የጭንቅ ቀን ሳይመጣ ኢትዮጵያዊ ፍቅርን መልሱ!!! – ከተማ ዋቅጅራ

 

ኢትዮጵያዊነት መሳጭ ነው። ኢትዮጵያዊነት ተነቦ የማያልቅ ጥልቅ ነው። ኢትዮጵያዊነት እንደ አለት የጸና ነው። ኢትዮጵያዊነት የክርስትና እና የእስልምና የሃይማኖት ጽናት ተምሳሌነት ነው። ኢትዮጵያዊነት የሰው ዘር መገኛ ነው። ኢትዮጵያዊነት ለአለም ውጥረት መተንፈሻ የተስፋ ምድር ነው። ኢትዮጵያዊነት ከደምና ከስጋ ጋር የተዋኅደ ውኁድ አንድነት ነው። ኢትዮጵያዊነት ኩላሊት ከሚያመላልሰው በላይ ረቂቅ ልብ ከሚያስበው በላይ ጥልቅ አእምሮ ከሚገነዘው በላይ ሰፊ ነው። በዚህ 26 አመት ውስጥ እንዲህ ብሎ መግለጽ ግን ወንጀል ነው። እንዲህ ብሎ ማሰብም የድሮ ስርአት ናፋቂም ያስብላል። እንዲህ ብሎ ስለእውነት መመስከርም በ21 ክፍለ ዘመን የማይታሰብ አስተሳሰብ አሳቢ ያሰኛል።

ታድያ እስቲ እናንተን እንስማችሁ የአሁን ስርአት ናፋቂዎች ምን እየሰራችሁ ነው? እውነትስ ካላችሁ ህዝቡ ውስጥ ያለውን ችግር ገልጻችሁ የመንገር አቅሙ ለምን አጠራችሁ? የ21 ክፍለ ዘመን የሚፈልገው አስተሳሰብ ምን ምን ናቸው? የሚሉትን በግልጽ ብታሳውቁን የሚሉ ጥያቄዎች ወደ ተናጋሪዋቹ ዘንድ ይመጣል ። መናገር ብቻ ሳይሆን ለምትሉት ነገር በቂ ማብራሪያ ከነሙሉ መረጃው ያስፈልጋል። ካለበለዛ የጭንቅ ቀን ስትመጣ ብቻ ኢትዮጵያዊ ነኝ በማለት ከችግር መውጣት አልያም ከተጠያቂነትም ማምለጥ አይቻልም።
ኢትዮጵያዊነት ከሰሜን እስከ ደቡብ ከምስራቅ እስከ ምዕራብ አንድ ነው የምንለው ለዚህ ነው ። ኢትዮጵያውያን እህቶቻችን በኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ አሸብርቀው ።

የሰሞኑ በወያኔ መንደር የሚደረገው ጫጫታ ይቺ ናት። ዶ/ር ቴዎድሮስ አድኀኖም ለምን ትቃወማላችሁ እያሉን ነው። ይህንን የማለት መብት አላቸው ነገር ግን የሚያቀርበት ክርክር 100% ተሸናፊ ያደርጋቸዋል። ምክንያቱም የጭንቅ ቀን ሲመጣ ብቻ ኢትዮጵያዊ ነኝ ማለት ዋጋ የለውምና ነው።
ያለጥፋታቸው እስር ቤት የሚማቅቁ የፖለቲካ እስረኞች ኢትዮጵያዊ ነን ብለው ጸንተው በመቆማቸው አይደለ እንዴ እናንተ የአጼ ስርአት ናፋቂዎች እየተባሉ መከራ የሚደርስባቸው። አንተ ሽንታም አማራ አንተ ሽንታም ጋላ አንተ ሽንታም ጉራጌ እያሉ አይደለ ህዝባችን የሚያሰቃዮአቸው።

ታድያ ዛሬ የምጥ ቀን ሲመጣ ኢትዮጵያዊ ነኝ ማለት እንዴት ልታስኬዱት አልያም በምን ልታስታርቁት ትችላላችሁ? በየ እስር ቤቱ ህክምና ተከልክለው የሚሞቱት የኢትዮጵያኖች ነብስ የማትጮህ ለጩኽቷም መልስ የማታገኝ ይመስላችኋልን? አብሮ ለመጮህ የፍቅር መሰረት ያስፈልጋል። አብሮ ለመኖርም መሰረቱ በኢትዮጵያ አንድነት ላይ መታነጽ አለበት።

ታድያ 26 አመት ሙሉ ፍቅርን ስታጠፉ ኢትዮጵያዊነትን ስታፈርሱ ከርማችሁ ዛሬ ከየት መጥቶ ነው ቴዎድሮስ አድኅኖም ኢትዮጵያ ስለሆነ መቃወም የለባችሁም የምትሉን ? ስለኢትዮጵያዊነት የሚነግረንን የዶ/ር ፍቅሬ ቶሎሳን መጽሐፍ እንዳይሸጥ አግዳችሁ በጭንቅ ሰአት ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ ማለት ምንም የሚመጣ ለውጥ የለም። ኢትዮጵያ ብሎ ስለዘፈነ በኢትዮጵያ ቴሌቭዥን መቅረብ የለበትም በማለ ጭራሹንም ያለምንም እፍረት እና በማን አለብኝነት መንፈስ የኢቲቪ ስራ አስክያጁ ይነሳ ህንጻውም ፈርሶ እንደ አዲስ ይሰራ ብላችሁ ስትጮሁ የነበራችሁት በጭንቅ ሰአት ቴዎድሮስ ኢትዮጵያዊ ነው ማለት ምን ማለት ይሆን? በደና ግዜ ያላከበራችሁትን እና የማትውቋትን ኢትዮጵያን በችግር ግዜ ከየት ልታመጡት ነው? እናም ይሄ የጭንቋ ቀን ጣር መጀመሪያ ነው እውነተኛዋ እና የቁርጧ ቀን ስትመጣ ዛሬ እዩኝ እዩኝ ነገ ደብቁኝ ያመጣልና የማታውቋትን እና በውስጣችሁ የሌለችውን ኢትዮጵያ በጭንቀት ሰአት አውጥታችሁ የምርጫ መመረጫ ለማድረግ መሞከር ሞኝነት ነው። ይህ ምሳሌነቱ በአሸዋ እንደተለሰነ መቃብር ነው። ፍሬ ከርስኪ!!!

ከተማ ዋቅጅራ
22.05.2017
waqjirak@yahoo.com

የዶ/ር ቴዎድሮስ ለዓለም ጤና ድርጅት ዳይሬክተር ሆነው ከተመረጡም ለሕወሓት የባሰ አደጋ ይዞበት ይመጣል

የጉዳያችን ማስታወሻ
ዶ/ር ማርጋሬት ቻን ተሰናባቹ የዓለም ጤና ድርጅት ዳይሬክተር

ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም ለዓለም ጤና ድርጅት ከፍተኛ የስራ ኃላፊነት ከቀሩት ሶስት ግለሰቦች ውስጥ አንዱ እጩ መሆናቸው እና የመጨረሻ ድምፅ የመስጠቱ ስነ-ስርዓት ማክሰኞ ግንቦት 15፣2009 ዓም ድምፅ እንደሚሰጥ ለማወቅ ተችሏል። ዛሬ ሰኞ ማለዳ በስዊዘርላንድ ዋና ከተማ ጄኔቭ በተሰናባቿ የድርጅቱ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ማርጋሬት ቻን (Dr Margaret Chan) ለቀጣይ ሰባት ቀናት በሚቆየው የድርጅቱ 70ኛ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ እንደተናገሩት ተሰብሳቢዎቹ ኢ-ፍትሃዊ እኩልነት በተቻለ መጠን እንዲቀንስ አበክረው እንዲሰሩ አሳስበዋል። “ፍትሃዊ እኩልነት ላይ ትኩረት መደረግ አለበት ስል ደግሞ” አሉ ወይዘሮዋ ዶክተር ቀጠሉና ” የዓለም ጤና ድርጅት የስነ ምግባር መመርያ መርህ ´የዓለም ጤና ድርጅት ለፍትሃዊ ተጠቃሚነት ፀንቶ ይቆማል´ የሚለውን አንቀፅ በማስታወስ ነው ” አሉ። ከእዚህ ጋርም አያይዘው ድርጅቱ ለምርምር ትኩረት እይዲያደርግ እና ከመንግስታዊ ካልሆኑ አካላት ጋር የሚደረገው ግንኙነት መጠናከር እንዳለበት ይህም የሲቪሉን ማኅበረሰብ ለማዳመጥ እንደሚረዳ እና የሲቪሉ ማኅበረሰብ መንግስትን እና እንደ ሲጋራ፣የምግብ እና አልኮል ፋብሪካዎች ሕብረተሰቡን የሚጎዳ ተግባራት ሲሰሩ አደብ የሚያስይዛቸው መሆኑን ጠቁመዋል።ከእዚሁ ጋር ተያይዞም የድርጅቱ ተሰናባች ዳይሬክተር ንግግር እንደጀመሩ ከአዳራሹ የጋዜጠኞች መቀመጫ ሰገነት ላይ ዶ/ር ቴዎድሮስን የሚቃወም ድምፅ ከአክቲቪስት ዘላለም ተሰማ ተሰምቷል።ዘላለም ከ190 በላይ የሀገር ተወካዮች ፊት ባሰማው ድምፅ ” ቴዎድሮስ ለፕሬዝዳንትነት አይሆንም! አፍሪካ ደግማ ታስብበት!” የሚል ድምፅ በእንግሊዝኛ አሰምቷል።የአክትቪስቱ ተቃውሞ በደቂቃዎች ውስጥ በዓለም ዙርያ በማኅበራዊ ሚድያ ተሰራጭቷል።

በድርጅቱ የዛሬ ውሎ ማብቂያ ላይ ማክሰኞ እለት የድርጅቱ ፕሬዝዳንትን ለመወሰን ምርጫ እንደሚደረግ እና ምርጫው ላይ አንድ ሀገር አንድ ሰው ብቻ እንዲወክል በድርጅቱ ህንፃ ሌላኛው ክፍል ላይ ነገ እንዲገናኙ ማሳሰቢያ ተሰጥቷል።

በሰሞኑ የዶ/ር ቴዎድሮስ ለዓለም ጤና ድርጅት ዳይሬክተርነት መወዳደር በሀገር ውስጥ እና በውጭ ሀገር በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ዘንድ ዓቢይ የፖለቲካ መከራከሪያ ሆኖ ቀርቧል።መመረጥ አለባቸው ብለው የሚከራከሩት መሰረት የሚያደርጉት የሕወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል ስለነበሩ በድርጅት ፍቅር የተጠመዱ፣ ሁለተኛዎቹ ከድርጅት ፍቅር በላይ የትግራይ ብሄርተኝነት አይሎባቸው ” የእኛ አካባቢ ነው” ከሚል ብቻ የሚደግፉ እና ሶስተኛዎቹ ሌላ ቦታውን ከሚይዘው ኢትዮጵያዊ ሰው ቢሆንበት ይሻላል የሚሉ ናቸው።

በተቃዋሚዎች በኩል ደግሞ ደጋግሞ የሚነገረው ዶ/ር ቴዎድሮስን የምንቃወመው ትግራይ ስለሆነ እና ስላልሆነ አይደለም የምትለው አረፍተ ነገር ቀዳሚ ስትሆን፣ ከእዚህ በተለየ ግን ዶ/ር ቴዎድሮስ የአንድ አካባቢ ፍላጎት እና ነፃነት አስከብራለሁ የሚለው ሕወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል ሆነው አብረው በወሰኗቸው ውሳኔዎች የበርካታ ግድያዎች፣እስሮች እና ሰቆቃዎች ተባባሪ ናቸው።በሌላ በኩል በዐማራ ክልል በተሰጠ የወሊድ መቆጣጠርያ እንክብል እና ክትባት ሳቢያ ከሁለት ሚልዮን በላይ ዜጎች እንዳይወለዱ አስደርገዋል።በሌላ በኩል በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ውስጥም ሆነ በዓለም አቀፉ ግሎባል ፈንድ ውስጥ የገንዘብ ቅሌት ውስጥ እጃቸው አለበት የሚሉ እና በኢትዮጵያ ተከስቶ የነበረው የኮሌራ በሽታ እንዲደበቅ አድርገዋል የሚሉ ይገኙባቸዋል።በተለይ የኮሌራ በሽታ መደበቅ ጉዳይ ላይ የኒው ዮርክ ታይምስ እና ዋሽንግተን ፖስት ጋዜጦችም ባለፈው ሳምንት በሰፊው የፃፉበት ጉዳይ ነው።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ግን ሌላው ሊተኮርበት የሚገባው ጉዳይ ዶ/ር ቴዎድሮስ ዓለም ዓቀፋዊ አስተሳሰብ የሚያላብሳቸው ምን ጉዳይ አለ? ብለን ብንጠይቅ ያለፈ ታሪካቸው በአንድ ክልል ነፃነት ቆምያለሁ የሚለው ስሙንም እስካሁኗ ሰዓት ድረስ የትግራይ ነፃ አውጪ ብሎ የሚጠራው ድርጅት ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል እንደነበሩ እና በእዚሁ መስመር ብቻ የውጭ ጉዳይነቱንም ሆነ የጤና ሚኒስትርነቱን ቦታ ይዘው እንደነበር የሚታወቅ ነው።ስለሆነም አንድ ሰው ብሔራዊ ሳይሆን በአንድ ክልል ነፃነት በቆመ ድርጅት አስተሳሰብ ታንፆ እንዴት ዓለም ዓቀፋዊ አስተሳሰብ ሊዳብር ይችላል? ዓለም አቀፋዊ አስተሳሰብ ሁሉን እኩል አድርጎ የማየት ክህሎት እንጂ የትግራይ ነፃ አውጪ ነኝ በሚል ድርጅት ግንብ ውስጥ መታጠር አይረዳም።ስለሆነም ዶ/ር ቴዎድሮስ ዓለም አቀፋዊ አስተሳሰብ ለማዳበር ከአንድ በዘር ላይ ከተመሰረተ ድርጅት አስተሳሰብ እራሳቸውን ማላቀቅ አስፈላጊ ነው።

በመጨረሻም ዶ/ር ቴዎድሮስ ለዓለም ጤና ድርጅት ዳይሬክተርነት ቢመረጡ ለሕወሐት ይዞ የሚመጣው እራሱን የቻለ አደጋ አለው።ብዙዎች የስርዓቱ ደጋፊዎች ሕወሓት አንዱ ባለሥልጣኑ ለከፍተኛ የዓለም ድርጅት መሪነት መመረጣቸው የስነ – ልቦና እርካታ እንደሚያገኙ የሚያስቡ አሉ።ሆኖም ግን ውጤቱ የተቃራኒው ነው የሚሆነው።የዶ/ር ቴዎድሮስ መመረጥ ሕወሓት ማን ነው? ምን ያህል ሕዝብ በድርጅቱ ውሳኔ ተገድሏል? ድርጅቱ ለአንድ ጎሳ የቆመ መሆኑን እራሱ ከስሙ ጀምሮ እንደሚተርክ፣ እና የመሳሰሉት ሁሉ ለዓለም የበለጠ ግልጥ ይሆናል። ይሄውም ዶር ቴዎድሮስ ከተመረጡም በኃላ የኢትዮጵያውያን ተቃውሞ እንደማይቆም ግልጥ ነው።

