የባለአደራ ምክር ቤት አባላት ከ ‘መፈንቅለ መንግሥቱ’ ጋር በተያያዘ በሽብር ፍርድ ቤት ቀረቡ

ጋዜጠኛና የሰብዓዊ መብት ተሟጋች እስክንድር ነጋ ጋዜጣዊ መግለጫ ሲሰጥ

የፌደራል ፖሊስ ከአዲስ አበባ ፖሊስ ጋር በመሆን በአንድ መዝገብ ስድስት ተጠርጣሪዎችን ዛሬ ፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ አንደኛ የወንጀል ችሎት አቅርበዋል።

ግለሰቦቹ አንደኛ ተጠርጣሪ በሪሁን አዳነ፣ መርከቡ ኃይሌ፣ ስንታየሁ ቸኮል፣ ጌዴዮን ወንድወሰን፣ ማስተዋል አረጋና አቶ ሐየሎም ብርሃኔ ናቸው። ፖሊስ ግለሰቦቹ ፍርድ ቤት የቀረቡት በአማራ ክልል ተፈፀመ በተባለው “መፈንቅለ መንግሥት” እና አዲስ በአበባው ግድያ “እጃቸው አለበት፤ በተለያየ ደረጃ ተሳትፎ ያላቸው ስለሆነ ጠርጥሬያቸዋለሁ ፤ ህገ መንግሥታዊ ስርዓት ለመናድ፤ በሽብር ተግባር ተሳትፈዋል።” በማለቱ እንደሆነ የአራቱ ጠበቃ የሆነው አቶ ሄኖክ አክሊሉ ለቢቢሲ ገልጿል።

አቶ መርከቡ ኃይሌና አቶ ስንታየሁ ቸኮል የምክርቤቱ አመራሮች ሲሆኑ አቶ ጌዴዮን ወንድወሰንም የባላደራ ምክር ቤቱ አባል ነው። አቶ በሪሁን አዳነ ጋዜጠኛ ሲሆን፤ አቶ ማስተዋል አረጋ የኮሌጅ መምህር መሆናቸውን የገለፀው አቶ ሄኖክ አቶ ኃየሎም ብርሃኔ ስለተባሉት ተጠርጣሪ ዝርዝር መረጃ እንደሌለው አመልክቷል።

• የአዲስ አበባ ባለአደራ ምክርቤት መግለጫ ምን ይላል?

• “የዲሞክራሲ ጥማት የማይቀለበስበት ደረጃ ላይ መድረሱን ተመልክቻለሁ”

ጠበቃው እንዳሉት ግለሰቦቹ በፀረ ሽብር አዋጅ መሰረት 28 ቀን የጊዜ ቀጠሮ ተጠይቆባቸዋል። ተጠርጣሪዎቹ አደረጉት የተባለው ነገር ተለይቶ በዝርዝር የቀረበ ሳይሆን በደፈናው “በመፈንቅለ መንግሥቱ” ጠርጥሬያቸዋለሁ የሚልና ዝርዝር ያልቀረበበት ነው።

ስለዚህም በመፈንቅለ መንግሰቱ ይህን ይህን አድርገዋል ብለህ በሁሉም ተከሳሾች ላይ አቅርብ፣ በሁለተኛ ደረጃ በዛሬው እለት ፖሊስ የምርመራ መዝገቡን ይዞ ስላልመጣ እነሱ ደግሞ የተከበረው ፍርድ ቤት መዝገቡን ይይልን እነዚህን ሰዎች ለመያዝ ምንም የሚያስጠረጥር ምክንያት የለም ሲሉ ለፍርድ ቤቱ ማስረዳታቸውን ጠበቃ ሔኖክ ተናግረዋል።

ክስ እንዳልተመሰረተ የሚናገረው አቶ ሔኖክ ማስረጃ ሊያሸሹ ስለሚችሉ በማረፊያ ቤት ቆይተው ምርመራው እንዲቀጥል ፖሊስ በጠየቀው መሰረት ፍርድ ቤቱም የግራ ቀኙን ክርክር ከሰማ በኋላ ፖሊስ አደረጉት የሚባለውን ነገር በዝርዝር ለየብቻ እንዲያቀርብ፤ የምርመራ መዝገብ ይዞ ባለመቅረቡም፤ የምርመራ መዝገብ ይዞ እንዲቀርብ በማለት ለሐምሌ 17 ቀጠሮ ትእዛዝ መስጠቱንም ያስረዳል።

• “የኢህአፓና መኢሶን ነገር አማራ ክልል ላይ ሊከሰት ይችላል ብዬ ነበር”

ግለሰቦቹ በትክክል መቼ እንደተያዙ ዝርዝሩን ባያውቅም ጥቃቱ ተፈፀመ ከተባለበት ከሰኔ 15 ቀን 2011ዓ.ም በኋላ ሰኔ 17 እና 18 መያዛቸውን ይናገራል።

ተጠርጣሪዎቹ ባህርዳር ሄደው ነበር ? ለሚለው ጥያቄ በሁሉም እርግጠኛ ባይሆንም ከሳምንት በፊት አቶ ስንታየሁ ወደ ባህር ዳር እንደሄደ፤ ባህርዳር የሄዱት በመኪና ባላደራ ምክርቤቱ እሁድ እለት ሊያደርገው ለነበረው ህዝባዊ ስብሰባ እንደነበር ሄኖክ አስረድቷል።

“ፖሊስ እንዳለው በስልክ እየተነጋገሩ ከጉዳዩ ጋር የተገናኘ ነገር ይፈፅሙ ነበር የሚል ጉዳይ አንስቷል። ፖሊስም ሁሉም ባህርዳር ሄደዋል ሳይሆን የሚለው ባህርዳር የሄዱትና ያልሄዱት ተሳትፎ አድርገዋል የሚል ነው” ሲልም አክሏል።

ስድስተኛው ተጠርጣሪ ጄኔራል ሰዓረና ሜጀር ጄኔራል ገዛኢ አበራ ሽኝት ፕሮግራም ላይ “የሃገሪቱ ከፍተኛ ባለስልጣናት ባሉበት ጥቃት ለማድረስ መሳሪያ ይዘው ተገኝተዋል” በሚል ሲያዝ ግለሰቡም የጥበቃ ስራ ስለሚሰራ መሳሪያ እንደያዘ ለፍርድ ቤቱ ማስረዳቱን አቶ ሔኖክ ይናገራል።

