ምርጫ በጊዜ ሠሌዳ መሰረት ይደረግ አይደረግ? ጉንጭ አልፋ ንትርክ!! (ግረማ ሠይፉ ማሩ)

ግርማ ሠይፉ ማሩ
ግርማ ሠይፉ ማሩ

ምርጫ አሁን ያለውን የጊዜ ሠሌዳ ጠብቆ መካሄድ አለበት የሚሉ እና አይደለም ምርጫው መዘግየት አለበት፡፡ የሚሉ የተለያዩ ግለሰቦች እና የቡድን ወኪሎች ሙግት ላይ ይገኛሉ፡፡ በግሌ ምርጫ “በተቻለ መጠን” የጊዜ ሠሌዳውን ጠብቆ መካሄድ አበለበት ብዬ አምናለሁ፡፡ ይህን የምልበትን ምክንያት በዝርዝር አቀርባለሁ፡፡ ይህ ማለት ግን ምርጫው በጊዜ ሠሌዳው ካልተካሄደ አገር ትፈረሳለች ከሚሉት ወገን አይደለሁም፡፡

ምርጫው በሕግ በተደነገገው መሰረት በመጪው ሁለት ሺ አስራ ሁለት ግንቦት ውር ላይ መካሄድ አለበት፡፡ ሕገ መከበር አለበት በሚል ጉንጭ አልፋ ክርክር ለሚከራከሩ መልሱ አጭር ነው፡፡ በአምስት ዓመት መካሄድ የነበረበት ምርጫ ሲራዛም ይህ የመጀመሪያው አይደለም፡፡ የአዲስ አበባ ምርጫ በቅንጅት ማሸነፍ ምክንያት ለሁለት ዓመት ተገፍቶ፤ ከአካባቢ ምርጫዎች ጋር እንዲደረግ መደረጉ አንዱ ሲሆን፣ አሁንም መደረግ ካለበት ጊዜ ለተጨማሪ አንድ ዓመት እንዲራዘም ተደርጓል፡፡ በቀጣይ አራት ወር ጊዜም ሊካሄድ አይችለም፡፡ በድጋሚ የመራዘም ዕድሉ ከፍተኛ ነው፡፡ በእኔ እምነት መራዘምም አለበት፡፡ ሰለዚህ ምርጫ በጊዜ ሠሌዳ መሰረት ባለመካሄዱ የሚፈጠር አገር የሚፈርስ ችግር የለም፡፡ ችግሩ ባልተመረጡ ሰዎች መገዛት ነው- እንችለዋለን፡፡ በተጭበረበረ ምርጫ መገዛት እና ሳይመረጡ መግዛት ያው አንድ ዓይነት ነው፡፡

ባለፉት ዓመታት (ምን አልባትም አንድነት ፓርቲ የሚሊዮኖች ድምፅ ለነፃነት!! በሚል ዘመቻ ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ) የተካሄዱት ሕዝባዊ እንቅስቃሴዎች ዋናው ጉዳይ የነበረው “ያልተመረጠ መንግሰት አይገዛንም” በሚል ነው፡፡ ግፍ፣ ጭቆና በቃን፤ ወያኔ ይወደም (ዳውን፣ ዳውን ወያኔ)፣ ወዘተ በሚል የተደረጉት እንቅስቃሴዎች ሕዝቡ የሥልጣን ባለቤት የመሆን ጥያቄ ነው፡፡ በ2004 መጀመሪያ ጀምሮ የታወጀው የሊዝ ዓዋጅ እና እርሱን ተከትሎ የመጣው የመሬት ወረራ ያንገሸገሸው ሕዝብ ድምፁን ያሰማው በመረጥኩት መንግሰት መተዳደር እፈልጋለሁ በሚል ነበር፡፡ ሰለዚህ ሕዝብ መሪውን መምረጥ እና መሾም ሲፈልግ መሻር ይፈልጋል ማለት ነው፡፡ የሕዝብ መሪውን የመምረጥ ፍላጎት በጥያቄ ውስጥ ካላስገባን ምርጫ ይራዘምን ምን አመጣው?

ምርጫ የዜጎች መብት ሲሆን ዜጋ የሚፈልገውን እናውቃለን የሚሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች በተደራጀ መልኩ ደግሞ አማራጭ ሃሳባቸውን ማቅረብ በፈቃደኝነት የወሰዱት ሃላፊነታቸው ነው፡፡ ይህም ሃላፊነት በዜጎች ይሁንታ ብቻ የሚገኝ ነው፡፡ የያዙት ሃሣብ የፈለገ ምርጥ እና ጥልቅ ቢሆን ሕዝብ ይሁን ብሎ የሥልጣን መንበር ካልሰጠ መተግበር አይቻልም፡፡ (ኢህአዴግ ባለፉት 27 ዓመታት ብቸኛውም መንገዴ የሚለው የተሳሳተ መንገድ ነው፡፡)

የዜጎችን መብት ተረድተናል ያሉ ተፎካካሪዎች የሚዳኙበትን ሕግና ደንብ በአግባቡ አዘጋጅቶ ጫወታውን የሚመራወው አካል ደግሞ የምርጫ አስፈፃሚው አካል ሲሆን በምርጫ አስፈፃሚ ቅር የተሰኘ ደግሞ አቤት የሚልበት ነፃ ፍርድ ቤት የግድ ይላል፡፡ እነዚህ አካላት የምርጫ ቦርድ እና ነፃ ፍርድ ቤት መኖር ወሳኝ የምርጫ ግብዓቶች ናቸው፡፡

ምርጫ ይራዘም የሚሉ ሰዎች ፍርድ ቤቱ ጠንካራ/ገለልተኛ ስለአልሆነ በምርጫ ወቅት በሚፈጠሩ ችግሮች ፍትሓዊ ውሳኔ አይገኝም  የሚለው አንዱ መከራከሪያቸው ነው፡፡ ፍርድ ቤቱን ገለልተኛ ለማድረግ ከዛሬ ጀምሮ ስንት ጊዜ እንደሚፈጅ ግን በግልፅ  አይናገሩም፡፡ ይባስ ብሎ ግን ይኽው ፍርድ ቤት ሙሰኞችን እና ሌሎች ወንጀለኞችን በአፋጣኝ ለፍርድ ያቅርብ ይላሉ፡፡ በእኔ አምነት ፍርድ ቤት ገለልተኛ መሆን አስፈላጊ መሆኑ ይገባኛል፡፡ ነገር ግን ይህ ሥራ በአንድ የምርጫ ዘመን የሚጠናቀቅ አይደለም፡፡ ሰለዚህ መንግሰት በፍርድ ቤቶች ጉዳይ ጣልቃ እንደማይገባ ማረጋገጥ በራሱ ፍርድ ቤቶችን አንድ ደረጃ ከፍ የሚያደርጋቸው ሲሆን የመዓዛ አሸናፊ የመሰሉ ሰዎች በቦታው መሾም ከተራ ጣልቃ ገብነት ይጠብቀዋል ብዬ አምናለሁ፡፡ በተቻለ መጠን የፍርድ ቤቱን ጫናም ለመቀነስ ተፉካካሪዎች በጨዋነት ለመጫወት መወሰን ይገባናል ብዬ አምናለሁ፡፡ በዚህ ሁኔታ ባለው ፍርድ ቤት ምርጫ ማካሄድ የምንችልበት ጊዚያው አውድ መፍጠር ይቻላል፡፡ የሚል ጽኑ እምነት አለኝ፡፡

ሌላው የምርጫ ቦርድ ጉዳይ ነው፡፡ ምርጫ ቦርደ ለሆዳቸው ያደሩ የምርጫ ቦርድ አባላትና ሠራተኞች በሰፈሩበት ሁኔታ ምን እንደሚሆን ያልረሳነው የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነው፡፡ አሁን በምርጫ ቦርድ የተጀመረውን ለውጥ በአፋጣኝ ወደ መሬት አውርዶ ተግባራዊ ለማድረግ ምን ያህል ጊዜ ይፈጃል? የሚሊዮን ብር ጥያቄ ነው፡፡ በእኔ እምነት በአርባ ሺዎች የሚቆጠሩ ምርጫ አስፈፃሚዎችን ለማዘጋጀት የሚፈጀውን ጊዜ ማስላት እና ይህን በቴክኖሎጂ ማገዝ ወሳኝ ጉዳይ ነው፡፡ የምርጫ አስፈሚዎች ሥልጠና በሶስት ወር የሚጠናቀቅ ነው፡፡ የምርጫ አስፈፃሚዎች አሁን ከዩኒቨርሲቲ የተመረቁ ተማሪዎችን በገለልተኝነት ማሳተፍ በተመረጡ ሰማኒያ ጣቢያዎች አምስት መቶ ምርጫ አስፈፃሚዎች ማዘጋጀት ለምን እንደ ችግር እንደሚታይ አይገባኝም? ይህ ችግር የሚሆነው አሰመራጮቹን ግልፅ ላልሆነ ተልዕኮ ለማስልጠን ሲፈለግ ብቻ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም እንደሚደረገው ገለልተኛ መስለው ገዢውን ፓርቲ የሚያስመርጡ ሴረኞችን ለመመደብ፣ ይህን የሚያሟሉትን ሆድ አደሮች ለመምረጥ የሚደረግ ሽፍጥ ሥራውን ያከብደዋል፡፡

ምርጫ ቦርድ በቀረው ጊዜ ይህን ለማድረግ ያስቸግረኛል በሚል ተጨማሪ ጊዜ የሚጠይቅ ከሆነ ያለ በቂ አጫውች ጫወታ መጀመር ሰለሌለበት ምርጫው ሊራዝም ቢችል በግሌ ምንም ግድ አይሰጠኝም፡፡ ምርጫ ቦርድ ይህን ማድረግ የማይችልባቸውን ምክንያቶች በዝርዝ ማቅረብ ይኖርበታል ብዬ አምናለሁ፡፡

ተፉካካሪ ፓርቲዎች ለምርጫ እራሳቸውን ብቁ አድርገው እስኪዘጋጁ ምርጫ ይራዘም የሚል አስቂኝ ምክንያት የሚቀርብ አይመስለኝም፡፡ ሃሣብ ያለው ለሕዝብ ለማቅረብ በቂ ጊዜ አለው፡፡ ሃሣብ ለሌው ደግሞ የፈለገ ቢራዘም በቂ አይሆንም፡፡ አሁን እንደ አዲስ ተነስቶ አገር መምራት ሰለማይቻል ሃሳብ አለን የሚሉ ሁለትም ይሁኑ ሶሰት ሲወዳደሩ በውድድሩ ውስጥ በመሳተፍ ልምድ መቅስም የተሻለው አማራጭ ነው፡፡ የተፉካካሪዎች አለመዘጋጀት ለምርጫ ለማራዘም ምክንያት ሊሆን አይችልም፡፡

ከምርጫ በኋላ የሚከሰቱ ግጭቶችን በመፍራት ምርጫ ይራዘም የሚሉ ቅን ዜጎች እንዳሉም አምናለሁ፡፡ አነዚህ ቅን ዜጎች ምርጫ በማራዘም ግጭት ማስወገድ እንደማይቻል አለመረዳታቸው ነው፡፡ የግጭት ምንጮች ተፉካካሪ ፓርቲዎች እራሳቸው ናቸው፡፡ እነዚህ ተፉካካሪ ፓርቲዎች ወደ ግጭት ላለመግባት ቁርጠኛ ውሳኔ በሕዝብ ፊት እንዲገቡ ለማስገደድ ምን ያህል ጊዜ በቂ ነው? የሚለው ጥያቄ መመለስ አለበት፡፡ ሚዲያዎች ሲቪል ማህበራት ይህን በማድረግ ዙሪያ ከፍተኛ ሚና መጫወት ይኖርባቸዋል፡፡ ሕዝቡ ለምርጫ ውጤት እንዲገዛ፣ ተፉካካሪዎች ከምርጫ በኋላ ለሚያደርጉት ጥሪ ጆሮ እንዳይሰጥ ማስተማር ይኖርባቸዋል፡፡ ሕዝብ በዚህ ደረጃ ከነቃ ማንም ለጊዚያዊ ድል ሕዝብ ወደ ሞት የሚጠራ ብጥብጥ አይከተልም፡፡ ሙከራና ፉከራ ብቻ ይሆናል፡፡

መንግስት በጀመረው መስመር ቁርጠኛ ከሆነ እና ሁሉም የመንግሰት መዋቅሮች ማንኛውንም ሠላማዊ የፖለቲካ እንቅስቃሴ እንዳይገድቡ መመሪያ የሚሰጥ እና ይህ መመሪያ በሚጥሱ የመንግሰት መዋቅሮች ላይ የማያዳግም እርምጃ ወስዶ ለሕዝብ ይፋ ማድረግ ከጀመረ በሠላማዊ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ሕዝብ የፈለገውን መርጦ ወደ መንበር ያመጣል በዚህ ጊዜ ተፉካካሪዎች ሁሉ አሸናፊ ይሆናሉ፡፡ አሁን በየቦታው የሚታዩት ግጭቶች ጊዚያዊና የታፈኑ ዜጎችና ቡድኖች ከአፈና አገዛዝ ሲወጡ ሊከሰት የሚችል ክስተት ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ መንግሰት በመዋቅሮቹ ቁርጥና እርምጃ ውስዶ ሠላማዊ ድባብ ማረጋገጥ የማይችል ከሆነ ምርጫ ማካሄድ አለመቻል ብቻ ሳይሆን ይህን ለማድረግ ምን ያህል እንደሚበቃው ማስላትም ሰለማይቻል እንደ ደርግ በጊዚያዊ መንግሰት ስም ለረጅም ዓመት መቆየቱ አይቀሬ ነው፡፡ ይህ የባስ አታምጣ የሚያሰኝ ነው፡፡

በአገራችን ጥንቅቅ ያለ እንከን የለሽ ምርጫ ማካሄድ ላይቻል ቢችልም፡፡ በወሳኝ መልኩ ሕዝብ ለሥልጣን ባለቤት የሚያደረግ (የመረጠው ብቻ በየደረጃው ባለ መዋቅር ሃላፊ የሚሆንበት) ሥርዓት መዘርጋት ይቻላል፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ምርጫ ለማራዘም  በቂ ምክንያቶች አሉ ብዬ አላምንም፡፡ ምርጫ ቦርድ ይህን ሁኔታ ገምግሞ በመረጃ አስደግፉ ከሚሰጠው ምክንት ውጭ በሰበብ ምርጫ ማራዘም ሌሎች ብዙ ንትሮኮች ከማምጣት ባለፈ ሕዝብ የመረጠው አካል እንዳያስተዳድረው ማድረግ ነው፡፡ ሰለዚህ ምርጫ በአፋጣኝ እላለሁ ……

ቸር ይግጠመን

ግረማ ሠይፉ ማሩ

አስደንጋጩ የግብርና ሚንስትር ሪፖርት! (ሙሉቀን ተስፋው)

የግብርና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ሳይንሳዊ ጥናቶች ወሳኝነት አላቸው። እንደየ አካባቢው አፈር እና አየር ንብረት ተስማሚ የሚሆኑ ምርጥ ዘሮችን በምርምር አግኝቶ ገበሬወች ማከፋፈል አስፈላጊ ነው። በዚህም ምክንያት የኢትዮጵያ ፌደራል መንግስት ብዙ ወጭ በማውጣት በተለያዮ የአገሪቱ ክፍሎች የግብርና ምርምር ተቋማትን ገንብቷል።

የኢትዮጵያ ግብርናና ትራንስፎርሜሽን ዓመታዊ ሪፖርት እንደሚያሳየው በአጠቃላይ 17 የግብርና ምርምር ተቋማት አሉ። አማራ ክልል ግን አንድ ምርምር ተቋም ብቻ ነው ያለው። አማራ ክልል በጤፍ፣በስንዴ፣በበቆሎ እና በተለያዮ የግብርና ምርቶች ታዋቂ ነው። ይህን ክልል በምርምር ማገዝ ሲገባ አንድ የግብርና ምርምር ተቋም ብቻ በቂ አይድለም።

ኢትዮጵያ በመሬት አቀማመጥ፣በአየር ንብረት፣በአፈር አይነት ,”ethiopia land of extremes” የምትባል ሀገር ናት። በጣም ቀጥቃዛ ፣ተራራማ ከሆነ አንድ የአማራ አካባቢ ተነስተህ ኪሜ ስትጏዝ በጣም ሞቃት ወደሆነ በረሃ ትደርሳለህ። ለዛም ነው በየአካባቢው የግብርና ምርምር ተቋም መከፈት ያለበት። ቀጥሎ እንደምትመለከቱት አብዛኛዎቹ የምርምር ተቋማት ከአዲስ አበባ በመቶ ኪሎ ሜትር ራዲየስ ወደ ኦሮሚያ ክልል ብቻ ነው የተገነቡት።

Ambo plant protection Research center, OROMIA
Debre zeit Agricultural Research center, OROMIA
Werer Agricultural Research center, OROMIA
Wondo Genet Agricultural Research center, OROMIA
Holetta Agricultural Research center, OROMIA
Jimma Agricultural Research center, OROMIA
Kulumsa Agricultural Research center, OROMIA
Melkassa Agricultural Research center, OROMIA
Chiro Agricultural Research center, OROMIA
Bako National Maize Research project, OROMIA

Assosa Agricultural Research center, BENISHANGUL

Pawe Agricultural Research center, BENISHANGUL
Tepi Agricultural Research center, SNNP
Mehoni Agricultural Research center, Tigrai
Forestry Agricultural Research center, AA

National Fish and other Aquatic lives Research center, AA
Fogera Rice Research and Training center, AMHARA

የፌደራል መንግስት አዳዲስ የግብርና ምርምር ተቋማት አማራ ክልል ውስጥ መገንባት አለበት።

(ማሳሰቢያ፤ በክልል ግብርና ቢሮ ሥር ያሉ የምርምር ተቋማት የሉበትም)።

የቤት እድሳቱ ላይ ላዩን ከሆነ የዉሸት እድሳት ነው (ግርማ ካሳ)

“ዛሬ በየቦታው የሞትና የመፈናቀል ዜና እየሰማችሁ ይሆናል። ሊታደስ እየፈረሰ ያለ ቤት ፍርስራሽ ስለሚበዛው በአከባቢው አቧራና የሚያውክ ነገር መኖሩ አይቀርም። እናንተ ግን ማወቅ ያለባችሁ ይህ እድሳት ተጠናቆ ውብ የሆነ ቤትና ውብ የሆነች ኢትዮጵያን የሚናስረክባችሁ መሆኑን ነው”

ይሄን ያለው ዶ/ር አብይ ነው። የሚሞቱትንና የሚፈናቀሉትን እንደ “ፍርስራሽ” ማስመሰሉ አልተመቸኝም። ሆኖም ግን ያለዉን በተግባር የሚያሳየን ከሆነ እሰየው ነው። ግን ይሄ ንግግሩ ከንግግር ያለፈ ይሆናል ብዬ አላስብም። በአንድ ትልቅ ዋና ምክንያት።

ቤት ከሚያፈርሱ ነገሮች አንዱ ምስጥ ነው። ኢትዮጵያን ሊያፈርስ ያለው ነገር፣ የኢትዮጵያ ምስጦች፡

– የጎሳና የዘር ፖለቲካው፣ 
– ዜግነትን ኢትዮጵያዊነትን ሳይሆን የብሄር ብሄረሰባ ሕዝብ የሚሉትን ወይም ዘርን ያንጸባረቀው ሕግ መንግስትና 
– ይሄ መሬት የትግሬ፣ ያ መሬት የኦሮሞ፣ እዚያ ማዶ የጉራጌ….በሚል፣ ዜጎች የከፋፈለው የጎሳና የዘር አወቃቀሩ 

ናቸው።

ዶ/ር አብይ እነዚህ ምስጦች ላይ ሳያነጣጥር፣ እንዴት አድርጎ ዜጎች በሁሉም የአገሪቷ ክፍለ በሰላም የሚኖሩባትን ዉብ ኢትዮጵያ እንደሚያስረከብን አላውቅም። እስክ አሁን ባለው ሁኔታ እነዚህን ምስጦችን ለማስወገድ፣ የዶ/ር አብይ አስተዳደር መሰረታዊ የሆኑ ለውጦችን ሊያሳይ እንደሚችል የሚያሳይ ምልክት አላየሁም። አዎን የአስተዳደር፣ የማንነትና የአከላለል ወሰኖችን የሚመለከት ኮሚሽን ተቋቁሟል።፡ሆኖም ይህ ኮሚሽን ሕገ መንግስቱን የሚያሻሻል ሳይሆን ለዜግነት ቦታ በማይሰጠው ሕገ መንግስት ላይ መሰረት በማድረግ አንዳንድ የአከላለል ማሻሻያዎችን ሊያደርጉ ይችላሉ። እንደዚያም ሆኖም አሁንም አከላለሉ የዘር ሆኖ ነው የሚቀጥለው። ያ ብቻ አይደለም፣ ኮሚሽኑ የሚያቀርበው ሪፖርት፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት በሚባለው ጸረ-ሕዝብና ጸረ-ዲሞክራሲያዊ አካል በኩል ነው የሚፈጸመው።

ብዙ ጊዜ በተለያዩ ጦማሮች እንደጠቀስኩት፣ አሁን ያለው ዘርን መሰረት ያደረገው ሕግ መንግስት ካልተሻሻለ፣ አሁን ያለው የጎሳ አወቃቀር ፈርሶ፣ ለአስተዳደር አመች የሆኑ፣ ዘርና ጎሳ ላይ ያላተኮሩ፣ ማንም ኢትዮጵያዊ ዘሩ፣ ሃይማኖቱ ሳይጠየቅ በሰላም መኖር፣ መማር፣ መነገድ፣ ኢንቨስት ማድረግ፣ ፣ መምረጥ፣ መመረጥ የሚችልበት ፌዴራል መስተዳድሮች እንዲፈጠሩና ዘር ክፖለቲካና ከአስተዳደር ከሕገ መንግስቱ እንዲወጣ ካልተደረገ ዉቢቷን ኢትዮጵያ አናያትም። 