አንድ የዓለም አቀፍ ድርጅት ፕሬዝዳንት በተንቀሳቀሰ ቁጥር ተቃውሞ የሚገጥመው ከሆነ ዓለም አቀፍ ሚድያዎችን ትኩረት በእጅጉ ይስባል።ተቃውሞ ማድረግ ደግሞ አንድ ግለሰም ምንም ያህል ዲፕሎማሲያዊ ከለላ ቢኖረውም የማንም ሰው መብት ነው። ይህ ማለት ኮንጎ ውስጥ ያለ ገጠር መንደር ውስጥ ያለች እናት ሕወሓት ማን ነው ? ትላለች ማለት ነው።ብራዚል ውስጥ ያሉ ወጣቶች ተቃውሞው እና ዶ/ር ቴዎድሮስ የመጡበትን ድርጅት ሕወሓት በአፍሪካ አደገኛ የሰብዓዊ መብት የጣሰ ድርጅት መሆኑ የበለጠ የታወቀ ይሆናል።የዓለም ጤና ድርጅት ዳይሬክተር በእየሄዱበት ተቃውሞ የሚገጥማቸው ብቸኛ ሰው ይሆናሉ ማለት ነው።በመሆኑም ሕወሓት በዶ/ር ቴዎድሮስ መመረጥ የበለጠ ለዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ የተጋለጠ ይሆናል።ይህ ሁኔታም ዶ/ር ቴዎድሮስ ከተመረጡ የስራ ጊዜያቸውን ሳይጨርሱ ስራቸውን ለመልቀቅ ሊያስገድዳቸው ይችላል።አንዳንድ ጊዜ እግዚአብሔር ያሰበው እና ሰው ያሰበው መለያየቱ እና እግዚአብሔር የበለጠ ሊሰራ ሲፈልግ እንዴት እንደሚሄድ የሚታይበት አንዱ አጋጣሚ ነው። ሕወሓት በዓለም ዙርያ የሰራቸው እኩይ ተግባራት ሁሉ እንዲጋለጥ የእግዚአብሔር መንገድ ይህ ሊሆን ይችላል።ለእዚህ አንድ አባባል አለ።አንድ ብርጭቆ ከሁለተኛ ፎቅ ላይ ቢወድቅ አይጎዳ ይሆናል ከአስረኛ ፎቅ ላይ ከወደቀ ግን ስብርባሪውም አይገኝም።ሕወሓት በዓለም ላይ የበለጠ እንዲጋለጥ ዶ/ር ቴዎድሮስ አስረኛ ፎቅ ላይ መውጣት አለባቸው ይሆናል።ከአስረኛ ፎቅ ላይ የወጣ የሕወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል የነበረ ሰው የሕወሓትን በዘር ላይ የተመሰረተ አደረጃጀት፣የኢትዮጵያን ምጣኔ ሀብት መቀራመት እና በሺህ የሚቆጠሩ ኢትዮያውያን መገደል እና ሰቆቃ ለዓለም የበለጠ በዶ/ር ቴዎድሮስ ላይ በሚደረጉ ቀጣይ ተቃውሞዎች እንዲጋለጥ የተወሰነው ከላይ እንደሆነ ማን ያውቃል? ” ማን ያውቃል የመስከረም ወር እና የመስቀል ወፍ ቀጠሮ እንዳላቸው” ነው ያሉት ደራሲ እና ገጣሚ መንግስቱ ለማ።
ጉዳያችን GUDAYACHN

ሕወሓትና ኢትዮጵያዊነት – የሕወሓት የክህደት ታሪክ

ሰማሀኝ ጋሹ (ዶ/ር)

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከሕወሃት ሰፈር እየተሰማ ያለዉ ሰለ ኢትዮጵያዊነት የመቆርቆር ስሜት ከማስገረም አልፎ ለሀገር አንድነትና ሉአላዊነት በመታገል የሚታወቀውን የህብረተሰብ ክፍል ‘በባንዳነትና አገር ክህደት’ እየወነጀለ ይገኛል። በተለይ የ ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም ለአለም የጤና ድርጅት ዳይሬከተር ጀነራልነት ዉድድር ጋር በተገናኘ በህወሓት አባላትና ጀሌዎች በማህበራዊ ሚድያ እየተናኘ ያለዉ ግለሰቡን ለእጩነት መቅረብ የሚቃወሙትን የህብረተሰብ ክፍሎች ‘ባንዳዎች’ በሚል ከፈተኛ የስም ማጥፈት ዘመቻ ነዉ። ሁኔታዉን አስገራሚ የሚያደርገዉ ሕወሃትን እቃወማለሁ የሚለዉ የአረና ፓርቲ አመራሮች ሳይቀሩ ቴድሮስ አድሃኖምን የማይደግፍ ባንዳ እንደሆነ የሚገልፅ መግለጫ አዉጥተዋል። ከዚህ ቀደም ሲልም የአባይን ግድብ አስመልክቶ በተነሳዉ ዉዝግብ በተመሳሳይ ከአባይ ግድብ በፊት ሰብአዊ መብት ይከበር የሚሉትን ኢትዮጵያዉያን ‘ከሀዲዎች’ና ‘የሻእብያ ተላላኪዎች’ በሚል ለማሸማቀቅ ከፈተኛ ሙከራ ቢያደርጉም በዉጭ ሃገራት የሞከሩት የቦንድ ሽያጭ  እንደተጨናገፈ ቀርቷል። በኢትዮጵያዊነት ጉዳይ ላይ በታሪክ በሀገር ከሃዲነት የሚታወቀዉ የሕወሃት ቡድን እንዴት ድንገት የኢትዮጵያዊነት ዋስና ጠበቃ ሆኖ ብቅ ሊል በቃ የሚለውን እንቆቅልሽ መመርመር አስፈላጊ ይሆናል።TPLF flag and Ethiopian flag

የሕወሃት የክህደት ታሪክ

ሕወሃት ከተመሰረተበት እለት ጀምሮ ኢትዮጵያና ኢትዮጲያዊነት ለሚባል እሴት ከፈተኛ ጥላቻ እንዳለዉ ታሪክ ከትቦት አልፎአል። ይህንን የክህደት ታሪክ ልዩ የሚያደርገዉ የትግራይ ህዝብና የቀድሞ ነገስታቱ ለኢትዮጵያዊነት ካሳዩት ቀናዊነት በተፃራሪነት የቆመ መሆኑ ነዉ። በ1968 ዓም ሕወሃት ባወጣዉ ማኒፌስቶ ትግራይን የኢትዮጵያ አካል አድርጎም አይመለከታትም።

ትግራይ አክሱም እስከወደቀችበት ጊዜ ድረስ የአክሱም መንግሥት እየተባለች ትጠራ ነበር። ኣክሱም ከወደቀች በኋላም እራሷን በማስተዳደር ለብዙ ጊዜ ብትኖርም ቅሉ ኣልፎ ኣልፎ ባካባቢዋ ለነበሩት ነገሥታት ግብር መክፈሏ አልቀረም።

የሕወሃት ለኢትዮጵያዊነት ያለዉ ጥላቻ የመነጨዉ ኢትዮጵያዊነትን ከአማራ ህዝብ ታሪክና ባህል ጋር የተቆራኘ አድርጎ ስለሚመለከተዉ ነዉ። የትግራይ ችግርና እርዛት ተጠያቂዉ አማራዉ እንደሆነ በማኒፌስቶዉ ያትታል።

በኣፄ ዪሐንስ ዘመነ መንግስት ኃይሏ በርትቶ በአካባቢዋ የነበሩትን ነገሥታት በቁጥጥሯ ሥር አውላ ነበር፤ ይሁን እንጅ አፄ ዩሐንስ ከሞቱ በኋላ በዳግማዊ ምኒልክ ኣማካኝነት ትግራይ በሸዋው ማእከላዊ ግዛት ሥር ወደቀች። ከዚህ ጊዜ ሀኋላ ነው የአማራው የመሳፍንት ቡድንና ተከታዮቹ የትግራይን ነፃነት ገፈው የሕዝቧን አንድነት ያናጉት። ግልጽና ስውር በሆኑ ዘዴዎችም (ሸዋዊ ዘይቤዎች) የትግራይ ሕዝብ በድንቁርና፣ በበሽታ፣ በረሃብ አዘቅት ውስጥ እንዲሰምጥ ያደረጉት። በተለይም ትግሬነቱን በፍጥነት እንዲክድና ያለውድ በግድ “አማራ ለማድረግ” ያልሞከሩት ዘዴ ባይኖርም መሬቱ ተቆራርሶ ስለተወሰደበትና የተደራረበ ጭቆና ስለደረሰበት አገሩን ጥሎ ተሰደደ። ባጠቃላይ ባሁኑ ጊዜ ትግራይ ነፃነቷ የተገፈፈች፣ መሬቷ ተቆራርሶ የተወሰዳባትና የተወሳሰብ ችግር የደቆሰው ሕዝብ የሚኖርባት ጭቁን ብሔር ናት።

በዚህም መሰረት በሕወሃት እምነት የትግራይ ህዝብ ብሔራዊ ትግል ፀረ-የአማራ ብሔራዊ ጭቆናና ከኢምፐርያሊዝም ነፃ የሆነ የትግራይ ዲሞክራሲያዊ ሪፖብሊክ ማቋቋም መሆኑን በወቅቱ ይፋ አደረጓል። አማራዉን ለማጥፋት በዋናነት ኢትዮጵያዊነትን መምታት እንዳለበት በማመን ሕወሃት የሞት ሽረት ትግል ማድረግ ጀመረ። ለዚህ የታሪክ ክህደት ጅማሮ ኢትዮጵያ የሚባለዉ ሃገር በዳግማዊ አፄ ምኒልክ እንደተፈጠረችና የመቶ አመት ታሪክ ብቻ እንዳላት ቢያንስ እስከ 2000 ዓም ድረስ የማያቋርጥ ዘመቻ አካሄደ። በጊዜዉ የነበሩት እነ መኢሶንና ኢሕአፓ የመሳሰሉት ፓርቲዎች ሕወሃት ከሚያራምደዉና በጊዜዉ ፋሽን ከነበረዉ ከማርክሳዊ የመደብ ትግልና የብሄር ብሄረሰቦች የራስን እድል በራስ መወሰን መብት ጋር ተመሳሳይ ቢሆንም እነዚህን ፓርቲዎች ሕወሃት አምርሮ ይጠላቸዉ ነበር። ይህ ጥላቻዉ በፖለቲካ አስተሳሰብ ልዩነት የተፈጠረ እንዳልሆነ ግልፅ ነበር። ነገር ግን እነዚህን ፓርቲዎች ሕወሃት የሚመለከተዉ የአማራ ፓርቲዎችና ኢትዮጲዊነትን ለማስቀጠል የሚሰሩ ፓርቲዎች አድርጎ ነበር። በዝነኛዉ የ 1968 ማኒፌስቶዉ ሕወሃት መኢሶንና ኢሕአፓን  የመሳሰሉትን ድርጅቶችን ‘ ተራማጅ” ነን ባዮች የሸዋ ምሁራን ትምክህተኞችና አድርባዮች ሆነው ስለሚገኙ በአንድ የፖለቲካ ማህበር ሥራ ተራማጅ ዓላማ ይዞ አብዮት ለማካሄድ እንደማይቻል’ ያስረዳል።

ይሄ በህወሃት ቡድን የተጠነሰሰዉ ፀረ ኢትዮጵያ እንቅስቃሴ ከኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ከሚባሉት የጎረቤትና የአረብ ሀገሮች በመታገዝ 17 አመቱ የትጥቅ ትግል ወቅት ቀጠለ። በመጨረሻም መንበረ ስልጣኑን በ1983 ዓም ሲቆጣጠር ኢትዮጵያን የማፈራረሱን ፕሮጀክት አጠናክሮ ቀጠለ። በፕሮግራሙ ጠላት አድርጎ ያስቀመጠዉን የአማራዉን ማህበረሰብ ለመበቀል ወሳኝ ምእራፍ አድርጎ የተመለከተዉን ኢትዮጵያዊ እሴቶችንና ተቋማትን ማፈራረሱን ተያያዘዉ። ለዚህ አላማ የመጀመርያዉ እርምጃ በሰኔ ወር 1983 ዓም በተደረገዉ የሽግግር መንግስት ምስረታ ምንም አይነት ህብረ ብሄራዊ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዳይካፈሉ መከልከል ነበር። በጉባኤው እንዲካፈሉ የተፈቀደላቸዉ የጎሳ ፓርቲዎች ብቻ ነበሩ። ኢትዮጵያዊነትና አማራነት ያንድ ሳንቲም ሁለት ገፅታዎች ናቸዉ ብሎ የሚያምነዉ ሕወሃት በብዙ ሺ የሚቆጠሩ አማራዎችን ከስራ በማባረር አማራዉ በየቦታዉ ሁለተኛ ዜጋ ሆኖ እንዲኖር አደረገ። በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍል የሚኖረዉ አማራም እንዲጨፈጨፍ ሁኔታዉን አመቻቸ።

ሌላዉ ኢትዮጵያዊነትን የማዳከም አጀንዳዉ የጎሳን ፖለቲካ በሀገሪቱ ዉስጥ መዘርጋትና ኤርትራን በማስገንጠል ሀገሪቱን ወደብ አልባ ማድረግ ነበር። አንዳንድ ወገኖች በጎሳ ላይ የተመሰረተዉ የፌዴራል ስርአት መብታችንን ያስከብርልናል ብለዉ ቢያምኑም የፖለቲካ ስርአቱ መዘርጋት ዋና አላማ አማራዉን ለማዳከም ኢትዮጵያን ማዳከም የሚለዉን አላማ ለመፈፀም የታቀደ ነዉ። በተለይ በአማራዉና በኦሮሞው መካከል የማይታረቅ ቅራኔ እንዳለ አስመስሎ በማቅረብ ሁለቱን ማህበረሰቦች በማጋጨት ስልጣኑን ማራዘም ነዉ። የአዲስ አበባ ህዝብ በማያቋርጥ ከበባ (siege) ዉስጥ እንዲኖር የተፈለገዉ ከዚሁ የሕወሃትን መሰሪ አላማ ለማስፈፀም ነዉ። በሽግግሩ ወቅት የነበረዉን የክልል 14 የአዲስ አበባ መስተዳድር አፍርሶ በህገ መንግስቱ የአዲስ አበባ ሁኔታ ግልፅ ባልሆነ መልኩ እንዲቀመጥ ተደርጓል። በአንድ መልኩ የኦሮምያ ክልል የባለቤትነት መብት እንዳለዉ ያልተቀመጠ ሲሆን በሌላ መልኩ ደግሞ አዲስ አበባ ራሱን የማስተዳደር መብት እንደሌሎች ክልሎች እንዳይኖረዉ ተደርጓል። በኢትዮጵያዊነት ላይ ይማያወላዉል አቋም ያለዉ የአዲስ አበባ ህዝብ እኔ ከሌለሁ ኦሮሞ ይዉጥሃል በሚል የሕወሃት ማስፈራርያ በስጋት እንዲኖር ተፈርዶበታል።