ጀነራል አሳምነው ጽጌ ይዞት የተቀበረው እውነት ምን ይሆን? – ተመስገን አስጨነቅ

ሀዘን በሀዘን ላይ እየተደረበ ተስፋችን እንዲሟጠጥ ቢያደርም መቆዘም እና ማልቀስ እንዲሁም ሙሾ ማውጣት መፍትሄ ሊሆን አይችልም። እውነታውን እና ሃቅን መጋፈጥ እና ቀጣይ አቅጣጫዎችን መንደፍ ተገቢ ነው። በተውኔት የተሞላው ትዕይን እውነት እነ ንጉሱ ጥላሁን እንዳሉት ከባህርዳር እስከ አዲስ አባባ የተዘረጋ የመፈንቅለ መንግስት መረብ ነው ወይስ ባህር ዳር ተጀምሮ ባህር ዳር የተጠናቀቀ ትዕይንት ነው የሚለውን ጉዳይ መርምሮ ህዝብ እውነታውን እንዲያውቅ ማድረግ የሁሉም ዜጋ ሃላፊነት ነው።

******

እንዳለመታደል ሆኖ አዴፓ ዛሬም አንድ እንኳ እውነትን ተጋፍጦ የሚመጣን መከራ መቀበል የሚፈልግ አመራር እንደሌለው አረጋግጦልናል። ሌላውን ሁሉ ተተነው ከጥቃት ተረፍን ብለው አማራ ቴሌቪዥን ላይ ማብራሪያ የሰጡ ሶስት ሰዎችን ስናይ ምን ያህል የተደበቀ እውነት እንዳለ ያስገነዝበናል። ሰባት ሁነው እንደተሰበሰቡ እና ከውጭ በኤፍ ኤስ አር የተጫነ ሰራዊት መጥቶ ጥቃት እንዳደረሰባቸው እና እነሱ በመስኮት ለማምለጥ ሲሯሯጡ አሳምነው ግራውንድ ላይ ሆኖ መመሪያ ሲሰጥ እንደነበር አብራርተዋል። የተሰበሰቡት ሰባት ሁነው ከነበር አሳምነው ከየት ብቅ ብሎ ነው ግራውንድ ላይ የግደሉ መመሪያ የሚሰጠው? እንደገናስ ሰባት የካቢኔ አባላትን ለመግደል አንድ ኤፍ ኤስ አር ልዩ ሃይል መጫኑ ምኑ ላይ ነው አስፈላጊነቱ? በስንት ወታደራ ዶክትሪን ሲታነጽ የኖረ ጀነራል ሲቪል ካቢኔ አባላትን በዚያው ላይ ወንድሞቹን በዚህ አይነት ሁኔታ የሚያስገድልበት ምክንያት በጭራሽ ሊታየኝ አልቻለም። እነሱን በመግደል የፖለቲካ ኪሳራ እንጂ ትርፍ እንደሌለው እንኳን አንድ ጀነራል አንድ ተራ ዜጋ ጠንቅቆ ይረዳል።
******

የሆነ ሆኖ የተከሰተው እና ጀነራሉ የልዩ ሃይል አባላትን ወደ ጥቃት እንዲዛወሩ ለምን አደረገ ብለን ስንጠይቅ ከወር ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ ራሱ አሳምነው ጽጌ የተናገረው ማስጠንቀቂያ ማሳያ ነው። የክልሉ መንግስት ሳያውቅ በሶስት አቅጣጫ በጎንደር፣ አጣየ እና በጃዊ የተፈጠሩ ጥቃቶችን የሚያጣራ ግብረ ሃይል ከፌደራል እንደመጣ ሲገልጽ ነበር። አያይዞም በቀጣይም የታቀዱ ብዙ ነገሮች እንዳሉ እና የክልሉ መንግስት ሳያውቅ ከፌደራል መንግስት የሚደረግ ሃይል የማስገባት እንቅስቃሴ ትልቅ ዋጋ ያስከፍለናል ሊታሰብበት ይገባል ሲል እንደነበር ሰምተነዋል። ከዚህም በፌደራል ደረጃ የታቀደ የጸጥታ ጉዳይን ኢላማ ያደረገ ጣልቃ ገብነት እንደነበር መገንዘብ ይቻላል።

******

ጀነራሉን ለማንሳት በሚደረገው ሴራ ውስጥ ጀነራል ሰአረ ጡረታ የወጣው አማካሪያቸውን ይዘው ልዩ ሃይልን ትጥቅ ለማስፈታት ባህርዳር ላይ ምክክር ሲያደርጉ ነበር የሚለው በቅርብ እየወጣ ያለው መረጃ ውሃ የሚያነሳ ነው። ይህን የሚያረጋግጠው አንደኛ ጀነራል ሰዓረ ተገደሉ የተባለበት የተውሸከሸከ ማብራሪያ ዋና ማሳያ ነው። በአንድ በኩል ቀጣይ የመረጃ ጥያቄ እንዳይመጣ የገደላቸው ሰው ራሱን አጠፋ ቀጥሎም “በኮማ” ላይ ነው የሚል የተምታታ መግለጫ ሰጡን። ሁለተኛው ጀነራል ሰዓረ የተገደሉት ባህርዳር በተከሰተው ችግር ስምሪት ለማድረግ እየሰሩ ባለበት ወቅት ነው ካሉ በኋላ ቤታቸው ውስጥ ነው የተገደሉት የሚል የተምታታ መግለጨ ሰጡን። ይህም ለመሆኑ ወታደራዊ መመሪያ እና ስምሪት የሚሰጠው ሊጠይቃቸው ከመጣ ጡረተኛ ጀነራል ጋር ቡና እየተጠጡ እየተቃለዱ ነው ወይ? የሚል ጥያቄ እንድናነሳ ያስገድደናል።
******

ጀነራል አሳምነው ጽጌ ልዩ ሃይሉን ለስምሪት እና ለጥቃት እንዲሰማራ ያደረገው ምንም እንኳ የቸኮለ እና ስሜት የተጫነው ውሳኔ ቢሆንም የመከላከያ ሃይሉ ትጥቅ ለማስፈታት ሲያደርግ የነበረውን እንቅስቃሴ ለመመከት እንደነበር መገንዘብ አያዳግትም። በዚህም ሂደት እና ግብግብ ወደ ስብሰባ አዳራሹ በር ላይ ያሉ ጥበቆችን በጣጥሰው የገቡ የልዩ ሃይል አባላት በሁለቱ ጀነራሎች እና በነ ዶክተር አምባቸው ላይ ጥቃት አደረሱ የሚለው የተሻለው ምልከታ ነው። አሳምነው ጽጌ በመከላከያ ከበባ ወዲያው ተገድሎ ይሁን አይሆን እንዴት እናውቃለን? በአንድ ወገን የሚለቀቅ መረጃን ተግተን እንዴትስ አምነን እንቀበለው? አሳምነው ጽጌ ከሁለት ቀን በኋላ ተገደለ የሚለውንስ እንዴት እንመነው?