የፈረሰውን ወይንም ሊፈርስ ያለውን ማደስ የተቀደሰ ተግባር ነው። ግን ለቤቱ መፈራራስ ምክንያት የሆነውን ሳይነኩ እድሳቱ ላይ ላዩ ከሆነ ግን እድሳቱ የዉሸት ነው።

ግልጽ ደብዳቤ ለግንቦት ሰባት አመራር አቶ ኤፍሪም ማዴቦ- ሙሉነህ እዮኤል

የግንቦት ሰባት ከፍተኛ አመራር የሆኑት አቶ ኤፍሬም ማዴቦ በትዊተር ገጻቸው በአርበኛ መሳፍንት ዙሪያ የጻፊትን ተከትሎ የተለያዩ አስተያየቶች እየተሰጡ ነው። ከተሰጡት አስተያየቶች መካከል ጦማሪ ሙሉነህ እዬኤል የሰጠው አስተያየት ይገኝበታል። “ተበዳዩን ከበዳዩ፤ ገዳዩን ከነፍሱ ተሟጋች እንዴት መለየት ተሳንዎት? የቆሰቆስከውን ሙቀው! ” በሚል ርእስ ጦማቲ ሙሉነህ ለአቶ ኤፍሬም ማዴቦ በጻፈው ግልጽ ደብዳቤ፣ አርበኛ መሳፍንት ተነጋረ የተባለውን ቆርጦ በማዳመጥ አስተያየት ከመስጠት ሙሉዉን ንግግር አቶ እፍሬም እንዲያዳምጡ በመጋበዝ ፣ ስለ አርበኛ መስፍንት ታሪክ በዝርዝር አስቀምጧል።

አቶ ሙሉነህ ” እንደ አይናችን ብሌን የምናየውን ለነፃነታችን፣ አሁን እርስዎም ለሚያጣጥሙት ነፃነት ባህር ማዶ እየተንፈላሰሰ ሳይሆን መሬታችን ላይ ከባዱን ትግል ተጋፍጦ ድል የነሳውን ጀግና መሳፍንትን ለመተቸት አንድም ይከብድዎታል ወዲያም ሲል እኛን ያነሳሳብዎታልና ይቅርብዎ። እግዜር ልቦናዎን ቀና ካስመለከትዎ ማስተካከያ ያድርጉ” ሲል አቶ ኤፍሪም ይቅርታ እንዲሉ ጠይቋል።

አቶ ኤፍሬም ድርጅታችው በይፋና በአደባባይ በዘር ከተደራጁ ከኦሮሞ ዴሞክራቲክ ግንባር፣ ከአፋርና ከሲዳማ ድርጅቶች፣ ከደሚት ጋር አብሮ እየሰራ፣ የኦሮሞ፣ የሲዳማና የአፋር ፣ የትግሬ ብሄረተኝነት ሳይቃወም፣ እንደዉም እየደገፈ፣ በአማራ ስር መደራጀቱን ሲያወግዝ እንደነበረ የሚታወቅ ነው።

ጦማሪ ሙሉነህ የጻፈውን እንደሚከተለው አቅርበናል፡

ይድረስ ለአቶ ኤፍሬም ማዴቦ
ተበዳዩን ከበዳዩ፤ ገዳዩን ከነፍሱ ተሟጋች እንዴት መለየት ተሳንዎት? የቆሰቆስከውን ሙቀው!
================
አቶ ኤፍሬም የግንቦት ሰባት ከፍተኛ የስራ አመራር ናቸው። በቲውተር ገፃቸው የጣፉት ጉዳይ እውን የሳቸው ይሆን ብየ ገባሁና አረጋገጥኩ። የሰነዘሩት አስተያየት የመልስ ምት የሚያሻው ነው።

መጀመርያ ስለ ጀግናው መሳፍንት በቅጡ አለማወቅዎት ያሳብቅብዎታል። ይህ ጀግና የላመ በልቶ የሞቀ ቤት እያደረ ወይም የከተሜ ኑሮ እየኖረ ሳይሆን ትክክለኛውን የአርበኝነት መራር ትግል የተጋተረና ያሸነፈ ነው!

ጀግናው መሳፍንት ከ20ኛው እድሜው ጀምሮ እዚህ ድረስ በትግል የዘለቀ ነው። ገና በሰባዎቹ ድፍን የቆላ ወገራ ህዝብ ተሃትን ሲጋተራት መሳፍንትም በኮበሌነቱ ሲታገል በጠላት እጅ ወድቆ ለሶስት አመታት በሽራሮ የመሬት ውስጥ እስር ቤት ስቃይ አይቷል። ከእስር አምልጦ ከወጣ ጀምሮም ዱር ቤቴ ብሎ ወያኔን ሲታገላት ኖሯል። በቅንጅት ጊዜ ሰላማዊ ምርጫ ይደረግ ሲባል ስመ ጥሩው መሴ በአካባቢው ምርጫ አሸንፎ ነበር። ኮሮጆ ሲገለበጥ የህዝብ ድምፅ ሳይከበር ሲቀር መልሶ በርሃ ገብቶ እስካሁኑ ጊዜ በትግል ባጅቷል። ይህን ተጋድሎ ማን አለፈበት? ይህንን ጀግና ለመተቸትስ ማንኛው የከተሜ “ታጋይ” ይቻለው ይሆን?

ስለ ጀግናው መሳፍንት በቀላሉ ዘርዝሬ አልዘልቀውም። ወደ እርሶ ጎልዳፋ መልእክት ልመለስ። “ትግሬ ይውጣ” አለ ነው ትችትዎ። ለማን አዛኝ የቅቤ አንጓች ለመሆን ነው ይህን አጣመው ያቀረቡት? ለመሆኑ የትኞቹ ትግሬዎች ይውጡ እንዳለ ሙሉ መልእክቱን ሰምተው ይሆን? ወይ አልሰሙም ወይም እንዳሰሙ ሆነዋል፤ ካልሆነም ገዳይ ትግሬም አይነካ ባይ ነዎት መሰል።

እግዜር ምክር ይለግስዎና ጋሸ መሳፍንት የተናገረውን ሙሉ መልእክት ደግመው ሰምተው ማስተካከያ ይስጡ። እኔ ምልዎት ግን በአማራው ሕዝብ ጉዳይ ድርጅትዎን ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባ አስተያየት በመስጠት የሚተካከልዎት ያለ አልመሰለኝም። ምናልባት ወቅት እየጠበቁ ጠቅ ከሚያደርጉ እንደ ተከዜ ማዶ ሰዎች በግላጭ ልክ ልካችንን ይንገሩንና እኛም ግር ሳይለን በመደብ እናስቀምጥዎታለን። ነገርን ነገር ያነሳዋልና የእርስዎ ድርጅት ሰዎች እንደዛሬው አያድርገውና ጀግናው መሳፍንት የከራረመበትን የውጊያ ጎራ የእኛ ነው እየተባለ ሲዘገብ እኛም በውስጥ የምትሰሙ መስሎን ተዉ እውነቱን እናውቀዋለን ብለናችሁ ነበር። የጋዜጠኛ ሲሳይ አጌናን አባባል ተውሰንም “የማናውቀውን እንድናምናቹህ የምናውቀውን አትዋሹን” ብለን ነበር። ከጋዜጠኛ መሳይ ጋር ጋሽ መሳፍንት በኢሳት ባደረገው ቃለ ምልልስ ስንለው የከረምነውን ሃቅ በአራት ነጥብ ደምድሞታል።

አቶ ኤፍሬም ለኤርትራ እና ለትግራይ ሕዝብ የሚያሳዩትን ተቆርቋሪነት ለአማራው እንዲያሳዩ መለመን ባያስፈልገንም ዝም ይበሉ። በነገርዎ ላይ እኔም ኢትዮጵያውያን በሙሉ በዜግነታቸው እኩል የሚተዳደሩባት የተከበረች ሃገር እንድትኖረን እጅጉን እመኛለሁ የወጣትነት እድሜየን በዛ መስመር እያሳለፍኩ ነው። ነገር ግን ከግራም ከቀኝም አማራን የጦስ ዶሮ የማድረግ ግልፅና ድብቅ ሴራ ልታገስ አልችልም።

ጋሽ መሳፍንት ወልቃይት ተወስዶበታል። ጠገዴ በርሃ ወርዶ ማረስ አይችልም። ሁመራ በወያኔ ሰፋሪዎች ተሞልታለች። ጠለምት እስከ ዋልድባ ገዳም ጭምር በወያኔ እብሪት ተወሮበታል። ቀን ይውጣልን ብለውም ይሁን በሌላ ስራ ምክንያት ጎንደርን ሃገር አድርገው የሚኖሩ ብዙ የኤርትራም የትግራይም ትግሬዎች ነበሩ አሉ። ታድያማ የወያኔ አለቅላቂ “የነበረው” ብአዴንን እያሽከረከሩ ህዝባችንን እጅግ ለከፋ ግፍ የዳረጉት ጉያችን ስር ያደጉ ትግሬዎች ናቸው። ስም ልጥራልዎት? እነ በረከት ስምኦን፣ እነ ካሳ ተክለብርሃን እያልኩ ልቆጥር አሰብኩና ከቀበሌ እስከ ክልል ያሉትን ቆጥሮ መዝለቅ አይቻልም። ከሸቀጣ ሸቀጥ እስከ ጅምላ አከፋፋይ፣ ከትላልቅ የኮንስትራክሽን ተቋራጭ እስከ አስተዳደር ጭምር ትግሬዎች የአማራን ክልል ሰንገው ይዘውታል።

የወልቃይትን ጉዳይ በብአዴን ስብሰባ ማንሳት እንዴት ሃጢያት እንደነበር የፖርቲው መሪዎች አሁን እየተናዘዙ ንስሃ እየገቡበት ነው። በአማራው ክልል ውስጥ ምን ያክሉ ቦታ በትግሬዎች ተሞልቶ እንደነበር የአዴፓ ወዳጅ ካለዎት ይጠይቁ።

እናማ ጀግናው መሳፍንት ለእነዚህ ጡት ነካሾች፣ ውለታ ቢሶች፣ ጀርባ ወጊዎች ግልፅ ምርጫ አቅርቦላቸዋል። ወያኔነትን ከመረጡ ተከዜን ይሻገሩ እንጅ ጉያችን ውስጥ ሆነው እየገደሉ እያስገደሉ መኖር አይቻልም። ጋሽ መሳፍንት የተናገረው እርስዎ መስማት ያልፈለጉት ለንፁህ ወንድም የትግራይ ህዝብ የተላለፈ መልእክት ግን አለ። ጋሽ መሳፍንት ሲጠቅስ ከትግራይ ህዝብ ችግር የለንም ወንድማማች ነን በመልካም ጉርብትና እንኖራለን ብሏል። ባጭሩ የጋሽ መሳፍንት መልእክት ለተስፋፊው ወያኔና ለግብረ አበሮቹ ነው። ጀግናው መሳፍንት አክሎ የተናገረው ከኢትዮጵያ ህዝብ ተዘርፎ ትግራይ ውስጥ ስለተከማቹት ፋብሪካዎችና ንብረት ነው። ወደ ህዝብ ይመለሱ ማለቱን እርስዎ አይደግፉም? እንዴት ነው ሁመራን የህወሃት የእርሻ ተቋም ድርጅት እየዘረፈ ይቀጥል የምንለው? ለመሆኑ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ በሞኖፖሊ የተቆጣጠሩት የህወሃት ድርጅቶች አይነኩ ባይ ነዎት እንዴ አቶ ኤፍሬም?

መደምደሚያ):- አቶ ኤፍሬም አጋጣሚ ያገኙ ሲመስልዎት አማራን ወጋ አደርጋለሁ ብለው ካሰቡ በግልዎም ሆነ በታቀፉበትም ድርጅት ኪሳራ እንጅ ትርፍ አያመጣም። እንደ አይናችን ብሌን የምናየውን ለነፃነታችን፣ አሁን እርስዎም ለሚያጣጥሙት ነፃነት ባህር ማዶ እየተንፈላሰሰ ሳይሆን መሬታችን ላይ ከባዱን ትግል ተጋፍጦ ድል የነሳውን ጀግና መሳፍንትን ለመተቸት አንድም ይከብድዎታል ወዲያም ሲል እኛን ያነሳሳብዎታልና ይቅርብዎ። እግዜር ልቦናዎን ቀና ካስመለከትዎ ማስተካከያ ያድርጉ። 
ሙሉነህ ዮሃንስ

ቢቢሲ – “ለረዥም ጊዜ ፖለቲካ ውስጥ የመቆየት ፍላጎት የለኝም” ፕ/ር ብርሃኑ ነጋ

አርበኞች ግንቦት 7 ሊቀመንበር የሆኑትና የምጣኔ ሀብት ባለሙያው ፕ/ር. ብርሃኑ ነጋን በጽህፈት ቤታቸው አግኝተናቸው በወቅታዊ የሀገሪቱ ጉዳዮች ላይ ቆይታ አድርገናል።

ቢቢሲ አማርኛ፡ አንዳርጋቸው ታፍኖ መወሰዱን ባወቅክባት ቅፅበት ምን ተሰማህ?

ፕሮፌ. ብርሃኑ ነጋ ፡ አንዳርጋቸው የተያዘ ጊዜ ኒው ዮርክ ነበርኩ። እንደተያዘ እዚያው የመን እያለ ነው የሰማሁት፤ በተያዘ በግማሽ ወይንም በአንድ ሰዓት አብረው ሲበሩ ከነበሩ ሰዎች ውስጥ ነው የሰማሁት። እዚያ ያሉ እኛን የሚያውቁ ሰዎች እንደዚህ አይነት ነገር አለ ተከታተሉ ብለው የነገሩን ያኔ ነው።

በዚያ በኩል እንደሚሄድም አላውቅም ነበር፤ በሌላ በኩል እንደሚሄድ ነበር የማውቀው። ያው መጀመሪያ ላይ ትደነግጣለህ። የመጀመሪያ ሥራህ የሚሆነው ወደ ኢትዮጵያ እንዳይሄድ ወይንም ችግር እንዳይደርስበት ማድረግ የሚቻለውን ለማድረግ ለተለያዩ መንግሥታት፣ አቅም ላላቸው ሰዎች፣ መንገርና አንድ ነገር እንዲያደርጉ መሞከር ነበር።

ቢቢሲ አማርኛ፡ እርሱ እስር ቤት በነበረበት ወቅት እርሱን በተመለከተ ምን አይነት ስሜቶችን አስተናገድክ?

ፕሮፌ. ብርሃኑ ነጋ፡ ከአንዳርጋቸው ጋር ለረዥም ጊዜ ነው የምንተዋወቀው። ብዙ አውርተናል። ምን እንደሚፈልግ አውቃለሁ። እኔም ምን እንደምፈልግ ያውቃል። ሲታሰር የተወሰነ የድርጀቱን ሥራ ኃላፊነት እርሱ ስለነበር የወሰደው ኢትዮጵያ መምጣቱን ካወቅሁ ጊዜ ጀምሮ ለእኔ ግልፅ የሆነልኝ በምንም አይነት እንደማይፈቱት፣ እንደማይገድሉትም አውቅ ነበር።

ጥያቄው ያለው እንዴት ታግለን ቶሎ ይህንን ነገር እናሳጥራለን የሚል ነው። ከዛ በኋላ ብዙ ጊዜ አልፈጀብኝም ሥራዬን ሁሉ ትቼ እርሱ የጀመራቸውን ሥራዎች ወደ መቀጠል ነው የገባሁት። በእንዲህ አይነት የትግል ወቅት አንዳርጋቸው ሲታሰር ምን ይፈልጋል? ማንም ሰው ቢለኝ፤ የታገለለትን አላማ ከዳር እንድናደርስለት ነው እንጂ የሚፈልገው ሌላ ለግሉ እንዲህ አይነት ነገር ይደርስብኛል የሚል የስሜት ስብራት ውስጥ እንደማይገባ አውቅ ስለነበር፤ ያለኝን ጠቅላለ ጉልበቴን ያዋልኩት እንዴት አድርገን ይህንን ትግል በቶሎ ገፍተን እርሱንና በየቦታው የሚታሰሩትን ጓዶቻችንን ነፃ እናወጣለን ወደ ሚለው ነው።

ከዚያ ባሻገር ግን የታገልንለትን አላማ፣ ኢትዮጵያን ዲሞክራሲያዊ የማድረግ አላማ፣ ከዳር እንዴት እናደርሳለን የሚለው ነው፤ ከዚያ ውጪ ሌላ አልነበረም። ከመጀመሪያው አንድ ቀን ሁለት ቀን ውጪ ጠንካራ የሆነ የስሜት መዋዠቅ ውስጥ መግባት አይገባም ብዬ ነው ለራሴ የነገርኩት።

አሁን ሥራው ይህንን ነገር ከዳር ማድረስ ነው። በእንዲህ አይነት ትግል ውስጥ ችግሮች ይፈጠራሉ፤ ግን እያንዳንዱ ችግር ላይ ከፍተኛ የሆነ የስሜት መዋዠቅ ካስቀመጥክ ሥራ አትሰራም። ሁሉን ነገር ዘግቼ ይህንን ነገር እንዴት ከዳር እናደረሳለን የሚለው ላይ ነው ጊዜዬን ያጠፋሁት።

ቢቢሲ አማርኛ፡ አሁን ያለው ለውጥ የሚሾፈረው በኢህአዴግ መሆኑ ምን አይነት ስሜት ነው የሚፈጥረው?

ፕሮፌ. ብርሃኑ ነጋ- አንዱ ትልቁ ጥያቄ ኢህአዴግን የምናየው የድሮው ኢህአዴግና የአሁኑ ኢህአዴግ አንድ ነው፤ ወይንስ ቢያንስ ያንን ለውጥ ካመጡ ሰዎች በኋላ በመሰረታዊ መልኩ ለውጥ አድርጓል የሚለውን መመለስ አለብህ።

የትግል ለውጥ ስትራቴጂ ለውጥ ስናደርግ የወሰንነው ይህንን ለውጥ ለማምጣት የመጡት ሰዎችን፤ በእንዲህ አይነት የተቃውሞ ፖለቲካ ውስጥ ስትሆን አንዱ ሥራህ የመንግሥት ስልጣንን በያዘው ኃይል ውስጥ ያለውን ነገር ማጥናት ነው።

ስለዚህ በኢህአዴግ ውስጥ የሚደረጉትን ለውጦች እንከታተል ነበር፤ እና አንዱ ትልቁ ጥያቄ የነበረው እነ ዐቢይ ሲመጡ ኢህአዴግን በአዲስ መልኩ ለማስቀጠል የመጡ ሰዎች ናቸው ወይንስ እውነተኛ ለውጥ ፈልገው የመጡ ናቸው የሚለውን መመለስ ነበር። እነዚህ ሰዎች ዝም ብሎ በፊት የወያኔ ሥርዓት ይከተል የነበረውን ነገር ለማስቀጠል የሚያስቡ ሰዎች እንዳልሆኑ ስንረዳ ብዙ ጊዜ አልወሰደብንም።

ምክንያቱም በከፊል የመጡትም በህዝብ ትግል ነው። ሀያ ምናምን ዓመት ያልተቋረጠ ትግል ሲካሄድበት የነበረው ከዛም ሦስት ዓመት ደግሞ ያላቋረጠና የተጋጋለ ሰፊ የህዝብ ትግል ሲካሄድበት የነበረው ነው። ኢህአዴግ በነበረበት ሊቀጥል እንደማይችል ግልፅ የሆነበት ጊዜ ነው። በዚያን ጊዜ የመጡት እነዚህ ሰዎች ኢህአዴግን ሸውደን ሌላ አዲስ መልክ አምጥተን እናስቀጥል ብለው የሚያምኑ ሳይሆኑ በርግጥም የበፊቱ ሥርዓት ተሸንፎ የመጡ ናቸው።

ይህንን አንዴ ከወሰንክ በኋላ፣ ተጋግዘህ ያንን ሥርዓት ለማቆም ትሞክራለህ እንጂ በፊት የነበሩት ሰዎች እንዲህ ነበሩና በመሳሪያ ልቀጥል የምትለው ነገር አይደለም። እኛ በምንም አይነት፣ መቼም ቢሆን የመሳሪያ ትግልን እንደጥሩ ነገር አድርገን ገብተንበት አናውቅም። ምርጫ አጥተን የገባንበት ነው። ያን አላስፈላጊ የሚያደርግ ነገር ሲፈጠር ደቂቃም አልፈጀብንም። ተመልሰን ወደ እውተኛ ሰላማዊ እንቅስቃሴ፣ ወደ እውነተኛ ዲሞክራሲያዊ መንገድ መሄድ የተሻለ ነው ብለን ነው የገባንበት።

በኢህአዴግ ውስጥ ወጥ ነው ማለት ባይቻልም ለውጡን ይዘው የመጡት ኃይሎች በርግጥም ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚፈልጉ መሆናቸውን እናምናለን። ያንን ሥርዓት ለማምጣት ከእነርሱ ጋር አብረን እንሰራለን፤ ከዚያ በኋላ ኢህአዴግ ካሸነፈ፤ እኛ እኮ በፊትም ኢህአዴግ ለምን አሸነፈ አይደለም፤ የሕዝብ ፍላጎት የህዝብ ፈቃድ አግኝቶ ያሸንፍ ነው የምንለው።

ማንም የህዝብ ፍቃድ አግኝቶ ያሸንፍ የህዝብ መብት ይከበር፣ ሰብዓዊ መብቶች ይከበሩ። የህግ ልዕልና ይኑር። እነኚህ ናቸው ጥያቄዎቹ። ማን ስልጣን ያዘ አይደለም። ዋናው ጥያቄ በምን መልክ ስልጣን ይያዛል? የህዝብ ፈቃድ አግኝቶ ነወይ? ህዝብ በፈለገ ጊዜ ሊያወርደው የሚችል ነወይ? ከዛ በተጨማሪ ደግሞ እውነተኛ ነፃ የሆኑ ተቋማት አሉ ወይ? ፍርድ ቤቱ በነፃነት ይሰራል ወይ? ጦር ኃይሉ በርግጥም ህብረተሰቡን የሚጠብቅ ነው ወይስ የአንድ ፓርቲ መሳሪያ? የምርጫ ተቋሞቹ እርግጥም ነፃና የህዝብ ፍላጎት የሚንፀባረቅባቸው ምርጫዎች ለማድረግ ፈቃደኞች ናቸው? እነዚህ ናቸው ጥያቄዎቹ። ያንን ለማድረግ ፍላጎት ያለው አካል እስከመጣ ድረስ እኛ ምንም ችግር የለብንም።

ቢቢሲ አማርኛ፦ ሥርዓቱን ሰው ባይጥለው ኢኮኖሚ ይጥለዋል ትል ነበር። አሁን ያለውንስ መንግት?

