ኢታርእየኒ ሙስናሃ ለኢትዮጵያ (የኢትዮጵያን ጥፋቷን አታሳየኝ) (ከይኄይስ እውነቱ)

የዛሬውን አስደንጋጭ ርእስ የመረጥኩት ኢትዮጵያ አገራችን የምትገኝበት አስከፊ ሁናቴ ወይም ምድር ላይ የሚታየው ጽድቅ መራር ከመሆኑ የተነሳ ባለአእምሮ እንደሆነ ሰውና እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ ከማሳሰብም አልፎ ሥጋቴ ጥግ ቢደርስብኝ እኔም በርእሰ መጻሕፍቱ እንደተመዘገቡ ደጋግ ሰዎች ጩኸቴን ለሕይወት ባለቤት ባደባባይ ለማሰማት ነው፡፡

ነገረ ኢትዮጵያን በውስጥ በአፍአ፣ በቀኝ በግራ፣ በፊት በኋላ እያገላበጥኹ አቅሜ በፈቀደው መጠን ስመረምረው ቀንድና ጭራ፣ መያዣ መጨበጫ የሌለው ውል አልባ ይሆንብኛል፡፡ ዕብደትና ድንቁርናው በእጅጉ ከመሰልጠኑ የተነሳ ከንቱዎች ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ለማጥፋት እየተጣደፉ ይገኛሉ፡፡ ለጥፋቱ የውጭም አይዟችሁ ባዮች አሏቸው፡፡ የሚናገር እንጂ የሚያዳምጥ የለም፡፡ የሚያዳምጥ የሚመስለውም ጭንቅላቱን በግልጽና በሥውር የሚነቀንቅ ነው፡፡ ነውሩ ሁሉ ምንቀረኝ እየተባለ ንቅስ ተደርጎ የተፈጸመበትና እየተፈጸመ ያለበት ዘመን ላይ እንገኛለን፡፡ ሥጋ የለበሱ አጋንንት ተፈትተው የተለቀቁባት አገር ሆናለች ኢትዮጵያችን፡፡ ዋና መገለጫውም ወያኔ ትግሬ፣ በኦነግ/ኦሕዴድ የሚመራው ‹አዲሱ ወያኔ› (Neo-Woyane)፣ በ‹ፖለቲካ ድርጅት› ሽፋን በጐሣ የተሰባሰቡትም ሆነ ከዛ ውጭ ተሰባስበናል የሚሉት ቊጥራቸው ከመቶው የዘለቀው የአዲሱ ወያኔ አጃቢዎች፣ ንስሓ ከገቡት ውጭ (የገቡ ካሉ) የኢትዮጵያን ፖለቲካ ምስቅልቅል ውስጥ የከተቱትና አሁንም ራሳቸውን ዋና ተዋናይ አድርገው ትውልዱን ግራ የሚያጋቡት ራሳቸውን የ‹ያ ትውልድ› ብለው የሚጠሩት አብዛኛው አባላት (በቅርቡ ከነዚህ መካከል አንዱ ከኢትዮጵያ ምድር ሰው ጠፍቶ ለጥፋቷ 24/7 ሲሠራ የነበረውን ‹ብዔልዜቡል› በረከትን አማክሩት ሲል ለአገዛዙ ‹ምክሩን ለግሷል›)፣ የዘረኝነት (መንደርተኝነት) ልክፍት፣ ቅጥ ያጣ የሥልጣንና የንዋይ ፍትወት፣ ኢትዮጵያን÷ መልካም ታሪኳንና እሤቶቿን ሁሉ አምርረው የሚጠሉ የትውልድ ጕድፎች፣ ከመጣው አገዛዝ ጋር ጭራቸውን እየቆሉ የሕዝብን ሰቆቃ የሚያራዝሙ፣ አንዳንዶችም ዐቢይን በማወደስ የተጠመዱ ‹ምሁራን›፣ በንቅዘትና በማን አለብኝነት ከባለጉት ተረኞች ጋር ተደምረው የሕዝቡን ሕይወት ሲዖል ያደረጉ ስግብግብ ነጋዴዎች፣የማሠማሪያውን መንጋ አጥፍተውና በትነው ተቅበዝባዥ ያደረጉ በመንፈሳዊ ድርቀትና ድቀት የተመቱ በሃይማኖት ሽፋን የሚንቀሳቀሱ ‹እረኞች›፣ የመንደር ወሮበሎችን የሚያበረታቱ የእንጨት ሽበት የወረራቸው ‹ሽማግሎች›፣ ወዘተ. የነውረኞቹ ስብስብ ውስጥ የሚጠቃለሉ ናቸው፡፡

