ለሰላምና ዴሞክራሲ መሠረቱ ብሄራዊ መግባባትና የሁሉም ባለድርሻዎች ተሳትፎ ነው

በሀገራችን በኢትዮጵያ በተደጋጋሚ የተፈጠሩ ሁኔታዎችን በትክክል መጠቀም ባለመቻሉ ከአምባገነን አገዛዝ ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመሸጋገር አልተቻለም። ከአንድ አምባገነን ወደሌላ አምባገነን አገዛዝ ስንሸጋገር ቆይተን እነሆ አሁን ከምንገኝበት ደረጃ ላይ ደርሰናል። በመሆኑም አምባገነንነት ሰፍኖ የሕዝባችን ስቃይና መከራ እንደቀጠለ ነው።

የቅርብ ጊዜ እውንታን ስንመረምር በኮሎኔል መንግሥቱ ይመራ የነበረው አገዛዝ ከሥልጣን በተወገደ ጊዜ ሀገራችን ኢትዮጵያ ወደ ባለብዙ ፓርቲ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመሸጋገር እጅግ ሰፊ አጋጣሚ እንደነበራት ነው። ሆኖም  በወቅቱ  ሥልጣኑን  አዲስ  አባባና አሥመራ ላይ የተቆጣጠሩት ህወሓት፣ ኦነግና ሻአቢያ ሌሎች የተደራጁ ኢትዮጵያውያንን በሰበብ በአስባቡ በሽግግሩ ሂደት ውስጥ እንዳይሳተፉና ሕዝብ የሚተዳዳርበትን ሕገ-መንግሥት በመቅረጽ ደረጃ ድርሻ እንዳይኖራቸው አድርገው ብዙሃኑን ባገለለ መልክ ለብቻቸው በፈጠሩት አገዛዝ ሕዝብን ለቀጣይ ስቃይ፣ ለመብት ረገጣና ለከፍተኛ ግፍ ዳረጉት።

ህወሓት-መራሹ አገዛዝ ለኢትዮጵያውያን ቃል የገባው የዴሞክራሲ መብት  መከበር፣ የፍትኅ መስፈን፣ እኩልነት፣ በነፃ የመደራጀት መብት መከበር፣ ሰላምና ብልጽግና፤ የራስን መንግሥት የመምረጥ መብት…ወዘተ፣ ከ26 ዓመታት በኋላ ዛሬም መጨበጥ የማይቻል የህልም እንጀራ ሆነው ቀርተዋል። አገዛዙ ከዴሞክራሲ አቀንቃኝነት ርቆ በዓለም ውስጥ ቀንደኛ ከሆኑት ፀረ-ነፃ ፕሬስ አገዛዞች ውስጥ አንዱ ሆኗል።

ይህ የሆነው አገዛዙ ገና ከመሠረቱ የአምባገነንነት መሠረት ይዞ በመነሳቱና አግላይ ሆኖ ስለተመሠረተ ነው። ሕዝባችን በሰጥቶ-መቀበልና በብሄራዊ መግባባት ሂደት የሚተዳደርበትን ሕገ-መንግሥት ለመቅረጽ ከመጣር ይልቅ የህወሓትን ድርጅታዊ አጀንዳ በሕገ-መንግሥት ስም እንዲጸድቅ ስለተደረገ ሕዝብ ገና ከጅምሩ የኔ  ብሎ አልተቀበለውም። የዛሬ 26 ዓመት የተፈጠረው ስህተት የሕዝባችንን ስቃይ  ማባባሰ  ብቻ ሳይሆን የሀገራችንንም ህልውና አጠያያቂ ደረጃ ላይ አድርሷል።

ከ26 ዓመታት የግፍ አገዛዝ  በኋላ  እነሆ  ሕዝቡ  ጭቆና  በቃኝ  ብሎ  ለሥርዓት  ለውጥ  አምርሮ እየታገለ ሲሆን አገዛዙም ክንዱ እየዛለ ነው።  የሕወሓት/ኢህአዴግ  አገዛዝ  በብዙ  ሕዝብ እጅግ የተጠላ አገዛዝ ነው። በመሆኑም ዛሬ በመላ ሀገሪቱ የከፋ ተቃውሞ ወጥሮ  ይዞታል። ህወሓት-መራሹ አገዛዝ አሁን ባለው ሁኔታ መቀጠል እንደማይችል ግልጽ

 

ሆኗል። አሁን ያለው ጥያቄ የአገዛዝ መወገድ አለመወገድ ሳይሆን መቼ? የሚለውና ወደ ዴሞክራሲያዊ  ሥርዓት  እንድንሸጋገር  የሚረዳ  መሠረት  እንጥል   ይሆን?   የሚሉት  ጥያቄዎች በብዙዎች ኣእምሮ ውስጥ ይመላለሳሉ።

በሸንጎ አመለካከት ከህወሓት-መራሹ አምባገነን አገዛዝ ወደ ሕገ-መንግሥታዊ ዴሞክራሲያዊ  ሥርዓት  ለመሸጋገር  ሀገራችን  የሽግግር   ሥርዓት   ያስፈልጋታል።   ይህ የሽግግር ሂደትም  ካሁን  በፊት  ከተሠሩት  ስህተቶች  ትምህርት  መውሰድ  እንጂ  ያንኑ  ስህተት መድገም የለበትም፡፡  በመሆኑም  አግላይነት  ቦታ  ሊኖረው  አይገባም።  የሽግግሩ  ሂደት  ሁሉንም  ባለድርሻዎች  አሳታፊና  የተለያዩ  አመለካከቶች  ያላቸው   ኢትዮጵያውያን  ሁሉ  የሚወከሉበት  ሊሆን  ይገባል።  የሽግግር  ሂደቱ  በባለድርሻዎች  ስምምነት  ላይ  ተመርኩዞ ነፃና ተዓማኒነት ያለው ምርጫ በአጭር ጊዜ  ውስጥ  የሚካሄድበት፣  የሕዝብን  ፈቃድ ያገኘ ድርጅትም የመንግሥት ሥልጣን የሚይዝበት ሂደት ሊሆን ይገባዋል።

በተደጋጋሚ እንደገለጥነው የሸግግር ሂደቱን እውን ለማድረግ ተመራጭ የሚሆነው ሁሉንም ባለድርሻዎች አሳታፊ የሆነ ድርድር በማካሄድ ነው። ይሁን እንጂ ህወሓት-መራሹ አገዛዝ በተቃዋሚነት ከተሰለፉ ድርጅቶች ውስጥ  “መረጋጋትን  ሊያሰገኙ  ይችላሉ“  ብሎ ከገመታቸው ድርጅቶች ጋር በቅርቡ የፖለቲካ ድርድር  ማካሄዱ  በስፋት  ተወርቷል።  ይህ  አካሄድ ከ26 ዓመት በፊት ሀገራችንን ወደ መገነጣጠልና ወደባሰ ምስቅልቅል ውስጥ ያሰገባ   የጎሳ ፖለቲካን በሕዝባችንና በመላ ሀገሪቱ ላይ በጉልበት  እንዲጫን  ያደረገውን  አገዛዝ  ምሥረታ ያስታውሰናል።

ኢትዮጵያ ከ26 ዓመት በኋላ ተመሳሳይ ስህተት መፈጸም አትችልም፣ ሕዝባችን በድጋሚ በአግላይነት ላይ የተመሠረተ ሌላ አምባገንን አገዛዝን ማስተናገድ አይችልም። ኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት ብሄራዊ መግባባትና የሁሉን አቀፍ ሥርዓት ምሥረታ ነው። ስለሆነም የሕዝባችንን ትግል ወደኋላ የሚወስድን የአግላይነት አደጋ ኢትዮጵያውያን ሁሉ ሊያወግዙት ይገባል።

ሀገራችን የገባችበትን ምስቅልቅል ፖለቲካ እፍኝ በማይሞሉ ድርጅቶች ምክክር የሚፈታ አይደለም። ማንኛውም ድርጅት በሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች የበላይነት የለውምና። ስለዚህ በጋራ ሀገራችን ውስጥ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን እውን ለማድረግ አማራጩ ሁሉንም አሳታፊ የሆነን የሽግግር ሂደት እውን ማድረግ  ነው። ለዚህም  ተቃዋሚዎች  ሁሉ በአንድነት መቆምና ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ምሥረታ የሚካሄደውን የሕዝብ ትግል በመደገፍና በማጠናከር በድርድርም ሆነ በሽግግር ጊዜ አሳታፊ የሆነ  ሥርዓት  መከተል  እጅግ አስፈላጊ መሆኑን ሸንጎ በአንክሮ እየገለጸ የድርሻውን ለማበርከትም ዝግጁነቱን ያረጋግጣል።

ኢትዮጵያ በልጆቿ አንድነት ታፍራና ተከብራ ለዘለዓለም ትኖራለች!

Advertisements

ዜና ከጎንደር! ህዝቡ እምብይ ብሏል! – አስናቀው አበበ

ሰበር ዜና ከጎንደር! ይሰራጭ!
ህዝቡ እምብይ ብሏል!
የህዝብ የሙያ ማህበራት አንሳተፍም አሉ!
ታዋቂ የሃገር ሽማግሌዎችም ጥሪውን አልተቀበሉም!
የጎንደር ህዝብ ተጠይፎናል፦ ጉባኤተኛ ትግሬወች!
ህዳር 9 2010
ጎንደር

ወያኔና ብአዴን ዛሬ በከፈቱት እናሞኛቹህ ድራማ ከመነሻው ጀምሮ የህዝብ ቁጣና ማግለል ገጥሞታል። ሲገቡ ተሸማቀው ከተማውን በወታደር አሳጥረው ነው። ዛሬ በክከፈተው የድራማ ጉባኤ ደግሞ በመቶዎች የሚቆጠሩ የተለያዩ የጎንደር ህዝባዊ የሙያና ንግድ ማህበራት አባላት እርቁ ላይ ተሳታፊ እንዲሆኑ ትናንት ትዕዛዝ ቢሠጣቸውም አሳስተፍም ብውለ ወስነው ቀርተዋል። የህዝባቸውን እውነተኛ እልህና ቁጭት የተረዱት ማህበራት ከህዝብ ውጭ አንሆንም ብለዋል። ህዝቡን ባይሰሙ ሊደርስባቸው የሚችለውንም ከባድ እርምጃ ቀድሞ እንደተነግሯቸውና ይህን አክብረው ከድርጊቱ ራሳቸውን ማግለላቸው ታውቋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ለእርቁ የፕሮፓጋንዳ ፍጆታ ሊጠቀምባቸው ያሰባቸውን ተፅእኖ ፈጣሪ ሰወች በየግላውቸ ህዝቡ ማስጠንቀቂያወችን ስላደረሳቸው ፕሮግራሙ ላይ ሳይሳተፉ ቀርተዋል። ፕሮግራሙን ወያኔወች ብቻቸውን ከብአዴን ካድሬወች፣ ሊጠብቋቸው ከመጡ ወታደር መኮንኖች እና ብዛት ካላቸው ቄሶች ተቀምጠውበታል፡፡ ለእርቅ መጥተን ጎንደሮች ተጠየፉን ሲሉ አንድ ታዳሚ የትግራይ ቄስ በምሬት ተናግረዋል። የእቅድ መክሸፉ ያጋጠመው ወያኔ ከፍተኛ የሆነ ንዴትና ከባድ ጭንቅ ውስጥ ነው። ይህን ዜና ከምስሉ ጋር አስተያዩት።