ከዚህ በኋላ እንግዲህ መፈንቅለ መንግስት የምትል ድራማ በንጉሱ በኩል እንድትወጣ ተደርጎ ከዚያም የሰዓረ አገዳደል ከአዲስ አበባ መሆኑ እና ከባህርዳሩ ጋር ትስስር እንዳለው የተነገረበት መንገድ ጠቅላይ ሚንስትሩ መግለጨ እስከሰጡበት ሌሎቱ ስድስ ሰዓት ድረስ የተሰራች ድራማ ናት ብሎ መገመት አያዳከትም።

******

የሆንነውን ሁሉ ሁነናል። ያው የተጎዳው ራሱን ለማስከበር ደፋ ቀና የሚለው የአማራ ህዝብ ነው። በዚህ ሂደት ግን አሁንም አጋጣሚውን ተጠቅሞ የአማራ ልሂቃንን< ተቋሪዎችን እና ወጣቶችን ለማሰር እና ወደ እስር ለማጋዝ የሚደረገው እሩጫ የበለጠ ዋጋ የሚያስከፍል ነው። ኮለኔል አለበል እና ጀነራል ተፈራ ማሞ የታሰሩበት ምከንያትስ ምን ታስቦ ነው? ሌሎችንም ከአዲስ አባባ እና ከባህርዳር እየመነጠሩ ለማስር እና ለማፈን የሚደረገው ሩጫ ተገቢ አይደለም። የሆነው ሁሉ የሆነው ባልበሰለ የፖለቲካ አካሄድ እና “ኮንስፓይሬሲ” ነው። አሁም ተጨማሪ ጠባሳ የሚጥል አካሄድ መከተሉ ኪሳራ እንጂ ጥቅም አይኖረውም።

******
መታወቅ ያለበት ከዚህ በኋላ በምንም ታምር አማራው በሚግዚት አስተዳደር ሊመራ እንደማይችል ነው። ክልሉን በፌደራል ሰራዊት ለማስተደራደር መሞከር እና ሞግዚት ለማስቀመጥ የሚደረገው አካሄድ እያንዳንዱ የሀገራችን “ኮርነር” የጦርነት ቀጠና እንዲሆን እድል ከመፍጠር የዘለለ ጥቅም አይኖረውም። ክልሉ እራሱን በራሱ ሰላሙን እንዲያረጋጋ እድሉን ሰጥቶ ውይይቶችን እና አጠቃላይ ሀገራቀፍ የሰላም እና የጸጥታ አወቃቀሩ ምን አይነት መልክ ይኑረው የሚለው ጉዳይ ላይ ተወያይቶ ሀገራቀፍ መፍትሄ መሻት የተሻለው አማራጭ ነው።
******
አዴፓ ግን አሁንም እውነታውን ለህዝብ ለማሳወቅ አረፈደበትም። አሳምነው ጽጌ ይዞት የተቀበረው እውነት ጊዜ እንደሚያወጣው ጥርጥር የለውም። በደፈናው የአማራ አመራሮች እርስ በእርሳቸው ተጫረሱ የሚል አጠቃላይ ገጽታ እንዲኖር የሚደረገው የሚዲያ ፕሮፖጋንዳ እና ዘመቻ እጅግ አሳፋሪ እና ሊታሰብበት የሚገባ ነው። በአንድ ወገን ብቻ በሚደረግ የመረጃ ፍሰት እና ፕሮፖጋንዳ የአማራን ስነልቦና ለመስበር የሚደረገው አካሄድ ፈጽሞ ሊወገዝ የሚገባው ጉዳይ ነው።

ሁሉም የማያልቅበት ፈጣሪ ሁሉንም መልክ ያስዝ!

ህይወታቸው ያለፉ ወንድሞቻችነን ነፍስ ይማር!

ለሁላችንም መጽናናቱን ፈጣሪ ይስጠን!

ተመስገን አስጨነቅ

አያያዙን አይተህ ሽልጦውን … የለውጥ ኃይሉ መዝረክረክ አገሪቱን ብዙ ዋጋ እያስከፈላት ነው፤ – ያሬድ ሃይለማሪያም

የሰሞኑ ግርግር፣ አሳዛኝ እና ልብ የሚያደሙ ክስተቶች እና የመፈንቅለ ትርምስ ዜናዎች ከብዙ አቅጣጫ እጅግ ተቃራኒ የሆኑ ብዙ አወዛጋቢ መረጃዎች እየወጡ ስለሆነ ለጊዜው በዝርዝር ጉዳይ ላይ አስተያየት ከመስጠት እቆጠባለሁ። እጄ ላይ ያሉት መረጃዎች ድምዳሜ እንድይዝ ሊያደርጉኝ የሚችሉ ቢሆንም መረጃዎቹ በሚመለከታቸው አካላት በኩል በዝርዝር ተገልጸው እስኪወጡ ድረስ ሕዝብ ሊያደናግሩ ስለሚችሉ አንዳንድ ጠቋሚ አሳቦችን ለጊዜው ወደጎን ብዮ በጥቅል አገሪቱ አሁን የምትገኝበት እና አሁን ላለችበት ችግር መንሰዔ ይሆናሉ ያልኳቸውን ሃሳቦች ለውይይት ይረዳ ዘንድ በዝርዝር ለማንሳት እሞክራለሁ።

ባለፉት አሥርት አመታት ሕዝብን እርስ በራሱ ለመከፋፈል ከተከናወኑት በርካታ ነገሮች ባልተናነሰ ሁኔታ የኢትዮጵያ ሕዝብ እንዲከፋፈል እና አንዱ በሌላው ላይ እምነት እንዲያጣ በዚህ አጭር የለውጥ ጊዜም ውስጥ ብዙ ሥራዎች ተሰርተዋል። ሚዲያዎች፣ በሁሉም ክልል የሚገኙ አክራሪ ብሔረተኞች፣ የብሔር መብት አቀንቃኞች፣ የፌደራል እና የክልል መንግስታት፤ እንዲሁም የማህበረ ድህረ ገጾች ለዚህ ችግር የየራሳቸውን አስተዋጽዖ አበርክተዋል።

ከሁሉ የከፋው እና አሁን ወዳለንበት ትርምስ ውስጥ ከከተቱን ምክንያቶች ዋና ዋናዎቹን ለመጥቀስ ያህል፤

+ የፌደራል መንግስት በሕገ መንግስቱ የተጣለበትን የሕግ የበላይነትን የማስከበር ተግባሩን ችላ ብሎት መቆየቱ እና በአግባቡ ሳይወጣ መቅረቱ፤

+ የፌደራል መንግስቱ ከክልሎች ጋር ያለውን ግንኙነት በአግባቡ አለመያዙ እና ክልሎች እራሳቸውን የቻሉ አገር እስኪመስሉ ድረስ እጅግ የተለጠጠ እና ልጓም ያልተበጀለት ሥልጣን እና ጉልበታቸውን እንዲያፈረጥሙ መልቀቁ፤