ጉልበተኞቹ አገዛዞች መንግሥታዊ ሥልጣንን እና ኃይልን ሕግን ለማስከበር÷ፍትሕ ርትዕን ለማደላደል ሳይሆን፤ ሥርዓተ አልበኝነትን ለማንገሥ፣ ዜጎችን ለማፈናቀልና ለማጉላላት፣ የርስ በርስ ግጭት ለመለኰስ፣ አገራዊ አንድነትን ለማናጋት፣ ለዝርፊያና የግል ጥቅም ማደላደያ እየተጠቀሙበት ይገኛሉ፡፡ እንደ አሸን የፈሉትና አዲሱን ወያኔ በአጃቢነት የተቀላቀሉት (ተቃዋሚም÷ተፎካካሪም ያልሆኑት) የፖለቲካ ነጋዴዎችም የሥልጣን ፍርፋሪ በመጠባበቅ ላይ ይገኛሉ፡፡ የወያኔን ነቀርሳ ሰነድ አዝለው ስለምርጫ ያወራሉ፡፡ ተቀድዶ የታሪክ ቆሻሻ ቅርጫት ውስጥ ከመጣል በቀር ለመሻሻሉ ምንም ዓይነት ዕድል የሌለው የወያኔ/ኦነግ ሰነድ አይነካብንም የሚለው የባለጌዎቹ ቁንጮዎች ጩኸት አሁንም ቀጥሏል፡፡ ሰብእናቸው ከአውሬ የከፋው እነዚህ ጉዶች ሳይገባቸው ስለ ሕግ የሚያወሩት በጠራራ ፀሐይ የዜጎችን ሰብአዊ መብቶቸ እየጣሱ ነው፡፡ ዐቢይም ሆነ ‹ዘመዶቹ› ባደጉበትና በለመዱበት ብቻ ሳይሆን ክፋቱን አልቀውት በአሳፋሪ መንገድ ቀጥለዋል፡፡ የቀደመውም ሆነ የአዲሱ ወያኔ አገዛዞች ያመረቷቸው በዜጎች ደምና በአገር ሀብት ዝርፊያ እጃቸው የጨቀየ ወንጀለኞች እስከ ነውራቸው (ጥቂት የማይባሉትም በዐቢይ አገዛዝ ውስጥ ሥልጣን ተሰጥቷቸው) በዐደባባይ ይንጎማለላሉ፡፡ በታሪክ ደጋግሞ እንደታየው በዳዮችን የምትሾም የምትሸልም፤ የአገር ባለውለታዎችንና ተቆርቋሪዎችን የምትወነጅል የምታሳድድ አገር ሆና ቀጥላለች፡፡ ባጠቃላይ ማኅበረ ፖለቲካዊና አኮኖሚያዊ ቀውስና ድቀት ውስጥ እንገኛለን፡፡ እንኳን ለጅምላ ጥፋት እየተጋን፤ አንድ ሆነን÷ በመከባበር ተነጋግረን÷ተደማምጠን÷ ዜጎች ሁሉ በአገራቸው ጉዳይ ያገባቸዋል ብለን (ዕጣ ፈንታችን÷ዕድል ተርታችን ለአገዛዞችና በውሸት ተቃዋሚነት ስም ለሥልጣን በቋመጡ አጃቢዎቻቸው ሳንተው) ብሔራዊ የሽግግርና የምክክር ጉባኤ ጠርተን ብንመክርም እንኳ ከገባንበት ዐዘቅተ በቀላሉ የምንወጣው አይመስልም፡፡ አሁን በያዝነው መንገድ በቡድንም በተናጥልም አንድም አትራፊ አይኖርም፡፡ የዓለሙ ሁሉ መሳቂያና መሳለቂያ ከመሆን በቀር፡፡ ይህ ዓይነቱ እገሌ ከእገሌ ሳይባል ሁሉም ሙልጩን የሚቀርበት ውጤት የኢትዮጵያን ጠላቶች ካልሆነ በቀር ማንን ሊያረካ እንደሚችል አላውቅም፡፡ በአርዓያ ሥላሴ የተፈጠርን ሰው ነን ካልን እንደ ሰው እናስብ እንደ ሰው እንኑር!!! አለበለዚያ በኢትዮጵያ ምድር አገር እበትናለሁ እያለ ማንም ማንንም ሊያስፈራራ አይችልም፡፡ 80 መንደሮች በተናጥል አገር አይሆኑም፡፡ ወይ አብረን ተያይዘን እንለማለን ወይ አብረን ተያይዘን እንጠፋለን፡፡ ለጥፋት መካከለኛ መንገድ የለውም፡፡ አሁንም ሆነ ወደፊት ኢትዮጵያ ውስጥ የትኛውም ክ/ሃገር ራሱን ችሎ መቆም አይችልም፡፡ በበጀት አንፃር እንኳን ብናየው ወያኔ በዘረጋው የውሸት ፌዴራላዊ መዋቅር እያንዳንዱ ክ/ሃገር የሚተዳደረው ከማዕከላዊ መንግሥት በሚደረግ የበጀት ድጎማ ሳይሆን የበጀት ምደባ ነው፡፡ ከ70 – እሰከ 90 በመቶ የሚሸፈን ወጭ ድጎማ ሊሆን አይችልም፡፡ ክፍላተ ሀገራቱ እንኳን ራሳቸውን የቻሉ አገሮች ሊሆኑ ቀርቶ የእውነተኛ ፌዴራላዊ ሥርዓት አባላት ለመሆን ብቃቱ የላቸውም፡፡ ለምን ራሳችንን እናታልላለን?