የጎንደር ህዝብ ተቃውሞ በዚህ እንደማይቆም የደረሰን መረጃ አስጠንቅቋል።
AsnakewAbebe

ወጣትነት በምስራቅ ኢትዮጲያ፣ ሀረር – ክፍል ሁለት (ኤድመን ተስፋዬ)

ኤድመን ተስፋዬ
ክፍል ሁለት

Ethiopia's Eastern city of Harar

ሀረር በምስራቁ የሀገራችን ክፍል ከሚገኙ ጥንታዊ ከተሞች መሀል ላቅ ያለ እድሜ ያላት ከተማ ነች፡፡ እ.ኤ.አ በ2007 በተካሄደው ሀገር አቀፍ የህዝብ ቆጠራ መሰረት የሀረር ህዝብ ብዛት 183,415 ነው፡፡ ህወሀት-ኢህአዴግ በምን መሰረት እንዳዋቀራቸው  በከማይታወቁት ክልሎች በተለየ መልኩ የሀረር ከተማ ብዙሀኑ ህዝብ በከተማ የሚኖርባት ከተማ ነች፡፡ እ.ኤ.አ በ2007 በተካሄደው አጠቃላይ የህዝብ ቆጠራ መሰረት ከአጠቃላዩ የሀረር ህዘዝብ ውስጥ 56.41 ፐርሰንቱ ኦሮሞ ሲሆን፣22.77 አማራ፣8.65 ፐርሰንቱ ሀረሪ (በቀድሞ አጠራሩ አደሬ)፣ 4.34 ፐርሰንት ጉራጌ፣3.87 ፐርሰንት ሱማሌ፣1.53 ፐርሰንቱ ትግሬ እንዲሁም 1.26 ፐርሰንቱ የአርጎባ ብሄር ተወላጅ ነው፡፡  በሀረር ከተማ ህዝቦች የሚነገርን ቋንቋ በተመለከተ እ.ኤ.አ በ2007 የተካሄደው የህዝብ ቆጠራ የሚያሳየን 56.84 ፐርሰን የሀረር ህዝብ ኦሮምኛ ተናጋሪ ሲሆን፣ 27.53 ደግሞ አማርኛ ተናጋሪ ነው፡፡ ሀረሪ፣ሶማሌ፣ትግራይ እና አርጎብኛ ተናጋሪ ህዝቦች ደግሞ እንደየቅደም ተከተላቸው7.33፣3.7 እና 2.9 ፐርሰንቱን ይይዛሉ፡፡ ከሀረር የአጠቃላይ ህዝብ ውስጥ 68.99 የእስልምና እምነት ተከታይ ሲሆን፣27.1 ፐርሰንቱ የኢትዮጲያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ተከታይ ነው፣ በተጨማሪም 3.4 ፐርሰንት የሚሆነው የሀረር ህዝብ ፕሮቴስታንቴ ፣ 0.3 ፐርሰንቱ የካቶሊክ፣ እንዲሁም የተቀረው 0.2 ፐርሰንቱ ደግሞ የባህላዊ እምነት ተከታዮች ናቸው፡፡

መስፈርቱ ምን እንደሆነ ለብዙሀኑ ግልፅ ባልሆነ ምክንያት ህወሀት – ኢህአዴግ ሀረርን እንዲያስተደዳር ለሀረሪ ህዝብ ሀላፊነቱን ከሰጠ ጀምሮ ሀረርን በማስተዳደር ላይ የሚገኘው ሀብሊ ነው፡፡ የሲዳማ ብሄርን የመሳሰሉ ብሄሮች ለብቻችን ክልል የሰጠን ሲሉ ከህወሀት ኢህአዴግ የሚሰጠውን መምላሽ ላስተዋለ የሀረር ህዝብ በሀብሊ የበላየረነት መተዳደሩ ላይ ጥያቄ ቢያነሳ አይገርምም፡፡ የሀረሪ ብሄራዊ ሊግ (ሀብሊ) ጥንታዊታን ሀረር ከተማን ማስተዳደደር ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ከተማዋ ከማደግ ይልቅ ባለችበት እንደቆመች፣ ነዋሪዎቿ ሀብሊ በፈጠረው የዘረኝነት ጦስ እየተለበለቡ ይገኛሉ፡፡

ጌታቸው ኢሳያስ እና ምንተስኖት እሸቱ በሀረር ከተማ የተወለዱ አብሮ አደግ ጓደኛሞች ናቸው፡፡ አኚህ ከደሀ ቤተሰብ የተወለዱት ሁለት ጓደኛሞች አስተዳደጋቸው እንደ አብዛኛው ኢትዮጲያዊ ነው፡፡ ጌታቸው ኢሳያስ  እንደ አስራ ሁለተኛ ክፍል ብሄራዊ ፈተና ሁሉ የዩኒቨርስቲ ትምህርቱን በጥሩ ውጤት አጠናቋል፡፡ ምንተስኖት በበኩሉ በሙያና ቴክኒክ ትምህርት ቤት በብረት ስራ የተመረቀ ወጣት ነው፡፡ ሁለቱ ጓደኛሞች ትምህርታቸውን ካጠናቀቁ በሁላ ወደ ስራ ፍለጋ  ነበር ያመሩት፡፡ ምንተስኖት  ከሰፈሩ ልጆች ጋር በመሆን ለኮንዶሚኒየም ቤቶች የሚሆን እና ለሌሎች ድርጅቶች በርና መስኮት እንዲሁም ሌሎች የብረት ውጤቶችን የሚሰራ ማህበር አቋቁመው ወደስራ ገቡ፡፡ ጌታቸው በበኩሉ ከዩኒቨርስቲ የተመረቀበትን ዲግሪ በመያዝ በሀረር ወደሚገኙ የመንግስት መስሪያ ቤቶች ስራ ፍለጋ አመራ፡፡

ጌታቸው ኢሳያስ ስራ ፍለጋ ባመራባቸው በሀረር የሚገኙ የመንግስት መስሪያቤቶች ከዲግሪው ይልቅ ሲጠይቁት የነበረው የክልሉን ቋንቋ ስለመቻሉ ነበር፡፡ በሀረር ተወልዶ ላደገው ጌታቸው ኢሳያስ ይህ ክስተት አስደንጋጭ ነበር፡፡ በሀረር ከተማ ተወልዶ ያደገ ከሀረሪ ብሄር ውጪ ያለ ወጣት ሀብሊ በሚያስተዳድራት ሀገሩ ስራ የማግኘቱ ነገር የማይታሰብ ነው፡፡ ብዙሀኑ በሀረር ተወልደው ያደጉ ወጣቶች በተወሉዱበት ሀገር ሀረር እንደ ጠራጊ፣ተላላኪ፣መዝገብ ቤት ባሉ የስራ መስኮች እንጂ በተማሩበት የሙያ ዘርፍ በመንግስት ቤት የመስራታቸው ነገር የማይታሰብ ነው፡፡ በሀገራችን ከተሞች በላቀ መልኩ የሀረር ወጣት ሀብሊ በሚያደርስበት አድሎ የተነሳ ከተማዋን ጥሎ ወደ ጎረቤት ከተሞች፣ ድሬደዋ መሰደዱ የተለመደ ነው፡፡ ከከተማዋ የወጣቶች መፍለስ ጋር በተገናኘ ሊጠቀስ የሚገባው በሺህ የሚቆጠር በሀብሊ አመራር የገፋው የሀረር ወጣት የአንድ አመት የመምህራርንነት ስልጠና ወስዶ ወደ አፋር፣አማራ ክለል፣ወደ ድሬደዋ የገጠር ቀበሌዎች የመፍለሱ እና የመሰደዱ ነገር ነው፡፡

በሌሎች የሀገሪቱ ክልሎች እንደተጀመረው ሁሉ በሀረሪ ክልል ወጣቶችን በማህበር በማደራጀት ብድር በማበደርና በማህበራት በማደራጀት በጥቃቅንና አዘነስተኛ ስራ ላይ ተሰማርተው ነበር፡፡ ጉድ እና ጅራት ከሁአላ ነው እንዲል የሀገሬ ሰው የማህበራቱ ዘላቂነት ግን ያው እንደተለመደው ከብሄር ጋር የተገናኘ ሆነ፡፡ በሀረር በአብዛኛው የሀረሪ ብሄር በማይበዛባቸው ቀበሌዎች አልያም የሀረሪ ብሄር በአባልነት በሌለባቸው  በማህበራቱ እንደተለመደው የሀብሊ የዘረኝነት አሰራር እምብዛም አላስኬዳቸውም፡፡ በሚያስገርም መልኩ በሀረሪ ክለል በአለም ባንክ እርዳታ ለኮብል እስቶን ማንጠፊያነት እንዲውል ተብሎ የተገኘውን ብዙ ሚሊየን ብር እነዚህ ማህበራት ብሩን ማግኘት ሲገባቸው የሀረሪ ብሄራራዊ ሊግ ቱባ ባለስልጣናት የማህበራቱን ፍቃድ በመጠቀም መስራታቸው ነበር፡፡ ሌላው በሚገርም ሁነታ ከማህበራት ጋር በተገናኘ በሀረር ያከው አሰቃቂ ነገር የሀረሪ ልማት ማህበር ሳምቲ በማህበር አደራጅቶ በጀጎል ዙሪያ ያሰባሰባቸው ወጣቶች እና አዛውንቶች ላለፉት ሁለት አስርት አመታት ሲዘልቁ እንደ እድገት በህብረት፣ጋራ ለለረማት የተባሉ ከሀረሪ ብሄር ውጪ ያሉ የሌላ ብሄር ተወላጆች በብዛት የሚገኙባቸው ማህበራት ከአንድ አመት በላይ መዝለቅ አለመቻላቸው ነው፡፡

ምንተስኖት ከሰፈሩ ልጆች ጋር በመሀበር ተደራጅቶ ይሰራው የነበረው የብረት ስራ ሀብሊ በሚያስተዳድራቸው የቤቶች ኤጀንሲ እና የጥቃቅን እና አነስተኛ ማደራጂያ ቢሮ ቅጥ ያጣ ዘረኝነት እና ቢሮክራሲ  የተነሳ ከአንድ አመት በላይ ሊዘልቅ አልቻለም፡፡ የነ ምንተስኖት ማህበር አንድ አመት ሙሉ እየሰራ ያገኘውን ገቢ ከሀረሪ ጥቃቅን እና አነስተኛ ቢሮ በከፍተኛ ወለድ የተበደረውን ብር ከመክፈል እና በእዳ ከመነከር ባለፈ ለማህበሩ አባላት ያተረፈው ምንም ነገር የለም፡፡ በሚያሳዝን መልኩ በነ ምንተስኖት የማህበር ፍቃድ የሀብሊ ቱባ ባለስልጣናት ዘመዶች እና ወዳጆች እነ ምንተስኖትን ቀጥረው ለጋራ መኖሪያ ቤት የሚሆን እንደ የብረት በር፣መስኮት መወጣጫ አሰርተው ዳጎስ ያለ ብር መስራታቸው ነው፡፡ በዚህ አይነቱ የተሳከረ የሀብሊ ዘረኝነት የተነሳ የነምንተስኖት ማህበር ሲፈርስ የማህበሩ አባላት ግማሾቹ ወደ ድሬደዋ እና ወደ መሀል ሀገር ሲፈልሱ ምንተስኖት የባጃጅ መንጃ ፍቃድ በማውጣት ሀረር ከተማ ላይ ባጃጅ መንዳት ጀመረ፡፡

