የምንፈልገው። ይሄ ልጅ ንፁህ ከሆነ እንዲለቀቅ ነው የምንፈልገው። የግድ መታሠር አለበት የሚል አቋም የለንም።»

ስጋት
እስክንድር፤ ይደርስብኛል ከሚለው ዛቻ እና ማስፈራሪያ አንፃር አደጋ ወይም ጥቃት ይደርስብኛል የሚል ስጋት ይኖርበት ይሆን?

«. . .እኔ የሚጠብቀኝ እግዚአብሔር ነው ብዬ ነው የማስበው። ከዚያ ባሻገር እኔ በግሌ ጥበቃ ይገባኛል ብዬ አላስብም። ጉዳዩ ከእኔ ጋር የተያያዘ አይደለም። የተነሳው ጥያቄ እኔ ኖርኩ አልኖርኩ የሚኖር ነው። በዲሞክራሲያዊ መንገድ እልባት እስካላገኘ ድረስ ማለት ነው። መኖር አልፈልግም ማለት ግን አይደለም» ይላል እስክንድር።

• “ከጄ/ል አሳምነው ጋ በምንም ጉዳይ ያወራሁበት አጋጣሚ የለም” እስክንድር ነጋ

አክሎም «ለሚስቴ መኖር እፈልጋለሁ፤ ለልጄ መኖር እፈልጋለሁ። ኖሬም ደግሞ ለሕብረተሰቡ ገንቢ የሆነ አስተዋፅዖ ማድረግ እፈልጋለሁ። ጥበቃ ግን ይከብደኛል። ኅሊናዬም አይፈቅደውም። ካለው ዛቻ አኳያ፤ በተለይ ደግሞ ትላንት በተግባር ስላየነው አያሳስበኝም ማለት ግን አልችልም፤ ያሳስበኛል» ብሏል።

ቢቢሲ ጉዳዩን በተመለከተ ፖሊስ በኩል ያለውን አስተያየት ለማወቅ ያደረገው ጥረት ሳይሳካ ቀርቷል።

– #BBC

ፌዴራላዊ ስርዐቱ የተተገበረበት መንገድ ዜጎችን ለሰብአዊ መብት ጥሰት አጋልጧል ተባለ

Daniel Bekele

Daniel Bekele, Chief Commissioner, Ethiopian Human Rights Commission.

አዲስ አበባ፤ በኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት ፌዴራላዊ ስርዐቱ የተተገበረበት መንገድ ዜጎችን ለሰብአዊ መብት ተጋላጭ ማድረጉን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽነር ዶክተር ዳንኤል በቀለ ተናገሩ::

ዶክተር ዳንኤል በተለይ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንዳብራሩት፤ ዜጎችን ለሰብአዊ መብት ጥሰት ተጋላጭ ያደረገው ፌዴራላዊ ስርዓቱ የተተገበረበት መንገድና የፌዴራል ስርዓቱ የመንግስት አወቃቀር አንዱ ችግር መሆኑን አሰረድተዋል:: የፖለቲካ ፓርቲ አወቃቀሩም ሌላው ምክንያት ሊሆን እንደሚችልም ጠቁመው በተለየ ማንነት ላይ ትኩረት ተደርጎ መሰራቱም ለግጭት መዳረጉንም ጠቁመዋል፡፡

የፖለቲካ ፓርቲዎች አወቃቀር፣ የመንግስት አወቃቀርና ህገ መንግስታዊ ማዕቀፍ መፈተሽ አለብን፣የፖለቲካ አወቃቀራችን በተፈጥሯቸው የአግላይነት ጸባይ ስላላቸው በውጤታቸው ደግሞ ለግጭት፣ ለብጥብጥና ለእርስ በእርስ አመጽ የሚጋብዙ ሆነው የሚታዩ ስለሚመስሉ ጉዳዩ ሊመረመር፣ ሊጠና እና ሊታይ ይገባዋል ያሉት ኮሚሽነሩ የፖለቲካ መሪዎችም በእዚህ ጉዳይ መወያየት መጀመር የሚገባቸው ይመስለኛል ብለዋል፡፡