በኢትዮጵያ ዘምናዊ ታሪክ ዉስጥ በሃገር ክህደት ስራዉ ተወዳዳሪ ያልነበረዉ መለስ ዜናዊ ለዚህ የፀረ ኢትዮጵያዊነት ራእይ አስፈፃሚነት ሚና ሕወሃት ያዘጋጀዉ ሰዉ ነበር። ኤርትራ ከኢትዮጵያ እንድትገነጠል በፊርማዉ ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት ደብዳቤ የፃፈዉ መለስ ዜናዊ በፀረ ኢትዮጵያዊ ንግግሮቹ ይታወቃል። ‘ባንዲራ ጨርቅ ነዉ፥ የአክሱም ሃዉልት ለወላይታዉ ምኑ ነዉ’ ፤ እንኳን ከናንተ ተፈጠርኩ’ በሚሉት ንግግሮቹ የሚታወሰዉ ዘረኛዉና አምባገነኑ መለስ ዜናዊ ከዩንቨርስቲ ጊዜዉ ጀምሮ በኢትዮያዊነት ላይ ከፈተኛ ጥላቻ እንደነበረዉ በቅርብ የሚያውቁት ምስክርነታቸዉን ሰጥተዋል። በአጠቃላይ ይሄ ሕወሃት ለዘመናት ያራመደዉ ፀረ ኢትዮጵያዊነት በይዘት ያልተቀየረ ቢሆንም በቅርፁ ግን ለዉጥ አሳይቷል። ይህንን ያካሄድ ለዉጥ በሚቀጥለዉ ክፍል እናያለን።

ኢትዮጵያዊነትን እንደ መሳርያ መጠቀም

ጠላቴ ነዉ የሚለዉን የአማራ ማህበረሰብ ኢትዮጵያዊነትን በመምታት ካዳከመዉና አማራዉ ይዞት ነበር የሚለዉን ስልጣን የአንድ አካባቢ ሰዎች  ከተቆጣጠሩት በኋላ የኢትዮጵያ እንደ ሃገር መቀጠል ለሕወሃት ጥሩ አጋጣሚ እንደሆነ ተረዳ። ስለዚህ ኢትዮጵያዊነትን አስፈላጊ ለሆነ የፖለቲካ አላማ ብቻ (instrumental approach) በመጠቀም እንዳይጠፋም እንድያድግም የሚያደርግ ፖሊሲ መከተል ጀመረ። ይህም ማለት አንድ ለሆነ የፖለቲካ ግብ ኢትዮጵያዊነትን ከተጠቀመ በኋላ ኢትዮጵዊነት አንሰራርቶ ስልጣኑን እንዳያሰጋዉ ‘ትምክህተኛና የቀድሞዉ ስርአት ናፋቂዎች’ በሚል እንደገና መድፈቅ ነዉ። የዚህ ፖሊሲ አዋጭነት የተሞከረዉ በኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ወቅት ነበር። በ1991 በተካሄደዉ የድንበር ጦርነት ወቅት የኤርትራን ሃይል መቋቋም ያቃተዉ ሕወሃት የኢትዮጵያን ህዝብ ለጦርነቱ ለማሰለፍ የሚጠላዉን ኢትዮጵያዊነትን እንዲሰብክ ተገደደ። መገናኛ ብዙሃን የተከለከሉትንና የጦርነት ናፋቂዎች ዜማዎች ናቸዉ የተባሉትን ሀገራዊ ዜማዎች በስፋት እንዲያሰሙ የተደረገ ሲሆን ህዝቡም ሃገሩን ለማሰመለስ ተንቀሳቀሰ። ጦርነቱን ኢትዮጵያ በአሸናፊነት ብትወጣም ከኢትዮጵያ ይልቅ ለኤርትራ የሚያደላዉ መለስ ዜናዊ ጦሩ ሙሉ በሙሉ ሻእብያን ሳይመታ እንዲቆም አዘዘ። ጦርነቱን በድል እንድንወጣ ከፈተኛ ሚና የተጫወቱት የቀድሞዉ መንግስት ወታደሮች እንደገና በስፋት ከሰራዊቱ ተቀነሱ። ስለ ኢትዮጵያዊነት በሚድያዉ የሚሰበከዉ ቀስ በቀስ እንዲቀር ተደርጎ እንደ ቀድሞው ‘ነፍጠኞችና ትምክህተኞች’ በሚል ኢትዮጵያውያንን ማሳደድ ተጀመረ።

ሕወሃት እንደገና የ1997ን ምርጫ ተከትሎ የኢትዯጵያዊነትን ካባ መልበስ ጀመረ። በኢትዮጵያዊነት መንፈስ የታጀበዉ የቅንጅት ማእበል የምርጫ ዘመቻ የዘረኞችን አጥር በብርቱ የነቀነቀዉ ሲሆን ኢትዮጲያዊነት ሊያጥፋዉ የማይችል እሳት መሆኑን ሕወሃት ተረዳ። ምርጫዉን በሃይል ከጨፈለቀ በኋላ እንደገና ኢትዮጵያዊነትን እንደ መሳርያ መጠቀም አማራጭ የሌለዉ መሆኑን ተገነዘበ። መለስ ዜናዊ የ2000 ዓም የሚልንየም በአል ሲከበር ባደረገዉ ንግግር የመቶ አመት ነዉ  በማለት ሲያጣጥለዉ የነበረዉን የኢትዮጵያን ታሪክ ምንም ሀፍረት ሳይሰማዉ ሀገሪቱ የብዙ ሺህ አመት ታሪክ እንዳላት መሰከረ። ከዚህ በመቀጠልም ሕወሃት የባንዲራ ቀን ማክበር ፥ ልማታዊ መንግስት በሚል የኢትዮጵያን ትንሳኤ አብሳሪ ሆኖ ብቅ አለ። የአባይ ግድብ ፕሮጀክትም ዋናዉ አላማ ህዝቡን ለማታለልና ኢትዮጵያዊ ለመምሰል የሚያደርገዉ ጥረት አካል ነዉ።

በእዉነት ሕወሃት ስህተቱን አርሞ ኢትዮጵያዊነትን ተቀብሎ ቢቀጥል እሰየዉ የሚያሰኝ ነገር ነው። ነገር ግን አሁንም ኢትዮጵያዊነትን የሚፈልገዉ ስልጣኑን ለማራዘምና ህዝቡን ለማታለል መሆኑ ግልፅ ነዉ። ለዚህም ብዙ አብነቶች ማቅረብ ይቻላል። አሁንም በኢትዮጵያዊነት ካባ ስር የአንድ አካባቢ ሰዎች ኢኮኖሚዉን፥ ፖለቲካዉን፥ ወታደሩንና ደህንነቱን ተቆጣጥረዉ መቀጠላቸዉ ዋናዉ ማስረጃ ነዉ። ሌላዉ ማስረጃ አሁንም እዉነትኛ በኢትዮጵያዊነት ላይ እምነት ያላቸዉን የፖለቲካ ድርጅቶችና መሪዎች ማሰርና መግደልን መቀጠላቸዉ ነዉ። እነ ቴዲ አፍሮ፥ እስክንድር ነጋ፥ ህብታሙ አያሌዉ፥ ተመስጌን ደሳለኝ፥ አንዱአለም አራጌና ሌሎች ታጋዮች በእስር እንዲማቅቁ የሚደረገዉ ብቸኛዉ ወንጀላቸዉ ኢትዮጵያን መዉደድ ሆኖ በመገኘቱ ነዉ። አሁንም ማንኛዉንም ለስልጣናቸዉ የሚሰጋቸዉን የኢትዮጵያዊነት እንቅስቃሴ በ‘ ትምክህተኝነት’ በማሳበብ መምታቱን ቀጥለዉበታል። ኢትዮጵያውያን በሊቢያ በታረዱ ጊዜ ድርጊቱን አዉግዞ የወጣዉን ህዝብ የቀጠቀጡትና በቅርቡ በአማራ ክልል የተነሳዉን አመፅ ለመጨፍለቅ ያደረጉት ጭፍጨፋ እዉነተኛ የኢትዮጵያዊነት ስሜት እንይነሳሳ ስለሚፈልጉ ብቻ ነዉ።

ትዉልዱ የህገሩን ታሪክና ባህል እንዳያዉቅ በማድረግ በቁስና በሱስ ሰቀቀን ብቻ እንዲሞላ ያደረጉት ለኢትዮጵያዊነት ካላቸዉ ጥላቻ የመነጨ ነዉ። ህገሪቱ በጎሳ ተከፋፍላ ከነገ ዛሬ ተበተነች እያልን እንድንሰጋ የተደረገዉ ኢትዮጵያን ለማጥፋት የተደረገዉ የረጅም ጊዜ ስራ ዉጤት ነዉ። እንዲህ ኢትዮጵያዊነትን ታጥቀዉ ለማጥፋት ላለፉት 40 አመታት የተሰማሩት የሕወሃት ጀሌዎች ናቸዉ ለኢትዮጲዊነቱ በህይወቱ የሚወራረደዉን ህዝብ ‘ከሃዲና ባንዳ’ እያሉ የሚሰድቡት። የቱንም ያህል እንደ እስስት ቢቀያየሩ የሕወሃት መሪዎችና አባለት ታሪክ በሃገር ክህደትና ማፈራረስ  የሚስታዉሳቸዉ ናቸዉ። ስለዚህም የምንወዳትን ሀገራችንን ከሕወሃት መንጋጋ አላቅቆ ከተደቀነባት ጥፋት በማትረፍ ወደ ሙሉ ክብሯ መመለስ የትዉልዱ ሃላፊነት ነዉ።

ዳኛ የለም እንጂ ዳኛማ ቢኖር …. | በያሬድ ኃይለማርያም

 

ዶ/ር ቴውድሮስ የወያኔ የአገዛዝ ስርዓት በኢትዮጵያ ውስጥ ላለቱት አሥርት አመታት ለፈጸማቸው የሰብአዊ መብት ጥሰቶችና የግፍ ተግባራት ቀጥተኛ ተጠያቂ ከሆኑት የስርዓቱ ቁንጮዎች መካከል አንዱ ነው፡፡ ዳኛ የለም እንጂ ዳኛማ ቢኖር … ይህ ሰው ሕግ ፊት ቀርቦ በአገሪቱ ማጎሪያ ቤቶች ሕክምና እየተነፈጉ ላለቁትና ዛሬም እየማቀቁ ላሉት ሰዎች፤ እንዲሁም ኦጋዴንን ጨምሮ በበርካታ የአገሪቱ ክፍሎች በሕክምና እጦት ለሚሰቃዩት ሰዎች ሁሉ ተጠያቂ በተደረገ ነበር፡፡

ቴውድሮስና ግብራበሮቹ የወያኔ ባለስልጣናት በቪላ ቤቶች፣ በሚሊዮኖች በተገዙ ውድ መኪኖች ሲንደላቀቁ እና ጥቂቶች የአገሪቱን ሃብት ተቀራምተው በሙስና ሲጨማለቁ የአገሬ ደሃ ሕዝብ አንዲት መርፌና እፍኝ ኪኒን መግዣ ጠሮበት፣ የወባ አጎበር መግዛት አቅቶት፣ ለልጆቹ የሚላስ የሚቀመስ ማቅረብ አቅቶት ከፊቱ በጠኔ ሲደፉ ማየት ያሳዝናል፡፡

የፌደራል መንግስቱ መቀመጫና የዶ/ር ቴውድሮስ መዋያና ማደሪያ በሆነችው አዲስ አበባ በቅርቡ የቆሻሻ ክምር ተንዶ በመቶዎች የሚቆጠሩ ወንድም እህቶቻችንን ያጣንበት አሳዛኝ ክስተት የቅርብ ጊዜ ሃዘናችን ነው፡፡ እነ ቴውድሮስ አደሃኖም በአስርት አመታት ጉዞዋቸው ያቆዩልን ኢትዮጵያ ምን እንደምትመስል በትንሹ ለማየት ይቺን የጺዮን ግርማን (Tsion Girma Tadesse) ሪፖርት አድምጧት፡፡

በየመንደሩ ከሄድን ደሞ ከዚህ በብዙ እጥፍ የሚዘገንኑና እንደ ሃገር የሁላችንንም አንገት የሚያስደፉ በርካታ ነገሮችን መታዘን እንችላለን፡፡ እንዲህ አይነቱ አገርንና ሕዝብን አዋራጅ የሆነ ተግባር ሊፈጸም የሚችለው እንደነ ቴውድሮስ አድሃኖም ያሉ ዳተኛና ለሰውልጅ ክብር ግድ የማይሰጣቸው እኩይ ፖለቲከኞች የሥልጣኑን መዘውር ሙሉ በሙሉ በተቆጣጠሩበት ሃገር ብቻ ነው፡፡ እንደ ቴውድሮስ ያለ ሰው ለፍርድ እንጂ ለአለም አቀፍ የጤና ተቋም መሪነት መመረጥ ቀርቶ የሚታጭ ሰው አይደለም፡

ቴዲ አፍሮ በኢህአዴግ ለምን ይጠላል? ወይም እንደ ትልቅ አደጋ ይታያል?

 

ከጌታቸው ስሜ

ቴዲ አፍሮ የሚነያሳቸው የኢትዮጵያዊነት ወይም የተለያየ ማህበረሰብ በፍቅር እንዲተሳሰር የሚያነሳሱ መልዕክቶች፤ የኢህአዴግ ባለስልጣናትን ለምን ያስደነግጣቸዋል? ለምን እንዲጠሉት ያደርጋቸዋል? የሚለው መሰረታዊ ጥያቄ ነው፡፡

ቴዲ አፍሮ አልበም ባወጣ ቁጥር የገዢው ፓርቲ መሪዎች፤ ተከታዮችና ደጋፊዎች ለምን ይንጨረጨራሉ? ጥላቻቻውን ለከት በለቀቀ ወይ ስነ ምግባር በጎደለው መንገድ ያንፀባርቃሉ፡፡ ግለሰብ የፓርቲው ደጋፎዎችና አባላት ስሜት በፓርቲው ቱባ መሪዎች በተለይ በህወሃት ደጋፊዎች ዘንድ ሲንፀባረቅ ይታያል፡፡

ይህንን ጥያቄ ሚዛናዊ ሆኜ ለማየት ሞክሬያለሁ፡፡ ነገር ግን የቴዲ አፍሮ በኢህአዴግ እይታ እንደ አንድ ስርዓቱን እንደሚገዳደር ተደርጎ መታየቱ፤ የስርዓቱን በመንግስት ቁመና ያለማሰቡን ያሳየናል፡፡ ከአንድ ለአገር የሚቆረቆር ድምፃዊ ጋር እንደ አንድ ጠላት (potential threat) ፍትጊያ ውስጥ መገባቱ፤ ገዥው ፓርቲ ድምፃዊው ለሚያነሳቸው መሰረታዊ የማህበራዊ ፍትህ ጥያቄዎች መልስ ለመስጠት አቅም እንደሌለው ያሳያል፡፡

የራሴን እይታ ልስጥ፡፡ ኢህአዴግ ኢትዮጵያዊነት የሚያስበረግገው ከሆነ በራሱ ድርጊት ኢትዮጵያን እንደማይፈልጋት ማሳያ ነው፡፡ አንድነትና ፍቅር ወይም ተከባብሮ መኖር የሚያስበረግገው ከሆነ፤ ማህበረሰቦች ወይም የተለያየ ባህልና እምነት ያላቸው በፍቅር እንዲኖሩ አይፈልግም፡፡ ምክንያቱም ይህንን የሚሻ ፓርቲ ይህንን ልዕልና የሚሰብክ ድምፃዊ ካለጠፋሁ ብሎ ሌት ተቀን አይብሰከሰክም፡፡