የሀብሊ የዘረኝነት በትር አላሳራ ያላቸው ብዙሀኑ የሀረር ወጣቶች ከማህበራቱ መፈራረስ በሁአላ ፊታቸውን ያዞሩት ወደ ባጃጅ ሹፌርነት ነበር፡፡ እዚህም እሳት አለ እንዲሉ የሀብሊ የዘረኝነት ብትር በባጃጁም ቢሆን አልቀረላቸውም፡፡ ከባጃጅ ትራንስፓርት ጋር በተገናኘ በሀረር  ከተማ በሀብሊ ቱባ ባለስልጣናት መሪነት የሚከወነው ህገ ወጥ ተግባር ከትራፊክ ፓሊስ ቅጣት እና ከመንጃ ፍቃድ ጋር እንዲሁም የሀረሪ መንገድ ትራንስፓርት መስሪያቤት በመስሪያቤትነት የሚጠቀምበትን ባለ አራት ፎቅ ህንፃ ኪራይ ጋር የተገናኘ ነው፡፡ በሀረር ከተማ ባጃጅን ጨምሮ የሌሎች መኪናዎችን የማሽከርከሪያ ፍቃድ የሚሰጡት እንደ አዜብ፣ሳቢት የመሳሰሉ የሐረሪ ብሄር ተወላጆች በባለቤትነት የሚያስተዳድሯቸው ተቋማት ናቸው፡፡እነዚህ ተቋማት የባጃጅ መኪና ለመንዳት የሚረዳ መንጃ ፍቃድ አስተምሮ  ለመስጠት እስከ ስድስት ሺህ ብር ይጠይቃሉ፡፡

የሀረሪ መንገድ ትራንስፓርት መስሪያቤት በመስሪያቤትነት የሚጠቀምበትን ባለ አራት ፎቅ ህንፃ ዳጎስ ባለ ወርሀዊ ክፍያ የተከራየው ከአንድ የሀረሪ ብሄር ተወላጅ ግለሰብ ነው፡፡ በሚያስገርም ሁኔታ የሀረሪ መንገድ ትራንስፓርት መስሪያቤት በመስሪያቤትነት የሚጠቀምበትን ይህን ባለ አራት ፎቅ ህንፃ ወርሃዊ የኪራይ ገንዘብ ለመክፈል ወሩ በደረሰ ቁጥር በሀረር ከተማ ካሉት ባጃጆች  ስነስርአቱን ጠብቀው ከሚሰሩት ቅጣት ቢል የዳቦ ስም በትንሹ መቶ ብር መውሰድ ባህል ሆኗል ሀብሊ በሚያስተዳድራት ሀረር፡፡ ሌላው ከባጃጅ ጋር በተገናኘ በሀረር ያለው ጉድ የሀረሪ ብሄራዊ ሊግ ቱባ ባለስልታናት ባለቤትነት ከተያዙት ባጃጆች ጋር ይገናኛል ፡፡ እነዚህ በተለምዶ ይለፍ በማባል የሚጣወቁት ባጃጆች የፈለጉትን ሰው ከህግ አግባብ ውጪ ቢጭኑ፣ ያለቦታቸው ቢቆሙ  በሀረሪ ትራፊክ ፓሊስ የማይቀጡ ናቸው፡፡

ሌላው ሀብሊ በበላይነት በሚመራት ሀረር ያለው ህገወጥነት፣ከቀበሌ ቤቶች፣ከኮንዶሚኒየም ባለቤትነት እና የመንግስት ቤቶች ጋር የተገናኘ ነው፡፡ በህግ እንደሰፈረው አንድ ግለሰብ ከቀበሌ የተከራየውን ቤት መልቀቅ ቢፈልግ ቁልፉን ለቀበሌው መመለስ እንጂ ለሌላ ሰው መሸጥም ሆነ በነፃመስጠት እንዲሁም ማከራየት አይችልም፡፡ በሀረር ከተማ ግን ነገሩ የተገላቢጦሽ ነው፡፡ አንድ ከሀረሪ ብሄር ውጪ ያለ በቀበሌ ቤት ውስጥ የሚኖር ግለሰብ የሚኖርበትን ቤት ህግን በመጣስ  መሸጥ ቢፈልግ መሸጥ የሚችለው ለሀረሪ ብሄር ተወላጅ ብቻ ነው፡፡ ምክንያቱም ይህን ሕገወጥ ድርጊት ህጋዊ በማስመሰል የቤቱን ስም ወደ ገዢ ማዞር የሚችሉት የሀረሪ ብሄር ተወላጆች ብቻ ስለሆኑ ነው፡፡ በዚህ አካሄድ ስንቱ የሀረሪ ብሄረሰብ ተወላጅ የቤት ባለቤት የመሆኑ ሁነት በሀረር ፍንትው ያለ ሀቅ ነው፡፡ ከኮንዶሚኒየም ጋር በተያያዘ የክልሉን ፕሬዝዳንት አቶ ሙራድን ጨምሮ ቱባዎቹ የሀብሊ ባለስልጣናት ከአራት እና አምስት በላይ የኮንዶሚኒየም ቤት  ባለቤት የመሆናቸው ነገር ለሀረር ህዝብ እንግዳ አይደለም፡፡ የኮንዶሚንየም ባለቤትነትን በብሄር ደረጃ ሀረር ላይ ካየነው ከየትኛው ብሄር በተለየ በአብዛኛው የኮንዶሚኒየም ባለቤት ሀረር ላይ የሀረሪ ብሄር ተወላጅ ግለሰብ ነው፡፡ ሌላው ከቤት ጋር በተገናኘ በሀረር ያለው አይን ያወጣ ሌብነት የሀብሊ ቱባ ባለስልጣናት በስልጣን ላይ ሳሉ በመኖሪነት እንዲያገለግላቸው የተሰጣቸውን የመንግስት ቤት ስልጣን ከለቀቁ በሁአላ የቤቱን ባለቤትነት በስማቸው አዙረው ቤቱን የግላቸው ማድረጋቸው ነው፡፡ ለዚህ ማስረጃ ከተፈለገ የቀድሞው የሀረር የፓሊስ ኮሚሽን በስልጣን ላይ ሳለ የተሠጠውን ከደሴ ሆቴል ጎን ያለውን የመንግስት ቤት ስልጣን ከለለቀቀ በሁአላ መመለስ ሲገባው ቤቱን በስሙ አዙሮ እስከ አሁን ድረስ በቤቱ መኖሩን ማቅረብ ይቻላል፡፡

ከቀትር በሁአላ የሀብሊ ባለስልጣኖች በቢሮአቸው በማይገኙበት ሀረር ከተማ ለብዙሀኑ ህዝብ ግራ በሚያጋባ መልኩ እና የማእከላዊ መንግስቱን መንግስት እና ሀይማኖት የተለያዩ ናቸው የሚለውን  የሀገሪቷን ህገ መንግስት መተፃረረ መልኩ የክልሉ መንግስት አልኮል እና ቢራ በመሸጥ ህዝቡን የሚያገለግሉ ሆቴሎችን በግብር ወዘተ ጋር ተገናኘ በሆኑ መንግስታዊ ምክንያቶች ማዋከቡ የተለመደ ነው፡፡ ሌላው ከሆቴሎች ጋር በተገናኘ  በሀረር ያለው አሳዛኝ ነገር ለቱሪስቶችም ሆነ ለሀገር ውስጥ እንግዶች እና ለነዋሪዎቿ አገልግሎት የሚሰጥ ዘመናዊ ሆቴሎች በዘመነ ሀብሊ ያልተገነባላት መሆኑነ ነው፡፡

በሀረር ከተማ እንደ ጌታቸው እና ምንተስኖት አይነት ተመሳሳይ ታሪክ ያላቸው ወጣቶች በዛ ያሉ ናቸው፡፡ የጌታቸው እና የምንተስኖት ታሪክ በሀረር የሚገኙ ወጣቶችን የማህበራዊ እና የኢኮኖሚ ሁነት የሚገልፅ ነው፡፡ ተወልደው ባደጉበት ከተማ፣አባቶቻቸው ሀገራቸውን ከውጪም ሆነ ከውስጥ ወራሪ ለመከላከል ሲሉ ደማቸውን እና አጠንታቸውን በከሰከሱበት ሀገር፣  ቋንቋ፣ ብሄር ስራ ለማግኘት እንደ ቅድመ ሁኔታ ተቀምጦ ሳለ በህገመንግስቱ የተቀመጠውን ማንኛውም ኢትዮጲያዊ ሰርቶ ሀብት የማፍራት መብት አለው የሚለውን ህግ በሚንድ መልኩ የሀረር ወጣቶች በከተማቸው የክልሉን ቋንቋ አትችሉም በሚል ብቻ የወጣትነታቸውን እድሜ በአልባሌ ነገር እንዲያሳልፉት ሀረርን የሚመራው ሀብሊ አስገድዷቸዋል፡፡

አንድም በህወሀት ኢህአዴግ የተሳከረ የኢኮኖሚ ፓሊሲ በፈጠረው የኑሮ ውድነት ሁለትም በሀብሊ የዘረኝነት አስተዳደር ወጣቶቿን በሁለት ቢላዋ የምታርደው ሀረር እስከመቼ ነው ለወጣቶቿም ሆነ ለብዙሀኑ ህብረተሰቧ ሲኦል ሆና የምትቀጥለው የሚለው አሁን ላይ በሀረር ከተማ እና አካባቢዋ ባሉ ብዙሀኑ ህዝብ የሚጠየቅ ጥያቄ ሆኗል፡፡

የጉናው ሰው!! አንዱዓለም አራጌ ማነው?

የትውልድ አካባቢና የልጅነት ጊዜ

አቶ አንዱዓለም አራጌ በጎንደር ክ/ሀገር በደብረታቦር አውራጃ በፋርጣ ወረዳ ጉና ተራራ ሥር ወይንም ግርጌ ክምር ድንጋይ ከተባለ ቦታ በ65 ዓ.ም ጥቅምት 25 ቀን ተወለደ፡፡ የኢትዮጵያ አብዮት ሊፈነዳ ሁለት ዓመት ሲቀረው በምጥ ዋዜማ ማለት ነው፡፡
“ሰው አካባቢውን ይመስላል” እንደሚባለው አንዱዓለም አራጌ በክ/ሀገሩ ከራስ ዳሽን ተራራ ቀጥሎ በሁለተኛ ደረጃነት ከሚጠቀሰው ጉና ተራራ ስር በመወለዱ ለኢሕአዴግ እንደ ጉና ተራራ ኮርቶና ከብዶ ታይቶታል፡፡ እናም አስሮ በሽብርተኝነት በመወንጀልአሞቱን ያፈሰሰ መስሎታል፡፡ አንዱዓለም አራጌ ግን እንዲህ በቀላሉ የሚፈታ አይደለም፡፡ ለምንም ነገር የማይበገር፣ ችግር የማይፈታው፣ ለቆመለት ዓላማ ወደ ኋላ የማይል፣ ከሁሉም በላይ ቅጥፈትንና እብለትን አጥብቆ ይጠየፋል፡፡ ባጭሩ ትክለ ሰውነቱ ወይንም ስብእናው በቁም ነገር የታነፀ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ለቆመለት ዓላማና ላመነበት ነገር ያላንዳች ይሉኝታና ፍርሃት ሽንጡን ገትሮ ይከራከራል፡፡ በዚህ አቋሙና ፅናቱም ነው ገና በለጋ እድሜው ሩጦ ሳይጠግብ፣ ሠርቶ ሣይደክም በተደጋጋሚ የእሥር ሰለባ ለመሆን የበቃው፡፡