+ እያንዳንዱ ክልል የራሱ ልዩ ኃይል እና ሚልሺያ እያሰለጠነ በትጥቅ እና ውትድርና በሰለጠነ ኃይል እንዲደረጅ መደረጉ እና የፌደራል መንግስቱም ይህን በቀጥታ የሚቆጣጠርበትን መንገድ ከመዘርጋት ይልቅ ጉዳዩን ሙሉ በሙሉ ለክልሎች መተዉ፤ በቅርቡ በደሴ በተደረገ ውይይት ጠቅላይ ሚኒስትሩ አንዳንድ ክልሎች በጀታቸውን ሚሊሻ ይቀልቡበታል ያሉትን ልብ ይለዋል፤

+ በመከላከያ ሠራዊት፣ በክልል ልዩ ኃይል፣ በሚሊሺያ እና በፌደራልና በክልል ፖሊሶች መካከል ያለው የሥራ ግንኙነት እና የኃላፊነት ድርሻ ግልጽነት የጎደለው እና በመካከላቸውም በግልጽ የሚታይ ፉክክር መፈጠሩ፤ ይህንንም ችግር የፌደራል መንግስቱ እያወቀ አፋጣኝ የመፍትሔ እርምጃ አለመውሰዱ፤

+ በክልሎች መካከል የሚታዩ ፉክክሮች እና ፍጥጫዎች በወቅቱ ምላሽ አለማግኘታቸው እና የፌደራል መንግስቱም ለጉዳዩ የሰጠው ትኩረት እጅግ አነስተኛ መሆኑ፤

+ የክልል የጸጥታ እና የደህንነት አወቃቀር እና ተቋማቱን የሚመሩት ሰዎች አሿሿም በቅጡ ጥናት ያልተደረገበት እና ከዚያ ይልቅ በክልሎቹ መካከል ያለውን ፍጥጫ ታሳቢ ባደረገ መልኩ የትግራይ ክልል ጌታቸው አሰፋን መሾሙን ተከትሎ በአማራ እና በኦሮሚያ ክልል የተደረጉት የጸጥታ ዘርፍ ሹመቶች የክልሎቹን የወደፊት አብሮነት ሳይሆን ፍጥጫን ታሳቢ ያደረገ መሆኑ፤

እና ሌሎችም በርካታ ምክንያቶች ተደማምረው ይህ ለውጥ ፈተናዎች እንዲበዙበት እና አገሪቱም እንዲህ ያለው ጭንቀት ውስጥ እንድትገባ አድርገዋል።

ሌላው የዚህ ለውጥ ትልቁ ፈተና ሥርዓት በያዘ መልኩ ያልተከናወነው የአገራዊ መግባባት፣ የተጠያቂነት እና የእርቅ ጉዳይ መልሰን መላልሰን ተመሳሳይ ችግሮችን እንድናይ እያደረገን ይመስለኛል። ለውጡ ለእነዚህ ነገሮች ቅድሚያ እና በቂ ትኩረት ካለመስጠቱ የተነሳ ሁለት አደጋዎችን ይዞ እየተጓዘ ነው።

፩ኛ/ ባላፉት አሥርት አመታት በአገሪቱ ውስጥ የተፈጸሙ በደሎች እና የመብት ጥሰቶችን በተመለከተ ጥፋቶቹንና ወንጀሎቹን ሁሉ በጥቂት ሰዎች ላይ እንዲቆለል የተደረገ ይመስላል። በጠአት የሚቆጠሩ ሰዎች ብቻ የሥርዓቱ አስነዋሪ ሥራ እንዲሸከሙ እና ወደ ፍርድ አደባባይ እንዲቀርቡ ከተደረገ በኋላ አብረዋቸው የወንጀሉ ዋና ተሳታፊ የነበሩ በሺዎች የሚቆጠሩ ከከፍተኛ እስከ ዝቅተኛ ደረጃ ያሉ ባለሥልጣናት ሸክማቸው ቀሏቸው እና ገሚሶቹም እራሳቸውን እንደ ጻድቅ ቆጥረው እየተመጻደቁ ሥልጣናቸውን እንደያዙ እንዲቀጥሉ አድርጓል። ይህ ጥቂቶችን ተጠያቂ ያደረገው የተንሻፈፈ የፍትሕ ሂደት ብዙዎች አጥፊዎችን ከተጠያቂነት እንዲያመልጡ ብቻ ሳይሆን በሕዝብ እና በአገር ላይ ላደረሱት ጉዳት ለደቂቃም እንዳይጸጸቱ አድርጓቸዋል። ትላንት ገራፊ እና አስገራፊ የነበሩ ሰዎች ዛሬ ቅዱስ ተሿሚዎች ሆነው ስለፍቅር እና ሰላም ከኛ በላይ ሰባኪዎች የለም ብለዋል።

፪ኛ/ በተቃራኒው ባለፉት አስርት አመታት ከላይ በጠቀስኳቸው ተሿሚዎች ሲሳደዱ፣ ሲገረፉ፣ ሲዋከቡ እና ታስረው ሲሰቃዩ የነበሩ ሰዎች በአካል እና በስነ ልቦና የደረሰባቸው ጠባሳ በቅጡ ሳይድን እና ሳይታከም ገሚሶቹ ለመደለያ በሚመስል መልኩ ተሹመዋል። ገሚሶቹም ይህ ለውጥ ለበደላችን ካሳ ይሰጠናል ብለው ደጅ ሲጠኑ ቆይተዋል። ገሚሶቹም በተለያየ መልኩ የፖለቲካ ትግሉን ከነ ቁርሿቸው ተቀላቅለዋል።

ይህ ለውጥ በቅድሚያ በእነዚህ ሁለት ኃይሎች፤ በዳይ እና ተበዳይ መካከል ያለውን ቂም እና ቁርሾ ያመረቀዘ እባጭ እውነት ላይ በተመሰረተ ፍትህ እና እርቅ ሳያመክን በሌሎች ሥራዎች ላይ ተጠምዶ ቆይቷል። ቂም ተይዞ ጉዞ እንዲሉ፤ ይህ የዘመናት ቁርሾ ሳይቀረፍ አገር የማዘመን እቅድ እና ቅዥት ውስጥ ገብቶ መጠመድ መዘዙን በቅጡ ያለማጤን ይመስለኛል። ይህ አይነቱ የቁርሾ እባጭ ተበዳዮችን በሹመት በመደለልም ሆነ ስብከት በሚመስል የፖለቲካ ዲስኩር እና የተስፋ ቃል አይሽርም። ብቸኛ ምሱ እውነት፣ ፍትሕ እና እርቅ ናቸው።