በእኔ እምነት ለሰብአዊ መብት ተጋላጭ ያደረገው ራሱ ፌዴራላዊ ስርዓቱ ሳይሆን ፌዴራላዊ ስርዓቱ የተተገበረበት መንገድና የፌዴራል ስርዓቱ የመንግስት አወቃቀር አንዱ ሊሆን ይችላል ያሉት ኮሚሽነሩ፤ የፖለቲካ ፓርቲ አወቃቀሩ፣ በተለየ ማንነት ላይ (የዘር ማንነት፣ የብሄር ብሄረሰብ ማንነት፣ የአካባቢ፣ የሃይማኖት ማንነት ላይ የተመሰረቱ አደረጃጀቶች) የተመሰረተ ፓርቲ ለግጭት ስለሚዳርግ አብዛኞቹ የአፍሪካ አገሮች እንዲህ አይነት የፖለቲካ አደረጃጀት በህጎቻቸው አልፈቀዱም ወይም በግልጽ ከልክለዋል ሲሉም አብራርተዋል፡፡ ‹‹ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲህ አይነት የፖለቲካ አስተዳደር እንዳለን ይታወቃል፡፡ ታሪካዊ መሰረትና ምክንያት አለው›› ሲሉም ጠቁመዋል፡፡

እስካሁን የመጣንበት መንገድ ያስገኘው ውጤትና የፈጠሩት ተግዳሮቶችም አሉት ያሉት ዶክተር ዳንኤል፤ ከተደረሰበት የፖለቲካ ምዕራፍ አንጻር ሂደቱን መርምሮ ችግሮችና ያስገኘውን ውጤት በማስመልከት ግልጽ ውይይት ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ ለሰብአዊ መብት ጥሰት ተጋላጭ ያደረገ የመንግስት አወቃቀር ካለውም አወቃቀሩን መፈተሽ እንደሚያስፈልግም ጠቁመዋል፡፡

‹‹ይህ ማለት ግን የፌዴራላዊ አስተዳደርን ማፍረስ ማለት አይደለም፣ ኢትዮጵያ ካላት ብዝሃነት አንጻር እንደ ኢትዮጵያ በርካታ ብሄር ብሄረሰብ ላላቸው አገራት የፌዴራላዊ አስተዳደር ተገቢ አስተዳደር ነው ሲሉም አብራርተዋል፡፡

ፌዴራላዊ አወቃቀር ህዝቦች፣ ሰዎች፣ ዜጎች በየአካባቢያቸው የራሳቸውን ጉዳይ በእየራሳቸው የሚያስተዳድሩበት መንገድ መሆኑን በመጠቆምም፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ተግባራዊ የሆነው አስተዳደር ግን በተለይ ከብሄር ብሄረሰብ ማንነት ጋር በጣም የተቆራኘ መሆኑን ነው የተናገሩት፡፡ በተለያዩ ክልሎችና በክልሎቹ ውስጥ ባሉ የተለያዩ የማንነት ጥያቄዎች እና የድንበርና የወሰን ልዩነት ላይ እጅግ አወዛጋቢ ክርክር የፈጠረ መሆኑ ለሰብአዊ መብት ጥሰት ተጋላጭ ማድረጉንም አልሸሸጉም፡፡

በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሚታዩ ግጭቶች ከማንነት ጥያቄና ከአካባቢ እና ከድንበር ጉዳይ ጋር ተያይዞ ‹‹ይህ የእኔ አካባቢ ነው፣ ይህ አካባቢ የአንተ አይደለምና ከእዚህ ትወጣለህ፣ የአንተ ድንበር እዛ ጋር ነው›› ከሚሉ ጥያቄዎች ጋር የተያያዘ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

አገራችን ውስጥ በየክልሎቹ ብቻ ሳይሆን በየቀበሌዎቹና በየወረዳዎቹ ደረጃ ያለ የማንነትና የአስተዳደር ወሰን፤ የአስተዳደር ወሰን መሆኑ ቀርቶ ልክ ከአጎራባች አገሮች ጋር እንዳለ አይነት የድንበር ወሰን ጋራ የሚመሳሰል እየሆነ መጥቷል ብለዋል፡፡

አሁን የተፈጠሩት ግጭቶችም በተለያዩ አካባቢዎች ያሉ የአስተዳደር ወሰኖችን እንደ ድንበር በመቁጠር ከሌላ አገር ጋር የተፈጠረ ችግር አይነት አዝማሚያ እንደሚታይበት ኮሚሽነሩ ገልጽው የፌዴራል ስርዓቱን በሚያጠንክር መልኩ የአስተዳደር ወሰኖችና የማንነት ጥያቄዎች በተገቢው መንገድ ተወያይቶ የፖለቲካ መፍትሄ መፈለግ ይሻላል ሲሉ መክረዋል፡፡