ፕሮፌ. ብርሃኑ ነጋ፡ ይኼ አዲሱ የለውጥ ኃይል ከነበረው የወጣ ነው ብለህ ብታስብ፣ ፕሮፓጋንዳውን ምናምኑን ትተህ የተረከበው ኢኮኖሚ ደንበኛ የዝርፊያ ሥርዓት የሽፍታ ኢኮኖሚ ሥርዓት ነበር። ዝም ብለህ ያገኘኸውን ዘርፈህ የምትሄድበት። የነበሩትን ፕሮጀክቶች ይካሄዱ የነበሩትን እንዳለ ብታይ ከዝርፊያ ጋር የተያያዙ ናቸው።

የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ምናምን ብለህ አንድ ጤነኛ ሰውና ስለከተማ ትራንስፖርት የሚያውቅ ሰው እንዲህ አይነት የከተማ ትራንስፖርት፣ በዚህን ያህል ወጪ አውጥቶ አይተክልም ነበር። በጣም ቀላል የሆኑ፣ በቀላሉ የከተማዋን የትራንስፖርት ችግሮች የሚፈቱ፣ እንደዚህ ከተማዋን ለሁለት ከፍለህ አስቀያሚ ሳታደርገው ልትፈታ የምትችልባቸው መንገዶች ነበሩ።

ፕሮጀክቶቹ በአንድ መልኩ ወይም በሌላ ለመስረቂያ ተብለው የተዘረጉ ናቸው። ለዚህ ነው ማለቅ ያልቻሉት። ለዚህ ነው ከአስር ከሃያ እጥፍ በላይ ወጪ የሚያስወጡት። እነኚህ ሁሉ የሆኑት ደግሞ በሕዝብ ስም በሚገኝ ብድር ነው። ይህ ሁሉ ብድር ሀገሪቱ ላይ ተከምሮ ወደ ሰላሳ ቢሊየን ዶላር ብድር ያለባት ሀገር ነች።

ይህ የሆነው ያ ሁሉ ብድር ከተሰረዘ በኋላ፣ በተለይ ከምርጫ 97 በኋላ የመጣ ይህንን የዘረፋ ሥርዓት ለማቆየት የተዘረጋ ሥርዓት ነው። ይኼ ነገር መጥቶ መጥቶ በተወሰነ ደረጃ ኢኮኖሚውን ዝም ብሎ ያራግበዋል። ምክንያቱም ዝም ብሎ ገንዘብ ኢኮኖሚ ውስጥ ስላለ። በኋላ ላይ ግን ተንገራግጮ መቆሙና ችግር ውስጥ መጣሉ የማይቀር ነው። እና በዚህ ምክንያት ይህንን ሥርዓት የተረከቡት ሰዎች በጣም ከባድ የሆነ ችግር ይገጥማቸዋል። አንደኛው እዳውን መክፈሉ፤ ሁለተኛ በአጠቃላይ የንግድ ሥራን በሚመለከት ያለው ባህል ተበላሽቷል። ሁሉም በስርቆት በማጭበርበር በምናምን አገኛለሁ ብሎ የሚያስብ የኢኮኖሚ ክላስ ነው የተፈጠረው።

ሀብታም የሚባሉትን፣ በአጭር ጊዜ ቢሊየነር ሚሊየነር ሆኑ የሚባሉትን፣ አይነት ግለሰቦችን ብታይ ቁጭ ብለው አስበው ምን ያዋጣል ለህብረተሰቡ የተሻለ እቃ እንዴት እናቅርብ በማለት አይደለም። ወይ መሬት ዘርፈው፣ ወይ ከባንክ ገንዘብ ተበድረው ያገኙት ነው። በዚያ አይነት መሰረት ላይ የቆመ ኢኮኖሚ ሁል ጊዜ ችግር ይገጥመዋል። ይህንን ሁሉ መቀየር በማክሮ ኢኮኖሚ ደረጃ ያሉብህን ችግሮች መፍታት ብቻ ሳይሆን የንግድ አመለካከቱን ባህሉን ራሱ መቀየር በጣም ሰፊ ሥራ የሚጠይቅ ነገር ነው።

ይህንን ለማስተካከል ግን በመጀመሪያ የፖለቲካው ሥርዓቱ መስተካከል አለበት። ከዚያም ባሻገር ግን ሰላምና መረጋጋቱ ወዲያውኑ መምጣት አለበት። ይህንን የፖለቲካ ነገር ሳታስተካክል የኢኮኖሚውን ነገር ማስተካከል ከባድ ነው። ለዚህ ነው ቅድሚያ የፖለቲካ ማስተካከያዎች መወሰድ ያለባቸው እንጂ፤ ቶሎ ብሎ የእነዚህን የኢኮኖሚ ችግሮች አንድ በአንድ መመልከት ግዴታ ነው። መንግሥትም ይኼን ይገነዘባል ብዬ አስባለሁ። የለውጥ ኃይልም ስለሆነ ከሌሎችም ሀገሮች በተወሰነ መልኩ እዳውን ለመቀነስ ትብብር ያገኛል ብዬ አስባለሁ። ምንም እንኳ ፖለቲካውን የመፍታት እርምጃ መውሰድ ቀዳሚ ቢሆንም የኢኮኖሚውንም ችግር ለመፍታት በአንድ ላይ እርምጃ መወሰድ አለበት።

ቢቢሲ አማርኛ-አንዳንድ የተወረሱብህን ንብረቶች ለማስመለስ ሞክረሃል?

ፕሮፌ. ብርሃኑ፡ እስካሁን አልተመለሱም። ይኼ ለውጥ ስለእኔ አይደለም። 100 ሚሊየን ህዝብ የሚበላው ያጣ ያለበት ሀገር አሁን የእኔን ንብረት መለሱ አትመለሱ በጣም ትልቅ ነገር አይደለም።

ቢቢሲ አማርኛ- ከኢኮኖሚ ውጪ የአብይ አስተዳደር ትልቁ ፈተና ከየት ይመጣል?

ፕሮፌ. ብርሃኑ፡ የደህንነት፣ ሰላም የማረጋጋት፣ ባለፈው27 ዓመት የተፈጠረው የክልል አደረጃጀት። የክልል አደረጃጀቱ ደግሞ ዝም ብሎ በዘር ላይ፣ በደም ቆጠራ ላይ መመስረቱ ብቻ አይደለም። በዚያ ላይ የተመሰረተው አከላለል የራሱ ጦር ያለው አገር ነው። አሁን እነዚህ ክልሎች የምትላቸው የራሳቸው ሀያ ሺህ፣ ሰላሳ ሺህ. . . ጦር አላቸው የሚባል ነው።

በአንድ ሀገር ውስጥ እስከ አፍንጫቸው የታጠቁ ክልሎች ሊኖሩ አይገባም። በአንድ ሀገር እንደዚህ አይነት ኃይል ሊኖር የሚገባው የመንግሥት መከላከያ ነው። ለሁሉም እኩል የሆነ፣ ሁሉንም በጋራ የሚያገለግል፣ የሁላችንንም ደህንነት የሚጠብቅ ኃይል። አሁን ግን በሁሉም ክልሎች ያሉ ኃይሎች አሉ።

እነዚህን ሁሉ እንዴት አድርጎ በአንድ ሀገራዊ የመከላከያ እዝ ስር ታደርጋቸዋለህ? በየአካባቢው ከብሔር ጋር በተያያዘ የተነሱ ግጭቶችን እንዴት ታስቆማቸዋለህ? እንደ አገር ወይ ከዚህ ችግር ወጥተን እንበለፅጋለን። ወይ እንደሃገር እንፈርሳለን። የተወሰነ ቡድን አልፎለት፣ ሌላው የማያልፍለት አገር ሊኖረን አይችልም።

ሁላችንም ተሰባስበን የምንኖርባት፣ የሁላችንም መብት የተከበረባት፣ የሁላችንም ባህል የሚከበርባት፣ የሁሉም ቋንቋ የሚከበርባት የተረጋጋች ሀገር መፍጠር በጣም ከባዱ ከእነ ዶ/ር አብይ ብቻ ሳይሆን ሁላችንም ይሄንን ዲሞክራሲያዊ ስርዓት በመገንባት ሂደት ላይ የሚገጥመን ችግር ነው።

ነገር ግን በደንብ መነጋገር ከቻልን በማስፈራራት ሳይሆን ቁጭ ብለው እየተነጋገሩ ህብረተሰቡ ያሉትን አማራጮች እየሰማ የምንነጋገርበት አይነት የፖለቲካ ምህዳር መፍጠር ከቻልን፣ የፖለቲካ ድርጅቶች በምን አይነት የፖለቲካ ሂደት ፖለቲካቸውን እንደሚያስተዋውቁ በደንብ ከተስማሙና ሁሉም ለዚያ ታማኝ ከሆኑ የምንወጣው ችግር ነው። የሚያቅተን አይደለም። አሁን ብዙ ችግር ያለ ይመስላል። ነገር ግን እነዚህን መሰረታዊ ነገሮች ማስተካከል ከቻልን ወደዚያ እንሄዳለን። ግን ትልቁ ተግዳሮት አሁን ያለው ግን ይኼ ነው። ፖለቲካውን ማረጋጋት፣ ፖለቲካውን ወደ ሰለጠነ ፖለቲካ መውሰድ ትልቁ ተግዳሮት ነው የሚመስለኝ።

ቢቢሲ አማርኛ፦ አሁን ያለው የሀገሪቷ ነባራዊ ሁኔታ አንተ ስትሄድ ከነበረው በበለጠ የብሔርተኝነት ስሜት ናኝቶ በኦሮሚያና በአማራ ክልል አንዳንድ ቦታዎች ተቃውሞ ሲገጥማችሁ እያየን ነው። እንዲህ ባለው ሁኔታ የድጋፍ መሰረታችን የት ነው የምትሉት?

ፕሮፌ. ብርሃኑ፦ ሁለት ነገር ማንሳት እፈልጋለሁ። አንደኛ ለእኛ የሚያሳስበን ነገር ምን ያህል የፖለቲካ ድጋፍ የት እናገኛለን የሚለው አይደለም። ትልቁ የሚያሳስበው ጥያቄ ይህችን አገር እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ አገር ማድረግ ላይ ነው። ትልቁ ጉልበታችንን የምናፈስበት ጉዳይ እሱ ነው። ሁለተኛ አንድ ነገር እውነታ ሆኗል ማለት አይቀየርም ማለት አይደለም። ኢትዮጵያ እኮ ደሃ ሀገር ነች። ይሄ እውነታ ሁሌም ደሃ አገር ያደርጋታል ማለት አይደለም።

የተለያዩ ፖሊሲዎችንም ያረቀቅነው ይህንን እውነታ ለመቀየር ነው። የኢትዮጵያም የፖለቲካ እውነታ በአብዛኛው ለ27 ዓመት ይሰማው የነበረ ፕሮፓጋንዳ ምክንያት ብሔር ብሔረሰቦች ስሜት ውስጥ ገብተዋል ከሆነ አንደኛ ቁጥሩ ላይ መስማማት አንችልም። ምክንያቱም በተጨባጭ የምናውቀው ነገር የለም። ምን ያህሉ ሰው በዜግነት ፖለቲካ ያምናል? ምን ያህሉስ በብሔር? የሚለው ሁኔታ ላይ በተጨባጭ የተሰራም ሆነ የተሰበሰበ ጥናት የለም።

በአብዛኛው ልኂቅ በብሔር ፖለቲካ ውስጥ እንደተዘፈቀ ግልፅ ነው። ህብረተሰቡ ገብቷል ወይ? የሚለው አጠራጣሪ ነው። ሁለተኛ ብዙ ሰው ዘንግቶታል እንጂ በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ ኢትዮጵያ ማህበረሰቧ የተደባለቀ ነው። ንፁህና ያልተቀላቀለ ማህበረሰብ ለማግኘት አዳጋች ነው። ሦስትና አራት ትውልድ ብንቆጥር ሁላችንም ከተለያየ ብሔር ጋር የተደባለቅን ነን። እሱ ቀርቶ በአንድ ትውልድ እንኳን አባት አንድ ብሔር እናት ሌላ ብሔር ሆና የተወለደው በትክክለኛ መንገድ ቢቆጠር ከማንኛውም ከአንድ ብሔር ነኝ ከሚለው የሚበልጥ ይመስለኛል።

ይሄ ሁሉ ከዚህ የብሔር ፖለቲካና ከመጣው ግጭት መውጣት የሚፈልግ የማህበረሰብ አካል ነው። እኛ የምንለው አንደኛ እነዚህ ሃሳቦች በነፃነት የሚገለፁበት፣ ህብረተሰቡ ከስሜት ወጥቶ ለአገራችን፣ ለህዝባችን፣ ለራሳችን የሚጠቅመን የቱ ነው ብሎ በደንብ ማሰብ በሚጀምርበት ጊዜ እነኚህ ነገሮች ይቀየራሉ። የፖለቲካ ስሜት የማይቀየር በድንጋይ ላይ የታተመ ነገር አይደለም። ሁልጊዜም ይቀያየራል።

ከአርባ አመት በፊት ሁላችንም ሶሻሊስቶች ነበርን። የሶሻሊዝም ርዕዮተ ዓለም በተግባር ሲታይ ምን እንደሆነ ካየ በኋላ ነው ሰው ሁሉ የሚያዋጣ አለመሆኑን ተረድቶ የተቀለበሰው።

ከ27 ዓመት በፊት ይሄ የዘር ፖለቲካ ሲመጣ፤ ብሔር ብሔረሰቦች በሰላም የሚኖሩበት ብልፅግና ያለበት ሁሉም እኩል የሚሆንበት ተብሎ ነበር። አሁን ስናየው ግን ሰላምና እኩልነት የሌለበት፣ ብሔርና ብሔረሰቦች ራሳቸውን ማስተዳደር ያልቻሉበት፣ የውሸት እንደሆነ ማህበረሰቡ ተገንዝቦታል።

አሁን እንግዲህ መጪውን ጊዜ ሰው ቁጭ ብሎ ማሰብ የሚጀምርበት ጊዜ ነው። በነፃነት ማሰብ፣ መወያየትና ሃሳቦቹን ለህብረተሰቡ ማቅረብ ከቻልን እኔ ብዙሃኑ ኢትዮጵያዊያን በዜግነት ላይ የተመሰረተ ፖለቲካ ይመርጣሉ ብዬ አስባለሁ። ስለዚህ አያስፈራኝም!

ስለዚህ ትልቁ ነገር እኛ እንደ ፓርቲ ምን ያህል ድምፅ እናገኛለን፣ የቱጋ እናሸንፋለን የሚለው አይደለም፤ ጥሩ የፖለቲካ ምህዳር ተፈጥሮ ሁሉም ሃሳቦች በነፃ የሚንሸራሸሩበት፤ በውሸት ስሜት ህብረተሰብን ማነሳሳት የሚቀርበት ሁኔታ እንዲፈጠር እንፈልጋለን።

ስሜት፣ መገፋፋትና ዘላቂ ጥቅምህን ማወቅ የተለያዩ ነገሮች ናቸው። ቀስ ብለው ሰዎች መወያየት ሲጀምሩም ነው ለእኔ፣ ለቤተሰቤ የሚበጀኝ፤ ዘላቂ ጥቅሜ ምንድን ነው? ብለው ማሰብ የሚችሉት። በዚያ ጉዳይ ላይ የዜግነት ፖለቲካ ከምንም ነገር በላይ ለዚች ሀገር ዘላቂ ሰላምና ብልፅግና መሰረት እንደሆነ ጥያቄ የለንም። ለዚሀም ነው ዛሬ ባይሆን መቼም ወደፊትም የዜግነት ፖለቲካ የበላይነት ጥያቄ ውስጥ የማናስገባው።

ቢቢሲ አማርኛ፡ ኤርትራ ውስጥ ስትንቀሳቀሱ በነበረበት ወቅት ከኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ጋር የነበራችሁ ግንኙነት ምንድን ነው?

ፕሮፌ. ብርሃኑ፡ ኤርትራ በነበርንበት ጊዜ ከኦሮሞ ነጻነት ግንባር አመራር ጋር ተገናኝተን አናውቅም። ከኦሮሞ ነጻነት ግንባር አባላት ጋር [ማለትም] ከተራ አባላት ጋር በአንድ ወይም በሌላ ምክንያት ከተለያዩ ሰዎች ጋር እንገናኛለን። ከኦሮሞ ነጻነት ግንባር የመጡ ብዙ የኦሮሞ ተወላጅ አባሎች ነበሩን፤ አሉን።

ከብሔር ውጪ የሆነ ለሁሉም ኢትዮጵያዊ ክፍት የሆነ ድርጅት ስለሆነ ከየትም አማራም፣ ትግሬም፣ ኦሮሞም የሚገባበት ድርጅት ነው። ብዙም ችግር ስላልነበረ ብዙ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ታጋዮች የነበሩ አባሎች ነበሩን። እኛም ጋር አባል ሳይሆኑ ኤርትራ ውስጥ ይኖሩ የነበሩ ብዙ የኦሮሞ ወገኖቻችን ጋር በጓደኝነት፣ በወዳጅነት ስንሠራ ነበር።

ከኦነግ ከወጡት ከእነ ከማል ገልቹ፣ ኮለኔል አበበ ጋር ብዙ ጉዳዮች ላይ አብረን እንወያያለን። ለሀገራችን የሚሻለው ምንድን ነው? የሚሉ ነገሮች ላይ እንወያያለን። እንደ ድርጅት ከዚህ በፊት ጀምሮና እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስም ከሌሎች የኦሮሞ ድርጅቶች ጋር አብረን እንሠራ ነበር። ከኦሮሞ ዲሞክራቲክ ፍሮንት ጋር በጋራ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ንቅናቄ የሚል ፈጥረን ስንንቀሳቀስ ነበር። ከነከማል ገልቹ ጋርም ተመሳሳይ ነበር።

ስለዚህ ለእኛ ኦሮሞ ሆነ፣ ትግሬ ሆነ፣ አማራ ሆነ፣ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ነው። እንደ ድርጅት የሀገሪቱን አንድነትና ለሁሉም ሕዝቦቿ እኩል የሆነች ሀገር እንድትሆን የሚፈልግ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ጋር አብረን እንሰራለን። አሁንም የኦሮሞ ወገኖቻችን ድርጅታችን ውስጥ አባል ናቸው።

አሁን ካለው በአቶ ዳውድ ኢብሳ ከሚመራው ኦነግ ጋር ኤርትራ ከገባን ሳይሆን ከሰባት፣ ስምንት ዓመት በፊት እንዴት በጋራ አብሮ እንደሚሠራ ውይይት ነበረን። ከዚያ በኋላ እዛም ውስጥ ችግሮች ነበሩ። እኛ ከበፊትም የነበረን ግልጽ የሆነ አንድ አቋም ነው። ለአገር አንድነት ቅድሚያ መስጠት አለብን። እንደ ሀገር አንድ ካልሆንን በጋራ ፖለቲካ መሥራት አንችልም የሚል አቋም ነው። ከማንኛውም ድርጅት ጋር ስንሠራ የምንለው በኢትዮጵያ ሀገራዊ አንድነት ታምናለህ? በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ታምናለህ? ነው። ከዚያ በኋላ ሌላውን ውይይት ማድረግ፤ መደራደርም እንችላለን።

ለመጨረሻ ጊዜ አቶ ዳውድን ያገኘሁት ወደ ኤርትራ ለአንድ ጉዳይ ስመለስ ኤርፖርት ውስጥ ነው። ሰላም እንባባላለን። እዚህም ተገናኝተናል። በፖለቲካ ፓርቲ ድርጅቶች ውይይት ውስጥ ገንቢ የሆነ ውይይት እናደርጋለን ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ። ይቺ አገር የጋራችን ነች። ለሁላችንም የምትሆን ሀገር መፍጠር ነው። የተሻለ ሀሳብ አለን የሚሉ ሀሳባቸውን ለማኅበረሰቡ አቅርበው በዚያ በሚደረግ ውይይት ሕዝብ የመረጠውን መቀበል ግዴታችን ነው።

ሁላችንም መረዳት ያለብን በአንድ ሀገር ውስጥ ሦስት ወይም አራት የታጠቁ ኃይሎች ሊኖሩ አይችሉም። ፖለቲካ እንደዛ ሊሆን አይችልም። በሰላማዊ መንገድ ፖለቲካችንን እንሠራለን ብለን ካሰብን፤ ሁላችንም መሳሪያ አውርደን እንገባለን ነው ያልነው። ስለዚህ አውርደን በሰላማዊ መንገድ ፖለቲካው ውስጥ ገብተን ለሀገራችን ይበጃል የምንለውን ለኅብረተሰቡ አቅርበን ሕዝቡ የሚወስነውን መቀበል ነው።

ቢቢሲ አማርኛ፡ ፕሬዘዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ለመጨረሻ ጊዜ ያገኘሀቸውስ መቼ ነው?