ለውጡ መስመሩን እየሳተ እና አገሪቱን ወደ ግጭት እንድታመራ እድል እየፈጠረ እንደሆነ ምልክት የታየው እኮ የትግራይ ክልል በወንጀል የሚፈለገውን እና የንጹሃን ደም በእጁ ያለውን ጌታቸው አሰፋን የክልሉ የጸጥታ ዘርፍ ኃላፊ አድርጋ ስትሾም፤ ያንኑ ተከትሎ በዚህ ጨካኝ ሰው ታስሮ ሲሰቃይ የነበረውን ብ/ጀ አሳምነው ጽጌን የአማራ ክልል መንግስት የጸጥታ ዘርፍ ሃላፊ አድርጎ ሲሾም እና በዚሁ ሥርዓት ተገፍቶ እና ቂም ቋጥሮ ከመንግስት በመክዳት ኤርትራ ጫካ የወረደውን ጀ/ል ጀማል ገልቹን የኦሮሚያ ክልል መንግስት የጸጥታ ዘርፍ ኃላፊ አድርጎ የሾማቸው እለት ነው። ይችን አገር አንድ አድርጎ እና ሰላም አስፍኖ ለመምራት የሚፈልግ ኃይል በምንም ሂሳብ እነዚህን ሦስት ሰዎች የዚህ ቁልፍ የሆነ ሥልጣን ኃላፊንተ ተሿሚዎች ሊያደርጋቸው አይገባም።

ሦስቱም በውስጣቸው እሳት አለ። ጌታቸው አልዋጥ ያለውን ሽንፈት እና የሥልጣን ንጥቂያ ለመበቀል ያቄመ ሰው ነው። የእሱ ቦታ ሹመት ሳይሆን ወደ ፍርድ አደባባይ ነው። ብ/ጀ አሳምነው ብዙ ስቃይ እና ሰቆቃን ያሳለፈ እና ለአገሩ የከፈለው መስዋዕትነት በዜሮ ተባዝቶ በዘረኛ ገራፊ መርማሪዎች በደል ይተፈጸመበት እና ለበደሉም ተገቢውን ፍትሕ ያላገኘ ሰው ነው። እሱ ላይ በደል ያደረሱ ሰዎች በሌላኛው ጫፍ መቀሌ መሽገው ሲደነፉ ማየት የዚህን ሰው ቁስል እንደመጓጎጥ ነው። በተጨማሪም በእሱ እስር እና ስቃይ ላይ እጃቸው እንዳለበት የሚገለጽ አንዳንድ የበአዴን አመራሮች ዛሬም አብረው በአንድ ግንባር ተሰልፈዋል። ይህ ሰው ለደረሰበት የአካል እና የስነ ልቦና ጉዳት በቂ ድጋፍ እና ካሳ እንዲያገኝ ተደርጎ በክብር ጡረታ እንዲወጣ ይደረጋል እንጂ እንዲህ ያለ እሳት ውስጥ እንዲገባ አይደረግም። ጀነራል ጀማል ገልቹም እንዲሁ የኦነግን አላማ አንግቦ ሲታገል የቆየ እና የተገፋ ሰው ሲለሆነ፤ በኦዴፓ ላይም ከህውሃት እኩል አቂሞ የቆዩ ሰው ስለሆነ በእንዲህ አይነት ኃላፊነት ላይ ሊቀመጥ አይገባውም ነበር። ኦዴፓ ቀድሞ እኚህን ሰው ማስወገዱ ዛሬ ባህርዳር ላይ የተከሰተው አደጋ የመጀመሪያው ገፈት ቀማሽ እንዳይሆን ሳያደርገው አልቀረም። የባህርዳሩ መፈንቅለ ትርምስ ከወራት በፊት አዳማ ላይ ሊሆን የማይችልበት ምን ምክንያት አለ?

ነገሬን ልቋጭና የለውጥ ኃይሉ መዝረክረክ አገሪቱን ብዙ ዋጋ እያስከፈላት ነው። እነ አብይ ከግርግሩ መልስ በጥሞና ከላይ የተነሱትን እና ሌሎች ትኩረት የሚሹ ጉዳዮችን ቅድሚያ ሰጥተው ከወዲሁ ነገሮችን ቢያስተካክሉ መልካም ነው። አንዱ የአብይ አስተዳደር ክሽፈት መገለጫ በዚህን ያህል ጊዜ ውስጥ ከትግራይ ክልል ጋር ያለውን ተቃርኖ መፍታት አለመቻሉ ነው። የትግራይን ህዝብ የወያኔ ምርኮኛ አድርጎ ኢትዮጵያ በለውጥ ጎዳና ላይ ነች የሚለው ትርክት ለውጡን እሩብ ሙሉ ነው የሚያደርገው።

ቸር ያሰማን!

የጠቅላይ ሚኒስትሩም እጅ ነፃ ነው ብሎ ለማመን የሚያስችል ሁኔታም ስለሌለ፣ እርሳቸው በሚያቋቁሙት አጣሪ ኮሚሽንም መተማመን የምንችል አይመስለኝም ያሬድ ጥበቡ

ያሬድ ጥበቡ

ባላወቅኩት ምክንያት በተለይ የሁለቱ ጄኔራሎች የሰአረና የአሳምነው ሞት መረረኝ ። ልጅነታቸውን ለህዝብ ትግል የሰጡ ጀግኖች በአልባሌ መንገድ ሲገደሉ ያማል። ጦር ሜዳ ላይ ከጠላት ጋር ተናንቀው መስዋእት ሆነው በነበሩ የለመድነውን “ትግል አይሞትም” እየዘመርን በሸኘናቸው ነበር ። አሟሟታቸው ለቀባሪ እንኳ ለማርዳት አይመችም። ለምን ተገደሉ? ማን ገደላቸው? እንዴት ተገደሉ? ወዘተ የሚሉት ጥያቄዎች ቀላል መልስ አልተገኘላቸውም። የሰአረን ሞት ከክንፈ አሟሟት ጋር የሚያመሳስሉ ብዙዎች ናቸው። እጅግ የበዙ ጥያቄዎች በዜጎች አንደበት እየተመላለሱና እየተነገሩ ነው።

ከብዙዎቹ በጥቂቱ የሚነሱት ጥያቄዎች ይህን ይመስላሉ።
1) የአዴፓ ከፍተኛ አመራር እንዴት ቅዳሜ ከሰአት በኋላ በ11 ሰአት ስብሰባ ሊጀምር ቻለ? ምን አጣዳፊ አጀንዳ ቢያጋጥመው ነው በሰንበት ምሽት ስብሰባ የጠራው? የፓርቲው ሊቀመንበር አቶ ደመቀ፣ ለህክምና ወደ ዲሲ በሄዱበት ቀን እንዴት የአመራሩ ስብሰባ ሊጠራ ቻለ?