ደጋፊዎቹ አንደ ግለሰብ የሚያንፀባርቁት ጥላቻ አደገኛ ቢሆንም፤ እንተወው ቢባል አንኳ፤ የፓርቲው አባላት ግን የሚያሳዩት ጥላቻ እንደ መንግስት አያስቡም የሚለውን ማረጋገጫ ይሰጣል፡፡ እንደ መንግስት ቢያስቡ፤ በኢቲቪ የተቀረፀ የቴዲ አፍሮ ቃለ – መጠይቅ እንደ አንድ ፓርቲውን ለአደጋ የሚዳርግ ተደርጎ አንዳይሰራጭ እገዳ ባልተደረገ ነበር፡፡ በኢህአዴግ አሰራር ደግሞ አንዳችም ነገር የፓርቲው ቁንጮ መሪዎች ሳያቁት የሚከናወን ነገር የለም፡፡ ስለዚህ እገዳው የአንድ የቴሌቪዥን ጣቢያ ስራ አስኪያጅ ውሳኔ ብቻ ተደርጎ መወሰድ የለበትም፡፡ የፓርቲው መሪዎች ውሳኔ በቀጥታ አለበት፡፡

ለዚህም ነው፤ ፓርቲው ቴዲ አፍሮን ልክ እንደ አንድ ስርዓቱን የሚያፈርስ ግዙፍ አደጋ አድርጎ የሚያየው፡፡ ድምፃዊው የሚያስተላልፋቸው መልዕክቶች በስርዓቱ አራማጆች ዘንድ ‹‹ለስልጣናችን አደጋ ናው›› ብለው ከማሰብ የመነጨ ነው፡፡

እስቲ አንድ ቅን አእምሮ ያለው ዜጋ ኢትዮጵያ ሁሉም ማህበረሰቦች ተከባብረው በእኩልነትና በልዮነት አንድነት እንዲኖሩ የሚሰብክን ድምፃዊ በጥላቻና የስርዓቱ አደጋ አድርጎ ማየት፤ ግፋ ሲልም አንዲሰናከልና እንዲሸማቀቅ መተብተብ ምን ይባላል፡

ሼህ መንደፈር፤ ጃህ ያስተሰርያል፤ ሃብ ዳህላክ፤ ኢትዮጵያ …. ሌሎችም የቴዲ አፍሮ ዘፈኖች የስርዓቱ መሪዎችና ደጋፊዎች ቢቻል የህዝብ ድምፅና እንጉርጎሮዎች መሆናቸውን አውቀው ልብ ሊገዙባቸው እንዲችሉ የማድረግ ሃይል ነበራቸው፡፡ አልተጠቀሙበትም፡፡

ድምፅዊው የማህበረሰቡን የኃላ፣ አሁንና የወደፊት ቀለም የማየት ሃይል አለው፡፡ የተሰራንበትን ማህበረሰባዊ ፈትል (social engineering) ልቅም አድርጎ አውቆታል፡፡

ድምፃዊው በዘፈኑ የሚያንፀባረቃቸው አርቆ ላስተዋለም ህገ መንግስቱ መግቢያ ላይ አንድ የኢኮኖሚና የፓለቲካ ማህበረሰብ ለመፍጠር… የሚለውን በጥልቀት የሚገልፅ ነው፡፡ አንድ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማህበረሰብ የሚኖረው ወደ አንድ ማህበረሰባዊና ኢኮኖሚያዊ የጋራ ተጠቃሚነትና አንድ የጋራ ማዕከላዊ አስተሳሰብ ሲኖር ነው፡፡ አሁን የሚሰራው ከዚህ ተቃራኒ ነው፡፡

የኢትዮ ሰማዩን ጌታቸው ረዳ በጨረፍታ

ዳግማዊ ጉዱ ካሣ

ግለሰብን ማዕከል ያደረገ በተለይ ሙገሣን ያዘለ መጣጥፍ ጽፌ ስለማወቄ አሁን ትዝ አይለኝም – በለመደብን የዘመን ወረርሽኝ ምክንያት ግለሰቡ ላይ ያለኝን ፖለቲካዊ ተቃውሞ ለማቅረብ ካልሆነ በስተቀር፡፡ አሁን ግን ባልተለመደ ሁኔታ በዚህ ብርቅና ድንቅ ዜጋ ላይ የተሰማኝን በድርበቡ ልናገር ይሄውና ጀመርኩ፡፡ በርሱ ውስጥም እርሱን መሰሎችን ሁሉ እንደማነሳ ይታወቅልኝ፡፡

ሰውን ለመወረፍ የሚተጋ ብዕርና አንደበት መመስገን የሚገባውን ግሩም ዜጋ ለማወደስ ቢሰንፍ አጉል ይሉኝታ ነው፡፡ በሀገሬ ኢትዮጵያ ወቅታዊና ዘመነኛ ሁኔታ ምክንያት እንቅልፍ አጥተው ከሚያ(ድ)ሩ ወገኖች አንዱ መሆኔን ላስታውስ ብደፍር ቅር የሚሰኝ አይኖርም ብዬ እገምታለሁ፡፡ ይህን መናገር ደግሞ አግባብ እንጂ ለራስ ሲቆርሱ ዓይነት ሊሆን አይገባም – የፈራሁ አስመሰለብኝ ልበል? ብዙ መሆን፣ ብዙ ማድረግ፣ ብዙ መሥራት እየቻሉ በሀገራቸው ጉዳይ ሌት ከቀን እየተጨነቁ አብዛኛውን ጊዜያቸውን የሚያባክኑና በዚያውም ይህችን አጭር ምድራዊ ዕድሜ በከንቱ የሚጨርሱ አሉ – ከነሱ ውስጥ አንዱ ነኝ፡፡ በግርድፍ ግምት በ30 ዓመታት ውስጥ …. ኢትዮጵያ ነፃ እስክተወጣ ከቆየሁ … ወይም ምናልባት ወያኔን ምሥጋን ይንሳውና ልጅ የሚወጣልኝ አይመስለኝም እንጂ የሚወጣልኝ ከሆነ …. ያኔ … እነዚህ ጅምር ዐረፍተ ነገሮች (ያልቃሉ)፡፡ የማይገባ ነገር ሲያጋጥም ትቶ ማለፍ ነው፡፡(የዛሬ ልጅ እንደዱሮው ዘመን ያባትን እግር ማጠብ ይቅርና ነጠላ ጫማ እንዲያመጣልኝ ባዘው በቃና ቲቪና በሞባይል ጌም ምክንያት ልቡ ጠፍቶ ትዛዜን የሚሰማኝ ተኝቼ ሁለትና ሦስት እመም እንቅልፌን ከደቃሁ በኋ ነው – ሊያውስ ወያኔ ሲያስተኛኝ አይደል! ልጅ ዱሮ ቀረ! በዋል ፈሰስ ልጆችን በመቀፍቀፍ የተለበለበ ግንድ እያሳደግን ነው – አእምሮው የኮሰመነ አካላዊ ዕድገት ብቻ!፡፡)

ወደጀመርኩት – ወደገደለው ላዝግም፡፡  ብዙ ጌታቸው ረዳዎች እንደሚኖሩ እገምታለሁ፡፡ እኔ ቢያንስ ሁለቱን አውቃለሁ፡፡ አንደኛው የወያኔ አፋዳሽ የሆነው የራያው ጌታቸው ረዳ ነው – የወያኔው ባለሥልጣን፡፡ የዩንቨርስቲ መምህር እንደነበርና ብዙ ችግር ያለበት ወፍ ዘራሽ ዜጋ መሆኑን ሰምቻለሁ፡፡ ሕወሓት ሁለት ታላላቅ ሞኛሞኝ ብሔሮችን የታቀደውን ያህል ባለማጋጨቱ ይህ ጅል ወያኔ በጸጸት መልክ ሲናገር በጀሮየ ሰምቼዋለሁ፡፡ መቀሌ ዩኒቨርስቲ ሲያሰተምር ከንዝህላልነቱ ብዛት የተነሣ ተማሪዎች ለፈተና ተቀምጠው ሳለ የማጠቃለያ ፈተና  ማውጣቱንና ማባዛቱን ረስቶት  ተማሪዎቹ በፈተና አዳራሽ ተቀምጠው እየጠበቁ ፈተናው ተባዝቶ መፈተናቸውን ሁሉ ከውስጥ አዋቂ ሰምቻለሁ፡፡ ሌላም ሌላም ሰምቻለሁ፡፡ ወያኔዎች የሚፈልጉትን ቆሻሻ ስብዕና አንድም ሳያዛንፍ መቶ በመቶ በማሟላቱ ምክንያት ለሥልጣን እንደታጨና እንደተሾመም ሰምቻለሁ፡፡ ለማንኛውም ስለዚህ ሰውዬ አሁን አያገባኝምና ምንም ባልናገር ምርጫየ ነው፡፡

የኢትዮሰማዩ ጌታቸው ረዳ፡፡ ይህ ምርጥ ዜጋ አሁን የሚሠራውን እንጂ የዱሮ ታሪኩን አላውቅም፡፡ ከፎቶው ውጭ በአካልም ሆነ በስልክ አንተዋወቅም፡፡ በሚዲያ ግን በሚገባ አውቀዋለሁ፡፡ የዚህን ሰው ድካምና ልፋት ኢትዮጵያ እናታችን እየመዘገበችለት ቢሆንም የበኩሌን ጥቂት ማለት እፈልጋለሁ – መብቴም ነው፡፡ ጥፋት ቢኖርበት እንደማንባርቅበት ሁሉ በአልሚነቱ አወድሰዋለሁ፡፡

ሰሞኑን አንድ መጣጥፍ ለተቃውሞው ጎራ ልኬ ነበር፡፡ እንደልማድ ሆኖብኝ ከላክሁ በኋላ የመጣጥፉን ርዕስ በኮፒፔስት እቀዳና ጉግል መፈለጊያ ላይ ደፍቼ ፈልግ እላለሁ፡፡ ያኔ በየትኛዎቹ ድረ ገፆች እንደወጣ አውቃለሁ፡፡ በየትኞቹ ደግሞ የቅርጫት ራት እንደሆነ ጊዜ እየሰጠሁ ቀስ በቀስ እረዳለሁ – የምዘናባቸውን ደግሜ በመላክ አስታውሳለሁ፡፡ በየትም ይውጣ በየትም አይውጣ ለኔ ዋናው ቁም ነገር አእምሮየን ሰቅዞ የሚያሰቃየኝ የእምዬ ኢትዮጵያ ጉዳይ ከኔ ወጥቶ ቢያንስ ለአንድ ሰው መድረሱ ነው፡፡ ዕድሌ ከሰመረ በዛ ባሉ ድረገፆች ይለጠፋል፡፡ ነገሬ አልጥም ካለና ከስኳሩ እሬቱ ከበዛ በጥቂቶች ወጥቶ በሌሎቹ ይቀራል፡፡ በውነቱ ምንም አይመስለኝም፡፡ ለምን ድርሻየን ተወጥቻለሁና፡፡ ሁሉንም ማስደሰት እንኳንስ እኔ ፍጡሩ ፈጣሪ ራሱም የሚችል አይመስለኝም፡፡ እናም ቢለጠፍ ባይለጠፍ በተለይ አሁን አሁን ምንም አልልም  – ማለቴ እንደዱሮው አይከነክነኝም፤  ምንአልባት እያደግሁ ይሆን? እንዲያ ከሆነ ደስ ይለኛል፡፡ ማደግን ማን ይጠላል! ይህን ስል ግን የራሳቸው ፍላጎትና የፖለቲካ አቋም የሆነውን ቢሆን የሰዎችን ሃሳብ ግን ተቀብለው ካለ (ምንም አድልዖ ብል ሰው እንዳይታዘበኝ ፈራሁ እንጂ) የሚያስተናግዱ እንደሀበሻ ድረገፅ ያሉ ለሁሉም ተደራሽ ሚዲያዎችን ጠቅሼ ሳላመሰግን ባልፍ አግባብ አይሆንም፡፡(የነዚህ ድረገፆች አስተዋፅዖ መቼስ ከሺህ ባታሊዮን ጦር ይበልጣል፤ ጊዜው ሲደርስ  …)

አቶ ጌታቸው ረዳን ለምን አሁን አነሳሁ? ከሌሎችስ በምን ይለያል? እነዚህን መሰል ጥያቄዎች ማንም ሊጠይቅ ይችላል፡፡

ጌታቸው በርግጥም ጌታቸው ነው፡፡ ስም ይቀድሞ ለነገር ይባላልና፡፡ የጌታቸው ብሔር ኢትዮጵያዊነት ነው፡፡ በወያኔ ቋንቋና የደም ምች ልክፍት ካየነው ደግሞ ጌቾ  ትግሬ ነው፡፡ ጌታቸው ተደብቀው ስለሀገራቸው የሚያብዱና የሚቆዝሙ ጥቂት ትግሬዎችን ወክሎ በዓለም አቀፍ ደረጃ በወያኔ ዕኩይ ድርጊት ምክንያት – ብዘው ተኝቶ እያንቀላፋ በሚገኝበት ወቅት – እንደጥቂቶቻችን ስለሀገሩ እያበደና እየሰከረ ያለ ግሩም ዜጋ ነው፡፡ ወንድምና እህቶቹ እንደዝንጀሮ ከያሉበት ተጠራርተው ሲያበቁ የኢትዮጵያን ክምር እየዘረጋገፉ የበሉትን በልተው የቀረውን ለነገ እንኳን እንዳይተርፍ ለባዕዳን እየሸጡና እያመነቃቀሩት በሚገኙበት ሁኔታ እርሱ የሞት ዐዋጅ እንደታወጀባቸው ዐማሮች በስደት እየኖረ፣ ድረገፅም ከፍቶ ስለዐማሮች ከዐማሮች ከራሳቸውም በላይ ከፍተኛ መስዋዕትነትን እየከፈለ ያለ ብርቅዬ ዜጋ ነው፡፡ ብዙ ዐማራ ወገኖቹ በወያና በቅጥረኞቹ እየታረዱ በተድላና በደስታ ሲኖር – በሀገር ውጥም በውጭ ሀገርም – እርሱ ግን ክርስቶሳዊ የሚሢሕነት ግዳጁን እየተወጣ ያለ ከንፍሮ የወጣ ንጹሕ ስንዴ ነው፡፡ በዚህ ረገድ ተናግሬ መጨረስ አይቻለኝም፡፡ ደግሞም ማጋነን የሌለበት እውነት ነው፡፡ እባካችሁን የሰውን ጠንካራ ጎን በሕይወት እያለ መመስከርን እንልመድ፡፡ በዚህ ረገድ ፈረንጆች ጎበዞች ናቸው መሰለኝ፡፡  እኛ የሚቀናን መዘራጠጥና መሰዳደብ ይመስለኛል፡፡ ከነብሂሉ “አመስጋኝ አማሳኝ” እንላለን፤ የአመስጋኝን ቅስም ለመስበር፡፡ ኩሸትንና ግነትን፣ በከንቱ መወዳደስንና በእከክልኝ ልከክልህ መንገድ እስካልተራመድን ድረስ በእውነት ላይ ተመርኩዘን ጥሩን ሰው ብናመሰግን ምን አለበት?  ተመስጋኝም ሳይኩራራና ምናባዊ የትዕቢት ቆጥ ላይ ራሱን ሳይሰቅል  ለበለጠ መልካም ሥራ እንዲተጋ ቢሆን አካሄዳችንና መዳረሻችን ያምራል፡፡ አቤት የሚቀረንን ነገር ሳስበው….፡፡ እንደማኅበረሰብና እንደሀገር መኖር ልንጀምር ስንውተረተር ወያኔ መጣና ድራሻችንን አጠፋው፡፡ ከዚህ ሁሉ የሞራል ስብራትና የኑሮ ንቃቃት መቼ ማገገም እንምንጀምር አንድዬ ይወቅ፡፡…