ፕሮፌ. ብርሀኑ፡ መጨረሻ የተገናኘነው ነሀሴ ላይ ነው። ወደዚህ ከመምጣቴ በፊት ለመሰነባበት ተገናኝተን በሀገራችን በአካባቢያችን ጉዳዮች ላይ አውርተናል።

ቢቢሲ አማርኛ፡ ምን አይነት ግንኙነት ነበራችሁ?

ፕሮፌ. ብርሀኑ፡ እሳቸው ፕሬዘዳንት ናቸው። እኔ አንድ ታጋይ ነኝ። ስለዚህ ምን ግንኙነት ይኖረናል? አንዳንድ ጊዜ እንገናኛለን። በሀገርና በአካባቢ ጉዳይ እናወራለን። ግን ከእሳቸው በታች ያሉ በእኛ ሥራ ዙሪያ አብረናቸው የምንሠራ ሌሎች ሰዎች አሉ። ፕሬዘዳንቱ ፕሬዘዳንት ናቸው፤ በየጊዜው እየሄድኩ እሳቸውን የማገኝበት ሁኔታ የለም።

ቢቢሲ አማርኛ፡ለወደፊት ጡረታ ወጥተህ ምናልባት በሲቪል ወይም በቢዝነስ ዘርፍ ስትሳተፍ ራስህን ታያለህ?

ፕሮፌ. ብርሀኑ፡ በጣም አያለሁ። የጀመርነው፣ በጣም ብዙ ሰው የሞተበት፣ የተጎዳበት፣ ይቺን ሀገር ዴሞክራሲያዊ የማድረግ ነገር በደንብ መሰረት ከያዘ በኋላ ለረዥም ጊዜ ፖለቲካ ውስጥ የመቆየት ፍላጎት የለኝም። በ94 [በአውሮፓውያኑ] ስመጣም ፖለቲካ ውስጥ ልገባ አልነበረም። አስተምር ነበር። በኢኮኖሚው ዙሪያ እሳተፍ ነበር። ጋዜጦች ላይ እጽፍ ነበር። የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ማኅበር ውስጥ እሠራ ነበር። ፖለቲካ የሚባል ነገር ውስጥ ተመልሼ እገባለሁ አላልኩም።

በልጅነቴ ኢሕአፓ ውስጥ ከገባሁ በኋላ ተመልሼ [ፖለቲካ ውስጥ] እገባለሁ ብዬ አላሰብኩም ነበር። በአንድ መልኩ ወይም በሌላ ፖለቲካ ውስጥ መልሶ ያስገባኝ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ውስጥ ለተማሪዎች ስለ አካዳሚክ ነጻነት ንግግር ካደረግን በኋላ ከፕሮፌሰር መስፍን ጋር ስንታሰር ነው። እንዲህ አይነት ሥርዓት ካለ፣ ነጻነት ከሌለ፣ በነጻነት መነጋገር ካልተቻለ ሌሎች የሚሠሩ ሥራዎችም የውሸት ይሆናሉ።

አካዳሚሽያን [ትምህርታዊ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩር ባለሙያ] ነኝ፣ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ውስጥ አስተምራለሁ ብለህ ነጻነት ከሌለህ፣ የምታስተምረውን ነገር በነጻነት ማስተማር ካልቻልክ፤ የምታስተምረው በተወሰነ ደረጃ የውሸት ነው የሚሆነው። የፖለቲካ ሥርዓቱ ለፖለቲካ ስልጣን ሳይሆን ለዕለት ተዕለት ሥራዎች እንኳ በእኩልነት ላይ የተመሰረተ አይደለም።

ባለፈው 27 ዓመት ውስጥ ነጋዴ ብትሆን የሚያሳብድ ነው የሚመስለኝ። ንግድ ማለት የውድድር ቦታ ከሆነ፤ የኢኮኖሚው ሥርዓት ሙሉ በሙሉ በአድልዎ ላይ የተመሰረተ ከሆነ ምንም ልትነግድ አትችልም። አንተንም ከፀባይህ አውጥተው እንደነሱ አጭበርባሪ ሆነህ የምትኖርበት ሁኔታ ነው የሚፈጠረው።

እንደ አንድ እውነተኛ ዜጋ ለመኖር የፖለቲካ ምህዳሩ ነጻነትህን የሚያከብር፣ በማኅበረሰቡ ውስጥ ሀሳብህን በነጻነት መግለጽ መቻልህ፣ በምትሠራው ሥራ ጣልቃ የማይገባ መሆኑ አስፈላጊ ነው። ከብዙ ሰዎች ጋር የምለየው በዚህ ነው። እነሱ ይሄ ፖለቲካ ውስጥ መግባት ነው የሚመስላቸው። እኔ ፖለቲካ ውስጥ መግባት አልለውም። ይሄ መሰረታዊ የሆነ ዜግነትህን ማስከበር ነው።

ኢትዮጵያዊ ነኝ ካልኩ እንደ ኢትዮጵያዊ ይገባኛል የምለው መሰረታዊ ነጻነት አለ። ያንን ካላገኘሁ ኢትዮጵያዊ አይደለሁም። ከዚህ ጠፍቼ፤ ከዚህ ሸሽቼ አሜሪካና አውሮፓ የምኖር ጊዜ ያለኝ ነጻነት ሀገሬ ውስጥ ካለው ነጻነት የበለጠ ከሆነ እውነተኛ ዜጋ አይደለሁም። ፖለቲካ ውስጥ ያስገባኝ ይሄ ነው።

እስር ቤት ከገባን በኋላ በጣም ብዙ ኦሮሞ ወገኖቻችን ታስረው ሳይ ሀገሪቱ ወደ ምን አይነት አደጋ ውስጥ እየገባች እንደሆነ ነው ያየሁት። አሁንም ለእኔ ፖለቲካ ማለት እነዚህን መሰረታዊ የሆኑ የዜግነት መብቶች ማስከበር፤ ሁሉም የሀገሩ ባለቤት የሚሆንበት ድባብ መፍጠር ነው። ይሄ የምርጫ ጉዳይ ሳይሆን ግዴታችን ነው።

ያንን ማድረግ ካልቻልክ፤ የዜግነት መብትህን እየወረወርክ ነው። ይህንን በፍጹም ማንኛውም ዜጋ ማድረግ የለበትም ብዬ አምናለሁ። ለእኔ ፖለቲካ የሚያያዘው ከዚህ ጋር ነው። ከዚያ በኋላ ያለው ምርጫ ምናምን አድካሚውና በፍጹም የማይረባው የፖለቲካ ክፍል ነው። ዋናው ሥራ ካደረስኩ በኋላ ለጡረታም ደርሻለሁ፤ ትንሽ የማርፍበት ጊዜ ነው።

የጎሳ አከላለልና የጎሳ ፖለቲካ ከኢትዮጵያ መወገድ ያለበት፤ አሳማኝ ምክንያቶች (ዶ/ር አበራ ቱጂ)

ጠቅላይ ሚንስትር ዶ/ር ዐቢይ ስልጣን ከያዙ ጀምሮ በኢትዮጵያ የተስፋ ጎህ ቀዷል። አዲሱም አመራር አበራታች ጥረት እያደረገ ነው። ያም ሆኖ ግን በአገሪቱ በጎሳ ክልል መካከል እየተፈጠረ ያለው ችግር ሁሉንም የአገሪቱን ክፍል እያዳራሰ ነው። በጎሳ መካከል የሚፈጠረው ችግር የአገሪቱን ዜጎች በእጂጉ የሚያሳስብ ጉዳይ ሆኗል። በኢትዮጵያ ወደ 2.5 ሚሊዮን የሚጠጋ ህዝብ በአገሩ ውስጥ ተፈናቅሏል። በራሱ አገር በኢትዮጵያ ውስጥ ስደተኛ ሆኗል። ብዙዎች በዚህ ግጭት ሞተዋል። ብዙዎች የመከራ ኑሮ እየገፋ ነው። ንጹህ ዜጋ በህዝብ ተከቦ በቪድዮ እየተቀረጸ ሲገደልና ሲሰቀል እስከማየት ደርሰናል። የጎሳ ፖለቲካ ዜጎችን እየበላ እያደገና አገር ለማጥፋት እየተዘጋጀ ነው።

የዚህ የአገራችን ችግር ስረ-መሰረቱ ህውሃት-ኢህአዴግ በኢትዮጵያ ላይ የፈጠረው፣ ሆን ተብሎ የተተከለ፣  ስርዓታዊና ህገ መንግሥታዊ መሰረት ያለዉ የጎሳ ወይም የዘር መድሎ ፖሊሲ ነው። ኢትዮጵያ ከገባችበት የፖለቲካ አዘቅት የምትወጣዉ ይህን የጎሳ ፖለቲካና በቋንቋ ላይ የተመሰረተ ከፋፍይና አድሏዊ አከላለል አስወግዳ፣ በምትኩም የዜግነት ፖለቲካና ሁሉንም በዕኩልነት የሚዳኝበት የህግ የበላይነት ስትመሰርትና በተግባር ስታዉል ብቻ ነው። ይህም ሲባል የጎሳ አደረጃጀት በኢትዮጵያ ያመጣዉ ቀዉስ በተግባርና በተጨባጭ ስለታየ ነዉ።  በአለማችን የመጨረሻ ድሃ ከሚባሉት አገሮች  መካካል ያለችዉ  ኢትዮጵያ፣ በሰላምና በአንድናቷ እንድትኖር፣ ብዙ ጊዜ በማይሰጠዉና ቀስፎ ከያዛት ድህነት ላይ ታተኩር ዘንድ፣ ይህን የጎሳ ፖለቲካና ግጭት ከስር መሰረቱ ማስወገድ ለጠቅላይ ሚንስትር ዶ/ር ዐቢይ አስተዳደርና ለኢትዮጵያ ህዝብ  የመጀመሪያዉ ስራ ሊሆን  ይገባል።  አገሪቱ በአንድነቷ እንድትቀጠልና የህዝብ እርስ በዕርስ ጦርነት እንዳይነሳ፣ በሩዋንዳ ያየነዉ በኢትዮጵያ እንዳይደገም፣ ከዚህ የበለጠ ቅድሚያ የሚሰጠዉ ጉዳይ የለም። በዶ/ር ዐቢይ የሚመራዉ የለዉጥ ሃይልም፣ በቅርብ ጊዜ ታሪክ ባልታየ ደረጃ፣ ከፍተኛ የህዝብ ተቀባይነትና ተወዳጅነት ስላለዉ፣ ይህንም የጎሳ ፖለቲካ ለማስወገድ ግንባር ቀደም ሚና ሊኖረዉ ይገባል። ይህንም ለማድረግ የኢትዮጵያ የህዝብ ድጋፍ አለዉ።

በአንድ ወቅት የተባይ ማጥፊያ ነዉ፣ ለችግርም መፍትሄ ነው ተብሎ  በመንግስት መመሪያ የተረጨ ኬሚካል ምድሩንና አየሩን ከመረዘዉ፣ ዉሃዉን ከበከለው፣ ጠቃሚ ተክሎችን የሚያጠፋ ከሆነ፣ መንግስት ምን ማድረግ አለበት?  መጀመሪያ መደረግ ያለበት፣ ይህን መርዘኛ ኬሚካል በጥቅም ላይ እንዳይዉል በአዋጅ ወይንም በህግ ማገድ ነው። ቀጥሎ መደረግ ያለበት፣ ምንም እንኳ ስራዉ አዳጋች ቢሆንም፣ ጤናማ አገርና ህዝብ እንዲኖር ሲባል፣ የተበከለዉን አካባቢ በተለያዩ በተፈተኑ ዘዴወች ማጽዳትና አካባቢዉን ወደ ጤናማ ይዞታዉ መመለስ ነው። ከዚህ ሌላ አማራጭ የለም፣ ምክንያቱም ምድራችን አንድ ብቻ ናትና።   

የአሁኑ የኢትዮጵያ ሁኔታ በዚህ ይመሰላል። ህዉሃት ወደስልጣን ሲወጣ፣ ከኦነግ ጋር በመሆን ኢትዮጵያን በጎሳ የሚከፋፍለዉን ህገ መንግስትና የጎሳ አከላለል አዉጥተው የአገሪቱ መታዳደሪያ አደረጉ።  በዚህም መሰረት ለሃያ ሰባት ዓመታት በአገሪቱ ዉስጥ ጥላቻ ተነዛ። በአሜሪካ ፎርቹን 500 ተብለዉ ከሚታውቁት ኢኮኖሚዉን ከሚመሩት ታላላቆቹ ድርጂቶች፣ ወደ ግማሽ የሚጠጉት የተመሰረቱት ከዉጭ በመጡ ሰዎች ወይንም በእነርሱ ልጆች ነው።  አገሩ ፈጠራንና ስራን እንጂ ጎሳን ወይንም የመጡበትን አገር ባለማየቱ ነዉ ሃያል ሆኖ የቀጠለዉ።  ኢትዮጵያ ዉስጥ ግን ዜጎች ከአንድ ክልል ሄደዉ በሌላ ክልል እንዳይሰሩ ተደረገ። ኢትዮጵያዊያን በተሰደዱባቸዉና ወላጆቻቸዉ ባልገነቧቸዉ ምዕራባዊያን አገሮች ለፖለቲካ ስልጣን በሚወዳደሩበት ዘመን፣  የአንድ ጥቁር ኬኒያዊ ልጅ የአሜሪካ ፕሬዘደንት ሲሆን አይተን፣ ኢትዮጵያዊያን ግን በአገራቸዉ ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሰዉ የመሥራት ተፈጥሯዊ መብታቸው ተነፈገ። ከወሊሶ ሂዶ ወልቂጤ ወይንም ከወልቂጤ ሂዶ ወሊሶ ስራ ማግኘት ጭራሽ የማይታሰብ ሆነ፡፡ ክፍፍሉ በሁሉም ዘርፍ ሆኖ በቤተሰብ ደረጃ ደረሰ።  የባህልን ትሥሥር በማወቅ ከሌላ አካባቢ ከመጡ ወገኖቻቸው ጋር ለመተዋወቅ ሊረዱ የሚገባቸዉ የከፍተኛ ትምርት ቤቶች ሳይቀር የጎሳ ክፍፍል ማሰልጠኛና የጠብ ሜዳዎች ሆኑ።  የተማሪዎች ማደሪያ አመዳደብና፣ የተማሪዎች ማህበር አደረጃጀት ሳይቅር በጎሳ የተከፋፈለ ሆነ።

የመንግስት ሰራተኞች በተወለዱበት አካባቢ እንዲወሰኑ ተደረገ። ይህም የሃሳብ ብዝሃነት እንዳይኖርና፣ አዲስና የተሻለ ሃሳብ በስራ ላይ እንዳይዉል አደረገ።  ዜጎች ከሌላዉ የአገሪቱ ክፍል ከመጣዉ ወገናቸዉ ጋር እንዳይተዋወቁ ሆን ተብሎ መጋረጃ ተደረገባቸዉ።  የመንግስትም ዋናዉ ስራ ህዝብን በጎሳ መለያየትና ማጠር ሆነ። በተጨማሪም ዜጎች የተለየና አማራጭ ሃስብ ማመንጨት እንዳይችሉ የሚያደነዝዝ የህዉሃት ፖለቲካ ሰበካ ተደረገባቸው።  ዜጎች ዕውነተኛ መረጃ አያገኙም፣ የተነገራቸውን ብቻ መቀበልና የታዘዙትን መከተል ባህላቸው እንዲሆን ተደረገ። አዲስ በሬ ወለደ ታሪክ በመፍጠር፣ አንዱ በሌላው ላይ ጥላቻና ጥርጣሬ እንዲኖረው ተደረገ። ለዚህ የትግራዩን የመምህር ገበረኪዳን ደስታን ታሪክ ትንተና ማየት ይበቃል።

በአጭሩ ኢትዮጵያ የብሔረሰቦች እስር ቤት ናት በማለት እንቅስቃሴያቸውን የጀመሩት የስድሳወቹ የተማሪ ፖለቲከኞችና ህዉሃት፣ የአሁኗን ኢትዮጵያ ጎሳዎች በየጉሪያቸው ተከፋፍለው የታሰሩባት ወህኒ ቤት አደረጓት።  አሁን በኢትዮጵያ የምናየው የጎሳ ግጭት የዚህ የኢሃዲግ የመንግሥት ህገ-መንግስታዊ ከፋፋይ ሥርዓት ውጤት ነዉ። በወያኔ በተደረገዉ የረጂም ጊዜ አዕምሮ አጠባ (brain wash) የተነሳ ወይንም በፍርሃት፣ ብዙዎች ይህን አፍጥጦ የመጣ ሃቅ መረዳት እየቸገራቸዉ ነው። ይህ አስከፊ የዜጎች ዕርስ በዕርስ መገዳደል መቆም አለበት። ብዙ ሰዉ በግልጽ ያልተገነዘበዉ ነገር ቢኖር፣ ህዉሃት ይህን ስርዓት የፈጠረዉ፣ ህዝቡን በጎሳ ከፋፍሎና ደካማ አሻንጉሊት የጎሳ መሪዎችን በማስቀመጥ፣ የአገሪቱን ሃብትና መሬት ለመዝረፍና ለመሸጥ መሆኑን ነው። ከኢኮኖሚያዊ ምክንያቱ በተጨማሪ፣ በህይወት ለመኖር ስንል፣ ይህ የሚያጫርሰን የጎሳ ክፍፍል አስተዳደር መቅረት አለበት። ለዚህም የሚከተሉት ዝርዝር አሳማኝ ምክንያቶች አሉ።

በማናዉቀዉ ፅንሰ-ሃሳብ እየተጋደልን ነው፤ በኢትዮጵያ ህገ መንግሥት ብሔር ብሄረሰቦች ህዝብ የሚለው ፅንሰ-ሃሳብና ትርጉሙ በውል ተለይቶ አይታውቅም፡፡  ፅንሰ-ሃሳቡም ለኢትዮጵያ አግባብ የለውም፡፡ ብሔር ብሔረሰብና ህዝቦች የሚለው ምን ለማለት እንደሆነ ለብዙው ኢትዮጵያዊ ቀርቶ ህግ አውጭ ነን ብለዉ ፓርላማ ዉስጥ የሚቀመጡት፣ ህግ አስፈጻሚ ነን የሚሉት ባለስልጣናት፣ የቃላቱን ወይንም ጽንሰ ሃሳቦቹን ትርጉም አያውቋቸውም። ስለዚህ ማነው ብሔር፣ ማነው ብሔረሰብ፣ ማነው ህዝብ የሚለው በትክክል አይታወቅም። ስለዚህ ኢትዮጵያዊያን ትርጉሙ ባልገባን ባዕድ ቃላት እርስ በዕርስ ተከፋፍለን እየተጋደልን ነው። ይህ በብሔር ብሔረሰብ ህዝብ የሚለው ከስታሊን ዘመን ፖለቲከኞች፣ አገራቸዉን ባግባቡ ያላወቁ በአስራ ዘጠኝ ስድሳዎቹ  ወጣት የተማሪ ፖለቲከኞች የተኮረጀና ለእኛ አገር ፍፁም አግባብነት የሌለው ባዕድ ነገር ነው እያጋደለን ያለዉ።

ያልነበረንና የማይኖርን ወሰን ለመፍጠር ሲባል ህዝብን ማጋደል፤ እነዚህ ብሔር ብሔረሰብ ህዝብ ተብለው በቋንቋ የተከፋፈሉ ክልሎች መካከል የማያሻማና ግልፅ ወሰንና የመለያ መስመር ለማድረግ የማይቻል ነዉ። የጎሳ የሃሳብ መስመሩ ያለው በወያኔ-ኢሃዲግ ፖለቲከኞች አዕምሮ እንጂ፣ በህዝቡና በመሬት ላይ የለም። ይህን በወያኔዎች የቅዠት ምናብ ያለ የጎሳ የሃሳብ መስመር በህዝቡ ወስጥ ለማስመር ሲባል ህዝብ ወደማይቆም ብጥብጥና ግጭት እየገባ ነው። ለምሳሌ የኦሮሞ ክልል አልቆ  የጉራጌ ዞን የሚጀምረው በትክክል ድንበሩ ወይንም መስመሩ የት ላይ ነው? በመካከል ሁለቱንም ቋንቋ የሚናገሩ የተሳሰሩ ዜጎች የሉም ወይ? በሱማሌና ኦሮሞ፣ በአማራና ትግሬ፣ እንዲሁም በሌሎችም መካካል ህዝቡን የጎሳ ፖለቲከኞች እንደፈለጉት መከፋፈል ባለመቻሉ ግጭቱ ይቅጥላል። የግጭቱ ምክንያት የማይለያይንና የተወሃደን ህዝብ ለመለያየት በሚደረግ ዋጋቢስ ትግል ነው።  