2)ስብሰባው የጄኔራል አሳምነውን በስልጣን መቀጠል አለመቀጠል ለመወሰን የተጠራ ነበርን? ጄኔራል አሳምነው ስብሰባው የት እንደሚካሄድና በምን አጀንዳ ላይ እንደሚወያይ ያውቁ ነበርን? ስብሰባው ከአዲስ አበባው ባለአደራ ኮሚቴ አባላት መምጣትና በሚቀጥለው ቀን ከሚደረግ ስብሰባ ጋር የተያያዘ ነበርን? ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስለዚህ ስለ እሁዱ ስብሰባ መደረግ ሃሳብ (ከንሰርን) ነበራቸውን? እንዲቆም ትእዛዝ ሰጥተው ነበርን? ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ እስክንድር ባህርዳር የሄደው ከጄኔራል አሳምነው ጋር መንግስት ሊያውጅ ነው የሚል ፍርሃት ነበራቸውን? ይህን ፍርሃታቸውን ለአዴፓ ከፍተኛ አመራር ገልፀው፣ አስቸኳይ ስብሰባ በቅዳሜ ምሽት የተጠራው ለዚህ ይሆን? ከሆነ የዶክተር አምባቸው አመለካከት ምን ነበር? በዶክተር አምባቸውና በጠቅላይ ሚኒስትሩ መሃል አለመግባባቶች ነበሩን? ዶክተር አምባቸው፣ “አማራ ሙያው በልቡ ነው!” ብለው ለህዝብ ሲናገሩ ከዶክተር አቢይ የደረሰባቸው ተቃውሞ ነበርን? በአጠቃላይ ግንኙነታቸው እንዴት ነበር?

3) የአዲስ አበባው ግድያ በስንት ሰአት ተካሄደ? ከባህርዳሩና ከአዲስአበባው ግድያ የትኛው ይቀድማል?

4) ዶ/ር አቢይ መፈንቅለ መንግስት እየተካሄደ ነው ብለው ካመኑ፣ አዲስ አበባ ላይ የሚካሄደውን የቺፍ ኦፍ ስታፋቸውን ግድያ ትተው እንዴት ባህርዳር ሊሄዱ ቻሉ? ለሥልጣናቸው ይበልጥ የሚያሰጋው ከባህርዳሩ ይልቅ የአዲስ አበባው ግድያ አይደለምን?

5) ዶ/ር አቢይ አዲስ አበባን መቼ ለቀቁ? ባህርዳር በስንት ሰአት ደረሱ? የሲቪል አቪየሽን ሎጎች ወይም መዘርዝሮች ምን ይላሉ? ጠቅላይ ሚኒስትሩ በስንት ሰአት የነረራ መስመር ጠየቁ? ምን ያህል ጦር አስከትተው ሄዱ? መቼም መፈንቅለ መንግስት ለማክሸፍ የሚጠብቋቸውን ሪፐብሊካን ጋርድስ ብቻ ይዘው ተጓዙ ብሎ ለማመን ከባድ ነው? ወይስ የጄኔራል ሰዓረን ሞት ሳይሰሙ ነው ወደ ባህርዳር ያቀኑት? የባህርዳሩን ጉዳይ ከጄኔራል ሰዓረ ጋር ተወያይተውበት ነበርን? ከተወያዩበት መፈንቅለ መንግስት አለ የለም፣ የፌዴራል መከላከያ ጦር ይግባ ወይስ አይግባ ላይ በጄኔራል ሰዓረና በጠቅላይ ሚኒስትሩ መሃል የሃሳብ ልዩነት ነበርን? ጄኔራል ሰዓረ “ይህ የክልሉ ጉዳይ ነው ጣልቃ መግባት የለብንም፣ ከገባንም የክልሉን ምክርቤት ጥሪ ካገኘን በኋላ ብቻ መሆን ይኖርበታል” ብለው በመተክል ላይ ቆመው ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ትእዛዝ እምቢተኛ ሆነው ሊሆን ይችላል? ጄኔራል ሰዓረ ይህን መሰል ፕሮፌሽናል ወታደራዊ መኮንንና በውሳኔያቸው የሚተማመኑ ሰው ነበሩን?

6) ጄኔራል ሰዓረ ስለተባለው “መፈንቅለ መንግስት” ያውቁ ነበርን? ካወቁ ኮማንድ ፖስት አቋቁመው ሁኔታውን ለመቆጣጠር አመራር መስጠት አልበነረባቸውምን? አመራር እየሰጡ ከነበረ ቤታቸው ምን ያደርጉ ነበር? አመራር እየሰጡ ከነበረ ጡረታ ከወጣ ጓደኛቸው ጋር እንዴት እየተዝናኑ አመራር ይሰጣሉ? ወይስ ሰለ ባህርዳሩ ሁኔታ ሳያውቁና የባህርዳሩ ችግር ከመፈጠሩ በፊት ነው ጄኔራል ሰዓረ የተገደሉት? ከባህርዳሩ በፊት ከሆነ የተገደሉት እንዴት ጠቅላይ ሚኒስትሩ አዲስ አበባን ለቀው ወደ ባህርዳር ሊሄዱ ይችላሉ?

7) የጄኔራል ሰዓረ “ገዳይ ነው” የተባለው ጠባቂያቸውን በሚመለከት የጠቅላይ ሚኒስትሩ ፅህፈትቤትና ፖሊስ የሰጣቸው እርስ በርሳቸው የሚጣረሱ ዜናዎችና መረጃዎች መንስኤያቸው ምን ይሆን? አንዴ ይዘነዋል፣ ከዚያ የራሱን ነብስ አጥፍቷል፣ ከዚያ ቆስሎ ህክምና ላይ ይገኛል ወዘተ የሚሉት በጣም የሚጋጩ መረጃዎችን መንግስት እንዴት ሊሰጥ ቻለ? ከግድያው ባህሪ የመነጩ ችግሮች ናቸውን? ገዳይ ነው የተባለው ዘብ ስም ማን ነው? ማን መረጠው? የሪፐብሊካን ጋርድ አባል ነውን? ለምን ያህል ወራት ወይም ዓመታት ይህን መሰል የባለሥልጣናት ዘብነት ሥራ ሠራ? ከዚህ በፊት እነማንን አገልግሎ ነበር? ስለቀድሞ ባህርዩ ምን የሚታወቅ ነገር አለ? ስለፖለቲካ አመለካከቱስ? አክራሪ የአማራ ብሄርተኛ ሊባል የሚችል ነውን? ይህ ይታወቅ ነበርን? ከታወቀስ እንዲህ ዓይነት ሥራ እንዴት ሊሰጠው ቻለ? ምን ያህል ጊዜ ከጄኔራል ሰዓረ ጋር ሰርቷል? ከጄኔራል አሳምነው ጋር ግንኙነት ነበረውን? በተለይ የግድያ እርምጃውን የወሰደ ቀን ከጄኔራል አሳምነው ጋር ተደዋውሎ ነበርን? የዘቡ የስልክ ሬከርዶች ወይም መረጃዎች ምን ይነግሩናል? ገዳይ ከተባለው ዘብ በቀር ሌሎች ዘቦች በቦታው ነበሩን? በዝርዝር ስለሁኔታው ምን ይላሉ?