እስከ መቼ በአእምሮም በቁስም የለየልን መናጢዎች ሆነን እንቀጥላለን? እስከ መቼ ዋናና አንኳሩን ጉዳይ ትተን በመደበኛውም ሆነ በማኅበራዊው የብዙኃን መገናኛዎች በጭፍጫፊ ጉዳዮች ላይ መላ ኃይላችንን እናባክናለን? መቼ ይሆን ኢትዮጵያ ውስጥ የሕዝብ ድምጽ የሚሰማው? መቼ ይሆን ሕዝብ ያልመረጣቸው/ያልወከላቸው ጮሌዎች አገር ማመሳቸውን የሚያቆሙት? መቼ ይሆን አገዛዞችን ሲያገለግሉ የኖሩትና እያገለገሉ ያሉት ደካማ ተቋማት የሕዝብን ፍላጎት የሚያስተናግዱት፣ ለእውነትና ለሕግ ተገዢ የሚሆኑት? መቼ ይሆን ተቋማዊ ገጽታ የተላበሰው ቡድናዊና አገራዊ ሸፍጥና ቅጥፈት የሚያበቃው? መቼ ይሆን ከመንደር ወጥተን በአገር፣ በክፍለ ዓለምና በዓለም ደረጃ የምናስበው? መቼ ይሆን ሌሎች አገሮች የደረሰቡት የሳይንስና ቴክኖሎጂ ደረጃና ብልጽግና በቁጭት የሚያነሳሳን? መቼ ይሆን አገዛዞቻችን ከድንቁርና ወጥተው የአገርንና የሕዝብን ጥቅም የሚያስጠበቁት፣ ለሥልጣን ሲሉ የባዕዳንን እና ተቋሞቻቸውን አጀንዳ ከማስፈጸም የሚታቀቡት? ባለቤት አልባ አድርገውን ብሔራዊ ምሥጦሮቻችንን የሚያባክኑት? መቼ ይሆን ዜጎች ከመንጋነት ወጥተው እንደ ግለሰብ በራሳቸው ለራሳቸው ቆመው በሰውነት የሚያስቡት? ምርጫ ፍላጎታቸውን በነፃነት የሚወስኑት? ለምን ማንም እንደ ከብት በፈለገው መንገድ ያሠማራናል? መቼ ይሆን ‹ሰው› ሆነን የምናልፈው? እነዚህ ሁላችንን የሚመለከቱ ጥያቄዎቸ እንቀጥል ካልን ማብቂያ የላቸውም፡፡ ጊዜና ቦታ ስለሚገድበን ለጊዜው በዚሁ እናብቃ፡፡ ለጠቢብ አንዲት ቃል ትበቃዋለች ይላልና ታላቁ መጽሐፍ፡፡