አንዱዓለም አራጌ አሥራ አንድ ዓመት እስከሚሞላው ድረስ ክምር ድንጋይ ከወላጆቹ ጋር ቆይቷል፡፡ አባቱ የቤተ ክህነት ሰው በመሆናቸው ልጃቸው በፅኑ የግብረገብ ሥነ ምግባር ኮትኩተውና ገርተው ከማሣደጋቸውም በላይ የቤተክህነት ትምህርት እንዲማርላቸው በመሻት ካንድ ከታወቁ መርጌታ ልከውት በተመላላሽነት እየተማረ እንዳለ አዲስ አበባ የሚኖሩ አያቱ ክምር ድንጋይ ይሄዳሉ፡፡ እሳቸውም የቤተክህነት ሰው ነበሩና ንቃቱን፣ ጨዋነቱን፣ ትህትናውንና አርቆ አስተዋይነቱን በዚያች አጭር ጊዜ ቆይታቸው አስተዋሉና “ይኸ ልጅ ዘመናዊ ትምህርት መማር አለበት” ብለው ወደ አዲስ አበባ ይዘውት ይመጣሉ፡፡

ሕይወት በአዲስ አበባ

አንዱዓለም አራጌ ካያቱ ጋር አዲስ አበባ ከመጣ በኋላ መስከረም መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት በመግባት ከ1-8ኛ ክፍል ድረስ ሁለት ጊዜ ደብል ወይንም አጥፎ በማለፍ በ6 ዓመት ውስጥ ስምንተኛ ክፍልን አጠናቀቀ፡፡ ዘጠንኛና አሥርኛ ክፍልን የተማረው ኮከበ ጽባህ ሲሆን የደረጃ ተማሪ ስለነበር 11ኛና 12ኛ ክፍልን የተማረውና ከፍተኛ ውጤት አምጥቶ ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ለመግባት የበቃው በሳንጅ ዮሴፍ ት/ቤት በመማር ነበር፡፡

አንዱዓለም አራጌ በከፍተኛ ውጤት አ.አ.ዩ በመግባት በታሪክ የመጀመሪያ ዲግሪውን አግኝቷል፡፡ በዩኒቨርስቲ ቆይታውም በተለያዩ ክበባት በመግባት በኃላፊነትም ሆነ በአባልነት ካንድ ንቁ ተማሪ የሚጠበቅበትን ግዴታ ተወጥቷል፡፡ በዩኒቨርስቲው ውስጥ በአራት ዓመት ቆይታው የት/ቤት ጓደኞቹ በሚያደርጋቸው ክርክሮችና በአቋሙ ፅናት እጅግ አድርገው ያደንቁት እንደነበር ዛሬ በቅርብ የሚያውቁት ይናገራሉ፡፡ አንዱዓለም አራጌ ከሚታወቅባቸው ቁም ነገሮች መሀከል ባገራችን ገና የሰላማዊ ትግል ፅንስ ሐሳብ በቅጡ ባልታወቀበት ወቅት እሱ ሰለሰላማዊ ትግል ይሰብክ ነበር፡፡ ይህንንም ሲያደርግ የአንጋፋ ሰላማዊ ታጋዮችን አርማ በማንሳትና መርሃቸውን እንደ ምርኩዝ በመጠቀም ነው፡፡ ማርቲን ኪንግ፣ ማንዴላ፣ ማኅተመ ጋንዲን ታሪካቸውን በማጥናትና የሄዱበትን መንገድ በመከተል በዩኒቨርስቲ ቆይታው መርሃቸውን መርሁ በማድረግ የትግል ብቃቱን እንዳዳበረ በቅርብ የሚያውቁት በአጽንኦት ይናገራሉ፡፡
የአንዱዓለም አራጌ ልዩ ባህሪውና ተሰጥኦው ወይንም ትክለ ሰውነት ከላይ ለመጥቀስ እንደሞከርነው በሰላማዊ ትግል ገና ከወጣትነቱ ዕድሜው ጀምሮ ቆርቦ እያለ ገዥው ፓርቲ “ሽብር አራማጅ” ብሎ በመወንጀል ጥላሸት ሲቀባው ማየትና መስማት ያለንበትን ዘመንና ሥርዓት ምን ያህል አስጨናቂና አስከፊ እንደሆነ መገመቱ ከባድ አይሆንም፡፡ እያንዳንዳችንም ውለን ስለመግባታችን ዋስትና የለንም፡፡ ሁላችንም የሱ እጣ እንደሚጠብቀንና ጥላሸት እንደምንቀባም በርግጠኝነት መናገር እንችላለን፡፡

የሥራ ዓለም
አንዱዓለም አራጌ ከአ.አ.ዩ ትምህርቱን ጨርሶ ከወጣ በኋላ በተለያዩ ድርጅቶች ውስጥ እየተቀጠረ ሠርቷል፡፡ ከነዚህ ውስጥ የዓለም ባንክና የኢትዮጵያ ኢኮኖሚክስ ባለሙያዎች መኅበር በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

የፖለቲካ ሕይወቱ
አቶ አንዱዓለም አራጌ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ቆይታው በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ የፖለቲካ ሀሁን ከመቁጠር ጀምሮ በማዳበር ብስለቱን ያስመስከረ ቢሆንም በድርጅት ውስጥ ታቅፎ መታገል የጀመረው ግን በ1992 ዓ.ም የኢዴፓ መሥራች አባል በመሆን ነበር፡፡ በኢዴፓ ውስጥ በቆየባቸው ዓመታትም ከቋሚ ኮሚቴ አባልነት ጀምሮ ደረጃ በደረጃ አድጎ ም/ዋና ጸሐፊ በመሆን በከፍተኛ ኃላፊነት ሠርቷል፡፡ በመሆኑም በ1997 ዓ.ም ኢዴፓ /ቅንጅትን ወክሎ በተወለደበት ክ/ሀገር ፋርጣ ወረዳ ለተወካዮች ም/ቤት ተወዳድሯልለ፡፡ በምርጫው ውጤት ቅንጅት ቢያሽንፍም ከፍተኛ አመራሩና አባላቱ በተለያዩ እስር ቤቶች ሲታሰሩ እሱም አብሮ ቃልቲ እስር ቤት ለሁለት ዓመታት ቆይቷል፡፡ በሁለት ዓመት ቆይታውም የብረት ግድግዳ በመሆን ፅናቱን አስመስክሯል፡፡ ከእስር ቢለቀቅም ከፖለቲካው ወደ ኋላ አላፈገፈገም፡፡ አንድነት ፓርቲን በመቀላቀል የብሔራዊ ም/ቤትና የሥራ አሥፈፃሚ አባል በመሆን ለዋና ጸሐፊነት ተመርጦ ላንድ ዓመት በቆራጥነት አገልግሏል፡፡ ብቃቱን በማስመስከሩም በም/ሊቀመንበርነት የሕዝብ ግንኙነት ሐላፊ ሆኖ ተመርጦ በማገልገል ላይ እንዳለ ነው ርምጃው ያልጣመው ገዥው ፓርቲ ከግንቦት 7 ጋር በማገናኘት የሽብርተኝነት ጥላሸት በመቀባት መስከረም 3 ቀን 10 ሰዓት ላይ ከመንገድ የታጠቁ ኃይሎች ከመኪና አስወርደው ይዘውት የሄዱት፡፡

የቤተሰብ ሁኔታ
ወጣቱ ፖለቲካኛ አንዱዓለም አራጌ ባለትዳርና የሁለት ህፃናት አባት ነው፡፡ አንዱዓለም አራጌ ትዳር የመሠረተው ከእስር ከተፈታ በኋላ በ2000ዓ.ም ከዶ/ር ሰላም አስቻለው ጋር በሥርዓተ ተክሊል ነው፡፡ እንግዲህ ስለሱ ባጭሩ ይህን ያህል ካልን በመጨረሻ ፍ/ቤት ቀርቦ ቃሉን ሲሰጥ በተናገረው ሀሳባችንን እንቋጫለን “መንግሥት ለኢትዮጵያ ሕዝብ የአፋና ሥራ እየሠራ ነው፡፡ እኔም አንዱ የዚህ ሰለባ ነኝ፡፡ ፍ/ቤት ነፃ ሆኖ የራሱን ሂደት ያያል የሚል እምነት ስለሌለኝ እስከመጨረሻው የሞት ፍርድ ድረስ ቢደርስብኝም ከመቀበል ሌላ የምከራከረውም ሆነ የምናገረው ነገር የለኝም”
ፍኖተ – ከነፃነት ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል
አንዱዓለም አራጌ መስከረም 4 ቀን 2004ዓ.ም፡፡

አቶ ማሙሸት አማረ ዐቃቤ ሕግ ባቀረበባቸው የሰነድ ማስረጃ ላይ ያቀረቡት ትችት

አቶ ማሙሸት አማረ ዐቃቤ ሕግ ባቀረበባቸው የሰነድ ማስረጃ ላይ ያቀረቡት ትችት

“በደህንነት ሪፖርቱ ተዘጋጀ የተባለው፣ ተከሳሽ ሲጠቀምባቸው ነበሩ የተባሉ ሰባት የሚደርሱ ተንቀሳቃሽ ስልክ ቁጥሮች ተጠልፈዋል በሚል ነው፤ ነገር ግን እነዚህ በማስረጃነት ቀረቡ የተባሉት ስልክ ቁጥሮች በእርግጥም በተከሳሽ ስም ስለመመዝገባቸው ከኢትዩ-ቴሌኮም ጋር የተደረገ የደንበኝነት ውል ማስረጃ አልቀረበም፣ የማን እንደሆኑም አይታወቅም፣ ይበልጡኑ ደግሞ፣ የደህንነቱ ሪፖርቱ ከምክንያታዊ ጥርጣሬ የጸዳ ሆኖ ትክክለኛ ፍትህ መስጠት እንዲቻል፣ ተደረገ የተባለው የተጠለፈው የስልክ ልውውጥ አብሮ ቀርቦ ተከራካሪ ወገኖች እንድንመለከተው ካለመደረጉም በላይ ፍ/ቤቱ እንኳን እንዲያዳምጠው ሳይደረግ በደፈናው የቀረበ ነው፡፡”

“ከሳሽ የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ማስረጃውን ከተከሳሽ የስልክ ቁጥሮች አሰባሰብኩት ብሎ ከማቅረብ ባለፈ ይህ ማስረጃ ሕጉ ባስቀመጠው ግዴታ መሠረት በፍርድ ቤት ፈቃድ መሠረት ስለመሰባሰቡ ያቀረበው አንዳችም ማስረጃ ሆነ ገለጻ የለም፡፡ ዐ/ሕግም ሆነ የደህንነት ተቋሙ፣ ስራቸውን ሲሰሩ፣ አገሪቱ ያወጣችውን ሕግ መሰረት አድርገው ስለማከናወናቸው ማስረጃ በማቅረብ ሊያረጋግጡ ይገባል እንጂ እርሱን ተከትለው ይሰራሉ ተብሎ ያለማስረጃ በፍ/ቤት ባለክርክር ላይ ግምት ሊወሰድበት አይችልም፡፡ የአገራችን ሕገ መንግስት በአንቀጽ 26 የዜጎች ግላዊ ህይወት የተጠበቀ መሆኑን ገልጾ፣ ይህ ግን ሊደፈር የሚችለው በአስገዳጅ ሁኔታ ሕግን ተከትሎ ብቻ እንደሆነ ንኡስ ቁጥር 3 አስቀምጧል፡፡ ዐቃቤ ሕግ ያያያዘው ማስረጃ፣ የተከሳሽን ሕገ መንግስታዊ መብቱ፣ የፀረ ሽብርተኝነት አዋጁን አስገዳጅ ድንጋጌ ተከትሎ በፍ/ቤት ፈቃድ ስላልተሰበሰበ፣ ሕገወጥ ማስረጃ ነው ተብሎ ውድቅ እንዲደረግልን እናመለክታለን፡፡”