በቀደም ለታ የሰደድኩትን መጣጥፍ በየት እንደወጣ ስፈትሽ ታዲያን በርሱ ድረገፅ መለጠፉን ተረዳሁ፡፡ በጣም ገረመኝ፡፡ ያን መጣጥፍ እንኳንስ የትግሬ ደም ያለበት ሌሎችም ፈርተው ትተውታል፡፡ ከዚያ ቅጽበት ጀምሮ አንዳች ነገር ተሰማኝ፡፡ ሰውነቴንም ወረረኝ፡፡ ገነት ዘውዴን የመሰለች “ዐማራ”፣ ልደቱ አያሌውን የመሰለ “ዐማራ”፣ በብአዴን ውስጥና በሕወሓት ውስጥ ለሆዳቸው ሲሉ ዐማራነታቸውን እንደኮት አውልቀው ጥለው ወይም ዐማራነት ቁምጥና ይመስል ደብቀው ዐማሮችን እያስፈጁ የሚገኙ ዜጎች ቁጥር ቀላል አለመሆኑን የሚገነዘብ ሰው ይህን ሰው ከትግሬዎች ጉያ ፈልቅቆ አውጥቶ እንደዚህ ለዐማራው ዋቢና ጠበቃ እንዲሆን ያደረገ አንድ ኃይል መኖር እንዳለበት ያምናል – ልክ እንደኔ፡፡ ለእግዚአብሔር የሚሣነው ነገር የለምና ሊሆን ያለው ሁሉ ሊሆን የግድ ሆነ- እናም የኢትዮጵያ አምላክ ይመስገን ዐማሮችን በትግሬ ጎራዴ የሚያስፈጁ ሆዳም ዐማሮች በሞሉባት ኢትዮጵያ ይህን መሳይ ከተራ ስብዕና በላይ ልዩ ስብዕናን የተላበሰ ትግሬ አገኘን፡፡ ይህን ሰው ማመስገንና መውደድ ምንድን ነው ኃጢኣቱ ታዲያ? “የጊዮርስን ግብር የበላ…” እንዳትሉኝ እንዲህ የምለው የአንዳንዶችን ሽርደዳ አስቀድሜ ስለማስብ ነውና ይቅርታ፡፡ (በነገራችን ላይ ጌች – በናታቸው ማሕጸን ውኃ ሆነው ቢቀሩ በሚሻላቸው ከንቱ ዜጎች – የየትኛውም ነገድና ጎሣ አባላት ሊሆኑ ይችላሉ – ዘለፋና ዛቻ እጅ ሳትሰጥ – አምናለሁ ደግሞ እንደማትሰጥ – በጀመርከው የተቀደሰ ተግባር ቀጥል፡፡ ፈለግህንም በመሰል ጥሩ ዜጎች ለማዳበር ሞክር፡፡)

“ታዲያ አሁን ምን ይጠበስልህ?” የሚለኝ ወለፈንዴ አይጠፋም መቼም፡፡ ምንም አይጠበስልኝም፡፡ ጌታቸውም ያደረገው ሰው ሆኖ ከተፈጠሩ ዘንድ ማንም ሊያደርገው የሚገባውንና የሚጠበቅበትን ነው በተግባር ያሣየው – የተሰጠውን መክሊት ተረድቶ በአግባ ተጠቀመበት፤ ለኅሊናው አደረ፡፡ በቃ፡፡ ከማንም ከምንም ሽልማትም ሆነ ከንቱ ውዳሤን የሚፈልግ አይመስለኝም፡፡ በሕይወቱ ቆርጦ ወደ ትግሉ የገባው ልዩ ሙገሳንና ውዳሴን ፈልጎም አይደለም – “በሕይወቱ ቆርጦ” ስል እነአሰፋ ጫቦ፣ እነሻለቃ ጃተኒና መሰል የወያኔና መሰል ሰይጣናት ረጃጂም ክንድ ሰለባዎች ትዝ አሉኝ፡፡ ለማንኛውም ይህንን ተፈጥሯዊ እንደሆነ የምገምትለትን ጠባዩንም ከርሱ ጋር ሳልነጋገር በ”ቴሌፓቲክ” ምናባዊ የጉዞ መስመር አውቀዋለሁ፡፡ የርሱን ዓይነት ዕድል የሚያገኙ ግን እጅግ በጣም ጥቂቶች ናቸው፡፡ በኛ ሀገር ሁኔታ ከአንድ እጅ ጣቶች ቁጥር እንኳን የማይዘሉ ናቸው፡፡ ከዚህ በላይ መታደል የለም፡፡ ሰው “ክሎን” እየተደገ አይዘራ ወይ አይሰራጭ ሆኖ እንጂ ጌችን በላብራቶሪ እያባዙ በመላዋ ሀገራችን ቢዘሩት ይሄኔ ኢትዮጵያ የት በደረሰች፡፡ በመንፈስ ቀናሁብህ ጌታቸው ረዳ!

ጌታቸው እያደረገ ያለው የሚጠበቅበትን ቢሆንም አድናቆትና አክብሮት ሊያሰጠው የቻለውን ነገር ትንሽ ሰፋ አድርጎ መመልከት ተገቢ ነው፡፡ የመንጋን ጭፍን ስሜት አሸንፎ ራስን መሆን እንደብርቅ በሚታይባት ዓለማችን ውስጥ ጌታቸውን የመሰሉ እውነተኛ ሰዎች ቢደነቁና ቢወደሱ ከሚገባቸው በታች ነው፡፡ በዚህ ዘመን ሰው መሆን ወይም ሰው ሆኖ ለመገኘት መሞከር ከባድ ነው፡፡ ለአብነት  ከመንጋህ መውጣት በራሱ አንድም ዕብድ ያሰኝሃል አንድም በሌላው አቅጣጫ ካየነው ለሰው መለኪያነት የሚውል እጅግ ጤናማ ስብዕናን ያሰጥሃል፡፡ ይህ ደግሞ እንደተመልካቹ ነው፡፡ ትግሬዎች ጌችን እንደ ዕብድና ወፈፌ ሊያዩት ይችላሉ፡፡ ጌችን እኔና መሰሎቼ እንደ የሰው መለኪያ ሚዛን ልንቆጥረው እንችላለን፡፡ እነዚህን መሰል ሰዎች ጠላታቸው ብዙ ነው ታዲያ፡፡ በዚህኛው ጎራ የክህደትን በዚያኛው ጎራ ያለመታመንን ችግር እያተረፉ የሚሰቃዩበት ሁኔታ መኖሩ አይካድም፡፡ ስለዚህም ነው  ይህን ዓይነቱን ፈተና ለማሸነፍ ጠንካራ ስብዕና መላበስ የሚኖርባቸው፡፡ ብዙ ፈላስፎች በወፈፌነት የተፈረጁትና የሚፈረጁት ከመንጋው የስቅሎ ስቅሎ የዕውር ድንብር ዳንኪራ ወጥተው በጤናማ አስተሳሰብ በመመራት ለማኅበረሰቡ የሚበጀውን ነገር ስለሚጠቁሙ ነው፡፡ ስንቶች እኮ ተሰቅለዋል፤ ስንቶች በመርዝ ተገድለዋል፡፡ ስንቶች እኮ ለእስርና ለግዞት ተዳርገዋል፡፡ ስንቶች እኮ ጎዳና ላይ ተጥለው አይሆኑ ሆነዋል፡፡ ይቺ ዓለም?

“ክርስቲያን በመሆኑ ብቻ በእምነቱ የምትገድሉት ከሆነ እኔን ከርሱ ቀድማችሁ ግደሉኝ” ብሎ አንገቱን ለሠይፍ የሚሰጥ ሙስሊም ሲገኝ የሰው መለኪያ ነው፡፡ “እስላም በመሆኑ ምክንያት የምትገድሉት ከሆነ በቅድሚያ የኔን ደረት በጦር ወግታችሁ ግደሉኝ” የሚል ክርስቲያን ሲገኝ ይህ ሰው የሰው መለኪያ ሚዛን ነው – እኔ በፍርሀት ተሸማቅቄ ብዙ ዐማሮች ሲገደሉና ሲታሰሩ በጎመን በጤና እሞቀ ቤቴ ቁጭ ብዬ ስኖር ጌታቸው ረዳ ስለኔ ይጮሃል፤ ስለኔ ይከራከራል – በዘሩ ሳያገባው በነገዱ ሳይመለከተው – ከሞቀ የአራት ኪሎ ቤተ መንግሥቱ ወጥቶ ለዚያውም፡፡ ሃይማኖትና ዘር ዓለምን እየበጠበጡና ከርሰ መቃብሯን እያቃረቡ እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡ እነዚህን ይበልጡን ሰው ሰራሽ የሆኑ ድንበሮች በመጣስ በሰውነት  የጋራ ገመድ ተመርቶ ለሰው ልጅ አጠቃላይ ነፃነት የቆመ ሰው ጽላት ቢቀረጽለት፣ ግዑዙ ሃውልት ቢቀምት ቢያንሰው እንጂ አይበዛበትም፡፡ ብዙ ማለት ይቻላል፡፡ጌታቸው ረዳ ከነዚህ ዓይነቶቹ ግሩም የዓለም ዜጎች አንዱ መሆኑን የምመሰክርለት መሃላ ቢፈቀድ ኖሮ በኅያው እግዚአብሔር ስም እየማልሁ ነበር፡፡

በደቡብ አፍሪካ የአፓርታይድን ሥርዓት የሚቃወሙና በዚያም ሳቢያ መከራ የሚገፉ ነጮች ነበሩ፡፡ በሌላም በኩል ከነጮቹ ጋር ተባብረው የአፓርታይድን ሥርዓት ዕድሜ የሚያራዝሙ ሆዳም ጥቁሮች ነበሩ፡፡ በፀረ ባርነት ትግል ወቅት (Negritude Movement) ጥቁሮች ለነፃነታቸው ሲታገሉ አንዳንድ ጥቁሮች ደግሞ በተቃራኒው  “ጥቁር የነጮች አገልጋይ እንዲሆን የተፈጠረ ነው” በሚል መፈክርና እምነት ከነጮች ጋር ተደርበው ጥቁሮች ወገኖቻቸውን ይዋጉ ነበር – ለዚያው መከረኛ ሆድ ብለው(ሆዳችን እንኳንስ በጀርባችን አልሆነ የሚባለው እውነት ነው!)፡፡ ለዚህ ነው እንግዲህ ሰው መሆን ከባድ ነው የሚባለው፡፡ ይህን መሰሉን የዘር፣ የቀለምና የሃይማኖት አሽክላ ሰብሮ በመውጣት ለእውነተኛ የሰው ልጅ ነፃነት መቆም ያስቀናል፡፡ ለዚህ ዓይነት ሰው አንድ መጣጥፍ አይደለም ብዙ መጻሕፍት ቢጻፉለትም አሁንም ያንሰዋል፡፡ ይህን ለመናገር አዲስ አበባ ላይ ተገኝቶ ትግሬዎች የሚያደርጉትን መመልከት ብቻ በቂ ነው፡፡ ከነዚህ ለይቶላቸው ካበዱና መሬትን ለመርገጥ ከተጠየፉ የጠፉ ትግሬዎች ውስጥ እንዲህ ዓይነት ሰው ማግኘት በበረሃ ላይ በዛፎች የተከበበ ምንጭ (oasis) እንደማግኘት ነው፡፡ የምለው የማይገባው ካለ ወደኢትዮጵያ ይምጣና ትንሽ ይጎብኘን – ካስቻለው፡፡

ስለጌች ሳነሳ ከአንዳንዶች ጋር የሚጋጭባቸውን ሁኔታዎች ዘንግቼ አይደለም፡፡ ጌታቸው የግንባር ሥጋ መሆኑን አውቃለሁ፡፡ ነገርን የማይሸፋፍንና መስሎ ማደርን የማይወድ ሰው ከጥቂቶች ጋር ብቻም ሣይሆን ከብዙዎች ጋር አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘም ከሁሉም ጋር መጋጨት አግባብ የሚሆንበት ጊዜ ሊያጋጥም ይችላል፡፡ ወደ ዝርዝሩ መግባት አልፈልግም – መነሻየ ያ ስላልሆነ፡፡ ግን ይህን መሰል ጠባዩን እንደማውቅለትና እንደምረዳለትም በዚህ አጋጣሚ መጠቆም ስለምፈለግ ነው፡፡ በተረፈ በነገር አለመስማማት ወደ ንቁሪያና መዘላለፍ ባይወስደን መልካም ነው፡፡ አለመስማማትን በጨዋነት ገልጦ በሚስማሙባቸው ነጥቦች ብቻ አብሮ መጓዝም ጨዋነትና ብልኅነት ነው – ለሁሉም፡፡ የኛ ሁኔታ ግን ወይ የነርሱ ነህ አለዚያም የኛ ነህ – ከዚህ ውጭ ያለህ አማራጭ ጠባብ  ነው፡፡ አማራጭ የማይሰጥ የልበሥውራን ፖለቲካ አራማጆች ሆነን ተቸግረናል፡፡ ሆደ ሰፊነት በእህል ብቻ ተወስኖ ቀረና ይህቺ ክብ ጠረጴዛ የሚሏት ነገር ለምግብ ቤት አገልግሎት ብቻ ዋለች፡፡ ፈርንጆች በዱላ ቀረሽ ክርክር ከተመነቃቀሩ በኋላ (ኧረ አንዳንዴስ ይደባደባሉ!) ከአዳራሽ ሲወጡ ይረሱትና በፍቅር ወደፊት ይቀጥላሉ፡፡ እኛ ግን አንዴውኑ አንጀምረው እንጂ የሽሚዛችንን እጅጌ መጠቅለል ከጀመርን የመረዝነውን ሰው ጉድጓድ ውስጥ ካላስገባን ዕረፍት የማናገኝ ጥቂቶች አይደለንም፡፡ ከዚህ በላይ መረገም ደግሞ የለም፡፡ ሰው የመሆኛችን ጊዜ ናፈቀኝ፡፡ የሚገርመው ደግሞ ከሀገር የወጡትም ስንትና ስንት ሥልጣኔና የሰው ልጅን መተሳሰብና አንድነት በየሚኖሩባቸው ሀገራት  እያዩ ዘር ከልጓም ይስባልና አንድም ነገር አይማሩም፡፡ እዚያም ሆነው ማባላትንና ማናከስን ይቀጥላሉ – ቢያንስ በኢንተርኔት ወንጭፍ፡፡