በመግቢያዬ ላይ ያነሳሁት የአስተያየቴ ርእስን በጸሎት መልክ ለእግዚአብሔር አምላክ ያቀረቡት ‹‹ በሆድ ሳልሠራህ ዐውቄሃለሁ÷ ከማኅፀንም ሳትወጣ ቀድሼሃለሁ÷ ለአሕዛብም ነቢይ አድርጌሃለሁ፡፡›› የተባለለት ከዐበይት ነቢያት አንዱ የሆነው የነቢዩ ኤርምያስ ደቀመዛሙርት ኢትዮጵያውያኑ አቤሜሌክና ባሮክ ናቸው፡፡ በነገራችን ላይ ነቢዩ ኤርምያስ በክፉዎች እጅ ተላልፎ ዐዘቅተ ኵስሕ (መፀዳጃ ቤት) በተጣለ ጊዜ ያወጣው ኢትዮጵያዊው አቤሜሌክ ነው፡፡ ሁለቱ የነቢዩ ኤርምያስ ደቀመዛሙርት መምህራቸው የፄዋዌን ነገር (እሥራኤላውያን በባቢሎን ተማርከው ለ70 ዘመናት በባዕድ ምድር በስደት እንደሚኖሩ÷ በባርነት እንደሚያዙና እንደሚገዙ) ሲናገር እየሰሙ የኢየሩሳሌምን ጥፋት አታሳየን እያሉ አጥብቀው ይጸልዩ ነበር፡፡ እግዚአብሔርም የነዚህን ቅዱሳን ጸሎት ሰምቶ ለነቢዩ ኤርምያስ በሰጠው ትእዛዝ መሠረት ከመአቱ በልዩ ጥበብ ሠውሮአቸዋል፡፡ ነቢዩ ኤርምያስ ከገባበት ዐዘቅተ ኵስሕ ኢትዮጵያዊ አቤሜሌክ እንዳወጣው ዛሬ ኢትዮጵያ ከገባችበት ‹‹ዐዘቅተ ኵስሕ›› የሚያወጣት አቤሜሌክ ያላት አይመስልም፡፡ ሕዝብ ‹ባሕረ ኤርትራን› ያሻግሩናል፣ ወደ ‹ምድረ ከነዓን› ይመሩናል  ብሎ ተስፋ የጣለባቸው ‹ሙሴዎች› እና ‹ጸያሕያነ ፍኖት› ሐሳውያን ሆነው መገኘታቸው ብቻ ሳይሆን ባደጉበት ቆሻሻ የፖለቲካ ባህል÷ በዘረኛና ደናቁርት የመንደራቸው ሰዎች ተጽእኖ ሥር ወድቀው የቁልቁለቱን መንገድ ከጀመሩት ውለው አድረዋል፡፡ ታዲያ ምን ይሻለናል?

ከእምነቱም ከበጎ ሥራውም አንዳች የሌለን የዚህ ዘመን ሰዎች ከኵተት እስከ ሽበት የክፋትንና የጥፋትን ጥግ ማየትና መስማት ዕጣ ፈንታችን ሆኖአል፡፡ ባይሆን ከዕብደቱና ድንቁርናው ተፋትተን ወደ ቀልባችን ከተመለስን፤ በእምነት ተቋማት አመራር ላይ ጥቂት መንፈሳውያን አባቶች ካገኘን፤ ለራሳቸውና ለሕዝብ የታመኑ÷ እውነትን ገንዘብ ያደረጉ ጥቂት ቅን መካርና ገሣጭ ሽማግሎችን ካገኘን፤ በጋራ ጥረታችንና ከልብ በሆነ ጸሎት ተደግፈን የጋራ ቤታችን ኢትዮጵያን ከሁሉም በላይ ከቅኝ አገዛዝ በነፃነት ያሸበረቀ መልካም ታሪኳን፣ ውብ ባህሏንና እሤቶቿን ይዘን፣ የገፀ ምድርና የከርሠ ምድር ሀብቶቿን በሥራ ላይ በማዋል፣ ለሁላችን የምትበቃና የምትመች አድርገን በሰላምና በእኩልነት ለመኖር ተስፋውና ዕድሉ አለ፡፡ ይሁን እንጂ በተለይ ላለፉት ሦስት ዐሥርታት ያየነው እና የምናየው ግን ከዚህ በተቃራኒው በመሆኑ በግሌ አምላኬን ኢታርእየኒ ሙስናሃ ለኢትዮጵያ(የኢትዮጵያን ጥፋቷን አታሳየኝ) እያልኩ ወላዲተ አምላክን እና ቅዱሳንን ጥግ አድርጌ እማፀነዋለሁ፡፡