(ሙሉውን የሰነድ ማስረጃ ትችት ከስር ይመልከቱ)

ቀን፡- 11/03/2010 ዓ.ም

በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት
ልደታ ምድብ 4ኛ ወንጀል ችሎት

አዲስ አበባ

ከሳሽ ————-የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ

ተከሳሽ ————- አቶ ማሙሸት አማረ ድልነሴ

ከሳሽ የፌዴራል ጠቅላይ ዐ/ሕግ በቀን 25/02/2009 ዓ/ም በቁጥር ፌ/ጠ/ዐ/ህግ/የተ/ድ/ተ/02/10 በተጻፈ ባቀረበው ክስ ላይ በቀረቡ ሰነድ ማስረጃዎች ላይ ከተከሳሽ በወ/መ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ. 146 መሠረት የቀረበ ትችት፤

ዐቃቤ ሕግ በሰነድ ማስረጃ ዝርዝር ተራ ቁጥር 1ኛ ላይ በብሔራዊ የመረጃና ደህንነት አገልግሎት ተቋም በቁጥር ደመ 42/119/09 በሐምሌ 3 ቀን 2009 ዓ.ም ተዘጋጅቶ ቀረበ ያለውን የቴክኒክ ማስረጃ በተመለከተ፤

ዐቃቤ ሕግ በሰነድ ማስረጃው ተራ ቁጥር 1 ላይ ከብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት በቁጥር፡- ደመ 42/119/09 በሐምሌ 3 ቀን 2009 ዓ.ም ተዘጋጅቶ ቀረበ ያለውን የቴክኒክ ማስረጃ በማያያዝ ተከሳሽ ህጋዊ ፖለቲካ ፓርቲ አባልነት እንደ ሽፋን በመጠቀም እራሱን አርበኞች ግንቦት ሰባት ብሎ ከሚጠራው የሽብር ቡድን ጋር የነበረውን እንቅስቀሴ ያሳያል ሲል አ/ቁ. 652/2001 አንቀጽ 14(1) ጠቅሶ በተከሳሽ ላይ ከስልክ ቁጥራቸው የተሰበሰበ ገጽ- 47 ማስረጃ አያይዟል፡፡

በቅድሚያ አንድ ማስረጃ ከላይ ዐ/ሕግ በጠቀሰው ሕግ አንቀጽ 14(1) ስር እንዲቀርብ ማስረጃው ከፍርድ ቤት ፈቃድ በመውሰድ መሰባሰብ እንዳለበት ሕጉ ግዴታን እንደሚከተለው በማለት ጥሏል፣” የሽብርተኝነት ድርጊትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የብሔራዊ የመረጃና ደህንነት አገልግሎት ከፍርድ ቤት ፈቃድ በመውሰድ…..” ማስረጃዎች ማሰባሰብ እንደሚችል ገልጿል፡፡

ከሳሽ የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ማስረጃውን ከተከሳሽ የስልክ ቁጥሮች አሰባሰብኩት ብሎ ከማቅረብ ባለፈ ይህ ማስረጃ ሕጉ ባስቀመጠው ግዴታ መሠረት በፍርድ ቤት ፈቃድ መሠረት ስለመሰባሰቡ ያቀረበው አንዳችም ማስረጃ ሆነ ገለጻ የለም፡፡ ዐ/ሕግም ሆነ የደህንነት ተቋሙ፣ ስራቸውን ሲሰሩ፣ አገሪቱ ያወጣችውን ሕግ መሰረት አድርገው ስለማከናወናቸው ማስረጃ በማቅረብ ሊያረጋግጡ ይገባል እንጂ እርሱን ተከትለው ይሰራሉ ተብሎ ያለማስረጃ በፍ/ቤት ባለክርክር ላይ ግምት ሊወሰድበት አይችልም፡፡ የአገራችን ሕገ መንግስት በአንቀጽ 26 የዜጎች ግላዊ ህይወት የተጠበቀ መሆኑን ገልጾ፣ ይህ ግን ሊደፈር የሚችለው በአስገዳጅ ሁኔታ ሕግን ተከትሎ ብቻ እንደሆነ ንኡስ ቁጥር 3 አስቀምጧል፡፡ ዐቃቤ ሕግ ያያያዘው ማስረጃ፣ የተከሳሽን ሕገ መንግስታዊ መብቱ፣ የፀረ ሽብርተኝነት አዋጁን አስገዳጅ ድንጋጌ ተከትሎ በፍ/ቤት ፈቃድ ስላልተሰበሰበ፣ ሕገወጥ ማስረጃ ነው ተብሎ ውድቅ እንዲደረግልን እናመለክታለን፡፡

ፍ/ቤቱ ይሄን ከላይ ያቀረብነውን ክርክር አያልፈውም እንጂ የሚያልፍበት በቂና ሕጋዊ ምክንያት ካለ ደግሞ በአማራጭ የሚከተለውን ክርክር እናቀርባለን፡፡ የደህንነት ሪፖርቱ ተዘጋጀ የተባለው፣ ተከሳሽ ሲጠቀምባቸው ነበሩ የተባሉ ሰባት የሚደርሱ ተንቀሳቃሽ ስልክ ቁጥሮች ተጠልፈዋል በሚል ነው፤ ነገር ግን እነዚህ በማስረጃነት ቀረቡ የተባሉት ስልክ ቁጥሮች በእርግጥም በተከሳሽ ስም ስለመመዝገባቸው ከኢትዩ-ቴሌኮም ጋር የተደረገ የደንበኝነት ውል ማስረጃ አልቀረበም፣ የማን እንደሆኑም አይታወቅም፣ ይበልጡኑ ደግሞ፣ የደህንነቱ ሪፖርቱ ከምክንያታዊ ጥርጣሬ የጸዳ ሆኖ ትክክለኛ ፍትህ መስጠት እንዲቻል፣ ተደረገ የተባለው የተጠለፈው የስልክ ልውውጥ አብሮ ቀርቦ ተከራካሪ ወገኖች እንድንመለከተው ካለመደረጉም በላይ ፍ/ቤቱ እንኳን
እንዲያዳምጠው ሳይደረግ በደፈናው የቀረበ ነው፡፡

የፀረ ሽብርተኝነት አ/ቁ. 652/2001 አንቀጽ 14(1)(ሀ) የሚለው ” በሽብርተኝነት ወንጀል የተጠረጠረን ሰው የስልክ… ግንኙነቶችን ለመጥለፍ ወይም ለመከታተል ይችላል” ነው፡፡ በዚሁ አንቀጽ መሠረትም፣ ከሳሽ ዐቃቤ ሕግ ከተከሳሽ የስልክ ግንኙነቶች ላይ ተከታትሎ የጠለፋቸውን ልውውጦች፣ ከሪፖርቱ ጎን ለጎንም ቢሆን አላቀረበም፡፡ ይህን ሕግ መሠረት አድርጎ የሰበሰበውን የስልክ ግንኙነት ለፍ/ቤቱ ካላቀረበ ደግሞ ተከሳሽ እነዚህን ስልክ ቁጥሮች ተጠቅሞ የሽብር እንቅስቃሴ ማድረግ አለማድረጉን በእርግጠኝነት ለመደምደም የማያስችል ስለሆነ ማስረጃው ውድቅ ሊደረግ ይገባዋል፡፡

ነገር ግን ፍ/ቤቱ ብይን ከመስጠቱ በፊት እነዚህን በደህንነት መስሪያ ቤቱ የተጠለፉ የስልክ ልውውጦችን አስቀርቦ መመርመሩ ትክክለኛ ፍትህ ለመስጠት እና እውነት ላይ ለመድረስ ወሳኝ በመሆኑ ከኢትዮ ቴሌኮም ወይም ከብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት በትእዛዝ ቀርበው ሊመረመሩ ይገባልናል ስንል እናመለክታለን፡፡

ዐቃቤ ሕግ በሰነድ ማስረጃ ዝርዝር ተራ ቁጥር 2ኛ ላይ በብሔራዊ የመረጃና ደህንነት አገልግሎት ተቋም በቁጥር ደመ 42/229/09 በሐምሌ 14 ቀን 2009 ዓ.ም ተዘጋጅቶ ቀረበ ያለውን የቴክኒክ ማስረጃ በተመለከተ፤

ዐቃቤ ሕግ በሰነድ ማስረጃው ተራ ቁጥር 2 ላይ ከብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት በቁጥር፡- ደመ 42/229/09 በሐምሌ 14 ቀን 2009 ዓ.ም ተዘጋጅቶ ቀረበ ያለውን የቴክኒክ ማስረጃ በማያያዝ ተከሳሽ ህጋዊ ፖለቲካ ፓርቲ አባልነት እንደ ሽፋን በመጠቀም እራሱን አርበኞች ግንቦት ሰባት ብሎ ከሚጠራው የሽብር ቡድን ጋር የነበረውን እንቅስቀሴ ያሳያል ሲል አ/ቁ. 652/2001 አንቀጽ 23(1) ጠቅሶ በተከሳሽ ላይ የተሰበሰበ ገጽ- 11 ማስረጃ አያይዟል፡፡
ይህ ማስረጃ ሲመዘን በአዋጁ አንቀጽ 23(1) መሠረት ተቀባይነት አለው ከሚባል ባሻገር፣ በምን አይነት ሁኔታ እና እንዴት እንደተገኜ የማይታወቅ፣ አንዳንድ ግዜም ተአማኒነቱ በእጅጉ አጠራጣሪ ስለሆነ ፍ/ቤቱ በተከሳሽ ላይ ሊያስረዳ ይችላል ብሎ ክብደት ሊሰጠው የሚገባ ማስረጃ አይደለም፡፡ ማስረጃው በየአንቀጾቹ መጨረሻ ላይ በመረጃ ተረጋግጧል እያለ ድምዳሜ ለመስጠት ቢሞክርም በምን አይነት መረጃ ተረጋገጠ፣ መረጃውስ ትክክል ነው ወይስ አይደለም? ብሎ ተከሳሽ እራሱን እንዲከላከል የማያስችል በመሆኑ የደህንነት መስሪያ ቤቱ የፈጠራ ማስረጃ ከመሆን ባለፈ አንድ የተከሰሰ ሰው ላይ ክብደት ተሰጥቶት ሊቀርብ የሚችል ማስረጃ አለመሆኑን ፍ/ቤቱ በማስረጃ ምዘና ወቅት የሚገነዘበው ጉዳይ ነው፡፡

ዐቃቤ ሕግ በማስረጃነት አያይዞ ባቀረበው የደህንነት ሪፖርት ላይ የሚከተሉት ነጥቦች አለመሟላታቸው ማስረጃውን ጎዶሎ/ደካማ(weak probative value) በማድረግ ክሱን እንዳላስረዳ የሚያሳዩ ነጥቦች ናቸው፤