ለማንኛውም ትኩረቴ የኢትዮሰማዩ አዘጋጅ ጌታቸው ረዳ ስለሆነ እንጂ በሀገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ሳቢያ አድናቆቴንና አክብሮቴን የምገልጽላቸው ብዙ ምርጥ ምርጥ ዜጎች እንዳሉ መናገር እፈልጋለሁ – ስላልተነሳሁበት ለምሣሌ የቴዲ አፍሮን መስዋዕትነት እዚህ ላይ አልጠቀስኩም፤ የጥቁሩን ዕንቁ የኦባንግ ሜቶንም ገድል አላወሳሁም – ማንን አንስቼ ማንን እተዋለሁና፡፡ ስንቱ አረሆ ወያኔን እያወደሰ በየምሽት ክበቡ ቀፈቱን ሲያንዘረጥጥ ይህ ብላቴና -ቴዎድሮ ካሣሁን – ስለሀገሩ ይዋደቃል፡፡ አሁንም “ሰው በመኪናው እንዳይገጭ” እየጸለይኩ ነው በነገራችን ላይ፡፡ ወይ ወያኔ! ወንጀልን በሴከንድ ውስጥ እንዴት ፍጥር እንደሚያደርጓት ይገርመኛል፤ ደግሞም አለማፈራቸው! …

ላጠቃል፡፡ ጌች እግዚአብሔር ይባርክህ፤ አንተን መሰሎችም እግዚአብሔር ይባርካቸው – ለመንታ መንገደኞችም ልብ ይስጣቸው፤ በዘረኝነት የጨለማ አረንቋ ውስጥ ለሚዳክሩትም እግዜር ይድረስላቸው – ያለኝ ብቸኛ ሀብት ምርቃት ነውና እኔንም ጌታ ይስማኝና የልቤ ሞልቶ የኢትዮጵያን ትንሣኤ ለ40 እና 50 ዓመታት ብቻም ቢሆን ያሳየኝና ይውሰደኝ – ከተመኙ አይቀር እንዲህ ነዋ! ውድ ወንድሜ የኢትዮሰማዩ ጌታቸው ረዳ በመጣጥፌ ምክንያት በሆዴ ያለውን አስወጣሃኝ – እግዜር ይይልህ እንዳልልህ አንጀቴ አይችልም፡፡ ደግሞም አንተን መሰል ቅንና ፀረ ወያኔ የሆኑ ትግሬዎችን እንደማስከፋ በኋላ ላይ በቁጭት ተገንዝቤ በመጣጥፌ ላይ አንድ አንቀጽ ጨምሬ ልኬ ነበር፡፡ አንተ የለጠፍከው ግን የፊተኛውን ነው፡፡ መቼም እስካሁን ዝም ብለህ ትቀመጣለህ ብዬ አልገምትምና ወ(ላ)ልደህ ከሆነ ዘርህ ይባረክ፡፡ በደጉ ዘመን እንደሙሤ ድልድይ ሆነው ይህን ክፉ ዘመን ከሚያሻግሩን ብርቅዬ ዜጎቻችን አንዱ ነህ ብዬ አምናለሁና እግዚአብሄር ጠባይህን አያስለውጥብን፡፡ አንዳንዴ ነሸጥ ሲያደርገን ባለውለታን እንደዚህ ማመስገኑና በደግ ማውሳቱ ክፋት የለውምና ሌሎቻችንም ይልመድብን፡፡ ቻው፡፡ ለገምቢ አስተያየት – ma74085@gmail.com – ማነህ እጅጉ ነህ እጅቡ የተባልክ ሰውዬ ደግሞ በአቡነ አረጋዊ ይሁንብህ የኔ ጽሑፍ ይቅርብህ፤ ስድብ ደግሞ የትንሽነት ምልክት ነው… እንዴ፣ ነውር አይደለም?)

ከዮናታን ተስፋዬ የባሰ “አሸባሪ” ከቶ ከወደየት ይገኛል?

ስዩም ተሾመ

ስዩም ተሾመ

የቀድሞው የሰማያዊ ፓርቲ አመራር ዮናታን ተስፋዬ ረጋሳ በተከሰሰበት የሽብርተኝነት ወንጀል ጥፋተኛ ተብሏል። በዮናታን የተከሰሰው “በፀረ-ሽብርተኝነት አዋጅ ቁጥር 652/2001 ዓ.ም አንቀፅ(4) ስር የተደነገገውን በመተላለፍ” ነው። በዚህም የኦነግ ዓላማን ለማሳካት አመፅና ብጥብጥ እንዲቀጥልና ሌሎችን ለማነሳሳት አስቦ በፌስቡክ ገፁ ላይ በሚወጣቸው ፅሁፎች የሽብርተኝነት ድርጊት ለመፈፀም ማቀድ፣ ማዘጋጀት፣ ማሴር እና ማነሳሳት ወንጀል ተከሷል። በማስረጃነት የቀረበው ከሕዳር 24/2008 ዓ.ም እስከ ታህሳስ 11/2008 ዓ.ም ባሉት ቀናት በፌስቡክ ገፁ ላይ ያወጣቸው ፅሁፎች ናቸው። ከእነዚህ ውስጥ በ2ኛ ተራ ቁጥር ላይ የተጠቀሰው እንዲህ ይላል፡-
“በቀን 11/04/08 ዓ/ም (ዲሰምበር 21 2015 4፡32 AM) ከቀኑ 10፡32 በሚጠቀምበት ፌስቡክ ‘ኢህአዴግ ችግር ማዳፈን እንጂ መፍታት የሚያስችል አቅም የለውም’ በሚል ከፃፈው ፅሁፍ ውስጥ ‘አምና ከ40 በላይ የኦሮሞ ተማሪዎችን ገደሎ ችግር የፈታ የመሰለው ኢህአዴግ ዘንድሮም ከአምናው ሳይማር ዜጎችን በመግደል ችግሩን ለመፍታት እየጣረ ነው። በቀና መንገድ ችግር ከመፍታት አፈና ምላሽ ሆኗልና ወደ የማይቀረው አመፅ እየተንደረደርን መሆኑን የሰሞኑ ተቃውሞና የገጠመው ምላሽ ከበቂ በላይ አስረጂ ነው’ የሚል ቀስቃሽ የሆነ ፅሁፍ በመፃፍ ሌሎችን እንዲነሳሱ በማድረጉ” አቃቤ ሕግ ለፌዴራል ክፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ ችሎት ካቀረበው የክስ ቻርጅ ውስጥ የተወሰደ

ታዲያ ይህ ፅሁፍ እንዴት ሆኖ ዮናታን በተከሰሰበት የሽብር ወንጀል በማስረጃነት ሊቀርብ ይችላል? በእርግጥ ለዚህ ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ በክስ ቻርጁ የተጠቀሱ ፅሁፎችን አንድ-በአንድ ብንመለከት “ይሄ እንዴት ፅሁፍ የሽብር ወንጀል በማስረጃነት ሊቀርብ ይችላል?” እያላችሁ ትጠይቃላችሁ። ይሁን እንጂ፣ በሕግ መሠረት ለአንዱም ጥያቄ አጥጋቢ ምላሽ አታገኙም። በእርግጥ ጥያቄው መልስ-አልባ ሆኖ ሳይሆን የተሳሳተ ስለሆነ ነው። ለተሳሳተ ጥያቄ ትክክለኛው መልስ ጥያቄውን ማስተካከል ነው። ለምሳሌ፣ ከላይ የተጠቀሰው ፅሁፍ “እንዴት በሽብር ወንጀል ተከሳሽ ላይ ማስረጃ ተደርጎ ሊቀርብ ይችላል?’ ብሎ መጠየቅ ስህተት ነው። ከዚያ ይልቅ፣ “ከሳሽ ወይም መንግስት ለምን በዚህ ፅሁፍ ተሸበረ?” በሚል መስተካከል አለበት።

ከ2007 ዓ.ም ጀምሮ የኢህአዴግ መንግስት ከሕዝብ ለሚነሱ ጥያቄዎች ምላሽ የሰጠበትን አግባብ በጥሞና ሲከታተል ለነበረ ሰው “ኢህአዴግ ችግርን ማዳፈን እንጂ መፍታት የሚያስችል አቅም የለውም” የሚለው ፅሁፍ ይዘት ሙሉ-በሙሉ “እውነት” እንደሆነ መገንዘብ ቀላል ነው። በተለይ በአምቦ ከተማ በተፈጠረው ችግር ተማሪዎች መገደላቸው የማይካድ ሃቅ ነው። በሕዳር 2008 ዓ.ም የአመፅና ተቃውሞ እንቅስቃሴው እንደገና ሲቀሰቀስ የኢህአዴግ መንግስት የሕዝብን ጥያቄ ተቀብሎ ችግሩን በቀና መንገድ ከመፍታት ይልቅ በኃይል ለማፈን በመሞከሩ ሀገሪቷን ለከፍተኛ አመፅና አለመረጋጋት ዳርጏታል። በዚህ ምክንያት፣ በመቶዎች የሚቆጠሩ ዜጎች መገደላቸውን፣ ብዙ ሺህዎችን ለአካል ጉዳት መዳረጋቸውንና ከመኖሪያ ቄያቸው መፈናቀላቸውን፣ እንዲሁም በቢሊዮን የሚቆጠር የሕዝብና የመንግስት ንብረት መውደሙን ማንም አያስተባብልም። ሌላው ቀርቶ ዮናታንን የከሰሰው መንግስት እንኳን ይህን ሃቅ ሊያስተባብል አይችልም።

ታዲያ የዮናታን ፅሁፍ ሙሉ በሙሉ የማይካድ ሃቅ ሆኖ ሳለ ፀኃፊው በሽብር ወንጀል የተከሰሰው ለምንድነው? ፀኃፊው “በሌላ ዓይነት የሽብር ድርጊት ተሰማርቶ ነበር” ቢባል እንኳን ይህን ፅሁፍ በማስረጃነት ሊቀርብ የሚችልበት አግባብ የለም፡፡ ስለዚህ፣ ተከሳሽ፥ ዮናታን ተስፋዬ የፈፀመው የወንጀል ተግባር በተጠቀሰው ፅሁፍ እውነትን በትክክል መግለፁ ነው። በከሳሽ፥ የኢህአዴግ መንግስት ላይ የደረሰው ጉዳት ደግሞ እውነት እንዲያውቅ መደረጉ ነው።

በመሰረቱ፣ እውነታን ከሌሎች መደበቅ በሚሹ ዘንድ ስላለፈው፣ ስለአሁኑ ወይም ስለወደፊቱ ግዜና ሁኔታ በትክክል መናገርና መፃፍ ከአሸባሪነት ተለይቶ ሊታይ አይችልም። በተለይ አምባገነን መንግስታት ደግሞ ሀገሪቱ ስላለችበት ሁኔታ፣ ሕዝቡ ስለሚያነሳቸው ጥያቄዎች፣ ሌላው ቀርቶ ስለራሳቸው ሥራና አሰራር ማንም እንዲያውቅባቸው አይፈልጉም። ምክንያቱም፣ ሁሉም አምባገነን መንግስታት በስልጣን ላይ መቆየት የሚችሉት፤ አንደኛ፡- ብዙሃኑ የሕብረተሰብ ክፍል ስለ ፖለቲካዊ መብቱና ነፃነቱ በቂ ግንዛቤ ከሌለው፣ ሁለተኛ፡- የሲቭል ማህበራትና ድርጅቶች በፖለቲካው ውስጥ ንቁ ተሳትፎ ካላደረጉ እና ሦስተኛ፡- የዓለም-አቀፉ ማህብረሰብ ስለ ሀገሪቱ ፖለቲካዊ ሁኔታ በቂ ግንዛቤ ከሌለው ነው።

ነገር ግን፣ የኢንተርኔት ፋይዳና አጠቃቀም ከላይ ከተጠቀሰው ሁኔታ ፍፁም ተቃራኒ ነው። ለምሳሌ፣ አንድ በጉዳዩ ላይ የተሰራ ጥናት የሚከተለውን ድምዳሜ አስቀምጧል፡-
“Four separate areas of Internet use threaten authoritarian regimes: mass public use, civil society organizations (citizens’ pressure groups), economic groups and the international community.”

እንደ ፌስቡክ ያሉ ማህበራዊ ድህረ-ገፆች በተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች ዘንድ እንደ የውይይት መድረክ ሆነው እያገለገሉ ይገኛል። ዜጎች ሃሳብና መረጃን በቀላሉ እንዲለዋወጡ ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል። የሙያና ሲቭል ማህበራት ከሕብረተሰቡ ጋር አሳታፊ የሆነ ግንኙነት እንዲኖራቸው እና በፖለቲካው ውስጥ የሚጠበቅባቸውን ሚና እንዲጫወቱ ያግዛሉ። የዓለም-አቀፉ ማህብረሰብ ስለ ሀገሪቱ ፖለቲካዊ ሁኔታ በቂ ግንዛቤ እንዲኖረው ያስችላሉ። በዚህ ምክንያት፣ እንደ ኢህአዴግ ባለ አምባገነናዊ መንግስት ላይ ከፍተኛ የሆነ የሕልውና አደጋ ይጋርጣሉ።

በአጠቃላይ፣ ዮናታን ተስፋዬ በፌስቡክ ገፁ ባወጣቸው ፅሁፎች ምክንያት በሽብርተኝነት ወንጀል መከሰሱና በዚህም ጥፋተኛ ሆኖ የመገኘቱ ሚስጥርን ለመረዳት ከዚህ ጋር አያይዞ መመልከት ያስፈልጋል። ለዚህ ደግሞ በክስ ቻርጁ ላይ በማስረጃነት የቀረቡትን ጽሁፎች በዝርዝር መመልከት ብቻ ይበቃል። ዩናታን ከሕዳር – ታህሳስ 2008 ዓ.ም ባሉት ቀናት በሀገሪቱ ስለተከሰተው አመፅና አለመረጋጋት በእውነታ ላይ የተመሰረተ ትክክለኛ መረጃ የያዙ ፅሁፎችን በፌስቡክ ገፁ ላይ አውጥቷል። በእነዚህ ፅሁፎች አማካኝነት ብዙሃኑ የሕብረተሰብ ክፍል፣ የተለያዩ የሲቨል ማህበራትና ድርጅቶች፣ እንዲሁም የዓለም-አቀፉ ማህብረሰብ በወቅቱ ስለነበረው የሀገሪቱ ፖለቲካዊ ሁኔታ ትክክለኛ መረጃ እንዲደርሳቸው አድርጓል። በዚህም በኢህአዴግ መንግስት ላይ የሕልውና አደጋ እንዲጋረጥ የበኩሉን አስተዋፅዖ አበርክቷል። በወቅቱ በሀገሪቱ ስለነበረው የፀጥታና አለመረጋጋት ችግር፣ ሕዝቡ ስለሚያነሳቸው የመብትና ነፃነት ጥያቄዎች፣ እንዲሁም የመንግስትን ሥራና አሰራር በመተቸትና በመፃፍ የኢህአዴግ መንግስትን አሸብሯል። በዚህ ምክንያት፣ መንግስት የፀረ-በሽብርተኝነት አዋጅ ቁጥር 652/2001 ጠቅሶ ከሰሰና ጥፋተኛ ነህ አለው። በእውነት ላይ የተመሰረተ ትክክለኛ መረጃ ክፉኛ ለሚያሸብረው መንግስት ከዮናታን ተስፋዬ የባሰ አሸባሪ ከቶ ከወደየት ይገኛል?