አዎ! አምላከ ኢትዮጵያ የኢትዮጵያን ትንሣኤ እንጂ ጥፋቷን አያሳየን፡፡

የጽንፈኛ ቄሮ መሪ ጦርነት አውጇል – እንግዲህ ሕዝብ ሆይ ራስህን ተከላከል #ግርማካሳ

የጽንፈኛው ቄሮ መሪ ጃዋር መሐመድ ለኦሮሞ ክልል መንግስት ሌላ መመሪያ አስተላልፏል። በፌስ ቡክ ገጹ ላይ የሚከተለውን ነበር የለጠፈው፡

“Dhaabbileen Miti-Mootummaa ( NGO) Oromiyaa keessa jiran irra jireessi isaanii Afaan Oromoon hin hojjatan. Kaayyoon isaanii ummata naannichaa tajaajiluu erga tahee afaan naanichaan dubbachuu qabu. Afaan Oromoon hojjachaa dhalattoota naannoo sanii hiree hojii dhoowwachaa itti fufuu hin qaban. Oromiyaa kleessa turuu yoo barbaadan afaan Oromoon hojjachuu; san didnaan dhoortoo isaanii qabatanii haa bayan.”

አንድ ላቲን የሚያነብ ፣ ግን በላቲን ኦሮምኛ በአገራችን ፊደል እንዲጻፍ እየሰራ ያለ የኦሮሞ ልጅ ወዳጄ፣ ብርሃኑ ገመቹ ትርጉሙን እንደሚከተለው አቀበለኝ።

“በኦሮምያ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ በብዛት በኦሮምኛ አይሰሩም። ዓላማቸው ህዝቡን ማገልገል ከሆነ የክልሉን ቋንቋ መናገር አለባቸው። በኦሮምኛ ባለመስራት የክልሉን ተወላጅ ስራ መንፈግ የለባቸውም። በኦሮምያ በስራ ለመቀጠል የሚፈልጉ ከሆን በኦሮምኛ መስራት አለባቸው። አለበለዚያ ግን በአስቸኳይ ተጠራርገው መውጣት አለባቸው”

ከዚህ በፊትም ጃዋር “Ethiopians Out of Oromia” እያለ የጽንፈኛ አክራሪዎችን ሰልፍ ሲመራ እንደነበረ ሁላችንም የምናውቀው ነው። ያኔ ጃዋር ብዙ ደጋፊ አልነበረውም። አሁን ግን በመቶ ሺሆች የሚቆጠሩ፣ ገደል ግቡ ቢላቸው ገደል የሚገቡ ጭፍን ደጋፊዎች አሉት። በተለይም በምእራብ አርሲ ፣ በባሌና በሃረርጌ ዞኖች።

በተጨማሪም በኦህዴድ/ኦዴፓ መዋቅር ውስጥም ከነ ዶ/ር አብይ በበለጠ በጣም ተጽኖ ፈጣሪ ነው። በአብዛኛው ነዋሪ በማይደገፍበት ቦታ ደግም፣ ያሰማራቸው የማፊያ ቄሮ ቡድኖች አሉ። በጣም ጥቂቶች። ለምሳሌ ለገጣፎ አብዛኛው ነዋሪ ኦሮሞዉን ሳይቀር በሰላም በፍቅር የሚኖር ነው። ግን እዚያ ፋይናንስ የተደረጉ ቄሮዎች፣ በአካባቢው የኦህደድ ሃላፊዎች እየተደገፉ፣ የነጃዋርንና እነከጃዋር ጋር የሚሰሩ ኦህዴዶችን ቁሻሻ ስራ እየሰሩ ነው። በመሆኑም ይሄን የጃዋር ንግግሩን ችላ ብሎ መቀመጥ በራስ ላይ መፍረድ ነው።

ይህ የጃዋር ንግግር፣ በኦሮሞ ክልል በሚኖሩ፣ ኦሮምኛ በማይናገሩ ዜጎቻችን ላይ ጦርነት ማወጅ ነው። ይህ ሰው በሲዳማ ዞን፣ ታናሽ ወንድሞቹ ኢጂቶዎች በጉልበት የፈለጉትን እንዲያደርጉ ቀስቅሶ፣ ኢጂቶዎችም የልብ ልብ ተሰምቷቸው አካባቢዉን እንዳሸበሩ፣ ከፍተኛ የዘር ተኮር ግድያዎች እንደፈጸሙ፣ ብዙ ንብረቶች እንዳቃጠሉ የሚታወስ ነው። ያኔ ጃዋር ምንም አልተባለም። አሁን ደግሞ በኦሮሞ ክልል፣ በሌሎች ማህበረሰባት በይፋ ዘመቻ አዉጇል።