የትኛዉ ቦታ ነው ለማን የሚሰጠው፣ በምንስ መሰረት?  በደም ወይም DNA ምርመራ ነው? በሚናገረው ቋንቋ ነው?  በህዝብ ብዛት ነዉ? በታሪካዊ ይዞታ ነው? ያስ ከሆነ ወደኋላ እስከመቼ ያለዉን ታሪክ ነዉ የምናየዉ? ቦታዉ በተሰየመበት ቋንቋ ነው? ለምሳሌ አሁን የቅማንት ነዉ፣ የአማራ ነው እየተባሉ ሰዎች የሚሞቱባቸው ቀበሌዎች ጉባይ፣ ሌንጫ፣ መቃ ይባላሉ። በቦታ ስም ካየን ኦሮምኛ ይመስላሉ። የቦታ ስም የተሰየመበትን ቋንቋ ካየን አንዳንድ የኦሮሞ የጎሳ ፖለቲከኞች ቅኝ ገዥ ናቸዉ የሚሏቸዉ፣ እቴጌ ጣይቱ ብጡል አዲስ አበባን የቆረቆሩት፣ የኦሮሞዉ የራስ ጉግሳ የልጅ ልጅ ልጅ ሲሆኑ፣ ባለቤታቸዉ አጼ ሚኒሊክ ከጣያሊያኖች ጋር ታሪካዊዉን ዉለታ የተፈራረሙበት ቦታ ደግሞ ከጢጣ አልፎ መርሳ ሳንደርስ ዉጫሌ ላይ ነዉ። ትንሽ ኦሮምኛ ለሚችል ሰዉ እንዲህ ያሉ የቦታ ስሞች በተለያዩ በሰሜኑ የአገራችን ክፍሎች መኖራቸዉን ሲሰማ፣ ምንም እንኳ ታሪክ ባያዉቅ፣  እንዴት ነዉ “የመቶ ዓመትን ታሪክ” ተብሎ የተነገረዉን ተቀብሎ የሚነዳዉ?  በሌላ በኩል ደግሞ አዲስ አበባ የኦሮም ብቻ ናት ሌላው መጤ ነው የሚሉት ጎሰኖች በ1450 አካባቢ በዚያዉ በአዲስ አበባ አካባቢ ጥንታዊ የኢትዮጵያ ከተማ እንደነበር ያለዉን የአርኪዮሎጂ መረጃ ማየት አይፈልጉም።  የጎሳ ፖለቲከኞች ይህን ትሥሥራችንን የሚያሳየዉን ሃቅ ግን መመርመርና ማጥናት አይፈልጉም። የተነገራቸዉን “የመቶ ዓመት ታሪክ” ይዘዉ ያላዝናሉ እንጂ።

ሁሉም የጎሳ ፖሊቲከኞች አንድ ትልቁንና የሚያግባባቸዉን ካርታ በመያዝ፣ ታላቋን ኢትዮጵያን የራሳቸዉ በማድረግ ፋንታ፣ የግላቸዉን ትንንሽን የሚያጋጩ ካርታዎችን በኪሳቸዉ ይዘዉ ንግስናቸዉን እየጠበቁ ነው። ግጭቱ በቋንቋ ተለያይቶ ብቻ ሳይሆን በመንደርም እየሆነና የማይቆም ነው።  በደቡብ አካባቢ የማይቆም የሚመስል የክልል፣ የወረዳና የራስ አስተዳደር ጥያቄ እየተነሳ ነዉ። ምንድን ነዉ መመዘኛዉ? ኢትዮጵያ የጎሳ ፖለቲካ መሞከሪያ ቤተ-ሙከራ (laboratory) ሆናለች። በድንቁርና ሙከራዉን በሚያክሂዱ “ተመራማሪወች” የቤተ-ሙከራዉ መሳሪያወችና እቃዎች እየተቃጣጠሉ ነው። አሁን የምንፈራዉ አጠቃላይ ቤተ ሙከራው እንዳይቃጠልና እንዳይወድም ነዉ። በዚህ በክልል ድንበር የተነሳ እስከአሁን ያለቁት ወገኖቻችን፣ የተፈናቀሉት ዜጎች በቂ ትምህርት አይሰጠንሞይ?  መቼ ነዉ የራሳችን ጉዶች የፈጠሩት መከራ የሚበቃን?  ኢትዮጵያዊያን ምን አደነዘዘን?

አንድ ክልል ለተወሰኑ የህብረተሰብ አካል ሲሰጥ፣ በሌላ አባባል ሌላው የህብረተሰብ ክፍል የዚያ አካል አይደለም ማለት ነው። ይህም “የኔ የብቻዬ ነው” ለማለት ነዉ። የአማራ ክልል ለአማራ ነው ማለት፣ በሌላ አባባል፣ የትግሬው አይደለም፣ የኦሮሞው አይደለም፣ የጉራጌው አይደለም ማለት ነዉ። ስለዚህ አከላለሉ፣ የአንተ ነው ተብሎ ለአንድ ጎሳ ሲሰጥ፣ ሌላውን በዚህ ቦታ አያገባህም፣ ይህ አካባቢ የኔ እንጂ የአንተ አይደለም ማለት ሲሆን፣ ህገ-መንግስታዊ የሆነ ፍፁም አግላይ የሆነ፡ አሰራር ነው። በየትም አለም ዜጎቹን እንዲህ የሚያገልና የሚከፋፍል ህግ የለም። ለምሳሌ በህንድ በማንነት ፖለቲካ አደረጃጅት አገር አፍራሽ መሆኑን የተረዳው የህንድ የመጨረሻዉ ፍርድ ቤት፣ የማንነት ፖለቲካ እንቅስቃሴ ህገ ወጥ እንደሆነ በይኗል፣ አግዷል።  የጎሳ አከላለል፣ የኢትዮጵያ ህዝብ የዉጭ ጠላት ቢመጣበት እንኳ ተግባብቶና ተባብሮ አገሩን መከላከል እንዳይችልና፣ ኢትዮጵያን ለማጥፋት የተሸረበ ስልታዊ (strategic) ደባ ነው።

የቡድን ጥያቄ የዜጋን መብት በማክበር ይፈታል። የጎሳ ፖለቲካ፣ ግለሰቦች የሃሳብ የበላይነት ማግኘት ሲያቅታቸው፣ ወደ ስልጣን ለመዉጣት የሚጠቀሙበት አቋራጭ መንገድ ነው።  የግለሰብ መሰርታዊ መብቱ ከተከበረ፣ ያማይከበር የቡድን መብት የለም።  በየትኛዉም የአገሪቱ ክፍሎች፣ በክልል ወይም ጎሳ ሳይወሰን፣ ዜጎች በአፍ መፍቻ በቋንቋቸው መማር፣ በቋንቋቸው መጠቀም፣ መዳኘት፣ የመስራት፣ ሃብት የማፍራት፣ መሪያቸዉን የመመረጥ፣ ሃሳብቸዉን የመግለጽና የመደራጀት መብታቸው ያለምንም ገደብ ሊከበርላቸው ይገባል። ይህን ለማደረግ የግድ የጎሳ አደረጃጀት ወይም ክልል አያስፈልግም። ለአንዱ መብት ለመታገል፣ የዚያ ሰዉ ጎሳ አባል መሆን አያስፈልግም፣ ዜጋ መሆን ብቻ ይበቃል።  ጎንደር ዉስጥ ያለ አንድ ኦሮምኛ ተናገሪ፣ የምችለው ቋንቋ ኦሮምኛ ብቻ ነዉ፣ በኦሮምኛ ልዳኝ ይገባኛል ካለ፣ አስተርጓሚ ሊመደብለት ይገባል። ይህን ለማደረግ የግድ የጎሳ ክልል አያስፈልግም። ይህ በየትኛዉም የገራችን ክፍል የዜጎች ሁሉ መብት ሊሆን ይገባል።

በጎሳ ግጭት የማይነካና የማይጎዳ ክልል ወይንም የህበረተሰብ ክፍል አይኖርም። ባለፉት ሦስት ዓመታት ብቻ ያየነው ይህን ነዉ።  የጎሳ ፖለቲካ መሃንዲስ ነን የሚሉት ግለሰቦች፣ ሌላዉ መጤ፣ ሰፋሪ፣ ቤት የለሽ፣  ነዉ እናባርረዋለን፣  የሚሉት ሳይቀር ራሳቸዉ ባጠመዱት ወጥመድ እየገቡ ነው። ኦሮሞ ከሶማሊ፣ጉጂ ከጌዶ፣ ቤኒሻንጉ ከኦሮም፣ ኦሮሞ ከአማራ፣ ሲዳማ ከወላይታ፣ አማራ ከቅማንት፣ አማራ ከትግሬ፣ ብዙ ቦታ ማቆሚያው የማይታወቅ ግጭት ተነስቷል። ይህ ችግር ወደ እኔ አይመጣም ብሎ ተዝናንቶ የሚቀመጥ የህብረተሰብ ክፍል የለም። በዚህ ከቀጠለ የጊዜ ጉዳይ ሆኖ እንጂ ሁሉንም ያዳርሳል። ስለዚህ ይህ ሁኔታ አንዱ ወገን አባራሪ ሆኖ ሌላው ተባራሪ፣ አንዱ አገር ሲመሰርት ሌላዉ አገር የሚፈርስበት ከስተት አይደለም፣ የዕርስ በዕርስ መተላላቅ እንጅ። አንዱ ወገን ሲጠቃ ሌላዉም አልሞት ባይ ተጋዳይ ሆኖ ራሱን ያዘጋጃል፣ በምላሹም ጥፋት ያደርሳል። እየገደለ ይሞታል። በነሩዋንዳ፣ የመን፣ ሶሪያ የደረሰው እልቂት በኛ ላይ ካልደረሰ አንማርም ብሎ እልቂትን መጋበዝ ከድንቁርናም አልፎ ደደብነት ነው።

በጎሳ ስም ማጥፋት እንጂ ተጠያቂ ጎሳ አይኖርም። በጎሳ ፖለቲካ መሪወች በጎሳ ስም በግለሰብ ላይ ጥፋት ይፈጸማሉ እንጂ ተጠያቂ የሚሆን ወይንም ሃላፊነት የሚወስድ ጎሳ ወይም ቡድን ግን አይኖርም፣ ሊኖርም አይገባም። በህግ አግባብ በማይጠየቅ ቡድን ስም፣ ግለሰቦች ወንጀል የሚፈጽሙበት አሰራር ነዉ።  ግለሰቦች በቡድን ስም ሃይል የሚያገኙበት ነገር ግን ጥፋቱን በህግ ወደማይጠየቅ ጎሳ የሚያላክኩበት፣ በወንጀላቸዉ ሲጠየቁም ጎሳችን ወደሚሉት ቡድን ሂደዉ የሚደበቁበት ሀገወጥነት ነዉ።

የጎሳ አከላለሉ፣ አሁን እንዳለ እንዲቀጥል ቢደረግ እንኳ፣ አገሪቱን ወደ ኢኮኖሚያዊ አዘቅጠት ከዚያም ወደ ማህበራዊ ቀውስ ይወስዳታል።  በየትም አገር ለዕድገት አስፈላጊ የሆኑ መሰረታዊ ነገሮች አሉ። አንዱና የመጀመሪያው የህግ የበላይነት ነው። ሌላው የንብረት ባለቤትነት መብት ሲሆን፣ ስራን፣ ችሎታን፣  ፈጠራንና፣ ተወዳዳሪነትንና  የሚያበረታታ ነጻ ገበያ ነው። ይህም የሰዉን ሃብት በነጻነት ማንቀሳቀስ ይጨምራል።  እዲሁም እነዚህን በስርዓትና በህግ የሚያስከበር ህጋዊ ተቋማት ሊኖሩ ይገባል። ማንም አካባቢ ሆነ ግለሰብ በራሱ ብቻ ምሉዕ እይደለም። አንዳችን ለአንዳችን እናስፈልጋለን። ነገር ግን ማንም ቢሆን ያለውን ሀብትና ዕዉቀት አውጥቶ ወይንም ሙያውን ተጠቅሞና ተቀናጅቶ ለመሥራት የህይወትና የንብረት ዋስትና ያስፈልገዋል።

በአሁኑ የኢትዮጵያ ሁኔታ ሰዎች ካደጉበት አካባቢ በግፍ እየተባረሩ፣ ምን አይነት ሰዉ ነው ህይወቱን ለአደጋ እየሰጠ አገርን አልምቶ ራሱንም የሚጠቅመው? ከምንም በላይ ከግዚአብሄር ቀጥሎ ሃይል ያለውን የሰው አዕምሮ አልምቶና እንደተፈላጊነቱ አዘዋዉሮ መጠቅም ካልተቻለ፣ ከድህነት መዉጣት አይቻልም። አደጉ የሚባሉት የአለማችን አገሮች እዚህ የደረሱት በቆዳ ስፋታቸው አይደለም፣ በተፈጥሮ ሃብታቸዉም አይደለም፣ የሰው ሃብታቸዉን አልምተው አስተምረዉና ይበልጥ ምርታማና ዉጤታማ በሚሆነብት ቦታ አሰማርተዉ፣ ያለዉን የማምረትና የመፍጠር ችሎታ በመጠቀማቸዉ እንጂ። የምጣኔ ሃብት እድገት ምንጩ ከሰዉ ልጅ አዕምሮ ነው።  ትርጉም ያለዉ የኢኮኖሚ ለውጥ ያመጣዉ ፈጠራ innovation ነዉ። ለዚህም አሜርካንን፣ ጀርመንን፣ ጃፓንንና ቻይናን የመሳሰሉትን አገሮች ማየት ይበቃል።

ዜጎች ለዓመታት ለፍተው ላባቸዉን አንጠፍጥፈው ያፈሩትን ንብረት በሚቀሙበት አገር፣ ንብረታቸው በጎሰኞች በሚቃጠልበት አገር፣ የውጭ አገር ባለሃብት ቀርቶ፣ ኢትዮጵያዊያን ያላቸውን ሀብት ያሸሹ እንደሁ እንጂ በልማት ላይ አያውሉትም። ምንም እንኳ እንድ አንዶች ቢኖሩም፣ ያገኙትን የተፈጥሮ ሃብት አራቁተውና በክለዉ፣ የኢትዮጵያን ባንኮች ዕዳ ላይ ጥለው፣ ዘርፈው ለመውጣት ካልሆነ፣ በአገሪቱ ሰላም ተማምነው ያላቸዉን ሃብት አፍስሠዉ ዘላቂ ልማት አያመጡም። ዘመናዊ ቴክኖሎጂ የሰዉን ልጅ ስራ እየተሻማ ባለበት ዘመን፣ በተራ ጉልበት ስራ ላይ በሚመሰረቱ የቻይና ፋብሪካዎችም ላይ መተማመንም አይቻልም። በቴክኖልጂ (robotics, 3D printing, artificial inteligence) ምርታማነታቸዉን ሲያሳድጉና በጥቂት ሰዎች ብቻ ማምረት ሲችሉ፣ ስራዉን ወደ አገራቸዉ ይመልሱታልና። በህዝብ ልማትና ምርታማነት ላይ ያልተመረኮዘ ዕድገት ዘላቂነት የለዉም፡፡ ወያኔ የፈጠረዉ የጎሳ ሥርዓት፣ ሰው በችሎታውና ዕውቀቱ ወይም የሥራ አፈፃፀሙ የሚለካበት ሳይሆን በጎሳ ፖለቲካ ታማኝነቱ ነዉ። ይህም ወጣቱን በአቋራጭ ሀገወጥ ሃብት ፈላጊ እንጂ የዕዉቀት ፍላጎት እንዳይኖረው አድርጓል፡፡

አንዲት አዋሳ ተወልዳ ያደገች ወጣት የዩኒቨርሲቲ ትምህርቷን አጠናቃ ሥራ እያፈለገች ያጋጠማትን የገለፀችው ልብ የሚነካ ነበር። አንድ አጎቷን ይህን ጠየቀቸው። አጎቴ፣ እኛ ምንድን ነን? አጎቷም ምን ማለትሽ ነው ይላታል፡ እሷም ዘራችን ምንድን ነው? አለች፣ አጎቷም በመገረም ዘሯ የተቀላቀለ መሆኑንና በቀላሉ ኢትዮጵያዊ መሆናቸዉን አብራራላት። እሷ ግን ሥራ ለማግኘት ዘር ይመረጣል። የተወለድኩት እዚህ፡ ነው። ነገር ግን አንቺ የዚህ ክልል ዘር አይደለሽም እያሉ ስራ ሊቀጥሩኝ አልቻሉም ብላ ወጣቷ በሃዘን ተናገረች። ከአገራችን በድህነት ወደኋላ ከመቅረት በተጨማሪ፡ ህውሃቶች ህዝቡን በጎሳ ከፋፍለው በፈጠሩት ስርዓት ሰው የሙያ ችሎተው ሳይሆን ዘሩ ታይቶ ሥራ የሚቀጠርበት አገር ሁኗል። በዚህ ሁኔታ ያደገ ወጣት ለአገሩ ምን አይነት በጎ አመለካከት ሊኖረዉ ይችላል?

አገራችን ያላትን የሰው ሃይል ማልማት እትችልም። ያላትንም የለማ ህዝብ በሚያስፈልግበት ቦታ መጠቀም አልቻለችም። ወደ 105 ሚሊዮን የሚጠጋ ህዝብ ያላትና 80 በመቶ ወጣት በሆነበት አገር፣ ወጣቱን በሥራ ማሰማራት ዋነኛ ጉዳይ መሆን ሲገባው፣ በጎሳ ፖለቲካ ላይ በማተኮረ ሰውን ሠርቶ እንዳይበላ ማድረግ በወገን ላይ የሚፈፀም ወንጀል ነው። በአንድ አካባቢ ሰልጥነው የተቀመጡ ሥራ አጥ ወጣቶች ሲኖሩ በሌላ አካባቢ ደግሞ ህዝቡ ባለሙያ አጥቶ በችግር ይሰቃያል። ይህም የጎሳ ፖለቲካ ያመጠው ጣጣ ነው።አገራችን ካለባት አጠቃላይ ድህነት በከፋ የገጠሩ አካባቢ ከፍተኛ የተማረ የሰው ሃይል እጥረትና ችግር አለበት። በከተማዎች አካባቢ የተጠራቀመው የሰው ሃይል ራቅ ወዳለዉ የአገሪቱ ገጠር  ክፍል ሄደ፡እንዳይሠራ፣ እንዳያለማ፣ የሰዉ ህይወት እንዳያድንና፣  አገሩንም እንዳያዉቅ፣ ይህ የጎሳ ክፍፍል መስናክል ሆኗል። በአገሪቱ ገበሬው ያመረተውን ምርት በማዕከላዊ ገበያ መሸጥ ባለመቻሉና የስርጭት ችግር በመኖሩ ነው በአገራችን የምግብ እህል እጥረት የሚፈጠረው ተብሎ፣ የገበያ ልውውጥ ማዕከል  (የኢትዮጵያ ምርት ገበያ) ያቋቋመዉ መንግሥት፣ ለዕድገት ፍጹም አስፈላጊ የሆኑትን የተማሩ ወጣቶች ግን ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ሄደው መሥራት እንዳይችሉ አድርጓል።

የጎሳ ፖለቲካና ግጭትና ዘረኛ ቅስቀሳ  በህዝብ መካከል የሚይረሳ የታሪክ ጠባሳ ጥሎ ያልፋል። ይህም ለወደፊት የአገሪቱን አንድነት አደጋ ላይ ይጥላል። የዘሬ ጥፋት የነገ ታሪካዊ ችግር ይሆናል።

ዘመኑ ከአንድ ክፍለ ዓለም ሌላው ክፍለ ዓለም መረጃ በቅፅበት የሚደርሰበት፣ የአገር ድንበሮች የሰውን እንቅስቃሴ የማይገድቡበት ዘመን ነው። የተፈጥሮ ሃብትም ቢሆን የልዩነትና የግጭት ምንጭ መሆን የለበትም።  እያንዳንዱ አካባቢ የራሱ የሆነ የተፈጥሮ ሃብት አለው። አንዱ ነዳጅ፡ ሲኖረው ሌላው እብነበረድ ሊኖረው ይችላል፣ አንዱ ደግሞ ለም የእርሻ መሬት ሊኖረው ይችላል፤ ሌላዉ ሲሚንቶን ማምረት የሚያስችል ሃብት ሲኖረዉ፣ ሌላዉ የዉሃ ሃብት ይኖረዋል።  ስለዚህ ሁሉም ዋጋ አለው ሁሉም ለአገራችንና ለህዝባችን ያስፈልጋል። ዘመኑ በጎሳ ታጥሮ የምንኖርበት አይደለም። የሚያዋጣዉና ሃይል የሚኖረን የጎሳን አጥር አስወግደን ስንተባበርና ሁላችንም በችሎታችን ስናበረክት ነው።

ኢትዮጵያ የጎሳ መብት የግለሰብን ወይንም የዜጋን መብት ያጠፋባት አገር ሆናልች።   ኢትዮጵያ ዜጋ የሌላት የጎስ ስብስብ ተደርጋለች። ስለዚህ የጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ መንግስት ተቀዳሚ ስራዉ ይህን የጎሳ አደረጃጀትና ፖለቲካ ማስወገድና ሁሉንም ኢትዮጵያዊ ያለአድሎ የሚይስተናግድ የዜግነት ፖለቲካን ማስፈን ነው።

ይህንም ማድረግ ይቻል ዘንድ ኢትዮጵያዊያን ረጋ ብለንና ምክንያታዊ፣ ገንቢና ሰላማዊ ወይይት በማድረግ፣ ችግሩን ከስር መሰረቱ በመመርመር፣ ካለፈዉ ስህተት በመማር፣ የወደፊት አቅጣጫችንን ራሳችን መንደፍ አለብን። ሃላፊነቱን ለተወሰኑ የጎሳ መሪወች መተዉ የለብንም። ሁላችንም እኩል ሃላፊነት አለብን። የኢትዮጵያ ምሁራን ፈረንጆች ከጻፉት የመማሪያ መጽሃፍ ዕዉቀት (textbook knowledge) በዘለለ፣ የአብዛኛዉን የአገራችንን ህዝብ ኑሮና ችግር ከተለያየ ዘርፍ ቀርቦ በማጥናት ለአገራችን ሁኔታ የሚስማማ አገር በቀል የመፍትሄ ሃሳብ ሊያቀርቡ ይገባል።  የኢትዮጵያ ህግ አዉጭወች፣ አገሪቱን ወደዚህ ደረጃ ያደረሱትን ከፋፍይና አግላይ ህጎች በማስወገድ፣ ሁሉም ዜጋ በእኩልነት የትም የአገሪቱ ክፍል በነጻነት የሚኖርበት ስርነቀል ህግ ሊያወጡ ይገባል። እንዲዚሁም የኢትዮጵያ ጦር ሃይል፣ የአገሪቱን ዳር ድንበርና የአገር አንድነትና የአገር ዉስጥ ሰላም ለድርድር የማይቀርብ መሆኑን አዉቆ፣ የተጣለበት ሃላፊነት በንቃት ሊወጣ ይገባል። የኢትዮጵያ የፖለቲካ መሪወችና ባለድርሻወች፣ የአገሪቱን ስልታዊ (strategic) ጥቅም፣ ለጊዚያዊና የአጭር ጊዜ የፖለቲካ ድል መስዋዕት ሳያደርጉ፣ ለዘላቂ ሰላምና ዕድገት መሰረት በሆነው የዜግነት መብትና ፖለቲካ ላይ ሊያተኩሩ ይገባል።

በተለያዩ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚገኙ የአማራ ክልል ተማሪዎች ወደ ክልላቸው ይመለሱ! (ፍሥሓ አንዳርጌ)

አዴፓ ለአማራ ህዝብ  መቆርቆር የሚጀምረው መቼ ነው? ከእንቅልፉ እስኪ ነቃ  ስንት አማራ  መፈናቀል፤ መሳደድና መገደል አለበት? ማንም እየተነሳ አማራን ቤተክርሲቲያን እንደገባ ውሻ ሲያሳድድ አዴፓ ምን ወስጥ ነው የተኛው?