የኢትዮጵያ ቤተ-ክርስቲያን ኢትዮጵያን የማዳን ኃላፊነት ከመቼውም ጊዜ በላይ እየገዘፈ መጥቷል (የጉዳያችን ማስታወሻ)

 

“ጆሮን የተከለው አይሰማምን? ዓይንን የሠራው አያይምን? አሕዛብንስ የሚገሥጸው፥ ለሰውም እውቀት የሚያስተምረው እርሱ አይዘልፍምን? የሰዎች አሳብ ከንቱ እንደ ሆነ እግዚአብሔር ያውቃል” መዝሙር 94፣ 9

ጌታቸው በቀለ | የጉዳያችን ማስታወሻ

ሁከት በዝቷል፣ጨዋነት ጠፍቷል፣ ኢትዮጵያውያን እርስ በርስ በጎሳ እንዲከፋፈሉ ሆነው በእራሷ በመገናኛ ብዙሃኗ እኩይ የክፍፍል ወሬ እየተነዛባት ነው።ትውልዱ በአራቱም አቅጣጫ እየተሰደደ ነው።ሰርቆ ህንፃ ያቆመ የሚደነቅባት፣ለፍቶ ሰርቶ የሚያድረው የሚናቅበት፣ሹማምንቷ የሀገሪቱን ገንዘብ በጠራራ ፀሐይ ይዘው ሲወጡ ከለንደን እስከ ታይላንድ አየር መንገዶች ላይ የሚያዙበት፣መሪ ተብሎ የተቀመጠው ሰው በቴሌቭዥን ሕፃናት ሳይቀሩ ሲያዩት ውሸት የሚያወራው የተባለበት፣ስታድዮም ውስጥ አብሮ ለመጫወት አንተ ከእዚህኛው ክልል አንተ ከእዝያ ማዶ ነህ እየታባባለ የሚቧቀስበት፣ ባለስልጣናቱ ሁሉ መድረክ ላይ ወጥተው ከኢትዮጵያውነታቸው ይልቅ ከእዚህ ዘር ነኝ የመጣሁት የሚባባሉበት፣ኢትዮጵያ ሴት ልጆቿ ከወላጆቻቸው ጋር ወግ ማዕረግ በማየቻቸው የአፍላ ወጣትነት ጊዜያቸው ለአረብ ሀገር የፈተና ሥራ ፍዳ የሚያዩበት፣ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንም ሆነች ሌሎች የእምነት አካላት ሁሉ በቀጥታ በፖለቲካ ጣልቃ ገብነት የተሾሙበት፣ ሕዝብ ሃዘን ላይ የሚገኝበት ወቅት ነው።

ይህ ብቻ አይደለም ወቅቱ ዓለም የኢትዮጵያን አካሄድ በጥንቃቄ እያየ እየተሳቀቀ እና ግራ እየተጋባ ያለበት ወቅት ነው። ወዲህ አዋጅ ያወጀበት ሕዝብ ላይ እልቂት የሚፈፅመው ስርዓት በእውር ድንብር አካሄድ ያገኘውን እያሰረ እና እየገደለ ልጆቿን እያሰቃየ በሌላ በኩል ኢትዮጵያን በባዕዳን ስትከበብ ሁሉ ምንም እንዳልሆነ ከማታለል በላይ የኢትዮጵያን ህልውና ከሚፈታተኑ ሁሉ ጋር ግንባር እየፈጠረ በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ጦርነት ያወጀበት ነው።በሕወሓት እና ሱዳን መካከል የተደረገው ስምምነት ክርስቲያኑን ሕዝብ በመግደል እና በመጨረስ አላማ ላይ ያለመ ነው።ኢትዮጵያውያን ከውስጥ እሳት ከውጭ ረመጥ ሆኖባቸው መከራቸው እየባሰ ነው።

የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንም ሆነች ሌሎች የእምነት አካላት ሁሉ ከላይ በተጠቀሰው ፈተና ውስጥ የተዋጡ መሆናቸው የአደባባይ ሚስጥር ነው።በኢትየጵያ ቤተ ክርስቲያን አንፃርም እነኝህ ፈተናዎች እና የስርዓቱ ቤተ ክርስቲያኒቱን የማጎስቆል እና የማዳከም ተከታታይ ሥራ ላለፉት 25 ዓመታት ተሰርቷል።ባለፉት 25 ዓመታት የስርዓቱ ዕቅድ ቤተ ክርስቲያኒቱን አሁን ካለችበት ደረጃ በበለጠ መልኩ መቆጣጠር እና ማዳከም ቢሆንም የተሸረበውን እኩይ ዕቅድ ስርዓቱ በፈለገው ደረጃ ሙሉ በሙሉ ሄዶለታል ማለት አይቻልም። ለእዚህም ማስረጃው የምዕመኑ መጠንከር እና የበለጠ ቤተ ክርስቲያኑን በቅርብ ማወቁ ነው።ይህም ሆኖ ግን ከላይ ያለው መዋቅር ንቁ እንዳይሆን ብቻ ሳይሆን በሙስና እና ብልሹ ተግባራት ሲታመስ ሕግ አስከባሪ ነኝ የሚለው ስርዓት አንድም እገዛ ሳያደርግ ይልቁንም ለሕገ ወጦች የፖሊስ ኃይል ሁሉ እየመደበ ቤተ ክርስቲያኒቱ አሁን ላለችበት ደረጃ አድርሷታል።

የሙስናውን ደረጃም በቅርቡ አቡነ ማቴዎስ ለሸገር ራድዮ እንደተናገሩት ” ሁኔታው ከአቅም በላይ ሆኗል” ብለዋል። ከአቅም በላይ የሆነ ነገር በእግዚአብሔር በምታምን ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ፈፅሞ ቦታ ባይኖረውም እርሳቸው ግን ብለውታል።በተለይ ይህ ፅሁፍ በሚፃፍበት ሰዓት በሀገር ውስጥ እና በውጭ የሚገኙ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት በአሜሪካ እና አዲስ አበባ የግንቦት ርክበ ካህናት የሲኖዶስ ስብሰባ ላይ ናቸው። በውጭ በአቡነ መርቆርዮስ በአገር ውስጥ በአቡነ ማትያስ ሰብሳቢነት። ይህ በእራሱ እንደ ሀገር አንዱ ስብራታችን ነው።የዘመናችን ቁስል ነው።ይህንን ቁስል ለልጆቻችን ሳይተላለፍ እንዴት ማጠገግ እና ማሻር ይቻላል? የሚለው በእያንዳንዱ ምእመን እና አባቶች ላይ የወደቀ ሸክም ነው።ይህ ሁሉ የሆነብን ይህ ስርዓት በጎሳ ላይ የተመሰረተ መከራ በላያችን ላይ ከጫነብን ጊዜ ጀምሮ ነው።እዳው ግን ይሄው እሳክሁን ቤተ ክርስቲያኒቱን እና ሀገሪቱን እያንገላታት ነው።የሚገርመው የቤተ ክርስቲያንን መከፋፈል በፅኑ ስርዓቱ እንደሚደግፈው ለመረዳት ላለፉት 25 ዓመታት ችግሩን እንደ ችግር አይቶ ለመፍታት ስንዝር ያህል የሄደበት ሂደት አለመኖሩን መመልከቱ በእራሱ በቂ ነው።ይልቁንም አባቶች በእራሳቸው ወደ ውይይት መድረክ ሲቀርቡ (የዳላስ ቅዱስ ሚካኤል ውይይትን ያስታውሷል) እነ አቦይ ስብሐት ተነስተው “መሰቀል አለባቸው” እና ሌሎችም አባባሎች በመናገር የቀድሞው ፕሬዝዳንት አቶ ግርማ ወ/ጊዮርጊስን የተናገሩትን እንዲያጥፉ በማስፈራራት ጭምር ኢትዮጵያ የቤተ ክርስቲያኗ አባቶች ለሁለት እንዲከፈሉ ከወትሮውም የሰሩ መሆናቸውን ዳግም አስመስክረዋል።

የኢትዮጵያ ጥሪ ለኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን

አሁን ኢትዮጵያ የኢትዮጵያን ቤተ ክርስቲያን እየተጣራች ነው።አንቺ ከሰማያዊ አምላክ ጋር ገፅ ለገፅ የተነጋገሩብሽ ቤተ ክርስቲያን ልጆቼ በዘር እየከፋፈለ የሚያፋጅ መንግስት ሲያምሰኝ ዝም አትበይ። ልጆቼ በእየእሥር ቤቱ ተወርውረው እየማቀቁ እና በጎጥ እየተለዩ እየተሰደቡ ነው እና ከሕዝቡ ጋር አብረሽ አልቅሺ። ዋልድባን የሚያህል ለመላው ዓለም የሚፀልዩ የተሰወሩ አባቶች ፀጋ የሰፈነበት ገዳም ያሉ አባቶች ሲሰደዱ እና ሲገረፉ ካህናቶችሽ ማቅ ለብሰው ያልቅሱ።እንባቸው በሕዝብ ፊት ይታይ።የሃይማኖት ሰው ሃዘን እግዚአብሔርን ከዙፋኑ ይጠራዋል።የአዳም እንባ መድኃኔአለምን ከዙፋኑ እንደሳበው። የእኔ ነገር እንዲህ ሕፃን አዋቂውን አስጨንቆት ሕዝቤ ይህ መንግስት እንደ ሩዋንዳ ሊያባላን ነው እያለ በጭንቀት ላይ ሆኖ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ሆይ! ከጳጳሳቶችሽ ከስር ባሉ ካህናቶችሽ እና ምእመናን ጋር በአደባባይ አልቅሺ።ማልቀስ ሲከለክሉሽ ካህናቱ ቢታሰሩ ይሻላቸዋል።የኢትዮጵያ እንባ መሬቱን እያራሰው የሲቃ ድምፅ አለምን ሳይቀር እያስተከዘ በሕዝብ መሃል ከመኖር ከታሰሩት ጋር መታሰር ይሻላል። እርግጥ ነው የዕለቱም ሆነ የሳምንታቱ ፀሎት፣ቅዳሴ እና ምልጃ ሁሉ እንደሚያግዘኝ አውቃለሁ።የአሁኑ ወቅት ግን ከእዚህ የበዛ ድምፅ ወደሰማይ ማሰማት የሚሻበት ወቅት ነው። እስከዛሬ በለሆሳስ ከነበረ ፀሎቱ አሁን በእንባ እና የምድርን ዳር በሚንጥ እንዲሁም ወደ እግዚአብሔር በበለጠ በመጮህ መሆን አለበት። እስከዛሬ ትንሽ ትንሽ በመራብ ከነበረ አሁን የበለጠ በመጦም መሆን አለበት።እስከዛሬ ልጆቼ በጎሳ እየከፋፈለ የሚያባላቸውን ስርዓት በፍርሃትም ሆነ በአርምሞ ዝም በማለት ከነበረ አሁን በግልጥ አደባባይ ወጥቶ በመናገር እና ልጆቼን ከጥፋት በማዳን መሆን አለበት።

በእዚህ ሰዓት ምእመን ጳጳሱን የሚጠብቅበት፣ዲያቆኑ ቄሱን የሚጠብቅበት ወቅት አይደለም።ምዕመኑም ዲያቆኑን የሚጠብቅበት አይደለም።ኢትዮጵያን በዘር ፍጅት ውስጥ ለመክተት የመጨረሻ አማራጭ አድርጎ ስርዓቱ ወስኗል።ወንጀልን ለመሸፈን በእርስ በርስ የዘር ፍጅት አስነስቶ በሕዝብ ደም ታጥቦ አቅጣጫ ለማስቀየር።ለእዚህ ብዙ ምልክቶች ታይተዋል።በሱማሌ እና ኦሮሞ፣በአፋር እና ትግራይ፣በአፋር እና አማራ፣ወዘተ ግጭቶች የተነሱት በስርዓቱ አነሳሽነት መሆኑ ግልጥ ሆኗል።በቅርቡ በመቀሌ ስታድዮም የተነሳው የባህርዳር ከነማ እና የመቀሌ አቻው መሃል የተነሳውን ብንመለከት ችግሩ ስርዓቱን ያሳሰበው ሳይሆን ይልቁንም በትዕቢት መመልከትን መርጧል። የትግራይ ፖሊስ አዛዥ ለጀርመን ድምፅ ራድዮ ሲመልሱ “ምን አገባችሁ” የሚል ምላሽ ነበር።ይህንን የሰሙ የስርዓቱ ደጋፊዎች እሰይ ደግ አደርጉ የሚል ምላሽ የሰጡ ሲኖሩ ሌሎች ጉዳዩ ያሳሰባቸው አሉ።ይህ ሁሉ የሚያሳየን መጪው ጊዜ ኢትዮጵያውያንን በመጪው ጊዜያት ህዝብን ሊያፋጅ የተዘጋጀ ሕዝብ እርስ በርስ እንዲታረቅ ምንም ጥረት የማያደርግ ይልቁንም እራሱ የፀብ ጫሪ መንግስት እንዳለን ካወቅን ሰንብተናል።በእዚህ ጊዜ የጎሳ ፖለቲካን አውግዘው ኢትይጵያውያንን የህብረት መንገድ የሚያሳዩ የሃይማኖት አርበኞች በመብራት ይፈለጋሉ።ይህንን የማያደርግ ሃይማኖተኛ ነኝ ብሎ ልናገር ከቶ አይችልም።ኢትዮጵያ የኢትዮያ ቤተ ክርስቲያንን ስትጣራ ከጳጳስ እስከ ተራ ምእመን ያለህ ሃይማኖት አለኝ የምትል ሁሉ ሕዝቤን ፍቅር እና አንድነትን እያስተማራችሁ ከተደገሰብኝ የእልቂት ድግስ አድኑኝ እያለች ነው።በሃይማኖት በኢትዮጵያ ላይ የተደገሰውን የእልቂት አዋጅ እንጋፈጥ።በሃይማኖት የተነሳን የሚችለው ምድራዊ ኃይል የለም።ሃይማኖት ብረቱን ያቀልጣል፣ተራራን ይንዳል፣ጨለማውን ይገፈዋልና።