አዲስ ዘመን ጥቅምት 22/2012

ዘላለም ግዛው

የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንቷ የት ገባች ??? ምንሊክ ሳልሳዊ

የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንቷ የት ገባች ??? ምንሊክ ሳልሳዊ

ስለፍትሕ ነው እያወራን ያለነው። ስለሕግ የበላይነት ነው እየጮኽን ያለነው። ስለሃገርና ሕዝብ መብት ነው እያወራን ያለነው።ይህ ሁሉ ወንጀል ሲፈፀም ከሕግ አንፃር ያለውን ሁኔታ ተከታትላ ለሕዝብ ማሳወቅ የሚገባትና የሕግ የበላይነት እንዲከበር መታገል የሚገባት ኃላፊነት የተጣለባት የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንቷ የት ገባች ??? ድምጿን ለምን አጠፋች ???

ሕወሓት ላይ ዘራፍ ስትል የነበረች ከደብረዘይት ወደ መቀሌ ተዋጊ ጀቶች ልካ እነጌታቸው አሰፋን ለማስደብደብ የዛተች የአሜሪካንን የሕግ ገጠመኞች ለኢትዮጵያ እጠቀማለሁ ብላ የፎከረችው ወይዘሮ መዓዛ ምን ይዋጣት ምን ይሰልቅጣት ሳይታወቅ ጠፍታለች። ዝምታዋ ወይ የተረኝነቱ አንድ አካል መሆኗን አሊያም ለሕግ የበላነት መከበር ደንታ ቢስ መሆኗን ያሳያል።

ሕግ ሲጣስ፣ ሕግ ሲናድ፣ ሕግ ሲዛባ፣ ሕግ የፖለቲካ መጠቀሚያ ሲሆን፣ ሕግ ንፁሃንን እያሰረ ወንጀለኞችን ሲንከባከብ የሀገሪቱ ትልቁ የሕግ አካል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዝምታ አደገኛ ነው።ይህ ሁሉ መንጋ ድንጋይ፣ አጠናና ስለት ተሸካሚ ጦር በአንድ ግለሰብ መሪነት አገር ሲያምስ፣ ሲገድል፣ ሲያቆስል፣ ንብረት ሲያወድም ዝምታን መምረጧ ኋላፊነቷን በአግባቡ ላለመወጣት ዘገምተኝነት ማሳየቷ ከተጠያቂነት አያድናትም። #MinilikSalsawi ምንሊክ ሳልሳዊ

Image may contain: 1 person, smiling

መንግስት የዜጐችን ደህንነት የማስጠበቅ ኃላፊነቱን ይወጣ!! የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ (ኢሰመጉ)

(ጥቅምት 17 ቀን 2012 ዓ/ም)

የኢፌዲሪ ሕገ-መንግሥት ክፍል አንድ አንቀፅ 14 ማንኛውም ሰው ሰብዓዊ በመሆኑ የማይደፈርና የማይገሠሥ፣ በሕይወት የመኖር፣ የአካል ደኅንነትና የነጻነት መብት እንዳለው ይደነግጋል፡፡ ማንኛውም ሰው በሕይወት የመኖር መብት እንዳለውና በሕግ በተደነገገ ከባድ የወንጀል ቅጣት ካልሆነ በስተቀር ሕይወቱን እንደማያጣ በሕገ መንግሥቱ አንቀፅ 15 ላይ ሠፍሯል፡፡ የሕገ መንግሥቱ አንቀፅ 32(1) ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ወይም በሕጋዊ መንገድ ሐገሪቱ ውስጥ የሚገኝ የውጭ ዜጋ በመረጠው የሐገሪቱ አካባቢ የመዘዋወርና የመኖሪያ ቦታ የመመሥረት መብት እንዳለው በግልጽ አስቀምጧል፡፡ እንደዚሁም፣ አንቀፅ 40 (1) ለማንኛውም ኢትዮጵያዊ ዜጋ የግል ንብረት ባለቤትነት መብት አጎናጽፏል፡፡