ዐቃቤ ሕግ በክስ ማስረጃነት አይይዞ ባቀረበው የደህንነት ሪፖርት ላይ ተከሳሽ ሽመልስ ለገሰ በተባለ የአርበኞች ግንቦት ሰባት አባል ተመልምሏል ቢልም፣ የትና እንዴት? እንደተመለመለ አይገልጽም፤

ዐቃቤ ሕግ በክስ ማስረጃነት አይይዞ ባቀረበው የደህንነት ሪፖርት ላይ ተከሳሽ የፖለቲካ ፓርቲ አባልነቱን፣ አመራርነቱን እንደሽፋን ተጠቅሟል፣ ከአርበኞች ግንቦት ሰባት ተልዕኮ ተሰጠው፣ እርሱም ስምምነት አድርጓል ቢልም፣ የትኛው የፖለቲካ ፓርቲ እንደሆነ፣ ተልዕኮ የተቀበለው በምን እንደሆነ፣ ስምምነቱን በምን? እንዳስታወቀ አይገልጽም፤

ዐቃቤ ሕግ በክስ ማስረጃነት አይይዞ ባቀረበው የደህንነት ሪፖርት ላይ ተከሳሽ በሚያዝያ/2007 ዓ.ም ለሽብር ቡድኑ አባላትን ከአዲስ አበባ መልምሎ ልኳል ቢልም፣ እነማንን፣ ብዛታቸው ስንት እንደሆነ፣ እንዴት? እንደላካቸው አይገልጽም፤
ዐቃቤ ሕግ በክስ ማስረጃነት አይይዞ ባቀረበው የደህንነት ሪፖርት ላይ ተከሳሽ ታህሳስ/2008 ዓ.ም ከተለያዩ አካባቢዎች የመለመላቸውን 11 የሽብር ቡድን አባላትን ቦሌ ክፍለ ከተማ ሰብስቦ አንዱን ብሄር በሌላኛው ብሄር እንዲነሳሳ ተልዕኮ ሰጥቷል ቢልም፣ ከየት አካባቢ እንደተመለመሉ፣ አነማንን መመልመሉን፣ የተሰበሰቡት ቦሌ ክ/ከተማ የት ቦታ እንደሆነ እና የትኛውን ብሄር በየትኛው ብሄር ላይ? እንዳነሳሳ አይገልጽም፣

ዐቃቤ ሕግ በክስ ማስረጃነት አይይዞ ባቀረበው የደህንነት ሪፖርት ላይ ተከሳሽ በየካቲት/2008 ዓ.ም አዲስ አበባ ያደራጃቸውን 12 አባላት ሰበሰበ፣ በየቀጠና አከፋፍሎ ልኳል ቢልም፣ እነማንን፣ የት እንዳደራጀ፣ ቀጠናዎቹ ስንትና እነማን እንደሆኑ አይገልጽም፤

ዐቃቤ ሕግ በክስ ማስረጃነት አይይዞ ባቀረበው የደህንነት ሪፖርት ላይ ተከሳሽ በግንቦት/2008 ዓ.ም ሰሜን ሸዋ ወታደራዊ ቤዝ መረጠ፣ ዘጠኝ አባላትን ለወታደራዊ ስልጠና ላከ ቢልም፣ ሰሜን ሸዋ የት ቦታ፣ ዘጠኝ አባላቱ እነማን እንደሆኑ፣ እንዴት እንደላካቸው አይገልጽም፤

ዐቃቤ ሕግ በክስ ማስረጃነት አይይዞ ባቀረበው የደህንነት ሪፖርት ላይ ተከሳሽ በግንቦት/2008 ዓ.ም ውጪ ከሚገኙ አመራሮች ደጋፊዎች 80ሺ ብር ተላከለት፣ መሳሪያ ገዛ፣ አውግቼው በተባለ ሰው ልኮ አስታጠቀ ቢልም፣ አመራሮቹ ደጋፊዎቹ እነማን እንደሆኑና የት እንደሚገኙ፣ ገንዘቡ በማንና እንዴት ተልኮለት እጁ እንደገባ፣ መሳሪያ የታጠቁት እነማን እንደሆኑ፣ አውግቸው የተባለው ሙሉ ስሙን አይግልጽም፤
ዐቃቤ ሕግ በክስ ማስረጃነት አይይዞ ባቀረበው የደህንነት ሪፖርት ላይ ተከሳሽ በሰኔ/2008 ዓ.ም ዘመነ ምህረት፣ ለገሰ ወልደሃና ከተባሉ የሽብር ቡድኑ አመራር/አባል ጋር አዲስ አበባ ተሰብስቦ ተልዕኮ ሰጥቷል ቢልም፣ አዲስ አበባ የት እንደተሰበሰበ እና ጊዜውን? አይገልጽም፤

ዐቃቤ ሕግ በክስ ማስረጃነት አይይዞ ባቀረበው የደህንነት ሪፖርት ላይ ተከሳሽ በህዳር/2009 ዓ.ም የመለመላቸውን፣ ያደራጃቸውን አባሎች/አመራሮች ጠርቶ ተልዕኮ ሰጠ ቢልም፣ እነማን እንደሚባሉ፣ የት አካባቢ እንደጠራቸው፣ በምን ጥሪ እንዳደረገላቸው አይገልጽም፤

ዐቃቤ ሕግ በክስ ማስረጃነት አይይዞ ባቀረበው የደህንነት ሪፖርት ላይ ተከሳሽ በተለያዩ ስልክ ቁጥሮች በመጠቀም ከውጭ 100 ሺ ብር በህዳር/2009 ተላከለት፣ በ50 ሺ ብር ጥይት ገዛ ቢልም፣ አመራር/አባላት የተባሉት እነማን እንደሆኑ፣ የተላከለትን ገንዘብ በምን አይነት ሁኔታ እንዲደርስ እንዳደረገ፣ ከየት አገርና በምን አይነት መንገድ እንደተላከለት፣ ገንዘቡን ለማን ሰሜን ሸዋ ውስጥ እንደሰጡ፣ ታጣቂዎቼ እነማን እንደሆኑ፣ ገንዘብና ስንቅ የሰጠው ማን እንደሆነ አይገልጽም፤

ዐቃቤ ሕግ በክስ ማስረጃነት አይይዞ ባቀረበው የደህንነት ሪፖርት ላይ ተከሳሽ በታህሳስ/2009 ዓ.ም ከአዲስ አበባ የተመለመሉትን 6 ሰዎች በገዛኸኝ በኩል ላከ ቢልም፣ የተላኩት እነማን እንደሆኑ፣ የሄዱበት ቦታ ሰሜን ሸዋ የት እንደሆነ፣ በምን እንደላካቸው፣ ገዛኸኝ የተባለውን ሙሉ መጠሪያው አይገልጽም፤

ዐቃቤ ሕግ በክስ ማስረጃነት አይይዞ ባቀረበው የደህንነት ሪፖርት ላይ ተከሳሽ በጥር/2009 ዓ.ም ውጭ ካሉ አመራሮች ስለአደረጃጀት መመሪያ፣ መተዳደሪያ ደንብ እና አመጽ ጽሁፍ ተልኮለት በህቡ አወያይቷል ቢልም፣ ከየት አገር እንደተላኩለት፣ አመራሮቹ ማን እንደሚባሉ፣ በምን አይነት መልኩ እንደተላከለት፣ የት እንዳወያየ፣ ማንን እንዳወያየ? አይገልጽም፤

ዐቃቤ ሕግ በክስ ማስረጃነት አይይዞ ባቀረበው የደህንነት ሪፖርት ላይ ተከሳሽ በታህሳስ/2009 ዓ.ም ለመሳሪያ መንዣና ትጥቅ ብር 80ሺ ብር ተልኮለት ከስልጠና ለተመለሱት አስታጠቀ ቢልም፣ እነማን እንዳስታጠቀ፣ ገንዘብ እንደሚያስፈልግ የገለጸው ለማን እንደሆነ፣ ከየት አገር ገንዘብ እንደተላከለት፣ በምን አይነት መንገድ ግንኙነት እንዳደረገ፣ ገንዘቡ በምን አይነት መንገድ እንደተላከለት፣ ጥይት የትና መቼ እንደገዛ? አይገልጽም፤

ዐቃቤ ሕግ በክስ ማስረጃነት አይይዞ ባቀረበው የደህንነት ሪፖርት ላይ ተከሳሽ በመጋቢት/2009 ዓ.ም ውጭ አገር ሄዶ የሽብር ተግባር እንዲመራ ተልዕኮ ተሰጥቶት ኬንያ ሊሄድ ሞያሌ ላይ ተያዘ ቢልም፣ ተልዕኮ ማንና እንዴት እንደተሰጠው አይገልጽም፤

ዐቃቤ ሕግ የሰነድ ማስረጃ አድርጎ ባቀረበው ሪፖርት ላይ ተከሳሽ ሙሉቀን ተስፋው እና ሸንቁጥ አየለ ከተባሉ የአርበኞች ግንቦት ሰባት አመራሮች ጋር ግንኙነት ፈጥሯል ያለ ቢሆንም መቼ፣ በምን አይነት መንገድ እና ለምን አላማ እንደተገናኘ አያስረዳም፡፡

ስለሆነም ይህ ሪፖርት ክሱን አስረጅ ሊሆን አይችልም፡፡ ከእነዚህ ግለሰቦች ጋር አለመገናኘቱ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ አቶ ሙሉቀን ተስፋው እና አቶ ሸንቁጥ አየለ የተባሉት ግለሰቦች የአርበኞች ግንቦት ሰባት የተባለው ድርጅት አባል ካለመሆናቸውም ባሻገር የዚህን ድርጅት አመለካከት የማያራምዱ እና በአብዛኛው “የአምሓራ ብሔርተኝነት” አራማጆች መሆናቸውን በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ በራሳቸው ገጾች ላይ የሚገልጹት አቋም(በተለጠይም አቶ ሙሉቀን ተስፋው “የጥፋት ዘመን” እና “አገር አልባ ባላ’ገር” የሚለውን አሳትመው በገበያ ላይ በመሸጥ የሚገኘውን የመጽሐፍ ስራቸውን ሊመለከተው ይችላል) መሆኑን መገንዘብ መቻሉ፣ የደህንነት ተቋሙ ማስረጃዎቹን ሰበሰብኩ ከማለት ባለፈ ስራውን ባግባቡ እንዳልሰራ ፍንትው አድርጎ ለፍ/ቤቱም የሚያስረዳ ነው፡፡

በደህንነት ሪፖርቱ ላይ ተከሳሽ ቅንነት፣ አምባሰል፣ ራስ ዳሽን፣ ሀብታሙ፣ አለምፀሀይ፣ ታምርነሽ እና ከሌሎች የአርበኞች ግንቦት ሰባት አባላት እና አመራሮች ጋር ግንኙነት ፈጥሯል ያለ ቢሆንም በመጀመሪያ ደረጃ እነዚህ ግለሰቦች በእርግጥ በህይወት ያሉ ግለሰቦች ናቸው ወይ? ካሉስ የት ነው ያሉት? መቼስ ነው ግንኙነት የፈጠሩት? ግባቸውስ ምንድን ነው? የሚለው ባልታወቀበት ሁኔታ በደህንነት ሪፖርት ላይ ስለተጻፈ ብቻ ማስረጃ ሆኖ ሊቀርብ አይገባም፡፡