ህወሓት ላለፉት ሩብ ክፍለ ዘመን አማራ የትምህርት እድል እንዳያገኝ በተጠና ስልት  በተለይም በከፍተኛ ትምህርት ተቋም የመማር እድሉ በእጅጉ እንዲቀጭጭ አድርጎት ቆይቷል፡፡ ከሁለተኛ ደረጃ ት/ቤቶች ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋም የሚገቡ የተማሪዎች ቁጥር እንዲቀንስ  በመንግስት ከፍተኛ ስራ ሲሰራ ቆቷል፡፡

በመንግስት የተጣለውን ይፋ ያልሆነ እገዳ ተቋቁመው ወደ ከፍተኛ ትምህርት ሲገቡ ተማሪዎች የሚጋጥማቸው ችግር  በጣም ብዙ ነው፡፡ ከሁሉም ችግሮች እየከፋ የመጣው ካለፈው አመት ማለትም 2010 ዓ.ም ጀምሮ በተማሪዎች ላይ የሚፈጸመው ግድያና ድብደባ ነው፡፡ በ2010 ዓ.ም በአዲግራት ዩኒቨርስቲ የደረሰው ግድያና  ድብደባ የሚታወስ ነው፡፡ በኦሮሚያ ክልል በሚገኙ ዩኒቨርስቲዎች ሙሉ ሰላማዊ ትምህርት ኖሮ አያውቅም፡፡ ድብደባና ማሳቀቅ የተለመዱ ተግባራት ከሆኑ አመታት ተቆጥረዋል፡፡ ትምህርት ሰላማዊና የተረጋጋ  መንፈስን ይጠይቃል፤ ሰላምና ደህንነት አደጋ ላይ በወደቁበት ተቋማት ትምህርት አይታሰብም፡፡ስለሆነም የአማራ ተማሪዎች ላለፉት ሩብ ክፍለ ዘመን ሙሉ አእምሮአቸውን የሚጠቀሙበት የትምህርት አካባቢ አግኝተው አያውቁም፤ ይህም በተማሪዎች ውጤት ላይ በሚያደርሰው ተጽኖ ምክንያት ለትምህርት ማቋረጥና  ዝቅተኛ ውጤት ይዳርጋል፡፡ ተከታታይ ተጽኖውም በተማሪዎች ቀጣይ ህይወት ላይ ይከሰታል፡፡

በዚህ ሁኔታ ሲታሰብ የአማራ ተማሪዎች  ከክልሉ ውጭ ወደ ተላያዩ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚሄዱት ለትምህርት ሳይሆን ለፖለቲካ ፍጆታ ብቻ ነው ማለት ይቻላል፡፡ አዎ! ለፖለቲካ ፍጆታ ብቻ ነው! የተማሪ ወላጆች በከፍተኛ ጭንቅት ላይ ኖረዋል፤ እየኖሩም ነው፤ ብዙ ወላጆች ውድ ሎጆቻቸውን በአረመኔዎች በመነጠቃቸው ለማገገም በሚያስቸግር ሁኔታ በሀዘን ተቆራምተዋል፤ ተሳፋ ቆርጠወል፤ የሐዘን ማቅ ለብሰዋል፡፡

አሁን አሁን ጀግንነት ይመስል  በግፍ የተገደሉ ተማሪዎችን እሬሳ ተሸክሞ ወደ ክልሉ መሄድ እየተለመደ መጥቷል፡፡ በሴት ተማሪዎች ላይ የሚፈጸመው የአስገድዶ መድፈርና የግድያ ሲታይ አማራ መንግስት  በሌላት ሀገር ውስጥ የሚኖር ህዝብ አስመስሎታል፡፡ ከአንድ ወር በፊት በአሶሳ በግፍ  3 ተማሪወች መገደላቸውና ከ40 ባላይ ተማሪዎች ከፍተኛ የአካላ ጉዳት መድረሱ ይታወሳል፡፡  ነገር ግን ከዚህ አሳዛኝ ክስተት  መማር የተቻለ አይመስልም፡፡  በአሁኑ ወቅት በኦሮሚያ ክልል  ቡሌ ሆራ ተብሎ በሚጠራው ዩኒቨርስቲ የአማራ ተማሪዎች በከፍተኛ የህይወት ስጋት ላይ መሆናቸው ይታወቃል፡፡

ህወሓትና ኦነግ በጣምራ  በአማራ ህዝብ ላይ ላለፉት 40 ዓመታት ግፍ ሲፈጽሙበት ኑረዋል፤ እየፈጸሙም ይገኛሉ፡፡ እነዚህ ሁለት ጸረ-አማራ ድርጅቶች እስካሉ ድርስ በአማራ ላይ የሚፈጸመው ግፍ ተጠናክሮና በአስከፊ ሁኔታ እንደሚቀጥል የአማራ ህዝብ ሊያውቀው ይገባል፡፡

 አሁን ያለው መፍትሄ አንድ ብቻ ነው እርሱም የአማራ ክልል ተማሪዎች በአማራ ክልል በሚገኙ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እንዲማሩ ማድረግ  ነው፡፡ሌሎችም እንዲሁ፡፡ ኢትዮጵያ በአሁኑ ሰዓት በተግባር የሚገለጽ አንድነት የላትም፤ ሶስት ባላንጣ መንግስታት(ህወሓት፣ ኦነግና ኦዴፓ)  ነው በእሰጥ አገባ የሚተራመሱባት፡፡ ስለዚህ በተግባር አንድነት በሌለባት ሀገር ከአማራ ክልል የሄዱ ተማሪዎች የአንድነት መስበኪያ ሁነው ህይወታቸውን ሊያጡ አይገባምም፡ የክልሉ ምንግስትም  አዴፓ ዝምታውንና ከአሽርነት ስራው ወጥቶ ተማሪዎችን ወደ ክልላቸው በመመለስ በህዝባችን ላይ እየደረሰ ያለውን የሀዘን ብትር ሊያስቆም ይገባል፡፡

የአማራ ህዝብም  አዴፓ እርምጃ ካልወሰደ ልጆቹን ወደ ክልሉ በማምጣት ከሞትና ከአካል ጉዳት ሊታደጋቸው ይገባል፡፡  

ተማሪዎችን ወደ ክልላቸው በመመለስ  የወደፊቱን  የአማራ ህዝብ  በምሁራን ድርቅ  ከመመታት እንታደግ!  

መለስ ዜናዊ መሓሪ ዮሐንስን የመሰሉ እሳት የላሱ ልጆችን ተክቶ አልፏል! (ዳግማዊ ጉዱ ካሣ)

በጣም ታሪካዊ ታሪክ በሀገራችን እየታዬ ነው፡፡ ሁሉም ነገር ግራ የሚያጋባ ነው፡፡ የቱን ይዘህ የቱን እንደምትጥልም አታውቅም፡፡ የዐይን ማረፊያ፣ የጆሮ መጽናኛ የሚሆን ደግ ነገር ለማግኘት ቀኑን ቀርቶ ዓመቱን በሙሉ ብትኳትን አሁን ባለው ወቅታዊ የኢትዮጵያ ሁኔታ አንድም ነገር አታገኝም፡፡

የመሓሪ ዮሐንስ ጉዳይ ደግሞ ትንሽ ለየት ይላል፡፡ በትራግይ ቲቪ የትግርኛ ፕሮግራም እንደተከታተልኩት በርሱ እምነት ኢትዮጵያ ውስጥ ዴሞክራሲ ይቅርና መንግሥትም የለም፡፡ በዚያ ሰሞን የተላለፉ የግፉኣን ሰቆቃም የነዶ/ር ዐቢይ ቅንብር የውሸት ድራማ ነው – ተጋሩን ለመነጠልና በሌሎች ለማስመታት፡፡ ትግራይ ቲቪ በኢትዮጵያ ምድር የሚገኝ ሚዲያ ሣይሆን አልባንያ ወይም ቻይና ውስጥ የሚገኝ እንደአቃቂ ፈረስ ግራና ቀኙን የተለጎመ የወያኔ ጋሪ ነው፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ድምፂ ወያኔ የሚባል አጋዥ የወያኔ ቱሪናፋ መጥቷል፡፡የሁለቱም ዓላማ አንድ ነው – ወያኔን ወደ ቀድሞ ሙሉ ክብሩና ግርማው መመለስ፡፡ ከዚም በኋላ ኢትዮጵያና ሕዝቧ ላይ ለ27 ዓመታት እንዳደረጉት ጥሬ እንትናቸውን በአራቱም ማዕዘን መልቀቅ፤ ጥሬ ብስናታቸውን ማቀርሸት፡፡ ከዚያም ሀገሪቱን ማግማትና የፈጣሪን አፍንጫ ሳይቀር በቁናሳቸው መቁረጥ፡፡ ይሄኛውንስ አያ’ርግብን፡፡ ህልም እልም፡፡ እነዚህኞቹን ደግሞ ጥቂት እንያቸው፡፡…

ዛሬ ጧት ደግሞ በወልቃይት ድረገፅ ያው እሳት የላሰ የመለስ ልጅ በትግርኛ ተናገረው ተብሎ ወደ እንግሊዝኛ ተተርጉሞ እንዳነበብኩት ከማስገረም አልፎ ሰዎቹ ምን ዓይነት የዕብደትና የጉሽ ጠላ ስካር ከፍተኛው ደረጃ ላይ እንደደረሱ በመገመት ክፉኛ ያሳዝናል፡፡ እነዚህን ሰዎች ከዚህም ሳይብስባቸው ወደ ጠበል የሚወስዳቸው ጤናማ ሰው ጠፋና እነሱም ሀገራችንም ተያይዘን ችግር ውስጥ ገባን፡፡ ይሄ ሆድ ለካን ስንቱን ያሳያል!

እውነትም መለስ አልሞተም፡፡ ብዙ ታዳጊ ወጣትና ጎልማሣ መለሶች አሉ፡፡ ትግራይ ቲቪን ክፈት፤ድምፂ ወያኔን ቲቪና ሬዲዮን ክፈት፤ “ህገ መንግሥቲ ተጣሂሹ፤ ህገ መንግሥቲ ይኮበር” ሲሉ በብዛት ታገኛቸዋለህ፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ እንዲያ ሲረገጥ፣ የኢትዮጵያ ወጣት እንዲያ ሲኮላሽና በየእስር ቤቱ በወያኔዎች ሲደፈርና በሲዖል ትሎች ሲንገበገብ፣ ወያኔ ትግሬ ከየጉራንጉሩ እየተጠራራ የኢትዮጵያን ሀብትና ሥልጣን በግላጭ ሲቀራመት፣ ቤንሻጉልና ሶማሌ – ጉሙዝና አፋር ክልሎች በወያኔ የእጅ አዙር ሰላዮችና የሦስተኛ ክፍል ምሩቃን  ጄኔራል ተብዬዎች ተይዘው ሀብታቸው ሲቦጠቦጥና በይምሰል ፌዴራሊዝም ሀገር ስትፈርስ ትንፍሽ ያላሉ ተጋሩ ዛሬ የነካቸው ነገር በውል ሳይታወቅ “ህገ መንግሥት ይከበር” ብሎ ማናፋት ነጋ ጠባ ከአፋቸው የማይለይ የዘወትር ጸሎታቸው ሆኗል፡፡መቼም ሀፍረትና ይሉኝታ ከትግራይ ምድር ጠቅልላ ከወጣች ብዙ ዓመታትን አስቆጥራለች – ሊያውም ጥንትም በዚያ ሥፍራ ኖራ ከሆነ፡፡ አንድ ትልቅ ክፍለ ሀገር በብዙ መለሶች እየታመሰች በምትታይበት የፉከራና የሽለላ ቱማታ ዘመን “ወያኔዎች ብቻቸውን ናቸው” እያሉ በመጽናናት ከፊት ለፊት የተደቀነን መራራ ትግል ለማንኳሰስ መሞከር አደጋ እንዳለው መጠቆም በቂልነት ማስፈረጅ የለበትም፡፡ ወንድሜ የበላን ያብላላዋልና እንኳንስ ለዘመናት የተረጨ የዘረኝነት መርዝ ታክሎበትና ትንሽም በላ ብዙ በስሜት የታወረ ወገናዊነት በምክንያት የተደረደረን እውነት ክፉኛ ሊገዳደር መቻሉ ግልጽ ነውና ስንቅና ትጥቅን ጠበቅ ማድረግ ይሻላል፡፡ “ ‹አይመጣም›ን ትተሸ ‹ይመጣል›ን ባሰብሽ” ነው ነገሩ፡፡

ጤናማ ተጋሩ ቢቆጠሩ አሥር የሚሞሉ አይመስለኝም፡፡ ካልሰለቻችሁኝ የምችለውን ያህል መቁጠር ልጀምር – የአርአያ ልጆች ገብረ መድኅንና (ዶ/ር) ኃይሉ  አርአያ፣ የገብረ ሥላሤ ልጆች አስገደና አምዶም ገ/ሥላሤ፣ ጌታቸው ረዳ(ኢትዮሰማይ ድገፅ አዘጋጅ)፣  ወዲ ሻምበል፣ የኢትዮሚዲያው አብርሃ በላይ (በተለይ በሰሞኑ ትንታኔው)፣… ሊያቅተኝ ነው መሰል፡፡ “ቸርነቴን ላብዛው”ና  ሣምራውያን ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት ተጋሩ – በገጠርም በከተማም – በግርድፍ ሥሌት አሥር ሽህ ይሁኑ እንበል ግዴለም፡፡ የማይሞቀው የማይበርደውን ግዴለሽ፣ “ከነገሩ ጦም ዕደሩ” ባይውን እንደኔ ፈሪ፣ በሀገራችን ምን እየተካሄደ እንዳለ እንኳን የማያውቀውን ገበሬና ባላገር  … ለጊዜው ከቁጥር ሳናስገባ እንተወው፡፡ በተረፈ ሆድ ይፍጀው፡፡ …..

“ከሰው መርጦ ለሹመት፣ ከእንጨት መርጦ ለታቦት” አዲዮስ! ዱሮ ቀረ፡፡በኔ የልጅነት ዘመን ሰው ሲሾም ተጠንቶ ነበር፡፡ ዛሬ ዛሬ ግን ቅድሚያው ጥናት የሰውዬው/የሰውዬዪቱ ዘር ሆነና ተቸገርን፡፡(ሴትም ሰው ናት!)

ይቺ “ምክትል ከንቲባ” እና “ምክትል አገረ ገዢ(በዘመኑ ቋንቋ ፕሬዝደንት)” የምትባል  አዲስ ፈሊጥ ከየት የመጣች ትሆን ግን? ዋናው ከንቲባና ፕሬዝደንት ጨረቃ ላይ ወይንስ በመሬት ውስጠኛ ክፍል ሰላማዊ ውቅያኖስ ወለል ላይ እንደምትገኝ በምትታመነው ቤርሙዳ ከተማ ውስጥ ይገኙ ይሆን? ደግሞስ ይቺ የፉጌ አባባል የማትፎርሸው እስከመቼ ድረስ ነው? የትግራዩስ ግዴለም – መለስ ቢሞትም በመንፈስ አብሯቸው ስላለ እስከወዲያኛው በምክትልነት ቢጠሩ ግልጽ ነው፡፡ የአዲስ አበባው ማለቴ የፊንፊኔው ምን የሚሉት ምክትል ከንቲባ ነው? ስላልገባኝ ነው፡፡ … ብዙ ሰዎች በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው በትግርኛና በኦሮምኛ ካማርኛ በቀር በሌላም ሲናገሩ ሌሎች ሰዎች የሚረዱዋቸው አይመስላቸውም፡፡ ሞኝነት ነው፡፡ የቋንቋን ባሕርይ ካለመረዳት የሚመነጭ ሞኝነት፡፡ በቋንቋ ምክንያት የዘረኝነት ልምሻ የሚጠናወታቸው ሰዎች ቋንቋ በዘር ሐረግ የሚተላለፍ ይመስላቸዋልና እነሱ ሲናገሩ የሚያዳምጡና የሚረዱ የነሱ “ወገኖች” ብቻ ይመስሏቸዋል – ይህ ነገር ጥናት የማያስፈልገው ጠቅላላ እውነት ነው፡፡…

አቶ ማነው እቴ ዶ/ር ደብረፅዮን ገረሚቻኤል የትግራይ ም/ፕሬዝደንት፤ ኢንጂኔር ታከለ ኡማ የአዲስ አበባ ከተማ ም/ከንቲባ መባል ከተጀመረ ዓመት ሊደፍን ምንም ያህል አልቀረውም – በለውጡ ሰሞን ከተሾሙ፡፡ የነዚህን ቦታዎች ዋና ሰው ለማግኘት ስባዝን እኔም ዓመት ሊሞላኝ ነው፡፡ እንታይ እዩ ጉዱ! ስለምታይ ነው እንዴ እንደዚህ የሚያጩቦረቡሩን በሌለ ባለሥልጣን? በውነት ምን ማለት ነው? ነው ሁላችንንም ገሪባ ‹ባላገር› አደረጉን?

እውቴን ነው – ዱሮ ሹመት እንደገና ዳቦ ለማንም ከበር መልስና ከበር ውጪ የሚታደል አልነበረም፡፡ በቆዬው ሲገርመኝ የሰሞኑ ደግሞ ከማስገረም አልፎ በጅልነት እያሳቀኝ ነው፡፡ ክፋቱ ከሚሾሙት ሰዎች መካከል አንዳንዶቹን በሚገባ አውቃቸዋለሁ፡፡ እናም እንደመጥፎ ዕድል ሆኖብኝ ሳጤናቸው አንዳቸውም ለሹመት የሚበቁ አይደለም፤ ግን ግን “አንተ የምታውቃቸው ሰዎች ሁሉ እንዴት ወልጋዳ ሊሆኑ ቻሉ?” ብላችሁ ደግሞ መመለስ የሚያቅተኝን ጥያቄ እንዳትጠይቁኝ፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ በአብዛኛው እውነተኛው ጽንስ ተወልዶም በሆድ ውስጥም እየጨነገፈ እንግዴ ልጁ ስለሚያድግ አሁን አሁን ሰው ብናጣ አይፈረድብንም፡፡ በክፋት አምባሳደርነታቸው ምክንያት ጥሎባቸውና በነሱም ስለሚብስ በወያኔዎች እንፈርዳለን እንጂ እኛም እኮ የለየልን ሟደድ ጅቦች ሆነናል፡፡ እስኪ በየመሥሪያ ቤቱ ሂዱ – በሙስናው መስፋፋትና በእምነት መጥፋት ትደነግጣላችሁ፡፡ ለእውነት መቆም ፋራነት ነው፤ለሀገር ማሰብ ጅልነት ነው፤ ለወገን ማሰብ ዕርም ሆኗል፤ በተገኘው መንገድ ሁሉ ራስን በገንዘብና በሥልጣን መካብ የሥልጡንነትና የዘመናዊነት መለኪያ ሆኗል፤ የብዙዎቻችን የዘመኑ ፋሽን “የትም ፍጪው ዱቄቱን አምጪው” ከሆነ ሰነበተ፡፡ አዲዮስ ኢትዮጵያ! አዲዮስ ሰብኣዊነት! አዲዮስ ብሔራዊ የሀገር ፍቅር ስሜት!