ኢትዮጵያ የተቀበለችውና የሕጓ አካል ያደረገችው የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ዓለም ዓቀፍ ቃል ኪዳን በአንቀፅ 2 እያንዳንዱ ይህንን ቃልኪዳን የተቀበለ አገር በግዛቱ ውስጥ ለሚኖርና በሥሩ ለሚተዳደር ማንኛውም ሰው በዘር፣ በቀለም፣ በፆታ፣ በቋንቋ፣ በሃይማኖት፣ በፖለቲካ ወይም ሌላ አመለካከት፣ በብሔራዊም ሆነ ማኅበራዊ አመጣጡ፣ በሀብት፣ በውልደት ወይም በሌላ መለኪያ ምንም ልዩነት ሳያደርግ በዚህ ሕግ ዕውቅና ያገኙትን መብቶችና ነፃነቶች እንዲያስከብር ግዴታ ይጥላል፡፡ በተመሳሳይ፣ ኢትዮጵያ ፈርማ የተቀበለችው የአፍሪካ የግለሰቦችና የሕዝቦች መብቶች ቻርተር አንቀፅ 1 በሠነዱ ውስጥ የተጠቀሱትን መብቶች የማክበር፣ የማስከበርና መብቶቹ የሚከበሩባቸውን ሁኔታዎች የማሟላት ግዴታ፣ በፈራሚ ሐገራት ላይ ይጥላል፡፡

እነዚህን የዜጎችን የአካል ደኅንነትና ነጻነት እንዲሁም የንብረት ባለቤትነት መብቶች የመጠበቅ ኃላፊነት በግንባር ቀደምትነት የተጣለበት መንግሥት ነው፡፡ ይሁንና እነዚህ ሐገራዊ፣ አሕጉራዊና የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌዎች ባለመከበራቸው እና መንግስት የማስከበር ኃላፊነቱን ባለመወጣቱ ከዚህ በታች የተዘረዘሩት የመብት ጥሰቶች ተፈጽመዋል፡፡

~ ከጥቅምት አንድ ቀን 2012ዓ.ም ከሌሊቱ ዘጠኝ ሰዓት ጀምሮ እስከ ጥቅምት ሁለት ቀን 2012ዓ.ም ከቀኑ 10 ሰዓት ድረስ አፋር ክልል አፋምቦ ወረዳ ‹‹ሰንጋ›› በሚባል መንደር ከሌላ አካባቢ መምጣታቸው በተገለጸ ታጣቂዎች በተፈጸመ ጥቃት የ17 ሰዎች ሕይወት ጠፍቷል፣ በርካታ ሰዎች የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል፤

~ ጥቅምት 11 ቀን 2012ዓ.ም ሌሊት አክቲቪስት ጃዋር መሐመድ በማኅበራዊ ድረ ገጽ ‹‹ጥበቃ እንዲያደርጉልኝ የተመደቡልኝ የጸጥታ ኃይሎች ሊነሱብኝ ነው፡፡ ቤቴም በጸጥታ ኃይሎች ተከብቧል›› የሚል መልዕክት በማስተላለፋቸው መልዕክቱን የተቀበሉ በመቶዎች የሚቆጠሩ ወጣቶች ሌሊቱን ወደ ግለሰቡ መኖሪያ ቤት አምርተዋል፤ በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ አካባቢዎችም የአክቲቪስቱ ደጋፊዎችና ተከታዮች በመሰባሰብ መንገድ ዘግተው የተቃውሞ ሰልፍ አድርገዋል፡፡ ይህ የተቃውሞ ሠልፍ ወደ ግጭት አምርቶ የበርካታ ዜጐች ሕይወት ጠፍቷል፣ በብዙዎች ላይ የአካል ጉዳት ደርሷል፣ ግምቱ ያልታወቀ ከፍተኛ ንብረት ወድሟል፣ የዜጐች ያለሥጋት የመንቀሳቀስ መብታቸው ተገድቧል፣ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ ባንኮች፣ የንግድ ድርጅቶችና ት/ቤቶች ተዘግተዋል፡፡