ከሁለት ወራት በፊት ኢትዮጵያ የነበርኩ ጊዜ ሰበታ፣ ሳንሱሲ፣ ለገጣፎ፣ አዳማ የመሳሰሉ በሸዋ ያሉ በርካታ አካባቢዎችን አይቻለሁ። በአዳማ እንዳለ ሰው አማርኛ ተናጋሪ ነው። ማስታወቂያዎች በላቲንም ይጻፋሉ፣ ያው በግዳጅ። ከዚያ በተረፈ ግን ሆቴል ቤቶች ፣ መጽናኛ ቦታዎች፣ ሱቆች፣ ምግብ ቤቶች..ሁሉም የሚሰሩትና የሚናገሩት በአማርኛ ነው።
አዳማ አዲስ አበባ ናት። ሰበታም እንደዚሁ ነው።መንደር ሱቆች ሁሉ ስገባ ነበር። በተለይም በምስራቅና ሰሜን ሸዋ ዞኖች ባሉ ከተሞች፣ በአዳማ፣ በቢሾፍቱ፣ በሞጆ፣ በዱከም፣ በቡራዩ፣ በጣፎ፣ በአለምገና፣በመተሃራ፣ በዝዋይ፣ በአርሲ ነገሌ … ኦሮምኛ የማይናገሩ ከሰባ፣ ሰማኒያ በመቶ በላይ ናቸው። በሻሸመኔ፣ ጂማ፣ አሰላ በመሳሰሉትም እንደዚሁ።

ከተሞቹን ትተን በወረዳ ደረጃ እንኳን ብንመለከት፣ ከአስራ ሶስት አመታት በፊት በተደረገው የሕዝብ ቆጠራ ውጤት መሰረት፣ በአዳማና አዳም ዙሪያ ወረዳ ከ65% በላይ፣ በደራ ከ53% በላይ፣ በፈንታሌ ከ61% በላይ ፣ በግራር ጃርሶ ከ50% በላይ፣ በሎሜ ከ43% በላይ፣ በቆቂር ከ41% በላይ፣ በአዳ ጩሉቃ ከ37% ..የሚሆኑት ኦሮምኛ ተናጋሪ አይደሉም። አሁንም ደግሞ ቆጠራ ቢደረግ፣ ቁጥሩ የበለጠ ነው የሚጨምረው። ያለ ንም ጥርጥር በሰሜን ሸዋ፣ በደቡብ ምእራብ ሸዋና በምስራቅ ሸዋ፣ ኦሮምኛ የአፍ መፍቻ ቋንቋቸው ከሆኑት፣ ኦሮምኛ የአፍ መፍቻ ቋንቋቸው ያልሆኑ ነው የሚበልጡት።

እንግዲህ ሜዳ ላይ ያለው እውነታ እንደዚያ ሆኖ ጥቂት ዘረኞች ፍላጎታቸው በሃይል፣ በማስፈራራት ለመጫን መሞከራቸው የተኛውን ዝሆን እንደመቀስቀስ ነው። ዝም ሲባሉ፣ ሰው ሲታገሳቸው የፈራቸው እየመሰላቸው ነው።

እነ ጃዋርን ተከትሎ የሺመልስ አብዲሳ መንግስት አፓርታይዳዊ፣ ሕግ ወጥ እንቅስቃሴዎች ለመጀመር ሊዳዳው ይችላል። ያንን መታገል ብቻ ሳይሆን ታግሎ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ማሸነፍ አማራጭ የሌለው ጉዳይ ነው የሚሆነው።

ደግሜ እላለሁ ህዝቡ ነቅቶ፣ በአስቸኳይ ካልተደራጀና ካልተንቀሳቀሰ ፣ ዝም ብሎ ከተቀመጠ ፣ የሚያድነው፣ ለርሱ የሚቆምለት ማንም አይኖርም። ሰዎቹ ጨካኝና ዘረኛ ናቸው። ሰው ዘቅዝቀው ከመስቀል ወደ ኋላ አይሉም። 1.4 ሚሊዮን ጌዶዎችን በጭካኔ ኦሮሞ አይደላችሁም ብለው ያፈናቀሉ ናቸው። በቡራዩ ያደረጉትን ሁላችንም እናስታወሳለን። በለገጣፎም እንደዚሁ። አሁን ጃዋር በአደባባይ የሰጣቸውን መመሪያ አያደረጉም ብሎ ማሰብ የዋህነት ነው።