8)የጄኔራል ሰዓረ ቤተሰቦችና የቤት ውስጥ ሠራተኞችስ በግድያው ወቅት የት ነበሩ? ማን ግድያውን እንደፈፀመ አይተዋልን? ገደለ ስለተባለው ዘብ የታዘቡት ነገር አለ? በቤታቸው ውስጥና በቤታቸው አካባቢ ያዩት የተለየ እንቅስቃሴ ነበርን? ከጄኔራል ገዛኢ ሌላ ከውጪ የመጣ ሰው ወይም ሰዎች ነበሩን? ጄኔራል ሰዓረ የሞቱ ቀን፣ ከዛፍ ተከላ ስምሪታቸው ከተመለሱ በኋላ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ሲወያዪ ተደምጠዋልን? ሲበሳጩ፣ በሃይለቃል ሲናገሩ ወይም ሲቆጩ ያዳመጣቸው የቤተሰብ አባል ነበርን?

9)ቅዳሜ እለት የጄኔራል አሳምነው ውሎ እንዴት ነበር? ለእነ እስክንድር ደማቅ አቀባበል ለማድረግ ሲተጉ ነው የዋሉት የሚሉት መረጃዎች እውነት ናቸውን? የጄኔራሉ የስልክ ጥሪዎች (የላኩዋቸውና የተቀበሉዋቸው) ለማንና ምን ይዘት የነበራቸው ነበሩ? ኢንሳ የባለሥልጣናትንና የሚጠረጠሩ ሰዎችን ስልክ ጠልፎ ስለሚተይብና የድምፅ ፋይልም ስለሚያስቀምጥ፣ እነዚህ ፋይሎች ምን ይሉ ይሆን?

10) የመፈንቅለ መንግስት ወሬ አቶ ንጉሱ ጥላሁን ካወሩ በኋላ ጄኔራል አሳምነው ለአንድ የአዲስ አበባ ጋዜጣ የሰጡት አጭር ቃለምልልስ ስለ ጄኔራሉ የወቅቱ ግንዛቤ ምን ይነግረናል? ይህ ቃለምልልስ በስንት ሰአት ተካሄደ? ያደረገውስ ጋዜጠኛ ማን ነው? የድምፅ ፋይል አለው ወይ? ጄኔራል አሳምነው ፈፅሞ በማያውቁት ሁኔታ ውስጥ ነው ወይ የተጠለፉት? ጄኔራል አሳምነው ለምን ተገደሉ? በምን ሁኔታ ነው የተገደሉት? ለመማረክ አይቻልም ነበርን፣ ወይስ መያዝ እየተቻለ ነው የተገደሉት? ጄኔራል አሳምነውን የሚያሳድደው አሃድ ከየትኛው ጦር የተውጣጣ ነበር? ወይስ ራሳቸው ባሰለጠኑት ልዩ ሃይልና አርሶአደር ነው የተገደሉት? የተልእኮው መሪ ማን ነበር? ተልእኮውንስ የሰጠው ማን ነበር? በህይወት ይዛችሁ እንዳትመጡ የሚል ተልእኮ ነበርን? ከሆነ ለምን?

11) ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስለ ባህርዳሩ ሁኔታና ስለ ጄኔራል ሰዓረ መገደል መቼ አወቁ? እንዴት አወቁ? ማን ደውሎ ነገራቸው? እንደሰሙ ምን እርምጃ ወሰዱ? እንደ አዲስ የታደሰው የጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ ውስጥ አሜሪካኖቹ ዘ ዎር ሩም የሚሉት ዓይነት የአስቸኳይ ጊዜ አመራር የሚሰጥበት ከውጪ በቀላሉ የማይደፈር የስብሰባ አዳራሽ አለ ወይ? ካለ፣ እነማን ተሰበሰቡ? በመካሄድ ላይ ያለው መፈንቅለ መንግስት ነው የሚለው ውሳኔ ላይ እንዴት ተደረሰ? ለምን ይህን መወሰን አስፈለገ? ይህ ውሳኔ የተካሄደው የጄኔራሉ መገደል ከመታወቁ በፊት ነው ወይ? ጄኔራሉ ከተገደሉ በኋላ ከሆነ ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዋና ከተማቸውን ለቀው ለመሄድ እንዴት ወሰኑ? ግድያው በጄኔራል ሰዓረ ብቻ ይቆማል ብለው እንዴት ሊተማመኑ ቻሉ? ጄኔራል አሳምነው በአስር ሺህዎች የሚቆጠሩ ልዩ ሃይሎችና በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ የገበሬ ሚሊሺያዎች እያሰለጠነ ነው የሚል እምነት ከነበራቸው፣ እንዴት በአፋጣኝ ወደባህርዳር ሄዶ እሳት ውስጥ ራሳቸውን መማገድ የተሻለው አማራጭ ነው ብለው ሊያስቡ ቻሉ? በአክሱም ጉዟቸው ወቅት ከዶክተር ደብረፂዮን ጋር በነበራቸው ቆይታ ስለዚህ የአማራ ክልል የልዮ ሃይልና ሚሊሺያ አደረጃጀት ተወያይተው ነበር ወይ? ከተወያዩ ምን መረዳዳት ላይ ደረሱ? አንዲት ፍየል ወደ ትግራይ እንዳታልፍ በታገደች ቁጥር በማነታችን የጥቃት ዒላማ ተደርገናል ብለው የሚያለቅሱት የወያኔ ሊቀመንበር እንዴት በሁለቱ የትግራይ ጄኔራሎች ግድያ መንግስቱን ሳይወቅሱ ቀሩ? ደብረፅዮን የሚያውቁት እኛ የማናውቀው መረጃ አለ ወይ? ወይስ በባህርዳር የተደረገው ፍጅት የአማራውን ክልል ያዳክመዋል እኛንም ወደማእከላዊ ሥልጣን ይመልሰናል፣ እስረኞቻችንንም ለማስፈታት ይረዳናል ብለው ስላመኑ ይሆን?