ይህ አስቸኳይ ጋዜጣዊ መግለጫ ይፋ እስከሚሆንበት ሰዓት ድረስ ኢሰመጉ በተለያዩ አካባቢዎች ከሚገኙ ምንጮቹ በሰበሰበው መረጃ መሠረት ግለሰቡ ያስተላለፉትን መልዕክት ተከትሎ በተነሣው ተቃውሞና በተፈጸመው ብሔርና ሃማኖት ተኮር ጥቃት በምሥራቅ ሐረርጌ ዞን፣ በሐረር ከተማ፣ በአወዳይ ከተማ፣ በድሬዳዋ ከተማ፣ በአዳማ፣ በባሌ ዞን ዶዶላ ወረዳ፣ በአምቦ ከተማ፣ በአርሲ ዞን ኮፈሌ ወረዳ፣ በዝዋይ ከተማ፣ አርሲ ነጌሌ፣ በባሌሮቤ በድምሩ ቁጥራቸው ከ67 በላይ ሰዎች መገደላቸውን፣ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች አካላዊ ጉዳት ደርሶባቸዋል፣ በርካታ የንግድ ድርጅቶች መቃጠላቸውን፣ በብዙ ከተሞች የንግድ እንቅስቃሴና ተቋሞች ተዘግተው መዋላቸውን አረጋግጠናል፡፡ ከሟቾቹ ውስጥ በርካቶቹ ጭካኔ በተሞላበት ሁኔታ በድንጋይ እና በዱላ ተወግረው መገደላቸው ሁኔታውን ይበልጥ አሰቃቂ አድርጐታል።

ኢሰመጉ የቆመው ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መዳበር፣ ለሕግ የበላይነት መስፈንና ለሰብዓዊ መብቶች መከበር ነው! EHRCO stands for Democracy, the rule of Law and the respect of Human Rights. በተጠቀሱት ሥፍራዎች እና በሐገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በተደጋጋሚ ከሚፈጠሩ ሁከቶች ጋር ተያይዞ ብሔርን እና እምነትን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶችና ግጭቶች በዜጎች ላይ ሲፈጸሙ ተስተውለዋል። ይሁን እንጂ ከዚህ በፊት በተደጋጋሚ እንደተስተዋለው ሁሉ የዞንና የወረዳ አስተዳደር አመራሮች እንዲሁም የጸጥታ አካላት በሕግ የተጣለባቸውን ለዜጎች ጥበቃ የማድረግ ግዴታ ባለመወጣታቸውና በፍጥነት ድርጊቶቹን ባለመቆጣጠራቸው ችግሩ በከፍተኛ መጠን ተባብሶ ወደ ከፍተኛ ቀውስ እያመራ ይገኛል። መንግሥት በተለይም ባለፉት ሁለት ዓመታት በተለያዩ አካባቢዎች መሠል ድርጊቶች ሲፈጸሙ በዝምታ መመልከቱ፣ የድርጊቶቹን አነሳሾች እና ፈጻሚዎች በሕግ ፊት ተጠያቂ ባለማድረጉ በመቶዎች የሚቆጠሩ ንጹሃን ክቡር ሕይወታቸውን አጥተዋል፣ አካላቸው ጐድሏል፣ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ከመኖሪያ ቀዬአቸው ተሰድደዋል፣ ዜጐች ለማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ተዳርገዋል፣ የሕዝቡ ተቻችሎ እና ተከባብሮ የመኖር ዕሤቶችን እንዲሸረሸር አድርጓል።

ይህ መግለጫ በሚጠናቀርበት ወቅትም ዜጎችን ብሔርና ሃይማኖትን መሠረት ላደረጉ ጥቃቶችና ግጭቶች ዒላማ የሚያደርጉ መልዕክቶች በማኅበራዊ ድረ ገጾች በስፋት እየተሰራጩ ይገኛሉ።

በተጨማሪም፣ በኦሮሚያ ክልል በባሌ ሮቤ እና በዶዶላ ወረዳዎች ለኢሰመጉ በስልክ በደረሰው መረጃ መሠረት አሁንም ተጨማሪ ጥቃት ለመፈጸም በጥቃት አድራሾቹ እየተዛተባቸው እንደሚገኝ፤ በዚህም ምክንያት ለሕይወታቸው በመሥጋት ከአራት ሺ በላይ የሚሆኑ ሰዎች በሁለት አብያተ ክርስትያናት ተጠልለው እንደሚገኙና በርካቶችም በቤታቸው ውስጥ በፍርኀትና በጭንቀት የድረሱልን ጥሪ እያቀረቡ ይገኛሉ፡፡
እንዲሁም፣ በድሬዳዋ ከተማ በተለያዩ አካባቢዎች ሃይማኖትንና ብሄርን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶች በስፋት እየተፈጸሙ ይገኛሉ፡፡ ይህ መግለጫ በሚጠናቀርበት ወቅትም የከተማዋ ነዋሪዎች በከፍተኛ ሥጋትና ፍርኀት ውስጥ እንደሚገኙ፣ ከሌላ የሐገሪቱ አካባቢዎች የመጡና ጥቃቱን የሚፈጽሙ ወጣቶች የጦር መሣሪያዎች እና ድምፅ አልባ የስለት መሣሪያዎች የታጠቁ እንደሆኑ ከአካባቢው ለኢሰመጉ እየደረሱ ያሉ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ የሐገር መከላከያ ሠራዊትም ግጭቱን ለመቆጣጠር ጥረት በማድረግ ላይ እንደሚገኝ ምንጮቻችን አረጋግጠዋል፡፡