ወያኔ በረጨብን ዲዲቲ ምክንያት ዘረኝነት ልንወጣውና ልናባርረውም ያልቻልነው ችግር መሆኑን ማመን አለብን፡፡ እኔም በበኩሌ ለ20 እና 30 ዓመታት ላያችን ላይ ተከምሮ እንደዛር ሲያስጨፍረን የነበረ የዘረኝነት ልክፍት በአንድ አዳር እንደማይለቀን አውቃለሁ፡፡ ግን ግን እንዲህ ማድረግ የምንችል ይመስለኛል፤ እንዲህ – ከዘረኝነት አረንቋ ተዘፍቀን መንጠራወዛችን የማይቀርልን ዕዳ ከሆነ በዘራችን ውስጥ የሚገኙ የተማሩና ከሙስና የፀዱ፣ በዕድሜም ሆነ በተሞክሮ የበሰሉ፣ ቀናነትና ሕዝባዊ ወገንተኝነት ያላቸው የራሳችን ጎሣ አባላትን እናፈላልግና እንሹም፡፡ በቃ፡፡ ይሄ ትልቅ መፍትሔ ነው፡፡ እርግጥ ነው – ድብቅ ዓላማና ፍላጎት ካለን እነዚህን መሰል የኛ ጎሣ አባላት ነገር ሊያበላሹብን፣ ሕዝብንም ሊያነቁብን  ይችላሉ ብለን እንፈራቸዋለንና ማስጠጋቱንና መሾሙን አንፈልገው ይሆናል፡፡ ይሁንና ለልጆቻችን ቀጣይ የወደፊት ሕይወት ስንል በዚህች መንገድ ጥቂት ለመጓዝ እንሞክር፡፡ እንዲህም ስል ከፍ ሲል የተናገርኩትን በመርሳት አይደለም – እንዲያው ከንፍሮም ጥሬ ይወጣልና በመጠኑ የተበላሹና በቀላሉ ሊስተካከሉ የሚችሉ ዜጎች ከሀገር ውስጥም ከውጪም ከተገኙ በሚል ተስፋ ነው፡፡ እንጂ እደግመዋለሁ – ዘመናችን አበለሻሽቶናል፡፡ ካህኑና ሼካው ሳይቀሩ አይደሉም እንዴ ከላይኛው የፈጣሪ መንገድ ይልቅ የታችኛውን ሰው-ሠራሸ ገንዘብ መርጠው እንደ ሙሤ ጽላትና እንደመሀመድ ካባ በርንና ዶላርን የሚያመልኩት?… አንተዋወቅም?… እ?

ወደ አስቂኙ ሹመታችን ልመልሳችሁ፡፡ ለምሣሌ ማንትስ የተባለችውን ካብ አይገባ ድንጋይ አምባሳደር አድርጎ ከመሾም ስንትና ስንት በሳልና ፖለቲካ ዐዋቂ የኦሮሞ ምሁራን ሞልተዋል፡፡ የአዲስ አበባን አካባቢ ሙልጭ አድርጎ በሙስና ዘረፈ የተባለን ሰው በአዲስ የወይን ጠጅ አቅማዳ ውስጥ ጨምሮ ሥራን ከማበላሸትና ትዝብት ውስጥ ከመግባት ስንትና ስንት ኦሮሞ ኢንጂኔሮች በሀገር ውስጥም ከሀገር ውጪም አሉ፡፡ ብዙ ጥፋቶች ሲፈጸሙ እናያለን፡፡ እንናገርማለን – ግን አሁንም ሰሚ የለም፡፡ ይሄ የአራት ኪሎ ወንበር በአሲድ ካልታጠበ ወይም በሸንኮራና በለብቃየሱስ ፍቱን ፀበሎች ለ21 ዓመታት በተከታታይ ካልተጠበለ ምድረ ጆሮ-አልባ እየተሰገሰገበት የሕዝብና የሀገር ዋይታና ልቅሶ መቀጠሉ ነው፡፡ እኔስ የምሥራች ቀኔ ቀርባለች ልገላገል ነው፡፡ የዚህችን ሀገር ነገር ከ’ንዳለመስማት የበለጠ ፀጋና ቡራኬ ደግሞ የለም፡፡ የሰዎች ‹ሬዚስታንስ›ና ‹ፊውዝ› ደግሞ ይገርመኛል፡፡ ምነው እኔንም ኬሬዳሽ ባደረገኝ!

በነገራችን ላይ የዚህች ሀገር አንዱና ዋናው በሽታ አንድን ሰው ስንወድና ስናፈቅር ለከት የሌለን መሆናችን ነው፡፡ በልክና በምክንያት ማፍቀርና መጥላት አናውቅበትም፡፡ ስናሳዝን! አንድን ሰው ስናፈቅር ወዲያውኑ – በአዲስ የእግሊዝኛ ልሣን ልናገር እባክህን – ወዲያውኑ immaculize and/or omni-potentize and/or omniscientize and/or omni-presentize … እናደርገውና ከፍ ሲል ከእግዚአብሔር ዝቅ ሲል ደግሞ ከመላእክት ጎን እናስቀምጠዋለን፡፡ ያንን ሰው ሲነኩብን እናብዳለን፤ infatuation እና/ወይም calf’s love ይሉታል ፊደል የቆጠሩቱ፡፡ ብሃፂሩ እንታወርና እናርፋለን፡፡ እሱም ፍቅራችንን ወይም ጥላቻችንን በአግባቡና በአመክንዮ manage ማድረግ አይችልም ወይም ያቅተዋል፡፡ ስለሆነም ስናፈቅረው ክንፍ አውጥቶ አየር ላይ እስኪንሳፈፍ ያብጥብናል፤ ከኛም ከመሬትም ይርቃል፡፡ ሲወርድ ግን አይጣል ነው – እየተምዘገዘገ ወርዶ ይፈጠፈጣል – ኮድኩዶ የያዘን ቋሚ ባህላችን፡፡ ያን መሰሉን ሰው ካስቀመጥንበት እግዚአብሔራዊ መንበር ስናጣው ደግሞ በተቃራኒው ጨርቃችንን እንጥላለን፡፡ ለዚህ ነው ፍቅራችንም ጠባችንም ሳያምር ቀርቶ ለዘመናት ስንወዛገብ በመኖራችን ምክንያት በመጨረሻው መጨረሻ እንደዚህ ያገር ቂጥ ሆነን የቀረነው – “ያገር መቀመጫ” ብለው ስለማያምር ነው፡፡ ብታምንም ባታምንም ችግራችን ሁሉ የሚሽከረከረው እዚህ አካባቢ በምናገረውና አንተም አንቺም ጠንቅቃችሁ በምታውቁት ነገር ዙሪያ ነው፡፡ እኛ ያላሳዘንንን ታዲያ ማን ያሳዝን? “እያደሩ ማነስ” በሚል አዝማች ዘፈን ወጥቶ ይሆን? I do not really know if I am a little bit pessimist. It is good, of course, to be optimist, when situations allow. Do they allow now? It may depend upon our perspective.

ታከለ ኡማን ዕጥፍ ድርብ የሚያስከነዱ ኦሮሞዎች ጠፍተው አይደለም፤ እነእንትናን በሰማይና በምድር የርቀት ልዩነት የሚበልጡ ኦሮሞዎች ታጥተው አይደለም፡፡

  ኤዲያ ምን አስለፈለፈኝ ግን … ምንስ ጥልቅ አደረገኝ፡፡ ስደተኛ በመሸበት አድሮ መሄድ እንጂ በሰው ቤት ምን ያገባዋል? ግን አንዱ በአንዱ ሲስቅ በምናባክነው ወርቃማ ጊዜ እየጠለቀች ያለችዋን ጀምበር እጅግ ከመሸም ቢሆን ለመጠቀም ሁሉም ብልኅና አስተዋይ ቢሆን ይሻለዋል፡፡ ባዶ እግሩን የሚሄድ ሕዝብ መሀል፣ በውኃ ጥም እየሞተ ያለ ሕዝብ መሀል፣ ሊያውም ለማይረባ ህክምና ሲባል በወሳንሳ ሸክም ብዙ ኪሎ ሜትሮችን የሚጓዝ ሕዝብ መሀል፣ በቀን አንዴ እንኳን ከደረጃ በታች የሆነ ምግብ መቅመስ የማይችል ሕዝብ መሀል፣ በትምህርት ዕጦት በደነቆረ ሕዝብ መሀል፣ ስደትና ሞት ርስተ ጉልቱ በሆነ ሕዝብ መሀል፣ ድህነት ቤቱን በሠራበት ህዝብ መሀል፣ ጎጠኝነትና ዘረኝነት ያሰከረው ወጣትና ጎልማሣ በወያኔ ከንቱ ልፋፌ-ጽድቅ ተማርኮ እርስ በርሱ ሊጨራረስ ያሰፈሰፈ ውሪ መሀል፣ በጥላቻና ቂም በቀል አብደው ወገንን ከወገን ለማፋጀት የቋመጡ አክቲቪስት ተብዬዎች በሚርመሰመሱበት ሕዝብ መሀል፣ ዕድሜ የማይገድባቸው ዶን ኪሾቶች በሞሉባት ሀገር ውስጥ  …. ከድሃው በተሰበሰበ የግብር ገንዘብ በአውሮፓ ሊሞዝንና በአውሮፓ ስታይል በተሠራ ቤት እየኖሩ በፖለቲካ ሰበብ ሕዝብ ላይ መሽናትና ማስታወክ የሚቀርበት ዘመን እንዲመጣ በተለይ እኔን መሰል ጭቁኖች ሌት ከቀን እንጸልይ፡፡ … ብቸኛ መድሓኒታችን ፈጣሪ ነው፡ የሰውን እስኪያንገሸግሸንና እስኪያቅረን አየነው፡፡ አጎቴ በርሀብ እየሞተ በከፈለው የግብር ገንዘብ ጡረታ ለወጣ ፕሬዝደንት ለቤት ኪራይ ብቻ በወር ከ400 ሽህ ብር በላይ ሲከፈል እንደማየት የትውልድና የመንግሥት መረገም የለም፡፡ ብዙ ጉድ ነው ያለው፡፡….ብቻ እሱ ይፍረድ! ግን ምን አገባኝ!!…..

ቀጣይዋን ግጥም ከሰው ጽሐፍ አንብቤ በቃሌ ጭምር ይዣታለለሁ – ተፅዕኖዋ ቀላል አይደለም፡፡

“ ‹እኔ ምን አገባኝ!› የምትሏት ሐረግ፤

እሱ ነው ሀገሬን ያረዳት እንደበግ፤”

በሚል ግጥም ልጽፍ ብድግ አልኩኝና፤

“ምን አገባኝ!” ብዬ ተውኩት እንደገና፡፡ (ደስ አትልም?)

Ma74085@gmail.com

የብሔር ፖለቲካ ሁልጊዜ ጥርጣሬን እንጂ መተማመንን አያመጣም – አቶ ኦባንግ ሜቶ

“ሃገሩም፣ ሕዝቡም፣ መሬቱም አየሩም እርቅ ይፈልጋል”

• የብሔር ፖለቲካ ሁልጊዜ ጥርጣሬን እንጂ መተማመንን አያመጣም
• ሁላችንም የምንመኛትን ኢትዮጵያ፣በተናጠል በመሯሯጥ አንፈጥራትም
• እርቁ ለወጣቶቻችን የሞራል ልዕልናን የሚያመጣ መሆን አለበት
• እርቅ ለከባድ ወንጀል አቋራጭ ማምለጫ መሆን የለበትም

የኢትዮጵያ መንግስት የብሔራዊ እርቅና መግባባት ጥያቄ በተነሳ ቁጥር “የተጣላ የለም” እያለ ጉዳዩን ውድቅ ሲያደርገው ቆይቷል፡፡ አሁን ግን የጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ መንግስት፤ የእርቅን አስፈላጊነትን አምኖበት ተነሳሽነቱን በመውሰድ
ብሔራዊ የእርቅ ኮሚሽን አቋቁሟል፡፡ “የአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ” መስራችና የሰብአዊ መብት ተሟጋቹ አቶ ኦባንግ ሜቶ፤ የእርቅ ኮሚሽን መቋቋሙን በእጅጉ ይደግፉታል – እርቅ ለሃገሪቱ ፈውስን ያመጣል በማለት። ዶ/ር ዐቢይ የእርቅ ኮሚሽን ማቋቋማቸው አርቆ
አሳቢነታቸውን ያሳያል ሲሉም አድንቀዋል። ለመሆኑ የእርቅ ኮሚሽን ፋይዳው ምንድን ነው? በእርቅ ሂደት ውስጥ የሚሳተፉት
እነማን ናቸው? እርቅ እንዴት ይፈጸማል? በሚሉና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ፣ አቶ ኦባንግ ሜቶን አነጋግሯቸዋል፡፡ እነሆ፡-