ከላይ እንዳያችሁት ጥያቄዎቹ ብዙ ናቸው። የጄኔራል ሰዓረ ገዳይ መያዙንም ሆነ መሞቱን እ ደገና ከሞት መነሳቱን በሚነግረን የፖሊስ ሃይል ሊጣራ ይችላል ብለን ለማመን አይቻለንም። ከአገዛዙ ነፃ በሆነ አጣሪ ኮሚሽን ሊጣሩ የሚገባቸው በሺህ የሚቆጠሩ ጥያቄዎች አሉ። በፌዴራል ደረጃ ነፃ አጣሪ ኮሚሽን የሚያስፈልገውን ያህል፣ በአማራ ክልል ደረጃም ነፃ አጣሪ ኮሚሽን ያስፈልግ ይሆናል። በክልሉ ውስጠ ከሚገኙ የኮሌጅ መምህራንና ሠራተኞች፣ ከህግ ባለሙያዎች ወዘተ የተውጣጣ ኮሚሽን ማቋቋም ይቻል ይመስለኛል። ማድረግ የማንችለው እንዲህ ዓይነቱን የተወሳሰበ ጉዳይ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ትተን እጃችንን አጥፈን መቀመጥ ነው። የውጪ ሃይሎችም እንዲገቡበት መፍቀድ የለብንም። ያ ፈሱን መቋጠር በማይችል አይሁድ ጥላቻ ምእራቡ ከማን ወግኖ እንደቆመ ግልፅ ስለሆነ፣ ነፃ ኮሚሽን ውስጥ ሊካተቱ አይችልም፣ አይገባምም ።

ዛሬ፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩም እጅ ነፃ ነው ብሎ ለማመን የሚያስችል ሁኔታም ስለሌለ፣ እርሳቸው በሚያቋቁሙት አጣሪ ኮሚሽንም መተማመን የምንችል አይመስለኝም። የኮሚሽኑ የማጣራት ውጤት ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩንም ነፃ የሚያወጣቸው፣ አለበለዚያ በጥርጥሬ ውስጥ የወደቀው አመራራቸው ትልቅ ችግር ይገጥመዋል የሚል ፍርሃት አለኝ። የራሳቸውን ንፅህና ለማሳየት ሲሉ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እራሳቸው የዚህን ብሄራዊ ነፃ አጣሪ ኮሚሽን የማቋቋም ጥሪ ተቀብለው ተግባራዊ እንዲሆን ቅድሚያ ሊሰጡት ይገባል። የትም ሃገር ጉብኝት ከመውጣታቸው በፊት ሊያከናውኑት የሚገባ ቀዳሚ ተግባር ነው ብዬ አስባለሁ።

ያሬድ ጥበቡ

የብርጋዴር ጄነራል አሳምነው አስክሬን ላሊበላ ገባ

ጄኔራል አሳምነው ፅጌ

የብርጋዴር ጄነራል አሳምነው ፅጌን አስክሬን ላሊበላ አየር ማረፊያ እንደደረሰ በስፍራው የሚገኙት የላሊበላ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ ማንደፍሮ ታደሰ ለቢቢሲ ገለፁ።

• ብርጋዴር ጄኔራል አሳምነው ፅጌ መገደላቸው ተገለጸ

• ስለ’መፈንቅለ መንግሥት’ ሙከራው እስካሁን የማናውቃቸው ነገሮች

ትናንት የብ/ጄነራል አሳምነው መገደል ከተሰማ በኋላ ቤተሰቦቻቸው አስክሬናቸው በክብር እንዲሰጣቸው ለወረዳው ጥያቄ በማቅረባቸው ጥያቄያቸውን መንግሥት ተቀብሎ አስክሬናቸውን እንደሸኘ አቶ ማንደፍሮ ተናግረዋል።

ዛሬ ከቀኑ 7፡00 ሰዓት አካባቢ የብ/ጀኔራሉ አስክሬን ከባህር ዳር ወደ ትውልድ ቀያቸው እንደሚላክ በስልክ እንደተነገራቸው የገለፁት ምክትል ከንቲባው አስክሬናቸውን በክብር ለመቀበል በአየር ማረፊያ እንደተገኙ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የጄነራሉ ቤተሰቦች፣ የአካባቢው ነዋሪዎች፣ የአካባቢው የመንግሥት አመራር አካላት፣ የፀጥታ ኃይሎችና የቤተክርስቲያን ቀሳውስት በአውሮፕላን ማረፊያው ተገኝተዋል።

ከቤተሰቦቻቸው ጋር ገና ስላልተነጋገሩ የብ/ጄነራሉ የቀብር ሥነ ሥርዓት የትና መቼ እንደሚፈፀም በእርግጠኝነት መግለፅ እንደማይችሉ የገለፁልን ምክትል ከንቲባው፤ ሕብረተሰቡ ኃዘኑን የሚገልፅበት በከተማ አደባባይ ትልቅ ድንኳን የተዘጋጀ መሆኑንና አስክሬናቸውም በዚሁ ድንኳን ውስጥ እንደሚያርፍ አስረድተዋል።

በዚያው ሥፍራ ሌሊቱን የፀሎተ ፍትሃት ሥነ ሥርዓት እየተደረገ እንደሚያድር መረጃ እንዳላቸው ገልፀውልናል።

ምክትል ከንቲባው ብ/ጄነራል አሳምነው ለአገር ያበረከቱት አስተዋፅኦ ከፍተኛ በመሆኑ የቀብር ሥነ ሥርዓታቸው በደማቅ ሁኔታ ለመፈፀም ኮሚቴ መዋቀሩን አክለዋል።

በዚህም መሠረት የቀብር ሥነ ሥርዓቱን በዲስፕሊንና በፕሮቶኮል ለመምራት የክብር ተመላሽ ጄነራሎች በአካባቢው ላይ በመኖራቸው በእነርሱ ይመራል ብለዋል።

በሌላ በኩልም የፀጥታ ሂደቱን የሚመራ ቡድን፣ የወጣቱ ሰላምና ደህንነት የሚከታተል ሌላ በወጣቶች የሚመራ ቡድን እንዲሁም የሃይማኖት ሥነ ሥርዓቱን የሚመራ ኮሚቴም ተዋቅሯል።

• ራሱን አጥፍቷል የተባለው የጄነራል ሰዓረ ጠባቂ ሆስፒታል እንደሚገኝ ተገለፀ

አቶ ማንደፍሮ እንደገለፁልን ትናንት ብ/ጄነራሉ መገደላቸውን ከተሰማ አንስቶ በሕብረተሰቡ ዘንድ የተዘበራራቀ ስሜት እንደሚታይ እንዲሁም በክልሉ አመራሮች ሞት ምክንያት ድንጋጤ ውስጥ መሆናቸውን ነግረውናል።

የአገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የመንግሥት አመራርና የፀጥታ አካላት ከህዝቡ ጎን በመሆን ቤተሰባቸውን በማፅናናትና ህዝቡንም በማረጋጋት ከፍተኛ ሚና እየተጫወቱ እንደሆነ አስረድተዋል።