መንግሥት ለእነዚህም ሆነ ለተመሳሳይ ድርጊቶች ሕጋዊ እና የማያወላውል እርምጃ በመውሰድ የዜጐችን በሕይወት የመኖር፣ አካላዊ ደኅንነት እና በፈለጉት የሐገሪቱ አካባቢዎች በነጻነት ተንቀሳቅሰው የመኖር መብታቸውን እንዲያከብር እና እንዲያስከብር ኢሰመጉ በድጋሚ ያሳስባል።

በተጨማሪም መንግሥት፡-
~በተለያዩ የብዙኃን መገናኛ ዘዴዎች አማካይነት ዜጎችን ለጥቃትና ለግጭት የሚያጋልጡ ቀስቃሽ መልዕክቶችን የሚያሠራጩ አካላትን እንዲቆጣጠር፣
~ተገቢውን ማጣራት በማድረግ ድርጊቱን ባነሣሡና የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶችን በፈጸሙ ግለሰቦችና አካላት እንዲሁም ይህንን የመከላከልና የመቆጣጠር በሕግ የተጣለ
ባቸውን ኃላፊነት ሳይወጡ በቀሩ የፀጥታ ኃይሎች እና የመንግሥት ኃላፊዎች ላይ ሕጋዊ እርምጃ እንዲወስድ፣
~ጉዳዩ ተጣርቶ የአካል ጉዳት ለደረሰባቸው፣ ለሟች ቤተሰቦች፣ ቤት ንብረት ለወደመባቸውና ለተፈናቀሉ ዜጎች ካሣ እንዲከፍል እንዲሁም ሰብዓዊ ድጋፍና ርዳታ የሚያገኙበትን መንገድ እንዲያመቻች፣
~በክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች በስፋት የሚስተዋለው የአክራሪ ብሔርተኛነት አስተሳሰብን መሠረት ያደረጉ ኢ-መደበኛ ቡድኖች እያደረሱ ያሉትን ጥፋት ለማስቆም የሚያስችል አስቸኳይ መፍትሄ በመስጠት ሕጋዊ እርምጃ እንዲወሰድ፣
~በፌዴራል መንግሥት አካላትና በክልል መስተዳድሮች መካከል ያለው ግንኙነት ሕግን መሠረት ያደረገና የሕዝቦችን የጋራ ተጠቃሚነት ያስከበረ መሆኑን እንዲያረጋግጥ፣
~በየደረጃው የሚገኙ የመንግሥት አካላት ፖሊቲካዊ ቁርጠኛነቱ ኖሯቸው የዜጎችን ሕይወትና የአገርን ሕልውና አደጋ ላይ የሚጋርጡ የጅምላ የወንጀል ድርጊቶችን እንዲያስቆሙ፣
~ግለሰቦችም በተለያዩ ሚዲያ እየተሠራጩ የሚገኙትንና ሕዝብን ለግጭትና ለጥቃት የሚያነሣሡ ንግግሮችና የሐሰተኛ መረጃ ከመፈብረክና ሳያመዛዝኑ ከማሠራጨት በመቆጠብ የበኩላቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ፣ በየአካባቢው የሚፈጸሙ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶችን እንዲቃወሙና ድርጊቶቹን እንዲከላከሉ ኢሰመጉ ጥሪውን ያቀርባል፡፡

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ /ኢሰመጉ/ ለሕግ ልዕልና፣ ለዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታና ለሰብዓዊ መብቶች መከበር የቆመ ድርጅት ነው፡፡
ሁሉም መብቶች ለሁሉም!!

ኢሰመጉ በአፍሪካ የሕዝቦችና የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን የታዛቢነት ቦታ አለው፤ የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ፌዴሬሽን (FIDH) አባል፣ የዓለም ዓቀፍ ጸረ-ሥቃይ ድርጅት (OMCT) አባልና የምሥራቅና የአፍሪካ ቀንድ የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾች ጥበቃ ኅብረት (DefendDefenders) መሥራች አባልም ነው፡፡