ዐቃቤ ሕግ ያቀረበው የደህንነት ሪፖርት ማስረጃ እርስ በእርሱ የሚጋጭ ስለመሆኑ፤

ከሳሽ ዐቃቤ ሕግ በዋናነት ተከሳሽ የአርበኞች ግንቦት ሰባት አባል እና አመራር በመሆኑ የተለያዩ ተልዕኮዎችን ተቀብሏል በማለት ክስ ያቀረበ ቢሆንም የሰነድ ማስረጃው በማድረግ ባቀረበው የደህንነት ሪፖርት ገጽ 16 እና 17 ላይ አርበኞች ግንቦት ሰባት አማራን የሚፈልገው ጉልበቱን ብቻ እንጂ ከዛ ባለፈ ድርጅቱ ለአማራ ህዝብ እንደማይጠቅም ተከሳሽ ገልጿል በማለት ያስቀምጣል፡፡ ይህም፣ ተከሳሽ የአምሓራን ጉልበት እንጂ ጥቅም በዘላቂነት አያስጠብቅም የሚሉት የሽብር ድርጅት አባል እንዳልሆኑ እና ሊሆኑም እንደማይችል ከማረጋገጥ አልፎ አቃቤ ሕግ ያቀረብኩትን ክስ ያስረዳልኛል በማለት ያቀረበው ሪፖርት እርስ በእርሱ የሚጣረስ መሆኑን ያስገነዝባል፡፡

ስለሆነም ፍ/ቤቱ ዐቃቤ ሕግ በተከሳሽ ላይ ያቀረበው የሰነድ ማስረጃ ከላይ ባነሳነው ምክንያት እንደ ክሱ ያላስረዳ በመሆኑ የቀረበብንን ክስ ውድቅ በማድረግ መከላከል ሳያስፈልገን ከክሱ እንዲያሰናብተን ስንል በትህትና እናመለክታለን፡፡

የተከሳሽ ጠበቃ ሄኖክ አክሊሉ

“በማያዳምጡ ተናጋሪዎች” እና “በማይናገሩ አድማጮች” መካከል መግባባት አይኖርም!

“በማያዳምጡ ተናጋሪዎች” እና “በማይናገሩ አድማጮች” መካከል መግባባት አይኖርም!

ሕወሃት/ኢህአዴግ መስራችና ከፍተኛ አመራር አቦይ ስብሃት ነጋ ከአዲስ ዘመን ጋር ያደረጉት ቃለ-ምልልስከተለመደው ወጣ ያለና በገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ ላይ ጠንከር ያለ ትችት የሰነዘሩበት ነው። አቦይ ስብሃት ከሁሉም ባለስልጣናት በተለየ ሃሳባቸውን በነፃነት ሲገልፁ በተደጋጋሚ ይስተዋላል። አሁንም የገዛ ፓርቲያቸውን ልክ-ልኩን ነገሩት እኮ! መቼም እንደሳቸው የተሰማውን በነፃነት መናገር የማይሻ ሰው ይኖራል ብዬ አላስብም። ይሁን እንጂ፣ አሁን ባለው ሁኔታ ልክ እንደ እሳቸው በነፃነት ወይም በድፍረት ለመናገር የሚደፍር ሰው መኖሩን እጠራጠራለሁ። በእርግጥ “ከሁላችንም በተሻለ ኢህአዴግን ያለ ስጋት የመተቸት ዕድል ያለው እሳቸው ብቻ ናቸው” ብል ማጋነን አይሆንም።

ይህ ፅኁፍ አቦይ ስብሃት “ለእኔ ብሔራዊ መግባባት ያለ አይመስለኝም። አሁን ላይ ያለው ትምክህት፣ ጠባብነት እና አክራሪነት ነው” በማለት በሰጡት አስተያየት ዙሪያ የሚያጠነጥን ነው። በእርግጥ እሳቸው እንዳሉት በሀገራችን ብሔራዊ መግባባት የለም። ነገር ግን፣ ብሔራዊ መግባባት እንዳይኖር ያደረገው ዋና ምክንያት ምንድነው? አቦይ ስብሃት የጠቀሱዋቸው የትምክህት፣ ጠባብነት እና የአክራሪነት አመለካከቶችን ከብሔራዊ መግባባት አለመኖር ጋር ተያያዥነት አላቸው? እነዚህንና ሌሎች ተያያዥ ጥያቄዎችን እንደሚከተለው ለመዳሰስ እሞክራለሁ።

በመሰረቱ በአንድ ሀገር ብሔራዊ መግባባት ሊኖር የሚችለው በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የጋራ የሆነ አቋምና አመለካከት ሲኖር ነው። ለዚህ ደግሞ በተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች ዘንድ በሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ግልፅና ነፃ የሆነ ውይይት በማድረግ የጋራ ግንዛቤ ሊፈጠር ይገባል። በመሆኑም፣ ብሔራዊ መግባባት እንዲኖር ዜጎች በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት የሚያደርጉበት፤ ሃሳብ የሚለዋወጡበት፣ እምነትና አመለካከታቸውን የሚያንፀባርቁበት፣ ያሏቸውን ጠቃሚ ልምዶች፥ ዕሴቶችና ባህሎች የሚጋሩበት…ወዘተ፣ ከፖለቲካዊ ወገንተኝነት የፀዳ የጋራ የሆነ መድረክ ሊኖራቸው ይገባል።

ይህ ካልሆነ በሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ የጋራ የሆነ ግንዛቤ በዜጎች ዘንድ መፍጠር አይቻልም። በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በቂ የሆነ ግንዛቤ የሌላቸው ዜጎች ብሔራዊ መግባባትን በሚያሳይ መልኩ የጋራ አቋምና አመለካከት እንዲያንፀባርቁ መጠበቅ “ላም ባልዋለበት…” የሚሉት ዓይነት ነው። ስለዚህ፣ በሀገራችን ብሔራዊ መግባባት ላለመኖሩ በዋና ምክንያትነት ሊጠቀስ የሚገባው ነገር ነፃና ገለልተኛ የሆነ የውይይት መድረክ አለመኖር ነው።

በተመሣሣይ፣ እንደ ትምክህት፥ ጠባብነትና አክራሪነት ያሉ ፅንፈኛ አመለካከቶች በሀገሪቱ ውስጥ እንዲስፋፉ ያደረገው ነፃ የውይይት መድረክ አለመኖሩ ነው። በተለይ ባለፉት 25 ዓመታት፤ ስለ ብሔራዊ አንድነትና የቀድሞ ታሪክ የሚናገሩትን ወገኖች “ትምክህተኞች”፣ የብሔርተኝነትና እኩልነት ጥያቄ የሚያነሱትን ወገኖች ደግሞ “ጠባቦች”፣ እንዲሁም ስለ ሃይማኖትና እምነት ነፃነት የሚጠይቁትን “አክራሪዎች” ብሎ በጅምላ በመፈረጅ ያላቸውን የተለየ ሃሳብና አመለካከት በነፃነት እንዳያንፀባርቁ ተደርገዋል።

ነገር ግን፣ ሃሳብና አመለካከታቸውን በነፃነት የሚያንፀባርቁበት የጋራ መድረክ አለመኖሩ ወይም መነፈጋቸው ይበልጥ ፅንፈኛ እየሆኑ እንዲሄዱና ይህንንም ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ በማህብረሰቡ ውስጥ ለማስረፅ ጥረት እንዲያደርጉ አድርጓቸዋል። ከዚህ በተጨማሪ፣ በውይይት ያልዳበረና በምክንያታዊ ዕውቀት ላይ ያልተመረኮዘ ግንዛቤ የሌለው ማህብረሰብ ለፅንፈኛ አመለካከቶች ተጋላጭ ቢሆን ሊገርመን አይገባም። ስለዚህ፣ ከብሔራዊ መግባባት በተጨማሪ፣ ለትምክህት፥ ጠባብነትና አክራሪነት አመለካከቶች በሀገሪቱ እንዲስፋፉ በዋና ምክንያትነት ሊጠቀስ የሚገባው ነገር በድጋሜ ነፃና ገለልተኛ የሆነ የውይይት መድረክ አለመኖሩ ነው።

ከላይ በዝርዝር ለመጥቀስ እንደተሞከረው፣ ለብሔራዊ መግባባት መጥፋት እና ለትምክህት፥ ጠባብነትና አክራሪነት መፈጠር ዋና ምክንያቱ ነፃና ገለልተኛ የሆነ መድረክ አለመኖር ነው። ነፃና ገለልተኛ የሆነ የውይይት መድረክ እንዲኖር ደግሞ በቅድሚያ ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት ያለ ምንም መሸራረፍ ሊከበር ይገባል። ምክንያቱም፣ ስለ ራሱ ችግር በግልፅ ለመናገር የሚፈራ ሰው ስለ ሌሎች ሰዎች ችግር ለመስማት ፍላጎት አይኖረውም። ስለ ራሱ መብትና ነፃነት መከበር በግልፅ ለመናገር ዕድል የሌለው ዜጋ ስለ ሀገር አንድነትና ልማት እንዲናገር መጠበቅ “የራሷ እያረረባት የሰው ታማስላለች” የሚሉት ዓይነት ይሆናል።

በፅሁፉ መግቢያ ላይ የሕወሃት/ኢህአዴግ ከፍተኛ አመራር የሆኑት አቦይ ስብሃት ነጋ “ከሁላችንም በተሻለ ኢህአዴግን ያለ ስጋት የመተቸት ዕድል ያላቸው እሳቸው ብቻ ናቸው” ብዬ ነበር። ነገር ግን፣ እንደ ችግር ለጠቀሷቸው የብሔራዊ መግባባት አለመኖር ሆነ ለትምክህት፣ ጠባብነት እና አክራሪነት አመለካከቶች መስፋፋት ዋናው ምክንያት አብዛኞቻችን ልክ እንደ እሳቸው የመናገር ነፃነት ማጣታችን ነው። ስለዚህ ችግሮቹ ዘላቂ መፍትሄ የሚያገኙት እኛም እንደ እሳቸው ሃሳብና አመለካከታችንን በነፃነት መግለፅ ስንችል ነው፡፡ 

እኔም ሆንኩ ሌሌሎች ልክ እንደ አቦይ ስብሃት የራሳችንን የፖለቲካ አቋምና አመለካከት፥ የወደፊት ተስፋና ስጋት በመንግስት ሚዲያዎች ላይ ያለ ፍርሃት የማንፀባረቅ ዕድል ሊኖረን ይገባል። ይሁን እንጂ፣ እንኳን እንደ እኔ ያለው ተራ ፀኃፊ ቀርቶ ሌሎች ከፍተኛ ባለስልጣናት ራሳቸው ከተለመደው የፓርቲ አቋም ትንሽ ወጣ ያለ ሃሳብና አስተያየት ለመስጠት ድፍረት/ነፃነት ያላቸው አይመስለኝም።

በአጠቃላይ፣ እርስ-በእርስ ለመነጋገር ሁላችንም እኩል የመናገር ነፃነት ሊኖረን ይገባል። እኩል ካልተነጋገርን አንግባባም፤ እኛ ካልተግባባን ብሔራዊ መግባባት አይኖርም። የተለያየ ቋንቋ፣ ባህል፣ ታሪክ፣ እምነት፣ ሃይማኖት፣…ወዘተ ያላቸው ብሔሮች፥ ብሔረሰቦችና ህዝቦች፣ የተለየ የፖለቲካ ልምድ፣ አቋምና አመለካከት ያላቸው የፖለቲካ ልሂቃን በነፃነት የሚነጋገሩበት የጋራ መድረክ በሌለበት እንዴት መግባባት ይቻላቸዋል?

ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት ባልተከበረበት ሀገር፤ “በማያዳምጡ ተናጋሪዎች” እና “በማይናገሩ አድማጮች” መካከል ሊኖር የሚችለው ብሔራዊ መግባባት ሳይሆን “ግራ-መጋባት” ነው። መደማመጥ በሌለበት መነጋገር ራስንና ሌሎችን ግራ-ከማጋባት የዘለለ ፋይዳ የለውም።

አቦይ ስብሃትን ጨምሮ ሁላችንም ብሔራዊ መግባባት እንጂ ግራ-መጋባትን የምንሻ አይመስለኝም። አሁን ላይ በግልፅ እንደሚስተዋለው ግን በሀገራችን ብሔራዊ መግባባት የለም። እርስ-በእርስ ተነጋግሮ ከመግባባት ይልቅ ሳይደማመጡና ሳይነጋገሩ በባዶ በሚጯጯሁ ሰዎች መካከል ምን ዓይነት መግባባት ሊኖር ይችላል?

አሁን በሀገራችን ያለው ሁኔታ ከግራ-መጋባት በስተቀር ለብሔራዊ-መግባባት ፍፁም አመቺ አይደለም። በሕገ-መንግስቱ መሠረት ዜጎች ሃሳብና አመለካከታቸውን ያለ ማንም ጣልቃ-ገብነት የሚገልፁበት ነፃና ገለልተኛ የሆነ መድረክ በመፍጠር፤ ብሔራዊ መግባባት እንዲሰፍን፣ ብሎም እንደ ትምክህት፥ ጠባብነትና አክራሪነት ያሉ ፅንፈኛ አመለካከቶች በሕብረተሰቡ ውስጥ እንዳይስፋፉ ለማድረግ ስር-ነቀል የሆነ ለውጥ ያስፈልጋል። ገዢው ፓርቲ ይህን ደረጃ ስር-ነቀል ለውጥ ለማምጣት ተግባራዊ እንቅስቃሴ ማድረግ እስካልጀመረ ድረስ በሀገራችን ላይ ከብሔራዊ መግባባት ይልቅ ግራ-መጋባት ጥላውን እንዳጠላ ይቀጥላል። ስለዚህ ጥያቄው “ብሔራዊ መግባባት ወይስ ግራ-መጋባት?” የሚል ነው።

**** 

ይህ ፅሁፍ በመጀመሪያ ለህትመት የበቃው “ብሔራዊ መግባባት ወይስ ግራ-መጋባት” በሚል ርዕስ Hornaffairs ላይ ነው፡፡

ማርጀቱንና መበስበሱን ያለሃፍረት የነገረን ሕወሃት ሞቱን እስኪያረዳን አንጠብቅም!!!

ማርጀቱንና መበስበሱን ያለሃፍረት የነገረን ሕወሃት ሞቱን እስኪያረዳን አንጠብቅም!!!
(ከሰማያዊ ብሔራዊ ሸንጎ የተሰጠ መግለጫ)

ላለፉት 26 ዓመታት ኢትዮጵያን በብረት መዳፍ ውስጥ አስገብቷት የነበረው ሕወሐት ማርጀቱንና መበስበሱን ሰሞንኑን መቀሌ ሲያደካሂደው በቆዬውና ባልቋጨው ስብሰባ ባቋራጭ በሰጠው መግለጫ አሳውቆናል፡፡ ለእርጅናዬ ምክንያት ናቸው ብሎ የገለፃቸው ነጥቦች ማለትም በሕወሃት ውስጥ የፀረ ዲሞክራሲ አስተሳሰብ መስፈን፣ በቡድን ተከፋፍሎ የአጥቂነትና የተከላካይነት ሽኩቻ መኖር፣ ከሌሎች እህት ድርጅቶቹ ጋር የነበረው ግንኙነት አሉታዊ የነበረ መሆኑና በዚህም ምክንያት ጠባብነትና የትምክህት አመለካከት መስፋፋታቸውን፣ ድርጅቱ ተተኪ አመራርን አለማፍራቱና ወጣትና ምሁራንን ማሰለፍ አለመቻሉ፣ በአጠቃላይም በተጠናወተው በትንሽ ነገር የመርካት አመለካከት ምክንያት ስትራቴጅካዊ አመራር መስጠት አለመቻሉንና በሐገሪቱ ያለውን የፖለቲካ የኢኮኖሚና የማህበራዊ ጥያቄዎች በቂ መልስ መስጠት አለመቻል የድርጅቱ ትልልቅ ችግሮች ናቸው ብሎ ገልጧል፡፡


ይህ መግለጫው ሕወሃት አሁንም ከማርጀቱ የተነሳ አዲስ ሃሳብ ማቅረብ እንዳልቻለና ያለበትንም ደረጃ በመሰረታዊ ሃሳብ ለመረዳት የሚያስችል ቁመና እንደሌለው በግልፅ አሳይቷል፡፡ ሕወሃት ከላይ ችግሮቼ ናቸው ብሎ የዘረዘራቸው ነጥቦች የችግሩ ማሳያ ምልክቶች እንጅ በራሳቸው ችግሮች አይደሉም፡፡ በሌላ አነጋገር የበሽታ ምልክቶችን እንደ ዋና በሽታ መውሰድ ማለት ነው፡፡ የሕወሃት ችግር በስትራቴጅካዊ አስተሳሰብ ስንመረምረው ሕወሃት ይከተላቸው የነበሩ መንትያ የአገዛዝ ስልቶች ማርጀትና መዳከም ምክንያት ተቀባይነት በማጣታቸው የተፈጠረ የፖለቲካ ቀውስ ነው፡፡ ሕወሃት ደረስኩባቸው የሚላቸው ችግሮችን ብናያቸው ከተፈጥሮ ባህሪው ጋር አብረው የነበሩና እስከ ዕለተ ቀብሩም አብረው የሚኖሩ እንጅ አዲስ ግኝቶች አይደሉም፡፡ በሕወሃት ውስጥ የፀረ ዲሞክራሲ አስተሳሰብ ሰፍኗል ሲል ቀደም ብሎ ዲሞክራት የነበረ ድርጅት ቀስ በቀስ የፀረ ዲሞከክራሲ አስተሳሰብ እያደገ እንደመጣ ለመግለፅ የተነገረ ይመስላል፡፡ በመሰረቱ ሕወሃት በአፈጣጠሩ ፀረ ዲሞክራሲ ዘረኛ ድርጅት ነው፡፡ ዲሞክራሲ ማለት በብዙሃን አመለካከት መገዛትና የአናሳዎችን መብት የማክበር የአስተዳደር መርህ ነው፡፡ ሕወሃት ግን በአናሳ ውክልና ተፈጥሮ ብዙሃንን ረግጦ የሚገዛ የአናሳ አገዛዝ ስርዓት ነው፡፡ ስለሆነም ሕወሃት ሲፈጠርም ከዲሞክራሲያዊ አስተሳሰብ በተቃራኒ የተፈጠረ ነው፤ ወደፊትም ዲሞክራሲያዊ እንዲሆን ባሕሪው አይፈቅድለትም፡፡ በተጨማሪም በጎሳ አስተዳደር ዘዴ ውስጥ አናሳዎች ብዙሃኑን ረግጠው ሲገዙ በሚፈጠረው “የእኛና እነሱ” አመለካከት ጋር ተያይዞ ጠባብነትና ትምክህት መኖር የማይቀር ከጎሳ ድርጅቶች የተፈጥሮ ባህሪይ ጋር ያለና እስከ ዕለተ መቃብራቸው አብሮ የሚኖር ነው፡፡
በአጠቃላይ ሕወሃት በመቀሌው ስብሰባ ችግሩን መገንዘብ አቅቶት በአዙሪት ውስጥ ሲዳክር ተስተውሏል፡፡ የሕወሃት ችግር ሲከተላቸው የነበሩ ከሁለት የአገዛዙ አስተሳሰቦች ማርጀትና ተቀባይነት ማጣት የመነጨ ነው፡፡ እነዚህም፡- 1ኛ ሕወሃት ራሱን ነፃ አውጭ አድርጎ በአሸናፊትና በነፃ አውጭነት አመለካከት የበላይ ሆኖ ሌሎችን ከዚህ አስተሳሰብ ተጠቃሚ አድርጎ በማሳየትና በበታችነት ከስሩ አሰልፎ ሲገዛበት የነበረው ስልት በበታችነት ሲገዙ የነበሩ ካድሬዎችና አስፈፃሚዎች በአጠቃላይ ለሕወሃት ርዕዮት ከመገዛት ይልቅ የየራሳቸውን ጥቅም እያሳደዱና በሙስና እየተዘፈቁ ከመምጣታቸው በተጨማሪ ወትሮም ቢሆን ያለእውቀትና ችሎታ በዘራቸው ወይም በአድርባነታቸው ብቻ በቢሮክራሲው የተሰገሰጉ ካድሬዎች በሕዝብ ስም የተሰጣቸውን ሥራና አደራ የመወጣት አቅም ማጣት ነው፡፡ 2ኛ፡-ሕወሃት የሕዝብን አንድነትና ጠያቂነት ለማዳከም በሕገ መንግስት ስም ኢትዮጵያን በጎሳ አስተዳደር ዘልዝሎና ከፋፍሎ በኃይል ጨፍልቆ የሚገዛበት ስልት በሕገ መንግስቱ የተሰጠን ስልጣን አልተከበረም በማለት ራሳቸውን ለስልጣንና ለአቋራጭ ጥቅም ያዘጋጁ የጎሳ ፖለቲካ ኃይሎች በሚያነሷቸው የተጋፊነት ጥያቄዎች መብዛት ነው፡፡
የሕወሃትን የነፃ አውጭነትና የበላይነት አመለካከት የማይሸከም ትውልድ በመፈጠሩና በሕዌሃት የአናሳ የቁጥጥር አመለካከት ውስጥ በሕገ መንግስቱ የተፈቀደውን የሌሎችን የጎሳ ድርጅቶች መብት ተፈቀዱ የተባሉትን መብቶች ሊያከብር ስለማይችል አሁን ባለንበት ጊዜ የሕወሃት በነፃ አውጭነት የበላይነትና በጎሳ ከፋፍለህ ግዛው ስልት ስልጣንን የማራዘም ዘዴ ጊዜ ያለፈበትና ቀን የጨለመበት በመሆኑ የሕወሃት የተፈጥሮ ሞት አይቀሬ ነው፡፡
ስለሆነም እኛ ኢትዮጵያውያን የሕወሃትን ሞት በማፋጠንና በኢትዮጵያ የሃሳብ ፖለቲካ አብቦ ዜጎች በሰብዓዊና በዲሞክራሲያዊ መብቶቻቸው ላይ ተመስርተው ሕዝባዊ አስተዳደርን ለማስፈን በሚደረገው ትግል የጋራ እርብርብ እንድናደርግ ጥሪያችንን እያቀረብን ሕወሃት ማርጀቱንና መበስበሱን እስከነገረን ድረስ “የሞተ አካል” ሞቱን በራሱ ሊያስረዳ እንደማይችል ተገንዝበን ይህንን የበሰበሰ አገዛዝ ግብዓተ መሬቱ እንዲጠናቀቅና በምትኩ ጊዚያዊ ሁሉን አቀፍ የባለ አደራ አስተዳደር እንዲሰየም ሁሉም ኃላፊነቱን እንዲወጣ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፡፡
ህዳር 10 ቀን 2010 ዓ.ም
አዲስ አበባ