አረሳት ኢትዮጵያን በዘማሪ ይልማ ኃይሉ

ባለ ሜካፑ ዶክተር – ዩሐንስ ደሳለኝ

በአገራችንም ሆነ በውጭም ባሉት ከትልቅ እስክ ትንሽ ሚዲያ የምንሰማው፣ የምናየው ነገር ግራ አጋቢና ጉድ ያሰኛል በተለይ የአገራችን ባለስልጣናት እየሆኑት ያሉትና ለመሆን የሚጣጣሩት ነገር አጀብ ያስኛል ፤ ካለፈው ዓመት ጀምሮ ጉደኛው ዶክተር ቴዎድሮስ አድሃኖም ለWHO (ለዓለም ጤና ተቋም )ለመወዳደር ሲነሳ ይችን አገር የሚመሯት ሰዎች በንዋይ የሰከረው ህሊናቸው ድንበር ተሻጋሪና አደገኛ መሆኑን ያመላከተበተለይ እኛ በውጩ ዓለም ያለን ኢትዩጵያኖች ልንረዳው የሚገባና በርተተን መታገል ያለብን የግዜው አንገብጋቢ ጉዳይ ነው ።|
ከላይ ርዕሴ ላይ እንደጠቀስኩት ባለሜካፑ ዶክተር ቴዎድሮስ ካፈርኩ አይመልስኝ ብሎ በብዙ ነገሮቹ የጠለሽውን ተፈጥሮአዊ ማንነቱን በሜካፕ ቀባብቶ ብቅ ያለው ፤ለመሆኑ ይህ ሰው ለዚህ ስፍራ ይመጥናል ወይ ? ለእዚህ ጥያቄ መልስ ለመስጠት ብዙ ሩቅ መሄድ አያስፈልግም በሙያው የጤና ሰው ሆኖ በተለያየ ወቅት የአገራቸውን የውጭ ፖሊሲ በችሎታቸው የምዕራባዊያንን ቀልብ የሳቡ ሞግተው ያሽነፉትን ጥቅሟን አስከብረው ካለፉት ከነአክሊሉ ሃብተወልድና መሰሎቻቸው ጋር በማይመጥን መልኩ የኢትዩጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሆኖ በታሪክ ስሙን ለማስጥራት ተሰለፈ ሆኖም ግን ወገኖቻችን በተለይ ደግሞ እህቶቻችን በየአረብ አገራቱ ሲገደሉና ሲታሰሩ ጆሮ ዳባ ልበስ አለ ይባስ ብሎ በ2015 እአ ወንድሞቻችን በሊቢያ በርሃ በአሲየስ ሲታረዱ ኢትዩጵያዊ መሆናቸውን እያጣራሁ ብሎ አረፈው ከዚሁም ጉዳይጋር ተያይዞ ከባድ ወቀሳ የደረሰበት ወያኔ የውጭፖሊሲው ከዱሮ የባሰ መበላሸቱ ሲያውቀውና ንዋይ ሲያጥረው በአንድ ውቅት HIV ለእኛ ጥቅም ነው የመጣው ያለውን ይህን ነውረኛ ሰው ከነበረበት ስልጣን አውርዶ ዛሬ ለWHO እንዲወዳደር ከፍተኛ ገንዝብ ተመድቦለት በወገኖቹ ደም ላይ አሁንም ቀልድ የጀመረው ።
በተለያየ ግዜ በተለያዩ የአገሪቱ ከልል የሚሰሩ ዶክተሮች ፣ የላብራቶሪ ሰራተኞችና ከሕክምና ሙያ የተያያዝ ስራ የሚሰሩ ሰዎች ጋር በነበረኝ ቅርበት ሁሌ ሲያማርሩ የሚሰማው ነገር ቢኖር በየግዜው በሚፈጥረው የመድሃኒትና የመሰረታዊ መገልገያ መሳሪያዎች አቅርቦት ላይ ነው ይህ ማለት እንግዲህ ለበሽታ ማስታገሻ ተብሎ የሚሰጠውንም ይጨምራል እንዲያውም አንዳንዶቹ ዶክተሮች ወደውት ከሰባት ዓመት በላይ ዋጋ የከፈሉለትን ሙያ እያማረሩ ግማሹቹ ተሰደዋል ግማሽዎቹ ያችኑ የሁለት ዓመት ግዴታቸውን ከተወጡ በኋላ ከተማ (በተለይ አዲስ አበባ)ገብተው ያዩትን ሁኔታ እንዳላዩ ሆነው ይኖራሉ ሞትና እንግልት የተፈረደበት የገጠሩ ህዝብ ዕድሜ ለነ ቴዎድሮስ አድሃኖም ፖሊሲ እየማቀቀ ይኖራል ፤ እንዲያውም ለዚህ ጉዳይ ማመላከቻ ይሆን ዘንድ በአንድ ወቅት አንድ ላብራቶሪ ውስጥ ከህንድ በመጣው የተጭበረበር ኬሚካል ምክኒያት ብዙ ሰው ለሌላ ህክምና ሄዶ ታይፎይድና ታይፈስ አልብህ ተብሎ መመለስ የዕለት ተለት ዜና ሆኖ ነበር በኋላ ላይ በተደረገ ማጣራት ይሄው ኬሚካል ውሃ እንኳን ሳይቀር ፖዘቲቭ እያለ አስቸግሮ ነበር በዚያም ጥርጣሬ ነበር የኬሚካሉ ፎርጅድነት ታውቆ ክገበያ የወጣው ነገር ግን ከዚሁ ጋር በተያያዝ በታዘዘላቸው መድሃኒት ምክኒያት ለጉበትና ለተለያዩ በሽታዎች የተጋለጡ ሰዎች በሆነ ወቅት የተለመደ የነበረው እንግዲህ ይሄን ሁሉ ጉድ የተሽከመው ሰውየ ነው በዓለም መሳቅያና መሳለቅያ ሊያደርገን ድቤውን እየጎሰመ ያለው ።
ወደ እናቶችና ህጻናት ሞት ስንመጣ ደግሞ ጉጀለው የወያኔ መንግስት ከIMF ገንዘብ መጠየቂያ ይሆነው ዘንድ በራሱ ቀመር በሰራው አሃዝ አለምን ያታልላል ነገር ግን ውደ ውስጥ ጠጋ ብለን ስናየው በየክልሉና ገጠር ቀበሌው ከወሊድ ጋር በተያያዘ የሚሞቱት ህጻናትና እናቶች ቤት ይቁጠራቸው፤ እንግዲህ አስተውሉ በአገሩ ህጻናት ደም ሌላው ደግሞ ሳይማሩ ባስተማሩትና ክብካቤና ክብር በሚገባቸው እናቶች ላይ ያሾፈው ባለሜካፑ ዶክተር ቴዎድሮስ ማን አለብኝነቱን በአለም መድረክ ለማሳየት የደፈረው፤ ወንድሞቸና እህቶቼ በተለይ እኛ በስደት ያለን ኢትዩጵያኖች በተገኘው አጋጣሚ በመረባረብ ይህን የጉጀሌው ተላላኪ ማስቆም ያለብን ።
በዚሁ አጋጣሚ በወያኔ ዘመን የተማረና የተመረቀ ልማታዊ ዶክተር እሱ ጋር ሊታከም የመጣን በሽተኛ የሰጠውን መልስ በግጥም መልክ አንድ ጓደኛ ያስቀመጥውን ጀባ ልበልና ላብቃ
ቀንስ
አንጀቱ ተጣጥፎ
እግሩ ተዝለፍልፎ
ለመራመድ ሰንፎ
ገላው ወዙን አጥቶ
ሁለመናው ከስቶ
ደራርቆ ገርጥቶ
በጓደኛው ታዝሎ ጤና ጣቢያ መጥቶ
ሃኪሙ ጋር ቢደርስ ለጉድ እያሳለው
ዶክተር “ያገር ፍርጃ” ምግብ ቀንስ አለው
ብታስደንቀውም ዓለም ተግልብጣ
ማልቀስ ቢፈልግም ብሶቱን ሊወጣ
እንባ አልቆበታል ኬ’ት አባቱ ይምጣ፟
የሚሆነው ቢያጣ ማልቀስ እያማረው እየሳቀ ወጣ
ዩሐንስ ደሳለኝ (ከጀርመን ፍራንክፈርት)

ባለ ሜካፑ ዶክተር – ዩሐንስ ደሳለኝ

በአገራችንም ሆነ በውጭም ባሉት ከትልቅ እስክ ትንሽ ሚዲያ የምንሰማው፣ የምናየው ነገር ግራ አጋቢና ጉድ ያሰኛል በተለይ የአገራችን ባለስልጣናት እየሆኑት ያሉትና ለመሆን የሚጣጣሩት ነገር አጀብ ያስኛል ፤ ካለፈው ዓመት ጀምሮ ጉደኛው ዶክተር ቴዎድሮስ አድሃኖም ለWHO (ለዓለም ጤና ተቋም )ለመወዳደር ሲነሳ ይችን አገር የሚመሯት ሰዎች በንዋይ የሰከረው ህሊናቸው ድንበር ተሻጋሪና አደገኛ መሆኑን ያመላከተበተለይ እኛ በውጩ ዓለም ያለን ኢትዩጵያኖች ልንረዳው የሚገባና በርተተን መታገል ያለብን የግዜው አንገብጋቢ ጉዳይ ነው ።|
ከላይ ርዕሴ ላይ እንደጠቀስኩት ባለሜካፑ ዶክተር ቴዎድሮስ ካፈርኩ አይመልስኝ ብሎ በብዙ ነገሮቹ የጠለሽውን ተፈጥሮአዊ ማንነቱን በሜካፕ ቀባብቶ ብቅ ያለው ፤ለመሆኑ ይህ ሰው ለዚህ ስፍራ ይመጥናል ወይ ? ለእዚህ ጥያቄ መልስ ለመስጠት ብዙ ሩቅ መሄድ አያስፈልግም በሙያው የጤና ሰው ሆኖ በተለያየ ወቅት የአገራቸውን የውጭ ፖሊሲ በችሎታቸው የምዕራባዊያንን ቀልብ የሳቡ ሞግተው ያሽነፉትን ጥቅሟን አስከብረው ካለፉት ከነአክሊሉ ሃብተወልድና መሰሎቻቸው ጋር በማይመጥን መልኩ የኢትዩጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሆኖ በታሪክ ስሙን ለማስጥራት ተሰለፈ ሆኖም ግን ወገኖቻችን በተለይ ደግሞ እህቶቻችን በየአረብ አገራቱ ሲገደሉና ሲታሰሩ ጆሮ ዳባ ልበስ አለ ይባስ ብሎ በ2015 እአ ወንድሞቻችን በሊቢያ በርሃ በአሲየስ ሲታረዱ ኢትዩጵያዊ መሆናቸውን እያጣራሁ ብሎ አረፈው ከዚሁም ጉዳይጋር ተያይዞ ከባድ ወቀሳ የደረሰበት ወያኔ የውጭፖሊሲው ከዱሮ የባሰ መበላሸቱ ሲያውቀውና ንዋይ ሲያጥረው በአንድ ውቅት HIV ለእኛ ጥቅም ነው የመጣው ያለውን ይህን ነውረኛ ሰው ከነበረበት ስልጣን አውርዶ ዛሬ ለWHO እንዲወዳደር ከፍተኛ ገንዝብ ተመድቦለት በወገኖቹ ደም ላይ አሁንም ቀልድ የጀመረው ።
በተለያየ ግዜ በተለያዩ የአገሪቱ ከልል የሚሰሩ ዶክተሮች ፣ የላብራቶሪ ሰራተኞችና ከሕክምና ሙያ የተያያዝ ስራ የሚሰሩ ሰዎች ጋር በነበረኝ ቅርበት ሁሌ ሲያማርሩ የሚሰማው ነገር ቢኖር በየግዜው በሚፈጥረው የመድሃኒትና የመሰረታዊ መገልገያ መሳሪያዎች አቅርቦት ላይ ነው ይህ ማለት እንግዲህ ለበሽታ ማስታገሻ ተብሎ የሚሰጠውንም ይጨምራል እንዲያውም አንዳንዶቹ ዶክተሮች ወደውት ከሰባት ዓመት በላይ ዋጋ የከፈሉለትን ሙያ እያማረሩ ግማሹቹ ተሰደዋል ግማሽዎቹ ያችኑ የሁለት ዓመት ግዴታቸውን ከተወጡ በኋላ ከተማ (በተለይ አዲስ አበባ)ገብተው ያዩትን ሁኔታ እንዳላዩ ሆነው ይኖራሉ ሞትና እንግልት የተፈረደበት የገጠሩ ህዝብ ዕድሜ ለነ ቴዎድሮስ አድሃኖም ፖሊሲ እየማቀቀ ይኖራል ፤ እንዲያውም ለዚህ ጉዳይ ማመላከቻ ይሆን ዘንድ በአንድ ወቅት አንድ ላብራቶሪ ውስጥ ከህንድ በመጣው የተጭበረበር ኬሚካል ምክኒያት ብዙ ሰው ለሌላ ህክምና ሄዶ ታይፎይድና ታይፈስ አልብህ ተብሎ መመለስ የዕለት ተለት ዜና ሆኖ ነበር በኋላ ላይ በተደረገ ማጣራት ይሄው ኬሚካል ውሃ እንኳን ሳይቀር ፖዘቲቭ እያለ አስቸግሮ ነበር በዚያም ጥርጣሬ ነበር የኬሚካሉ ፎርጅድነት ታውቆ ክገበያ የወጣው ነገር ግን ከዚሁ ጋር በተያያዝ በታዘዘላቸው መድሃኒት ምክኒያት ለጉበትና ለተለያዩ በሽታዎች የተጋለጡ ሰዎች በሆነ ወቅት የተለመደ የነበረው እንግዲህ ይሄን ሁሉ ጉድ የተሽከመው ሰውየ ነው በዓለም መሳቅያና መሳለቅያ ሊያደርገን ድቤውን እየጎሰመ ያለው ።
ወደ እናቶችና ህጻናት ሞት ስንመጣ ደግሞ ጉጀለው የወያኔ መንግስት ከIMF ገንዘብ መጠየቂያ ይሆነው ዘንድ በራሱ ቀመር በሰራው አሃዝ አለምን ያታልላል ነገር ግን ውደ ውስጥ ጠጋ ብለን ስናየው በየክልሉና ገጠር ቀበሌው ከወሊድ ጋር በተያያዘ የሚሞቱት ህጻናትና እናቶች ቤት ይቁጠራቸው፤ እንግዲህ አስተውሉ በአገሩ ህጻናት ደም ሌላው ደግሞ ሳይማሩ ባስተማሩትና ክብካቤና ክብር በሚገባቸው እናቶች ላይ ያሾፈው ባለሜካፑ ዶክተር ቴዎድሮስ ማን አለብኝነቱን በአለም መድረክ ለማሳየት የደፈረው፤ ወንድሞቸና እህቶቼ በተለይ እኛ በስደት ያለን ኢትዩጵያኖች በተገኘው አጋጣሚ በመረባረብ ይህን የጉጀሌው ተላላኪ ማስቆም ያለብን ።
በዚሁ አጋጣሚ በወያኔ ዘመን የተማረና የተመረቀ ልማታዊ ዶክተር እሱ ጋር ሊታከም የመጣን በሽተኛ የሰጠውን መልስ በግጥም መልክ አንድ ጓደኛ ያስቀመጥውን ጀባ ልበልና ላብቃ
ቀንስ
አንጀቱ ተጣጥፎ
እግሩ ተዝለፍልፎ
ለመራመድ ሰንፎ
ገላው ወዙን አጥቶ
ሁለመናው ከስቶ
ደራርቆ ገርጥቶ
በጓደኛው ታዝሎ ጤና ጣቢያ መጥቶ
ሃኪሙ ጋር ቢደርስ ለጉድ እያሳለው
ዶክተር “ያገር ፍርጃ” ምግብ ቀንስ አለው
ብታስደንቀውም ዓለም ተግልብጣ
ማልቀስ ቢፈልግም ብሶቱን ሊወጣ
እንባ አልቆበታል ኬ’ት አባቱ ይምጣ፟
የሚሆነው ቢያጣ ማልቀስ እያማረው እየሳቀ ወጣ
ዩሐንስ ደሳለኝ (ከጀርመን ፍራንክፈርት)