ጄኔራል አደም መሐመድ የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ሆነው ተሾሙ

ባሕርዳር፡ግንቦት 30 /2010 ዓ/ም (አብመድ)የኢፌደሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ጄኔራል አደም መሐመድን የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አድርገው ሾሙ።

የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ጄኔራል አደም ከግንቦት 30 ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ የተሾሙ ሲሆን፥ ያላቸው የስራ ልምድ ከግምት ውስጥ መግባቱ ተመልክቷል።
ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ በጥር 26 ቀን 2010 ዓ.ም ለመከላከያ ሰራዊት አባላት ወታደራዊ ማዕረጎችን በሰጡበት ወቅት ለሌ/ጀኔራል አደም መሐመድ የጀኔራልነት ማዕረግ መስጠታቸው ይታወሳል።

ከዚህ በፊትም በቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በምክትል ጠቅላይ ኤታማዦር ማዕረግ መሾማቸው ይታወሳል።
በሌላ በኩል በመንግስት የተለያዩ የኃላፊነት ቦታዎች ላይ ለረጅም ዓመታት ያገለገሉ ሁለት የሥራ ኃላፊዎች በጡረታ ተሰናብተዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት እንደገለጸው፥ ለረጅም ዓመት በተለያየ የመንግስት ኃላፊነት ያገለገሉ ሁለት የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ከግንቦት 30 ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ በጡረታ ተሰናብተዋል።

በዚሁ መሰረት በጡረታ የተገለሉት በቅርቡ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔነታቸውን ያስተላለፉት አቶ አባዱላ ገመዳ እና በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር የነበሩት አምባሳደር ግርማ ብሩ ናቸው።
አቶ አባዱላ ገመዳ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ሆነው ለረጅም ዓመታት አገልግለዋል። ቀደም ብሎም የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት ሆነው መስራታቸው ይታወሳል።

በአሜሪካ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር የነበሩት አቶ ግርማ ብሩ ደግሞ የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር፣ የገንዘብና ኢኮኖሚ ሚኒስትር ዴኤታና በሽግግሩ ወቅት የመከላከያ ሚኒስትር ዴኤታ ሆነው ማገልገላቸው ይታወሳል።

መንግሥት በቅርቡ ለረጅም ዓመት ያገለገሉ አምስት የስራ ኃላፊዎች በጡረታ ማሰናበቱ ይታወሳል።
በዚህም መሰረት በጡረታ እንዲያርፉ የተደረጉ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች የውጭ ግንኙነት ስትራቴጂክ ጥናት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ጄኔራል አቶ ስብሐት ነጋን ጨምሮ ዶክተር ካሱ ኢላላ ከፖለሲ ጥናትና ምርምር ማዕከል፣ አቶ በለጠ ታፈረ ከተቀናጀ የመሬት አጠቃቀም፣ ዕቅድና ፖሊሲ ዝግጅት ፕሮጀክት፣ አቶ ታደሰ ኃይሌ ከንግድና ኢንዱስትሪ የፖሊሲ ዕቅድ አፈጻጸምና ክትትል፣ እና አቶ መኮንን ማንያዘዋል ከፖሊሲ ምርምር ማዕከል መሆናቸውን ኢዜአ በዘገባው አስታውሳል።

Source – Amhara Mass Media Agency

Leave a comment