መንግስት ብሔራዊ የእርቅ ኮሚሽን አቋቁሟል፡፡ በአሁኑ ወቅት የእርቅ ኮሚሽኑ ለአገሪቱ ያለው ፋይዳ ምንድን ነው?
የእርቅ ጉዳይ በጣም ዘግይቷል፡፡ ብዙ ስንጠብቀው የነበረ ጉዳይ ነው፡፡ እርቅ ማድረግ ለሃገሪቱ ፈውስን ያመጣል፡፡ አሁን መታሰቡ በራሱ መልካም ነው። ሃገሪቱ ለውጡን ወደፊት እንድታሻግርና ብሔራዊ መግባባት እንዲፈጠር፣ እርቅ ትልቁን ድርሻ ይይዛል። እርቅና ብሔራዊ መግባባት የተለየ ትርጉም የለውም፤ ሰላም መፍጠር ነው ትርጉሙ፡፡ እርቅን አልፈልግም ሲል የነበረ፣ ሰላምን አልፈልግም ማለቱ ነው፡፡ እርቅን እፈልጋለሁ የሚል ደግሞ ሰላምን አብዝቶ የሚሻ ነው። የአንድነት ምንጩ ሰላምና ብሔራዊ መግባባት ነው፡፡ ብሔራዊ መግባባት ደግሞ የሚመጣው በእርቅ ነው። አሁን ሃገሩም፣ ሕዝቡም፣ መሬቱም አየሩም እርቅ ይፈልጋል፡፡ ሁላችንም ደምተናል፣ ብዙ ቁስል አለን፣ መአት ግፍን ተቀብለናል፡፡ ይሄን መሻር የሚቻለው በእርቅ ብቻ ነው፡፡ እርቅም ብሔራዊ መግባባትን ያመጣል፡፡ የኛ ድርጅት አንዱ አላማ “ለመተማመን እንነጋገር” የሚል ነው፡፡ የሃገራችን አንዱ ችግር መተማመን ማጣት ነው፡፡ የብሔር ፖለቲካ ነው የተጫነብን፡፡ የብሔር ፖለቲካ ሁልጊዜ ጥርጣሬን እንጂ መተማመንን አያመጣም፡፡ ባለፉት 13 ዓመታት የብሔር ብሔረሰቦች ቀን መከበሩ በራሱ ያለመተማመናችን ውጤት ነው፡፡ አንድነት የሚል ቃል በዚህ የብሔር ብሔረሰቦች በአል ላይ ብዙም ሲነገር አይስተዋልም። አሁን ያለፉትን 27 ዓመታት ያለመተማመን ምዕራፍ ዘግተን፣ ቁስሎችን በእርቅ አክመን ወደፊት መሻገር፣ ከፊት ለፊታችን ያለ መልካም ዕድል ሆኖ ይታየኛል፡፡
የእርቅ ኮሚሽን የሚያስፈልጋቸው እንደኛ ዓይነት አገራት ብቻ ናቸው ወይስ–?
በርካታ አገራት የእርቅ ኮሚሽን አላቸው፡፡ በቋሚነት ነው የሚሰራው፡፡ እኔ በምኖርበት ካናዳ የእርቅ ኮሚሽን አለ፡፡ በአውስትራሊያና በሌሎች አገራትም አለ፡፡ እኛ ብዙ ችግር አለብን፤ በዚያው ልክ የዳበረ የእርቅ ባህላዊ ስርአት አለን፤ ነገር ግን የእርቅ ኮሚሽን የለንም፡፡ ብዙም ችግር የሌለባቸው አገራት በቋሚነት የእርቅ ኮሚሽን ካላቸው፣ እኛ ብዙ ችግር ያለብን እንዴት አይኖረንም? ከአፄ ኃይለ ሥላሴ መንግስት ከስልጣን መነሳት ጀምሮ በደርግ፣ በኢህአዴግ ዘመን—እስካሁን ብዙ ቅራኔዎች ናቸው በሀገሪቱ ያሉት፡፡ በቀይ ሽብር እርስበርሳችን ተጨራርሰናል፡፡ ከቀይ ሽብር ጎን ለጎን የእርስበርስ ጦርነት ውስጥ ነበርን፡፡ ኢህአዴግ ከገባ በኋላ ስለ ሃገር አንድነት የተወራበት አጋጣሚ የለም፡፡ አንድ ህዝብ፣ አንድ ቤተሰብ እንደሆንን ሳይሆን የተለያየን እንደሆንን ነው ሲነገር የኖረው፡፡ ይሄ የህዝባችንን ስነ ልቦና ገዝግዞታል፡፡ ለዚህ ሁሉ እርቅ ያስፈልገናል፡፡ ከገጠር እስከ ከተማ – በእያንዳንዱ ቀበሌና ጎጥ እርቅ ያስፈልጋል፡፡ እኛ ከዚህ ቀደም ያቋቋምነው ድርጅት በዋናነት እርቅ ላይ አተኩሮ መሥራት ነበር ዓላማው። በወቅቱ ብዙ ነገር ሞክረን አልተሳካም፡፡
ምን ነበር የሞከራችሁት?
በሃገራችን እርቅ ለማምጣት ነበር የሞከርነው። ነገር ግን ባለው መንግስት ተቀባይነት ባለማግኘቱ አልተሳካም፡፡ አሁን ዶ/ር ዐቢይ የእርቅ ኮሚሽን ማቋቋማቸው፣ አርቆ አሳቢነታቸውን ያሳያል፡፡ እርቅ ቋሚ ነው መሆን ያለበት፡፡ እኛ የራሳችን አገራዊ ባህልና ወግ አለን፡፡ በሱ መሰረት የሽምግልና ባህላችንን ተጠቅመን ነው እርቅ ውስጥ መግባት ያለብን፡፡ በዚህ ሃገር እኮ እንደ ህዝብ፣ እንደ ሃገር እስከ ዛሬ ያቆየን የመንግስት መኖር አይደለም፤ ባህላችንና የሽምግልና ጥልቅ መሰረታችን ነው፡፡ እኛን እንደ ኢትዮጵያ ያቆየን የቤተ-መንግስት ህግና አዋጅ ሳይሆን የባህላዊ እርቅና ሽምግልና ስርአታችን ነው የሚል እምነት አለኝ፡፡ የኛ ሃገር ችግሮች በሙሉ የተፈቱት በዛፍ ጥላ ስር እንጂ በመስታወት በተንቆጠቆጠ ዘመናዊ ህንፃ ውስጥ አይደለም፡፡ አሁንም እርቅ ስንል ህገ መንግስቱ የውጪ ሃገር “ኮፒ” ነው እንደሚባለው ሁሉ፣ የእርቅ ስርአቱ “ኮፒ” እንዳይሆን መጠንቀቅ አለብን፡፡ “ቅጂ” ያው “ቅጂ” ነው፤ ኦርጂናል አይሆንም፡፡ እኛ የራሳችን የእርቅ ባህል አለን፡፡ ይሄን አውጥተን መጠቀም አለብን፡፡ እኔ ወደዚህ ከመጣሁ በኋላ በኦሮሚያ፣ ጉራጌ፣ አማራና ሌሎችም አካባቢዎች ያሉ የሽምግልና ስርአቶችን ስመለከት ነበር የቆየሁት፡፡ አስደናቂ ሆኖ ነው ያገኘሁት፡፡ ለዚህ ነው ሀገሪቱ በቤተ-መንግስት ህግ ሳይሆን በሃገር ሽምግልና ነበር የቆመችው ያልኩት፡፡
አገራዊ እርቅ እንዴት ነው የሚፈጸመው?
እርቅ ማለት ያበጠ ቁስልን ማዳን ነው፡፡ ያበጠ ቁስል የሚድነው ውስጡ ያለው ቆሻሻ ሲወጣ ብቻ ነው፡፡ በቁስል ላይ የሚያደርቅ መድሃኒት ከማድረጋችን በፊት ቆሻሻውን እንደምናወጣ ሁሉ በደልንና መገፋፋትን በእርቅ ለማዳን ከፈለግን፣ በመጀመሪያ ያበጠው ቁስል ፈንድቶ ቆሻሻው መፅዳት አለበት፡፡ ይሄን ክፉ ነገር ከእያንዳንዳችን ውስጥ የምናወጣው በውይይት ነው፡፡ በመነጋገር ነው፡፡ ሃገራችን እኮ ባለፉት 27 ዓመታት ጨለማ ውስጥ ነበረች፡፡ አሁን ዶ/ር ዐቢይ ከመጡ በኋላ ትንሽ ብርሃን አግኝተናል፡፡ በብርሃን ውስጥ እውነትን መፈለግ ይቻላል፡፡ እውነት ብርሃን ነው፡፡ ጨለማ ብርሃንን እንደሚሸሽ ሁሉ ውሸት እውነትን ይሸሸዋል፡፡ ፊት ለፊት አይጋፈጠውም፡፡ ዛሬ ብርሃን ሲመጣ ሌቦቹ፣ ነፍሰ ገዳዮቹ ሸሽተዋል፡፡ እርቅን ስንጀምር ከጨለማው ሳይሆን ከብርሃኑ ነው። ከብርሃን ስንጀምር በኃይል እያበራን፣ ጨለማውን እየገፈፍን እናበራዋለን፡፡ ለዚህ ደግሞ እውነተኛ እርቅን የሚፈልጉ ሃገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን ሞልተዋል። እነሱን ፊት አውራሪ ማድረግ ይቻላል፡፡ ዶ/ር ዐቢይ የጀመረው ጥሩ ስራ አለ፡፡ ያንን ሁላችንም ጉልበት ሆነን የበለጠ ልናሰፋው ይገባል፡፡ በሃገራችን ቁርሾዎችን በእርቅ ዘግተን መሻገር የምንችልባቸው እድሎች በርካታ ነበሩ፤ ግን አልተጠቀምንባቸውም። አሁን ከንቀት ባህሪ ወጥተን እያንዳንዱን መልካም ነገር መጠቀም ያስፈልጋል፡፡ የትም አይደርሱም የሚለው ንቀት አይሰራም፡፡ ወያኔዎች ከጫካ ሲመጡ “እነዚህ የትም አይደርሱም” ተብለው ነበር፤ ነገር ግን ባለፉት 27 ዓመታት የት እንደደረሱ በሚገባ አሳይተውናል። ይሄን መልካም አጋጣሚ እንዳናባክነው ሁላችንም የየድርሻችንን መወጣት አለብን፡፡ ሁላችንም የምንመኛትን ኢትዮጵያ፣ በየፊናችን በተናጠል በመሯሯጥ አንፈጥራትም፡፡ እየተደማመጥን የበራውን ጥቂት ብርሃን እየተከተልን፣ በየመንገዳችን አብሪዎችን እየጨመርን ስንጓዝ ነው፣ ሁላችንም የምንመኛትን ብሩህ ኢትዮጵያን ልናገኝ የምንችለው፡፡ ለዚህም ምሁራን፣ ፖለቲከኞች፣ የሃይማኖት አባቶች ከፍተኛ ኃላፊነት አለባቸው፡፡
ሁልጊዜም ስለ እርቅ ሲነሳ፣ ማን ከማን ጋር ነው የሚታረቀው? የሚል ጥያቄ ይሰነዘራል፡፡ በእርቁ የሚካተቱት እነማን ናቸው?
ማን ከማን ጋር ነው የሚታረቀው? የሚለው ጥያቄ ሁሌም ይገርመኛል፡፡ ማን ያልተጣላ አለና ነው ይሄን የምንለው? ከራሳችን ጋር እንኳ ሳይቀር ተጣልተናል እኮ! በብሔር ተከፋፍለን፣ በፖለቲካ ተከፋፍለን ተጣልተናል፤ ተቋስለናል፡፡ በምድራችን ላይ ያልተጣላ ሰው የለም፡፡ ስለዚህ እርቁ መንፈሳዊ ነው። እርቁ ከራስ ይጀምራል፡፡ ከራሳችን ጋር ስለተጣላን ሁላችንም በቅድሚያ ከራሳችን ጋር ታርቀን፣ ክፉ ሃሳብን ከልባችን አንቅረን አውጥተን ጥለን፣ አዲስ የይቅርባይነት ልብን ማግኘት አለብን፡፡ ከዚያ ወደ እርስበርስ እርቅ መሄድ እንችላለን፡፡ እንደሚታወቀው በሃገራችን አንድም በብሔራዊ መልኩ የተቋቋመ የፖለቲካ ድርጅት የለንም። ፓርቲዎች በየብሔራቸው የተሰፉ ናቸው። ኢህአዴግ የነፃ አውጪዎች ስብስብ ሆኖ ነው ሀገር ሲመራ የቆየው እንጂ ብሔራዊ የአንድነት ሃይል ሆኖ አልነበረም፡፡ ነፃ አውጪነት በራሱ እርቅ ያስፈልገዋል። እኛ በብሔር፣ በጎጥ የተከፋፈልን ነን። በዚህ ብዙ ተጎዳድተናል፡፡ እርቅ ያስፈልገናል። በሀገራችን ያልተጣላ ሰው የለም፡፡ ብሔራዊ (ህብረ ብሔራዊ) ተቋም የለንም፡፡ ሁሉም ጎጡን እያሰበ ነው የሚጓዘው። በዚህ ሁላችንም ተጣልተናል፡፡ ኢትዮጵያን (ምድራችንን) ማሰብ የተውነው ለዚህ ነው፡፡ ባንጣላ ኖሮ 1.8 ሚሊዮን ዜጎች አይፈናቀሉም ነበር፡፡ የተጣላ ባይኖር ኖሮ፣ አሁን እኔና አንተም የእርቅን ጉዳይ መነጋገር አያስፈልገንም ነበር፡፡ አንዱ አንዱን ሲበድል ኖሯል፤ በሁሉም መንገድ በደሉ ደርሷል፡፡ ድሮ መሬት ላራሹ ነበር ትግሉ፤ ነገር ግን በኋላ ይሄ ተቀይሮ መሬት ለብሔሩ፣ መሬት ለጎሳው እያልን ሌላውን ወደ መግፋት ነው የተገባው፡፡ በብሔራዊ ደረጃ ማሰብ እየቻልን፣ ወደ ጎጠኝነት ነው የወረድነው፡፡ ከመሬት ላራሹ ሰፊ ፅንሰ ሃሳብ ወርደን፣ ወደ መሬት ለብሔሬ ነው የገባነው። ብዙ በደል ደርሷል፡፡ ብዙ ተበዳድለናል፡፡ ስለዚህ እርቅ በእነዚህ ሁሉ አካላት ዘንድ ያስፈልጋል፡፡
ከአገራዊ እርቁ የሚጠበቀው ውጤት ምንድን ነው?
እርቁ እንደገና ባለሙሉ ሰብዕና አድርጎ እንዲሰራን ነው የሚያስፈልገው፡፡ እንደገና ኢትዮጵያዊነትን እንድንገነባ፣ እንደገና አዲስ የሰብዕና ማንነት እንድንላበስ ነው የሚፈለገው፡፡ አንድን ሰው በሰውነቱ እንጂ በዘሩ፣ በብሔሩ፣ በመልኩ፣ በቋንቋው ሳይሆን በሰብዕናው ብቻ እንድንመለከተው የሚያደርግ እርቅ ነው የሚያስፈልገው፡፡ እርቁ መደማመጥን መከባበርን፣ መዋደድን፣ ቅንነትን፣ የይቅርታ ልማድን የሚያመጣ እንዲሆን ነው መሰራት ያለበት፡፡ ለወጣቶቻችን የሞራል ልዕልናን የሚያመጣ እርቅ እንዲሆን ነው መሰራት ያለበት፡፡ ዛሬ እናቶቻችን ቃና ቴሌቪዥን ተመልካች ሆነዋል። ስለዚህ እናቶቻችን ከቃና፣ ወጣቶቻችን ከምርቃና ወጥተው፣ የሞራል ልዕልናን ተላብሰው፣ ሀገራቸውን ወደፊት እንዲያሻግሩ የሚያግዝ እርቅ ነው መሆን ያለበት፡፡ ኢትዮጵያን በሞራል ልዕልና መገንባት መቻል አለብን፡፡ ሰብአዊነትን የሚገነባ እርቅ ነው የሚፈለገው፡፡
በዚህ እርቅ እነማን ናቸው በዋናነት ተሳታፊ መሆን ያለባቸው?
በትክክል የሃገር ፍቅር ያላቸው ሰዎች በዋናነት እንዲሳተፉ መደረግ አለበት፡፡ በእርቅ ጉዳይ ሰፊ ልምድ ያላቸው አሉ፡፡ እነሱ ተሳታፊ መሆን አለባቸው። የሃይማኖት አባቶች፣ የሃገር ሽማግሌዎች አሉን፡፡ በርካታ ስነ ምግባር ያላቸው ኢትዮጵያውያን አሉ፡፡ ከዶ/ር ዐቢይ የሚጠበቀው እነዚህን ኢትዮጵያውያን በባትሪ መብራት አፈላልጎ ማግኘት ነው፡፡ እነዚህ ሰዎች ከተሰበሰቡ ከእነሱ ብዙ ማትረፍ እንችላለን፡፡ እርቁ የፖለቲካ ጉዳይ አይደለም፤ ኢትዮጵያን እንደ ኢትዮጵያ የማቆየት ጉዳይ ነው፡፡
የእርቅ ባህላችን ተሸርሽሯል፤ የአገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች ተአማኒነት ቀንሷል የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ ከዚህ አንፃር እርቁ ስኬታማ የሚሆን ይመስልዎታል?
ይሄን ከሚሉ ሰዎች አንዱ እኔ ነኝ፡፡ የሃይማኖት አባቶች እኮ የሃይማኖት አባቶች ሳይሆን የፖለቲካ አባቶች ነው የነበሩት፡፡ የሃይማኖት አባቶች እግዚአብሔርን የሚፈሩ ሳይሆን መንግስትን የሚፈሩ ነበሩ፡፡ ሽማግሌዎችም የሃገር ሽማግሌዎች ሳይሆን የመንግስት ሽማግሌዎች ሆነው ነው የቆዩት። በዚያው ልክ ለእውነት፣ ለእምነት፣ ለምድራዊና ሰማያዊ ፍትህ የታገሉ የሞቱ የሃይማኖት አባቶች አሉን፣ ነበሩን። እነዚህ ጥቂቶች ናቸው። እነዚህን እግዚአብሔርን የሚፈሩ ትክክለኛ የሃይማኖት አባቶችና ሽማግሌዎች በባትሪ መፈለግ ነው ያለብን፡፡ እነዚህን ነው የምንፈልገው እንጂ ትናንት በሌላ ጉዳይ ውስጥ የነበሩትን አይደለም። እነዚህን በመምረጥ በኩል ዶ/ር ዐቢይ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ አለባቸው፡፡ ከቀጣፊ ምሁር ይልቅ ያልተማረ፣ ፈጣሪውን የሚፈራ ሰው ይሻለናል። እንደዚህ ዓይነት ሰዎችን ነው በዚህ መድረክ ፊት አውራሪ አድርጎ ማቅረብ፡፡
ከእርቁ በፊት የእውነት አፈላላጊ ኮሚሽን ተቋቁሞ፣ የተፈፀሙ ግፎችና በደሎች መነገር አለባቸው የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ በዚህ ላይ የእርስዎ አቋም ምንድን ነው?
አንዱ መሰራት ያለበት በዚህ ጉዳይ ላይ ነው። እውነትን ከስሩ መፈለግና ማጥራትማ አስፈላጊ ነው። አለበለዚያ አለባብሰው ቢያርሱ በአረም ይመለሱ ነው የሚሆነው፡፡ ገለልተኛ አካል መቋቋም አለበት፡፡ ነፃና ገለልተኛ የሆነ የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ተቋቁሞ እውነቱ መጣራት ይኖርበታል፡፡ ገለልተኛ የሆነ መርማሪ መቋቋምና ከደርግ ዘመን ጀምሮ በግፍ የሞቱ ሰዎች እውነት መውጣት አለበት፡፡ ይሄ መሆኑ አንድም መማሪያ ይሆናል። ከስህተታችን መማር እንድንችል ስህተቱ በግልጽ መቅረብ ይኖርበታል፡፡ እንደውም በተሰሩ ስህተቶች መግባባት ላይ ከደረስን በኋላ ሃገሪቱ ዲሞክራሲን ለመውለድ ስታምጥ በቆየችባቸው ያለፉት 40 እና 50 ዓመታት የተፈፀሙ ስህተቶችን የሚዘክር ሙዚየም መቋቋም አለበት፡፡ ሙዚየሙ የበቀል ማስታወሻ ሳይሆን የመማሪያ መሆን አለበት። በዚህ ጉዳይ ላይ እኔም እያነጋገርኳቸው ያሉ አካላት አሉ። የሚቋቋመው ሙዚየም የበቀል ማስታወሻ ሳይሆን ታዳጊዎች ኢትዮጵያ ምን እንደነበረች የሚማሩበት መሆን አለበት፡፡ ይሄ እንዲሆን ደግሞ የእውነት አፈላላጊ አካል መቋቋምና ያለ ቂም በቀል በሁሉም ወገን የደረሱ ጉዳቶችን ማፈላለግ አለበት፡፡ ያለፈውን ምዕራፍ የምንዘጋበት የማስታወሻ ሙዚየም ነው መቋቋም ያለበት፡፡
በአንድ በኩል ወንጀል ፈፅመዋል የተባሉ ግለሰቦችን ለህግ የማቅረብ ተግባር እየተከናወነ ነው፤ በሌላ በኩል ደግሞ የእርቅ ኮሚሽን እየተቋቋመ ነው። እነዚህን ሁለት መንገዶች እንዴት ነው አስታርቆ መጓዝ የሚቻለው?
ብዙ በደል የፈፀሙና ሰውን የገደሉ ለህግ መቅረብ እንደሚገባቸው ጥርጥር የለውም፤ ፍትህ መኖር አለበት። ወንጀል የሰሩ ሁሉ በሰሩት ወንጀል በህግ መጠየቅ አለባቸው፡፡ የከፋ ወንጀል በእርቅ መሸፈን የለበትም፡፡ ብዙ ሰው የገደለ፣ የገረፈ፣ ያሰቃየ፣ ሃገር የዘረፈ ይቅርታና እርቅ አያሻውም፡፡ እርቅ ለከባድ ወንጀል አቋራጭ ማምለጫ መሆን የለበትም፡፡ በዚህ የእርቅ ሂደት አንዱ ጥንቃቄ የሚያሻው ጉዳይ ይሄ ነው።
ወደ ሃገር ቤት ከተመለሱ በኋላ በበርካታ የሃገሪቱ አካባቢዎች ተዘዋውረዋል፡፡ በተጓዙባቸው አካባቢዎች ምን ታዘቡ? የህብረተሰቡን ሥነ ልቦናስ እንዴት አገኙት?
ያየሁት ትልቁ ነገር፣ ህዝባችን ከጠበቅሁት በላይ ጥሩ ህዝብ መሆኑን ነው፡፡ በየሄድኩባቸው ቦታዎች ሁሉ ከገበሬውም ከሃገር ሽማግሌዎችም ከሃይማኖት አባቶችም ከወጣቶችም ጋር ለመገናኘት ሞክሬያለሁ። ከበርካቶቹ ጋር ተወያይቻለሁ፡፡ ከእነዚህ ውይይቶች የተገነዘብኩት ፖለቲከኞቹ እንጂ ህዝባችን አሁንም ስለ ኢትዮጵያ አንድነት የሚጨነቅ መሆኑን ነው። ግን ባለፉት 27 ዓመታት የተረጨው የዘር መርዝ ፖለቲካ አመራሩን አበላሽቶታል፡፡ ደግነቱ መርዙ ህዝቡ ጋ ያን ያህል አልደረሰም፡፡ ህዝቡ አሁንም አብሮ በመኖር ስሜት ውስጥ ነው፡፡ አሁንም ህዝባችንን አንድ ለማድረግ የመርዙን ኃይል ማርከስ ይቻላል፡፡ በየቦታው ግጭት የሚፈጥሩት ቡድኖች እንጂ ህዝቡ አይደለም፡፡ ህዝባችን ጤናማ ነው፤ በሽታው ያለው ፖለቲከኞቹ ጋ ነው፡፡ ህዝባችን ሃገር ወዳድ እንደሆነ ታዝቤያለሁ፤ ነገር ግን አርአያዎቹን ፍለጋ ላይ ነው፡፡ ህዝቡ እግዚአብሔርን ይፈራል፤ ፖለቲከኞቻችን ግን በተቃራኒው ናቸው። ውስጣቸው የጥላቻ፣ የቂም በቀል ፖለቲካ ነው ያለው፡፡ እኔ በህዝባችን ተስፋ ስለማደርግ፣ በቀላሉ ከጥፋት መንገድ መመለስ እንችላለን ብዬ አምናለሁ። እኛን አንድ ያደረገን ኢትዮጵያዊነታችን ነው፡፡ ከዘር የበላይነት ወደ ኢትዮጵያዊነት የበላይነት የሚደረገው ትግል እንደሚሳካ አልጠራጠርም፡፡ ጥላቻን በህዝቡ በጎነት መፈወስ እንችላለን፡፡
እውነት ማለት ብርሃን ነው፡፡ በእውነት ጥላቻን ማሸነፍ፣ ጨለማን መግፈፍ እንደምንችል ባደረግኋቸው ጉብኝቶች ታዝቤያለሁ። ሰውን እንደ ሰውነቱ የሚያከብር ህዝብ አለን፡፡ በዚህ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ጥቂት የእውነት ብርሃን በሁላችንም ሰፍቶ ጨለማውን ሁሉ መግፈፍ እንደምንችል ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ለዚህ እያንዳንዳችን ኃላፊነት አለብን።

Addis Admass Newspaper

ጉዞ አድዋ ፖለቲካ አይደለም (በጥላሁን ጽጌ)

🙂

ጉዞ አድዋ ፖለቲካ አይደለም
በጥላሁን ጽጌ

አድዋ ፖለቲካ አይደለም። ታሪክ ነው። የማንነታችን መገለጫ ነው። የጥቁር ህዝቦች ሁሉ የአሸናፊነትና የድል አድራጊነት አሻራችን ነው። አድዋ ማለት አፍሪካ በኢትዮጵያውያን ተወክላ ነጮችን በእንብርክክ ያስኬደችበት እንቁ የድልና የደም መሬታችን ነው። አድዋ ፖለቲካ አይደለም። ሆኖ አያውቅም። ሊሆንም አይገባውም።
የኦሮሞ ፈረሰኞች ከጣሊያን መድፈኞች ጋር ተፋልመዋል፣ የጋሞ ጦረኞች የጣሊያን ጠብመንጃ አንጋቾችን ደረት በሳስተውበታል፣ የአማራና የትግሬ ሸማ ለባሽ ገበሬ ቤተሰቡን ጥሎ በጎራዴና በአሮጌ ጠብመንጃ ዘምቶ ለሀገሩ ክብር ሲል አድዋ መሬት ላይ ደሙን አፍስሷል።
አድዋ ቆሻሻውን ፖለቲካ የሚወክል አይደለም። ፋሽስት ጣሊያን ለሁለተኛ ጊዜ በሰሜን በደቡብ በምስራቅ መጥታ የወረረችንና በበቀል ስሜት ዘግናኝ እልቂት የፈፀመችብን ዳግም በአንድነት አርበኞች እንድንሆን ያስገደደን የአድዋ ድል የሁሉም ኢትዮጵያውያን ተዋፅዖ ያለበት በአለም ውድ መዝገብ ላይ ያረፈ ታሪካችን፤ ነጮችን አንገት ያስደፋ ጣሊያንን ያሸማቀቀ የጋራ እሴታችን ያረፈበት ክፈለዘመናትን ተሻገሪ ስማችን ስለሆነ ነው።
አድዋን ፖለቲካ ውስጥ አስገብተን ዛሬ ላለንበት የርስበርስ መጠላለፍና የጥላቻ ጉዞ ማድመቂያ እንዲሆን ለክርክር የምንመርጠውና በብሔር ፖለቲካ ጠረጴዛ ላይ የምናስቀምጠው ቆሻሻ አጀንዳ አይደለም።
አድዋ ንፁህ ነው። ድሉ የንፁህ አያቶቻችን ነው። አሸናፊነቱ የጋራ ውጤታችን ነው። ከአድዋ ድል ላይ ማንም ይሄ የኔ ድርሻ ነው ብሎ ዘግኖ ሊወስድ አይችልም። አካፍሉኝ ማለትም አይችልም። አድዋ የእኛ ትውልድ ውጤት አይደለም። ይህ ታሪክ የእኒያ የጀግኖቹ ድል ነው። የእነሱ ደም ነው የፈሰሰው የእነሱ አጥንት ነው የተከሰከሰው። እኛ የአሁኖቹ ምንም ያዋጣነው ነገር የለም። እኛ ልናደርግ የምንችለው ብቸኛ ነገር ያንን ድል መጠበቅ፣ ለአያቶቻችን ክብር መስጠትና ድሉን እስከ አለም ፍፃሜ ድረስ የኢትዮጵያ ኩራት የአፍሪካ ሀብት ማድረግና ማድረግ ብቻ ነው። ይሄንን ማድረግ ካልቻልን ደሞ ይመለከተናል ብለው አድዋን የሚዘክሩትን በአባቶቹ ድል የሚኮራውን አካል አናጥቃው። እኛ ምንም ማድረግ ካልቻልን ስለአድዋ ክብር ሲሉ ከአዲስአበባ እስከ አድዋ አንድ ሺህ ኪሎሜትሮችን በእግራቸው የሚጓዙትን መልካም ሰዎች በራሳቸው ስሜት እንዲቀሳቀሱ እንተዋቸው። አድዋ የሀገር ክብር፣ የቀደሙት ሁሉም ጀግና ኢትዮጵያውያን በደም ቀለም በአጥንት ብዕር በትልቅ ብራና ላይ የፃፉት የማይለቅ የማይፋቅ የጋራ ሀብታችን ነው። አድዋ ፖለቲካ አይደለም!
Adwa is the hub of Ethiopian patriotism, stop hate speech against Travelers of thousands of kilometres to praise the victory of Adwa!
ጥላሁን ጽጌ አመሰግናለሁ 
እግዝአብሔር ኢትዮጲያን አብዝቶ ይባርክ! !